You are here:መነሻ ገፅ»ኪነ-ጥበብ
ኪነ-ጥበብ

ኪነ-ጥበብ (217)

በጥበቡ በለጠ

 

 

ከሐምሌ 23 እስከ 26 ቀን 2007 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማዕከል በሚካሄደውና መጠሪያውን “ንባብ ለሕይወት” ያለው የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ ላይ በበርካታ ደራሲያን የተደረሱ መጽሐፍት ለምርቃት እንደሚበቁ ተገለፀ።

ከእነዚህ መጽሐፍት መካከልም አብዛኛዎቹ ገና ለገበያ ያልቀረቡና አዳዲስ ናቸው። በደራሲና በተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ ከልሌ የተተረጐመው የታዋቂው ደራሲ የጀምስ ሬድ ፊልድ መጽሐፍም ከሚመረቁት ውስጥ አንዱ ነው። ጀምስ ሬድ ፊልድ The Celectine Prophecy (An Adventure) በማለት የደረሰውን አፈወርቅ በቀለ “የመጨረሻው መጀመሪያ (የሰማየ-ሰማያት ትንቢት) ጀብዱ” በማለት ተርጉሞታል።

ይኸው መጽሐፍ በሰላሳ ሀገሮች ውስጥ፣ ከስምንት ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ የተሸጠ ሲሆን፣ በዓለም ውስጥ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት፣ በወቅቱ በአሜሪካ ውስጥ፣ ጠንካራ የማስታወቂያ ሽፋን ከነበራቸው መጽሐፍት ሁሉ የበለጠ መሸጡም ይነገርለታል።

ይህን በደራሲና ተርጓሚ አፈወርቅ በቀለ የተዘጋጀውን መጽሐፍ የአርትኦት ስራውን የሰራው ደራሲ አበረ አዳሙ መሆኑም ታውቋል። መጽሐፉ 284 ገጾች ያሉት ሲሆን፣ አፈወርቅ የጤናው ሁኔታ እንደ ቀድሞው ጤነኛ ባልሆነበት እና ከህመምና ከህክምና ጋር እየታገለ ጽፎ የጨረሰው የትግል ውጤቱ ነው። ይህን መጽሐፍ ወደ አማርኛ እንዲተረጉመው የሰጠውም ገጣሚና ደራሲ ስንቅነህ እሸቱ መሆኑንም አፈወርቅ ገልጿል። አፈወርቅ በቀለ ከዚህ በፊት “የደም ጐርፍ”፣ “የአሁንነት ኃይል”፣ “የአምላክ ፈዋሽነት ኃይል” እና ሌሎችንም መፃሕፍትን እና መጣጥፎችን ከ1950ዎቹ ዓመተ-ምህረት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ውስጥ የራሱን ድርሻ እያበረከተ ያለ አንጋፋ ደራሲ ነው።

ሌላው በዚሁ የመጽሐፍት አውደ-ርዕይ ላይ ለምረቃ ከሚበቁት መጽሐፍት ውስጥ በደራሲ አብነት ስሜ የተዘጋጁት ሁለት መፃሕፍት ይገኙበታል። መጽሐፍቶቹ አንደኛው “የቋንቋ መሰረታዊያን” የተሰኘ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ “ሳይኪ እና ኪዩፒድ” ይሰኛል።

በደራሲ አብነት ስሜ የተዘጋጀው “የቋንቋ መሰረታዊያን” የተሰኘው መጽሐፍ በውስጡም የቋንቋን ልዩ ልዩ ብያኔዎች፣ የተግባቦት መዋቅርን፣ የእንስሳት ተግባቦትን፣ የቋንቋን ንድፋዊ ገፅታዎችን፣ የቋንቋ ጥንተ አመጣጥ መላምቶችን፣ ስለ አፍ መፍቻ ቋንቋ፣ ሁለተኛ ቋንቋን መማርና መልመድን በተመለከተ፣ የቋንቋን ተግባራት፣ ቋንቋና ማኅበረሰብ እና ሥርዓት ጽሕፈትን እንዲሁም በሌሎችም ሰፋፊ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር አድርጐ ያዘጋጀው መጽሐፉ ነው። ይህ የአብነት ስሜ መጽሐፍ በቋንቋ እና በባሕል ላይ ለሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች እንደ መምሪያ የሚያገለግል መሆኑንም ለማየት ችለናል።

በቀደመው ዘመን የቋንቋ ትምህርት በቤተ-ክህነት ውስጥ ብቻ ተገድቦ ለብዙ ዘመናት ከቆየ በኋላ ዘመናዊ ትምህርት ወደ ሀገራችን ሲገባ ከዓለም ፍልስፍና እና አስተሳሰብ ጋር ተቀናጅቶ መሰጠት ከጀመረ ብዙ እድሜ ባያስቆጥርም በአሁኑ ወቅት ግን ትምህርቱ በመስፋፋት ላይ ይገኛል።

በ1944 ዓ.ም ተክለማርያም ፋንታዬ፣ ሆህተ ጥበብ ዘስነ ጽሁፍ፣ በሚል ርዕስ የቋንቋ መማርያ አሳትሟል። በ1947 ዓ.ም ታዋቂው ደራሲ በእምነት ገብረ አምላክ፣ “የአንድ ቋንቋ እድገት - አማርኛ እንዴት እንደተስፋፋ” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትሟል። ከእርሱ በፊትም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ቋንቋን በተመለከተ ጽፈዋል። በ1948 ደግሞ ብላታ መርስኤ ሐዘን ወልደቂርቆስ የአማርኛ ስዋሰው በሚል ርዕስ አሳትመዋል።

ከዚያም በኋላ ዘመናዮቹ የቋንቋ ምሁራን እንደ ፕሮፌሰር ባዬ ይማም፣ ዶ/ር ጌታሁን አማረ እና ዶ/ር ግርማ አውግቸውን የመሳሰሉ አያሌ ጠቢባን ቋንቋ ላይ እየፃፉ እየተመራመሩ ይገኛሉ። የአብነት ስሜ የቋንቋ መሰረታዊያን መጽሐፍም በሀገሪቱ ውስጥ በእውቀት ላይ በተመሠረተ መልኩ የሚካሄዱትን የቋንቋ ጥናትና ምርምሮች የበለጠ ከፍ እንደሚያደርገው ይታወቃል። ኢትዮጵያ የአያሌ ቋንቋዎች መገኛ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ጥናቶች ስሜታዊ እና ፖለቲካዊ ጫና ሳያድርባቸው በእውቀት ላይ ተመስርቶ ብቻ እንዲተነተኑ እንደ አብነት ስሜ አይነት የቋንቋ ጥናት መጽሐፍት በጣም አስፈላጊ መሆናቸው ይነገራል። ይህ መጽሐፍም በዚሁ ከሐምሌ 23 እስከ 26 በሚካሄድው የመፃሕፍት ዐውደ-ርዕይ ላይ ሐምሌ 24 ቀን 2007 ዓ.ም በ11 ሰዓት በኤግዚቢሽን ማዕከል ይመረቃል።

ሁለተኛ የአብነት ስሜ መጽሐፍ ለልጆች ያዘጋጀው ዳጐስ ያለው የተረቶችና የእንቆቅልሾች መጽሐፍ ነው። ርዕሱ ሳይኪ እና ኪዩፒድ ይሰኛል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ተረቶች ደራሲው አብነት ስሜ Most Beloved Stories ከተሰኘ መጽሐፍ የተረጐማቸው ሲሆን፤ የመጽሐፉ ተረቶችም የተሰበሰቡት የአሜሪካ እና የአውሮፓ ወላጆች በ“ተረት ምሽት” ላይ ከተረኳቸው ውስጥ በጣም ተወዳጅ የሆኑትን መርጧቸው ነው። “ሳይኪ እና ኪዩፒድ” የተሰኘው ተረትም የግሪክ አፈ-ታሪክ መሆኑንም አብነት ስሜ ገልጿል። ይህ የአብነት መጽሐፍ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጀ 411 ገጾች ያሉት ነው። ለልጆች የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍም ሐምሌ 24 በ11 ሠዓት ይመረቃል። አብነት ስሜ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ኮከብ እና ፍካሬ ኢትዮጵያ የተሰኙ ሁለት ተወዳጅ መጽሐፍትን ያሳተመ ደራሲ ነው።

በአሁኑ ወቅትም በቋንቋ የዶክትሬት ድግሪውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምሮ ዕጩ ተመራቂ ነው።

ከዚሁ ከልጆች መጽሐፍት ጋር ተያይዞ ሌሎች ሁለት መጽሐፍትም በዚሁ ኤግዚቢሽን ላይ ይመረቃሉ። እነዚህ ሁለት መጽሐፍትን ያዘጋጁት ሩሲያ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ንጉሴ ካሳዬ ናቸው። እርሳቸውም የቋንቋ እና የሥነ-ጽሁፍ ምሁር ሲሆኑ፤ ለኢትዮጵያ ልጆች ያዘጋጇቸውን ሁለት መጽሐፍት ከሩሲያ ድረስ ይዘው በመምጣት ለልጆች በነፃ እንደሚሰጡ ታውቋል። የፕሮፌሰሩ መጽሐፍትም የፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 26 ቀን 2007 ዓ.ም በአራት ሰዓት በኤግዚቢሽን ማዕከል ይመረቃሉ። በዚሁ በመጽሐፍት ዐውደ-ርዕይ ላይ ሌሎችም በርካታ መፃህፍት ከመመረቃቸውም በላይ የመፃሕፍት ገበያውም በእጅጉ እንደሚደራ ይጠበቃል። ገበያ ላይ የሌሉ፣ የጠፉ እና አዳዲስ መጽሐፍት በዝቅተኛ ዋጋ ለአንባቢያን እንደሚቀርቡ ለማወቅ ተችሏል።

በዚሁ ከሐምሌ 23 እስከ 26 ቀን በኤግዚቢሽን ማዕከል በሚካሄደው ታላቅ የመጽሐፍት ዐውደ-ርዕይ ላይ የዓመቱ ምርጥ የንባብ አምባሳደሮች እና በኢትዮጵያ የታሪክ ጽሁፍ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያበረከቱ አንድ ታላቅ ሰውም ይሸለማሉ። ከአንድ መቶ አስር በላይ ተሳታፊዎች የሚካፈሉበትን ይህን የመጽሐፍ ኤግዚቢሽን ያዘጋጀው ታዋቂው ጋዜጠኛ እና የማስታወቂያ ባለሙያ የሆነው ቢኒያም ከበደ ነው።

በጥበቡ በለጠ

 

በቅርቡ እዚህ በመዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ ብስራተ ገብርኤል አካባቢ የተገነባው እጅግ ዘመናዊው አዶት ሲኒማ እና ቴአትር፣ በኃይሉ ፀጋዬ ተደርሶ በተስፉ ብርሃኔ የተዘጋጀውን “ከራስ በላይ ራስ” የተሰኘውን ቴአትር ማሳየት ጀመረ።

 

ከራስ በላይ ራስ ሐምሌ 8 ቀን 2007 ዓ.ም በአዶት አዳራሽ አያሌ ሕዝብ በታደመበት ስነ-ስርዓት ተመርቋል። በእለቱ ንግግር ያደረጉት የአዶት ሲኒማ እና ቴአትር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ብርሃኑ እንደተናገሩት፣ አዶት ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከሰላሳ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጎ ይህ የኪነ-ጥበብ ማዕከል ገንብቶና አሟልቶ ሥራውን ሲያስጀምር ትርፉ እሩቅ እንደሚሆን፣ በአንፃሩ ግን በባህሉና በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ በሚያግዘው ነገር ከወዲሁ ውጤታማ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበር ብለዋል። አክለውም እንደገለፁት፣ ዛሬ በመደበኛነት የመድረክ ቴአትርን ለመጀመር በኃይሉ ፀጋዬ ተደርሶ፣ በተስፉ ብርሃኔ ተዘጋጅቶና በፕሮሜቲዎስ ፕሮዳክሽን ሥራ አስኪያጅ በሙሉ ቀን ተሾመ ፕሮዲዩስ የተደረገውን “ከራስ በላይ ራስ” ቴአትርን አበበ ተምትም፣ ፍቃዱ ከበደ፣ ሄኖክ ብርሃኑ እና ሄለን በድሉ ሲጫወቱ ልናሳያችሁ በመታደላችን ደስ ብሎናል ሲሉ ተናግረዋል።

 

አዶት ሲኒማና ቴአትር የተመረጡ ፊልሞችን ብቻ ለማሳየት ባደረገው ጥረት የበሰሉ እና ጥሩ የኪነ-ጥበብ ጣዕም ያላቸው ተመልካቾችን ለማግኘት ችለናል ሲሉ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል። አያይዘውም እነኚህ የኛው ደንበኞች ደረጃቸው ከፍ ያለ የመድረክ ትርኢቶችን እንደየቤታቸው በሚያዩት በአዶት ሲኒማና ቴአትር እንዲመለከቱ ስንጥር ቆይተን ዛሬ ለዚህ የምረቃ ቀን ስለበቃን እናንተንም ደስ እንደሚላችሁ እርግጠኞች ነን ሲሉ ተመልካቹ በሙሉ ድምፅ ድጋፉን ለግሷቸዋል።

ከራስ በላይ ራስ ዘወትር ረቡዕ በአዶት ሲኒማና ቴአትር አዳራሽ መታየት መጀመሩንም በይፋ ተናግረዋል።

በጥበቡ በለጠ

 

የሐገር ፍቅር ቴአትር ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 11 ቀን 2007 ዓ.ም 80 ዓመቱን ደፈነ። የ80 ዓመት አዛውንት የሆነው ይህ ቴአትር ቤት እንዴት ተመሠረተ ብለን ስንጠይቅ አንድ ሰው ከፊታችን ብቅ ይላሉ። እኚህ ሰው መኮንን ሀብተወልድ ይባላሉ።

 

መኮንን ሀብተወልድ በኢትዮጵያ የፖለቲካ የኢኮኖሚ፣ የማሕበራዊ ጉዳዮች ታሪክ ውስጥ ያላቸው ድርሻ እጅግ ከፍተኛ ነበር። ኢትዮጵያን ለማዘመን በተደረገው ርብርብ ውስጥ አሻራቸው ደማቅ ሆኖ የሚታይላቸው ሰው ነበሩ። እኚህ ሰው ስማቸው ከሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ጋር ይጠቀስ እንጂ፣ ሰውዬውማ የሀገሪቱን ስልጣኔ እንደ ውጋገን ሆነው ብርሃን ያሳዩ እና ብዙ የደከሙ ናቸው። ዛሬ መኮንን ሀብተወልድን በጨረፍታ ላስታውሳቸው ወደድኩ።

 

የመኮንን አባት ሀብተወልድ ሀብቴነህ ይባላሉ። እናታቸው ደግሞ ወ/ሮ ያደግድጉ ፍልፍሉ ሲሆኑ ሁለቱም የመንዝ እና ቡልጋ ተወላጆች ናቸው። በጋብቻቸው ወቅትም ስምንት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፤ መኮንን ሀብተወልድ ሁለተኛ ልጃቸው ናቸው። መኮንን ሀብተወልድ የተወለዱት ጥቅምት 19 ቀን 1886 ዓ.ም ከአዲስ አበባ በ45 ኪ.ሜ በምትርቀው አድአ ከተማ ነበር። ይህ ማለት የዛሬ 121 ዓመት ነው።

 

የመኮንን አባት ሀብተወልድ የቤተ-ክህነት ሊቅ ነበሩ። በተለይ እንጦጦ ራጉኤል ቤተ-ክርስቲያን ካገለገሉ እና በቤተ-ክርስትያኒቱም የተሰሩትን ታላላቅ ታሪካዊ ጉዳዮችን ካከናወኑ የድሮ አባቶች መካል አንዱ ነበሩ። ልጃቸው መኮንን ሀብተወልድም የእርሳቸው እግር ተከትሎ ቤተ-ክርስቲያኒቱን እንዲያገለግል ብርቱ ፍላጎት ነበራቸው። መኮንን እድሜው ለትምህርት ሲደርስ አማርኛን፣ ፅህፈትን፣ ንባብን ተማረ። ከዚያም ዳዊት ደገመ። ለከፍተኛ ትምህርት ተብሎም ወደ ዝቋላ ወንበር ማርያም ተላከ። እዚያም ግዕዝን፣ ዜማን፣ ቅኔን፣ ድጓን፣ ፆመ ድጓን ተምሮ በ15 ዓመት እድሜው አጠናቀቀ።

 

ወዲያውም እንደ አባቱ ፍላጎት የእንጦጦ ራጉኤል ደብር አገልጋይ ዲያቆን ሆነ። በዚህ ወቅት አንድ ቀን አጤ ምኒልክ ይታመሙና ለጠበል ሕክምና ወደ ራጉኤል ይሄዳሉ። እዚያ ራጉኤል ካሉት ዲያቆናት መካከል መኮንን ሀብተወልድ ከአጎቱ ልጅ ጋር ከታከለ ወ/ሃዋርያት ጋር ሆኖ ዜማ ለማሰማት ይመረጣሉ። ምኒልክ በሚጠመቁበት ወቅት እነ መኮንን በሚያሰሙት ዜማ ይመሰጣሉ። ይደነቃሉ። በጣምም ወደዷቸው። ታዲያ በዚያን ወቅት እቴጌ ጣይቴ ለዲያቆናቱ ለመኮንን እና ለታከለ ሽልማት እንዲሰጧቸው ታሪካቸው ያወሳል።

 

ታዲ ምን ያደርጋል ከጊዜ በኋላ መኮንን ሀብተወልድ በፀና ይታመማሉ። በሐገር ባሕል ህክምና በፆም በፀሎቱም ታከሙ። አልሆን አለ። ሰዎች ተሰብስበው መከሩ። ይህ ልጅ አካባቢ ቢቀይር ይሻላል፤ አየሩ ትንሽ ቆላነት ያለው ቦታ ይሂድ ተብሎ ተወሰነ። ከዚያም ወደ አርሲ ቦኩ ተላኩ። እውነትም ተሻላቸው። ታዲያ በአርሲ ቆይታቸውም ከወ/ሮ በላይነሽ ቤዛ ጋር ትዳር መስርተው ሁለት ልጆችን ወለዱ። ልጆቻቸውም ጥላሁን እና ከበደ ይባሉ ነበር። ጥላሁን በዘመኑ ወረርሽኝ በነበረው በፈንጣጣ በሽታ ሞተ።

 

አርሲ ከሶስት ዓመታት በላይ ከቆዩ በኋላ መኮንን ቤተሰቦቹን ሊጠይቅ ወደ አድአ ይመጣል። በወቅቱ ወረርሽኝ ከፍቶ ቤተሰቦቹ እና የአካባቢው ሕዝብ በሽታ ላይ ነበር። እንደውም ከቤተሰቦቹ መካከል ሁለቱ ሞተው አገኛቸው። ስለ እነሱ ህልፈት እያለቀሰ ሳለ ማታ እራሱም በወረርሽኙ ተያዘ። ሕመም ጀመረው።ሊጠይቅ የመጣው መኮንን የአልጋ ቁራኛ ሆነ። በአጋጣሚ አባቱ ስላልታመሙ ጤነኛ ሰዎች ፈላልገው ልጃቸውን መኮንን በቃሬዛ ተሸክመው ወደ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል አመጡት። ሆስፒታል ውስጥም ህክምና እየተከታተለ እያለ በበሽታው እንደማያገግም ታወቀ። ተስፋ ተቆረጠ። አባቱ ሀብተወልድ ልጃቸው ሆስፒታል ውስጥ ሞቶ አስክሬኑን ይዞ ከመሄድ በህይወት ይዘውት ሊሔዱ ሲሰናዱ አንድ መልዕክት ከዘኛቸው ከእማሆይ አጥሩ ዘባ ደረሳቸው።

የእማሆይ አጥሩ ዘባ መልዕክት ምንድንነው?

