You are here:መነሻ ገፅ»ርእሰ አንቀፅ
ርእሰ አንቀፅ

ርእሰ አንቀፅ (217)

 

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት ባደረገው ስብሰባ በሀገሪቱ ባልተለመደ ሁኔታ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጦችን ያመጡልኛል ያላቸውን ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡

ይኸውም፣ በመንግስት እጅ ያሉ ሆቴሎች፣ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ እና የተለያዩ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች፥ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በአክስዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ ውሳኔ አሳልፏል። እንዲሁም፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክስዮን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች እንዲተላለፍም መወሰኑ ይታወሳል፡፡

የሀገሪቱ የብሄራዊ የፕላን ኮሚሽንም፣ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በወጭ ንግድ መዳከምና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ አደጋ ውስጥ መግባቱን አምኗል፡፡ ባለፉት ጥቂት አመታት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች የሚገኘው ገቢ በአማካይ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ላይ ሲሆን፣ ከውጭ ምርቶችን ለማስገባት የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ ደግሞ 16 እስከ 17 ቢሊየን ዶላር መሆኑን ግልፅ አድርጓል፡፡

ኮሚሽኑ፣ የሀገሪቱ አጠቃላይ እዳ 26 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ተሻግሯል ብሏል። ይህ ሁኔታ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት ጋር ሲታይ የውጭ ባለሀብቶችን እንዳይመጡ እና መተማመንን ያጠፋል ሲል ስጋቱን አስቀምጧል፡፡

ይህንን ግልፅነት የሞላበት የመንግስት መረጃ ለሕዝብ መቅረቡ፣ በመንግስትና በሕዝብ መካከል መተማመን ይፈጥራል፡፡ የቀረበውም የመንግስት የወጪገቢ ሰነድ ትርጉም የሚሰጥ ነው፡፡ የበለጠ ከህዝብ ጋር በመመካከር ጉዳዩን በማበልጸግ የተባለው የፕራይቬታይዜሽን ፖሊሲ አማራጭን መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ሕዝብም ጉዳዩን ሲያውቀው መንግስትን የመታገስና የማገዝ አማራጮችን ይመለከታል፡፡

ኮሚሽኑ፤ “ላለፉት አመታት በጥሩ ሁኔታ የመጣውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ውድቀት ውስጥ እንዳይገባም የአሁኑ ፕራይቬታይዜሽን እንደ መፍትሄ መቀመጡን” ያስረዱበት መንገድ መፈተሽ አለበት፡፡

በእኛ እምነት፣ የሀገሪቷ ኢኮኖሚ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ የገባው፣ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ አራማጆች በሀገሪቷ እድገት ውስጥ ከፍተኛ ተዋናኝ ኃይል በመሆናቸው ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች በመጀመሪያ ደረጃ በሕግ የበላይነት መስመር ማስያዝ ሳይቻል፤ የህዝብ ሐብትን በሽርክና በመሰጥ በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ የተጀመረውን ልማት ማስቀጠል አይቻልም፡፡ አለመቻሉም ብቻ ሳይሆን፤ በቀጣይ በሀገሪቷ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖራቸውን ሚና አሁን ላይ ሆኖ መናገር በጣም ከባድ በመሆኑ፣ ቅድሚያ በኪራይ ሰብሳቢው ኃይል ላይ የህግ የበላይነት ሊተገበር ይገባል እንላለን፡፡

 

ከቅርብ ወራት ወዲህ እየተባባሰ የመጣው ዋጋ ንረት አሳሳቢና አስፈሪ ሆኗል። ለየት ባለ መልኩ የእህልና የምግብ ውጤቶች የዋጋ ውድነት መታየት ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል ጭምር የጎዳ ሆኗል። በአጭሩ በአሁኑ ጊዜ ዋጋ ያልጨመረ ሸቀጥ ፈልጎ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል። የሕዝብ የዕለት ተዕለት ምግብ የሆነውና መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ አደርግበታለሁ የሚለው የዳቦ ምርት ሳይቀር ዋጋ በመጨመሩ አብዛኛው በደመወዝ የሚተዳደር የህብረተሰብ ክፍል መኖር ወደማይችልበት ደረጃ እያንደረደረው ነው። በአሁኑ ወቅት አንድ እንቁላል ዋጋ ከብር አምስት እየዘለለ ነው። የትራንስፖርት፣ የትምህርት ቤቶች ክፍያዎችና የመሳሰሉት በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመሩ ነው።

በተለይ ከዶላር ምንዛሪ ወይንም ከብር መውደቅ በኋላ ይህ ችግሩ በይበልጥ እየተባባሰ መምጣቱ ማስተዋል ለቻለ የምንዛሪ ለውጡ ቀድሞውንም በቂ ጥናት ተደርጎበት የተወሰደ እርምጃ ስለመሆኑ አጠያያቂ ያደርገዋል። በአንድ በኩል የዋጋ ንረቱ እየከፋ ሲሄድ በሌላ በኩል በተለይ ተቀጣሪ ሠራተኛው ችግሩን ሊቋቋም የሚችልበት የደመወዝ ዕድገት ወይንም የኑሮ ማሻሻያ እየተደረገለት አይደለም። ይህ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአገሪቱን አምራች ዜጋ በመጉዳት ምርታማነት እንዲቀንስ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ለማንም ግልጽ ነው። የምርታማነት መዳከም ደግሞ የአገር ኢኮኖሚ መዳክም አድርጎ መውሰድ ያስፈልጋል።

