You are here:መነሻ ገፅ»አንዳንድ

 

በታይዋን የሚንቀሳቀስ አንድ ኩባንያ እናንተ ለመጋባት ወስኑ እንጂ የጥሎሹን ነገር በእኔ ጣሉት እያለ ነው። ሮማንቲስ የተባለው ይህ ኩባንያ ሙሽሮች በሰርጋቸው እለት ለወላጆቸው የሚሰጡትን ጥሎሽ በኪራይ መልክ ማቅረብ ከጀመረ ሶስት ወራትን ማስቆጠሩ ተገልጿል። በታይዋን ከጥንት ጀምሮ በጋብቻ ወቅት ለሙሽሪት ቤተሰብ ጥሎሽ መስጠት ልጃቸውን በጥሩ ሁኔታ በማሳደጋቸው የሚገባቸውን ክብር መስጠት ተደርጎ ይቆጠራል። ታዲያ በርካታ ወንዶች ማግባት ቢፈልጉም ይሄን ጥሎሽ መስጠት ባለመቻላቸው ብቻ ሲቸገሩ በማየታቸው ይሄንን ኩባንያ ማቋቋማቸውን መስራቾቹ ተናግረዋል። ኩባንያው ለጥሎሽ የሚሆኑ የወርቅ፣ የብር እንዲሁም የገንዘብ ጥሎሽ የሚያከራይ ሲሆን፤ ሁሉንም ጥሎሾች ለሚከራዬ ጥንዶችም መኪና ያለ ኪራይ ይመርቃል። ተከራዮች የጥሎሽ እቃዎቹን ከመውሰዳቸው በፊት ስምምነት መፈረም ይኖርባቸዋል።

ሃሳቡን ለየት የሚያደርገው ግን እነዚህን የጥሎሽ እቃዎች መንካት እንኳን አለመፈቀዱ ነው። ሙሽሮቹም ሆኑ ጥሎሽ የሚገባቸው የሙሽሪት ወላጆች እነዚህን የጥሎሽ እቃዎች ከማየት ውጪ በእጃቸው መንካት አይፈቀድላቸውም። ገንዘቡን ጨምሮ እቃዎቹ ለሰርጉ ማድመቂያ ብቻ በመድረክ ላይ እንዲቀመጡ ይደረጋል እንጂ ለምንም አይነት አገልግሎት አይውሉም። እቃዎቹን ማንም ሰው አቅም አለኝ ብሎ መግዛትም ሆነ ለሌላ አላማ መከራየት የማይፈቀድለት ሲሆን፤ ከተቀመጡበት የሚነሱት ጭምር በኩባንያው ሰራተኞች ብቻ ነው። ኩባንያው በእነዚህ ሶስት ወራት ውስጥ በዚህ አዲስ የንግድ ሃሳብ ከፍተና ትርፈ ማግኘቱን ጠቅሶ ያስነበበው ሮይተርስ ነው።

 

ኢትዮጵያዊው ወጣት ከእግሮቹ ይልቅ በሁለት እጆቹ በመራመድ እና በርካታ ተግባራትን በማከናወን አለምን አስደምሟል ይላል ቢቢሲ። በትግራይ ክልል ነዋሪ የሆነውና የ32 ዓመቱ ወጣት ድራር አቦሆይ ከቢቢሲ ጋር ያደረገውን ቃል ምልልስ ጠቅሶ ዜናውን ያስነበበው ኦዲቲ ሴንትራል ነው። ድራር ገና ከልጅነቱ ጀምሮ የቻይና እና የአሜሪካ ፊልሞችን ሲመለከት እንዳደገ እና በፊልሞቹ ላይ ይመለከታቸው የነበረቱን እንቅስቃሴዎችም ይለማመድ እንደነበር ተናግሯል። በአሁኑ ጊዜም ጠዋት ላይ ለሶስት ሰዓታት እንዲሁም ማታ ላይ ለሶስት ሰዓታት ልምምድ የሚደረግ ሲሆን፤ በሁለት እጆቹ በመራመድ እና እግሮቹን ወደ ላይ በመስቀል ተራሮችን መውጣት፤ መኪና መጎተት፣ እንዲሁም ሰዎችን በጀርባው ላይ አዝሎ መጓዝ እንደሚችል ለቢቢሲ አሳይቷል ተብሏል። ወጣቱ በዚህ አስደናቂ ድርጊቱ ስሙን በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ የማስፈር ፍላጎት እንዳለውም ገልጿል። ሁለቱም እግሮቹ ጤናማ መሆናቸውንም ዘገባው አስነብቧል።

