You are here:መነሻ ገፅ»ኪነ-ጥበብ
ኪነ-ጥበብ

ኪነ-ጥበብ (257)

 

በጥበቡ በለጠ

በቴአትር ጥበብ ጠቀሜታ ላይ ክርክር የተጀመረው ገና ከክርስቶስ ልደት በፊት በ400 አ.አ አካባቢ በፕሌቶ እና የፕሌቶ ተማሪ በነበረው በአርስቶትል ነው። የሶቅራጥስ ደቀመዝሙር የነበረው ፕሌቶ በምድር ላይ ያለው የትኛውም በስሜት ህዋሶቻችን የምንረዳው አለም የማናየው እና በስሜታችን የማንረዳው አለም ነፀብራቅ ነው የሚል ፍልስፍና አለው። ከዚህ ፍልስፍናው በመነሳት ኪነ-ጥበብ ዋጋ የሌለው ነው ይላል። ይህ የፕሌቶ አባባል ኪነ-ጥበብ የእውነተኛው (የገሀዱ) አለም ነፀብራቅ ነው የሚለውን አስተሳሰብ በመቃወም የቀረበ ሲሆን ለፕሌቶ የገሀዱ አለም እራሱ የማይታየው እና የማይዳሰሰው አለም ነፀብራቅ ነው እንጂ እውነት አይደለም። ስለዚህም የኪነ-ጥበብ ስራ ከእውነት ሁለት እጅ የራቀ ስለሆነ ዋጋ የሌለው እንደሆነ ይናገራል።


ቪንሲትባሪ የተሰኘው ፈላስፋ ፊሎሶፊ በተሰኘው መፅሐፉ ‘‘ጥበብ በተመልካቹ ትክክለኛ እውቀት የማይሰጥ ነው ብሎ ስለሚያምን ፕሌቶ ዘ ሪፐብሊክ በተሰኘው መፅሐፍ ውስጥ ቦታ የሚሰጠው አይደለም’’ ሲል ያስቀምጣል።


የፕሌቶ ተቃውሞ በአውሮፓ ታሪክ የጨለማው ዘመንን ተከትሎት በመጣው ከ9 መቶ ዓመተ ምህረት እስከ 11ኛው እና 12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነበረው መካከለኛው ዘመን ውስጥም በቤተክርስቲያን ሰዎች አማካኝነት ቀጥሎ ነበር። በተለይ የመካከለኛው ዘመን ቤተክርስቲያን ቴአትር ከሃይማኖት እውቀቶች ውጪ ይሰብካል፤ ሰዎችን ያሳስታል ብላ ስለምታመን የትኛውም ስፍራ እንዳይታይ መአቀብ ጥላ ነበር።


ልክ እንደ መካከለኛው ዘመን ቴአትር ምንም አይጠቅምም በሚል ሙሉ በሙሉ መአቀቡ አይጣልበት እንጂ ሶሻሊዝምን በሚከተሉ ሀገሮችም ቴአትር (በተለይ እውናዊ ቴአትር) ለማኀበራዊ ለውጥ የማይጠቅም፤ የላብ አደሩን ትግል ወደፊት የማያራምድ፣ ውበትን አብዝቶ እና እውቀትን አሳንሶ ስለሚሰጥ ሰዎች እውቀት በቀላሉ እንዲያገኙ የማያደርግ ጥበብ እንደሆነ ያስቀምጣሉ።


ከሶሻሊስት እና አምባገነን ሀገሮች በተቃራኒው ቴአትር ምንም አይነት አስተምሮታዊ እና ማኀበራዊ ፋይዳ ሊኖረው አይገባም የሚሉት ጥበብ ለጥበብ ደንታ (Art for Art sake) አቀንቃኞች ናቸው። የዚህ ሀሳብ አቀንቃኞች ‘‘ጥበብ ምንም ጥቅም አይሰጥም’’ ብለው ሲነሱ ከሶሻሊስት ሀገሮች እጅጉን በተለየ መንገድ ነው። የሶሻሊስት ሀገሮች ቴአትር ልብ ስለሚያንጠለጥል፣ እጅጉን ለውበት ስለሚጨነቅ በቀላሉ እውቀትን አያስተላልፍም በሚል ተነሳስተው ቴአትር አይጠቅምም ይላሉ። የጥበብ ለጥበቡ ደንታ አቀንቃኞች ደግሞ ቴአትር ለማስተማር እና ለማሳወቅ ሲል ልብ አንጠልጣይነትን ወይም ውበትን አይፈጥርም። ስለዚህ ማስተማርም ማሳወቅም የለበትም ይላሉ። በዚህም ሀሳብ ተነሳስተው የጥበቡ ለጥበቡ ደንታ አቀንቃኞች የቴአትርን የማስተማር እና የማሳወቅ ባህሪ ከውስጡ አውጥተው ውበትን ብቻ በስራቸው ውስጥ ይፈጥራሉ ያሳያሉም።


ዘ ቴአትር የተሰኘው መፅሐፍ፤ በተለይ ቴአትር በፀሐፌ-ተውኔቱ ምናብ የሚፈጠር ሰለሆነ ተመልካቹ ፀሀፌ-ተውኔቱ ያነሳውን ሃሳብ አምኖ ለመቀበል እና ለውጥን ለማምጣት ቁርጠኝነትን ላያሳይ ይችላል በማለት የቴአትርን ጠቀሜታ የሚያጠይቁ ሰዎች እንዳሉ አንስቶ ይገኛል።


ኢማኑኤል ካንት በመባል የሚታወቀው ፈላስፋም ቴአትር ከቁምነገር ይልቅ ወደቀልድ የሚያደላ ነው በማለት ጥቅም የሌለው እንደሆነ ይናገራል።
‘‘ቴአትር አይጠቅምም’’ የሚለው አስተሳሰብ በመፃህፍት ብቻ ሳይሆን በአጠገባችን ያሉ ሰዎችም እምነት ነው። በአንድ ወቅት ‘‘ቴአትር ያስተምራል፣ ያሳውቃል እንዲሁም ለመኀበራዊ ለውጥ ይጠቅማል የምትሉት ውሸት ነው’’ በማለት ክርክር የተገጠመበትን ሁኔታ አስታውሳለሁ። ቴአትር አይጠቅምም የሚሉት ወገኖች ‘‘ቴአትርን ለማስተማሪያነት ስታቀርበው ስህተት የሆኑ ነገሮችን ለማረሚያ ነው። ለምሳሌ ሴተኛ አዳሪነት ጥሩ አይደለም ብለህ ለማለት በምትሞክርበት ጊዜ አንተ መጥፎ ነው ያልከውን በቅን ጎኑ የሚወስዱት አሉ። ሌላው ሰዎች በባህሪያቸው መሞከር የሚፈልጉ ፍጡራን ናቸው። ስለዚህ መጥፎ ነው ያልከውን ነገር ሊሞክሩ ይችላሉ። በዚህ አይነት ሁኔታ ብዙ መጥፎ የሆኑ ነገሮችን ልታስተምር ትችላለህ’’ ይላሉ። በተለይ ሃይማኖታዊ አቋም ያላቸው ቴአትሮች ለአለማዊ (መጥፎ) ተግባር ከዋለ አለማዊነትን (መጥፎነትን) የሚሰብክ ነው ብለው ያስባሉ።


ቴአትር አይጠቅምም ከሚለው ሀሳብ ወጥተን ቴአትር ይጠቅማል ወደሚለው ሀሳብ ስናመራ የቴአትር ጠቀሜታ መነገር የጀመረው ከፕሌቶ አስቀድሞ እንደነበር መገመት ይቻላል። ምክንያቱም ፕሌቶ ቴአትር አይጠቅምም የሚለውን ሀሳብ ለማንሳት ከሱ አስቀድሞ ቴአትር ይጠቅማል፣ እውነተኛው አለምም የተቀበለው ነው የሚል ሀሳቡ መኖር ስለነበረበት ነው።


ከላይ በተደጋጋሚ ያነሳነው የፕሌቶ ተቃውሞ የገጠመው የራሱ ደቀመዝሙር በነበረው በአርስቶትል ነው። ለአርስቶትል እውነት በስሜት ህዋሳችን የምንረዳው ሁሉ ነው። ሰው እና በገሃዱ አለም የሚገኝ ነገር ሁሉ ለአርስቶትል እውነት ነው። ሰው ስንል ደግሞ ስጋ እና መንፈስ (ስሜት) ያለው ፍጡር ነው። ነገር ግን መንፈስ ወይም ስሜት ተጨባጭ አይደለም። ተጨባጭ አይሁን እንጂ ሰዎች ስለ አለም ያላቸውን እምነት አጭቀው የሚያኖሩበት ነው። አንድ የኪነ-ጥበብ ሰራ ደግሞ ከያኒው በመንፈሱ ውስጥ ስለአለም ያለውን አመለካከት የሚያወጣበት ነው። ስለዚህ ለአርስቶትል ቴአትር ኢ-ተጨባጭ የሆነው የሰው ልጅ ስሜት ተጨባጭ ሆኖ የሚገለፅበት ነው።