በየጊዜው የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች፣ ሸማቾች ባለስልጣን እና የመሳሰሉ መንግሥታዊ ተቋማት ችግሩን የፈጠሩት አንዳንድ ነጋዴዎች መሆናቸውን በመግለጽ ማስፈራሪያ አዘል መልዕክቶች ሲያቀርቡ ይሰማሉ። በሌላ በኩል በተግባር የሚስተዋለው ችግሩ ከመፈታት ይልቅ እየተባባሰ የመሄዱ ጉዳይ ነው። ይህ ለምን ሆነ ቢባል የችግሩ መሠረታዊ ምንጩ ነጋዴዎች ብቻ አይደሉምና ነው። የአንድ ሰው ሕመሙ ባልታወቀበት ሁኔታ ታክሞ መዳን እንደማይቻለው ሁሉ የዋጋ ንረቱም ችግር ትክክለኛ መንስኤ ምክንያቱ ካልታወቀ መፍትሔ ለመስጠት አዳጋች ይሆናል።

መነሻ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን መንግሥት ይህ የዋጋ ንረት እየከፋ መምጣት ሊያሳስበው ይገባል። እንደከዚህ ቀደሙ "ስንዴ ጭኛለሁ፣ ስኳር አቅርቤያለሁ.." በሚል ችግሩን ማስታገስ የሚቻል አለመሆኑ ተጨባጭ ሁኔታው ጮሆ እየተናገረ ነው። እናም የዋጋ ንረቱ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በአስቸኳይ ይጠና፣ አስቸኳይ እና ውጤታማ መፍትሔም ይቀመጥለት።

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ አጂላ እና ጉለፋ በተባሉ ቀበሌዎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ሰሞኑን እንደተፈናቀሉና የመብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው በተለይ በማህበራዊ ድረገጾች የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ከርሟል። በተመሳሳይ ሁኔታም ቀደም ብሎ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአማራ ተወላጆች የመፈናቀል አደጋ ገጥሟቸዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ከኦሮሚያ ክልል እየተሰጡ ያሉ መግለጫዎች መካከል ሰዎቹ በሕገወጥ መንገድ መሬቶችን መያዛቸው፣ ለሌሎች ማስተላለፋቸውና ይህንን ሥርዓት ለማስያዝ የወረዳው አስተዳደር የይዞታ ልኬት መጀመሩን ይህ ሒደት ጥቅማችንን ያሳጣናል ያሉ ግለሰቦች ሌሎችን አስተባብረው ወደ ፊንፊኔ (አዲስ አበባ) በመምጣት አቤቱታ ማስማታቸውን አግባብ አይደለም ብለዋል። በአጭሩ መግለጫው በአካባቢው የተጣሰ መብት የለም የሚል ይዘት ያለው ነው።

ጠ/ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከአንድ ወር ተኩል በፊት በዓለ ሲመታቸውን በፈጸሙበት ዕለት ከተናገሯቸው አበይት ጉዳዮች ቀዳሚው ኢትዮጵያዊነት እና አንድነትን ማስቀደምን የሚመለከት ነው። ዜጎች ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ወላይታ…ሳይባባሉ፣ እንደከዚህ ቀደሙ በሠላም በፍቅር በመቻቻል የሚኖሩባት ኢትዮጵያ እንደምታስፈልገን ጠ/ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ያስተጋቡት እውነታ ነው።

በቅርቡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች ከሶማሌ ክልል አለአግባብ ሲፈናቀሉ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ቁጣቸውን ገልጸዋል። በተመሳሳይ መንገድ ሶማሌዎች ከኦሮሚያ አካባቢዎች መፈናቀላቸውም እንዲሁ። በዚህም ምክንያት መላው ሕዝብ ዘር፣ ቀለም ሳይለይ ተፈናቃዮችን አቅም በፈቀደ ለማገዝና ወገንተኝነቱን ለመግለጽ ከዳር እስከዳር ተንቀሳቅሷል። ይህ ዓይነቱ እኩይ ድርጊት በየትኛው ወገን እንዳይደገም ከማሳሰብ አልፎ አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ አሁን ድረስ መንግስትን በመወትወት ላይ ይገኛል።

