ጃንሆይ ወደ ፓሪስ አይላኩኝ

Thursday, 01 December 2016 15:05

 

ጃንሆይ፣ በዘውዱ በዓል ጊዜ ወደ ፓሪስ ሊልኩኝ ማሰብዎን ማስታወቅዎ ይታወሳል። ይህ ሥራ እንዲቀርልኝ መለመኔና የግርማዊነትዎን ሐሳብ ለማሰናከል የደፈርሁት በሁለት ምክንያት ነበር። መዠመርያ፣ ግርማዊ ፊትዎን አልፎ አልፎ ማየት ለኔ ሕይወት እንደመስኖ ውሃ የሚያለማ ነውና ከፊትዎ መራቁን ስለፈራሁ ነበር። ሁለተኛው ምክንያት፣ የአገር ውስጥ ጶሊቲካ ተካክሎ ካልሄደ በውጪ አገር ለሚላኩ መልክተኞች የፖለቲካ ሥራቸው ተካክሎ ሊሄድላቸው አይቻልምና በአሁኑ ጊዜ በውጪ አገር ሚኒስትሮች መሾም ለመንግስትዎ ኪሳራ እንጂ ጥቅም አይደለም የማለት ሐሳብ ስላለኝ ነበር። በሌላም በኩል ሰው የሆነ ሁሉ የእራሱን እውቀትና ሥራውን፣ ዋጋውንም ለዘወትር ከፍ አድርጎ የሚገምተው ስለሆነ በውጪ አገር ከሚይዝልዎ ሥራ ይልቅ በአገር ውስጥ የምሰራልዎ የሚሻል እርዳታ የሚሆን ስለመሰለኝ ነበር። ምንም የእድሜዬን ልክ ባያሳይ የዘመኔ ቁጥር ስለበረከተ፣ የሸመገለም ሰው ሞቱ በቅጽበት ነውና መቃብሬ አገሬ እንዲሆንልኝ ነበር።

አሁን ግን የእውቀቴንና የጉልበቴን ልክ የሚይዝልዎን ሥራ በረቀቀው ማስተዋልዎ ገምተው የአዘዙኝን ሥራ ለመቀበልና ለመፈፀም የተዘጋጀሁ ነኝ። 66 ዓመት ያሳለፈ ሽማግሌ መሰናበት ቢለምን የሚገባው መሆኑን ባውቅ በምድር ላይ በምንቀሳቀስበት ሰዓት ሁሉ በተቻለኝ ጌታዬን አንድረዳ፣ ፈቃድዎን እንዳደርስ የአደረግሁትን ቃል ኪዳን መፈፀሜ ይሆንልኛል። ከዚህ በኋላ ቀጥዬ የማመለክታቸው ነገሮች ለስራዬ እንዲዘጋጁልኝ ግርማዊነትዎን እለምናለሁ፡-

1ኛ/ የምሰራው ሥራና የምሰራበት ጊዜው እስከ ይህን ያህል ዓመት ተብሎ በጽህፈት እንዲወሰንልኝ የምቆይበትም ጊዜ እጅግ ቢበዛ ከሁለት ዓመት እንዳያልፍብኝ።

2ኛ/ በማናቸውም ሥራዬ እኔን መስሎ የሚረዳኝ መልካም ፀሐፊ በሚበቃ ማደርያ እንዲቀጠርልኝ።

3ኛ/ በጅሮንድ ዘለቀ የተወሰነላቸው ገንዘብ ለኪሳቸው የማይበቃ ሆኖ ከዚህ የቤታቸውን ክራይ ያስወስዳሉ ይባላልና በማደርያ ማነስና ወይም በጊዜያቱ ባለመቀበል የተነሳ ከአሁን በፊት የተላኩትን መልዕክተኞች ያገኛቸውን በኔም በራሴ የደረሰብኝን ችግር አውቃለሁና ሥራውም ለጋስነትና እጀ ሰፊነት የሚያስፈልገው ሥራ ነውና እጅ በማጠር የተነሳ እኔም ተነቅፌ መንግስቴንም እንዳላስነቅፍ የማደርያዬ ልክ ባጭሩ እንዳይወሰንብኝ። ይልቁንም የምቀመጥበት በሦስት አገር ላይ ስለሆነ ከአንዱ አገር ወደ አንዱ አገር መመላለሻው ኪሳራው ከማደርያውና ከሌላው ነገር የኪሳራ ገንዘብ የተለየ መሆኑ ከጃንሆይ እውቀት የተሰወረ አይደለም።

4ኛ/ ልዑል አልጋወራሽ አውሮጳን የጎበኙ ጊዜ ለብዙ ሰው ንሻን ሸልመዋል። የምስክሩን ወረቀት እንልካለን ተባለ እንጂ ለአንድም አልተሰጠ። ከዚያ ወዲህ ተልኮ እንደሆነ አላውቅም። አልተላከ እንደሆነ ግን የተሰጠው ንሻንና የተሸለመው ሰው ቁጥር በነጋድራስ ኃላፊ እጅ ነውና የጃንሆይ ፈቃድ ቢሆን በቁጥሩ ልክ የምሥክር ወረቀቱን ተቀብዬ እንድሄድና እንዳካፍል እለምናለሁ። ይህንን የኋለኛውን ነገር ማመልከቴ እዚያ በደረስሁ ጊዜ የቀረው ቢቀር በፈረንሣዊና በእንግሊዝ አገር የተሸለሙት ሰዎች እኔን መጠየቃቸው አይቀርም በማለት ነው።

ከቤተመንግስት ዶሴ - በመኩሪያ መካሻ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
412 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1001 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us