You are here:መነሻ ገፅ»ኪነ-ጥበብ
ኪነ-ጥበብ

ኪነ-ጥበብ (258)

 

በጥበቡ በለጠ

 

ለዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት ኢትዮጵያዊ ወግና ቁም ነገር ሁሌም ባወራለት ስለማይሰለቸኝ ሰው ነው።
ኢትዮጵያ የታላላቅ ታሪኮች ባለቤት መሆኗን፣ የሰው ዘር መፈጠሪያ እንደሆነች ለመጀመሪያ ጊዜ ስላበሰረውና እንዲሁም ደግሞ በኢትዮጵያ ፍቅር ወድቆ ዜማውም፣ ብዕሩም፣ ቴአትሩም፣ ግጥሙም፣ መንፈሱም ኢትዮጵያ እንደሆነች በፍቅር ስለተለያት ባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ይሆናል፡-


ኢትዮጵያ እና ሕዝቦችዋ በመድረክ ላይ ገዝፈው እንዲወጡ፣ በታሪክ ውስጥ ገናና ህዝቦች እንደሆነ ሲፅፍላቸው፣ የኢትዮጵያም አንድነት ከብረት በደደረ መልኩ እንዲጠነክር ለኢትዮጵያ ሰማዕት የሆኑ ባለታሪኮችን በምሳሌነት እያቀረበ ፀጋዬ ገ/መድህንት ብዙ የሰራ የዚህች ሀገር ባለቅኔ ነው።


ፀጋዬ አፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ሽጉጣቸውን መዝዘው ራሳቸውን ለኢትዮጵያ ሲሉ የሰውበትን ታሪክ በመመርኮዝ የንጉሡን ስብዕና ወደ ፍልስፍና ቀይሮታል። ይህም ፍልስፍና ቴዎድሮሳዊነት እንዲባል ያደረገበት ነው። ቴዎድሮሳዊነት ማለት ለሐገር ክብር፣ ለኢትዮጵያ ፍቅር ራስን መሰዋትን ይመለከታል። ፀጋዬ ቴዎድሮስ በተሰኘው ግዙፍ ቴአትሩ ያሳየው ይህን ፍልስፍና ነው። ከኢትዮጵያ በላይ ምንም ነገረ የለም በማለት ራስን መስጠት። የኢትዮጵያን ክፉ ከማይ እኔ በቅድሚያ ልሰዋ ማለትን በቴዎድሮስ በኩል አሳይቷል።


አፄ ቴዎድሮስ ይህችን ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራትን ሐገር አንድነቷ ተጠብቆ፣ አንዲት ታላቅ ሀገር የመመስረት ህልም እና ይሄን ህልም ዕውን ለማድረግ የወጡ የወረዱበትን የትግል ሜዳ በማሳየት ያ ታላቅ ህልም እንደገና ሊጨልም አፋፍ ላይ ሲደርስ እና ተስፋ ሲያስቆርጥ የኢትዮጵያን ክፉ ከማይ ልሰዋ ያሉበትን ታሪክ በመምዘዝ ኢትዮጵያዊነትን ያስተማረበት ትልቅ ቴአትሩ ነው።
በዚህ ተውኔት ሁሉንም ታዳሚ በመንፈስ በማሳተፍ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ያደርጋል። አፄ ቴዎድሮስም እንዲህ ይላሉ።


…ለማናችንም ቢሆን ከእንግዲህ ከቶ እረፍት የሚሉት የለም። ሁሉም ፋንታውን ይጣር! ይድከም! በአዲስ መንፈስ ይነሣ!... ዛሬ በኢትዮጵያ የመከራ ቀን ይኸው ያለሕያው እግዚአብሔር ወገን የላትምና፣ ዛሬ በኢትዮጵያ በነፃነቷ በታሪኳና በሕዝብዋ አንድነት የመከራ ቀን፣ ያልተነሳላሰትን፣ ያልታጠቀላትን የሀገር ወገን፣ እኔ አባ ታጠቅ በስመ ቃሉ ረግጬዋለሁ! ይኸው እርግማኔ ይድረሰው! በዚህች በመከራዋ ሰዓት ላላቀፉት፣ ላልቀሙላት ወገን ከቶም ዘር አይቁምላት። ያልደገፉት ደጋፊ ይጣ! ብድሯን ያልከፈለ ልጅ ዕዳው በልጅ ልጆቹ ግፍ ይክፈለው። የኢትዮጵያ ሐቋን የከለከላት ሐቁ ስላቅ ሆኖ ይነቀው። እትብቷን የገፈፈ የገዛ እትብቱ እባብ ሆኖ ይጥለፈው… ይኸው ለማናችንም ቢሆን የኢትዮጵያ ልጅ ነኝ፣ ወገን ነኝ ለሚል ወገን ከእንግዲህ ከቶም እረፍት የሚሉ የለም።


ይሄ ሁሉ የአፄ ቴዎድሮስ እርግማን የሚዘንበው የእንግሊዝ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር ደፍረው በመግባታቸው ይህንን ድፍረት ለመከላከል ወደ መቅደላ ላልመጡ፣ የሀገራችን ጥቃት ላልተከላከሉ ሰዎች የቀረበ እርግማን ነው።


የኢትዮጵያ ግዙፍነት፣ ኢትዮጵያ ማለት ፍቅር ማለት እንደሆነችና ይህንንም ፍቅሯን ታላቅነቷን ማጣት ደግሞ የማይገባ መሆኑን ፀጋዬ በቴዎድሮስ ውስጥ ገብቶ ያሳያል።
ሎሬት ፀጋዬ በቴዎድሮስ ብቻም አያልቅም። ኢትዮጵያዊነትን ለመገንባት ሌሎች ታላላቅ ሰብዕናዎችንም ይጠቀማል። ለምሳሌ አቡነ ጴጥሮስን እንደ ገፀ-ባህሪ ወስዷቸው እርሳቸውንም ወደ ፍልስፍና ቀይሯቸዋል። ያ ፍልስፍና ጴጥሮሳዊነት ይባላል። ጴጥሮሳዊነት የሃይማኖት ሰው ሆኖ ውሸት ቅጥፈት፣ በደል፣ መከራ፣ ግድያ ሲፈፀም ዝም ብሎ አለማየት ነው። ጴጥሮሳዊነት የሃይማኖት ሰው ሆኖ ለኢትዮጵያ መሞትን፣ ለኢትዮጵያ ሲባል በጥይት ተደብድቦ መገደልን የሚያሳይ ጥልቅ ፍልስፍና አድርጎት ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ወደ መድረክ አመጣው።


ፀጋዬ ገ/መድህን ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት በተሰኘው ቴአትሩ በተሰኘው ቴአትሩ አቡነ ጴጥሮስ የኢጣሊያ ፋሽስቶች ኢትዮጵያን ወርረው፣ ሕዝቡን ሲያሰቃዩ፣ ሀገሪቷን በቅኝ ለመግዛት ሲዶልቱ እምቢኝ አሻፈረኝ ብለው ፋሽስቶችን በግላጭ ሲያወግዙ ታስረው ተሰቃይተው፣ ከእርስም እንዲለቀቁ ፋሺስቶች የኢትዮጵያን ህዝብ ስበኩልን ብለዋቸው ሁሉ ጠይቀዋል። ግን አቡነ ጴጥሮስ ለኢጣሊያ ፋሽስቶች የተገዛ ኢትዮጵያዊን ገዘቱ። እናም ደረታቸውን ለመትረየስ ጥይት ሰጥተው ለኢትዮጵያ ክብር ሲሉ እስከ ወዲያኛው አሸለቡ። ጴጥሮሳዊት ይህ ነው። ለኢትዮጵያ መሞት።


በጣም የሚገርመው ነገር አቡነ ጴጥሮስ ፋሽስቶችን ሲቃወሙ፣ በተቃራኒው ደግሞ ለፋሽስቶች ያደሩ የሃይማኖት አባቶች ነበሩ። ጴጥሮሳዊነት ልዩነት የሚያመጣው በዚህ ወቅት ነው። ለእውነት፣ ለሀገር መሰዋትን። ፀጋዬ ገ/መድህን በነዚህ ታላላቅ ሰዎች ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን የሚገነባ የብዕር አርክቴክት ነበር።


ሎሬት ፀጋዬ መች በነዚህ ብቻ ያቆማል። ዘርአይ ደረሰ በሮም አደባባይ ለኢትዮጵያ ክብር ሲል የዋለውን ውለታ ቴአትር ጽፎለት ወደ መድረክ አምጥቶ ኢትዮጵያዊነትን አስተምሮበታል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ተደፈረ ብሎ ዘርአይ ደረስ የከፈለውን መስዋዕትነት ጎልቶ እንዲታይ ያደረገ የጥበባት ሊቅ ፀጋዬ ገ/መድህን ሁሌም ስሙ ይነሳል።
ፀጋዬ ጉዳዩ አያልቅም። የኢትዮጵያዊነትን መሠረትና ካብ እያነፀ በህዝቦች ውስጥ ትልቅ አምድ ያስቀመጠ ነው። ሌላው ግዙፍ ቴአትሩ ምኒልክ የሚሰኘው ነው። በአፄ ምኒልክ አመራርና ጀግንነት ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን አስተምሯል።


ፀጋዬ ገ/ መድህን ምኒልክ በተሰኘው ታሪካዊ ተውኔቱ ላይ በምኒልክ አንደበት እንዲህ ይላል፡-


… ሰው በተለይም የመንግስት ኃላፊነት ያለው ሰው ባለው ነገር ላይ እንጂ በተጨባጭ በሚዳሰሰውና በሚጨብጠው ነገር ላይ እንጂ፣ በሚመኘውና በሚያልመው የሃሳብ እስትንፋስ ላይ ዓላማውን ሊያዋቅርና ሊገነባው አይችልም። ለዚህ ነው ያገርህን ያበሻን ቤት አሰራር ተጨባጭ አገነባብ ባጭር ምሳሌ ላስተምርህ ማለቴ… አየህ ኢያሱ… ያበሻ ቤቱ፣ ያበሻ፣ ጣሪያው ምሶሶ ጉልላቱ፣ ያበሻ ማዕዱ ምድጃና መሶቡ ያበሻ አውድማው አዳራሹና አደባባዩ እንደ ፀሐይ ኮከብ ብርሃን ጮራ፣ እንደ ቀለበት የህብር ዙሪያ እንደ ክበብ ነው። ባህልህን አስጠንቅረህ ካላወክ አገርህም አያውቅህ! ሕዝብህም አታውቀው! ሕዝብህን ማወቅ ማለት የሕዝብህን የባህል ብልት ጠንቅቀህ መገንዘብ ነው። ሕዝብህን ማወቅ ደግሞ አገርህን ማወቅ ነው። ማንነቱን ያላጤንክለትን ህዝብ ነገ ማስተዳደሩ ያቅትሃል እያሱ….


ይላሉ አጤ ምኒልክ የልጅ ልጃቸውን ወራሴ መንግስታቸውን ሲመክሩት። ይህን ምክር ፀጋዬ ገ/መድህን ምኒልክ በተሰኘው ግዙፍ ቴአትሩ ውስጥ ፅፎታል።


ፀጋዬ ገ/መድህን እነዚህን ታላላቅ ኢትዮጵያዊያንን በመድረክ ላይ ነብስ ዘርቶባቸው እያናገራቸው ስለ ኢትዮጵያዊነት እና ስለ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ ሲገነባ የኖረ የብዕር ሰው ነበር።


ፀሐፌ- ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን ቅኔዎችም ሆኑ የተውኔት ፅሁፎች፣ በሁሉም ሀገር ቋንቋዎች ታትመው የሀገር ባህል አስተዋውቀዋል። ፕሬዘንስ አፍሪካን፣ አፍሪካን ፐየትስ፣ አንቶሎጂ፣ ሎተስ፣ ወዘተ ባሉት አለም አቀፍና የአፍሪካ ታላላቅ የሥነ-ፅሁፍ መድብሎች ውስጥ ታትመዋል። በእንግሊዝኛ የፃፋቸው ታሪካዊ ተውኔቶቹ በአፍሪካ የተለያዩ ቦታዎችና በአውሮፓም እንደ ለንደን፣ ሮም፣ ኮፐንሀገንና ቡዳሬስት ባሉ ከተሞች፣ በአሜሪካም በኮሎምቢያም ዋሽንግተን ካሊፎርኒያ እና በሚኒያፖሊስ ዩኒቨርስቲዎች በመድረክ ታይተውለታል። ኮልዡን ኦፍ አልታርስ፣ ቴዎድሮስ…. ዳካር ሴኔጋል ድረስ ተጠርቶ ከተሸለመው ኮማንደር ኦፍ ዘ ሴኔጋል ናሽናል ኮን ኒሻን ሽልማት ጀምሮ ሌሎች አለም አቀፍ ክብርና ሽልማቶችን ያገኘ የዚህች ሀገር ብርቅ ሰው ነበር።

በጥበቡ በለጠ

 

የየካቲት አብዮት 44 አመታት አስቆጠረ፡፡ ኢትዮጵያ አሮጌ፤ ያረጀና የበሰበሰ ስርአት ነው ብላ ንጉሳዊውን መንግስት ፍርክስክሱን አውጥታ አዲስ ስርአት መሰረተች፡፡ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ መጣ፡፡ ትውልድ በቀይ ሽብርና በቀይ ሽብር ተቧድኖ አለቀ፡፡ ኢትዮጵያ ከጦርነትና ከግጭት አዙሪት አልወጣ ብላ ረጅም ጊዜ አስቆጥራለች፡፡ ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያዊ ሁሉ መለያው ስደት ሆነ፡፡ እግርና ችጋር የሐገሪቱ መለያ ሆነ፡፡ የአሁኑ ትውልድ ያን ትውልድን ይተቻል፡፡ ያ ትውልድ ለዚህ ችግር አበቃን የሚሉ ብዙ ወጣቶች አሉ፡፡


ክፍሉ ታደሰ የያ ትውድ ተወካይ ነው፡፡ ኢ.ሕ.አ.ፓ/ን በግንባር ቀደምትነት ከመሠረቱት እና የ1960ዎቹን ትግል እስከ 1970ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ከመሩት የያኔው ወጣት ምሁራን መካከል አንዱ ነው፡፡ እነ ክፍሉ ታደሰ ኢትዮጵያን በዴሞክራሲ፣ በሰብዐዊ መብት፣ በፍትህ፣ በእኩልነት፣ ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ ረገድ እንለውጣታለን ብለው ከያሉበት ተጠራርተው ኢሕአፓን /የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ/ን መሠረቱ፡፡ ቀደም ብለውም የፊውዳል ኢትዮጵያን አስተዳደር በዘመናዊ መንገድ ለመምራት ‘መሬት ላራሹ’ የሚለውን መርህም ለረጅም ጊዜ ሲያቀነቅኑ ቆይተዋል፡፡ ለጥቆም የተማሪው፣ የሰራተኛው፣ የገበሬው፣ የጦር ሠራዊቱ እንቅስቃሴ እያየለ መጣ፡፡


ለውጥ አቀንቃኙ ወጣትም ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊ አስተዳደር ሊለውጣት ተደራጅቶ ብቅ ብሏል፡፡ ታዲያ ድንገት ከጦር ሠራዊቱ የተውጣጡ መኮንኖች የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴን ሥርዓተ-መንግስት በኃይል አፍርሰው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር መንግሥት መሠረቱ፡፡ ሲቀነቀን የነበረውን የተማሪውን ጥያቄና ጩኸት ወስደው ለአብዮቱ ጉዞ ተጠቀሙበት፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ፣ ነፃ ፕሬስን እና በፓርቲ መደራጀትን አገዱ፡፡ ግጭቶች ተጫሩ፡፡ ወደ አሰቃቂ ግድያዎች ተገባ፡፡ ኢሕአፓ ነው ተብሎ የሚታሰብ ወጣት ሕይወቱ ታጨደ፡፡ የቀበሌና የአብዮት ጥበቃ አባላትን ጨምሮ ከፍተኛ የደርግ አመራሮች በኢሕአፓ ወጣቶች ላይ ነፃ እርምጃ አወጁ፡፡ በየጐዳናው፣ በየቤቱ መረሸንም ጀመሩ፡፡ በዚያ ትውልድ እንደ ጤዛ በረገፈበት ወቅት ክፍሉም የዚያ ሁሉ መከራና ስቃይ ተቋዳሽ ነበር፡፡ ክፍሉ ተአምራዊ በሚባል ሁኔታ ከእልቂቱ ከተረፉት ጥቂት የኢሕአፓ አመራሮች መካከል አንዱ ነው፡፡ በሕይወት በመኖሩም የዚያን ዘመን ታሪክን ያ ትውልድብሎ በሦስት ተከታታይ መፃሕፍት ዘከረ፡፡ ለትውልድ አስተላለፈ፡፡


የኢሕአፓ ወጣቶች የመጨረሻውን የሞትሽረት ትንቅንቅ ሲያደርጉ ይታያል፡፡ መጽሐፉን ያዘጋጀው ክፍሉ ታደሰ በዚህ ሁሉ እልቂት ውስጥ፣ ትንቅንቅ ውስጥ፣ መከራ ውስጥ የነበረና ከዚያም በሕይወት ተርፎ ያየውን፣ የሰማውን፣ የፃፈውን፣ ያነበበውን፣ የጠየቀውን ታሪክ ያ ትውልድ ብሎ አዘጋጅቶ ሰጥቶናል፡፡ ክፍሉ ታደሰ የኢሕአፓን የትግል ታሪክ ያ ትውልድ በሚል ርዕስ እስከ ፍፃሜው ድረስ በዝርዝር በመፃፍ የሚስተካከለው የለም፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ The Generation በሚል ርዕስ እነዚህን ሦስት ተከታታይ መፃሕፍቶቹንም ቀደም ሲል ያሳተመ ሲሆን መጽሐፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ስርጭት የነበረውና 1960ዎቹን የኢትዮጵያን ታሪክ ለቀሪው ዓለም ያስተዋዋቀ ነው፡፡


ስለ ያ ትውልድ ታሪክና ማንነት ከክፍሉ ታደሰ በኋላ የተለያዩ ፀሐፍት እነደየግንዛቤያቸው መፃሕፍትን አዘጋጅተው አሳትመዋል፡፡ ጥቂቶቹን ለመጠቃቀስ ያህል የፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀን መጽሐፍ ማስታወስ እንችላለን፡፡ The Ethiopian Revolution:- War in the Horn of Africa. የተሰኘው መጽሐፋቸው ስለ ያ ትውልድ ጥናት አድርገው ያዘጋጁት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ዓለም አስረስ የተባሉ ፀሐፊ ያዘጋጁት መጽሐፍም ተጠቃሽ ነው፡፡ History of the Ethiopian Student Movement (in Ethiopia and North America): Its impact on Internal Social Change, 1960-1974 ይሰኛል፡፡ መጽሐፉ በተለይ በውጭ ሀገራት ውስጥ የነበሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ለለውጥ ትግሉ መፋፋም ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ይዘክራል፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ቀደም ብለው ከተፃፉት የያ ትውልድ መዘክሮች አንዱ ጆን ማርካኪስ እና ነጋ አየለ ያዘጋጁት Class and Revolution in Ethiopia የተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ የአብዮቱ ሞቅታ ባልቀዘቀዘበት ወቅት የታተመ መጽሐፍ በመሆኑ በሰፊው ተነቧል፡፡


