የጃንሆይ ምስክሮች

Wednesday, 24 January 2018 14:19

 


ዜድ.ቲ.

 

በሹምሹሩ ሰዓት፣ ጃንሆይ እጅ ከነሱት ራሶች መሀል ለትልቅ ቦታ የመረጡትን ጭንቅላት ይመለከታሉ። ሆኖም ከዛ በኋላ ያ አስተዋዩ የግርማዊ ጃንሆይ አይን እንኳ፣ ያ እራስ ምን እንደሚሆን ለመገመት አይቻለውም። ያ በዛ አዳራሽ ውስጥ ጎንበስ ቀና ሲል የነበረ ጭንቅላት በሩን አልፎ ሲወጣ ሽቅብ ይመዘዝና ፍፁም በመገተር የወሳኝነት ቅርጽ ይላበሳል። አዎ ጌታዬ፣ የንጉሱ ሹመት ሃይል እጅግ አስገራሚ ነው። አንድ ተራ ጭንቅላት፣ በጭንቀትና በፍርሃት ይወዛወዝ የነበረ፣ ለመዞርና እጅ ለመንሳት ዝግጁ የነበረ፣ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ በሹመት ከተቀባ በኋላ እንቅስቃሴው ውሱን ይሆናል። አሁን በሁለት አቅጣጫ ብቻ ነው የሚንቀሳቀሰው። ወደ መሬት በጃንሆ ፊትና ሽቅብ ወደ ሰማይ በሌላው ሰው ፊት። አንዴ በዛ እንቅስቃሴ ከተቃኘ በኋላ ያ ጭንቅላት ዳግም እንዳሻው አይንቀሳቀሱም። ለምሳሌ ድንገት ከኋላ ሆነህ ብትጠራው አንገቱን ከማዞር ይልቅ ሙሉ አካሉን ነው የሚያዞረው።


የአዳራሹ የፕሮቶኮል ሹም ሆኜ እሰራ በነበረ ጊዜ ይህን ሁኔታ በደንብ አስተውዬዋለሁ። ሹመቱ መሠረታዊ የሆኑ አካላዊ ለውጦችን በሙሉ በተሿሚው ላይ ያስከትል ነበር። ይህ በጣም ያስገርመኝ ስለነበር ሁኔታውን በደንብ ተከታትልኩት። በመጀመሪያ የሰውየው ሙሉ አካል ይለወጣል። በመጀመሪያ የሰው ቅርጽ የነበረው አካል አሁን አራት ማዕዘን የወረቀት ቅርጽ ይሆናል። ግዙፍና የተረጋጋ ማዕዘን፣ ይህ የመረጋጋትና የስልጣን ክብደት ምልክት ነው። ይህ ቅርፅ የማንም ሰው ቅርፅ ሳይሆን የክብርና የኃላፊነት ቅርፅ እንደሆነ ማየት እንችላለን።


ያንን ቅርፅ አጅቦ የተረጋጋ እንቅስቃሴ ይመጣል። በጃንሆይ የተመረጠ ሰው አይቦርቅም፣ አይዘልም፣ ወይም አይሮጥም። እርምጃው የተረጋጋ ነው።


የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ያለውን ቁርጠኝነት ለመገልፅ ሰውነቱን ላመል ወደፊት ጎበጥ አድርጎ በእግሮቹ መሬቱን ቆንጥቶ ይቆማል። ከዚህ በላይ የፊቱ ሁኔታ ፈፅሞ የተረጋጋና እንዲያውም ኮስተርተር ያለና ፀጥ ያለ ይሆናል። በአጠቃላይ እንግዲህ ይህ ሁኔታ ከሌላው ጋር የስነልቡና ግንኙነት ላለመፍር የሚደረግ ነው። አንድ ሰው ከዚህ ፊት አጠገቡ ሆኖ መዝናናት፣ ማረፍ ወይም ትንፋሹን መሰብሰብ አይችልም። አስተያየቱ ይለወጣል፣ ርዝመቱና ማዕዘኑ ይለዋወጣል። አስተያየቱ ፈፅሞ ሊደረስበት የማይችል ነጥብ ላይ ያርፋል።


አነጋገሩ ጭምር ነው የሚቀየረው። ጎርነን ያለ ድምፅ ማውጣት፣ ጎሮሮን ማጥራት፣ ቆም ማለት፣ የድምፀት ለውጥ የተወሳሰቡ ቃላትን መጠቀም ይጀምራል። በአጠቃላይ ሁሉን ነገር ከሌላው ሰው የበለጠ አውቃለሁ የሚለው አስተሳሰብ ቀላል፣ ግልፅና ሙሉ አረፍተ ነገሮችን ይተኳቸዋል። ስለዚህ እኛ ከሚፈለገው በላይ ይሆንብንና እንሄዳለን። እሱም ጭንቅላቱን ሽቅብ ከፍ በማድረግ እንድንሄድ ፈገግ ይላል።


ሆኖም ጃንሆይ ሹመት ብቻ አይደለም የሚሰጡት። ታማኝነት አጉድሎ ሲገኝ ሽረትም አለ። ስለ ጋጠወጥ አነጋገሬ ይቅርታ አድርግልኝና አሸቀንጥረው መንገድ ላይ ይወረውሩታል። ከዛ አስገራሚ ክስተት ይታያል። ልክ ከመንገዱ ሲያልፍ ሹመቱ ያመጣው ለውጥ ብን ብሎ ይጠፋል። አካላዊ ለውጦቹ ራሳቸውን ይተካሉ። ያ መንገድ ላይ የተጣለ ሰው ተመልሶ ራሱን ይሆናል። እንዲያውም በጣም የተጋነነ ከሰዎች ጋር የመኖር የመግባባት አዝማሚያ ያሳያል። ልክ ሁሉንም ነገር ወዲያ ጥሎ ሊነሣ እንደማይፈልግ በሽታ “ሁሉንም ርሱት” ሊል የፈለገ ይመስላል።
ምስጢራዊ ንጉስ ቀነዳማዊ ኃይለስላሴ - በዮሐናን ካሣ

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
106 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 938 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us