የዓለማችን ፂማሟ ሴት

Wednesday, 07 December 2016 15:56

 

የ23 ዓመቷን ባለሙሉ ፂም ሴት እናስተዋውቃችሁ። ሔርናም ካኑዑር ትባላለች። ይህች ወጣት ፖሊሳይስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም የሚል ችግር ያለባት እንደሆነች ባለሙያዎች ገልፀዋል። የዚህ ችግር ባህሪይ ደግሞ ከሚገባው በላይ ፀጉር በሰውነት ላይ እንዲበቅል ማድረግ ነው። በዚህም ሳቢያ ሔርናም ከሚገባው በላይ ፀጉር በፊቷ ላይ የበቀለባት ሲሆን፤ ባለሙሉ ፂም ሴትም ተብላለች። ሔርናም በፊቷ ላይ ፀጉር መብቀል የጀመረው የ11 ዓመት ታዳጊ እያለች ሲሆን፤ እያደርም ፀጉሯ በፍጥነት ወደ ክንዶቿ እና ወደ ደረቷ መሰራጨት ጀመረ። በወቅቱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ስለነበረችም ህይወቷ ሁሉ በስቃይ የተሞላ ነበር። “በጣም አስፈሪ ህይወት ነበር። ተኝቼ መንቃትን ጭምር ጠልቼ ነበር” ስትልም የነበረውን አስቀያሚ ህይወት ትገልፀዋለች።

በወቅቱ ሄርናም ይሄንን ፀጉር ለማጥፋት ብዙ ጥረቶችን አድርጋለች። በሳምንት ሁለት ጊዜ ትላጨው ነበር። ይሄ ደግሞ ፀጉሯ የበለጠ እንዲበዛ እና እየሰፋ እንዲሄድ ነበር ያደረገው። በዚህም ሳቢያ ከቤት ለመውጣት እንኳን እየተሳቀቀች የ14 ዓመት ታዳጊ ሳለች ህይወቷን ለማጥፋት ሞክራ ነበር። ነገር ግን ምንም ለውጥ ልታወጣ አለመቻሏን አይታ ራሷን መጠየቅ ጀመረች። ከጓደኞቿ ጋር መገናኘትም ሆነ የወንድ ጓደኛ ማግኘት አለመቻሏ ሌላ ጭንቀት ነበር። በቴሌቪዥን እና በመጽሔት ላይ የምትመለከታቸውን ቆነጃጅት እያየች በራሷ ተስፋ ትቆርጥ እንደነበር ትናገራለች።

ይሄ ሁሉ ሲሆን በተለይ ከታናሽ ወንድሟ እና ጓደኞቿ የምታገኘው አበረታች ድጋፍ ራሷን እንድትቀበል አደረጋት። ልክ 16 ዓመት ሲሞላትም ፂሟን መላጨት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አቆመች። በሰውነቷ ላይ ያለውን ፀጉር ሳትቆርጥ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ እንዲያድግ ማድረጓ የፈጣሪን ፍጥረት ማክበር እንደሆነ በመረዳት እንደተፈጠረች መኖርን መረጠች። በዚህም ሳቢያ ፂሟንም ሆነ ክንዶቿ ላይ ያለው ፀጉር እንደፈለገ እንዲያድግ ፈቀደችለት። “በስተመጨረሻ ራሴን በተፈጥሮ ይዘቴ አገኘሁት” ስትልም የውሳኔዋን ትክክለኛነት ተናግራለች። ሔርናም በዚያ ሁሉ መከራ ውስጥ ማለፏ ለእውቅናም አብቅቷታል። በ2014 የዓለማችን ባለሙሉ ፂም ሴት ተብላ በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ስሟ ሰፍሯል። “አሁን በራሴ እተማመናለሁ። ራሴንም ወድጄዋለሁ” ስትልም ትናገራለች።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
859 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us