 

እማሆይ አጥሩ ዘባ ሕልም ታይቷቸዋል። መኮንን ሀብተወልድን በተመለከተ በህልማቸው ያዩትን ነገር ለአባት ለመምሬ ሀብተወልድ እንዲህ በማለት አቀረቡ፡-

“በሕልሜ የታመመውን ልጅህን ማማ ላይ ቆሞ ወፍ ሲያባርር አይቼው ስገረም፣ አንድ መልአክ የመሰለ ሰው በድንገት አጠገቤ መጥቶ፣ ስሚ! ይለኛል። ይህ የምታይው ልጅ ወደፊት የመንግሥት ሹም፣ የንጉስ ባለሟል፣ የንጉሥ ታማኝ ይሆናል። ሰዎች አይበላ፣ አያስበላ የሚል ስም ያወጡለታል። የዕድሜ ፀጋ ያገኛል። ግን ሕመም አይገድለውም. . .” ብሎኝ ከአጠገቤ ተሰወረ። ለሕልሜ ፍቺ አያስፈልገውም ግልጽ ነው። ይልቁንስ እኔ የምመክርህን ስማኝ! መኮንን እዚያው ሀኪሞቹ ዘንድ ይቆይ! ሲሻለው ሥጋ ወደሙ እንዲቀበል አድርግ! ወደፊት የአሩሲውን ኑሮ ትቶ በዚያው በንጉሡ ከተማ ጎጆ ያብጅ! ለእኔ እንደሚታየኝ መኮንን ትልቅ ሰው ሆኖ ስምህን ያስጠራል።ግን እኔና አንተ እንደርስበትም፤ አናየውም” ብለው ይናገራሉ እማሆይ አጥሩዘባ። (የዘውዴ ረታ፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስት ገፅ 528)

እማሆይ አጥሩዘባ እንዳዩት ህልም ተስፋ የተቆረጠበት መኮንን ተሻለው። ከሞት አፋፍ ወደ ህይወት ተመለሰ።

 

አባቱ መምሬ ሀብተወልድ ልጃቸውን ወደ አርሲ ከመመለስ በእማሆይ አጥሩዘባ ህልም መሠረት እዚሁ አዲስ አበባ እንዲኖር ወሰኑ። በኋላ የጓደኛቸው ልጅ ወደ ሆነው አቶ በቀለ ደስታ ዘንድ ሔዱ። ልጃቸውን ለአቶ በቀለ በአደራ ሰጡት። በቀለም መኮንን የፍል ውሃ መግቢያ ትኬት ሻጭ አድርጎ አስቀጠረው። የመኮንን ስራ እና ህይወት አዲስ አበባ ላይ ተጀመረ።

 

መኮንን ከሌሊቱ አስር ሰዓት እስከ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ያለእረፍት ሲሰራ ይቆያል። ከስድስት ሰዓት በኋላ ነፃ ነው። በዚህች በእረፍቱ ሰዓት ፈረንሳይኛ እና የሂሳብ ትምህርት እንዲማር ሰዎች መከሩት። ወደ አሊያንስ ፍራሲስ ሔዶ ተመዘገበ። ዘመናዊ ትምህርት መማር ጀመረ። ትምህርቱን ተምሮ ከጨረሰ በኋላ ስራውን መቀየር ፈለገ።

 

የላጋር ጉምሩክ ለመቀጠር አመለከተ። የተማረበትን ሰነድ ለኃላፊው አቀረበ። ኃላፊውም ነገ የሂሳብ ሠራተኛ ሆነህ ስራ ጀምር አሉት። መኮንን ስለተሰጠው እድል አመስግኖ ነገር ግን ችሎታው ሳይመዘን፣ ሳይፈተን እንዴት መቀጠር ይችላል? መጀመሪያ ችሎታዬን ፈትኑኝ፤ ከዚያም ካለፍኩ ቅጠሩኝ ይላቸዋል። ኃላፊውም ጉዳዩ ገረማቸው። ይህ ሰው ነገረኛ ሳይሆን አይቀርም ብለው ጠረጠሩ። እንዴት ሰው ስራ ጠይቆ ግባ ሲባል ካልተፈተንኩ አልገባም ይላል? እያሉ ተደነቁ።

ኃላፊውም እሺ ትፈተናለህ ብለውት አንድ ግብጻዊ ረዳታቸውን ፈትነው ብለው ያዙታል። ግብፃዊውም ለፈተና መኮንን ያስቀምጠዋል። ከዚያም እንዲህ አለው?

 

-    እንግሊዝኛ ትችላለህ?

-    አልችልም። የምችለው ፈረንሳይኛ ነው።

-    እንግሊዝኛ ሳትችል እንዴት ልትቀጠር ትመጣለህ?

-    አንድ ሰው ከዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ፈረንሳይኛ ከቻለ በቂ ነው። እኔ ደግሞ የመጣሁት የሂሳብ ስራ ላይ ለመቀጠር እንጂ ለእንግሊዝኛ ቋንቋ አይደለም። ከፈለክ ፈረንሳይኛውንም ልትፈትነኝ ትችላለህ።

-    እኔ እንግሊዝኛ ስለምችል ነው እዚህ የምሰራው ይለዋል ግብፃዊው።

-    መኮንንም ሲመልስ፣ አንተ ግብጻዊ ነህ። እንግሊዝኛ ሀገርህን በቅኝ ግዛት ስለያዙ የግዴታህን እንግሊዝኛ ማወቅ አለብህ። እኔ ነፃ አገር ነኝ። ስለዚህ ግዴታ የለብኝም። ደስ ያለኝን መማር አለብኝ። ይልቅ አንተ ፈረንሳይኛ ስለማታውቅ ፈረንሳይኛ መፈተን አልቻልክም። ስለዚህ ለአለቃህ ሔጄ ጉዳዩን አመለክታለሁ አለ።

 

መኮንን ሀብተወልድ እንዴት አይነት ሞገደኛ ሰው ሆነ። ግብፃዊው ፈርቶት ሂሳብ ፈተነው። መኮንንም ፈተናውን በሚገባ አለፈ። ጉምሩክ ተቀጠረ።

በጥቂት ጊዜ ውስጥ የጉምሩክን አሰራር ለመቀየር የተለያዩ ጥናቶችን እና አማራጮችን ማቅረብ ጀመረ። አስቸጋሪ ሆነው የቆዩ አሰራሮችን ሁሉ ወደ ዘመናዊነት ቀየረ። መኮንን በመስሪያ ቤቱ ውስጥ በእድገት እድገት እየጨመረ ሄደ። የገቢዎች የሂሳብ ሹም ሆኖ ተሾመ። ታዲያ እርሱ ይህን ሁሉ እድገት እያገኘ ሲሄድ አባቱ መምሬ ሀብተወልድ ይህን ሳያዩ አረፉ። በህልማቸው ያዩት እማሆይ አጥሩ ዘባም አረፉ። ህልሙ እውን ሆነ።

 

በዚህ ወቅት መኮንን ሀብተወልድ የታናናሽ ወንድሞቹ ሕይወት አሳሰበው። እናም ሊያሳድጋቸው ወሰነ። በአባቱ ምትክ ሆኖ ወንድሞቹን ለወግ ለማዕረግ ሊያበቃ ተዘጋጀ። እነዚህ ሶስት ወንድሞቹ ራጉኤል ቤተ-ክርስትያን ውስጥ የዲቁና ትምህርት ይማሩ ነበር። እነርሱም አክሊሉ ሀብተወልድ፣ መክብብ ሀብተወልድ እና አካለወርቅ ሀብተወልድ ይባላሉ።

 

እነዚህ ሶስት ወንድሞቹን እቤቱ አመጣቸው። ከዚያም ዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት አስገባቸው። ከት/ቤት መልስ በአሊያንስ ፍራሴስ ፈረንሳይኛን እንዲማሩ ማድረግ ጀመረ። ማታ ማታ ደግሞ እሱ ለታናናሽ ወንድሞቹ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ምን እንደሆነች፣ ታሪኳ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ፤ ያለባት የተማረ የሰው ኃይል እጥረት እንደሌሎቹ ሀገራት አላሳድጋት እንዳለ፣ ስለዚህ እናንተ ታናናሽ ወንድሞቼ ተምራችሁ ይህችን አገራችሁን ማገልገል አለባችሁ እያለ ያስተምራቸዋል። ኢትዮጵያ ምን አይነት ለውጥ እና ሽግግር ማምጣት እንዳለባት ማታ ማታ ያስተምራቸዋል።

 

የመኮንን ሀብተወልድ ወንድሞች በትምህርታቸው የቀለም ቀንድ ሆኑ። ሶስቱም እሳት የላሱ ተማሪዎች ሆኑ። በ1911 ዓ.ም አልጋ ወራሽ የነበሩት ራስ ተፈሪ (በኋላ አፄ ኃይለሥላሴ) ወደ ውጭ ሀገር ሔደው የሚማሩ ጎበዝ ተማሪዎችን ማሰባሰብ ጀመሩ። በዚያን ጊዜ 33 ተማሪዎች ተመረጡ። ከነዚህ ውስጥ የመኮንን ሶስቱም ወንድሞቹ ማለትም አክሊሉ ሀብተወልድ፣ መክብብ ሀብተወልድና አካለወርቅ ሀብተወልድ ተመረጡ። ሶስቱ የሀብተወልድ ልጆች እየተባሉም መጠራት ጀመሩ።

እነዚህ ወደ ውጭ ሀገር ሔደው እንዲማሩ የተመረጡት ጎበዝ ተማሪዎች ቤተሰቦቻቸው መቃወም ጀመሩ። እንዴት ወደ ውጪ ይሔዳሉ? ከሔዱ የኦርቶዶክስን ሃይማኖት ይረሳሉ፤ ሌላ ሃይማኖት ይከተላሉ በማለት ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀመሩ። ራስ ተፈሪ የሚቻላቸውን ሁሉ አደረጉ። ከወላጆች ተቃውሞ የተነሳ ቀኛዝማች ኃይሌ ኪዳነወልድ የተባሉ ወላጅ ሁለት ልጆቼ ሄደው የፈረንጅ ነገር ከሚማሩ ሁሉም ማለትም 33ቱም ተማሪዎች ይለቁ ብለው የሚሔዱብን የባቡር ሐዲድ ሊቆርጡ በሸፈቱ ጊዜ በፀጥታ ኃይሎች ተይዘዋል። ግን በመጨረሻም እነዚህ 33 ወጣቶች በህዳር ወር 1919 ዓ.ም ኢትዮጵያን ለቀው ወደ ውጭ ሀገር ሔዱ።

መኮንን ሀብተወልድ ሶስቱን ወንድሞቻቸውን ወደ ውጭ ሀገር ለትምሀርት ከላኩ በኋላም ሀገራቸውን ማገልገል ጀመሩ። የሀገር ግዛት ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊም ሆኑ። እነዚህ እያለ 1927 ዓ.ም ደረሰ። የጉድ ዘመን ነበር።

 

ፋሺስት ኢጣሊያ በ1888 ዓ.ም አድዋ ላይ በአፄ ምኒልክ ጦር ድል የተደረገችበትን የ40 ዓመት ቂም ቋጥራ ጦሯን ወደ ኢትዮጵያ ልታዘምት ነው። ከፍተኛ ዝግጅትም እያደረገች ነው። ታዲያ ኢትዮጵያዊያኖች በሙሉ በተጠንቀቅ እንዲቆሙ፣ ሀገራቸውን ከባዕድ ወረራ እንዲከላከሉ መኮንን ሀብተወልድ አንድ ማህበር አቋቋሙ። ይህ ማበር “የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገር ፍቅር ማህበር” ይባላል።

 

ማህበሩ ዛሬ የሀገር ፍቅር ቴአትር የሚለውን ወልዷል። መኮንን ሀብተወልድ የሀገር ፍቅር ቴአትር ወላጅ ናቸው። ግንቦት 11 ቀን 1927 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገር ፍቅር ማህበርን ሲመሰርቱ ዋና አላማቸው ኢትዮጵያን ከጠላት ወረራ መከላከል ነበር። ልዩ ልዩ የተማሩ ኢትዮጵያዊያን ከጠላት ወረራ መከላከል ነበር። ልዩ ልዩ የተማሩ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ማህበር ውስጥ እየተገኙ ለሕዝቡ ስለ ሀገር ምንነት ንግግር ያደርጉ ነበር። ከነዚህ ከተማሩ ኢትዮጵያዊያን መካከል የመጀመሪያው የአጭር ልቦለድ ድርሰት ደራሲ ተመስገን ገብሬ አንዱ ነበር።

 

እነ መኮንን ሀብተወልድ በዚህ ማህበር አማካይነት ህዝቡ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት አሰረፁ። ጦርነቱም አይቀሬ ሆነ። ኢትዮጵያም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ በሆነው በፋሽስት ኢጣሊያ ተወረረች። እነ መኮንን ሀብተወልድ የቀሰቀሱትም ሕዝብ ወደ አርበኝነቱ ገባ።  ማዕከላዊ መንግሥቱ ፈረሰ። ጃንሆይም ተሰደዱ።

 

ጦርነቱ ቀጠለ። ከአምስት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ አርበኞች የተዋረደውን አንድነታቸውን እንደገና አመጡት። ፋሽስቶችን ድል አድርገው መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም የቡልጋ አርበኞች አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። በወሩ ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም በስደት ሲታገሉ የነበሩት አፄ ኃይለሥላሴ፣ መኮን ሀብተወልድ እና እነ ተመስገን ገብሬ፣ ዮፍታሔ ንጉሴ በጣም ብዙ ሆነው አዲስ አበባ ገቡ። አፄ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ሰቀሉ። ታሪካዊ ንግግርም አደረጉ።

 

እንደገና የፈራረሰችውን ኢትዮጵያን ወደ መገንባት ስራ ተገባ። መኮንን ሀብተወልድ ወደ ውጭ ሀገር ልከዋቸው የነበሩት ወንድሞቻቸውም ተምረው መጡ።

ከመኮንን ወንድሞች መካከል አክሊሉ ሀብተወልድ እጅግ የሚደነቅ አዋቂ እና የተግባር ሰው በመሆናቸው በበርካታ የኃላፊነት ቦታ ላይ መቀመጥ የቻሉ ናቸው። በመጨረሻም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር እስከመሆን ደረሱ። ታዲያ የዚህ ሁሉ ውጤት ጠንሳሹ መኮንን ሀብተወልድ ናቸው። አክሊሉ የሚባል የኢትዮጵያ “ጂኒየስ” ያፈሩ ናቸው።

 

ተበታትኖ የነበረው የሀገር ፍቅር ማህበርም እንደገና ተሰባስቦ ወደ ኪነ-ጥበባት ዘውግ ውስጥ ገባ። ልዩ ልዩ ቴአትሮች እየተሰሩ ስለ አለፈው የጦርነት ዘመን እና ፍዳ፣ ስለ እማማ ኢትዮጵያ ብሎም ስለ ሌሎች ጉዳዮች ጥበባዊ ስራዎችን ማቅረብ ጀመረ። የዛሬው ሀገር ፍቅር ቴአትር ኢትዮጵያዊነት ከውስጣቸው ሲንፎለፎል የነበሩ ሀገር ወዳዶች ያቋቋሙት ቤት ነው። ሐምሌ 11 ቀን 1927 ዓ.ም

 

ባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ኢትዮጵያ የዲሞክራሲና የስልጣን ሾተላይ አለባት የሚል አባባል ነበረው። እናም በታህሳስ ወር 1953 ዓ.ም ጀነራል መንግሥቱ ንዋይ እና ወንድማቸው ገርማሜ ንዋይ በጠነሰሱት መፈንቅለ መንግሥት አልተባበር ካሏቸው ሰዎች መካከል መኮንን ሀብተወልድንም ገደሏቸው። ለኢትዮጵያ ስልጣኔ ሲዋትቱ የነበሩት መኮንን ሀብተወልድ አለፉ።

 

ሌላ አሳዛኝ ነገር ደግሞ መጣ። 1966 ዓ.ም አብዮት ፈነዳ ተብሎ የመኮንን ሀብተወልድ ወንድም ፀሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን ጨምሮ 60 ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆችን ደርግ በአንዲት ሌሊት ፈጅቷቸው አደረ። የስልጣኔ እና የዲሞክራሲ ሾተላይ ማለት ይሄ ነው።

 

ያለፈው ብዙ ነገር ያሳዝናል። ግን የ80 ዓመቱ አዛውንት፣ የሀገር ፍቅር ቴአትር ያለፈውን ዘመን ሁሉ እንዴት አድርጎ ያሳየን ይሆን? ለመሆኑ የ80 ዓመት ልደቱንስ ያከብራል ወይ? የመኮንን ሀብተወልድ አስተዋፅኦ እና ግዙፍ ታሪክ በሀገር ፍቅር ውስጥ እንዴት ሊዘከር፣ ሊታሰብ ይችላል? ሀገር ፍቅር የትልቅ ታሪክ ቤት መገለጫ ስለሆነ ትልልቅ ዝግጅቶች ይጠበቁበታል።

 

 

