You are here:መነሻ ገፅ»ኪነ-ጥበብ
ኪነ-ጥበብ

ኪነ-ጥበብ (262)

 

በጥበቡ በለጠ

ሕፃኑ ሰኔ 12 ቀን 1916 ዓ.ም ባሌ ክፍለ ሀገር ከዱ በሚባል ሥፍራ ከአቶ ሳህሉ ኤጄርሳና ከወ/ሮ የወንዥ ወርቅ በለጠ ተወለደ።

አምስት ዓመት ሲሞላው ትምህርት ይማር ዘንድ አባቱ ወደ ጎባ ይዘውት ሄዱ። ቤተሰቦቹ በሥራ ምክንያት አንድ ቦታ የሚቀመጡ አልነበሩምና መንገዳቸውን ጊኒር ወደ ሚባል ቦታ አደረጉ። እዚህም ብዙ አልቆዩም። ወደ ጎሮ፣ በመቀጠልም ወደ አርከሌ፣ ከዚህ ተመልሰው ደግሞ ሐረር ገቡ። ከቤተሰቡ ጋር ከአካባቢ አካባቢ ሲንከራተት የነበረው ህፃን ትንሽ ፋታ ያገኘው ሐረር ከገባ በኋላ ነበር። ትምህርት ቤት ገብቶ አልፋ ቤት እንዲቆጥር ተደረገ። የሚማረው በፈረንሳይኛ ቋንቋ ነበር።

  ወላጅ አባቱ አሥራ አራት ዓመት ሲሞላው አቶ መንበረ ወርቅ ኃይሉ ለተባሉ ግለሰብ በአደራ ሰጡት። ታዳጊው የወላጆቹን ቤትና ፊደል የቆጠረበትን ቀዬ ለቅቆ ወደ አዲስ አበባ መጣ። አዲስ አበባ መጥቶ ቀበና አካባቢ ከሚገኘው ኮከበ ጽባህ ት/ቤት ገብቶ ትምህርቱን እንደቀጠለ ብዙም ሳይቆይ የማይጨው ጦርነት ኦጋዴን ላይ ተቀሰቀሰ።

የታዳጊው ተስፋ የጨለመው ይሄኔ ነበር። ቤተሰቦቹ የሚኖሩት ሐረርና ባሌ በመሆኑ አጎቶቹና አጠቃላይ ዘመዶቹ ሳይቀሩ ወደ ኦጋዴን ለጦርነት ዘመቱ። ከታዳጊው ዘመዶች መካከል ግን ከጦርነቱ የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም። ሁሉንም የማይጨው እሳት በላቸው። ታዳጊው በየዕለቱ የሚመጣበትን መርዶ እየሠማ እህህ ማለት ሥራው ሆነ። ይባስ ብሎ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ከአባቱ በአደራ የተቀበሉት ብቸኛ አሳዳጊው አቶ መንበረ ወርቅ ኃይሉ አዲስ አበባ ላይ በጣሊያንያውያን በስቅላት ተቀጡ።”

ታዳጊው ብላቴናም ማንም በማያውቀው ከተማ ልቡ በከፋ ሀዘን እንደተሰበረ ብቻውን ቀረ። ምንም እንኳ ታዳጊው በዚህ ቁጭት ከጠላት ጋር ለመፋለም ልቡ ክፉኛ ቢነሳሳም በበረታ የእግር ሕመም ሳቢያ ሐሳቡን እውን ማድረግ አልተቻለውም። እንደውም የእግር ሕመሙ ስለጠናበት ለሕክምና ወደ ሆስፒታል መሄድ ግድ ሆነበት።

ሆስፒታል ውስጥ እንዳለም ኑሮን ለማሸነፍ፣ እህል ቀምሶ ለማደር የሐኪም ቤቱ ኀላፊ የሆነውን ጣሊያናዊ ጫማ ይጠርግ ነበር። ሕክምናውን እየጨረሰ ሲመጣ ከጣሊያናዊው ጋር በመግባባት እግረ መንገዱን መርፌ መቀቀል፣ ቢሮ ማፅዳት የመሳሰሉ ሥራዎችን ይሠራ ነበር። በኋላም ክትባት እስከ መከተብ ደርሶ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ፈረንሳይኛ ቋንቋ በመቻሉ የጣሊያንኛን ቋንቋን ለመልመድ ብዙም ጊዜ ስላልወሰደበት ለሕክምና ለሚመጡ ሰዎች በአስተርጓሚነት ያገለግልም ነበር።

ወጣቱ ሆስፒታል ብዙ አልቆየም። አንድ ጣሊያናዊ አትክልት ተራ አካባቢ ክሊኒክ ሲከፍት ይዞት ሄደ። ሆስፒታል ሳለ የተማረውን የሕክምና ሙያ ከቀጣሪው ጋር በመሆን መሥራቱን ተያያዘው።

ጣሊያናዊው ወደ አገሩ ሲሄድ ክሊኒኩ ውስጥ ይታከም የነበረ ሌላ ጣሊያኒያዊ ከአትክልት ተራ አለፍ ብሎ “ሎምባርዲያ” የሚባል ሆቴል ውስጥ በቦይነት ቀጠረው። እግረ መንገዱንም የመስተንግዶ ሙያ አሰለጠነው። ይህ ጣሊያንያዊም ብዙ አልቆየም፤ ስለታመመ ወደ አገሩ ተመለሰ።

የወጣቱ እንግልት በዚህ አልተቋጨም። ጣሊንያዊው ወደ አገሩ ከመሄዱ በፊት በያኔው መጠሪያው እቴጌ ሆቴል አስቀጠረው።

ይህ ታሪክ ከተፈፀመ 60 ዓመት እላፊ ሆኖታል። በእንዲህ ዓይነት የህይወት ውጣ ውረድ ያለፈው ሰው ግን ዛሬም አለ።

“የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች እንደምን ናችሁ ልጆች!”በማለት ለአርባ ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ተረት በመተረት ብዙ ኢትዮጵያውያንን በመምከር ያሳደጉት አባባ ተስፋዬ ከላይ የተጠቀሰው ታሪክ ባለቤት ናቸው። ታሪካቸውን ከእቴጌ ሆቴል በመለጠቅ እንዲህ ይተርካሉ፤

“ሆቴሉን ይመራ የነበረው ጣሊያኒያዊ ስልጡን በመሆኔና የወሰደኝ ጣሊያኒያዊ አደራ ስላለበት በጣም ይወደኝ ነበር። በዚህ ምክንያት የሆቴሉ የምግብ ክፍል ረዳት ኀላፊ አደረገኝ።”

አባባ ተስፋዬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዘመናዊ ሙዚቃ ጋር የተዋወቁት እዚህ ሆቴል ውስጥ እንደነበር ሲናገሩ፣ “ሙዚቃ ስለምወድ ክራር እና ማሲንቆ እጫወት ነበር። ሆቴሉ ውስጥ ያገኘሁትን ፒያኖ እየነካካሁ ጥሩ ፒያኖ ተጫዋች ሆንኩ” ብለዋል።

“አንድ ጊዜ ከጣሊያን አርቲስቶች መጥተው ያረፉት እቴጌ ሆቴል ነበር። ትርዒቱን ያቀርቡ የነበረው ሲኒማ ኢትዮጵያ አዳራሽ ስለነበር ቀን ቀን የሚበሉትንና የሚጠጡትን ይዤላቸው ስሄድ የሚሠሩትን በደንብ እመለከት ነበር። ትንሽ ቆይቼ እነሱ ሲሉ የነበሩትን መልሼ እልላቸው ስለነበር ይገረሙና፣ ‹ይሄ ጠቋራ እንዴት ነው የኔን ቃል የሚጫወተው የኔን ቃል እንዴት ነው የሚናገረው› ይሉ ነበር።”

ይሁን እንጂ የሆቴሉ ሥራና ኑሮ ያን ያህል የተመቻቸው አልነበረም። እንደውም ከእሳቸው በሥልጣን ከፍ ካለው ጣልያንያዊ ጋር እንደማይግባቡ ያስታውሳሉ፤

 “ከኔ በላይ ያለው ጣሊያኒያዊ ኀላፊ ጥቁር በመሆኔ አይወደኝም ነበር። አንድ ቀን አምሽቼ ወደ ሥራ ገባሁ። ሰሃንና ጭልፋ ይዤ ወደ ምግብ ማብሰያው ስሄድ ያ የማይወደኝ ጣሊያንያዊ፣ ‹እስካሁን የት ቆይተህ ነው አሁን የምትመጣው› ብሎ በቃሪያ ጥፊ መታኝ። ሰሃኑን አስቀመጥኩትና በጭልፋው ግንባሩን አልኩት። የሆቴሉ ኀላፊ ጩኸት ሰምቶ መጥቶ ሲያይ ሰውየው ደምቷል።”

የአባባ ተስፋዬና የጣሊያንያዊው አለቃቸው ግብግብ በዚህ አልተጠናቀቀም። እንደውም ከአዲስ አበባ ለቅቀው ወደ ሐረር እንዲሄዱ ምክንያት ሆነ። ሌላ መከራ፣ ሌላ ጭንቀት።

“የሆቴሉ ኀላፊ ‹ማነው እንዲህ ያደረገው ብሎ ሲጠይቅ እኔ መሆኔ ተነገረው። አንጠልጥሎ በርሜል ውስጥ ከተተኝና እንዳልወጣ አስጠንቅቆኝ ሄደ። ፖሊስ ሁኔታውን ሰምቶ ሊይዘኝ ሲመጣ አላገኘኝም። ከለሊቱ ስድስት ሰዓት ሲሆን ጣሊያኑ መጥቶ አወጣኝና የሚስቱን ካፖርት አልብሶ ወደ ቤቴ ወሰደኝ። ‹ነገ በጠዋት ባቡር ጣቢያ እንገናኝ› ብሎኝ ሄደ። በማግስቱ ባቡር ጣቢያ ስደርስ ጣሊያኑ በካልቾ ብሎ ለሌላ የምግብ ቤት ኀላፊ ለነበረ ጣሊያንያዊ አስረከበኝ።”

አባባ ተስፋዬ ከአለቃቸው ጋር በተጣሉ በሁለተኛው ቀን በባቡር ድሬዳዋ ተወሰዱ። ድሬደዋም ሲደርሱ ቀጥታ ያመሩት ወደ ሐረር ነበር። ሐረር ሲደርሱ ግን ዘመድ አልባ አልሆኑም። ከአንዲት አክስታቸው ጋር ተገናኙ። ይህ ለዘመድ አልባው ተስፋዬ ደስ ያሰኘ አጋጣሚ ነበር።

“ድሬደዋ ስደርስ ሐረር በሚሄድ አብቶብስ ከዕቃ ጋር ተጭኜ ሄድኩ። ውስጥ እንዳልገባ የተፈቀደው ለጣሊያኖች ብቻ ነበር። ሐረር ስደርስ አክስት ስለነበሩኝ እያጠያየኩ ሄድኩ። አክስቴ ሲያዩኝ አለቀሱ። ‹እኛ እኮ ሞተሃል ብለን ነበር› አሉና አዘኑ።”

አባባ ተስፋዬ ምንም እንኳ አክስታቸውን አግኝተው ደስ ቢሰኙም የመሥራት ፍላጎትና አቅም ነበራቸውና ያለ ሥራ ቁጭ ማለትን አልፈቀዱም። በማግስቱ ጠዋት ሐረር ወዳለው እቴጌ ሆቴል ቅርንጫፍ ሄዱ። “ኀላፊው ጀርመናዊ ነበር።” ይላሉ አባባ ተስፋዬ ያንን አጋጣሚ ሲያስታውሱ፤

“ኀላፊው ጀርመናዊ ነበር። አዲስ አበባ እቴጌ ሆቴል በቦይነት መሥራቴን ስነግረው ‹በኋላ ተመልሰህ ና!› አለኝ። አዲስ አበባ ስልክ ደውሎ መሥራቴን አረጋግጦ ጠበቀኝና ከሰዓት ስመለስ ቀጠረኝ።”

ሥራ እንደጀመሩ ትንሽ ቆይቶ ጣሊያን ተሸንፎ ኢትዮጵያን ለቆ ወጣ። “ሆቴሉን ልዑል መኮንን ገዙትና ‹ራስ ሆቴል› አሉት።” የሚሉት አባባ ተስፋዬ በሆቴሉ የምግብ ቤቱ ኃላፊ ሆነው እንደተሾሙ ይናገራሉ። በመቀጠልም፣ “መኳንንቱ ወደ ሆቴሉ ለእረፍት ሲመጡ ፒያኖ እየተጫወትኩ አዝናናቸው ነበር።” ይላሉ።

“ጃንሆይ ለጦርነቱ ድጋፍ ላደረጉ የደቡብ አፍሪካ ወታደሮች ጅጅጋ ላይ መሬት ሰጥተዋቸው ስለነበር ይህን አስመልክቶ በእቴጌ ሆቴል የእራት ግብዣ ተዘጋጀ። በግብዣው ላይ የእንግሊዝና የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ መዝሙር ማርሽ ተመታ። የኛ ይቀጥላል ብዬ ስጠብቅ የለም። ንድድ አለኝና ለጄኔራል አብይ ፒያኖ መጫወት እንደምችልና የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙርን እንድጫወት ጠየቅሁኝ። ስለተፈቀደልኝም በዚያ ወቅት የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር መታሁ። ያኔ ሁሉም ብድግ ብለው ሠላምታ ሰጡ።”

በ1934 ዓ.ም በጦርነቱ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆች ይሰብሰቡ የሚል ትዕዛዝ ከመንግስት ተላለፈ። ይህን የመንግስት ትዕዛዝ የሰሙት አባባ ተስፋዬ ከሐረር ተመልሰው አዲስ አበባ እንደመጡ ይናገራሉ። ይሄኔ ነው ወደ ኪነ ጥበቡ ዓለም ጥቅልል ብለው የመግባት ዕድሉ የገጠማቸው።

በ1934 ዓ.ም ግድም ዕጓለ ማውታን ተሰባስበው በሚያድጉበት ት/ቤት ገብተው መማር ቀጠሉ። በ1937 የማዘጋጃ ቴአትር ቤት የቴአትር ፍላጎት ያላቸውን ሲያሰባስብ ሸላይ፣ ፎካሪና ተዋናይነታቸውን የሚያውቁና የሚያደንቁ ባለሥልጣኖች ላኳቸው። ማዘጋጃ ቤት ገብተው ለ11 ወራት ያህል ሙዚቃ፣ የቀለም ትምህርት፣ ፈረንሳይኛና እንግሊዘኛ በነፃ ተማሩ። ለሚቀጥሉት 11 ወራት ያህል ደግሞ በወር 11 ብር እንደ ደመወዝ ይከፈላቸው ነበር። ይሀ እንግዲህ ወደ 1939 ግድም ሲሆን ከትምህርቱ ጋር ምግብ፣ ልብስና መኝታ ተሰጥቷቸዋል። መኝታው ባዶ ፍራሽ ነበር።

ይህ ወቅት እነ ግርማቸው ተ/ሐዋርያት ብቅ ብቅ ያሉበት ጊዜ በመሆኑ በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ወቅት ነበር። ይሄኔ አባባ ተስፋዬ ወደ ቴአትሩ መድረክ ብቅ አሉ። በጊዜው ሴት ተዋንያት የሌሉ በመሆኑ ብዙ ቴአትር ላይ የሴት ገፀ ባሕርይን ተላብሰው የሚጫወቱት ወንዶች ነበሩ። ከነዚህ ወንዶች መካከል ደግሞ አባባ ተስፋዬ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ፤

 “የአቶ አፈወርቅ አዳፍሬ ቴአትር ወጣ። አርእስቱን አላስታውሰውም። ብቻ “የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የሚል ነገር አለው። በቴአትሩ ውስጥ ሴት ገፀ ባሕርይ ስለነበረች እንደ ሴቷ ሆኜ የተጫወትኩት እኔ ነኝ። ብዙ ቴአትሮች ላይ ለምሳሌ ‹ጎንደሬው ገ/ማርያም›፣ ‹ቴዎድሮስ›፣ (የግርማቸው ተ/ሐዋርያት) ‹ንፁ ደም›፣ ‹አፋጀሽኝ›፣ ‹መቀነቷን ትፍታ›፣ ‹ጠላ ሻጯ›፣ ‹የጠጅ ቤት አሳላፊ›… በመሳሰሉት ቴአትሮች ላይ ሴት ሆኜ ሠርቻለሁ። ይህም የሆነበት ምክንያት በዚያ ዘመን ሴት ተዋንያን ስላልነበሩ ነው።”

አባባ ተስፋዬ ሴት ሆነው ሲጫወቱ ሜካፑን ( ) የሚሠሩት እራሳቸው ነበሩ። መድረክ ላይ ወጥተው ሲተውኑ ፍፁም ሰው እንደማያውቃቸው እንዲህ በማለት ይናገራሉ፤

“እኔም የሴቶቹን አባባል፣ አረማመድ፣ አነጋገር ሁሉ ስለማውቅ እነሱኑ መስዬ እጫወት ነበር። ተደራሲያኑ ሴት የለም ብለው እንዳይመለሱ ሴት አለ ብለን እንዋሽና እኔ እሠራው ነበር። ብዙ ጊዜ እንደ ሴት ሆኜ ስሠራ ካዩኝ ተመልካከቾች መካከል ለትዳር የተመኙኝ ነበሩ።” 

 አባባ ተስፋዬ ሴት ገፀ ባሕርያትን ተላብሰው የተጫወቱት ለአራት ዓመታት ያህል ነው። ከአራት ዓመታት በኋላ ግን ‹ሰላማዊት ገ/ሥላሴ› የተባለች አርቲስት በመምጣቷ ወንድ ገፀ ባሕርይን ተላብሰው መተወኑን እንደቀጠሉበት ተናግረዋል።

የአባባ ተስፋዬ የቴአትር ሥራ በአገር ውስጥ ብቻ የተገደበ አልነበረም። ወደ ኮርያ ድረስ ሄደው ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን አርበኞችን በፉከራና በሽለላ ይቀሰቅሱ፣ ቴአትርም እየሠሩ ያዝናኑ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዛ በኮሪያ ቆይታቸውም የሃምሳ አለቅነትን ማዕረግ እንዳገኙ ዛሬም ድረስ የሚያነሱት አጋጣሚ ነው። 

በቴአትር ትወና ብቃታቸውና በሙዚቃ ችሎታቸው የወቅቱ ባለስልጣናት በእጅጉ ይገረሙ ነበርና ወደ ጃፓን ሄደው የጃፓንን ቴአትር ቤቶች እንዲመለከቱ ልከዋቸው ነበር። ከሦስት ወራት ቆይታ በኋላም ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ በሳቸው የህይወት ታሪክ ዙሪያ የተጻፉ ጽሑፎች ይናገራሉ። 

ብሔራዊ ቴአትር በ1948 ዓ.ም ሲከፈት በማዘጋጃ ቤት አብረዋቸው ይሠሩ ከነበሩ ተዋንያን ጋር ወደ ብሔራዊ ቴአትር ተሸጋግረዋል። “ፀጋዬ ኀይሉ” የተባሉ ጸሐፊ በጥር ወር 1979 ዓ.ም በታተመው የካቲት መጽሔት ላይ “አባባ ተስፋዬ በብሔራዊ ቴአትር ከተቀጠሩ ዕለት እስከ ጡረታ መውጫቸው ድረስ በተሠሩ ተውኔቶች በሁሉም ላይ ተካፍለዋል ማለት ይቻላል። በቴአትር ቤቱ አንድ ቴአትር ከተዘጋጀ በዚያ ቴአትር ውስጥ ተስፋዬ መኖራቸውን የሚጠራጠር ተመልካች አልነበረም” ሲሉ የአባባ ተስፋዬን የብሔራዊ ቴአትር የሥራ ዘመን ቆይታቸውን ገልፀውታል።

አባባ ተስፋዬ በብሔራዊ ቴአትር ቆይታቸው ከሰባ በላይ ቴአትሮች ላይ የተሳተፉ ከመሆናቸውም በላይ፣ “ብጥልህሳ? ነው ለካ?” እና “ጠላ ሻጭዋ” የተባሉ ተውኔቶችን ጽፈዋል።

“በቴአትር ቤት ቆይታዬ ለሰዎች የሚያስቸግር ቴአትርን እኔ ነበርኩ የምሠራው። የአሮጊት ጠጅ ሻጭ ሆኜ፣ ሌባ፣ ሰካራም ሆኜ እሠራ ነበር። አንድ ቴአትር ላይ አጫዋች፣ ባለሟል፣ ድንክ ሆኜ ሠርቻለሁ።”

በተዋጣ ተዋናይነቱ በሕዝብ ዘንድ የሚታወቀው አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ ስለ አባባ ተስፋዬ የትወና ብቃት ሲናገር፣ “ጋሽ ተስፋዬ ትራጀዲም ኮሜዲም መጫወት ይችላል። ኮሜዲ በሚጫወትበት ጊዜ ዋና ችሎታው የገፀ ባሕሪውን (የድርሰተ ሰቡን) ደም፣ ሥጋና አጥንት ወስዶ የራሱ ያደርገዋል። ይላበሰዋል። በዚህም የደራሲውን ሥራ አጉልቶ ያወጣዋል።” ብሎ ነበር፤

በእርግጥም አባባ ተስፋዬ “ሁሉንም አይነት የቴአትር ዘርፎች ስጫወት (ኮሜዲ፣ ትራጀዲ…) ይሳካልኝ ነበር” በማለት የወጋሁ ንጋቱን አስተያየት ያጠናክራሉ። ፍፁም የተሰጣቸውን ገፀ ባሕርይ ተላብሰው እንደሚጫወቱም ስለራሳቸው ይመሰክራሉ።

“‹ኦቴሎ›፣ ‹የከርሞ ሰው›፣ ‹አስቀያሚ ልጃገረድ› ግሩም ነበር። በተለይ ‹ኦቴሎ› ውስጥ ኢያጎን ሆኜ ስጫወት ብዙ ነገር ደርሶብኛል። ብዙ ሰዎች ጠልተውኝ ነበር። መኳንንቱ ሳይቀሩ ‹የታለ ያ ሰው ያስገደለ› እያሉ ያስፈልጉኝ ነበር። ባልና ሚስት በመኪና እኔን ለመውሰድ ተጠይፈውኝ ሁሉ ነበር። በመንገድ ሳልፍ ወይም አብቶብስ ስጠብቅ፣ ‹እዩት ይሄ እርጉም መጣ!› እያሉ ይሰድቡኛል፤ ይሸሹኝማል።”

አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ አባባ ተስፋዬን የሚያውቋቸው ከዛሬ ሀምሳ ዓመት በፊት ነው። ብዙ ቴአትሮች ላይም አብረው ተውነዋል። ስለአባባ ተስፋዬ የሚሉት ነገር አለ፤

“ተስፋዬ ሳህሉን ከ1944 ዓ.ም ጀምሮ አውቀዋለሁ። ባለ ብዙ የሙያ ባለቤት ነው። ቢያንስ ቢያንስ ከሰባ በላይ የሚሆኑ ቴአትሮች ላይ ሠርቷል። ‹ስነ ስቅለት› ላይ ጲላጦስን ሆኖ ሲሠራ እንደ ተዓምር ነው የተቆጠረለት። ‹ዳዊትና ኦሪዮን› ላይም ተጫውቷል። ባላምባራስ አሸብር ገ/ሕይወት የጻፉት ‹የንግስት አዜብ ጉዞ ወደ ሰለሞን› የሚለው ቴአትር ላይ አሣ አጥማጅ ሆኖ ሠርቷል። ብሄራዊ ቴአትር ከመጡት ጀርመኖች ጋር እስክንለያይ ድረስ ‹ፊሸር› እያሉ ነበር የሚጠሩት። ‹ኦቴሎ› ላይ ኢያጎን ሆኖ ሲሠራ ብዙ ተመልካቾች፣ ‹ክፋቱንና ጭካኔውን በድምፁ ብቻ ሳይሆን በዓይኑም ጭምር ተናገረለት› ብለው የመሰከሩለት ነው። ፀጋዬ ገ/መድኅንም በጣም አድንቆታል።”