ይህ ቁስል ሳይሽር ዛሬ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል የአማራ ተወላጆች መሬት በሕገወጥ መንገድ ሲጠቀሙ በመገኘታቸው አኩርፈው ለአቤቱታ አደባባይ ወጡ ዓይነት ውሃ የማይቋጥር ምክንያት በመስጠት የወገኖቻችን መፈናቀልና የመብት ጥሰት ደርሶብናል ላሉ ወገኖች የማይመጥን ምላሽ አቅርበዋል። ለምን የሌሎች ክልል ተወላጆች የሚኖሩበት አካባቢ ብቻ ተለይቶ የመሬት ልኬት ማድረግ አስፈለገ? ልኬቱ ከመካሄዱ በፊት ከሕዝቡ ጋር በቂ ውይይትና መተማመን ተደርጓል ወይ? ለሚለው የሰጡት መልስ የለም።

ማንም ይሁን ማንም፤ የትኛውም የብሄር ተወላጅ ይሁን በኢትዮጵያ ሕገመንግሥት መሠረት በመረጠው በየትኛውም ክልል ሄዶ የመኖር፣ ሐብት የማፍራት… መብት አለው። ከሕጉም በላይ የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ ለዓመታት የገነባው ትስስር በፖለቲከኞች ቀርቶ በማንም ሊበጠስ የማይችል መሆኑም የሚታወቅ ነው። ዘርን መሠረት ባደረገ ጥላቻ የሌላ ክልል ተወላጆችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ማጥቃት፣ ኢንቨስትመንትን ማደናቀፍ እጅግ አደገኛ ውጤት ያለው ምልክት ነውና የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ጉዳዩን ከማንኛውም አጀንዳ በላይ ሊይዙትና በፍጥነትም ተገቢውን እርምጃ ሊወስዱበት የሚገባ ነው።

እንዲህ ዓይነቱ የፖለቲከኞችና የአንዳንድ ደካማ ካድሬዎች እርምጃ እንደከዚህ ቀደሙ እየተለባበሰ፣ በተለያዩ ፍረጃዎች እየታጀበ የሚሄድ ከሆነ ወይንም የዘር ጥቃቱ በአስተዳደር አካላት ጭምር የሚታገዝ ከሆነ ስለኢትዮጵያዊነት፣ ስለአንድነት መዘመር ሕዝብን በከንቱ መደለል ይሆናል።

ስለዚህም የክልሎቹ መንግስታት በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ አቋማቸውን ለሕዝብ እንዲገልጹ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደነበሩበት እንዲመለሱና ሠላማቸው እንዲረጋገጥ መርዳት፣ እንደአስፈላጊነቱ ተገቢውን ካሳ መስጠት ይገባል፡፡ አጥፊ አመራሮችን ለይቶ ለሕግ ማቅረብም በቀጣይ መሰል ጥፋት በእንዝላልነት እንዳይፈፀም ጥብቅ መልዕክት ይኖረዋል።¾

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ከአንድ ወር በፊት በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት ንግግር ለተቀናቃኝ ሀይሎች የአብረን እንስራ ግብዣ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

ለዚሁ ግብዣ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) ግንባር ቀደም ሆኗል። በዚህም መሠረት መንግስት ለኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር ጋር ድርድር መጀመሩን በይፋ ሰሞኑን ገልጿል።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት እንደገለጸው የአገሪቱን ህገ መንግስት ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን መንግሥት በገለጸው መሠረት፤ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰላም ጥሪ ማስተላለፉን አስታውሷል።

በዚህም መሠረት መቀመጫውን ከሃገር ውጭ ካደረገውና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) ተብሎ ከሚጠራው ድርጅት ጋር ድርድር አድርገዋል ብሏል መግለጫው።

ድርድሩ ይሳካም፣ አይሳካም መንግስት ለዘላቂ ሰላም የወሰደው እርምጃ ይበል የሚያሰኝ ነው።

ሌሎችም ተቀናቃኝ ኃይሎች የትጥቅ ትግል ያወጁት ጭምር ከመንግሥት ጋር በመነጋገርና በመደራደር በሠላማዊ መንገድ ለመታገል ቢሞክሩ አትራፊ ይሆናሉ።

መንግሥትም የፓለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ ለህዝብ የገባውን ቃል ሊተገብር ይገባል።

 

ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አዶ ሻኪሶ አካባቢ በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ ከተሰማራ 20 ዓመታትን አስቆጥሯል። ሌሎች የመንግሥትና የግል ባለሃብቶችም በአካባቢው ከ70 ዓመታት በላይ በተመሳሳይ ሥራ ላይ መሆናቸው የሚታወቅ ነው።