በጥበቡ በለጠ

ሕይወትን በሁለት ነገሮች ማቆየት እንችላለን። አንድም በስጋዊ ለሆዳችን ጥያቄ መልስ እየሰጠነው። ሁለትም ለመንፈሣችን ለህሊናችን ረቂቅ ነገር እየሰጠነው። የሰው ልጅ ሰው መሆኑም የሚለየው ስጋዊ እና መንፈሳዊ ነገሮች ውስጡ ስላሉ ነው። እንስሳት መንፈሳዊ ነገር የላቸውም። ሰውና እንስሳት በስጋ ሲገናኙ በህሊና ግን ይለያያሉ። ሰው ህሊና አለው። ዛሬ የምናወጋውም ይህን ሰው የመሆኑን ምስጢር የሚያበለፅጉትን የሚያሳድጉትን ረቂቃን ጉዳዮችን ነው። እነርሱም መፃሕፍት ናቸው። ሰው የመባልን፣ ሰው የመሆንን ልዩ ፀጋ ፍንትው አድርገው የሚያሳዩን የህሊና ምግቦችን ትንሽ እስኪ ቀመስመስ እያደረግናቸው ብንቆይስ።

ከፊታችን ሐምሌ 23 እስከ 26 2007 ዓ.ም እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በኤግዝቢሽን ማዕከል “ንባብ ለሕይወት” በሚል ታላቅ የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ ይካሔዳል። በዚህ ዝግጅት ላይ ከ100 በላይ በሀገሪቱ ያሉ የመፃህፍትን አከፋፋዮችና አሣታሚዎች ይሣተፋሉ። ከዘጠና ሺ በላይ በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተፃፉ መፃሕፍት ለእይታና ለሽያጭ ይቀርባሉ። የመፃሕፍት ምረቃ እና ውይይቶችም ይደረጋሉ። የዓመቱ የንባብ አምባሳደሮችም ይፋ ይደረጋሉ። ሌሎችም በርካታ ዝግጅቶች በኤግዚቢሽኑ ላይ መካተታቸውን የፕሮጀክቱ ኃላፊ የሆነው ጋዜጠኛና የማስታወቂያ ባለሙያው ቢንያም ከበደ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልጿል። አዘጋጁ ደግሞ ማስተር ፊልምና ኮሚኒኬሽንስ ነው።

 

ማስተር ፊልምና ኮሚኒኬሽንስ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ እመርታ ላይ ለሚገኘው የፊልም እንቅስቃሴ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ምክንያቱም ላለፉት 15 ዓመታት ብቻ እጅግ በርካታ የፊልም ኤዲተሮችን፣ የካሜራ ባለሙያዎችን፣ ዳይሬክተሮችን፣ የድምጽና የመብራት ባለሙያዎችን እና ከፊልም ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሙያዎችን እያስተማረ በማስመረቁ የተመረቁትም ወጣቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን የፊልም ስራ ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረሣቸውን በገሃድ የሚታይ እውነታ ነው። በኢትዮጵያ ፊልም ስራ ውስጥ ውጤታማ የሆነው ማስተር፣ አሁን ደግሞ የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ አዘጋጅቶ አንባቢ ትውልድ እንዲስፋፋ ለማድረግ “ንባብ ለሕይወት” ብሎ ቆርጦ ተነስቷል። በነገራችን ላይ፣ ማስተር ፊልምና ከሚኒኬሽንስ ዛሬ በሀገራችን በስፋት የምናየውን የኤግዚቢሽን ሥራ ፈር በመቅደድ እና በማስተዋወቅም ረገድ ድርሻው ግዙፍ ነው። ማስተር ወደ መፃህፍት አውደ-ርዕይ እና ወደ ንባብ ጉዳዮች ከገባ እንደ ቀደሙት ስራዎቹና ተግባሮቹ ይህንንም ጉዳይ ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሰዋል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።

 

በሐገራችን ኢትዮጵያ የንባብ ጉዳይ ተደጋግሞ እየተወተወተ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ንባብ የሰውን ልጅ ከእንስሳ ባህሪ ለየት አድርጎት ስብእናው የላቀ እንዲሆን የማድረግ ኃይል ስላለው ነው። ማስተር ፊልምና ኮሚኒኬሽንስ “ንባብ ለሕይወት” ሲልም ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው። ቀደም ሲል እንደገለፅኩት መብላትና መጠጣትን ሰውም ሆነ ሌሎች እንስሳትም ለመኖር ሲሉ ይጠቀሙበታል። ንባብ ደግሞ የሰውነትን ልዕልና፣ የአስተሳሰብን ከፍታ፣ የማስተዋልን ረቂቅ ኃይል፣ የትህትናን ገፀ-በረከት፣ የፍቅን ችሮታ፣ የአስተዳደርን ብልሃት ወዘተ ስለሚያጎናፅፍ ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠው ብቸኛው ሀብት ነው። ይህ ሃብት ተከማችቶ የሚገኘው መፃህፍት ውስጥ ነው።

 

መፃሕፍት ዝም ብለው ጠንካራ ልባድ እና የውስጥ ገፆች ብቻ ያላቸው አይደሉም። ውስጣቸው ሰው አለ፤ ሕዝብ አለ፤ ታሪክ አለ፤ የሰው ልጅ ውጣ ውረድ አለ፤ አለምን የገዙ፣ በአስተሳሰብ ሊቅነታቸው አርአያነታቸውን የምንከተላቸው ፈላስፎች፣ ተመራማሪዎች፣ የህይወት መንገድ እያመቻቹልን እነሆ በዚህ ተጓዙ፣ ያኛው ብዙ አሜኬላና እንቅፋት አለው እያሉ የዚህችን ዓለም ምስጢራት ይገላልፁልናል። መፃሕፍት ውስጥ ዋዛ እና ለዛ አለ። በዋዛና በለዛ ቋንቋ ተቀነባብሮ የሕይወትን አቅጣጫ እንድንፈትሽ እንድናውቅ፣ እንድንመራመር፣ እንድንጠይቅ፣ እንድንመልስ፣ እንድናብራራ ያደርጉናል። ለሰውልጅ በተሰጠው መንበር ላይ ቁጭ ብለን ሰው የመሆናችንን፣ ሰው የመባላችንን ልዩ ገፀ-በረከት የሚያጎናፅፉን ሀብቶቻችን ናቸው።

 

መፃሕፍት ሲከፋን የሚያፅናኑን፣ ስንሳሳት የሚያርሙን፣ ትዕቢትን፣ ጉራን፣ ጀብደኝነትን ከውስጣችን አስወግደው የመልካምነትን ስብዕና የሚገነቡልን የሊቃውንቶች ስጦታ ናቸው። መፃህፍት በመደርደሪያ ላይ ቆመው ስናያቸው ነብስ የሌላቸው የሚመስሉን የዋሃን እንኖራለን። ይልቅስ የሕይወት ምስጢራት፣ ያልተፈቱ የሚመስሉንን የሕይወት ጉዞዎች፣ አቅጣጫቸው የማይታወቅ የሚመስሉን የሕይወት ጎዳናዎች በሙሉ በመፃህፍት ውስጥ ከነ መፍትሔያቸው ቁጭ ብለዋል። ስለ መፃሕፍት ርዕሰ ጉዳይ ከፃፉልን የሀገራችን ደራሲያን መካከል አንዱ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ናቸው። ሻምበል አፈወርቅ ዛሬ በአፀደ ስጋ በዚህች ምድር ባይኖሩም በመፅሐፍቶቻቸው ግን ሕያው ናቸው። በሰው ልጅ ዘር ሁሉ ስማቸውን የሚያስጠሩላቸውን ከ17 በላይ መፃሕፍት አበርክተውልን ያለፉ ናቸው። እኚህ ሰው በ1972 ዓ.ም “የእውቀት አውራ ጎዳና” በሚል ርዕስ ስለ መፃሕፍት ጉዳይ ውብ የሆነ ፅሁፍ አበርክተውልናል። እንዲህ ይላሉ፡-

 

“ በመፃሕፍት ቤታችን ላይ ተደርድረው ለሰው ልጅ ዘር ውለታ የዋሉ. . . ትዝታቸው እንኳ እንደ በረከት የሚቆጠር ታላላቅ ሃሳቦችን ያመነጩና ዓላማዎችን የቀየሱ ታላላቅ ሰዎች ይጠብቁናል። . . . እነዚህ ሰዎች እውነትን ውበትን ፍቅርን ብርሃንን ነፃነትን እና ሥልጣንን ፈር ያስያዙ የሁሉም አገርና የሁሉም ዘመን መምህራን ናቸው። የነሱ ብርሃን ባይኖር ዓለም በጨለማነት ይገኝ ነበር. . . በአሁኑ ዘመን በየአገሩ በአስተዋይነት እና በአዋቂነት ላቅ ብለው በመታየታቸው ምሳሌነታቸው ይረዳል እየተባሉ የተደነቁ ሰዎች ሁሉ ለዚህ የበቁት እነዚህን ታላላቅ መፃሕፍት ደጋግመው ያነበቡ በመሆናቸው ብቻ ነው። እኛም ለነዚህ መፃሕፍት ማንበቢያ በየቀኑ ጥቂት ደቂቃዎች ብንሰዋ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ምን ያህል ከፍተኛ ለውጥ እንደሚገጥመን መረዳት እንችላለን”

በማለት ወርቃማው ብዕረኛ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ በ1972 ዓ.ም ፅፈዋል።

 

አለማንበብ በጨለማ ውስጥ እንደመጓዝ ይቆጠራል። ጨለማው የማየት፣ የመለየት፣ የመወሰን. . . ብቃታችንን ይገድብብናል። በራሳችን ምሉዕ እንዳንሆን ያደርገናል። ንባብ ግን ጨለማውን በረጋግዶ ወደ ኋላ እና ወደፊት ብዙ ሺ ዓመታት እንድናይ እና እንድንኖርበት ያደርጋል።

 

ዛሬ በሕይወት የሌሉትን አለቃ አያሌው ታምሩን ከአስር ዓመታት በፊት በተደጋጋሚ ቃለ-መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር። አለቃ ገና የአራት ዓመት ህፃን እያሉ ሁለቱም ዓይኖቻቸው ታወሩባቸው። ለብዙዎቻችን ይህ አጋጣሚ እጅግ አሳዛኝ ክስተት ሆኖ በሕይወት ጎዳና ላይ ውጤታማ ሆነን እንዳንጓዝ ሳንካ ሊሆንብን ይችላል። ነገር ግን ትንሹ አለቃ አያሌው ምንም እንኳ የዓይን ብርሃኑን ቢያጣም በማንበቡ ብቻ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የዘላለም ብርሃን አብርቶ ያለፈ የስኬት ተምሳሌት ነው።

 

አለቃ አያሌው ታምሩ አይኖቻቸው ባያዩም በጣቶቻቸው ፊደልን ለይተው፣ ፊደል አውቀው፣ አንብበው፣ ተምረው በእውቀት አውራ ጎዳና ላይ መንሸረሸር ጀመሩ። መዝሙረ ዳዊትን፣ ዜማን፣ ፆመ ድጓን፣ ምዕራፍን፣ ድጓን፣ ቅኔን፣ አቋቋምን እየተማሩ የየትኛውም ዘመን ሰው ሆኑ። አለቃ መች በዚህ ብቻ አቆሙ፡ የአለምን ምስጢራት ሁሉ ከልዩ ልዩ መፃህፍትና ደራሲዎች የተጠራቀመ እውቀት ገበዩ። በመጨረሻም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ውስጥ የሊቃውንቶች ሊቅ ተብለው “ሊቀ-ሊቃውንት” የተባለውን ማዕረግ አግኝተዋል። የቤተ-ክርስትያኒቱም የሊቃውንት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ነበሩ። በርካታ መፃህፍትንም አሳተሙ። በዘመነ አፄ ኃይለስላሴም የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው የግብረ-ገብ እና የሃይማኖት መምህርም ነበሩ። ታዲያ እኚህን ሰው ከታላላቅ ሰዎች መንበር ላይ ያስቀመጧቸው ንባብ እና መፃሕፍት ናቸው።

 

በማንበባቸው ብቻ የስኬት ሰገነት ላይ የደረሱት የየትኛውም ዘመን ሰዎችን ከሀገራችንም ሆነ ከባህር ማዶ እየጠቃቀስን ማውጋት እንችላለን። ግን ማንን አንስተን ማንን እንተዋለን? ብዙ ናቸው። የብዙዎች ማሳያ ይሆነን ዘንድ ግን በ1985 ዓ.ም በአፀደ ስጋ የተለየንን ጳውሎስ ኞኞን እናስታውስ። የቀለም ትምህርቱን በችግር ምክንያት አራተኛ ክፍል ላይ አቋረጠ። ግን ማንበቡን አላቋረጠም። በማንበቡ ብቻ የአራተኛ ክፍሉ ጳውሎስ ኞኞ በመጨረሻም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የስኬት ተምሳሌት ሆኖ ዝንት ዓለም የሚጠራ ሰው ሆኖ አልፏል። ምርጥ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ጥሩ ብንባል ጳውሎስ ኞኞ፣ መርጥ ታሪክ አዋቂ እና ፀሐፊ ጥሩ ብንባል ጳውሎስ ኞኞ፤ ትጉህ ተመራማሪ ጳውሎስ ኞኞ . . . እያልን ዘላለም እንድንጠራው ያደረገን የመፃህፍት ንባቡ ያጎናፀፈው ፀጋ ነው።

 

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ፣ እንደ ግለሰብ ራሳችንን እስኪ ዞር ብለን እንየው? በቤታችን ምን ያህል መፃሕፍቶች አሉን? እኛስ በቀን ምን ያህል እናነባለን? ለወለድናቸው የአብራካችን ክፋዮችስ ንባብን አውርሰናል ወይ? እነዚህን ጥያቄዎች በእዝነ ልቦናችን እንደያዝን እስኪ ወደ ሌላም ምዕራፍ እንጓዝ።

 

ኢትዮጵያ የተሳፈረችበት የታሪክ መርከብ ጉዞው ላይ ብዙ ውጣ ውረዶች አሉ። መርከቧ ውስጥ ብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊነት አሉ። እነዚህ ሕዝቦች በጉዟቸው ወቅት የሚወሱላቸው አያሌ ታሪኮች አሉ። እርስ በርሳቸው በተከባበሩ እና በተዋደዱ ጊዜ እንደ አክሱም ዘመን ስልጣኔ፣ ለአለም አሳይተዋል። እንደ ትንግርትና እንደ ብርቅዬነት እስከ አሁን ድረስ ምስጢራቸው ያልታወቁትን የቅዱስ ላሊበላን 11 ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያናትም አንፀዋል። በጎንደር ዘመን ላይ በኪነ-ሕንፃውም ሆነ በሥነ-ጽሁፍ እጅግ ዘምነው እንደ ብርቅም ታይተዋል። እነዚህ ኢትዮጵያዊያን የተሳፈሩበት የታሪክ መርከብ ወጀብ ተነስቶ ከወዲያ ወዲህ ሲያጋጫት ደግሞ፣ እንኩትኩት ብለው በድህነቱም በስልጣኔውም የአለም ጭራ ሆነው ይታያሉ። የመርክቢቱ ጉዞ እንዳይደናቀፍ እውቀትና ንባብ የግድ መምጣት አለባቸው። የኢትዮጵያን የታሪክ መርከብ ወደ ኋላ የሚያስቀረው ተሳፋሪዎቿ አለማንበባቸው ነው። እነዚህ ኢትዮጵያዊያን በሌላ የመርከብ ተጓዦች የተበለጡትም ባለማንበባቸው ነው። እናም የኢትዮጵያ መርከብ ለሕይወቷ ለሕልውናዋ ንባብ ያስፈልጋታል ብዬ በፅኑ አምናለሁ። ጋዜጠኛውና የማስታወቂያ ባለሙያው ታታሪው ቢንያም ከበደም የዚህችን መርከብ ጉዞ መንገራገጭ እንዳያሰናክለው “ንባብ ለሕይወት” ብሎ ትልቅ አላማ ሰንቆ መነሳቱም ለዚሁ ነው።

 

ኢትዮጵያ የተጓዘችበትን የታሪክ ጉዞ መለስ ብለን ስንመለከተው 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የስልጣኔ ሾተላይ እንዳጋጠማት እናስባለን። በዚህ ወቅት “ዘመነ መሳፍንት” የተሰኘ አገዛዝ ብቅ አለ። ትንንሽ ንጉሶች በየአካባቢው ነገሱ። ኢትዮጵያ ተከፋፈለች። ማዕከላዊ መንግስት ጠፋ። ይህ ዘመን የኢትዮጵያ ጨለማው ወቅት ነበር። የተፃፉ መፃህፍትን ማግኘት አስቸጋሪ ነው። የእልቂትና የጦርነት የግድያ ታሪኮች ነበሩ። በወቅቱ አሳዛኙ ነገር ደግሞ ልክ በዚያን ወቅት አውሮፓ ወደ ኢንዱስትራላይዜሽን /ወደ ኢንዱስትሪ ዘመን/ ተሸጋገረች። ኢትዮጵያ ደግሞ ወደ ከፋፍህ ግዛ የዘመነ አፄዎች ታሪክ ውስጥ ታጎረች። ይህ የጨለማ ወቅት ከ80 ዓመታት በላይ ቆየ። ከዚያም ካሳ ኃይሉ /አፄ ቴዎድሮስ/ ተነስቶ ጠራርጎ እስከሚያጠፋቸው ድረስ አያሌ ጥፋቶችን ፈፅመዋል።

 

አፄ ቴዎድሮስ የዘመነ መሳፍንትን አስተዳደር አስወግደው አንዲት ኢትዮጵያን መሠረቱ። ከዚያም በተለይ መቅደላ አምባ ላይ ትልቅ የቤተ-መዛግብትና የመፃህፍት የቅርሶች ማኖርያ መዘክር ሰሩ። በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ታላላቅ የፅሁፍ ቅርሶችን ሰብስበው በዚህ ቤተ-መዘክር ውስጥ ማኖር ጀመሩ። ይሁን እንጂ የቴዎድሮስ ጉዞም እንቅፋት በዛበት። የብሪታኒያ ወታደሮች ብዙ ሺ የህንድ ወታደሮችን አስከትለው ወደ መቅደላ አምባ ዘመቱ። ቴዎድሮስም ራሳቸውን ለሀገራቸው ክብር ሲሉ ሰው። ነገር ግን እንግሊዞች በመቅደላ አምባ ላይ ተከማችተው ያገኟቸውን የኢትዮጵያ ብርቅዬና ድንቅዬ የፅሁፍ ሀብቶች በብዙ ዝሆኖችና ፈረሶች ጭነው ወደ ለንደን አቀኑ። ዛሬ የለንደን ሙዚየምን እና የአውሮፓ ሙዚየሞችን ያጨናነቁት የብራና ፅሁፎች ከመቅደላ የተዘረፉ ናቸው። እንግሊዝ ሀገር የሚገኘው ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ከኢትዮጵያ ተዘርፈው ለንደን ሙዚየም ውስጥ የሚገኙት ብራናዎች በገንዘብ ሲተመኑ ሁለት ቢሊዮን ፓውንድ ያወጣሉ ሲል ጽፏል።