ይህንን የአርስቶትልን ሀሳብ የሚደግፈው የሳይኮአናሌስስ አባት ተብሎ የሚጠራው ሲግመንድ ፍሮይድ ነው። ለፍሮይድ ሰው ሊያስታውስ የማይፈልጋቸውን ትላልቅ ፍላጐቱን እና ድርጊቱን የሚደብቅበት የአእምሮ ክፍል አለው። ነገር ግን ፍላጎቱን እና ድርጊቱን ደብቆ ለሁሌውም ማቆየት አይቻለውም። ስለዚህም ፍላጐቱ እና ድርጊቱ በህልሙ በንግግሩ በድርጊቱ ሳያውቀው ይገለፁበታል፤ በፀፌ ተውኔቱም በውስጡ ያጨቃቸውን ፍላጎቶች ሳያውቀው ይፅፋቸዋል። ስለዚህም ኪነ ጥበብ ሊታወስ የማይፈለግ ነገር ግን ሊረሳ የማይችል ፍላጐት ወይም የተደበቀ ማንነት መግለጫ ነው።


አርስቶትል ፖየትሪ “POITERY” የተሰኘው መፅሐፍ ውስጥ ጥበቡ ከታሪክ ይልቅ አለም አቀፋዊ የሆነ እና የአለምን እውነት በውስጡ የያዘ እንደሆነ ያስቀምጣል። አለም አቀፋዊ ከመሆኑ ባሻገር ተፈጥሮን በትክክል የሚገልፅ ነው ይላል። እንደውም ፍልስፍናዊ ስለሆነ ህይወትን በመመርመር ፍፁም እውነት የሆነውን የአለም ገፅታ ይናገራል ብሎ ፅፏል።


ፕሌቶም እኛ እውነተኛ (ገሀድ) ብለን የምናምነው አለም እውነት ነው ብሎ አያስብም። ስለዚህም ነው ቴአትር የእውነተኛው አለም ነፀብራቅ አይደለም የሚለው እንጂ እውነት ያልሆነው አለም ቅጂ እንደሆነ ግን በተዘዋዋሪ ይናገራል። እንደውም ለመኀበራዊ ለውጥ ካልዋለ መአቀብ ሊጣልበት እንደሚገባም ይናገራል።


ከ1866-1952 የኖረው የኢጣሊያኑ ፈላስፋ ቤንዴቶ ክሮብ ልክ እንደ አርስቶትል ሁሉ ቴአትር ከአእምሮ የሚወጣ እንደሆነ ያስባል። ከአርስቶትል በተለየ ሁኔታ ክሮስ ጥበብ ስለ አነድ ነገር የጠለቀ እውቀት የሚሰጥ ነው ብሎ ያስባል።


ቴአትር እውቀት ይሰጣል ከሚለው አስተሳሰብ በተጨማሪ ቴአትር ሰዎች የደረሱባቸውን ፖለቲካዊ ተፅእኖዎች የሚቃወሙበት እንደነበር ታሪክ ያወሳል። በተደጋጋሚ ስሙን ያነሳነው አርስቶትልም ትራጄዲ የከፍተኛውን (የነገስታቱን) ኮሜዲ የዝቅተኛውን ማኀበረሰብ ህፀፅ ማሳየት አለበት ሲል ይበይናል። በርግጥም በግሪክ የቴአትር ታሪክ ውስጥ ቴአትር ፖለቲካዊ ብልግናዎችን የማጋለጥ ጠቀሜታ ነበረው። በተለይ የግሪክ ጥንታዊ (ኦልድ) ኮሜዲ ተብሎ የሚጠራው ዘመን ፖለቲካዊ ሀሳቦችን እና ድርጊቶችን በመሄየስ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ ጥበብ እንደነበረ ዊኪፒዲያ የተሰኘው የመረጃ መረቡ ያወሳል። ስለዚህም ቴአትር ፖለቲካዊ ስህተቶችን ማሳየት አንዱ ጠቀሜታው ነው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል።


ከክርስቶስ ልደት በኋላም የነፃነት ቴአትር (Theatre for liberation)፣ የጭቁኖች ቴአትር (Theatre of the oppressed)፣ የሴታዊነት ቴአትር (Feminist theatre) ወዘተ በመባል የሚጠሩት የቴአትር አይነቶች ሰዎች ለለውጥ እንዲነሱ በማድረግ የትግል መሳሪያ የመሆንን ግልጋሎት የሰጡ እና እየሰጡ የሚገኙ ናቸው።


ከላይ አንስተናቸው የነበሩት የሶሻሊስት ሀገራትም ቴአትር አይጠቅምም ብለው አልቀሩም። ይልቁንም የቴአትርን ውበት የመፍጠር አቅም በመቀነስ እና የማስተማር አቅሙን በማጉላት አመክኖአዎ፣ ኤፒክ (Epic) የተሰኘ ቴአትር አይነት ፈጥረው ቴአትርን በእጅጉ ተጠቅመውበታል። እንደ ብረሽት የመሳሰሉ ሰዎች የፈጠሩት አመክኖአዊ ቴአትር ሶሻሊስት በሆኑ ሀገሮች ማኀበረሰቡን ማርክሳዊ ፅንሰ ሀሳቦች በማጥመቅ፤ ላብ አደሩን በማደራጀት እና ለለውጥ ትግል በማንቀሳቀስ ጠቅሟል።
ቴአትር በታሪክ ውስጥ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ብቻ አልነበረም የነበረው። ለቴአትር በሯን ዘግታ የነበረችው የመካከለኛው ዘመን ቤተክርስቲያንም በሯን ለቴአትር ክፍት ካደረገች በኋላ ወንጌልን ማስፋፊያ አድርጋዋለች።
አሁን ባለንበት ዘመን ከፍተኛ ማኀበራዊ ፋይዳ እየሰጠ የምናገኘው ቴአትር ለልማት (Theatre for Development) የተሰኘው ነው። ፖለቲካዊ ቴአትሮች ህዝቡን በፖለቲካው ላይ ለውጥ እንዲያመጣ የመቀስቀስ፣ የማደራጀት፣ የማታገል እና ለውጥ እንዲያመጣ የማድረግ ሚና እንደነበራቸው ሁሉ ቴአትር ለልማትም በአንድ ጎኑ ፖለቲካዊ ግልጋሎት የሰጠ ቢሆንም በሌላ ጎኑ ግን ደሀ የሆነውን ህዝብ ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እንዲቀርፉ ደሀነት ያመጡበት ችግሮች ምን እንደሆነ ከማሳየት ጀምሮ ለውጥ ማምጣት እስኪችሉ ድረስ እረድቷቸዋል።


ዘ ቴአትር የተሰኘው መፅሐፉ የቴአትርን ጠቀሜታ ከታሪክ፣ ከፍልስፍና እና ከሳይንስ ጋር ተነፃፅሮ የሚቀመጥ ነው በማለት ከላይ ከተቀመጠበት ሁኔታ በተለየ መልኩ ያሰፍረዋል።
ይኸውም ቴአትር ከታሪክ ይልቅ በአንድ ወቅት የተፈጠረን ሁኔታ በደረቁ የማይዘገብ በመሆኑ ለተመልካቹ አንድን ታሪካዊ ክስተት ከነስሜቱ ያቀርባል። ለምሳሌ በ1998 የተፈጠረው ግርግር በቴአትር መልክ ሲቀርብ በወቅቱ በግርግሩ ላይ የነበሩት ሰዎች ምን ያደርጉ ምን ይሉ እንደነበር እና ስሜታቸው እንዴት እንደነበር በፊት ለፊት በማሳየት ታሪካዊ ክስተቱን እንደነበር አድርጎ ይገልፃል። ሌላው ከታሪክ ይልቅ በአንድ ታሪካዊ ክስተት ወቅት በየጎጡ እና በየሰፉ የተፈጠሩ ሁኔታዎችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላልፋል።


ፍልስፍና ነጠላ ሰዎች ለአለም ያላቸው አመለካከት በመሆኑ ለማኀበራዊ ፍልስፍናዎች ትኩረት የማይሰጥ ነው። ከዚህ አንፃር የቴአትር ጠቀሜታ ከማኀበራዊ ኑሮ እና አመለካከቶች ውስጥ ፍልስፍናዊ አመለካከቶችን ነቅሶ በማውጣት የማሳየት ሚና ይኖረዋል።


