የህዝብ ቁጥር

Wednesday, 13 December 2017 12:39

 

መጀመሪያ መንግስት የሆነ ሁሉ ያገሩን የህዝብ ቁጥር አውቆ መቀመጥ የግድ ነው። ከኛ መንግስት በቀር የህዝቡንም ቁጥር የማያቅ መንግሥት የለም። ቢኖርም መሳቂያ ነው። አሁንም የህዝባችንን ቁጥር ቢጠይቁን ይህን ያህል ነው ብለን መናገር አንችልም። ይህም እንደ ውርደት ይቆጠራል።


ሁለተኛው ብዙ ሥራዎች ሥራ ፈቶች፣ አውታች፣ ትውልዳቸውና አገራቸው ማይታወቅ ሰዎች ከከተማችን እየገቡ በገንዘብ፣ በሴት፣ በድንገት እያደረጉ አቁስለው ገድለው በከንቱ የሰውን ደም አፍሰው ተዛውረው ይቀመጣሉ። ከዚህም በፊት እየገደሉ የጠፉትን አይተናል ሰምተናል። አሁን ከከተማው ብዙ ሥፍራዎች አሉ። ከተማው እየሰፋ እነርሱም እየበዙ ይሄዳሉ፤ ብዙም ስርዓት ያጠፋሉ። ነገር ግን የከተማውና የባላገሩ ሰው ሁሉ ከቤተሰብ ጋር ተፅፎ የውጭ ሰው እንዳያስገባ፣ ቢያስገባም ለዘበኛ ሹም እያስታወቀ የሆነ እንደሆነ ሥራፈቱና አውታታው፣ ቀጣፊው፣ ተንጠርጥሮ ይለያል። ከዚህ ወዲያ የግዛት ሚኒስትር ሹሞች የተወለደበትን አገር፣ ዘሩን፣ ስሙን፣ ያባቱ ስም ይጠይቁታል። የአገሩን ስምና የአባቱን የራሱን ስም ይነግራቸዋል። ከዚህ በኋላ እራሳቸውም በመዝገባቸው እየፈለጉ ያገሩንና የእርሱን፣ የባቱን፣ የዘሩን ስም ያገኙታል። ከዚህ ወዲያ ሲወሰልት ካገኙት ወደ አገርህ ተመልሰህ ትገባ? ወይስ ከዚህ ስራ ትፈልጋለህ? ብለው ጠይቀውት የመረጠውን አንዱን ይሰጡታል። ከዚህ ወዲያ ሲወሰልት ያገኙት እንደሆነ በሥርዓቱ መሠረት ይቀጣል። ስለዚህ የአገር ሁሉ ቢፃፍና ቁጥር ቢታወቅ ለሁሉ ነገር ይበጃል። ደግሞ በከተማ የሚሞት ሰው ሁሉ በሞተበት ቀን ዕለቱን፣ ያባቱና የራሱ ስም ለሹሙ ለዘበኛ አለቃ እየተነገረ እንዲፃፍ ሕግ ማቆም የግድ ያስፈልጋል።


ይህንን ሁሉ ማድረግ የሚገባው የግዛት ሚኒስቴር ነው። እንግዲህ ሕዝብ ሁሉ ይቆጠር ይጻፍ እያለ ለአገሩ ገዥዎችና ለሹማምንት ወረቀት በማተም ትዕዛዙን ይሰጣል።


የግዛት ሚኒስቴር ማለት የህዝብን ጉዳትና ጥቃት፣ የመንግስትንም ከብርና ጥቅም፣ የአገርንም ሥርዓት ጸጥታንም የሚጠብቅ ታላቅ የዘበኛ ሹም ማለት ነው። ስለዚህ እርሱ የማይገባበት የመንግስት ሥራ የለምና ሹም የተባለ ሁሉ የርሱን ቃል ይሰማል። በሥርዓትም፣ በግዛትም፣ በፍርድም በሁሉም ነገር ያስተዳድራል። የሚመጣውንም ትውልድ እግዜር እንደፈቀደ ያድርገው ያልን እንደሆነ ሕዝቡም እረኛ የሌለው በግ ይሆናል። ኢትዮጵያም ያሚን ባሏ የሞባት ልጅ እርግጥ ትሆናለች። ልጅ ከእዳ በቀር ምንም ገንዘብ ሳይተውላት እንደሚሞት አባት ትሆናለች። ደግሞም ለአባቱ አገር የማይዋጋ የማያስብ ሰው በእግዜር ዘንድ የተወደደ አይሆንም። የአውሮፓውያን አባቶች እኛ እንብላ፣ እንጠጣ፣ እኛ እናጊጥ፣ የሚመጣው ትውልድ ራሱ ይወቅበት ብለው አስበው ቢሆን እንኳን የሰው አገር ሊፈልጉ አገራቸውንም እስካሁን ባልቻሉ ነበር። ይህንን ሁሉ መናገራችን የግዛት ሚኒስትር ንጉሳቸውን ይወዳሉ፣ ለአገራቸው ያስባሉ፣ ለድሃ ያዝናሉ የሚል ዝና ብንሰማ ነው እንጂ ሌላ መኳንንት ይህንን ቢነግሩት ይሰራዋል ብለን አናስብም። ይህንንም የተፃፈውንም ቃል አስተውለው እንዲያነቡት እለምናለሁ።


/ሰኔ ፩ ቀን ፲፱፻ ዓ.ም/ (1900)።
ከቤተ መንግስት ዶሴ - የብላታ ወልደማርያም መዘክር

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
114 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1094 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us