 

ኢትዮጵያ የፅሁፍና የታሪክ ሀብታም ነች። እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ሀብቷ ታሪኳ ነው። ይህን ታሪኳን በአግባቡ የምንሰበስበው ቅርሶቿን፣ መፃህፍቶቿን ስናውቅ እና ስንመረምር ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /UNESCO/ ከኢትዮጵያ ምድር ብቻ 12 የሥነ- ፅሁፍ ሀብቶችን የዓለም ታላላቅ ቅርሶች ብሎ መዝግቧቸዋል። ይህ ቁጥር በጣም ብዙ ነው። የሚሳየንም ነገር ቢኖር ሀገሪቱ የሥነ-ፅሁፍ ምድር እነደሆነች ነው። ለምሳሌ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው “መፅሐፈ ሔኖክ” በዓለም ላይ የጠፋ ምዕራፍ ነበር። ይህ መፅሐፈ ሔኖክ በውስጡ ሄኖክ የአዳም የልጅ ልጅ ከሆኑት የመፅሐፍ ቅዱስ አበው አንዱ ሲሆን፣ መፅሐፉም ከተፃፈ ዘመን ጀምሮ እስከ አለም ፍፃሜ በዚህ ዓለም ላይ ስለሚሆነው ማናቸውም ነገር የሚናገር የትንቢት መፅሐፍ ነው። ምድር ላይ ጠፋ ተባለ። ግን ኢትዮጵያዊያን አባቶች በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግዕዝ ቋንቋ ተርጉመውት አስቀምጠውታል። ጀምስ ብሩስ የተባለ የስኮትላንድ አገር አሳሽ እ.ኤ.አ. የካቲት 14 ቀን 1770 ዓ.ም ወደ ጎንደር መጥቶ ከእቴጌ ምንትዋብ ጋር ተዋውቆ፣ በቤተ-መንግስታቸው ተቀምጦ ልጃቸውንም አግብቶ ሲኖር ቆይቶ ወደ ሀገሩ ሲሄድ መፅሐፈ ሔኖክን ሰርቆ አመለጠ። ዛሬ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው መፅሐፈ ሔኖክ ከኢትዮጵያ የተገኘ ነው። ጀምስ ብሩስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከሔደ በኋላ እ.ኤ.አ በ1790 ዓ.ም Travels to Discover the Source of the Nile በሚል ርዕስ ግዙፍ መፅሐፍ አሳትሟል።

 

የኢትዮጵያን ታሪክ ለማወቅ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ እንግሊዝ ብሎም እስራኤል የግዕዝን ቋንቋ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎቻቸው ውስጥ ያስተምራሉ። ካስተማሩም በኋላ ጥንታዊ የኢትዮጵያን ብራናዎች ከግዕዝ ወደ አማርኛ እያስተረጎሙ ታላቅ ጉዳዮችን ይቀስማሉ። እኛ ዘንድ ግን ብራናዎቻችንን የመተርጎም ፍላጎቱ ብቻ ሳይሆን የግዕዝ ቋንቋችን ራሱ አደጋ ውስጥ እየገባ ነው። የእውቀት የሥነ-ፅሁፍ ሀብታሞች ሆነን ግን ገና አልነቃንም። ብልጦቹ አውሮፓውያን ከኛ ብዙ ነገር ቃርመዋል። ብራናዎቻችን ውስጥ የህክምና ጥበብ አለ፤ አስትሮሎጂ አለ፤ ስነ-ፅሁፍ አለ፤ ጂኦግራፊ አለ፤ የሂሳብ ቀመር አለ፤ ፍልስፍና አለ። የሌለ ነገር የለም። የፅሑፍ መሠረታችን ጥልቅ ነው። ጠንካራ ነው። እላዩ ላይ ትንሽ መገንባት ብንችል የት በደረስን!

 

ከሐምሌ 23 -26 ቀን 2007 ዓ.ም በኤግዚቪሽን ማዕከል የሚካሔደው የኢትዮጵያ የመፃሕፍትና የትምህርት ተቋማት አውደ-ርዕይ ስንቆጭበት የኖርንበትን የሥነ-ፅሁፍ ታሪካችንን ከሚያድሱልን ተግባራት መካከል አንዱ ነው። ምክንያቱም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹ አሳታሚዎች፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ መፃህፍት አከፋፋዮች፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የጀርመን የባህል ተቋም፣ የኢትዮጵያ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማህበር፣ የብሪትሽ ካውንስል ሌሎችም የመንግስት አካላት ሁሉ ለዝግጅቱ ርብርብ እያደረጉ ነው። ማህበራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ ብለው እነ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ኤቢ ሀም ኢንተር ፕራይዝም የመፃሕፍትን እና የንባብን ጉዳይ በመደገፍ ላይ ናቸው። ልዩ ልዩ የብዙሃን መገናኛዎችም የጉዳዩን ትልቅነት ተረድተው ሽፋን እየሰጡት ነው።

 

በዚሁ አውደ ርዕይ ላይ ለልጆችም ትልቅ ቦታ ተሰጥቷል። የንባብ ባህላቸው የሚገነባው ከዚሁ ከልጅነት እድሜ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል። ውይይቶችና አውደ ጥናቶችም ይቀርባሉ። ጋዜጠኛውና የማስታወቂያ ባለሙያው ቢኒያም ከበደ ይህን ትልቅ ጉዳይ በኃላፊነት ወስዶ አንባቢ ትውልድን ለማስፋፋትና ለመገንባት የሚደረገውን ትግል እዳር ለማድረስ መነሳቱ በበኩሌ አድናቆት አለኝ።

 

በመፃሕፍት አውደ-ርዕይ ላይ መገኘት መሳተፍ መወያየት ከትልቁ የሕይወት ዘመን ስራዎቻችን መካከል አንዱ መሆን አለበት። ጉዳዩ መፃሕፍት ናቸውና። ውስጣቸው ብዙ ነገር አለ። ትውልድ፣ ሀገር፣ ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ሀዘን፣ ደስታ፣ ስንቱ ተገልፆ ያልቃል? ተመግበን ከማንጨርሰው የዕውቀት ማዕድ መካከል መፃህፍት ዋናዎቹ ናቸው። ከማያልቀው የሰው ልጅ ስጦታ ጋር አብረን እንኑር።

በጥበቡ በለጠ

የኢትዮጵያዊው ሎሬት እና ባለቅኔ ፀጋዬ ገ/መድህን ታላላቅ የጥበብ ሀብቶች ፎቶ ኮፒ ተደርገው ሰሞኑን እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ተቸበቸቡ። መፅሐፍቶች ኮፒ ተደርገው የተሸጡት አራት ኪሎ ከምኒልክ ት/ቤት ፊት ለፊት ላይ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በአዘጋጀው የመፅሐፍት አውደ-ርዕይ ላይ የተሳተፉ ሁለት ነጋዴዎች ናቸው።

 

በኢትዮጵያ የኪነ-ጥበባት ዓለም ውስጥ ታላቅ ቦታ የሚሰጣቸው እነዚህ መፃሕፍት በተራ ነጋዴዎችና ኃላፊነት በማይሰማቸው ቸርቻሪዎች ድፍረት እየተባዙ ሲሸጡ ያያቸው ተቆጣጣሪ አካል ባለመኖሩ ድርጊታቸው ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መጥቶ ነበር። ኮፒ እየተደረጉ የተቸበቸቡ የባለቅኔው ስራዎች የሚከተሉት በዋናነት ይገኛሉ።

 

1.  በ1957 ዓ.ም ያሳተመው ሃምሌት የተሰኘው የትርጉም ስራው አንዱ ነው። ፀጋዬ በኢትዮጵያ የትርጉም አለም ውስጥ በተለይ ቴአትር ላይ እጅግ ድንቅ የሚባል ችሎታውን ያስመሰከረበት የታላቁ ፀሐፊ ተውኔት የዊሊያም ሼክስፒር ስራ ነበር። ፀጋዬ ሼክስፒርን ሙሉ በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣበት የተነገረለት የጥበብ ስራ ነው። ሃምሌት በዩኒቨርስቲ የቴአትርና የትርጉም ብሎም የሥነ ጽሁፍ ትምህርት ውስጥ ከዋና ዋና ማጣቀሻዎች አንዱ ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ነው። በሃምሌት ውስጥ ትውልድ አለ፤ እውቀት አለ፤ ጥበብ አለ፤ ታሪክ አለ፤ ክብር አለ። ኃላፊነት በማይሰማቸው ነጋዴዎች እጅ ግን ይህ ሁሉ ክብር ባዶ ሆነ ፎቶ ኮፒ እያደረጉ ሃምሌት ቸበቸቡ

 

2.  ሌላው የተቸበቸበው የፀጋዬ ስራ ሀሁ በስድስት ወር የተሰኘው የቴትር መጽሐፉ ነው። ይህ ቴአትር ደርግ ወደ ስልጣን እንደመጣ በ1967 ዓ.ም ተፅፎ እነ ወጋየሁ ንጋቱን የመሳሰሉ ታላላቅ ተዋንያን የተሳተፉበት የጥበብ ስራ ነው። በሀገሪቱ የቴአትር ታሪክ ውስጥ የክብር ቦታ ከሚሰጣቸው ስራዎች መካከል ከፊት የሚሰለፍ ነበር። እሱም በዚህ ዘመን ክብር አጣና ኮፒ ተደርጎ ተቸበቸበ።

3.  ማክቤዝ የተሰኘው በተዛማጅ ትርጉም ያዘጋጀው መጽሐፉም ኮፒ ተደርጎ ተቸብችቧል። ማክቤዝ ዊሊያም ሼክስፒር ከፃፋቸው ታላላቅ ቴአትሮች መካከል አንዱ ነው።

 

እነዚህ ነጋዴዎች መፅሐፎቹ በገበያ ላይ አለመኖራቸውን እና ተፈላጊነታቸውን በማወቅ ኮፒ አድርገው እንደሸጧቸው ለማወቅ ተችሏል። መፅሐፎቹን የገዙም አካላት እጅግ የሚፈልጓቸው ህትመቶች በመሆናቸው እያንዳንዳቸውን ኮፒ ከ50 ብር በላይ ሸምተዋል።

 

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የስራ አመራር አባል የሆነው ገጣሚ ይታገሱ ጌትነት ከሰንደቅ ጋዜጣ ለቀረቡት ጥያቄ በሰጠው መልስ ድርጊቱን በጥብቅ አውግዞ እንዲህ አይነት አፀያፊ ስራ የሚሰሩ መፅሐፍት ነጋዴዎችን የጠቆመን ሰው ባለመኖሩ ልንይዛቸው አልቻልንም ብሏል። እንደ ይታገሱ ገለፃ፤ በኤግዚቢሸኑ ላይ መሳተፍ ለሚፈልጉ መፅሐፍት ሻጮች ቀደም ሲል ደንቦችን አውጥተናል ብሏል። ከደንቦቹ መካከልም መፅሕፍትን እና የሌሎች ሰዎች ስራዎችን ኮፒ አድርጎ መሸጥ እንደማይቻል፣ የተሰረቁ መጽህፍትን መሸጥ እንደማይቻል፣ የመሸጫ ዋጋቸው የተፋቀ እና የተሰረዘ መፅሐፍት ፈፅሞ ወደ ገበያው እንዳይገቡ ተስማምተን ነው ቦታ የሰጠናቸው ብሏል። አሁንም ቢሆን እንዲህ አይነት ድርጊት ውስጥ ሲገቡ ጥቆማ ስላልደረሰን እርምጃ አልወሰድንም ሲል ተናግሯል።

 

የታላቁ ሊቅ የፀጋዬ ገ/መድህን ሰራዎች ገበያ ላይ አለመኖራቸውም ሌላው ችግር ነው። በአሁኑ ወቅት እጅግ ከሚፈለጉት የፅሁፍ ሃብቶቻችን ውስጥ ፀጋዬ ገ/መድህን በድንቅ ችሎው የፃፋቸው ስራዎቹ ናቸው። ምናልባት እነዚህን የፀጋዬን ስራዎች ከቤተሰቦቹ ጋር በመነጋገር ደራሲያን ማህበር፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ፣ ሻማ ቡክስ፣ አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅትና ሌሎችም ማሳተም የሚችሉበትን ሁኔታ ቢያመቻቹ በጣም ጥሩ ይሆናል።

 

የሼክስፒር ስራዎች ላለፉት 400 ዓመታት እና እስከ አሁንም ድረስ በአለም የመፅሐፍት ገበያ ውስጥ ሁሌም እንደ አዲስ አሉ። የኛ ሼክስፒር “ፀጋዬ ገ/መድህን” ግን በፎቶ ኮፒ መቸብቸብ የለበትም። ስራዎቹ የዚህች ሀገር መድመቂያ እና መከበሪያ ስለሆኑ ሁሌም ከእይታ መራቅ የለባቸውም።

 

ቴአትርን ከመድረክ ውጭ ለሚያውቀው ዜጋው በ1950ዎቹ ውስጥ በመፅሐፉ እያሳተመ የቴአትርን ሀሁ ያስተማረ ባለውለተኛም ነው። ገና በ16 ዓመት እድሜው 1949 ዓ.ም አምቦ ከተማ ውስጥ ተማሪ ሳለ “ንጉሥ ዳዮኒሰስና ሁለቱ ወንድሞቹ” በሚል ርዕስ ከመማሪያ መፅሐፉ ላይ ያለውን ፅሁፍ ወደ ቴአትር ለውጦ፣ አዘጋጅቶ በመድረክ አቀረበው። በዚህ ቴአትሩ ገና በ16 ዓመቱ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገስት ዘኢትዮጵያ ዘንድ ሽልማት ያገኘ የብርቱነት ተምሳሌ ነው። የእርሱ ስራዎች በ1950ዎቹ ውስጥ በኦክስፎርድ ፕሬስ አማካይነት ይታተሙ የነበሩ ናቸው። ዛሬም ትውልድ እንዲነባቸው እንዲያያቸው በከፍተኛ ጥራት ደረጃ መታተም አለባቸው እላለሁ።

በአንጋፋው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አማካይነት ሰኔ 30 የንባብ ቀን እንዲሆን ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን፣ ይኸው ማህበር አንባቢ ሕዝብ እንዲስፋፋ ደግሞ የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ አድርጎ ሰሞኑን ከተማዋን አሟሙቋታል።

ሰኔ 30 የንባብ ቀን ተብሎ በብሔራዊ ደረጃ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረው ባለፈው ዓመት ሲሆን ዘንድሮም የንባብ ሆኖ እንዲውል ተደርጓል። ንባብ የየእለት ተግባር ስለሆነ በዓመት አንድ ቀን ደግሞ ቢዘከር ጠቃሚነቱን የበለጠ በትውልድ ስነ-ልቦና ውስጥ ማስረፅ እንደሚቻል ይነገራል።

ግን እንዲህ አይነት ለሕዝብና ለሀገር ጠቀሜታው ተዘርዝሮ የማያልቅን ነገር መንግስት ተቀብሎት አብሮ ሊዘምርለት፣ ሊያስተጋባው ይገባል። ተማሪዎች፣ ሠራተኞች፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የንባብን ዘላቂ ጥቅም እንዲረዳ ሰፊ መድረክ ሊፈጥር ይገባል። በተለይ ባህል ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር አንባቢ ትውልድ መፍጠር ዋነኛው ግባቸው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የማያነቡ ሕዝቦች በጨለማ ውስጥ እንደሚጓዙ መንገደኞች እንደሚመሰሉ ከተነገረ ቆይቷል። በጨለማ ጉዞ አቅጣጫው ይጠፋል፣ መንገዱ ያወናብዳል፣ ከኋላም ከፊትም የማየት እይታን ይጋርዳል። ፈሪ ያደርጋል። ማሰብና መፍትሔ ማምጣት አያስችልም። በጨለማ ውስጥ መጓዝ ድፍረት ያሳጣል። እርዱኝ መንገድ ስጡኝ፣ አሳልፉኝ እያስባለ ያስለምናል። የጨለማ ጉዞ ካለ መሪ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ ማንበብ ብርሃን ነው የሚለውን አባባል እንድንይዘው ይገፋፋናል። እውነትም ማንበብ ብርሃን ነው። ስንቶች አይነ-ስውራን እህትና ወንድሞቻችን ስላነበቡ ብቻ ለወግ ማዕረግ በቅተዋል። ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል ያለው ማን ነበር? ይሄ አባባል ደግሞ ያላነበበ እንደ ሰው አይቆጠርም የሚልም አንደምታ አለው።

 

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከሰሞኑ ያዘጋጀው ሌላው በጎ ነገር የመፃሕፍ አውድ ርዕይ ነው።  የኢትዮጵያ መፅሐፍት ህትመትና የሽያጭ ስርጭት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ውድቅ ነበር። አሁን ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ወደ ላይ የማንሰራራት ዝንባሌ ይታይበታል። ይህ ሊሆን የቻለው ስለ መፃህፍት ተደጋጋሚ የሆኑ አውደ-ርዕዮች፣ ውይይቶች በመኖራቸውና የተሻለ እንቅስቃሴ በመምጣቱ ነው።

 

ታዲያ ይህን ግለት እና ሞቅታ ከፍ ለማድረግ በተለይ ከትምህርት ተቋማት ብዙ ይጠበቃል። ትምህርት ሚኒስቴር በየገጠሩ ለሚገኙ ተማሪ ቤቶች እንደ ድሮው መፃህፍት መግዣ በጀት መድቦ መፃሕፍት ቢገዛ ታላቁን ግብ ተወጣ ብዬ አስባለሁ። ባህል ሚኒስቴር ደግሞ የንባብ ባህል፣ የመፃህፍት ሽያጭና ስርጭቱ እንዲመነደግ፣ ሀገርና ወገን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲመጡ የሚያደርጉ ደራሲያንን፣ የጥበብ ሰዎችን በየጊዜው እውቅናና ክብር ቢያሰጥ፣ ወይ የት በደረሰን!