ቴአትር እንደ ሳይንስ አንድን ማኀበረሰብ የመመርመር፣ የማጥናት ሚና ይጫወታል። እንደ አይታዬ ቴአትር ያሉት ቴአትሮች አንድ ማኀበረሰብ ለአንድ ነገር ያለውን አመለካከት ለመመርመር የሚረዱ ናቸው።


ቴአትር ለተመልካቹ ከሚሰጠው ጥቅም በዘለለም ለከያኒውም የመንፈስ እርካታን ይሰጣል። ለከያኒው የሚሰጠው የመንፈስ እርካታ ብቻ ሳይሆን የገንዘብ ጠቀሜታንም ነው።
ከያኒያኑ ከቴአትር ገንዘብ እያገኙ ህይወታቸውን መምራት መቼ እንደጀመሩ በትክክል ባይታወቅም የቴአትር ምሁራን ግን በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢጣሊያን የነበሩትን እነ ኮሜዲያ ዴላ አርቴን ይጠቅሳሉ። ከዛ ጊዜ ጀምሮም ቴአትር ለከያኒው የገንዘብ ምንጭ በመሆን እስከ ዛሬ እያገለገለ ይገኛል። ከያኒው እና ኪነቱ ገንዘብ ባገኙ ቁጥር ለሰሩበት ግብርን ስለሚከፍሉ ለሀገር ውስጥም ገቢን የማስገባት ጥቅም እየሰጡ እስከ ዛሬ ቆይተዋል።

 

በጥበቡ በለጠ

ብዙ ሰው የትንሳኤን በአል ለማክበር ወደ እየሩሳሌም እየሔደ ነው። እውነትም እየሩሳሌም ብዙ ነገሮች አሉ። ነገር ግን የኛው ቅዱስ ላሊበላ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ዳግማዊት እየሩሳሌምን መስርቷል። ላስታ ላሊበላ! ቡግና ወረዳ፣ ሮሐ ከተባለች ቦታ። ትንሳኤን እዚያ ነኝ። ስለዚህ ባወራለት ስለማልጠግበው ቅዱስ ላሊበላ በዚህ ሕማማት ውስጥ ትንሽ ባጫውታችሁስ?

 

የላሊበላ ቤተሠቦች የዛጉዌ ሥርወ-መንግሥት ነገስታት ናቸው። አባቱ ዣን ሥዩም ይባላል። እናቱ ኪዮርና ትባላለች። የተወለደው ቡግና አውራጃ ላስታ ውስጥ በ1101 ዓ.ም እንደሆነ የቤተ-ክርስትያን መረጃዎች ያመለክታሉ። በተወለደ ጊዜም ንቦች እንደከበቡት ይነገራል። ንቦች ማር ባለበት ቦታ አይጠፉም። እናም ላሊበላ ማር ሆኖ ሣይታያቸው አልቀረም። አፈ-ታሪክ እንደሚያወሣው ላሊበላ የሚለው መጠሪያ ስሙም የተገኘው ከዚሁ ከማር ጋር በተያያዘ ነው። ላል ማለት ማር ሲሆን ላሊበላ የሚለው ሥም ማር ይበላል የሚል ትርጉም እንደሚሠጥ ይነገራል። ይህ እንግዲህ ከዛሬ 800 አመታት በፊት በነበረው የአገውኛ ቋንቋ ውስጥ ያለ ትርጉም መሆኑ ነው።

 

ላሊበላ በተወለደ ጊዜ ስለ እሡ ብዙ ነገር ይነገር ነበር። ይህም የአባቱን ዙፋን እንደሚወርስ፣ ኢትዮጵያ ላይ እንደሚነግስ ሀገረና ሕዝብ እንደሚመራ ታላቅ ሠው እንደሚሆን በስፋት ይነገር ነበር። በዚህ ምክንያት ያባቱ ልጆች የሆኑት ወንድሙ እና እሕቱ ይጠሉት ነበር። ላሊበላን ለማጥፋት ይጥሩ ነበር።

 

ላስታ ውስጥ ታዋቂ የቤተ-ክሕነት ሠው የሆኑት አፈ-መምህር አለባቸው ረታ እንደሚተርኩት ከሆነ ያባቱ ልጅ እህቱ ላሊበላን መርዝ አበላችው። እንዲሞት። እናም ሞተ። ግን ደግሞ ከሞቱም ነቃ። ምክንያቱም ፈጣሪ ጊዜክ አልደረሠም አለው። ጌታም እንዲህ አለው፡- አንተ ላሊበላ በስሜ አብያተ-ክርስትያናትን ታንፃለህ። ላንተም መጠሪያ ይሆናሉ። የክርስትያኖችም መሠብሠቢያ ትሠራለህ ይለዋል።

ላሊበላም ለጌታ እንዲህ ይጠይቀዋል፡- ሰለሞን እንኳን እየሩሳሌምን ሲሠራ ዝግባውንም ፅዱንም ከፋርስ እና ከልዩ ልዩ ቦታዎች እያመጣ ነው። እኔ በየትኛው አቅሜ ነው አብያተ-ክርስትያናትን የማንፀው? ይለዋል።

 

ጌታም እንዲህ መለሠ፡- ከአንድ ቋጥኝ ድንጋይ ትፈለፍላለህ። አንተ ላሊበላ አንፅካቸው እንድትባል ነው እንጂ የማንፃቸው እኔ ነኝ አለው። ከዚያም ላሊበላ ከሞተበት ነቃ ይላሉ አፈ-መምህር አለባቸው ረታ የቤተ-ክርስትያንን ገድለ ላሊበላ እየጠቃቀሡ።

 

ሌላው የላሊበላ ታሪክ እንደሚያወሣው በመንድሙ እና በእህቱ አማካይነት ችግር ቢደርስበትም ራዕይ ታይቶት ትዳር ይመሠርታል። ባለቤቱ መስቀል ክብሯ ትባላለች። የተጋቡት በቁርባን ነው። ነገር ግን ከወንድሙ እና ከእህቱ የሚደርስበትን ጫና ለመቋቋም ከባለቤቱ ጋር ሆኖ ተሠደደ። እሡ ወደ እየሩሳሌም ሔደ። ባለቤቱ ደግሞ አክሡም ውስጥ አባ ጴንጤሊዮን ከሚባል ገዳም ገባች።

 

ላሊበላ በእየሩሳሌም 12 አመታት ያሕል ቆየ። በዚህ ጊዜ በርካታ ትምህርቶችን ቀሠመ። እብራይስጥ እና አረብኛን መናገር መፃፍ ቻለ። ከብዙ ሠዎች ጋር ተገናኝ።

እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ሌላ ክስተት ተፈጠረ። ላሊበላ እንዲሠደድ ምክንያት የሆነው ወንድሙ ንጉስ ሐርቤይ በፀፀት ውስጥ ገብቷል። መንፈሡ ተረብሿል። ፈጣሪ እየወቀሠኝ ነው ይላል። ወንድምህ ላሊበላ እንዲሰደድ አድርገሃል፤ ይሔ ሐጥያት ነው፤ ስለዚህ ወንድምህን ፈልገህ ወደ ሐገሩ አምጥተህ፤ ይቅርታ ጠይቀህ ዙፋኑን ለእሡ ስጥ ይለዋል።

 

በመጨረሻም ላሊበላ ከእየሩሳሌም ወደ ሐገሩ መጥቶ አባ ጴንጤሊዮን ገዳም ውስጥ የምትገኘውን ባለቤቱን መስቀል ክብሯን ይዟት ወደ ላስታ ይመጣል። ወንድሙ ሐርቤይ ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሠብስቦ ጠበቀው። ድንጋይ ተሸክሞ ይቅርታ ጠየቀው። ወንድሜ ላሊበላ እንድትሠደድ ያደረኩ እኔ ነኝ። ለዚህም ስራዬ ጌታ ሲገፅፀኝ ቆይቷል፤ እናም ይቅረ በለኝ አለው። ላሊበላም ይቅርታ አደረገለት። ሐርቤይም የኢትዮጵያን ንጉስነት ትቶ ለላሊበላ ሠጠው። ጌታ ነግሮኛል። የኢትዮጵያ ንጉሥ አንተ ላሊበላ ነህ አለው። እናም የስልጣን ሽግግሩ ከሐርቤይ ወደ ላሊበላ በሠላም ተሸጋገረ።

 

