You are here:መነሻ ገፅ»ኪነ-ጥበብ
ኪነ-ጥበብ

ኪነ-ጥበብ (262)


በጥበቡ በለጠ

 

በዚህች ምድር ላይ በሰው ልጅ አዕምሮ ከተሰሩ አስደማሚ ጉዳዮች መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ምስጢር ሆነው ስለቆዩት የቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ህንፃዎችና ራሱ ቅዱስ ላሊበላስ ቢሆን ማን ነው? በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነው።


እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ 10 አብያተ ክርስቲያናት ትንግርት ሆነው ብቅ አሉ። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት የታነፁት ከአንድ አለት ውስጥ ተፈልፍለው ነው። ስማቸውም ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያናት ወይም በእንግሊዝኛው Rock hewn Churches ይባላሉ።


እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ማለትም UNESCO ምድር ላይ ካሉ እፁብ ድንቅ ኪነ-ሕንፃዎች መካከል እንደ ትንግርት እየቆጠራቸው ስለ እነሱ ብዙ ፅፏል። ከዚህ ሌላም የሰው ልጅ ሁሉ ቅርስ ናቸው ብሎ በዓለም መዝገብ ላይ ካሰፈራቸው በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።


ንጉስ ላሊበላ እነዚህን አብያተ-ክርስቲያናት ለምን ሰራቸው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ጥንታዊ ሠነዶች እንደሚጠቁሙት፣ ኢትዮጵያዊያን በድሮ ጊዜ ወደ እየሩሳሌም በእግራቸው እየተጓዙ ተሳልመው ይመጡ ነበር። ታዲያ በዚህ ጉዞ ውስጥ በርካቶች በግብፅ በረሀ ውስጥ በሽፍቶችና በቀማኞች ይገደሉ ነበር። ይዘረፉ ነበር። ብዙዎች ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም በእግር ተጉዘው ወደ ሀገር ቤት በህይወት የሚመለሰው በጣም ጥቂቱ ነበር። ታዲያ የሕዝቡ ሞት እና እንግልት ያሳሰበው ቅዱስ ላሊበላ ዳግማዊት ኢየሩሳሌምን በኢትዮጵያ እገነባለሁ ብሎ ተነሳ። እናም በ23 ዓመታት ውስጥ በሰው ልጅ አዕምሮ ድንቅ የሚባሉትን 10 ኪነ-ህንፃዎችን ከአንድ አለት ፈልፍሎ ካለምንም የኮንስትራክሽን ስህተት ሠርቶ ጨረሰ።


እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ግን መልስ የሌላቸው። ከነዚህም መካከል እነዚህን ኪነ-ህንፃዎች የሰሯቸው ጥበበኞች በቁጥር ስንት ነበሩ? የሚል ጥያቄ። ግን ማንም ሊመልሰው አይችልም። ሌላው ጥያቄ 23 ዓመታት ሙሉ እንዲህ አለት እየፈለፈሉ ሲሰሩ ለምን ስህተት አልፈፀሙም? ለምን ፍፁም እንከን የለሽ አድርገው ሠሩት? ማነውስ በዘመኑ አርክቴክት የነበረው? የኪነ-ህንፃዎቹ ዲዛይን ምን ላይ የተነደፈው? ማነውስ ከአለት ፈልፍዬ ይህን ተአምር ልስራ ብሎ መጀመሪያ ያሰበው? ብዙ የማይመለሱ ጥያቄዎች አሉ። ለዚህም ነው ላሊበላ የምድሪቱ ትንግርት ነው የሚባለው።
የላሊበላ ምስጢራት ተዘርዝረው አያልቁም። ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ኩነ-ህንፃዎቹ በሙሉ ማለት ይቻላል የታላላቅ ፍልስፍናዎችና አመለካከቶች ማንፀባረቂያ የሆኑ ምልክቶች አሉት። ግድግዳው በሙሉ ጥበብ ነው። ከ6 ሚሊየን ይሁዲዎችን እንዲገደሉ ያደረገው አዶልፍ ሂትለር ይጠቀምበት የነበረው የስዋስቲካ ምልክት ከ800 ዓመታት በፊት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ተንፀባርቀዋል። የግሪኮች መስቀል የሚባለው ባለ ድርብ የመስቀል ቅርፅ ከዛሬ 800 ዓመታት በፊት ላሊበላ ላይ ነበሩ። በአስረኛው መቶ ክፍለ ዘመን አውሮፓ ውስጥ ተዋጊዎች ነበሩ የሚባሉት በስም አጠራራቸው ቴምፕለርስ /መስቀላዊያን/ ተብለው የሚጠሩት ይይዙት ነበር የሚባለው መስቀል ክሩዋ ፓቴ ይባላል። ይህ የመስቀል ቅርፅ ላሊበላ ላይ አለ። እናስ ላሊበላ እነዚህን መልክቶች ከየት አመጣቸው? አወዛጋቢ ጥያቄ ነው።


የሚገርመው ነገር፣ አንዳንድ ፀሐፊያን እነዚህን የመስቀል ቅርጾች እያዩ የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰጡ ቆይተዋል። በመስቀሎቹ ቅርፅ ምክንያት እነዚህን የቅዱስ ላሊበላን ኪነ-ህንፃዎች የሰሯቸው ከውጭ ሀገር የመጡ ባለሙያተኞች ናቸው በማለት የፃፉ አሉ። እውን የሰራቸው ማን ነው?


የላሊበላን ኪነ-ህንፃዎች የሰሯቸው እነማን ናቸው? የሚለው ጥያቄ ከዛሬ 400 ዓመታት ጀምሮ አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቶ ነበር። አወዛጋቢ ያደረገው ፖርቹጋላዊው አገር አሳሽ ቄስ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ በ1520 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለአራት ዓመታት ቆይቶ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ ባሳተመው መፅሐፉ የገለፀው ነው።


አልቫሬዝ ሲገልፅ በኪነ-ሕንፃዎቹ አሠራር በእጅጉ ተደንቋል። እኔ ያየሁትን ብፅፍ የሚያምነኝ የለም ብሎ ተጨንቋል። እንዲህም ብሎ ፃፈ።


እኔ ያየሁትን ላላያችሁ ሰው እንዲህ ናቸው ብል የሚያምነኝ የለም። ነገር ግን ያየሁት ሁሉ ዕውነት መሆኑን በሃያሉ እግዝአብሔር ስም እምላለሁ።


እያለ ፖርቹጋላዊው ቄስ እና ፀሐፊ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ስለ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ትንግርታዊ አሠራር ፅፏል።


ከዚያም ሲገልፅ እነዚህን አብያተ-ክርስያናት ማን ሰራቸው ብዬ ስጠይቅ ፈረንጆች ናቸው ብለው ቄሶች ነገሩኝ ብሎ ፅፏል። ከዚያ በኋላ የመጡ አጥኚዎች በሙሉ በፈረንጆች የተሰሩ ናቸው እያሉ ፅፈዋል። የቅዱስ ላሊበላ ገድል ወይም ገድለ ላሊበላ ደግሞ የሚናገረው ሌላ ነው። ገድለ ላሊበላው ፈረንጆች ሰሩት አይልም። ገድለ ላሊበላው ጉዳዩን ወደ መንፈሳዊ ፀጋነት ይወስደዋል። እነዚህ ኪነ-ህንፃዎች የተሰሩት መላዕክት እያዘዙት በቅዱስ ላሊበላ አማካኝነት እንደሆነ ነው የሚገልፀው። “ስራው ረቂቅ ከመሆኑ የተነሳ ከመላዕክት ውጭ በሰው እጅ ብቻ እንዲህ አይነት ተአምራዊ ኪነ-ህንፃ ሊሰራ አይችልም” በሚል የዕምነት ሰዎች ይከራከራሉ። ክርክሩ አያልቅም። ምክንያቱም ኪነ-ህንፃዎቹ ምስጢር ናቸውና!


ግን የዛሬ 60 ዓመት ላይ የኢትዮጵያ የነፃነት አርበኛና ሞደርናይዘር የብልፅግና አመላካች የነበረችው እንግሊዛዊቷ ሲልቪያ ፓንክረስት በዚህ በላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ላይ የሚሰነዘሩት አስተያየቶች ቆረቆሯት። እርሷ ደግሞ ሰዓሊ ናት። ጋዜጠኛ ናት። ደራሲ ናት። እናም ላሊበላ ላይ መመራመር ጀመረች። እነዚህን ኪነ-ህንፃዎች ማን የሰራቸው ብላ ጠየቀች። ብዙ የውጭ ሀገር ፀሐፊያን ፈረንጆች እንደሰሯቸው እየተቀባበሉ ፅፈዋል። እናም ይህ አባባል ሲልቪያን ቆረቆራት።


ስለዚህም የላሊበላን አብያተ-ክርስቲያናት የሚመስሉ ኪነ-ህንፃዎች በሌሎች ሀገሮች መኖርና አለመኖራቸውን ለማወቅ ሲልቪያ ፓንክረስት ዓለምን ማሰስ ጀመረች። በግበፅ፣ በእስራኤል፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በህንድ፣ በቻይና ብሎም በልዩ ልዩ የጥንታዊ ስልጣኔዎች መገኛ በሚባሉት ስፍራዎች በሙሉ ዞረች። ኢትዮጵያንም ዞረች አየች። ውስጠ ሚስጢሯን አጠናች። ከዚያም Ethiopia A Cultural History የተሰኘ ግዙፍ መፅሐፍ አሳተመች። በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ስለ ቅዱስ ላሊበላ አብያተ-ክርስያናት አሠራር ለመጀመሪያ ጊዜ የተደራጀ ጥናትና ምርምር የሰራች የኢትዮጵያ ፍፁም ወዳጇ የሆነች ሴት ሲልቪያ ከወደ እንግሊዝ ትጠቀሳለች።


የሲልቪያ ፓንክረስት ዓለምን የማሰስ ጉዞ ማጠናቀቂያው የሚከተለው ነው። አንደኛ የቅዱስ ላሊበላን ኪነ-ህንፃዎች የሚመስሉ አሠራሮች በየትኛውም ሀገር በዚያ ዘመን እንዳልተሰሩ አረጋገጠች። እንደ ሲልቪያ መከራከሪያ፣ ፈረንጆች ሰርተውት ቢሆን ኖሮ በፈረንጅ ሀገር ቅርፃቸውና አሻራቸው ይኖር ነበር ብላ ፃፈች። ግን የለም። እንደ ሲልቪያ ገለፃ፣ የቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ህንፃዎች አሠራር የተቀዳው ከዚያው ከኢትዮጵያ ውስጥ ነው።


የጥንታዊ አክሱማውያን ጥበቦች በላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ላይ ሙሉ በሙሉ ተንፀባርቀዋል። ከአለት ላይ ፈልፍሎ ኪነ-ህንፃዎች መስራት ማነፅ የኢትዮጵያዊያኖች የጥንታዊ ስልጣኔያቸው ነው። “ቅዱስ ላሊበላም እነዚያን አሠራሮች ፍፁም ውበትና ለዛ አላብሶ አስደማሚ አድርጐ ሠራቸው እንጂ የውጭ ሀገር ሰው ፈፅሞ አልነካቸውም” እያለች ሲልቪያ ፓንክረስት በጥናትና ምርምር መፅሀፏ ገልፃለች።


ታዲያ እነዚህ የኢትዮጵያ ብርቅ የጥበብ ውጤቶች የሆኑት አብያተ-ክርስትያናት በአሁኑ ወቅት ክፉኛ አደጋ ውስጥ ናቸው። የመሰንጠቅ እና የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። እናም ጉድ ከመሆናችን በፊት ሁሉም አካላት ላሊበላን ሊጠብቀው ይገባል። ኢትዮጵያ ስትጠራ ቀድሞ ብቅ የሚል የስልጣኔ መገለጫ ነውና።

ጽዮን ማርያም

December 06, 2017

በጥበቡ በለጠ

 

ጽዮን ማርያም በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ውስጥ የምትገኝ በምድራችን ላይም እጅግ ጥንታዊ ከሆኑ የክርስትና ማዕከል መካከል አንዷ ናት። ጽዮን ማርያም የብዙ ጉዳዮች መገለጫ ናት። በዚህች ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው አስርቱ ትእዛዛት የተፃፉበትና የተቀረፁበት ፅላት ወይም ፅላተ-ሙሴ የሚገኝበት ምድር ነች። በክርስትናው ዓለም ውስጥ ቅዱስ ስፍራ ተብለው ከሚጠሩት መካከል ግንባር ቀደሟ ነች።


ይህች ቤተ - ክርስትያን ሕዳር 21 ቀን ዓመታዊ ክብረ በዓሏ፣ ንግስናዋ ነው። ታዲያ በዚህ ክብረ በዓል ላይ ለመታደም ከዓለም ዙሪያ አያሌ ቱሪስቶች አክሱም ከተማ ታድመዋል። ከተማዋ በሃይማኖቱ ተከታዮች በቱሪስቶች ተጨናንቃለች።


በክርስትናው ዓለም ውስጥ ትኩረት በመሳብ አክሱም ፅዮንን የሚያክል ስፍራ የለም። ምክንያቱም የፈጣሪ ትዕዛዛት ያሉበት ቦታ ስለሆነ እና ከዚህ በላይ ደግሞ በምዕመናን ዘንድ የሚታንበት ማስረጃ ስለሌለ ጽዮን ማርም በክርስትናው ዓለም ውስጥ ጎላ ብላ ትጠቀሳለች።


ጽላተ-ሙሴ ዛሬ 3ሺ ዓመት ከእየሩሳሌም መንበሯ ተወስዶ ወደ “ኢትዮጵያ መምጣቱ ይነገራል” ያመጣው ደግሞ ቀዳማዊ ምኒልክ ነው” የንግስት ሣባ ልጅ።
ጽዮን ማርያም የጽላተ - ሙሴ መቀመጫ ከመሆኗም በላይ ኢትዮጵያዊው ንጉስ ኢዛና ወደ ክርስትና ሲቀየር በዘመናዊ መልክ ፅዮን ማርያምን ከዛሬ 1600 ዓመታት በፊት አነጻት። እናም የኢትዮጵያ አስተዳደርና የሀይማኖት ማዕከል ሆነች።


የኢትዮጵያ ነገስታት ወደ ስልጣን ሲመጡ መጀመሪያ አክሱም ጽዮን ሔደው የንግስና ቆብ የሚጭኑበት የአመራር ስፍራ ናት። ኢትዮጵያ እንድትመራ፣ ሕዝቦችዋ መሪ እንዲኖራቸው ቀብታ የምትልክ ቤተ-ክርስትያን ነበረች።


አክሱም ጽዮን እንደ ቅዱስ ያሬድ አይነት የዜማና የመዝሙር ሊቅ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ለዚህች ምድር ያፈራች ስፍራ ናት።
ከዚህ ሌላም ፈላስፋዎቹን እነ ዘርአያዕቆብን እና ወልደ ሕይወትን የፈጠረች ምድር ነች።


አክሱም ታላላቅ መሪዎች እነ ካሌብና ገብረመስቀልን የመሣሰሉ የስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በእምነትም በአገር አመራርም ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ገናና ነገስታት አፍርታለች። ዓፄ ካሌብ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ውስጥ ድንቅ ኪነ-ሕንጻዎችና በማነጽ፣ የስልጣኔ ተምሳሌት የሆኑ፣ የሀገርንም ዳር ድንበር ለማስከበር ዓፄ ካሌብ ወደር የማይገኝላቸው ገናና መሪ ነበሩ።


አክሱም ሌላም አስገራሚ መሪ ነበራት። ይህ ሰው ንጉስ ባዜን ይባላል። የንጉስ ባዜን ታሪክ እንደሚያወሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት ኢትዮጵያን ለስምንት ዓመታት መርቷታል። ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ደግሞ ወደ እየሩሳሌም ቤተልሔም ሔዶ ኢየሱስን ያየ የኢትዮጵያ ብቸኛው መሪ እንደሆነ ታሪክ ገድሉ ይተርካል። የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ አይቶ ወደ ኢትዮጵያ ሀገሩ መጥቶ ከዚያም ለስምንት ዓመታት ሀገሩን እንደመራ ይነገርለታል።


ይህ ንጉስ ከዚህች ዓለም በሞት ከተለየ በኋላም የተቀበረበት ቦታም በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪካዊ ሆኖ የቱሪስት መስዕብ ከሆነ ቆይቷል። መካነ መቃብሩ የሚገኘው ከአክሱም ወደ አድዋ በሚወስደው አውራ ጎዳና፣ ከአክሱም ከተማ መውጫ ላይ ወደ ግራ ከሚገኝ ኮረብታማ ግርጌ ነው። ለመካነ መቃብሩ ምልክት እንዲሆንም በደንብ የተጠረበና ቁመቱ 6 ሜትር የሆነ አንድ ባለግርማ ሀውልት ተተክሎበታል። ይህ መካነ መቃብር ተቆፍሮ የወጣው በ1957 ዓ.ም ነው። ደረጃዎቹም ከድንጋይ የተፈለፈሉ ደረጃዎች አሉት። ውስጡም አደራሽ አለ። ይህ አስገራሚ ንጉስ ባዜን፤ ገና ያልተነገሩለት እጅግ ብዙ ታሪኮች አሉት። ወደፊት እናወጋለታለን።


አክሱም ጽዮን የአለምን ስልጣኔና ግስጋሴ ችግርና ስኬትን ሁሉ እያየች እየታዘበች የኖረች የረጅም ዘመን መካነ ታሪክ፣ የሰው ዘር ሁሉ ሄዶ እንዲጎበኛት እንዲያያት የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት /UNESCO/ የሚመከርባት አክሱም ተወስቶ የማያልቅ ታሪክ አላት።


የፅሁፍ ጥበብ የተንጸባረቀባት፣ ትምህርት ያበበባት፣ የሊቃውንተ መናሀሪያ ሆና ኖራለች።


በዮዲት ጉዲት መነሳት አክሱም እየተዳከመች ሄደች። ፈራረሰች። ወርቃማ ታሪኳም ከዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ተዳከመ።


በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም በተነሳ የእርስ በርስ ጦርነት አክሱም ጽዮን ፈራረሰች። ከዚያም አገር ሲረጋጋ በ1635 ዓ.ም አፄ ፋሲል ከጎንደር ወደ አክሱም ሄደው የጎንደር የኪነ-ጥበባት ቅርስ የሚታይበትን ቤተ-ክርስትያን አሰሩላት። ይህ የአፄ ፋሲል ኪነ-ህንፃ ዛሬም በግርማ ሞገሱ ድምቀት አክሱም ከተማ ላይ ተገማሽሮ ይታያል።


አሁን ደግሞ አጅግ ዘመናዊ ሆኖ የሚታየውን ግዙፉን የፅዮን ማርያምን ቤተ-ክርስትያን ያሰሩት አፄ ኃይለሥላሴ ናቸው። ባለቤታቸው እቴጌ መነንም በ1845 ዓ.ም ባለ አንድ ፎቁን የፅላት ቤት አሰርተዋል።


አክሱም ፅዮን የኢትዮጵያ የእምነት፣ የታሪክ፣ የፍልስፍና የአስተዳደር፣ የብዙ ነገሮች መገለጫ ናት። የሀርቫርድ ዩኒቨርስቲው የአለማችን የክርስትና ዕምነት ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሄነሪ ሊዊስ ጌት wonders of the African world የተሰኘውን ትልቁን ዶክመንተሪ ፊልማቸውን ሲሰሩ አክሱምን “የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የስልጣኔ ማዕከል” ሲሉ ገልጸዋል። ዘጠኝ ሰዓታትን የሚፈጀው ይህ ግዙፍ ዶክመንተሪ ፊልም የአክሱም ጽዮንን ሙሉ ታሪክ ሁሉ ዘርዝሮ የሚያሳይ ነው።


ግርሀም ሀንኩክ የተባለው ጋዜጠኛና ጸሐፊ The sign & the seal በተሰኘው መጽሐፉ “አክሱም ጽዮን ውስጥ ፅላተ ሙሴን አገኘሁ” ብሎ በመፃፉ የአለም ታሪክ ተቀይሯል።


ምክንያቱም ፅላተ-ሙሴ በምድር ላይ ሁሉ ተፈልጎ ጠፍቷል። ኢትዮጵያ ግን አለኝ እኔ ዘንድ ነው ብላ የምትናገር ሀገር ብቻ ሳትሆን ብዙ ማስረጃዎችንም የምታቀርብ ምስጢራዊት ሀገር መሆኗን አያሌ ጸሐፊያን ገልፀዋል።


ህዳር 21 ቀን ይህች የኢትዮጵያ እና የዓለም የክርስትናው ተከታይ ሕዝብ ሁሉ የእምነት መገለጫ የሆነውን ጽላተ-ሙሴን የያዘችው አክሱም ጽዮን በየዓመቱ ትነግሳለች። ታሪኳን ስንመረምር ኢትዮጵያ ምን ያህል የምድሪቱ አስገራሚ ሀገርና መኩሪያ እንደሆነች እንገነዘባለን።¾

በጥበቡ በለጠ

 

