የግጥምጥሞሽ ዓለም

Wednesday, 10 August 2016 13:46

አንዳንድ ጊዜ ነገሮች ከምናስበው በላይ ሲገጣጠሙ ያስገርመናል። በተለይ መንታ ሆነው በሚወለዱ ሰዎች ዘንድ ነገሮች ከመገጣጠም አልፈው አንድ አይነት ሲሆኑ ይታያሉ። እስኪ በማይታመን መልክ ግጥምጥሞሽ ያላቸው አንዳንድ ነገሮች እንመልከት። ይህኛው አስገራሚ ግጥምጥሞሽ የተስተናገደው ኦሃዮ ግዛት ውስጥ ነበር።

አንዲት ሴት መንታ ወንድ ልጆችን በሆስፒታል ውስጥ ትገላገላለች። ልክ ህጸናቱ እንደተወለዱም ሁለቱም በተለያዩ ወላጆች ዘንድ እንዲያድጉ ነበር የተደረገው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተለያዩት ህጻናት አንዳቸው ሌላኛው እስከመፈጠሩም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ለሁለቱም ህጸናት በጉዲፈቻ የወሰዷቸው አሳዳጊዎቻቸው የወጣላቸው ስም ጀምስ የሚል ነበር። እነዚህ ልጆች ሲያድጉ ሁለቱም የፖሊስ መኮንን ሆኑ። ትዳር ሲመሰርቱም ሁለቱም ያገቧቸው ሴቶች ስም ሊንዳ ነበር። ሁለቱ ጀምሶች የወለዱት አንዳንድ ወንድ ልጅ ብቻ ሲሆን የሁለቱም ልጆች ስም አለን ነበር። መንትዮቹ ጀምስ እና ጀምስ የየራሳቸው ውሻ የነበራቸው ሲሆን፤ የውሾቻቸው ስምም ቶይ ነበር። እነዚህ መንትዮች ከቆይታ በኋላ ሁለቱም ትዳራቸውን ያፈረሱ ሲሆን፤ በስተመጨረሻም ሁለቱም ቤቲ የተባሉ ሴቶችን አግብተዋል።

እስኪ አሁን ደግሞ በአለማችን ላይ የነበሩ መሪዎችን የህይወት ግጥምጥሞሽ እንመልከት። አዶልፍ ሂትለረ የተወለደው ናፖሊዮን ቦናባርቲ በተወለደ በ129 ዓመት ነው። ሂትለር ወደ ስልጣን የመጣውም ናፖሊዮን ስልጣን በያዘበት በ129 ዓመት ነው። በተመሳሳይ መልኩ ሒትለር ሩሲያ ላይ ወረራ ያካሄደው ናፖሊዮን ከወረራት ከ129 ዓመታት በኋላ ነው። በመጨረሻም ሒትለር ተሸንፎ ስልጣን የለቀቀው የፖሊዮን ስልጣን በለቀቀ በ129 ዓመት ነው።

የጣሊያኑ ንጉስ ኡምቤርቶ ቀዳሚዋ የሚያዘወትሩት ምግብ ቤት ነበራቸው። የዚህ ምግብ ቤት ባለቤት ንጉሱ በተወለዱበት እለት በተመሳሳይ ከተማ የተወለደ ነው። በተጨማሪም የንጉሱም ሆነች የምግብ ቤቱ ባለቤት ሚስቶች ስማቸው ማርገሪታ ነው። በመጨረሻም የእነዚህ ሰዎች ግጥምጥሞሽ ህይወትን በማጣት ተደመደመ። በነሐሴ 29 ቀን 1900 ዓ.ም የምግብ ቤቱ ባለቤት በተተኮሰበት ጥይት ተመትቶ መንገድ ላይ የመሞቱ ዜና ለንጉሱ የደረሳቸው ሲሆን፤ በዚያው እለት ከቆይታ በኋላ ንጉሱ በተመሳሳይ መልኩ ግድያ ተፈፀመባቸው።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
526 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ መስከረም አያሌው

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us