ይህም ሆኖ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሚድሮክ ወርቅ ኩባንያ በአካባቢ ላይ ብክለት እያስከተለ ነው፣ በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት አድርሷል በሚል የተሳሳተ ክስ በሚያቀርቡ አንዳንድ ወገኖች አማካይነት ኩባንያው ፈቃዱ እንዳይታደስ ወይንም እንዲዘጋ ዘመቻዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። አሁንም ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ኩባንያው የአካባቢ ጥበቃን አስጠንቶ፣ በኩባንያው ውስጥ ይህንን የሚመለከት ራሱን የቻለ ክፍል አዋቅሮ ሥራውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እያከናወነ መሆኑን ከመግለጽ አልፎ ጉዳዩን በገለልተኛ ወገኖች ጥናት እንዲካሄድበት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ከአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ የባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ ጥናቱ ሲካሄድ ቆይቷል። ከፋብሪካው የሚወጣው ፍሳሽም በአውሮፓ ከታወቁ ላብራቶሪዎች ተጨማሪ ፍተሻ እንዲካሄድበት በማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በኩል ናሙናው ተልኮ በውጤቱም አንዳች ጉድለት ሳይገኝ ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ሚኒስቴሩ የ20 ዓመታት ጊዜውን ያጠናቀቀውን የለገደንቢ የመጠቀሚያ ፈቃድ ለተጨማሪ 10 ዓመታት እንዲታደስ ፈቅዷል።

ሚድሮክ የወርቅ ማዕድን ኩባንያ ከየትኛውም ወገን ቅሬታ ለምን ተነሳ ብሎ አያውቅም። ጉዳዩ መነሳቱ ተገቢና አግባብም ነው ብሎ ያምናል። ጉዳዩ ተነስቶ በሳይንሳዊ መንገድ ለማጣራት የተሄደበት ርቀት ምንም እንኳን ተጨማሪ ወጪንና ጊዜን የወሰደ ቢሆንም ጉዳዩን ለማጥራት ካለው ትልቅ ፋይዳ አንጻር ሲመዘን አሁንም በተገቢነቱ ላይ ቅሬታ አቅርቦም አያውቅም። በዚህ ሁሉ ሒደት ተጉዞ የተገኘውን ውጤት በመካድ “ካልፈረሰ ሞቼ እገኛለሁ” ማለት ለአገር ልማትና ዕድገት ከሚያስብና ከሚቆረቆር የትኛውም ወገን የሚጠበቅ አይደለም።

ሰሞኑንም ራሳቸውን የጉጂ ቄሮ ብለው የሚጠራ ቡድን ለሻኪሶ ከተማ ብሔር ብሔረሰቦች በሙሉ በሚል በበተነው ወረቀት የሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ የሻኪሶ/ ለገደንቢ ማምረቻ ከሚያዚያ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ እንዲያቆም፣ ይህ ባይሆን እርምጃ እንደሚወስድ ያስጠነቅቃል። ይህ ማስጠንቀቂያ ቀነ ገደቡ ከመድረሱ አስቀድሞ ወደማዕድን ማምረቻው የሚሄድ ከፍተኛ ኤሌክትሪክ ሀይል ተሸካሚ መስመር ላይ ጉዳት በማድረስ ፋብሪካው የኤሌክትሪክ ሀይል እንዳያገኝና ምርቱን እንዲያቆም አድርገዋል። ይህ ዓይነቱ ጥቃት ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ ላይ ብቻ የተቃጣ አድርጎ መውሰድ አይቻልም። ጥቃቱ በአጠቃላይ በኢንቨስትመንት ላይ የተቃጣና ምክንታዊ ያልሆነ፣ በጥላቻ የታጀበ መሆኑ እንደአገር አሳዛኝና የደረሰንበትን የዝቅጠት ደረጃ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

ሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ በሮያሊቲ፣ በተለያዩ የግብር ክፍያዎች ከአጠቃላይ ገቢው እስከ 50 በመቶ ወጪ በማድረግ በየዓመቱ ለፌዴራልና ለክልል መንግሥታት ገቢ ያደርጋል። ከ1 ሺ 200 በላይ ሠራተኞች ሕልውናም የተመሠረተው በዚሁ ኩባንያ ነው። ኩባንያው ከኢንቨስትመንቱ በተጨማሪም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ያላሰለሰለ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወቅ ነው።

እናም በጥቂቶች አሻጥር ሚድሮክ ከዘርፉ ገፍቶ ለማስወጣት የሚደረገው ርብርብ ሌሎች ኢንቨስተሮችን ጭምር የሚያስበረግግ አደገኛ ውጤት ያለው መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።

እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ ምንም እንኳን በከፍተኛ አገራዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም ባላቸው ሽርፍራፊ ጊዜም ቢሆን ሻኪሶ/ለገደንቢ የሚገኘውን የሚድሮክ ወርቅ ማዕድን ኩባንያ አለአግባብ ገፍቶ ለማስወጣት እየተደረገ ያለውን ተገቢ ያልሆነ ርብርብ ለማስቆም ተገቢውን አመራር ሊሰጡ ይገባል። የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ በተመሳሳይ ሁኔታ በሚድሮክ የወርቅ ማዕድን ኩባንያ ላይ የከፋና የማይመለስ ጉዳት ከመድረሱ አስቀድሞ በየደረጃው የሚገኙ የተሳሳተ ግንዛቤ የያዙ አመራሮችን ጨምሮ ሕዝቡ በማሳመን ልማታዊ ባለሃብቱን ሊያበረታቱና የተጋረጠውም አደጋ በአስተማማኝ መልኩ ሊቀለብሱ ይገባል።¾

የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በየዓመቱ ሜይ 3 ቀን ይከበራል። በዚህ መሠረት በሀገራችንም በነገው ዕለት (ሚያዚያ 25 ቀን 2010 ዓ.ም) የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ታስቦ ይውላል። ይህ ቀን የነጻነት ቀን ነው። ይህ ቀን “keeping power in check: Media, justice & The rule of Law” (ሚዲያ ለፍትሕና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው) በሚል መርህ ተከብሮ ይውላል። በዓሉ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት ፕሬሱን ለመደገፍ፣ የሐሳብ ብዝሃነት እንዲስፋፋ ለመስራት ቃል በገባበት በዚህ ወቅት መከበሩ ለየት ያደርገዋል። የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች በምህረት በተለቀቁበት ወቅት መከበሩ የተለየ ድባብ ያላብሰዋል።

ፕሬስ በሙሉ አቅሙ እንዲንቀሳቀስ እንዲያድግ፣ እንዲፋፋ በመረጃ መበልጸግ አለበት። ፕሬስ ተልዕኮውን በፍጥነትና በጥራት እንዲወጣ በመረጃ መታገዝ የግድና ወሳኝ ነው። የመረጃ ነጻነት ጉዳይ በሕገመንግሥቱ የተደነገገ ነው። በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነጻነት አዋጅ 590/2000 የመረጃ ነጻነትን በሕግ ደንግጓል። በተግባር ግን መረጃ የማግኘት ነጻነት በኢትዮጵያ የተረጋገጠ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም። በሕገመንግሥት ጭምር የተረጋገጠን ነጻነት አስፈጻሚው አካል እያከበረ አይደለም።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደረጃ ያሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለያዩ የፕሬስ መግለጫዎች ላይ የግል ጋዜጦችን የማሳተፍ በጎ ጅምር እያሳዩ መሆናቸው በጥሩ ጎኑ የሚወሰድ ቢሆንም በአንጻሩ ጥቂት የማይባሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት አሁን ድረስ የግል ጋዜጦችን የሚሸሹ፣ ለግል ጋዜጦችም በር የሚዘጉ፣ የግሉን ፕሬስ በመርገምና በመኮነን የሚረኩ መሆናቸው አነጋጋሪ ነው። በተዋረድም ወደታች ሲመጣ ተመሳሳይ ችግሮች የሚታዩ መሆኑ የፕሬስ ሥራን አዳጋች አድርጎታል። በተለይ በመንግሥታዊ ተቋማት መረጃ ማግኘት መብት፣ መስጠት ደግሞ ግዴታ መሆኑ ጭራሽኑ ተዘንግቶ ልመና ሆኗል። በዚህ ረገድ አስፈጻሚው አካል በጥልቀት ራሱን ፈትሾ ተገቢውን ቁርጠኛ እርምጃ ሊወስድና ፕሬሱን ሊያግዘው ይገባል።

ሌላው ፕሬሱ በሰው ኃይልና በፋይናንስ እንዲጠናከር መንግስታዊ ማስታወቂያዎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያገኝ መደረግ አለበት። ይህ መሆኑ ፕሬሱ በፋይናንስ ተጠናክሮ ብቃት ያለው የሰው ኃይል እንዲያፈራና መረጃ የመስጠት ስራውን ለማጠናከር ትልቅ እገዛ ይኖረዋል። በዚህም ረገድ በመንግሥት የተያዙ ዕቅዶች በፍጥነት ወደ መሬት እንዲወርዱና እንዲተገበሩ የአብዛኛው ፕሬስ ፍላጎት ነው።

ፕሬሱም በራሱ ውስጥ በበርካታ ችግሮች የተተበተበ መሆኑ ይታወቃል። ወደውስጡ ተመልክቶ ጉድለቱን ማረም ተገቢ ይሆናል።

እናም የዓለም አቀፉን የፕሬስ ነጻነት ቀን ስናስብ የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ በፕሬሱ ላይ የተጋረጡ ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ አቋም በመያዝ፣ የችግሩም ብቻ ሳይሆን የመፍትሄው አካል ለመሆን ቃል በመግባት ጭምር ሊሆን ይገባል።¾

 

ባለፉት ሶስት ዓመታት በሀገራችን የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት የበርካታ ንፁሃን ዜጐችን ሕይወት መቅጠፉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በተያያዘም፣ የሀገሪቷ ኢኮኖሚ በተለይ የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ በሚቻልበት ሁኔታ ተግባራዊ አለመሆኑን ቁጥሮች አመላካች ናቸው።