የቀድሞው ፕሬዘደንት መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በ1951 ዓ.ም “አየርና ሰው” የተሰኘ በአየር የበረራ ታሪክ ላይ ተመርኩዞ የተጻፈ መጽሀፍ በድጋሚ ታትሞ ነገ ከጥዋቱ 2፡30 ጀምሮ በቢሾፍቱ አየር ሀይል ቅጽር ግቢ ውስጥ በልዩ ወታደራዊ ስነ ስርአት ይመረቃል። የመቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ከ1930 ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአየር ሀይል ባልደረባና አብራሪ ሆነው ስራ የጀመሩ ናቸው። ታሪካቸውም ከመጀመሪያዎቹ የተማሩ የአየር ኃይል መኮንኖች ምድብ ውስጥ ይጠራሉ። ከአየር ኃይልነት እስከ ሀገር ፕሬዘዳንትነት ሀገራቸውን አገልግለዋል። በድርሰት አለም ውስጥም የደራሲያን ማህበር ከመስራች አመራር አባላት መካከል አንዱ ናቸው።

 

ይህ ነገ አያሌ ታዳሚያን በሚገኙበት ስነ ስርአት በደብረዘይት ቢሾፍቱ አየር ኃይል ግቢ ውስጥ የሚመረቀው ይህ መጽሀፍ በበረራ ታሪክ ውስጥ በአማርኛ በ1951 ዓ.ም የታተመ የመጀመሪያው መጽሀፍ ነው። ስለዚሁ መጽሀፍ ግርማ ሲጽፉ የሚከተለውን ብለዋል።

 

አየርና ሰው የተሰኘውን መጽሐፍ ስጽፍ በዚያን ጊዜ እንግሊዝኛ የተማሩ ብዙ ሰዎች ባልነበሩበት ጊዜ ነበር ፈረንሳይኛ ማወቅ የግድ ይላል።

 

ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ስለአየር ንቅናቄ ስለማያውቁ አይሮኘላንን ቴክኖሎጂ ያስገኘው ነገር መሆኑን በአማርኛ በመጻፍ አስተዋጽኦ ለማድረግ አሰብኩ።

 

የአየር ንቅናቄ ታሪክ ከ400 ዓመታት በፊት በእውቁ ሳይንቲስት ኢጣሊያዊ ሊዎናርዶ ዳቪንቺ ተተለመ። ከመትለምም አልፎ ንድፈ ኃሳቡን ጻፈ። ሄሊኮኘተር የምትመስል ስዕል በመሳል ከአየር የከበደ ነገር በየአር ውስጥ ለመንሳፈፍ የሚችል መሆኑን ገልጾ ጻፈ።

 

ይሁን እንጂ የሊዎናርዶ ዳቪንቺ ሀሳብ ይፋ ወጥቶ ዋጋ ያገኘው በተጻፈ በ190 ዓመቱ ነው። በተፃፈ በ190 ዓመቱ ፍልስፍናው ከተገለጸ በኋላ ሰው እንዳሞራ በአየር ውስጥ የመብረር ምኞቱ እየሰፋ ሄዶ በ1903 ዓ.የብስክሌት ጠጋኞች የሆኑ የራይትስ ልጆች አልቪራና ዊልበር ራይትስ በትንሽ ሞተር የታገዘ የመጀመሪያውን ከአየር የከበደ መሣሪያ ሠርተው በአየር ውስጥ ከ40 ሜትር በላይ በረሩ። ይህ ነው የአውሮኘላን ታሪክ።

 

ከአየር የከበደ መሣሪያ በአየር ላይ በረረ። የሌዎናርዶ ዳቪንቺ ህልም እውን ሆነ።”

 

የቀድሞው የኢ.... ፕሬዚደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ

 መጽሀፉን በተመለከተ ዶክተር ዳዊት ዘውዴ 2002 . የሚከተለውን ጽፈው ነበር።

ክቡር ኘሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የመቶ አለቃ በነበሩበት ጊዜ አየርና ሰው በሚል ስያሜ አሳትመውት የነበረውን የእድሜ ባለጸጋ መጽሐፍ ከሃምሣ አንድ ዓመታት በኋላ እንደገና እንዲታተም የተባበሩትን በቅድሚያ ላመስግናቸው።

መጽሐፉ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ የቀሰመውን እውቀት በማዳበር እንዴት አይሮኘላንና ሌሎችንም በራሪና ተንሳፋፊ መሣሪያዎችን ሊፈጥር እንደቻለ የሚያስረዳና የሚያስተምር ቋሚ ሰነድ ነው በውስጡ ያካተታቸው ጉዳዮች የዘመኑን ሁኔታ ያንፀባርቃሉ።

አርና ሰው የተባለው መጽሐፍ መሠረት ያደረገው ክቡር ኘሬዚዳንት ግርማ በነበራቸው የበረራ ፍቅርና ዝንባሌ ላይ ሲሆን ሌዎናርዶ ዳቪንቺ በፀነሰው ንድፍ ላይ ተንተርሰው የራይትስ ወንድማማች የማብረር ችሎታቸውን እንዴት እንደገነቡና ዘመናዊ የአየር አገልግሎት እንዴት እንደዳበረ እየተራቀቀም እንደመጣ በዝርዝር ይተነትናል። ቀደም ብለው የተደረጉ ምርምሮችን መሠረት አድርገው የዘመናችን የበረራ ምጥቀትና እድገት የቴክኖሎጂ ፈሩ ከምን ተነሥቶ የት እንደደረሰ ባቀረቡበት በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ቁም ነገሮችን ቀላልና ግልጽ በሆነ ዘዴ አስተላልፈውልናል።

መጽሐፉ ወቅታዊና ዘመናዊ የአየር አገልግሎት ለሰው ልጅ ያበረከተውን ከፍተኛ ጥቅም አጉልቶ ከማሳየቱም በላይ በሰዎች መካከል ግንኙነትን በማዳበር ወሳኝ ሚና እንደተጫወተ በማስገንዘብ መገናኘት ቋንቋ ለቋንቋ ለመግባባትና የአንዱን የሥልጣኔ እርምጃ ሌሎች ተካፋይ ለመሆን እንዲችሉ ምክንያት ነው ይላል አይሮኘላን የሰውን ልጅ የጠቀመውን ያህል በአንደኛውና በሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች ጊዜና ከዚያም ወዲህ ያደረሳቸው ጉዳቶች በዚሁ መጽሐፍ ተገልጸዋል። በዓለም ዙሪያ በሥራ ሲዘዋዎሩ ከአይሮኘላን የበረራ ጉዞ ጋር የተያያዙ ገጠመኞችንም በዚሁ መጽሐፍ ውስጥ አክለዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ አይሮኘላን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የነበረውን ሁኔታ ክቡር ኘሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በታሪክነት መዝግበውታል። በአገራችን የአየር መጓጓዣ እንዴት እያደገ እንደመጣና ለሥልጣኔ ጉዞ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሆነም በሰፊው አውስተውታል። ራሳቸው ተካፋይ የሆኑበትና የሰለጠኑበት ሙያ በኢትዮጵያ እንዴት እንደተስፋፋም መጽሐፉ በሰፊው ያብራራል። የሲቪል አቪዬሽን አገልግሎት ከበረራው ጋር ተጣምሮ በኢትዮጵያ ማደጉንም ይገልጣል።

ወቅታዊና በሥነ-ጽሑፍ ምርምር የተደገፈ መጽሐፍ ከመሆኑም በላይ ሰው ከአየር ጋር ያለውን የተፈጥሮና የሥነ-ጥበብ ጥምር ታሪካዊ ግንኙነቶችን በጥልቀት አጉልቶ ያሳያል።

በጊዜው የመቶ አለቃ አሁን ኘሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በዚህ መጽሐፍ የሥነ-ጽሑፍ ችሎታቸውንም አስመስክረዋል።

 

ዳዊት ዘውዴ (ዶክተር)

ታህሣሥ 2002 .

ከዚህ ሌላ ደራሲው የመቶ አለቃ ግርማ /ጊዮርጊስ ስለ መጽሀፋቸው ላይ 1951 . አንድ አስገራሚ ነገር ጽፈዋል። የጻፉት ስለ አጼ ኃይለስላሴ ልጅ ስለ ልዑል መኮንን ነው። ይህም እንዲህ ይነበባል።

ግርማዊ ሆይ

ልዑል መኰንን መስፍን ሐረር ከጠላት ወረራ በኋላ የመብረር ትምህርት ሲጀመር ከመጀመሪያዎቹ በራሪዎች አንዱ ከመሆናቸው በላይ በመብረር ላይ በነበራቸው ጥልቅ ፍቅር ምክንያት የግል አውሮኘላኖች እየገዙ ሲያመጡ መንግሥቱ በዚያን ጊዜ ለትምህርት የነበረው አውሮኘላኖች ቁጥር ያነሰ ስለነበረ አብዛኛውን ጊዜ በልዑልነታቸው አውሮኘላን እንጠቀም ነበር።

ከዚህም ሌላ በመኖሪያ ቤታቸው ልዩ ልዩ ግብዣና የትምህርት ሲኒማዎችን እያሰናዱ በየጊዜው ያደርጉልን የነበረው እርዳታ ለትምህርታችን መስፋፋት የቱን ያህል እንደጠቀመን በዚች አጭር መግለጫ አትቶ ለመጨረስ አይቻልም።


ልዑልነታቸው ሰው አቅራቢ፣ ደግና ቸር፣ ደፋር ጅግና፣ አስተዋይ፣ አስተተዳዳሪ ከትልቅ መሪ የሚጠበቅ ችሎታና ቁም ነገር በሙሉ አሟልቶ የሰጣቸው በመሆናቸው የምንመለከታቸው እንደ አንድ መስፍን ሳይሆን እንደ ታላቅ ወንድማችን ነበር።

ልዑልነታቸው የመብረር ልምምድ ሲያደርጉ በነበረበት ጊዜ አብሮ የመብረር ዕድል ያጋጠመን ብዙዎቻችን በመብረር በነበራቸው ችሎታና ፈቃድ አድናቂዎቻቸው ነን።

ይህን የመሰለ የሞራል ደጋፊ የችግር ተካፋይ መሪ ከመካከላችን በመለየታቸው በአየር ሥራዎች ዙሪያ ለሚገኙት ከፍ ያለ ኃዘን እንደደረሰ ግልጽ ነው።

የሰው መታሰቢያው ለትውልድ የሚያልፈው በሐውልት የተቀረጸ በጽሑፍ የሰፈረ ሲሆን፣ መሆኑን በማመን በበኩሌ ልዑልነታቸው በአየር ሰዎች መሀል መታሰቢያ እንዲኖራቸው በማሰብ ቀደምት የአየር ጥናት መግለጫ የሆነችውን ይህቺን መጽሐፍ በታላቅ ትሕትና አበረክታለሁ።

ባሪያዎ

የመቶአለቃግርማወልደጊዮርጊስ።

ከዚህ በመለጠቅም መጽሀፋቸው ላይ የሚከተለውን መግቢያ ጽፈዋል።

 

መግቢያ

ሰው ራሱን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ በአንዳንድ ነገሮች ላይ ልዩ ዝንባሌ ይኖረዋል።

በልጅነቴ መኖሪያዬ ጃንሜዳ ልዑል አልጋ ወራሽ ግቢ ሲሆን የምማረው ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ነበር።

በዚያን ጊዜ አውሮኘላን የሚያርፈው ጃንሜዳ ላይ ስለነበር በየዕለቱ ሲነሣና ሲያርፍ የልጅነት ጠባይ እያታለለኝ በማየት ሰዓት አሳልፍ ነበር። በዚህ ምክንያት አስተማሪዬ አቶ ኮስትሬ ወልደ ጻድቅ ይቀጡኝ የነበረው ምሑራዊ ቅጣት የአየር ሰው ለመሆን ከነበረኝ ምኞት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ሳስታውስ እኖራለሁ።

ምንም እንኳን ለማመን አስቸጋሪ ቢመስል በዚያን ዘመን በአውሮኘላኑ ጭራና ክንፉ ላይ የሚታየው ተነቃናቂ ክፍል የአውሮኘላኑ ማዘዣ መሆኑ ይገባኝ ነበር። እጅግ ያስደንቀኝ የነበረው አውሮኘላኑ ሲነሣ ከግራና ከቀኝ ክንፉ ጎኑ ሰዎች ደግፈው እየሮጡ ለመነሳት ሲል ይለቁት የነበረው ነው። አየር ኃይል ትምህርት ቤት እስከገባሁና የአየርን ንቅናቄ ምሥጢር እስካወቅሁ ድረስ ይህ የሚደረግበትን ምክንያት ለመረዳት ጊዜ  ወስዶብኛል በትምህርት ረገድ ሁኔታውን ጠልቄ ስከታተል በዚያን ዘመን የነበሩ አውሮኘላኖች ፍጥነታቸው በጣም ዝግ ያለ ሆኖ ንፋስ ስለሚያስቸግራቸው የመነሻ ፍጥነት እስኪያገኙ ድረስ ሚዛናቸውንና አቅጣጫቸውን ጠብቀው እንዲሔዱ ለማድረግ የተፈጠረ ዘዴ መሆኑን ለመረዳት ቻልሁ።

ለምሳሌ ያህል የነበሩትን አውሮኘላኖች ፍጥነት ለመገመት ይጠቅማል ብዬ የማስታውሰው ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አውሮኘላን በእንጦጦ በኩል ለማረፍ ጃንሜዳን ሲጠጋ አፈ ንጉሥ አጥናፌ ግቢ ውስጥ ከባሕር ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ቀረ። የኢትዮጵያ አውሮኘላን ከባሕር ዛፍ ላይ ያርፋል እየተባለ ስለተወራ አገራችንን ለመውረር ይሰናዳ የነበረው ጠላታችን ተሸብሮ ነበር ይባላል። ምክንያቱ ግን የአውሮኘላኑ ፍጥነት በጣም ያነሰ ከመሆኑም በላይ አውሮኘላኑ ቀላል ስለ ነበረ ነው አውሮኘላኑ የባሕር ዛፎችን ቅርንጫፎች ሰባብሮ ጠንከር ያለው አንጠልጥሎ ሲያስቀረው በአውሮኘላኑ ውስጥ የነበሩት ነጂዎች ካደጋ የዳኑት።

ይህ በእኛ ሀገርና በእኛው እድሜ የተደረገ ሆኖ እኛም የዓይን ምስክር ስንሆን የሰው ልጆች በአውሮኘላን ኢንዱስትሪ መሻሻልና መለዋወጥ እጅግ ከፍ ካለ የእውቀት ደረጃ ላይ በአሁኑ ጊዜ የደረሱበት ሲገመት ያለፈው ለሰሚ የቆየ ተረት ይመስላል። የሆነውን ጽፎ ማቆየት ጠቃሚ ነው። ስለዚህ በተለይም ስለ አቪየሽን ቴክኒክ በውጭ አገር ቋንቋ የተጻፉትን በማንበብ ዘመናዊውን የቴክኒክ እርምጃ ለመከታተል ለማይችሉ አንባቢዎች የአየርና ሰው በሚል አርእስት የጻፍኩት ልዩ ልዩ ሐሳብ በጋዜጣ ካሁን በፊት በየጊዜው ተገልጿል።

ይህንኑ በመጽሐፍ ቅፅ ባዘጋጀው የበለጠ ይጠቅም ይሆናል በማለት በራሴ ልምድ /ኤክስፔሪየንስ/ ያገኘሁዋቸውንና በመከታተልም የደረስኩባቸውን የምትገልጽ ይህችን የመጀመሪያ የአየር ጥናት መግለጫ መጽሐፍ ለአየር ሥራ መስፋፋት ይጥሩ ለነበሩት ለተወዳጁ መስፍን ልዑል መኰንን ኃይለሥላሴ መታሰቢያ አድርጌ ለማበርከት ደፈርኩ።

 

የአዕዋፍ የመብረር ዘዴ

የክንፍ ባለቤቶች አዕዋፍ እንደምን እንደሚበሩ ማጥናት የመብረር ምኞት የነበራቸው ሁሉ ለአሳባቸው ማረፊያ ምክንያት ሆነ። ትላልቅና ትናንሽ አሞራዎች እንደምን እንደሚበሩና ሚዛናቸውንም እንደሚጠብቁ በክንፋቸው እንደምን እንደ ሚጠቀሙባቸው ማጥናት ለአሁኑ ጊዜ መብረር ዋና መሠረት ነው።

አዕዋፋት ሊበሩ የሚችሉት ክንፋቸውን በማጠፍና በመዘርጋት ነው። ማናቸውም ሕይወት ያለው ፍጥረት ራሱን የሚረዳበት ልዩ ልዩ አካል ከፈጣሪው ተሰጥቶታል። የአዕዋፋት ክንፋቸውን ስንመለከት ለሚኖሩበት አገር የአየር ሁናቴ በመጠናቸው ተገቢ የሆነ መሣሪያ አላቸው በብርድ አገር የሚሩት የውስጥ ሰብ የላይ ድርብ ሲኖራቸው በቆላ አገር የሚኖሩት ጅማታማ ሆነው ለነፋስ የሚሆን ክንፍ አላቸው። እንደሌላው ፍጡር ሁሉ እነዚህ ፍጥረታት የሚኖሩት ፈጣሪያቸው ባደላቸው መልካም መሣሪያ አማካይነት ነው።

ረጅምና አጭር፤ መሐከለኛ ሚዛን የሌለው በራሪ አሞራ እስካሁን ድረስ አልታየም። የአሞራ ክንፍ ብዙ ጊዜ ካገለገለ በኋላ በርጅና ምክንያት አልፎ አልፎ ላባው ይወድቃል። አወዳደቁም ከሁለት ክንፎቹ አንድ አንድ ላባ በትክክል ይወድቃል እንጂ ከያንዳንዳቸው ሁለት ወይም ሦስት አይወድቅም። አገልግሎታቸውን የፈጸሙት ላባዎቻቸው ምንም በርጅና ምክንያት ቢወድቁ በሚወድቁት ልክ አዲስ ላባዎች ከሥር ይበቅላሉ። አዲሶቹ ላባዎች አሮጌውን እየገፉ ያድጉና በአዲስ ጉልበት አገልግሎታቸውን ይቀጥላሉ። ይህም መለዋወጥ የሚከናወነው አሞራው ባለው ክብደት መጠን ለመብረር የተወሰነለትን ርቀት ከበረረ በኋላ ነው።

እያንዳንዱ አዕዋፍ በሰማይ ላይ ልዩ ልዩ የመብረር ዘዴ አለው። ክንፉን ለማጠፍ ከፍ ያለ ጉልበት ስለሚያስፈልገው ማናቸውም አዕዋፍ የሚበላው ምግብ እንደ ነዳጅ የሚያበረው በመሆኑ በብዙ ይመገባል።

በአገራችን በጣም ከታወቁት ለምሳሌ ያህል ከበራሪዎች ውስጥ አንበጣን እንመልከት። አንበጣ ምንም እንኳን አወጣጡ እንደትል ሆሄ የመብረር ዕድሜው ያጠረም ቢሆን መብረር ከቻለበት ወድቆ እስከ ሚያልቅበት ጊዜ ድረስ በእህልና በማናቸውም ለምለም ቅጠል ላይ የሚያደርሰው አደጋ ከፍ ያለ ነው።

አንበጣ በሰማይ ላይ እየበረረ ለመቆየት የሚችለው በላዩ ላይ ያለው ስብ እስኪያልቅ ድረስ በመሆኑ ስለዚሁ ጉዳይ ጥናት ካላቸው ሊቃውንት ታውቋል። አንድ አንበጣ በራሱ ክብደት ልክ በቀን ውስጥ ይበላል ተብሏል። እንግዲህ አንድ አንበጣ ሁለት ግራም ክብደት ቢኖረው በቀን ሁለት ግራም መመገብ አለበት። የአንድ አንበጣ መንጋ 125 ቶን ክብደት ሲኖረው ሙሉ ቀን ለመብረር 125 ቶን ምግብ መመገብ ይኖርበታል። ኃይልና ብርታት የሚሰጠው ስብ ሲያልቅ ሌላ ለመጨመር ወደ ምድር ይወርዳል። ከስቶና በጣም ርቦት ስለሚወርድ በመሬት ላይ ያገኘውን ማናቸውንም ነገር ሳይመርጥ ጥርግ አድርጐ ይበላል።

ለረጅም ጉዞ የሚያበቃ ስብ ካጠራቀመ በኋላ እንደገና መሬት ለቆ ይነሣና ንፋስ ወደ መራው ሥፍራ ይበራል። በዚህ ምሳሌ ማስረዳት የምፈልገው በአየር ላይ የሚበር ሁሉ ከፍ ያለ ምግብ እንደሚጨርስ ወይም እንደሚያስፈልገው ነው። ይሁን እንጂ ሰው ክንፍ የሌለው ፍጡር ስለሆነ በምግብ ኃይል በሰማይ ላይ ሊበር አይችለም። ነገር ግን ለሰው ልጆች ጥበብ ስለተገለጠ ምንም ራሳቸው ክንፍ አውጥተው መብረር ባይችሉ ክንፍ ያለውን ሠርተው ለመብረር በመቻላቸው ከአዕዋፍ ጋር ተስተካክለዋል ሊባል ይቻላል። የመብረርን ትምህርት ያስተማረ ወይም ለማስተማር ምክንያት የሆነው በቆላ አገር የሚኖር ትልቁ ጆፌያማ አሞራ ነው።

