You are here:መነሻ ገፅ»ኪነ-ጥበብ
ኪነ-ጥበብ

ኪነ-ጥበብ (209)

በጥበቡ በለጠ


    በሐገራችን ኢትዮጵያ “ስፖንሰር” የሚለው ቃል በእጅጉ ተደጋግሞ መነገር ከጀመረ 20 ዓመታትን አስቆጥሯል። ይህ ቃል በተለይ አያሌ የመንግሥት እና የግል ኩባንያዎችን በተለይ ደግሞ የሚሸጥና የሚገዛ ቁሳቁስ ያላቸው ድርጅቶች ወደ ገበያው ለመግባት “ይህን ነገር ስፖንሰር ያደረገላችሁ. . .” እየተባሉ መተዋወቅን ስለሚፈልጉ ቃሉ በተደጋጋሚ በሕዝቡ ውስጥ እየሰረፀ መጣ። ከዚህ ሌላም ጥሩ ነገር ሲሰራ ወይም ሲታሰብ አእምሮአቸው ክፍት የሆነ ሰዎች ደግሞ ለዚያ በጎ አስተሳሰብ ድጋፍ ያደርጉና ከዚያም “ስፖንሰራችን እከሌ ነው” እየተባለ ይነገርላቸዋል። ለመሆኑ አሁን አሁን እያየነው የመጣነው የሀገራችን የስፖንሰር ሺፕ እና አንዳንዴ ደግሞ የማስታወቂያ ጉዳይስ እንዴት ነው ብለን ጥቂት ነጥቦችን ለዛሬ እንጨዋወት።

     የስፖንሰር ሺፕ ጥያቄ በአብዛኛው ተደጋግሞ የሚነሳው በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ነው። በተለይ ደግሞ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ድራማዎች፣ ጥበባዊ ውይይቶች፣ አውደ ጥናቶች፣ ሲምፖዚየምና ወርክሾፖች ብሎም ሌሎችም ጉዳዮች ሲዘጋጁ ስፖንሰር የማፈላለግ ተግባር ይከናወናል። በዚህ ስፖንሰር በማፈላለጉ ስራ ደግሞ እንደ ሙያ የያዙት ሰዎች ተመድበው የኮሚሽን ተከፋይ ሆነው ይሰሩታል።

     እንደ ሙዚቃ ኮንሰርቶች አይነት በራሳቸው ገቢ የሚያስገኙ ዝግጅቶች በመሆናቸው፣ የስፖንሰሮቹ ተሳትፎ ተጨማሪ ገቢ መሰብሰቢያ ሊሆን ይችላል። በዚህም አጋጣሚ የሙዚቃውን ድግስ ድጋፍ ያደረገው አካል “ስፖንሰራችን እከሌ. . .” እየተባለ ይጠራል። ምርትና አገልግሎቱንም ያስተዋውቅበታል። አዲስ ካሴትና ሲዲ የሚያሳትሙ ድምፃዊያንና ድምጻዊያት በየከተማው ላይ ቢልቦርድ ለማሰቀል ስፖንሰር ያስፈልጋቸዋል። የኮሜዲ ሲዲዎችን የሚያወጡ የሚያሳትሙ ከያኒያንም ስፖንሰር እያፈላለጉ ነው የሚሰሩት። አብዛኛዎቹ አርቲስቶች ከፎቶዋቸው ግርጌ ወይም ጎን አንድ የሀገራችን ቢራ ተገማሽሮ ቆሞ እናየዋለን። ቢራ ፋብሪካዎቻችን ውድድር የያዙ የሚመስለውም ዘፈኖችን፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን፣ ካሴቶችን፣ ኮሜዲዎችን ስፖንሰር በማድረግ ነው። እዚህ አካባቢ ብዙ ሃሜታዎች እና ክፍተቶችም እየታዩ ነው። እከሌ ቢራ አንድ ሚሊዮን ብር ስፖንሰር አደረገኝ የሚሉ ከያኒያን እየበዙ መጥተዋል። በቢራዎችና በከያኒዎች መካከል አደገኛ የሆነ የጥቅም ትስስር ማለትም ሙስና እየታየ ነው። በቢራ ፋብሪካዎችና በአንዳንድ የጥበብ ባለሙያዎች መካከል እየተዘረጋ ያለው የሙስና ኔትወርክ ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ቸል እንዲባሉ አድርጓል። በተለይ ይህን የጥቅም ትስስር ወደፊት በዝርዝር ለማቅረብ እሞክራለሁ።

    ቢራ ፋብሪካዎች ሙዚቃን ብቻ የሙጥኝ ብሎ ስፖንሰር ከማድረግም ወጣ ብለው ታላላቅ ማህበራዊ ኃላፊነቶችንም መወጣት ይጠበቅባቸዋል። እንደሚታወቀው ኢንዱስትሪ ነክ ድርጅቶች ምርት በሚያመርቱበት ወቅት ተረፈ ምርቶቻቸው ለአካባቢ ብክለት ይዳርጋል። ከፋብሪካ የሚወጡት ጭስ እና ሌሎች ውዳቂ ነገሮች አካባቢ ላይ እና ዜጋ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ማምጣታቸው አይቀርም። ለዚህ ሲባል ደግሞ ኢንዱስትሪዎች በየአመቱ ለማህበረሰቡ እና ለሀገር የሚበጁ ጉዳዮች ላይ ድጋፍ ያደርጋሉ። በውጭው አለም እንዲህ አይነት ድጋፎች “Social Responsibility” ወይንም ማኅበራዊ ኃላፊነት በመባል ይጠራሉ። በሀገራችን “ማሕበራዊ ኃላፊነት” እየተባለ ይጠራል። ለመሆኑ ፋብሪካዎቻችን ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ወይ? የሚል ጥያቄ አንስተን መወያየት እንችላለን።

     ማሕበራዊ ኃላፊነት ስንል በተለይ ለሕዝብ፣ ለሀገር፣ ለትውልድ የሚጠቅሙ እና በሰው ልጅ የአስተሳሰብና የኑሮ ሁኔታ ላይ የተሻለ ነገር ይፈጥራሉ ተብለው የሚታሰቡ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግን ይመለከታል። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ የጥናትና የምርምር ስራዎችን መጥቀስ ይቻላል። የተለያዩ ምሁራን የሚፅፏቸው፣ የሚያሳትሟቸውና የሚያሰራጯቸው እውቀቶች ድጋፍ አድራጊ አካላት እያጡ እንዲሁ ተልኮስኩሰው የሚቀሩበት ሁኔታ እናያለን። በሀገራችን ውስጥ ያሉትን የጥናትና የምርምር ውጤቶችን የውጭ ሀገራት የተለያዩ ኩባንያዎች ድጋፍ ሲያደርጉ ይስተዋላል። ኢትዮጵያዊ ኩባንያዎች በእንዲህ አይነት ለትውልድ በሚጠቅሙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን “Social Responsibility” የማይወጡት ለምንድን ነው? ብለን መጠየቅ መወያየት ይቻላል።

     ለዛሬ ግን ቢራ ፋብሪካዎቻችን እየበዙ በመምጣታቸውና ሌሎች ፋብሪካዎችም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ውስጥ ዋነኛዋ የንግድ መናኸሪያቸው እንደሆነች በማመን እየመጡ ስላሉ አንዳንድ ነገሮችን እያስተካከልን እንድንጠብቃቸው ለማሳሰብ ስለፈለኩ ነው። እቤታችንን ስርዓትና ደንቡን፣ አስተሳሰቡን አርቀን አበጅተን እንግዳ ካልጋበዝን፣ በተበላሸ ቤት የገባውም እንግዳ እንደተበላሸው ነዋሪ ይሆንብናል። ስለዚህ እየታዩ ያሉትን ማሕበራዊ ኃላፊነትን ያለመውጣት ክፍተቶችን ማስተካከል ግድ ይለናል።

     ኢትዮጵያ የዘፈን እና የስፖንሰር አገር ብቻ አይደለችም። ትልልቅ ሃሳቦችን የሚያመነጩ ምሁራን ያሉባት፣ የጥናትና የምርምር ስራዎች የሚዘጋጁባት፣ የተለያዩ አለማቀፍ ጉባኤዎች የሚደረጉባት፣ ወደ ተሻለ ማህበረሰብ ግንባታ ውስጥ የገባች ሀገር ናት። ታዲያ ይህን የማሕበረሰብ ግንባታ የሚደግፉ፣ ከጎን የሚቆሙ፣ የሂደቱም አጋዥ ኃይሎች ያስፈልጋሉ።

አንድ ምሳሌ ላስቀምጥ፡- ገብረ-ፃድቅ ደገፉ የተባሉ ኢትዮጵያዊ ከዚህ በፊት አንድ አስደማሚ መፅሐፍ አሳተሙ። መፅሐፉ ከ400 ገፆች በላይ ያለው ነው። ርዕሱ “NILE HISTORICAL LIGAL AND DEVELOPMNTAL PERSPECTIVES” የሚል ርዕስ ያለው ነው። ይህ መፅሐፍ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዟ ላይ ከተዘጋጁ ሰነዶች መካከል ዋነኛው ነው ማለት ይቻላል። የታተመው በ1995 ዓ.ም ነው። መፅሐፉ የኢትዮጵያን ጥቅም በአለም አደባባይ ላይ ቆሞ ለማክበር የሚታገል፣ አባይ የኢትዮጵያ ታሪካዊና ሕጋዊ የባለቤትነት ድርሻን የሚያስረዳ፣ ገና የህዳሴ ግድቡ ስራ ሳይታሰብ ቀደም ብሎ ብዙ ሃሳቦችን ያጫረ፣ ያበራ እና ያሳየ ድንቅ ሃሳብ ያለው መፅሐፍ ነው። ታዲያ ይህ መፅሐፍ ሲታተም ኢትዮጵያዊያን ኩባንያዎች አንዳቸውም ድጋፍ አላደረጉለትም ነበር።መፅሐፉ በውስጡ የያዘው የነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለችና የጎመራች እንድትሆን የብረት ማዕዘን የሆነ የአባይ ማስረጃ ያቀረበ ነበር። ታዲያ እንዲህ አይነቱን ስራ ካልደገፍን ማህበራዊ ኃላፊነት “Social Responsibility” ማለት ለኛ ሀገር ምን ይሆን? ኢትዮጵያ በዘፈን እና በስፖርት ብቻ የት ትደርሳለች?

     ዛሬም ቢሆን በዚሁ በአባይ ወንዝ ላይ ለሚቀጥለው ትውልድ የተጻፈ፣ የተሰነደ፣ ትክክለኛ መረጃ የሚሰጥ የፅሁፍ ዶክመንት ለማዘጋጀት ደፋ ቀና የሚሉ ምሁራን እና ተቋማት ድጋፍ የሚሰጣቸው ኃይል በመጥፋቱ የእውቀት ስራው እየቀጨጨ በመምጣት ላይ ነው። በአንጻሩ ደግሞ ግብፆች በአባይ ወንዝ ላይ ለሚፅፍላቸው፣ ለሚያጠናላቸው፣ ትንሽም ቢሆን ድጋፍ ነገር ለሚጭርላቸው አካል የሚያቀርቡለት ልግስና በእጅጉ የገዘፈ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ቆም ብለን ስለ ማህበራዊ ኃላፊነት የመነጋገሪያ ጊዜያችን መሆኑን የሚያስረዳ ቀይ መብራት በርቶብናል።

     አሁን አሁን ቢራ ፋብሪካዎችም ሆኑ ሆቴሎቻችን፣ ባንኮቻችን፣ ኢንሹራንሶቻችን፣ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎቻችን ወዘተ በአብዛኛው ድጋፍ የሚያደርጉት ለመዝናኛው ክፍል ነው። አንዳንዴ ደግሞ በየመንደሩ ላሉ ለአስረሽ ምቺው ዝግጅቶች ሁሉ ግንባር ቀደም ተሰላፊዎች እየሆኑ ነው። በሬዲዮና በቴሌቭዥን ለሚተላለፉ ዝግጅቶች የሚደረጉ የስፖንሰርሺፕ ድጋፎች አብዛኛዎቹ ማህበራዊ ለውጥ፣ ሀገራዊ ለውጥና እድገት ለሚያመጡ ፕሮግራሞች አይደለም። በየኮሪደሩ ለሚደረጉ የወሬ ሽኩሽኩታዎች ብዙ ብር ሲያወጡ ይስተዋላል። ለማይመለከተን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ስፖንሰር የሚያደርጉ ግዙፍ ተቋማትን ስመለከት “እውነት ያለሁት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው?” ብዬም የምጠይቅበት ጊዜ አለ።

     በየሳምንቱ ለእንግሊዝ ሀገር የእግር ኳስ ክለቦች ጨዋታ በF.M. ሬዲዮ ጣቢያዎቻችን በኩል የሚወጣውን የስፖንሰሮች ገንዘብ ለሌላ ኢትዮጵያዊ ለሆኑ ፕሮጀክቶችና ስራዎች ወጥቶ ቢሆን ኖሮ ሀገራችን የት በደረሰች? እያልኩ ቁጭት ይለኛል። እንግሊዞች ሀገራቸው ውስጥ ለተጫወቱት ጨዋታ የኛ ሀገር ስፖንሰሮች ይህን ሁሉ ገንዘብ በማውጣት የሚረባረቡበት ነገር ምንድንነው? ማህበራዊ ኃላፊነታቸው ለማን ነው? ለእንግሊዝ ወይስ ለኢትዮጵያ? እያልኩ አስባሁ። እስኪ ሌሎቻችሁም ይህን ሃሳብ አጠንክራችሁ ተወያዩበት።

     ጠዋት ማታ በድጋፍ አድራጊ ስፖንሰሮች ታጅቦ በጆሯችን የሚጠቀጠቅብን የእንግሊዝ እግር ኳስ ጨዋታና ታሪክ ለዚህች ሀገር ወጣቶች የሚያመጣው ባህላዊ፣ ኪነ-ጥበባዊ፣ ስነ-ልቦናዊ፣ ታሪካዊ፣ ፍልስፍናዊ ወዘተ አስተሳሰብ ምንድ ነው? በየቀኑ እንግሊዝን አልመን፣ እንግሊዝን ሰምተን፣ እንግሊዝን ተሸክመን እንድንውል እንድናድር የሚያደርጉት እነማን ናቸው? የሚል ጥያቄ ብናነሳ፣ በሀገራችን ያሉ ስፖንሰር አድራጊ ኩባንያዎች ናቸው። እነዚህ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ ሕጻናት ነገ የተሻሉ አሳቢዎች፣ አላሚዎች እንዲሆኑ ብዙም አይጥሩም። የልጆች አእምሮ ብልፅግና ላይ ለሚሰሩ ድርጅቶች አይደግፉም። እነርሱ ሲመጡ በጀት ጨርሰናል ይላሉ። የነ አርሴና ማንቼ. . . ጨዋታ ላይ ግን ስፖንሰር በማድረግ የልጆቻችንን ጆሮና መንፈስ ሲረብሹት ይውላሉ። አሁን አሁን ደግሞ ትውልዱን የማደንዘዝ ተፅዕኖም እየፈጠሩ መሆኑ ቀስ በቀስ እየታየ ነው። እናም ስፖንሰር አድራጊ ተቋማት ማህበራዊ ኃላፊነት Social Responsibility ን እየተወጡ ነው ወይ?

