ፅናት

Wednesday, 25 January 2017 13:01

 

ወይ በጊዜ ጉዳይ

በስልጣን በንዋይ

ነፃነት ተጥሶ

ውሸት ገኖ ነግሶ

ሀቅ እውነት ኮስሶ

ጠኔ አጣፍቶት ሲሞት

በቅጥፈት ተስቦ. . . ደዌ ቢንጠራወት

አብሬ እሞታለሁ. . . መች ፍንክች እላለሁ።

      ወይ እንደዚህ ሆኖ

      እውነት ተኮንኖ

      ቀጣፊ አንደበቶች. .  ተገምደው ወፍረው

      ጋራ ኮረብታውን. . . ቢይዙት ጠፍረው

      በቀጭኗ ቅዋ. . . የሸረሪት ድሬ

      ካስቀረሁ ይበቃል . . . ትንኝን አስሬ።

ወይ እንደዚህ ቢሆን. . . በአምባገነን ችሎት

ቁጣ ቢያስገመግም . . . በነጎድጓድ ድምጸት

ቃል አለብኝና.  . . እንዳላጎበድድ

ክንዴ አይዝል. . . ልቤ አይርድ

ትንሿን ኮሽታ . . . የሀቅ የእውነት ድምፀት

                        እተነፍሳለሁ

አፌን ብታፈንም. . . በዓይኔ እናገራለሁ።

      ይኸውልህ ቃሌ . . . የኔ ፍልስፍና

      እንኳን መብላትና . . . ቀላሉ ፈተና

      ቢዳፈን ቢከመር. . . የመከራ ቃንቄ

      መተንፈስም ቢሆን. . . የመኖር ጥያቄ

      አላስብለትም . . . ለኔ አይደለም ጭንቄ

      አልኖር ተንፏቅቄ።

ብሎኝ ያ ታላቄ. . . ቃሉን አከበረ

ያ የደሜ ክፋይ . . . ከእውነት አደረ።

            ዋኔዋ - በአስናቀ አካልነህ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
322 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ መስከረም አያሌው

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us