 

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር እነዚህን ሁለት ታላላቅ መርሃ ግብሮችን የማዘጋጀት እቅዶቹን የበለጠ እንዲያስፋፋቸው በዚህ አጋጣሚ ሳልጠቁም አላልፍም። በተለይ የመፃህፍት አውደ-ርዕዩ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ በየጊዜው ቢሞከር አንባቢን ያመጣል፤ ደርቆ የሰነበተውን የመፅሐፍት ሽያጭና ስርጭትም ከፍ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ። የማንክደው ነገር ከባለፉት 20 ዓመታት አሀን የተሻለ ነው።  ለውጥ መጥቷል። መቶ ሺ እና ከዚያም ያለፈ የመፃሕፍት ቁጥር ያሳተሙ ሰዎች አሉ። ግን መፃህፍት ፕሮሞተር ይፈልጋሉ። ሕዝብ ውስጥ የሚከታቸው ነበልባል ድምፆችና ታታሪ የሚዲያ ሰዎች ያስፈልጓቸዋል። እነዚያም ሰዎች መጥተዋል። መንገድ ላይ ናቸው። እነርሱን ደግሞ ሳምንት ይዤያቸው እቀርባሁ። መልካም የንባብ ቀን ይሁንልን!

በኢትዮጵያ የባህላዊ የህክምና ጥበብ ላይ፣ በተለይ ደግሞ ልዩ ልዩ እፀዋትን በመጠቀም ሰዎች እንዴት ራሳቸውን ከበሽታ መከላከል እና መፈወስ እንደሚችሉ የሚያብራራ ግዙፍ መፅሐፍ ህክምና በቤታችን በሚልር ርዕስ አሳትማ ያሰራጨች፣ ስለ ቤት እንስሳት መኖ እና አጠባበቅ መፅሐፍ አዘጋጅታ ለኢትዮጵያ ገበሬዎች ለቤት እንስሳት እንክብካቤ መኖ ልማት ባህላዊና በተፈጥሮ መድሃኒት ብላ ያደረሰች፣ ስለ እፀዋት ለኢትዮጵያ ታዳጊዎችና ህፃናት መፅሐፍ ፅፋ ያስነበበች፤ ህይወቷን ኑሮዋን ሁሉ ኢትዮያዊያን በቤታቸው በአካባቢያቸው በሀገራቸው ያሉ ተክሎችን እፀዋትን በመጠቀም ራሳቸውን እንዲጠብቁ ብላ የሰጠች ታታሪ ደራሲት በመሆኗ የኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ለበቀለች ቶላ እውቅና እና ሽልማት ሰጥቷቷል።

 

የሴት ደራሲያን ማህበርም ታታሪዋ በቀለች ቶላ ሚዲያ የማያውቃት ግን የሴቶ ተምሳሌት ናት ሲሉ ገልፀዋታል። የኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ዳይሬክተሯ ዶ/ር እልፍነሽ ኃይሌ ሲናገሩ የኢትዮጵያ ሴቶች በበርካታ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፉ አመርቂ ውጤት እንደሚያመጡ ጠቅሰው እንደ በቀለች ቶላ አይነት ደግሞ ራሱን ሸሸግ አድርገው ግን ለሀገርና ለወገን በጎ ተግባር የሚፈፅሙ ሰዎችን ማዕከሉ መሸለሙ እንደሚያስደስታቸው ተናግረዋል።

 

በእለቱ ንግግር ካደረጉት ውስጥ የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ደራሲት የምወድሽ በቀለ ስትገልጽ- በቀለች ቶላን ሚዲያው እያወቃትም፤ ግን የሰራችው ስራ ትልቅ ቦታ የሚያስቀምጣት እንደሆነ ገልጻለች።

 

በሰራቸው ስራ እውቅና እና ሽልማት የተሰጣት በቀለች ቶላም የተሰማትን ደስታ ገልፃ- ወደፊትም የኢትዮያን ብዝሃ ህይወት በመመርመር የምታሳትማቸው መፃህፍት እንዳሉም ገልጻለች። በዚሁ እለት ስለ ደራሲዋ ማንነት እና አበርክቶ በገጣሚ አበበች አማካይነት ጥናት ቀርቧል። በቀለች ቶላ የመጀመሪያ ድግሪ በሶሲዮሎጂ እንዲሁም የማስተርስ ድግሪ ያላት ባለሙያ ነች።

በጥበቡ በለጠ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ የመፃሕፍት ሕትመትና ስርጭት ከነበረበት አዘቅት ወጣ እያለ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን የሚያመለክቱን ጉዳዮች አሉ። ለምሣሌ አያሌ ሰዎች በየመንደሩ እና አደባባዩ መፃሕፍትን ይዘው ሲሸጡ፣ ጎዳና ላይ ዘርግተው ሲሸጡ፣ ሕንፃዎችን ተከራይተው ሲሸጡ፣ አውደ-ርዕይ አዘጋጅተው ሲሸጡ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም በመፃሕፍት ኤግዚቢሽን እና ሕትመት ላይ መሣተፉ፣ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ብሎም የጋዜጣና የመፅሔት አምዶች ለመፃሕፍት ሽፋን መስጠታቸውን ስንመለከት ከቀድሞው የተሻሉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን እንረዳለን።

 

ከዚህ በተለየ ሁኔታ ደግሞ የመጡ ክስተቶችም አሉ። በመፅሐፍት ንባብ ላይ አደጋ ውስጥ የገቡ የአፃፃፍ ርዕሰ ጉዳዮች ይታያሉ። ለምሳሌ የልቦለድ ሥነ - ፅሁፍ አሁን ባለው የመፃሕፍት እንቅስቃሴ አንባቢ የማጣት ድርቀት ይታይባቸዋል። እነርሱን ተከትሎም የግጥም መፃሕፍትም ገበያው ላይ ቀዝቀዝ ያሉ ናቸው። ይሔ ለምን ሆነ ብሎም ማጥናት እና ጉዳዩን ለውይይት ብሎም ለመፍትሔ ማብቃት ያስፈልጋል። ለመሆኑ አሁን በመፅሐፍት ስርጭት ላይ ከፍተኛውን ድርሻ እያገኙ ያሉት ርዕሰ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

 

ከመፅሐፍት አከፋፋዮችና ሻጮች አካባቢ ካገኘኋቸው መረጃዎች አንፃር ፖለቲካዊ መፃሕፍት፣ የፖለቲካ ወግ ያላቸው ርዕሰ ጉዳዮች፣ በተለይ ደግሞ የገዢውን መንግስት የሚተቹ ፅሁፎች እና የታሪክ መፃሕፍት በንባቡ ዓለም ቀዳሚ ምዕራፍ እንዳደያዙ ገልፀውልኛል።

 

በርካታ ጋዜጠኞችና አምደኞች ደግሞ ወደ መፃሕፍት ማሳተም ስራ ውስጥ በመግባታቸው የዘርፉን እንቅስቃሴ አሹረውታል። አሹረውታል ያልኩት ጋዜጣ አንባቢ የነበረውን ሰው ወደ መፃሕፍት ንባብ አምጥተውታል። በጋዜጦችና በመፅሔቶች ላይ ይፅፏቸው የነበሩትን መጣጥፎች ወደ መፃሕፍት ሕትመት ስላመጧቸው ፖለቲካዊ ሞቅታ እና ግለት ያላቸው ስነ -ፅሁፎች እየተበራከቱ መጥተዋል። በእንደዚህ አይነት ጭብጦች ላይ ያተኮሩ መፅሐፍትን በተለይ ከ1960ዎቹ ትግል በኋላ የመጡትን የተወሰኑትን ከዚህ በፊት አጭር ዳሰሳ አድርጌባቸው ነበር። አሁን ደግሞ በዘመነ ኢሕአዴግ ውስጥ የታዩትን ልዩ ልዩ ጉዳዮችን የሚያሳዩ ሥነ -ፅሁፎች በርከት ብለዋል።

 

በዚህ ዘመን ውስጥ ያሉትን አፃፃፎች ለመቃኘት ደፋ ቀና በምልበት ወቅት አዳዲስ መፃሕፍትም እየተደመሩብኝ መጡ። በቅርቡ እንኳን ሙሉዓለም ገ/መድሕን የኢሕአዴግ ቁልቁለት የሚል መፅሐፍ ሲያሳትም፣ አለማየሁ ገበየሁ ደግሞ የረከሰ ፍርድ በሚል ርዕስ መፅሐፍ አሳትሟል። ከዚህ በፊት የታተሙትን ፖለቲካዊ ቃናቸው ጎልቶ የሚታዩትን መፃሕፍት የተቀላቀሉት እነዚህ ሁለቱ መፃሕፍት የራሳቸው የሆነ ልዩነትን ይዘው ነው የመጡት።

 

የሙሉዓለም ገ/መድህን የኢሕአዴግ ቁልቁለት የተሰኘው መፅሐፍ 235 ገፆችን የያዘ እና 14 ምዕራፎችን ያካተተ ነው። እነዚህ ምዕራፎች ዝርዝር ገለፃዎችና ትንታኔዎችን በውስጣቸው የያዙ ሲሆን፣ በስልጣን ላይ ያለውን መንግሥት እንዲሁም ደግሞ በተቃውሞ መስመር ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ፓርቲዎችን ድክመትና ጥንካሬያቸውን የሚያሳይ ነው። ከዚህ አልፎ ደግሞ በተለይ በገዢው ፓርቲ ላይ መራር ሂስ በመስጠት ትልቁን ድርሻ የሚይዝ መፅሐፍ ነው።

 

የሙሉዓለም ገ/መድህን፣ የኢሕአዴግ ቁልቁለት መፅሐፍ ውስጥ የተዘረዘሩት ምዕራፎች ፀሐፊው ከዚህ በፊት በፋክት፣ በአዲስ ጉዳይ እና በሎሚ መፅሔቶች ላይ የፃፋቸውን መጣጥፎች ገሚሶቹን አሻሽሏቸውና የተለያዩ መረጃዎችን አክሎባቸው ሰብሰብ አድርጎ ያሳተማቸው ናቸው።

 

ጋዜጠኛ አለማየሁ ገበየሁ ደግሞ የረከሰ ፍርድ በተሰኘው መፅሐፉ 14 ርዕሰ ጉዳዮችን በ189 ገፅ መፅሐፉ እየዘረዘረ ፅፏል። አለማየሁ ገበየሁ አሁን ኑሮውን በውጭ ሀገር ያደረገ ሲሆን በሀገር ውስጥ ሳለ በጋዜጠኝነቱ እየተዘዋወረ ሲሰራ የገጠሙትን ታሪኮች ከማስታወሻ ደብተሩ ላይ እያጣቀሰ ሰፋ ዘርዘር አድርጎ የፃፋቸው ታሪኮች ናቸው። እርሱ እንደሚለው “ትናንሽ ታሪኮች ደንበኛ ታሪክ ከመሆናቸው በፊት ጋዜጣ ላይ ይሰፍራሉ። ጋዜጣ ላይ ከመስፈራቸው በፊት ደግሞ ጋዜጠኛው ማስታወሻው ደብተር ላይ ይሰፍራሉ። የአንድ ጋዜጠኛ ሀብትም ይሄው ነው። እውነት እላችኋለሁ ጋዜጠኛ ሀብት የለውም፤ ከማስታወሻ ደብተሩ በቀር። እድሜ ያጨራመታትን ማስታወሻ ደብተሬን እንደ ቀልድ ማገላበጥ ጀመርኩ። ያልተከተበ ጉዳይ የለም. . .። . . . እናም . . . ይህችን ማስታወሻ ደብተሬን ለናንተ በማጋራቴ ደስ ብሎኛል” ይለናል።

 

ሙሉዓለም ገ/መድህን ቀደም ሲል በልዩ ልዩ መፅሔቶች ላይ የፃፋቸውን፣ አለማየሁ ገበየሁ ደግሞ ከማስታወሻ ደብተሩ ላይ ያገኛቸውን ትውስታዎች ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ሥነ- ጽሁፍ በተለይም ፖለቲካዊ ዘውግ ወዳላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ተቀላቅለዋል። እርግጥ ነው አለማየሁ ገበየሁ በመፃህፍት ሕትመት የመጀመሪያው ባይሆንም በአዲሱ መፅሐፉ ግን ለየት ባለ ርዕሰ ጉዳይ ቀርቧል።

 

መፃሕፍቶቹ በውስጣቸው የያዙትን ርዕሰ ጉዳይ በአጭሩ ላስረዳ። የሙሉዓለም ገ/መድህን፣ የኢሕአዴግ ቁልቁለት መራር ሃሳቦች የሚንፀባረቁበት፣ በተለይ ደግሞ ገዢው ፓርቲ ለዲሞክራሲና ለሰብዐዊ መብት መከበር ያልቆመ መሆኑን፣ በሀገሪቱ ውስጥ የሚካሔዱ የመብት ጥሰቶችን እና ድርጊቶችን በትንታግ ቃላትና ገለፃ የሚተነትን ነው። የሙሉዓለም ገ/መድህን የሰላ ሂስ በመንግስት ላይ ብቻ አይደለም። በተቃውሞ መስመር ውስጥ ገብተው የረጅም ዘመን የፖለቲካ ትግል የሚያደርጉትንም ፓርቲዎች ይተቻል። የውስጥ አሰራራቸውን፣ ራዕያቸውን እና ያስመዘገቡትን ውጤት እያነሳሳ በሚፈጁ የቃላት ውርጅብኞች ይተነትናቸዋል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ኦነግ /የኦሮሞ ነፃነት ግንባር/ እየተባለ ስለሚጠራው የፖለቲካ ቡድን ከ40 ዓመታት በላይ የተራዘመ ትግል ያደረገው ሀገራዊ አጀንዳ የሌለው በመሆኑ እና ኢትዮጵያንም እንደ ሀገር ለመመልከት ችግር ያለበት በመሆኑ ከስኬቱ ውድቀቱ መብዛቱን ያመለክታል ፀሐፊው። ቀደም ባለው ዘመን ኢትዮጵያዊ ለመሆን መደራደር እንፈልጋለን ይሉ የነበሩት የኦነግ ከፍተኛ አመራር የነበሩት ሌንጮ ለታ፣ ዛሬ ከፓርቲው ራሳቸውን አግልለው ሌላ ፓርቲ መስርተው በተወሰነም ደረጃ ኢትዮጵያዊ የሆነ አጀንዳ ቀርፀው ዳግም ብቅ ማለታቸውም ተአማኒነት የሚያስገኝላቸው እንደማይሆን ሙሉዓለም ገ/መድህን ያስረዳል።

 

ከዚህ በተጨማሪም የቀደመው ትውልድ ማለትም 1960ዎቹ ትውልድ ጥሎት ያለፈው መጥፎ አሻራም በዚህ ዘመን ላይ ላለው ወጣት ትልቅ ሳንካ እንደሆነበትም ይገልጻል። ያለፈው ትውልድ ከውይይትና ከድርድር ውጭ መልስ ይመላለስ የነበረው ከጠመንጃ ላንቃ ከሚንፎለፎሉ አረሮች አማካይነት ስለነበር ዜጎች አለቁ፤ እናቶች አነቡ፤ ትውልድ ተሰደደ፤ ቀሪውም ከፖቲካው መድረክ ራሱን አቀበ። ፍራቻ ነገሰ። አድርባይነት ተስፋፋ። የ40 ዓመት የኢትዮጵያ ፖለቲካ መረጋጋት እንደጠፋበት የሙሉዓለም መፅሐፍ ይገልጻል። ስለ ስደተኛ ፖለቲከኞች፣ ነፍጥ አንስተው ስለሚዋጉ ኃይሎች፣ ከፖለቲካው ዓለም ራሳቸውን ስላገለሉ ሰዎች፣ ስለ ብሔራዊ እርቅ አስፈላጊነት፣ ስለ ነጻው ፕሬስ ሳንካዎችና ሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ዳሷል።

 

ጋዜጠኛ ዓለማየሁ ገበየሁም በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ፅፏል። የሃሳብ መነሻውን ከጋዜጠኛ ማስታወሻ ደብተሩ ላይ እየወሰደ ሥነ - ፅሁፋዊ ገለፃ እና ትርክቶችን በያዙ ቃላት ፅፏል። በተለይ በምርጫ 97 ወቅት እርሱ የመንግስት ጋዜጠኛ ሆኖ በምርጫ ጣቢያዎች እና በድምፅ ቆጠራ ወቅት ያያቸውን እና በማስታወሻ ደብተሩ ላይ ያሰፈራቸውን ሃሳቦቹን እየዘረዘረ አቅርቧል። በስራ አጋጣሚ በተገኘባቸው ስብሰባዎች ላይ የታዘባቸውን አያሌ አስተዳደራዊ እና ስሜታዊ መልሶችን ሁሉ በመፅሐፉ ውስጥ በወግ የአቀራረብ ስልት ይተርካል።

 

በዓለማየሁ ገበየሁ ብዕር ውስጥ ብዙ የትዝብት ሀቆች እንደተገለፁበት ከሚያሳዩን ቦታዎች አንዱ በስብሰባዎች ወቅት የሚነሱ ጥያቄዎችና ከሰብሳቢው አካል ደግሞ የሚሰጡ መልሶች ናቸው። ለምሳሌ ጥቂቶቹን እንይ፤

 

“የኢህአዴግ የፍትህ ስርዓት ሽባ ሆኗል። የሆነ ቦታ ያጠፋ ሰው፤ የሆነ ቦታ የሚሾምበት ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። ዳኞች በነፃነት አይወስኑም፣ ዳኛው ጨክኖ ቢወስንም ወዲያው ፖሊስ ያፈርሰዋል. . .”