ራንዲ ባልስቪክ የተባሉ ሰው ደግሞ Haile Selassie’s Student: Rise of Social and Political consciousness በሚል ርዕስ ስለ ክፍሉ ታደሰ ትውልድ ጽፈዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ የፖለቲካና የአስተሳሰብ ምህዋር እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስላደረጉት የ1960ዎቹ ወጣቶች ፍልስፍና ላይ ትኩረት የሚያደርግ መጽሐፍ ነው፡፡ ሌላው አስገራሚ መጽሐፍ ራውል ቫሊዲስ የፃፉት Ethiopia the Unknown Revolution የተሰኘው ሲሆን፤ የታተመው ደግሞ ኩባ ነው፡፡ መጽሐፉ የኢትዮጵያን አብዮት አወንታዊ በሆነ መልኩ እየገለፀ የሚተርክና አያሌ መረጃዎችንም የሚሰጥ ነው፡፡ አብዮት ተቀጣጥሎ ትውልድ ሁሉ በፍሙ እና በነበልባሉ ሲቀጣጠል በዓይናቸው ያዩት ደግሞ ዴቪድ ኦታዋ እና ማሪና ኦታዋ የተሰኙ አሜካውያን ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ ነበሩ፡፡ ያዩትን የታዘቡትን፡- Ethiopia:- Empire in Revolution ብለው መጽሐፍ አድርገውት ለንባብ አብቅተውታል፡፡ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ Radicalism and Cultural Dislocation የሚሰኝ መጽሀፍ አሳትመዋል፡፡ የእርሳቸው ጽሁፍ የሶሻሊዝም እንቅስቃሴ በቀጣይ ኢትዮጵያ ላይ ያመጣውን ልዩ ልዩ ተፅዕኖ አሳይቷል፡፡


እኚሁ ምሁር ሌላው ያሳተሙት መፅሐፍ Ideology and Elite Conflicts: Autopsy of the Ethiopian Revolution የተሰኘ መጽሐፍ ሲሆን፤ እርሳቸውም እስከ ደርግ ፍፃሜ ድረስ የነበረውን በምሁራን መካከል የታየውን የአመለካከት ልዩነት ያሳዩበት መጽሐፍ ነው፡፡ ዶናልድ ዶንሃም የተባሉ ሰውም 20 ዓመታት አጥንቼው ነው የፃፍኩት የሚሉት Marxist Modernየተሰኘው መጽሐፍም የኢትዮጵያን የለውጥ አብዮት የሚዳስስና በተለይም የተማሪዎችን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነው፡፡


ኤድዋርድ ኪሲ የተሰኙ ፀሐፊም Revolution and Genocide in Ethiopia and Cambodia በተሰኘው መጽሐፋቸው በኢትዮጵያ እና በካምቦዲያ ውስጥ ተቃዋሚዎች ላይ የተወሰደውን የጭካኔ እርምጃ ከዘር ማጥፋት ድርጊት ጋር አገናኝተውት እያነፃፀሩ ያቀረቡበት መጽሐፍ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ፀሐፊ ዶ/ር አንዳርጋቸው ጥሩነህ በዚሁ በኢትዮጵያ አብዮት ላይ The Ethiopian Revolution 1974 - 1987 A Transformation from an Aristocratic to a Totalitarian Autocracy በሚል ርዕስ የአብዮቱ መምጣት መንስኤው ምን እንደሆነ እና ያስከተለውንም ውጤት ለማሳየት ሰፊ ጥረት አድርገዋል፡፡ ባቢሌ ቶላም To kill a Generationበሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን የትውልድ እልቂት በጥሩ ሁኔታ ያሳየበት መጽሐፍ ነው፡፡


በዚሁ በኢትዮጵያ አብዮት ላይ ከተጻፉ የእንግሊዝኛ ጽሁፎች መካከል Documenting the Ethiopian Student movement: - An Exercise in Oral History የተሰኘው መጽሀፍም በፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ተዘጋጅቷል፡፡ መጽሀፉ በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት የሚባሉ አፍአዊ ታሪኮችን ሰብስቦ ለመሰነድ የሞከረ ነው፡፡ ጳውሎስ ሚልኪያስም Haile Selassie, Western Education, and Political Revolution in Ethiopia የተሰኘ መጽሀፍ በማዘጋጀት ልዩ ልዩ መረጃዎችን በመሰብሰብ ስለ ቀዳማዊ ኃይለስላሴና ስለ ደርግ አንዳንድ ምስጢራትን የጻፉበት ሰነድ ነው፡፡


ሪስዛርድ ካፑስንስኪ የተባለ የፖላንድ ጋዜጠኛም The Emperor፡- Downfall of an Autocrat በሚል ርእስ መጽሀፍ አሳትሟል፡፡ መጽሀፉ የጃንሆይን ውድቀት ከቅርብ አገልጋዮቻቸው እየጠየቀ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከዚሁ መጽሀፍ ጋር ተመሳስሎ ያለው ሌላው መጽሀፍ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደኖረ የሚነገርለት ፓትሪክ ግሊስ የጻፈው The Dying Lion: - Feudalism and Modernization in Ethiopia የተሰኘው መጽሀፍ ነው፡፡


የጃንሆይን ስርአተ-መንግስት የመውደቅያ ምክንያቶች በዝርዝር የጻፈበት ነው፡፡ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት የነበረን ነጠላ ታሪክ ማለትም በአንድ ሰው ታሪክ ላይ ተመርኩዘው ከተጻፉ መጻህፍት መካከል የሕይወት ተፈራ Tower in the Sky የተሰኘው መጽሀፍ ይጠቀሳል፡፡ ሕይወት የኢሕአፓ አመራር አባል የነበረውን የፍቅረኛዋን የጌታቸው ማሩን ሁኔታና በአጠቃላይ በፓርቲውና በዘመኑ ስለነበረው ጉዳይ ጽፋለች፡፡ መጽሀፏን በአማርኛም ቋንቋ በጌታነህ አንተነህ አስተርጉማ አቅርባለች፡፡ የአስማማው ኃይሉ ከጐንደር ደንቢያ እስከ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የተሰኘው መጽሐፍና የኢሕአሠን ታሪክ የዘከረበት መጽሐፍ በውብ አፃፃፉ የተመሰገነበት ነው፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሀርቃ ሀሮዬም በደቡብ ክልል ስለነበረው የኢሕአፓ እንቅስቃሴ ከግል ገጠመኛቸው በመነሳት መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡


በዘመኑ ከኢሕአፓ በተፃራሪ የቆሙትና ከደርግ ጋር አብሮ በመስራት ለውጥ እናመጣለን ያሉት የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ /መኢሶን/ አመራር የሆኑት አንዳርጋቸው አሰግድ በአጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ ብለው ስለትውልዳቸው ዘክረዋል፡፡ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም ትግላችን በሚል ርዕስ የእርሳቸውን የአገዛዝ ዘመን ሊያስረዱ የሞከሩበት መጽሐፍም ታትሟል፡፡ የሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ እኛ እና አብዮቱ፣ የሌሎች የዘመነ ደርግ ፖለቲከኞችና ጦር ሠራዊቶች ብዙ ጽፈዋል፡፡ ከወጣትነት አስከ አሁንም ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ዶክተር መረራ ጉዲና የኢትየጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የህይወቴ ትዝታዎች፣ የሀይሉ ሻወል ሕይወቴና የፖለቲካ እርምጃዬ ሌሎችንም በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ያሉ ጸሀፊያንን ጨምሮ ዛሬ በኢሕአዴግ ፓርቲ ስር የተሰባሰቡ ፀሐፊያንም ስላሳለፉት የ1960ዎቹ ታሪክ ጽፈዋል፡፡


ያንን ዘመን ወደ ፈጠራ ስነ-ጽሁፍም በማምጣት የባየ ንጋቱ፣ የማይቸነፍ ፀጋ ፣ የካሕሳይ አብርሃ የአሲምባ ፍቅር፣ የቆንጂት ብርሃኑ፣ ምርኮኛ እና ሌሎችም ፀሐፊያንን እና ጽሁፎቻቸውን መጠቃቀስ ይቻላል፡፡ ክፍሉ ታደሰ ስለ ትውልዱ፣ ያ ትውልድ ብሎ በጀመረው መንገድ ብዙዎች ፀሐፊያን ብቅ ብለውበታል፡፡ እነዚህ የክፍሉ መጻህፍት ከሌሎች የሚለዩት የኢሕአፓን ታሪክ ከዘሩ፣ ከጽንሱና፣ ከውልደቱ እስከ እድገቱና ፍጻሜው ድረስ ከውስጥ ሆኖ እሱ ራሱ የኖረበትን ታሪክ በሦስት ተከታታይ መጻህፍት መዘከሩ ነው፡፡


ክፍሉ ታደሰ ሌላ መጽሐፍ አሳተመ፡፡ ኢትዮጵያ ሆይ ይሰኛል፡፡ ክፍሉ የያ ትውልድ ከፍተኛ አመራርና ታጋይ ሆኖ፣ የመከራውም ገፈት ቀማሽ ሆኖ ሳለ፣ በተቻለው መጠን የዘመኑን ሁኔታ ለማንም ሳያዳላ ለመጻፍ ሞክሯል፡፡ ጉዳዩ ግን ኢትዮጵያ ከዚህ ሁሉ አብዮት በኋላ፣ ከዚህ ሁሉ እልቂት በኋላ የት ደረሰች? የሚለው ነው፡፡ 44 ዓመታት ያለፈው የኢትዮጵያ አብዮት ዛሬስ እንዴት ነው? የተከፈለው መስዋእትነት የት ደርሷል? ትውልድ ጉም ሆኖ ተበትኗል ወይስ ገና ዶፍ ሆኖ ይዘንባል? ወይስ ታላቁ ባለቅኔ ዮፍታሄ ንጉሴ እንዳለው ስንዴዋ ሞታ፣ ተቀብራ፣ በስብሳ ከዚያም አድጋና አፍርታ ትመግበን ይሆን? የኢትዮጵያን አብዮት የ44 አመታት ጉዞን ትርፍና ኪሳራውን ለማወቅ የክፍሉ ታደሰ መጻህፍት ብዙ መረጃዎችን ይሰጡናል፡፡

 

በጥበቡ በለጠ

 

መጪው የካቲት ወር ነው። በኢትዮጵያ አብዮት ውስጥ ባለታሪክ ወር ነው። ውድ አንባብዎቼ የዛሬ 43 ዓመት እና ከዚያ በፊት በነበሩት ጊዜያት በኢትዮጵያ ውስጥ የወጣት፣ የሠራተኛው፣ የገበሬው እና በመጨረሻም ወታደራዊ እንቅስቃሴ መጥቶ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ስርአተ መንግሥት ወደቀ። ኢትዮጵያንም ለሦስት ሺ ዘመናት እየተፈራረቀ ይመራት የነበረው ሰለሞናዊው ሥርወ-መንግሥት ወደቀ። ከዚህ ስርአት መውደቅ ጋር ተያይዞ ልዩ ልዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቋቁመው፣ ከዚያም ወደ ግጭት አምርተው ኢትዮጵያውያን በሚዘገንን መልኩ አለቁ። ይህን የኢትዮጵያዊያንን አሣዛኝ ክስተት፣ ታሪክ ፀሐፊያን እንዴት ገለፁት በሚል ርዕስ ጥቂት ቆይታ እናደርጋለን።
ኢትዮጵያ በ1968 እና 69 ዓ.ም ላይ ታሪኳ በእጅጉ አሣዛኝ ነበር። ብዙ ሺ ወጣቶች በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር ግጭቶች አልቀዋል። በ1960ዎቹ ብቅ ያሉት ባለ አፍሮ ፀጉራም ወጣቶች፣ በማርክስ፣ በኤንግልስ እና በሌሊን አስተምህሮቶችና ፍልስፍናዎች የተራቀቁት የኮሚኒስት እና የሶሻሊዝም ርዕዮት የሚያስተጋቡት እኒያ ወጣቶች በእርስ በርስ ግጭት ሕይወታቸው ረግፏል።


ለመሆኑ የ1967፣ 68፣ 69፣ ዓ.ምረቶች የኢትዮጵያ ወጣቶች እልቂት መንስኤም ምንድን ነው? ለምን ትውልድ እንደ ቅጠል ረገፈ? ዛሬ ላይ ቆመን ወደ ኋላ ስናይ ገዳይም ሟችም በምን ሁኔታ ውስጥ ሆነው መጥፎ ታሪክ ያስመዘገብነው?


እነዚህ ጥያቄዎች ብዙ ፍልስፍናዊ ማብራሪያ እና ትንታኔ የሚጠይቁ ናቸው። ነገር ግን ዋና ዋናዎቹን ከልዩ ልዩ ምሁራን የታሪክ ድርሣን ውስጥ ያገኘኋቸውን ምክንያቶች ላጫውታችሁ።
በ1950ዎቹ ውስጥ ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ወርቃማ ዘመኗ ነበር። ለምሣሌ በዚያን ዘመን የአፍሪካ የእግር ኳስ ዋንጫ አሸናፊ የሆነችበት ነው። ስለዚህ በእግር ኳሱ መንግሥቱ ወርቁን የመሣሰሉ የኳስ ጠቢቦች የመጡበት ወቅት ነው። በማራቶን ሩጫም በባዶ እግሩ ሮጦ አለምን ጉድ ያሰኘ ባለድል አበበ ቢቂላን የመሣሰሉ ዝና ብዙ ሰዎች ከዋክብት ሆነው ብቅ አሉ።


በሙዚቃው አለም፣ በረቂቅ ሙዚቃና ፍልስፍና ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ ተአምር ሊያሣይ ጐልቶ የወጣበት፣ የክብር ዘበኛ፣ የምድር ጦር፣ የፖሊስና የሌሎችም የሙዚቃ ቡድኖች ኢትዮጵያ ላይ የገነኑበት፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ እና ሙሐመድ አህመድ በወርቃማ ድምፃቸው ሙዚቃን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ወደ ላይ ከፍ ያደረጉበት ዘመን ነበር።


በስዕል ጥበብ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን የሽልማት ድርጅት ተሸላሚዎቹ እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፣ የአብስትራክት ስዕል ጠቢቦቹ ገብረክርስቶስ ደስታ እና እስክንድር ቦጋሲያን ፍክትክት ብለው የወጡበት ወርቃማ ዘመን ነበር።


በድርሰት አለም በተለይ በልቦለድ ሥነ-ፅሁፍ ውስጥ እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪው ፍቅር እስከ መቃብር ብቅ ያለበት፣ ታላቁ የሥነ-ፅሁፍ ሰው ክብር አቶ ሀዲስ አለማየሁ የደራሲያን አባት ሆነው የመጡበት ዘመን ነበር።
የትምህርት ተቋማት፣ ከተሞች፣ መንገዶች፣ ሕንፃዎች እየፈኩ የመጡበት፣ እንደ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና እናታቸው ወ/ሮ ሲልቪያ ፓንክረስት የኢትዮጵያን ማንነት እና አኩሪ ታሪክ ለአለም በሰፊው ያስተዋወቁበት ወቅት ነው።


ዘመን ሰበር የብዕር ባለቤቶቹ ታላቁ ሰው ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ የለዛና የቁም ነገር ብዕር ባለቤት አብዬ መንግሥቱ ለማ፣ ከብዕሩ ጫፍ ወርቅ የሆነ ታሪክ የሚንፈለፈልለት ብርሐኑ ዘሪሁን፣ እውነት ነው ብሎ ለሚያምነው ጉዳይ ደረቱን የሚሰጠው ሰማዕቱ ደራሲ አቤ ጉበኛን የመሣሠሉ ፀሐፌ-ተውኔቶች፣ ደራሲያንና ባለቅኔዎች ያን ዘመን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የጥበብ ብርሃን ረጩ።


እነዚህና ሌሎችም ጉዳዮች እየጐመሩ ሲመጡ ከኢትዮጵያ አልፎ ባህር ማዶ ያለውን ዕውቀት ሰብስበው እንዲመጡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አያሌ ወጣቶችን ወደ ውጭ ሀገራት ለትምህርት መላክ ጀመሩ።
ወጣቶቹ ሩሲያ፣ ቻይና፣ አውሮፓ፣ አሜሪካ እና ሌሎችም ሀገራት ሄዱ፣ ተማሩ። በወቅቱ ሀገራት በኮሚኒስት፣ በሶሻሊስት እና ከዚያ ባለፈ ደግሞ በካፒታሊስት አስተሣሰቦች የተቃኙ ነበሩ። በተለያዩ ሀገራት የለውጥ አብዮቶች፣ ስር ነቀል ለውጦች ይካሄዱ ነበር፡፣ የማርክስ፣ የኤንግልስ እና የሌኒን ፍልስፍናዎችን ወራሾች በመሆን የኢትዮጵያ ወጣቶች አዲስ መንገድ ጀመሩ።


የሶሻሊስት ንቅናቄዎችን አስተሣሰቦችን በማንበብ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ለየት እያሉ መጡ። በሃይማኖት እና በኢትዮጵያዊ ግብረ ገብ ያደጉ ወጣቶች አዲስ አውሮፓዊ ፍልስፍና ውስጣቸው ሲገባ፣ አብሯቸው የኖረውን ጥንታዊ ማንነታቸውን እያስለቀቃቸው መጣ።


ወጣቶቹ ኢትዮጵያን የሚያዩበት መነፅር መስታወቱም ሆነ ፍሬሙ የተሰራው በውጭ ሀገራት ባገኙት ትምህርትና ፍልስፍና ሆነ።
ያንን ዘመን በመኖርና በማጥናት መፃህፍትን ካሣተሙ ሰዎች መካከል ጳውሎስ ሚልኪያስ አንዱ ናቸው። እርሣቸው ያሣተሙት መፅሃፍ Haile Selassie, Western Education and Political Revolution in Ethiopia የሚሰኝ ነው። ወደ አማርኛ ስናመጣው ኃይለስላሴ፣ የምዕራባውያን ትምህርት እና የፖለቲካ አብዮት በኢትየጵያ የሚሰኝ ነው።


ታዲያ በዚህ መፅሐፍ ውስጥ እምናገኘው ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በተለይ ከባህር ማዶ ያለውን የፖለቲካ ፍልስፍና አምጥተው ኢትዮጵያ እንድትለብሰው፣ እንድትታጠቀው ሙከራ አደረጉ።
አንዱ የሩሲያን የፖለቲካ ፍልስፍና ሊያላብሣት ሲሞክር፣ ሌላው የቻይናን፣ ሌላው የአውሮፓን፣ ሌላው የአሜሪካን፣ ሌላውም እንደዚያ እያለ ሊያላብሳት ሲጥር ኢትዮጵያ መልኳን፣ አምሣያዋን አጣች የሚሉ የዘመኑን ታሪክ የፃፉ ብዕረኞች ይገልፃሉ።


በዘመኑ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ጠፋ የሚሉ ብዕሮች አሉ “መሬት ላራሹ” የሚለው መፈክር እንዳለ ተገልብጦ ከሩሲያ መጣ። Land For Peasant የሚለው የሩሲያ አብዮት አንዱ መቀስቀሻ ወደ ኢትዮጵያም ሲመጣ መሬት ላራሹ በሚል መሬት አንቀጥቅጥ እንቅስቃሴዎችን አመጣ። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደኖረ የሚነገርለት ፓትሪክ ግሊስ የተባለ ታሪክ ፀሐፊ በእንግሊዘኛ ቋንቋ The Dying Lion:- Feudalism and Modernization in Ethiopia የተሰኘ መፅሐፍ አሣትሟል። መፅሃፉን ወደ አማርኛ ስንመልሰው እየሞተ ያለው አንበሣ፣ ፊውዳሊዝም እና ዘመናዊነት በኢትዮጵያ የሚል ርዕስ ይኖረዋል።


በዚህ መፅሃፍ ውስጥ እንደሚጠቀሰው ከሆነ የኢትዮጵያ አብዮት በሁለት ቅራኔዎች የተሞላ ነበር። አንደኛው ከውስጥ ባለ ለረጅም ጊዜ በኖረው የሀገሪቱ ማንነት እና አዲስ በመጣው ዘመናዊ አስተሣሰብ መሀል የሚያስታርቅ ድልድይ ሣይኖር ኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት ፈነዳ።


በዚህ የአብዮት ፍንዳታ ወቅት መለዮ ለባሹ ወታደር ወደ ሥልጣን መጣ። አብዮቱ እየተወጠረ የመጣ ስለነበር የመነጋገር፣ የመቻቻል፣ አንዱ የሌላውን ኃሣብ ተቀብሎ የማስተናገድ ባህል አልነበረም። መሐል ላይ የሚያገናኝ የኃሣብ ድልድይ አልተሰራም ነበር። የመገናኛ ድልድይ ባለመኖሩ ተኩስ ተጀመረ።


