አስደናቂዎቹ ትዳሮች

Wednesday, 24 August 2016 13:57

 

የዓለማችን ድንቃድንቅ መዝገብ በዓለማችን ላይ የሚከሰቱ አስገራሚ እና የሰውን ልጅ ድንቅ ችሎታ የሚያሳዩ ነገሮችን በየጊዜው እየሰበሰበ ያሰፍራል። በመዝገቡ ላይ የሰፈሩት እውነታዎች በየአመቱ በየጎራቸው እየተመደቡ ይፋ ይደረጋሉ። እስኪ ለዛሬው ጋብቻ እና ከጋብቻ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ ከሰፈሩ እውነታዎች የተወሰኑትን እናካፍላችሁ።

የዓለማችን ረጅሙ እና አጭሩ ጋብቻ

ለረጅም ጊዜ የጋብቻ ዓለም አብረው በመኖር ረገድ በዚህ መዝገብ ላይ ስማቸውን ያስመዘገቡት ኸርበርት እና ዘልምይራ ፊሻር ናቸው። እነዚህ ጥንዶች በጋብቻው ዓለም 86 አመት ከ9 ወራት ከ16 ቀናት አብረው ኖረዋል። ለዚህን ያህል አመት በጋብቻ የኖሩት ጥንዶቹ በፈብሪዋሪ 27 ቀን 2011 ባልየው አቶ ኸርበርት ህይወታቸው ሲያልፍ እድሜያቸው 106 አመት ሲሆን፤ እነዘህ ጥንዶች ከ86 አመት በላይ በቆዩበት የጋብቻ ጊዜ አምስት ልጆችን ወልደው ነበር።

ከእነዚህ ጥንዶች ተቃራኒ በሆነ መልኩ ደግሞ የአለማችንን አጭር የጋብቻ ጊዜ እንመልክት። ይህ ጋብቻ በተለያዩ የስክሪን ስራው በሚታወቀው ሩፎልፍ ቫሊንቲኖ እና በተዋናይት ጆን አከር መካከል የነበረ ጋብቻ ነው። እነዚህ ጥንዶች የተጋቡት በ1919 ሲሆን ጋብቻቸው የቆየውም ለ20 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። ጥንዶቹ ለመጋባት የወሰኑትን ውሳኔ በደንብ አስበውበት እንዳልወሰነ በመናገራቸው ገና በ20 ደቂቃዎች ውስጥ ጋብቻቸው ፈርሷል።

በስተርጅና የተፋቱ ጥንዶች

በርቲ እና ጆሲ ውድ የተባሉት ጥንዶች እድሜያቸው ከገፋ በኋላ ትዳራቸውን በመፍታት በዚህ ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስማቸውን ያሰፈሩ ጥንዶች ሆነዋል። እነዚህ ጥንዶች በጋብቻ አለም ለ36 ዓመታት የቆዩ ሲሆን፤ እድሜያቸው 98 አመት ሲሆን ግን ይሄንን ጋብቻቸውን አፍርሰው ነው ለዚህ ክብር የበቁት። ትዳራቸውን እንዲፈቱ ያስገደዳቸው ነገር ምን እንደሆነ ግን የተጠቀሰ ነገር የለም።

በተደጋጋሚ ትዳር የመሰረተች ሴት

ሊንዳ ዎልፊ ትባላለች። ይህች ሴት በህይወት ዘመኗ ለበርካታ ጊዜያት ትዳር በመመስረት እና በመፍታት እስከ አሁን ተወዳዳሪ አልተገኘላትም። ሊንዳ ገና የ16 ዓመት ታዳጊ እያለች ነበር የመጀመሪያ ትዳሯን የመሰረተችው። በ16 ዓመቷ የመሰረተችው የመጀመሪያ ትዳሯ በፍቅር ከተጣመረችው ወንድ ጋር የተመሰረተ ነበር። በዚህ መልኩ ጋብቻን አንድ ብላ የጀመረችው ሊንዳ 23 ጊዜ ትዳር መስርታ አፍርሳለች። የመጨረሻ ትዳሯ የነበረውን ጋብቻ የፈፀመችው በ1996 በፈረንጆች ሲሆን፤ ይህን ያደረገችውም ለእውቅና ብላ ነበር። ሊንዳ ካገባቻቸው ወንዶች መካከል ሙዚቀኛ፣ አናጢ፣ ቤት የሌለው ሰው እንዲሁም በወንጀል ተፈርዶበት ቅጣቱን የጨረሰ ሰው ይገኝበታል፣ በመጨረሻ ጋብቻዋም ሰባኪ አግብታ ነበር።

እጅግ በጣም ውዱ ጋብቻ

በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ዋጋ የወጣበት እና እጅግ ውዱ ጋብቻ የአቡዳቢው ሼክ ሞሀመድ ቢን ዘይድ ቢን ሱልጣን አል ናህያን ጋብቻ ነው። ጋብቻው የተደረገው በ1981 ሲሆን፤ በሰርጉ ላይ ከ20 ሺህ በላይ እንግዶችን ሊያስተናግድ የሚችል ስታዲየም ተሰርቷል። በሰርጉ ላይም 50 የአረብና የአፍሪካ አቀንቃኞች የተገኙ ሲሆን፤ የተለያዩ ሀገራት ባለስልጣናትም ታድመዋል። ከእነዚህ ውስጥም 34ቱ በግል ጀት ወደ ሰርጉ የመጡ ባለስለጣኖች ነበሩ። ለዚህ ሰርግ በአጠቃላይ 100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
550 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us