ድንቅ ተፈጥሮ

Wednesday, 03 August 2016 14:15

በዓለማችን ላይ እጅግ ረቂቅ ከሆኑ አያሌ ክስተቶች አንዱ ውልደት ወይም ልደት ነው። ተረግዞ ለዘጠኝ ወራት በእናት ማህፀን ውስጥ ቆይቶ መወለድ እጅግ የረቀቀ ክስተት ሆኖብን ሳለ ደግሞ አንዳንድ ከአእምሮ በላይ የሆኑ ውልደቶች ያጋጥሙናል። እስኪ ከሰው ልጅ አስተሳሰብ እና ችሎታ በላይ የረቀቁ አንዳንድ አስገራሚ የውልደት ክስተቶችን እንመልከት።

ከሁለት ወንድ በአንድ ጊዜ የተወለዱ መንትያዎች

ሚያ ዋሺንግተን ትባላለች። ይህች ሴት በአንድ ወቅት መንታ ሴት ልጆችን ትወልዳለች። መንታ መውለዷ ላያስገርም ይችላል። የሚያስገርመው ነገር ግን ይህች ሴት የወለደቻቸው ልጆች ከተለያዩ አባቶች የተረገዙ መሆናቸው ነው። ዋሺንግተን ከተለያዩ ወንዶች ጋር ባደረገቻቸው የወሲብ ግንኙነቶች እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ እንዲፈጠር እንዳደረገም ተገልጿል። ይህ ሐቅ ሊወጣ የቻለውም ከተወለዱት መንታ ህፃናት መካከል አንደኛው ምኑም አባቱን መምሰል ባለመቻሉ በተደረገ ምርመራ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፤ እንዲህ አይነቱ ክስተትም በሳይንሱ ሄትሮፓሬንታል ስፐር ሬኩንዴሽን የሚባል እና እንዲህ አይነቱ የአወላለድ ችግር እጅግ ጥቂት በሆኑ ሰዎች ላይ ብቻ የሚከሰት ክስተት ነው ተብሏል። እውነታው ከታወቀ በኋላ የዋሺንግተን ባል ከሌላ ወንድ የተፀነሰውን ልጅ በጉዲፈቻ ወስዶ ከራሱ ልጅ ጋር እንዲያድግ አድርጓል።

የተለያየ ቀለም ያላቸው መንትያዎች

መንትያ ሆነው ተወልደው የተለያየ መልክ ያላቸው ህፃናት በጣም ጥቂት ናቸው። ነገር ግን መንትያ ሆነው የተለያየ ቀለም ያላቸው ህፃናት አሉ ብንልዎ ምን ይሰማዎት ይሆን? እንዲህ አይነቱ ክስተት ከአንድ ሚሊዮን ጥንዶች በአንዱ ላይ ብቻ የሚከሰት መሆኑን ሳይንሱ ያስቀምጣል። ምናልባትም ከነዚህ አንድ ሚሊዮን ጥንዶች መካከል ኪያን እና ሬሚ ሆግሰን አንዳቸው ይሆኑ ይሆናል። እነዚህ ጥንዶች በ2008 (እ.ኤ.አ.) ሚያ እና ሊህ ዱራንት የተባሉ መንታ ሴቶችን ወልደዋል። ሆኖም ሚያ ጥቁር ፀጉር ያላት እና የሰውነት ቀለሟም ጥቁር፣ የዓይኗ ቀለምም ነጭ ሆኖ ስትወለድ ዱራንት በተቃራኒው ወርቃማ ቀለም ያለው ፀጉር፣ ሰማያዊ የዓይን ቀለም እንዲሁም ነጭ የሰውነት ቀለም ኖሯት ተወልዳለች። እነዚህን ጥንዶች ለየት የሚያደርጋቸውም ከሰባት ዓመት በፊት እንዲሁ መንታ ሴት ልጆችን ወልደው ሁለቱም ልጆች የተለያየ ቀለም ያላቸው በመሆናቸው ነው።

 