ንጉሥ ላሊበላ ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካና የአስተዳደር ሕይወት ውስጥ በ1157 ዓ.ም ብቅ አለ። ላሊበላ ቄስ እና ንጉስ ነው። እጁ ላይ መቋሚያና መስቀል፣ አንደበቱ ላይ ትህትናና አስተዳደር የበዙበት የ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አስገራሚ መሪ ሆኖ መጣ።

ቀደም ሲል በፈጣሪ እንደተነገረው የሚታወቀውንም የአብያተ-ክርስትያናቱን ግንባታ ጀመረ። በ23 አመታት ውስጥ 10 አብተ-ክርስትያትን ከአለት ፈልፍሎ ሠራ። እነዚህ አብያተ ክርስትያናት ዛሬም ድረስ የሠው ልጅ ምስጢራት ሆነው አሉ። እንዴት እንደታነፁ በግንባታው ላይ ማን እንደተሣተፈ፣ እንዴትስ እንደታሠቡ ወዘተ የሚተነትን የኪነ-ሕንፃ ፈላስፋ አልተገኘም። በዚህም ምክንያት የብዙ ጭቅጭቆች እና ውዝግቦች ምክንያት ሆኖ ለበርካታ አመታት ቆይቷል።

 

የአብያተ-ክርስትያናቱ የአሠራር ምስጢር ባለመታወቁ የተነሣ የሐይማኖት ሠዎች መላዕክት ላሊበላን እያገዙት በ23 አመታት ሠርቶ አጠናቀቃቸው ይላሉ። ቀን እሡ እየሠራ ሌሊት መላዕክት እሡ የሠራውን አጥፍ እያረጉለት ተሠርተው ተጠናቀቁ የሚሉ በርካታ የቤተ-ክርስትያን መረጃዎች አሉ።

 

በሌላ መልኩ ደግሞ የውጭ ሀገር የኪነ-ሕንፃ ባለሙያዎች ናቸው የሠሯቸው የሚሉ ፀሐፍትም አሉ። የላሊበላን ኪነ-ሕንፃዎች ለመጀመሪያ ጊዜ መጥቶ በማየት እና ለአለም በማስተዋወቅ ረገድ ፖርቹጋላዊውን ቄስ ፍሪንሲስኮ አልቫሬዝ የሚደርስ የለም። አልቫሬዝ በ1520 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከጐበኘ በኋላ The Portuguese  Mission in Abyssinia የተሠኘ ግዙፍ መፅሃፍ አሣተመ። በዚህ መፅሃፍ ውስጥ ስለ ቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎች አሠራር የሚከተለውን ብሏል፡-

 

እነዚህን የቅዱስ ላሊበላን አብያተ-ክርስትያናት ላላያቸው ሠው ይህን ይመስላሉ ብዬ ብናገር የሚያምነኝ የለም። ነገር ግን ስለ እነሡ የምፅፈው ሁሉ እውነት መሆኑን በሐያሉ በእግዚአብሔር ስም እምላለሁ በማለት ፅፏል። አልቫሬዝ ያየውን ነገር ማመን አልቻለም ነበር። ላላያቸው ሠው ደግሞ ይህን ይመስላሉ ብሎ ማስረዳትም ከባድ ነው። ማንም አያምነኝም ብሎ ሠጋ። እናም ቄሡ አልቫሬዝ ማለ፤ ተገዘተ።

በአልቫሬዝ መፅሃፍ ውስጥ ሌላው አጨቃጫቂ ጉዳይ አብተ-ክርስትያናቱን ማን ሠራቸው የሚለው ነገር ነው። አልቫሬዝ እንደፃፈው ማነው የሠራቸው ብሎ ሲጠይቅ ፈረንጆች ናቸው የሠሯቸው ብለው ቄሶች ነገሩኝ ብሏል።

 

ታዲያ ከዚያ በኋላ የመጡ የሐገር ውስጥ እና የውጭ ፀሐፍት አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል ፈረንጆች ሠሩት ወደሚለው እምነት አዘንብለው ቆይተው ነበር።

የሐገራችን ታዋቂ ፀሐፊዎቸ ሣይቀሩ የላሊበላን ኪነ-ሕንፃዎች ሣይቀሩ የላሊበላን ኪነ-ሕንፃዎች የሠሯቸው የውጭ ሀገር ሠዎች እንደሆኑ ጭምር ፅፈዋል። ለምሣሌ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ብላቶን ጌታ ኀሩይ ወ/ስላሴ በ1921 ዓ.ም ባሣተሙት ዋዜማ በተሠኘው መፅሐፋቸው ተክለፃዲቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ አክሱም ኑቢያ ዛጉዌ በተሠኘው በ1931 ዓ.ም ባሣተሙት መጽሐፍ ብርሃኑ ድንቄ አጭር የኢትዮጵያ ታሪክ ብለው በ1941 ዓ.ም ባሣተሙት መጽሐፍ ዶ/ር ሥርጉው ሀብለስላሴ Ancient and Medieval Ethiopian History በተሠኘው መጽሐፋቸው እና ሎሎችም ጎምቱ የኢትዮጵያ የታላላቅ የታሪክ ፀሐፊዎች የላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎች አሠራር ላይ የውጭ ሀገር ሠዎች ተሣትፏቸውን ፅፈዋል። እነዚህ ደራሲያን ፅሁፋቸው የተጠቀሙበት ምንጭ የውጭ ደራሲያንን ፅሁፍ ነው።

 

እነዚህን ፅሁፎች ሁሉ ያነበበችው እና ከእንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው ሲልቪያ ፓንክረስት በላሊበላ አብያተ ክርስትያናት አሠራር ላይ ሠፊ ጥናትና ምርም ጀመረች። ከጥናቷ ውስጥ ዋነኛው ጉዳይ አለምን መዞር ነበር። እንደ ላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት ጋር የሚመሣሠሉ ኪነ-ሕንፃዎች በሌሎች ሐገሮች መኖርና አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ አለምን አሠሠች። ከዚያም አንድ ውጤት ላይ ደረሠች።

 

ሲልቪያ ፓንክረስት Ethiopia :- A Cultural History የተሠኘ ግዙፍ መጽሐፍ አሣተመች። በዚህ በፅሃፍ ውስጥ የቅዱስ ላሊበላ አብተ-ክርስትያናት አሠራር የአለማችን ብርቅዬ ጥበቦች መሆናቸውን ገለፀች። በአለም ላይም በየትኛውም ሀገር ይህን መሳይ ጥበብ እንደማይገኝ ፃፈች እንደ ሲልቪያ አባባል እነዚህ የቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎቸ የኢትዮጵያዊያኖች ብቻ ጥበቦች ናቸው በማለት ገለፀች። የውጭ ሀገር ሠዎች ሠርተዋቸው ቢሆን ኖሮ ተመሣሣያቸውን በሌላ ሀገር አገኝ ነበር። ነገር ግን አላገኘሁም እያለች ሲልቪያ ፅፋለች።

 

ሲልቪያ ስትገልፅ ላሊበላ የአክሡም ዘመን ቀጣይ ኪነ-ሕንፃ ነው። ይህ ጥበብ በኢትዮጵያ ውስጥ እያደገ እና እየበለፀገ መጥቶ ላሊበላ ዘንድ ሲደርስ በእጅጉ ፍፁምነትን ተላብሶ መውጣቱን ፅፋለች። ሲልቪያ ላሊበላን ጨምሮ አያሌ የኢትዮጵያን ታሪኮች በመፃፍ በአለም ላይ ያስተዋወቀችን ታላቅ እንግሊዛዊት ናት። ሲልቪያ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ወራሪ ሐይል ስትወረር ለሐገራችን የታገለች የቁርጥ ቀን ወዳጃችን ናት። ወደ ኢትዮጵያም መጥታ እዚሁ ኖራ ነው ይህችን አለም በሞት የተሠናበተችው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ኃይማኖትም ተጠምቃ የክርስትና ስም ወጥቶላት ኖራለች። ቀብሯም የተፈፀመው እዚሁ ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ነው።

 

የሲልቪያ ፓንክረስት ብቸኛ ልጅ የሆኑት አንጋፋው የታሪክ ሊቅ ኘሮፌሠር ሪቻርድ ፓንክረስትን ስለ ላሊበላ አብተ-ክርስትያናት አሠራር ተደጋጋሚ ቃለ-መጠይቅ አድርጌላቸው ነበር። እርሣቸው ሲናገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ከላሊበላ በፊት ከ150 በላይ አብያተ-ክርስትያናት ከቋጥኞች እየተፈለፈሉ ተሠርተዋል። ያ ጥበብ እያደገ መጥቶ ነው ላስታ ቡግና ውስጥ፣ ቅዱስ ላሊበላ ካለምንም የኮንሥትራክሽን ስህተት ብርቅዬ ኪነ-ሕንፃዎችን ገነባ። ይሔ ጥበብ የመነጨው ከዚሁ ከኢትዮጵያ ውስጥ ነው በማለት ሪቻርድ ፓንክረስት ይገልፃሉ።

