አባትና ልጆቹ

Wednesday, 28 December 2016 13:40

 

በድሮ ጊዜ አንድ ሀብታምና አዋቂ ገበሬ ይኖር ነበር። ይህም ገበሬ በርካታ ልጆች ነበሩት። ገበሬው ልጆቹ ጊዜያቸውን በማይገባ ነገር ከሚያባክኑ ይልቅ ሥራ እንዲወዱና እንዲያከብሩ ያለመታከት ይነግራቸው ነበር። እነሱ ግን “እኛ ለምን እንሰራለን። ብዙ አሽከሮች አሉ። እነሱ አይሰሩትምን?” እያሉ ይመልሱለታል።

ለብዙ ጊዜያትም “ከቶ እነዚህን ልጆች ምን ባደርጋቸው ሥራ ይለምዱ ይሆን? እኔ ከሞትኩ በኋላስ እራሳቸውን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?” እያለ ያስብ ነበር።

በመጨረሻም ዕለተ ሞቱ መቃረቡንና ከልጆቹ የሚለይበት ቀን መድረሱን ተረዳ። ስለዚህም ሁሉንም ልጆች ጠራና “ሰማችሁ ልጆቼ! እስካሁን ድረስ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ እያደረግሁ አሳድጌአችኋለሁ። ሥራ ወዳዶች እንድትሆኑና ጊዜያችሁን ባልባሌ ቦታ እንዳታሳልፉም መክሬያችኋለሁ። ከእንግዲህ ሕይወታችሁን መምራት ያለባችሁ እናንተ ናችሁ።” አለና ለጥቂት ጊዜ ፀጥ አለ። ቆይቶም “እነሆ ዕድሜዬ ገፍቷል። ጤንነትም አይሰማኝም። በአጭር ቀናት ውስጥ እንደምሞትም ይሰማኛል። ዛሬ የሰበሰብኳችሁም ሀብቴን የቀበርኩበትን ቦታ ልነግራችሁ ነው” አላቸው።

ልጆቹም ገንዘቡን ለማግኘት በነበራቸው ጉጉት “የት ነው? የት ነው?” በማለት ጠየቁት። አባታቸው ጉጉታቸውን በደንብ ተገነዘበና “የትኛው ቦታ እንደሆነ በትክክል ልነግራችሁ አልፈልግም። ነገር ግን በእርሻዎቻችን ውስጥ መሆኑን ልጠቁማችሁ እወዳለሁ። ስለዚህ ሌላ ማንንም ሳትጨምሩ እራሳችሁ ያረሳችሁት እንደሆነ ወርቁን ታገኙታላችሁ። ስለዚህ እንደሞትኩ በሶስተኛው ቀን ወርቁን ፈልጉት” ብሎ መከራቸው።

ይህንን እንደተናገረም ሕይወቱ አለፈች። በሶስተኛው ቀንም ሁሉም ልጆች በሁሉም እርሻዎች ተሰማርተው በዶማ በመቆፈሪያ በተጠመዱ በሬዎች መሬቱን ገለባብጠው አረሱት። ዳሩ ግን አባታቸው ከመሬት ላይ ቀብሬዋለሁ ያለውን ወርቅ ከቶ ሊያገኙ አልቻሉም።

ተስፋ ቆርጠው ከመሰናበታቸው በፊትም “አባታችን ወርቁን እርሻው ውስጥ ቀብሬዋለሁ ብሎን ነበር። ይሁንና ልናገኘው አልቻልንም። ምናልባት ሲቀብር ያየ ሰው ወስዶት ይሆናል። ስለዚህ ምን ብናደርግ ይሻላል?” ሲሉ ተወያዩ።

በመጨረሻም “አባታችን ለምን ይህን እንዳለን ምስጢሩን የሚፈታልን አዋቂ እስክናገኝ ድረስ ወይን እንትከልበት” አሉና ተከሉበት። ለረጅም ሰዓታት ያለመታከት በመሥራትም ይንከባከቡት ጀመር። ከዱር እንስሳትም ጠበቁት።

የወይን ተክሉም ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ አፈራ። ወደገበያ ወስደው ሲሸጡትም ከፍተኛ ወርቅ አወጣላቸው “እንዴ! ይህን ያህል ማግኘት ከቻልን ለምን እርሻውን እንደገና አናለማውም” ተባብለው ካለፈው ዓመት በተሻለ ሁኔታ ገለባብጠው አረሱት መሬቱ እንዲዳብርም ፍግ ጨመሩበት። የወይን ተክልም ተከሉበት። የበለጠ ምርት አመረቱና በከፍተኛ ዋጋ ሸጡት።

በነሱ አካባቢ የወይን ምርቱን ከፍተኛ ዋጋ የሸጡ እነሱ እንደሆኑም ይነገር ጀመር። በሁለት ዓመታት ውስጥ ከአባታቸው የበለጡ ሀብታሞች ሆኑ። ከፍተኛ ሀብት በማሰባሰባቸውና ሥራ በመውደዳቸውም ሁሉም አከበራቸው። አደነቃቸው።

ከዕለታት አንድ ቀን ተሰባስበው ሲጨዋወቱ አንደኛው ልጅ “አባታችን ደጋግሞ ሥራ እንድንወድና ጊዜያችንን በአልባሌ ስፍራ እንዳናጠፋ አዘውትሮ ይነግረን ነበር። ጠንክራችሁ  መሬቱን ካረሳችሁበትና ወይንም ከተከላችሁበት ብዙ ሀብት ታገኙበታላችሁ ማለቱ ይሆን እንዴ?” በማለት ጠየቀ። ሁሉም “አዎን! ጠንክሮ መሥራትና ጊዜን በከንቱ አለማሳለፍ ያስከብራል” አሉ።

            የኤዞፕ ተረቶች - በተሾመ ብርሃኑ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
401 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1038 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us