በ21 ሳምንት ውስጥ የተወለደው ህፃን

እ.ኤ.አ. በ1987 በካናዳ ኦታዋ የተከሰተ ክስተት ነው። አንድ ህፃን ከተረገዘበት ጊዜ አንስቶ ከ37 እስከ 41 ባሉት ሳምንታት ውስጥ ሲወለድ ትክክለኛ የአወላለድ ጊዜ ይባላል። ነገር ግን ከዚያ ጊዜ ቀደም ብሎ ከተወለደ የመወለጃ ቀኑ ሳይደርስ የተወለደ (Premature) ይባላል። ይሄንኛው ህፃን ግን በአስገራሚ ሁኔታ የተወለደው በተረገዘ በ21 ሳምንት ከ5 ቀኑ ነበር። በተወለደበት ወቅትም ክብደቱ 482 ግራም ብቻ ነበር። በ22 ሳምንታቸው የተወለዱ ህፃናት እንኳን በህይወት የመትረፍ እድላቸው 10 በመቶ ሆኖ ሳለ ይህ ህፃን ግን ያለምንም ችግር ተወልዶ ማደግ ችሏል።

ግዙፉ ህፃን

ሲወለድ ከፍተኛ ክብደት ኖሮት በመወለድ ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘው ካርሜሊና ፌዴሌ ከተባለችው ጣሊያናዊት ሴት የተወለደው ልጅ ነው። ይህ ህፃን እ.ኤ.አ. በ1955 ሲወለድ የነበረው ክብደት 10 ነጥብ 2 ኪሎ ግራም ነበር። በዚህ ረገድ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው በ2009 ከኢንዶኔዥያዊት እናት የተወለደ ህፃን ሲሆን፤ ህፃኑም በወቅቱ 8 ነጥብ 7 ኪሎ ግራም ክብደት ነበረው። ይህች ሴት እንዲህ ግዙፍ ህፃን የወለደችው የስኳር ህመምተኛ በመሆኗ ሳቢያ እንደሆነም ተገልጿል።

በዛፍ ላይ የተወለደው ህፃን

ካሮሊና ክሊንዲዛ ሞዛምቢካዊት ሴት ናት። በ2000 (እ.ኤ.አ.) ክረምት ወቅት ከፍተኛ ጐርፍ ይነሳና መኖሪያ ቤቷን ያጥለቀለቀዋል። በዚያ ወቅት የደረሰች ነፍሰጡር የነበረችው ካሮሊናም ጐርፉን ተከትሎ በመጣ ዘንዶ ላለመነከስ ስትል በአቅራቢያዋ በሚገኝ ዛፍ ላይ ትወጣለች። የጐርፉ እድሜ በመርዘሙም ለአራት ቀናት ያህል ምንም ምግብ እና ውሃ ሳትቀምስ በዛፍ ላይ ለመቆየት ተገደደች። እዚያ እያለችም በአራተኛው ቀን ሮሲታ የተባለች ሴት ልጅ እዚያው ዛፍ ላይ ወልዳለች። ደግነቱ ብዙም ሳትቆይ የወታደሮች ሄሊኮፕተር ደርሶ ታድጓታል።

አምስት ሆነው የተወለዱ ህፃናት

ነገርየው የሆነው እ.ኤ.አ. በግንቦት 28 ቀን 1934 በሀገረ ካናዳ ነው። ኤልዘር እና ኦሊቫ ዲዮኔ የተባሉት ጥንዶች በአንድ ጊዜ አምስት ሴት ልጆች የተወለዱላቸው ጥንዶች ናቸው። አኒቴ፣ ሲሲሊ፣ ኤምሊ፣ ሜሪ እና ዩቮን የተባሉት አምስት ሴቶች በአንድ ጊዜ ከአንድ ማህፀን የተወለዱት ሴት ልጆች ናቸው። እነዚህ ህፃናት ዘጠኝ ወር ሲሞላቸው ከቤተሰባቸው ተለይተው የመንግስት ሀብት እንዲሆኑ ከተደረገ በኋላ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገባቸው እንዲያድጉ ተደርጐም ነበር። በዚህ መልኩም ለዘጠኝ ዓመታት ያህል በቱሪስቶች እየተጐበኙ እና ፎቶ እየተነሱ ለሀገሪቱ ገቢ ያስገኙ የነበረ ሲሆን፤ እነርሱ ግን ከገቢው ላይ ምንም የሚደርሳቸው ነገር አልነበረም። በመጨረሻም ወላጆቻቸው ተከራክረው መልሰው የወሰዷቸው ሲሆን፤ ህፃናቱ እያደጉ ሲሄዱም አምስቱም ተመሳሳይ የአኗኗር ዘይቤ እንደነበራቸው በታሪክ ተፅፏል።

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
428 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us