ቤተመንግስቱ ውስጥ መከፋት፣ ድፍረት ማጣት፣ ነገ ስለሚመጣ ነገር ባለ ፍርሃት የተሞላ ጥበቃ ነበር። ጃንሆይ ድንገት አማካሪዎቸውን ጠርተው ልማትን ስለመዘንጋታቸው ከወቀሱና ከነቀፏቸው በኋላ አባይ ላይ ግድብ ልንሰራ መሆኑን አሳወቁ። “ነገር ግን ክፍለ ሀገሮቹ እየተራቡ ባለበት፣ ህዝቡ ሰላም ባጣበት፣ ወገኖቹ ስርዓተ መንግስቱን ስለማቅናት በሚንሾካሾኩበት፣ ወታደራዊ መኮንኖቹ በመኳንንት ላይ ባመፁበትና በከበቧቸው ሰዓት እንዴት ነው ግድቦችን የምናቆመው?” ሲሉ ግራ የተጋቡ አማካሪዎች አጉረመረሙ። “የግድቦቹን ነገር ረስቶ ረሃብተኞቹን መርዳት ይሻላል።” የሚል ጉርምርምታ በየመተላለፊያዎቹ ላይ ተሰማ። ለዚህ ገንዘብ ሚኒስትሩ መልስ ሰጡ። “ግንቦቹ ከተገነቡ ውሃ ውደ መስክ መልቀቅ የሚቻል ይሆናል፤ ከዚያ ይሄ በቂ ሰብልና ከረሃብ የተነሳም እልቂት እንዳይኖር ያደርጋል።


“እሺ ይሁን፣ ግድቦችን መስራት ስንት ጊዜ ይፈጃል?” ሲሉም አጉረመረሙ። “በመሃሉ ህዝቡ በረሃብ ያልቃል።” “ህዝቡ አይሞትም” ገንዘብ ሚኒስትሩ ገለፁ።


“እስካሁንኮ አልሞተም፣ ስለዚህም አሁንም አይሞትም። ግን ግድቦችን ካልገነባን እንዴት ነው ሌሎች ላይ ልንደርስ ወይም ልንቀድማቸው የምንችለው?”


“ግን ከነማን ጋር ነው እየተወዳደርን ያለነው?” ወሬኞቹ አጉረመረሙ። “ከነማን ስትሉ ምን ማለታችሁ ነው? ግብጽስ?” “ግንኮ ጌታዬ ግብጽ ከኛ በሀብት ትበልጣለች፣ ግን ራሷ ግብጽ እንኳን ከኪሷ አውጥታ ግድቦችን መስራት አልቻለችም። ለግድቦችን ታዲያ ፈንድ የምናገኘው ከየት ነው?” በዚህ ጊዜ ሚኒስትሩ በትክክል በጥርጣሬ ተበሳጨ። እናም ማስተማር ጀመሩ፣ አንድ ሰው ለአገሩ እድገት ሲል ራሱን መሰዋቱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይነግሯቸው ጀመር። በተጨማሪም፤ ጃንሆይ አዘዋል። አይደለም እንዴ? የምናድገው ለቅፅበት ሳናርፍ ልባችንና ነፍሳችንን እዚያው አሳርፈን ነው። የማስታወቂያ ሚኒስቴሩም የግርማዊነታቸው ውሳኔ አዲስ ድል መሆኑን አስታወቁ። ወዲያውም ግድቦቹ ተሰርተው ሲጠናቀቁ ሁሉም ሰው እንደሚበለጽግና አሉባልተኞችም እንደሚያፍሩ የሚናገሩ መፈክሮች በከተማይቱ አውራ ጎዳናዎች ላይ ታዩ።