ኢሕአፓ፣ መኢሶን፣ ሰደድ፣ አብዮት ጥበቃ፣ ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር እየተባባለ ኢትዮጵያዊ የተማሪ ወጣት እርስ በርሱ ተላለቀ።
ኤድዋርድ ኪሲ የተሰኙ ታሪክ ፀሐፊ Revolution and Genocide in Ethiopia & Cambodia የተሰኘ መፅሃፍ አሣትመዋል። መፅሐፉ አብዮትና ዘር ማጥፋት በኢትዮጵያ እና በካምቦዲያ ምን ይመስል እንደነበር ብዙ ዋቢዎችን በማንሣት የሚዘክር ነው። ያንን አስፈሪ የእልቂት ዘመን በታሪክ ድርሣን ውስጥ ያስቃኛል።


ታዲያ ብዙ ፀሐፊያን እንደሚገልፁት ኢትዮጵያ ውስጥ በቀይ ሽብር እና በነጭ ሽብር እልቂት እየተመተረ የወደቀው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሀገሬ ኢትዮጵያን እኔ በጣም እወዳታለሁ በሚል የኃሣብ ፍጭት ምክንያት ነው። ይህን የኢትየጵያን ፍቅር በአግባቡ ባለመነጋገር፣ ባለ መቻቻል፣ ባለመከባበር፣ ምክንያት መግለፅና ማሣደግ አልተቻለም። እናም ብዙ ሺ ወጣት ኢትዮጵያዊያን በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ አንደ ቅጠል ረገፉ።


በርካታ ፀሐፊያን በመፃህፍቶቻቸው እና በጥናቶቻቸው እንደሚገልፁት ኢትዮጵያ ሰላምን የሚያስከብሩ ተቋማት ስለሌሏት፣ የሰብዓዊ መብት መጠበቂያ ጠንካራ ተቋማትን ባለማቋቋሟ፣ የመነጋገርና የመቻቻል ባህል ባለማዳበሯ፣ የሕግ የበላይነትን የሚያስከብሩት ኃይሎች ስራቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ ለተከሰተው የኢትዮጵያዊያን እልቂት እንደ ምክንያት ያስቀምጡታል።
ይቀጥላል

 

በጥበቡ በለጠ

 

ኢትዮጵያ ዓለም አሸባሪ ነው ብሎት ያገለለውን ሰው፣ በርካቶች የተገኘበት ቦታ ሊገድሉት የሚያስሱትን ሰው፣ ኢትዮጵያ ግን በውስጥዋ ደብቃ አኑራዋለች። ማኖር ብቻ አይደለም። የኔ ዜጋ ነው ብላ ፓስፖርት ሰጥታ፣ ከአገር ወደ አገር ኢትዮጵያዊ ሆኖ እንዲዘዋወር አድርጋለች። ኢትዮጵያ ዜጋዋ ያልሆነውን ሰው የኔ ዜጋ ነው ብላ ፓስፖርት የሰጠችው ሰው የቀድሞን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላን ነው። ውድ አንባቢያን ሆይ፣ ለዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት ኢትዮጵያዊ ወግ ኤልሰን ማንዴላን ኢትዮጵያ ገና በወጣትነቱ ዘመን እንዴት አድርጋ አወቀችው? ለምንስ ኢትዮጵያዊ አደረገችው በሚሉትና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ጥቂት ቆይታ እናደርጋለን።


ኔልሰን ማንዴላ፣ በዚህች ፕላኔት ላይ ልዩ ሰው ሆነው ይጠራሉ። ምክንያቱም 27 ዓመት ሙሉ በአፓርታይድ ስርዓት ታስረው ሲፈቱ እና ቀጥሎም ወደ ምርጫ ገብተው የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ወደ ቂም በቀል አልገቡም። 27 ዓመታት ያሰሯቸውን ነጮች ይቅር ብለዋቸዋል። ከዚህ በኋላ ደቡብ አፍሪካ የጥቁሮችም፣ የነጮችም ሀገር ናት ብለው ተናገሩ።


ከዚያም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ብሔራዊ እርቅ አምጥተው ሀገሪቷን ወደ ሠላም አመጧት። ቂምን፣ መገዳደልን፣ መሻኮትን ያስቀሩት የደቡብ አፍሪካው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ይቅርታን የት ተማሩ? በውስጣቸውስ እንዴት አደረ? የሚሉ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩ ማንዴላ ብዙ ነገሮችን የተማሩት ኢትዮጵያ ውስጥ በኖሩበት ወቅት ነው ይላሉ።
እኚህ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑ ታላቁ ማንዴላ ገና ወጣት ታጋይ እያሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት መጡ? እንዴትስ ተሸሸጉ? እንዴት ፓስፖርት ተሰጣቸው? ማነው ገና በጥዋቱ ማንዴላ ወደፊት ታላቅ ሰው ይሆናል ብሎ የተነበየው? በነዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ጥቂት ላውጋችሁ።


ANC የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረንስ የተሰኘው የፖለቲካ ፓርቲ መሪ የነበሩት ማንዴላ በወጣትነት ዘመናቸው በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከሌሎች የደህንነት እና የመረጃ ሰዎች ጋር በመሆን ማንዴላን በድብቅ ወደ ኢትዮጵያ አስገቡ። ከዚያም አባታዊ ምክርና ማበረታቻ አድርገው ማንዴላ በኢትዮጵያ ውስጥ ወታደራዊ ትምህርት እንዲማሩና የደቡብ አፍሪካን የአፓርታይድ ስርዓት ለመታገል የሚያስችላቸውን ብቃት እንዲያገኙ ማንዴላን መጠለያ ሰጧቸው።


ከዚያም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኘው በኮልፌ ፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ ገቡ። ከዚያም ማንዴላን ብቻ የሚጠብቁ የደህንነት ሰዎችን አስቀመጡ። ለነዚህ የደህንነት ሰዎች ትዕዛዝ ተሰጠ። ይህን ሰው ማንዴላን ከሁሉም በላይ በጥንቃቄ ጠብቁት። ሚስጢራዊ እንግዳችን፣ ሚስጢራዊ ቤተኛችን ነው እየተባለ በስርዓት ይጠበቁ ነበር።


ታዲያ በዚያን ወቅት እነ አሜሪካ እና ሌሎች የነጭ አክራሪዎች ማንዴላን ለመግደል በየቦታው እያነፈነፉ ነበር። ኢትዮጵያ በወቅቱ የአሜሪካ መንግስት ወዳጅ ሆና ሳለ፣ ግን ከአሜሪካ ግድያ ሸሽጋ ማንዴላን በቤቷ አስቀምጣ ታኖራለች።


ዓለም ዛሬ እንደ ብርቅ ሰው እያደነቀ ታሪካቸውን የሚያወጋላቸውን ኔልሰን ማንዴላን ሸሽጋ ያኖረችው ኢትዮጵያ ናት። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የማንዴላን ብክለት፣ የማንዴላን የወደፊት ታላቅነት እንዴት ሊያውቁ ቻሉ? እንዴትስ ከዓለም ሁሉ ደብቀውት አኖሩት የሚለው ጥያቄ ወደፊት ሲብራራም፣ ግን ማንዴላ ከ1954 ዓ.ም እስከ 1981 ዓ.ም ፓስፖርታቸው የሚያሳየው የኢትዮጵያ ዜጋ መሆናቸውን ነው። ማንዴላ ኢትዮጵያዊ ነበሩ።


ኔልሰን ማንዴላ አፓርታይድን በሚታገሉበት ወቅት ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር የሚዘዋወሩበት ፓስፖርት የኢትዮጵያ ነበር። ኢትዮጵያ በ1954 ዓ.ም ለማንዴላ ፓስፖርት አዘጋጅታ ሰጥታ ነበር።


ኢትዮጵያ ለኔልሰን ማንዴላ ዜጋዬ ነው ብላ እንዴት ፓስፖርትን ያህል ነገርን ሰጠች? ፓስፖርቱ ላይ የተገለፀው ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። በፓስፖርቱ ላይ የተገለፀው የማንዴላ ፎቶዋቸው እንዳለ ሆኖ ስማቸው ግን ተቀይሯል። ኢትዮጵያ የማንዴላን ስም ስም ቀይራ David Motsamayi በሚል መጠሪያ የራሷን ስም አውጥታለታለች። ይህ ዴቪድ የተባለው ኢትዮጵያዊ ኔልሰን ማንዴላ ነው። በፓስፖርቱ ላይ እንደተገለፀው ስራው ጋዜጠኛ ነው ይላል።


ቁመቱ - 1.78
የዓይኑ ቀለም - ቡናማ
የጠጉሩ ቀለም - ጥቁር


እያለች ኢትዮጵያ ለማንዴላ ፓስፖርት አዘጋጅታ፣ የኔ ዜጋ ነው ብላ ከሀገር ሀገር እንዲዘዋወር አድርጋለች። ደቡብ አፍሪካ ለ300 ዓመታት ያህል በነጮች የበላይነት ስትገዛ የኖረች እና ጥቁር ዜጎቿ ደግሞ በባርነት መከራቸውን ሲያዩ መኖራቸው ይታወቃል። ከዚህ አስከፊ ህይወት ደቡብ አፍሪካውያንን ለማውጣት ኔልሰን ማንዴላ እና ጓደኞቻቸው ራሳቸውን መስዋዕት እያደረጉ ከፍተኛ ትግል ጀመሩ። ይህን ትግላቸውን በመደገፍ የደቡብ አፍሪካን ዘረኛ የአፓርታይድ ስርዓት ለመጣል ያስችላት ዘንድ ለነፃ አውጪ መሪው ለኔልሰን ማንዴላ እንደ ልብ እንዲዘዋወር ፓስፖርት ሰጣቸው።


ኔልሰን ማንዴላ ከእስር እስከሚፈቱ ድረስ የነበራቸው ፓስፖርት David Motsamayi በሚል ስም ኢትዮጵያ የሰጠቻቸው መንቀሳቀሻ ነው። ማንዴላ የደቡብ አፍሪካን ፓስፖርት ያገኙት ከ27 ዓመታት እስር በኋላ ነጻ በተለቀቁ በስምንተኛው ቀን ነበር። እስከዚያው ቀን ድረስ ግን ፓስፖርታቸው ላይ ያለው ዜግነት ኢትዮጵያዊ ነበር። በነገራችን ላይ ማንዴላን 27 ዓመታት ያሳሰራቸውም ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ነው። ምክንያቱ እንዲህ ነው።


ፓርቲያቸው ANC ለስብሰባ ጥሪ ያደርግላቸዋል። ማንዴላም ኢትዮጵያ ውስጥ ያላቸውን ትምህርት አቋርጠው ወደ ደቡብ አፍሪካ ይጓዛሉ። በዚህ ወቅት ፓስፖርታቸው የኢትዮጵያ ነው። ከዚህ ሌላ ኢትዮጵያ ለማንዴላ ሽጉጥና ጥይቶችም ሰጥታቸዋለች።


ደቡብ አፍሪካ እንደደረሱ በደህንነት ሃይሎች ልዩ ክትትል ማንዴላ ተያዙ። ከዚያም ፍርድ ቤት ቀረቡ። ክሳቸውም ሁለት ነገር ነው። አንደኛው የደቡብ አፍሪካን መንግስት በኃይል ለመጣል ወታደራዊ ስልጠና ኢትዮጵያ ውስጥ መውሰዳቸው ነው። ሁለተኛው ክስ ሀሰተኛ የመጓጓዣ ሰነድ ፓስፖርት መያዛቸው ነው። እነዚህ ሁለቱም ጉዳዮች ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዙ ናቸው።
ኔልሰን ማንዴላ A Long walk to freedom /ረጅም ጉዞ ለነፃነት/ ብለው መፅሐፍ ያሳተሙበት ታሪክ ሰውየው ከኢትዮጵያ ጋር እጅግ የጠበቁ ቁርኝት ነበራቸው።


በ1955 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ ሳሉ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ ተገኝተው የወደፊቷ አፍሪካ የዕርቅ እና የአንድነት እንድትሆን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንግግር ሲያደርጉ ማንዴላ ሰምተዋል። እናንተ የአፍሪካ መሪዎች አሁን ስልጣን ስትይዙ በዘመኑ ቅኝ ግዛት የበደሏቸውን ገዢዎች አትበቀሉ። ይቅር በሏቸው እያሉ ንግግር አድርገው ነበር። በአንዳንዶች አባባል ኔልሰን ማንዴላ የዛሬ 55 ዓመት የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ላይ ተገኝተው የሰሙት የእርቅና የሠላም ጥሪ በኋላ ላይ ራሳቸው በነጭ የደቡብ አፍሪካ አገዛዞች ላይ ይቅርታን እንዲያደርጉ በጎ ተፅዕኖ ሳያሳድር እንዳልቀረ ይገመታል።


ዓለም ማንዴላ የሠላም፣ የእርቅ፣ የአንድነት ተምሳሌት ናቸው በማለት ይጠሯቸዋል። እኚህን የአፍሪካ የፍቅር ተምሳሌት ከሞትና ከአደጋ ሸሸጋ ያኖረችው ኢትዮጵያ ናት።
ኢትዮጵያ እንደ ኔልሰን ማንዴላን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎችን ጠብቃ፣ አስተምራ፣ በጨለማው ዘመን መጠለያ ሰጥታ ያኖረች የአፍሪካ ሕብረት እናትም አባትም ነች።


በጥበቡ በለጠ

 

ለዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት ታሪክ አንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊን ያስታውሳል። እኚህ ኢትዮጵያዊ ዝናና ተግባራቸው ከሀገር አልፎ የአፍሪካ መከታ የሆኑ ናቸው። የአፍሪካ ህብረት እንዲመሠረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉትን አምባሳደር ከተማ ይፍሩን በጥቂቱ እናስታውሳለን።


ከዛሬ 55 ዓመት በፊት የአፍሪካ ሀገራት ጥቂቶቹ ገና ከቅኝ ግዛት መከራ የተላቀቁበት ወቅት ነበር። እናም መጪዋ አፍሪካ ጠንካራ እንድትሆን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት ዋነኛው አቀነባባሪ፣ ዋነኛው ባለታሪክ፣ ዋነኛው ዋልታና ማገር ከተማ ይፍሩ ናቸው።


በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ኢትዮጵያን ሲያገለግሉ የነበሩት እኚህ ሰው የቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የአፍሪካ መሪዎችን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን አሳምነው አስተባብረው የዛሬ 55 ዓመት አዲስ አበባ ላይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ያደረጉ ጎምቱ ኢትዮጵያዊ።


ግን የአፍሪካ መሪዎች በተሰበሰቡ ቁጥር ይህን ታላቅ ሰው ሲያስታውሱት፣ በስሙ አንዲት ነገር እንኳ ሲሰይሙ አይስተዋልም። ወደፊት ገና የሚበለበል ታሪክ የሚነገርለት ከተማ ይፍሩ የአህጉሪቱ ታላቅ ሰው ነበር። በጥቁር አለም ውስጥ ጥቁር መሪዎችን አስተባብሮ ‘OAU’ የተባለውን ድርጅት ለመመስረት ኢትዮጵያ የተጓዘችበትን ረጅም መንገድ፣ መስቀሉን ተሸክሞ ዘላለማዊ አምድ ያቆመው፣ ከተማ ይፍሩ ማን ነው የሚለውን ጥቂት እንቃኝ።


ከተማ ይፍሩ ከአቶ ይፍሩ ደጀን እና ከወ/ሮ ይመኙሻል ጎበና ታህሳስ 9 ቀን 1921 ዓ.ም በሐረር ጋራሙለታ አውራጃ ተወለዱ። ኢትዮጵያ በፋሽስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ስትወረር ከተማ ይፍሩ የ7 ዓመት ልጅ ነበሩ። ታዲያ በዚያን ወቅት የኢጣሊያ ፋሽስቶች ከፍተኛ ሀይልና መሣሪያ ይዘው ስለመጡ አያሌዎች አለቁ። ሕፃናትና ሴቶች ለከፋ ችግር ተጋለጡ። የሰባት ዓመቱ ከተማ ይፍሩም ከአባታቸው ጋር በመሆን ከሐረር ወደ ባሌ፣ ከዚያም በእንግሊዞች ስር ወደነበረችው ሶማሌ ላንድ ተሰደዱ። በዚህ የስደት ጉዞ ውስጥ ከኢጣሊያ ጋር እየተዋጉ ነበር። እናም የሰባት ዓመት ህፃን የነበሩት ከተማ ይፍሩ በዚ እድሜያቸው ጦርነትን ስደትን አይተዋል፤ ተሳትፈዋል። በዚሁ በስደት ጊዜያቸውም ሶማሌያ በርበራ ውስጥ በተዘጋጀው የስደተኞች ትምርት ቤት ገቡ። መከራው አላባራ አለ። ጣሊያኖች ከኢትዮጵያ አልፈው በርበራን ወረሩ። ከተማ ይፍሩ በዚያ እድሜያቸው እንደገና ወደ ሌላ ስደት ተጋለጡ። ከሶማሌያ ተነስተው ወደ ኬኒያ ተሰደዱ። ኬኒያም ትምህርታቸውን ቀጠሉ። እዚያም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ።


ከነፃነት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሐገራቸው ተመለሰ። ቀጥሎም አጎታቸው ዘንድ አምቦ ሔዱ። አምቦ እያሉ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አምቦን ሊጎበኙ ሲመጡ ከተማ ይፍሩ ደብዳቤ ጽፈው ለጃንሆይ ሰጡ። የደብዳቤው ይዘት አዲስ አበባ ሄደው መማር እንደሚፈልጉና ለዚህም ጃንሆይ እንዲረዷቸው ነበር። ጃንሆም ደብዳቤውንም ሆነ ታዳጊውንከተማይፍሩን ወደ አዲስ አበባ አምጥተው አስተማሩ፡፤
የከተማ ይፍሩ ህይወት ይገርማል። ከስደተኝነት ወደ ቤተ-መንግስት ልጅነት ተቀይሮ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀቁ።


አምባሳደር ከተማ ይፍሩ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ነሐሴ 10 ቀን 1944 ዓ.ም እንደተመለሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል። ቀጥለውም በረዳት ሚኒስትርነት እስከ 1950 ድረስ ሰርተዋል። ከግንቦት 14 ቀን 1950 ጀምሮ ደግሞ ወደ ጽህፈት ሚኒስቴር ተዛውረው ረዳት እና ምክትል ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል። አምባሳደር ከተማ ይፍሩ እንደገና ወደ ቀድሞው መስሪያ ቤታቸው ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በእድገት በመዘዋወር ከሐምሌ 26 ቀን 1953 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 16 ቀን 1963 ዓ.ም ድረስ በሚኒስትር ደኤታ እና በሚኒስትርነት ከፍተኛ አገልግሎት አበርክተዋል።


የአፍሪካ ሕብረት እንዲመሠረት ትልቁን ሚና የተጫወቱት አምባሳደር ከተማ ይፍሩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቋሚ መልዕክተኛ በመሆን ትልቅ ተግባር ፈፅመዋል። በገለልተኛ መንግሥታት ጉባኤዎች ላይ ኢትዮጵያን ወክለው በመሳተፍ ውጤት ያስገኘ የአደራዳሪነት ሚና ተጫውተዋል። በዚህ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራቸውም በሳልነታቸውን አስመስክረዋል።


አምባሳደር ከተማ የአፍሪካ መሪዎችን በተመለከተ መጪውን ጊዜ አስቦ ተተኪ መሪ በማፍራት ረገድ የወቅቱ መሪዎች በርካታ ሊሻገሩት የሚገባቸው ድክመት እንደነበረሰባቸው ሁሌም በአፅንኦት ይናገሩ ነበር።


አምባሳደር ከተማ ከዲፕሎማሲያዊ ተግባራት በተጨማሪ በንግድ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም መስሪያ ቤት በኃላፊነት አገልግለዋል።
ከ1961 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ረሰገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንድታገኝ የሚጠበቅባቸውን ተግባር ፈፅመዋል።