 

የኢትዮጵያ እስራ ምዕት/ሚሊኒየም/ን በማስመልከት አንድ ዶክመንተሪ ፊልም በ1999 ዓ.ም ከጓደኞቼ ከኤሚ እንግዳ እና ከአመለወርቅ ታደሰ ጋር በመሆን ሠርተን ነበር። ፊልሙ የ1፡30 ሲሆን ሙሉ በሙሉ ትኩረቱን ያደረገው በቅዱስ ላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎችና ታሪክ ላይ ነበር። የፊልሙ ርዕስ Lalibela:-Wonders and Mystery ይሠኛል። በአማርኛ ላሊበላ ትንግርትና ምስጢራት ልንለው እንችላለን።

 

በዚህ ፊልም ውስጥ በርካታ የታሪክ ሠዎች የኪነ-ሕንፃ ባለሙያዎች እና ተንታኞች  ተሣትፈውበታል። ፊልሙ እ.ኤ.አ 2007 ዓ.ም ለንደን የሚገኘው የብሪትሽ ሙዚየም ምርጥ የአፍሪካ ዳክመንተሪ ብሎት ለንደን ውስጥ ቀኑን ሙሉ እንዲታይ አድርጐታል። ከዚያ በኋላ ደግሞ በልዩ ልዩ የአውሮፓ ከተሞች አንዲሁም በአሜሪካ የአለም ባንክ ጽ/ቤት እና በበርካታ ስቴቶች እንዲታይ ተደርጓል።

 

ይህ ፊልም የተሰራበትት የአቀራረፅ ጥራቱ እና ቴክኖሎጂው የረቀቀ ሆኖ አይደለም። ፊልሙ የተወደደው በውስጡ ባለው የቅዱስ ላሊበላ ታሪክ ነው። በሠው ልጁ ታሪክ ውስጥ ኘላኔቷ ካሏት ትንግርቶች መካከል አንዱ ላሊበላ በመሆኑ ነው።

ላሊበላ ፎቅ ቤትን ወደ ላይ አይደለም የሰራው። እለት እየፈለፈለ ወደ ታች ነው የሠራው። ሰዓሊ እና ቀራፂ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲት የሥነ-ጥበብ መምሕር የሆነው በቀለ መኮንን ሲናገር የሰው ልጅ ወደ ታች ፎቅ ቤት የሠራው እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ይላል። እሡም ቅዱስ ላሊበላ ነው።

 

ዶ/ር አያሌው ሲሣይ የአገው ሕዝቦችና የዛጉዌ ሥርወ መግንስት ታሪክ የተሠኘ መፅሐፍ አላቸው። በዚህ መጽሐፋቸው ውስጥ ስለ ዛጉዌ ሥርወ መንግሥት እና ስለ ነገስታቱ ብዙ ማብራሪያ ሠጥተዋል። በተለይ ስለ ቅዱስ ላሊበላ ሲፅፉ የዚህ ንጉስ ዘመን መንግሥት የኢትዮጵያ የብርሃን ዘመን እንደነበር አውስተዋል።

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነው አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ በላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎች አሠራር ጥበብ በፍቅር የወደቀ ሠው ነው። ምክንያቱም የአብራኩን ክፋይ ልጅን ቤተ-ላሊበላ በማለት ስም ሰይሞለታል። ላሊበላ ለራሡ ማረፊያ የሚሆን ቤት አልሠራም። ቤተ-መንግስቱ የት እንደሆነ አይታወቅም። ነገር ግን በርካታ አብያተ-ክርስትያናትን አሣንጿል። ለዚያም የአሠራራቸው ምስጢር እስከ ዛሬ ድረስ ምን እንደሆነ አይታወቅም። ስለዚህ ፋሲል የላሊበላን ቅንነት እና ጥበበኝነት ለማስታወስ የልጁን ስም ቤተ-ላሊበላ በማለት ሰየመው።

 

ላስታ ውስጥ ተወልደው ለከፍተኛ ደረጃ ከደረሡ ሰዎች መካከል አንዱ ዲያቆን መንግሥቱ ጐበዜ ነው። መንግሥቱ ጐበዜ በታሪክ የመጀመሪያ ድግሪውን ሲሠራ በላሊበላ ላይ ነው ጥናቱን ያደረገው። ሁለተኛ ድግሪውን በአርኪዮሎጂ ሲሠራም መንግሥቱ ጐበዜ ጥናት ያደረገው በላሊበላ ኪነ-ሕንፃዎች ላይ ነው።

 

የዚህች ኘላኔት ድንቅዬ ስራ ነው ላሊበላ በማለት የሚናገሩት ኘሮፌሰር ዴቪድ ራፍካይንድ ናቸው። ኘሮፌሰር ራፍካይንድ በአሜሪካ እና በአውሮፓ የታወቁ የአርክቴክቸር /የኪነ-ሕንፃ/ ታሪክ ተመራማሪ ናቸው። እርሣቸው ሲናገሩ ላሊበላ እንዴት እንደተሠራ ማወቅ አስቸጋሪ ነው ይላሉ። ለምሣሌ አለት ሲፈለፈል ምን ታስቦ ነው? አርክቴክቱ ማነ ነው? ምን ላይ ዲዛይኑ ተሠራ? የመሣሠሉት ጥያቄዎች በሙሉ መመለስ አይችሉም። ስለዚህ ምስጢር ወይም Mystery ነው በማለት ኘሮፌሰር ዴቪድ ራፍካይንድ ይገልፃሉ።

 

ላሊበላ ሀገሩ ኢትዮጵያን 40 አመታት መርቷታል። በዘመነ ስልጣኔ የሐገሩን ዜጐች መብትና ጥቅማቸውን ጠብቆ የኖረላቸው መሪ ነበር። ግብፆች በአባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን የበላይነት ያስቆመም መሪ ነበር። አባይን እገድባለሁ እያለ በየጊዜው ስለሚነሣ ግብፅ ለኢትዮጵያ  መንግሥት የሚገባውን ወሮታ በየጊዜው ትከፍል ነበር።

 

ላሊበላ ቄስ ሆኖ ሲቀድስ፣ ንጉስ ሆኖ ሀገረ ኢትዮጵያን የመራ የ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስመ ገናና መሪ ነበር።

ኢትዮጵያን በአለም ላይ ስመ ገናና እንድትሆን ካደረጓት ስራዎች መካከልም የቅዱስ ላሊበላ ፍልፍል ኪነ-ሕንፃዎች ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስ እና የባሕል ድርጅት እፁብ ድንቅ ከሆኑ የሠው ልጅ ስራዎች መካከል አንዱ አድርጓቸው በአለም ቅርፅነት ከመዘገባቸው ቆይቷል። ላሊበላ በሠራቸው ስራዎች ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያ ትጠቀማለች።

 

ዛሬ ምሽት ላይ የገና በአል ላስታ ላሊበላ ውስጥ እጅግ በደመቀ ሁኔታ ይከበራል። ከሐገሪቱ ልዩ ልዩ ስፍራዎች የመጡ ምዕመናን እና ከአለም ዙሪያ ገናን ላስታ ውስጥ ለማክበር የሚመጡ ሠዎች 10 የላሊበላን ረቂቅ ኪነ-ሕንፃዎችን ያያሉ።

 

 

በአንደኛው ምድብ፡-

1ኛ ቤተ-መድኃኔዓለም

2ኛ ቤተ-ማርያም

3ኛ ቤተ -መስቀል

4ኛ ቤተ-ደናግል

5ኛ ቤተ-ደብረ ሲና /በጣራው ስራ ቤተ-ሚካኤል፤ ቤተ ጐልጐታና የሥላሴ መቅደስ

 

በሁለተኛው ምድብ

6ኛ ቤተ-ገብርኤልና ሩፋኤል /በአንድ ጣሪያ ውስጥ ያሉ/

7ኛ ቤተ-መርቆርዮስ

8ኛ ቤተ-አማኑኤል

9ኛ ቤተ-አባሊባኖስ

በብቸኛነት ራሡን ችሎ የሚገኝ

10ኛ ቤተ-ጊዮርጊስ ናቸው።

 

