መንግሥት፤ የሼህ አልአሙዲንን ጉዳይ ከብሔራዊ ጥቅም አንፃር ሊከታተለው ይገባል

Wednesday, 08 November 2017 18:41


በሳዑዲ አረቢያ በሳውድ ቤተሰቦች መካከል የተቀሰቀሰው ዘውድን የመቆጣጠር ውስጣዊ የፓለቲካ ሽኩቻ በርካታ የሳዑዲ ልዑላንን እና ባለሃብቶችን ለቁም እስር ዳርጓል። ከሳዑዲ ንጉሳውያን ቤተሰቦች የሥልጣን ሽኩቻ ጋር ተያይዞ የክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ በቁም እስር ላይ መሆናቸውን የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መገናኛ ይፋ አድርገዋል።


ሼህ ሙሐመድ በሀገራችን ውስጥ የመንግስት ለውጥ ሲደረግ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ለዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ ሳቢ ባልነበረበት እንዲሁም ኢህአዴግ ወደሥልጣን ከመጣ በኋላ ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ባልነበረበት ወቅት፤ ሀብታቸውን ይዘው ወደ ሀገር ውስጥ በመምጣት በ“ሸራተን አዲስ” ዓለም አቀፍ ሆቴል ግንባታ ሀ ብለው የጀምሩት ኢንቨስትመንት በአሁኑ ወቅት ከ70 በላይ ኩባንያዎችን መክፈት የቻሉ፤ የልማት ጀግና ናቸው።


ዓለም አቀፍ ቢሊየነሩ ሼህ ሙሐመድ፤ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በኢንቨስትመንት ያበረከቱት አስተዋፅዖ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ላይ እምነት እንዲጥሉና ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንታቸውን ይዘው እንዲመጡ መንገድ የጠረጉ መሆናቸውን መቼም ልንዘነጋ የማንችል የሀገር ባለውለታ ናቸው። በተለይ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እንደ አሸን የፈሉት እንደ ሕንድ፣ ቻይና፣ ቱርክ እና የናይጄሪያ ቢሊየነር አሊኮ ዳንጐቴን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ አዋጪ መሆኑን፣ የተግባር ልምድ የቀሰሙት ከሼህ ሙሐመድ የኢንቨስትመንት ስኬት መሆኑ የአደባባይ እውነት ነው።


ሼህ ሙሐመድ በኢትዮጵያ ውስጥ በከፈቱዋቸው ከ70 በላይ ኩባንያዎቻቸው አማካይነት ከ110 ሺ በላይ ሠራተኞችን መቅጠር ችለዋል። በሺ የሚቆጠሩ የንግድ ሸሪኮችንና አጋሮችን አፍርተዋል። ለሀገሪቱ ኢኮኖሚም በታክስና ግብር እንዲሁም በሮያሊቲ መልክ በየዓመቱ ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ እያደረጉ የሚገኙ ባለሃብት ናቸው።


ከሌሎች የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች የሚለያቸው ሀገር ወገን በልማትም በችግርም ጊዜ ሲፈልጋቸው ከማንም ቀድመው የሚገኙ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ናቸው።


ሼህ ሙሐመድ፣ በግለሰብ ደረጃ የሚመዘኑ ወይም የሚቀመጡ አይደሉም። በኢትዮጵያ ልማት ውስጥ ከመንግስት ቀጥለው ሁለተኛው የኢኮኖሚ ባለቤት እና ለዜጎች የሥራ እድል ፈጣሪም ናቸው። ይህም በመሆኑ፣ የትኛውም መንግስት ብሔራዊ ጥቅሙን እንደሚያስቀድመው ሁሉ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የእኚህን ሀገር ወዳድ ባለሀብት ጉዳይ ከብሔራዊ ጥቅም አንፃር በትኩረት ሊከታተለው ይገባል እንላለን። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
112 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us