እንዲሁም “ብረት ቅርጽ የሚይዘው በግለቱ ሲመቱት ነው” እንዲሉ፣ ወቅታዊ የሀገራችን የፖለቲካ አለመረጋጋትን በመጠቀም ሶስተኛ ወገኖች ፍላጎታቸውን ሊጭኑብን ሊቀጠቅጡን ሲንቀሳቀሱ አስተውለናል። በተለይ ስትራቴጂክ ጠላታችን የሆነችው ግብፅ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ታሪካዊ የውሃ ድርሻዬን ለማስጠበቅ ማንኛውንም መንገድ እጠቀማለሁ የሚል መግለጫ ይዛ ብቅ ብላለች። አሜሪካም በበኩሏ የኢትዮጵያን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አስጠብቃለሁ የሚል አዋጅ አጽድቃለች። ምስጋና ይግባቸው ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ፣ ለቀጣዩ ትውልድ በአሜሪካ መንግስት የተሰፋ ዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ቀረጢት እንዲዘጋጅለት በር ከፍተዋል፤ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ እንዲሉ።

ከላይ የሰፈረው ሐተታ መሬት ላይ ያለ ጥሬ ሃቅ ነው። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በቀጥታ ወደጉዳዩ ከመግባታቸው በፊት የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በሕዝቡ ተቀባይነት እንዲያገኝና ሕዝቡንም የለውጡ ባለቤት ለማድረግ የጀመሩት የሰላም ኮንፈረንስ፣ ለቀጣይ ለሀገሪቷ ጉዞ ምትክ አልባ ጅማሮ እንደሆነ አሻሚ አይደለም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ የተመለከትነውም ሕዝቡን የማቀራረብ፣ የማዋሃድ፣ ያሉ ቅሬታዎች ብዙ ሥራዎች ቢጠይቁም በአስተሳሰብ ደረጃ እንዲሽሩ ሕዝቡን ሲያዘጋጁ፣ ሕዝብን እንደሕዝብ የበደለ የታሪክ ባለቤት አለመሆናችን፣ ማክረር ማቄም ተገቢ እንዳልሆነ በቻሉት መጠን በመድረኮቹ ላይ ሲያስተጋቡ ነው። አንዳንዴ እንደውም ከፍተኛ ትህትና በተሞላበት፣ ምክር አዘል፣ ልመና በሚመስል ሁኔታ ዝቅ ብለው አንዱ ሕብረተሰብ ሌላው ላይ መጥፎ ነገር እንዳይሰነዝር ሲተጉ አይተናል።

ሆኖም ግን በአንዳንድ መድረኮች ሆን ተብለው በሴራ ፖለቲካ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰላምና የአብሮነት ጥሪያቸውን ለማጨለም የሚቀርቡ ጥያቄዎች በሰማን ጊዜ ቅስማችን ነው የተሰበረው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሁላችን መሆናቸው እየታወቀ “የአንተ” እየተባሉ ምላሽ እንዲሰጡ በተጠነሰሰ ወጥመድ ውስጥ እንዲወድቁና ቅቡልነታቸው እንዲደበዝዝ የተሄደበት ርቀት የሚያስተዛዝብ ነበር። በተለይ ገዢው ፓርቲ የአራት ፓርቲዎች ጥምረት መሆኑ እየታወቀና ፓርቲው እንዴት እንደሚሰራም ጭምር እየታወቀ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈላጭ ቆራጭ ስልጣን ያላቸው ይመስል፣ አንዳንድ ምላሽ እንዲሰጡባቸው የቀረበላቸው ጥያቄዎች በራሱ በገዢው ፓርቲ አንዳንድ ከፍተኛ አመራሮች፤ የተወጠነ ሴራ መሆኑን ለመገመት የሮኬት ሳይንስ ማጥናት አያስፈልግም።  

አንድ ወር ያልሞላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለዘመናት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እየተንከባለሉ ለመጡ የፖለቲካ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ መጠየቅ፤ ተገቢነት ይጎድለዋል። ስለዚህም የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰላም፣ የአብሮነት እና የመፈቃቀር ሀገራዊ ውይይቶችን በሴራ ፖለቲካ ለመጥለፍ መሞከር ተደማሪ ፖለቲካ አይደለም። ይልቁንም፤ ማንም አትራፊ ሊሆን ወደማይችልበት የመጨረሻው መጀመሪያ የመጠፋፋት ጉዞ ነው የሚሆነው። ቆም ብለን የሠላሙን መንገድ መምረጥ የተሻለ አማራጭ ሳይሆን ብቸኛው አማራጭ መንገድ ነው።¾

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በወልድያና በፋሲል ከነማ ጨዋታ በተከሰተው ረብሻ ምክንያት ሰሞኑን የቅጣት ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ነው። ከፌዴሬሽኑ ውሳኔ መካከል ብዙዎችን ያስገረመውና ያሳዘነው የሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ ስታዲየምን ለአንድ ዓመት ውድድሮችን እንዳያስተናግድ ያስተላለፈው ውሳኔ ይገኝበታል። በፌዴሬሽኑ ውሳኔ መሠረት ስታዲየሙ ክለቡ ጥፋት ካጠፋበት ከሚያዚያ 03 ቀን 2010 ዓ.ም እስከ ሚያዚያ 02 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚዘጋጁ ማናቸውም ውድድሮች እንዳይካሄድበት ታግዷል።