አባባ ተስፋዬ ከሚሠሯቸው ቴአትሮች በተጨማሪ በተለያዩ መድረኮችና በቴሌቪዥን በሚያቀርቧቸው የምትሃት (የማጂክ) ትርዒቶች ይታወቃሉ። ስለምትሃት ችሎታቸው የሚከተለውን ይላሉ፤

“ምትሃቱን ያሰለጠነኝ በጃንሆይ ፈቃድ አንድ እሥራኤላዊ ነው። ኮሪያም አይቼ ስለነበር ትንሽ ትንሽ እችል ነበር። ያንን ሳሳየው ደስ ብሎት አስተማረኝ። በጅምናስቲክ የሚሠሩትን በገመድ ላይ መሄድ፣ አክሮባት አሰለጠነን። ስመረቅ ጃንሆይ ሽልማት ሲሰጡኝ፣ ‹አስተምርበት እንጂ እንዳታታልልበት!› አሉኝ”

“ይሁን እንጂ በዚህ ጥበቤ ያተረፍኩት አድናቆትንና ከበሬታን ሳይሆን በሰዎች ዘንድ መጠላትን ነው” የሚሉት አባባ ተስፋዬ “ሰዉ እውቀት ስለማይመስለው አስማተኛው በማለት ይጠላኝ ነበር።” ሲሉ በሐሳብ ወደ ኋላ ሄደው ያስታውሳሉ።

ከቴአትር ሙያቸው በመለጠቅ አባባ ተስፋዬ በብዙሃኑ የሚታወቁት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን፣ በልጆች ፕሮግራም ላይ በሚያቀርቡት አስተማሪ፣ መካሪና አዝናኝ በሆኑት ተረቶቻቸው ነው። ለ42 ዓመታት በዚህ ፕሮግራም ላይ ያገለገሉት አባባ ተስፋዬ በፕሮግራሙም ብዙ ኢትዮጵያውያን ልጆችን እንዳሳደጉበት ይናገራሉ። ለመሆኑ ወደ እዚህስ ሙያ እንዴት ገቡ!? አባባ ተስፋዬ የሚሉት አላቸው፤

“በ1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲቋቋም ሁሉ ነገር ተዘጋጀ። ኮንትራቱን የያዘው አንድ እንግሊዛዊ ነበር። ያኔ የልጆች ፕሮግራም አልነበረምና ሄጄ ለሳሙኤል ፈረንጅ ነገርኳቸው። ‹አይ ያንተ ነገር!› አሉና እውነትም ኮንትራቱን ሲያዩት የለም። ፈረንጁን ሲጠይቁት ‹ሰው አላችሁ ወይ?› አለ። እኔ እንድሠራ ሳሙኤል ፈረንጁን ጠቆሙት። እስኪ ግባና አሳየኝ ሲል የነበረኝን አስቂኝ ማስክ ይዤ ወጥቼ ያን አጥልቄ አሳየሁት። ባሳየሁት ነገር ተገረመና፣ ‹አንተ እዚህ ምን ትሠራለህ?› አለኝ። ‹አገሬን ስለምወድ ውጪ ወጥቼ መቅረት አልፈልግም። የአገሬ ሰው መቼ ጠገበኝና እንዲህ ትለኛለህ?› አልኩት። ኅዳር 1 ቀን 1957 ዓ.ም ‹ጤና ይስጥልኝ ልጆች የዛሬ አበባዎች!› ብዬ በቴሌቪዥን ቀረብኩ።”

“ለልጅ ልዩ ፍቅር አለኝ። መንገድ ላይ እንኳ መክሬ ተቆጥቼ ነው የማልፈው።” የሚሉት አባባ ተስፋዬ ፕሮግራማቸውን ወላጆች ሳይቀሩ እንደሚወዱት ይናገራሉ።

“በየአጋጣሚው፣ ‹እኛ በእርስዎ ምክር አድገን፣ ልጆቻችንንም በእርስዎ ምክር አሳድገናል› የሚሉኝ ብዙ ናቸው። ልጅ በልጅነቱ ነው መመከር ያለበት ያሉኝ ነገር ከአእምሮዬ አይወጣም።”

አባባ ተስፋዬ ሥራቸው ያስገኘላቸው የሕዝብ ፍቅር እንጂ የገንዘብ ሀብት እንዳልሆነ ደጋግመው የሚናገሩት ነው፤

“ቴሌቪዥን ስገባ መጀመሪያ እንግሊዙ ጥሩ ገንዘብ ይከፍለኝ ነበረ (በወር 175 ብር ነበር የሚከፍለኝ)። በኋላ ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት ‹ተስፋዬ አሄሄሄ ወፍ እንዳገሯ ነው የምትጮኸው፤ …እንደ ፈረንጅ አይደለም የምንከፍልህ፤ ሰባ ብር ይበቃሃል› አሉኝ። በፕሮግራም ስለሆነ ጥሩ ነበር። ያም በኋላ ደርግ ሲመጣ 50 ብር አደረጋት። እሱም ጥሩ ነበረ። ግን ሲሄድ ሃያ አምስት ብር አድርጓት ሄደ። አሁን ባሉትም ሃያ አምስት ብር ነው። ሃያ አምስት ብሯንም ቅር አላለኝም። እኔ ልጆች አእምሮ ውስጥ እንድገባ ነው የምፈልገው። ሕግ እንዲማሩ፣ ሲያድጉ እንዳያጠፉ፣ ጎበዝ ተማሪ እንዲሆኑ ነበር የምፈልገው፡ ተረቶቼ ስነ ምግባርን ነበር የሚያስተምሩት።”

አባባ ተስፋዬ ለረዥም ዓመታት በቴሌቭዥን ለልጆች ተረትን ከመተረታቸው በተጨማሪ በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋፅዎ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በዛ ያሉ የምስክር ወረቀቶችና ሽልማቶችን ተቀብለዋል። ከነዚህ መካከል የኢትዮጵያ የኪነ ጥበባትና የመገናኛ ብዙኀን ሽልማት ድርጅት በቴአትር ዘርፍ በተዋናይነት የ1991 ዓ.ም የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ያደረጋቸው በዋናነት የሚጠቀስ ነው።

አባባ ተስፋዬ ከኪነ ጥበብ ሥራ ጋር በተያዘ  ግብፅ፣ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ሱዳን እና ሌሎችም አገሮች ደርሰው መጥተዋል።

“ከውጪ ስመጣ ሁሉ ጊዜ ለቅሶ ይይዘኛል።” የሚሉት አባባ ተስፋዬ ከኮርያ እስከ ጃፓንና ጀርመን ድረስ ሄደው ሲመለሱ በእጅጉ የሚያሳስባቸው ያገራቸው አለማደግ እንደሆነ ይናገራሉ፤

“መቼ ነው አገሬ አድጋ የማያት፣ ከሣር ቤት የምንወጣው መቼ ነው። እያልኩ እፀፀታለሁ። ቤቶቹ በቆርቆሮ ሲተኩ ደግሞ መቼ ነው መንገድ የሚሠራው ስርዓት የምንማረው መቼ ነው የሚለው ይቆጨኝ ነበር። በፊት አገሬ መንገድ ስለሌላት በጣም እናደድ ነበር። አሁን ግን እየተሠራ በመሆኑ ደስ እያለኝ ነው። ምነው የኔንም ቤት አፍርሰው መንገድ በሠሩ እላለሁ።”

አባባ ተስፋዬ ለሕፃናት የሚሆኑ አራት የተረት መጽሐፍትን ጽፈዋል። ከመድረክ ላይ የተቀዱ ሁለት ካሴት አላቸው። “ከብሔራዊ ቴአትር ጡረታ ከወጣሁ 24 ዓመት ሆኖኛል።” የሚሉት አባባ ተስፋዬ “አራት የተረት መጽሐፌን፣ ቲሸርቴንና ካሴቴን ትላልቅ ሱቅና ቡና ቤት መንገድ ላይ እያዞርኩ በመሸጥ ራሴን እደጉማለሁ” ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪ አባባ ተስፋዬ ከብሔራዊ ቴአትር በጡረታ  300 ብር ያገኛሉ።

“የወለድኳቸው ሁለት ልጆች ቢሆኑም አንዱ ልጄ ሞቷል።” በማለት የሚናገሩት አባባ ተስፋዬ ከቤተሰባቸው ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ይገልፃሉ። ከአምስት የልጃቸው ልጆችና አራት የእህታቸው የልጅ ልጆች ጋር እህታቸውን ጨምሮ 14 ቤተሰብ አብረው እንደሚኖሩም አያይዘው ገልፀዋል።

ባለቤታቸውም ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየታቸው በፊት በሥራቸው ላይ ያሳድሩት የነበረውን አዎንታዊ ተፅእኖ የሚገልፁት እንዲህ በማለት ነበር፤

 “ባለቤቴ ሥራዬን ትወድልኝ ነበር። በርታ ትለኝ ነበር። ስበሳጭ ስናደድ ለእርሷ ነበር የምነግራት። ‹ግዴለም ተስፋ ቻለውና አሳልፈው› ትለኝ ነበር። ከ 48 ዓመት የትዳር ህይወት በኋላ የዛሬ ሦስት ዓመት ሞታብኛለች።”

አንዱ ልጃቸው ትንሽ ሆኖ ቴአትር እንደሠራ የሚያስታውሱት አባባ ተስፋዬ ኮንጎ ይኖር የነበረው ትልቁ ልጃቸው ሙዚቃ መጫወት ይችል እንደነበር ገልፀዋል። የልጃቸው ልጅ ከአባቱ ጋር ሆኖ የሙዚቃ ክሊፕ ቤታቸው ውስጥ ባለው ስቱድዮ እየሠራ ሲሆን፣ እርሳቸውም በዋና ገፀ ባህርይነት የሚተውኑበት ፊልም ለመሥራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አቶ ተፈራ ተስፋዬ  ይባላሉ። የአባባ ተስፋዬ ሁለተኛ ልጅ ናቸው። “የአራት ዓመት ልጅ ካለሁበት ጊዜ አንስቶ እስከ 1970ዎቹ ድረስ አብሬ እየሄድኩ ቴአትር እመለከት ነበር።” የሚሉት አቶ ተፈራ፣ “ቤት ውስጥ ሲለማመድ አይ ነበር። ግን ምንም አልረዳውም ነበር። ትምህርቴ ላይ ነበር የማተኩረው። ሌላው ዘመኑ ነው መሰለኝ በጣም ስለምናከብረው አንቀራረብም። ግን ምግብ እየተበላ ዝም ብለን እየተጫወትን ድንገት ትዝ ሲለው ጮኾ ያጠናውን ቴአትር ይወጣው ነበር። ብዙ የሚያስቸግረው የፀጋዬ ገ/መድኅን  ቴአትር ነው። ቃላቱ ከበድ ከበድ ያሉ ስለነበሩ እየበላም ሲለማመድ አየው ነበር።”

አቶ ተፈራ የስድስት ዓመት ልጅ እያሉ ቴዎድሮስ ቴአትር ላይ ምኒሊክን ሆነው የተጫወቱ ሲሆን ቴአትሩ ላይ አባታቸው አባባ ተስፋዬ ራስ መኮንን ሆነው እንደሠሩ ተናግረዋል። አጫጭር የቴሌቭዥን ድራማዎች ላይም መተወናቸውንም አያይዘው ገልፀዋል።

ወ/ሮ ወይንሸት ተሾመ የአባባ ተስፋዬ ልጅ ባለቤት ስትሆን እሷም ስለ አባባ ተስፋዬ የምትለው አላት፤

‹አባባ ተስፋዬ የኛ ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብም አባት ናቸው። ልጃቸውን በማግባቴ ለ 19 ዓመታት ያህል አውቃቸዋለሁ። ለ 15 ዓመታት ደግሞ አብረን ኖረናል። ጥሩ አባት ናቸው። ከውጪ ሲመጡ የቤተሰቡ አባል ጎድሎ ማየት አይፈልጉም። ገና ሲገቡ ምሳ በልታችኋል ወይ ይላሉ። ሌላ ቦታ ከተጋበዙ ደውለው ይናገራሉ። ዘመዶቻቸውን ሰብስበው ይይዛሉ።”

ዛሬ አባባ ተስፋዬ 84 ዓመታቸው ነው። ለ 42 ዓመታት ካገለገሉበት የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ከሥራ እንዲወጡ ተደርገዋል። ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የወጡበትን ምክንያት አባባ ተስፋዬ እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ፤

“ልጆች ይቀርባሉ በዝግጅቱ ላይ። ልጆች እያዘጋጁ አነጋግራቸው ይላሉ ብዙ ጊዜ ቴቪዥኖች። እና ሕፃናቶች ተሰብስበው መጥተው ነበረ - እኔ ጋር። እና ሁል ጊዜ የማደርገው ነው፤ አንድ ትንሽ ህፃን ልጅ ተረት ሲያወራ ‹አንድ ጋና ና ፈረንጅ ነበረ…› ብሎ ጀመረ። እንግዲህ እያዳመጥኩት ነበርና እኔ ምን ምን አልኩት፤ የሕፃን አነጋገር በመጠቀም ‹አንድ ጋያና ፌየንጅ ነበረ። እና እሹ› እያለ ያወራል። እኔ እንግዲህ ጋና እና ፈረንጅ የሚለው ነው አእምሮዬ ውስጥ የመጣው። እንዲህ ዓይነት የእንግሊዞች ተረት አለ። አፍሪካ ሲገቡ አንግሊዞች ለአሽከራቸው በዚህ ሰዓት አብራ፣ በዚህ ሰዓት ደግሞ እንዲህ አድርግ የሚል በመጽሐፍ ላይ የተጻፈ አለ። እና እሱ መሰለኝ። እኔ በፍፁም አላወቅሁም። ይሄንንም ለሥራዬ ሣምንት ስመጣ፣ ‹ሥራ የለህም እኮ ትተሃል› ብላ አንዲት ተላላኪ ልጅ ወረቀት ሰጠችኝ። እኔም ተመልሼ አልሄድኩም። ቀረሁ ቀረሁ… ወዲያው ደግሞ በሬዲዮን፣ ‹በስህተት የተላለፈ ቃል ነው› የሚል ነው መሰለኝ ያስተላለፉት። .. ድሮም ቃላት ይሰነጠቁ ነበር።” 

እዚህ ላይ የጽሑፋችንን መዝጊያ የምናደርገው በሚከተለው አጭር ጽሑፍ ነው፤ “…ልብ በሉ! 40 ዓመታት! በእንደዚህ ዓይነት ኪነ ጥበብ ውስጥ ለረዥም ዘመናት ከቆየ ሰው የሚገኘው ልምድ፣ ዕውቀት፣ ትዝታ፣…በምን ሊለካ ይችላል!? …ትራጀዲ፣ ኮሜዲ፣ “ፋርስ”፣…የሰጧቸውን በትክክል የሚጫወቱ ከዚህ በተጨማሪ ሙዚቀኛ፣ ምትሐተኛ (ማጂሺያን)፣ ዘፋኝ፣ የሕፃናት አስተማሪ፣ የውዝዋዜ አሠልጣኝና አስተዋዋቂም ጭምር ናቸው። ይገርማል! አንድ ሰው እንዴት የአምስት ኪነ ጥበብ ዘርፎች ባለ ሙያ ሊሆን ይችላል!?”

አባባ ተስፋዬ ከአማርኛ ቋንቋ ውጪ የኦሮምኛ፣ የወላይትኛ፣ የጣሊያንኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ችሎታ አላቸው።

 

ማስታወሻ

ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ሐምሌ 22 ቀን 2009 ዓ.ም ለ34ኛ ጊዜ ተማሪዎችን በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ባስመረቀበት ሥነሥርዓት ላይ አርቲስት ተስፋዬ ሣህሉ (አባባ ተስፋዬ) በአርአያነታቸው ተመርጠው ከክቡር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ እጅ በተወካያቸው በኩል የዕውቅና ሽልማት አግኝተዋል። ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓ.ም በተወለዱ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በአባባ ተስፋዬ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጻል።

 

በጥበቡ በለጠ

የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበርካታ ኪነጥበባዊ ሀብት  ባለቤት ነች። ስለ ቋንቋ ብናወራ ከዚህችው ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ውስጥ የፈለቁ ቅኔዎችን፣ ሰዋስዎችን፣ አንድምታዎችን ወዘተ እናገኛለን። ታሪክን ብንጠይ፣ ተዝቆ የማያልቅ የኢትዮጵያውያን ታሪክ ከኖህ ዘመን እስከ እኛው ድረስ ትተርክልናለች። የመንግስት አስተዳደርና ስርአትን ስንጠይቃት ከፍትህ ዶሴዋ፣ “ፍትሀ ነገስት ወፍትሕ መንፈሳዊ” የተሰኘውን የአስተዳደርና የዳኝነት መፅሐፏን ታቀርብልናለች። ስለ ነገስታት ስንጠይቃት “ታሪከ ነገስታትን” ታስነብበናለች። ቤተክርስቲያኒቱ ኢትዮጵያን የተመለከቱ ጉዳዮች በተነሱ ቁጥር የመመለስ ብቃት እንዳላት የብዙ ጥናትና ምርምር ውጤቶች ያሳያሉ። በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ የአስተዳደርና የፖለቲካ ስርአት ውስጥ እስከ አፄ ኃይለስላሴ መንግስት ድረስ ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበረች። ደርግ ሲመጣ ለብዙ ዘመን የነበረችበትን የሀገር አስተዳደር ተሳትፎዋን ወሰደባት። አንዳንዶች ያንን ዘመን ሲገልፁት፣ “ቤተ ክርስቲያኒቱ ፀጋዋን የተጠቀመችበት ወቅት ነው፤” ይሉታል።

በ1995 ዓ.ም አለቃ አያሌው ታምሩን ቃለ መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር። እንደሚታወቀው አለቃ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ “ሊቀ ሊቃውንት” አንዱ ነበሩ፡፡ የሊቆች ሊቅ ማለት ነው። በወቅቱ አለቃ የጋዜጦች ሁሉ የፊት ገፅ ዜና ነበሩ። እኔም በጥያቄዎቼ መሀል ያቀረብኩላቸው “እርስዎ የመንግስት አሰራርን እና አካሄድን ሁሉ ይተቻሉ፤ በሕግ ደግሞ የተደነገገው መንግስት በሀይማኖት ውስጥ፣ ሀይማኖት በመንግስት ውስጥ ጣልቃ አይገቡም የሚል ነው” አልኳቸው።

አለቃ በአባባሌ ተቆጡ። ማን ባቆመልህ ምድር ላይ ሆነህ ነው ሃይማኖቷ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ አያገባትም የምትለው!? ይኸችው ቤተክርስቲያን አይደለችም እንዴ ከባእዳን ወራሪዎች ኢትዮዽያን የተከለከለችው ቤተክርስቲያን ናት’ኮ ህዝቦችን እያስተባበረች፣ እየመከረች፣ እየገሰፀች ሀገራቸውን በነፃነትና በአንድነት እንዲጠብቁ ያደረገች ይህችው ቤተክርስቲያ ናት’ኮ። ካህናቶቿን እና ሊቃውንቶቿን፣ ታቦቷን ሳይቀር በየጦር አውድማው እያሰለፈች ኢትዮጵያን የጠበቀች የቤተክርስቲያን አይደለችም?! ካህናት ያለቁት ኢትዮጵያዊያን ከባእዳን ወረራ እየጠበቁ ነው! ትምህርትስ ቢሆን ይህችው ቤተ ክርስቲያን አይደለችም እንዴ ያስተማረችና ለወግ ማእረግ ነገስታቶችን ያቀረበችው?! ኢትዮጵያ በቅኝ ገዢዎች መዳፍ ስር እንዳትወድቅ አድዋ ላይም ሆነ በሌሎች አውደ ግንባሮች ላይ ከሰራዊቱ ፊትና ኋላ በመሰለፍ በፀሎትና በምህላም በሱባዔም ፈጣሪዋን እየተማፀነች ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቆም በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅዎ ያደረገችው ቤተ ክርስቲያኒቱ ናት! እና በምን ምክንያት ነው አሁን በኢትዮጵያ አስተዳደር ውስጥ አያገባትም የምትለው?! እያሉ አፋጠጡኝ።

የአለቃ አያሌውን አባባል፣ አገላለፅ ለብዙ ጊዜ አስበው ነበር። በውስጡ ብዙ እውነታዎች አሉት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን በሀገሪቱ የመንግስት ስርዓት ውስጥ ትልቅ ሚና ነበራት። ቤተ ክርስትያኒቱ ቀብታ ያልሾመችው ንጉስ ተቀባይነት የለውም። ከዚህም በተጨማሪ በአያሌ የአስተዳደር ውሣኔዎች ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበራት። ይሄ ሁሉ ፀጋዋ የተነጠቀው ዘመነ ደርግ ሲመጣ ነው። ከአፄ ኃይለስላሴ ጋር አዲዮስ ሃይማኖት ተብሎ ለብቻዋ ተቀመጠች።

ቤተ ክርስትያኒቱ በሀገር አስተዳደር ውስጥ የነበራትን ሚና እንዴት ተነጠቀች? ደርግ ለምን ከለከላት? ምን ጥፋት ሰራች? ሀገርን የጐዳችበት የታሪክ አጋጣሚ አለ? ጥቅሟና ጉዳቷስ ታይቷል? ቤተ ክርስትያኒቱ ይህን የአስተዳደር ፀጋዋን ስትነጠቅ ልክ አይደለም ብሎ የተከራከረላት አለ? ወይስ ቤተ ክርስትያኒቱ ራሷ በደርግ ውሳኔ አምናለች? እነዚህ አንኳር ጥያቄዎች በወቅቱም ሆነ ከዚያ በኋላ እንደ መብት የተጠየቁ አይመስለኝም።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ከመንግስት አስተዳደር ውስጥ እጇን እንድታነሳ የተደረገ ጉልህ ትግል አልነበረም። ቢኖርም በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ግራኝ አህመድ ከቱርኮች ጋር በማበር በክርስትያናዊው መንግስት ላይ ያወጀውና ያነሳው ጦርነት ነው። ከ1515-1531 ዓ.ም በነበረው የግራኝ አህመድ ጦርነት ለ15 ዓመታት ኢትዮጵያ ስትፈርስ፣ ስትወድም ቆይታለች። በታሪኳ ከፍተኛ አደጋ ያየችበት ወቅት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም በጐንደር የስልጣኔ ዘመን በአፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግስት ከ1595 ዓ.ም እስከ 1626 ዓ.ም ባለው ዘመንም ቤተ-ክርስትያኒቱ ፈተና ውስጥ ነበረች። ፖርቹጊዞች እና ስፓንያርዶች ባመጡት ሃይማኖት ምክንያት ኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን መመሪያዋ እንደማታደርግ በአዋጅ ተነገረ። ግጭት ተነሳ። ህዝቡ እርስ በርሱ ተላለቀ። በሱስንዮስ አደባባይ ከስምንት ሺ በላይ ምዕመን ሞቷል። ከዚያ በኋላ ነው አፄ ፋሲል ወደ መንበረ ስልጣኑ ሲመጡ መንግስት የተረጋጋውና ሃይማኖቷም የቀድሞ ቦታዋን ያገኘችው። ወደ ኋላ ከሄድንም በዮዲት ጉዲት ዘመን ከ842-882 ዓ.ም ለ40 ዓመታት ይሁዲነትን ለማስፋፋት ባደረገችው ጥረት በርካታ አብያተ-ክርስትያናትና ቅርሶች ከመውደማቸውም በላይ የቤተ-ክርስትያኒቱ ህልውና አስጊ ሆኖ ነበር።

እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የታሪክ አጋጣሚዎች ዋናዎቹ የቤተ-ክርስትያኒቱ የፈተና ወቅቶች ነበሩ። እነዚህን በፅናትና በመስዋዕትነት አልፋቸዋለች። ማለፍ ያልቻለችው የደርግ ስርዓትን ነበር። ደከማት መሰለኝ ደርግ ሲቀማት ዝም አለች። ወይም ደግሞ ተስማምታለች ማለት ነው። አልያም የዘመኑ አስተሳሰብና ፍልስፍና አይሎ የአዲሱ ትውልድ ጥያቄ በመሆኑ ቤተ-ክርስትያኒቱ በፀባይ ቦታዋን ለቃለች ማለት ይቻላል።

አዲሱ ትውልድ የኮሚኒስት አስተሳሰብና ፍልስፍና ቅኝት ነው። ያ ደግሞ ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት የለውም። የሃይማኖትን እሳቤዎች ፍርስርሳቸውን የሚያወጣ ነው። ገና ከጅምሩ ፈጣሪ የሚባል የለም በማለት ይጀምራል። ስለዚህ እነ መላእክት፣ እነ ቅዱሳን፣ እነ ሰማዕታት ወዘተ የሚባሉ የሃይማኖቷ መገለጫዎች በዚህ ኰሚኒስታዊ አስተሳሰብ ውስጥ ቦታ የላቸውም። እናም ኮሚኒዝምና ሶሻሊዝም የኢትዮጵያ የፍልስፍና እንዲሁም የአስተዳደር መርሆዎች ሆኑ። የማርክስ፣ የኤንግልስ እና የሌኒን ፍልስፍናዎች ከቤተ-ክርስትያኒቱ በላይ ለደርግ አስተዳደር የቀረቡ ሆኑ። ታዲያ ቤተ-ክርስትያን ምን ትሰራለች!? ከሃይማኖት ይልቅ እነ ማርክስ በጣሙን ተሰበኩ። መድረኩን ከሃይማኖቷ የተረከቡ ሆኑ።

ኢህአዴግ ደርግን ተዋግቶ ሲጥል የሚሰጠው ምክንያት ደርግ አረመኔ፣ አፋኝ፣ ገዳይ በመሆኑ እንዲሁም የዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ስለሚያደርግ ነው ይላል። ለመሆኑ ደርግስ ቤተ-ክርስትያኒቱን ከሀገር አስተዳደር ሚና ውስጥ ሊያስወጣት ምን ብሎ ይሆን? እርግጥ ነው በ1960ዎቹ ውስጥ የተቀነቀነው የለውጥ አብዮት ተማረ የሚባለውን ትውልድ የልዩ ልዩ ሀገሮች ፍልስፍናዎች ማርኰት ወስዶታል። ትውልድ ከሃይማኖት አፈንግጦ ሌላ ፍልስፍና አቀንቃኝ ሆኖ የታየበት ወቅት ነበር። በአንፃሩ ከሃይማኖት ሚና እና ፍልስፍና ይልቅ ሌሎች የተደመጡበት ወቅት ነበር ማለት ይቻላል። ፈሪሃ እግዚአብሔር የሚባል ነገር የለም። ፈሪሃ ማርክስ፣ ፈሪሃ ኤንግልስ፣ ፈሪሃ ሌኒን የሚባሉ እምነቶች ከፈሪሃ መንግስቱ ኃይለማርያም ጋር ሆነው 17 ዓመታት ቆይተዋል።

ኢህአዴግ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ላይ መጣ። ወዲያው አቡነ መርቆርዮስ ከሀገር ወጡ። የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ፓትርያርክ ነበሩ በዘመነ ደርግ። ምነው ቢባሉ ለደህንነቴ በመስጋት ነው አሉ። አንድ የሃይማኖት መሪ፣ የራሱን ደህንነት ለመጠበቅ ሃይማኖቱንና ህዝቡን ጥሎ ይሄዳል? የፈለገ የደህንነት ስጋት ቢኖርስ? ለእግዚአብሔር ማደር? ስጋትን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ሰጥቶ የመጣውን ሁሉ በፅናት መቀበልስ እንዴት አልቻሉም? በአቡነ መርቆርዮስ ላይ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ። ሀገርን እና ሕዝብን ጥሎ በመሄድ የመጀመሪያው ፓትሪያርክ ናቸው።

አቡነ ጳውሎስ በዚህ ክፍተት ውስጥ የመጡ የቤተ-ክርስትያኒቱ መሪ ነበሩ። በእርሳቸው ዘመን ደግሞ ቤተ-ክርስትያኒቱ ከውጪያዊ ጫና በላይ በውስጣዊ ችግሮች ተተብትባ ቆይታለች። የጳጳሳት ፀብ፣ የቀሳውስት አቤቱታ፣ የምዕመናን አያሌ ጥያቄዎች፣ የገንዘብ እና የውስጥ አስተደደሮች በማኅበረ ቅዱሳኖች ላይ የሚደረገው ጫና ወዘተ በጉልህ የታዩ ችግሮች ነበሩ። በኢህአዴግ ዘመን ቤተ-ክርሰትያኒቱ ከመንግስት ጋር ሆና አያሌ ተግባራትን ስታከናውን ነበር። ይህም ሃይማኖትና መንግስት በውስጥ ስራቸው ጣልቃ አይገባቡም የሚለው ሀሳብ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።

አንዳንድ ሰዎች ቤተ-ክርስትያኒቱ ከ40 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ይዛ እንዴት በፓርላማ ውስጥ እንኳን አትወከልም ይላሉ። እርግጥ ነው በሀገሪቱ ውስጥ በሃይማኖት ስም በፖለቲካ መደራጀት አይቻልም። ይሁን እንጂ በፓርላማ ውስጥ የድምፅ ውክልና ቢኖር በልዩ ልዩ የፓርላማው ውሳኔዎች ላይ ድምጿ ይሰማ ነበር የሚሉ አሉ። ኦርቶዶክስ የአርባ ሚሊዮን ሕዝቧን ድምፅ ለማሰማት ጥያቄ መጠየቅ አለባት የሚሉም አሉ።

በነገራችን ላይ በፓርላማ ውስጥ የአካባቢ ጥበቃ ወንበር፣ የቤተ-እምነቶች ወንበር፣ የሴት መብት ተከራካሪ ቡድኖች ወንበር፣ የአካል ጉዳተኞችና ድኩማን የውክልና ወንበር ወዘተ ቢኖር ከየአቅጣጫው ድምጾች ይሰማሉ የሚል እምነት አለ። እነዚህ ድምጾች እንደማንኛውም የፓርላማ አባል ተወዳድረው አሸንፈው የሚመጡ ሳይሆን መንግስት በራሱ ፍላጐት የሚደለድላቸው ነው። ፓርላማው ውሣኔ ሲያሳልፍም ድምፃቸው ይቆጠራል። ሀገራችን ወደፊት ይህን አሰራር ከተገበረችው የተሻለ የድምፅ ውክልና ይኖራል ተብሎ ይታመናል።

ወደ ዋናው ርዕሰ ጉዳያችን ስንመለስ፣ ይኸችው ቤተ-ክርስትያን የመነጋገሪያ አጀንዳችን ናት። በሀገር አስተዳደር እና ጥበቃ ላይ ሰፊ ድርሻ የነበራት ቤተ-ክርስትያን፣ አሁን ላይ ሆነን ስናያት ያንን ብቃቷን መተግበር ትችላለች? አሁን ያሉት የሃይማኖት አባቶች ምን ያህል ራሳቸውን ከዘመናዊው አስተሳሰብ ጋር እያገናኙት የሃይማኖቱን አስተምህሮና ፍልስፍና ለትውልድ ያስጨብጣሉ? የሚለው ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል። ለምሳሌ የሊቀ ጳጳሳት ሹመት በራሱ የእድሜ ጣሪያ የለውም? እንደ ልብ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የሚያስተምሩ፣ አንደበታቸው የሰላ፣ ሌላውን ማሳመን፣ ማስተማር፣ መገሰፅ፣ ማስታረቅ ወዘተ የሚችሉ ከአንደበታቸው ማር ይፈሳል የሚባሉ ሊቀ-ጳጳሳትን ማዘጋጀት (ማብቃት) አይቻልም ወይ?

የቤተ-ክርስትያኒቱ አስተምህሮት እየቀነሰ ሲመጣ፣ ድምጿ አልሰማ ሲል እንደ ኰሚኒዝም፣ ሶሻሊዝም ያለ አዳዲስ መጤ አስተሳሰቦች በአንድ ግዜ ገነው ይወጣሉ። ነገ ምንአይነት ፍልስፍናና አስተሳሰብ እንደሚመጣ አናውቅም። ግን ሃይማኖቷ የአያሌ ታሪኰች እና የአስተሳሰቦች ማዕከል በመሆኗ፣ የቋንቋና የሥነ-ጽሁፍ እጅግ በርካታ ስራዎች ባለቤት በመሆኗ፣ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብት  በመሆኗ፣ ከ40 ሚሊየን ህዝብ በላይ ተከታይ ያላት በመሆኗ ወዘተ ለኢትዮጵያ እድገትና ትንሳኤ ብዙ ነገር ማበርከት ትችላለች። ጥያቄው ግን እንዴት? የሚል ሲሆን፣ ማንስ ይመልሰው?

 

በጥበቡ በለጠ

 

ስለ ንባብ ምን ተባለ

-    “የኔ ምርጥ ጓደኛ ብዬ የምቀርበው ሰው ያላነበብኩትን መፀሐፍ “እንካ አንብብ” ብሎ የሚሰጠኝ ነው።” አብርሃም ሊንከን።

-    “ዘወትር ባነበብኩኝ ቁጥር ውስጤ የነበረውና ያለው ትልቁ የመቻል አቅም ይቀሰቀሳል።” ማልኮም ኤክሥ።

-    “ለአንድ ሰው መፅሐፍ ስትሸጥ የሸጥከው ብዙ ወረቀቶችን፣ የተፃፈበትን ቀለምና ጥራዙን አይደለም። ለርሱ የሸጥክለት ዋናው ነገር ሙሉ የሆነ አዲስ ህይወትን ነው።” ክርስቶፈር ሞርሌይ

-    “በዚህ ዘመን በየትኛውም ሁኔታ በጣም ግዜ የለኝም፣ እረፍት የለኝም ብለህ የምታስብ ቢሆን እንኳን ለማንበብ የግድ ግዜ መስጠት አለብህ። ይህን አላደረክም ማለት ግን በገዛ ፍላጎትህ ራስህን አላዋቂ እያደረከው ነው ማለት ነው።” ኮንፊሽየሥ

-    “መፅሐፍትን በሚገባ ማንበብ ማለት በድሮ ዘመን ይኖር ከነበረ በጣም አስተዋይ ሰው ጋር መወያየት ማለት ነው።” ሬኔ ዴካርቴሥ

-    “ማስቲካ ለማምረት ከምናወጣው ወጪ በላይ ለመፅሐፍቶች ብዙ ወጪን ባናወጣ ኖሮ ይህች ሀገራችን እንዲህ የሠለጠነችና የዘመነች አትሆንም ነበር።” አልበርት ሀባርድ (አሜሪካዊ)

-    “ከየትኛውም ነገር በላይ ትልቁንና ከፍተኛውን ደስታ የማገኘው ሳነብ ነው።” የፋሽን ዲዛይነሯ ቢልብላሥ

-    “መፅሐፍን ከማቃጠል የባሰ በርካታ ወንጀሎች አሉ። ከነዚህ መሃል መፅሐፍትን አለማንበብ አንዱ ትልቁ ወንጀል ነው።” ጆሴፍ ብሮድስኪ

-    “አላዋቂነትንና ችኩልነትን የምንዋጋበት ብቸኛው ወሳኝ መሣሪያ ማንበብ ነው።” ሌኖርድ ቤይንሥ ጆንሰን

-    “ዛሬ ያነበበ ነገ መሪ ይሆናል።” ማርጋሪት ፉለር

-    “መፅሐፍን የማያነብ ሠው ማንበብን ከነጭርሱ ከማይችል ሠው በምንም አይሻልም።” ማርክትዌይን

-    “አንድ መፅሐፍ ባነበብን ቁጥር እዚህ ምድር ላይ በሆነ ቦታ ለኛ አንድ በር እየተከፈተልን ነው።” ቬራናዛሪያን

-    “ማንበብ ከምንገምተው በላይ ዘላቂ የሆነ ደስታን ነው የሚሰጠን።” ላውራቡሽ

-    “አንድ ሠው ምን አይነት ማንነት እንዳለው ያነበባቸውን መፀሀፎች አይቶ መናገር ይቻላል።” ራልፍ ዋልዶ ኤመርሠን

-    “አንድ ባህል ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዳይተላለፍ ከተፈለገ መፀሀፎችን ማቃጠል አያስፈልግም። ይልቅ ሠዎቹ መፅሐፍ ማንበብን እንዲያቆሙ ማድረግ በቂ  ነው።” ራይ ብራድበሪ

-    “ለማንበብ ግዜ የለኝም ካልን ለማውራትና ለመፃፍ እንዴት ግዜ እናገኛለን?” ስቴቨን ኪንግ

-    “ህፃናት እንደሚያደርጉት ለመገረም ብለው መፅሐፍን አያንብቡ። ለመማርም ሆነ ህልመኛ ለመሆንም ፈልገው አያንብቡ። ይልቅ ለመኖር ሲሉ ነው ማንበብ ያለብዎት።” ጉስታቮ ፍላውበርት

-    “ከመናገርህ በፊት አስብ። ከማሠብህ በፊት አንብብ።” ፍራን ሌቦውትዝ

-    “አንተ ያላነበብከውን መፅሐፍ አንብብ ብለህ ለልጅህ አትስጠው።” ጆርጅ በርናንድ ሾው

-    “በአሁኑ ሰአት እየተቃጠሉ ካሉ መፅሐፍት በላይ የሚያሳስበኝ በአሁኑ ሰዓት እያልተነበቡ ያሉ መፀሀፎች ናቸው።” ጁዲ ብሉሜ

-    “ልጆቼ ወደፊት ሲያድጉ ማንበብ የሚወዱና ለእናታችን ትልቅ መፅሐፍ መደርደሬ እንስራላት ብለው የሚጨነቁ ቢሆኑ ደስታዬ ወደር አይኖረውም።” አና ክዊድሰን (የኒዮርክ ታይምስ ፀሃፊ)

-    “ከውሻ ውጪ የሠው ልጅ ታማኝ ወዳጅ መፅሐፍት ናቸው። ከውሻ ጋር ወዳጅ ስንሆን ግን የማንበብ እድላችን በጣም ያነሠ ነው።” ጉርቾ ማርክሥ

-    “መፅሐፍ ማለት በኪሳችን ይዘነው የምንዞረው በመልካም ፍሬዎች የተሞላ እርሻ ነው።” ቻይናውያን

-    “መፅሐፍ የሚያነቡ ሠዎች ብቸኝነት አያጠቃቸውም።” አጋታ ክርስቲ

-    “መፅሐፍ ማንበብ ነፍስን ያክማል።” በቴክሳስ ላይብረሪ መግቢያ ላይ የተፃፈ

-    “መፅሐፍ የሌለበት መምሪያ ቤት ማለት መስኮት የሌለበት ቤት ማለት ነው።” ሎነሬች ማን

-    “ከየትኛውም መዝናኛ በላይ እንደማንበብ ዋጋው ርካሽ ሆኖ በቀላሉ የሚያዝናና ነገር የለም። ደግሞም በማንበብ እንደሚገኘው ዘለቄታዊ ደስታ ሌሎች መዝናኛዎች ዘላቂ ደስታን አይሠጡም።” ሌዲ ሞንታኑ

-    “እኔ ዘወትር የማስበው በቀጣይ ስለማነበው መፅሐፍ ብቻ ነው።” ሮኦልድ ዳህል

 

 

የሀገር ውስጥ ሰዎች አባባል ስለንባብ

-    “ማንበብ የአአምሮ ምግብ ነው፤ ዋናው የአእምሮ ምግብ!”  ደራሲ ስዩም ገ/ህይወት

-    “ማንበብ ህይወትን የምንቀይርበት ትልቅ መሳሪያ ነው። ያለ ንባብ ህይወትን በአግባቡ መምራት አይቻልም።” አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው

-    “ማንበብ የእውቀት ብርሃን ነው። ስለዚህ ባነበብን ቁጥር ውስጣችንም ሆነ በዙሪያችን ያለው ውጫዊ ነገር በሙሉ በብርሃን የተሞላ ይሆናል።” ሰአሊ አንዷለም ሞገስ

-    “ሰው ምግብ ሳይበላ እንደማይውለው እኔም ሳላነብ አልውልም። ምክንያቱም ማንበቤ እኔን ከምንም ነገር በላይ ተጠቃሚ አድርጎኛል።” ሀይለልዑል ካሳ (የባንክ ባለሙያ)

-    “ንባብ ያልታከለበት ግንዛቤ ግልብ ያደርጋል።” ደራሲ በአሉ ግርማ

-    “መፅሐፍትን ማንበብ ታሪክህን በሚገባ እንድታውቅ ያደርግሀል። ታሪክህን ስታውቅ ደግሞ ራስህን ታውቃለህ።” አምባሳደር ዘውዴ ረታ

-    “በዚህች ጥንታዊ ሀገር መፅሐፍትን መፃፍ ብቻ ሳይሆን ማንበብ፣ ማስነበብ፣ ማስፃፍ፣ ሲነበቡ መስማት ጭምር የተከበረ ነገር ነበር።” ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

-    “ማንበብ በሁሉም ነገር ምልዑ ሆነን እንድንንቀሳቀስና ከግዜው ጋር አብረን እንድንራመድ ያስችለናል።” ፍቅር ተገኑ (የፀጉር ውበት ባለሙያ)

-    “ማንበብ እኮ ሁሉን ነገሮች ያንተ እንዲሆኑ ያደርጋል። ስታነብ ትዝናናለህ። ማንበብህን ተከትሎ ደግሞ ስለሁሉም ነገር ማወቅና መረዳት ትጀምራለህ።” ድምፃዊ ፀሃዬ ዮሀንስ

-    “ማንበብ ያልኖርነውን ትላንት ዛሬ ላይ መኖር እንድንችል ያደርጋል። ከዛ ካልኖርንበት ዘመን እንኳን ጓደኞች እንዲኖሩን፤ የነርሱንም ያህል ዘመኑን የኖርነው ያህል እንዲሰማን ያስችላል።”  ገጣሚናጋዜጠኛ ዳዊት አለሙ

-    “መፅሐፍ ያጣ አእምሮ፤ ውሃ ያጣ ተክል ማለት ነው። ሰው ራሱን አውቆና ችሎ እንዲኖር መፅሐፍ ማንበብ በእጅጉ ይጠቅማል።” መምህርንጉሴ ታደሰ መምህር

-    “ማንበብ ከባይተዋርነት ያድናል። ባነበብን ቁጥር በአለም ላይ ስላሉ ነገሮች ስንሰማም ሆነ ስናይ አዲስ አይሆንብንም። ወዳጆችን ለማፍራትም አንቸገርም። ማንበብ የሙሉነት መስፈርት ነውና።” ገጣሚና ጋዜጠኛ ፍርድያውቃል ንጉሴ

-    “ማንበብ አእምሮን አያስርብም። የሚያነብ ሰው ዘወትር ንቁና በአስተሳሰቡ የበለፀገ ነው።” ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ)

-    “እውቀቴን ሁሉ ያገኘሁት በማንበብ ነው። በአጭሩ ማንበብ አዋቂ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ሰው ያደርጋል።” ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ

-    “ማንበብ ፍፁም ደስተኛ ያደርጋል። እስከዛሬ ባላነብ ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር? እያልኩ ዘወትር አስባለሁ።” ህዝቅያዝ ተፈራ (የህግ ባለሙያ)

-    “ማንበብ በጣም ያዝናናል። በየትኛውም ግዜ የሚወጡ መፅሐፍትን ማንበብ የሃሳብ ሀብታም ያደርጋል።” ተዋናይ ዋስይሁን በላይ

-    “እኔ ማታ ማታ አነባለሁ። ሁሌ አንብቤ ሳድር በጣም ደስተኛ ከመሆኔም በላይ የደንበኞቼን ባህርይ እንድረዳ ረድቶኛል።” ካሳሁን ፈየራ (የታክሲ ረዳት)

-    “ማንበብ በየትኛውም ነገር ላይ ተፈላጊውን ተፅዕኖ መፍጠር እንድትችል ያደርግሃል። ከሰዎች ጋርም በቀላሉ እንድትግባባ መንገዱን ይጠርግልሃል።” እድሉ ደረጀ (የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች)¾

 

በበኃይሉ ገ/እግዚአብሔር

 

ከዚህ በታች የቀረበው ግጥም ርዕስ ከንፈር መጠጣ ነው፤ በኢትዮጵያ ስነጽሑፍ ውስጥ የመጀመሪያው አጭር እና የማይጻፍ ርዕስ ያለው ግጥም ይህ ይመስለኛል።

እምጭ (ከንፈር መጠጣ)

እመጫቷ

እጆቿን ዘርግታ፣

ልጆቿን አስጥታ፣

ከጠዋት እስከ ማታ፣

ትላለች፤

‹‹ወገኖቼ ስለ ልደታ!››

(ሰኔ 1 ቀን 2006 ዓ.ም፤ ጠዋት 2፡00 ሰዓት ላይ አንዲት መንገድ ዳር ከልጆቿ ጋር ቁጭ ብላ የምትለምን ሴት አይቼ የጻፍኩት ግጥም)

ግጥም መጻፍ እወዳለሁ። ‹‹ግጥም ሙያ አይደለም፤ እጣ ፈንታ እንጂ!›› እንዲል ፈረንጅ ከልጅነቴ ጀምሮ አብሮኝ ያደገ ጥበብ ነው ግጥም። በተለይ ሲርበኝ ግጥም መጻፍ ደስ ይለኛል። እንደውም ከምግብ ይልቅ ሰውነት የሚሆነኝ እንጀራ ሳይሆን ግጥም መጻፍ ነው ብል ማጋነን አይሆንም።

በቅርቡ እናቴን እንዲህ አልኳት፤ ‹‹አንቺ እናቴ! እንጀራ በበርበሬ አማረኝ!›› እናቴም እንደ ማፈርም፣ እንደ መሳቀቅም ብላ፣ ‹‹ልጄ ሆይ! ዘንድሮ ተረት የሆነው ድኅነት ሳይሆን በርበሬ አይደለምን?›› አለችኝ፤ አዘንኩ። እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ ገጣሚ በጣም አዘንኩ። ወዲያው፣