     በስፖንሰር አድራጊ ተቋማት ላይ ከሚታዩ ችግሮች መካከል በአምቻና በጋብቻ፣ በትውውቅ፣ በጓደኝነት ወዘተ የመጠቃቀም ሁኔታ ነው። በከተማችን ውስጥ የሚገኙ ጥቂት ግለሰቦች የማስታወቂያና የስፖንሰርሺፕ ጥያቄዎች የሚሟሉላቸው ሆነዋል። እነዚህ ግለሰቦች ከመንግስት እስከ ግል ኩባንያዎች ድረስ ያሉ የግንኙነት መረቦቻቸውን ዘርግተው የማህበራዊ ኃላፊነት መወጫ መንገዱን ሁሉ እየዘጋጉት ይገኛሉ። እነዚህ ግለሰቦች የሚሰሩት ፊልም ካለ፣ ቴአትር ካለ፣ እርሱን የሚመሩት መድረክ ካለ ስፖንሰሮቹ ይጎርፋሉ። የስፖንሰርሺፕ ጉዳይ ማህበራዊ ኃለፊነትን መወጫ ከመሆን አልፎ ትውውቅ ሆኗል። መጠቃቀምም በእጅጉ አዘንብሎበታል። የክልልና የወረዳ ዝግጅቶች ሳይቀሩ በጥቂት ግለሰቦች እጅ ወድቀዋል። ለመሆኑ ሀገሪቷ ሌላ ሰው የላትም ወይ? የሚያሰኝ ጥያቄም የሚጠይቁ ሞልተዋል።

     አንዳንድ ኩባንያዎች ደግሞ አሉ። በራቸውን ዘጋግተው ስፖንሰር የማያደርጉ። ስፖንሰር የሚለውን ቃል መስማት የማይፈልጉ ሁሉ አሉ። በራቸው ላይ “የስፖንሰር ሺፕ ጥያቄ አናስተናግድም” ብለው የሚፅፉም አሉ። እነዚህ ኩባንያዎች አትራፊ እስከሆኑ ድረስ ማህበራዊ ሃላፊነት Social Responsibilityን የሚወጡበት ማናቸውም ሀገራዊ ጉዳይ ከመጣባቸው የመደገፍ መብትም ደምብም በሀገራችን አለ። ግን የአስተሳሰብ አድማስን ላቅ አድርጎ ከማስፋት ወደ ማጥበብ ያዘነብሉና ከሀገራዊ ተሳትፎ ራሳቸውን አግልለውና ሰውረው ይኖራሉ።

     በዚሁ በስፖንሰርሺፕ ጉዳይ ከሚታዩ ችግሮች መካከል የጠያቂው ብዛትም የትየለሌ ሆኖ መገኘቱ ነው። አንዲት ትንሽዬ ግሮሰሪ ለማስመረቅ ከተነሳው ሰው ጀምሮ አያሌ ታላላቅ የሚባሉ ግለሰቦችና ተቋማትም ስፖንሰር ይጠይቃሉ። ከመብዛታቸው የተነሳም ወደ ማሰልቸት ገብተዋል። በነዚህ ስፖንሰር ጠያቂዎች መብዛት የተነሳ ታላቅ ሀገራዊ ጉዳዮችን የሰነቁ ሃሳቦች ተመልካችና ሰሚ አጥተው መና ሲቀሩ ኖረዋል፤ አሁንም በችግር ውስጥ ናቸው።

     ይህን ስርዓት ያጣውን የስፖንሰር ሺፕ ጉዳይ የሚያቃና አንድ ጠንከር ያለ ደንብና መመሪያ ያስፈልጋል። ማህበራዊ ኃላፊነት መወጫ መንገዶች ናቸው ተብለው፣ ታውቀው፣ ተለይተው የተቀመጡ ግልፅ አቅጣጫዎች መኖር አለባቸው። በዚህች ሀገር ውስጥ የጥናትና የምርምር ማዕከሎች የሚያወጧቸው ህትመቶችና ዝግጅቶች እየቀጨጩ መጥተዋል። በአንጻሩ የእንግሊዝ እግር ኳስ ጨዋታዎች፣ የሙዚቃ ኮንሰርቶች፣ የዓመት በአል ዝግጅቶች፣ ቀልዶች፣ የምግብ፣ የመጠጥ፣ የሸቀጣሸቀጥ ኤግዚቢሽኖች እየገዘፉ መጥተዋል። የእውቀት የፈጠራ፣ የግኝት፣ የሃሳብ፣ የሥነ-ፅሁፍ፣ የባህል፣ የቱሪዝም፣ የህጻናትና የወጣቶች አእምሮ ማበልጸጊያ ላይ ድጋፍ አድራጊ አካል መንምኗል።

     በአጠቃላይ ግን ይህ ፅሁፌ በልዩ ልዩ ጉዞዎቼ የታዘብኩትና በሰነድም ከሰበሰብኳቸው ዶክመንቶች በመነሳት የፃፍኩት ነው። ወደፊት እንደ አስፈላጊነቱ የስፖንሰሮችን እና የሚታዩ የስህተት ድርጊቶችም አጫውታችኋለሁ። ከሁሉም በላይ ግን ሀገራዊ እና ትውልዳዊ ርዕሰ ጉዳዮች በተነሱ ቁጥር የሚቻላቸውን ድጋፍ የሚያደርጉ፣ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ከፊት የሚሰለፉ ጥቂት ተቋሟትን ሳላመሰግን ፅሁፌን አልደመድምም። እነርሱን በርቱ እላለሁ። እውቀት ላይ፣ ትውልድ ላይ፣ ሀገር ላይ፣ ልማት ላይ፣ ምርምር ላይ፣ ጥናት ላይ፣ ባህል ላይ ወዘተ የሚያተኩሩ በመሆናቸው ከላይ የሰፈረው ተጓዥ ትዝብቴ እነርሱን አይመለከትም።

በጥበቡ በለጠ 

     ባለፈው ሳምንት በተለምዶ መምህር ግርማ ወንድሙ በመባል ስለሚጠሩት፣ በማዕረግ ስማቸው ደግሞ “መልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ” ፣ ጥያቄ አዘል መጣጥፍ አቅርቤ ነበር። እኚህ አባት በየአውደምህረቱ ከሰዎች ላይ ስለሚያስወጧቸው ሰይጣኖች ርዕሰ ጉዳይ ለመወያያ የሚሆኑ ጥያቄዎችን ነበር የሰነዘርኩት፡ በነዚሁ በተነሱት ጥያቄዎች ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በድረ-ገፅ አማካይነት አንብበዋል። ወዳጄ የሆነው ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ደግሞ በራሱ ፌስ ቡክ ላይ ሰው እንዲነጋገርበት ካስቀመጠው ሰዓት ጀምሮ አያሌ አንባቢዎች መልስ ሲሰጡበት ቆዩ። አብዛኛዎቹ ሰዎች ለተጠየቀው ጥያቄ ተገቢውን መልስ አልሰጡም። እንደውም የተነሳውን ጥያቄ ራሱ የሚቃወሙ በርከት ያሉ አንባብያን ገጥመውኛል። አንዳንዱ ጥያቄውን ራሱ መስማት የዘገነነው አለ። ሌላው ደግሞ ፅሁፉን ጨርሶ ያነበበ የማይመስልም አለ። ምክንያቱም የሚሰጠው መልስ ከጥያቄው ጋር ፈፅሞ አይገናኝምና ነው። ጥቂት የሚባሉ ሰዎች ደግሞ በሚገባ አንብበው ተገቢውን ምላሽ ሰጥተዋል። ለኔ ግን ትልቁ ጉዳይ በዚህ ሁሉ ሺ ሰው ውስጥ ጥያቄውን ማንሸራሸሩ ነበር።

     መምህር ግርማ ወንድሙ ስለሚያባርሯቸው ሰይጣኖች ጉዳይ ጠይቄ ሳልጨርስ በአናቱ ላይ ደግሞ አንድ አስገራሚ ነገር ገጠመኝ። የቀድሞው ጎበዝ ድምጻዊ (ዘፋኝ) የነበረው ጥበቡ ወርቅዬ፣ እሱም እንደ መምህር ግርማ ወንድሙ የሰይጣን መንፈስ እያተረማመሰ ሲያስወጣ ተመልክቼ ማሰብ ማሰላሰሌን፣ መጠየቄንም ቀጠልኩበት።

     ጥበቡ ወርቅዬ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታይ መሆኑን እና ከዘፈን፣ ከዳንኪራ ብሎም ከሃጢያት መንገድ መውጣቱ በቅርቡ በልዩ ልዩ ሚዲያዎች ሲነግረን ሲያጫውተን ቆይቷል። ጥበቡ ወርቅዬ ዘፈን ማቆሙና ሃይማኖቱን መቀየሩ ብሎም መንፈሳዊ ሰው መሆኑ ገርሞኝ ሳላበቃ ይሔው የቀድሞ ድምፃዊ ዛሬ ደግሞ ፈጣሪያችንን ተፈታታኝ የሆነውን ሰይጣን፣ የሰው ልጆችን ሁሉ ለመከራና ለስቃይ የሚዳርገውን ሰይጣን፣ አለምን ለእርኩሰትና ለሀጢያት የሚያጋልጠውን ሰይጣን አባራሪ፣ አስወጪና የኢትዮጵያዊያን ሕሙማን ፈዋሽ ሆኖ ተመርጧል።

     ጥበቡ ወርቅዬም ሰይጣኑን እያነጋገረው፣ እያስጨነቀው፣ እያስጓራው፣ እያስጮኸው፣ እያንከባለለው፣ እያንደፋደፈው ሲያስወጣ በየመድረኩ እያየን ነው። ጥበቡ ወርቅዬን ከሰይጣኑ ጋር ሲያወራም አየሁት፡ ሰይጣኑን “እኔን አታውቀኝም?” እያለ ይጠይቀው ነበር። በዚህ ጊዜ ሰይጣኑ ጥያቄውን ፈርቶ ይርበተበት ነበር። ድሮ አንተ ዘንድ ነበርኩ፤ ዛሬ ደግሞ አንተን አባራሪ ሆኛለሁ እያለ የቀድሞው ድምጻዊና ዳኪረኛ ጥበቡ ወርቅዬ በአዲሱ የመንፈሣዊነት ጎዳና ላይ አየሁት። መቼም ለዚህ ወግና ማዕረግ መብቃት፣ መመረጥ ያስደስታል። ግን ደግሞ ሰው ስለሆንን የሚያስብ የሚጠይቅ አእምሮ ስላለንም አንዳንድ ጥያቄዎች በውስጤ ብቅ ማለታቸው አይቀርም።

     እኔ በበኩሌ ለመምህር ግርማ ወንድሙ ያቀረብኳቸውን ጥያቄዎች አይነት በጥበቡ ወርቅዬ ላይም እጠይቃለሁ። የሚመልስልኝ የሃይማኖት መሪ፣ አዋቂ ካለም እሰየሁ። ከሌለም ደግሞ ከአንባቢዎቼ ጋር ብንወያይበት ጥቅሙ ለሁላችንም ነው። የቢላ ስልቱ የሚወጣው እርስ በርሱ ሲፋጭ ነው። የረጋ ወተትም ቅቤ የሚወጣው ሲናጥ ነው። እኛም በሃሳብ ሽርሽር ተፋጭተን አእምሯችን ውስጥ አንድ ነገር እናስቀምጥ። ጠያቂና አሳቢ አእምሮ ከሌለን ሰው የመባላችን ምስጢርም አጠራጣሪ ይሆናል። ስለዚህ እስኪ እንጠይቅ።

     ጥበቡ ወርቅዬ አሁን በቅርቡ ድምጻዊ የነበረ፣ ከመንፈሳዊ ሕይወት ራቅ ብሎ በአለማዊው ሕይወት ጎልቶ ይታይ የነበረ ድምፃዊ እንደነበር እሱ ራሱ ከሰጣቸው መልሶች መገንዘብ ይቻላል። ይህ በሀጢያት ጎዳና እንደነበር ሲገልፅልን የነበረ ድምጻዊ ድንገት ተነስቶ ኢትዮጵያዊያንን ከሰይጣን ቁራኛ የሚያላቅቅ ታላቅ መንፈሣዊ ሆኖ ስናየው ያስገርማል። “እግዚአብሔር ከሐጢያተኞች መሀል መርጦት ለታላቅ ክብር አበቃው፤ ይህ ደግሞ የእርሱ ስራ ነው” ብዬ በመመለስ ይህን ጉዳይ ማለፍ አልቻልኩም። እግዚአብሔር ከመረጠ ለአያሌ ዘመናት ወይም እድሜ ልካቸውን በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ የኖሩ፣ ለዘመናትም ለሕዝብ ኑሮና ብልጽግና ሲፀልዩ፣ በፈጣሪያቸው ሲያምኑ የኖሩ ሰዎች ለምን አልተመረጠም ብዬ እጠይቃለሁ፡ እግዚአብሔር ለፈውስ የሚመርጠው ማንን ነው? ምርጫውስ ፍትሐዊ ነው? ብዬ ጠይቃለሁ።

     በጥቂቱ ተቀርፆ ያየሁት የጥበቡ ወርቅዬ የፈውስ መርሃ-ግብርም ጥያቄ እንዳነሳ ገፋፍቶኛል። በፕሮቴስታንት ቤተ-ክርስትያን ለዚያውም በአንዲት የማምለኪያ ስፍራ ከተገኙት አማኒያን ውስጥ ይህ ሁሉ ሰይጣን አለ ወይ ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል። ምክንያቱም የጥበቡ ወርቅዬን የፈውስ መርሃ-ግብር ሲካሔድ ሰይጣን ትርምስምሱ ሲወጣ ፊልሙ ያሳያል። እዚህች ኢትዮጵያችን ውስጥ በአንዲት ቦታ ላይ ብቻ በዚህ ሁሉ ሰው ውስጥ ሰይጣን ከሰፈረ መፍትሔው ምንድን ነው? ለመሆኑ ሕዝቡን እንዲህ የሚያወራጨውና የሚያንደባልለው ሰይጣን ነው ወይ?

     በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን በኩል ያሉት መምህር ግርማ ወንድሙ ሰይጣንን በመቁጠሪያ እና በመስቀል አስጨንቀው ሲያስወጡት ይታያል። ከፕሮቴስታንት በኩል ያለው ጥበቡ ወርቅዬ ደግሞ ሰይጣንን እስኪ እየኝ እያለው ትክ ብሎ እየተመለከተው፣ በእጆቹ መዳፍም የሕሙማንን ሰውነት እየደባበሰ ሰይጣንን ያባርራል። ለመሆኑ ሰይጣኖች የኦርቶዶክስና የፕሮቴስታንት ተብለው ይከፈላሉ ወይ? ልዩነትስ አላቸው ወይ? የሰይጣን ማስወጫው ምንድን ነው? መስቀል? መቁጠሪያ? መዳፍ? ፀሎት? እምነት? ሌላም ካለ እንነጋገርበት።

     መምህር ግርማ ወንድሙ እና ጥበቡ ወርቅዬ ሰይጣን ሲያያቸው እንዲህ የሚርበተበትላቸው ከሆነ ለምንስ በጋራ ተቀናጅተው ይህን ሁሉ ህዝብ የሚያሰቃዩትን ሰይጣኖች አያስወጡልንም?

     ሌላው ጥያቄዬ የሰይጣን መገኛው የት ነው የሚለው ነው? ድሮ ልጅ ሳለን በመቃብር ስፍራ በጠራራ ፀሐይ እና በምሽት አትጓዙ ሰይጣን አለ እንባል ነበር። በጠንቋይ ቤት፣ ባዕድ አምልኮ በሚሰራባቸው ቦታዎች፣ ሌሎችም የሰይጣን መገኛዎች ናቸው ተብለው የተፈረጁ ቦታዎች ነበሩ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የክርስትያን የማምለኪያ የተቀደሱ ቦታዎች ናቸው የሚባሉት ላይ ይህ ሁሉ ሰይጣን ሲወጣ እያስተዋልን ነው። ሰይጣን የአምልኮ ቦታ ላይ የመቆም ሃይል አለው ወይ? ለመሆኑ መኖሪያው የት ነው?