ጥር 6 ቀን 2009 ዓ.ም በኢፌዲሪ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በክብር እንግድነት በተገኙበት የተመረቀውና ወደ ግማሽ ቢሊየን ብር የፈሰሰበት የሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ ስታዲየምና የስፖርት ማዕከል በአገራችን በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ የመጀመሪያ የሆነ ስታዲየም መሆኑ ይታወቃል። ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በብቃት ማስተናገድ ከሚችሉ የአገራችን ስታዲየሞች ግንባር ቀደሙም ነው። ይህን ስታዲየም ገንብተው ለሕዝብ ላስረከቡት ለክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ እና በሙያቸው ደከመኝ ሰለቸን ሳይሉ በአነስተኛ በጀትና በአገር ውስጥ ቴክኖሎጂ ታግዘው ለፍሬ ያበቁት ዶ/ር አረጋ ይርዳውና ባልደረቦቻቸው ምኞትና ህልም ስታዲየሙ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን በብቃት ማስተናገድ እንዲችል፣ ወጣቱ ስፖርትን በማዘውተር አምራች ዜጋ እንዲሆን ማገዝ ነበር። ይህ አገራዊ ራዕይ መደገፍ ደግሞ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብቻም ሳይሆን ከስፖርት ቤተሰቡ የሚጠበቅ ነበር። ግን ይህ አልሆነም።

ፌዴሬሽኑ አጥፊዎች ላይ የወሰደው እርምጃ ተገቢነት ላይ ለጊዜው የምንሰጠው አስተያየት ባይኖርም ከጥፋቱ ጋር ተያይዞ አንድን ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያሟላ ብቸኛ ስታዲየም ለቅጣት መዳረግ ወይንም መዝጋት አርቆ ማስተዋል የተሳነው ግብታዊ እርምጃ ነው። በዚህ እርምጃ ተጎጂው አገር እንጂ የወልድያ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ብቻ ሊሆን አይችልም። ክለቦች ባጠፉት ጥፋትም እንደወልድያ ያሉ የሕዝብና የአገር መገልገያ ስታዲየምን እንዲዘጋ መወሰን በምንም መልኩ አስተማሪ ቅጣት ለሆን አይችልም።

ይህ የፌዴሬሽኑ እርምጃ አንድ በንጉሱ ጊዜ የሚነገር አባባልን አስታወሰን። በዘመኑ ጥፋት ሲፈጸም “ማጥፋቱንስ ወታደር አጥፍቷል፤ ግን ገበሬው ይካስ” ይባል ነበር። ዘንድሮም በክለቦች ጥፋት የስታዲየም ባለቤት ያልሆነን ክለብ የሚጫወትበትን ስታዲየም ለቅጣት የመዳረግ አሳዛኝ ውሳኔ አይተናል። እናም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደገና ውሳኔውን ሊመረምርና አስተማሪ ቅጣት ሊጥል ይገባል።

የገዢው ፓርቲ (ኢህአዴግ) ሁለት ጎምቱ ባለስልጣናት በቅርቡ በግንባሩ ውስጥ አለመተማመንና የስልጣን ሽኩቻ እንዲሁም የመለስ ራዕይ ገብቶሃል፣ አልገባህም በሚል ሽኩቻ በቀድሞ ጠ/ሚ ኃይለማርያም አመራር ላይ ጉዳት መድረሱን ይፋ አድርገዋል፡፡

አንዱ ከፍተኛ ባለስልጣን፣ “በአንድ ድርጅት ውስጥ አለመተማመንና አድርባይነት እንዲሁም የስልጣን ሽኩቻ ካለ አጠቃላይ አመራሩን በተለይም ውሳኔ ሰጪውን አመራር ይጎዱታል። እነዚህ ችግሮች በቀድሞው የድርጅታችን ሊቀመንበር ላይም ሆነ በአጠቃላይ የድርጅት የመምራት ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበራቸው” ብለዋል፡፡

ሌላው ከፍተኛ ባለስልጣን በበኩላቸው ከኢሕአዴግ መርህ ባፈነገጠ መልኩ በተፈጠረ ጉድኘት ቀድም ሲል ለነበሩት ጠ/ሚ ተገቢውን እገዛ አልተደረገላቸውም እንዲሁም የመለስ ራዕይ ገብቶሃል፣ አልገባህም በሚል ሽኩቻ በሴራ መጠለፋቸውን በአደባባይ አስረጂ ሆነው ቀርበዋል፡፡

እነዚህ ከፍተኛ የመንግስትና የፓርቲ ባለስልጣናት ያልተረዱት ዋናው ጉዳይ፣ ለቀድሞ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መተባበር፣ አለመተባበር፣ መታዘዝ፣ አለመታዘዝ እንደመብት ማቅረባቸው ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ከሕገመንግስት የሚገኝ በመሆኑ ለሕገመንግስቱ ተገዢ ያልነበሩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንደነበሩ መስማት አስገራሚ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትርን ሥራ ማደናቀፍና በሕገመንግሥታዊ ስልጣኑ ላይ ማሴር፣ በሀገር ልማት፣ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በብሔራዊ ጥቅም፣ በእያንዳንዱ ዜጋ ዕለታዊ ሕይወት ላይ ማሴር፣ በአጠቃላይ ሕገመንግሥቱን እንዳይተገበር እንቅፋት መሆን ወንጀል መሆኑን መዘንጋቱ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ዓይነት ተግባር ማካሄድም እንደሕጋዊ አሠራር ታይቶ መደራደሪያ ሆኖ መቅረቡ እንደአገር አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ አብይ ወንጀል ነው፡፡

