የመኖር ግዴታ

Wednesday, 25 January 2017 12:51

 

የተሟላ ኑሮ ለመኖር የሁሉም ምኞት ነው።  ይህን መልካም ምኞት ከግቡ ለማድረስ ምን ማድረግ ያስፈልጋል? እርሻን ማስፋፋትን? እንዱስትሪውን በያለበት ማቋቋም? ከብትን በብዛት ማርባት? ንግድን ማጠንከር ወይንስ ለሌሎች ተቀጥሮ መሥራት? የተጠቀሱት አቢይ ጉዳዮች ሁሉ አስፈላጊዎች ናቸው።  የመመራመር የመፈልሰፍና የመላቅ ስሜት ያለው የሰው ልጅ መንፈስ በአጭሩ ሊገታ አይችልም።  አካባቢውን ለማሻሻልና የተደላደለ ኑሮ ለመኖር ጥረቱና ትግሉ አይቋረጥም።  ለኑሮው ወሰን ለአስተያየቱ ገደብ እንዲኖረው አይፈለግም።  ሁልጊዜ ወደፊት የመራመድና የአሸናፊነትን ዕድል ለማግኘት የጋለ ምኞቱ ነው።  

ለመኖር የሚያስፈልጉት ግዴታዎች በርከት ያሉ ናቸው።  ከምግብ ከልብስ ከመጠለያና ከሀብት በፊት መሠረታዊ መብት በሕግ የተጠበቀ ሆኖ መገኘት አለበት።  ነፃነት ካለ መብትም አለ።  መብት ካለ ደግሞ ሁሉም አለ።  ትምህርት ፍትሕ፣ ጤና ጥበቃ ቅን አስተዳደርና የሕይወት ዋስትና የሚገኘው በመብት ነው።  ይህም መብት ትርጉም ኃይል የሚኖረው ዘላቂ ነፃነት ተመሥርቶ ሲገኝ ነው።  በኢትዮጵያ ይህ ሁሉ አለ።  በግርማዊ ጃንሆይ መልካም ፈቃድ የመምረጥና የመመረጥ መብት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተሰጥቶአል።  በዚህም ሕግ መሠረት ወንጀል ያልሰራና ብሔራዊ መብቱን ያላጣ ሁሉ አማካሪውን ሊመርጥና ራሱም ለእጩነት ቀርቦ ለመወዳደር ይችላል።

እያንዳንዱ ዜጋ የመኖር መብት አለው።  በመኖርም አገሩ ከእርሱ የምትጠብቀውን ድርሻ መፈፀም አለበት።  በመኖር ወገኖቹ እንዲደሰቱ ቤተሰቦቹ እንዲጠቀሙና አገሩ እንድትኮራበት መጣጣርና ብልጫ ማሳየት ፋንታው ነው።  መኖር ብቻ አይበቃም።  መኖሩን በሥራው በእምነቱና በምግባሩ መግለጽ ይገባዋል።  የአካባቢውን እንቅስቃሴ የኢኮኖሚውን ሁኔታ የፖለቲካውን አዝማሚያ የማኅበራዊውን ኑሮ ማደርጃና የአስተዳደሩን አመራር የሚያጠነክሩትን መሠረተ ጉዳዮች መከታተል የመኖር ግዴታ ነው።  የእያንዳንዱ ዜጋ ሕይወት በዚህ ላይ የተገነባ ስለሆነ ከዚህ ሊርቅ ወይንም ሊያመልጥ አይችልም።  በተቻለው መጠን የተሻሻለና የተቃና ኅብረተሰብ እንዲኖር እንዲጎለምስና እንዲያግድ ምክንያት ለመሆን መተባበር ያስፈልጋል።

የመኖር ግዴታን የሚያሳውቀው ፓርላማ ነው።  በሕዝብ ከሕዝብ ተመርጠው በምክር ቤት የሕዝብ እንደራሴ በመሆን የሚያማክሩት ምርጦች ለመረጧቸው ሰዎች በቅንነት የሚያገለግሉ ሆነው እንዲገኙ ያስፈልጋል።  ሕጋዊ ፓርላማ በጎሳ፣ በሃይማኖትና በቀበሌ፣ ክልል የተወሰነ አይደለም።  ለጠቅላላው ሕዝብና አገር የሚሠራ የማያወላውል መሠረቱ የፀና ግንዱ የጠነከረ አስተያየቱ የበሰለ ውሳኔው የረቀቀና ዓላማው የማይቆጠብ ሆኖ የተቋቋመ ታሪካዊ ድርጅት ነው።  ዘለቄታ አለው።  ሕዝብ እስካለ ድረስ ፓርላማ ይኖራል።  ፓርላማ ከሕዝብ ሕይወት ጋር የተሳሰረ መከታውና ጋሻው ነው።  ጃንሆይ ፓርላማን የመሰለ ታላቅ ስጦታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከቱበት ዋናው ምክንያት ሕዝቡ መብቱንና ግዴታውን አውቆ በነፃነቱ ኮርቶ የመምረጥና ዕድል ኖሮት ዘመኑን በደስታ እንዲያሳልፍ ነው።

የአንድ አገር ዜጎች የሆኑ ሁሉ የተስተካከለ መብትና ግዴታ አላቸው።  ግዴታቸውን አውቀው ኑሮአቸውን ለማቃናት የሚፍጨረጨሩ ሲሆኑ ተጠቅመው ይጠቅማሉ።  በግለሰብ ደረጃ አሳብ እንደሚወጠንና ዘለቄታ ያለው ፕላን እደሚታቀድ የታወቀ ነው።  ይህም ጠቃሚ አሳብ በሥራ የሚገለጥ ሲሆን ከግለሰብ አልፎ ለኅብረተሰቡ የሚዳረስ ይሆናል።  የፓርላማ መኖር ይህን የመሰለውን መሠረተ ነገር ያጠነክራል።  በጋራ ጉዳይ የሚመክሩ የሚወያዩ ሕግ የሚያፈልቁና ውል የሚያፀድቁ የሕዝብ አማካሪዎች ከሕዝብ መካከል ተመርጠው ሕዝብን በመወከል ለሕዝብ የሚናገሩና የሚከራከሩ ናቸው።  ሕዝብና መንግሥት አንድ ነው።  መንግሥት ለሕዝብ የሚሰራውንና የሚለግሰውን ለማሳወቅ የሚችሉት ከሕዝብ የተመረጡ እንደራሴዎች ናቸው።  ሕዝቡ የመኖር ግዴታውን ተረድቶ በሕጉ መሠረት ከተራመደ ሊሻሻልና ሊበለፅግ ሊሰለጥንና ሊደረጅ ይችላል።  የምክር ቤት መኖር ይህን ሁሉ የሚያስገኝ ታላቅ መብት መሆኑን በመገንዘብ በጥንቃቄ እንድንጠቀምበት ያስፈልጋል።  

የጃንሆይ ስጦታ - በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ በ፵ኛው ዘመነ መንግሥት ታተመ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
366 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 945 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us