      ታላቁ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በ1985 ዓ.ም ያሳተሙት ኢትዮጵያ ከየት ወደየት የተሰኘ ግሩም መፅሐፍ አላቸው። በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ልዩ ልዩ መጣጥፎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ “እግዚአብሔርና እኛ” የተሰኘው ፅሁፍ አንዱ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን፣ በዚህ ፅሁፋቸው እኛ ኢትዮጵያዊያን ከፈጣሪያችን ጋር ያለን ግንኙነት እንዴት ነው? አምልኳችን በምን ላይ የተመሰረተ ነው? እምነት ራሱ ምንድን ነው የሚሉትንና የመሳሰሉትን ሃሳቦች የያዘ ርዕሰ ጉዳይ ነው።

     እንደ ፕሮፌሰር መስፍን አፃፃፍ ከሆነ እኛ ኢትዮጵያዊያን በተለይ አሁን ያለነው ትውልዶች፣ ሁሉንም ነገር ፈጣሪና መላዕክት አልያም ሌላ አካል እንዲሰጠን እንጠብቃለን። እኛ እግዚአብሔር ብርታትና ጥንካሬ ሰጥቶን ያሰብነው ያለምነው ቦታ ላይ ለመድረስ ጥረት አናደርግም፤ ሁሉንም ነገር የሚሰጠንን ኃይል እንጠብቃለን የሚል ጭብጥ ያለው ጽሁፍ ነው። እውነት ግን እምነት እና እኛ ግንኙነታችን እንዴት ነው ብለን እስኪ እንጠያየቅ።

     መቼም ኢትዮጵያ በክርስትናውም ሆነ በእስልምናው ታሪክ ውስጥ ስሟ ከፊት ጎልቶ የሚነገርላት ናት። ለምሳሌ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስሟ ተደጋግሞ የተነገረላት ሀገረ- እግዚአብሔር ናት በሚል ትታወቃለች። እየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ሰባ ሰገሎች ለክብሩ መገለጫ ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ፣ የከበሩ ማዕድናት ይዘው ወደ እስራኤል እንደሔዱ ሁሉ፣ በወቅቱ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የነበረው ንጉስ ባዜንም ወደ እስራኤል ሔዶ የጌታን መወለድ ተመልክቶ የመጣ ሰው መሆኑ ይነገራል። የፅላተ-ሙሴ መቀመጫ በሆነች ሀገር፣ አድባራትና ገዳማት ከታላላቅ ታሪኮቻቸው ጋር ባበቡባት ጥንታዊት ምድር ላይ ዛሬ ዛሬ እየተከወኑ ያሉ እምነቶች ቆም ብለን “ምን አይነት ክርስትና ነው እያራመድን ያለነው” ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደናል። በዚህች ሀገር ውስጥ በአሁኑ ወቅት የተደናበሩ ፈረንጆች ሁሉ እየመጡ ኢትዮጵያዊያንን ከሰይጣንና ከደዌ እየፈወስን ነው በማለት በየማምለኪያ ቦታው ዶክመንተሪ ፊልሞች እየሰሩ እያሳዩን ይገኛሉ። አሁንም የኢትዮጵያ ሰይጣን ብዛቱ እና የሚያጠምቀውና የሚያስወጣው ሰውም እንዲሁ የትየለሌ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው።

     ሰይጣንን ከሰው ላይ ለማባረር አቅም ያላቸው እነማን ናቸው? ዘፋኞች? ወታደሮች? አማኞች? ኦርቶዶክሶች? ፕሮቴስታንቶች? ካቶሊኮች?. . . ኧረ እነማን ናቸው? የእምነት ተቋማት ራሳቸው ጠንካራ አቋም ሊኖራቸው ግድ ይላል። ዛሬ ዝም ብለው የሚያዩት ይህ ጉዞ፣ ነገ ሌላ ቅርጽና ስርዓት ይዞ ብቅ ይላል። ከፊት ያለው ፈተና ከባድ ይመስላል።

     በአጠቃላይ አንባቢዎቼን የምጠይቀው ነገር እስኪሰከን ብለን እናስብ። የእምነታችን፣ የፈጣሪ አምልኮታችን ፍልስፍና ምንድን ነው? ሰዎች ተነስተው በቀደዱልን ጎዳና የምንፈስ ነን ወይ? እንነጋገርበት!


 

ሰይጣን ሰለጠነ፣ 

ከባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ 1958 ዓ.ም

 

 

 

ሰይጣን ሠለጠነ

ቀንዶቹን ነቃቅሎ፣

ጭራውንም ቆርጦ፣

ከሰው ልጆች ጋር አንድነት ተቀምጦ፣

ሊኖር ነው ጨምቶ፣

ከሰው ልጆች ጋር ሊጋባ ተጫጭቶ፣

ሰይጣን ሰለጠነ፣

ዘመናዊ ሆነ።

      ፊደል ቆጠረና ዳዊትም ደገመ፣

      በስመ አብ ብሎ፣ ውዳሴ ማርያምን

አንቀጸ ብርሃንን ፣መልካ መልኩን ሁሉ፣

አጠና ፈጠመ።

ከዚህም በኋላ ፆሞ ፀሎት ጀመረ፣

በመጨረሻውም አቡን ተክሌ አጥምቀው

ከርስትና አነሱት።

ግና ተቸገረ፣

እንዲያው በየለቱ

ጨርሶ አላውቀም ለማን እንደሆነ ፆምና ፀሎቱ፣

ቢጨንቀው ጊዜና ቆይቶ ሰንብቶ፣

ክርስቲያን የሆነ አንድ ሰው አግኝቶ

ተወዳጀውና ብሶቱን ነገረው ሁሉንም ዘርዝሮ

በጣፈጠ ቋንቋ በውነት አሳምሮ

”አትቸገር” አለው ክርስቲያን ወዳጁ አፅናናው መልሶ፣

ሰይጣን ካሰበው አለመጠን ብሶ፣

“ይህስ ቀላል ነገር ችግርም የለው፣

እንደኛው ክርስቲያን ሆንክ ማለት ነው”

በጥበቡ በለጠ


በቅርቡ በወጣው የአብነት አጐናፍር የሙዚቃ አልበም ውስጥ አንዲት ዘፈኑ ትገርመኝ ነበር። ይህችም ዘፈኑ “ሲነግሩህ ውለው ሳትሰማ ግባ” የምትል ተደጋጋሚ ዜማው ናት። እናም ብዙ ታሳስበኝ ነበር። ለምንድንነው እየነገረኝ ውሎ ሳልሰማ የምገባው? እያልኩ አሰብኩ። መስማት ከሌለብኝ ለምንድንነው የነጋሪውንም የራሴንም ጊዜ የማቃጥለው? መስማት ከሌለብኝ ለምን ቁጭ ብዬ አዳምጣለሁ? ወይስ ቁጭ ብዬ እንድሰማ የሚያሳድደኝ ነገር አለ? እያልኩ ስለዘመኔ ሁኔታ አሰላሰልኩ። ሳሰላስል ቆይቼ መምህር ግርማ ወንድሙን አሰብኳቸው። በማዕረግ ስማቸው መልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ ነው የሚባሉት። በተለምዶ ግን ሰዎች “መምህር” ይሏቸዋል። የእርሳቸውን ልዩ ልዩ ሲዲዎች በተለያዩ ጊዜያት አይቻለሁ። ሰምቻለሁ። ግን ምንም አላልኩም። አይቼም ሰምቼም ዝም ነው ያልኩት። “ሲነግሩህ ውለው ሳትሰማ ግባ” ይሆን እንዴ ነገሩ? ብቻ፣ ዛሬ ግን፣ ስለእኚሁ መምህርና ድርጊት ብሎም እየሰሩ ስለሚገኙት “ተአምራዊ ጉዳይ” ጥቂት ነጥቦችን አነሳስቼ ከዚያም ለሁላችንም እንደመወያያ ይሆነን ዘንድ ሀሳቤን ክፍት አድርጌ አልፌዋለሁ።

መምህር ግርማ ወንድሙ በተለያዩ አብያተ-ክርስትያናት ቅፅር ግቢ ውስጥ እየተገኙ ያስተምራሉ፣ በመለጠቅም ሰዎች ከያዛቸው ክፉ መንፈስ ያላቅቃሉ። ይህንንም በተለያዩ ጊዜያት ባሳተሟቸው ሲዲዎች ውስጥ መመልከት ይቻላል። መቼም የሰው ልጅ በክፉ መንፈስ ተሳስሮ መከራውን ሲያይ ቆይቶ በኋላም ከዚያ እጅና እግሩን ከያዘው እርኩስ መንፈስ፣ ከዚያ ክፉ ከሚያሳስበው እርጉም ቁራኛ ከሆነው መንፈስ፣ በስቃይ ሀበላ ከሚንጠው የመከራ ሸክም ከሆነው መንፈስ ከመገላገል የበለጠ ትልቅ ተግባር የለም። ሰዎች ሲፈወሱ ማየት በራሱ ያስደስታል። የመምህር ግርማ ወንድሙ ድርጊትም በአብዛኛው የፈውስ መርሃ ግብር ስለሆነ ከዚህ አንፃር እወደዋለሁ። ነገሩ እየቆየ ሲመጣ ግን አንዳንድ ጥያቄዎችም በውስጤ ማደግ ጀመሩ።

የመጀመሪያው ጥያቄ መምህር ግርማ ወንድሙ ሰይጣንን እያሰቃዩት፣ እያስፈራሩት፣ በአደባባይ እያወሩት፣ እየጠየቁት፣ በመጨረሻም ሲያባርሩት በተቀረፁት ሲዲዎቻቸው አማካይነት መገንዘብ ይቻላል። ግን መምህር ግርማ ከዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ የኃይማኖት አባቶች መካከል ሰይጣንን እንዲህ አድርጐ የመደብደብ፣ የማዋራት፣ የመመርመር እና በሰይጣን የተለከፉ ሰዎችን የመፈወስ ፀጋ እንዴት ተጐናፀፉ ብዬ እጠይቃለሁ። ጥያቄው ለራሴ ነው። በዚህች ቤተ-ክርስትያን ውስጥ ብዙ አባቶች መጥተው አልፈዋል። አሁንም በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መነኮሳት፣ ባሕታውያን፣ ሊቀ-ጳጳሳት ወዘተ አሉ። እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ ለፈጣሪያቸው ክብር የሚፀልዩ፣ የሚጾሙ ፍፁም ክርስትያን የሆኑ አያሌ ብፁአን አባቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ታዲያ መምህር ግርማ ወንድሙ ለየት ባለ መልኩ ጐላ ብለው ወጥተዋል። የሰው ልጆችን ሁሉ ወደ ሐጢያት መንገድ የሚመራውን ሰይጣን እያሽቀነጠሩ ሲያባርሩ በየአውደ ምህረቱ እናያለን። ይህ መቼም ትልቅ መሰጠት ነው። ይህን ሁሉ ሰይጣን የማተራመስ ኃይሉን እንዴት አገኙት እያልኩ አስባለሁ።

ሁለተኛው ጥያቄዬ፣ መምህር ግርማ ወንድሙ ከልዩ ልዩ ሰዎች ውስጥ የተጠናወታቸውን ሰይጣን ሲያስወጡ እንመለከታለን። ለመሆኑ የወጣው ሰይጣንስ የት ነው የሚሄደው? ከአንድ ወጥቶ ወደየት ይሄዳል?

ሦስተኛው ጥያቄዬ፣ በየአውደ ምህረቱ ሰይጣን አለበት ተብሎ የሚወጣው፣ የሚለፈልፈው፣ በስቃይ ውስጥ ያለው ሕዝብ ብዛቱ የትየለሌ እየሆነ እየመጣ ነው። ለመሆኑ ኢትዮጵያውያን ይህ ሁሉ ሰይጣን የሰፈረባቸው ሕዝቦች ናቸው ወይ? ኢትዮጵያዊያን ይህን ሁሉ ሰይጣን የተሸከሙ ሰዎች ከሆኑ ሀገሪቱ ላይ ራሱ ሰይጣን ሰፍሯል ማለት ነው። እናም ሰይጣኑን ከሀገሪቱ ላይ ለመንቀል መፀለይ ይሻላል ወይስ በየአውደ-ምሕረቱ እያንዳንዱን ሰው እየጠሩ ‘ልቀቀው’ ማለት ይሻላል? እያልኩ አስባለሁ።

አራተኛው ጥያቄዬ፣ ሰይጣን ሰፍሮባቸዋል ተብለው ወደመድረክ ወጥተው የሚናዘዙት ሰዎች በአብዛኛው የተማሩ፣ ትንሽ ላቅ ያለ አስተሳሰብ ያላቸው፣ በማኅበራዊ ኑሯአቸው ቀናዎች፣ የተሻለ ማሰብና መተግበር የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው። አብዛኛዎቹ ሐጢያት ያልሰሩ ናቸው። ሰይጣናዊ ድርጊት ውስጥ ያልገቡ ናቸው። በዚህች ሀገር ውስጥ ታላላቅ ወንጀሎችን የሚሰሩ ሰዎች ሰይጣን ይዞኛል ብለው ሳይለፈልፉ እንዴት እነዚህ የዋህ ኢትዮጵያውያን በሰይጣን ተለከፉ እያልኩ አስባለሁ።

የሰውን ልጅ ያጠፉ፣ የገደሉ፣ ዘር የጨፈጨፉ፣ ያሰደዱ፣ ያሰሩ፣ ያሰቃዩ… ሐጢያተኞች ሳይለፈልፉ እንዴት እነዚህ ምስኪን ኢትዮጵያውያን ይለፈልፋሉ እያልኩ አስባለሁ። እጠይቃለሁ።

አምስተኛው ጥያቄዬ፣ ክርስትያን መሆን ጥቅሙ ምንድንነው? ሰዎች ክርስትያኖች ሆነው፣ እያመኑ፣ እየፀለዩ፣ እየጾሙ ለሰይጣን ጥቃት የሚጋለጡ ከሆነ መፍትሔው ምንድን ነው? መምህር ግርማ ወንድሙ ባይኖሩ ኖሮ ያ ሁሉ ሰይጣን የተጠናወተው ክርስትያን ምን ይሆን ነበር እያልኩ አስባለሁ፤ እጠይቃለሁ።

ስድስተኛው ጥያቄዬ፣ የመቁጠሪያው ጉዳይ ነው። መምህር ግርማ ወንድሙ ሰዎችን ከሰይጣን ሲያላቅቁ ሁሌም ከእጃቸው ትልቅ መቁጠሪያና አነስተኛ መስቀል አይለይም። መቁጠሪያውንም በታማሚው አንገት ላይ ያንጠለጥላሉ። ለመሆኑ መቁጠሪያ ኃይል አለው ወይ? ሰዎችን ከሰይጣን የመገላገል ልዩ ፀጋ አለው ወይ? እያልኩ እጠይቃለሁ፤ አስባለሁ።

በርግጥ መምህር ግርማ ወንድሙ በ2005 ዓ.ም በሳተሙት “በማለዳ መያዝ የክፉ መንፈሶች ድርጊት” በተሰኘው መፅሐፉቸው ውስጥ በገፅ 155 ላይ ስለ መቁጠሪያ የሚከተለው ተፅፏል፡-

“በቤተ-ክርስትያናችን ካህናትና በንስሐ አባቶቻችንና በተባረከ መቁጠሪያ፤ በእግዚአብሔር አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በእመቤታችን ድንግል ማርያምና በቅዱሳን መላእክት ስም፤ ሁለቱ ትከሻዎቻችን መሃል፤ ጀርባችንን እንዲሁም፤ ሕመም የሚሰማን ቦታ ስንቀጠቀጥ፤

