ጅማ

Wednesday, 03 May 2017 12:21

 

በይርጋ አበበ

ጅማ የምትገኘው የጊቤ ካኬን ወንዝ ከደቡባዊ-ምዕራብ ወደ ሰሜናዊ-ምሥራቅ ተከትሎ ባለው ረጅምና ጠባብ መሬት ላይ ነው። እሷም ወደ ጊቤ የሚገቡ ብዙ ትናንሽ ወንዞች በሚመነጩባቸው ተራራዎች ስለተከበበችና ውሃም እንደልቧ ስለምታገኝ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ በጣም ለም ከሆኑ ቦታዎች አንዷ ናት። የተንሰላሰሉትም ተራራ ጫፎች ለዘመናት በቆየ ጥቅጥቅ ባለ ደን ተሸፍነዋል። አየሩ በቂ ርጥበት ያለውና የማይለዋወጥ በመሆኑ በኢትዮጵያ ተራራዎች ደቡባዊ-ምዕራብ፣ ማለትም በከፋ አካባቢ ብቻ የሚበቅለውን ቡና እንኳ ለማልማት ምቹ ነው። ድንቅ የሆነው የተፈጥሮ ሁኔታ ጅማን ከኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ብዙ ሕዝብ ከሚኖርባቸውና ከምርታማ ባታዎች አንዷ ሲያደርጋት፣ ሀብታም ለሆኑ በአካባቢዋ ላሉ አገሮች አማካይ በመሆኗ ደግሞ የንግድ ማዕከል ሆናለች። ከጅማና ጐረቤቶቿ ከሆኑት ከከፋ፣ ከኩሎ፣ ከኰንታና ከሊሙ የሚገኙትን ቡና፣ ዝባድ፣ የዝሆን ጥርስ፣ ማር፣ ሰም፣ እህልና ፈረስ ከባህር ማዶ በሚመጡ ጨርቃ ጨርቅ፣ የጦር መሣሪያና ዶቃ ለመለወጥ አረቦች፣ ሐበሾችና ኦሮሞዎች ወደዚህ ይጐርፋሉ። እነኝህም ውድ ዕቃዎች በጎጃምና በትግራይ በኩል አድርገው ወደ ምፅዋ ወይም በሐረር በኩል አድርገው ሕንድ ውቅያኖስ ዳር ወደሚገኝ አንድ ወደብ ይላካሉ።

***          ***          ***

ዳሩ ግን ከንግድና ከእጅ ጥበብ ጋር አብሮ የባሪያ ንግድና የእስልምና ሃይማኖት መስፋፋታቸው በጣም ያሳዝናል። ዙፋን ላይ ያለው ሥርወ መንግሥትም ሆነ መላው ሕዝብ የእስልምና ሃይማኖት ጽኑ ተከታዮች ከሆኑ ይኸው ሦስት ምዕተ ዓመታት አልፏቸዋል።

***          ***          ***

የጅማ ሕዝብ ባለፀጋ በመሆኑ ሃብቴን አጣለሁ ብሎ ስለሚፈራ የተዋጊነት ወኔው ሁልጊዜም ዝቅተኛ ነው፤ ስለዚህም ኃይለኛ ለሆኑት ጎረቤቶቹ ማለትም መጀመሪያ ለከፋው ንጉሥ፣ ከዚያም ለጎጃሙ ንጉሥ፣ በመጨረሻም ከ1878 ዓ.ም ጀምሮ ለንጉሥ ምኒልክ እንደገበረ ነው። በአሁኑ ጊዜ ጅማ በውስጥ አስተዳደር ረገድ ራሷን የቻለች ሆና ለንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ግብር የመክፈልና ለአገሪቱ ጠቅላላ የሆኑ ሕጎችን የማክበር ግዴታ አለባት። የበላይ ዳኝነትና የሞት ቅጣት የመፍረድ ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነው።

ዐፄ ምኑልክ ባሪያ ሲሸጥ የተገኘ በሞት እንዲቀጣ በመደንገግ የባሪያ ንግድን ከከለከሉ በኋላ ጅማ ከዚህ ንግድ ዋና ማዕከሎች አንዷ በመሆኗ በብልጽግናዋ ላይ ትልቅ ጉዳት ደርሷል። እንደዚሁም በፊት በጅማ ውስጥ በጣም ተስፋፍቶ የነበረውን በቅጣት መልክ ወንጀለኞችን ባሪያ የማድረግ ልማድንም ንጉሠ ነገሥቱ አስቀርተዋል። ወንጀል ሠርተው የተፈረደባቸው ሰዎች የንጉሡ ንብረት በመሆን በቀላሉ የማይገመት ገቢ ያስገቡለት ነበር። አሁን ግን የጦር ምርኮኞች እንኳ እስከ ሰባት ዓመት ብቻ አገልግለው ነፃ ይሆናሉ። እነኝህ በጎ መንፈስ ያላቸው ሕጎች በመደንገጋቸው ባርነት ከነጭራሹ የጠፋ ሊመስል ይችላል። ዳሩ ግን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ካየን የባሪያ ልጆችና የልጅ ልጅ ልጆች አሁንም ቢሆን የእኛ ገበሬዎች በገባርነት ዘመን ይገኙበት በነበረው የጥገኝነት ሁኔታ ይገኛሉ። የሚኖሩትም በንጉሦቹ መሬት ላይ ሲሆን፣ በወር ስምንት ቀን ለእነሱ ከመሥራታቸውም ሌላ የተቀረውንም አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፉት ለጭቃ ሹሙ አገልግሎት በመስጠት ነው። አንዳንድ የድሮ ባሮች በንጉሡ ግቢ ውስጥ ሥራ ቤት ሆነው ያገለግላሉ።

የጅማ ርዕሰ ብሔር የካኬ ዘር የሆነውና ዙፋኑን ከአባቱ ከአባ ዱላ የወረሰው አባ ጅፋር ነው። በአባ ዱላ ዘመን ጅማ በከፋ ሥር የምትገኝ ጥገኛ የንጉሥ መንግሥት ነበረች። አባ ጅፋር ከነገሠ በኋላ ጅማ በመጀመሪያ የጎጃሙ ከዚያም ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት የሸዋው ንጉሥ የምኒልክ ገባር ሆነች። ጅማ የምኒልክ ገባር ከሆነች ከሁለት ዓመታት በኋላ አባ ጅፋር የሐበሻ ወታደሮችን እያባበለ በማስኮብለል ሠራዊቱን ለማጠናከር በመሞከሩ ዐፄ ምኒልክ ለሁለት ዓመታት አንኮበር ላይ አሰሩት። አባ ጅፋር የእሥራት ጊዜውን ሲጨርስ ዐፄ ምኒልክ መልሰው ዙፋኑ ላይ ያስቀመጡት ሲሆን፤ እሱም ይህን ዓይነት ጥሩ ትምህርት ካገኘ በኋላ በጣም ታዛዥና ግብሩን በጥንቃቄ የሚከፍል ገባር ሆነ።

ከዐፄ ምኒልክ ሠራዊት ጋር /አሌክሳንደር ብላቶቪች፤ ትርጉም በአምባቸው ከበደ/¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
431 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 914 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us