ምንም እንኳን ይሄ ጉዳይ አመፀኞቹን ቢያበሳጫቸውም የግድቦቹን ስራ ለመቆጣጠር ልዩ ተግባር በንጉሱ የተቋቋመው ዘውዳዊ ምክር ቤት አባላት የግድቦቹ ነገር ከሙስናና ረሃቡን ከማባባስ ውጭ ምንም ጥቅም ባለማስገኘቱ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ እስር ቤት ተወረወሩ። ያም ቢሆን ይሄ በባለስልጣናቱ በኩል የተወሰደው ርምጃ ጃንሆይን ሳያሳዝናቸው አልቀረም ስል ሁል ጊዜ አስባለሁ።


አይበገሬው አመቱ ሁሉ በየጊዜው በሚጨምር ጫና ትከሻውን እየከበዳቸው መሆኑ ተሰምቷቸዋል። በመሆኑም አለምን የሚያስደንቅ ቆንጆ ሀውልት ጥለው ለማለፍ ፈልገዋል። እንዲህ ከሆነ ከብዙ ዓመታትም በኋላ ዘውዳዊዎቹን ግድቦች ያዩ ሁሉ “ተመልከቱ! ከንጉስ ነገስቱ በቀር እነዚህን ነገሮች ማን ሊሰራቸው ይችል ነበር እነዚህን እጅግ የተለዩ፣ አስደናቂዎች! ተራሮች ሁሉ ወንዞችን አቋርጠው የሚመለከቷቸው!” ሲሉ ይጮሃሉ። ወይም በሌላ አቅጣጫ ብንመለከተው፣ ንጉሰ ነገስቱ ግድቦችን ከመገንባት ይልቅ ረሃብተኞችን መመገብ ይሻላል። ለሚሉት ወሬዎችና ጉርምርምታዎች ጆሮ ሰጥተው ቢሆን ኖሮ ረሃብተኞቹኮ ቢጠግቡም ኖሮ ቀስ በቀስ ቀናቸው ሲደርስ መሞቸው አይቀርም ነበር፤ የሚታወሱበት ምንም ምልክት ሳይተው እነሱም ሆኑ ንጉሰ ነገስቱ።

 

ሚስጥራዊው ንጉሥ - ዮሐንስ ካሳ

ፊሊፒናዊው ራቢን ኢናጄ በየዓመቱ የክርስቶስን ስቅለት ለማሰብ አጅና እግሮቹን በሚስማር በመነደል በእንጨት መስቀል ላይ ይሰቀላል። ራቢን ይሄን ድርጊት ሲፈፅም ዘንድሮ ለ32ኛ ጊዜ መሆኑ ተገልጿል። በየአመቱ በእለተ ስቅለት በእንጨት መስቀል ላይ በመሰቀል የክርስቶስን ህመም እና ስቃይ የሚያስታውስ ሲሆን፤ ለዚህ ድርጊቱ ብርታት የሚሰጠውም ጠንካራው የካቶሊክ እምነቱ መሆኑን ገልጿል። ድርጊቱን ለረጅም ጊዜ ከመደጋገሙ የተነሳ አሁን ላይ ምንም አይነት ህመም እየተሰማው እንዳልሆነ ተናግሯል። በፊት በፊት እንዲህ አይነቱን ስቅለት ፈፅሞ ወደቤቱ ሲገባ በሚስማር የተወጋው አካሉ ቆሳስሎ እና ደምቶ እንደነበር የገለፀው ራቢን፤ አሁን ግን ምንም አይነት እንዲህ አይነት ስሜት እየተሰማው እንዳልሆነ ተናግሯል። ስቅላቱን በርካታ ሰዎች በተሰበሰቡበት የሚያካሂደው የ58 ዓመቱ ራቢን እድሜው 60 ዓመት እስኪሚሞላ ድረስ ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ ይሄንን ስቅለት የማከናወን ሀሳብ እንዳለውም ለሮይተርስ ገልጿል።