 • የማቃጠል ወይም የመለብለብ፤ የመውረር ወይም የመንዘር፤
 • የመብላት ወይም የማሳከክ፤ ከአንዱ ሰውነት ክፍላችን ወደ ሌላው የመዞርና፤ እንደ ድንጋይ በድን መሆን እንዲሁም፤
 • ጭንቅላታችንን ሁለት ከፍሎ፤ የራስ ምታት ዓይነት ስሜት ከተሰማን፤ ሰይጣን በውስጣችን አለ ማለት ነው”

በማለት መምህር ግርማ ወንድሙ ጽፈዋል። አያይዘውም መፍትሔውንም በሚከተለው መልኩ አስቀምጠውታል።

“የእግዚአብሔርን መንገድ ይዘን፤ እየጾምን እየፀለይን፣ እየተባረክን፣ እየሰገድን እና ሥጋና ደሙን እየወሰድን ከላይ እንደተገለፀው በመቁጠሪያችን እየቀጠቀጥን ክፉ መንፈሶችን በመታገል የእግዚአብሔር ልጆች መሆን እንችላለን።”

ይላሉ። እኔ ግን መምህር ግርማ እርኩስ መንፈሶችን የሚታገሉበት ይህ መቁጠሪያ ከዚህ ከላይ ከገለፁበት በተሻለ ማብራሪያና ትንታኔ ቢያክሉበት የተሻለ ነው እላለሁ።

በርግጥ ጥያቄዎቼ ብዙ ቢሆኑም፣ ሁላችሁንም ላለማሰልቸት ሲባል እዚህ ላይ ልግታቸው። ነገር ግን ጥያቄዎቹ ለመምህር ግርማ ብቻ የቀረቡ አይደሉም። ስለ ሃይማኖት አውቃለሁ፤ ተምሬያለሁ፤ መንፈሶችን መርምሬያለሁ መረጃ መስጠት እችላለሁ የሚል ሁሉ ተጠይቋል፤ እንዲፅፍም ተጋብዟል።

መቼም በዚህች የሦስት ሺ ዓመት ታሪክ አላት እያልን በምናወድሳት ሀገር፣ ክርስትናንም ሆነ እስልምናን በመቀበልና በማስፋፋት ከቀዳሚዎቹ ሀገራት ተርታ በምናሰልፋት ኢትዮጵያ ላይ፣ ልዩ ልዩ ድንቅዬ አብያተ-ክርስትያናት፣ ገዳማት፣ አድባራት በሚገኙባት ኢትዮጵያ፣ አያሌ ብፁአንና ቅዱሣን በተፈጠሩባትና ገቢረ-ተአምራት በሰሩባት ኢትዮጵያ፣ ይህ ሁሉ የኃይማኖት ድርሳናት በተፃፉባት ኢትዮጵያ ላይ የሰይጣን ድርጊትና ኃይል ይህን ያህል ሰፍሮ ከተስተዋለ ሀገሪቱ መላዋ ፀሎት ያስፈልጋታል። ከሰይጣን የሚያላቅቃት እምነት ያስፈልጋታል።

እርግጥ ነው ከባሕል ትምህርቶች ዘርፍ ውስጥ አንዱ መንፈሣዊነት ነው። በሃይማኖቱም ረገድ ትልቁ ጉዳይ መንፈሣዊነት ነው። መንፈሣዊነት ደግሞ የበጐና የርኩሰት ተብሎ ቢከፈልም በየትኛውም የባሕልና የእምነት ትምህርቶች በተደጋጋሚ የሚሰበከው በጐ መንፈሳዊነት ነው። ትውልድ የሚታነፅባት፣ ሀገርና ወገን የሚያድግባት፣ የተሻለ አስተሳሰብና አመለካከት የሚዳብርበት መንፈስ በዚህች ሀገር ላይ እንዲሰፍን ማድረግ ይገባል። ከሃይማኖት አባቶች፣ ከመንግሥት፣ ከባሕል ተመራማሪዎችና ከሁሉም ዜጋ ብዙ ይጠበቃል።

እንደ መምህር ግርማ ወንድሙ መፅሐፍ ገለፃ ከሆነ ደግሞ እዚህ ኢትዮጵያችን ውስጥ ለአያሌ ክፉ መንፈሶች ተጋልጠናል። ከእነዚህም ውስጥ፡- የዛር መንፈስ፣ የዓይነ-ጥላ መንፈስ፣ የዝሙት መንፈስ፣ የቡዳ መንፈስ፣ የግፍ መስተፋቅር መንፈስ፣ የዓውደ ነገሥት መንፈስ፣ የፃረ-ሞት፣ የሙት ጠሪ መንፈስ (ኤኬራ ዲቢፍቱ)፣ የሥነ-ልቦናና የፍልስፍና መንፈሶች፣ የአንደርቢ መንፈስ፣ በመተት የሚላኩ፣ የተባይና የነፍሳት ወረራ፣ የንቅሳቶች መንፈስ፣ የሰላቢ መንፈስ፣ የቁራኛ መንፈስ፣ የአዚም መንፈስ፣ ሱሉስ የዝውውር መንፈስ፣ ሟርት፣ መተት፣ አስማት፣ ድግምት እና ሌሎችም እርኩስ መንፈሶች በሀገራችን ውስጥ እንዳሉ ፅፈዋል። ከዚህ ሁሉ አደገኛ መንፈሶች ለመዳን ደግሞ ከእምነት ተቋማት ምን ይጠበቅ? ከእያንዳንዱ ግለሰብ ዘንድ ምን ይደረግ? መንግስትስ ምን መስራት አለበት? ማኅበራዊ ተቋሞቻችንን እንዴት እንመስርት ወዘተ የሚሰኙት ጉዳዮች ላይ መነጋገር ይቻላል።

በአጠቃላይ ግን፤ ድህነት፣ ረሃብ፣ መሃይምነት በእጅጉ ነግሶባት የምትገኘው ሀገራችን ላይ፣ ይህ ሁሉ እርኩስ መንፈስ ደግሞ ተጠናውቷት ካለ ጉዳዩ አስቸጋሪ ነው። በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ልዩ ልዩ የፀበል ቦታዎች ላይ የማያቸውን የአካላዊ እና የመንፈሣዊ ሕሙማንን ስቃይ ሳስተውል፣ እንደነ መምህር ግርማ ወንድሙ ደግሞ በየአውደ ምህረቱ ሰይጣን የያዛቸውን ሰዎችና ችግራቸውን ስመለከት፣ በየአብያተ-ክርስትያናቱ ጥግ ተኮልኩሎ የማገኛቸውን ነዳያንና ነዳያት (ለማኞች) ለማሰብ ስሞክር፣ በየቀኑ በየአብያተ-ክርስትያናቱ የሚፈፀሙትን የቀብር ስነ-ስርዓቶች ለመቁጠር ሳስብ፣ በፕሮቴስታንት እምነት ውስጥም የፈውስ መርሃ ግብር ተብሎ ወደ መድረክ እየወጣ ተፈውሰሃል የሚባለውን ወገኔን ሳስበው፣ በሙስሊሙ ሃይማኖት ውስጥ ያለውን በየዓረብ ሀገራቱ የሚንገላታውን ዜጋዬን ሳስበው፣ ለመሆኑ በምን ምክንያት ነው የዚህ ሁሉ የመከራ ቀንበር ተሸካሚ የሆነው እላለሁ። ግን የሃይማኖት ተቋሞቻችን አስተምሮት፣ ፍልስፍና፣ ዶግማ፣ ቀኖና ወዘተ የሚባሉት ነገሮች በስርዓት መመርመር ያለባቸው ይመስለኛል። የተሻለ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር እንዲመጣ የሃይማኖት ተቋማት ሚና ምን ይሆን? ልንነጋገርበት ይገባል።

    እነ መምህር ግርማ ወንድሙም ቢሆኑ የድህነትን፣ የአስተሳሰብን፣ የመከራን፣ የእንግልትን…. ክፉ መንፈስ ከኢትዮጵያ ላይ እንዲነቀል ካልፀለዩ፤ በመቁጠሪያ ብቻ የሰውን ጀርባ እየመቱ የተሻለች ኢትዮጵያን ማምጣት አይቻልም።

በጥበቡ በለጠ  


ከትናንት በስቲያ የአድዋን ድል 119ኛ ዓመት በዓልን አከበርን። በዚህ ወቅት በርካታ ወጣት ኢትዮጵያዊያን በዓሉን ምክንያት በማድረግ በእግራቸው ለአያሌ ቀናት ሲጓዙ ቆይተው የአድዋ ተራራ ላይ ደርሰው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ተክለው አውለበለቡ። በዓሉን ከአካባቢው ሰዎች ጋር ሆነው አደማመቁት። ይህን የወጣቶቹን ጉዞ ከሚያስተባብሩት መካከል አንዱ የሆነው የኬር አድቨርታይዚንግ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ የሆነው ወጣት መሐመድ ካሣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ‘ሄሎ ሌዲስ’ በተሰኘው ፕሮግራም ከአድዋ ተራራ ላይ ሆኖ ቃለ-መጠይቅ ይደረግለት ነበር። በዚህ ቃለ-መጠይቁ መሐመድ ካሣ ሲናገር፣ በዓሉ በጣም ደማቅ እንደነበርና ብዙ የአክሱምና የአድዋ ብሎም ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች በስፋት ታድመውበት ስለነበር በእጅጉ እንዳስደሰተው ገለፀ። በመቀጠል ግን የተናገረው ነገር ቆንጠጥ የሚያደርግ ነበር። ይህም ስለ ኢትዮ-ቴሌኮም ጉዳይ ነበር። ኢትዮ-ቴሌኮም በሀገራችን ውስጥ ልዩ ልዩ በዓላት ሲከበሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ቀድሞ ይልክ ነበር። ነገር ግን በዚህኛው የአድዋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት እስከ አሁን ድረስ አልላከም፤ ግን መላክ ነበረበት የሚል ሃሳብ ያለው መልዕክት መሐመድ ካሣ ከአድዋ ተራራ ላይ አስተላለፈ።

ይህን ጉዳይ ከጓደኞቼ ጋር ሆኜ ነበር በመኪና ውስጥ የሰማሁት። ሁሉም ጓደኞቼ ‘ግን እውነት ቴሌ ምን ነካው?’ ማለት ጀመሩ። መሐመድ ቴሌን ሲወቅስ ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ይሆናል። ከዚያም 30 ደቂቃዎች ባልሞሉበት ጊዜ ውስጥ ቴሌ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ላከ። ነገሩን በጥሞና አሰብኩት።

እውነት ቴሌ ለምን እስከዚያ ሰዓት ድረስ መልዕክት አልላከም? አድዋ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ድል ሆኖ ሣለ ጉዳዩ ለምን ተዘነጋ እያልኩ አሰብኩ። ሌላው ጉዳይ ቴሌን የቀሰቀሰው መሐመድ ካሣ ነው ወይ? ብዬም አሰብኩ። ምክንያቱም መሐመድ ከተናገረ በኋላ ቴሌ መልዕክቱን ላከ። አንድ ነገር ደግሞ ደስ አለኝ። ይሄ የመሐመድ ካሣ ቅሬታ ወዲያው መልስ ማግኘቱ።

ከሁሉም ነገር በላይ ግን ትልቁ ጥያቄ አድዋ የሚዘነጋ በዓል ነው ወይ የሚለው ነው። አድዋ ከኢትዮጵያዊያን ሁሉ አልፎ የጥቁር ሕዝብ በሙሉ መኩሪያ መመኪያ ከሆነ ከመቶ ዓመታት በላይ ቆይቷል። ጥቁሮች ለነፃነታቸው ያደርጉ የነበሩት ትግል አድዋን መሠረትና መነሻ በማድረግ ነበር። ጥቁር ከታገለ ማሸነፍ እንደሚችል ፅኑ እምነት የተጣለበት የድል ቀን ነው።

ለዚህ ጉዳይ አንድ ምሣሌ ላስቀምጥ። ወደ ደቡብ አፍሪካ ልውሰዳችሁ። በአንድ ወቅት ወደ ደቡብ አፍሪካ ለትምህርት በተጓዝኩበት ጊዜ አያሌ አብያተ-ክርስትያናት በኢትዮጵያ ስም እንደሚጠሩ ለመገንዘብ ቻልኩ። ጉዳዩን በዝርዝር ለማወቅ ያጓጓል። እንዴት በደቡብ አፍሪካዊያን ሃይማኖት ተከታዮች ውስጥ የኢትዮጵያ ስም ተደጋግሞ ተገለፀ? የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ በአዕምሮዬ ውስጥ ተመላለሰ። ሌሎችም እጅግ የሚገርሙ ነገሮችን በደቡብ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ መካከል የተገማመዱ የተሳሰሩ ገጠመኞችን አስተዋልኩ። እናም የነዚህን ምክንያት እየመረመርኩ ለበርካታ ጊዜያት ቆይቻለሁ።

የአድዋ ድል በ1888 ዓ.ም የካቲት 23 ቀን ሲበሰር፣ ደቡብ አፍሪካዊያን በነጭ የአፓርታይድ መንግስታት ግፍ እየተፈፀመባቸው ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ ቆይተዋል። ልክ የአድዋ ድል የዓለም ዜና ሲሆን፤ የደቡብ አፍሪካውያን ትኩረት ኢትዮጵያ ሆነች። ጥቁሯ ኢትዮጵያ የነጭ ወራሪዎች እንዴት አሸነፈች? እንዴት ድል አደረገች? ምስጢሩስ ምንድን ነው? ብለው ደቡብ አፍሪካዊያን ማጥናት ጀመሩ።

ከጥናታቸው ውስጥ ያገኙት አንዱ ውጤት ሃይማኖት ነበር። የኢትዮጵያ ተዋጊዎች ፅኑ የሃይማኖት ፍቅር ስለነበራቸው በእምነታቸው ውስጥ የነበሩትን ታቦታት ተሸክመው ወደ ጦር ሜዳ ተጉዘው ነበር። ታቦታቱን የያዙበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። አንደኛውና ዋነኛው ኢትዮጵያ አድዋ ላይ ከተሸነፈች በተለይ የኦርቶዶክስ ሃይማኖቷ ይጠፋል። አዲስ የቅኝ ገዢዎች ሃይማኖት ይስፋፋል። ስለዚህ ታቦታቱ ራሳቸው የእምነቱ ፅኑ መገለጫዎች ስለሆኑ ለዚህች ኢትዮጵያ ለምትባለው ምድር የመንፈስ ተራዳኢነታቸውን ከአርበኞቹ ጋር ሆነው እንዲሰጡ ተፈለገ። ስለዚህ ከፀሎት ከምህላ ከቅዳሴ ጋር ታጅቦ የአድዋ ተራሮች ከጦርነቱ በፊት አርበኞች ከፈጣሪያቸው ዘንድ መንፈሣዊ ብርታትን ለማግኘት ፀለዩ። በጦርነቱም ወቅት በግማሽ ቀን ውስጥ ድልን ተጐናፅፈው አስደናቂ ታሪክ ሰሩ።

ይህ ምክንያት ለደቡብ አፍሪካዊያን ትልቅ ትርጉም ነበረው። እምነት፣ ፅናት፣ መንፈሣዊነት የሚል ፍልስፍና ውስጣቸው ገባ። ስለዚህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች ሆኑ። ይህ ሃይማኖት አፍሪካዊ ነው፤ የጥቁር ሃይማኖት ነው የሚል የራሳቸውን ትርጓሜ ሰጡት። በዚህ ምክንያት ነው እስከ አሁን ድረስ ያሉት እነዚህ አብያተ-ክርስትያናት በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት። እነርሱም፡-

 1. African United Ethiopian Church
 2. The Ethiopian Mission in South Africa
 3. National Church of Ethiopia in South Africa
 4. St. Philip’s Ethiopian Church of South Africa
 5. Ethiopian Church Lamentation in South Africa
 6. Ethiopian Church of God the Society of Paradise

