የ17 ወሩ እርግዝና

Wednesday, 24 August 2016 13:56

ቻይናዊቷ ሴት ለ17 ወራት ያረገዘችውን ልጅ ተገላገለች ይለናል የሲሲቲቪ ዘገባ። በቻይና ቲያንፒንግ ከተማ የሁናን ግዛት ነዋሪዋ ሴት በዚህ ባልተለመደ ክስተትም ስሟን በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ማስፈር ችላለች። ዋንግ ሺ የተባለችው ይህች ሴት በፈረንጆቹ ጥር ወር 2015 የፀነሰችውን ልጅ ከ17 ወራት በኋላ ነበር የተገላገለችው። ሺ ያረገዘችው ፅንስ መውለድ የነበረበት ባለፈው የፈረንጆቹ ህዳር ወር ቢሆንም እርሷ ግን ልጁን መወለድ የቻለችው ባለፈው ነሐሴ 18 ቀን 2016 ነው። የተወለደው ህጻን ክብደትም  3 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም ነው።

ሺ የመውለጃ ቀኗን ቆጥራ ወደ ሆስፒታል ባመራችበት ወቅት ነበር ጉዳዩ የታወቀው። የህክምና ባለሞያዎቹ  የነገረቻቸውን ነገር ማመን ቢያቅታቸውም ሁኔታዎች ግን አምነው እንዲቀበሉ አድርገዋቸዋል። ምርመራ ሲደረግላትም የእንግዴ ልጇ በደንብ አለመጠንከሩ ተረጋግጧል። በዚህም ሳቢያ ልጁ ለመወለድ ዝግጁ እንዳልሆነ ተነገራት። ያም ሆኖ ግን ሺ እና ባለቤቷ ለእርግዝና ክትትል በየሰባት ቀኑ ወደ ሆስፒታል ይመላለሱ እንደነበር ተገልጿል። እርግዝናዋ 14 ወራት ሲደርስ ሺ ልጇን የመውለድ ተስፋዋ እና ጉጉቷ በመጨመሩ በጣም ዝግጁ እንደሆነች ብትናገርም አሁን ደግሞ ፅንሱ አልጠነከረም በመባሏ እንደገና ለተጨማሪ ጊዜ እንድትጠባበቅ መደረጉን ገልጻለች።

“ለረጅም ጊዜ እርጉዝ ሆኜ በመቆየቴ በጣም ሀፍረት ነው የተሰማኝ። በሚቀጥው ወር ጤናማ ልጅ ውጤታማ በሆነ መልኩ እገላገላለሁ የሚል ተስፋ አለኝ” ስትል ከመውለዷ አንድ ወር ቀደም ብላ ሺ ተናግራ ነበር። በዚሁ ወቅትም “ለህክምና ክትትል ብቻ እስከ አሁን ድረስ ከ1ሺህ 500 ዶላር በላይ ወጪ አድርገናል። አሁን ግን ትእግስታችን እየተሟጠጠ ነው” ስትል በነገሩ መሰላቸቷንም ተናግራለች። ሺ እጅግ በተራዘመው እርግዝናዋ ሳቢያ ከገንዘብ ወጪ በተቃራኒው 26 ኪሎግራም ክብደት በመጨመሯ በወለደችበት ወቅት የነበራት የሰውነት ክብደት 78 ኪሎግራም ደርሶ ነበር። ፒፕልስ ደይሊ እንደዘገበው ደግሞ ሺ በዚህ ባልታሰበ ክስተት ቀደም ብሎ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን ማሻሻል ችላለች። ከዚህ ቀደም ለረጅም ጊዜ በነፍሰ ጡርነት በመቆየት ረገድ ክብረወሰኑን ይዘ የነበረችው አሜሪካዊቷ ቢዮላህ ሀንተር የነበረች ሲሆን፤ ይህች ሴት ልጇን በ1945 የወለደችው በእርግዝናው በ375 ቀናት ነበር። ሺ ግን ልጁን ያረገዘችው ለ517 ቀናት በመሆኑ ክብረወሰኑን አሻሽላዋለች።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1057 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ መስከረም አያሌው

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us