የጦርነት ፀሎት

Wednesday, 30 August 2017 12:57

 

ኑና እንገዳደል በሉ እንተላለቅ፤

በሰላ ቆንጨራ እንሞላለቅ፤

በሴት፣ በህፃናት ደም እንጨማለቅ፤

ሬሳን በሬሳ እንረማመደው፤

አንገቱን ቀንጥሰን እጁን እንጉመደው፤

እንደ ሰባ ሙክት ሰውን እንረደው።

ዋይታና ሰቆቃ ይሙላልን በአገሩ፤

ጥንብ አንሳና ጅቦች ደጃችን ይስፈሩ፤

ሬሳው ይጎተት በየመንገዱ ላይ፤

ልባችን ደንድሮ ይስከር በሰው ስቃይ።

አስክሬን በክብር ቀባሪ እንዳያገኝ፤

በየሜዳው ይውደቅ በግራና በቀኝ፣

ኑና እንገዳደል! በሉ እንተራረድ!

በቆምንበት ምድር አሁን ቁጣ ይውረድ፤

የእሳት ላንቃው ይንደድ!!

ቀዬውን ያውደው የሙታኑ ሽታ፤

የተረፈው ይለቅ በአተት፣ በበሽታ!!

በካራ፣ በሜንጫ አይኖች ይጎልጎሉ፤

ወንዞቹ በሬሳ በሰው አካል ይሙሉ፤

እንኳን ቅጠልና ሳሮች አይብቀሉ።

ኑና እንተላለቅ ሆ! ብለን በቁጣ!

የሰው ልጆች ግንባር በጥይት ይበጣ!

ሆዱ ተተልትሎ አንጀት፣ ጉበት ይውጣ!!

በአገሩ ላይ ይፍሰስ ጥይት እንደቆሎ፣

ሰላምና ፍቅር ይታይ ፍትህ ጎድሎ፤

የሰው ልጅ ሰውነት ጎዳና ይሰጣ፣

ጨርሱኝ እያለ ነፍሱ ግን አትውጣ፤

የጥላቻን ማሳ በጎሳ እያለማን፤

የሰውን ልጅ ህይወት እንሙላው በእርግማን!!

ደግሞ ከዚህ መለስ ብጥብቱ ይምራ፤

ሄትለርን ቀኝ አድርጎ ሙሶሎኒን ግራ፤

በሉ እንተባበር ለዚህ ሁሉ ጣጣ፣

ህጻናት ግንባር ላይ ጥይቱ ይንጣጣ!!

ደሞ እንደጥሩ ጠጅ እንደብርዝ ይጠጣ፣

ሰው መሆን ትርጉሙን የሚያውቅ እስኪመጣ።

      የሰው ልጅ ፊት ከስሎ፤ መልኩ ከአመድ ይንጣ፣

      ስጋው በቁም አልቆ አጥንቱ ደጅ ይውጣ!!!

      “ይሄ ሁሉ ለምን?” የሚል እስኪመጣ፤

ሰው መሆን ትርጉሙን የሚያውቅ እስኪመጣ። 

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
82 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us