በሰሞነ ህማማት በተለይ የቅዱስ ላሊበላ እና የጌታችን የመድሃኒታችን የእየሡስ ትንሳኤ በአል በተለየ ሁኔታ ይከበራል።

ዶ/ር አያሌው ሲሣይ በመጽሐፋቸው ሲገልፁ የአከባበሩ ሥነ-ሥርዓት በሌሎች የኢትዮጵያ አብያተ ክርስትያናት በሙሉ ከሚደረገው ለየት ያለና እጅግ በጣም የደመቀ በጣሪያ-የለሸ ቦታ ላይ የሚከናወን ነው። የአስሩ የላሊበላ አብያተ-ክርስትያናትና የዙሪያ ገቡ አድባራት ካህናት/መዘምራን ዲያቆናት ቀሳውስት/ በጥንግ ድርግብ፣ በሸማ፣ በካባ፣ በማጌጥ እና ማበሸብረቅ መቋሚያ፣ ፀናጽል፣ ከበሮ፣ መስቀል፣ ዣንጥላ እና የመሣሠሉትን ይዘው ግማሾቹ ማሚጋራ ተብሎ በሚታወቀው በቤተማርም የቋጥኝ አጥር ዙሪያ ከላይ ወጥተው በመደርደር ሲሰለፉ ቀሪዎቹ በበኩላቸው ከታች ከግቢው ከወለሉ በመሆን ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ ይላሉ። ሲተረጐምም የዓለም መድሐኒት ተወልደ። የሚለውን የቅዱስ ያሬዳን ዕዝል ዜማ ተራ በተራ እየተቀባበሉ ይወርብታል። ይዘምሩታል።

ላሊበላ ኪነ-ሕንፃው ተአምር፤ ሐይማኖታዊው ክብረ-በዓል መንፈስን የሚያፀዳ ቦታው የተባረከና የቅዱሣን ደብር ነው። ላስታ ላሊበላን እንያት።

 

“ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” በሚል መሪ ቃል በደብረማርቆስ ከተማ ጎዛምን ሆቴል የስነ-ፅሁፍ ምሽት መሰናዳቱን ዘመራ መልቲ ሚዲያና ፕሮዳክሽን አስታወቀ። ቅዳሜ (ሚያዝያ 7 ቀን 2009 ዓ.ም) ከምሽቱ 11፡30 ሰዓት የሚጀምረው ይህ የጥበብ ድግስ አንብበው ለወገን የሚያጋሩት ማንኛውንም አይነት መፅሐፍ በማበርከት መሳተፍ እንደሚቻል አዘጋጆቹ ተናግረዋል። የተሰበሰበው መፅሐፍ ለህዝብ ቤተ መፅሐፍት እንደሚበረከት የተጠቆመ ሲሆን፤ በመፅሐፉ የውስጥ ገፅ ላይ የለጋሹን ስምና ፊርማ እንዲኖርበትም አዘጋጆቹ ጠይቀዋል። የስነ-ፅሁፍ ምሽቱን ለመታደም አንድ መፅሐፍ እንደመግቢያ ይዞ መገኘት በቂ ሲሆን፤ ከጥበብ ድግሱ ባለፈ የመፅሐፍ ንባብን ለማበረታታት የሚያግዙ መጣጥፎች፣ የወግና የስነ-ግጥም ስራዎች እንዲሁም ጭውውቶች እንደሚቀርቡ የፕሮግራሙ አዘጋጆቹ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። 

 

በጥበቡ በለጠ

ቅድስና ከረከሰውና ከተበላሸው የስጋ ህይወት ውጭ ባለው ሌላኛው መንፈሳዊ ህይወት ውስጥ ለመኖር የሚመጣ ዓለም ነው። ቅዱስ ሲባል ሙሉ ህይወቱን ለሰማይ አምላክ የሰጠ፣ ከኛ ምድራዊያን የዓለም ህዝቦች በጣም በተሻለ ለፈጣሪ የቀረበ ነው።

ይህ ከላይ በርዕስነት የቀረበው ሃሳብም እንደኛ ስጋና ነብስ ተሰጥቶት ባይንቀሳቀስም በውስጡ ፍፁም መንፈሳዊ ህይወትን የሚቃኝ ነው። ከመንገዶች ሁሉ ወደ ፈጣሪ የሚወስደውን የተሻለ መንገድ የሚመራን፣ ብርሃን ረጭቶልን የነፍስን ደማቅ ዓለም የሚገልፅልን እና የሃሰትን መንገድ እንዳንሻ የሚያደርግ ነው ይላሉ የእምነት ሰዎች።

በዘመናዊው የዲሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ውስጥ ሲዳክሩ የነበሩ እና በሶሻሊዝም መርህ ውስጥ ጭልጥ ብለው ወዛደራዊ ዓለማቀፋዊነት፣ የላብ አደር፣ ብሎም በማርክሲስት ሌኒኒስት ፍልስፍና ህግጋት ይመሩ የነበሩ ሰዎች ሀሳቡን አይቀበሉትም። የነሱ ቅዱሳት ሌሎች ናቸው። እነዚህን ሁለት ፅንፎች ለማወዳደር ጊዜውም መድረኩም አይበቃም። ይሁን እንጂ ለሚሊዮኖች የመንፈስ ምግብ ስለሆኑት ቅዱሳን መፃህፍት ለዛሬ ትንሽ እናውጋ።

በረጅሙ ወደ ኋላ መለስ ብለን እንንደርደርና እንነሳ። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ850 አመተ ዓለም ስነ-ፅሁፍ ሱሜሪያዊያን፣ ቻይናዊያን፣ ግሪኮችና ሮማዊያን ዘንድ እንደ ዳበረ ታሪክ ያወሳል። ይህ የስነ-ፅሁፍ ፈለግ ከእምነቱም በአለማዊ ህይወቱም እያጣቀሰ ነበር ሲራመድ የቆየው።

ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያም ስንመጣ በተለይ በአራተኛው ክፍለ ዘመን ወይም እ.ኤ.አ በ340 አመተ ዓለም ንጉሥ ኢዛና ከባዕድ አምልኮ ወደ ክርስትናው ዓለም ሲገባ አዳዲስ ነገሮች መጡ። አንደኛው በተለይ ለብዙ ዘመናት ከተንሰራፋው ባዕድ አምልኮ ወጥቶ ክርስትናው ላይ ወዳጅነት ሲመሰረት በቃል ስብከት ከማድረግ በተጨማሪ በጽሁፍም የተጀመረበት ወቅት በመሆኑ ነው። ቅዱስ ሃሳቦች በጽሁፍ መስፈር የጀመሩበት ጊዜ መሆኑ በታሪክ ድርሳን ውስጥ ቁልጭ ብሎ ሰፍሯል።

በቀደመው ዘመን ለተጠራበት ነገር ሁሉ አለሁ ብሎ ግንባር ቀደም የሚሆነው የግዕዝ ቋንቋ ለዚህም እምነት መስፋፋት አለበት ብሎ ከተፍ ያለው እሱ ነበር። በተለይ የክርስትናው እምነት ውስጣቸው ገብቶ ፍፁም ሀሴትን የሚሰጣቸው ሰዎች ግዕዝ የመላዕክት ቋንቋ ነው ሲሉ በስፋት ይሰማሉ።

በመጀመሪያ ደረጃ የጽህፈቱ ተግባር ያቀናው መፅሐፍ ቅዱስን ወደ መተርጐም ነው። ከመፅሐፍ ቅዱስም በመጀመሪያ የተተረጐመው ብሉይ ቀጥሎም ሀዲስ ኪዳን ነበር።

ከብሉይ ኪዳን ጋር ሲነፃፀር አጭር ነው። ሁለቱም የተተረጐሙት በግዕዝ ነው። ግዕዝ የትርጉም ስራ ማከናወኛ ሆነ የተባለውም ከዚህ ዘመን ጀምሮ ነው። በተለይ ብሉይ ኪዳን እንደየ አተረጓጐሙ እና ሁኔታው አንዳንድ ችግሮች ነበሩበት የሚሉ የስነ-መለኮት ተመራማሪዎች ያጋጥሙ ነበር።

አንዳንድ ሰዎች ብሉይ ኪዳን የተተረጐመው ከኢብራይስጥ ነው ይሉ ነበር። ሌሎች ደግሞ ኧረ ተው ከግሪክ ቋንቋ ነው ትርጓሜ የመጣው” ብለው ምንጩን ለማግኘት ደፋ ቀና የሚሉ ታታሪ ተመራማሪዎች አሉ። እባካችሁ የጠራውን አንዱን እውነታ ንገሩን ብለው ዳር ቆመው ወሬ የሚጠብቁ እንደ እኔ አይነት ሰዎችም መኖራቸውን አትዘንጉ። አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ ብቻ ናቸው የተተረጐመው ከግሪክ ቋንቋ ነው በማለት በሙሉ ልብ የተናገሩት።