‹‹ዋ! በርበሬ፤

አንተ በርበሬ፤

የእኛ ወዳጅ እስከ ዛሬ፤

ለምን ሆንክብን በሬ!?›› ብዬ ስንኞችን ከአእምሮዬ ጓዳ አውጥቼ ግጥም አሰናኘሁ። …በጥቅሉ ድህነት ወይም ረሃብ የኔ የግጥም ምንጮቼ ናቸው።

ከቀናት መካከል ባንዱ፤ ለአንዱ ሃያሲ የግጥም ሥራዎቼን ሰጠሁት፡ ‹‹አደከምከኝ!›› አለ መጀመሪያውኑ በደከመ ድምፅ። ‹‹ምን አደከመህ?›› አልኩት ውስጥን በሚመረምር የገጣሚ ዐይን እያየሁት። ‹‹ካንተ ጋር ግጥማቸውን እንዳይላቸው የጎበኙኝ ሰዎች በዙና ደከምኩ›› አለ በመታከት። ይባስ ብሎ፣ ‹‹ገጣሚያን በጣም በዙ። ይህ ከሆነ ገጣሚነት የተሰጥኦ ጉዳይ መሆኑ ቀረ ማለት ነው›› ብሎ ታላቅ ትካዜ ውስጥ ገባ። ተበሳጨሁ። ‹‹አንተ ሃያሲ ስለምን ትሆናለህ ከይሲ? ምድር በገጣሚያን ብትሞላ ጉዳቱ ምንድር ነው?›› ስልም ጠየቅኩት፤ መልስ ግን አልነበረውምና ዝም  አለ።

በሌላኛው ዕለት ደግሞ ወደ ሌላኛው ሃያሲ ዘንድ አቀናሁና ግጥሞቼን ሰጠሁት። ሃያሲው በጥሞና እንዳነበበው ሲነግረኝ ደስ አለኝ። ‹‹ርዕስ አወጣጥ ትችልበታለህ!›› አለኝ። በሆዴ፣ ‹‹ኧረ መግጠምም እችላለሁ›› እያልኩ ደስታዬን ተደሰትኩ።

ከግጥሞቼ መካከል ከፍተኛ ምናባዊነት የሚስተዋልበትን አንድ ግጥም አነሳና፣ ‹‹እዚህ ጋር ‹ልክ እንደ በረሸሽ ከውስጥ እንደሚሸሽ› ብለሃል፤ ለመሆኑ ‹በረሸሽ› የሚለው ቃል ትርጉም ምንድር ነው?›› አለኝ። ሳቄ መጣ። እውነቴን ነው የምለው ሳቄ መጣ። ከሃያሲ የማልጠብቀው ጥያቄ ነውና ከውስጠቴ የሚመጣውን ሳቅ መገደብ አልተቻለኝም። እንደገጣሚ የአስተውሎት ሳቅ ስቄ ስጨርስ፣ ‹‹ግጥሙ የሚለው ልክ እንደበረሸሽ ከውስጥ እንደሚሸሽ ነው አይደል?›› ስል ጠየቅኩት ሃያሲውን፤ ‹‹አዎን!›› አለ። ‹‹በቃ በረሸሽ ማለት በግጥሙ ውስጥ እንደተጠቀሰው ከውስጥ የሚሸሽ ነገር ማለት ነው›› ብዬ መለስኩ እየሳቅኩ። ወዲያው ይህን ከማለቴ አንድ ግጥም መጣልኝ።

‹‹ሳቄ መጣ

ከውስጠት የወጣ፤

ሳቄን ሳቅ ቢጠራው

ሳቄን ሳቅ አነቀው›› አልኩ።

የሃያሲው ትችት በዚህ አላቆመም፤ አንድ ወደ ጎን ባለብዙ ሐረግ ስንኝ፣ ወደታች በጣም ረዥም ግጥሜን አነሳና፣ ‹‹አሁን ይሄ ግጥም ፀጋዬ ቤት ነው ወይስ ፀጋዬ ኮንዶሚኒየም!?›› ብሎ ወረፈኝ። ተናደድኩ፤ በጣም ተናደድኩ ‹‹ቆይ የራሴን ቤት መፍጠር አልችልም!›› አልኩ እንባ እያነቀኝ። 

‹‹የሰቡ የአማርኛ ቃላትን መጠቀም ትወዳለህ። እሺ መጉነጥነጥ ምንድነው?›› አለኝ። አሁንም ተበሳጨሁ። ‹‹ደራሲ ቃላት ይመርጣል፤ ገጣሚ ቃላት ይፈጥራል ሲባል አልሰማህም!›› አልኩ ተቆጥቼ። ሃያሲው እየተበሳጨ ጥያቄውን ወደ ሌላ  አደረገ።

‹‹ውዴ ሆይ እስኪ እንንሸራሸር›› በሚል ርዕስ በጻፍከው ግጥም ውስጥ፣ ‹በቀለበት መንገድ እንጓዝ ተቃቅፈን› የሚል ስንኝ አንብቤያለሁ፤ ከግርጌው ላይ ደግሞ ‹1982› የሚል ዓመተ ምህረት ተጽፏል።››

‹‹አዎ! ግጥሙን የጻፍኩበት ዓ.ም ነው›› አልኩት አንድም ሳያስቀር በማንበቡ እየተደነቅኩ።

‹‹የቀለበት መንገዱ ግን ያን ጊዜ አልነበረም። ታዲያ አንተ ዓመተ ምሕረቱን ከየት አመጣኸው?›› አለኝ።

‹‹ምንድነው የሚለው ይኼ ሰውዬ?›› የሚያወራው ሁሉ ግጥሜ ሳይገባው ነውና በጣም ተናደድኩ። ‹‹ያልከው ሁሉ ትክክል ነው። የገጣሚ አገር ግን አዲስ አበባ ብቻ አይደለችም። ገጣሚ የትም ነው አገሩ። በግጥሙ ውስጥ የተጠቀሰው የቀለበት መንገድ በምናብ የፈጠርኩት እንጂ ይሄ ዲዛይኑ ላይ ቀለበት፤ ካለቀ በኋላ ማጭድ የሚመስለውን የአዲስ አበባ መንገድ አይደለም።›› ሃያሲው ይህ ንግግሬ የገባው አልመሰለኝም። በቸልታ እራሱን ነቅንቆ ወደ ሌላ ጥያቄ አመራ።

ከግጥሞቼ መካከል ‹‹እቃዬ ወደቀ›› በሚል ርዕስ የጻፍኩትን ቅኔ ለበስ ባለአራት ስንኝ ግጥም በሃያሲ ዐይኑ ትክ ብሎ እያየ፤ ‹‹እና ምን ይሁን?›› አለኝ። ‹‹ምኑ?›› አልኩት። ‹‹እቃው ስለወደቀ ምን ይፈጠር ብለኽ ነው ይህን የጻፍከው?›› አለኝ። በዚህ ጊዜ ፈገግ አልኩ እንደ ገጣሚ። ግጥሙን እስኪ አንብበው አለኝ። እንደሚከተለው አነበብኩለት። ያውም በቃሌ፤

እቃዬ ወደቀ

እጄ ላይ የነበረው እቃ፣

ተዘናግቼ ወሬዬን ስደቃ፤

ላንቃዬን ሳንቃቃ፣

ወደቀ በቃ።

‹‹ሰው የሰጠኝ ያማረ ብዕር ነበር። በጣም የምወደው። አንድ ቀን በእጄ ይዤው ከጓደኛዬ ጋር ሳወራ ወድቆ ተሰበረብኝ። ከዚያ ወዲያው ይህቺን ልብ የምትነካ ግጥም ጻፍ አደረግኳት!›› አልኩት ፈገግታዬን ሳልቀንስ። ከዚያም ሃያሲው በመርማሪው ዐይኑ እያየኝ፣ ‹‹ግጥም የቀውሶች ቋንቋ አይደለም!›› አለና ግጥሞቼን አፍንጫዬ ላይ ወርውሮልኝ ሄደ። በወቅቱ እንደ ሰው ተከፋሁ፤ እንደገጣሚ ግን በሃያሲው ድርጊት ደስ ተሰኘሁ። ሃያሲው ግጥሞቼ ገብተውት አስተያየት ቢሰጠኝ ኖሮ መልካም ቢሆንም ሂስ መቀበል የእንደኔ ዓይነቱ በሳል ገጣሚ ግዴታ ነውና ተቀበልኩ። አዎ! ሂስ ያሳድጋልና።

አለቃ ባሳዝነው፣ ‹‹አንዳንድ ቃላትና ፍቺዎቻቸው›› በሚለው አዲሱ መጽሐፋቸው ‹‹ሂስ›› የሚለውን ቃል እንዲህ ይፈቱታል። ‹‹ሂስስ… ሂ…ስስ፤ ሂድስ፤ ሄዛ፣ ሂድ ወደዛ፤ ሂ…ስ!››

 

 

በጥበቡ በለጠ

 

ኢትዮጵያን በተመለከተ በርካታ ደራሲያን፣ ፈላስፋዎችና ተመራማሪዎች አያሌ ርዕሰ ጉዳዮችን ጽፈዋል። ኢትዮጵያን የምናውቀው በመጻሕፍቶችዋ፣ ለዘመናት ቆመው በሚታዘቡት ሐውልቶችዋ፣ ወድቀውና ፈራርሰው የሚያነሳቸው አጥተው በሚታዘቡን ታላላቅ ቅርሶችዋ፣ በቋንቋዋ፣ በሐይማኖትዋ፣ በባሕልዎችዋ፣ በአፈ ታሪክዎችዋ /legends/፣ እና በሌሎችም የማንነት ማሳያ መንገዶች ነው። ንባብ ለሕይወት የተሰኘው ትልቁ የመጽሐፍት አውደ ርዕይ ከፊታችን ከሐምሌ 21 እስከ 25 ይካሔዳል።

ይህ አውደ ርዕይ ዋና ጉዳዩ አንባቢ ትውልድ እንዲፈጠርና አንባቢ እንዲስፋፋ ማድረግ ነው። የዕውቀት ዋነኛው ምንጭ ንባብ መሆኑን ማስረጽ ነው። ያላነበበ ትውልድ በሁሉም ነገር ኋላ ቀር ነው። ንባብ የሌለበት ሕይወት ሙሉ ሊሆን አይችልም። ሐብት ንብረት ቢከማችም ንባብ የሌለበት ሕይወት እርካታ የለውም። ያላነበበ ልበ ሙሉ መሆን አይችልም። ሁሌም ተጠራጣሪ፣ ኮሽ ባለ ቁጥር ደንባሪ ይሆናል። ያላነበበ ማንነቱን አስረክቦ ይሸጣል። ያላነበበ መከራከሪያ፣ መደራደሪያ አቅም የለውም። ያላነበበ የተባለውን ሁሉ እሺ ብሎ የሚቀበል ነው። ያላነበበ አይጠይቅም፣ አያስብም። ንባብ ለሕይወት የሚጠቅመን በሕይወት ጉዟችን ውስጥ ደንቃራ ጉዳዮች እንዳያጋጥሙን፣ ቢያጋጥሙንም ባለን የንባብ ትጥቅ እንድንከላከልና እንድንቋቋም ያገለግለናል። ንባብ የሕይወት መቀጠያና ማቆሚያ ምርኩዝ ነው።

 ይሕችን እንደመንደርደሪያ ከወሰድኩ ለዛሬ ደግሞ ኢትዮጵያ ስለምትባለው አገራችን ልዩ ልዩ ደራሲያን ምን አሉ የሚለውን ጉዳይ እያነሳሳን እንጨዋወት። ቅድሚያውን ለውጭ አገር ዳራሲያን ልስጥ። ከውጭ ሲያዩን እኛ ኢትዮጵያዊያን ምን እንመስላለን የሚለውን በጥቂቱ ልደስሰው። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን በተለይም በውጭ ሀገር ፀሐፊዎች ዘንድ እንዴት ተገለፁ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሁሉንም ጽሁፎች ማንበብ ግድ ይላል። ነገር ግን የእውቀትና የምርምር ፀጋ የተሰጣቸው አንዳንድ ፀሐፍት ያነበቧቸውን ሁሉ ሰብስበው እንዲህ ተፅፏል ብለው ያቀብሉናል። በዚህም የተነሳ የዛሬ ሦስት ሺ ዓመት ግድም ከተፃፉት ሠነዶች ጀምሮ ኢትዮጵያ ነክ ርዕሰ ጉዳዮች እንዴት ተፃፉ? ምንስ ይላሉ? በሚለው ኀሳብ ላይ ቆይታ እናደርጋለን።

በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፈ ታሪክ ውስጥ አንድ አስገራሚ ገጠመኝ አለ። ይህም አፄ ኃይለሥላሴ ከመንበረ ስልጣናቸው የወረዱ ቀን፣ ወታደሮችም ኢትዮጵያን ለመምራት ስልጣን የያዙ ቀን፣ አንድ ሰፊ እውቅና የተሰጠው መጽሐፍም የዚያኑ ቀን ለንባብ ገበያ ላይ የወጣበት እለት ነበር። ይህ መጽሐፍ በፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን አማካይነት የተፃፈው Greater Ethiopia (ገናናዋ ኢትዮጵያ) የተሰኘው መጽሐፍ ነው።

Greater Ethiopia የተሰኘው መጽሐፍ በውስጡ እጅግ በርካታ የሚባሉ ትልልቅ ኀሳቦችና ምርምሮችን የያዘ ነው። ስለ ኢትዮጵያም ማንነትና ታሪክ በሰፊው የተተነተነበት የአያሌ አስተሳሰቦች ጥርቅምና ትንታኔ ያለበት መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ ኢትዮጵያን ከአንትሮፖሎጂ እና ከሶሲዮሎጂ አንፃር ዝርዝር አድርጐ ለማሳየት የተፃፈ የጥናትና ምርምር ውጤትም ነው።

ፀሐፊው ዶናልድ ሌቪንም በቺካጐ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፕሮፌሰር ቢሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በመቆየት ሀገሪቷን አጥንተዋት በርካታ ጥናትና ምርምር የፃፉ ገናና ምሁር ናቸው። ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በዚሁ Greater Ethiopia በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዳመለከቱት ኢትዮጵያ በፕላኔታችን ካሉት ሀገሮች ውስጥ በቀደምት ስልጣኔ ከሚታወቁት መካከል አንዷ መሆኗን የልዩ ልዩ ደራሲያንን ጽሁፎች በዋቢነት እያሳዩ መስክረውላታል። ከዚሁ ጋርም ተያይዞ ኢትዮጵያን በአሉታዊ መልኩ የገለጿትን ደራሲያንንም አስተዋውቀውናል።

ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ኢትዮጵያን የውጭ ሀገር ፀሐፊዎች በአምስት ደረጃዎች ከፋፍለው እንደሚገልጿት ጽፈዋል። እነዚህም የሚከተሉት ናቸው።

1.  ኢትዮጵያ በጣም የራቀች ምድር ነች ብለው ያስባሉ። /A far - off place/

2.  ኢትዮጵያ የአማኒያን ሀገር ናት ይላሉ። /Ethiopia the pious/

3.  ኢትዮጵያ ድንቅ የሆነች የንጉሥ ሀገር ነች ይላሉ። /A magnificent Kingdom/

4.  ኢትዮጵያ የአረመኔ ሀገር ነች ይላሉ። /Savage Abyssinia/

5.  ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት ሰንደቅ ነች ይላሉ። /A bastion of African Independence/

በእነዚህ ከላይ በተዘረዘሩት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በልዩ ልዩ አለማት ያሉ ደራሲያን ኢትዮጵያን እንዴት እንደገለጿት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በመፅሐፋቸው ውስጥ ያብራራሉ።

1. ኢትዮጵያ በጣም የራቀች ሀገር ናት

በዚህ ርዕስ ዙሪያ የተለያዩ ጥንታዊ ደራሲያን ጽፈውበታል። ለምሳሌ የዛሬ ሦስት ሺ ዘመን ላይ እንደኖረ የሚነገርለት ዓይነስውሩ የግሪክ ታሪክ ፀሐፊ ሐመር፣ ኢትዮጵያን በተመለከተ ጽፏል። ሖመር ኦዴሲ በተባለው መጽሐፉ ውስጥ በመጀመሪያው አንቀፅ ላይ ኢትዮጵያዊያን ከሰው ዘር ሁሉ በርቀት ላይ የሚገኙ ህዝቦች መሆናቸውን ጽፏል። በዚህም የተነሳ ሰዎች ኢትዮጵያን እጅግ ሩቅ ቦታ ላይ የምትገኝ ምድር አድርገው ያስቧት ነበር። ሄሮዱተስ የተባለው ጦረኛም ጦሩን ሲያዝ እስከ ምድር መጨረሻ ማለትም እስከ ኢትዮጵያ ድረስ ማዘዙ ተፅፏል።

ኤስኪለስ /Aeschylus/ የተባለው ጥንታዊው ፀሐፌ-ተውኔት ፕሮሚስስ ባውንድ በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ አንዲት “ኢዮ” የምትባል ሴትን በመጥቀስ፤ ይህችም ሴት “ወደ ሩቅ ምድር፣ ወደ ጥቁሮች አገር፣ ህዝቡ የፈካች የፀሐይ ጨረር እየሞቀ ወደሚኖርባት እና ጅረት ወደሚፈልቅባት” እንድትሄድ አድርጓታል። “ኢዮ” የሄደችው ወደ ኢትዮጵያ ነበር።

እንግዲህ ለጥንታዊያኑ ግሪኰችና ለሮማዎች ኢትዮጵያ ሩቅ ምድር ሆና ነው በህሊናቸው የተሳለችው። ፍራንክ ስኖውድን የተባለ ፀሐፊ Blacks in Antiquity /ጥቁሮች በጥንት ዘመናት/ በተሰኘው መፅሐፉ ኢትዮጵያዊያን ለምን የሩቅ ሀገር ህዝቦች ሆነው እንደተፃፉ ያብራራል። የመጀመሪያውን ምክንያት ሲገልፅ በጣም የራቁ ሀገሮች የቆዳ ቀለማቸው እንደሚለይ እና በዚህም የተነሳ መሆኑን ያብራራል።

ጥንታዊው የግሪክ ፈላስፋ አሪስ ጣጣሊስ (አርስቶትል) የኢትዮጵያዊያን ጠጉር ከርዳዳ የሆነው የሚኖሩበት ቦታ ላይ ያለው አየር ሞቃት ስለሆነ ነው በሚል እንደፃፈ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን Greater Ethiopia በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ ገልፀዋል።

በክርስትናው ዓለም ውስጥ በደራሲነቱ የሚታወቀው ቅዱስ አውግስቲንም፤ የቀደሙትን ደራሲያን ኀሳብ በመመርኰዝ “ንግስተ ሣባ ኢትዮጵያዊት እንደሆነች አስረግጦ ከገለፀ በኋላ በአዲስ ኪዳን “የሰለሞንን ጥበብብ ለመስማት በጣም እጅግ ሩቅ ከሆነ ቦታ መጣች” ተብሎ ከተፃፈ ኀሳብ ጋር ያያይዘዋል።

የቤዛንታይኑ ፀሐፊ አስጢፋኖስም ኢትኒኮን /Ethnikon/ በተባለው የመልክዐም ምድር ኢንሳይክሎፒዲያ መፅሐፉ ውስጥ ኢትዮጵያዊያንን በተመለከተ የገለፀው ከሖመር ጋር ተመሣሣይ ነው። ይህም “እጅግ የሩቅ አገር ሰዎች” በማለት ይጠራቸዋል። ከዚህ በመለጠቅም በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ አክሱም እንደሆነችም ጽፏል በማለት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ገልፀዋል።

ሐይማኖተኛዋ ኢትዮጵያ

በዚህ ክፍል ውስጥም በርካታ ፀሐፊያን ልዩ ልዩ አመለካከታቸውን እንዳሰፈሩ Greater Ethiopia የተሰኘው መፅሐፍ ይገልፃል። ለምሳሌ የዛሬ ሦስት ሺ ዓመት የተፃፈው የግሪካዊው ደራሲ የሖመር ኦሊያድ የተሰኘው መፅሐፍ ገና ከመግቢያው ላይ፣ የግሪኰች የአማልክት አምላክ የሚባለው “ዚየስ” ከርሱ በታች የሚገኙትን አማልክቶች ሁሉንም ይዞ ለአስራ ሁለት ቀናት ፍፁም ቅዱስ ወደሆኑት ኢትዮጵያውያንን ለመጐብኘት መሄዱ ተፅፏል። በዚሁ በሆመር በተፃፈው ሌላኛው መፅሐፍ ማለትም በኦድሴይ ውስጥ ደግሞ ፓሲዶን የተባለው ገፀባህሪ፣ “ከሩቆቹ ኢትዮጵያዊያን ድግስ ላይ እጅግ ተደስቶ ቆየ” ይላል።

ከክርስቶስ ልደት በፊት በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት ላይ የነበረው የግሪኩ ሊቅ ዲዎደረስ ሲክለስ ሲፅፍ፣ ኢትዮጵያዊያን አማልክቶች ሁሉ የሚገዙላቸው፣ እንደውም የአማልክቶች ሁሉ ፈጣሪና አዛዥ መሆናቸውን ሁሉ ዘርዝሮ ጽፏል።

የቤዛንታይኑ እስጢፋኖስም “በአማልክት ማምለክን የጀመሩ እና ያስፋፉ ኢትዮጵያዊን ናቸው” በማለት እንደፃፈም ተገልጿል። ከዚሁ ከእስጢፋኖስ ጋር ዘመንተኛ የነበረው ላክታኒሻስ ፕላሲደስ የተሰኘ ሌላ ደራሲ ይህንኑ ኀሳብ በማጐልመስ የሚከተለውን ጽፏል።

“አማልክት ኢትዮጵያዊያንን የሚወዱበት ምክንያት ፍትሀዊ ስለሆኑ ነው። ፍትሀዊነት የእኩልነት ባህልና ሀቀኝነት ስላላቸው ጁፒተር ከሰማየ ሰማያት ተነስቶ ወደ ኢትዮጵያዊያን እየሄደ ከነርሱ ጋር መዝናናት ያዘወትራል ሲል ሖመር እንኳ ሳይቀር ጽፏል። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊያን ከማንኛውም ህዝብ የላቀ ፍትሐዊነት ስላላቸው አማልክቱ ከተከበረ መኖሪያቸው እየወጡ እነሱን መጐብኘት ያዘወትራሉ።” ብሏል።

ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በዚህ Greater Ethiopia በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደሚያወሱት ኢትዮጵያዊያን ፍትሃዊ እና ሃይማኖት አጥባቂዎች እንደሆኑ ጥንታዊ ፀሐፊያን መግለፃቸውን አፅንኦት ሰጥተው ፅፈውበታል።

በሦስተኛው ምዕት ዓመት ኢትዮፒካ በሚል ርዕስ ሄሊዮዶሩስ የተባለው ደራሲ በፃፈው ልቦለድ ውስጥ የቀረቡት ገፀ-ባህርያት በሃይማኖታቸው የበቁ እና ወደ ፅድቅ መንገድ ላይ ያሉ ነበሩ። ይህንን የፅድቅ ኀሳብ በመከተል ይመስላል ሳሙኤል ጆንሰን የተባሉት ደራሲ ራሴላስ በተሰኘው መፅሐፋቸው ውስጥ የቀረበውን ኢትዮጵያዊ መስፍን ሐቀኛ፣ ቅን እና የበጐ ምግባሮች መፍለቂያ አድርገው የሳሉት።