የመብረርን ዘዴ በትክክል በጆፌ አሞራ ለመቅዳት ቢሞክርም ሰው ባየ ጊዜ ፈጥኖ በመነሣት ስለሚሸሸ ገና አልተቻለም። አሞራ የሚነሣውና የሚያርፈው የነፋሱን አቅጣጫ በመከተል ነፋስ ወደነፈሰበት ነው። ንፋሱ ጠንካራ በሆነ ጊዜ ፈጥኖ ለመነሣት ይችላል። ከመሬት ወደ ሰማይ ሲነሣ ለትንሽ ጊዜ በመሬት ላይ ያኰበኩባል። ይህንኑ ለመገንዘብ አሞራ በአረፈበት ሥፍራ ንፋስ ወደሚነፍስበት ወገን ድንጋይ ቢወረውር ነፋሱ ወደ ነፈሰበት ካልተነሣ መውደቁን ስለሚያውቅ ለመነሣት የሚያስችለውን የነፋስ ኃይል እስኪያገኝ እያኰበኰበ ሰው ወዳለበት እንኳን ቢሆን ይሮጣል።

በበጌምድር ጠቅላይ ግዛት ከወዴት እንደመጡ ያልታወቁ ልዩ ምልክትና ቀለበት ያላቸው ሁለት አሞራዎች በአንድ ሥፍራ አርፈው ሰው በደረሰባቸው ጊዜ ተነስተው ለመብረር ወደ ሰውዬው አኰበኰቡ ሰውዬው አደጋ የሚጥሉበት መስሎት አንደኛውን በዱላ ደብድቦ ሲገድለው ሁለተኛው ፖስተኛ የያዘውን ፖስታ እንደያዘ አመለጠ ተብሏል። ይህን በሰማሁ ጊዜ የመብረርን ጥበብ አስታወስኩ ምንም እንኳን እቦታው ሆኜ ሁኔታውን ባላይ በግምት እንደመሰለኝ ፖስታ የያዙ እነዚህ ሁለት አሞራዎች ከተለቀቁበት ወደ ሥፍራቸው ለመድረስ ሲጓዙ ደክሞአቸው ወይንም የአየሩን ሁናቴ ለማሳለፍ አርፈዋል። በድንገት የደረሰባቸው ሰው የሚመጣው ከወደንፋሱ አቅጣጫ ስለነበር ሳይደርስባቸው ከሰውዬው ዘንድ ደረሱ። ያላወቀውና ካሁን ቀደም ያልደረሰበት ነገር ስለአጋጠመው ሰውየው ደንግጦ ራሱን ለማዳን ባደረገው መከላከል ከአሞራዎቹ አንዱን ለመግደል ተገደደ። ባልታሰበ አደጋ ጓደኛው በሞት ቢለየውም አንደኛው መልክተኛ መልክቱን ለማድረስና ግዳጁን ለመፈፀም በኃይል በሮ አመለጠ።

የመብረር ፍቅር ካደረብኝ ጊዜ ጀምሮ በተፈጥሯቸው የመብረር እድል የተሰጣቸውን ሁሉ ማጥናት ወደድሁ። በሰማይም ሆነ በመሬት በራሪ የሆነ ነገር ባየሁ ጊዜ አተኩሬ ሳልመለከት አላልፍም። በምዘዋወርበት ጊዜ ሁሉ በመንገድ ዳር የቆሙና ከመንገድ ውጭ በመሬት የዕለት ምግባቸውን የሚቃርሙ አሞራዎች ደንግጠው በሚነሱበት ሰዓት የአየርን አቅጣጫ በመከተል ሰው ወዳለበት ሲመጡ እደነቅ ነበር። ይህ የሚሆንበትን ምክንያት ለማወቅ ሜቴዎሮሎጂ ላልተማረ ሰው አስቸጋሪ ነው። አሞራዎች ይህን የሚያደርጉት ባለማወቅና አደጋ ባለመፍራት ሳይሆን ፈጥኖ ለመነሣት ፈጣን ንፋስና ሙቀት አየር ስለሚያስፈልጋቸው ነው። ከዚህም በቀር ንፋስ በኋላ የሆነ እንደሆነ የሚበቃ ፍጥነት ባለማግኘት ወድቀው የሞት አደጋ እንደሚደርስባቸው ስለሚያውቁ በትንሽዋ ሞቃት አየር ለመጠቀም በሚነሱበት ጊዜ ወደ መንገድ መብረር ግድ ይሆንባቸዋል።¾

 

በጥበቡ በለጠ

 

ጣና ሐይቅ ለኢትዮጵያ የታሪክና የማንነት መገለጫ የሆነ ግዙፍ ቅርስ ነው። ጣና ውስጥ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የኢትዮጵያ ቅርሶች የሚገኙበት ምስጢራዊ ውሐ ነው። በርካታ እድሜ ጠገብ ጽላቶች፣ ንዋየ ቅዱሳት፣ ብርቅዬ የብራና መጻህፍት፣ የታላላቅ መሪዎችና ቅዱሳን አጽም፣ ከኦሪት እስከ አዲስ ኪዳን የተንጣለለ ታሪክ፣ ብዙ ብዙ ገና ያልደረስንባቸው ምስጢራዊ ታሪኮች ያሉበት የኢትዮጵያዊያን ሁሉ መስታወት ነው። ይህ መስታወታችን እየደበዘዘ ሊሰባበር መንገዱን ይዞታል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ይህን መስታወታችንን ከክፉ አደጋ የመጠበቅ ሀላፊነት አለብን። ጣና ከታመመ አባይም አዙሮ ይጥለዋል። ከጣና ማህጸን ስለሚወጣ ህመሙ ህመማቸው ነው።


ዓባይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ታሪክ፣ የጥበበኞች ቋንቋ እና ሃይማኖት ሁሉ ሆኖ ቆይቷል። ለምሳሌ ዓባይ እየተንደረደረ ጥልቅ ብሎ የሚወጣበት ጣና ሃይቅ ከጎጃም እስከ ጎንደር ድረስ ተለጥጦ 3 ሺህ 600 ካሬ ኪሎ ሜትር ሸፍኗል። በዚህ ደሴት ላይ ከጥንታዊው ከኦሪቱ ዘመን እስከ ዛሬ ድረስ ይፀለያል ይዘመራል፣ ይሸበሸባል። ምክንያቱም በሐይቁ ላይ 37 ደሴቶች አሉ። እነዚህ ደሴቶች ላይ ደግሞ ከ21 የሚበልጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ገዳማት አሉ። ገዳማቱ ውስጥ የዓለም ታላላቅ ቅርሶችና ታሪኮች ያሉባቸው ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስ እና የባህል ድርጅት /ዩኔስኮ/ ቱሪስቶች እንዲይዋቸው ደጋግሞ የሚወተውትላቸው አስገራሚ ቦታዎች ናቸው።


ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የካቲት /መጋቢት 2001 ዓ.ም በሐመር መጽሔት ላይ ስለ ጣና ሐይቅ እንዲህ ብሏል፡-


ሶስት ሺ ስድስ መቶ ሰላሳ ሰባት ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውን ይህን ሐይቅ ጌታ በተወለደበት ወቅት በግብፅ ላይ ምርምር በማድረጉ የሚታወቀው ግሪካዊ ተመራማሪ ስትራቦ፣ “ሴቦ” በማለት ይጠራው ነበር። የሁለተኛው ክፍለ ዘመን የግብፅ መልክዓ-ምድር ተመራማሪ የነበረው ገላውዴዎስ ፕቶሎሜም፤ “ኮሎ” ይለው ነበር። የአቴናው ድራማ ፀሐፊ ኤስኪለስ ደግሞ፣ “መደብ የተቀባይ ሐይቅ የኢትዮጵያ ጌጥ” ይለው ነበር። ይህ ሰው፣ ይህን ያለው ደግሞ አምስት መቶ አመት ቅድመ-ልደተ-ክርስቶስ መሆኑን ስናስብ በዚያ ዘመን፤ የዓለም ዓይኖች ከሚያርፍባቸው ሀገራት፣ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የነበረች መሆኗንም እንገነዘባለን።


በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ሀይቆች ትልቁ የጣና ሃይቅ ነው። ስፋቱ 3 ሺህ 637 ካሬ ኪ.ሜ ሲሆን በውስጡ በሚገኙ ደሴቶችና በዙሪያው በርካታ የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖትን የሚከተሉ ገዳማት ይገኛሉ። አንዳንዶቹ ገዳማት ከ700 ዓመት እድሜ በላይ ያላቸውና ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ ውድ የታሪክ ቅርሶችና የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ነገስታትን አጽም የያዙ ናቸው። በመሆኑም ገዳማቱ የአገሪቱ ቤተክህነት ሙዚየም ናቸው ለማለት ይቻላል።

 

ደብረማርያም


ከባህር ዳር ከተማ የሰሜን ምስራቅ አቅጣጫን በመያዝ በጀልባ ለሃያ ደቂቃ አሊያም በእግር ለአንድ ሰዓት ተኩል በመጓዝና የአባይን ወንዝ በታንኳ በማቋረጥ የደብረማርያም ገደም ወደምትገኝበት ደሴት መግባት ይቻላል። የተለያዩ ታሪካዊ ቅርሶችን የያዘችው የደብረ ማርያም ገዳም በአፄ አምደ ጽዮን መዘነ መንግስት /1307-1337ዓ.ም/ እንደተመሰረተች ይነገራል።


አካባቢው በሁለት ተጨማሪ ስሞች ይታወቃል። እነኚህም ጉማሬ ባህር እና አባይ ራስ ይባላሉ። ጉማሬ ባህር የተባለው በአካባቢው ጉማሬዎች ስለሚገኙ ሲሆን አባይ ራስ የተባለው ደግሞ የአባይ ወንዝ የሀይቁን ውሃ ሰንጥቆ የሚወጣበት ስፍራ በመሆኑ ነው።

 

ክብራን ገብርኤልና እንጦስ


ከባህር ዳር ከተማ ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ የ45 ደቂቃ የጀልባ ጉዞ በኋላ ብዙም ያልተራራቁ መንትያ ደሴቶች ይገኛሉ። ደሴቶቹ የሚገኙት ማራኪ በሆነ ተፈጥሯዊ የመሬት አቀማመጥ ባለውና በደን በተሸፈነ ኮረብታማ ስፍራ ነው። ደሴቶቹ ክብራን ገብርኤልና እንጦስ በመባል ይታወቃሉ። ክብራን ገብርኤል የወንድ እንጦስ ደግሞ የሴት መናንያን መኖሪያ በመሆን ለብዙ አመታት ቆይተዋል። ይሁን እንጂ በአንዳንድ ችግሮች ምክንያት የእነጦስ መነኮሳት ወደ ሌላ አካባቢ መሰደዳቸው እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ገዳሙ ጠፍ /ባዶ/ ሆኖ መቆየቱ ይነገራል። አሁን ግን ቤተክርስቲያን ተሰርቶና የኢየሱስ ታቦት ገብቶ ገዳሙ ወደ ወንዶች ገዳምነት ተለውጧል።


የክብራን ገብርኤል ቤተክርስቲያን መጀመሪያ የተሰራው በአፄ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግስት ሲሆን በዳግማዊ ዳዊትና ኋላም በአዲያም ሰገድ እያሱ በድጋሚ እንደተሰራ ይነገራል። ቤተክርስቲያኑ በወጉ በተጠረቡ ቀያይ ድንጋዮች የታነፀ ነው። በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ከድንጋይ የተጠረቡ 12 አመዶች ይገኛሉ። ከመቅደሱ ግድግዳ ጋር ተያይዞ በተሰራ ክፍል ውስጥ የገዳሙ መስራች የአቡነ ዘዮሀንስ መቃብር ይገኛል።


በደሴቱ አናት ላይ በታነፀው የክብራን ገብርኤል ቤተክርስቲያንና እንዲሁም በአፄ ፋሲል እንደተሰራ በሚነገርለት ዕቃ ቤት ውስጥ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ በሀወርያው ሉቃስ እንደተሳለች የሚነገርላት ስዕለማርያም ከብረት የተሰራው የአቡነ ዘዮሃንስ የፀሎት ልብስ የአፄ ኢያሱ አልጋና ሰይፍ የንጉስ ተክለ ሃይማኖት ተደራራቢ አልጋ ከእንጨት የተሰሩ መቅረዝና አገልግል መስቀሎቸ የገበታ ላይ ስዕሎችና የብራና መጻሕፍት ይገኙባቸዋል። ወደ ክብራን ገብርኤል መግባት የሚፈቀድላቸው ወንዶች ናቸው።

 

ዘጌ


ታላቁ የኢትዮጵያ የስነ ጽሁፍ ሰው ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ የተወለደባት ደሴት ነች። የጣናን ሀይቅ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ በመገፋት ተንሰራፍቶ የሚታየው ባህረገብ መሬት/ፔኒንሲዩላ/ ዘጌ ይባላል። በቅርብ ርቀት ሆነው ሲመለከቱት ክንፉን ዘርግቶ የተቀመጠ አሞራ ይመስላል። ዘጌ ከባህር ዳር ከተማ 15 ኪ.ሜ ያህል የሚርቅ ሲሆን በጀልባም አንድ ሰዓት ተኩል ያህል ያስኬዳል። በመኪና ደግሞ ሁለት ሰዓት ይፈጃል። ርቀቱም 23 ኪ.ሜ እንደሆነ ይገመታል።


በዘጌ ባህረ ገብ ምድር ላይ ሰባት የሚሆኑ አብያተክርስቲያናት ይገኛሉ። እነኚህም መሀል ዘጌ ጊዮርጊስ አቡነ በትረማርያም አዝዋ ማርያም ውራ ኪዳነ ምህረት ደብረስላሴ ይጋንዳ አቡነ ተክለሃየማኖትና ፉሬ ማርያም ይባላሉ። ከመጨረሻዎቹ ሁለቱ በስተቀር ሌሎቹ ገዳማት አነስተኛ ጀልባዎችን ሊያስጠጉ የሚችሉ ወደቦቸ አሏቸው።


በጣና ሀይቅና በዙሪያው የሚገኙት አብዛኞቹ ገዳማት ሰባቱ ከዋክብት በሚል መጠሪያ ከሚታወቁት የሃይማኖት አባቶች ጋር የተሳሰረ ታሪክ አላቸው። መነሻቸው ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንደሆነ የሚነገርላቸው እነኚህ ጻድቃን የሃይማኖት መሪዎች አቡነ ታዴዎስ፣ አቡነ ዘዮሀንስ፣ አቡነ በትረ ማርያም፣ አቡነ ሂሩት አምላክ፣ አቡነ አሳይ፣ አቡነ ዘካርያስና አቡነ ፍቅረ እግዚ ዮሃንስ ይባላሉ። አቡነ ታዴዎስ ደብረ ማርያምን አቡነ ዘዮንስ ክብራን ገብርኤልን አቡነ በትረማርያም ዘጌን አቡነ ሂሩት አምላክ ዳጋ እስጢፋኖስን አቡነ አሳየ ምንዳባን አቡነ ዘካርስ ደብረ ገሊላን አቡነ ፍቅረ እግዚዮሃንስ ደግሞ ጣና ቂርቆስን እየገደሙ እንዳቀኑ ይነገራል።


ከዘጌ ገዳማት በእድሜ አንጋፋ እንደሆነ የማነገርለት የመሃል ዘጌ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ነው። ቤተክርስቲያኑ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተመሰረተ የመስራቹን የአቡነ በትረ ማርያምን ገድል ዋቢ በመጥቀስ ካህናቱ ይገልጻሉ። አቡነ በትረ ማርያም ከሸዋ ልዩ ስሙ ሙገር ከተባለ አካባቢ እንደመጡ ይታመናል።


በመሀል ዘጌ ጊዮርጊስ በርካታ ጥንታዊ ቅርሶች ይገኛሉ። ከብረት የተሰራው የአቡነ በትረ ማርያም የፀሎት ልብስ የጥንት ነገስታትና መኳንንት ስጦታዎች የብራና መጻሕፍት ከቅርሶቹ ጥቂቶቹ ናቸው። ቤተክርስቲያኑ በተለያየ ጊዜ የመፍረስና እንደገና የመሰራት ዕድል ቢገጥመውም የጥንቱን እደ ጥበብ የሚመሰክሩ የእንጨት ቅርጻ ቅርጾች በመስኮቶቹና በሮቹ ላይ አሁንም አሸብርቆ ይታያል።


ከጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አጠገብ ጥንታዊ ገጽታቸውን ጠብቀው ከቆዩት ጥቂት ቤተክርስቲያናት መካከል አንዱ የሆነው የበትረ ማርያም ቤተክርስቲያን ይገኛል። ይህ ቤተክርስቲያን አቡነ በትረ ማርያም ካረፉ በኋላ ረዳታቸው በነበሩት በአቡነ በትረሎሚዎስ አማካኝነት በመቃብራቸው ላይ ለመታሰቢያነት የተተከለ ነው። ውስጡ ባማሩ ጥንታዊ የሃይማኖት ስዕሎች ያሸበረቀውና በክብ ቅርጽ ተሰርቶ በባህላዊ የሳር ክፍክፍ የተከደነው የበትረ ማርያም ቤተክርስቲያን የጥንቱን ዘመን የቅርጻ ቅርጽ ጥበብ የሚዘክሩ በሮችና መስኮቶች አሉት።


በጥንታዊ ቅብ ስዕሎች ከሚታወቁት የዘጌ ገዳማት አዝዋ ማርያምና ውራ ኪዳነ ምህረት ሳይጠቀሱ የሚታለፉ አይደሉም። በአፆ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግስት እንደተሰራች የሚነገርላት አዝዋ ማርያም በመቅደስዋ ዙሪያ ያማሩ የግድግዳ ቅብ ስዕሎችን የያዘች ነች። አንዳንዳቹ ስዕሎች ዙሪያቸው በብር ጉባጉብቶች የተዋቡ ናቸው። በዘጌ የሚገኙ የሌሎች አብያተክርስቲያናት ስዕሎች የተሰሩት በአዝዋ ማርያም ስለነበር አንዳንድ ጊዜ ስዕል ቤት ተብላ ትጠራለች።


የውራ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግስት በአቡነ ዘዮሃንስ እንደተመሰረተች ይነገራል አቡኑ ከሸዋ መርሃቤቴ የመጡ ሲሆን በቀድሞው ደብረ አስባ ገዳም በአቡነ ሕዝቅያስ እጅ ቅስና እንደተቀበሉ በጣና ሃይቅ ደቡባዊ ምስራቅ ዳርቻ በደራ ወረዳ ከሚኖሩ ጥቂት የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ጋር ቆይታ አድርገው ወደ ክብራን ደሴት እንደሄዱ ገድላቸው ያትታል።


ውራ ኪዳነ ምህረት በክብ ቅርጽ የተሰራች ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ናት። የቅኔ ማህሌቱ ከሸንበቆ ቅድስቱና መቅደሱ ከጭቃና ከድንጋይ የተሰሩ ሲሆን እስከ ቅርብ ጊዜ ጣሪያው በሳር ክፍክፍ የተሸፈነ ነበር። የመቅደሱ ዙሪያ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተሳሉ የሚነገርላቸው ውብ የሃይማኖት ስዕሎች ያጌጠ ነው። ጥንታዊ የብራና መጻህፍት፣ የነገስታት ዘውዶች ካባዎችና መስቀሎች ከታሪካዊ ቅርሶቿ ናቸው። ውራ ኪዳነ ምህርትን ወንዶችም ሴቶችም ሊጐበኟት ይችላሉ።


በዘጌ ባረ ገብ መሬት ላይ የጣና ሀይቅንና አካባቢውን ሰፊ በሆነ አድማሳዊ ርቀት ለመመልከት የሚያስችል የአራራት ተራራ አለ። በዚህ ተራራ አናት ላይ የይጋንዳ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን ይገኛል። አፄ አዲያም ሰገድ እያሱ ዘመነ መንግስት እንደተመሰረተ የሚነገርለት ይህ ቤተክርስቲያን በቅርስ ክምችታቸው ከሚታወቁት የዘጌ ገዳማት አንዱ ነው። ከሀይቁ ዳር ወደ ይጋንዳ የሚወስደው የእግር መንገድ አቀበት የበዛበት ሲሆን ቢያንስ አንድ ሰዓት ያስኬዳል።

 

ደቅ ደሴት


ጣና ሀይቅ ካሉት ደሴቶች ትልቁ ደቅ ደሴት ነው። ከባህር ዳር ከተማ ሰሜናዊ አቅጣጫ 37 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል። ይህ ደሴት የሰባት ደብር አገር ተብሎ ይታወቃል ምክንያቱም ከደሴቱ በቅርብ ርቀት የሚገኘውን ዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ጨምሮ ሰባት አድባራትን ስለያዘ ነው። እነዚህም ናርጋ ስላሴ ቅድስት አርሴማ፣ ኮታ ማርያም፣ ዝባድ ኢየሱስ፣ ጆጋ ዮሀንስና ጋደና ጊዮርጊስ ናቸው። ደቅ የሚለው ቃል በግዕዝ ልጅ ወይንም ትንሽ ማለት ሲሆን ደሴቱ ከሌሎች ደሴቶች ትልቁ ሆኖ ሳለ ለምን ይህ ስም እንደተሰጠው በውል አይታወቅም።