እነዚህ ቅዱሳት መፃህፍት የተተረጐሙት በሃይማኖት ምክንያት ከሶሪያ ተሰደው የመጡ መነኮሳት እንደሆኑም ሹክ የሚሉ ፀሀፍት አሉ። እነዚህ ፀሐፊዎች የሚያነሱት መረጃ ደግሞ እንደ ቄስ፣ አርባ የመሳሰሉ ቃላትን በመንቀስ የተገኙት ከሶርያ ነው የሚል አዝማሚያ አላቸው።

በቅርቡ አንድ ጆሽዋ የተባለ አይሁዳዊ ፎቶግራፍ አንሺ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር። የመጣበት ምክንያት ስለ ቤተ-እስራኤላውያን የብዙ ሺ አመታት የኢትዮጵያ ቆይታና ተግባር በፎቶ ግራፍ ሊያነሳ ነበር። በርግጥም ብዙ ነገር ተሳክቶለታል። ይህን ሰው አግኝቼው ኢትዮጵያን እንዴት ትገልፃታለህ አልኩት። ጆሽዋም ፈገግ ብሎ አንዳንዴ ሀገሬ እስራኤል ያለሁ የመስለኛል አለኝ። ምነው አልኩት። እሱም የተለመደውን ፈገግታውን እያሳየኝ ኢትዮጵያ ውስጥ እስራኤል በጣም ትጠቀሳለች። በየቤተ ክርስትያኑ የእስራኤል አምላክ ይባላል። በላሊበላ አብያተ ክርስትያናት፣ በጐንደር አብያተ መንግሥታት ግድግዳ ላይ ሁሉ የዳዊት ኮከብ አለ፣ ቄሶቹ ስማቸው ‘ካህን' ይባላል። እኔ ሀገር ደግሞ ‘ካህን' ይባላሉ። እነዚህንና የመሳሰሉት ነገሮች ሳይ ሀገሬ ያለሁ እየመሰለኝ ነው አለኝ።

ኢትዮጵያ ሀገራችን ከብዙ ሀገሮች ጋር በነበራት ግኑኙነት የተነሳ ከየሀገራቱ የምታገኛቸውን ታላላቅ ምልክቶችና አርማዎች በማስታወሻነት በቤተክርስትያኖቿ ውስጥ አስቀምጣቸዋለች። በተለይም ደግሞ ከክርስትናው እምነት በፊት የነበሩትንም አርማዎች ሁሉ ከየሀገራቱ ተጠቅማባቸዋለች። አንዳንዱን ደግሞ ወደ ሀገርኛም ቀይራ ከራሷ እምነትና ቀኖና ጋር አዋህዳቸዋለች። ለምሳሌ ኦርጅናሌው የዳዊት ኮከብ ምልክት ከ800 አመታት በሆናቸው ቤተ-ክርስትያኖች ውስጥ ይገኛል። አስገራሚው ነገር ይኸው ምልክት ወደ ኢትዮጵያውኛ ተቀይሮ መሀሉ ላይ የመስቀል ምልክት ተደርጐበት የቅዱስ ላሊበላ ማህተም ነው ይባል ነበር።

ከዚህ ሌላ በህንድ ሀገር ውስጥ የፀሐይ ምልክት ነው የሚባለው የስዋስቲካ አርማ በሀገራችን አብያተ ክርስትያናት ከአንድ ሺ አመታት በላይ አገልግሎት ላይ ውሏል። ዛሬም በየሄድንበት ታሪካዊ የእምነት ቦታዎች ላይ ሁሉ እናየዋለን። ኢትዮጵያ የየሀገራቱ የታሪክ ማህደር ሆና መቆየቷን የምታስመሰክርባቸው ሁኔታዎች በርካታ ናቸው ማለት ይቻላል። በአጠቃላይ ግን ይህን ምልክት አዶልፍ ሂትለር ለአገዛዙ ዘመን አርማ አድርጐት መቆየቱም መረሳት የለበትም።

ወደ ጀመርነው ቅዱሳን መፃህፍት እንመለስ። እስከ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ቅዱሳን መፃህፍት ወደ ኢትዮጵያ በሙሉ ተተርጉመው አልቀዋል። በዚህም የግዕዝ የቃላትና የመንፈስ ሀብቱ በልፅጓል። እንዲያውም ከራሱ አልፎ ለዓለም ስነ-ጽሁፍ አንድ ውለታ አድርጓል። ለምሣሌ መጽሐፈ ሔኖክ በሌላው ዓለም በጦርነትና በተለያዩ ምክንያቶች ጠፍቶ ነበር። በኋላ በግዕዝ ውስጥ ተገኘ። ከግዕዝ ውስጥ ተተርጉሞ እንደገና ለዓለም ተሠራጭቷል። በሀገራችን የቋንቋ አርበኛ ወይም ጀግና ቢኖር ኖሮ ግዕዝ ቋንቋ ላበረከተው ውለታ ከዩኔስኰ አንዳች ነገር ያስደርግ ነበር። ከታሰበ አሁንም ግዜ አለ።

ግዕዝ ከቅዱሳት መፃህፍት ሌላ የሃይማኖት ማስተማሪያ ሰነዶችም እንደተፃፉበት የቋንቋ ሊቁ ዶ/ር አምሳለ አክሊሉ በጥናታቸው ላይ ገልፀዋል። ከእነዚህ ውስጥም የሚከተሉትን ማየት ይቻላል።

ቄርሎስ

ቄርሎስ የትርጉም መፅሐፍ ነው። መፅሐፉ ስሙን የወሰደው መግብያው ውስጥ በፃፈው ሰውዬ ቄርሎስ በሚባለው ሰውዬ ነው። ምሁራን እንደሚናገሩት ቄርሎስ መግቢያውን እንጂ መፅሐፉን በጭራሽ አልፃፈውም ይላሉ።

ይህ መፅሀፍ ሦስት ክፍሎች አለት፡-

1.  የቄርሎስ መግብያ ሀተታ

2.  ስለ ክርስቶስ፣ ስለ ሥላሴ ባህሪ የተሰጠን ሀተታ የሚያካትቱ ናቸው።

ሀተታው ክርስቶስን መሠረት አድርጐ ነው የተፃፈው። ልዩ ልዩ የትምህርት ፅሁፎችም አሉበት። ይህ መፅሐፍ የተተረጐመበት አመት በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ Weischer የተባለ ሰው እ.ኤ.አ በ1971 በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር መጽሔት ላይ ፅፎታል።

ፊሳሊጐስ

በኢትዮጵያ ውስጥ በትርጉም ስራ እኔ በበኩሌ ከፍተኛ ቦታ የምሰጠው መጽሐፍ ቢኖር ይሄኛው ነው። ጉዳዩ አስገራሚ ነው።

ይህ ፅሁፍ /ትርጉም/ የስነ-ፍጥረት ሀተታ ነው። ስለ ልዩ ልዩ እንስሳትና ማዕድናት የተፈጥሮ ባህሪ በሰፊውና በጥልቀት የሚገልፅ መፅሐፍ ነው። የመፅሀፉ ዓላማ የክርስትና እምነት ማስተማርና ማስፋፋት ነው። ታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚያስረዱት መጽሐፉ በግብፅ እስክንድርያ ከ200-300 ድህረ ክርስቶስ በሦስት ቋንቋ የተፃፈ ነው ይላሉ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግዕዝ የተተረጐመው ከግሪክ ነው። ወደ ኢትዮጵያም እንዲገባ ምክንያት ሆነውታል ተብለው በሰፊው የሚነገርላቸው ሶርያዊያን መነኮሳት ናቸው። ኮንቲሮሲኒ የተባሉት አጥኚ ገለፁት የሚባለው እውነታ፣ መጽሐፉ የተተረጐመው የመጀመሪያዎቹ ቅዱሳት መፃህፍት ከተተረጐሙ በኋላ እንደሆነ ነው። ይህ መጽሐፍ በመካከለኛው ዘመን ሰፊ ተቀባይነት የነበረው ሃሳብ እንደነበር ይወሳል። በኋላ ግን ይላሉ አጥኚዎች፣ ጉዳዩ ዋጋ እያጣ የመጣው ዘመናዊ የሳይንስ እውቀት እየተስፋፋ ሲመጣ እንደሆነ ይገልፃሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ዛሬም ተቀባይነቱን ሳይለቅ በቀሳውስት ዘንድ ለዘለዓለም ይኖራል።

