ክብር ለማዲያትሽ

Wednesday, 08 February 2017 14:45

ስሚኝ እናት ዓለም

እዚህ ካለሁበት፣ ከሀገሬ መዲና፤

ውበት ዘውድ ሲያስደፋ፤ መጥተሽ ባየሽና፤

ምናለ በፎከርኩ

ምናለ በሸለልኩ

አንቺ ትብሽ ብዬ፤

ዕድሜ በለገስኩሽ፤ የ‘ኔን ከ‘ኔ አጉድዬ።

ብታክት ነው እንጂ፤ እንዳይጎድል ሌማቱ፣

ቀና ደፋ ስትል፣ ለቁርስ፣ ምሳ፣ እራቱ፣

እናትስ ቆንጆ ናት፣ እራሷን ብትጠብቅ

ባለ ብዙ ውበት፣ እልፍ ‘ምታስደንቅ

እያልኩ አውርቻለሁ

እናት ውብናት ብዬ

ተወራርጃለሁ።

ቀደሞ ፈጥሯት ኖሮ ለቤቷ፣ ለአዳሟ

ስታትር ስትለፋ፣ ልትኖር እንደ አቅሟ

ለልጆችዋ ስትል፣ ስብር ብሎ ቅስሟ

ትታ እናት ዓለም፣ ለራሷ መኖርን፣

መኖርን ለስሟ

ይኸው እንግዲህ ዛሬ. . .

ውብ ፊቷ በለዘ፣ ዓይኗ በጭስ ሟሟ።

ይሁንና. . .

ገምጋሚ ምን ያውቃል?

ማዲያት ያወጣ ፊት “ውብ አይደለም ይላል!

ባያውቀው ነው እንጂ፣ ማዲያት ላንቺ ፀጋ

እኔን ለማሳደግ፣ የከፈልሺው ዋጋ።

            የጭን ሥር ብሌኖች - በእስጢፋኖስ በፈቃዱ (አቢ)

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
358 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ መስከረም አያሌው

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us