በእስልምናው ዓለምም ኢትዮጵያ ገናና ሀገር ሆና ትጠቀሳለች። የዓለም ሙስሊሞች ባብዛኛው ኢትዮጵያ የተከበረች እና በነብያቸውም የምትወደድ የሰላም ምድር መሆኗ ይነገራል። ለምሳሌ ሲራ በሚል ርዕስ ስለ ነቢዩ መሐመድ የሕይወት ታሪክ ያዘጋጀው ኢብን ሒሻም የፃፈው በዋቢነት ይጠቀሳል። እንደ እርሱ ገለፃ፣ “ቁራይሽ” የሚሰኙት የመካ ገዢዎች የነብዩ መሐመድን ተከታዮች እያሳደዱ ቢያስቸግሩዋቸው፣ ለተከታዮቻቸው የሚከተለውን ምክር እንደለገሷቸው ሲራ በተሰኘው ጥንታዊ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፤

“ወደ ሀበሻ ሀገር ብትሄዱ፣ በግዛቱ ማንንም የማይጨቁን ንጉሥ ታገኛላችሁ። ያቺ ሀገር የጽድቅ ሀገር ናት። ፈጣሪ አሁን ካለባችሁ ስቃይ ሁሉ የሚያሳርፋችሁ እዚያ ብትሄዱ ነው”

አስደናቂዋ የንጉሥ ሀገር

በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ታላላቅ ነገስታት በልዩ ልዩ ደራሲያን ሥራዎች ውስጥ ተጠቅሰዋል። ለምሳሌ ፐሊኒ /Pliny/ የተባለው የጥንት ፀሐፊ ኢትዮጵያ እና ነገስታቶቿ ኃይለኞች እንደሆኑ፣ እስከ ትሮጃን ጦርነቶች ድረስ ዝነኛ እና ገናና እንደነበረች ጽፏል።

በሦስተኛው ምዕተ ዓመት አካባቢ የነበረው ማኒ የተባለው ፀሐፊ፣ በዚህች ፕላኔት ላይ ካሉ ሃያላን መካከል አክሱም (ኢትዮጵያ) ሦስተኛ ነች ብሎ ጽፏል። የቀዳማዊ ጀስትን ተከታይ ደስትያን ከ (527-567) ፋርስን ለመቋቋም አርዳታ ፈልጐ መልዕክተኞቹን ወደ ኢትዮጵያ ልኳል። ከነኚህ መልዕክተኞች ውስጥ አንዱ ቡድን የኢትዮጵያን ቤተ-መንግሥት ሲያደንቅ እንዲህ ብሏል ይላሉ ፕ/ር ዶናልድ ሌቪን፤

“የኢትዮጵያ ንጉሥ የወርቅ ቅብ ጦርና ጋሻ ባነገቡ መማክርት ታጅቦ አራት ዝሆኖች የሚስቡት፣ በወርቅ የተለበጠ ባለ አራት እግር መንኰራኩር ሰረገላ ላይ ተቀምጦ፣ ህዝቡን ይቀበላል”

አረመኔዋ ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያን እየካቡ የፃፉ በርካታ ደራሲያን የመኖራቸውን ያህል ያንጓጠጡ እና መጥፎ ብዕራቸውንም ያነሱ አሉ። ከእነዚህም አንዱ ዴዎደረስ የተባለ ፀሐፊ ነው። እሱም ሲፅፍ “ኢትዮጵያዊያን በአባይ ወንዝ በስተደቡብ በወንዙ ግራና ቀኝ ሰፍረው የሚገኙ አሉ። ፍፁም አውሬዎች ስለሆኑ የዱር አውሬን ተፈጥሮ ያሳያሉ። ገላቸው ጭቅቅታም ነው። ጥፍራቸው እንደ አውሬ ጥፍር እንዲተልቅ ያደርጉታል። ሰብአዊ ልግስና በመካከላቸው የለም። በሌላ ሥፍራ ያለው የሰው ዘር እንደሚያደርገው ለሥልጣኔ ህይወት የሚሰሩ ተግባሮችን ሲፈፅሙ አይታዩም” ብሏል።

ሌሎች የላቲን የጂኦግራፊ ሊቆች እነ ፕሊኒ፣ እነ ሶሊነስ፣ እንዲሁም ፖምፓኒያስ ሜላን ስለ ኢትዮጰያ ከእውነት የራቀ አስቀያሚ ነገር ጽፈዋል። ይሁን እንጂ በ1520 እ.ኤ.አ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ስድስት ዓመት ቆይቶ፣ ዞሮ ታሪክ የፃፈው ፖርቹጋላዊው ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ኢትዮጵያ በዚያን ዘመን ከአውሮፓ ሀገራት ጋር ያን ያህል ልዩነት እንደሌላት ፅፏል።

በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የአባይን መነሻ ለማጥናት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ጀምስ ብሩስ በፃፈው መፅሐፍ ኢትዮጵያዊያን አንድ በሬ በቁሙ እያለ ከነህይወቱ ከላዩ ላይ ሙዳ ሥጋ እየቆረጡ እንደሚበሉ ጽፏል። ይህም ጽሁፍ ስህተት ነው። ጀምስ ብሩስ “መጽሐፈ ሄኖክ” የተሰኘው የብራና ጽሁፍ ወደ ሀገሩ ስኰትላንድ ሰርቆ ይዞ ሄዷል። ኢትዮጵያ በነበረበት ጊዜም ጐንደር ውሰጥ የእቴጌ ምንትዋብን ልጅ አስቴርን አግብቶ ቤተ-መንግስት ውስጥ ይኖር ነበር።

ሌሎችም ደራሲያን ኢትዮጵያ ያልሰለጠነች፣ የጨካኞች ሀገር እንደሆነች በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ፃፉ። ይህ ደግሞ ከአውሮፓ ውስጥ ኢጣሊያ ወደ ኢትዮጵያ መጥታ በቅኝ ግዛት ለመያዝ እንዲያነሳሳት አደረገ። በመጨረሻም ወደ ኢትዮጵያ ዘምታ በ1888 ዓ.ም ላይ በአድዋ ጦርነት ኢጣሊያ ብቻ ሳትሆን ነጭ የተባለ ዘር ሁሉ ትልቅ ሽንፈት ደረሰበት። ያልሰለጠነች ብለው ገምተው የዘመቱባት ኢትዮጵያ በግማሽቀን ጦርነት ድባቅ መታቻቸው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ምድር

በኢትዮጵያ ላይ በልዩ ልዩ መንገድ የሚፃፈው ሁሉ በነጮች መዳፍ ውስጥ አላመግባቷን ነው። ዲወደረስ የተባለው ደራሲ ሲገልፅ እንዲህ ብሏል፤

“ኢትዮጵያዊያን በባዕድ ንጉስ ከቶ ተገዝተን አናውቅም፤ በመካከላችን ሙሉ ሰላም ሰፍኖ ነፃ ህዝቦች ሆነን ኖረናል ይላሉ” በማለት ፅፏል።

የ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የታሪክ ሊቅ የነበረው ፖርቹጋላዊው ሉዊስ ኡሬታ “ሐበሻ የሚለው ቃል ትርጉም (በአረብኛ በቱርክና በኢትዮጵያ ቋንቋዎች) የባዕድ ንጉስ ግዛት የማይታወቅ ነፃና ራስ ገዝ ማለት ነው፤ ኢትዮጵያ የምትባለው አገርም ልክ እንደምነግራችሁ ነች” ብሎ ፅፏል።

ኢትዮጵያ ዝናዋ እየጐላ የመጣው የተቃጡባትን ጦርነቶች ሁሉ ማሸነፍ በመቻሏ ነው። ለምሳሌ በ1870 የግብፅን ወራሪ ጦር፣ በ1880 የመሀዲስቶችን ወረራ ማሸነፍ፣ በ1888 የኢጣሊያን ወረራ የውርደት ማቅ ማልበስ፣ እና በሌሎችም የዓለም ትኩረት መሆን ጀመረች።

ኢትዮጵያ በነጮች መዳፍ ስር ለነበሩ የአፍሪካ ሀገራትና ለጥቁር ዘር ሁሉ የነፃነት ሞዴል ሆነች። የናይጄሪያው መሪ ናምዲ አዚክዊ የፃፉትን አቶ ሚሊዮን ነቅንቅ እንዲህ ተርጉመውታል።

“ኢትዮጵያ በዓለም ገፅ ከጠፉ የጥቁር ግዛቶች የተረፈች ብቸኛ የተስፋ ችቦ ነች። የአፍሪካዊያን አባቶችና አያቶች በዚህ አህጉር አቋቁመውት ለነበረው ሥርዓተ መንግሥት ሐውልት ነች። ጓደኞቿ አገሮችና ወራሾቻቸው ከፖለቲካ ታሪክ ገፅ ውስጥ ከተሰረዙ በኋላ ኢትዮጵያ በነፃነት መቆየቷ እጅግ የሚያስደንቅ ነው።”

የጋናው ኑክሩማን፣ የኬንያው ኬኒያታ በኢትዮጵያ ላይ ብዙ ጽፈዋል። የጥቁሮች የነፃነት ተምሳሌት ነች ብለዋል። የዌስት ኢንዲስ ሰው የሆነው ማርክስ ጋርቬይም ኢትዮጵያን እና ንጉሷን ከፍ ከፍ በማድረግ የጥቁሮች መሪ አደረጋት።

ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር የጥቁሮች ተቃውሞ አየለ። እ.ኤ.አ በ1935 ዓ.ም ላይ አፍሮ አሜሪካን በተባለው መጽሔት ላይ W.E.B.D እንዲህ ፃፈ፤ “የኢጣሊያ ወረራ የጥቁር ህዝቦች የታሪክ መታጠፊያ” ብሎ በመሰየም “ነጭ እንዳሰኘው ‘የቀለም’ ህዝቦችን ወግቶና ወሮ የራሱ የሚያደርግበት ጊዜ አከተመ። አበቃ” በማለት የትንቢት ጽሁፍ አቅርቧል።

ኦፖርቹኒቲ የተባለ የጥቁሮች የህይወት ታሪክ ዜና ጋዜጣ የገለፀው እንዲህ ተተርጉሟል።

“ኢትዮጵያ በመላው ዓለም የጥቁር ህዝቦች የመንፈሣዊ አባት አገር ሆናለች። ከባሂያ እስከ በርሚንግሃም፣ ከኒውዮርክ እስከ ናይጄሪያ የአፍሪካ ደም ያለባቸው ሁሉ ከዚህ ቀደም ተሞክሮ በማያውቀው አስተሳሰብ አንድነት ተቆስቆሰዋል” ብሏል።

ጆርጅ ኤድመንድ ሄይንስ የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ እንደፃፈው፤ “ኩሩዋ እና ነፃዋ ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ደም ላላቸው ለጥቁሮች የነፃነት፣ የራስ መቻል፣ ከዘመናዊ ስልጣኔ መልካም መልካሙን የመቅሰምና የንቃተ ህሊና ምልክት ሆናለች” ብሏል።

ለዛሬ ጽሁፌ መነሻ የሆኑኝ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ከዚህ በፊት በአያሌ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያዊ ጥናቶችን አድርገዋል። ከነዚህም ውስጥ እ.ኤ.አ 1996 ዓ.ም The Battle of Adwa, Ethiopia and the Bible (1968) እና  Wax and Gold (1965) ብሎም ሌሎችን ውብ የጥናትና ምርምር ስራዎችን አበርክተዋል።

 

“ሳተናው እና ሌሎች…” በሚል ርዕስ በጋዜጠኛ ደረጀ ትዕዛዙ የተዘጋጀው የአጫጭር ልቦለዶች እና የግጥም ስራዎች ስብስብ ለንባብ በቃ።

በተለያዩ ዘመናት የተጻፉ ስምንት አጫጭር ልቦለዶች እና አርባ አንድ ግጥሞችን ያካተተው ይህ ወጥ ስራ፤ በተለያየ መልኩ የሰው ልጆችን ባህሪያት፤ ማለትም ቅንነትን፣ ክፋትን፣ ትዕግስትን፣ እምነትን፣ ተንኮልን፣ ፍቅርን፣ ጥላቻን  ወዘተ የሚያመላክት ነው። አገራዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮችንም በመጽሐፉ ዳሷል። 

 

በድንበሩ ስዩም

      የኢዲ ስቴላር ትሬዲንግ እህት ኩባንያ የሆነው አሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ከትናንት በስቲያ ሐምሌ ሶስት ቀን 2009 ዓ.ም በተለምዶ ሲ. ኤም ሲ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማህበር ሕንፃ ላይ አያሌ ታዳሚያን በተገኙበት ሥነ- ሥርዓት የሬዲዮ ጣቢያውን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ በጋራ የሰጡት የአሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ መስራችና ባለቤት አቶ እሸቱ በላይ፣ የአሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ እና የሬዲዮ ጣቢያው ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ካሳ አያሌው ካሣ ናቸው።

በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የጣቢያው አመራሮች እንደገለፁት አሐዱ ሬዲዮ በዋናነት የሚሰራባቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች አስረድተዋል። ከነዚህ መካከልም ሬዲዮ ጣቢያው በየሰዓቱ ዜና የሚያቀርብ ሲሆን ስርጭቱም ለ24 ሰዓታት የማይቋረጥ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ አሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ኢትዮጵያዊ በሆኑ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የገለፁት የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ታሪኮች፣ ባህሎች፣ እምነቶች፣ ፍልስፍናዎች፣ አስተሣሰቦች፣ ፖለቲካዊ አመለካከቶች፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ጉዳዬ ብሎ የያዛቸው ስራዎቹ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ ጉዳዮችንም ወደ ኢትዮጵያ ሲተረጎሙ አንዳች ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን ካረጋገጠ በኋላ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።

ኃላፊዎቹ በእጅጉ አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩበት ጉዳይ ሬዲዮ ጣቢያው የሚሠራው ለኢትዮጵያዊያን ስለሆነ “የኢትዮጵያዊያን ድምጽ” ብለውታል። ኢትዮጵያ ያለፈ ታሪኳ፣ አሁን ያለችበት ሁኔታ እና የወደፊቷ ኢትዮጵያ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሬዲዮ ጣቢያ ነው ተብሏል።

ከታዳሚያን የተነሱ ልዩ ልዩ ጥያቄዎቸም በዕለቱ ተነስተዋል። የአሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ኤዲቶሪያል ፖሊሲን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ሲመልሱ፣ አሐዱ ሬዲዮ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ሕግን፣ የሀገሪቱን ልዩ ልዩ ህጎችና ደንቦች በማክበር፣ አለማቀፍ ስምምነቶችን እና የጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባርን መሠረት አድርጎ የተሰናዳ መመሪያ እንዳላቸው አውስተዋል።

ከጋዜጠኞች ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ከተሰጠ በኋላም የአሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ 94.3 FM አደረጃጀቱ ምን እንደሚመስል ጉብኝት ተደርጓል። ሬዲዮ ጣቢያው እጅግ ዘመናዊ በሆነ ቴክኖሎጂ የተደራጀ መሆኑ ይፋ ሆኗል። አሐዱ ሬዲዮ ጣቢያ ከበርካታ ተባባሪ አካላት ጋርም እንደሚሰራ ተነግሯል። በዕለቱ በፅሁፍ የቀረበው ጋዜጣዊ መግለጫም የሚከተለውን ይመስላል።

አሐዱ ሬዲዮ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ በተሰማራው እና የኢዲ ስቴላር ትሬዲንግ እህት ኩባንያ በሆነው ኢዲ ስቴላር ሚዲያ ሴንተር የተቋቋመ፣ ዘርፈ ብዙ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት ነው።

ኢዲ ስቴላር ባለፉት 20 ዓመታት በአገር ውስጥ እና በውጭ አገሮች በልዩ ልዩ ኢንዱስትሪዎች ላይ ተሰማርቶ ካከናወናቸው ሥራዎች ጎን ለጎን፣ ታላላቅ የአደባባይ ላይ ሥራዎችን ሲሠራ የቆየ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ከጅምሩ እንደ ህልም ይዞ ሲንቀሳቀስበት የቆየውን የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን መገናኛ ብዙኃን የመክፈት ዕቅዱን ለማሳካት መንገዱን ሲያመቻች ቆይቷል። ዋነኛ ሥራዎቹንም ከሕዝብ ጋር የሚያገናኙ ድልድዮች ላይ ያተኮሩ እንዲሆኑ በማሰብ ታላላቅ የንግድ ትርዒቶችን አካሂዷል፤ የአገር ውስጥ እና የውጭ ታላላቅ ኢቨንቶችን አስተባብሯል፤ ከአስር ዓመት በላይ የሬዲዮ ፕሮግራም በተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ አዘጋጅቶ ሲያቀርብም ቆይቷል፤ በየተወሰነ ጊዜ የሚወጣ መጽሔትም አሳትሟል።

“አውቶሞቲቭ ጆርናል” የሬዲዮ ፕሮግራም፣ አውቶ ፕላስ” መጽሔት፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ በዐይነቱ የመጀመሪያ እና ብቸኛ የሆነውናኢንተርናሽናል አውቶሞቲቭ ፌር” የተባለው ዓለማቀፍ የንግድ ትርዒት፤ በየጊዜው የሚያስተባብራቸው አውደ ጥናቶች፣ ታላላቅ ጉባዔዎች እና ሌሎችም የመድረክ ዝግጅቶች ኢዲ ስቴላር የመገናኛ ብዙኃንን ሥራ ባህሉ አድርጎ ለመቆየቱም ምስክሮች እና ለአሐዱ ሬዲዮ 94.3 ኤፍ ኤም መንገድ ጠራጊዎች ናቸው። ኢዲ ስቴላር የብሮድካስቲንግ ፈቃድ ያገኘው ዘንድሮ ቢሆንም፣ ለስምንት ዓመታት ያህል የንግድ ሬዲዮ ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

“አሐዱ” በግእዝ ቋንቋ “ቀዳሚ፣ የመጀመሪያ“ የሚል ትርጉም አለው፤ አሐዱ ሬዲዮም እንደ ስሙ በመረጃ፣ በቴክኖሎጂ፣ እና በአቀራረብ ራሱ ቀድሞ፣ አድማጮቹን ቀዳሚ ለማድረግ የሚተጋ የሬዲዮ ጣቢያ ነው።

አሐዱ ሬዲዮ፣ ምንም እንኳን የንግድ ሬዲዮ ቢሆንም፣ በመረጃ እና ዕውቀት አማካይነት፣ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን በማስታወስ እና በማስተዋወቅ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ህይወትን የማጠናከር ኃላፊነትን ወስዷል። የአሐዱ ሬዲዮ ተልዕኮ ለኢትዮጵያዊያን (እና ለመላው የሰው ልጅ) ታማኝ እና ወሳኝ የመረጃ፣ የቁም ነገር እና የመዝናኛ ምንጭ መሆን ነው።

የአሐዱ ሬዲዮ ርዕይ ደግሞ በዘርፉ የልህቀት ማዕከል (Centre of Excellence) መሆን ነው።

ይህንኑ ተልዕኮውን ለመወጣት እና ርዕዩን ለማሳካት ይችል ዘንድ ጣቢያው ሶስት ጠንካራ ምሶሶዎችን አቁሟል፤ እነዚህም ሦስት ምሶሶዎች፡-

1.  በማኅበረሰቡ አኗኗር እና አስተሳሰብ ላይ አወንታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ፣ ደጋግ ኢትዮጵያዊ እሴቶች እንዲከበሩ እና ለቀና ማኅበራዊ ትስስር እንዲውሉ የሚያሳስብ፣ እውነተኛ፣ ሚዛናዊ፣ የሚጠቅም መረጃ፣

2.  ይህንን በጥንቃቄ የተሰበሰበ፣ የተተነተነ፣ እና በጥንቃቄ የተዘጋጀ መረጃ ወደ አድማጭ በላቀ የድምፅ ጥራት ማቅረብ የሚያስችል፣ ዘመኑ የደረሰባቸው የሥልጣኔ ግብዓቶች የተሟሉለት ዘመናዊ የድምፅ መቅረጫ፣ ማቀናበሪያ እና ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂ፤ እንዲሁም

3.  ሐቀኛ እና ሕዝባዊ ፋይዳ ያላቸውን መረጃዎች ሰብስቦ፣ ከግራ ከቀኝ አስተንትኖ፣ በዘመናዊው የሬዲዮ ቴክኖሎጂ መረጃዎቹን አቀናብሮ አየር ላይ የሚያውል የሰለጠነ፣ በሙያው ልምድ ያካበተ፣ አዳዲስ ነገር የመፍጠር አቅም

4.  ያለው፣ ተግባብቶ በቡድን ሊሠራ የሚችል፣ እርስ በርሱ ለመማማር ዝግጁ የሆነ፣ ለሚሠራው ሙያ እና ለሚያገለግለው ሕዝብ ክብር ያለው የሰው ኃይል ናቸው።

በእነዚህ ወሳኝ ምሶሶዎች፡- በመረጃ፣ በቴክኖሎጂ እና ሁለቱን አስተባብሮ ወደ አድማጭ በሚያደርሰው የሰው ኃይል አማካይነት አሐዱ ሬዲዮ፣ በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ በሬዲዮ ሞገዱ አማካይነት፣ ሕዝቡን ከመረጃ እና ከዕውቀት ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል፤ የመዝናኛዎችም አመንጪም ይሆናል።

አሐዱ ሬዲዮ ዘርፈ ብዙ መገናኛ ብዙኃን ለመሆን ባለው ዕቅድ መሠረት፣ ከሬዲዮው ጎን ለጎን ጠንካራ የድረ ገፅ መገናኛ ብዙኃን እያደራጀ ነው። ድረ ገፁ የአሐዱ ሬዲዮን መሠረታዊ ባህርያት ተከትሎ፣ ከድምፅ ባሻገር መረጃዎችን በጽሑፍ፣ በፎቶ፣ እና በቪዲዮ አስደግፎ ያቀርባል፤ የሬዲዮውን ስርጭትም በኢንተርኔት አማካይነት በቀጥታ ያስተላልፋል፤ ተቀናብረው የተዘጋጁ ፖድካስቶችንም ሥርጭቱን በቀጥታ መከታተል ላልቻሉ ተከታታዮች ያጋራል። የአሐዱ ድረ ገፅ መረጃዎችን በፍጥነት ያካፍላል፣ በፍጥነት ያድሳል።

የአሐዱ የማኅበራዊ ድረ ገፅ መገናኛዎች (ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ዩቲዩብ፣ ትዊተር…) የአሐዱን የሬዲዮ እና የድረ ገፅ ተግባራት እንዲያግዙ ተደርገው ተቀርፀዋል። በእነዚህ የአሐዱ ማኅበራዊ የድረ ገፅ መገናኛዎች አማካይነት፣ መረጃዎችን፣ ምሥሎችን፣ ጥቆማዎችን የመስጠት፣ በሕዝብ አስተያየት ላይ የተመረኮዙ ጥናቶችን (polls) የማካሔድ፣ ከሬዲዮው አድማጮች እና ከድረ ገፁ ተከታታዮች ጋር ቀና የሆነ መስተጋብር የመፍጠር አገልግሎት ይኖራቸዋል።

የአሐዱ ሬዲዮ ተልዕኮ እንዲሳካ የሚያግዙን፣ ሌሎች ዕድሎቻችን አብረውን እንዲሠሩ በጥንቃቄ የመረጥናቸው ተባባሪ አዘጋጆቻችን ናቸው። እነዚህ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ልምድ ያካበቱ ድርጅቶች እና ባለሙያዎች ትምህርታዊ እና አዝናኝ ፕሮግራሞቻቸውን አሰናድተው፣ በአሐዱ በኩል ከአድማጮች ሊገናኙ ተዘጋጅተዋል።