ደቅ ደሴት መጀመሪያ ለመነኮሳት ብቻ እንጂ ለአለማውያን ኗሪዎች ያልተፈቀደ ነበር። ኋላ ግን ቀስ በቀስ በርካታ ሰዎቸ ወደ ደሴቱ በመምጣት በመስፈርና በመዋለድ የኗሪው ቁጥር ከፍ ሊል ችሏል። የደሴቱ ኗሪዎች አማርኛ ተናጋሪና የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ብቻ ናቸው።
የአካባቢው ኗሪዎች ወደ ደሴቱ ሕዝብ በብዛት የገባበትን ዘመን በኦሪት የተለያዩ ጊዜያት ከፋፍለው ይናገራሉ። የመጀመሪያው በግራኝ አህመድ ጦርነት ወቅት ሁለተኛው እቴጌ ምንትዋብ የናርጋ ስላሴ ቤተክርስቲያንን በሚያሰሩበት ወቅት ሦስተኛው በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት አራተኛው ደግሞ በአፄ ዮሃንስ 4ኛ ዘመነ መንግስት በነበረው የድርቡሾች ወረራ ወቅት ነበር።


ደቅ ደሴትን ከሌሎች ደሴቶች ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የቀድሞ ነገስታት የስልጣን ተቀናቃኞቻቸውንና ተቃዋሚዎቻቸውን በግዞት የሚያቆዩበት ቦታ በመሆኑ ነው የሚሉ የታሪክ ፀሃፊዎች አሉ። ለምሳሌ በአፄ ሕዝብ ናኝ ዘመን የደብረ ጽሞና ገዳም መስራች በነበሩት በአባ ሲኖዳ ላይ ንጉሱን የሚቃወም ንግርት ተናግረናል በሚል ክስ ቀርቦባቸው በአፄው ትዕዛዝ ወደ ደቅ ደሴት እንደተጋዙና ሕይወታቸውም እዚያው እንዳለፈ በዲማ ጊዮርጊስ የሚገኘው ገድላቸው ያትታል።


በክረምት ወራት በሃይቁ ሙላት ሳቢያ ወደ ደሴትነት የሚለወጠውና በበጋው ወራት ውሃው ሰጐድል የደቅ ምህራባዊ አካል በመሆን ደሴቱን የሚቀላቀለው የናርጋ ስላሴ ገዳም የወንዶችና የሴቶች የቁሪት ገዳም በመባል ይጠራል። ገዳሙን የአፄ በካፋ ባለቤት የነበሩት እቴጌ ምንትዋብ /1730-1755/ ናቸው። የናርጋ ስላሴ ቤተክርስቲያን በክብ ቅርጽ ከድንጋይ ከኖራና ከእንጨት የተሰራ ሲሆን ቁመታቸው አራት ማትር ስፋታቸው ደግሞ ሁለት ሜትር የሆኑ ስምንት ግዙፍ በሮች አሉት። መቅደሱ በጥንታዊ የሃይማኖት ስዕሎች ያሸበረቀ ነው። ስዕሎቹ የተሳሉት በመቅደሱ ዙሪያ ሲሆን በስተምዕራብ የክርስቶስን ታሪክ ከውልደት እስከ እርገት በስተደቡብ የቅድስት ማርያምን ስደትና ተአምራት በስተምስራቅ የከርስቶስት ተአምራት በስተሰሜን ደግሞ የሰማዕታትን ገድል ይዘክራሉ። ከቤተክርስቲያኑ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ የተሰሩ የጐንደር ዘመን የኪነህንጻ ጥበብ የሚንፀባረቅባቸው ባለፎቅ የጥበቃ ማማዎችና የሌሎች ሕንጻዎች ፍርስራሾች በግቢው ውስጥ ይገኛሉ። የእቴጌ ምንትዋብና የልጃቸው የአፄ ኢያሱ አልጋዎችና ካባ ልዩ ልዩ የብራና መጻሕፍትና የእጅ መስቀሎቸ በቅርስነት ተቀምጠዋል።


በደቅ ደሴ ምዕራባዊ አቅጣጫ ዙሪያዋን በትላልቅ ዛፍ ተከባ የምትገኝ ጥንታዊ ገዳም አለች። ቆላ ቅድስት አርሴማ ትባላለች። በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ መንግስት እንደተመሰረተች ይነገራል። በአሁኑ ሰዓት ከአንድ ጠንካራ ገበሬ ቤት ብዙም ልቃ የማትታየው የቅድስት አርሴማ ገዳመ ታቦቷ አባ ዮሃንስ በተባሉ መነኩሴ ከኢየሩሳሌም እንደመጣ የገደሟ ካህናት ይገልጻሉ። እንደ አፈ-ታሪኩ ከሆነ በስሟ ቤተክርስቲያን የቆመላት ቅድስት አርሴማ በትውልድ ጀርመናዊት ነበረች ይባላል። ከደናግልት ጋር ወደ አርሜንያ ተሰዳ ለዕምነቷ ብዙ ፈተናን የተቀበለቸ በኋላም የተሰየፈች ሰማዕት እንደነበረች ገድሏ ላይ እንደተፃፈ ይነገራል። ከመቅደሱ አናት ላይ በአብዛኛው ደብዝዘው የሚታዩት የግድግዳ ቅብ ስዕሎች የሰማዕቷን ገድሎች ይተርካሉ።


በደቅ ደሴት ላይ የመጀመሪያዋ ቤተክርስቲያን እንደሆነች የሚነገርላተ ኮታ ማርያም ናት። ቤተክርስቲያኗ ዳጋ እስጢፋኖስ ገደም በነበሩት በአባ ሂሩት አምላክ እንደተመሰረተች የገዳሟ ካህናት ይገልጻሉ። ኮታ ማርያም በክብ ቅርጽ የታነፀች ዙሪያዋ ከእንጨት ከጭቃና ከኖራ የተሰራ ጣሪያዋ በሳር ክፍክፍ የተከደነ ነው። ወለሉ ደግሞ በጥንቃቃ ተሰንጥቀው በጠፍና በተያያዙ ሸንበቆዎች ተሸፍኗል። ጣሪያውን ደግፈው የያዙት 12 ረዣዥምና ወፋፍራም አምዶች ናቸው። በመቅደሱ ዙሪያ የተገጠሙት መስኮቶች ልዩ የቅርጻ ቅርጽ ጥበብ ይታይባቸዋል። በ1978፣ በ1983 አና በ1984 ዓ.ም አንዳንድ የቤተክርስቲያኗ አካሎች በባህል ሚኒስቴር የቅርስ ጥገና ባለሙያዎች የተወሰነ እድሳት ተደርጐላቸዋል። በመቅደሱ ግድግዳ ላይ የነበሩት ጥንታዊ የቅዱሳን ስዕሎች ግን ከእድሜ ብዛትና ከእንክብካቤ ጉድለት ክፉኛ ተጐድተዋል።


ከጣና ሃይቅ ደሴቶች ለደቅ ደሴት የሚቀርበው የዳጋ ደሴት ነው። ደሴቱ ከሃይቁ ከፍ ብሎ የሚገኝ በመሆኑ ከማንኛውም የሃይቁ ዳርቻ ሊታይ ይችላል። ዳጋ ጥቅጥቅ ባለ ጫካ የተሸፈነና በውስጡ የእስጢፋኖስን ገዳም የያዘ ነው። እንደ ገዳሙ ካህናት አስተያየት የዳጋ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያ በፄ ይኩኖ አምላከ ዘመነ መንግስት በአቡነ ሂሩት አምላክ እንደተመሰረተ ይታመናል።


የዳጋ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን በቅርፁ ከሌሎቹ የሀይቁ ገዳማት የተለየ ነው። ቤተክርስቲያኑ በመረከብ ቅርጽ የተሰራ ሲሆን ምሳሌውም በጥፋት ውሃ ዘመን የሰው ዘር በኖህ መርከብ አማካይነት መዳኑን ለማመልከት እንደሆነ መነኮሶቱ ይናገራሉ።


ዳጋ እስጢፋኖስ በርካታ መናኒያን መነኮሳት የሚገኙበትና ትክክለኛው የገዳም ሕይወት ስርዓት የሚታይበት ስፍራ ነው። ገደሙን ልዩ ከሚያደርጉት ባህሪያት በመካከለኛው ዘመን የነበሩ የኢትዮጵያ ነገስታት አዕፅምት ሳይፈራርሱ በክብር ተቀምጠው መገኘታቸው ነው። ነገስታቱ በሕይወት ዘመናቸው ለገደሙ ያበረከቷቸው ስጦታዎችም በገዳሙ እቃ ቤት በቅርስነት ተቀምጠው ይገኛሉ። ዳጋ እስጢፋኖስ የአንድነት ገዳምና ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ ነው። 

 

ዋለልኝ አየለ

 

ትናንት መስከረም 28 ቀን 2010 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጄንሲ (ወመዘክር) በበዕውቀቱ ሥዩም የግጥም መድብል የማለዳ ድባብ ላይ በጎተ ወርሃዊ የመጻሕፍት ውይይት፤ ተደርጓል። በመጽሐፉ ላይ ዳሰሳ ያደረገውም የስነ ጽሑፍ ባለሙያው ሰለሞን ተሰማ(ጂ) ነው። እኔ ደግሞ በውይይቱ ላይ የተነሱትን ሀሳቦች የራሴን ትዝብትና አድናቆት ጨምሬ መዳሰስ ፈለኩ።


ከመድረኩ ድባብ ልጀምር። መጽሐፉ የበዕውቀቱ ሥዩም ስለሆነ እንኳንስ መቀመጫ መቆሚያም አይገኝም ብየ ነበር። ዳሩ ግን እዚያ አዳራሽ ከሚደረጉ ውይይቶች ሁሉ ሰው በመጠበቅ ዘግይቶ ያየሁት ነበር። በዚያች ጠባብ አዳራሽ ውስጥ እንኳን ከኋላ በኩል ጭራሽ ባዶ ወንበሮች ነበሩ። ምክንያቱ ምን እንደነበር እርግጠኛ ባልሆንም ስገምት ግን በሚገባ አልተነገረም (አልተዋወቀም)። እኔ የነገርኳቸው ጓደኞቼ እንኳን ባልነግራቸው ኖሮ እንዳልሰሙ ነው የነገሩኝ። ፌስቡክም በሚገባ አላስተዋወቀውም(ሰሞኑን በነ አባዱላ ወሬ ተወጥሮ ይሆናል)።


ሌላኛው ግምቴ በዕውቀቱ ሥዩም በዚህ መጽሐፉ የ‹‹ኗሪ አልባ ጎጆዎችን›› ያህል ትኩረት አልሳበም። በዕውቀቱ ስለሆነ ከዚህ በላይ ነበር የተጠበቀ። እኔ ደግሞ በግሌ(በጣም በግሌ) አቅራቢው አላስደሰተኝም ነበር። ከዚህ በፊት በሌሎች ውይይቶች ስለማውቀው የማይመለከተውን ነው የሚያወራ። የሄድኩት ተወያዮች ለሚያነሱት ሀሳብ ብየ ነው(በእርግጥ ከአዋያዩም ብዙ ነገር ነው ያወቅኩ)። ከባለሙያውም ከተወያዮችም ‹‹የማለዳ ድባብ›› ላይ የተነሱትን ሀሳቦች በጣም በአጭሩ ላቅርብ።


አቅራቢው ሰለሞን ተሰማ(ጂ) በአሰኛኘት ወይም በምት ላይ እንደሚያተኩር ነው አስቀድሞ የተናገረው፤ ሆኖም ግን ውይይቱ በሀሳብና በይዘት ላይም ነበር። በተለይም በዕውቀቱ ራሱን የተመለከቱ ግጥሞች ተነስተዋል። ሰቆቃወ በውቄ፣ ለአንዲት ማስቲካ ሻጭ ብላቴና፣ ለአንዲት ተመዋጽች ብላቴና፣ እንደምነሽ ሸገር፣ ለአባቴ፣ በሞቷ ፊት ለፊት እና ይድረስ የሚሉት በዕውቀቱንና የበዕውቀቱን ዘመን የሚያሳዩ ናቸው። እሱንና ዘመኑን የሚያሳዩ ናቸው።


አቅራቢው፤ በዕውቀቱ ለቅርጽ እንደማይጨነቅ ተናግሯል። በቃላት አጠቃቀምም የማህበረሰቡን ወግና ባህል የሚጥሱ ቃላትን መጠቀሙ አግባብ እንዳልሆነ ተናግሯል። በዕውቀቱ አዳዲስ ቃላትን መፍጠር እየቻለ እነዚህን መጠቀሙ ልክ አይደለም። ለምሳሌ የሴትን ሀፍረተ ሥጋ ለመግለጽ በግጥሙ ውስጥ ‹‹እንትን›› ማለት ሲገባው በቀጥታ እንደወረደ ጽፏል። በገጽ 62 ላይ ‹‹ኬላ ነኝ›› በሚለው ግጥሙ እንዲህ ይላል።
……………….
ገና ሲያዩኝ አንሶላ የሚያስቡ
ከግንባሬ ላይ እምስ የሚያነቡ
………………
በእውቀቱ እዚህ ግጥም ላይ ይህን ቃል ከሚጠቀም እንደተባለውም ‹‹እንትን›› የሚያነቡ ብሎ ቢጠቀም ስነ ጽሑፋዊ ውበት ይኖረዋል። እዚህ ላይ እኔ የሚታየኝ ባህልና ወግን መጣስ ሳይሆን ስነ ጽሑፋዊ ውበት ማጣት ነው። በስነ ጽሑፍ ውስጥ (በተለይ በግጥም ውስጥ) ፈልገህ የምታገኘው ትርጉም መኖር አለበት። በዚያ ላይ በዚህ አውድ ውስጥ ‹‹እንትን›› ቢባል ምን እንደሆነ ግልጽ ነው።


ሰለሞን በዕውቀቱ ቃላት እንደሚደጋግም አንስቷል። እዚሁ ላይ ከተሳታፊዎች የተነሱ ሀሳቦችን ልጥቀስ። በዕውቀቱ የሚደጋግማቸው ቃላት አሰልቺና ያላስፈላጊ ሳይሆን የራሳቸው ውበት ያላቸው ናቸው። መደጋጋማቸው በምክንያትና ለዛ ያላቸው ናቸው።
ሌላው በዕለቱ ሰፊ መከራከሪያ የነበረው በመጽሐፉ ገጽ 34 ላይ ‹‹የቴዎድሮስ ማመንታት በመቅደላ›› የሚለው ግጥም ነበር። እዚህ ላይ አቅራቢው እንዳለው በዕውቀቱ ለአጼ ቴዎድሮስ ያላቸውን ጥላቻ አሳይቷል። አጼ ቴዎድሮስን አሳንሷቸዋል።


ከተሳታፊዎች በተነሳ ሀሳብ (በተለይም አንድ ተሳታፊ ሲናገር) ‹‹ሰለሞን፤ ከዚህ በፊት በዕውቀቱ ለአጼ ቴዎድሮስ ያለው አመለካከት ዝቅተኛ ነው፤ እየተባለ የሚወራው ተፅዕኖ አሳድሮብሃል፤ በሌሎች ጽሑፎቹ ስለ አጼ ቴዎድሮስ የጻፈውን ይዘህ እዚህ ላይ ሳይገባህ ነው የተናገርክ። በዚህ ግጥም ላይ አጼ ቴዎድሮስን የሚያሳንስ ነገር የለም›› የሚል አስተያየት ሰጥቷል።


የሰውየው አስተያየት ልክ ይመስለኛል። በዕውቀቱ ስለ አጼ ቴዎድሮስ ምንም አይነት አቋም ይኑረው በዚህኛው ግጥም ግን አጼ ቴዎድሮስን የሚያሳንስ ነገር የለም። አንድ ተሳታፊ እንደተናገረው ደግሞ ‹‹የተጠቀማቸው ቃላት ለንጉሥ የሚሆኑ አይደሉም፤ ለጎረምሳ የሚሆኑ ናቸው›› ብሏል። በፍቅር ውስጥ ደግሞ ንጉሥም ጎረምሳም እኩል ነው። በዚያ ላይ ይህ ግጥም ነው።


እኔ እንደታዘብኩት አቅራቢው ብዙ ግጥሞችን ሳይገቡት ተንትኗል፤ ከቅርጽ አኳያም አንድ ስንኝ መሆን ነበረበት፤ እዚህ ላይ መከፈል ነበረበት የሚሉ ሀሳቦችን አንስቷል። የቅርጽ ነገር ለብዙ ሰዎች አከራካሪ ስለሆነ እንዲህ ማለት የሚከብድ ይመስለኛል። ‹‹ለዜማ ያስቸግራል›› የሚባለው ግን አያስማማኝም። ብዙ ግጥም የማንበብ ችግር ያለባቸው ሰዎች አሉ። ዜማ በአጻጻፍ ብቻ ሳይሆን በአነባበብም ጭምር ነው።


ከአንድ ተሳታፊ የተነሳ ሀሳብ እጅግ አስደስቶኛል። እስከዛሬ ልብ ያላልኩት፤ ግን ልክ የሆነ። በዕውቀቱ ለእነዚያ መሳይ ግጥሞቹ ርዕስ አይችልም። ምናልባት ዋናው ትኩረት ርዕስ መሆን የለበትም የሚባል ከሆነ አላውቅም። ግን ልጁ እንዳነሳው የበዕውቀቱ ርዕሶች የዘገባ ርዕሶች ናቸው። የቅኔ ርዕስ ሳይሆን የጋዜጣ ወይም የማብራሪያ ርዕሶች ነው የሚመስሉት። ለአንዲት….፣ ለአንድ…. ለአንድ ቴሌቭዥን፣ ላባቴ፣ የመኖር ትርጉሙ…. እያለ የማብራሪያ ርዕስ ነው የሚሰጣቸው። በዕውቀቱ ስለሆነ ርዕሱንም ቅኔ ማድረግ ይቻለው ነበር። በእርግጥ የበዕውቀቱ ምጥቀት ሀሳብ ላይ እንጂ ቋንቋ ላይ አላደንቀውም።


የግጥም ቋንቋን በተመለከተ እባካችሁ ሃያሲዎች መድረክ ይኑራችሁ!

 

የመጽሐፉ ርዕስ        ሳተናውና ሌሎች…
የመጽሐፉ አይነት     የአጫጭር ልቦለዶችና የግጥም ስብስብ
ጸሐፊ                   ጋዜጠኛና ደራሲ ደረጀ ትዕዛዙ

 

አስተያየት፡- ከዘመዴ

 

ደራሲው ከጅምሩ ተደራሲያንን ወደ ንባብ የጋበዘው የመጽሐፉን መታሰቢያነት «የጥበብ ስራዎችን በብዕራቸው እያረቁ የኢትዮዽያ ስነ ጽሑፍ ያብብ ዘንድ ለተጉ አርታኢያን እና በሰላ ትችታቸው ደራሲያንን እየገሩ ትክክለኛውን መንገድ ላመላከቱ ሃያሲያን ይሁንልኝ» ሲል ባሰፈረው የመሸጋገሪያ ድልድይ ነው። 128 ገፅ ያለው መጽሐፉ በተለያዩ ዘመናት የተጻፉ ስምንት አጫጭር ልቦለዶች እና አርባ አንድ ግጥሞችን አካቷል። በ55 ብር ከ75 ሣንቲም የመሸጫ ዋጋ ለንባብ በቅቷል። ይህ ወጥ ስራ፤ የተለያዩ ማህበረሰባዊ እውነታዎችን እና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ዳሷል።
የፈጠራ ስራ እምብዛም በማይስተዋሉበት በዚህ ወቅት ከሰሞኑ ለንባብ የበቃው የጋዜጠኛና ደራሲ ደረጀ ትዕዛዙ «ሳተናው እና ሌሎች…» የአጫጭር ልቦለዶች እና የግጥም ስብስብ ስራ፤ ንባብን ሊጋብዙ ቁም ነገሮችን ይዟል። ከይዘት፣ ከቋንቋ፣ ከታሪክ አወቃቀር፣ ከስነ ጽሑፍ አላባውያን አጠቃቀም አንጻር በጥልቀት ተንትኖ የመጽሐፉን ምንነት ለመበየን የሐያሲያን ደርሻ እንደሆነ ትቼ፤ እኔ የወፍ በረር ቅኝቴን እንዲህ በምሳሌ ላመላክት። የተለያዩ ዘመናት የጋዜጠኝነት ተግባር ምን እንደሚመስል በንፅፅር ያቀረበበት «ሳተናው» የተሰኘው አጥር ልቦለድ ምንም እንኳ የበቃ እና የነቃ ቢሆን ጋዜጠኛ ሙያውን የሚስትበት ወይንም የሚታለልበት አጋጣሚ እንደሚኖር የሚያመላክት ነው።


ጋዜጠኛ በሙያዊ ተግባሩ ሁሌም ሃሳብ እየያዘ እንደሚኖር፣ ሙያዊ ኃላፊነቱ እንደሚያስጨንቀው፣ ሁሌም የስሜት መዋዠቅ ውስጥ እንደሚኖር ያሳያል። ደራሲው በጋዜጠኝነት ህይወት ውሰጥ ሲኖር ልምዱንና አስተውሎቱን እንዳላባከነ በልቦለዱ ውስጥ ይታያል። «ታታ» በተሰኘው ልቦለድ ስሜትን ፈታ የሚያደርግ፤ ከዚያም አልፎ ሳቅን የሚያጭር ነው። በልጅነት የአብሮነት ሕይወት ውስጥ የሚስተዋሉ ገጠመኞችን በማራኪ አቀራረብ ተቀምጧል። ልቦለዱ አንድ ከገጠር ወደ ከተማ የመጣ ብላቴና ከከተሜ ልጆች ጋር ሲገጥም የሚያየውን አበሳና የእሱ የአልሸነፍም ባይነት የሚፈጥረው አካላዊና ዓዕምሯዊ ሹኩቻ ታሪክ ልብ እያንጠለጠለ ይወስዳል። አካባቢያዊ ተፅዕኖ በማንነት እና በውስጣዊ አቅም ላይ ሊፈጥር የሚችለውን እክል ሰብሮ የወጣው ዋና ገፀ ባህሪው ታታ፤ አሜሪካን አገር ድረስ ሄዶ ብዙ ቆይቶ ሲመለስ እነዚያ ሲያዋክቡት የነበሩትን የከተሜ ልጆች በፍቅር ሲፈልግ ይታያል።


