የወርቅ ጥሎሽ ግብጻዊያንን እያከራከረ ነው

Wednesday, 10 August 2016 13:40

 

በግብፅ ትዳር መመስረት የፈለገ ጉብል ለወደፊት ሚስቱ ለምትሆን ሴት ከወርቅ የተሰሩ ስጦታዎችን የማበርከት የውዴታ ግዴታ አለበት። እነዚህ ስጦታዎች በጌጣጌጥ መልክ የተሰሩ መሆን ያለባቸው ሲሆን፤ ይህ ባህላዊ ስርዓትም በአረብኛ ሻብካ ይባላል። ይህ ባህላዊ ስርዓት ታዲያ ከወርቅ ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ ክርክር ፈጥሯል። ወጣት ወንዶችንም ግራ እያጋባቸው ይገኛል።

የአንድ ግራም ባለ 21 ካራት ወርቅ ዋጋ በአሁኑ ወቅት 445 የግብፅ ፓውንድ (50 ዶላር) መድረሱን የገለፀው ቢቢሲ፣ ይህ ከፍተኛ ዋጋ ከሌሎች ወጪዎች ጋር ተደማምሮ የሀገሪቱን ጉብሎች ሃሳብ ውስጥ እንደከተታቸው ዘግቧል። ወንዱ ትዳር ከመመስረቱ በፊት የተለያዩ ከወርቅ የተሰሩ ጌጣጌጦችን ለወደፊት ሚስቱ በጥሎሽ መልክ ማበርከት፤ የጥሎሽ ገንዘብ ለቤተሰቦቿ የመስጠት እንዲሁም መኖሪያ ቤት የመግዛት ግዴታ አለበት። በመሆኑም ወጣት ወንዶች እነዚህን ሁሉ ተደራራቢ ወጪዎች ለመሸፈን በመቸገራቸው ይሄ የወርቅ ጌታጌጥ ጥሎሽ እንዲቀር ንቅናቄ እያደረጉ ይገኛሉ። ከባለፈው አርብ ጀምሮም በማህበራዊ ድረ-ገፅ ጭምር ንቅናቄ እየተደረገ ሲሆን፤ አብዛኞቹም የወርቅ ስጦታው ይቅር የሚለውን ሃሳብ እየደገፉት መሆኑ እየተገለፀ ይገኛል።

የተወሰኑት ሰዎችም የወርቅ ስጦታው በብር እንዲቀየር ሃሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ ይሄንን ሃሳብም ለዚህ አላማ በተከፈተ ድረ-ገፅ እያንጸባረቁት ይገኛሉ። “በርትታችሁ በመስራት አብራችሁ ኑሩ፤ ሚስቶች ሸቀጥ አይደላችሁም፣ ሙሽራውም ነጋዴ አይደለም” በሚል መሪ ቃል ባህላዊ ስርዓቱን የመቃወሚያ ድምጻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። የወርቅ ጥሎሽ ስርዓት መወገድ ወጣቶችን ለጋብቻ ለማበረታታት እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ትዳር እንዲመሰርቱ ያግዛቸዋል በማለትም ውሳኔያቸውን እያሳወቁ ይገኛል። በርካታ የሀገሪቱ ሴቶች ለጉዳዩ አዎንታዊ ምላሽ እየሰጡ  ናቸው ያለው ዘገባው፤ ሌሎች ግን ባህላዊው መንገድ እንዲጠበቅ ፍላጎት እንዳላቸው አስነብቧል። የወርቅ ስጦታው በብር ይቀየር የሚለውን ሃሳብ የምትደግፍ አንዲት ሴት “የብር ስጦታ መስጠት የድህነት መገለጫ ሳይሆን፤ ቤተሰቡ ሙሽራው ያለበትን የገንዘብ ኃላፊነት እንዲረዳው ማድረጊያ በመሆኑ ጋብቻው እንዳይፈፀም የሚደርግበት ምንም ምክንያት የለም” ስትል ሃሳቧን አስቀምጣለች። በተቃራኒው ሃሳቡን እደማትደግፈው የገለፀች አንዲት ሴት በበኩሏ “ይሄ ሞኝነት ነው። ስጦታው ለሙሽራዋ የሚበርከት የጥሎሽ አካል ስለሆነ፣ ይሄንን ጥሎሽ መስጠት ያልቻለ ወንድ ባል ሊባል አይገባውም” ስትል ሃሳቧን አስቀምጣለች። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
461 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ መስከረም አያሌው

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us