አሐዱ ሬዲዮ ቀድመውት እየተደመጡ፣ እየታዩ እና እየተነበቡ ያሉትን መገናኛ ብዙኃን እንደሙያ አጋሮቹ ስለሚቆጥራቸው፣ እና የእነሱ ስኬቶች ለበለጠ ስኬት እንደሚያተጋው ስለሚያምን፣ ምን ጊዜም ቢሆን ከእነርሱ ጋር ተባብሮ ለመሥራት በሩን ክፍት አድርጎ ይጠብቃል፤ የአብረን እንሥራ ጥሪውንም ያስተላልፋል።

 

በጥበቡ በለጠ

      ከሐምሌ 5 ቀን 1942- ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ የሥነ - ግጥም፣ የቴአትር፣ የሥነ-ጽሁፍ ሊቁ ደበበ ሰይፉ የተወለደው በዛሬው ዕለት ግንቦት 5 ቀን ነው። ደበበን በተወለደበት ቀን በፎቶዎቹ እንዘክረው።

 

(ከዛሬ 127 ዓመታት በፊት)

ጆሴፍ ኦርዋልድ እንደታዘበው

ሻለቃ ኢ. እር. ዊንጌት እንደዘገበው

(Ten Year’s ine Captinvity in the Mahdis’ Camp 1892)

 

በክፍለጽዮን ማሞ (ትርጉም)

ዘመቻ ተክለሃይማኖት

የእንግሊዝን የበላይነት ለመቋቋምና ከረር ያለ ሃይማኖታዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመመሥረት በ1870ዎቹ በሱዳን አንድ ጠንካራ መንግሥት በአልማህዲ መሪነት ተቋቋመ። ንቅናቄው ግብፅን በመቆጣጠር የናይልን ወንዝ እስከምንጩ ድረስ ለመያዝ በመስፋፋት ላይ ለነበሩት እንግሊዞች ትልቅ ስጋት ከመሆኑም በላይ ለኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ እና ለአማራው ንጉሥ ተክለሃይማኖት የእግር እሳት ሆነ። በመሪው በማህዲ ስም ማህዲዝም (አንዳንድ ጊዜም ድርቡሽ) እየተባለ የሚጠራው ይህ እስላማዊ መንግሥትን በወታደራዊ ኃይል ጭምር በአካባቢው ለመገንባት የተጀመረው ንቅናቄ ካርቱምን በመክበብና በማጥቃት እዚያ የነበረውን የእንግሊዝ ባለሥልጣን በመግደል፣ እንደዚሁም የኢትዮጵያን ሰሜናዊ ምዕራብ አካባቢዎች በየጊዜው በማጥቃት ግልጽ ጦርነት አወጀ።

በተለይ ገላባት ላይ ሴቶችና ህፃናትን ጨምሮ በርካታ የእንግሊዝ ወታደሮች በደርቡሾች ተከበው ለረሃብና ለውኃ ጥም በመዳረጋቸው የእንግሊዝ መንግሥት የአፄ ዮሐንስን እርዳታ በመጠየቅ ለእልቂት የተደረጉትን የግብጽና የእንግሊዝ ዜጎች እንዲያስለቅቁላቸውና እንግሊዝም የኢጣሊያ በቀይ ባህርና በዛሬዋ ኤርትራ ስታደርግ የነበረውን ወረራ አቁማ የኢትዮጵያን ምድር ለቅቃ እንድትወጣ እንዲያደርጉ አድዋ ላይ ውል ገቡ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዚሁ በአድዋ ስምምነት መሠረት ወታደሮቹን በመላክ የእንግሊዝን ዜጎች በረሃ ላይ በመክበብ እልቂታቸውን ሲጠብቅ የነበረውን የድርቡሽ ኃይል በመደምሰስ ካስለቀቀ በኋላ በጎንደር በኩል ምጽዋ ድረስ በሰላም ሸኘ። ደርቡሾች የዚህ የገላባትን ጥቃት ለመመለስ ሌላ ዝግጀት በማድረግ ከተማዋን ለመቆጣጠር ጊዜ መጠበቃቸው አልቀረም። ንጉሥ ተክለሃይማኖትም ደርቡ ሽንፈትን በፀጋ እንደማይቀበል ስለሚያውቁ ዝግጅታቸውን አጠናከሩ። ብዙም ሳይቆይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የድርቡሽ ሠራዊት ለውጊያ የተሰናዳ መሆኑመረጃ ደረሳቸው።

ንጉሥ ተክለሃይማኖት 20‚000 ፈረሰኞችን ጨምሮ ወደ 100‚000 የሚጠጋ ሠራዊት መርተው ማህዲስቶችን ለመግጠም ጋራ ሸንተረሩን አቋርጠው ገላባት (መተማ) ወረዱ። የማህዲዝምን ኃይል የተሞላበት አገዛዝ በመቃወም የካዱ በርካታ ታላላቅ የጦር መሪዎች የንጉሥ ተክለሃይማትን ሠራዊት ተቀላቅለዋል። የገላባትን ምሽግ አጠናክሮ የያዘው ዋድ አርባብ የተባለው የጦር አዛዥ የተክላሃይማኖትን ዘመጫ በሰላዮች አማካይነት ይከታተልና በየጊዜውም መረጃ ይደርሰው ነበር። ይህ የውጊያውን መጀመር በንቃት ይጠባበቅ የነበረ የዋድ አርባብ ጦር የውጊያ ልምድን ያዳበሩ 16‚000 ተዋጊዎችን ያደራጀ ኃይል ነበር።

የንጉሡ ሠራዊት በተለይ ፈረሰኛው ምድብ በሙሉ ወኔና ጀግንነት የድርቡሽን ምሽግ ጥሶ መግባት ጀመረ። ድርቡሾች ወደ ኋላ ማፈግፈግ፣ ሀበሾቹም ማጥቃትና ድል በድል ላይ መጎናፀፍ ቀጠሉ። የገላባት ከተማ በእሳት ነደደች። በበረሃማው አውሎ ነፋስ የተባባሰው የእሳት ንዳድ እየዘለለ የድርቡሾችን የጥይት መጋዘን አቃጠለ። በቃጠሎው የፈነዳው የጥይት ባሩድ በሽሽት ላይ የነበረውን የማህዲስት ቶር እየተከታተለ አነደደው። የንጉሥ ተክለሃይማኖት ሠራዊት ከጦርነቱ ወላፈን የተረፉትን ሴቶችና ህጻናት እንዲሁም ሰላማዊ የሱዳን ዜጎች በምርኮ በመሰብሰብ ይዟቸው ሄደ። ገላባትን ምድረበዳ በማድረግ አገሩ ገባ።

ይሁን እንጂ ከዚህ ውጊያም በኋላ ድርቡሾች ወጣ ገባ እያሉ በንፁሃን ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በቤት ንብረታቸው ላይ ወረራ መፈፀማቸውን አላቆሙም።

ከአልማህዲ እረፍት በኋላ የድርቡ መንግሥት መሪ የነበረው ኸሊፋ አብዱላሂ በሐምሌ ወር 1880 ዓ.ም (ጁላይ 1887 እ.ኤ.አ.) ለአፄ ዮኝስ አንድ ደብዳቤ ላከ። ደብዳቤው የሰላም ጥሪ ያዘለ ሲሆን በኢትዮጵያና በሱዳን መንግሥታት መካከል እርቀ ሰላም እንዲወርድ አፄ ዮሐንስ የሚከተሉትን ሶስት ጉዳዮች እንዲፈፀሙ በቅድመ ሁኔታነት ይጠይቃል።

አንደኛ ፡- አፄ ዮሐንስ እስልምናን እንዲቀበሉ፣

ሁለተኛ፡- በንጉሥ ተክለሃይማኖት ሠራዊት የተማረኩት ሴቶችና ህጻናት እንዲመለሱ፣

ሦስተኛ፡- በማህዲ አገዛዝን በመቃወም ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፉት ዋና ዋና የጦር አዛዦች ተላልፈው እንዲሰጡ።

አፄ ዮሐንስ ለደብዳቤው ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ዝምታን መረጡ።

ወራት እንደ ቀናት ነጎዱ። ኸሊፋ አብዱላሂ የገላባትን ጥቃት ለመበቀል ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት መግጠም ጊዜው ደርሶ እንደሆነ ጦር አለቆቹን በመሰብሰብ ምክክር ጀመረ። ውሳኔው ግልፅ ነበር። ጦርነቱ ሳይውል ሳያድር እንዲጀመር አብዛኞቹ የድርቡሽ ጦር አዛዦች ተስማሙ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ግዙፍ የጦርነት ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸው በድርቡሾች ሰፈር ተሰማ። ይህ ዜና ኸሊፍ አብዱላሂ ለዘመቻው ይበልጥ ቆርጦ እንዲነሳ አደረገው። የእህቱን ልጅ አቡ አንጋን የዘመቻው መሪ አድርጎ ሾመው። ኸሊፋ ሠራዊቱን ባርኮ ሲሸኝ ከፍ ባለ ድምጽ እያንዳንዱ የማህዲስት ተዋጊ ለማህዲ እምነት ካለአንዳች ፍርሃት እንዲዋደቅ ያደረገው ንግግር ሠራዊቱን በጠቅላላ በእንባ አለበሰው። ከጥንተ ታሪክ ጀምሮ በወታደራዊ ኃይሏ ከግብጽ ይልቅ ጎልታ የምትታየውን ኢትዮጵያን እንደዚህ በመሰለ ጦርነት ማሸነፍ የተለመደ ባለመሆኑ ኸሊፋው እየደጋገመ ልብን በሚቀሰቅስ ንግግሩ ሠራዊቱ በቁርጠኝነት እንዲዋጋ ተማፀነ።

የውጊያ አመራሩን ከኸሊፋ የተረከበው አቡ አንጋ 81‚000 ተዋጊዎችን በመምራት ሀገሪቱን ወረረ። የድርቡሽ ጦር የኢትዮጵያን ጋራና ሸንተረር በማቆራረጥ በርካቶች በድካም መንገድ ላይ የቀረቡትን ረዥም ጉዞ ለመጓዝ የሰሜን ምዕራብ ወረዳዎችን በቁጥጥሩ ሥር አደረገ። ፈጣሪ ለኢትዮጵያ የሰጠውን በረከት በየመንገዱ ወረረ። ሱዳኖች ምን ጊዜም እንደ ዕፁብ ድንቅ ምድር የሚያዩአትን ሀገር በተፈጥሮ ፀጋዋን በመልካምነቷ ይበልጥ እየተገረሙ የገበሬውን ሴት፣ ሚስትና ንብረት ይፈሩ።

የንጉሥ ተክለሃይማት ሠራዊት ደምቢያ (ሳር ውኃ) ላይ መሽጓል። ደምቢያ ከመተማ (ከገላባት) በስተምሥራቅ በስድስት ቀናት የእግር መንገድ ርቀት ላይ ይገኛል። ተክለሃይማኖት ከደምቢያ ምሽጋቸው ላይ ሆነው የአቡ አንጋን ጦር መምጣት በትዕግስት ይጠባበቃሉ።

አቡ አንጋ ደምቢያ ላይ እንደደረሰ ሠራዊቱን ለውጊያ በማነቃቃት፣ በዋና ዋና የጦር አዛዦች የአራት ማዕዘን ዙሪያ መሀል ሆኖ ውጊያውን ለማስጀመር ተቃርቧል። ውጊያው ተጀመረ። ድርቡሾች ወደ ሀበሾቹ ሠፈር መገስገስ ጀመሩ። የሀበሾቹ ሠራዊት ብዛት እንኳን በጦርነት በዓይን እይታም የሚያልቅ አይመስልም።

የንጉሥ ተክለሃይማኖት ሠራዊት ግንባሩን ለአረር ደረቱን ለጦር አጋልጦ እየሰጠ የመጣበትን ወረራ ማጥቃት ጀመረ። በድፍረት ክብራቸውን ለማዋረድ የተነሳባቸውን ጠላት ለመመከት የአንበሳ ሞት ለመሞት በጀግንነት ተዋደቁ። በተለይ ፈረሰኛው ተዋጊ ለነፍሱ ሳይሳሳ የድርቡሽን ምሽግ መሀል ለመሀል ሰንጥቆ በመግባት አርበኝነቱን አስመሰከረ።

ሆኖም ድርቡሾች በተለይ ትኹሪሮቹ (ጥቋቁሮቹ) ተዋጊዎች እንደወትሮው ሁሉ ልዩ የውጊያ ስልታቸውን አሳዩ። በታጠቁት የጦር መሳሪያ የኢትዮጵያዊያንን ደም አፈሰሱ። በዚህ ያልተበጉሩት ሀበሾች ግን የድርቡን ጠንካራ ምሽግ ለመስበር አሁንም ወደፊት እያሉ ተዋጉ። ዞሮ ዞሮ የድርቡሾች የበላይነት እርግጥ እየሆነ ሄደ። የንጉሡ ሠራዊት በድርቡሾች እጅ ገብተው ስቃይና ውርደትን ከማየት ጦርነቱ ማብቃቱ እርግጥ ሆኖም እያለ እስከመጨረሻው ድረስ በያዙት ሁሉ እየገደሉ መሞትን መረጡ።

በደምቢያ ጦርነት ድርቡሾች ሊያሸንፉ የቻሉባቸው ሦስት ዋና ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል።

አንደኛ፡- ጠንካራ ወታደራዊ ዲሲፒሊን ማለትም የእርስ በእርስ መናበብና ቅንጅት፣

ሁለተኛ፡- የሠራዊቱ አሰላለፍ (ስትራቴጂ) የበላይነት፣

ሦስተኛ፡ የተሻለ የጦር መሣሪያ፣

በዚህ ዐውደ ውጊያ አብዛኞቹ የንጉሥ ተክለሃይማኖት ምርጥ የጦር አዛዦች ተሰውተዋል። በድርቡሾቹ እጅ ከተማረኩት መካከል ወደገላባት የተወሰዱት ወንድ ልጃቸው ይገኙበታል።

ከድሉ በኋላ ድርቡሾች የንጉሡን የጦር ሰፈር ወረሩት። በርካታ የጦር ሜዳ ድንኳኖች፣ የጋማ ከብቶች፣ እና ሁለት መድፎች ከእጃቸው ገቡ። የጋማ ከብቶች ብዛት ከቁጥር በላይ ስለነበረ እነሱን እየነዱ የስድስት ቀናት ጉዞ ከሚጓዙ እንስሶቹን አንገታቸውን በመቁረጥና በማቃጠል ግፍ ፈፀሙ።

ወደ ቀደምትዋ የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ጎንደር የሚወስደው መንገድ አሁን ለድርቡሽ ሠራዊት ወለል ብሎ ታየው። አቡ አንጋ ጎንደር ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብትና ንብረት አገኛለሁ ብሎ በጥድፊያ ገሰገሰ። ከጦር ሜዳው የ50 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት ተጉዞ ጎንደር የገባው የድርቡሽ ጦር ስንጥር ሳያስቀር ከተማዋን መዘበረ። ከዝርፊያ በኋላ ከተማዋን በእሳት አቃጠለ። ቤተክርስቲያኖች ተዘረፉ፣ በእሳትም ጋዩ። ካህናትም ከየተደበቁበት እየተያዙ ከጣሪያ ላይ እየተወረወሩ ተገደሉ። የጎንደርና የአካባቢዋ ነዋሪ ሕዝብ ተጨፈጨፈ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ህጻናት ለባርነት ተጋዙ።

 

ሰሚ ያጣ የሰላም ጥሪ

  አቡ አንጋ በንጉሥ ተክለሃይማኖት ላይ ያገኘውን ድል ተከትሎ በኢትዮጵያ ሰሜን ምዕራብ ወረዳዎች የሚኖሩት ማህበረሰቦች እስልምናን ተቀበሉ። አቡ አንጋ ውጊያ የተካሄደባቸውን ሥፍራዎች ካረጋጋ በኋላ ከሊፋ አብዱላሂ ወደነበረበት ጊዜያዊ አምድሩማን ቤተመንግሥት ጉዞ ጀመረ። በዚህ ጊዜ ነበር ከሊፋ ከኢትዮጵያው ንጉሠ- ነገሥት በብራና ላይ በአማርኛ ቋንቋ የተፃፈ ደብዳቤ የደረሰው። አምድሩማን ውስጥ ይኖሩ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን ዓረብኛን የሚያቀላጥፉ ሁለት ሰዎች ለአስተርጓሚነት ተጠርተው ቀረቡ።

ለድርቡሹ መሪ ከአፄ ዮሐንስ የተላከው ደብዳቤ የሚከተለውን ያዘለ ነበር።

 

ይድረስ ለወንድሜ ኸሊፋ አብዱላሂ፣ ለጤናዎ እንደምን ሰንብተዋል። በሁለታችንም ሕዝቦች መሀል የገባውን ጠብ ለማብረድና ሚዛናዊ እርቀ ሰላም ለማድረግ ከልብ የፈለቀ ፍላጎቴን ልገልፅልዎት እወዳለሁ።

የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ከአንድ ከሀም የዘር ሐረግ የመጣን ወንድማማቾች ነን። በአሁኑ ጊዜ ማቆሚያቸው የት እንደሆነ የማይታወቅ ፈረንጆች እርስዎንም እኔንም እየከበቡን ነው። ፍጥነታቸውም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይገኛል። የኢትዮጵያና የሱዳን ሕዝቦች ወንድማማችነትና ጉርብትና እነዚህን ባዕዳን ለመከላከል እንጂ እርስ በእርስ ጦርነት ልናውለው አይገባንም።

ከሊፋ አብዱላሂ ለአፄ ዮሐንስ የሚከተለውን ምላሽ ላከላቸው።

 

 

ይድረስ ለዮሐንስ

የላከው ደብዳቤ ደርሶኝ ተረድቼዋለሁ ያቀረብከው የሰላም ጉዳይ እርቁ የሚወርደው ማተብህን በጥሰህ ሰላምታ የምትሰጠኝ እንደሆነ ነው። ሃይማኖቴን የምትቀበል ከሆነ አንድ ሆነናልና መልካም ወዳጅነት ሊኖረን ይችላል። ለዚህ ዝግጁ ካልሆንክ ግን የፈጣሪም የነቢይም ወዳጅ አይደለህምና አንተን ለመደምሰስ ግዴታ አለብኝ። ይህን ከማድረግም ሌላ አማራጭ የለኝም።

የተጀመረው የወንድማማቾች ጦርነት አንዱ ሌላውን እስካላጠፋ ድረስ የማይበርድ መሆኑ እርግጥ ሆነ።

 

ዘመቻ ዮሐንስ

  አፄ ዮሐንስ ገላባትን፣ ብሎም አምድሩማንንና ካርቱምን በመያዝ የድርቡሽ መንግሥት ለመገርሰስ ዝግጅት መጀመራቸው ሱዳን ውስጥ ጭምጭምታ ተሰማ። ዮሐንስ በዋነኞቹ የጦር መሪዎች በእነ ራስ አርአያ ድምፁ፣ ራስ ሚካኤል (መሐመድ አሊ)፣ ራስ ኃይለማርያም ጉግሳ፣ ራስ አሉላ፣ ስልሕ ሻንቆ እና ሌሎችም ታላላቅ የጦር አዛዦች የሚንቀሳቀሱ ክፍለ ሠራዊቶችን በመምራት በቅድሚያ ገላባትን ለመዝመት ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸው ወሬው ተናኘ። 20‚000 ፈረሰኞችን ጨምሮ ከ150‚000 በላይ ሠራዊት መርተው አፄ ዮሐንስ ገላባትን ለማጥቃት ዕቅድ እንደነደፉ የድርቡሽ ሰላዮች ዝርዝር መረጃውን ለድርቡሽ መሪ አቀረቡ።

ዜናው ገዝፎ በተሰራጨ መጠን ገላባትም ሆነ አምድሩማን በሽብርና በጭንቅ ይናጡ ጀመር። ለእኛ በማህዲው ምርኮ ሥር ላለነው የውጭ ዜጎች ግን የኢትዮጵያ ሠራዊት መምጣት ታላቅ የተስፋ ብርሃንን ፈነጠቀልን።

የገላባቱ ምሽግ ዋና አዛዥ ሸክ በኪ ጡማል በመምጣት ላይ ያለውን ጠላት ከምሽግ ውስጥ ሆኖ መዋጋት ወይስ ገና ከመንገድ ላይ መቁረጥ የትኛው እንደሚሻል አማካሪዎቹን አወያየ። ካለምንም ማወላወል ምሽጋቸውን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ዘዴ መሆኑ እርግጥ ነበር። እንደማዕበል የሚነጉደውን የኢትዮጵያ ሠራዊት ከምሽግ ወጥቶ መመካት የማይታሰብም የማይሞከርም ነበር።

ዮሐንስን ለመግጠም የተመደበው የዘኪ ጥምር ጦር 80‚000 ደርሷል። ከቁጥሩ በላይ ጦሩ ምሽጉን አጥብቆ በመያዝ የመጣበትን ጦር ለመመከት ቁርጠኛ ነበር። አዋጅ ነጋሪዎች በገጠር በከተማው እየዞረ ሱዳናዊ ሁሉ የዕለት ተግባሩን ትቶ ጠብመንጃውን አንግቶ፣ ጎራዴውን ታጥቆ አገሩን እንዲከላከል የመሪአቸውን ትዕዛዝ አሰሙ። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የዘመቻ ዝግጅት ከተነገረው በላይ ተጠናክሮ መቀጠሉን የድርቡሽ ወታደራዊ ምንጮች ገለፁ። እነዚህ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት መረጃዎችን ያሰባሰቡ የነበሩ ሰላዮች የኢትዮጵያን ሠራዊት እንቅስቃሴ በሚከተለው መልክ አቀረቡት።

“የሀበሻ ሠራዊት እንደሰማይ ከዋክብት እንደባህር አሸዋ ህልቆ መስፈርት የለውም። ሠራዊቱ ሲርመሰመስ ለዓይን እይታ የሚታክት፣ መጨረሻው ከአድማስ ባሻገር የሆነ፣ የዘመቻው ንቅናቄ በሚያስነሳው ምድራዊ ደመና ጸሐይን ያጠቆረ አስፈሪ ኃይል ነው።”

ይህ ደማቅ ወታደራዊ ዘገባ የድርቡሾች ዋና ከተማ አምድሩማንን ከወዲህ ወዲያ በሽብር አናወጣት። ከዕለታት አንድ ቀን ሱዳን በሀበሻ እንደምትተፋ፣ የንጉሡ ፈረስም ኮቴው በፈሰሰው ደም ተውጦ፣ እንደ ወሬ ነጋሪ ከጥፋት በተረፈችው አንዲት ዛፍ ጥግ ታስሮ እንደሚታይ እንደ ትንቢት የሚነገረው አፈ -ታሪክ ጊዜው መድረሱና ትንቢት የተነገረለት የሀበሻ ንጉሥ ዮሐንስ እንደሆነ ትንቢት ተናጋሪዎች አስረዱ።