የአውሮፓና የእንግሊዝ እግርኳስ፣ ኢንተርኔት ወይንም ማህበራዊ ድረ ገጽ በተለይም ፌስ ቡክ በማህበረሰባችን ውስጥ የጊዜ፣ የገንዘብ እና የአዕምሮ አጠቃቀም ላይ ምን ያህል አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ በግልፅ የሚስተዋል ጉዳይ ነው። ይህ ሁነት በተለይ በወጣት ተጋቢዎች ላይ እየፈጠረ ስላለው ውጥንቅጥ የአብሮነት ሕይወት በጥሩ ሁኔታ ያመላከበት ስራው በ«መንታ ፍቅር» ልቦለድ ላይ እናገኛለን። ዕይታው የመባነን ስሜትም ይፈጥራል። ቅናትና በቀልን በ«ጉማጅ ፀጉር»፣ ቀብቃባነትን በ«ብሬ ቡራቡሬ» ልቦለዶች ላይ ልብ በሚያንጠለጥል ትረካ እናገኛለን። ደራሲው ምናበ ሰፊ መሆኑን የሚያሳዩለት የተለያዩ ማህበረሰባዊ ችግሮችና ዕውነታዎች በተለየ ዕይታ ማቅረብ መቻሉ ነው።


እዚህ ላይ የወቅቱ ፈታኝ አገራዊ አጀንዳ በልቦለዱ ውስጥ መካተት መቻሉም ይጠቀሳል። በ«ሰውየው» ልቦለድ ስራው። ዛሬ በተለያዩ መንግስታዊ መስሪያቤቶች ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ከአሁን አሁን፣ ከዛሬ ነገ የፍርድ ቤት ማዘዣ ወይንም የፖሊስ መጥሪያ ደረሰኝ እያሉ መባተታቸው አልቀረም። እዚህ ስጋት ውሰጥ ያሉት ደግሞ በሙስና ወንጀል እጃቸው ያደፈ፣ ህሊናቸው የጎደፈ ሰዎች ናቸው። ይህን ዕውነታ ደረጀ በብዕሩ ሲከሽነው ተራ ስብከት ወይንም የሆይሆይታውን ዘመቻ አጋዥ አድርጎ አይደለም። በጥበባዊ ቃላት ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታውን አመላከተበት’ጂ። በአጠቃላይ ደራሲው ጥሩ ስራ ይዞልን ቀርቧል። በቀላል አቀራረብና በሚጥም ቋንቋ አንባቢን የመያዝ አቅም ያለው መጽሐፍ አበርክቷል። በአቀራረቡ ሁሉም ልቦለዶቹ እጅግ በጣም አጫጭር ናቸው።


ጎላ ባለ ፊደል (Font) የተጻፉ ሆነው እያንዳንዳቸው በአማካኝ ስምንት ገጽ የያዙ ናቸው። አፍንጫ፣ ፀጉር፣ ቁመና… እያለ የገጸ ባህሪያትን ማንነት ለተደራሲው ለማሳየት ብዙ አልደከመም። «ተደራሲው ያግዘኝ» አይነት ይመስላል። አንዳንድ የስነ ጽሑፍ ጠቢባን «… እንዲህ አይነት የአጻጻፍ ስልቶች በዘመናዊ ልቦለድ አጻጻፍ የሚመከሩ ናቸው» ይላሉ። ደራሲው በተወሰኑ ልቦለዶቹ ላይ ከገፀባህሪያት ንግግር (dialogue) ይልቅ ትረካ ላይ አተኩሯል። ይህ ምናልባት ተመካሪ የአፃፃፍ ስልት እንዳልሆነ ልብ ይሏል። ንግግር አንዱ የሥነ ጽሑፍ ውበት ገላጭ ስልት እንደሆነ ማመኑ ግድ የሚል ይመስለኛል። ከዚህ ሌላ እንደ «እድናለሁ» እና «ምን ይዋጠኝ?» የተሰኙ ልቦለዶቹ ሁሉ ቀጥታ የሚነግሩ፣ የሚመክሩ ወይንም የሚሰብኩ አሥር ሃይማኖታዊ ግጥሞች በመጽሐፉ ተካተዋል። የጭብጣቸው ተመሳሳይነት ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ የሚያደርጋቸው ይመስላል።


እነዚህ ልቦለዶችና ግጥሞች በተለየ በሌላ መንፈሳዊ የልቦለድና የግጥም መድብል ቢወጡ መልካም ይሆን ነበር። በተለያዩ ዘመናት የተፃፉ ከመሆናቸው አንፃር በግጥሞቹ ውስጥ አንዱ ከሌላው በግላጭ የሚታይባቸው የብስለት ልዩነት አለ። «ዼጥሮስ ያባነነው ዶሮ»፣ «ኖሮ ያልኖረ»፣ «ባይተዋር» እና «ዓለም ላንቺ!» የተሰኙ የቅርብ ጊዜ ግጥሞች ብስለት እንደሚታይባቸው ሁሉ፤ «ቆምጣጣ ፍቅር»፣ «ማሪኝ»፣ «የልቤ ሳቅ» የመሳሰሉት ግጥሞች ከቃላት ጋጋታ በስተቀር ግጥምነታቸውን የሚያጎላ እምቅ የሃሳብ ብስለት ጎምርቶ አልታየባቸውም። በጥቅል ዕይታ ግን የአብዛኛው ግጥሞች አሰነኛኘት፣ ከተለመደው የሳድስ ፊደላት አጠቃቀም ወጣ ብሎ በውድ ቃላትና ፊደላት ቤት አመታታቸው፣ ሪትም መጠበቃቸው፣ ዜማ ሰጪነታቸውና ጠንካራ መልዕክታቸው የመጽሐፉን ዋጋ ከፍ እንዲል ያደርገዋል።


አልፎ አልፎ በግጥሞቹም ሆነ በልቦለዶቹ የፊደልና የስርአተ ነጥብ ግድፈት መታየቱም አልቀረም። ምናልባት መጽሐፉ ዳግም የመታተም ዕድል ከገጠመው ይህ ሁሉ ይስተካከላል የሚል እምነት አለ። ሽፋኑ እጅግ በደመቀ ቀይና ሰማያዊ ቀለም አሸብርቋለ። ይህ አይነት አቀራረብ ብዙውን ጊዜ በልጆች መጽሐፍት ላይ የሚመከር ነው፤ ደራሲው ይህን ሲያደርግ የውስጥ ቁምነገሩን እንዳይጋርድበት ስለምን አልተጠነቀቀም? ያስብላል። በጥቅሉ መጽሐፉ በተለያየ መልኩ የሰው ልጆችን ባህሪያት፤ ማለትም ቅንነትን፣ ክፋትን፣ ትዕግስትን፣ እምነትን፣ ተንኮልን፣ ፍቅርን፣ ጥላቻን ወዘተ ዳሷል። በጥሩ የአሰነኛኘት ጥበብ ግዙፍ አገራዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮችንም በጥልቅ ሃሳብ ዳሷል። ሊነበቡ ከሚመከሩ የፈጠራ ስራዎች አንዱ ነው ለማለት ያስደፈራል።


የአሳታሚን ደጅ ጥናት ችሎ፣ የማሳተሚያ ገንዘብን ቋጥሮ፣ የማከፋፈሉን አበሳ ታግሶ እንዲህ ጥበብን ለተደራሲ ለማድረስ መታተር ምስጋና የሚያሰጥ ነው እላለሁ። ያም ሆኖ ይህ መጽሐፍ ከተወሰኑ አከፋፋዮችና መጽሐፍ መደብሮች ሌላ በአዟሪዎች እጅ እምብዛም አለመታየቷ «ለምን ይሆን?» ያስብላል። እዚህ ላይ ከመጽሐፍት ገበያ ጋር የሚያያዝ ውስጤ የሚብላላን አንድ ሃሳብ አንስቼ ምልከታዬን ልቋጭ። አንዳንድ ጊዜ ጥበባዊ ስራ ጊዜና ወቅት አላቸው የሚያስብል ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። ዛሬ ጥበባዊ ስራና ንባብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኗቸውን ያበረቱት የሶሻል ሚዲያዎች ብቻ አይደሉም። የአከፋፋዮች፣ መጽሐፍት አዟሪዎችና የሽያጭ መደብሮችም ጭምር እንጂ። «እንዴት?» ቢሉ እነዚህ የንግድ ዘርፎች ከገቢ ጥቅም አንፃር ስም ያላቸው ሰዎችን መጽሐፍት ተመራጭነታቸውን በማጉላት ማሻሻጣቸው ነው።


በየመደብሮች፣ አከፋፋዮችና አዟሪዎች ፊት ለፊት የሚታዩት የእነዚህ ሰዎች መጽሐፍቶች ናቸው። ይህ መሆኑ ደግሞ ጥበብ በጥቂት ሰዎች አስተሳሰብ እንዳትመራ፣ አንባቢያን በእነሱ የአመለካከት ተፅዕኖ ስር እንዳትወድቅ ስጋት ያሳድራል። ዛሬ ዛሬ እንደሚስተዋለው የፖለቲካና የታሪክ መጽሐፍት ጊዜያቸው ነው። ወጎች እና ሙያዊ መጽሐፍትም ተፈላጊነታቸው በርትቷል። ምን ያህል ይሄዳሉ የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አንድ ነገር ሆኖ፤ አነስተኛ ገፅ ያላቸው የግጥም መጽሐፍትም በገበያው ፉክከር ውስጥ እየተፍጨረጨሩ መሆኑ ይታያል። እንደ እኔ አስተውሎት በዚህ ዘመን (ካለፉት አምስት ስድስት ዓመታት ሊባል ይቻላል) የረጃጅም ልቦለዶችና የአጫጭር ልቦለዶች ስራ ገበያውን አልገዙትም። ለምን? የሚለው ጥያቄ የአጥኚዎችን ምላሽ የሚያሻ ሆኖ፤ በእኔ ትዝብት የአከፋፋዮች፣ የሸያጭ መደብሮች እና የአዟሪዎች አድሏዊ ተፅዕኖ ነው ለማለት እደፍራለሁ።
ምክንያቱም አንባቢያን ሊመሰጥባቸው፣ ጥበባዊ ዋጋቸው ከፍተኛ መሆኑን ሊገነዘብ የሚችልባቸው መጽሐፍት አሉና። እንዲህ ያሉ መጽሐፍት ቢወጡም ገበያው ስላላበረታታቸው በየስርቻው እንዲሸጎጡ ግድ ብሏል። ረጅምና አጫጭር ልቦለዶች እንዲሁም ግጥሞች ጥበባዊ ዋጋቸው ከፍተኛ ነው። እኔ እንደሚገባኝ ዋናው የጥበባዊ ስራ መለኪያዎችም እነዚህ የስነ ጽሑፍ ውጤቶች ናቸው። እንደ ፍቅር እስከመቃብር፣ እንደ ጉንጉን፣ ሰመመን፣ ከአድማስ ባሻገር …የመሳሰሉ መጽሐፍትን የሚመጥኑ ሰራዎች ዛሬም የሉም አይባልም። የዚህን ዘመን የአንባቢያን እና የገበያውን ሁኔታ በመፍራት ደራሲያን ለህትመት አላበቋቸው ይሆናል እንጂ «ይኖራሉ» ብዬ እገምታለሁ። ምክንያቱም ስነ ጽሑፍም ከሰዎች አስተሳሰብና የንቃተ ህሊና ዕድገት ደረጃ ጋር አብሮ የሚያድግ ነውና።


ደራሲያን ያንን አቅም አውጥተው ወደ አንባቢያን ዘንድ ለመድረስ ያሉባቸው መሰናክሎች እንዳይራመዱ ካላደረጋቸው በስተቀር ደራሲያን ዘንድ እወቀቱ፣ ክህሎቱ፣ አቅሙም አለ። ምንም ጥርጥር የለውም። «ለሁሉም ጊዜ አለው» እንደሚባለው ካልሆነ በስተቀር። በዚህ ከፍተኛ አድሏዊነት የገበያ ፉክክር ውስጥ የፈጠራ ስራውን ይዞ ወደ አንባቢያን ለመድረስ የጣረው ደራሲና ጋዜጠኛ ደረጀ ትዕዛዙ መጽሐፉ ጥበባዊ ዋጋው ቀላል የሚባል አይደለም። ከተጽዕኖው ባለፈ ገበያውን ሰብሮ የመውጣቱ አቅም በመጽሐፉ ጥንካሬ ቢወሰንም፤ የደራሲው ብርታት ግን ለሌሎች አርአያነት ያለው ነው ለማለት እደፈራለሁ።


ደረጀ በመጽሐፉ መግቢያ ከልጅነቱ ጀምሮ በጋዜጦችና ራዲዮ ፕሮግራሞች ላይ ሲያደርግ የነበረው ነጻ ተሳትፎ ለፈጠራ ሥራ ብሎም ለጋዜጠኝነቱ ሙያ ጥሩ መንደርደሪያ እንደሆነው፤ በፈጠራ ስራ ደረጃ መጽሐፉ የመጀመሪያ ሥራው መሆኑን፣ ለቀጣይ ስራ እንደሚተጋም ገልፆም ነው ወደ ንባቡ የጋበዘው። የታዋቂው ጋዜጠኛ ደራሲና የታሪክ ተመራማሪውን ዻውሎስ ኞኞ የሕይወት ታሪክ ግሩም አድርጎ አዘጋጅቶ እንዳስነበበን ሁሉ አቅሙ ሌላም ድንቅ ስራ ያመጣልናል የሚል ተስፋን ያሳድራል።

 

·        ግሼን ደብረ ከርቤ እንዴት እና መቼ እንደደረሰ፤

·        የዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን የማይሽረው ሚና፤

በውብሸት ሙላት

የዚህ ጽሑፍ ምንጭ ‘’መጽሐፈ ጤፉት’’ ስለሆነች በቅድሚያ ስለመጽሐፏ ጥቂት ነጥቦችን ማንሳቱ ተገቢ ነው። ግሼን ደብረ ከርቤ ማርያም፣ለመስከረም 21 ንግሥ የሄደ ሰው ስለዚች መጽሐፍ ላይሰማ አይችልም። በዕለቱ በአደባባይ ስትነበብ፣ ስትተረክ፣ ስትተረጎም ትውላለች፤ በደብሩ ሊቃውንት። እኛም ስለዚች መጽሐፍ ከልጅነታችን ጀምረን ስትጠራ የሰማነውና የማናውቀው በአንስታይ ጾታ ስለሆነ የተለመደው አጠራር መጠቀም ተመርጧል።

የመጽሐፈ ጤፉት ስያሜ የመነጨው ከጽሑፉ ደቃቅነት ነው። ፊደላቱ እንደጤፍ ቅንጣት ቢያንሱ፣ ድቅቅ ቢሉ “መጽሐፈ ጤፉት” ተባለች። የመጽሐፏ ይዘት ወይም መጠን ግን ትንሽ አይደለም። ሙሉው የብራና መጽሐፍ ዳጎስ ያለ ነው።

መጽሐፈ ጤፉት በአንድ ጊዜ፣አልተጻፈችም። ይሁን እንጂ ብዙው ክፍሏ በአንዴ የተጻፈ ይመስላል። የመጽሐፈ ጤፉት ደራሲም ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ መሆኑን ለማወቅ ብዙ አዳጋች አይደለም። የተጻፈበትን ሁኔታም፣የደራሲውንም ማንነት በተመለከተ መጽሐፉን ያነበበ ማንም ሰው ይሄንን በቀላሉ ይረዳዋል።

ለዚህ ጽሑፍ በምንጭነት ያገለገለው በመሪጌታ የማነ ብርሃን ተተርጉሞ፣በግሼን ደብረ ከርቤ ደብር ሰባካ ጉባኤ አማካይነት በ2006 ዓ.ም. የታተመው ነው። መጽሐፏ የተወሰኑ ቦታዎች የምትሸጥ ቢሆንም በሶፍት ኮፒም ትገኛለች።

በመጽሐፈ ጤፉት ላይ፣  መስቀሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ከተሰቀለበት በኋላ ጠፍቶ እንዴት፣ የት እና መቼ እንደተገኘ ተገኘ ተገልጿል። ወደ ግብጽ መቼና እንዴት እንደተወሰደም ተተርኳል። ከግብጽ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ፣ ግሼን ደብረ ከርቤ እንዴት እንደደረሰ እና የነገሥታቱ በተለይምም የዓፄ ሰይፈ አርዓድ፣ የዓፄ ዳዊት ካልእ እና የዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ሚና ምን እንደነበር ተወስቷል።

ግሼን ከደረሰ በኋላ እንዴት እንተቀመጠ፣ የት እንደተቀመጠ፣ ለመስቀሉ ደኅንነትና ጉዳት እንዳይደርስበት ምን መደረግ እንደሚገባ ትዕዛዛት ተላልፈዋል። የደብሩና የአምባሰል አስተዳዳሪ (የዣንጥራሩ) ግንኙነት ምን መሆን እንዳለበትም ንጉሣዊ ድንጋጌዎች አሉት። በወቅቱ፣ ከአምስት መቶ በላይ የሚሆኑ የነገሥታቱ ቤተሰቦች በአምባው ላይ ይኖሩ ስለነበር እነሱንም የሚመለከት ሕግጋት ተሠርቷል።

ታሪኩንም ደንቡንም የጻፈው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ነው። ንጉሠ ነገሥቱ፣ መስቀሉ ከግብጽ እንዴት እንደመጣ፣ ግሼን እንዴት እንደደረሰ፣ ቤተ ክርስቲያናቱ ስለታነጹበት ሁኔታ፣ መስቀሉ እንዴት እንደተቀመጠ የሚያትቱን ክፍሎች እዚያው በደብሩ እያሉ የተጻፉ ይመስላል። የመስቀሉን የቀደመ ታሪክ እንዲሁም የደብሩን እና የዣንጥራሩን ግንኙነት ደግሞ ኋላ ከደብረ ብርሃን (ከዋና ከተማው) ሆኖ በሌላ ጊዜ የላካቸው ይመስላል።  እስኪ ስለመስቀሉ የሦስቱን ነገሥታት ሚና በቅድሚያ እንመለከት።

ዓፄ ሰይፈ አርዓድ (1328-1356)፤

ንጉሡ፣ ወደ ምስር (ግብጽ) ወርደው እንደነበር መጽሐፈ ጤፉት ላይ ተገልጿል። የሔዱትም በዘመቻ መልክ ነው። የወቅቱ የግብጽ ንጉሥ (መርዋን አልጋዲን) ከኢትዮጵያ ጋር በሃይማኖት አንድ በሆኑት በእስክንድርያ ሕዝበ ክርስቲያን ላይ አገዛዙን ከማጽናቱ ባለፈ የእስክንድርያውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚካኤልን (47ኛው ሊቀ ጳጳስ) ስላሰራቸው ለማስፈታት ወደ ግብጽ ዘምቷል።

የግእዙ ንባብ እንዲህ ይላል፤

“ወሶበ ሰምዓ ንጉሠ ኢትዮጵያ ሰይፈ አርዓድ  ከመ ኰንንዎ መኳንንተ ተንባላት ለዝንቱ አብ ሊቀ ጳጳሳት አባ ሚካኤል ወሞቅሕዎ። ቀንዓ ቅንዓተ መንፈሳዊተ በእንተ ዘዘኮነ እስክንድርያ ወኢትዮጵያ አሐተ ሃይማኖተ። ወወረደ ብሔረ ግብፅ ዘምስለ ብዙኃ ሠራዊት።”

ታሪከ ነገሥቱም ቢሆን ንጉሡ ወደ ግብፅ መውረዳቸውን ይገልጻል። ልዩነታቸው የታሰሩት ሊቀ ጳጳስ ስም ላይ ብቻ ነው። በታሪከ ነገሥቱ የሊቀ ጳጳሱ ስም አባ ማርቆስ ነው።

ዓፄ ሰይፈ አርዓድም ግብፅ ወርደው ለመርዋን አልጋዲን ጳጳሱን ከእስር እንዲፈታ ካልሆነ ግን በመካከላቸው ፍቅር እንደማይኖር ስለጻፈላቸው ከእስር ፈቷቸው። ንጉሡም ለሊቀ ጳጳሱ እጅ መንሻ ወርቅ ልከው ወደ አገራቸው ተመለሱ። ስለሆነም፣ በመጽሐፈ ጤፉት መሠረት በዐፄ ሰይፈ አርዓድ ዘመን መስቀሉ አልመጣም። ይሁን እንጂ፣ ታሪኩ ከላይ በቀረበው መልኩ ተካትቷል።