 

የሚል ጥያቄ ሲቀርብ የተሰጠው መልስ የሚከተለው እንደነበር መጽሐፉ ይገልፃል፡-

 

“ዳኞችን እያስገደዱና እያስፈራሩ እንዲወስኑ የሚደርግበት አሰራር የለም። ወ/ሮ ብርቱካን ሚድቅሳ ስዬን በነፃ ነው ያሰናበቱት። መንገድ ላይ እንዲያዙ መደረጉ የፍትህ ስርዓቱን የሚቃወም አይደለም። ተፅዕኖ የሚባለው ወ/ሮ ብርቱካን ላይ ተፅዕኖ ተደርጎ በነፃ መልቀቅ የለብሽም ቢባል ነበር” 58

 

 

ሌሎችንም በዚህ አይነት ሁኔታ የተሰጡ ጥያቄና መልሶችን እናነባለን። የጋዜጠኛው የማስታወሻ ደብተሩ ትዝታዎች ናቸው። በርግጥ እንዲህ ባለው መድረክ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችና መልሶች ሙሉ በሙሉ የመንግሥት አቋም ናቸው ስለማይባል፣ በተለይ ደግሞ መድረኩን እንደሚመራው ሰው አስተሳሰብና ችሎታ የሚወሰን ነው። ግን የሚያሳየው የአስተዳደር ክፍተት ደግሞ ሰፊ ነው።

 

እነዚህ ሁለት መፃሕፍት ዋነኛ ጭብጣቸው መንግሥትና ሕዝብ ነው። ያዩትን የታዘቡትን አንዱ በመራር ፅሁፍ ሌላኛው ደግሞ ሥነ-ፅሁፋዊ ቀለም እየቀባባው ጽፈዋል። ሁለቱም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የመፅሐፍት ገበያ ውስጥ ተፈላጊ እየሆኑ ከመጡ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ዘውጋቸውን መሰረት አድርገው ተቀላቅለዋል።

 

አሁን ባለንበት ወቅት የመፅሐፍት ሽያጩ የደራላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ፖለቲካዊ ቃና፣ ፖለቲካዊ ሽሙጥ፣ ፖለቲካዊ ወግ፣ የግል የሕይወት ታሪኮች በተለይ በፖለቲካው መድረክ ውስጥ የነበሩ ሰዎች የሚፅፏቸው መፃሕፍት በተደጋጋሚ እየታተሙ ይሸጣሉ። በአዟሪዎች ተደብቀውና ተሸሽገው የሚሸጡ ዋጋቸውም ውድ የሆኑ የእነ ኤርሚያስ ለገሰ እና ነገደ ጎበዜ መፃሕፍትም አሉ።

 

የበርካታ ጋዜጦችና መፅሔቶች ሕልውና እያከተመ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኞች ወደ መፅሃፍት ሕትመትና ስርጭት ውስጥ እየገቡ በመሆኑ አዲስ የሥነ-ፅሁፍ ዘውግ ኢትዮጵያ ውስጥ እየጎለመሰ መታየት ጀምሯል። ቀደም ሲል ጋዜጦች እና መፅሔቶች ላይ የምናያቸው ፖለቲካዊ እና በተለይ ያለውን ስርዓት በሰላ ሂስ የሚነቅፉ ፀሐፊያን የኢትዮጵያ የመፅሐፍት ህትመት ሂደት ውስጥ ተቀላቅለዋል።

 

ፖለቲካዊ ሥነ-ፅሁፍ በተለይ በውስጡ ተጨባጭ የሆኑ ነገሮችን ከመያዙ አንፃር እና ልዩ ልዩ ትርጓሜዎች ተሰጥቶት ስለሚፃፍ የአንባቢን ቀልብ የመያዝ ችሎታው ትልቅ ነው። ምንም አይነት የፖለቲካ ፓርቲ ባልነበረበት ዘመን እነ ፍቅር እስከ መቃብር፣ አደፍርስ እና ከአድማስ ባሻገር የመሳሰሉ ረጃጅም ልቦለዶች በመጀመሪያ የተወደዱት በውስጣቸው ፖለቲካዊ ትርጓሜ ያሏቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ስለያዙ ነው በሚል ነበር። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ስለ አበባ ደማቅነት፣ ፍካት፣ ስለውቢቷ ወጣት ደም ግባት፣ ተክለ ሰውነት፣ ስለ ደኑ፣ ስለመልክአምድሩ ወዘተ ውበት መፃፍ ብዙ አዋጪ እየሆነ እንዳልመጣ የመፅሐፍት ገበያው ያሳያል። ከዚያ ይልቅ የፖለቲካው ትኩሳት ያጋላቸውና ያሞቃቸው መፃሕፍት መድረኩን እየተቆጣጠሩት ነው።

 

ጋዜጦችና መፅሔቶች እንደ ቀደሙት ዓመታት በሰፊው ገበያ ላይ ባለመኖራቸውና ህልውናቸውም በእጅጉ በመዳከሙ የተነሳ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ሌላ ምዕራፍ እየያዘ በመምጣት ላይ ነው። የተመሰገን ደሳለኝን፣ የአለማየሁ ገላጋይን፣ የሙሉነህ አያሌውን እና የኃይለመስቀል በሸዋም የለህን፣ የአንዷለም አራጌን፣ የርዕዮት ዓለሙን እና የሌሎችንም በርካታ የወቅቱ ፖለቲካዊ መፃህፍትን ስናገላብጥ የምሬት ሥነ-ፅሁፎች በስፋት የታዩበት ዘመነ እየሆነ መጥቷል።

 

በአጠቃላይ ሲታይ በኢትዮጵያ ውስጥ አብዮቱ በ1966 ዓ.ም ከፈነዳ በኋላ ላለፉት 40 ዓመታት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥነ -ፅሁፍ ምን ይመስላል በሚለው ርዕሰ ጉዳይ መነጋገር ይገባል። ከዘመነ ኢሕአፓ በኋላ በርካታ ፀሐፊያን በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን ፖለቲካ እና እልቂት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነበር የፃፉት። በዚህም ሳቢያ መፅሐፍቶቻቸውን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አላነበበም ነበር። አሁን ከቅርብ ጊዜ በኋላ የኢሕአፓን ዘመን ጨምሮ እኛ እስካለንበት ይህ ዘመን ድረስ ስርዓት ተኮር፣ መንግስት ተኮር፣ ፓርቲ ተኮር፣ ትግል ተኮር ወዘተ መፃሕፍት እየመጡ ነው። እስኪ ሳምንትም በአዲሱ የሥነ -ፅሁፍ ዘውጋቸው ላይ ጥቂት ነጥቦችን ለማንሳት ተቀጣጥረን ብንለያይስ? መልካም ሳምንት!። 

በጥበቡ በለጠ


    በኢትዮጵያ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ስማቸው በእጅጉ ጎልቶ ከሚጠሩት ሰዎች መካከል አንዱ ዳሪዮስ ሞዲ ነው። ዳሪዮስ ሞዲ በሬዲዮ ጋዜጠኝነት በተለይም በዜና እና በልዩ ልዩ ዘገባዎች የአፃፃፍ እና የአቀራረብ ቴክኒክ ውስጥ ሙያዊ አስተዋፅኦ በእጅጉ ሰፊ ነው። አያሌዎች በእርሱ የጋዜጠኝነት ተሰጥኦ እና ድምፅ ተማርከው ወደ ሙያው ገብተዋል። በሙያ ውስጥም የነበሩት ከእርሱ ተምረው ራሳቸውን አሳድገዋል። ለመሆኑ የዳሪዮስ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ብቃት መለኪያው ምንድን ነው ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል። በጥቂቱ የተወሰነውን መግለፁ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

     በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ውስጥ ድምፅ ትልቁን ቦታ ይወስዳል። ድምፅ ሲባል የፃፍነውን ወይም የተፃፈልንን ነገር የምናቀርብበት ለዛ ነው። ሬዲዮ በባሕሪው በጆሮ የሚደመጥ በመሆኑ የሚቀርበውን /የሚተላፈውን/ ርዕሰ ጉዳይ እንዲደመጥ የማድረግ ችሎታ ከጋዜጠኛው ይጠበቃል። ጋዜጠኛው በተወሰነ ደረጃ የተፈጥሮ የድምፅ ለዛ ሊኖረው ይገባል። ይህን የድምፅ ለዛውን እንደየሚቀርበው ወሬ፣ ዜና፣ ታሪክ፣ ትረካ ወዘተ እያስማማ የአድማጩን ጆሮ መማረክ አለበት። ቃላት በባሪያቸው ይጠብቃሉ፣ ይላላሉ። ግን የሚላሉትና የሚጠብቁት በውስጣቸው ባሉት ፊደላት ላይ አንባቢው /ጋዜጠኛው/ በሚፈጥረው ድምፀት ነው። ይህን ማወቅና ማቅረብ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት የመጀመሪያው ሀሁ ነው። በዚህ ረገድ ደግሞ ዳሪዮስ ሞዲ አፉን የፈታበት ነው ብሎ መናገር ይቻላል።

     ሌላው ደግሞ ለሬዲዮ ዜናም ሆነ ዘገባ ወይም ታሪክ ሲፃፍ እንደ ጋዜጣ እና መፅሔት ፅሑፎች አለመሆኑን ማወቅ ነው። በጋዜጣና በመፅሔት የሚፃፉ ፅሁፎች አንባቢው በአይኑ እያየ የሚያነባቸውና ካልገባውም ወደ ኋላ ተመልሶ አንብቦ የሚረዳበት፣ የቃሉ ፍቺ ከከበደው መዝገበ ቃላት ሁሉ አምጥቶ የሚረዳበት ነው። ሬዲዮ አድማጭ ግን ካልገባው አልገባውም። ካመለጠው አመለጠው። ወደ ኋላ ተመልሶ የሚረዳበት አጋጣሚ የለም። ስለዚህ ለሬዲዮ አድማጭ የሚፃፉ ስክሪብቶች ቀለል ያሉ ናቸው። ቅለታቸው የሃሳብ ቅለት አይደለም። የአገላለፅ ቅለት ነው። ሁሉም ሰው ሳይቸገር ሊረዳቸው የሚችሉ፣ በሙያ ቃላት ያልታጀቡ፣ እንደ ንግግር፣ እንደ ጨዋታ በጆሮ የሚፈሱ መሆን አለባቸው። የሬዲዮ ጽሁፎች ምንም እንኳን በአይን የማይታዩ ቢሆኑም በጆሮ ሲገቡ ግን ምስል መከሰት እንዳለባቸው የሙያው ጠበብቶች ጽፈውበታል። በዚህ ለሬዲዮ ተብለው በሚፃፉ ጽሑፎች ታሪክ ውስጥም ዳሪዮስ ሞዲ ከፊት ከፊት የሚሰለፍ አንጋፋ ባለሙያ ነበር።

     እኔም ከ15 ዓመታት በፊት የዩኒቨርስቲ ትምህርቴን በማጠናቀቅበት ወቅት የሰራሁት የመመረቂያ ወረቀት በሬዲዮ ጋዜጠኝነት በተለይም በዜና አቀራረብና ንባብ ላይ ያተኮረ ነበር። ይህ የጥናት ወረቀት እንደ ማመሳከሪያ አድርጎ ያቀረበው መረጃ፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ውስጥ በተለይም “ዜና ፋይል” እየተባለ በሚጠራው ፕሮግራም ላይ ነበር። በዚህ በዜና ፋይል ውስጥ የተፃፉ ዜናዎችን በምመረምርበት ወቅት በርካታ ጠንካራ ጎኖችን አግኝቼ ነበር። ለምሳሌ በሌሎች ጋዜጠኞች የተፃፉ ዜናዎችን በብዛት ያርም /የአርትኦት/ ስራ ይሰራ የነበረው ዳሪዮስ ሞዲ ነበር። ዜናዎችን ያረመበት እና አስተካክሎ የፃፈበት መንገድም የሬዲዮ ዜና አፃፃፍ ቴክኒኮችን በሚገባ የተከተሉ እንደነበሩ በጊዜው ለማወቅ ችያለሁ። በጥናቴ ውስጥም በዝርዝር ተካቷል። ስለዚህ ዳሪዮስ ሞዲ በኢትዮጵያ የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

     ግን ይህን ሁሉ መዘርዘር ሳያስፈልግ የዳሪዮስ ሞዲን አስገምጋሚ የሬዲዮ ድምፅ በመስማት ብቻ ብዙ መናገር ይቻል ነበር። ዳሪዮስ ሞዲ ዜና ሲያነብ አድማጩን ሁሉ ቁጭ አድርጎ፣ የሚጓዘውም ቆሞ እንዲያደምጠው የማድረግ ኃይል አለው።

ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት የመሩት ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ባልተጠበቀ እና ባልታሰበ ሁኔታ ከሀገር የመውጣታቸውን ዜና ለሚሊዮኖች ያበሰረው (ያረዳው) ዳሪዮስ ሞዲ ነው። ዜናው የቀረበው ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ነበር። ዳሪዮስ የሚከተለውን አነበበው፡-

“ለረጅም ዓመታት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲካሔድ የነበረው የርስ በርስ ጦርነት ያስከተለውን የኢትዮጵያዊያን ህይወት መጥፋትና ከኑሮ መፈናቀል ለማስቀረት በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም። ይልቁንም ወደ ባሰ ደረጃ እየተሸጋገረ በመሔድ ላይ ይገኛል። ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቆምና ሰላምም እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከስልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዚዳት መንግሥቱ ኃይለማርያም ከስልጣቸው ወርደው ከኢትዮጵያ ውጪ ሔደዋል። “

        ይህን ዜና ያነበበው የአስደማሚ ድምፅና ላዛ ያለው ዳሪዮስ ሞዲ ነበር። ዜናው በእጅጉ አስደንጋጭ ነበር። “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” እያሉ የፈከሩት መንግሥቱ፣ “አንዲት ጥይት እና ሰው እስከሚቀር እንዋጋለን!” ያሉት መንግሥቱ፣ “ማዕረጋቸውን ቆርጥን፣ ቂጣቸውን በሳንጃ ወጋን!” ያሉት መንግሥቱ፣ “ቀኝህን ለመታህ ግራህን ስጠው የሚለው አባባል የሚያስቃቸው መንግሥቱ፣ “ኢትዮጵያ ትቅደም እያሉ በወኔ የሚናገሩት መንግሥቱ፣ ከአብዮታዊ መሪያችን ቆራጥ አመራር ጋር ወደፊት የተባለላቸው መንግስቱ፣ አገር ጥለው ሔዱ ሲባል ያስደነግጣል። ለዚያውም የት እንደሔዱ እንኳን አይታወቅም ነበር። የኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ በእጅጉ አሳሳቢ ነበር። ጦርነት ከሰሜን ኢትዮጵያ በብርሃን ፍጥነት ወደ ታች እየተጓዘ ነው። እናም ዳሪዮስ ሞዲ በነበልባል ድምፁ ይህን ዜና በማቅረቡ ታሪካዊ ሰው እንዲሆንም አድርጎታል። ለመሆኑ ዳሪዮስ ሞዲ ይህን ዜና እንዴት አነበበው ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል። በአንድ ወቅት “ኢትዮጵ” በመባል ትታወቅ የነበረችው መፅሔት ግንቦት ወር 1994 ዓ.ም የሚከተለውን ቃለ-ምልልስ ከዳሪዮስ ጋር አድርጋ ነበር።

ኢትዮጵ፡- ዳሪዮስ ያንን ዜና ስታነበው ፍርሃት አልተሰማህም?

ዳሪዮስ፡- ለምን ትንሽ ሰፋ አድርጌ አልገልፅልህም፤ በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የነበሩት አቶ አብዱልሐፊዝ ዩሱፍ ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማርያምን ወደ ቢሯቸው ያስጠሩታል። ጌታቸው ያኔ የቅርብ አለቃዬ ነበር። ጌታቸው ከሚኒስትሩ ቢሮ ተመልሶ እንደመጣ “ቆይ ከዚህ እንዳትሄድ” አለኝ። “ለምን” ስለው “የሚነበብ ዜና አለ” አለኝ። “እኔ እኮ ተረኛ አይደለሁም አልኩት። “አይ አንተ ነህ የምታነበው” አለኝ። እና በዚያው አነበብኩት።

ኢትዮጵ፡- ዜናው ምን እንደሆን አስቀድሞ አልተነገረህም?

ዳሪዮስ፡- በፍፁም! እንኳንስ እኔ፣ ጌታቸው ራሱ ያወቀ አልመሰለኝም። ብቻ በቃ “የሚነበብ ዜና አለ” ነው የተባልኩት። ስድስት ሰዓት ሲደርስ ስቱዲዮ ገባሁ። ያኔ ወረቀቱን ሰጠኝ። “ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ሲባል ከሀገር እንዲወጣ ተደርጓል” ይላል።

ኢትዮጵ፡- አልደነገጥክም?

ዳሪዮስ፡- በጭራሽ! እንዲያውም እውነት ለመናገር ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ። ልክ አንብቤ እንደጨረስኩ “አሁን ወደምትፈልግበት መሔድ ትችላለህ ተባልኩ”።

    ዳሪዮስ ሞዲ ለበርካታ የሬዲዮ ጋዜጠኞች መፈጠር እንደ ማንቂያ እና መቆስቀሻ ሆኖ አገልግሏል። ነጋሽ መሐመድ፣ ዓለምነህ ዋሴ፣ ቢኒያም ከበደ፣ ደረጄ ኃይሌን የመሳሰሉ ጎበዝ የሬዲዮ ጋዜጠኞች ሞዴላቸው ዳሪዮስ ነበር።

የዳሪዮስ ሞዲ ልዩ መገለጫ ናቸው ከሚባት ውስጥ ለልጆቹ የሚያወጣላቸው ስም ነው። ስማቸው ከወትሮው ስም ለየት ያለ፤ አንዳንዴም ደንገጥ የሚያደርግ ነበር። በዚሁ ዙሪያ የዛሬ 13 ዓመት 1994 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ከወጣው ኢትዮጵ መፅሔት ላይ የሰፈረውን ባወጋችሁስ፡-

ኢትዮጵ፡- ዳሪዮስ ለልጆችህ የምትሰጠው ስም አስገራሚ ነው ይባላል። የሰሙ ሰዎች ለማመን ያቅታል ነው የሚሉት።

ዳሪዮስ፡- ለምን ያቅታቸዋል?

ኢትዮጵ፡- አስገራሚ ስለሆነ ነዋ!

ዳሪዮስ፡- ምን የሚገርም ነገር አለውና?

ኢትዮጵ፡- እስኪ ለምሳሌ ከልጆችህ ስሞች መካል አንዱን ጥቀስልኝ?

ዳሪዮስ፡- ቼ ጉቬራ

ኢትዮጵ፡- እሺ ሌላስ?

ዳሪዮስ፡- ትግል ነው።

ኢትዮጵ፡- የምርህን ነው ዳሪዮስ?

ዳሪዮስ፡- አዎና! ትግል ነው ዳሪዮስ።

ኢትዮጵ፡- ከሴቶቹ መካከል ለምሳሌ?

ዳሪዮስ፡- አምፀሸ ተነሺ!

ኢትዮጵ፡- እየቀለድክብኝ ነው?

ዳሪዮስ፡ ቀልድ አልወድም! “አምፀሸ ተነሺ ዳሪዮስ” ብዬሀለሁ።

ኢትዮጵ፡- እና አሁን ይሄ እውነት የልደት ስማቸው ነው? ትምህርት ቤትም በዚሁ ነው የሚጠሩት?

ዳሪዮስ፡- ስማቸው እኮ ነው!