አምባሳደር ከተማ ይፍረቱ የአፄ ኃይለሥላሴ ስርዓት ሲወድቅ የደርግ እስር ቤት የገቡ ሲሆን ከእስር በኋላም ከመጋቢት 1977 እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ ጣሊያን ሮም በሚገኘው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም መስሪያ ቤት በዋና አማካሪነት እና በናይሮቢ የምስራቅ አፍሪካ የመስሪያ ቤቱ ዋና ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል።


አምባሳደር ከተማ ይፍሩ ባበረከቷቸው ግዙፍ ውለታዎች ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ተቀብለዋል። ከነዚህም ውስጥ በኢትዮጵያ የክብር ኮከብ ሜዳሊያ እና ልዩ ልዩ ኒሻኖ፣ የስደተኛ ባለ አራት ዘምባባ ሜዳሊያ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የሶቭየት ሕብረት፣ የጣሊ፣ የየጎዝላቪያ፣ የሴኔጋል፣ የኬኒያ፣ የናይጄሪያ፣ የጋና፣ የዛየር፣ የግብፅ፣ የብራዚል፣ የሚክሲኮ፣ የካናዳ፣ የጃፓን እና የኢንዶኔዥያ ሀገራትን ሽልማት ተቀብለዋል።


ከተማ ይፍሩ ትሁት፣ ተግባቢና ኢትዮጵያ ሀገራቸውን ከምንም በላይ አጥብቀው የሚወዱ ሰው እንደነበሩ ጓደኞቸው፣ ቤተሰቦቻቸው፣ የሚያውቋቸው ሰዎች ሁሉ የሚናገሩት ሲሆን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ተግባራቸው እንደሚመሰክር ብዙዎች ያስረዳሉ።


የአፍሪካ መሪዎች አዲስ አበባ ለስብሰባ በመጡ ቁጥር ከተማ ይፍሩ ሊታወሱ ይገባል።


ጥቁሮች ከባርነት እና ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ ከዚያም ዛሬ የአፍሪካ ሕብረት ተብሎ የሚታወቀውን የቀድሞውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመሠረቱ፣ የአፍሪካን የጨለማ ዘመን የቀየሩ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ከተማ ይፍሩ ሁሌም አይረሱም።

 

    በጥበቡ በለጠ

 

 በ17ኛው እና በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ከነበሩ ስልጡን ከተሞች መካከል አንዷ እንደነበረች ስለሚነገርላት፤ አፄ በ1624 ዓ.ም. የመሠረተቋትን ጎንደር ከተማን ነው፡፡ ጎንደር ከሰሞኑ ሙሽራ ነች፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጥምቀት እየመጣ ነውና፤ ታይታ የማትጠገበዋ ጎንደር ከተማ ጥምቀት ሲመጣ ደግሞ ይበልጥ እዩኝ እዩኝ ትላለች፡፡ ዛሬ በጥቂቱ እናያታለን፡፡

ስለ ጎንደር ከተማ በስፋት ከፃፉ ሰዎች መካከል ታላቁ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና እናታቸው ሲሊቪያ ፓንክረስት ናቸው፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያን ታሪክ በስፋት የፃፉት ልጅና እናት ጎንደርን የብዙ ስልጣኔዎች ማሳያ አድርገው ፅፈዋል፡፡

ለምሳሌ በ1624 ዓ.ም አራት ፎቅ ያለው ግርማው እጅግ የሚያምር ቤተ መንግስት አፄ ፋሲል የከተማዋ አናት ላይ አገማሸሩ፡፡ የሚገርመው ሕንፃው ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች በርካታ ነገሮችን ንጉሱ አከናውነዋል፡፡ ዘመናዊ ጦር አደራጅተዋል፡፡ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ምሁራንን ከያሉበት አሰባስበዋል፡፡ የቤተ-መንግስት ሊቃውንትን በብዛት አፍርተዋል፡፡ በጦርነት የፈረሰችውን አክሱም ፅዮን ማርያምን ውብ በሆነ በጎንደር የአገነባብ ስልት አሣንፀዋል፡፡

ጎንደር ከአፄ ፋሲል በኋላ በመጡ ልዩ ልዩ ነገስታት እስከ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ ድረስ ተዓምር የሚባል ሥልጣኔ አሳይታለች፡፡

በስነ ስዕሉ ቢሄድ በደብረ ብርሃን ስላሴ ቤተ-ክርስቲያን የጣሪያና የግድግዳ ስዕሎች ላይ የቀረቡት ስዕሎች እስከ ዛሬ ድረስ የአለማችን የስነ ጥበባት ሊቆች ሚስጢራቸውን እያጠኑት ይገኛሉ፡፡ ስዕሎቹ ፈፅሞ አይወይቡም፣አይደበዝዙም፡፡ ጭራሽ ያንፀባርቃሉ፡፡ እነዚህን የ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስዕሎች ተመራማሪዎች Gonderian Art ወይም የጎንደሮች ጥበብ እያሉ ይጠሯቸዋል፡፡ ስለ ስዕሎቹ ሚስጥራት ወደ ፊት አጫውታችኋለሁ፡፡ ለዛሬ ግን ጎንደር ሙሽራ መስላ ስለምትታይበት የጥምቀት በዓል በጥቂቱ ላውጋችሁ፡-

  

• ግን ጥምቀትን ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ የአደባባይ በዓል አድርጎ የጀመረው ንጉስ ላሊበላ ነው፡፡ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ተነስተው ጉዞ አድርገው፣ውጭ አድረው እንደገና ወደ መንበረ ክብራቸው እንዲመለሱ ያደረገው ድንቅዬው ንጉስ ላሊበላ ነው፡፡ ስለዚህ የጥምቀት በዓል የተጀመረው እዚሁ ላስታ ላሊበላ ሮሃ ከተባለች ቦታ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ በልካም በዓል፡፡

ጐንደር ላይ የጥምቀት በዓል እጅግ በደመቀ መልኩ ይከበራል። በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ ጥምቀት ሲባል ጐንደር ጐልታ ትነሳለች። በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋህዶ ሃይማኖት ውስጥ ጐንደር እንዴት የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ዋነኛዋ ማዕከል ሆነች? በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰትን እያስተናገደች ያለችው ጐንደር፤ የታቦታት ምድር ነች እየተባለ ይነገራል። እንዴት?

በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ 44 ታቦታት አሉ ተብሎ ይታሰባል። እነዚህ ታቦታት ደግሞ በሙሉ የሚገኙት በጐንደር ከተማና ዙሪያዋ ነው ተብሎ ይታመናል። በዚህም የተነሳ የጐንደር ከተማ ዋነኛዋ የኦርቶዶክስ አማኒያን መዳረሻ ወይም ማዕከል ናት በሚል ትታወቃለች። ጥያቄው እነዚህ ሁሉ ማለትም 44ቱ ታቦታት እንዴት ጐንደር ውስጥ ተሰባሰቡ የሚለው ነው። በዘርፉ ምርምር ያደረገው ብርሃኑ አድማስ እና ሌሎች በርካታ ታሪክ ተመራማሪዎች በጉዳዩ ላይ ሃሳብ ሰጥተዋል።

ጐንደርን የኦርቶዶስ ሃይማኖት ማዕከል ካደረጓት ምክንያቶች አንዱ ከጽላተ ሙሴ ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው። ቀዳማዊ ምኒልክና አጃቢዎቹ ጽላተ-ሙሴን ንጉስ ሰሎሞን ሳያውቅና ሳይሰማ ከእየሩሳሌም አሸሽተው ወደ አክሱም አምጥተው ነበር። ከዚያም ንጉስ ሰሎሞን ሰራዊት ይዞ መጥቶ ይወጋናል፤ ጽላቱንም ይወስድብናል የሚል ስጋት በኢትዮጵያዊያን ዘንድ አድሮ ነበር። ስለዚህ ጽላቱን አሸሽቶ ሰው በቀላሉ ወደማይደርስበት አካባቢ ለማስቀመጥ ተወሰነ። በዚህም መሠረት በጣና ሃይቅ ላይ ጣና ቂርቆስ ላይ ተቀመጠ። እንግዲህ ጐንደር ከኦርቶዶክስ እምነት ጋር መቆራኘት ጀመረች። ጽላቱን ተከትለው ሊቃውንት በስፍራው መሰባሰብ ጀመሩ። አቡነ ሰላማ እና ቅዱስ ያሬድም እዚያ መጥተው እንደቆዩ አጥኚዎች ይገልፃሉ። ይሄ እንግዲህ አንደኛው ምክንያት ነው።

ጐንደርን የክርስትና ማዕከል ካደረጓት ሁኔታዎች መካከል በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የዮዲት ጉዲት የጥፋት ዘመን ነው ብለው ማብራሪያ ይሰጣሉ እነ ብርሃኑ። ዮዲት ጉዲት በአክሱም ስልጣኔ ላይ ጠንካራ ክንዷን አሳርፋ በርካታ ጉዳት ስታደርስ አያሌ ቅርሶችና ታቦታት ወደ ጣና መሸሽ ጀመሩ። ቀሳውስትና ሊቃውንትም አብረው ከታቦታቱ ጋር በመጓዝ በጐንደር ዙሪያ መከማቸት ጀመሩ። ይህንን ጉዳይ አክሊለብርሃን ወልደቂርቆስም ፅፈውታል።

በሶስተኛ ደረጃ ጐንደርን የኦርቶዶክሶች ዋነኛ ማዕከል ካደረጓት ምክንያቶች የአንበሳ ድርሻውን የሚወስደው የግራኝ መሐመድ መነሳት ነው። ግራኝ መሐመድ ከምስራቅ ኢትዮጵያ ተነስቶ ክርስቲያኖችን እና የክርስትና ተቋማት ላይ ጉዳት እያደረሰ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ መጓዝ ጀመረ። በየስፍራው ያሉ ቀሳውስትና ሊቃውንትም የግራኝን ጦርነት በመሸሽ ታቦታትን፤ መፃሕፍትን እና ልዩ ልዩ የቤተ-ክርስትያን መገልገያዎችን በመያዝ በጣና እና በዙሪያው መከማቸት ጀመሩ። እነዚህ የታሪክ አጋጣሚዎች ጐንደርን የኦርቶዶክሶች ዋነኛ መናኸሪያ እያደረጓት መጡ።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚጠቀሰው የግራኝ መሐመድ አሟሟት ነው። ግራኝ መላው ኢትዮጵያን ከያዘ በኋላ መንግስት ሆኖ ኢትዮጵያን ሊመራ የቀረው አንድ ዘመቻ ብቻ ነበር። ይህም ጐንደርን ነው። 15 ዓመታት ሙሉ ድል በድል ሆኖ የተጓዘው ግራኝ ጐንደር አካባቢ ዘንታራ በር በምትባል ቦታ ላይ ተገደለ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ ተብሎ የሚጠራው አፄ ገላውዲዮስና ተከታዮቹ የ15 ዓመታቱን አስከፊ ጦርነት ጐንደር ላይ አቆሙት፤ ፈፀሙት። እናም ጐንደር ከሃይማኖት ማዕከልነቷም አልፋ የድል ማብሰሪያ ምድር ሆነች ይላሉ ፀሐፊዎች። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መዲና እየሆነች መጣች።

ጐንደር በልዩ ልዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የታቦታት፤ የቀሳውስት፤ የሊቃውንት፤ የመፃህፍት እና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት መገለጫ የሆኑ በርካታ ጉዳዮች የተከማቹባት ስፍራ ሆነች። አፄ ፋሲልም በ1624 ዓ.ም ወደ ስልጣን ሲመጡ ከተማዋን የኢትዮጵያ መናገሻ አድርገው ቆረቆሯት። ዛሬም ድረስ የአለምን ቱሪስቶች ከሚያማልለው ቤተ-መንግስታቸው በተጨማሪ ሰባት አብያተ-ክርስትያናት” በዘመነ ስልጣናቸው ማሰራታቸውን የጐንደርን ታሪክ ጠንቅቆ የሚያብራራው አሁን የኔ አፄ ፋሲል ቤተ-መንግስት ኃላፊ የሆነው ጌትነት ይግዛው ንጉሴ ነው። እርሳቸው መጤ የሚሉትን ሃይማኖት ሁሉ ተፅእኖ እያሳደሩበት የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን እጅግ በጠነከረ መልኩ ጐንደር ላይ አስፋፉ። ከዚህ ሁሉ በኋላ ጐንደር ማበብ (Flourish) ማድረግ ጀመረች ይላሉ ፀሐፊዎቹ።

የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ የተሰራው፤ ክርስትና በኢትዮጵያ እና የጐንደር ጥምቀት የሚሰራው ዶክመንተሪ ፊልም እነዚህን ታሪኮችና ሌሎችንም አጠቃሎ መያዙን በዚህ አጋጣሚ መግለፁ ጠቀሜታው የጐላ ነው።

የጐንደር ጥምቀት የሚከበረው አፄ ፋሲል ባሰሩት ዋና የመዋኛ ስፍራቸው ላይ ነው። በፋሲል የመዋኛ ቦታ ላይ ከመቼ ጀምሮ ነው ታቦታት ከያሉበት አብያተ ክርስትያናት ወጥተው፤ እዚያ አርፈው፤ ከዚያም ጥምቀት በዓል ማክበር የተለመደው?

ዛሬ የአለም ቱሪስቶችን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ከያሉበት ተሰባስበው በአፄ ፋሲል የመዋኛ ገንዳ ላይ ጥምቀትን የሚያከብሩት ጅማሮው የተከሰተው በአፄ ሰሎሞን ዘመነ መንግስት (ከ1770-1773) ለሶስት ዓመታት በስልጣን ላይ በቆየው መሪ ነው። አፄ ሰሎሞን የአፄ ፋሲል አምስተኛ ትውልድ ሲሆን፤ የአዲያም ሰገድ ኢያሱ የልጅ ልጅ ነበር። አፄ ሰሎሞን ጥምቀት እዚያ የመዋኛ ስፍራ ላይ እንዲከበር ያደረገው በነገሰ በመጀመሪያው ዓመት ማለትም በ1770 ዓ.ም እንደሆነ ያሬድ ግርማ፤ የጐንደር ታሪክ በተሰኘው መፅሐፋቸው ውስጥ ይገልፃሉ።

የጐንደርን ጥምቀት ለማየት እና ለማክበር የመጡት ምዕመናንና ምዕመናት ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ስለሆነ በአሁኑ ወቅት ጐንደር ከተማ ውስጥ ያሉት ሆቴሎች ሁሉ በእንግዶች መያዛቸውን የከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገልፆልኛል። የመኝታ ክፍሎችን ያጡ እንግዶች አቅራቢያ ባሉት አዘዞ እና ባህርዳር ከተሞች አርፈዋል።

የጥምቀት በዓል እየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀበት ከዮርዳኖስ ወንዝ /ፈለገ ዮርዳኖስ/ ጀምሮ በኢትዮጵያው ጐንደር ፋሲለደስ ድረስ ለዘመናት እየደመቀ መጥቷል። በአሜሪካ የኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ታሪክ መምህር የሆኑት ፕ/ር አየለ በከሬ እዚህ አዲስ አበባ መጥተው የሰጡኝ መግለጫ የጐንደር ታሪክ፤ ጥምቀት፤ 44 ታቦታት ታሪክና የኦርቶዶክስ አማኒያን ማዕከል መሆኗን በአሁኑ ወቅት አለም በሰፊው አውቆታል ብለውኛል። እንደ ፕሮፌሰር አየለ ገለፃ፤ Wonders of the African World የተሰኘው የፕሮፌሰር ሄነሪ ሉዊስ ጌትስ ዶክመንተሪ ፊልም አፍሪካን ከጐንደር ጀምሮ የቀድሞ ስልጣኔዋን ስለሚያሳይ ዝናዋ እየናኘ መምጣቱን አውግተውኛል። ስለዚህ ዛሬ ዛሬ የጥምቀት በዓል ሲጠራ ኢትዮጵያ ደምቃ የምትታይበት ቀን እየሆነ መጥቷል። መልካም በዓል።  

 

በጥበቡ በለጠ

 

በምድር ላይ በሰው አዕምሮ ከተሠሩ ድንቅ ሥራዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱት የቅዱስ ላሊበላ የአለት ፍልፍል አብያተ-ክርስትያናት ናቸው። እነዚህ ሕንፃዎች የተሠሩት ከ800 ዓመታት በፊት ነው። አደጋ ውስጥ በመሆናቸው የዛሬ 10 ዓመት ግድም የጣሪያ መጠለያ ተሰርቶላቸው ነበር። የተሠራው መጠለያ የአገልግሎት ዘመኑ አምስት ዓመት ነበር። እናም አምስት ዓመቱን ከጨረሰ አምስት ዓመት ሆኖታል። እድሜውን ጨርሷል። ይህ መጠለያ ራሱ ኪነ-ህንፃዎቹ ላይ እንዳይወድቅ ስጋት አለ። ይህንን ስጋት በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት መስጠት አልተቻለም። ስለዚህ እነዚህ እድሜያቸው ከ800 ዓመታት በላይ የሆናቸው ብርቅዬ ኪነ-ህንፃዎች አስፈሪ አደጋ ውስጥ ናቸው። በተለይ ደግሞ የገና በዓል ሰሞን!