ዓፄ ሰይፈ አርዓድም በ1328 ዓ.ም. ነግሠው 28 ዓመታት ከገዙ በኋላ እንዳረፉ መጽሐፏ ገልጻለች። ቀጥሎም ልጃቸው ውድም አስፈሬ ለ10 ዓመታት ነግሷል።

ዳግማዊ ዓፄ ዳዊት (1366-1397)፤

መጽሐፈ ጤፉት፣ እንደመጽሐፍ የተጻፈችበት ምክንያትን እንዲህ በማለት ይጀምራል።

“… ንዌጥን  በረድኤተ እግዚአብሔር ሕያው ዘከመ ተረከበ መስቀለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ መንግሥቱ ለዳግማዊ ዳዊት…. ወዘከመ መጽአ ውስተ ብሔረ ኢትዮጵያ በመዋዕለ መንግሥተ ወልዱ ዘርዓ ያዕቆብ። ወቦአ ውስተ ደብረ ነገሥት አሀገረ አምባሰል።”

የአማርኛ ትርጉሙም እንዲህ ነው። “በዳግማዊ ዳዊት ዘመነ መንግሥት የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል እንደተረከቡ፤ ልጃቸው ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ በነገሡበት ዘመንም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አምባሰል ደብረ ነገሥት እንደገባ (እንደተቀመጠ) እንናገራለን።”

ከዚህ የምንረዳው ዓፄ ዳዊት መስቀሉን ከግብፆች ተረክቧል። ይኹን እንጂ፣ በዓጼ ዳዊት ዘመን ወደ ኢትዮጵያ አልገባም።

ታዲያ ዓፄ ዳዊት ተረክበውት ከነበረ፣ ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ  እስኪነግሥ (ቢያንስ ለ35 ዓመታት ያህል የት እንደነበር አሁንም በመጽሐፈ ጤፉት በዝርዝር ተተርኳል። ታሪኩም በአጭሩ እንዲህ ነው።

የምስሩ ንጉሥ፣ ዓፄ ሰይፈ አርዓድ መሞቱን ሲሰማ በድጋሜ ጳጳሱን አሰሯቸው። በዚህን ጊዜም ከምስር ሕዝበ ክርስቲያን በተጨማሪ የሮም፣ የቁስጥንጥንያ፣ የሶሪያና አርመን ክርስቲያኖች በግብፁ ንጉሥ ድርጊት ምክንያት መስቀሉን መሳለም እንዳልቻሉ እና የኢትዮጵያን ንጉሥ እንዲረዷቸው ጥያቄ አቀረቡ።

ይኼን የሰማው፣ ለሃይማኖቱ ቀናተኛ የሆነው ዳግማዊ ዳዊት ወደ ግብፅ ዘመተ። ንጉሡም ካርቱም በደረሰ ጊዜ የዓባይን ወንዝ ወደበርሃ እንዲፈስ በማድረግ አቅጣጫውን እንዲቀየር አደረገው።  ግዕዙ እንዲህ ይነበባል። “ወሶበ በጽሐ ኀበ ካርቱም ወጠነ ከመ ይሚጦ ለፈለገ ዓባይ ከመ ይክልኦሙ ማየ ፈለገ ዓባይ…”

የዓፄ ዳዊትን አድራጎት የሰማው የግብፁ ንጉሥ፣ የመርዋን አልጋዲን ልጅ አህመድ፣ ጳጳሱንም ሆነ ሌሎች እስረኞች ከእስር ለቀቃቸው። በመቀጠልም ጳጳሱንና የየአገራቱን ሕዝበ ክርስቲያን፣ ዓፄ ዳዊትን ዓባይ እንደቀድሞው እንዲፈስ እንዲሁም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለእጅ መንሻ የሚሆን ወርቅ በመላክ ጭምር አስለመኑ።

 ዓፄ ዳዊት ግን ጉዞውን ሳያቆም  ወደ አስዋን ወረዱ። ወርቁንም ሳይቀበል መልሶ ላከ። የውሃውንም ፍሰት አላስተካክልም አለ። ይልቁንም “መስቀሉን ስጠኝ” በማለት መልዕክት ሰደደ። “ወንጉሠ ምስርሰ አህመድ ወመኳንንተ ተንባላት ተሐውኩ ብዙኃ በምክንያተ ዝንቱ።” ይላል ግዕዙ። “በዚህም ምክንያት የአሕዛቡ የምስር ንጉሥ አህመድና መኳንንቱ ፈጽመው ታወኩ።” የንጉሡን ቁርጠኝነት ሲያውቁ መስቀሉን፣ ሉቃስ የሣላቸውን ሰባት የእመቤታችንን (የማርያምን) ሥዕሎች ዮሐንስ ወንጌላዊ የሣለውን ሥዕል ጨምሮ ላከ።

ይህም የተደረገው መስከረም 10 ቀን ነው። ንጉሡም በዚህ ቀን ታላቅ በዓልን አደረገ። በዚህ ብቻ ሳይበቃም፣ ከመስከረም 17 ጀምሮ ለ7 ቀናት ታላቅ በዓልም ተደረገ። ከዚህ በኋላም፣ እነዚህን ቅርሶች በመያዝ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ላይ ሳለ፣ ስናር የተባለ ቦታ ላይ ዓፄ ዳዊት በድንገት አረፈ። ያረፈው፣ ጥቅምት 9 ቀን ነው። ሰላሳ ዓመት፣ ከ6 ወራት፣ ከ9 ቀናት ገዝቶ ሞተ።

በመሆኑም፣ ዓፄ ዳዊት መስቀሉን የተረከበው በ1397 ዓ.ም. መስከረም 10 ቀን ሲሆን የሞተው ደግሞ በዚሁ ዓመት (ሱዳን ውስጥ) ስናር ላይ ነው። ከዚያም፣ጣና፣ ዳጋ እስጢፋኖስ ተቀበረ። (ዓፄ ዳዊት ያረፉበትን ዓመት በተመለከተ በርካታ መጽሐፍት ላይ ልዩነት እንዳለ ያጤኗል። በዚህ ጽሑፍ ላይ ግን እንዳለ የመጽሐፈ ጤፉት ነው የተገለጸው።) 

ታሪከ ነገሥቱ በበኩሉ ባዝራ (በቅሎ) ግምባራቸው ላይ ረግጣ እንደገደለቻቸው ይገልጻል። መጽሐፈ ጤፉት፣ በምን ምክንያት እንደሞቱ ባይናገርም፣ ሊሞቱ ሲሉ በዚሁ ስናር በተባለው ቦታ ጥቅምት 9 ቀን ለልጆቻቸው የመንግሥትን ሥርዓትና ወግ ጽፈው እንዳረፉ ይናገራል። ከመሞታቸው በፊት እንደሚሞቱ ያወቁት ምናልባት የባዝራዋ ጎድቷቸው ነገር ግን በቅጽበት ባለመሞታቸው ሊሆን ይችላል።

ይሁን እንጂ ንጉሡ ሲሞቱ ቅርሶች አብረው አልመጡም። ዘርዓ ያዕቆብ  እስኪነግሥ ድረስ እዚያው ስናር እንደቀሩ አሁንም መጽሐፈ ጤፉት ትነግረናለች። በዳዊትና በዘርዓ ያዕቆብ መካከልም ሌሎች ልጆቹ እንደነገሡም እንዲሁ ተተርኳል።

በመሆኑም፣ መስቀሉንም ሆነ ሌሎቹ ቅርሶችን ዓፄ ዳዊት ተረክቧቸው ነበር። ነገር ግን በንጉሡ ድንገተኛ ዕረፍት ምክንያት ስናር ላይ ቀሩ።

ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ (ከ1427 ጀምሮ)፤

ዓፄ ዳዊት በስናር አርፎ በዳጋ እስጢፋኖስ ሲቀበር መስቀሉ እና ሌሎቹ ቅርሶች እዚያው ስናር እንደቀሩ ተገለጿል። ዓፄ ዳዊት በሕይወት በነበረበት ወቅት “ይነብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” የሚል ህልም ዐይቶ እንደነበር ተጽፏል። ትርጓሜውም “መስቀሌ በመስቀል ላይ ይቀመጣል፤” ነው።

ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብም በ1427 ዓ.ም. ነገሠ። ኋላ ላይ እንደ አባታቱ ህልም ተገለጠለት። ይህ የኾነው ደግሞ በነገሠ በ15 ዓመቱ ነው። 1442 ዓ.ም. መሆኑ ነው። ህልሙም፣ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” የሚል ነው። ትርጓሜውም “መስቀሌን በመስቀል ላይ አኑር/አስቀምጥ!” የሚል ነው። ለአባታቱ በትንቢትነት፣ወደ ፊት በሚፈጸም መልኩ የታየው ህልም፤ ለዘርዓ ያዕቆብ በትእዛዝነት ተገለጠ።

ንጉሡም ከሊቃውንቱ ጋር በመመካከር፣ ስለ ህልሙ ሲያወጣና ሲያወርድ አንድ ዓመት አለፈ። ከዚያም፣ሊቃውንቱና የመንግሥቱ አማካሪዎች ፍቹን ነገሩት። “ወእሙንቱኒ ይቤሉኒ እስመ መስቀለ ክርስቶስ አምኃሁ ለአቡከ ሀሎ በእደ መኰንነ ተንባላት ዘመካ መዲና” ብለው ለገሩኝ ሲሉ ራሳቸው ንጉሡ ተናግረዋል። ትርጓሜውም፣ “እነሱም ይኽማ ለአባትህ እጅ መንሻ ሆኖ የመጣው የክርስቶስ መስቀል በመካ መዲናው ሹም እጅ አለና አምጣ!” ሲልህ ነው ይሉታል።

ከዚያም ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብም “ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት” በማለት ወደ መካ መዲናው ሹም ዘመቻ ጀመሩ። የመካና መዲናው ሹም ስምም ‘ጋፍሔር’ ይባላል። በዚያን ዘመን የነበረው የምስሩ ንጉሥ ደግሞ ‘አሽረፍ’ ነበር። ከጽሑፉ መረዳት የሚቻለው ጋፍሔር፣ በንጉሥ አሽረፍ ሥር የነበረ ገዥ መሆኑን ነው።

ጋፍሔርም፣ የዘርዓ ያዕቆብን መምጣት ሲሰማ “የአባትህ ገንዝብ በእጄ አለና ተቀብለህ ወደ አገርህ በሰላም ተመለስ” የሚል መልዕክት ላከለት። ዘርዓ ያዕቆብም መስቀሉን፣ ሰፍነጉን፣ ከለሜዳውን፣ ሥዕሎቹን፣ የቅዱሳኑን አጽም እና ሌሎችንም በመቀበል ከነሠራዊቱ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።

ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በኋላ ለሦስት ዓመታት ያህል በየተራራው በመዞርና በማሳረፍ እንደ ህልሙ ለመፈጸም ንጉሡ ጥሯል። ከሦስት ዓመታት መንከራተትና ልፋት በኋላ እስከ ዓፄ ይኩኖ አምላክ ድረስ ደብረ ነጎድጓድ፣ ቀጥሎም ደብረ ነገሥት የተባለችው የአሁኗ ግሼን ደብረ ከርቤ አምባ ላይ ደረሰ። የተራራውን ግርጌ በመከተል ሦስት ጊዜም ዞራት።ድጋሜ ከመልአክ በህልም ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ ከወቅቱ ጳጳሳት ከአባ ሚካኤል እና ከአባ ገብርኤል ጋር በመሆን ወደ አምባው በ1446 ዓ.ም. መስከረም 21 ቀን ገቡ።

ከአምባው ላይ ቀደሞ በ514 ዓ.ም. በዓፄ ካሌብ ዘመን፣ በአባ ፈቃደ ሥላሴ፣ የናግራን መነኩሴ አማካይነት የተተከሉ የማርያምንና የእግዚእብሔር አብ ቤተ ክርስቲያናት ስለነበሩባቸው የእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያንን ድጋሜ በማሳነጽ በመሠረቱ ሥር መስቀሉንና ሌሎቹን ቅርሶች አስቀመጣቸው።

የቤተ ክርስቲያኑ ግንባታም ሦስት ዓመታት ፈጅቷል። ቤተክርስቲያኑ የነበረበት ቦታ ርጥበት ያለበት ስለነበር ርጥበቱን የሚያጠፋ አፈር አድርገውበታል። ለመስቀሉ እና ለሌሎች ቅርሶች ማስቀመጫ ይሆን ዘንድ አርባ ክንድ ወርድ፣ ርዝመትና ከፍታ ያለው ጉድጓድ በማስቆፈር እና ዙሪያውን በመገንባት ርጥበቱም እንዲጠፋ በሰማንያ ስምንት ግመሎችና በመቶ አጋሰስ ከኢየሩሳሌም አፈር በማስመጣት  ለግንባታው ውሏል።

ከዚያም መስቀሉን፣ ሥዕላቱን፣ የቅዱሳኖቹን አጽም፣ ሰፍነጉን፣ ጅራፉን፣ ከለሜዳውን ወዘተ በምን ሁኔታ እንደተቀመጠ በዝርዝር ተገልጿል። የእነዚህ ቅርሶች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ለጉዳትም ለመቅሰፍትም ስለሚሆን ጊዜው እስኪደርስ ማንም እንዳያወጣቸው ትእዛዝ ተበጅቷል። በተለይ መስቀሉ በተለያዩ ሁኔታ ከተዘጋጁ ድርብርብ ሳጥን ውስጥ ሌላ የወርቅ እና የዕንቁ ሳጥን በማዘጋጀት በውስጡም በሰንሰለት በማሰር በአየር ላይ ብቻ እንዲረብ (እንዲጠለጠል) መደረጉን ተጽፏል።

መስቀሉም ሲመጣ፣ እንደሰው እንዲቆም አድርገው የውጮቹ ጠቢባን ሰገባ እና እግር እንዳዘጋጁለትም ተገልጿል። በመጨረሻም፣ የጉድጓዱ አፍ ተዘግቶ በላዩ ላይ ድጋሜ የእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ታነጸ። የማርያምን ቤተክርስቲያንም እህቱ ዕሌኒ (ሚስቱ አይደለችም) በድጋሜ አሳንጻው አብረው በ1449 ዓ.ም. መስከረም 21 ቀን ተመረቁ። ቅዳሴ ቤታቸው በድጋሜ ተከበረ።

ሲጠቃለል፣ መስቀሉንና ሌሎች ቅርሶችን ዓፄ ዳዊት በ1397 ዓ.ም. መስከረም 10 ቀን ተረክቧል። ነገር ግን፣ ስናር ላይ ሲደርስ ስላረፈ እነዚህ ቅርሶችም እዚያው ለ46 ዓመታት ይህል በአሕዛብ እጅ ሰንብተዋል። ኋላ ላይ በ1443 ዓ.ም. ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ከነበሩበት ቦታ በመስመጣት በ1446 መስከረም 21 ቀን አምባሰል፣ደብረ ነገሥት (ደብረ ከርቤ ብለው የሰየሟት) ደርሷል። ንጉሡም አብሮ በመሔድ፣ቤተክርሰቲያኑንም አሳንጿል። ሥርዓቱንም አብጅቷል።

መስቀሉ መስከረም 21 ቀን ግሼን ደብረ ከርቤ ደረሰ። ቤተ ክርስቲያናቱ ከእንደገና ታንጸው፣ መስቀሉም በክብር ተቀምጦ ክበረ በዓሉ የተከናወነው መስከረም 21 ቀን ነው። መስከረም 21 ቀን ምን ጊዜም ግሼን ትከበራለች። ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብን ክፍሉን ከጻድቃኑ ጋር ያድርግል።

"ዮ ማስቀላ"

September 28, 2017

 

ወንድማገኝ አንጀሎ ሲሳይ

 

ቁጪ ኦይሳ ደሬ!!!
ሳሮ ሳሮ አይመላ ሎኦ፤
ዳፊን ዱጾንታይ ወርቃ ወደሮ፤
ቁጪ ደሬ አሲ አይመላ ሎኦ::

 

የብሔረሰቦች፣ የቱባ ባህሎችና፣ የአኩሪ ታሪኮች ሀገር የሆነቸው ኢትዮጵያችን ካሏት 13 ወራቶቿ ውስጥ በመስከረም ወሯ በተለየ መልኩ ትወለዳለች፣ ትወደሳለች፣ ትዋባለች፣ ትደምቃለችም። ለውልደትና ድመቀቷ ደግሞ የዘመን መለወጫና የመስቀል በዓላቶቿ ያሏቸው ሚና የጎላ ነው። እንደ ኢትዮጵያችን ተጨባጭ ሁኔታ በሀገራችን የሚከበሩ በዓላት ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊና፣ መንግስታዊ ይዘት ያላቸው ናቸው። ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ይዘት ካሏቸው በዓላቶች ውስጥ ደግሞ የመስቀል በዓል አንዱ ነው።


መስቀል ለህዝበ ክርስቲያኑ ኢየስስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ኃጢዓት ሲል የተሰቀለበት፣ ደሙ የፈሰሰበት፣ ስጋው የተቆረሰበት፣ ሰላምን ያወጀበት፣ ድህነትን የፈጸመበት፣ ኦሪትን ያሻገረበት፣ አዲስ ኪዳንን ያወጀበት፣ ዳግመኛ ለፍርድ እንጂ ስለሰው ልጆች ኃጢአት ሲል ሊሰቀል እንደማይመጣ ቃሉን ያጸናበት፣ ሰዎች ዳግመኛ ስለ ኃጢዓታቸው ምክንያት እንዳይኖራቸው ያደረገበት በመሆኑ ምልክታቸው፣ ትምክህትና አርማቸው ነው። እናም ይህ መስቀል ለዘመናት ጠፍቶና ተደብቆ ነበርና ንግስት ዕለኒ ባስደመረችው ደመራ አማካኝት በመገኘቱ የተገኘበትን እለት መነሻ በማድረግ ብሎም መስቀል ለክርስቲያኑ ካለው ትርጉም አንጻር በየዓመቱ መስከረም 17 በመላ ሀገራችን በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። ቀኑም ሆነ መስቀሉ የሚከበሩ እንጂ የሚመለኩም አይደሉም።


የመስቀል በዓል ከኃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ በሰው ልጆች ማህበራዊ ህይወት ውስጥም ጎልቶ የገባ በመሆኑ ባህላዊ ይዘትንም የያዘበት ሁኔታ አለ። ለአብነትም በሰሜኑ የኢትዮጵያችን ክፍል ሴቶች በግንባራቸው ላይ በመነቀስ ብሎም በደቡብ ኢትዮጵያ በአከባባር ደረጃ ባህላዊ ይዘቱ የሰፋ መሆኑን መጥቀስ ይቻላል። በደቡብ የሀገራችን ክፍል ለአብነትም በጉራጌ ብሎም በጋሞ (በዶርዜ - በመሀል ከተማ/በአዲስ አበባ ይበልጥ በዚህ ስሙ ስለሚታወቅ ነው) አካባቢዎች በሰፋ መልኩ ለዘመናት ሲከበር እንደነበረ ታሪክ (ሳይቆራርጥና ሳይሸራረፍ አስቀድሞ የነበረ እንደሆነ በሚያሳይ መልኩ) ይነግረናል፤ መረጃዎችም ያሳዩናል።


የመስቀል በዓል (ወይም ማስቃላ) ልክ እንደ የጉራጌ ብሔረሰብ ሁላ በጋሞ ብሔረሰብም ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ከሌሎች በዓላት በተለየና በደመቀ መልኩ/ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል። በዓሉ ከሌሎች በዓላት የሚለይበት አያሌ ምክንያቶች ቢኖሩትም የአንድ ቀን በዓል ብቻ አለመሆኑ ማለትም ከዋናው የመስቀል በዓል ቀን ወይም ከመስከረም 17 አንድ ሳምንት ቀድሞ የሚጀመርና ከመስከረም 17 አንድ ሳምንት በኋላ/ዘግይቶ የሚጠናቀቅ በአጠቃላይ 15 ቀናቶችን እንዲሁም በዝግጅቱ ደግሞ ዓመት የሚፈጅ መሆኑ በዋናነት የሚጠቀስበት መለያው እንዲሆን አስችሎታል።


በእነዚህ የበዓሉ ጊዜአቶች ውስጥ የተበታተነ ይሰበሰብበታል፤ እርቆችም፣ ጋብቻዎችም፣ መልካም ምኞቶችና ምርቃቶችም ይከናወኑበታል። አሮጌ የተባሉ ነገሮች ሁላ በአዲስም ይተኩበታል። ለዚህም በበዓሉ ዕለት የሚደመረው የደመራ ብርሃን እንደመሸጋገሪያ ድልድይ ከመታሰቡም በላይ ተስፋም ይፈነጠቅበታል። በዓሉን ከቤተሰብ፣ ከዘመድና ወዳጆቻቸው ጋር ለማክበር በማለት ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ወደ አካባቢው የሚጎርፈው የብሔረሰቡ ተወላጆች ቁጥር የትየሌሌ በመሆኑ የትራንስፖርት ችግር በዋናነት በዚሁ ወቅት ሲከሰትም ይታያል።


ይህ የመስቀል በዓል ከዚህ በፊት ሁሉም የአካባቢው ደሬዎች በተሰባሰቡበት ለአብነትም በዲታና በቦንኬ ወረዳዎች እጅጉን ሳቢና ማራኪ በሆነ መልኩ እንደተከበረ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ዓመትም (በ2010 ዓ.ም) የጋሞዎቹ ምድር በሆነቸው በደሬ ቁጫም በደማቅ ሁኔታ በትላንትናው ዕለት ተከብሯል። በዕለቱም የደሬ ቁጫ ሕዝብ እንግዶቹን በአግባቡ ተቀብሎ በአግባቡም ሸኝቷል:: በክብረ በዓሉ ወቅትም በተለኮሰው ችቦ አማካኝነት አብሮነት፣ አንድነትና ፍቅር ባማረ መልኩ ተገልጿል፣ ታይቷል፣ ተሰብኳልም።