 

- በአውስትራሊያ አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ከ50 ኪሎግራም በላይ ብዛት ያለው ድንች በቤቱ ማከማቸት አይፈቀድለትም ነበር። ይሄ የሚደረገውም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ምርት ለመቆጣጠር በማሰብ ነው። ይሄን ለማድረግም የሀገሪቱ ድንች ገበያ ኮርፖሬሽን ቁጥጥር ያደርጋል።


- በታይላንድ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ ድብልቅ መጠጥ መጠጣት የሚፈልግ ሰው መጠጡን መግዛት የሚፈቅድለት በምሳ ሰዓት አሊም በእራት ሰዓት ብቻ ነው። ይህ ህግ በምግብ ቤቶች እና በመጠጥ ቤቶችም ጭምር ይተገበር ነበር።


- በስዊዘርላንድ ማንም ሰው ቢሆን ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ ሽንት ቤት ተጠቅሞ ውሃ መልቀቅ አይፈቀድለትም። ይሄ የሚሆነውም በአካባቢ የሚለቀቀውን ድምፅ ለማስቀረት በማሰብ ነው።


- በጀርመን ለተወለዱ ልጆች የሚወጡት ሰዎች የህጻኑን ፆታ ለይተው የሚጠቁሙ ካልሆኑ ከመከልከላቸውም በተጨማሪ በህግ ያስቀጣሉ።


- በጆርጂያ ከተማ ማንም ሰው ዶሮ ይዞ የመኪና መንገድ ሲያቋርጥ ቢገኝ በህግ ይቀጣ ነበር።

ባንድ አገር ጦርነት ተነሳና ለአካለ መጠን የደረሰ ወንድ ልጅ በሙሉ እንዲሰለፍ ታወጀ። ሁሉም ስንቁን ባህያ አመሉን በጉያ ይዞ ዘመተ። አንድ ፈሪ “አልዘምትም” ብሎ ሲያንገራግር ከቆየ በኋላ “ካልዘመትህ መሬት አታገኝም፣ ሚስት አታገባም፣ ከሰው አትቆጠርም” ብሎ ምስለኔው አዘመተው። ከሱ ሰፈር ዘጠኝ ጎበዛዝት ጓደኞቹ አብረው ዘምተዋል።

 

ይህ ነፍሱን በነጠላው ጫፍ የቋጠረ ዛርጢ ጥይት ሳይሰማ በድርጭት እንቅስቃሴ እየበረገገ ስላስቸገረ ከጦርነቱ መሀል ገብቶ ስም ከሚያጠፋና ሬሳ ከሚያበዛ ስንቅ አጋስስና አህያ እንዲጠብቅ ተወሰነ። እንደልማዱ እየበረገገ መንጋ ሲጠብቅ ከርሞ ተመለሰ። ጀግኖቹ እየጣሉ ወድቀው አገራቸውን አስከብረው ቀሩ።


ዛርጢ ከተማ ሲገባ ዋና ወሬ አላስጨብጥ አለ። ስለጦርነቱም ማብራሪያና መግለጫ ለመስጠሰት ከጀለ። የጦር ሜዳውን ሁኔታ እያነሳ አስቸገረ።