     ዳሪዮስ ሞዲ ላመነበት ነገር እስከ መጨረሻው ድረስ በአቋሙ ፀንቶ የመቆየት ብቃት ያለው ጋዜጠኛም ነበር። ይህንን ፀባዩን የሚያሳይልን ደግሞ በአንድ ወቅት የተከሰተው ሁኔታ ነው። ጉዳዩ፣ አንድ ሰው የማይወዳቸው ምክትል ምኒስትር ከስራ ቦታቸው በእድገት ይቀየሩና ወደ ሌላ መስሪያ ቤት ይዘዋወራሉ። ታዲያ በዚህ ወቅት ሰራተኛው መዋጮ አድርጎ የአሸኛኘት መርሃ ግብር ያደርጋል። ዳሪዮስ ግን አስገራሚ ነገር ፈፀመ። ታሪኩን ከኢትዮጵ መፅሔት ጋር እንዲህ ተጨዋውቶታል፡-

ኢትዮጵ፡- ለምክትል ሚኒስትሩ መሸኛ ከሰራተኛው ገንዘብ ሲዋጣ አስር ሳንቲም ብለህ ሊስቱ ላይ ሞልተሃል ይባላል።

ዳሪዮስ፡- አይ ተሳስተሃል. . .!! አምስት ሳንቲም ነው ያልኩት። ግን እኮ ታዲያ ለበቀል አይደለም። እንደውም ከኔ በላይ የተጎዱ ሰዎች ነበሩ። እነዚያ ሰዎች ከአቅማቸው በላይ አዋጥተዋል። ይህንን ሳይ ተናደድኩና አምስት ሳንቲም ብዬ ሞላሁ። “ቦቅቧቆች! ያንን ያደረኩት።

ኢትዮጵ፡- ሚኒስትሩ ተናደው ወደ ቢሮህ ድረስ መጥተው ሳንቲሟን አፍንጫህ ላይ ወርውረው ሔዱ የተባለውስ?

ዳሪዮስ፡- ውሸት ነው። ምክንያቱም እኔ ሳንቲሟን ገቢ አላደረኩም። አምስት ሳንቲም ብዬ ከስሩ ሌላ ነገር ፃፍኩበት።

ኢትዮጵ፡- ምን ብለህ?

ዳሪዮስ፡- ከደሞዜ ላይ የሚቆረጥ!

    እንዲህ አይነት የሚያስቁ የሚያስገርሙ ድርጊቶችና ገጠመኞች ያሉት ዳሪዮስ ሞዲ፣ በሬዲዮ የጋዜጠኝት ታሪክ ውስጥ ሙያውን ጠንቅቆ የሚያውቅና በስራውም እንከን የማይገኝበት ጋዜጠኛ እንደነበር አብረውት የሰሩ ሁሉ ይመሰክራሉ።

ዳሪዮስ ሞዲ ገና ስራ በያዘበት ወር 1964 ዓ.ም የመጀመሪያ ደሞዙን እንዳገኘ ውብ ከነበረችው ባለቤቱ ከመሳይ ጋር ጋብቻ ፈፀመ። ላለፉት 43 ዓመታትም ዳሪዮስና መሳይ ፍቅርና ደስታ የተሞላበት ሕይወት ከልጆቻቸው ጋር አሳልፈዋል። ነገር ግን የዛሬ አራት ወር ባለቤቱ መሳይ አረፈች። ከሰሞኑ ደግሞ ይሔው የነጎድጓዳማና የነበልባል ድምፅ ባለፀጋው ዳሪዮስ ሞዲ ተከተለ።

     ብዙዎች የሬዲዮ ጋዜጠኞች በሞት ያጣነው ዳሪዮስ ለሙያው ት/ቤት ሆኖ አገልግሏል ባይ ናቸው። ባለፈው እሁድ የቀብር ስነ-ስርዓቱ ሲከናወን የዳሪዮስን የህይወት ታሪክ የፃፈውና ያነበበው ጋዜጠኛ ቢኒያም ከበደ ነበር። በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ውስጥ ዳሪዮስን ተካተዋል ከሚባሉት ውስጥ ቢኒያም ከበደ አንዱ ሲሆን፣ እሱም የዳሪዮስን ታሪክ እንዲህ ፅፎ እየተንሰቀሰቀ አነበበው፡-

የተፃፈለትን ያላነበበ ጋዜጠኛ

     “ጋሽ ዳሪዮስ ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን የጋዜጠኞች አባትም ነበረ። ይሄ ታሪክ ብቻ ሊሆን ይችላል። ነበር ቅርብ ነው። ነበር እያልን ዳርዮስን ብቻ ሳይሆን ሙያውንም አብረን እንቅበረው።

     በፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ፎቶ ቤት ሞሪስ እልቪስን የከፈቱት የሚስተር ሞዲ ጉስታቭ ልጅ ነው፤ ዳሪዮስ ሞዲ። በትውልድ ፐርሺያዊ በዜግነት እንግሊዛዊ ከሆኑት ከሚስተር ጉስታቭ እና ከወ/ሮ አማረች መኩሪያ ታህሳስ 12 ቀን 1939 ዓ.ም እዚያው ራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ተወለደ። የድርሰትና የግጥም ዝንባሌ የነበረው ዳሪዮስ ሞዲ ማንበብ፣ ሁኔታዎችን በጥልቀት ማስተዋልና መመርመር የጀመረው ከልጅነቱ ጀምሮ ነው።

     በኢትዮጵያ ስር ነቀል ለውጥ እንዲመጣ ሲታገሉ ከነበሩት ተማሪዎች በተለይም ከጥላሁን ግዛው ጋር ለአንድ አላማ ተሰልፈው በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ላይ ቢቆይም የጥላሁን ግዛውን መገደል ተከትሎ ድርጊቱን በፅኑ ካወገዙት አስር ጓደኞቹ ጋር የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ጥሎ ወጥቷል። ዘመኑም 1962 ዓ.ም ነበር። በወቅቱ በነበረው መንግሥት አመለካከቱ ያልተወደደለት ዳሪዮስ፣ ድፍን ሁለት ዓመት ሙሉ ስራ የሚቀጥረው አላገኘም ነበር። ይሁንና በግሉ የትርጉም ስራዎችን ይሰራ ስለነበር በ1964 ዓ.ም በብስራት ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ ለመቀጠር ምክንያት ሆነው። ህይወቱ መስመር ያዘ፡-

በመልካም ፀባይ እና ባህሪዋ የቁንጅና ጣሪያ ከሆነችው መሰረት ኃይሌ /መሳይ/ ጋር ትዳር መሰረተ። ትዳሩም ፀንቶ አራት ወንድ ልጆችን እና ሶስት ሴት ልጆችን አፈራ።

     ዳሪዮስ ሞዲ ለሬዲዮ የተፈጠረ ምሉዕ በኩልዔ የሆነ ጋዜጠኛ ነበረ። ተስምቶ የማይጠገብ፣ እያነበበ የሚስረቀረቅ የሬዲዮ ሞገድን የሚገዛ ባለግርማ ድምፅ የታደለው ዳሪዮስ ሞዲ፣ ከዜና ባህሪው ተነስቶ አነባነቡን የሚከተል እንከን አልባም ዜና አንባቢ ነበር። መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር የሚሉት ጎልቶ ይደመጥላቸው ዘንድ የሚዲያው ልሳንና የድምፅ ሞገድ ዳሪዮስ ነበር። እንደየጊዜው የአዳዲስ ምዕራፍ መሸጋገሪያ ድልድይ ድምፅ ሆኖም አገልግሏል። እስከ ዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ሚዲያ ስራ ውስጥ እንደ ዳሪዮስ አይነት የትርጉም ጌታ አልተገኘም። ዳሪዮስ ዘንድ በይመስለኛል እና ይሆናል በሚል አቻ ትርጉም አይገኝም። የቀደምት አባቶቹን መዝገብ እየፈተሸ፣ ለዘመናዊው አለምም እንዲስማማ የራሱንም የትርጉም መንገድ እየፈለገ የሚማስን የቃላት ዲታ እና ታላቅ ሙያተኛ ነበር። የራሱን ትርጉም የሕዝብ ቋንቋ ማድረግ የቻለ፣ የቋንቋ ምሁራንም ደግመው ደጋግመው የሚመሰክሩለት የትርጉም መምህር ነበር። አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያኒኛ የመተርጎም ብቃት የመነጨው ካልተቋረጠ የንባብ ብቃቱ ነው።

     ስራው ላይ እንዳቀረቀረ እስከወዲያኛው ያንቀላፋው ይህ ሰው በቁሙ አስታውሶ፣ ሙያዊ ልቀቱን መዝኖ መሸለም ባልተለመደበት ሀገር እንደዋዛ ኖሮ ማለፉን ለምናውቅ ለኛ የእግር እሳት ነው።

     በብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ የጀመረው የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ሕይወቱ በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለ30 ዓመታት ቢቀጥልም ይከፈለው የነበረው ደሞዝ የሰውየውን አስደናቂ ችሎታና የሙያ ልቀት የሚመጥን ቀርቶ ለወር አስቤዛ የማይበቃ ነበር። እንዲህም ሆኖ ህይወት ለዳሪዮስ ሬዲዮ ነው። ጡረታም ወጥቶ የናፈቀውን ሬዲዮ ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን በሸገር እና በሬዲዮ ፋና ቀጥሎበት ቆይቷል።

     ዳሪዮስ ሞዲ ወር ጠብቆ ከሚያገኘው ከሶስት አሃዝ ባልበለጠ ደሞዝ ራሱን እና ቤተሰቡን ለማስተዳደር ቢቸገርም ያን ወርቃማ ድምፁን ግን ለማስታወቂያ ለማዋል፣ ማስታወቂያ ሊሰራበት ግን ፈቃደኛ አልነበረም። ዜና ላይ የሚሰማ ድምፅ እንዴት ሆኖ ሸቀጥ ይተዋወቅበታል ሲል ይሞግታል። ይህ በራሱ የሙያውን ሥነ-ምግባር መጣስ ነው ሲል ለሙያው መርህ እና ልዕልና አጥብቆ ይከራከራል።

     የመጨረሻዎቹ ሶስት ዓመታት ለዳሪዮስ ጥሩ አልነበሩም። ለዘመናት ማልዶ ከስራው ገበታው የማይታጣው ዳሪዮስ ህመም ደጋገመው። እንደ ልብ መተንፈስ ተሳነው። በኦክሲጅን እየተረዳ ቆየ። ዳሪዮስ የልብ ትርታው ቀጥ የምትል የምትመስለው ኦክሲጅን ሲያጣ ብቻ አልነበረም። ካላነበበና ዜና ካልሰማ እስትንፋሱ ያለ አይመስለውም።

ጋሽ ዳሪዮስ ሰውን ቶሎ የማይቀርብና ከቀረበም የእድሜ ልክ እውነተኛ ወዳጅ የሚሆን፣ ትሁት ደግ እና እውቀቱን ያለ ስስት የሚሰጥ ታማኝ ሰው ነበር።

እንደው በቀዝቃዛው በክረምቱ ሰሞን

እንከተላለን አንድ ጎበዝ ቀድሞን

አይ ጉድ መፈጠር ለመሰነባበት

ዳሪዮስን መቼም ማንም አይደርስበት

ሮጥን ሮጥን የትም አልደረስንም

ማን ይከተለዋል ውድ ዳርዮስን

ብለን ለመሰነባበት ከእግዚአብሔር አስገራሚ ስራ አንዱን እንደ ማሳረጊያ እንይ።

     ለ43 ዓመታት ከጎኑ ያልተለየችው፣ ለትዳሯም ለልጆቿም ህልውና የደከመችው፣ ልጆቿ እንኳን አይተዋት ስሟ ሲጠራ የሚንሰፈሰፉላት መሳይ፣ ልክ የዛሬ አራት ወር ከሁለት ቀናት ታማ አርብ እለት ሆስፒታል ገባች። ዳሪዮስም ለመጨረሻ ጊዜ ሆስፒታል የገባው በዕለተ አርብ ነበር። አርብ ለቅዳሜ አጥቢያ ከሌሊቱ 11 ሰዓት በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ባለትዳሮቹ ነፍሳቸው ተለየች። ልክ እንደዛሬው በዚህ ስፍራ መሳይን ሸኘናት። ዳሪዮስ ተከተላት። አርብ፣ ቅዳሜ እሁድ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ይህችን አለም ተለዩ።”

     እኛም የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አባላት በጋዜጠኛ ዳሪዮስ ሞዲ ሞት የተሰማንን ሀዘን እየገለፅን፣ ለቤተሰቡ፣ ለልጆቹ እና ለመላው አድናቂዎቹ መፅናናትን እንመኛለን።

በጥበቡ በለጠ

     በኢትዮጵያ የሙዚቃ ዓለም ውስጥ በተለይ በድምፃዊያን ተርታ ስናስቀምጥ ጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ መሐሙድ አሕመድ. . . እያልን መዘርዘራችን የተለመደ ነው። በተለይ መሐሙድ ደግሞ የጓደኞቹ የጥላሁን ገሠሠ፣ የብዙነሽ በቀለ አድናቂ እና ወዳጅ በመሆኑ ለራሱ ዝናና ክብር ብዙም ሳይጨነቅ ረጅም ጊዜ አሳልፏል። መሐሙድ የጥላሁን ገሠሠ ስም ሲጠራ ቀድሞ የሚገኘው እሱ ነው። ለጥላሁን ግንባሩን የሚሰጥ የምን ግዜም ወዳጁ ነው።

     በ1995 ዓ.ም በኢግዚቢሽን መአከል 50ኛ ዓመት የመድረክ ዘመን ለጥላሁን ገሠሠ ሲከበር ዋነኛው ተደሳች መሐሙድ ነበር። በእያንዳንዱ የፕሮግራም እንቅስቃሴ ውስጥ መሐሙድ ነበር። ስለ ጥላሁን ገሠሠ መሐሙድን ጥያቄዎች እቅርቤለት ነበር። ስለ ጥላሁን ገሠሠ ካጫወተኝ ውስጥ የማልረሳው ጉዳይ አለ።

     “ጥላሁን ገሠሠ የአደራ ጓደኞዬና ወንድሜ ነው” ሲል ገልፆልኛል መሐሙድ። ጉዳዩ እንዲህ ነው፡-

     ጥላሁን እና መሐሙድ አንድ ቀን ወደ ወሊሶ ይሄዳሉ። ወሊሶ ውስጥ የጥላሁን አያት ይኖራሉ። ከአያቱ ጋር ሲጫወቱ ውለው ወደ አዲስ አበባ ሊመጣ ሆነ። በዚህ ግዜ ጥላሁን ከሰዎች ጋር ሲያወራ፣ አያቱ መሐሙድን ወደ ጓሮ ወስደውት ከመሬት ላይ ሳር ነጭተው በእጁ አሲዘውት እንዲህ አሉት፡-

“ጥላሁን ገሠሠ ወንድምና እህት የለውም። ያለኸው አንተ ነህ። አደራ ሰጥቼሃለሁ። በምድር የሰጠውክን በሰማይ እጠይቅሃለሁ” ብለውት አደራ ለመሐሙድ ሰጡት።

     ጥላሁን ገሠሠ ይህን አደራ አያውቅም። መሐሙድም ነግሮት አያውቅም። ግን ሁል ጊዜ ጥላሁን ባለበት ቦታ ሁሉ መሐሙድ አለ። የአደራ ወንድሙ፣ የአደራ ጓደኛው ነበር።

     መሐሙድ አሕመድ ጥላሁን ገሠሠን እያነገሰ በመኖሩ እርሱን የሚያየው ጠፍቶ ነበር። የዛሬ ዓመት ግድም በሬዲዮ ፋና በአዲስ ጣዕም የሬዲዮ ዝግጅት ክፍል ይህን ድምፃዊውን በተመለከተ ሰፊ ፕሮግራም ተሰርቶ ነበር። በተለይ የሐገራችን ዩኒቨርስቲዎች ለበርካታ ታዋቂ ሰዎች የክቡር ዶክትሬት ድግሪ ሲሰጡ መሐሙድ አሕመድ እንዴት ይዘነጋል በሚል ርዕስ የከያኒውን ፕሮፋይል ጥልቀት ባለው መልኩ ሰርቶ አየር ላይ አውሎት ነበር።

      ልክ በዓመቱ ደግሞ ከሰሞኑ የክቡር ዶ/ር ሼህ መሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ይህን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ሌጀንድ አክብረው የሚገባውን ማዕረግ አሳይተውታል። በኢትዮጵያ ታሪክ ላበረከተው የኪነ- ጥበብ ስራ በአደባባይ አምስት ሚሊዮን ብር የተሸለመ ከያኒ የለም። መሐሙድ የልፋቱን ዋጋ ተክሷል።

     ይህን መርሃ ግብር እውን እንዲሆን ላመቻቹ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል። በርግጥ በዚህ በሸራተን ሆቴል በተካሔደው መርሃ ግብር በአዘጋጆቹ ስለ መሐሙድ አሕሙድ የጥበብ አበርክቶ አጭር ዶክመንተሪ ቢቀርብ እና ስራዎቹና ማንነቱም በዝርዝር ቢነገር ጥሩ ነበር። ወደፊትም በሕይወት እያለ የሕይወት ታሪኩ በመፅሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ ቢቀርብ በ70ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ያለውን መሐሙድን ይበልጥ ህያው ያደርገዋል።

      የመሐሙድ ስም ሲጠራ አብረው ብቅ የሚሉት ዘፈኖቹ አያሌ ናቸው።

“ካንቺ በቀር ሌላ ብሞት አልመኝም

ግን እስከ አሁን ድረስ አላወቅሽልኝም”

ብሎ የዘፈነልን መሐሙድ ኢትዮጵያንም እየዞረ ስለ ከተሞችና ነዋሪዎቻቸው አዚሟል።

“የድሬ ልጅ ናት የከዚራ

ስለ ውበቷ ስንቱን ላውራ

የሀረር ልጅ ናት የአዋሽ ማዶ

ልቤ ተጨንቋል እሷን ወዶ”

ሲል፤ አይደለም የሐረርና የድሬ ልጅ፣ መላው ኢትዮጵያ ከርሱ ጋር ያውረገርጋል።

“የዘገየሽበት ምን ይሆን ምክንያቱ

አይኖቼ ተራቡ ደረሰ ሰዓቱ”

ሲለንማ የፍቅር ሐድራዎች በሙሉ ጓዛቸውን ሰብስበው ይሰፍሩብናል።

     ሐገሩን ለቆ በውጭው ዓለም የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ በያለበት እየዞረ መሐሙድ እንዲህ ይለዋል።

“መቼ ነው?

ዛሬ ነው?

ሀገሬን የማየው?

ኢትዮጵያን የማየው?”

እያለ ያዜማል። አብሮ ያለቅሳል።

     አጉል ነገር ጀመርኩ። የመሐሙድን ሙዚቃዎች ተንትኜ መጨረስ አልችልም። ግን ለአሁን የዛሬ ዓመት በአዲስ ጣዕም የሬዲዮ ዝግጅት ላይ ከቀረበው የመሐሙድ ፕሮፋይል ጥቂቱን ባቋድሳችሁስ?

