የፍቅረኛሞችን ልብ ምት የሚያነበው ቀለበት

Wednesday, 17 August 2016 12:16

በኢንተርኔት አለም የተፈጠሩ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በረጅም ርቀት ላይ የሚገኙ ሰዎች እንዲቀራረቡ የማድረግ አገልግሎት ይሰጣሉ። ከዚህም ይባስ ብሎ ግን እጅግ ውስብስብ የተባለ አንድ አዲስ ቴክኖሎጂ በቅርቡ ወደ ገበያ ይገባል እየተባለ ነው።

ተች ኤች ቢ ሪንግ የተባለው ይህ ቴክኖሎጂ በጣት ላይ የሚጠለቅ የጋብቻ ቀለበት ሲሆን፤ ይህ ቀለበትም የፍቅረኛሞችን ትክክለኛ የልብ ምት አንብቦ የሚያስተላልፍ ቴክኖሎጂ ነው። አንድ ሰው የስማርት ስልኮች አፕሊኬሽኖችን ከጫነ በኋላ ከዚህ ቀለበት ጋር በማያያዝ ነው መጠቀም የሚችለው። በመቀጠልም ለዚህ በተዘጋጀው ቦታ ላይ የፍቅረኛውን ሙሉ መረጃ መሙላት አለበት። ከዚህ በኋላ ቀለበቱን በጣቱ ላይ በማጥለቅ በማንኛውም ሰዓት ሌላኛው የፍቅር ጓደኛ ያለውን ስሜት የልብ ምቱን በማዳመጥ ማወቅ ይችላል። በዚህ መሠረት የራሱን የስሜት ሁኔታ በቀጥታ ወደ ጓደኛው መላክ ይቻላል፤ የሌላውንም በወቅቱ ማንበብ ይችላል።

ቀለበቶቹ ከብረት እና ከወርቅ የሚሰሩ ሲሆን፤ ከመፋፋቅ እና በውሃ ከመራስ የሚከላከላቸው ነገር የተገጠመላቸው ናቸው። ቀለበቶቹ ከመቶ በላይ ተጓዳኝ ቁሳቁሶች የተገጠሙ፣ ባትሪ ያለው እና ከአፕሊኬሽኖች ጋር የሚያገናኘው ስሜት መለኪያ የተገጠመለት ነው። የቀለበቶቹ ስፋት 12 ነጥብ 1 ሚሊሜትር ሲሆን፤ ውፍረቱ ደግሞ 3 ነጥብ 8 ሚሊሜትር መሆኑ ተገልጿል። አንድ ሰው ቀለበቶቹን መግዛት የሚችለው ለጥንድ የሚሆነ ሁለት ቀለበቶችን ነው። ለቀለበቶቹ የወጣላቸው ዋጋም ከወርቅ ለተሰሩት ከ3ሺህ ዶላር ጀምሮ ሲሆን፤ ከብረት ለተሰሩትም ከ6 መቶ ዶላር ጀምሮ ነው። ኩባንያው ቀለበት እንዲሰራ ቅድመ ትእዛዝ ከነሐሴ ወር ጀምሮ መቀበል መጀመሩን የገለፀ ሲሆን፤ ከመጪው ህዳር ወር ጀምሮ በባለ 18 ካራት ወርቅ የተሰራ የወርቅ ቀለበት እንዲሁም ከታህሳስ ወር ጀምሮ ከብረት የተሰራ ቀለበት ለገበያ ለማቅረብ ማሰቡን በመጥቀስ ያስነበበው ኢዲቲ ሴንትራል ነው።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
593 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us