ምንም እንኳን በዓሉ በዚህ መልኩ መከበሩ መልካም ቢሆንም ለቀጣይ ከዚህ በተሻለ መልኩ ሊያድግ፣ ሊበለጽግ እንዲሁም ከአካባቢያዊና ሀገራዊ እይታ በዘለለ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅናን ሊያገኝ ስለሚገባው በዚሁ ዙሪያ ላይ አያሌ ስራዎች ከወዲሁ ተጠናክረው ሊሰሩ ይገባል እላለሁ። ይህም የአንድ ጊዜ ወይም አጋጣሚ ሳይሆን ጤናማ እይታንና ጠንካራ መንፈስን ተላብሶ ወጥና ዘላቂ በሆነ መልኩ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር አስተማማኝ መሠረትን የሚጥል ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ በዓሉ በተለያዩ አቀራረቦች በአንድ ቦታ (በማዕከል) እንዲሁም ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ (ከአንዱ ደሬ ወደ ሌላ ደሬ) እየተዘዋወረ መከበር መቻሉ የትውልዱን ግንዛቤ አስፍቶ የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ ለትውልዱ ከራሱ ደሬ አልፎ የሌላውንም ደሬ እንዲያውቅ፣ አውቆም አብሮነቱን እንዲያጠናክር ዕድልን ይፈጥርለታል። እናም የተጀመረው ሊጠናከር ይገባል። ጥሩም ጅማሮ ነው።


በዓሉም እንደሌሎቹ የኢትዮጵያችን ይበልጥ ደግሞ እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ለብሔረሰቡ ተወላጆች ሲወርድና ሲዋረድ የመጣ የማንነታቸው ጉዳይ ነውና ምንም እንኳን በሲምፖዚየም መልክ የተጀመረ የሚበረታታ እንቅስቃሴ ቢኖርም ከላይ የጠቀስኳቸው ሀሳቦችን ጨምሮ ከአሳታፊነት፣ ከምንም ነገር በላይ ታሪካዊና ባህላዊ ይዘቱን ሊያጎላ፣ ባህላዊ አልባሱን ሊያስተዋውቅና፣ ቋንቋውን ሊያሳድግ ከሚችልበት አግባብ አኳያ ብዙ ሊሰራበትና ሊተዋወቅ ይገባል እላለሁ።

 

በጥበቡ በለጠ

Artመስከረም ወር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ክስተት ያለው የወራቶች ሁሉ አስገራሚ ወር ነው። ይህ የሆነበትም ምክንያት መስከረም ሁለት ቀን 1967 ዓ.ም አብዮት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ፈነዳ። አብዮቱ ሲፈነዳ ኢትዮጵያ ከሦስት ሺ ዓመታት በላይ ጠብቃ ያኖረችው የንጉሣዊ አስተዳደር ተገረሠሠ። በተለይ ደግሞ የሰለሞናዊው ስርወ መንግሥት ወራሽ የሚባሉት ቀዳሚዊ ኃይለሥላሴ ኢትዮጵያን ለ44 ዓመታት ከመሩ በኋላ ሲወርድ ሲወራረድ የኖረው አስተዳደር ተገረሠሠ። ወታደሮች በመፈንቅለ መንግስት የአዛውንቱን የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ሥርዓት ጥለው ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ መሠረቱ። “ስዩመ እግዚአብሔር” ወይም በእግዚአብሔር የተሾሙ እየተባሉ የሚነገርላቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ከቤተሰቦቻቸውና ከባለስልጣኖቻቸው ጋር ሆነው ወደ እስር ቤት ተወረወሩ። ደርግ የ82 ዓመት አዛውንት አሰረ እየተባለም በወቅቱ በነበሩ የውጭ አገር መገናኛ ብዙሃን ተዘገበ።

ኢትዮጵያ የማይታመን ነገር እየታየባት እንደሆነ ይወራ ነበር። በሕዝቡ ለረጅም ዓመታት እንደ ንጉስ ብቻ ሳይሆን መለኮታዊ ኃይል አላቸው እየተባለ የሚታመንባቸውን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን የሚጥልና የሚያስር ጉልበት ከቶስ ከየት ተገኘ እየተባለ ግራ የገባቸውም ነበሩ።

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በዘመን ስልጣናቸው የኤሌ ተግባራት ባለቤት ሆነው ስለቆዩ በእጅጉ ይከበሩ እና ይፈሩ ነበር። ከአፄ ምኒልክ ሞት በኋላ ስልጣን ወደ ልጅ እያሱ ከመጣ ጀምሮ ከዚያም ወደ ንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ መጥቶ በመጨረሻም ራስ ተፈሪ ወይም ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘንድ እስከሚደርስ ድረስ የነበረው የቤተ-መንግስት ሽኩቻ እና ትግል አሸንፈው ንጉስ የመባላቸው ጉዞ በራሱ አስደናቂ ነበር።

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በ1923 ዓ.ም ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ  የማስተዳደሩን ሥራ ከተረከቡ በኋላ ሀገሪቱን ወደ ዘመናዊ ጉዞ ለመውሰድ መጣራቸውን ታሪካቸውን የፃፉ ደራሲያን ይገልጻሉ።

አፄ ኃይለሥላሴ በአዲሱ የአመራር ጎዳናቸው ፓርላሜንት በዘመናዊ መልክ ለማቋቋም ብርቱ ጥረት አድርገዋል። የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት አፅፈው አጸድቀዋል።

በነዚህና በመሣሰሉት ጉዞ ውስጥ እያሉ ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወረረች። ሀገሪቱ አስከፊ መቀመቅ ውስጥ ገባች። ከሰማይ ላይ የመርዝ ጋዝ በአውሮፕላን ይጣልባት ጀመር። ፋሽስቶች ያለ የሌለ ሃይላቸውን አደራጅተው ጥንታዊቷን የነፃነት አገር ወረሩ። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ከካቢኔዎቻቸው ጋር መክረው ለዲፕሎማሲ ትግል ከኢትዮጵያ ወጥተው ወደ እንግሊዝ ተጓዙ። ስደተኛ የኢትዮጵያ ንጉስ ሆኑ።

ታዲያ በስደት ዘመናቸው ውስጥ ሆነው የማይታመን አስገራሚ የዲፕሎማሲያዊ ትግል አደረጉ። ከወደ እንግሊዝ ሲልቪያ ፓንክረስት የምትሰኝ የምንግዜም የኢትዮጵያ ወዳጅ አፈሩ። ከሲልቪያ ፓንክረስት እና ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር ሆነው የእንግሊዝንና የመላው አለም ኃያል መንግስታት ለማሳመን ብርቱ ትግል አደረጉ።

ዛሬ የተባበሩት መንግስታት እየተባለ በሚጠራውና በወቅቱ ሊግ ኦፍ ኔሽን በሚባለው ስብሰባ ላይ ተገኝተው አለምን ያስደመመ ንግግር አደረጉ። ንግግራቸውም ወዲያው ተተርጉሞ በአለም ተሰራጨ። ለንግግራቸው ርዕስ የተሰጠው እግዚአብሔርና ታሪክ ፍርዳችሁን ሲያስታውሱት ይኖራሉ የሚል። God and history will remember your jejment በዚሁ ንግግራቸው ያሳሰቡት ፋሽስቶች ኢትዮጵያን ወርረው ህዝቧን በግፍ እየጨረሱት ስለሆነ ዓለም ተባብሮ ኢትዮጵያን ነጻ እንዲያወጣ ነው። ካለበለዚያ ትልቁ አሳ ትንሹን ይዋጠው የምትሉ ከሆነ ነግ በራሳችሁ ሲደርስ ታዩታላችሁ ብለው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በሊግ ኦፍ ኔሽን ስብሰባ ላይ ትንቢት ተናገሩ ተብሎ እስከ ዛሬ ይወሳል። ምክንያቱም አዶልፍ ሂትለር ተነስቶ 6 ሚሊዮን አይሁዳዊያንን ሲፈጅ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የተናገሩት ትንቢት ነው ተብሎም በብዙ ሰዎች ዘንድ ይታመናል። በዚህ ምክንያት አለማቀፋዊ ተቀባይነታቸው የአለምን መሪዎች ትኩረሰት ሳበ።

ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የእንግሊዝን መንግስት አሳምነው ከጎናቸው አቁመው በውድ አርበኞቻቸው መስዋዕትነት ፋሽስት ኢጣሊያን ከኢትዮጵያ ምድር በድል አባረሩ። ከ5 ዓመታት የውጭ አገር ስደታቸው ተመልሰውም ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ወደ ዙፋናቸው ተመለሱ። ከዚያም በጦርነት የወደመችውን አገራቸውን መልሶ የማቆም ስራ ውስጥ ገቡ።

በተለይ በትምህርቱ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የኢትዮጵያ ልጆች በጥራት እንዲማሩ በር ከፈቱ። አያሌዎች በየሀገራቱ እየሄዱ እንዲማሩ አደረጉ። የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ያደረጉትን ብርቱ ትግል ብዙዎች ጽፈውላቸዋል።

በተለይ ደግሞ የካሪቢያን ምድሯን፣ የጀማይካዊያኑን መዲና ኪንግ እስተገን ከረገጡበት ሰዓት ጀምሮ የጃንሆይ ታሪክ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀየረ። በጃማይካዊያን ዘንድ መሲህ ተደርገው ተቆጠሩ። ምድራዊ ሰው ብቻም አይደሉም ብለው አመኑባቸው። በዚህም የራስ ተፈሪያዊያን እምነት በአለም ላይ ተስፋፋ። የሬጌ ሙዚቃ ስልቱ ሁሉ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ከፍ አድርጎ መጥራት ሆነ።

በአለም ላይ ግዙፍ እንደሆኑ የሚነገርላቸው እንደ ኦክስፎርድ እና ሀርቫርድን የመሣሠሉ 20 ዩኒቨርስቲዎች በልዩ ልዩ ጊዜ ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የክብር ዶክተሬት ድግሪ ሰጧቸው። ንጉሠ ገናና ሆነው ሆነው ወጡ።

በቻይና በኮሪያ ባደረጉት ጉብኝት በመቶ ሺ የሚቆጠር ሕዝብ እየወጣ ሊያያቸው ጎዳናውን ማጥለቅለቅ ጀመረ። በአሜሪካና በእንግሊዝ ዘንድ ደግሞ ክብራቸው ገዝፎ ወጣ። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በዘመነ አገዛዛቸው ኢትዮጵያ በኪነ-ጥበብ አለም፤ ኢትዮጵያ በስፖርቱ አለም፣ ኢትዮጵያ በሚሊቴሪውና በትምህርቱ አለም ቀደም ሲል ከነበረችበት ሁኔታ በእጅጉ ከፍ ከፍ ብላ የታየችበት እንደሆነ ብዙዎች ጽፈዋል።

ታዲያ ምን ያደርጋል ሁሉም ነገር እንደነበር አይሆንም። በአስተዳደር ዘመን የተፈፀሙ አንዳንድ ስህተቶች ሳይታረሙ ማደግ ጀመሩ። የታላቁ ጀግና የበላይ ዘለቀ በስቅላት መቀጣት፣ እነ ጀነራል መንግሥቱ ንዋይ እና ገርማሜ ንዋይ የሞከሩትን መፈንቅለ መንግሥት ተመርኩዞ አስተዳደራዊ ለውጥ ማምጣት አለመቻል፣ የመሬት ላራሹ ትውልድ እየገነነ መምጣት እና በ1965 ዓ.ም የተከሰተው የሰሜን ኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ ተከተለና ወትሮም ሲቀጣጠል የነበረው የለውት ፍላጎት ፍም ተከማቸ እና አብዮት ፈነደ። የነበረው እንዳልነበረ ሆነ። አብዮት ፍንዳታው በመዝሙሮች ተቀጣጠለ። መሬት ላረሹ ታወጀ። መፈክር ማሰማት የወቅቱ ፋሽን ሆኖ ብቅ አለ።

Art2መስከረም ሁለት ቀን 1967 ዓ.ም ሐሙስ ዕለት፣ ንጉሡ ፊት ቀርበው የሚያስረዱ በሻለቃ ደበላ ዲንሣ መሪነት ከመለዮ ለባሹ የተውጣጡ አባላት ተመረጡ። የተመረጠው ቡድንም ለሦስት ሰዓት ሩብ ጉዳይ ሲሆን ወደ ኢዮቤልዩ ቤተ-መንግስት አመራ። ቡድኑ ቤተ-መንግስት ደርሶበ በመኖሪያ ቤታቸው በሚገኘው ሳሎን ንጉሡ ከመኝታ ቤታቸው ተጠርተው እስኪመቱ ድረስ ሲጠባበቅ ቆየ። የንጉሡን ከሥልጣን መውረድ እማኝ እንዲሆኑ ተብለው ቀደም ሲል ተነግሯቸው የነበሩት ልኡል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴም በቦታው ተገኙ። ከዚያም ሻለቃ ደበላ ዲንሣ ሰላምታ ሰጥተው ከደርግ የተሰጣቸውን ፅሁፍ ማንበብ ጀመሩ። ጽሁፉም እንዲህ ይላል፡-

        -    ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ታሪክ ለረጅም ጊዜ የኖረውን ዘውድ ሕዝቡ በቅን ልቦና የአንድነት ምልክት ነው ብሎ የሚያምንበት ቢሆንም ከ50 ዓመት በላይ ከአልጋ ወራሽነት ጀምረው ሀገሪቱን ሲመሩ ከሕዝብ የተሰጥዎትን ክብር ሥልጣን አለአግባብ በልዩ ልዩ ጊዜ ለራስዎና በአካባቢዋ ለሚገኙት ቤተሰብዎችዎና ለግል አሽከርዎችዎ ጥቅም በማዋል ሀገሪቱን አሁን ካለችበት ችግር ላይ እንድትወድቅ ከማድረግዎም በላይ ዕድሜዎ ከ82 ዓመት በላይ በመሆኑ በአካልዎም ሆነ በአእምሮዎ በመድከምዎም ከእንግዲህ ወዲህ ይህን ከፍተኛ ኃላፊነት ሊሸከሙ አይችሉም” የሚል ፅሁፍ ሻለቃ ደበላ ዲንሣ አነበቡ።

ከዚያም ጃንሆይ እንዲህ አሉ፡-

“ያላችሁትን በጥሞና አዳምጠናችኋል። ለአገር በጎ አስባችሁ ከተነሳችሁ የአገርን ጥቅም ከራስ ጥቅም ማስቀደም አይቻልም። እኛ እስከ ዛሬ አገራችንን እና ህዝባችንን አቅማችን በፈቀደውና በምንችለው ሁሉ አገልግለናል። አሁን ተራው የኛ ነው ካላችሁ ኢትዮጵያን ጠብቁ።” (ሲሉ መለሱ)

 

በመጨረሻም ሻለቃ ደበላ ዲንሳ እንዲህ አሉ፡-

“ለግርማዊነትዎ ደህንነት ሲባል ሌላ ቦታ የተዘጋጀ ስለሆነ ወደ ተዘጋጀልዎት ስፍራ እንድንሄድ እጠይቃለሁ” በማለት የ82 ዓመት አዛውንት ንጉስ በቮልስ ዋገን መኪና ይዘው ከቤተ-መንግስት ወጡ።

እኚህ ታላቅ ንጉስ ከዚያ በኋላ በእስር ማቅቀው በአሰቃቂ ሁነታ ተገለው ተቀብረዋል። ጃንሆይ ማን ገደላቸው? ግድያው ምን ይመስል ነበር? በአልጋ ወራሽነት ኢትዮጵያን ለ14 ዓመታት ያገለገሉት፣ በንጉሠ ነገስታትነት ለ44 ዓመታት ኢትዮጵያን የመሯት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በታሪክ ውስጥ አይረሱም። 

 

የአፄ ኃይለሥላሴ ግድያ

ውድ የሰንደቅ ጋዜጣ አንባቢዎቼ፣ ለዛሬ ይዤላችሁ የቀረብኩት፤ ኢትዮጵያዊ ስንክሳር ኢትዮጵያን ለ14 ዓመታት በአልጋወራሽነት ለ44 ዓመታት በንጉሠ ነገስታትነት መርተው በኋላም መስከረም ሁለት ቀን 1967 ዓ.ም በወታደሮች መፈንቅለ መንግስት ለእስር በኋላም ለአሠቃቂ ሞት ስለተዳረጉት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ማን ገደላቸው በሚለው ርዕሠ ጉዳይ ላይ ጥቂት ቆይታ እንድናደርግ ነው።

-         -    -

      

ኢትዮጵያ እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ የምትመራው በንጉሣዊ አስተዳደር ነበር። የኢትዮጵያ ነገስታት የዘርና የደም ተዋረዳቸው የሚቆጠረው ከእስራኤሉ ንጉስ ሰለሞን ዘንድ ነበር። ይህ ሥርዓት ለ3 ሺህ ዓመታት ቀጥሎ ነበር። ነገር ግን መስከረም ሁለት ቀን 1967 ዓ.ም ይህ የታሪክ ሰንሰለት ተቆረጠ። በወቅቱ የመጨረሻው ንጉስ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በ82 ዓመታቸው መፈንቅለ መንግስት ተደርጐባቸው ከነ መላው ቤተሰቦቻቸውና ሚኒስትሮቻቸው ብሎም ከባለስልጣኖቻቸው ጋር ወደ እስር ቤት  ታጐሩ።

ለረጅም ዓመታት በአፍሪካ፣ በጥቁር ዓለምና በልዩ ልዩ ታላላቅ መንግስታት ፊት ክብር አግኝተው የነበሩት ንጉስ በሀገራቸው ልጆች አማካይነት ታሰሩ። እስር ቤት ሳሉም እጅግ ለክብራቸው በማይመጥን ሁኔታ ውስጥ ይሰቃዩ እንደነበር ታሪክ ፀሐፊዎቻቸው ያወሳሉ።

ቀጥሎም እኚህ ባለ ብዙ ዝና የነበሩ ንጉስ መገደላቸው መሞታቸው ተነገረ። በወቅቱ ጉዳዩ እጅግ አስደንጋጭ ነበር። የ82 ዓመት አዛውንትን፣ ንጉስን የሚገድለው ማን ነው? ተባለ። ጃንሆይን ማን ገደላቸው? እንዴትስ ሞቱ? ይህ ጥያቄ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲያነጋግር ቆይቷል።

በጃንሆይ የመጨረሻ የሕይወት እስትንፋስ ላይ ተመርኩዘው አያሌ ደራሲያን ልዩ ልዩ ሃሳቦችን የያዙ አመለካከቶችን ሲያንፀባርቁ ቆይተዋል። የልቦለድ ድርሰት የፃፉም ደራሲያን አሉ። አንዳንድ ደራሲያን የደርግ ሰዎች በትራስ አፍነዋቸው ነው የገደሏቸው ብለው ፅፈዋል። ሌሎች ደግሞ ግድያውን ከቀድሞው ፕሬዝደንት አሁን ሐራሬ ዚምቧቡዬ ከሚገኙት ከ/ኮል መንግስቱ ኃይለማርያም እንደፈፀሙት ወይም እንዳስፈፀሙት የፃፉ አሉ። ሌሎች ደግሞ ልቦለዳዊ ቀለም ሰጥተውት ጃንሆይ አልሞቱም ከእስር ቤቱ እንዲወጡ ተደርጓል ብለው የደህንነት መዋቅር ዘርግተው የፃፉ ደራሲያን አሉ። ከዚህ ሌላ ደግሞ በተለይ በንጉስ ኃይለሥላሴ የሚያምኑቱ ጃማይካዊያን ወይም ራስ ተፈሪያዊያን፣ ጃንሆይ አይሞቱም አርገዋል ብለው ያምናሉ። ሞታቸውን አይቀበሉትም።

እነዚህ ሁሉ አስተሳሰቦች ባሉበት ሁኔታ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ከጐንደር ጠቅላይ ግዛት የፓርላማ አባል የነበሩት የሕግ ባለሙያው አቶ በሪሁን ከበደ በ1993 ዓ.ም 1333 ገፅ ያለው፣ የአፄ ኃይለሥላሴ ታሪክ የተሰኘ ግዙፍ መፅሐፍ አሳተሙ። መፅሐፉ ስለ ንጉሡ ታሪክ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ በብዙ የታሪክ ማስረጃዎች ተሰንዶ የተዘጋጀ ነው። ታዲያ በዚህ መፅሐፍ ውስጥ የጃንሆይ አሟሟት እና አገዳደል እንዴት እንደነበር ደራሲው እማኞችን በመጥቀስ አደራጅተው ፅፈዋል።

አቶ በሪሁን ከበደ በፃፉት የአፄ ኃይለስላሴ ታሪክ የተሰኘው መፅሐፍ ውስጥ ስለ ንጉሡ ግድያ አስመልክቶ የተፃፈው የሚከተለውን ይመስላል።