በ1881 ዓ.ም ወርኀ የካቲት መጨረሻ ላይ ንጉሠ ነገሥቱ ጎንደር ከተማን ለቅቀው በመውጣት ሕዝብን ለማጥፋት የተነሳውን ቁርጠኛ ጠላት ለመደምሰስ ሠራዊታቸውን በረድፍ በረድፍ አስከትለው ወደ ገላባት ተመሙ። እስከተማዋ አቅራቢያ እንደደረሱ “እንደሌባ ተሸሎክሉኮ መጣ” እንዳትለኝ ለፊልሚያው ተነስቻለሁና ተነስ፤ ሲሉ ለድርቡሹ አዋጊና የጦር አዛዥ መልዕክት ሰደዱለት፣ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ከወንዶቹ ሌላ በርካታ ቁጥር ያላቸው ወይዛዝርት አብረው ተሰልፈዋል። እነዚህ ሴት ዘማቾች የትዳር ጓደኞቻቸውን፣ የእጮኞቻቸውን፣ የወንድሞቻቸውንና የአባቶቻቸውን የሞትና የመከራ ጽዋ ለመቅመስ ኑሮአቸውን በትነው፣ ጎጆአቸውን ዘግተው ወደ ጦር ሜዳ የዘመቱ ናቸው።

በቅዳሜ መጋቢት 1 ቀን 1881 ዓ.ም አፄ ዮሐንስ የገላባትን ምሽግ ማጥቃት ጀመሩ ሠራዊታቸው መሪውን እየተከተለ ከምሽጉ ውስጥ በፉከራና በቀረርቶ እየዘለለ ገባ። ከጦር አውድማው የሚነሳው አቧራ አውሎ ነፋሱ ብድግ ሲያደርገው እሽክርክሪት እየሰራ በውጊያው መሀል ሰይጣናዊ ጭፈራውን አቀለጠው። ከወዲያም ከወዲህ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለዘመን ፍጻሜ የሚዋደቁት ወታደሮች አንዱ ሌላውን ለመለየት በማይቻልበት ሁኔታ የሞትና የመከራው ብዛትና ጥልቀት የቀኑን ብርሃን ጽልመት አለበሰው። ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ ጦርነቱ መሀል ገብተው ሲዋጉ ያየው የኢትዮጵያ ወታደር መንፈሱ በአንዳች ወኔ እየተፈነቀለ ግስጋሴውን ቀጠለ። የድርቡሾች ጠንካራ ምሽግ መላላትና መሳሳት ጀመረ።

ከድርቡሾች ሰይፍና የጥይት አረር ይልቅ የኢትዮጵያ ጦር የከበደው ነገር በአገር ምድሩ የበቀለው እሾህማ ጥቅጥቅ የቆላ ግራር ነበር። ለድርቡሾች ተደራቢ ምሽግ ሆነላቸው። ሀበሾቹ ግራሩን ግራ ቀኝ ረግጠው እየዘለሉ፣ አንዳንድ ጊዜም እያቃጠሉ ወደ ዋናው የድርቡሽ ማዘዣ ጣቢያ ዘልቀው ለመግባት ሲዋጉ የድርቡሽ ሠራዊት አጋጣሚውን በመጠቀም ጥይቱን አርከፈከፈው። በዚህ የትንቅንቅ ሰዓት ነበር ከማህዲ ሰፈር አምልጠው ለኢትዮጵያ ሠራዊት እጃቸውን የሰጡ ትኹሪሮች (ደቡብ ሱዳናውያን) ጠቃሚ መረጃ የሰጡት። በድርቡሾች የጦር ሰፈር “ደካማው የውጊያ ግንባር” ዋና አሊ ራሱ በሚያዋጋበት ግንባር በኩል መሆኑን ምርኮኞቹ ተናገሩ። የኢትዮጵያ ሠራዊት አብዛኛው ኃይሉን ወደ ሾክ ዋድ አሉ የጦር ግንባር በማዞርና በመረባረብ ለመጨረሻው ድል የሞት ሽረት ውጊያውን አፋፋመ።

 

ዋይታና እልልታ

  በሁለቱም ወገን ከተከፈለ ከባድ የሕይወት መስዋዕትነት በኋላ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደ ውቅያኖስ ማዕበል እያስገመገመ ከፊት ለፊቱ የቆመውን ሁሉ እየደመሰሰ የደርቡሾችን ወታደራዊ እምብርት ዘልቆ በመግበት የበላይነቱን ተቀዳጀ። ድልን ጨብጦ በመገስገስ ላይ የነበረውን ኃይል በተመለከቱ ጊዜ ከኋላ ሆነው ግፋ በለው እያሉ እልል ሲሉ የዋሉት በሺዎች የሚቆጠሩ የድርቡሽ ሴቶች ልብ የሚነካ እዬዬና ዋይታ ያሰሙ ጀመር። የኢትዮጵያ ጦር አሁንም ማጥቃቱን በመቀጠልና ያገኘውን ድል በማጠናከር የድርቡሾችን ምሽግ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ። ይህ ግስጋሴ ሀበሾችን ወደ ፍፁም ድል በር የሚያደርሰው ወሳኝ እርምጃ ነበር።

ጦርነቱ ጠላትን ወገን የማይለይበት፣ ዋይታና እልልታ የተደበላለቀበት፣ የሀም ልጆች በጥፋታቸው እንዲጠፉ ከላይ የታዘዘላቸውን የመከራ ፍርድ የሚፈፀምበት የዘመን ፍፃሜ ይመስል ነበር። የገላባት (መተማ) ጦርነት ከዚያም ከዚህም የሀም ዘሮች እንደ ቅል ቢረግፉም ድል ፊቷን ወደ ዮሐንስ ማዞሯ አጠራጣሪ አልነበረም። ሀበሾች የድርቡሽን የትጥቅና የስንቅ ማከፋፈያ ማዕከልን ተቆጣጠሩ። የጦር አዛዡ አቡ አንጋ ጦርነቱን ይመራ የነበረው ከዚሁ ሠፈር ሆኖ ነበርና የዮሐንስ ወታደሮች የማዘዣ ጣቢያው መደምሰስን ተከትሎ የድርቡሾችን የሬሳና የቁስለኛ ክምር በማገላበጥ የራሱን የአቡ አንጋን አስክሬን ለማግኘት ፍለጋ ጀመሩ። ጎንደር በእሳት ስትጋይ ቃጠሎው እስኪቆም ድረስ ከዳር ቆሞ ሲመለከት የነበረው አቡ አንጋ ከተቻለ ከነሕይወቱ ካልሆነም ሬሳውን በማንደድ የጎንደርን ጥፋት ለመበቀል ነበር የኢትዮጵያውያኑ ምኞት። አቡ አንጋ ግን ሸሽቶ አምልጧል።

ከማዘዣ ጣቢያቸው ሙሉ በሙሉ መደምሰስና ትጥቅና ስንቃቸው በኢትዮጵያ ሰራዊት መማረክ በኋላ የድርቡሾች ወኔ ሟሸሸ። የድርቡሽ ጦር በእጁ የያዘው ጥይትና ሌላ አስፈላጊ የውጊያ መሣሪያ አልቆ መዋጋት በማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ የዮሐንስ ዘማች ኃይል አሸናፊነት እርግጥ ሆነ።

 

የንጉሥ ራስ

ድርቡሾች ተሸንፈው እግሬ አውጭኝ እያሉ በሚሸሹበት ሰዓት ንጉሠ ነገሥት በአንዲት ጥይት ተመትተው መውደቃቸው በኢትዮጵያውያን ሰፈር ተሰማ። ወሬው እንደ እሳት ቋያ እየተቀጣጠለ ጦሩን በጠቅላላ ከወዲያ ወዲያ እያገላበጠ ያንገበግበውና ግራ ያጋባው ጀመር። በድርቡሽ ቆራጥነት ያልተፈቱት ሀበሾች በድል አፋፍ ላይ ቆመው የድርቡሽን ሽሽት አሻግረው በሚመለከቱበት ሰዓት በንጉሠ ነገሥታቸው መመታት ድንጋጤ ጥርጣሬና ተስፋ መቁረጥ ወረራቸው። ከድል በኋላ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ በተተኮሰችው ጥይት ምክንያት የኢትዮጵያውያኑ ሠፈር ተስፋ መቁረጥና ትካዜ ገባበት። ካለ መሪ ካለ አስተባባሪ የቀረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ያፈሰውን የድል አዝመራ ሳይሰበስብ ፊቱን ወደ አገሩ በማዞር ጉዞ ጀመረ። ድል ፊቷን ወደ ኢትዮጵያውያን ብታዞርም እቅፍ ድግፍ አድርገው ስላልተንከባከቧት ድርቡሽን መረጠች። የአፄ ዮሐንስ በጥይት መመታትና የሠራዊታቸውም ማፈግፈግ የሰሙት ድርቡሾች ነገሩ እውነት አልመስል እያላቸው ከየተበተኑበት እየተሰበሰቡ ወደተደመሰሰው ምሽጋቸው መመለስ ጀመሩ። እዚያ ሲደርሱ የሰሙት ሁሉ እውነት መሆኑን አረጋገጡ።

የኃይለኛው የጦር መሪ የዋድ አሊ ክፍለ ሠራዊት ሳይቀር አብዛኛው የድርቡሽ ጦር ከበርካታ የጦር አለቆች ጋር ሙሉ በሙሉ የተደመሰሰ ቢሆንም በአፄ ዮሐንስ መመታትና በሠራዊታቸውም መበተን የመዋጋት ፍላጎታቸው እንደገና ያንሰራራው ማህዲስቶች የለቀቁትን ምሽግ እንደገና በመቆጣጠር በየቦታው የወደቀውን ሙትና ቁስለኛ ኢትዮጵያዊ አንገት እየቆረጡ ለድል ማብሰሪያነት በግመሎቻቸው እየጫኑ ወደ አምድሩማን ላኩ። የገላባቱን ጦርነት አምድሩማን ላይ ሆኖ በጭንቅ ሲከታተል የነበረው የማህዲስቶቹ ጌታ ኸሊፋ አብዱላሂ የሀበሾች ራስ ቅሎች ተደርድረው ሲቀርቡለት አይቶ ኸሊድ አህመድን እጅግ አድርጎ አመሰገነው።

የማህዲስቶች መንፈስ ግን ገና ሙሉ በሙሉ አልተረጋጋም። ሀበሾች ኃይላቸውን አደራጅተው በሁለተኛው ቀን አዲስ ውጊያ ይጀምራሉ ብለው ጠብቀውም ነበር። ቀናት አለፉ ድርቡሾች ተገረሙ። ከኢትዮጵያውያን በኩል የጥይት ድምጽ ፈፅሞ አልተሰማም። የድርቡሽ ሰላዮች የኢትዮጵያውያንን ኮቴ ተከታትለው እንዳረጋገጡት ደግሞ ሠራዊቱ በጠቅላላ በሀዘንና በትካዜ ጉዞውን ወደ ተከዜ አቅጣጫ መቀጠሉን ተረዱ። መረጃው የደረሰው የድርቡሽ ክፍለ ሠራዊት አዛዥ ዘኪ ጡማል ተበታትኖ አገሩ ለመግባት በየአቅጣጫው ይጓዝ የነበረውን የአፄ ዮሐንስ ጦር ተከታትሎ ለመግጠም ወሰነ። የድርቡሽ ኃይል በመጋቢት 11 ቀን 1981 ዓ.ም ተከዜ ወንዝ ላይ ደረሱ። በወንዙ ዳርቻ የሰፈረውን ገና አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ዘማች ጦር ከፊት ለፊት ገጠመው። ውጊያው ተጧጧፈ። በእልህና በቁጭት አዲስ ውጊያ የከፈተው የድርቡሽ ኃይል በመሪው ድንገተኛ ሞት ምክንያት ሰማይ ፈርሶበት ካለ መሪ የቀረውን ሠራዊት ያጠቃ ጀመር። የድርቡሽን የሞት ሽረት ጥቃት መመከት ያልቻለው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከፍተኛ ጉዳት ደረሰበት የተከዜ ወንዝን ለመሻገር በየአቅጣጫው ተበተነ። ድርቡሾች ኢትዮጵያውያን የለቀቁትን ሠፈር ተቆጣጠሩ። ዓይኖቻቸውን የገባው ነገር በስም የታሸገ ረዥም ሳጥን ነበር። ውድ ዕቃ የያዘ መስሏቸው ከፍተው ለማየት ጓጉ። ሳጥኑ የአንድ ረዥምሰው አስክሬን የተኛበት መሆኑን ያወቁት ከፍተው ከተመለከቱ በኋላ ነው። የተራ ሰው አለመሆኑን በቀላሉ ተገነዘቡ። የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አስክሬን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ እዚያ ቦታ ይገኛሉ ብሎ ለመገመት ግን ከማንም ሰው አስተሳሰብ ውጭ ነው። እውነታው ግን ይኸው ነበር። ዘኪ ነገሩን በመጀመሪያ በጥርጣሬ ዓይን ነበር የተመለከተው። በውጊያው የተማረኩት ቁስለኛ ኢትዮጵያውያን ተጠየቁ። በሳጥኑ ውስጥ ያለው አስክሬን የአፄ የዮሐንስ መሆኑን አረጋገጡለት። የዮሐንስ አንገት በሰይፍ ተቆርጦ ለድል ማብሰሪያነት በግመል ተጭኖ ወደ አምድማን ተላከ።

 

የንጉሥ ራስ በአደባባይ

የአፄ ዮሐንስን አንገት የተላከላት አምድሩማን ከተማ በሆታና በእልልታ ተናወጠች። የማህዲስቶቹ መሪ ኸሊፋ አብዱላሂ በመላዋ ሱዳን የድል እንቢልታ እንዲነፋ፣ ከበሮ እንዲደለቅ፣ ተኩሱ እንዲቀልጥና ጎራዴ እንዲያፏጭ አዘዘ። ጎን ለጎን መጠነ ሰፊ ፍለጋ እንዲካሄድ ተወሰነ። ከዮሐንስ በተጨማሪ የሌሎች ታላላቅ የሀበሻ ምድር የጦር ጀግኖች አንገት ተቀልቶ እንደሆነ ለድሉ ተጨማሪ ድምቀት ተፈለገ። የራስ አሉላ፣ የራስ ኃይለማርያም ፣ የራስ ሳልሕ ሻንቆ አንገትም እንዲሁ ተቆርጦ በግመል ኦምድሩማን ገብቷል እየተባለ በስፋት ተወራ። ቀስ በቀስ ግን ወሬው ወሬ ሆኖ ቀረ።

ያም ሆኖ የኸሊፋ አብዱላሂ የደስታ ስሜት ዳርቻ ሊገኝለት አልቻለም። በድርቡሾች ቁጥጥር ስር ገብተን ነፃነት ለተነፈግነው ለእኛ ለአውሮፓውያን ቁም እስረኞች ግን የጭለማ ወቅት ነበር። ነፃነታችን በኢትዮጵያውያን እጅ መሆኑን እናውቅ ነበርና።

የተሰየፈው የዮሐንስ አንገት በግመል ላይ ተጭኖ በሕዝቡ ሆታና እልልታ ታጅቦ በኦምድሩማን ከተማ አደባባዮች እንዲዞር ተደረገ። “ይህን ያየ ይቀጣ” ተባለ “የሱዳኖች ሆታና ጭፈራ ቅጥ አጣ” ኸሊፋ አብዱላሂ በድል ሰከረ።

 

ምርኮ

በምርኮ ከተገኙት የንጉሠ ነገሥቱ ንብረቶች መካከል ሶስት ጊዜ ተለብዶ በብራና ላይ ዘርዘር ተደርጎ በአማርኛ ቋንቋ የተፃፈ አንፀባራቂና አስገራሚ ወንጌል ይገኝበታል። “Crosidi Paris” የሚል ጽሑፍ ያረፈበት የቀናትና የወራት መቁጠሪያ ያለው የወርቅ ሰዓት፣ የጦር ሜዳ መነጽር እና ከንግሥት ቪክቶሪያ ለንጉሠ ነገሥቱ የተላከ ደብዳቤ ትኩረትን የሚስቡ ነበሩ። ከንግሥቲቱ የተላከውን ደብዳቤ ለማንበብ ዕድል አግኝቼለአው የሚከተለውን ቁም ነገር ያዘለ ነው።

 

 

ይድረስ ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ዮሐንስ ራብዐይ። ስለ እርስዎና ስለመላ ቤተሰብዎ ሰላምና ጤና እንደምን ሆነዋል። ታላቋ ብሪታንያ የግብጽ የበላይ አስተዳዳሪ በመሆንዋ የኢትዮጵያ የቅርብ ጎረቤት ልትሆን በቅታለች። ይህ መልካም አጋጣሚ ከግርማዊነትዎ ጋር የዘላቂውን የሰላምና የወዳጅነት ግንኙነት በበለጠ ለማጠናከር ይጠቅመናል የሚል ከልብ መነጨ እምነት አለኝ።

በተረፈ ለግርማዊነትዎ የተሟላ ጤንነት፣ ሰላምና ረዥም እድሜ እመኛለሁ።

 ከንግሥት ቪክቶሪያ የተላከው የወዳጅነትና የመልካም ምኞት መልዕክት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቨሎርድ ሶልሰበሪ ፊርማ አርፎበት ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪ የንጉሠ ነገሥቱ የዘመቻ ድንኳን፣ እንዲሁም በልዩ ልዩ ቀለማት የደመቁ መስቀሎች ተመልክቼአለሁ።

 

የዕድል ድል

የአፄ ዮሐንስ ራስ አንገት በአምድሩማን አደባባይ ለትንግርት ቀርቦ እንደበቃ የዕለቱ እለት በቆዳ ተለብዶ ወደ ደንጎላ (ዳርፉር ግዛት) ከዚያም አልፎ እስከ ግብጽ ድንበር ድረስ በግመል ተጭኖ እንዲወሰድ ግብፆች “ይቅርና እናንተ የዮሐንስ ዕጣ ፈንታም ይኸው ነው” የሚል ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ነው።

የኸሊፋ አሸናፊነት የበላይነትና ማን አለብኝነት ሰማይ ጥግ ደረሰ። የማህዲስም ተከታዮች ፈንጠዝያ እየበረደ ሲሄድ በከተማው ስዟዟር ካየኋቸው ዘግናኝ ነገሮች መሀል የተሰየፉ የሰው ልጆች ራስ ቅሎች ፀጉር እስኪገፈፍ ድረስ በየጉድጓዱ ተከምረው እንዲበሰብሱ መደረጋቸው ነበር። ከድርቡሽ ተቃዋሚዎች መሀል የእነ ሱልጣን ዮሱፍ፣ አቡ ገማዥ፣ ሱልጣን ኢሳና የሌሎች ሱዳናውያን እንደዚሁም የበርካታ ኢትዮጵያውያን ራስ ቅሎች በየጉድጓዱ ተጥለው አላፊ አግዳሚው ሁሉ አፍና አፍንጫውን ከድኖ እንጨት ይሰድባቸዋል። ራቅ ካሉ አካባቢዎች ተይዘው ከነቆባቸው አንገት አንገታቸው የተሰየፉ ካህናትና መነኮሳት በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ተጥለው አይቻለሁ። ሁሌም በዚያ መንገድ በወጣሁ በወረድሁ ቁጥር ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲህ እንደምን ሊጨካከን እንደቻለ መልስ እያጣሁለት መንፈሴ ይረበሽ ነበር።

ይህ ትንግርታዊ ትርኢት የማህዲዝም ኃይል ከየት እስከየት እንደደረሰ በማሳያነት የቀረበ ቢሆንም በጦር ሜዳው ውሎ ላይ እንደቅጠል የረገፉትን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያንን ነፍስ የሚመለስ አልነበረም። የደረሰው ያ እልቂት ያየ ተመልካች ፈጣሪ ሱዳን ላይ ያወረደው መዓት እንጂ በሰው ኃይል የተፈጠመ ነው ብሎ ለመቀበል ይከብደዋል።

የሆነ ሆኖ ለጊዜውም ቢሆን ኸሊፋ አብዱላሂ የምድሪቱ ጌታ ሆኖ መታየቱ አልቀረም። እርሱ ባላቀደው መንገድ እንዲህ ዓይነት ያልተተበቀ ድል መቀዳጀቱ ህልምና እውነት እየተቀላቀለበት “እንዴት ሊሆን ቻለ” እያለ መደመሙ አልቀረም።

በድርቡሽ በኩል የገላባትን (የመተማን) ጦርነት የመሪው ዘኪ ጡማል እንደነበር ከፍ ሲል ገልጸናል። ዘኪ የኸሊፋ አብዱላሂ የቅርብ ዘመድ ነው። ቢሆንም በጦርነቱ ስለደረሰበት ሽንፈት ከፍተኛ ኪሳራና ስለረገፈው ስፍር ቁጥር የሌለው ተዋጊ ዝርዝር በገባ ለመሪው ማቅረብ አልፈለገም። ህዝቡም በዮሐንስ አንገት መሰየፍ ከተሰማው መጠን የሌለው የድርቡሽ ደስታ የተነሳ ስለሠራዊቱ ጉዳትና ኪሳራ ለማወቅም ሆነ ለመጠየቅ ጊዜ አልነበረውም። ከዚህ በላይ መሪአቸውን በሚያሞካሹና ስለአሸናፊነቱ በሚመፃደቁ ሰዎች የተከበበው ኸሊፋ ስለጦር ሜዳው እውነተኛ ውሎ ሊነግረው የሚችል አልነተገኘም። ቢገኝም እንኳ በወታደራዊ ኃይሉ ምድርን ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ያንቀጠቀጠውን የዮሐንስን አንገቱን ቆርጦ በቆዳ ሰፍቶ መተረቻ በሚያደርግበት ወቅት ስለማህዲዝም ውድቀትና ኪሳራ የሚሰማበት ጆሮ አልነበረውም።

 

ዋናው ጠላት

ሱዳን በማህዲስቶች አክራሪነትና ጦረኝነት የተነሳ የገባችበት ቀውስ ለአንድ ዓመት ያህል ሕዝቦችዋ በረሃብ እንዲሰቃዩ አደረገ። የድርቡሾች መሪ ግን በአጋጣሚ ያገኘውን ድል ገና አጣጥሞ ስላላበቃና ስልጣን የማደላደሉ ሥራ ላይ በመጠመዱ የሱዳን ዋና ጠላት ከረሃብ በላይ ሌላ ሊኖር እንደማይችል ገና አልተገነዘበውም። ኸሊፋ ስለአገኘው የበላይነትና አዲሱን የአክራሪነት እምነት ይበልጥ ስለሚያስፋፋበት መንገድ ማሰብ እንጂ አፍጥቶ ስለመጣው የረሃብ ጠላት የሚጨነቅበት ፋታ አልነበረውም፡

ሆኖም መከራ ሁሉንም አስተማሪ ነውና ረሃብ ሕዝቡን እየፈጀው ሲሄድ ኸሊፋም ስሜቱ እየበረደ፣ ፊቱንም ወደ ሕዝቡ ችግር እያዞረ መጣ። ከጦርነቱ ፍፃሜ በኋላ በሁለቱ አገሮች ሕዝቦች የገባው ድርቅና ረሃብ ሁለቱንም ሕዝቦች ለሰላምና ለወዳጅነት ያቀራርብ ጀመር። የቆየ የንግድ ግንኙነታቸውን ቀስ በቀስ እንደገና ማደስ ጀመሩ። የዚህም አገር (የሱዳን) እንዲሁም የዚያ አገር (የኢትዮጵያ) ነጋዴዎች ንግድ ልውውጣቸውን እንደ ድሮው ባይሆንም አለፍ አለፍ እያሉ አካሄዱ።