 

አገር ምድሩ፣ በተለይ ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወህዶ ሃይማኖት ተከታዮች የእየሱስ ክርስቶስን እና የቅዱስ ላሊበላን ልደት ለማክበር ላስታ ላሊበላ ላይ ይከትማሉ። እናም በሕዝብ ጭንቅንቅ ምክንያት እነዚህ ኪነ-ህንፃዎች ለአደጋ የመጋለጥ እድላቸው በእጅጉ ሠፊ ነው።

 

በዚህች ምድር ላይ ከተፈጠሩ የኪነ-ሕንፃ አርክቴክቶች መካከል ወደር የለውም እየተባለ ስለሚነገርለት ቅዱስ ላሊበላ እና ስለሰራቸው ትንግርታዊ ጥበባት ጥቂት እንጨዋወታለን።

 

ይህ ሳምንት በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ምዕመናን እና ሀገር ጐብኚዎች ወደ ቅዱስ ላሊበላ መናገሻ ከተማ ወደ ሮሃ ይጓዛሉ። ምክንያታቸው ደግሞ የገና በዓልን በዚሁ በደብረ ሮሃ ለማክበር ነው። ሰዎች የገና በዓልን ለምን በላሊበላ ርዕሠ አድባራት ያከብራሉ ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል። ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል።

 

አንደኛው ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ጉዞ ነው። ሰዎች በዓመት አንድ ጊዜ ወደ ቅዱስ ላሊበላ ገዳማት ሄደው ከተሳለሙ፣ ከፀለዩ ረድኤት፣ በረከት ጤና ብሎም መንፈሳዊ ልዕልና ያገኛሉ የሚባል ፅኑ እምነት ስላለ ምዕመናን በተለይም የእየሱስ ክርስቶስና የቅዱስ ላሊበላ የልደት ቀን በተመሳሳይ ዕለት ስለሚከበር በዓሉ በእጅጉ ስለሚደምቅም ጭምር እጅግ ብዙ የሚባል የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ተከታዮች ወደ ስፍራው ይጓዛሉ።

 

ሁለተኛው ምክንያት ለጉብኝት ነው። በተለይ ደግሞ ከውጭ ሀገራት የሚመጡ ሰዎች። ኢትዮጵያን የሚጐበኙ ቱሪስቶች በከፍተኛ ደረጃ ቁጥራቸው የሚያሻቅበው በዚህ ወቅት ነው። ጉዞ ወደ ቅዱስ ላሊበላ ትንግርታዊ አብያተ-ክርስቲያናትን ለመጐብኘት፣ ጉዞ ኢትዮጵያዊያን የገናን በዓል ደብረ ሮሃ ላሊበላ ከተማ ውስጥ የሚያከብሩበትን ሥርዓት ለማየት እና መንፈስን ለማርካት ሺዎች ባህር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ይገሰግሳሉ። እናም ሰሜን ወሎ ውስጥ፣ ላስታ ላሊበላ፣ ሮሃ ከተባለችው ስፍራ ላይ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በጋራ ይታደማል።

 

በነገራችን ላይ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ማለትም UNESCO በዚህ በገና በዓል ወቅት የዓለም ቱሪስቶችን የሚመክረው ወደ ደብረ ሮሃ ላሊበላ ከተማ ሄደው እንዲታደሙ ነው።

 

ይኸው የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ማለትም UNESCO የላሊበላን አብያተ-ክርስትያናት ከምድሪቱ ድንቅ ሥራዎች ረድፍ ውስጥ ለምን አስቀመጣቸው? በውስጣቸውስ ምን ቢኖር ነው ማለታችን አይቀርም።

 

ለምሳሌ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ፣ ሀገሪቷን ዞሮ አይቶ ግዙፍ መፅሐፍ ያሳተመው ፖርቹጋላዊው መልዕክተኛ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ፣ የላሊበላን ኪነ-ህንፃዎች አሠራር ከተመለከተ በኋላ በዓይኑ ያየውን ማመን አልቻለም። ግራ ተጋባ። የሰው አዕምሮ እንዴት ይህንን ለመስራት አሰበ? ከዚያስ ካለ ምንም የኮንስትራክሽን ስህተት እንዴትስ አድርጐ ሠራው እያለ አሠበ፣ ተመራመረ። ከዚያም Portuguese Mission in Abyssinia በተሰኘው መፅሐፉ ውስጥ የሚከተለውን ፃፈ።

 

የቅዱስ ላሊበላን አብያተ ክርስቲያናት አሠራር ላላያቸው ሰው ይህን ይመስላሉ ብዬ ብፅፍ ማንም አያምነኝም። ነገር ግን ከዚህ ቀጥሎ የምፅፈው ነገር ሁሉ እውነት መሆኑን በሃያሉ በእግዚአብሔር ስም እምላለሁ” እያለ በመሀላ አስረግጦ ነው የፃፈው - ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ

 

ከዚህ በኋላ የመጡ የኪነ-ህንፃ ጥበብና ሳይንስ ተመራማሪዎች በሙሉ ብዙ ብዙ ፅፈዋል። የተለያዩ አመለካከቶችና ፍልስፍናዎች ማንፀባረቂያ ማዕከል አድርገው የቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ህንፃዎች ላይ ሲራቀቁባቸው ኖረዋል።

እነዚህን ኪነ-ህንፃዎች በእንግሊዝኛ Rock Hewn Churches ይሏቸዋል። ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያናት ለማለት ፈልገው ነው።

 

ኢትዮጵያን ከኢጣሊያ ፋሽስቶች መረራ ነፃ ለማውጣት በተደረገው መስዋዕትነት ውስጥ ከኢትዮጵያ አርበኞች ጐን በመቆም ታሪክና ትውልድ ፈፅሞ የማይረሱትን ውለታ ለኢትዮጵያ ያበረከተችው እንግሊዛዊቷ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሲሊቪያ ፓንክረስት Rock Hewn Churches of Lalibela Great Wonders of the World ለዓለም ህዝብ ፅፋ አስነበበች። በአማርኛ የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስትያናት፣ የምድሪቱ ትንግርቶች ተብሎ ሊተረጐም ይችላል። እናም በዚህ ፅሁፏ ሲልቪያ ፓንክሪስት ስለ ላሊበላ ኪነ-ህንፃዎች አሠራር ምስጢር፣ ታሪክ፣ ጥበብ ብሎም ኢትዮጵያ ራሷ ምን አይነት ጥንታዊ ስልጣኔ እና ማንነት ያላት ሀገር መሆኗን ሲልቪያ ፓንክረስት Ethiopia a Cultural History በተሰኘው ከ750 በላይ ገፅ ባለው መፅሐፏ የኢትዮጵያን ዘላለማዊ ሐውልት ሠርታለች። እናም የቅዱስ ላሊበላን ታሪክ ለመላው ዓለም ሥርዓት ባለው ሁኔታ ያስተዋወቀች ጥበበኛ፣ አርበኛ፣ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ ብሎም የኢትዮጵያ የስልጣኔ አራማጅ /Modernist/ የምትሠኘው ሲልቪያ ፓንክረስት ከወደ እንግሊዝ ትጠቀሳለች።

 

ከዚያ በኋላም እንደ ፕሮፌሰር ዴቪድ ፍሊፕሰን የመሳሰሉ ተመራማሪዎች ላሊበላ ላይ እና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ጥንታዊ ኪነ-ህንፃዎች ላይ ሰፊ ምርምር በማድረግ መፃህፍትን ማሳተም ጀመሩ።

 

በመቀጠልም የኢትዮጵያ ታላላቅ የታሪክ ፀሐፊያን እነ ዶ/ር ስርግው ኃብለስላሴ፣ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፣ ብላቴን ጌታ ሂሩይ ወ/ስላሴ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ድንቄ፣ ተክለፃዲቅ መኩሪያ፣ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የመሳሰሉ ግዙፍ ሰብዕናዎች ላሊበላ ላይ ፅፈዋል ተፈላስፈዋል።

 

እንደ ዶ/ር አያሌው ሲሳይ አይነት ፀሐፊያንም የዛጉዌን ስርወ መንግስት እና በአጠቃላይ በቅዱስ ላሊበላ የኪነ-ህንፃ ምስጢራት ላይ ምርምር አድርገው ፅፈዋል። ግርሃም ሀንኩክ The sign & seal በተሰኘው መፅሐፉ ስለ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት አሠራር የተሳሳተ መረጃ ሰጥቷል ብለውም ሞግተውታል።

 

በዚሁ በእኛ ዘመን ደግሞ ሠዓሊውና ቀራፂው በቀለ መኮንን ስለ ላሊበላ ሲናገር እንዲህ ይላል፣ የሰው ልጅ ፎቅ ቤትን የሚሠራው ከመሬት ተነስቶ ወደ ላይ ሽቅብ ነው። ነገር ግን ቅዱስ ላሊበላ ይህን በሂደት ቀየረው። የሰው ልጅ ፎቅ ቤትን አለት እየፈለፈለ ከላይ ወደ ታች መስራት ይችላል ብሎ ያሰበ፤ ቀጥሎም የሰራ የፕላኔቷ ድንቅ አርክቴክት ነው በማለት በቀለ መኮንን ላሊበላን ይገልፀዋል።

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ህንፃ መምህር የሆነው አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ደግሞ ስለ ቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ህንፃዎች ሲናገር እንዲህ ብሏል፡- የቅዱስ ላሊበላ ህልም እየሩሳሌም የምትባለዋን ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የማምጣት ፕሮጀክት ነው። ዳግማዊት እየሩሳሌምን ድንቅ በሆነ ኪነ-ህንፃ ማምጣት። ይህ ትልቅ ፕሮጀክት ነው። ይህንን ትልቅ ፕሮጀክት በሰው አዕምሮ ሊታሰብ በሚያዳግት ጥበብ ላሊበላ ላይ ተሰርቷል - ይላል ኢትዮጵያዊው የኪነ-ህንፃ መምህር ፋሲል ጊዮርጊስ።

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ቁፋሮ (አርኪዮሎጂ) መምህር የሆነው እና ላሊበላ ላይ ለረጅም ዓመታት ሲመራመርና ሲፅፍ የኖረው ዶ/ር መንግሥቱ ጐበዜ ሲገልፅ፣ ቅዱስ ላሊበላ አለት ፈልፍሎ አስር አብያተ-ክርስቲያናትን የሰራበት ዲዛይን /ንድፍ/ የራሱ ነው። የትኛውም ጥበበኛ ይህን ንድፍ ኮርጆ እንኳን መስራት አይችልም። ምክንያቱም ከጥበብ ባሻገር ሌላ መንፈሳዊ ኃይልም የተጨመረባቸው የጥበብ ውጤቶች ናቸው ይላቸዋል።

 

አያሌ ልሂቃን የሚፈላሰፉባቸው እነዚህ ኪነ-ህንፃዎች ዛሬም ድረስ የአሠራር ሚስጢራቸው ለሰው ልጅ አዕምሮ አልተገለፀም። የላሊበላ ኪነ-ህንፃዎች አሠራር ሚስጢራዊ ናቸው። እነዚህን ምስጢራት ለማየት ለመሳለም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ወደ ስፍራው እየተጓዙ ነው። የእየሱስ ክርስቶስን እና የቅዱስ ላሊበላን ልደት በጋራ ለማክበር። ታዲያ ሁላችንም ቆም ብለን አንድ ነገር ማሰብ አለብን። ከ800 ዓመታት በላይ ፀሐይን፣ ዝናብን፣ አደጋን፣ ጦርነትን ተቋቁመው እስከ ዛሬ ድረስ የኖሩልን እነዚህ ምስጢራዊ ቅርሶች እንዳይጐዱብን መጠበቅ ግድ ይለናል። ለቀጣዩ ትውልድም በሥርዓት እንዲተላለፉ ይህ ትውልድ ኃላፊነት አለበት። ምክንያቱም ላሊበላ የመላው ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ቅርስ ስለሆነ እኛ ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት አለብን።

 

የሰው ልጅ ሁሉ ቅርስ የሆኑትን የቅዱስ ላሊበላ ጥበቦች ባለቤት እኛ ኢትዮጵያዊያን ስለሆንን ኃላፊነታችን ድርብ ድርብርብ ነው። መልካም የገና ሳምንት ይሁንላችሁ።

በጥበቡ በለጠ

ኢትዮጵያ የበርካታ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ታሪኮች ባለቤት እንደሆነች ተደጋግሞ የተነገረ ጉዳይ ነው። ታዲያ ከነዚህ ታላላቅ ታሪኮች መካከል ግዙፍ ቦታ የሚሰጠው በቋንቋና በሥነ-ጽሁፍ የመበልጸግ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ የግዕዝ ቋንቋ በምድሪቱ ላይ ቀደምት ናቸው ከሚባሉት የሰው ልጅ የልሳን መሣሪያዎችና መግባቢያዎች መካከል ዋነኛው ነው። ቋንቋው በውስጡ እጅግ የሚያስገርሙ፣ የሚደንቁ የሰው ልጆችን ጥንታዊ ታሪክ የያዘ ነው። ይህ የኢትዮጵያ የበኩር ልጅ የሆነው የግዕዝ ቋንቋ ዛሬ ዛሬ ክፉኛ ተዳክሞ አንዴ የሞተ ቋንቋ ነው ሲባል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በመሞት ላይ ያለ ቋንቋ ነው እየተባለ የሚጠቀስ ነው። ባጠቃላይ ግን የግዕዝ ቋንቋ ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ያለ የኢትዮጵያ ልጅ ነው። ዛሬ በጥቂቱ የምናወጋው ስለዚሁ አካላችን፣ አንደበታችን ስለሆነው የግዕዝ ቋንቋችን ነው።

የግዕዝ ቋንቋ በዓለም ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር ከተደረገባቸው የሰው ልጅ ሀብቶች መካከል አንዱ ነው። ከጥንት ጀምሮ የሚመራመሩ ሰዎች የግዕዝ ሀገሩ የት ነው ብለው ሲያጠኑ ቆይተዋል። ለምሳሌ የሩሲያ የቋንቋ ተመራማሪዎች የሆኑት Igor Diaknoft እና A.B Dogopolky የተባሉት ተመራማሪዎች ግዕዝ በአረብ ምድር የመጀመሪያዎቹ የአፍሪካውያን ወይም የኩሻውያን ቋንቋ ነው ይላሉ።

በአሜሪካ በኮርኔስ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ኢትዮጵያዊው ምሁር ፕሮፌሰር አየለ በክሪ፣ ከዚህ ቀደም በዓለም ላይ ሰፊ ስርጭት የነበረውን በኢትዮጵያ ፊደሎች፣ በግዕዝ ፊደሎች ላይ መሠረት አድርገው Ethiopic የተሰኘው መፅሐፍ አዘጋጅተዋል። እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም የቋንቋ ምሁራን አፍሮ ኤዥያቲክ ተብለው የሚጠሩት የቋንቋ አይነቶች አብዛኛዎቹ የሚገኙት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ግዕዝም ከነዚያ ውስጥ አንዱ መሆኑን ይናገራሉ።

ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ፣ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች ፍቅር ወድቆ፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች ፍቅር ወድቆ፣ የኢትዮጵያን ቋንቋዎች በማጥናትና በመመራመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረገው Lionel Bender ግዕዝን ካጠኑ ሰዎች መካከል አንዱ እርሱ ነው። ቤንደር በ1966 ዓ.ም በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ባሳተመው ቋንቋ በኢትዮጵያ /Language in Ethiopia/ በሚሰኘው መፅሐፉ ሲገልፅ የግዕዝ ቋንቋ ተወልዶ ያደገው እዚሁ ኢትዮጵያ መሆኑን ይገልፃል። ታላቁ ኢትዮጵያዊ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌም በ1948 ዓ.ም በታተመው መፅሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገብ ቃላት በተሰኘው መፅሐፋቸው ሲገልፁ ግዕዝ ከየትም ቦታ ያልመጣ፣ እዚሁ የኢትዮጵያ ምድር ላይ ተወልዶ የተስፋፋ ሴማዊ ቋንቋ እንደሆነ ይገልፃሉ።

የበርካታ የቋንቋ ምሁራን የጥናትና ምርምር ጽሁፎችና መፃህፍት እንደሚገልፁት ግዕዝ ኢትዮጵያ ቋንቋ ነው። በኢትዮጵያ ምድር ላይ ተወልዶ የአለምን ጥንታዊ ስልጣኔና ግስጋሴ ሲዘግብ የኖረ ቋንቋ እንደሆነ ተስማምተውበታል። ስለዚህ ስለቋንቋው በአጭሩ እንጨዋወት።

የግዕዝ ቋንቋ እጅግ ጥንታዊ ከመሆኑ የተነሳ የመላዕክት ልሳን ነበር ብለው የፃፉና የሚናገሩ በርካቶች ናቸው። አንዳንድ ፀሐፊያን ስለ ቋንቋዎች ጥንታዊነት ሲፅፉ እየሱስ ክርስቶስ በምን ቋንቋ ይናገር እንደነበር ሁሉ ገልጸዋል። እየሱስ ክርስቶስ ከዛሬ ሁለት ሺ ዓመታት በፊት የሚናገርበት ቋንቋ አረማይክ በሚባለው ቋንቋ እንደነበር የፃፉ አሉ። አረማይክ ቋንቋ በአሁኑ ወቅት ሞተዋል ከሚባሉት ውስጥ ነው። ምክንያቱም ተናጋሪ ቤተሰብ ስለሌለው ነው። ግን በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የጥናትና የምርምር ቋንቋ ሆኖ እያገለገለ ነው። የግዕዝ ቋንቋም ልክ እንደ አረማይክ ቋንቋ ሁሉ የምድሪቱ ቀዳማዊ ልሳን ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ በግዕዝ ቋንቋ ያልተፃፈ ታሪክና ምስጢር የለም። የኢትዮጵያ እና የዓለም ጥንታዊ ታሪኮች በግዕዝ ቋንቋ ተፅፈው ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ከ500ሺ በላይ ጥንታዊ ብራናዎች መኖራቸው ይነገራል። እነዚህ ብራዎች ውስጥ የተፃፈው በግዕዝ ቋንቋ ነው። የግዕዝ ቋንቋን የመክፈቻ ቁልፍ መያዝ የአለምና የኢትዮጵያን ታሪክ ማወቂያ ዋነኛው ቁልፍ ነው።

የግዕዝን ቋንቋ ስርአተ- ሰዋሰው /grammar/ ለማጥናትና የቋንቋውን አፈጣጠር ለመመርመር ጥናት የተጀመረው ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነው። የመጀመሪያውን የግዕዝ ቋንቋ ሰዋሰው ያጠናው ጀርመናዊው ኢዮብ ሉዶልፍ ነው። ጊዜውም በ1673 ዓ.ም የዛሬ 409 ዓመት ነው።

የመጀመሪያው የግዕዝ ሰዋሰው በሮም አውሮፓ የታተመው በ1638 ዓ.ም ነው። ሌሎች በርካታ ተመራማሪዎችም ተጠቃሾች ናቸው። ነገር ግን ጀርመናዊውን አውግስቶስ ዲልማንን የሚያክል የግዕዝ ቋንቋ ባለውለተኛ የለም።

የግዕዝ ቋንቋ ውስጥ ሀይማኖት አለ፣ ፍልስፍና አለ፣ ሳይንስ አለ፣ የሒሳብ ስሌትና ቀመር አለ፣ ስነ-ከዋክብት አለ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ፣ ፊዚክስ ሁሉም የሰው ልጅ የምርምርና የስልጣኔ ፈርጆችን የያዘ ቋንቋ ነው። በአንድ ወቅት የBBC ቴሌቪዥን የሳይንስ ክፍል ጋዜጠኞች እንዳረጋገጡት ዛሬ አለምን ያጥለቀለቀው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የስራና የፈጠራ ምክንያት የሆነው የሂሳብ ስሌት መጀመሪያ ላይ ጥንት ይጠቀሙበት የነበረው ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ ያረጋገጠበትን ዶክመንተሪ ፊልም ለህዝብ አቅርቧል። በሂሳብ ስሌት ውስጥ 0 እና 1 ቁጥርን በመጠቀም በሂሳብ ሲራቀቁ የነበሩት ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ዛሬ በሰለጠነው አለም ላይ ኮምፒውተርን ለመፍጠር የ0 እና የ1 ቁጥር ስሌት ዋነኛው መፍጠሪያ ነው። የዚህን የቁጥር ስሌት ተጠቃሚዎች ጥንታዊዎቹ የግዕዝ ቋንቋ ተጠቃሚዎች ኢትዮጵያዊያን ነበሩ።

የዚህ ሁሉ ምጥቀትና እድገት ባለቤት የሆነው የግዕዝ ቋንቋ በዘመናት ውስጥ እየተዳከመ መጣ። ጥንት የኢትዮጵያ ቋንቋ የነበረው ግዕዝ በአማርኛ እና በትግርኛ ቋንቋዎች እየተዳከመ መጣ። በተለይ አማርኛ ቋንቋ እየገዘፈ ሲመጣ ግዕዝ ፊደላቱን ለአማርኛ አስረክቦ እየከሰመ መጣ።

በተለይ አፄ ቴዎድሮስ ወደ ስልጣን ሲመጡ ግዕዝ ሙሉ በሙሉ ተዳክሞ አማርኛ ቋንቋ ጠንክሮና በርትቶ ወጣ። የአፄ ቴዎድሮስ ደብዳቤዎችና ታሪኮች ሁሉ በአማርኛ ቋንቋ መፃፍ ጀመሩ። ከዚያ በኋላም የመጡት ነገስታት እና ምሁራን ዝንባሌያቸውን ለአማርኛ ቋንቋ ሰጡ። አማርኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገናን ቋንቋ ሆነ። ጥንታዊው ግዕዝ ደግሞ እየተዳከመ ሄደ።

በዚህ የተነሳ ዛሬ ግዕዝ ቋንቋ ስለደረሰበት ከባድ አደጋ ብዙ አስተያየቶች ይሰጣሉ። ግዕዝ ቋንቋ ሞቷል የሚሉ ምሁራን አሉ። አንድ ቋንቋ አፍ መፍቻ ቋንቋ ካልሆነ፣ በግዕዝ ቋንቋ የሚናገሩ፣ የሚጫወቱ፣ የሚፅፉ፣ የሚዘፍኑ፣ የሚዘምሩ ከሌሉ ቋንቋው ሞቷል ማለት ነው ሲሉ የቋንቋ ምሁራን ይገልጻሉ።