Art3ጃንሆይ ከመስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ታላቁ ቤተ-መንግስት እስከተዘዋወሩበት እስከ ጥቅምት 15 ቀን 1967 ዓ.ም ድረስ ልጃቸው ልዕልት ተናኘወርቅ አብረዋቸው እንዲውሉና እንዲያድሩ ስለተፈቀደላቸው አንዲት ፍራሽ እንድትገባ ተፈቀደላቸው። ከወለል ላይ እያነጠፉ ሲተኙ ሰንብተዋል። ወደ ታላቁ ቤተ-መንግስት ተዛውረው እንዲታሰሩ ከተደረገ በኋላ ግን ልዕልቲቱ አብረው ወደዚያ እንዲሄዱ አልተፈቀደላቸውም።

ጃንሆይ ወደታሰሩበት ቤት መጥተው ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ሳይለዩዋቸው ምግባቸውን እያቀረቡ፣ አልጋቸውን እያነጠፉ፣ ልብሳቸውን እያጠቡ፣ ቤቱን እያፀዱ አብረዋቸው እያደሩ ያገለግሏቸው የነበሩ ሁለት አስገራሚ ሰዎች ነበሩ፤ እነርሱም፡- 1ኛ - ወሠኔ አማረ

                        2ኛ - እሸቱ ተክለማርያም የሚባሉ ናቸው። እነዚህ ሰዎች የጃንሆይ የእስር ቤት አገልጋዮች ነበሩ። የክፉ ቀን ተገኖች።

ታዲያ አንድ ቀን ማለትም ጃንሆይ በታሠሩ በ11 ወር ከ20 ቀን ነሐሴ 20 ቀን 1967 ዓ.ም ከምሽቱ 3 ሰዓት ሲሆን፤ 1ኛ - ኮ/ል ዳንኤል አስፋው

                          2ኛ - ኮ/ል እንዳለ ገላ

                          3ኛ - ሻለቃ የጐራው ከበደ የሚባሉ የደርግ ሰዎች መጡ።

የጃንሆይን ጠባቂዎች አልጋችሁን ይዛችሁ ውጡ አሏቸው። ጠባቂዎቹም ወደ ጃንሆይ ዘንድ ቀርበው የተነገራቸውን ትዕዛዝ ለእሳቸው ተናገሩ። ጃንሆይም የሰጧቸው መልስ፤ ቤቱ ጠቧቸው ከሆነ ወደፊት በሰፊው አሠርተን እናስረክባችኋለን ብላችሁ ንገሯቸው ካሉ በኋላ መስኮቱን ከፍተው - ጌታዬ በእውነት ኢትዮጵያን ያላገለገልኩ ከሆነ ፍርድህን ስጥ - ብለው እንባቸውን ወደ ባዕታ ቤተ-ክርስትያን ትይዩ ሆነው አፈሰሱ - በማለት ጠባቂዎቻቸው እማኝነታቸውን ሠጥተዋል።

ቀጥሎም ጠባቂዎቻቸው ከጃንሆይ ክፍል ወጡ። ከዚያም ሦስቱ የደርግ ሰዎች ጃንሆይ ወዳሉበት ክፍል ገቡ። በሩንም ዘጉት። 45 ደቂቃዎች ቆይተው ወጡ። ጠባቂዎቻቸው ወሠኔ አማረ እና እሸቱ ተ/ማርያም ከቤቱ ታዛ ተጠግተው አልጋቸውን ዘርግተው ከውጭ አድረው ነበር። ጃንሆይ ሁልግዜ በጥዋት እየተነሱ ፀሎት ማድረግ ልማዳቸው ስለሆነ እንደተለመደው በጠዋት ተነስተው ፀሎት ያደርጋሉ ብለው ቢጠብቋቸው ሳይነሱ ስለቀሩ ተጠራጥረው ደጃፉን ከፍተው ገቡ። ሲገቡ ጃንሆይ ይለብሱት በነበረው አንሶላ ተሸፍነው አገኟቸው። አንሶላውን ገልጠው ሲያዩዋቸው ሞተው አገኟቸው።

በምን አኳኋን እንደሞቱ ለማወቅ እሬሳቸውን አገላብጠው ለማየት ሲሞክሩ የነበሩትን ጠባቂዎቻቸውን የፀጥታ ሰዎች ገብተው አስወጧቸው። ከደጅ ሆነው ሲጠባበቁ ጧት አንድ ሰዓት ተኩል ሲሆን፤ መንግስቱ ኃይለማርያም እና አጥናፉ አባተ መጥተው የጃንሆይ አስክሬን ወዳለበት ክፍል ገብተው መሞታቸውን አረጋግጠው ሲወጡ፣ “ምነው አሟቸው ሰንብተው ነበር?” ብለው በማሾፍ ወሰኔ አማረ እና እሸቱ ተ/ማርያምን ጠይቀው ከነሱ የሚሰጣቸውን መልስ ሳያዳምጡ በፍጥነት ሄዱ።

የመፅሐፉ ደራሲ አቶ በሪሁን ከበደ ሲቀጥሉ እንዲህ አሉ፡-     

እነ ወሰኔ አማረ የመጨረሻውን ሁኔታ ሳናይ አንሔድም ብለው ከቤቱ ደጃፍ ላይ ተቀምጠው ዋሉ። ከቀኑ 11 ሰዓት ሲሆን እነዚያ ነሐሴ 20 ቀን 1967 ዓ.ም ማታ በሶስት ሰዓት መጥተው የነበሩት ኮ/ል ዳንኤል አስፋው፣ ኮ/ል እንዳለ ገላ፣ ሻለቃ የጎራው ከበደ ጥቂት ወታደሮች አስከትለው መጥተው አስክሬኑ ከነበረበት ቤት አውጥተው ይዘውት ሄዱ። ወሰኔ አማረና እሸቱ ተ/ማርያም የተቀበሩበትን ቦታ አላዩም ብለው ፅፈዋል።

የጃንሆይ አሟሟት በአቶ በሪሁን ከበደ ገለፃ ይህን ይመስላል። የተቀበሩበት እና የአቀባበሩ ትርኢት ደግሞ እጅግ ዘግናኝ ነው።

የደርግ መንግስት ጃንሆይን ጨምሮ 60 ታላላቅ ሚኒስትሮቻቸውን ሲገድል በሬዲዮ እንደ ታላቅ ጀብድ ተነገረ።

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ኢትዮጵያን ለ44 ዓመታት በንጉሠ ነገስትነት ሲመሩ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል። የኢጣሊያን ፋሽስቶች ከኢትዮጵያ ምድር በድል ካሸነፉ በኋላ በ1933 ዓ.ም ረጅም ንግግር አድርገዋል።

  

በጥበቡ በለጠ

 

ከበደች ተክለአብ 11 ዓመታትን በሶማሊያ እስር ቤቶች ማቅቃለች፡፡ እስር ቤቱ ወጣትነቴን በልቶታል ትላለች፡፡ ግን ከ11 አመታት እስር በኋላ ተምራ ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ገብታ ተመርቃ፣ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት እዛው ዩኒቨርሲቲው ውስጥ መምህርት ሆነች፡፡ ከአፍሪካ ዘመናዊ ሰአሊያን ምድብ ውስጥ ተቀመጠች፡፡ ድንቄዬ ጥበበኛ፡፡

 

 

ከበደች ተ/አብ የተወለደቺው እዚሁ አዲስ አበባችን በ1948 ዓ.ም ነው፡፡ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷንም የተከታተለቺው እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ በቀድሞው ልዑል ወሰን ሠገድ እና በልዑል መኰንን የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፤ ከዚያም በ1966 ዓ.ም ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር በሆነው በስነ-ጥበብ ት/ቤት የስዕል ትምህርት መማር ጀመረች፡፡ ታዲያ በዚህ ወቅት ወጣቶች በወቅቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ ስለነበራቸው እርሷም የደርግን ስርዓት በመቃወም ቀንደኛ የኢ.ህ.አ.ፓ. አባል ሆነች፡፡ በተለይ በ1967 እና 68 ዓ.ም. በቀይ ሽብር አማካይነት ግድያው በከተማው ውስጥ እያየለ መጣ፡፡ ለእርሷም ህይወት ጉዳዩ እጅግ አስጊ ሆነ፡፡ እናም አዲስ አበባን ለቃ መውጣት ግድ ሆነባት፡፡ በ1969 ዓ.ም. ከወንድሟ ጋር በመሆን ወደ ሐረር ጠፋች፡፡ እዚያም ነገሮች እጅግ መጥፎ ሁኔታ ላይ ስለነበሩ ወደ ጅቡቲ በእግሯ መጓዝ ትጀምራለች፡፡ በዚህ ወቅት ነው በህይወት ዘመኗ ሁሉ የማትረሳው ስቃይ ውስጥ የገባቺው፡፡ ከበደች ኢትዮጵያን ሊወሩ ባሰፈሰፉ የሶማሊያ ወታደሮች እጅ ወደቀች፡፡ ያቺ ለጋ ለግላጋ የ21 ዓመት ወጣት በአረመኔዎች ቁጥጥር ስር ዋለች፡፡

 

እጅግ ጨካኝ የሆኑት እነዚህ ወራሪዎች መጀመሪያ በደቡብ ሶማሊያ ወደምትገኘው እስር ቤት ወደ መንዴራ ወሰዷት፡፡ እዚያም የተወሰነ ጊዜ በስቃይ ካሳለፈች በኋላ እጅግ መከራዋ ወደበዛበት ሀዋይ እስር ቤት አዛወሯት፡፡ ወጣቷ ከበደች በርካታ ኢትዮጵያዊያን“ ኢትዮጵያዊያት የታሰሩበትን ይሄን እስር ቤት ስትቀላቀል ምድር ላይ ያለ ዘግናኝ ድርጊት ሁሉ የነበረበት እንደሆነ ታስታውሳለች፡፡ ለምሳሌ በዚህ እስር ቤት መኝታ በፈረቃ ነው፡፡ ሰው በፈለገው ጊዜ መተኛት አይችልም፡፡ ምክንያቱም እስር ቤቱ እጅግ መርዘኛ በሆኑ እባቦችና ጊንጦች እንዲሁም በሌሎች እንስሳት የተከበበ ስለሆነ አንዱ ሲተኛ ሌላው እነዚህን እንስሳት እየጠበቀ ይከላከላል፡፡ የምድር ሲኦል፡፡ እንደገና ደግሞ ሀይለኛ የምግብ እጦት ነበር፡፡ ብዙ ጓደኞቿ በምግብ እጦት አጠገቧ ወድቀዋል፡፡ ሞተዋል፡፡ ከነገ ዛሬ የእርሷም ዕጣ ፈንታ ይህ እንደሆነ ብትጠብቅም፤ ግን ደግሞ ተስፋ ታደርጋለች፡፡ አንድም ተስፋ እንኳን ባይኖር፤

 

ሰቆቃው ብዙ ነው፡፡ እስረኞች ከባድ የሥራ ጫና ይደርስባቸው ነበር፡፡ እስከ ወገባቸው ድረስ የሚውጣቸው ውሃ ውስጥ እየገቡ የሩዝ እርሻ ላይ እንዲሠሩ ይገደዳሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ምን ያህል ለሴቶች አስቸጋሪ እንደነበር ሁላችንም ልንገነዘበው እንችላለን፡፡ ብዙዎች በሽታ ላይ እየወደቁ ያልቁ ጀመር፡፡ በዚህ መሀል ከእስረኞቹ መካከል የህክምና ሙያ ያላቸው ሰው ተመረጡና እስረኞችን መንከባከብ ጀመሩ፡፡ እኚህ እስረኛ ሲስተር በላይነሽ ቦጋለ ይባላሉ፡፡ ከበደችም ምንም እንኳን ሰዓሊ ብትሆንም፤ የተማረች ስለነበረች የሲስተር በላይነሽ ረዳት ሆና ታሳሪዎችን ማገልገል ጀመረች፡፡

 

ይሄ አጋጣሚ ደግሞ አንድ ጥሩ ነገር ፈጠረላት፡፡ ለበሽተኞች መድሃኒት የሚታዘዝበት ወረቀትና ብዕር ማግኘት ቻለች፡፡ እናም በዚህ የመድሃኒት ማዘዣ ወረቀት ላይ በየጊዜው የሚመጡላትን የግጥም ሀሳቦች መፃፍ ጀመረች፡፡ ግጥሞቿ ለታሪክ እንዲኖሩ እድሉን አገኙ፡፡ እናም በርካታ ግጥሞችን እየፃፈች ለታሳሪ ጓደኞቿ ማታ ማታ ታነባለች፡፡ ህፃናት ታስተምራለች፡፡ ‹‹አይዟችሁ! ይሄ ቀን ያልፋል›› ትላለች፡፡ እንደገና ሰው ሲያልፍ ደግሞ ታያለች፡፡ ‹‹ይሄም ያልፋል›› ትላለች፡፡

 

ከበደች በዚህ የሲኦል ምሳሌ በሆነው በሀዋይ እስር ቤት 11 ዓመታት ከፍተኛ ስቃይ ደረሰባት፡፡ ግን መንፈሰ ጠንካራ ሆና ችግሮችን ሁሉ ብትቋቋምም ‹‹እስር ቤቱ የወጣትነት እድሜዬን በላው›› ትላለች፡፡

የ11 ዓመቱ መአት ሊያልቅ ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ እና የሱማሊያ መንግሥታት የምርኮኞችና የእስረኞች ልውውጥ ሊያደርጉ ሆነ፡፡ በሀዋይ እስር ቤትም ወሬው ተሰማ፡፡ እነ ከበደች አብረዋቸው ታስረው ለነበሩትና በስቃዩ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡት ጓደኞቻቸው አለቀሱ፡፡ ግን ውድ ጓዶቻችን ተረስታችሁም አትቀሩም አሉ፡፡ እናም በ1980 ዓ.ም. የመከራ ቀንበር ለ11 ዓመታት ከተሸከመቺበት ከመንዴራ እና ከሀዋይ እስር ቤት ወጥታ ወደ ትውልድ ሀገሯ መጣች፡፡ እዚህም የትግል አጋሮቿ አብዛኛዎቹ የሉም፡፡ ግማሹ ተገድሏል፤ ግማሹ ተሰዷል፤ ትውልዷ ባክኖ ቀረባት፡፡ ያ ሁሉ ወኔ የነበረው ወጣት የለም፡፡ ምን ሆኖ ይሆን አለች፡፡ ሀዋይ እስር ቤት ትውልዷን እንዳታየው፣ እንዳትቀርበው፣ እንዳታወራው እንዳትሰማው አድርጓታል፡፡ እነ እከሌ የት ሄዱ? ብዙ ጥያቄዎች መጡባት፡፡ አሳዛኝ መልሶች ስትሰማ ቆየች፡፡

 

የከበደች ህይወት ከዚህ በኋላ ምን ይሁን? ህይወት ትግል ናት፡፡ ከእስር ቤት በኋላም ትግል አለ፡፡ ኑሮ አለ፡፡ በኑሮዋ ደግሞ አንድም አስታዋሽ አጥተው በሱማሌ በረሃ ላይ እንደዋዛ ለወደቁት ወገኖቿ ሐውልት የሚሆን ነገር ማቆም አለባት፡፡ ሁለትም የነገዋ ከበደች ደግሞ ሰው መሆን አለባት፡፡ እናም በሁለቱም አቅጣጫ ተግባሯን ማከናወን ያዘች፡፡

 

የመጀመሪያ ሥራዋ አድርጋ የያዘቺው በእስር ቤት እያለች በመድሃኒት ማዘዣ ወረቀቶች ላይ የፃፈቻቸውን ግጥሞች ‹‹የት ነው?›› በሚል ርዕስ አሳትማ መፅሐፍ ማድረግን ነው፡፡ እነዚህ ግጥሞች በሙሉ የእስር ቤቱን ህይወት የሚገልፁ ከመሆናቸውም በላይ ለነዚያ ጓደኞቿ ትልቅ የማስታወሻ ሐውልቶች ሆነው አሉ፡፡ ገናም ይኖራሉ፡፡

 

 

ሁለተኛ ተግባሯ ደግሞ መጽሐፏን አሳትማ እንደጨረሰች በእስር ቤት የተበላውን የከበደችን ማንነት እንደገና መገንባት ሆነ፡፡ እናም ከስድስት ወር በኋላ ወደ ምድረ አሜሪካ ተጓዘች፡፡ እዚያም ከስነ-ጥበብ ት/ቤት ያቋረጠቺውን የወጣትነት ትምህርቷን ለመማር ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ አመለከተች፡፡ ችሎታዋ ብቁ ስለሆነ በ1983 ዓ.ም. ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ገባች፡፡ በ1985 ዓ.ም. በስቱዲዮ አርት የመጀመያ ዲግሪዋን በከፍተኛ ማዕረግ ጨረሰች፡፡ እንደገና በ1989 ዓ.ም. በረቂቅ ስነ-ጥበብ /Masters of Fine Arts/ ከዚሁ ከሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ የማስትሬት ዲግሪዋን በከፍተኛ ማዕረግ አግኝታለች፡፡ ከዚያም በአሜሪካ ሀገር ባሉት ዩኒቨርሲቲ­‹ ውስጥ ስዕልን ለማስተማር ተፈላጊ ከያኒ ሆነች፡፡ እናም በልዩ ልዩ ዩኒቨርሲቲ­‹ ውስጥ ካስተማረች በኋላ አሁን በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የስዕል ጥበብ መምህርት ናት፡፡

 

የከበደች ስዕሎች በተለይም የሰውን ልጅ የመከራ እና የስቃይ ግዞትን በማዕከላዊ ጭብጥነት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ዘ-ባር እና ሼክል የተሰኙትም ስዕሎቿ ይህን የሰው ልጅ የመከራ ቀንበር የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ይህም የሆነው ራሷ በቅርበት ካየቻቸው ሰቆቃዎች በመነሳት ነው፡፡ የስዕል ሃያሲውና የዲጂታል አርት ባለሙያው ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላም በአንድ ወቅት እንደ ባለቅኔዋ ከበደች አብስትራክት የሚባለው የረቂቅ ስዕል አሳሳል ጥበብ ላይ ያዘነበለች ቢሆንም፤ የራሷ የሆኑ ወጥ /Original/ ፍልስፍናዎች አሏት፡፡

 

የከበደች ስዕሎች ዛሬ ከአፍሪካ ሰዓሊያን ምድብ ውስጥ በመግባት ለተለያዩ ዓውደ ርዕዮች በግንባር ቀደምትነት የሚመረጡ ሆነዋል፡፡ እነዚያን የእስር ቤት ግፎች በማስታወስ ወደፊትም በሰው ልጆች ላይ እንዲህ አይነት ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ ያሳስባሉ ስራዎቿ፡፡

 

በተለይ ደግሞ የመንዴራውና የሀዋይ እስር ቤቱ ለጓደኞቿ ሞትና ግዞት መታሰቢያ እንዲሆን መጽሐፍ ጽፋ ያቆመችላቸው ሐውልት ውስጥ ያሉት ግጥሞች የሰውን ልጅ ስሜት በእንባ ያረጥቡታል፡፡ የተማሪ ቤት ጓደኛዬ ኪዳን ሙሉጌታም ስለዚህቺው ድንቅዬ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ጥናት መስራቷንም በዚሁ አጋጣሚ ላደንቅላት እወዳለሁ፡፡ ከበደች ‹‹የት ነው?›› በሚለው የግጥም መጽሐፏ ውስጥ 29 ግጥሞችን ጽፋለች፡፡

 

ይህች ድንቅዬ ኢትዮጵያዊት ከሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ በመቀጠል /University of Georgia/ በዚሁ በስዕል እውቀቷ እያስተማረች ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ኩዊንስ ቦሮው በተሰኘ ዩኒቨርሲቲ ጥበብን ጣስተምራለች፡፡ በበርካታ አውደ ርዕዮች /ኤግዚቢሽኖች/ ስዕሎቿ ተመራጭ ናቸው፡፡ ዋሽንግተን ውስጥ ያለውን የኢትዮጵያን ኤምባሲ ከታዋቂው ሰዓሊ ከእስክንድር ቦጐሲያን ጋር ሆነው የአልሙኒየም ቅርፅ ሥራውን የሠሩት አብረው ነበር፡፡ ከበደች ‹‹እስክንድር ቦጐሲያን በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ መምህሬ ነበር፡፡ ከዚያም በዚሁ በስዕል ጥበብ ጓደኛሞች ነበርን፡፡ እስክንድር ጥበብን የሚፈልግበትን፣ የሚያይበትን ዓይኑን ሰጥቶኛል፡፡ እኔም የሱን ሥራ ሳይሆን የምኮርጀው፣ ጥበብ እንዴት መታየት እንዳለባት ነው ከሱ የወሰድኩት›› በማለት እውነተኛ የእስክንድር ተማሪ መሆኗን ትናገራለች፡፡ በምድረ አሜሪካ ያሉ ሀያሲዎች ‹‹ለአፍሪካ ሴቶች በጽናቷ እና በጥንካሬዋ አርዓያ ናት›› ይሏታል ከበደችን፡፡ አንድ ቀን ደግሞ ወይ ባህል ሚኒስቴር፣ ወይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ወይ የጀርመን ባህል ተቋም፣ ወይ የሴቶች ማህበራት ወይ ሌላ ተቋም ጋብዘዋት ሀገሯ መጥታ እናወራት ይሆናል፡፡ መልካሙን ሁሉ ለእርሷ እና ለምትወዳት ኢትዮጵያ፡፡          

Page 2 of 19

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us