አሁንም ከፍተኛ የፓርቲና የመንግሥት ባለሥልጣኖች፤ ዛሬ ደግሞ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተባብረን እንሰራለን የሚል መሀላ ለአደባባይ ማብቃታቸው በሕግና ሥርዓት ላይ ያላቸው አረዳድ ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው፡፡

ስለዚህም የቀድሞ ጠ/ሚኒስትሩን ሕገመንግሥታዊ ሥልጣን ሆን ብለው በሴራ ያኮላሹ ባለሥልጣናት ለሕግ መቅረብ አለባቸው፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ አዲሱ ጠ/ሚ ከመንግሥትና ከፓርቲ ሴረኞች ተመሳሳይ የሴራ ጥቃት እንደማይደርስባቸው ለሕዝብ ማረጋገጫ ማቅረብ አይቻልም፡፡


የኢህአዴግ ምክርቤት በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን በለቀቁት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ምትክ ዶ/ር አብይ አህመድ የግንባሩ ሊቀመንበር እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ በመሰየም በፓርላማ ሹመታቸውን አስጸድቋል። ኢህአዴግ በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት እየተባባሰ የመጣው ሕዝባዊ ቁጣ ተገቢውን መልስ ለመስጠት ጥልቅ ተሀድሶ እንደሚያካሂድ ለሕዝብ በገባው ቃል መሠረት ሥር ነቀል ለውጥ ማካሄድ ለምርጫ የሚቀርብ ሳይሆን የህልውና ጥያቄም ጭምር ሆኖ ከፊቱ ተደቅኗል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ ይህን ለውጥ የተሳካና ብዙሃኑን ያረካ እንዲሆን አስተዋጽኦቸው ላቅ ያለ እንደሚሆን ይገመታል።


ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ያደረጉት ንግግር መሳጭና የብዙዎች ቀልብ የሳበ ነበር። በዚሁ ንግግራቸው ስለኢትዮጵያዊነትና አንድነት ደጋግመው በማንሳት የህዝብን ስሜት መኮርኮር ችለዋል። በተጨማሪም በወሳኝነት በሕገመንግሥቱ የሰፈሩ የህግ የበላይነት፣ የፕሬስ ነጻነት፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶችና የመሣሠሉ አበይት ጉዳዮች በአፈጻጸም እንዳይሸረሸሩ እንደሚሰሩ ዘርዘር ባለ ገለጻቸው ተናግረዋል።


በውጭ ግንኙነት ረገድም እንደኤርትራ ካሉ መንግሥታት ጋርም ሠላምን እንዲሰፍን እንዲሁም በውጭ የሚኖረው ዲያስፖራ ወገን ወደአገሩ እንዲገባ ጥሪ አቅርበዋል።


ይህ የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ሕዝብን አረጋግቷል፣ መጪውን ጊዜ ተስፋ እንዲያደርግ፣ በአገሩ ተስፋ እንዳይቆርጥ አድርጓል። ይህ አስተዋፅኦ ብቻውን ከባድ ዋጋ ያለው ነው። ይህ ዓይነት አቅም ያለው መሪ ማግኘትም መታደል ነው።


ይህም ሆኖ ግን እጃችንን አጣጥፈን ኢዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተአምር እንዲያወርዱልን ማናችንም መጠበቅ አንችልም። ዶ/ር አቢይ ህልማቸውን ማሳካት የሚችለው ይሄ ሕዝብ ነው። ሕዝቡ ሙስናና ብልሹ አሠራርን በመዋጋት፣ ለአገሩ ልማትና ዕድገት በንቃት በመሳተፍ ገንቢ ሚናውን በየደረጃው ሲወጣ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ውጤት መታየት ይጀምራል።


የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎችም ቢሆኑ ከዘረኝነትና ጠባብነት አስተሳሰብ ተላቀው አገራችን ከገባችበት ማጥ እንድትወጣ ያላቸው ሚና የላቀ ነው። በኢትዮጵያዊ ሕብረብሔራዊ ስሜት መጓዙ ከማንም በላይ ጠቀሜታው ለራሱ ለኢህአዴግ መሆኑን መረዳት ይገባል። መጪው ጊዜ የእርቅና የሰላም እንዲሆን ኢህአዴጎች ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ልባዊ ድጋፍና ትብብር በማድረግ የጥልቅ ተሀድሶ ሒደቱን ሊደግፉና ሊያሳኩ ይገባል።

Page 1 of 16

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us