ሌሎች ደግሞ ግዕዝ የማን ቋንቋ ነው ብለው ይጠይቃሉ። ግዕዝ ባለቤት አለው ወይ? ግዕዝ የኔ ቋንቋ ነው የሚል ኢትዮጵያዊ ብሔረሰብ ወይም ማህበረሰብ አለ ወይ? ብለው የሚጠይቁ አሉ። አንድ ቋንቋ በህይወት እንዳለ ከማረጋገጫው አንዱ ቋንቋው የኔ ነው የሚል ማህበረሰብ መኖር አለበት ይባላል። ግዕዝ ደግሞ የኔ ነው የሚለው ህዝብ የለውም። ኢትዮጵያን ሲያዘምን ሲያሳድግ፣ ታሪኳን፣ ማንነቷን ሲጽፍ ቆይቶ ዛሬ ተናጋሪ የሌለው፣ አፉን በግዕዝ የሚፈታ ህጻን ልጅ የሌለው መካን ቋንቋ ሆኗል።

ግዕዝ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ቢሆንም እንዳይጠፋ፣ ትንሽም ቢሆን እየተነፈሰ እንዲኖር ያደረገችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሀይማኖት ናት። ቋንቋው ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ መገልገያ በመሆኑ ትንፋሹ ፈፅሞ  አልጠፋም።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም የግዕዝ ቋንቋን በማስተማር ረገድ ያበረከተው አስተዋፅኦ የሚያስመሰግነው ነው። በዚህም የቋንቋ ምሁሮቹ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ፕሮፌሰር አብርሀም ደሞዝ፣ ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ፣ እነ አቶ ተክሉ ሚናስ እና ሌሎችም የግዕዝ ቋንቋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነፍስ እንዲዘራ ያደረጉ ልሂቃን ናቸው።

የግዕዝ ቋንቋ እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ ጀርመኖች፣ ጣሊያኖች፣ እንግሊዞች እና በአሜሪካን ልዩ ልዩ ዩኒቨርስቲዎችም ለረጅም አመታት በትምህርት እየተሰጠ ይገኛል። የምድሪቱ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች የግዕዝ ቋንቋ ውስጥ ያለውን ምስጢራት በየጊዜው እየተረጎሙ ያሳትመዋቿል።

የግዕዝ ቋንቋ በሀገሩ ኢትዮጵያ ክፉኛ ታሞ ህክምና ይፈልጋል። ግዕዝ ካለበት ችግር እንዲላቀቅ እንደ መምህር ደሴ ቀለብ አይነት የቋንቋ ተቆርቋሪዎች ትንሳኤ ግዕዝ ብለው መጽሐፍ ከማዘጋጀታቸውም በላይ የግዕዝ ቋንቋ ተማሪዎችን እያፈሩ ይገኛሉ።

ሌሎችም በርካታ ታታሪ ኢትዮጵያዊያን ቋንቋው ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ምድር እንዳይጠፋ የሚቻላቸውን ሲያደርጉ ኖረዋል። ዛሬ ዛሬ ደግሞ ባህል ሚኒስቴርም ቋንቋውን ካለበት አደጋ ለመታደግ ጥረት እያደረገ ነው።

ያም ሆነ ይህ የግዕዝ ቋንቋ በሀገሩ ኢትዮጵያ ሞተ እንዳይባል፣ ትንሳኤ ግዕዝ ያስፈልገዋል። እስራኤሎች የሞተውን የአብራይስጥ ቋንቋ እንደገና አስነስተው ዛሬ ከአለማችን የጥናትና የምርምር ቋንቋዎች መካከል አንዱ አድርገውታል።

ኢትዮጵያም የማንነቷ መገለጫ የሆነውን የግዕዝ ቋንቋን ከህመሙና ከስቃዩ ገላግለው የጥንት ማንነቱን እና ክብሩን እንድታጎናጽፈው ከሁላችንም ብዙ ይጠበቃል።

        

 

 

በጥበቡ በለጠ

ለዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት ኢትዮጵያዊ ጥበበኛ፣ ኢትዮጵያን እጅግ የሚወዳት፣ በኢትዮጵያ የሥዕል እና የሥነ-ግጥም ዓለም ውስጥ ድምቅምቅ ብሎ ሁሌም ስሙ ስለሚጠራው ስለ ታላቁ ጥበበኛችን ስለ ገብረክርስቶስ ደስታ ነው። ገብረ ክርስቶስ ደስታ “ስሞት ሀገሬ ቅበሩኝ” እያለ በግጥም እየተቀኘ ሲማፀን የኖረ ባለቅኔ ቢሆንም፤ ሞቶ የተቀበረው ግን በባዕድ ሀገር ነው።

ገብሬ “ሀገሬ” ብሎ ሲቀኝ እንዲህ አለ፡-

ውበት ነው አገሬ

ገነት ነው አገሬ

ብሞት እሄዳለሁ ከመሬት ብገባ

እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ

ባሳብ እሄዳለሁ ቢሰበርም እግሬ

አለብኝ ቀጠሮ ከትውልድ አገሬ።

አለብኝ ቀጠሮ

ከትውልድ አገሬ ካሳደገኝ ጓሮ

“ብሞት እሔዳለሁ ከመሬት ብገባ” እያለ የዛሬ 50 ዓመት ግጥም የፃፈ ሰው ዛሬም አፅሙ በምድረ አሜሪካ ነው። ዛሬ ስለ ጥበበኛው ገብረክርስቶስ ደስታ ጥቂት ነጥቦችን እንጨዋወታለን።

ገብረክርስቶስ ደስታ ጥቅምት 5 ቀን 1924 ዓ.ም በሐረር ከተማ አደሬ ጢቆ ተወለደ። አባቱ አለቃ ደስታ ነግዎ ሲባሉ እናቱ ደግሞ ወ/ሮ አፀደማርያም ወንድማገኝ ይባላሉ።

ገብረክርስቶስ ደስታ በ1920ዎቹ ወደዚህች ዓለም ብቅ እንዳሉት የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጆች መካከል አንዱ ነው። የሥዕል ጥበብ ገና ሕፃን ሳለ ጀምሮ ውስጡ ተፀነሰ። ገና የአስር ዓመት ልጅ ሳለ ሐረር ውስጥ ተወዳጅ ሥዕሎችን መውለድ የቻለ የጥበብ ክስተት ነበር።

እንዲህ እያለ የሥዕል ጥበብ ውስጡ እየዳበረ መጣ። ከዚያም ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋክሊቲ ገባ። ለሁለት ዓመታት ተምሮ አቋረጠ። ቀጥሎም ወደ ጀርመን ሀገር ሔዶ በኮሌኝ የሥዕል አካዳሚ ተማረ። ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያም መጥቶ ማስተማር ጀመረ። በ1955 ዓ.ም የሥዕል አውደ-ርዕይ ሲከፍት በሥራዎቹ ተደንቀው መጥተው የከፈቱለት እና የመረቁለት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ነበሩ። ከዚያም በ1958 ዓ.ም በሥዕል ጥበብ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ሽልማት ድርጅት የሸለመው የኢትዮጵያ ብርቅዬ አርቲስት ነው እየተባለ ብዙ ተፅፎለታል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ ሰው ሕይወት እና ሥራዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይትና ክርክር ከተደረገባቸው ሰዎች መካከል እንደ ገብረክርስቶስ ደስታ ትልቁን ድርሻ የሚወስድ የለም። ገብረክርስቶስ ደስታ ሕይወቱና ሥራዎቹ እየተተነተኑ የቀረቡበት አጋጣሚው በራሱ ሊነገርለት ስለሚገባ እሱንም ላውጋችሁ።

ገብሬ በዘመነ ደርግ ከሥርዓቱ ጋር ችግር ስለተፈጠረበት ወደ ኬኒያ ተሰደደ። ከዚያም ወደ ጀርመን ሐገር ሄደ። ጀርመን ሀገር ውስጥ በርካታ የሥዕል ሥራዎቹን ተአምር ሊባል በሚችል መልኩ ሠራ። አያሌ የጀርመንና የአውሮፓ ሠዓሊያን ጥበበኞች በዝህ ሰው ሥራዎች በእጅጉ ይደነቁ ነበር። ገብረክርስቶስ ስለ ሥዕል ጥበብና በአጠቃላይ ስለ ኪነ-ጥበብ ሲናገርና ሲያቀርብ ለመስማት ለማየት ልሂቃን ከያሉበት ይሰባሰቡ ነበር። ከኢትዮጵያ ምድር የተከሰተ የጥበበኞች አውራ ሆኖ አውሮፓ ውስጥ ተከሠተ። ሰፊ መነጋገሪያም ሆነ።

ግን ደግሞ፤ ሐገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ዜጐች በፖለቱካ ልዩነቶቻቸው እየተገዳደሉ፣ የበርካታ እናቶችና አባቶች ለቅሶና ጩኸት እየተሰማው ሠላም እንዳጣ ይነገራል። ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጐቿ ፍጅት እና እስራት፣ ቶርቸር ጥበበኛው ገብሬ ጀርመን ውስጥ ቢኖርም ጉዳዩ ይበጠብጠው ጀመር። እና አሁንም መራቅ መሄድ ፈለገ። ደሞ ወደ ዓለም ጥግ። ከጀርመን ብርር ብሎ ሊሄድ ተነሳ። አንድ ነገር ደግሞ አሰረው። በርካታ የሚባሉ፣ ዓለም በቅርስነት እንደ ዓይኑ ብሌን የሚያያቸውን ሥዕሎች ሠርቷል። እነሱን ምን ያድርጋቸው? ልጆቹ ናቸው።

ኸረ ልጅ ማሰሪያው ኸረ ልጅ ገመዱ

ጐጆማ ምን አላት ጥለዋት ቢሔዱ

ይላል የሐገሬ ሰው። እናም ገብሬን እነዚህ የጥበብ ልጆቹ ያዙት። ከራሱ ጋር ሲሟገት ቆየ እና አንድ መላ ዘየደ።

ጀርመን ያደገ የበለፀገ ምድር ነው። ለጥበብና ለጥበበኛ ከፍተኛ ክብር ያለው ሥርዓት ነው። ስለዚህ ገብሬ ለጀርመን መንግስት ተናዘዘ። ኑዛዜው እንዲህ ይላል፡-

“ውድ የጀርመን መንግስትና ሕዝብ ሆይ፤ ሀገሬ ኢትዮጵያ ሰላም ሆና የተረጋጋች ወቅት እነዚህን ሥራዎቼን ወደ ሀገሬ ላኩልኝ እስከዛው ከናንተ ዘንድ ይኑርልኝ። አደራ” ይላል።

ይህ ኢትዮጵያዊ የጥበብ ባለቅኔ ይህን ከተናዘዘ በኋላ

ውበት ነው አገሬ

ገነት ነው አገሬ

ብሞት እሄዳለሁ ከመሬት ብገባ

እዚያ ነው አፈሩ የማማ ያባባ

እያሉ የኢትዮጵያን ፍቅሩን ራሮቱን የተነፈሰበትን ታላቁን ግጥም ፃፈ። ግን ደግሞ እንደገና ተሰደደ። ከጀርመን ወደ አሜሪካ ሄደ።

ታላቁ ደራሲ በዓሉ ግርማ፣ እውነተኛ ደራሲ ነብይ ነው ይል ነበር። እናም ገብረክርስቶስ ደስታ ምድር ላይ ብዙም እንደማይኖር የተረዳ ይመስላል። ምክንያቱም ለጀርመን መንግስትና ሕዝብ ተናዘዘ። ሀገሬ ብሎ ግጥም ፅፎ ብሞትም ሀገሬ እሄዳለሁ እያለ ተቀኘ። ወዲያውም ወደ አሜሪካ ሄደና ሎውተን ኦክላሆማ ውስጥ ለትንሽ ግዜ ሥዕል ሲያስተምር ቆይቶ መጋቢት 21 ቀን 1974 ዓ.ም የኢትዮጵያ የጥበብ ፈርጥ የሆነው ታላቁ ባለቅኔ በድንገተኛ ህመም ብቻውን ሆስፒታል ገብቶ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ማየት እንደናፈቀ ማረፉ ተነገረ። ሥርዓቱ ቀብሩም እዚያ ተፈፀመ። ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ የዚህን የጥበበኞች ሁሉ አውራ የሆነውን የዜጋዋን አፅም ወደ ትውልድ ቦታው አምጥታ በሥርዓት ሐውልት አላቆመችለትም።

ግን ደግሞ በ1995 ዓ.ም እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ያለው የጀርመን የባህል ተቋም /ጐተ-ኢኒስቲቲዩት/ የፕሮግራም ክፍል ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ተናኘ ታደሰ ከባልደረቦቻቸው እና ከገብረክርስቶስ ደስታ ጓደኞች፣ ተማሪዎች እና ወዳጆች ጋር በመሆን የዚህን ሰው ኑዛዜ ለማስፈፀም እንቅስቃሴ አስጀመሩ። “ሀገሬ ሰላም ከሆነች ሥዕሎቼን ወደ ሀገሬ ውሰዱልኝ” ያለውን ኑዛዜ ለማስፈፀም ሰፊ ዘመቻ ተጀመረ።

ከዘመቻው ውስጥ አንዱ ገብረክርስቶስ ደስታ ማን ነው? ምን አይነት ኢትዮጵያዊ ነው? ለሀገሩና ለዓለም ሕዝብ ያበረከተው አስተዋፅኦ ምንድን ነው? ሥራዎቹ እንዴት ይታያሉ? እንዴትስ ይተነተናሉ? የገብረ-ክርስቶስን ታላቅነት ጥበበኛነት ትውልድ ሁሉ እንዲማርበት፣ ዘላለማዊ እንዲሆን ምን ይደረግ ተብሎ እነ ወ/ሮ ተናኘ ታደሰ አቀዱ፣ እቅዳቸውንም ለማስፈፀም ሥራ ተጀመረ።

የመጀመሪያው ውይይት 1995 ዓ.ም አራት ኪሎ በሚገኘው የጀርመን የባህል ተቋም ውስጥ ተደረገ። የውይይቱን መነሻ ሀሳብ እንዲያቀርቡ የተጋበዙት የገብሬ የልጅነት ጓደኛ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ እና የገብሬ የሥዕል ተማሪ የነበረው ዮሐንስ ገዳሙ ናቸው። በውይይቱም አያሌ ታዳሚያን ቢገኙም ረብሻ ተነሳ። የረብሻው መነሻ ተስፋዬ ገሠሠ ገብረክርስቶስ ደስታ በአንድ ወቅት ስላጋጠመው የቆዳ ህመም /ለምፅ/ ደጋግመው ሲናገሩ፣ አቁም! ይሄን አትናገር! ስለ ሥራውና አበርክቶው አውራ የሚል እንደ ብራቅ የጮኸ ድምፅ መጣ። ለተወሰኑ ደቂቃዎች ውይይቱ ታወከ። ከዚያም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋው የሥነ-ጽሑፍ ምሁር ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ አረጋግተውት ውይይቱ እንደገና ተጀመረ። እንደገና ሲጀመር ተስፋዬ ገሠሠ ስለ ገብሬ አፍነው ያቆዩአቸውን እርሳቸው ምስጢር ናቸው ብለው የሚያምኑባቸውን ድብቅ ታሪኮች በይፋ ተናገሩ። ግን የህዝቡ ስሜት አሁንም የዚህን ጥበበኛ ታሪክ የበለጠ ማወቅ ነበር። ሌላ ቀጠሮ ተያዘ።

በሁለተኛው ቀጠሮ ላይ ስለ ገብረክርስቶስ ደስታ የግጥም ሥራዎች ትንታኔ ይዘው የመጡት ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ነበር። አዳራሹ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞላ። ዶ/ር ፈቃደ ገብረክርስቶስ ደስታ ምን አይነት ባለቅኔ እንደነበር እየዘረዘሩ አቀረቡ። ግጥሞቹን ሲያነቧቸውም የህዝቡ ስሜት ከፍተኛ ነበር።

ከዚያም ውይይት ተጀመረ። በውይይቱ መሀል አንድ ጥያቄ ተነሳ። ገብረክርስቶስ ደስታ ሠዓሊ ነው ወይስ ገጣሚ የሚል። አደገኛ ክርክር ተፈጠረ። ሠዓሊዎቹ ገብሬ ሠዓሊ ነው፤ ገጣሚነቱ ከሥዕል ቀጥሎ ነው የሚመጣው አሉ። የሥነ-ፅሁፍ ሠዎች ደግሞ ኸረ ሰውዬው ታላቅ ባለቅኔ ነው እያሉ የማይቋጭ ማብራሪያ ሰጡ። ክርክሩ መቋጫ አጣ። መሸ። እንደገና ሌላ ቀጠሮ ተያዘ። ገብሬ ሠዓሊ ነው ገጣሚ በሚለው ለመከራከር የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ጥበበኞች ቀጠሮ ያዙ።

በቀጠሮው ቀን ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ አወያይ ሆኑ። ቀኑ የአዋቂዎች የጦርነት ቀን ይመስል ነበር። በዕውቀት አደባባይ የሚደረግ ፍልሚያ ነበር። ሠዓሊዎች ሽንጣቸውን ገትረው ገብሬ ምን ያህል የሥዕል ጥበበኛ እንደነበር ማስረጃቸውን ይዘው መጡ። ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ እና ቀራፄ በቀለ መኮንን እና ፕ/ር አቻምየለህ ደበላ ከአሜሪካ ድረስ መጥተው የገብረክርስቶስን ሠዓሊነት ሲተነትኑ አመሹ።

ይሄ ሳይቋጭ ገብሬ አዝማሪ ነው፤ የሙዚቃ ሰው ነው እያለ ግጥሞቹን ከሙዚቃ አንፃር የሚተነትን መጣ። እሱም ዛሬ በህይወት የሌለው የሥነ-ግጥም መምህሩ ብርሃኑ ገበየሁ ነበር። የብርሃኑ ገበየሁ ገለፃ እንደ ተአምር ሲደመጥ ከቆየ በኋላ ሌላ አስገራሚ ነገር ብቅ አለ።

የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው ገጣሚ ነብይ መኮንን ደግሞ ገብሬ እናንተ እንደምትሉት ብቻ አይደለም። ገብሬ የሳይንስ ሰው ነው ሲል ገለፀው። ሲያብራራውም ሥዕሎቹም ሆኑ ግጥሞቹ የሳይንስ ፅንሠ ሃሳብ በከፍተኛ ደረጃ የሚያንፀባርቁ ናቸው እያለ ተነተነ።

ውይይቱ መቋጫ አጣ። ገብሬ ይሄ ነው ተብሎ መደምደምያ ጠፋለት።

በመጨረሻም ታላቁ የሥነ-ፅሁፉ ምሁር ዶ/ር ዮናስ አድማሱ፣ አንድ ማሳረጊያ አቀረቡ። ማናችሁም ብትሆኑ ይሄን ሰው መግለፅ አትችሉም። ይህ ሰው በሁሉም መስክ ጥበበኛ ነው። ስለዚህ ሠዓሊ፣ ገጣሚ፣ አዝማሪ፣ የሳይንስ ሰው፣ ብትሉት በቂ አይደለም። እንዲህ ዓይነት ሰው ከያኒ ነው የሚባለው በማለት መቋጫ ያልተገኘለትን ክርክር ፈር አስያዙት።

ውይይቱ እንዲህ እያለ ለብዙ ጊዜ ከሄደ በኋላ ገብሬ የብዙ ሰው ቀልብ ገዛ። ከዚያም በኑዛዜው መሠረት ሥራዎቹ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ጉትጐታ ተጀመረ። የጀርመን መንግስትም ተባበረ። እዚህ አዲስ አበባ ውስጥም የገብረክርስቶስ ደስታ ማዕከል በሚል አ.አ.ዩ ቤት ሰጠ። በስሙ ጋለሪ ተከፈተ። እናም በመጨረሻ እነዚያ የሰው ልጅ ሁሉ ቅርስ የሆኑት ሥዕሎቹ ከጀርመን ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ መጥተው ዛሬ እዚህ 6 ኪሎ ይገኛሉ። እነዚህን ተአምራዊ ሥዕሎቹን ሁላችሁም ሄዳችሁ ጐብኟቸው። እነሱን ስታዩ ኢትዮጵያ ምን አይነት የጥበበኞች ሁሉ አውራ የሆነ ሊቅ እንደነበራት ትረዳላችሁ።

