ስለ አንድ ሽማግሌ ሰውና ስለ አንዲት ሴት ልጅ

Wednesday, 17 May 2017 12:29

 

በመስኮብ ሀገር ሦስት ሴቶች ልጆች ያሉት አንድ ሽማግሌ ነበረ። ከሦስቱ አንዲቱ በመልኳና በጥበብዋ እጅግ ስመ ጥሩ ናት። አንድ ቀን ወደ ገበያ ሲወጣ ልጆቼ ሆይ፤ ከገበያ ምን ገዝጬላችሁ ልምጣ አላቸው። ሁለቱ ልጆቹ ጌጥ ገዝተህልና ና አሉት። አንዲቱ ግን እኔ ምንም አልፈልግም፤ ነገር ግን የምመክርህን ምክር ስማኝ አለችው። ለጊዜው ነገሩ ከበደው፤ ነገር ግን ልጁ እጅግ ብልህ መሆኗን ያውቃልና ይሁን ንገሪኝ አላት። ወይንማውን በሬ ወደ ገበያ አውጥተህ ስትሸጥ፣ ዋጋ ንገር ያሉህ እንደ ሆነ የንጉሡን ግራ ዓይኑን አምጡና በሬውን ውሰዱ በላቸው አላቸው። እርሱም በገበያ ተቀመጠና የበሬውን ዋጋ ንገር ሲሉት ልጁ እንደመከረችው የንጉሡን ግራ ዓይኑን አምጡና ውሰዱት ይል ጀመረ።

ይህን ወሬ ንጉሡ ስምቶ እጁን ይዛችሁ አምጡልኝ ብሎ አዘዘ። ሽማግሌውም በቀረበ ጊዜ ንጉሥ ሆይ፤ እንደዚህ ያደረገችኝ ልጄ ናትና ማረኝ እያለ ይለምን ጀመረ። ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ ሔደህ ልጅህን አምጣትና እምርሃለሁ አለው። ሽማግሌውም እያዘነና እየተንቀጠቀጠ ሔዶ ልጁን ይዞ ወደ ንጉሡ ቀረበ። ንጉሡም ልጅቱን ባያት ጊዜ ለበሬው ዋጋ የንጉሡን ግራ ዓይን አምጡና ውሰዱ በላቸው ብለሽ ለአባትሽ የመከርሽው ስለምን ነው አላት።

ንጉሥ ሆይ፤ አልቀጣሽም ብለህ ማልልኝና እነግርሃለሁ አለችው። አልቀጣሽም ብሎ ማለላት።

ንጉሥ ሆይ፤ ድኃና ጌታ ተጣልተው ወዳንተ የመጡ እንደ ሆነ በቀኝ የቆመውን ጌታውን ብቻ ታያለህ እንጂ፣ በግራ የቆመውን ድኃውን አታይም፤ ስለዚህ መቸም ግራ ዓይንህ ሥራ ካልያዘልህ ብዬ ነው አለችው።

ንጉሡም የልጅቱን ንግግር ሰምቶ እጅግ አደነቀ። ወዲያውም ወንድ ልጁን ጠርቶ ልጄ ሆይ፤ በመልክና በእውቀት ከርሷ የምትሻል ሴት የለችምና እርሷን አግብተህ መንግሥቴን አዘህ ኑር አለው። ልጁም እርሷን አግብቶ እርሱ ንጉሥ እርሷ ንግሥት ተብለው ኖሩ።

ልጆቼ ሆይ፤ መልካም ንግግርና ጥበብ ሰውን ታስከብራችና ንግግራችሁ ሁሉ፤ በመልካምነትና በጥበብ ይሁን። የጥበብም መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።

            (ወዳጄ ልቤና ሌሎችም - ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ)

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
398 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 918 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us