ወፈፌው መካሻ

Wednesday, 16 August 2017 12:08

 

…… መካሻ ከወይዘሮ በለጡ ቤት ቀጥታ ያመራው ወደ እነ የሺ ጎጆ ነበር። እቦታው ደርሶ ወደ ውስጥ ገባ ሲል፤ የሺ ፍራሹ ላይ በአንቅልፍ እንደማንጎላጀጅ እያደረጋት ነበር።

ቅድም ወደ ነበረበት እንጨት ላይ መካሻ ሲቀመጥ፤ የሺም ጋደም ካለችበት ፍራሽ ላይ ቀና ብላ ዓይኖቿን በእጆቿ ጠራረገችና ተደላድላ ተቀመጠች።

“ደረጀን አገኘኸው?” ስትል ጠየቀችው።

 

“አላገኘሁትም። አሁን ተመልሼ የመጣሁት ቅድም ያቋረጥኩትን የሹመቴን ነገረ ስራ ለመጨዋወት ነው” አላትና ከቂጡ ደልደል ብሎ እንደመቀመጥ ብሎ “ሽማግሌው በእሷ በተኛችው ህጻን የሰራውን ስራ፤ ማለቴ የወንጀል ባለ ድርሻነቱን ታሪክ አንድ ሳታስቀሪ ንገሪኝ” አላት።

 

“ልነግርህ ስል አንተ ታች ላይ ትላለህ” አለችው።

“ይሄው አሁን መጥቼያለሁ፣ ንገሪኝ።”

“ያው ቅድም እንደ ጀመርኩልህ ሽማግሌው ‘ከዘመዶችሽ ልጆች አንዱን አሳድጋለሁ ብለሽ አምጥተሽ ለምኚበት’ ቢሉኝ፣ ‘እኔ ምን ዘመድ አለኝና ነው፣ ብዙዎቹ በድረቁም በበሽታውም አልቀዋል። ያሉትም ቢሆን ድህነቴን ስለሚያውቁ ምን ብለው ልጆቻቸውን ለእኔ ይሰጡኛል’ ብላቸው፤ ‘እንደዛ ከሆነ በሆነ ዘዴ አንድ ህጻን ስረቂና የራስሽ ልጅ አስመስለሽ ለምኚበት፤ ሟቿ ባለቤቴ በሰማይ ቤት ነፍሰን ይማረውና በዚህ፣ በዚህ ጎበዝ ነበረች። እሷ በሆነ ዘዴ ባመጣችው ህጻን ነው ደህና ገንዘብ ተገኝቶ፤ ነፍስ ውጪ፣ ነፍስ ግቢ ሲባል የበረው ቀርቶ፣ ምግቡም ሕክምናውም እንደ ልብ ተገኝቶ የተረፍኩት’ ሲሉኝ ግዜ…” መካሻ በስሜት የሺን አቋርጦ “ተረምረም” አለ ጮክ ብሎ።

 

መካሻ እንደ ማሰብ ብሎ “ቆይ ግን ደረጀ ህጻን በመሰረቁ ሃሳብ የነበረው አቋም ምን ነበር? መቼም በሃሳቡ ቢስማማበት አይደል እንዴ ታቦት እናነግሳለን ብላችሁ ልጅ ለመስረቅ ገጠር ድረስ ተያይዛችሁ የሄዳችሁት?” ሲል ጠየቃት።

 

“ለደረጀ ሽማግሌው የመከረኝን ሁሉ ግልጽ አድርጌ አልነገርኩትም። ‘ጠራ ውስጥ የህዳር ሚካኤልን ለማንገስ ብዙ ሰው ስለሚሄድ ደህና ፍራንክ አናጣምና እንሂድ እና እንለምን ብየው ነው ተያይዘን የሄድነው’ አለችው።”

“አንቺም የሽማግሌው ተባባሪ ነሽ ማለት ነው” ሲል ለራሱ አጉተመተመ። የሺ መካሻ ምን እንዳለ አልሰማችውም።

 

የሺ እሩቅ ሀገር የሄደች ይመስል በሃሳቧ ጭልጥ ብላ ከሄደችበት መለስ ስትል “እዛ እንደ ደረስን የሆኑ ሰዎች ጋ ጠጋ ብለን እንዲያሳድሩን ጠየቅናቸው። እሺ ምን ከፋን ብለው አሳደሩን። ያሳደሩን ሰዎች ንጋት ላይ ባልየው ቀደም ብሎ ወደ እርሻው፤ ሚስትየዋም ከተል ብላ ‘ትንሽ እምትቆዩኝ ከሆነ፤ ህጻንዋን እያያችሁልኝ፤ ውሃ ቀድቼ አሁን መጣሁ’ ብላ እንስራዋን ተሸክማ ከቤቱ ስትወጣ፤ እኔ ፈጥኜ ብድግ አልኩና ህጻንዋን በራሷ አንቀልባ አዝዬ ‘ተነስ እንውጣ አልኩት’። ደረጀ እንደ እብድ ፈጦ ተመለከተኝ። ቀደም ብዬ ከቤቱ ስወጣ ሲያየኝ የደመ ነፍሱን ተከትሎኝ መጣ። ኋላ ላይ፣ መንገድ ከገባን በኋላ ነው፣ የኔንም የእሱንም አቅመ ደካማ መሆናችንን አስረድቼው፣ ነግሬው፣ ቢያንስ ህጻንዋ ጦም አታሳድረንም ብዬ ነው ያሳመንኩት። በእርግጥ እሱ ሌላም ምክንያት ነበረው” አለችው።

 

“አሄሄ! የምን መሸዋወድ ነው? ኮረፌውን እና አረቄውን እንደልቡ ለመጋት ነው እንጂ ህጻን ለመስረቅ ደግሞ ምን ምክንያት ይኖራል?” አላት በቁጭት።

“ሁሌ ልጅ፣ ልጅ የሚለውን ንዝንዙን አሁን አንተ ጠፍቶህ ነው፤ እኔን የምትጠይቀኝ?” በማለት ብስጨትጭት አለች። “ልጅ ከጭቃ ተጠፍጥፎ አይሰሩት ነገር። ብንለው፤ ብንሰራው አልሆነልንም። ለዚህም መሰለኝ አሱም ልጅ አገኘሁ ብሎ በህጻንዋ መሰረቅ ዝም ያለው።” ….. (ገጽ 76-77)

(ምንጭ- ከቀለመ ገብሬ “ወፈፌው መካሻ” ልቦለድ መጽሐፍ ተቀንጭቦ የተወሰደ)¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
140 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1064 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us