 

በአሰፋ ሀይሉ

 

እንግዲህ አሁን ልንናገር የምንጀምረው ስለ አንድ አብረቅራቂ ኮከብ ነው። ስለ አንድ ኢትዮጵያዊ ዕንቁ። የዚህ ሰው እጆች ከእዝጌሩ ተቀብተው የተሰጡት - ግዑዙን ነገር ህይወት ይዘራበት ዘንድ ነው። የዚህ ሰው አዕምሮ፣ የዚህ ሰው ዕይታ፣ የዚህ ሰው ሁሉ ነገሮች ከፈጣሪው የተሰጡት የእኛን - ምድራዊውን - ህይወታዊውን ነገር ሁሉ - ህያውነቱን እስከ ዝንተዓለም እንደጠበቀ - ከትውልድ ትውልድ ድረስ - ለታሪክ፣ ለንግርት ለለውጥ - ህያው ሆኖ እንዲቀር በሚያስችለን ዕንቁ ጥበብ ይራቀቅ ዘንድ ነው። ይህ ሰው ይተኩሳል። ተኳሽ አርበኛ ነው። የሚተኩሰው ግን ጠብ-መንጃ አይደለም።


የዚህ ሰው መዋጊያ ጠብ-መንጃም አይደለም፤ ዲሞትፈርም አይደለም። ይህ ሰው አነጣጥሮ የሚተኩሰው - በሚታወቅበት ድንቅ ካሜራው ነው። ባለካሜራው ተኳሽ! አዳኙ ካሜራችን። በካሜራው ሥርቻችንን እያደነ አነጣጥሮ ያነሳዋል። በካሜራው ጉድለታችንን እያሰሰ አንጥሮ ያወጣዋል። በካሜራው አሣዛኝ ታሪካችን ላይ አነጣጥሮ ይተኩሳል - እናም ህያው አድርጎ መልሶ ለራሳችን ያሳየናል ግዳዩን። ይህ ሰው የመላ ጥቁር ሕዝቦች አምባሳደር ተብሎ እስከመጠራት የደረሰ ሰው ነው። ይህ ሰው የኢትዮጵያዊነት ልቀት ህያው ማሣያ ነው። ይህ ሰው አንድ ሰው ነው። እርሱም ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ የተሰኘ - ድንቅ አብረቅራቂ የጥበብ ኮከብ።


ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ - በየካቲት 25 ቀን፤ 1938 በጎንደር ተወለደ። ልብ እንበል ይህን። ፕ/ር ኃይሌ ገሪማ የተወለደው - ፋሺስት ኢጣልያ - በሃገራችን ሕዝቦችና በተዋጓት ጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች ላይ - የምትችለውን ሁሉ ጥፋቶችና መቅሰፍቶች አድርሣ - በአልበገርም ባዮቹ ጀግኖች አርበኞቿ ተጋድሎ እና መስዋዕትነት እና የማይነቃነቅ አልገዛም-ባይነት - ከዚህች የጥቁር አናብስት ምድር - በመጣችባቸው እግሮቿ - በበረረችባቸው ክንፎቿ - የጀግኖቹን እመጫት ነብሮች ታላቅ ክንድ ቀምሳ - ለነፃነታቸው እምቢኝ ባሉ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ክንፎቿን ተመትታ - በጥጋብ ገብታ በውርደት ከሃገራችን ፋሺስት በወጣች - በ5ኛ ዓመቱ መሆኑ ነው። እና - ያኔ - የጀግኖች አርበኞች ቆራጥ የአፍሪካዊ አይበገሬ መንፈስ ሳይበርድ - የጀግኖች አርበኞች ደም ሣይደርቅ - የቆራጦች ኢትዮጵያውያን ጉልበት ሣይልም - የኢትዮጵያዊነት፣ የአፍሪካዊነት፣ ታላቅ የአትንኩኝ-ባይነት መንፈስ በምድሪቱ ላይ እንደጋመ - ነው - ኃይሌ ገሪማ - ወደዚህች ጉደኛ የጀግኖች ምድር ብቅ ያለው። እናም - እናማ - ይህ የአርበኞች አይበገሬ መንፈስ - ያ የጥቁር ሕዝቦች ታላቅ የነፃነት ጭስ - ከኃይሌ ጋር - አብሮ ተወለደ - አብሮት ኖረ - እስካሁንም አብሮት አለ።


ብዙዎች ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማን በአንድ ነገር ግለጹት ቢባሉ - መምህር ብቻ ነው ብለው አያቆሙም። የሚገርም የሲኒማ ፀሐፊ ነውም ብለው አያበቁም። በዕዝነ ህሊናው መቶ ዓመታትን ወደኋላ ገሥግሶ - ልክ አሁን ያለና በዓይኑ በብረቱ ያየ አስመስሎ - የጥንቱን እንደ አዲስ ሕይወት ዘርቶ - ከሽኖና አስውቦ - የሚያቀርብልህ - አስማተኛ ምልከታዎች ያሉት አስማተኛ የፊልም ዳይሬክተር ነውም ብቻ ብለው አያበቁም - የሚያውቁትን ሰዎች፣ እና ድርሳናት ሁሉ ብትጠይቃቸው - ስለ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ። ሁሉም የሚነግሩህ ምን ብለው መሠለህ? - ይህ ሰው የጥቁሮች ነፃነት ሃዋርያ ነው ብለው ነው። ብዙዎችን ብትጠይቃቸው ስለ ኃይሌ የሚናገሩት - ይህ ሰው የዓለምን ጭቁኖች ታሪክ - በካሜራው ጥበብ - እንደ አዲስ አድርጎ የተረከ - እንደ አዲስ አድርጎ ያሳየ - እንደ አዲስ አድርጎ በታሪክ ድርሳን፣ በፊልም ስክሪን፣ ለታሪክ ያኖረ - ድንቅ የፀረ-ባርነት ትግል ግንባር ቀደም አነጣጥሮ ተኳሽ ነበር ብለው ነው የሚነግሩህ!!! በካሜራው እያነጣጠረ፣ በካሜራው የሚነሣ፣ የጥበብ ጀግና ነውና - የጭቁን ሕዝቦችን እውነተኛ አይበገሬነት - በካሜራው እያንበለበለ የሚተኩሰው - ይህ የኩሩ ማንነታችን አብሣሪ - ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ።


ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ - በ1979 ዓመተ ምህረት - በእንግሊዝ ሃገር፤ በኤደንበርግ ዩኒቨርሲቲ በጎብኝ ሌክቸረርነት ተጋብዞ - ያቀረባቸው ሦስት ሌክቸሮች ነበሩ። በመጽሐፍም ታትመውለታል። ‹‹የሶስተኛው ሲኒማ ጥያቄዎች›› በሚል የብዙ የዘርፉን ምሁራን የተጻፉ የጥናት ጽሑፎች የተጠረዙበት ዕውቅ መጽሐፍ ውስጥ። ያ መጽሐፍ የጥቁር ሕዝቦችን፣ የሶስተኛውን ዓለም ሕዝቦች፣ የሲኒማ ጥበብ በሚተነትኑ ድርሳናት ላይ ሁሉ - እንደ ዋነና ዋቢ መጽሐፍ ተጠቅሶ ታገኘዋለህ። እዚያ መጽሐፍ ላይ ፕ/ር ኃይሌ - በገጽ 65 ላይ - ‹‹ሀ›› ብሎ ጽሑፉን ሲጀምር - እንዲህ ብሎ ነው የሚጀምረው፡- ‹‹እኔ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለኝ፣ በስደት ሥራ እየሠራሁ በምኖርባት አሜሪካ ነዋሪ የሆንኩ ኢትዮጵያዊ ነኝ›› ብሎ ነው። እንዲህ ነው እንጂ ኢትዮጵያዊነቱን የሚያስቀድም ቁርጥ የአፍሪካ ልጅ! አፍሪካዊነትህ፣ ጥቁርነትህ፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነትህ፣ ኢትዮጵያዊ መልክህ፣ እንደነብር የተዥጎረጎረው የአናብስት ማንነትህ - በዓለም ፊት ሊያኮራህ፣ ሊያጀግንህ እንጂ - እንደምንስ ብሎ አንገትህን ሊያስደፋህና ሊያሸማቅቅህ ይችላል? - ያ እንደማይሆን ነው ኃይሌ ገሪማ - በምሁራን መድረክ፣ በመጽሐፉ፣ በአንደበቱ ሁሉ - ‹‹እኔ ኢ ት ዮ ጵ ያ ዊ ነኝ!›› ሲል የሚገኘው። እንዴ!? ይህ ሰው እኮ ከአርበኞች ማጀት ውስጥ የተወለደ፣ የአርበኞች መንፈስ ባረበበባት ነፃይቱ የ1930ዎቹ ኢትዮጵያ ዘመን የተወለደ ልባም ኢትዮጵያዊ እኮ ነው! ንፁህ ልባም ኢትዮጵያዊ።


ደስ የሚልህ ደግሞ - በዚያ መጽሐፍ ላይ - ስለ ሶስተኛው ዓለም የሲኒማ ፍልስፍና - እየተነተነ ብዙ ጥናቶችን ያቀረበው ሌላ ኢትዮጵያዊም ሰው ስታገኝም ጭምር እኮ ነው - የዩሲኤልኤ ፕሮፌሰሩን - በ2003 ዓ.ም. በ70 ዓመት ዕድሜው በሞት ያጣነውን - የድንቁን ኢትዮጵያዊ ምሁር - የፕሮፌሰር ተሾመ ወልደ ገብርዔልን የጥናት ጽሑፎች። ዛሬ ዛሬ የበዙ ድርሳናት ላይ የፕ/ር ተሾመ ወልደ ገብርኤልን ስም ታያለህ። ‹‹የሶስተኛው (ዓለም) ሲኒማ›› ምን ማለት እንደሆነ ፍቺ የሰጠው እርሱ ነውና - ከፅንሰ-ሃሳቡ ፈጣሪዎች - ከላቲኖቹ ከእነ ፈርናንዶ ሶላና እና ኦክታቪዮ ጌቲኖ ቀጥሎ ማለት ነው።
ኃይሌ ገሪማ በተማረበት በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ - ከአጋሮቹ ጋር - የተሰጠው ቅፅል ስም ነበር፡- የ‹‹ኤል ኤ አመፀኛ!›› ‹‹የሎስ አንጀለስ እምቢ-ባዮች!›› የሚል። ‹‹LA Rebels››፣ ‹‹LA Rebellion›› የሚሰኝ። ታዲያ ከዚህ በላይ - ይህ ሰው - የትም ሄደ የት - አልበገርም ባይ እንደሆነ - ማሣያ የሚሆን - ምን ሌላ ማስረጃ ያስፈልጋል?! - ምንም!


ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ የሲኒማቶግራፊ መምህር፣ የራሱን ፊልሞች በራሱ በጀት መሥራት የሚታወቅ - አንቱ የተሰኘ አንጋፋ ፊልም-ሠሪ ነው። በእርሱ የተኮተኮቱ በርካታ የፊልም ባለሙያዎች - በየፊልም ኢንዱስትሪው ታላቅ ስኬትን ተቀዳጅተዋል። ለእርሱም ትልቅ አክብሮት አላቸው። እርሱ ግን በአንድ ወቅት ከሆሊውድ ፊልሞች ምኑን ወይም የትኛውን እንደሚያደንቅ ሲጠየቅ የሰጠው መልስ ብዙዎችን ሲያነጋግር ነበር። እንዲህ ነው ያለው፡- ‹‹እኔን እንዴት ስለ ሆሊውድ ፊልሞች ትጠይቀኛለህ? ሌላ ሰው ብትጠይቅ ይሻልሃል። እኔ በዕድሜዬ የሆሊውድ ፊልሞችን ተመልክቼ አላውቅም። ለመጀመሪያ ጊዜ የአንድ የሆሊውድ ፊልም ጀምሬ ነበር። እርሱንም አጋጣሚ ያገኘሁት በኢትዮጵያ አየር መንገድ እየተጓዝኩ እያለ ስለተከፈተ አማራጭ በማጣቴ ያደረግኩት ነው!››። ይገርማል ይህ ሰው። እንዴ! እርሱ የሚያስተምራቸው ተማሪዎች ናቸው ሆሊውድ ላይ ፊልሞችን የሚሰሩት። እነርሱን ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያገኛቸዋል። እና ምን ልሁን ብሎ ነው የእነሱን - እርሱ ‹‹ዕቃ-ዕቃ›› ወይም ‹‹ቀባ-ቀባ›› ብሎ የሚገልጸውን - የሆሊውድ ፊልም የሚመለከተው?።


ግን ግን - ኃይሌ - ስለምን ‹‹ሆሊውድ››ን ጠምዶ ያዘው? - ምክንያቱ ይህ ነው። በ1960ዎቹ ‹‹ባለቀለም ቆዳ ያላቸው ሕዝቦች›› (‹‹ከለርድ ፒፕልስ››) - ጥቁሮች፣ ሕንዶች፣ ሂስፓኒኮች፣ ቻይኖች(?)፣ እና ሌሎች ሕዝቦች ምሁራንን - በእነዚህ ባለቀለም ሕዝቦች ላይ በነጭ መንግሥታት የሚካሄደው የጅምላ ዘረኝነት እና አስከፊ ከባርነት ያልተናነሰ ኢ-ሰብዓዊ አገዛዝ - ለአንድ ታላቅ እንቅስቃሴ አነሳሳቸው። ያም በስነፅሑፍ፣ በሥዕል፣ በሙዚቃ፣ እና በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች ውስጥ ያሉ የባለቀለም ዝርያ ያላቸው ምሁራን - ሆነ ብለው - በነጮቹ ከሚነገረው ማንነት የተለየ፣ በቅኝ ገዢዎቹ ከተጻፈው ታሪክና ትረካ የተለየ፣ ኢምፔሪያሊስቶቹ ጥቁሮች እነዚህ ናቸው ብለው ከሚስሏቸው አካይስት ምስል የተለየ፣ የጥቁሮች፣ የላቲኖች፣ የህንዶች፣ የሌሎችም በጭቆና ሥር ያሉ ሕዝቦችን - እውነተኛውን - በኢምፔሪያሊስቶች ያልተበረዘውን፣ ያልተከለሰውን፣ ያልጠለሸውን - እውነተኛውን - የተለየውን - የራሳቸው የሆነውን - ድንቅ ልዩ ማንነታቸውን - በጥበብ ሥራዎቻቸው ሁሉ ሊያንፀባርቁ - ተማምለው፣ ተስማምተው፣ ቆርጠው እንዲነሱ አደረጋቸው። እናም ‹‹ዘ ብላክ ሬኔይሳንስ ሙቭመንት›› (‹‹የጥቁሮች ለተሻለ ለውጥ የመነሣሣት እንቅስቃሴ››) በምድረ አሜሪካ ተወለደ።


የጥቁሮችን የተለዩ ጽሑፎች ይፅፉ የነበሩት እነ ዲ ኤች ሎረንስ፣ የጥቁሮች ሥዕል ይህ ነው ብለው በልዩ የአሳሳል ዘይቤ የሠሩት እነ ጃክሰን ፖሎክ፣ እነ እስኩንድር ቦጎስያን፣ የጥቁሮች ሙዚቃ ይሄ ነው ብለው ጉድ የሚያሰኝን የሙዚቃ ዛር ለምድረ አሜሪካ ብቻ ሣይሆን ለመላው ዓለም እንዲበቃ አድርገው ያንበለበሉት እነ ዱክ ኤሊንግተን፣ እና የሃርለም ሬኔሰንስ የጃዝ ሙዚቃ ጥቋቁር ፈርጦች በየሙያ መስኩ - ታላቁን፣ በጨቋኞች ተዳፍኖ የቆየውን፣ ያን ኃያል የጥቁሮች የጥበብ መንፈስ ተላብሰው - የተዛባን ታሪክ ሊያድሱ፣ ሆነ ብሎ እንዲጨቀይ የተደረገን ታላቅ ማንነት አንፅተው ሊገልጡ፣ ሁሉም - በታላቅ የአርበኝነት መንፈስ - ለታላቅ የጥበብ ተጋድሎ - ሆ ብለው በአንድነት ተነሡ። ኃይሌ ገሪማም ደግሞ በበኩሉ - የሠለጠነበትን፣ የተራቀቀበትን፣ ያን አነጣጥሮ የሚተኩስበትን የጥበብ ነፍጥ - ካሜራውን አንግቶ - የጎበጠውን የጭቁኖች ታሪክ ሊያቃና፣ ከጠቆረው በላይ ጽልመት የተጋረደበትን የአፍሪካውያን የጭቆና ታሪክ፣ እና ታላቁን የተዳፈነ የአፍሪካውያንን የአይበገሬነት መንፈሥ - ከተቀበረበት ነፍስ ዘርቶ ሊያስነሣ - እነሆ ወደ ፍልሚያው ጎራ ተቀላቀለ - ጥበብን፣ እና ያን የማይሞተውን ታላቁን ኢትዮጵያዊ የአርበኝነት መንፈሱን ታጥቆ።


እና ለኃይሌ ገሪማ - እና ለአቻ የሙያ ጓደኞቹ - የሆሊውድ ፊልሞች ማለት - እኛን ጥቁሮችን - እና ሌሎችን ዘሮች፣ ባህላችንን፣ ማንነታችንን፣ ታሪካችንን፣ እውነተኛ ፍላጎታችንን - እኛ እንደሆንነው ሣይሆን - ለገዢዎቹ በሚመች መልኩ ጠፍጥፎ - አርክሶ - አሰይጥኖ - አስቀይሞ - ለታዳሚ የሚያቀርብ - ከእውነት የራቀ - የዜጎችን አዕምሮ - በገዢዎች ዕዝነ አምሳል ሊቀርፅ የተነሳ - የውሸት መፈልፈያ - ተቋም - የጭቁን ሕዝቦችን አሰቃቂ ጭቆና ከዓለምም ከራሳቸው ከጭቁኖቹም ዕይታ ለመሰወር የሚሰራ - የሐሰት መፈልፈያ - የጭቆና ማራመጃ - ኢንዱስትሪ ነው።


ታዲያ እነ ኃይሌ ገሪማ ይህንን ብቻ ብለው አላቆሙም። የዓለምን ጭቁን ሕዝቦች ሁሉ እውነተኛ ታሪክ፣ እውነተኛ ያልተቀባባ የባርነት ህይወት፣ እውነተኛ የሕይወት፣ የኑሮ ጉስቁልና፣ በጨቋኞች ያልተበረዘ፣ በገዢዎች ያልደበዘዘ… እውነተኛ ውስጣዊ የጀግነት መንፈሥ የሚያሣይ ራሱን የቻለ - ከምዕራባዊው የታይታ፣ እና የዋዋቴ፣ ግልብ የሆሊውድ የፊልም ኢንዱስትሪ - ማለትም ከ1ኛው ዓለም ሲኒማ - በቅርፁም፣ በይዘቱም፣ በአሠራሩም፣ በዓላማውም፣ በሥርጭቱም፣ በሁሉ ነገሩ የሚለይ - ራሱን የቻለ የሲኒማ ፍልስፍናን ሰንቀው ተነሱ። ከዚያም ካለፈ ደግሞ - ይህ የሚፈጥሩት 3ኛው የሲኒማ ፍልስፍና - 2ኛው የሲኒማ ዓለም ተብሎ ከሚታወቀው - እና ከ1ኛው ዓለም የሆሊውድ ሲኒማም ከሚለየው - ከህንዶቹ የ2ኛው ዓለም የቦሊውድ ሲኒማም ራሱ የተለየ እንዲሆንም ጭምር ተለሙ - እነ ኃይሌ ገሪማ፣ እነ ሴኔጋላዊው አንጋፋ የፊልም ሠሪ እነ ኦስማን ሴምቤን፣ ኢትዮጵያዊው (የባርባዶስ ተወላጁ) እነ ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ፣ እና ሌሎችም የፊልም ዓለም ድንቃ-ድንቅ ፈርጦቻችን።