“ለመሆኑ የት ነበር የዘመትኸው?” አለው አንዱ
“ራያ” አለ ዛርጢ
“ስንት ሆናችሁ ዘመታችሁ?”
“አስር ነበርን”
“ስንታችሁ ተመለሳችሁ?”
“እንደፈራነው አይደለም። ከአስሩ እኔ ተመለስሁ” አለ ዛርጢ።


ሙሻዙር
ከመርስዔ ኀዘን አበበ

 

ሴትየዋ አንዲት በሙያዋ የታወቀች የቤት ሠራተኛ ይቀጥራሉ። ሠራተኛዋም የእጅ አመል ኖሮባታል ለካ የጓዳ አይጥ ሆና አስቸገረቻቸው። ሙያዋን ስለሚወዱትም ጥፋቷን ችለው አብረው ይኖራሉ። አንድ ቀን ታዲያ ለምሳ እንድታዘጋጅ የተሰጣትን ስጋ በመከታተፍ ላይ ሳለች ከጥሬው ሥጋ ጐመድ እያደረገች ስትበላ አይተው በድርጊቷ ቢናደዱም አይተው እንዳላዩ ዝም ይሏታል። ትንሽ ቆይታ ይህች ሰራተኛ ሌባ ጣቷን በቢላዋ በመቁረጧ ደሟን እያዘራች ወደ አሰሪዋ በመሄድ “እሜቴ የእርስዎ ቢላ ባለጌ ነው ሌባ ጣቴን ቆረጠኝ” ብላ ታሳያቸዋለች። ቀድሞ ነገር የገባቸው አሰሪዋም፤ አመልካች ጣቷ መቆረጡን ቢያዩም በነገር መንካት ስለፈለጉ ብቻ “ባክሽ ምን ደህና ጣት አለሽ ሁሉም ሌባ ጣት ነው” አሏት።¾

 

በአብዛኛው ሀበሻ ዘንድ ከመወደድ ይልቅ ጥላቻ የሚሰጠው ውሻ ከሰሞኑ ለየት ያለ ነገር ሲደረግለት ተስተውሏል። ኦዲቲ ሴንትራል ሰሞኑን ያስነበበው ዜና ለቡቺ ባለ 137 ሺህ ዶላር ልብስ ተዘጋጅቷል ይላል።


በዶጊ አርመር እና ቬሪፈርስት ቱ ኩባንያዎች ትብብር የተሰራው ይሄ የውሻ የጀርባ ልብስ (ጃኬት) የአለማችን እጅግ ውዱ የውሻ ልብስም ተብሏል። ይሄ የዓለማችን ቅንጡ እና ያጌጠ የውሻ ጃኬት የተሰራው በ24 ካራት ወርቅ ሲሆን፣ የተለያየ መጠን ያላቸው ጥቁር ዳይመንዶች እና የከበሩ ድንጋዮችም አሉበት። ጃኬቱ ውሻዎን ከሌሎች ውሾች ንክሻ የመከላከል እንዲሁም የቢላን ስለት የመቋቋም አቅም አለው ተብሏል። ጃኬቱ ውሻውን ከጅራቱ መጀመሪያ አስከ አንገቱ ድረስ የሚሸፍን ሲሆን፤ በላዩ ላይም የሚያስጌጡት ሪቫኖች እና የተለያዩ ጌጣጌጦች አሉበት። ጃኬቱን ለውሾቻችሁ ልደት በስጦታ መልክ ለማበርከት የምትፈልጉ አሁን እድሉ ተመቻችቶላችኋል ያለው የዜና ዘገባው ውሻውን ለሚወድ ሰው 137 ሺህ ዶላር ምንም አይደለም ይላል።

 