ታላቁ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ይህን የደቡብ አፍሪካን እና የኢትዮጵያን ትስስር ሲገልፁ ከአድዋ ድል በኋላ ከፍተኛ ተስፋ እና መነቃቃት በደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ መታየቱን “Ethiopian Echoes in Early Pan-African Writings” በተሰኘው ጥናታቸው ያወሣሉ። ከአድዋ ድል ማግስት ጀምሮ የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ተረቶች እና ሥነ-ጽሁፎች የታሪክ መዋቅራቸው ሁሉ ተቀይሯል። በነጭ የደቡብ አፍሪካ ወታደሮችና ደህንነቶች የሚፈለጉ የልቦለድ ገፀ-ባህሪዎቻቸው ሁሉ የሚሰደዱት ወደ ኢትዮጵያ እንደሆነ መፃፍና መተረክ ጀመሩ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የነፃነት ሀገር ስለሆነች፣ ነጮች ጥቁሮችን ሊይዙ ሊያስሩ የማይችሉበት ምድር ስለሆነች - ነፃ መውጫ አገር አድርገው ሳሏት።

በጣም የሚያሳዝነው ነገር፣ ኢትዮጵያ ከአድዋ ድል በኋላ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተከሰተውን ወዳጅነት ትኩረት አለመስጠቷ ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሪዎች ተደጋጋሚ የሆነ የግንኙነት መረብ ዘርግተው ቢሆን ኖሮ መላው ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የሃይማኖቱ ተከታይ ይሆኑ እንደነበር የሚገልፁ በርካታ ጥናቶች አሉ። አሁን ደግሞ ይህን የደቡብ አፍሪካውያንን ስሜት በመገንዘብ የማኅበረ ቅዱሳን ምሁራን አባላት ወደዚያ በመጓዝ በሚሰጡት ትምህርት ትልልቅ ለውጦች እየመጡ መሆኑን መረዳት ችያለሁ።

የአድዋ ድል ኢትዮጵያን በሰፊው ያስተዋወቀ የታሪክ ክስተት ነው። ራይሞንድ ጆናስ የፃፈው “The Battle of Adwa African Victory in the Age of Empire” የሚለው መፅሐፍና በሙሉ ቀን ታሪኩ የተተረጐመው አፄ ምኒልክ እና የአድዋ ድል በተሰኘው መፅሐፍ እንደተጠቀሰው፣ ‘አትላንታ ኮንስቲቲዩሽን’ የተሰኘው ጋዜጣ መጋቢት 4 ቀን 1896 እ.ኤ.አ. ‘የጣሊያን ክፉ ዕጣ’ በሚል ርዕስ ከ3ሺ በላይ የኢጣሊያ ወታደሮች በአድዋ ጦርነት ማለቃቸውን ዘግቧል።

ኒውዮርክ ወርልድ እና ቺካጐ ትሪቢውን የሚሰኙት የዘመኑ ዓለም አቀፍ ጋዜጦችም የአድዋን ድል ለዓለም አሰራጭተዋል። መጽሐፉ ሲገልፅ፣ እንደ ዛሬው ‘ታይም መፅሔት ሁሉ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ‘ቫኒቲ ፌይር’ ታዋቂ መፅሔት ነበር። በ1897 እ.ኤ.አ. ቫኒቲ ፌይር የፊት ገፁ ላይ የአፄ ምኒልክን ምስል ይዞ በመውጣት ንጉሡን ለመላው ዓለም አስተዋውቋቸዋል።’ ከቻርልስ ዳርዊን፣ የሩሲያው አሌክሳንደር፣ ናፖሊዮን ሳልሳዊ እኩል የአፄ ምኒልክ ፎቶግራፍ ተከትሎ አፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ከዓለም ታዋቂ ግለሰቦች ተርታ ተሰለፉ።

ከዚሁ ጋር በመለጠቅ በርካታ አውሮፓውያንም አዳዲስ ለተወለዱ ሕፃናት ልጆቻቸው “ምኒልክ” የሚል ስም ሰጧቸው ሲል Raymond Jonas በመፅሐፉ ውስጥ የገለፀውን ሙሉቀን ታሪኩ ተርጉሞ አስነብቦናል። ከዚሁ ከአድዋ ድል በኋላ አንዳንድ ደብዳቤዎች ንጉሡን የገንዘብ ውለታ የሚጠይቁም ነበሩ። አንዲት አድናቂያቸው በፃፈችላቸው ደብዳቤ አፄ ምኒልክ ለጅምር መኖርያ ቤቷ ማስጨረሻ የሚሆን 200 ፍራንክ እንዲልኩላት ጠይቃቸውም ነበር።

“የምኒልክ እና የጣይቱ የዓለም አቀፍ ዝና በጨመረ መጠን በርካታ ጥያቄዎች ከየአቅጣጫው መነሳት ጀምረውም ነበር። ኢትዮጵያ የመጀመሪያ የአፍሪካ ልዕለ-ኃያል እየሆነች ነው? ፖለቲካዊ ድሉ የኢትዮጵያ የንግድ ትንሳኤ መነሻ ይሆን? የይሁዳ አንበሳ ነገድ የሆኑት አፄ ምኒልክ የመላው ጥቁር ሕዝብ መሪ መሆን ይችላሉ?” የሚሉት ጥያቄዎች የልዩ ልዩ ፀሐፊያን የመከራከሪያ አጀንዳዎች ነበሩ።

የአድዋ ድል ኢትዮጵያ ከቅኝ አገዛዝ በትር የተላቀቀችበት ቀን ነው። የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን በማንም ነጭ ጦረኛ ያልተገዙበትን ታሪክ እንዲናገሩ ልሣን የሆናቸው ቀን ነው። የአድዋ ድል በብዙ ሺ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ደምና አጥንት የተገኘ የመስዋዕትነት ነፃነት ነው። ታዋቂዋ ድምፃዊት፣ በአድናቂዎቿ አጠራር “ባለቅኔዋ ድምፃዊት” እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)፣ አድዋ በተሰኘው ድንቅ ሙዚቃዋ ‘ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ’ እያለች እነዚያን የነፃነት ሰማዕቶችን ትዘክራቸዋለች። ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በ1950ዎቹ አድዋ ምርጥ ግጥም ፅፏል። በመድረክ ባይታይም ቴአትርም ምኒልክ በሚል ርዕስ ፅፏል። ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ Adwa:- An African Victory የተሰኘ ፊልም ሰርቷል። ቴዲ አፍሮም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶት ብዙ ወጪ በማውጣት የአድዋን ጀግኖች ዘክሯል። በዚህ ረገድ ጳውሎስ ኞኞን ሳልረሳ በርካታ ከያኒያንና ከያኒያትን መጠቃቀስ ይቻላል። እነርሱ አድዋን ለትውልድ አስተላልፈዋል። ዋናው ጥያቄ አሁን ላለው ትውልድ አድዋ ምኑ ነው? የሚለው ነው።

የአድዋ ድል ታስቦ ብቻ የሚውል በዓል ነው። ጉዳዩ ግን ትልቅ ትርጉም አለው። ልክ እንደ ሌሎቹ በዓላት ሕፃናት ተማሪዎቻችን በየትምህርት ቤቶቻቸው ሊያከብሩት የሚገባ ነው። ዩኒቨርሲቲዎችና ትልልቅ የእውቀት ተቋማት ውይይቶችና ጥናቶችን የሚያቀርቡበት ቀን መሆን ይገባዋል። ምክንያቱ ደግሞ ያ የአድዋ ድል የዛሬ ነፃነታችን መገለጫ ቀን በመሆኑ በየዓመቱ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባዋል ብዬ በግሌ አስበዋለሁ። ይህን የምልበት፣ በዚህ የድል ቀን ላይ ተመርኩዘው የፃፉ ታላላቅ የዓለማችን ታሪክ መርማሪዎች ሁሉ እንደሚጠቅሱት ከሆነ ኢትዮጵያ በጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ግርማ ሞገስ የምታገኝበት የድል ቀኗ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም እንደሆነ በሰፊው ይገልፃሉ። ታዲያ ይህን ቀን ሰፊ ትኩረት ብንሰጠው መላው ጥቁር ሕዝብ በየዓመቱ ወደ ኢትዮጵያ እየጐረፈ የነፃነት ደሴቱ ላይ ፈልሰስ ብሎ እንዲሄድ ማድረግ ይቻል ነበር።

ትልቁ ታሪካችን፣ ትልቁ ማንነታችን እንዳይከሰስ፣ ግርማ ሞገሱ እንዳይከስም ከሁላችንም ብዙ ነገር ይጠበቃል። በተለይ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ዩኒቨርሲቲዎቻችን እና ኮሌጆቻችን፣ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየዓመቱ አድዋ ላይ ልዩ ዝግጅት ቢኖራቸው ጥቅሙ ለሀገርና ለሕዝብ ነው። የሀገራችንንም የታሪክ፣ የባሕል፣ የነፃነት፣ የአርአያነት ተምሳሌት በሰፊው ያሳያል ብዬ አምናለሁ። ምስጋና ለአድዋ ጀግኖች ይሁን! 

የአጤ ምኒልክ እናት

በጥበቡ በለጠ

 

በኢትዮጵያ የታሪክ አፃፃፍ ሒደት ውስጥ የአጤ ምኒልክን ታሪክ በሚገባ የፃፈ ሰው ቢኖር ጳውሎስ ኞኞ ነው። ጳውሎስ አጤ ምኒልክን አብሯቸው የኖረ እና ከእጃቸው የበላ የጠጣ ይመስል እያንዳንዱን ጥቃቅን ታሪካቸውን ሁሉ ለትውልድ ያስተላለፈ ብርቅዬ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ታሪክ ፀሐፊ እና ዲስኩረኛ ነበር። በአጤ ምኒልክ ታሪክ ብቻ ሦስት ታላላቅ መፃሕፍትን ያበረከተ ጆቢራ ከያኒ ነበር። አንደኛው ቀደም ባሉት ዘመናት አዘጋጅቶት በ1984 ዓ.ም ያሳተመው 509 ገጾች ያሉት አጤ ምኒልክ የሚለው መጽሐፉ ነው። ሁለተኛው እርሱ ከሞተ በኋላ አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት ከጳውሎስ አንድያ ልጅ ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በመተባበር 2003 ዓ.ም ያሳተሙት አጤ ምኒልክ በሀገር ውስጥ የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች የሚለው 622 ገጾች ያሉት ግዙፍ መጽሐፍ ነው። ሦስተኛው ደግሞ አሁንም አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅትና ሀዋርያው ጳውሎስ በመተባበር ያሳተሙት አጤ ምኒልክ ከውጭ ሀገራት የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎች ባለ 337 ገጾች የሆነው መጽሐፍ ነው። በእነዚህ ታላላቅ መፃሕፍቶቹ የአድዋውን ጀግና ጳውሎስ ኞኞ ከልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች አንፃር ዘክሯቸዋል። የፊታችን ሰኞ የካቲት 23 ቀን የአድዋ በዓል ነውና እኔም ጳውሎስ ኞኞ ሰጥቶን ካለፋቸው ታሪኮች ውስጥ በጣም ያስገረመኝን የአጤ ምኒልክን አፈጣጠር የተመለከተውን ወግ ላጫውታችሁ ብዬ አሰብኩ። ታሪኩ እንዲህ ነው፡-

የኋለኛውን የሀገራችንን ታሪክ ስንቃኝ ብዙ አስገራሚ ነገሮችን እናገኛለን። ለምሳሌ መነኩሴዎችና ትንቢት ተናጋሪዎች በሰፊው የሚታመንባቸው ወቅት ነበር። እነርሱ የተናገሩት መሬት ጠብ አይልም፤ እውነት ነው ተብሎ ይታመናል። የነገስታት ጋብቻ ሁሉ የሚወሰነው በኮከብ ቆጣሪዎች አማካይነት ነበር። እከሊትን ካገባህ የስልጣን ዘመንህ የተረጋጋ፣ እድሜህ የረዘመ፣ ሕይወትህ የለመለመ… እየተባለ ብዙዎች በዚህ መስመር ተጉዘውበታል። ለጦርነት ዘመቻ ሁሉ የሚወጣው እነዚህ “አዋቂዎች” በሚያዙት መሠረት ነበር። ጉዳዩ እስከ ቅርብ ጊዜ ይሰራበት ነበር። በ1950ዎቹ የተነሱት ማርክሲሰት ሌኒኒስት ፍልስፍናዎችና ትግሎች እያዳከሙት መጡ እንጂ፣ እንዲህ አይነቱ “እምነት” በሀገራችን ትልቅ ቦታ ነበረው።

ይህን ርዕሰ ጉዳይ አያሌ ምሳሌዎችን እየጠቃቀስን ወደፊት እንጨዋወትበታለን። ለዛሬ ግን ቀደም ብዬ ወደጀመርኩት ርዕሰ ጉዳይ ላምራ። አጤ ምኒልክ እጅግ ብልሕ መሪ እንደነበሩ ታሪካቸውን የፃፉ ሁሉ ይመሰክራሉ። ጳውሎስ ኞኞ ደግሞ ምኒልክ ወደዚህች ዓለም ሲመጡ፣ ሲፈጠሩ ጀምሮ የተለየ ታሪክ እንዳላቸው ጽፎልናል። ምኒልክ በትዕዛዝ የተወለዱና ልዩ ፍጡር መሆናቸውን ጭምር የሚያስረዳው የጳውሎስ ገለፃ የሚከተለው ነው፡-

“ምኒልክ በ1836 ዓ.ም ነሐሴ 12 ቀን ቅዳሜ ዕለት ተወለዱ። አባታቸው ኃይለመለኮት ሳህለሥላሴ ሲሆኑ፤ እናታቸው ወ/ሮ እጅጋየሁ ለማ አዲያሞ ይባላሉ።

“የምኒልክ እናት ወ/ሮ እጅጋየሁ የንጉሥ ሣህለሥላሴ ሚስት የወ/ሮ በዛብሽ ገረድና የልጆች ሞግዚት ነበሩ። እጅጋየሁ የግርድና ሥራ የጀመሩት በንጉሥ ሣህለሥላሴ ቤት አልነበረም። ንጉሥ ሣህለሥላሴ ቤት ከመቀጠራቸው በፊት የአንኮበር ቤተ-ከርስትያን አለቃ የነበሩት የመምህር ምላት ገረድ ነበሩ። በአለቃ ምላት ቤት ግርድና ተቀጥረው ሳለ አንድ ቀን ጧት ለጓደኞቻቸው “… ዛሬ ማታ በሕልሜ ከብልቴ ፀሐይ ስትወጣ አየሁ…” ብለው ተናገሩ።

“ሥራ ቤቶች የሰሙት ወሬ መዛመቱ አይቀርምና ወሬው ከጌትዮው ከአለቃ ምላት ዘንድ ደረሠ። አለቃ ምላትም “እንግዲያው ይህ ከሆነ ወደላይ ቤት ትሂድ” አሉ። የላይ ቤት የሚባለው የአንኮበሩ የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ቤተ-መንግሥት ከኮረብታ ላይ በመሆኑ አገሬው በተለምዶ “ላይ ቤት” ይለዋል።

“እጅጋየሁ እንደተመከሩት ከንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ቤት ሔደው ተቀጠሩ። የእጅጋየሁ የሕልም ወሬ ተዛምቶ ንጉሥ ሣህለ ሥላሴም ቤት ገብቶ ስለነበር የንጉሥ ሣህለሥላሴ ባለቤት ወ/ሮ በዛብሽ ከልጃቸው ሁሉ አብልጠው ሰይፉ ሣህለሥላሴን ይወዱታል። ስለዚህ ሰይፉ ከእጅጋየሁ ልጅ እንዲወልድ ማታ እጅጋየሁን ወደ ሰይፉ መኘታ ቤት ልከው ያን ጐረምሳ እንድትጠብቅ አደረጉ።