በነጋዴዎች መካከል የንግድ መስመሮች ቢከፈቱም ድርቡሾች ግን ዛሬም ቢሆን በማህዲስቶች ዘመቻ፣ በረሃብና በርስ በርስ የሥልጣን ሽሚያ የተዳከመችውን ኢትዮጵያ በተከታታይ ከማጥቃት አልቦዘኑም። ኢትዮጵያውያን በርስ በርሱ ቁርቁስ ውስጥ በመግባታቸው ኃይላቸውን እንደገና አደራጅተው በረሃብና በጦርነት የተደከመውን የድርቡሽን ኃይል እንደገና ለመውጋት አልቻሉም።

የሱዳን ምድር ቀስፎ የያዘው ረሃብ እየከፋና እየሰፋ ሄደ። ኢትዮጵያ ጋር ፍጹም ሰላምን መስርቶ የሁለቱም አገራት ሕዝቦች የሚበጃቸውን ማድረግ እንጂ ቂም በቀል ከውድመት በቀር ምንም ፋይዳ የሌው መሆኑ ግልጽ  ሆነ።

እንደ እነ ሼክ አብዱራህማን፣ ዋዲ እና አቢ ደገል የመሳሰሉ ሩቅ አሳቢ የሱዳን አባቶች የችግር ሁሉ ብቸኛ መፍትሄ ንግድ እንጂ ጦርነት አለመሆኑን በየአደባባይ አስተማሩ። ሀበሻና ሱዳን የፈረሰውን የሰላም ድልድይ እንደገና ገንብተው እነሆ እስከዛሬ ባልተቋረጠ ሰላማዊ ጉርብትና አብረው ይኖራሉ።

  

 

በጥበቡ በለጠ

 

ከሐምሌ 21 እስከ 25 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል አመታዊው ንባብ ለሕይወቱ የመፅሐፍት አውደ-ርዕይ ይካሄዳል። በዚህ አውደ-ርዕይ ላይ በርካታ መፅሐፍት አከፋፋዮች፣ ደራሲያን፣ አንባቢያን፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎችም ሠዎች ይታደሙበታል። ንባብ ለሕይወት የመፅሐፍት አውደ-ርዕይ አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ብዙ የሚጥር ፕሮግራም ነው። ከብዙሃን መገናኛ ጋር እና ከደራሲያን ጋር አያሌ ተግባራትን ያከናውናል። ከዚህ ቀደም በደራሲነት እና በድርሰት ላይ ውይይት መደረጉ ትዝ ይለኛል። እሱን መሠረት አድርጌ ዛሬ ደራሲ ማን ነው በሚል ርዕስ እስኪ እንጨዋወት።

 

ይህን ርዕስ መርጦ አንድ ፅሁፍ ለመፃፍ የማይሞከር፣ የማይገፋ ሀሳብ ለማስተናገድ እንደመሞከር ነው። በጣም ሰፊ ነው። ከየቱ ተጀምሮ የትኛው ላይ ማቆም እንዳለብን ሁሉ አይታወቅም። ነገር ግን እስኪ አንድ ዳሰሳ እናድርግና ወደ ቀጭኑ ወይም ጠባቡ መስመር እየገባን እሱንም እያደማነው፣ እየመረመርነው እንሂድ በሚል የሩቅ አላማ ተስፈኛ ሆኜ ነው ዛሬ የተነሳሁት።
አንድ ጊዜ የቅርብ ወዳጄ የሆነ ሰው “ኢትዮጵያ ደራሲዎቼ ብላ የምትቆጥረው ከማን ጀምሮ ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። እንደሚመልስ ሰው Well! ብዬ ቀረሁ። ሳስበው አጣብቂኝ ጥያቄ ነው። ወደኋላ ሄዶ ሉሲን ድንቅነሽን ይዛ መጥታ የሰው ልጅ መገኛ፣ የዓለም ቁንጮ ነኝ ብላ የሦስት ሚሊዮን አመት ታሪክ መዛ የተቀመጠች ሀገር የደራሲዎቿስ መነሻ ከየትኛው ክፍለ ዘመን ላይ ይነሳል?። ከዚያው ከነጋድራስ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገ/እየሱስ ጦቢያ፤ እንጀምር ወይስ ሌሎች ጐምቱ ደራሲዎች ከርሱ በፊት ነበሩን? አዎ ነበሩን ማለት ይቻላል። ነገር ግን ደራሲ ማለት በራሱ ምንድን ነው?
ብዙ ሰዎች ደራሲን ከፈጠራ ሙያ ጋር ያያይዛሉ። ደራሲ ፈጣሪ ነው ይላሉ። ደራሲ ገፀ-ባህሪያት ፈጥሮ፣ ታሪክ አበጅቶላቸው፣ መኖሪያ ስፍራ ሰጥቷቸው፣ እንዲንቀሳቀሱ፣ እንዲተነፍሱ፣ እንዲያወሩ፣ የዚህችን ውጣ ውረድ የበዛባትን ዓለም መከራ መቋቋም ካልቻሉ እንዲሞቱ የሚያደርግ ሰው ነው የሚሉ አሉ። በዚህ ብያኔ የሚፀኑት ሰዎች የታሪክ ሰነዶችን የሚመዙት የልቦለድ ስራዎችን ከፃፉ ደራሲዎች አንፃር ነው። ይሄ ደግሞ 1900 ዓ.ም ላይ ያርፍና ከዚያ ላይ ነው የሚነሳው። ይህን ሀሳብ የሚደግፉት ሰዎች ሌላም ነጥብ ያነሳሉ። ደራሲ የሚባለው ሰው መፅሀፍ ፅፎ ያሳተመ፣ ያሰራጨ፣ ወይም አንባቢያን ዘንድ ያደረሰ መሆን አለበት ሲሉ ሰምቻለሁ።


ሌሎች ይነሱና ደግሞ ያላሳተመ ሰው ‘ደራሲ’ እንዴት ነው ሊባል የማይችለው ብለው ቡራ ከረዩ ይላሉ። ለምሳሌ እንደ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ያሉ ሰዎች የፃፏቸው ድርሰቶቻቸው በተለያዩ እክል ምክንያት ለ30 አመታት ቁጭ ካሉ በኋላ ነው የህትመት ብርሃን ያዩት። እና እነስብሃት አጋጣሚዎች ተሳክቶላቸው ባያሳትሙ ኖሮ ደራሲ ላይባሉ ነው? ብለው ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ አያሌ ናቸው። ለነገሩ ለእነዚህ አይነት ደራሲዎች እንግሊዝኛው “Un Published Writer” ይሏቸዋል። ‘ያላሳተመ ደራሲ’ እንደማለት ነው።


ከዚህ ሌላ ደግሞ ከፈጠራ ፅሁፍ ባሻገር ያለውን ስራስ የሚሰራው ሰው ምን ሊባል ነው? ብለው የመከራከሪያ ነጥብ መዘው የተነሱ ሰዎች አሉ። መፅሀፍ አሳትመው ለልጅ ላዋቂው ከስነ-ምግባር እስከ ታላላቅ ፍልስፍና ያስተማሩ ያሳወቁትስ ምን ልትሏቸው ነው? ሃይማኖትን ተመርኩዘው፣ ከሃይማኖት ጐን ቆመው ሃይማኖታዊ ወግና ስርአትን ለማስተማር ልዩ ልዩ ምሳሌዎችን እየፈጠሩ፣ እየተረኩ ያሳወቁ ያስተማሩ አበው ምን ሊባሉ ነው?


ክርክሩ ማብቂያ የለውም። አጨቃጫቂው ደራሲ የሚለው ቃል ነው። ደራሲንና ፀሐፊን ለይታችሁ ተናገሩ የሚሉም አሉ። ደራሲ የሚባለውን ከፈጠራ ፅሁፍ ጋር ብቻ ያቆራኙታል። ፀሐፊ የሚባለው ደግሞ ይሄው እኔ እንደምፅፈው አይነት ፅሁፎች ላይ የሚያተኩረውን መግለጫ ነው። ቃል ብዙ ነገር ይጠራል።
አሁን አሁን ደግሞ መፅሀፍ ማለት ምን ማለት ነው እየተባለ ነው። አንድ መፅሀፍ፤ መፅሀፍ ለመባል ማሟላት የሚገባው መስፈርት አለ። ከነዚህ መስፈርቶች አንዱ የገፅ ብዛቱ እና የመፅሀፉ መጠን ነው የሚሉ የስነ-ፅሁፍ ምሁራን አሉ። በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገጽ ብዛታቸው በጣም አናሳ የሆኑና እንዲሁም ቅርፃዊ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ‘መፅሀፎች’ እየታተሙ ነው። እነዚህ መፅሀፍ ሊባሉ አይችሉም እየተባለ ነው። ነገሩ እንዲህ አይነት መፅሀፍትን ማሳተም በሀገራችን ዛሬ የተጀመረ አይደለም። በተለይ 1950ዎቹ ውስጥ በስፋት ተስተውሏል። ይህ የ1950ዎቹ ሁኔታ ናይጄሪያ ውስጥ ከነበረው የድርሰት አብዮት ጋር አብሮ የሚነሳ ነው።


ናይጄሪያ ውስጥ በ1950ዎቹ ‘ኦነትሽያ ማርኬት’ የሚባል መጠሪያ የተሰጠው ‘የስነ-ፅሁፍ ገበያ’ ነበር። ይህ ሁኔታ እንዲህ ነው፡-
አስርም ይሁን ሃያ ገጽ ያላቸው መፅሀፎች በብዛት ይታተሙ ነበር። እነዚህ ለንባብም ሆነ ለዋጋ ርካሽ ስለነበሩ በጣም ይነበቡ ነበር። የናይጄሪያም ስነ-ፅሁፍ ሲጠራ ይሄ ዘመን አብሮ ይወሳል። የደራ ‘የስነ-ፅሁፍ ገበያ’ የነበራት ወቅት ነውና። ታዲያ በዚያን ዘመን በእኛም ሀገር እንዲህ አይነት ፅሁፎች እንደበሩ በሙሉ ድፍረት መናገር በሚያስችል መረጃ ማውጣት ይቻላል። ዛሬ ዛሬም ይህ ሁኔታ ብቅ እያለ ነው።


ይሄ እንግዲህ ደራሲ የሚባለውን ስብዕና ብያኔ ለመስጠት ምን ያህል አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳሉና እንዲሁም ደግሞ አንድ መፅሀፍ በራሱ፣ መፅሀፍ ለመባል የደረጃ መመዘኛ እንዳለው የሚያሳስቡ ድምጾች ብቅ ብቅ ማለት ስለጀመሩ እንደ መወያያም ያገለግለናል። በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውይይት ማለት ነው።


ድሮ ድሮ ልበልና ከ1920ዎቹ በፊት የደራሰዎቻችን ሙግት ነበር። የዕውቀት ክርክር። ለምሳሌ ያህል ደራሲ አፈወርቅ ገ/እየሱስ ስለ አፄ ምኒልክ በፃፉት መፅሀፋቸው ውስጥ የምኒልክን ጀግንነት፣ አርቆ አስተዋይነት፣ ብልህነት ወዘተ. በጥልቀት ዳሰዋል። አፈወርቅ በዚህ ብቻም አላበቁም የምኒልክን ታሪክ ሲፅፉ አፄ ቴዎድሮስን በቃላት ጐነጥ አድርገው አልፈዋል። ታዲያ ከዚህ በተቃራኒ የሆነ ደግሞ ሌላ ደራሲ መጣባቸው። ገብረህይወት ባይከዳኝ።


ገብረህይወት ባይከዳኝ በዚያን ዘመን ከነበረው ማህበረሰብ አንፃር ህዝብን እንደ ህዝብ የሚወቅስበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ገብረህይወት ‘የኛ ህዝብ የሚሠራለትን፣ ጐበዝ የሆነን ሰው አይወድም። የሚወደው ሰነፍ፣ ወይም መጥፎ የሆነውን ነው’ የሚል አንድምታ ያለው ሃሳብ ይሰነዝር ጀመር።


እናም ስለ አጤ ምኒልክ ታሪክ የተፃፈውን መፅሐፍ ተችቷል። አጤ ምኒልክን ለማሞገስ ቴዎድሮስ መሰደብ የለባቸውም ብሎ የተነሳ ሰው ነው። እንደ ገብረህይወት አባባል አጤ ምኒልክ የተወደዱት ጐበዝ በመሆናቸው አይደለም። ጐበዝ የሆነማ ሰው አይወደድም እንዲያውም በተቃራኒው ያለው ነው የሚወደደው ይል ነበር።


ይህንን ሀሳቡንም ሲያጠናክር በዚያን ዘመን ወደ ሐረር አካባቢ የነበረን ክስተት ያስታውሳል ገብረህይወት። እንደ ገብረህይወት አፃፃፍ አንድ ብልህ ሰው ሐረር ውስጥ ለሰዎች መሬት ትሽከረከራለች ብሎ ሊያስረዳ ይሞክራል። ህዝቡ ደግሞ “አቤት ውሸት፣ አይ ዘመን እንዳው የቀጣፊዎች ሆኖ አረፈው? ይሄው በአይናችን የምናያትን ፀሐይ በምስራራቅ ወጥታ በመዕራብ የምትጠልቀውን ትቶ ንቅንቅ የማይለውን መሬትን ይሽከረከራል ይላል። “ቀጣፊ” ተብሎ ሰውየው ተተቸ። አይንህ ለአፈር ተባለ። የሚገርመው ነገር ሰውየው ጭራሽ ታሰረ። መሬት ትሽከረከራለች በማለቱ።


ገብረህይወት ባይከዳኝ የኛ ህዝብ እንዲህ ነው አዋቂውን አያስጠጋም። እንዲያውም ያስረዋል። ስለዚህ እዚህ ሀገር ሰው የሚጠላው ሰው ጥሩ ነው ማለት ነው እያለ ተጠየቅ ሎጂክ ያዘለ ክርክር ጀምሮ ነበር። አፄ ቴዎድሮስ ህዝብ የጠላቸው ጐበዝ ስለነበሩ ነው የሚል እሳቤም ነበረው።
የሁለቱ ደራሲዎቻችን ክርክር ዛሬ ላይ ቁጭ ብለን ስንመለከተው በራሱ ታላቅ የፈላስፎች ጉባኤ ይመስላል። ሁለቱም ሰዎች በዘመናቸው ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ዘመናዊውን ትምህርት ቀስመው፣ እውቀት አዳብረው ከመጡ በኋላ ነው የሀሳብ ሙግት ውስጥ የገቡት።
አፈወርቅ ገ/እየሱስ ከያኒ ልንለው የምንችለው ሰው ነው። በሁሉም መስክ የተዋጣለት ነበር። ልቦለድ ደራሲ ነው። ፀሐፌ ተውኔት ነው፣ ምርጥ ሰአሊ ነው፣ የታሪክ ፀሐፊ ነው፣ ጋዜጠኛም ነበር በህይወቱ ፍፃሜ አካባቢ።


አፈወርቅ ገ/እየሱስ ሰብዕናው በስርአት መፈተሽ አለበት። ይህንን ስል ለምሳሌ ምኒልክና የኢጣሊያ መንግሥት ውጫሌ 17 ውል ተፈራርመው ሲጨርሱ አፈወርቅ ሮም ከተማ ውስጥ ነበር። ያ ውል ሲደርሰውም የትርጉም መዛባት እንዳለበት ተገነዘበ። መገንዘብ ብቻም ሳይሆን የተፈፀመውን ስህተት ደብዳቤ ፅፎ ለምኒልክ ያሳወቀ ሰው ነው። ከዚያም የአድዋ ጦርነት እንዲነሳ ሆነ። ታዲያ አፈወርቅ ገ/እየሱስ የአድዋ ጦርነት እንዲነሳ የመቀስቀሻ ደውል ያሰማ ሰው ነው ማለት ይቻላል።


ከአድዋ በኋላ ያለው አፈወርቅ በጥበብ የተራቀቀ ነው። ለምሳሌ ለሀገራችን የዘመናዊ ስዕል አሳሳል ፈር ቀዳጅ ነው። አያሌ ስዕሎችን ሸራ ወጥሮ አበርክቷል። በፀሐፌ ተውኔትነቱም ልዩ ልዩ ቴአትሮችን አበርክቷል። ነገር ግን ዛሬ ዛሬ እነዚህ ፅሁፎች የሉም። ንብረቶቹ በተለይም ለኢጣሊያ በባንዳነት አድረሃል በሚል ሰበብ ከወረራው በኋላ ተዘርፈዋል። ወይም ሆን ተብለው ተቃጥለውበታል። አሁን ድረስ እጃችን ላይ ቢኖሩ አያሌ ጥናቶችና ምርምሮችም መነሻቸው የአፈወርቅ ተውኔቶች ይሆኑ ነበር።


አፈወርቅ ገ/እየሱስ በስዕል ስራው እንግልትና መከራ የደረሰበት ሰው ነው። ለቤተ-መንግሥት ቅርብ በመሆኑ የአጤ ምኒልክንና የእቴጌ ጣይቱን መልክ በስዕል ያስቀምጠዋል። በወቅቱ ፎቶ ግራፍ እምብዛም ስለሌለ ስዕል ዋነኛው የምስል ማኖሪያ ጥበብ ነበር። ከእቴጌ ጣይቱ ጋርም የቅርብ ዝምድና ነበረው። ታድያ እቴጌን ሲስል አንድ ያልተጠበቀ ነገር ብቅ አደረገ። እቴጌ ጣይቱ ጥርሳቸው በተፈጥሮ ወደፊት ወጣ ያለ ነው። አፈወርቅ ደግሞ ይህንን ጥርስ በስዕል ያሳያል ብሎ ያሰበ የለም። እናም እንዳለ ሳለው። እቴጌ ተቆጡ፤ ቁጣም ብቻ ሣይሆን ቅጣትም ደርሶበታል።
አፈወርቅ በዚህ አዝኖ የምኒልክና የጣይቱ ባላንጣ አልሆነም። ለስርዓቱ ቀረብ ብሎ ብዙ ነገር አበርክቷል። ከምኒልክ ስርአት በኋላ በመጣው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ደግሞ ፍፁም የተለየ ስብዕና ተላብሶ ብቅ አለ።


ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር ከወራሪዋ ጋር አብሮ ተሰለፈ። በዘመኑ አጠራርም ባንዳ ተባለ። ባንዳ የተባለበት ሁኔታ ኢጣሊያ የኢትዮጵያን መላ ግዛት በወረራ ስትይዝ ህዝቡ ፀጥ ረጭ ብሎ ካለ ሁከት እንዲኖር አፈወርቅ ሰባኪ እንዲሆን ተደረገ። እሱም እሺ አሜን ብሎ ተቀበለው። በወቅቱ በኢጣሊያኖች አማካይኝነት ይታተም የነበረውን “የቄሳር መንግሥት መልዕክተኛ” የተሰኘውን ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት መስራት ጀመረ።


ጋዜጣው በስፋት የሚያተኩርባቸው ርዕሰ ጉዳዮች የኢጣሊያኖችን ቅዱስነት፣ የጥበባቸውን ርቀት፣ የስልጣኔያቸውን ልዕለ ኃያልነት፣ ለኢትዮጵያ እና ለህዝቦቿ ያላቸውን ፅኑ ፍቅር ወዘተ በጐ ነገሮችን ያወሳል። ከዚህ ሌላ ደግሞ ወራሪዋን ኢጣሊያን ለመመከት በአርበኝነት ወደ ጫካ የገቡትን ተዋጊዎች አለማወቃቸውን፣ በአስተሳሰብ ወደ ኋላ የቀሩ እንደሆኑ አፈወርቅ ገ/እየሱስ ይፅፍ ነበር። አርበኞቹን ኑ ወደ ቤታችሁ ግቡ፣ ጫካ ለጫካ ምን አንከራተታችሁ እያለ ይሰብካቸው ነበር።


ከአድዋ ጦርነት በኋላ እስከ ሁለተኛው የኢጣሊያ ወረራ ድረስ 40 ዓመታት ተቆጥረው ነበር። እናም አፈወርቅ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን አስተዳድራ ቢሆን ዛሬ ዛሬ ሀገሪቱ የታላቆች ታላቅ ትሆን ነበር በማለት ኃይለኛ ሰበካ ያካሂድ ነበር። እንደውም “አርባ ዓመት ያለጥቅም አለፈ” በሚለው መጣጥፉ ይህንኑ ጉዳይ አብራርቶ ፅፏል።


አንዳንድ ሰዎች ስለ አፈወርቅ ስብዕና ሲናገሩ ሰውየው የሀገሩን እድገት ስልጣኔ በጣም የሚፈልግ ነበር። አውሮፓ ሄዶ ስለተማረ የዓለምን የእድገት ደረጃ አይቷል። ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ ደግሞ ሲመለከት የኢንዱስትሪውም አብዮት ሆነ ልዩ ልዩ የእድገትና የብልፅግና ዘውጐች የሏትም። እናም ጣሊያኖች ቢገዙን ሳይሆን ቢያስተዳድሩን ካለንበት ደረጃ አፈትልከን እንወጣለን የሚል አመለካከት ነበረው ይላሉ። ይህ አባባል በብዙዎቹ በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ እንደሚያመጣ መናገር ይቻላል።


ሌላው የሚገርመው ነገር በዚሁ አፈወርቅ በሚያዘጋጀው ጋዜጣ ላይ አምደኞች የነበሩ ታዋቂ የኢትዮጵያ ልጆች መኖራቸው ነው። ለምሳሌ ታዋቂው ደራሲ ከበደ ሚካኤልና ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የፃፏቸው መጣጥፎች አሉ። ተሰማ እሸቴ የኢጣሊያኖተን ስልጣኔና እውቀት ዘርዝረዋል።


በአጠቃላይ ግን የሀገሩን እድገትና ስልጣኔ የማይመኝ የማይናፍቅ የለም ማለት ይቻላል። ነገር ግን ስልጣኔው በየትኛው መንገድ ይሁን የሚለው የአቅጣጫ ምርጫ ነው ልዩነት የሚያመጣው። በአሁኑ ጊዜ ‘አብዮታዊ ዴሞክራሲ’ እና ‘ሊብራል ዴሞክራሲ’ የሚሉ አስተሳሰቦች እያንዳንዳቸው ለእድገት ይሆኑኛል የሚሏቸውን ነጥቦች ይጠቅሳሉ። የድሮውም አስተሳሰብ አፋጣኝ እድገት ለማግኘት ‘በሰለጠነው’ ኃይል ተገዝተን እንደግ የሚል የአፈወርቅ ሀሳብና ኧረገኝ እንዴት ተደርጐ በቅኝ ተገዝቼ እኖራለሁ? በነፃነቴ ራሴን እየመራሁ ቆሎም ቆርጥሜ እቀጥላለሁ የሚሉ ፅንፎች ነበሩ። ጉዳዩ አጨቃጫቂ ነው።


እንግዲህ አፈወርቅ ገ/እየሱስ የመጀመሪያው የአፍሪካ ልብወለድ መፅሀፍ ደራሲ ነው ይባላል። ጦቢያ። የአጤ ምኒልክንም ታሪክ ፅፏል። ከጥበብ ጋር ኖሯል። አሳይቷል፤ አስተምሯል።
ኢጣሊያ ከኢትዮጵያ ምድር ተሸንፋ ተባራ ስትወጣ አፈወርቅ ግን ያው ሀገሩ ኢትዮጵያ ቀረ። ሽምግልናም አይሎበት ደክሟል። ግን ታሰረ። በግዞት ኖረ። ተሰቃየ። የዓይን ብርሀኑንም አጥቷል። የህይወት ውጣ ውረድን በብዕሩ እንዳሳየ ሁሉ በዕውናዊ ህይወቱም እላይ አታች ብሎ ይህችን ዓለም 1939 ላይ ተሰናበተ።

Page 3 of 19

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us