     ታላቁ የሙዚቃ ሰው መሐሙድ አሕመድ ኒውዮርክ አሜሪካ ውስጥ ልኬ የዛሬ ዓመት ኮንሰርት እንዲያቀርብ ፕሮግራም ተይዞለት ነበር። ኮንሰርቱን ያዘጋጁለትም አካላት በወቅቱ ትልልቅ ማስታወቂያዎችን በየከተሞች እና በድረ-ገፆች ጭምር ይሰሩለት ነበር። ማስታወቂያዎቹ እንደሚገልጹት ከሆነ ደግሞ ታላቁ የአፍሪካ አንጋፋ ድምፃዊ ሙዚቃዎቹን ሊያቀርብ ነው፤ በማለት ደረጃውን ከኢትዮጵያ አውጥተው በአፍሪካ ደረጃ አስቀምጠውት ነበር። በዚሁ በኒውዮርክ ሬድ ሁክ፣ ቦርክሌይ ውስጥ በሚቀርበው የመሐሙድ አሕመድ ኮንሰርት ቀደም ብለው አዘጋጆቹ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መሐሙድ ከአፍሪካ ምድር ከተገኙ ምርጥ ድምፃዊያን መካከል አንዱ መሆኑን ዋቢ እየጠቃቀሱ ይናገሩ ነበር። ይህን ኮንሰርት ያዘጋጁለት ድርጅቶችም መቀመጫቸውን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያደረጉት “ዘ ኢሹ ፕሮጀክት ሩም” እና “ፓዮኒየር ዎርክስ ፎር አርትስ” የተባሉ ድርጅቶች ናቸው። እነዚህ ሁለቱ አለማቀፍ ድርጅቶች ልክ የዛሬ ዓመት ባወጡት መግለጫ፣ መሐሙድ አሕመድ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ “ወርቃማ ዘመን” እየተባለ በሚጠራው ከ1950 ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ እስከ ስልሳዎቹ አጋማሽ ድረስ በታየው ድንቅዬ ዘመን ላይ፣ እንደ ከዋክብት ሲያበሩ ከነበሩ የሙዚቃ ሰዎች መካከል አንዱ እንደሆነም ገልጸውለታል።

     ከሀምሳ ዓመታት በላይ ከመድረክ ላይ ሳይወርድ፣ መድረክን ለረጅም ሰዓታት እየተቆጣጠረ ጡዑመ ዜማዎችን ሲያንቆረቁር የኖረው መሐሙድ አሕመድ፣ በአፍሪካ የጥበብ መድረክ ላይ በሕይወት ያለ ባለታሪክ /A Living Legend/ በማለት አዘጋጆቹ ጠርተውታል።

     ስለ መሐሙድ አሕመድ የሙዚቃ ክህሎት፣ ተሰጥኦ እና አቀራረብ እየዘገቡ ያሉት የሙዚቃ ልሂቃን እንደሚናገሩት ከሆነ፣ መሐሙድ የሀገሩን የኢትዮጵያ ሙዚቃ በልዩ ልዩ መድረኮች ላይ በማቅረብና እናት ሀገሩን ኢትዮጵያን በጥበቡ ዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ወደር የማይገኝለትን አስተዋፅኦ ማድረጉን ይናገራሉ። አሁንም እንኳን በ70ዎቹ የእድሜ አጋማሽ ላይ ሆኖ ካለምንም የትንፋሽ መቆራረጥ መድረክ ላይ ሆኖ እየዘፈነ፣ እየተውረገረገ፣ እየጨፈረ፣ እየተረከ . . . የጥበብ መንፈስን የሚያረካ ተአምረኛ ከያኒ እንደሆነም አስመስክሯል።

      መሐሙድ አሕመድ የሚዘፍናቸው ጥዑመ ዜማዎች ከኢትዮጵያ አፈርና ነብስ ያልተወለዱትን አውሮፓውያንን ሳይቀር የሚማርኩ እንደሆኑም እማኝ እየጠቀሱ መናገር ይቻላል። ድምፁ እና የአቀራረብ ቃናው ለአውሮፓ የሙዚቃ አፍቃሪዎችም ጆሮ ግቡ ሆኖ እንደሚያስደስታቸው ይወሳል። በዚህም የተነሳ እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም የዓለም አቀፉን የቢቢሲ ሬዲዮ ጣቢያን ሽልማት፣ በምርጥ ድምጻዊነት ተመርጦ የሽልማት አክሊል የደፋ ከያኒ ነው። በዚህም ሽልማት የተነሳ መሐሙድ ዓለማቀፋዊ እውቅናው እየገዘፈ መጣ። በልዩ ልዩ ሀገራት ውስጥ መሐሙድ ሙዚቃ ያቀርባል ከተባለ ጥቁሩም ነጩም እኩል ተጋፍቶ በመግባት በዝግጅቱ ላይ ይታደማል። በቢቢሲ ሬዲዮ ጣቢያ ምርጥ ድምጻዊና ከያኒ ተብሎ የተመረጠ ስለሆነ ዝናው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።

     ወደዚህች ዓለም በ1934 ዓ.ም የመጣው መሐሙድ አሕመድ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በሙዚቃ ምትሃት እንደተለከፈ ይናገራል። በትምህርት ቤት ውስጥ ሆኖ ያዜማል። ትምህርቱንም አቋርጦ በሊስትሮ ስራ በተሰማራበትም ወቅት ያዜማል። ሙዚቃ ከደሙና ካጥንቱ ብሎም ከመንፈሱ ጋር የተዋሃደችው ገና በጨቅላ እድሜው ጀምሮ እንደሆነ መሐሙድ ይናገራል።

     ቀጥሎም አሪዞና ተብሎ በድሮ አራዶች ዘንድ ይጠራ በነበረው ጭፈራ ቤት /ናይት ክለብ/ ውስጥ በአስተናጋጅነት ይቀጠራል። ይህ አሪዞና ተብሎ የሚጠራው ክለብ ከ1955 ዓ.ም በፊት ታዋቂ ቤት ነበር። የሚገኘውም መድሐኒአለም ት/ቤት ፊት ለፊት ሲሆን፣ ቤቱም የራስ ኃይሉ ቤት እንደሆነም ይወሳል። እዚያ ቤት በአስተናጋጅነት የተቀጠረው መሐሙድ፣ አንድ ቀን የክለቡን ኃላፊ ይለምነዋል።

     “እባክህ ከነዚህ ድምጻዊያን ጋር አንድ ዘፈን ልዝፈን? እባክህ ፍቀድልኝ” እያለ ይማፀነዋል።

     ታዲያ አንድ ቀን ኃላፊው ፈቀደለት። መሐሙድም አዜመ። በተፈጥሮ የተሰጠውን የሙዚቃ ፀጋ አሳየ። ሁሉም ታዳሚ አድናቆቱን ገለፀለት። ደጋግሞም ማዜም ጀመረ። ታዲያ አንድ ቀን፣ የክቡር ዘበኛ ሙዚቃ ኃላፊዎች አሪዞና ክለብ ሊዝናኑ ይመጣሉ። መሐሙድ አሕመድ የተባለ ድምፃዊ የነ ጥላሁን ገሠሠን ዘፈኖች ልዩ በሆነው የድምፅ ለዛው ያቀነቅናቸዋል። የክለቡንም ታዳሚ ቁጭ ብድግ ያደርግበታል። በድምፁና በአቀራረብ ችሎታው የተማርኩት ክቡር ዘበኞች በታህሳስ ወር 1955 ዓ.ም መሐሙድን ከአሪዞና ክለብ ማርከው ወደ እነርሱ የሙዚቃ ካምፕ አስገቡት። ከዚያች ቀን ጀምሮ ኢትዮጵያም በሙዚቃው ዓለም የሚያስከብራትን የወርቃማ ድምፅ ባለፀጋውን መሐሙድ አሕመድን አገኘች።

      ወደ ክቡር ዘበኛ ሙዚቃ የተቀላቀለው መሐሙድ አሕመድ፣ እዚያም ጥላሁን ገሠሠንና ብዙነሽ በቀለን የመሳሰሉ ተአምረኛ ድምፃዊያንን አገኘ። እንደ ኮ/ል ሳህሌ ደጋጎ እና ተዘራ ኃይለሚካኤልን የመሳሰሉ የሙዚቃ ሊቆች ጋርም ተዋሃደ። ከዚያም የራሱን ለዛ እና ማንነትን ይዞ ተወዳጅነትን ደርቦ እና ደራርቦ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ወደ ላይ ይዞት ወጣ።

      መሐሙድ አሕመድ በ1955 ዓ.ም ክቡር ዘበኛን ሲቀላቀል የተጫወታት የመጀመሪያ ዘፈኑ እስከ አሁን ድረስ ተወዳጅነቷ እያየለ እስከዚህ ዘመን ደርሳለች። ገናም በትውልዶች ውስጥ ታልፋለች።

ካንቺ በቀር ሌላ ብሞት አልመኝም

ግን እስከ አሁን ድረስ አላወቅሽልኝም

ሰላምን ለማግኘት አጥብቄ ብመኝም

ታበሳጪኛለሽ ግን አላወቅሽልኝም

ከሕይወቴ ይልቅ አስባለሁ ላንቺ

ግን ድካሜ ሁሉ አልገባሽም አንቺ

     “ካንቺ በቀር ሌላ ብሞት አልመኝም” ብሎ ሙዚቃ የጀመረው መሐሙድ አሕመድ ተአምረኛ የሚባሉ ሙዚቃዎችን መጫወት ጀመረ።

“እንቺ ልቤ እኮ ነው ስንቅሽ ይሁን ያዢው

አንጀትሽ ሲታጠፍ ምሳ ብለሽ ጋብዢው

ስፍራው ጉራንጉር ነው ያለሽበት ሰፈር

አይሻልሽም ወይ የልቤ ላይ መንደር”

     የግጥሟ ሃሳብ ጥልቀትና ምጥቀት እንዲሁም የዜማዋ ልኬት፣ ከዚያም የሙሐመድ የአዘፋፈን የድምፅ ለዛ ታክሎበት፣ እንቺ ልቤ እኮ ነው ስንቅሽ ይሁን ያዢው፣ አንጀትሽ ሲታጠፍ ምሳ ብለሽ ጋብዢው የምትሰኘዋ ሙዚቃ ከሰው ልጅ የጥበብ መንፈስ ጋር ዘላለም ትኖራለች።

     የመሐሙድ ዘፈኖች አንዴ ተሰርተው ከወጡ በኋላ በአድማጮች ዘንድ ዘላለማዊ ተወዳጅነትን ይዘው የመቆየት ብቃት አላቸው። ምክንያቱ ደግሞ ርዕሰ ጉዳያቸው የሰው ልጅ የጋራ ጉዳይ መሆናቸውም ጭምር ነው። የሺ ሐረጊቱን የመሳሰሉ ዘፈኖቹ ታሞ የተኛን ሁሉ ቀና አድርገው የመፈወስ ኃይል እንዳላቸው ገጠመኞቻቸውን የገለፁልኝ ሰዎችም አሉ።

     በነዚህና በሌሎቹም ስፍር ቁጥር በሌላቸው ሙዚቃዎቹ የተወደደው ሙሐሙድ፣ የራሱን ማንነት እና ቀለም ወደሚያሰጠው ማዕረግ ተሸጋገረ። የሙዚቃ ሰዎች ሙሐመድን “የትዝታው ንጉስ” እያሉ ይጠሩት ጀመር። የትዝታን ሙዚቃ በመጫወት ወደር የማይገኝለት ከያኒም እየሆነ መጣ። እሱ ራሱ ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት ካሊፎርኒያ ውስጥ የሙዚቃ ኮንሰርቱን ካቀረበ በኋላ ስለ ትዝታ ሙዚቃ የሚከተለውን ሃሳብ ተናግሮ ነበር።

“ትዝታ ዘፈኖች ከእኔ የትዝታ ትዝታዎች ናቸው። ትዝታን እኔ ብቻ ሳልሆን ማንም ሰው ሲጫወተው ሰውነቴን ይወረኛል። በተለይ ክራር የሚጫወት ሰው የክራር ቅኝቱን ሲጀምር ሰውነቴን ያሳክከኛል። ያቁነጠንጠኛል። አልዋሽም! ትዝታን ስጫወት ሰውነቴን ራሴን እረሳዋለሁ”

ብሏል።

     ይህ ድምፃዊ ሐገሩ ኢትዮጵያን በተለያዩ ሐገሮች ውስጥ በችሎታው በማስተዋወቅ ግዙፍ ውለታ የዋለና እየዋለም ያለ ትልቅ የጥበብ አምባሳደር ነው። ከዓመታት በፊትም ወደ እስራኤል ሀገር ሄዶም የሙዚቃ ኮንሰርቱን ሲያቀርብ በሺ የሚቆጠሩ ታዳሚያን ተገኝተው ተደስተው ወጥተዋል። በወቅቱም የእስራኤል ልዩ ልዩ ቴሌቪዥኖች 50 ዓመታት መድረክ ላይ ከተአምረኛ ሙዚቃዎቹ ጋር ስለሚውረገረገው ድምጻዊ ሰፊ ሽፋን ሰጥተውት ነበር። በወቅቱም በዚህችው የኢትዮጵያ የመንፈስ ወዳጅ በሆነችው በእስራኤል ውስጥ የሚገኘው በአማርኛ የሚተላፈው ቴሌቪዥን ጣቢያ ለመሐሙድ አጠር ያለች ዶክመንተሪ ፊልም ሰርተው አሰራጭተዋል።

     በዚህ ዶክመንተሪ ላይ መሐሙድ ሲናገር፣ ብዙውን ጊዜ የዘፈኖቹን ሃሳብ ለገጣሚያን እየነገረ፣ በዚህ ሃሳብ ላይ ግጥም ፃፉልኝ እያለ እንደሚያፅፍ እና እንደሚያቀነቅንም አውስቷል።

     ለምሳሌ በያዘው ሃሳብ እና በአገጣጠም ስልቱ ብሎም በዜማው በእጅጉ የተወደደለትን “ተው ልመድ ገላዬ” የተሰኘውን ዘፈን የመጀመሪያው የሃሳቡ ጠንሳሽ መሐሙድ ራሱ ነው።

ተው ልመድ ገላዬ

ተው ልመድ ገላዬ

ትቶ የሔደን ሰው አትበል ከለላዬ

ተው ልመድ ገላዬ

     ይህን የመሳሰሉ የሙዚቃ ሃሳቦችን የፈጠረ ነው። ከዚህ ሌላም የጉራግኛ ብሔረሰብን ዘፈን ወደ አደባባይ አምጥቶ ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረውና ተወዳጅ ሆኖ እንዲመጣ ከፍተኛ ውለታ ያበረከተ ከያኒ ነው።

     መሐሙድ አሕመድ ለ50 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ በጦር ሜዳዎችና በዱር በገደሉ እየተጓጓዘ አዚሟል። ወገኑን አዝናንቷል። በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስለ ፍቅር ሲያቀነቅን ኖሯል። ከዛሬ 16 ዓመታት ጀምሮ ከፈረንሳዊው የሙዚቃ ፕሮሞተር ከፍራሲስ ፋልሴቶ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን አልፎ በዓለም አቀፍ የሙዚቃ መድረኮች ላይ እየሰራ ነው። በሚያቀርባቸው ኮንሰርቶች ሰፊ ተቀባይነት ካገኘ ውሎ አድሯል። መሐሙድ እረፍት የሌለው ተጓዥ ድምፃዊ! አይታክቴ ከያኒ ነው!

     መሐሙድ ዛሬም በሕይወት በመኖሩ ምክንያት ልንሳሳት ልንጨነቅለት፣ ልናስደስተው የሚገባ ሰው ነው። ዛሬ በሕይወት የሌሉት ምርጥ ጓደኞቹ ጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ታምራት ሞላ፣ ተፈራ ካሳ፣ ተዘራ ኃይለሚካኤል፣ ኮ/ል ሳህሌ ደጋጎ እና ሌሎችም የኢትዮጵያ ምርጥ ከያኒያንና ከያኒያት በሙሐሙድ ልቦና ውስጥ ሕያው ናቸው። ዛሬም ስለ እነሱ አውርቶ አቀንቅኖ አይጠግብም። ወዲያውም እንባውን መቆጣጠር አይችልም።

“ስንቱን አስታወስኩት

ስንቱን አሰብኩት

ልቤን በትዝታ ወዲያ እየላኩት

አንዴ በመከራው አንዴ በደስታዬ

ስንቱን ያሳየኛል ይሄ ትዝታዬ”

እያለ ያቀነቅንላቸዋል። መሐሙድ የፍቅር ሰው ነው።

     ከዚህ ሁሉ የ50 ዓመታት የሙዚቃ ጉዞ በኋላ አንድ ቀን ወጣቱ ድምፃዊ ጎሳዬ ተስፋዬ መሐሙድ ዘንድ መጣ። ጥሩ የሃሳብና የዜማ ስልት ያለውን ሸግዬ ሙዚቃ በጋራ አቀነቀኑ።

“በድንገት ያለፈውን ጊዜ በትዝታ

ባሰበው ተጉዤ ወደ ኃላ

እኔስ አጣሁ መላ”

            መሐሙድ

“ይቅርና ማሰብ በትካዜ

አጫውተኝ ስላለፈው ጊዜ”

ጎሳዬ

     በዚህ ዘፈን ውስጥ ተግተልትለው የሚመጡት ሀሳቦች በሙሉ የመሐሙድ ትዝታዎች ናቸው። በእጅጉ የሚወዳቸው ጓደኞቹ ትዝ ይሉታል። ያለፈው ሕይወታቸውና ፍቅራቸው ፊቱ ላይ ግጥም ይላል። መሐሙድ ያለፉ ጓደኞቹን ማሳያ ቋሚ ምስክር ነው። ቋሚ ባለታሪክ። ፈረንጆቹ /A Living Legend/ የሚሉት የኪነት ሰው ነው። መሐሙድ የሚሣሣለት አርቲስቶችን ነው። በሀገራችን ውስጥ ያሉ አያሌ ዩኒቨርስቲዎች አንዳቸውም ለመሐሙድ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አልሰጡትም። ቢሰጡት ለእነርሱም ክብር ነበር። ሕዝብና ዓለም የሰጠው ክብር ግን ትልቅ ነው። የክቡር ዶ/ር ሼህ መሐሙድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ደግሞ የሚገባውን አደረጉለት።

     የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በታደሙበት ደማቅ መድረክ ላይ ላበረከተው ታላቅ አስተዋፅኦ የአምስት ሚሊዮን ብር ሽልማት አበርክተውለታል። ምስጋና ይገባቸዋል!


Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100
Page 9 of 16

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us