ምንም እንኳ - የ2ኛው ዓለም የቦሊውድ የፊልም ኢንዱስትሪ - ምንም እንኳ ለአጫዋችነትና የኢምፔሪያሊስቶችን ማንነት ብቻ ለማቆየት ከሚሰራው ከ1ኛው ዓለም የሆሊውዱ የፊልም ኢንዱስትሪ በመሠረተ-ሃሳብ ደረጃ የተለየ ቢሆንም - ምንም እንኳ ይህ የቦሊውድ የእስያኖች የፊልም ኢንዱስትሪ - የራስን ሃገር-በቀል የሕንዳውያን ሕዝቦች ባህልና ማንነት ማንፀባረቂያ ሆኖ ቢያገለግልም እንኳ - በዓላማው ግን በዋነኝነት - ለንግድ ትርፍ ሲባል እየተመረተ የሚቸበቸብ በመሆኑና - እንዲሁም ለቱሪስት መሣቢያነት እየተባለ - ሕንዶችን እንደሆኑት እንደእውነተኛ ማንነታቸው ሣይሆን - የውጭ ሃገር ሰዎች እንደሚስሏቸው ያለ ውሸተኛ ማንነት እያላበሰ የሚሰራ በመሆኑ - እነ ኃይሌ ገሪማ፣ እነ ጌቲኖ፣ እነ ሶላና፣ እነ ሴምቤን፣ እነ ተሾመ፣ እና ሌሎችም በርካቶች ሃቀኛ የጥበብ ፋናዎች አንድ ቁርጥ ውሳኔ አደረጉ።


ያም ውሳኔ ይህ ነበር፡- የ3ኛው ዓለም ሲኒማ - ከ1ኛውም ዓለም ሲኒማ የተለየ፤ ከ2ኛውም ዓለም ሲኒማ የተለየ ሆኖ - ለተረሱ፣ ለተረገጡ፣ ታሪካቸውና ማንነታቸው ተከርቸም እንዲገባ ለተደረጉ ሕዝቦች እውነተኛ ማንነት ማሣያ፣ ከጭቆና ለመታገያ፣ እና ካሉበት የጭቆና ካቴና ነፃ ይወጡ ዘንድ ለማታገያ፣ እና እውነተኛ አይበገሬ የኋላ ማንነታቸውን እንዲፈልጉ፣ እንዲያገኙትና ያንን ያገኙትን ታላቁን ማንነት እንዲላበሱት፣ በአንድነትም ‹‹ሣንኮፋ ሣንኮፋ ሣንኮፋ›› ብለው በሕብረት እየዘመሩ - የጥንቶቹን የአያቶቻቸውንና የቅድመ-አያቶቻቸውን ታላቁን የአፍሪካውያን የጀግንነትና የአርበኝነት መንፈስ ተላብሰው - ለህዳሴያቸው፣ ለታላቅነታቸው፣ ለከፍታቸው ሆ! ብለው እንዲነሱ - ተግቶ የሚሠራ - ፍፁም እውነተና ማንነትን የተላበሰ - ልዩ የሆነ - ራሱን የቻለ - የጭቁን ሕዝቦች የፊልም ኢንዱስትሪ ይሆናል ብለው ተነሱ - ይህ - የ3ኛው ዓለም ሲኒማ። እና ለእንዲህ ዓይነቱ አፍሪካዊ ተፋላሚ ጥበበኛ - የሆሊውድ አርቲፊሺያል ‹‹ድሪንቶ›› ወይም (ከይቅርታጋር) ‹‹አርቲ-ቡርቲ›› - ከቶውኑ ምን ሊፈይድለት? - እናም አያየውም። በእኛ አውሮፕላን ላይ ካልሆነ በቀር።


ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ በአሜሪካ ዩሲኤልኤ የፊልምን ጥበብ ከተማረ በኋላ - በወቅቱ ለጥቁሮች መብት ሆ ብለው እጃቸውን ጨብጠው እንደተነሱት - እንደዘመነኞቹ አፍሪካን-አሜሪካውያን አርበኞች - እንደ እነ ማርቲን ሉተር፣ እንደነ ማልኮልም ኤክስ፣ እንደነ ሁዌይ ኒውተን፣ እንደነ አንጄላ ዴቪስ፣ እንደቀደሙትም እንደነ ማርከስ ጋርቬይ ሁሉ - እርሱም - ኃይሌ ገሪማም - እነሆ የጥበብ መሣሪያውን ሰንቆ - ለታላቅ ግዳይ በግንባር ቀደምትነት ተሠለፈ። እናም የተረሱ ያልተዳሰሱ በጠንካራው የጭቆና መዳፍ ውስጥ የወደቁ እውነተኛ የተራቆቱ ነፍሶችን እውነተኛ ታሪክ በፊልም ሥራዎቹ ይሸነሽነው ገባ። ገና ያኔ - በ1964 ዓመተ ምህረት - ኃይሌ ገሪማ - ‹‹አወር ግላስ›› የተሰኘና ‹‹ቻይልድ ኦፍ ሬዚስተንስ›› የተሰኘ - ሁለት ፊልሞችን ሠራ። ቆየት ብሎ በ1968 ዓመ ምህረት ደግሞ ሁለት ፊልሞችን አከታትሎ እንካችሁ አለ፡- ‹‹ቡሽ ማማ››፣ እና ‹‹ምርጥ ሶስት ሺህ ዓመት›› (ወይም ‹‹ሃርቨስት 3000 የርስ››) የሚ ፊልሞቹን። ኃይሌ - ቡሽ ማማን ሲሠራ - በወቅቱ በታወቁ ሚዲያዎች ከሚቀነቀኑት - በሃሺሽ፣ ግድያ፣ እና የጨቀዩ የሴተኛ አዳሪ ሕይወቶች የተሞሉትን ስለጥቁሮች ህይወት የሚያወሱ ፊልሞችን ታሪክ በሚቀለብስና - የጥቁሮች እውነተኛ ሕይወት ይኸውላችሁ፣ የዚያም ምክንያቱ ይኸውላችሁ ብለ ቀልብጭ አድርጎ ያሳየበትን የመሪ አቀንቃኟን ባተሌ የዶሮቲንና - ቬትናም ዘምቶ ወደሃገሩ ሲመለስ የጀግና አቀባበል ይደረግልኛል ብሎ ሲጠብቅ - ያላለመው ውርደት፣ ሥራ-አጥነትና ዘረኝነት የጠበቀውን ባሏን - የቲ.ሲ.ን ታሪክ የሚዘግብ ፊልም ነበር። በዚህ ፊልሙ - ኃይሌ - ድህነት፣ ውርደት፣ እና ተከትለው የሚመጡት አስከፊ ህይወቶች - ሆነ ተብሎ የተደራጀ የገዢዎች ተቋማዊ ጭቆና ውጤቶች መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ ለዓለም አሣየ። እናም ታሪክ ሰራ። እውነተኛውን የ3ኛውን ዓለም ሲኒማ እንካችሁ ብሎ።


እና ደግሞ ኃይሌ። በቃ ያን እውነተኛ የጥቁር አናብስትን የጀግንነት መንፈስ፣ ያን የጥቁሮች የማያልቅ የአርበኝነት ብርታትን ለማግኘትም የፈለገ ነው የሚመስለው። ከላይ የገለጽነውን ‹‹ምርጥ ሶስት ሺህ ዓመት››ን ሊሠራ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ። በዚያም ፊልሙ በፊውዳላዊቷ ኢትዮጵያ የሚደርስበትን ተነግሮ የማያልቅ የጭቆና ቀንበር ሰባብሮ ጀግንነቱን ስላስመሰከረ ልባም ጭሰኛ ታሪክ ተረከበት። በ1970ም ዓመተ ምህረት ኃይሌ ወደ አሜሪካ ተመልሶ የሠራው፡- ‹‹ዊልሚንግቴን 10 ዩኤስኤ 10000›› የተሰኘ ፊልሙ - የአሜሪካኖች የፍትህ ሥርዓት ምን ያህል በዘረኝነት የተጨናቆረ፣ የፍትህ ተቋማቱ ምን ያህል የግፈኞችና ዘረኞች መሣሪያ እንደሆነ - ዊልሚንግተን ቴን እየተባሉ የሚጠሩትን 9 ጥቁሮች እና 1 ነጭ ፍርደኞች ሕይወት በመዳሰስ ለዓለም አሣየ። የጥቁሮችን አስከፊ የከተማ ደህነትና ጉስቁልና የሞላው እውነተኛ ህይወት ደግሞ እንዲሁ በ1976 ዓመተ ምህረት በሠራው - እና ዳግመና ከቬትናም ጦርነት ዘመቻ መልስ በድህነት ሊኖር ስለተጣፈ ስለአንድ ጥቁር ወጣት አሣዛኝ ህይወት - ‹‹አሽዝ ኤንድ ኤምበርስ›› በተሰኘ ፊልሙ - ዳግም እውነቱን በውብ ታማኝ ካሜራዎቹ እያፍረጠረጠ ተረከው። በ1978 ዓመተ ምህረት ደግሞ ስለአንድ ታዋቂ ጥቁር አሜሪካዊ ገጣሚ ህይወትና ስለኖረበት ዘመን ገጽታ የሰራውም ፊልም አለ፡- ‹‹አፍተር ዊንተር፡- ስተርሊንግ ብራውን›› የሚል ዶክመንተሪ (ዘጋቢ) ፊልም።


እና በመጨረሻ - ይህ የጥቁሮች ነፃነት ታጋይ ጥበበኛ - ይህ የጥቁሮች ታሪክ ነጋሪ - ይህ የጭቁኖች ሕዝቦች አንደበት - ይህ የተረሱ ሕዝቦች ዓይን - ፕሮፌሰር ኃይሉ ገሪማ አራት ዕውቅ ፊልሞችን ሠራ፡- ‹‹ሣንኮፋ››ን (በ1986 ዓ.ም.)፣ ‹‹ኢምፐርፌክት ጆርኒ››ን በ1987፣ ‹‹አድዋ - የአፍሪካውያን ድል››ን በ1992 ዓ.ም.፣ እንዲሁም ‹‹ጤዛ››ን በ2001 ዓ.ም.። የዚህ ሰው ገድል እና ሥራዎች፣ እና አስደናቂ ታሪኩ፣ እና ሥኬቶቹ - እንኳን እንደኔ ባለ ኢምንት ብዕር - በሙያው በተካኑት እና ተማሪዎቹም የሙያ አጋሮቹ በሆኑት በኢትዮጵያዊው የጋና እና የሃዋርድ ፊልም ምሩቅ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የሲኒማ ምሁር በእነ ዳዊት ላቀው ብዕር እንኳ አርትዖት ተደርጎበት፣ አጥሮ፣ ተቆራርጦ ቢፃፍ ቢዘከር ራሱ - እንኳን ይህች ገጽ - ብዙ ጥራዛት፣ ብዙ የፊልም ሪሎች አይበቁትም - ለዚህ ድንቅ ኢትዮጵያዊ አብረቅራቂ የጥበብ ፋና - ለኃይሌ ገሪማ ህይወት እና ሥራዎች!!! እናም ሌላ ጊዜ የምንመለስበት ሆኖ - ለአሁኑ - ስለሁለቱ ፊልሞቹ ብቻ ጥቂት ብለን እናብቃ። ስለ ሳንኮፋ እና ስለ ጤዛ።


የፕ/ር ኃይሌ ‹‹ሣንኮፋ›› ፊልም ሥፍራውን ጋና ውስጥ ያደረገ ሥራ ነው። ጋና ውስጥ በውቅያኖሱ ዳርቻ - በኬፕ ኮስት ላይ - የሚገኝ - በጥንት የባርነት ዘመን - ከገባህበት የማትወጣበት - ‹‹ዘ ዶር ኦፍ ኖ ሪተርን›› የተሰኘ - ትልቅ አስፈሪ ጥንታዊ በር ያለበት - የጥንት አፍሪካውያን ባሮች - ወደ አሜሪካ በባርነት በመርከብ ታፍገው ከመጫናቸው በፊት - ተጠርዘው፣ ተከርችመው የሚከርሙበት የባሮች ማራገፊያ ወደብ ላይ ነው የታሪኩ መጀመሪያ ሥፍራ። እና አንድ የአፍሪካውያን አታሞ ይደበደባል፡- ‹‹ሣንኮፋ! ሣንኮፋ! እናንት የሞታችሁ መንፈሶች! ተነሡና ታሪካችሁን ተናገሩ!›› እያለ ይጀምራል። ሣንኮፋ ማለት በጋናውያን የአካን ቋንቋ - የአሁኑን ማንነትህን ለማግኘት ወደ ኋላህ ወደ ጥንቱ ታሪክህ ተመልሰህ መዳሰስ ማለት ነው።


እና በዚያን ሠዓት በዚያ ሥፍራ የተገኘች ሞና የተሰኘች አፍሪካዊት-አሜሪካዊት ሴት - እዚያ ጥንት ከገባህ የማትወጣበት የባሮች ቅፅር ውስጥ ስትገባ - የሰማችው የሣንኮፋ አታሞ ድብደባ - የጥንታውያንን የሞቱ አፍሪካውያን ባሮች መንፈስ ይቀሰቅስና - እርሷም - ወደጥንቱ የባርነት ዘመን - እንደ ‹‹ታይም ትራቭል›› ወይም ‹‹ፍላሽ ባክ›› በመሠለ የኋልዮሽ የዘመን ጉዞ ተመንጭቃ - ወደባርነት ካቴና ውስጥ ትገባለች። በዚያ ቅፅር በሣንኮፋ መንፈስ ወደባርነት ዘመን የተመለሰችው ሞና - ራሷን ምን ሆና ታገኘዋለች? በባርነት ወደ አሜሪካ ልትሸጥ የተዘጋጀች አፍሪካዊት ባሪያ። እና በቃ ነጮቹን የባሪያ ፈንጋዮችም ታገኛቸዋለች። በመጀመሪያ ራሷን ትክዳለች። ‹‹እኔ እኮ አሜሪካዊ ነኝ! አፍሪካዊ አይደለሁም!›› ትላለች። አይሰሟትም። ማንም ሁኚ ማን አንቺ አንድ ባሪያ ነሽ ነው መልሳቸው። እና የስቃይ መዓት ያወርዱባታል፣ ይተለትሏታል፣ ይደፍሯታል። በመጨረሻም ወደ ላፋዬት በባሮች የሚታረስና የሚለቀም ሰፊ የአሜሪካ የጥጥ እርሻ ላይ በባርነት ትሰማራለች።


እዚያ ሞና እጅግ የሚያሰቅቁትን የባርነት አስከፊ ገጽታዎች ትመለከታለች። ጆ የሚባል ከነጭ የተወለደ ጥቁር አፍሪካዊ የገዛ እናቱን ክርስቲያን ስላልሆንሽ ብሎ ሲገድል፣ ራሱን ሲያጠፋ ትመለከታለች። ልታመልጥ ስትል ተይዛ ለከፋ ስቃይ ትዳረጋለች። አፍቃሪም ታገኛለች። ከሕንድ በባርነት የመጣ። በመጨረሻም እውነተኛ የአፍሪካውያንን ጭቁን ማንነት ትረዳለች። እሱዋም ከእነዚያ ጋር አንድ እንደሆነች ትረዳለች። እና ለነፃነታቸው ከሚታገሉ ህቡዕ ቡድኖች ጋር ትቀላቀላለች። በመጨረሻም ነፃ ትወጣለች። እና ልክ በሣንኮፋ የከበሮ መንፈስ ወደ ኋላው ዝርዮቿ ወዳሳለፉት አስከፊ የባርነት ህይወት ተመልሳ - ያን አስከፊ ቅድመ-አያቶቿ የከፈሉትን መስዋዕትነት ስትረዳ - የራሷን እውነተኛ አፍሪካዊ ማንነት ተላብሳ ዳግም ወደገባችበት - ማንም ከገባ በማይመለስበት በር - በነጻነት ትመለሳለች - ከበላይዋ ደግሞ የሣንኮፋን - የአፍሪካውያንን ቀደምት አይበገሬ መንፈስ የምትጠራው - የሣንኮፋ ዘማሪ ወፍ - በነፃነት ወደ አፍሪካ ሠማያት እየበረረች!!! ነፃነት ለአፍሪካን ምድር! አንድነትን ለአፍሪካውያን! አፍሪካዊነትን ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ እየዘመረች!!! እንዲህ ነበር እንግዲህ የኃይሌ ገሪማ - እውነተኛው - ከንፁህ አፍሪካዊ አርበኛ መንፈስ የተቀዳ - የሣንኮፋ ቅዳሴ!!! የአፍሪካውያንን መንፈስ በካሜራዎችህን በማይነጥፍ አዕምሮሕ ኃይል የቀሰቀስህ - አንተ ጋሼ ኃይሌ - አንድዬ የአፍሪካውያን አምላክ - ረዥም ዕድሜሜን ይሰጥህ ዘንድ በእናቶቻችን ምርቃት መረቅኩህ - አውሎ ያግባህ - ዕድሜ-ይስጥህ! ኑር! ተጓዝ! እና ሌለችንም መንገድ ምራ!!!


አሁን በመጨረሻ እናገርለታለሁ ያልኩት - ራሴም የመጀመሪያዋ ዕለት ካየሁበት የኤግዚቢሽን ማዕከል ሲኒማ ቤት - እስከ በፊልም-ነጣቂዎች ተሞጭልፎ በዲቪዲ እስከደረሰኝ የሥርቆት ኮፒ ድረስ ደግሜ ደጋግሜ ስላየሁት - የፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማን - ‹‹ጤዛ›› ፊልም - እና የመሪ ተዋናዩን የአንበርብርን - እና የከበበውን እግር-ተወርች የሚቆላልፍ የሃገራችን ከባቢ ህይወት፣ የመከነ ተስፋ፣ ወደፊት ይበራ ዘንድ የምናሳድረውን የነገአችንን ጥልቅ ሕልም፣ እና እንደዘንዶ የጠነከረውን እርስበርሱ የማይጨራረሰውን የነገውን ኢትዮጵያዊ ልባም ትውልድ - ይህን ሁሉ - በዚህች አጭር ሥፍራ ለመተረክ - ጊዜና ቦታ አጠረኝ። እና ያን የኃይሌን ዝክር ደግሞ - በሌላ ጊዜ ራሱን በቻለ ጽሑፍ ላካፍል ቃል ገብቼ - ለአሁኑ ተሰነባበትኩ። የደበዘዘብንን መንገድ ለሚያመላክቱን፣ የጠፋብንን ማንነት ለሚጠቁሙን፣ ለእነዚያ እውነተኛ የአፍሪካ ጥቁር አንበሶች ምሁራን፣ ትውልዶች፣ እውነተኛ የአፍሪካ አርበኞች - ከልብ ከመነጨ ክብርና ፍቅር ጋር - የኢትዮጵያ አምላክ በረከቱን ሁሉ እንዲያዘንብላቸው፣ ላለፉትም ዘለዓለማዊ ነፍሳቸውን በአፀደ ገነቱ እንዲያሸበርቅልን - ከመላ አፍሪካውያን ልጆች ጋር አብረን - በጉባዔ ፀለይን - ከልብ ተመኘን - በእናቶቻችን በአባቶቻችን አንደበት - የምርቃትን መዓት አወረድን። ያለፈበትን ታሪክ የማያውቅ ሕዝብ ወደፊት የለውም። ይጠፋል። የቀደሙትን የማያከብር ትውልድም የማያላውስ ዳፍንት ይወርሰዋል። ባለበት ይውዘመዘማል። ታሪካችንን እንዘክር። ታላላቆቻችንን እናክብር። ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር። አበቃሁ።


ለዚህ ትረካችን በምንጭነት የተጠቀምንባቸውን የጥበብ ሥራዎች፣ ደራሲዎች፣ ፀሐፍት፣ እና የድረ-ገጽ ምንጮች ሁሉ - በደፈናው ከመቀመጫችን ብድግ ብለን እጅ ነስተን አመሰገንን። መልካም ጊዜ ለሁላችን። ቻው።

Page 1 of 19

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us