“የልጅ ሰይፉ አሽከሮች የእጅጋየሁን መላክ እንዳወቁ ለጌታቸው ለልጅ ሰይፉ ተናገሩ። ሰይፉ የሚወዳት ሌላ ሴት አለችው። የአዲሲቱን የእጅጋየሁን መምጣት እንደሰማ ተናዶ እንዳያባርራትም እናቱን ፈርቶ ከወንድሙ ከኃይለመለኮት ዘንድ ሄዶ “እባክህ ሌላ ሴት ከሌለህ እሜቴ የላኳትን ያቺን ገረድ ውሰድልኝ” አለ። ኃይለመለኮትም እሺ ብሎ ከእጅጋየሁ ጋር ባደረጉት ግንኙነት ልጅ ተፀነሰ።

“እናትየዋ ወ/ሮ በዛብሽ የእጅጋየሁን መፀነስ እንዳዩ ከሰይፉ ያረገዘች መስሏቸው ተደሰቱ። በኋላ ግን ከሌላው ልጃቸው ከኃይለመለኮት ማርገዝዋን ሲሰሙ ተናደው እጅጋየሁን በእግር ብረት አሰሩዋት። ቆይቶም በአማላጆች ተፈታች። ንጉሥ ሣህለሥላሴ ይህን ወሬ ሰሙ። ልጃቸው የንጉሥ ልጅ ሆኖ ገረድ በማፀነሱ ተናደው ወሬው እንዳይሰማ እጅጋየሁን ከርስታቸው ከአንጐለላ ሄዳ እንድትቀመጥ አደረጉ።

“እጅጋየሁ የመውለጃ ጊዜዋ ሲደርስ ወንድ ልጅ ወለደች። የእጅጋየሁን መውለድ ንጉሥ ሣህለሥላሴ ሲሰሙ የልጁን ሥም “ምን ይልህ ሸዋ በሉት” ብለው ስም አወጡ። ‘ምን ይልህ ሸዋ’ ያሉበት ምክንያት የእኔ ልጅ ከገረድ በመውለዱ ሸዋ ምን ይል ይሆን? ለማለት ፈልገው ነው። በኋላ ግን በሕልማቸው ከምን ይልህ ሸዋ ጋር አብረው ቆመው ከእሳቸው ጥላ የልጁ ጥላ በልጦ፣ በእግር የረገጡትን መሬት ሲያለካኩ እርሳቸው ከረገጡት ልጁ የረገጠው ረዝሞ አዩ። ይህን ሕልም ካዩ በኋላ “ምኒልክ የእኔ ስም አይደለም። የእሱ ነው። ስሙን ምኒልክ በሉት” ብለው አዘዙ።

“እዚህ ላይ ንጉሥ ሣህለሥላሴ “… ምኒልክ የእኔ ስም አይደለም የእሱ ነው…” ያሉት በጥንት ጊዜ “ምኒልክ በሚል ስም የሚነግሥ ንጉሥ ኢትዮጵያን ታላቅ ያደርጋታል” የሚል ትንቢት ስለነበረ ሣህለሥላሴ ሲነግሱ “ስሜ ምኒልክ ይሁን” ብለው ነበር። ምኒልክ በሚለው ስም ሣህለሥላሴ ለምን እንዳልነገሱ ክብረ-ነገሥት በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ብንመለከት “… የሸዋው ንጉሥ ሣህለሥላሴ፣ ምኒልክ በሚባል ሥም ሊነግሱ ሲሉ አንድ መነኩሴ በዚህ ስም አትንገስ። መጥፎ አጋጣሚ ያመጣብሃል። ይህ ስም የሚስማማው ከመጀመሪያው ወንድ ልጅህ ከኃይለመለኮት ለሚወለደው ነው። ይህም ስም የሚወጣለት የልጅ ልጅህ ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርግ ትልቅ ንጉሥ ይሆናል አላቸው…” ይላል። ስለዚህ ነው የልጁን ስም ምኒልክ ያሉት።

“ይሔው ከድሃ መወለድ በዘመኑ እንደ ነውር ተቆጥሮ፣ ምኒልክ በሣህለ ሥላሴ ቤተ-መንግሥት ውስጥ እንዳያድጉ ተደርጓል። ፀሐፌ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ እየፈሩ ከፃፉት ብጠቅስ፤ “… ስለ ሕዝብ ዕረፍትና ጤና፣ የተወለደው ምኒልክ በአንጐለላ መቅደላ ኪዳነ ምህረት ክርስትና ተነስቶ ጠምቄ በሚባል ሀገር በሞግዚት አኖሩት….” ብለዋል። አንጐላላ ከደብረብርሃን ከተማ አጠገብ ያለ መንደር ነው። መንዝ ውስጥ ባለው ጠምቄ በሚባለው አምባም ከእናታቸው ጋር ሰባት ዓመት ተቀመጡ።

“ፈረንሣዊው ሄነሪ አውደን በ1872 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር። ስለ ምኒልክ ትውልድ ሲተርክ “… ምኒልክ በተወለዱ ጊዜ መስፍኑ (ኃይለመለኮት) ልጁን አልቀበልም ብለው ካዱ። በነገሩ መሐል ወ/ሮ በዛብሽ ገብተው ሌሎቹንም ዘመዶቹን ሰብስበው ልጁ ኃየለመለኮት መሆኑን አምነው ተቀበሉ።…” ይላል።

“ብዙ ታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚሉት ወ/ሮ እጅጋየሁ ውብና ከደህና ቤተሰብ መወለዳቸውን ይገልፃሉ። የአባታቸውንም ስም ግን የሚገልፅ የለም። ለማ አዲያሞ ይባላሉ። ይህን ሲተነትኑም አንዳንዶቹ ከጉራጌ አገር የተማረኩ ባርያ ናቸው ይሏቸዋል። ባርያ ማለት በገንዘብ የሚሸጥ ብቻ ሳይሆን በጦርነት የሚማረክ ሁሉ ባርያ ይባላል። ይህ ሁሉ ይቅርና ዋናው ቁም ነገር ታሪክ መስራት እንጂ ትውለድ አይደለም። ታላቁ ናፖሊዮን እንደዘመኑ አፃፃፍ ወደ ላይ የሚቆጠር አልነበረውምና ታሪኩን የሚፅፈው ፀሐፊ ቀርቦ “የትውልድ ታሪክዎን ከየት ልጀምር?” ቢለው “ያለፈውን ትተህ ከእኔ ጀምር” አለ እንደሚባለው ነው።

ዛሬ በአጤ ምኒልክ ዙሪያ እንድታነቡልኝ የጋበዝኳችሁ ጽሁፍ ምክንያቱ ደግሞ የአድዋ ድል መባቻ ሳምንት በመሆኑ ነው። እኚህ በጥቁር ዓለም ውስጥ እጅግ ገናን ስም እና ዝና ያላቸው ንጉስ፣ ኢትዮጵያ በነጮች የቅኝ አገዛዝ ስር እንዳትወድቅ ተአምራዊ በሚባል የጀግንነት ውሎ ሀገራቸውን ነፃ ያወጡ መሪ ናቸው።

“ምኒልክ ተወልዶ ባያነሣ ጋሻ፣

ግብሩ ዕንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ።”

ተብሎ የተገጠመላቸው ናቸው። መልካም የአድዋ ድል ሣምንት እመኝላችኋለሁ።

በጥበቡ በለጠ


ታላቁ ኢትዮጵያዊ ባለቅኔ፣ ፀሐፌ-ተውኔት፣ መራሔ-ተውኔት፣ ታሪክ ፀሐፊ እና የስነ-ሰብ ተመራማሪ የነበረው ፀጋዬ ገ/መድህን ከዚህች ዓለም በሞት የተለየው የካቲት 18 ቀን 1998 ዓ.ም ነበር።

ፀጋዬ በ1950ዎቹ ውስጥ ብቅ ካሉት የኢትዮጵያ ብዕረኞች መካከል ከግንባር ቀደሞቹ አንዱ ነበር። ልዩ የግጥም ችሎታ፣ ልዩ የቴአትር ፀሐፊና ተመራማሪ ነበር። በዓለም ታሪክ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ሰፊ ምርምር ያደረገ የጥበብ ሰው ነበር።

ፀጋዬ ከፃፋቸው ታሪካዊ ቴአትሮች መካከል ጴጥሮስ ያችን ሰዓትዘርአይ በሮማ አደባባይ፣ ቴዎድሮስ፣ እና ምኒልክ ይገኙበታል። ከእነዚህ ቴአትሮች ውስጥ ምኒልክ እስከ አሁን ድረስ በመድረክ አልተሰራም። ጉዳዩ እንቆቅልሽ ነው። ይህን የመሰለ ታላቅ ተውኔት እስከ አሁን ድረስ ተሰርቶ አለመቅረቡ ችግሩ እምኑ ላይ እንደሆነ መገመት አይቻልም። ነገር ግን ታሪኩ ጐበዝ አዘጋጅ ይፈልጋል። አርቲስት ስዩም ተፈራ ወደፊት አዘጋጀዋለሁ ብሎ በአንድ አጋጣሚ ተናግሮ ነበር። እስከ አሁን ድረስ እርሱም አላዘጋጀውም። ብሔራዊ ቴአትር፣ ሀገር ፍቅርና ማዘጋጃ ቤቱ ዝም ብለዋል። ቢያንስ የአድዋ በዓል በሚከበርበት ወቅት የዚህን ታላቅ ባለቅኔ ቴአትር መስራት እንዴት አልቻሉም!?

     ፀጋዬ እጅግ ግዙፍ የሚባሉ የጥበብ ስራዎችን አበርክቶ ከዚህች ዓለም የተሰናበተው በዛሬዋ እለት የካቲት 18 ቀን 1998 ዓ.ም ነበር። ዘጠኝ ዓመት ሆነው። ይህን ሰው ለመዘከር ስራዎቹን ማቅረብ ግድ ይለናል። ፀጋዬ የኢትዮጵያ ሼክስፒር ነውና!

     ዮሐንስ አድማሱ

     ዮሐንስ አድማሱ ኢትዮጵያዊ ታላቅ ባለቅኔ ነበር። እጅግ ምናባዊ ጥልቀትና የገዘፈ ሀሳብ ያላቸውን ግጥሞችን በመጻፍ ይታወቃል። በአዲስ አበባ ኒቨርሲቲ ውስጥ ተወዳጅ የስነ-ጽሁፍ መምህርም ነበር። ከነዚህ ሙያና ተሰጥዎቹ በተጨማሪ ጎበዝ ሃያሲ ነበር። በኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ ውሰጥ ካበረከታቸው አያሌ ጉዳዮች መካከልም ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

1.  ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ አጭር የህይወትና የጽሁፉ ታሪክ

2.  ጠባሳው (ያልታተመ አጭር ታሪክ)

3.  ጠገራው (ያልታተመ አጭር ልቦለድ)

4.  ውርርዱ (ያልታተመ አጭር ልቦለድ)

5.  ከራኒው (ያልታተመ አጭር ልቦለድ)

6.  የቼሆቭን The Lament የተሰኘ አጭር ልቦለድ በ1962 ዓ.ም ሰቆቃው ብሎ ተርጉሟል

7.  የዶስቶዬቭስኪን The Brothers Karamazove የተሰኘውን ልብ-ወለድ ተርጉሟል።

ሌሎችንም በርካታ ስነ-ጽሁፋዊ ውለታን ለሀገሩ አበርክቶ ያለፈ “ተወርዋሪ ኮከብ” (shooting Star) ነበር።

ከአያሌ ስራዎቹ መካከል በግንቦት ወር 1961 ዓ.ም በመነን መጽሄት ላይ የልቦለድ ሥነ-ጽሁፍ ጉዞ በሚል ርእስ ሂሳዊ ደሰሳ አድርጎ ነበር። ጽሁፉ በርካታ የአትየጵያን ልቦለዶች በተለይ ከ1963 ዓ.ም በፊት የነበሩትን ምሁራዊ ድፍረት በተሞላበት ብእር በሚከተለው መልኩ ጽፎት ነበር።

     ሥነ ጽሁፍ የሰው ሐሳብና ስሜት በኪነት ኀይል ግዘፍ ነሥቶ፣ አካል ገዝቶ የሚታይበት ጥበብ ነው። የአማናዊ ሥነ ጽሑፍም ምንጩ የሰው ልጅ እውነታ (ሪያሊቲ) ነው። እውነታውም በልደትና በሞት መካከል የተዘረጋ ህላዌ ነው።

     ሥነ ጽሑፍ ጠቅላላ ዓላማው ማስደሰት ነው። ይኸንንም ጉልህ ዓላማ የሚፈጽመው ሁሉን አቀፍ የሆነ የሕይወት ሒስ በማቅረብ ነው። ሥነ ጽሑፍ ጉልህ ዓላማውን ለመፈጸም ጥራትና ወጥነት እንዲኖረው ያስፈልጋል። “በኖኅ ዘመን በቀን ብዛት፣ የማይነቅዝና የማይሻግት፣” መሆን አለበት። አለዚያ አጉል ጉሕና ወይንም ብስና እንጂ ሥነ ጽሑፍ ሊሆን አይችልም። ሥነ ጽሑፍን ሥነ ጽሑፍ የሚያደርገው የደራሲው የኪነት ኀይሉ፣ የማስተዋልና የማንጠር ስጦታው፣ ያስተዋለውንና ያነጠረውን ከሰው ልጅ እውነታ ጋራ በቋንቋ ኀይል አገናዝቦና አዋሕዶ እነሆኝ ብሎ የሚያቀርብበት ልዩ ችሎታው ነው። ግልብ ደራሲ ግልብ ተመልካች ነው። ጽሑፉም በዚያው ልክ ግልብ የችርቻሮ ጽሑፍ ይሆናል። 

     ይህን አባባል መሠረት በማድረግ ከሰላሳ ሶስት እስከ ሰላሳ አንድ ዓመተ ምሕረት ድረስ ስላለው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ጉዞ አንዳንድ ነገር ለማውሳት እወዳለሁ።

     በጠቅላላው በነዚህ በሃያ ሰባት አመታት ውስጥ አማርኛ ያፈራው ሥነ ጽሑፍ ብዛት እንጂ ጥራት የለውም። ከጥልቀት ይልቅ ግልብነት፣ ከውበት ይልቅ አስቀያሚነት፣ (አስቀያሚነት ውበት ነው ወይንም ውበት አለው ካልተባለ በቀር) ከሥነ ጽሑፋዊ እውነት ይልቅ የአንቀጸ ብጹዓን ምኞት ይገኝበታል። ሥነ ጽሑፍ የሕይወት ሒስ በመሆን ፈንታ የወሸነኔ ስሜት መግለጫ ሆኗል። እስከ አሁን ድረስ አካሄዱ አጉል ነው። የጎድን ነው። አቅጣጫም ያለው አይመስል። የወደፊት አካሄዱን መተንበይ ባይቻልም፤ እስከ አሁን ድረስ ተመልክተን የተገነዘብነው አካሄዱ አብነት ለመሆን የሚችል አይደለም። በአጭሩ በሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ያፈራነው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ፤ ቀደም ካለው የአማርኛ ስነ-ጽሁፍ አዝመራ ጋራ ሲነጻጸር ደረጃው፣ ጥራቱና ወጥነቱ፣ በዚያውም መጠን ውበቱና አስደሳችነቱ አለመጠን ዝቅ ያለ ነው።