የካንሳስ ነዋሪው አዛውንት ለተከታታይ አምስት ዓመታት ያለመታከት ያደረጉት ጥረት ውጤቱ አምሮላቸዋል። ጌሪ ሺናሌይ የተባሉት የ67 ዓመቱ የካንሳስ ነዋሪ ለተከታታይ አምስት ዓመታት ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸውን ሎተሪዎች በመቁረጥ በስተመጨረሻም የግዛቲቱን ትልቅ ሽልማት እንዲያሸንፉ አድርጓቸዋል ሲል ያስነበበው የፒአይ ድረ-ገጽ ነው። ሺናሌይ ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት በተመሳሳይ ቁጥሮች ሎተሪ ሲቆርጡ ቆይተው ባለፈው ሳምንት በነዚያው ቁጥሮች በግዛቲቱ ትልቁ የሆነውን የ22 ሺህ ዶላር ጃክፖት ሎተሪ ማሸነፍ ችለዋል። ካሸነፉ በኋላም በሰጡት አስተያየት “እነዚህን ቁጥሮች በህይወት ኖሬ ሎተሪ በምቆርጥባቸው ጊዜያት ሁሉ የመሞከር ፍላጐት ነበረኝ። ለምን 130 ዓመት አልኖርም፤ ሎተሪ መቁረጥ ካለብኝ ከእነዚህ ቁጥሮች ውጪ የመቁረጥ ፍላጐት የለኝም። መቼ እንደሚሆን ባላውቅም አንድ ቀን እንደሚሳካልኝ ግን እርግጠኛ ነበርኩ። አሁን ስለተሳካልኝ ደስተኛ ነኝ” ብለዋል። ሎተሪ ባሸነፉበት ገንዘብም ጋራዥ የመክፈት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።¾

 

ሰሞኑን ከወደቻይና የተሰማ አንድ ዜና ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸውን አዘውትረው ለህፃናት የሚሰጡ ሰዎችን ያስጠነቀቀ ይመስላል፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ነው፡፡ ሉ የተባለችው ቻይናዊት እናት የሁለት ዓመት ልጇ ትምህርታዊ ቪዲዮዎችን ከአይፎን ስልኳ ላይ እንዲመለከት በማለት ስልኳን ትሰጠዋለች፡፡ ህጻኑም በዘፈቀደ ሲነካካ ያልተፈለገ መተግበሪያ ውስጥ በመግባት ስልኩ ለቀጣዮቹ 47 ዓመታት በፊት አገልግሎት እንዳይሰጥ አድርጎታል፡፡ ቴክኒሺያኖች እንደተናገሩት ህጻኑ በዘፈቀደ ስልኩን እየነካካ ሳለ ስልኩ ዝግ ሆኖ የሚቆይበትን የጊዜ ገደብ የሚስተካከልበት ሲስተም ውስጥ በመግባት የጊዜ ገደቡን 47 ዓመታት ወይም ከ25 ሚሊዮን ደቂቃ በላይ አድርጎ መርጦታል፡ ይህ ሊሆን የቻለውም ህጻኑ በተደጋጋሚ የተሳሳተ የይለፍ ኮድ በማስገባቱ ነው ተብሏል፡፡ ሉ ስልኩ አገልግሎት እንዲሰጥ ለቀጣዮቹ 47 ዓመታት መጠበቅ ካልሆነም እንደአዲስ በላዩ ላይ ያሉ መረጃዎችን አጥፍቶ ማስጀመር እንዳለበት የአፕል አይፎን ቴክኒሺያኖች የገለፁላት ሲሆን እርሷም አስገራሚ መለስ ሰጥታለች፡፡ “እውነቱን ለመናገር ለቀጣዮቹ 47 ዓመታት ስልኬ እስከሚከፈት መጠበቅ እና ለልጅ ልጇም የአባቱ ስህተት እንደሆነ መናገር አልፈለገም” ስትል እስከዚያ ልጇም አባት እንደሚሆን እርሷም አያት እንደምትሆን የጊዜውን ርዝመት አስረድታለች ሲል ያስነበበው ኢዲቲ ሴንትራል ነው፡፡

Page 1 of 51

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us