  እያደር ይጫጫል፣ እየሰነበተ ይደገድጋል፣ እየባጀ፣ እየከረመም ይመነምናል። ለዚህ አሳዛኝ ከቶም ድቀታዋ ሁነት ምክንያት ከሆኑት ከብዙዎቹ ነገሮች ሦስቱን ጠቅሼ ከመዘርዘሬ አስቀድሞ ጥራት፣ ወጥነት፣ ጥልቀትና ውበት ያላቸው ሁለት መጽሐፍት መጥቀስ እፈልጋለሁ። ሁለቱ መጻሕፍት “እንደ ወጣች ቀረች” እና “ፍቅር እስከ መቃብር” ናቸው። (ከነዚህ ከሁለቱ ደረጃ ባይደርሱም ሌሎች መጻሕፍትም በመጠኑ አሉ።)

     እነዚህ ሁለቱ መጸሕፍት የኪነት ውጤት ናቸው። ጥልቀታቸውም፣ ውበታቸውም፣ ሌላውም መልካም የምንለው ጥራታቸውም ከዚሁ ከኪነት መንፈሳቸው ይሠርጻል። በ“ቴክኒክ” (ቅርጽ) በኩል ከሞላ ጎደል ምሉዕ ናቸው። በትልም፣ በባሕርያት አቀራረጽ፣ በአተራረክ፣ በቋንቋ... ወዘተ። እነዚህ ሁለት የልብ ወለድ መጻሕፍት በመጀመሪያዎቹ አንቀጾች የሰነዘርኋቸውን ሐሳቦች በሙሉም ባይሆን በከፊል አቀናብረው ይዘዋል። ሁለቱም ሁለት ልዩ እውነታ ያቀርባሉ። በአንድ ነገር ይተባበራሉ፣ ይገናኛሉ። ሁለቱም ያቀረቡልን የሕይወት ሒስ ነው። ሁለቱም በየገጾቻቸው በሚገኙት ቃላት ኀይል እንድናዳምጥ፣ እንዲሰማን፣ በተለይም እንድናይ ለማድረግ ሞክረዋል። ይኸም ሙከራቸው በሙሉም ባይሆን በከፊል ስለተቃናላቸው የምንፈልገውን ነገር እንድናገኝ በዚህም እኛ አንባቢያኑ ሐሴት እናደርጋለን።

     በጠቅላላው ከስልሣ ሶስት ዓመተ ምህረት ወዲህ ጥሩ የምንላቸው የአማርኛ (የኪነት) መጻሕፍት ጥቂት ናቸው። ከመቶ ዘጠና ዘጠኙ “ብላሽ” ናቸው።

     ለምን?

     ደራሲያኑ በደፈናው ወይንም በጠቅላላው ልዩ ልዩ የኪነት ጽሑፍ ቴክኒክ አያውቁም፤ ቢያውቁም አይጨነቁም። ጽሑፋቸውን የቴክኒክ ግብዝነት አለልክ ያጠቃዋል። የጽሑፍ ቴክኒክ ለኪነት ጽሑፍ አብይ ከሆኑት ነገሮች አንዱና ዓይነተኛው ነው። የሀገራችን የኖረ፣ የቆየ የጽሑፉ ቴክኒክ አለ፤ የውጭ ሀገርም የፅሑፍ ቴክኒክ አለ። ደራሲያኑ የውጭውንም ሆነ የሀገራችን የፅሑፍ ቴክኒክ አብስለው እና ጠንቅቀው አያውቁትም።

     በሀገራችን (ለምሳሌ ያህል) የታወቀ፣ የተለመደ፣ ከሙያ የዋለ የገድል አፃፃፍ ቴክኒክ አለ። ገድል የአንድ ሰማዕት ወይም የአንድ ፅድቅ የሕይወት ታሪክ ነው። ገድል በጠቅላላው የሚያወጋው ወይም የሚተርከው የሰማዕቱን ወይም የጻድቁን ተጋድሎ ነው። ስለ ሰማያዊ ልዕልና፣ ለሰማያዊ ክብር መንፈሳዊ የሆነ ምድራዊ ተጋድሎ። አተራረኩ ከመንፈሳዊ እውነት ላይ የተመሠረተ ነው። ትልም እና ባህሪያት የአተራረክ ስልትም አለው። የአተራረክ ፈሊጥም አለው። ብሎም “ገድለ ተክለ ሐይማኖትም” መጥቀስ ይበቃል። አንቱ የሚባል ወይም ለመባል የሚሻ ደራሲ የገድልን አጻጻፍም አጥርቶ ማወቅ ግዴታው ነው። ብዙ ነገር ይማራል፣ አያሌ ጥበብ ይቀስማል። በቴክኒክ ይበለፅጋል።

     የቅኔ ቴክኒክ አለ። ይኽንንም ቴክኒክ ማወቅ የማንኛውም ደራሲ፣ በተለይም የገጣሚ ተግባርና ግዴታ ነው። (የቀረውን እንዳለፈው ያነቧል።) ሌሎችም ብዙ የጽሑፍ ቴክኒኮች በሀገራችን በብዛት ይገኛሉ፣- የተረት፣ የሙሾ፣ የእንቆቅልሽ፣ የእንካስላንትያ፣ የቀረርቶ… ወ.ዘተ። እነዚህን ሁሉ አንቱ የሚባል ወይም ለመባል የሚሻ ደራሲ አጠናቆ ማወቅ ግዴታው ነው።

     ከውጭም አለም የተገኙ የጽሁፍ ቴክኒኮች አሉ። የተውኔት የረዥም ልብ ወለድ የአጭር ልብ ወለድ ወዘተ። ደራሲዎቻችን የውጭውንም የጽሑፍ ቴክኒክ አጥርተው አያውቁትም። በአጭሩ የሚጽፉት አገኝ አጣቸውን ነው፤ የሚጽፋት በንዝሕላልነት ብዙ ጊዜም በግዴለሽነት በማን አለብኝ መንፈስ ነው። ለዚህም ምስክር የሚሆኑ ብዙ መጻሕፍት አሉ። ለጊዜው ግን አንዱን መመልከት ይበቃል። “አድልዎን በሰይፍ” መጽሐፋ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ “ብላሽ” ነው” ። ጉድለቱን ጉልህ አድርጎ ማሳየቱ ነው ታሪኩ የሚተረከው በአንደኛ መደብ ነጠላ ቁጥር /እኔ/ ነው። አንድ ታሪክ በአንደኛ መደብ መተረክ የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ታላቅ ጥንቃቄ ይጠይቃል። አደገኛ ነው። በተለይ ለጀማሪ ደራሲ ክፉ አዚመኛ አንጋዳ ነው። እላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ገጽ ድረስ በአንደኛ መደብ ይተርክና መጽሐፉ ሊያበቃ ጥቂት ሲቀረው ”ሞትኩ” ይላል። ይኸን የሚለው የታሪኩ ዋና ባሕርይ ነው። “ሞትኩ” ካለም በኋላ ታሪኩን ይተርካል። ሙቷል በዓፀደ ሥጋ አይገኝም ማለት ነው። ይኸ ንስሐ የሌለው ታላቅ የቴክኒክ በደል ነው። እንደዚህ ያለው በደል የሚፈጸመው ምናልባት ካለማወቅ ይሆናል፣ ምናልባትም ከንዝሕላልነት ወይንም ከንቀት ምክንያቱ የትኛው እንደሆነ አላውቅም። ከደራሲው ጋር መነጋገር ምክንያቱን ለማወቅ ይረዳ ይሆናል። ይኸንና ይኸንን የመሰለ የቴክኒክ ጉድለት ያለባቸው መጻሕፍት እጅግ ብዙ ናቸው። የሚከተሉትን ይመለክቷል፡- “ውብ ነበረች፤ ሥራ ገንዘቡና ጓደኛው”፤ “የጉድጓዱ ምስጢር”፤ “ንስሐ”፤ “እውነት ስትጠፋ” ፤“የሐሳብ እስረኛ”፤ “ከማን አንሼ”፤ “እኛም ይድረሰን..ወዘተ” እነዚህ ጥቂቱ ናቸው።

     የዘመናችን ደራሲያን በጽሑፍ ቴክኒክ በኩል ከሀገራቸውም አልሆኑ፣ ከውጭውም አልሆኑ። የሀገራችንንና የውጭን አዳቅለውም መጢቃ ቴክኒክ አላቀረቡልንም። ወይንም ከሁለት አንዱን ብቻ ተከትለው ወጥ ጽሑፍ አላበረከቱም። እስከ አሁን ድረስ ቴክኒካቸው ውጥንቅጥ የልብ ትኩሳት የልብ ቃር የሚሆን አጉል ቅይጥ ነው። ከሥርዓት ይልቅ ምስቅልቅል የሰፈነበት ነው።

     ምናልባት ከዚህ ውጥንቅጥ ከዚህ ምስቅል ኢትዮጵያዊ የሆነ ወጥ ቴክኒክ እንደ ብሂል እንደ ሠረዝ እንደ ጎዳና ቅኔ ያለ ይፀነስ ይሆናል። ይኸ መቸም ምኞት ነው። ምኞቱ እውት እንዲሆን የኔ ብቻ ሳይሆን ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ማደግ መዳበርና ኃይል መሆን የሚቆረቆር ኢትዮጵያዊ ሁሉ ፍላጎት ነው።

     ሁለተኛው ነቁጥ የሒስ ጥበብ አለመለመድና የሐያሲ አለመኖር ነው። በባህላችን የሒስ ሰዎች አሉ። ከዚህም የተነሣ ደራስያኑ መጻሕፍታቸው በጋዜጣም ሆነ በመጽሔት ሲተቹ /በቀጥተኛ ሒስ/ አንዳንዶቹ ያኩርፋሉ፤ አንዳንዶቹ ይዝታሉ፤ አንዳንዶቹ በጋዜጣም ሆነ በመጽሔት ይሳደባሉ፤ ይኸ መንፈስ ከየት እንደመጣ አላውቅም። ጉዳዩ ጥልቅ ምርምርና ጥናት የሚያስፈልገው ነው። ይሁን እንጂ አንድ የማውቀው ነገር አለ። ሒስ በቅኔ ቤት የተለመደ ነው። የቅኔው ተማሪ ከቅኔው ትምህርት ሌላ በጥበቡ የሚጎለምሰው የኪነት ተውህቦውን የሚያተባው የሚያራቅቀውና የሚያደረጀው በሒስ ጥበብ ነው። የተማሪውን ቅኔ የቀለም ጓደኞቹና መምህሩ ይተቻሉ። እሱም እንደዚሁ ያደርጋል። ተማሪዎቹ የመምህራቸውን ቅኔ ይተቻሉ። አንዳንዴም ብትንትኑን ያወጡታል። ኩርፊያና ስድብ ዛቻና ቅያሜ የለም፤ ይህ መልካም ጥበብ እያለ ደራስያናችን ለምን በሒስ /በደንበኛ ሒስ/ ይቆጣሉ።

     ሒስ ለሥነ ጽሑፍ ሕይወት መጠበቂያ ዓይነተኛና ፍቱን መድኃኒት ነው። ሒስ ጉድለትንም ጥራትንም መግለጫ ጥበብ ነው። ማስተማሪያም ነው። እንደ ስድብ እንደ ነውር መቆጠር የለበትም። በሒስ መስተዋትነት ስኃውን የማይከላ ሥነ ጽሑፍም ሆነ ደራሲ ከበድን አንድ ነው። ተገቢ ቦታውም ቤተ መዘክር ነው።

     ሶስተኛ ነቁጥ፤ ያለፋት የሃያ ሰባት ዓመታት የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ሶስተኛ ጉድለቱ የቋንቋ ነው። በጠቅላላው ቋንቋው ውበት ጥራትና ተጠየቅ የተለየው በፀያፍ /ሰዋሰው/ የተበከለ በቃላት እጥረት የተሞሸረ ነው። ይኸን ጉድለት የፈጠሩ ደራስያኑ ናቸው እንጂ ቋንቋው አይደለም። ቋንቋው ማለፊያ ባለሙያ ልባም ደራሲ ካገኘ ብዙ ሰንፍ የሚያስገባ አይመስለኝም። ለዚህም አብነት የሚሆኑ የሚከተሉት ቀደምት ደራስያን ናቸው። አፈወርቅ ገብረእየሱስ፣ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ብላቴንጌታ ሕሩይ ወልደ ሥላሴ፣ አለቃ ታዬ፣ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ወዘተ። በመጻሕፍት በኩል /እላይ የተጠቀሱት ደራስያን ከጻፏቸው መጻሕፍት ሌላ/ መጽሐፈ መነኮሳትና አርባዕቱ ወንጌልን መመልከት ይበቃል።

     የአሁኑ ዘመን ደራስያን አማርኛ ለምን ተበላሸ? በዚሁስ የሚቀጥለው ለምንድን ነው? ሁለት ምክንያት መስጠት ይቻላል። አንደኛ ደራስያኑ ትምህርት ቤት በነበሩበት ጊዜ ጥሩ አማርኛ እንዲማሩ አልተደረገም። ሁለተኛ ደራስያኑ የሚያነቡ አይመስልም። ጥሩ ጥሩ የሆኑ ተነበው በቋንቋቸው ጥራት በዘይቤያቸው ውበት የሚለዩ መጻሕፍት ጠፍተው አይደለም አሉ። ከፍ ብዬ የጠቀሰኋቸው መጻሕፍት ጥቂቱ ናቸው፤ እነሱን የመሳሰሉ በብዛት አሉ። ፈልጎ ማንበብ ብቻ ነው የሚያስፈልገው። መጻሕፍቱን የጠቀስኳቸው ስለ ይዞታቸው ሳይሆን /ይዞታቸውን የማይፈቅዱ ይኖሩ ይሆናል/ በጠቅላላው ስለቋንቋቸው ጥሩነት ነው፤ ስለምናባቸው /ኢማጂኔሽን/ ስፋት ነው፤ ስለ ዘይቤያቸው አስገራሚትና ውበት ነው። ዛሬ ያሉንም ሆኑ ወደፊት የሚነሱት ደራስያን እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን መጻሕፍት በየጊዜው ቢያነቡ ቋንቋቸው ይዳብራል፤ አስተሳሰባቸው ይተባል፤ ሐሳባቸውን -ጃ ሳይላቸው እንደ ልባቸው መግለጽ ይችላሉ። የማይሰለች ለዛና ወዝ፣ ውበትና ጥራት ያለው “ዞሌ” ጽሑፍ መጻፍ ይችላሉ።

     የጽሑፌ ኃይለ ቃል በድርሞ መልክ የሚከተለው ነው። በአለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ያፈራነው የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ በጠቅላላው ጥራቱና ወጥነቱ አለመጠን ዝቅ ያለ ነው። ይኸው የሆነበት ምክንያት

ሀ/ በቴክኒክ ጉድለት

ለ/ በሒስና በሐያሲ እጦት

ሐ/ በደራስያት አማርኛ መበላሸት

      ከነዚህም ምክንያቶች ለሁለቱ  ለ “ሀ” ና ለ “ሐ” ኃላፊዎቹ በከፊል ደራስያኑ ናቸው። አያነቡም፤ የማወቅና የማጥናት ጉጉት የላቸውም። ለሁለተኛው ምክንያት “ለ” ኅላፊነታቸው ኢርቱሀ ነው። ሒስ አለመቀበላቸው ወይንም በሒስ መበርገጋቸው።

     የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ የተሻለ ደረጃ እንዲይዝ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ተፅእኖው ለመላው ዓለም እንዲተርፍ ከተፈለገ ደራስያናችን /ዛሬ ያሉትም ሆኑ ወደፊት የሚሱት/ ታላቅ ተጋድሎ ማድረግ አለባቸው። የተጋድሎ ጎዳና ረዥም ሁኖ ጎዳጉድ የበዛበት፤ ቅርቅፍት ነው፤ ተስፋ የመቁረጥ ግን አያስፈልግም። እንደጥንታውያኑ ለሀገራቸው ነጻነት ሕይወታቸውን በየጎራው በየሜዳው በየአረሁ እንደሰውት ኢትዮጵያዊን አባቶቻችን ባጭር ታጥቆ የሥነፍሑፍ ዘገር ነቅንቆ፤ የሥነ ጽሑፍ ጋሻ መክቶ ለሥነ ጽሑፍ መጋደል የየአንዳንዱ ደራሲ ፈንታ ነው።

      ኢትዮጵያውያን ደራስያን በዓለም የሥነ ጽሑፍ ሸንጎ ላይ ተሰልፈው የሚወዳደሩበትን ዕለት በናፍቆት እጠባበቃለሁ።

      (የዚህ ሂስ አቅራቢ ዮሀንስ አድማሱ በአጸደ ስጋ የኖረው ከመስከረም 1929 እስከ ሰኔ 1967 ዓ.ም ነበር።

በጥበቡ በለጠ

 

የኪነ-ጥበብ ሰዎች በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነትና ፍቅር መሠረት በማድረግ ለበጎ ተግባር ራሳቸውን ማሰለፍ ባደጉት ሀገራት በአብዛኛው የተለመደ ነው። የኪነ-ጥበብ ሰዎች ለበጎ አድራጎት ተግባር አድናቂዎቻቸውን ሲጋብዙ እና የተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎችን ሲያከናውኑ ከፍተኛ ገቢ ማሰባሰብ እና ያንን ገቢ ደግሞ ለምግባረ ሰናይ አገልግሎት ሲያውሉ ሕዝባዊና ማህበራዊ ጥሪያቸውን ኃላፊነታቸውን ተወጡ ተብሎም ይነገራል።

ማህበራዊ ኃላፊነት /Social Responsibility/ በኪነ-ጥበብ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው። ጥበበኞች ለሕዝባቸው፣ ለወገናቸው፣ ለሐገራቸው ልማት ብልፅግና እንዲሁም ርዕይ ከሁሉም ቀድመው ከፊ መሰለፍ እንደሚገባቸው ብዙዎች ያምናሉ።

በቀደመው ዘመን ኢትዮጵያ በረሀብ ስትመታ እነ ማይክል ጃክሰን፣ ቦብ ጊልዶፍና፣ እነ ሄሪ ቤላሮንቴን የመሳሰሉ ታላላቅ ጥበበኞች የጥበብ ተሰጥኦዋቸውን ሰንቀው ለሀገራችን ችግር ቀድመው የደረሱልን ነበሩ። በዝግጅቶቻቸውም ትልቅ ገቢ አሰባስበዋል።

በሀገራችንም ቢሆን ጥበበኞች ብዙም ሳይሆን አልፎ አልፎ ሙያቸውን ለበጎ ተግባራት ሲያውሉ ይታያሉ።

ከሰሞኑ ደግሞ ኒውዮርክ ውስጥ ያሉ ወጣት ሰዓሊያን ከተለያዩ ዓለማት ተሰባስበው የተሠጣቸውን የጥበብ ፀጋ ለበጎ ተግባር አውለውታል። እነዚህ የጥበብ ባለሙያዎች በዕድሜያቸው በጣም ወጣቶች ናቸው። የተሰበሰቡትም ከኢትዮጵያ፣ ከካናዳ ከአሜሪካ እና ከልዩ ልዩ የአውሮፓ ከተሞች ነው።

ለዚህ ለበጎ ተግባራቸውም የሰጡት መጠሪያ Artists for Charity (AFC) ወይም ወደ አማርኛ ስንመልሰው አርቲስቶች በግብረ ሰናይ ዓላማ እንደ ማለት ነው። በማናታን ኒውዮርክ የተሰባሰቡት እነዚህ ጥበበኞች ልዩ ልዩ ሥራዎቻቸውን በጨረታ በመሸጥ ፣ ታዳሚዎቻቸውን ደግሞ የሚግቢያ ዋጋ በማስከፈል ለበጎ ተግባር የሚል ገንዘብ አሰባስበዋል። ገንዘቡ በHIV ኤድስ ምክንያት ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት እንዲሁም ደግሞ ከዚሁ ባይረስ ጋር አብረው የተወለዱ ልጆችን መደጎሚያ ብሎም ደግሞ ልጆቹ ወደፊት ለመሆን የሚፈልጉትን ነገር ህልማቸውን ማሳኪያ ይሆን ዘንድ የተቻላቸውን አድርገዋል።

እነዚሁ ወጣት የስዕል ባለሙያዎች በዩናይትድ ስቴትስ ርዕሰ ከተማ በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ይህን ጥበብን ለበጎ ተግባር የማዋል መርሃ ግብራቸውን ከሰሞኑ ያካሂዳሉ። ወጣቶቹ ሰዓሊያን የሚባሰቡበት ለ8ኛ ጊዜ በሚካሔደው የጥበበኞች የበጎ ሥራ ቀን ላይ ተሳትፈው በብዙ ችግሮች ውስጥ ላሉ ህፃናት መደጎሚያ የሚሆን ገቢ ለማሰባሰብ ነው።

ከአዘጋጆቹ መካከል የሆነው ኢትዮጵያዊው ወጣት አርቲስት እንደሚናገረው ከሆነ ይህ መርሃ ግብር የሚካሔደው በጎ ፈቃደኛ በሆኑ የጥበብ ሰዎች አማካይነት ነው። እነዚህ ሰዎች ጊዜያቸውን እና ሙያቸውን ብሎም ገንዘባቸውን ለዚህ ለተቀደሰ ዓላማ የሚያውሉ መሆናቸውን ተናግሯል።

እነዚህ በጎ ፈቃደኛ ሰዎች ከተለያዩ የጥበብ መስኮች ውስጥ የተውጣጡ ብሎም ደግሞ ከአሜሪካ፣ ከካናዳ እንዲሁም ከአውሮፓና ከአፍሪካ መምጣታቸውንም ተናግሯል።

ከበጎ ፈቃደኞቹ መካከል አንዷ የሆነችው አሜሪካዊቷ ሀና ስትናገር ልጆች ህልም አላቸው፣ አንደ ለመሆን የሚያልሙት ነገር አለ። ውስጣቸው የሚነግራቸው ነገር አለ። እዚያ ነገር ላይ ለመድረስ ደግሞ አጋዥ ይፈልጋሉ። ምክንያቱም አቅም የላቸውማ። ስለዚህ እኛ ደጀን ልንሆናቸው ይገባል የሚል ሀሳብ ሰንዝራለች።

በተለይ ከዚሁ ከHIV ቫይረስ ጋር የሚኖሩት ህፃናትም የወደፊት ህልማቸውን ሲናገሩም ተደምጠዋል።

-    ሳድግ አርቲስትነት መሆን ነው የምፈልገው፣

-    ሳድግ ፓይለት ነው መሆን የምፈልገው፣

-    ሳድግ ደራሲ ነው መሆን የምፈልገው፣

-    ዳንሰኛ ነው መሆን የምፈልገው፣

-    ኢንጂነር /መሀንዲስ/ ነው መሆን የምፈልገው፣

እነዚህ ከHIV ቫይረስ ጋር የሚኖሩትን ህጻናት ጥበበኞች የትም ቦታ ቢኖሩ መረዳት እንደሚገባቸው አዘጋጆቹ ይናገራሉ። ህፃናቱ በHIV ወላጆቻቸውን ያጡ በመሆናቸውና ከቫይረሱ ጋርም ስለሚኖሩ ክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው አዘጋጆቹ ወጣት አርቲስቶች ይናገራሉ።

በዚሁ በአርቲስቶች ድጋፍ ተጠቃሚ የሆኑ ታዳጊ ህፃናትም ስለ HIV ኤድስ ቫይረስም ማብራሪያ ሰጥተዋል። እነዚህኑ ልጆች መሠረት አድርጎ በተሰራው ዶክመንተሪ ፊልም ወስጥ የሚከተለውን ብለዋል። “ነገን ለማየት ህልም አለን። ያንን ህልማችንን ደግሞ እውን የምናደርገው እኛም ጠንክረን እናንተም ስትወዱን ስታቀርቡን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በነዚህ ወጣት አርቲስቶች የሚደገፉት ህፃናት ኑሯቸው ከቀን ወደ ቀንም እየተሻሻለ መምጣቱን ይናገራሉ።

ከአሜሪካ ሆነው ኢትዮጵያዊያን ህጻናት የሚረዱትን ወጣቶች በማስተባበር እየሰራች ያለችውና በሃያዎቹ የእድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኘው ታታሪዋ ወጣት አበዛሽ ታምራት ነች። በእርሷ አማካይነት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ከተለያዩ አለማት እየተሰባሰቡ ሙያቸውን ለበጎ ዓላማ እያዋሉት ይገኛሉ።

እንደ አበዛሽ አባባል፣ አሁን ከተለያዩ የዓለማችን ሀገራት የተውጣቱ በጎ ፈቃደኛ ሰዎች ለውጥ ማምጣት ችለዋል። ለእነዚህ ህጻናት አጋርነታቸውን ገልጸዋል። ወደፊትም በሌሎች ሀገራት ያሉና የእኛን ድጋፍ ለሚሹ ህፃናት በሙሉ ከጎናቸው መቆም አለብን ብላለች።

    በአጠቃላይ ሲታይ፣ እነዚህ ወጣት የኢትዮጵያ አርቲስቶች ጥበብን ለበጎ ተግባር ማከናወኛ አድርገው ብዙ እየተጓዙ ነው። ሌሎችም የእነርሱን አርአያነት ከተከተሉ ጥበብ ማህበራዊ አገልግሎቷ ሰፊ ይሆናል ተብሏል።

በጥበቡ በለጠ


በዓለም አቀፉ ደረጃ በአያሌ ቱሪስቶች የሚነበበው `Rough Guides` በመባል የሚታወቀው የህትመት ውጤት በቅርቡ ለአንባቢዎቹ አንድ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ይህም ጥያቄ እ.ኤ.አ. በ2015 ዓ.ም ማየት የምትፈልጓቸውን አስር የዓለማችን ሀገራትን ጥቀሱ የሚል ነበር። በዚሁ እጅግ ተነባቢ በሆነው የቱሪስቶች ጋይድ መፅሐፍ ውስጥ በተሰጠው ምላሽ ኢትዮጵያ ከተመረጡት አስር ሀገራት መካከል የሰባተኛ ደረጃን ማግኘቷን ድርጅቱ በድረ-ገፁ ባሰራጨው ዜና ይፋ አድርጓል።

ኢትዮጵያ በምርጫው ውስጥ መካተቷ እና የዚህ ሁሉ ቱሪስት የፍላጎት አቅጣጫ መሆኗ ወደፊት ሀገሪቱ ከዚሁ ዘርፍ ልትጠቀምበት የምትችልበት እድል በእጅጉ ፈክቶ እያንፀባረቀ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል።

በዚሁ `Rough Guides` በተሰኘው የቱሪስቶች መፅሀፍ ውስጥ አስር ምርጥ የቱሪስቶች ምርጫ የሆኑት የ2015 ዓ.ም ሀገራት ይፋ ሆነዋል። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው፡-

 1. 1. ዩናይትድ ኪንግደም (UK)
 2. 2. ግሪክ
 3. 3. አይስ ላንድ
 4. 4. ኢንዶኔዥያ
 5. 5. ጃፓን
 6. 6. ቺሊ
 7. 7. ኢትዮጵያ
 8. 8. ቱርክ
 9. 9. ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ (USA

 10. 10. አየርላንድ

ሆነው በቱሪስቶች ተመርጠዋል።

ኢትዮጵያ ከነዚህ አስር ሀገራት ውስጥ በቱሪስቶች ምርጫ ውስጥ መካተቷን በተመለከተም የመፅሐፉ ድረ-ገፅ ማብራሪያ ሰጥቶበታል። እንደ ድረ-ገፁ ገለፃ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ አያሌ የቱሪዝም መስዕብ ያላት ሀገር መሆኗ ተዘግቧል። በተለይ ደግሞ በተፈጥሮ መስዕብም ቢሆን ከታላቁ የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ጀምሮ ልዩ ልዩ ግዙፍ ተራሮች ያሏት ሀገር በመሆኗ መልክአ ምድሯም እንድትመረጥ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ዜናው በሚከተለው መልኩ ገልጾታል፡-

From the dramatic Great Rift Valley to the lush highlands, the diversity of Ethiopia’s landscapes might surprise you.

በማለት ገልጿል።

ይህን የ2015 ዓ.ም ምርጥ አስር የዓለማችን የቱሪስቶች ምርጫን ይፋ ያደረገው ድረ-ገፅ roughguides.com/best-places/2015/peoples- choice/ የሚሰኝ ሲሆን፤ ኢትዮጵያንም በተመለከተ አዲስ መፅሐፍ በቅርቡ አሳትሞ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።

በጥበቡ በለጠ


የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በዘንድሮው የ2015 ዓ.ም ከሸለማቸው ምርጥ ሰዓሊያን መካከል ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሰአሊት ጁሊ ምሕረቱ አንዷ በመሆን ተሸላሚ ሆናለች።

ጁሊ ምሕረቱ ለሽልማት ያበቃት በአለማችን ውስጥ ያሉ ህዝቦችን፣ ሐገራትን በስዕል ጥበቧ ባህላቸውን እና ታሪካቸውን እያቀለመች የማቀራረብና የመግለፅ ችሎታዋ ከእለት ወደ ዕለት አስደማሚ እየሆነ በመምጣቱ እንደሆነም ተገልጿል።

ጁሊ ምህረቱ እ.ኤ.አ. በ1970 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተወለደች ሲሆን እ.ኤ.አ. በ1977 ዓ.ም ደግሞ ወደ አሜሪካ በመጓዝ ትምህርቷም ሆነ ሥራዋ በዚህችው አሜሪካ ውስጥ ሆኗል። በግማሽ ጎኗ ከኢትዮጵያዊ ቤተሰብ የተወለደችው ይህች ሰዓሊት በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ውስጥ ካሉት ዘመናዊ ሰዓሊያን ተርታ ስሟ ከፍ ብሎ የሚጠራ ነው።

በኒውዮርክ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ጁሊ ምሕረቱ በሥዕል ችሎታዋ አያሌ የአሜሪካንን ሽልማት ያገኘች ስትሆን ስራዎቿም በልዩ ልዩ የአሜሪካን ታላላቅ ጋላሪዎችና ሙዚየሞች ውስጥ የተቀመጡላት ናት።

በአሜሪካ መንግሥት ስቴት ዲፓርትመንት አማካይነት የባሕል ዲፕሎማሲን በማስፋፋት ረገድ ተጠቃሽ መሆኗ የተነገረላት ጁሊ ምህረቱ፤ በእንግሊዝና በአሜሪካ፣ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ ብሎም በሌሎችም ሀገራት ውስጥ ያሉ የባህል ትስስሮችን አጉልታ በማሳየት ስሟ ከፍ ብሎ ይጠራል።


የ2015 ዓ.ም የስቴት ዲፓርትመንት ተሸላሚ መሆኗም በዓለም አቀፉ ደረጃ በእጅጉ ከሚከበሩ ሰዓሊያን ተርታ የሚያስገባት መሆኑም ተነግሮላታል።

ጁሊ ምህረቱ፤ በተለያዩ ታላላቅ መድረኮች ላይ ተሸላሚ እንደሆነ የሚነገርለትን እና በዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ የአያሌ ጭቅጭቆች፣ ክሶች እና ውዝግቦች ማዕከል የሆነውን “ድፍረት” የተሰኘውን ፊልም ኤግዘኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰር እንደሆነችም ይታወቃል።


Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100
Page 10 of 15

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us