ስርዓተ መነኮሳት

በግብፅ ውስጥ በተለይም በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስርዓተ መነኮሳት ተስፋፍቶ እንደነበር የቋንቋን ውልደትና እድገት የሚያጠኑ ምሁራንም ሆኑ ስነ-መለኮታውያን ያስረዳሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ከግብፅ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስለነበራት ይህ የምንኩስና እና የብህትውና ህይወት በዚህችው ሀገር ተስፋፍቶ ኖሯል። ዛሬም እያየለ መጥቷል። ከግብፅም ሆነ ከማንኛውም ሀገር በልጧል። የሀገራችን ገዳማት ውስጥ ምንኩስናው ተበራክቶ ይታያል።

ለጊዜው ሰፊ ጥናት ያልተደረገበት አባ ባኮምዮስ የሚባል ሰው ግብፅ ውስጥ የብህትውና ኑሮ ጀመረ። ይህ መነኩሴ ራሱ ባህታዊ ብቻ አልሆነም። ህግም አውጥቷል። እሱ ያወጣው ህግ በግሪክና በላቲን ተፅፎ በዓለም ላይ ተበትኗል። በዚህ መሠረት ስርአተ መነኮሳት በሚል ርዕስ ኢትዮጵያ ውስጥ ተተርጉሟል። ለኢትዮጵያዊያን መነኮሳት መንገድ ጠራጊና መሪ እንዲሁም መሠረት ሆኗል። ከኢትዮጵያ የቤተ-ክርስትያን ህግጋትና ሁኔታ ጋር ተስማሚ እንዲሆን ነው የተተረጐመው:: ዛሬ ኢትዮጵያን የመነኮሳት ምድር ያደረጋት መጽሐፍ እሱ ነው እያሉ ብዙዎች ጣታቸውን ይቀስሩበታል።

ቀሳሪዎቹ ደግሞ ከእምነት ኬላ አምልጥው በአለማዊው ህይወት አስበው፣ አውጥተው፣ አውርደው ቃላት የሚሰነዝሩ ናቸው። የዓለም ፖለቲካዊ አካሄድ ግምት ውስጥ በማስገባት ማብራሪያ ይሰጣሉ። የዛሬዋን ግብፅ ጠቁመው ለኢትዮጵያ የሰጠችንን ‘የቤት ስራ' በትጋት እየሰራንላት ነው እያሉ በአደባባይም ባይሆን በባንኮኒ ጨዋታ የሚያወጉኝ ምሁራን አሉ።

ምሁራኑ የአባይን ወንዝ ጉዳይ የጨዋታ መክፈቻ አድርገው ወደ ታላቁ ሀሜት ይገባሉ። አንደኛው ሀሜት እነዚህ የእምነት ቀኖናዎች፣ ዶግማዎች ጠንካራ ትዕዛዞች ወዘተ. ድሮ ድሮ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ ሲሰነዘሩ የቆዩ ነበሩ። ግብፆቹ እርግፍ አድርገዋቸው ሲተው ኢትዮጵያዊያኖቹ ደግሞ የበለጠ አስፋፍተዋቸው ይዘዋቸዋል። እናም ቆም ብለን አሰብ አድርገን የአባይን ጨዋታ እናምጣ ይላሉ።

‘እምነት እየጠነከረ ሲሔድ ድህነትን ያስከትላል’ የሚል ቀመር ያላቸውም አሉ። እንደ ማስረጃም የሚያዩት የሃይማኖት ሰዎችንም ወይም መሪዎችን የፈሰሰ ውሃ እንኳን አያቀኑም የሚሏቸው በርካታዎች ናቸው። ሃይማኖታዊ ስርዓተ ትምህርቱም ተስፋፍቶ በመላው ህዝብ ላይ የስራን ባህል እንዳይቀንስ የማንቂያ ደወል ቢጤ ጥቆማ ያደርጋሉ በዓለማዊ መንገድ የሚያስቡት ሰዎች። ከ366 የአመቱ ቀኖች ውስጥ ስራ አይሰራባቸውም የሚባሉት ተቆጥረው ሲወጡ አስደንጋጭ ነው። ስለዚህ ጥንቡን የጣለውን የድህነት ገጽታችንን መለስ ብለን መመልከትና አንኳሩን ምክንያት ማወቅ አለብን።

*   *   *   *

ኤፒክ ምንድን ነው?

ኤፒክ በጥንት ግሪካዊያን ዘንድ የዳበረ ስነ-ፅሑፍ ሲሆን ረጅም፣ ተውኔታዊ ሳይሆን ተራኪ፣ ጀግናዊ ግጥም ነው። የሰውን ልጅ ታላላቅ ክንዋኔዎች፣ ጥበቦች፣   አፈ-ታሪኮች፣ ሌሎችንም የሀገርና የህዝብ ታሪኮች የያዘ ነው።

የኤፒክ ገፀ-ባህሪያት

የኤፒክ ገፀ-ባህሪያት ሁለንተናዊ /Universal/ ናቸው። ከራሳቸው እድል ጋር የሰዎችን ወይም የሀገርን እድል ይዘው ስለሚነሱ ታላላቅ ጀግኖች /Hero's/ የሚያትት ነው።

ለምሳሌ ያህል ግሪካዊው ዓይነ ስውር ደራሲ የነበረው ሆሜር ሁለት መፃህፍትን ፅፏል። ኦልያድ እና ኦዲሴይ የተሰኙ። የኦልያድ ገፀ-ባህሪ Achilles ይባላል። አኪሊስ የጦር ጀግና ሲሆን በሱ ምትክ ጓደኛው ይሾማል። እንዲህ አይነት ትራጄዲ የሚደርስባቸው ገፀ-ባህሪያት በስነ-ፅሁፍ ውስጥ አኪሊስ ታይፕ /Achilles Type/ በመባል ይታወቃሉ።

የኦዲሴ ገፀ-ባህሪ ኦዲስስ /Odysseus/ ሲሆን ከጦር ሜዳ ቤቱ ለመድረስ መከራውን ያየ ሰው ነው። ቤቱ ሲደርስ ሌላ ችግር ተፈጥሮ ይጠብቀዋል። ይህ ዓይነት ትራጄዲ የሚገጥማቸው ገፀ-ባህሪያት /Odysseus Type/ ይባላሉ።

መቼት /Setting/

የኤፒክ መቼት እጅግ ሰፊ ነው። በምድር፣ በሰማይ፣ በባህር፣ በአውሎ ነፋስ፣ በጫካ ... ሊፈፀም ይችላል።

በኤፒክ ውስጥ ገፀ-ባህሪያት ከፍተኛ ትግሎችን ያደርጋሉ። የማይታወቁ መናፍስት፣ የማይታወቁ ኃይሎች ሁሉ ተሳታፊ ይሆናሉ። ይህም ማለት በታሪኩ ውስጥ መለኮታዊ ኃይላት ሁሉ ተሳታፊዎች ናቸው።

በአቀራረቡ ከፍተኛ የትረካ ብልሀት የሚታይበት ነው። በግጥም፣ በምጣኔ፣ በሉአላዊ /Elevated/ ቋንቋ የሚቀርብ ነው። የጥበብን አማልክት እየተማፀነ የመሄድ ዘዴ አለው።

ታሪኩ በንግርት /Foreshadowing/ አልያም በምልሰት /Flashback/  ሊቀርብ ይችላል። ብቻ እንደ የሁኔታው“ እና አመቺነቱ ይቀያየራል።

በታሪኩ ውስጥ የሚካተቱት ገፀ-ባህሪያት በአብዛኛው ታላላቅ ገዢዎች፣ ሀብት እውቀት ፀጋ ያላቸው ብቻ ልዕለ ሰብአዊያን ናቸው።

ኤፒክ የአንድ ዘመንን ታሪክ ብቻ አያወሳም። በዘመነ ሂደት ውስጥ የሚታዩትን ለውጦች እንቅስቃሴዎች እየመዘዘ ውብ በሆነ ቋንቋ ያሳየናል።

ኤፒክ በሁለት ይከፈላል። አንደኛው የቃል /Oral ወይም Primary epic/ በመባል ሲታወቅ ሁለተኛው ደግሞ የፅሁፍ /Written ወይም Secondary epic/ ይባላል።

ከሆሜር ኤፒኮች ሌላ በዓለም ከሚታወቁት ውስጥ በ10ኛው ክፍለ ዘመን የተፃፈው የዴንማርክን ታሪክ የሚገልፀው Beowulf የተሰኘው መፅሐፍ ነው። መፅሐፉ የDanish Kingdom Beowulf የተባለው ጀግና ሆርትጋር ከተማን ለመታደግ ከድራጐን ጋር ያደረገውን ትግል የሚያወሳ ነው።

ሌላው በቨርጂል የተፃፈው Aeneid የተሰኘው ኤፒክ ነው። በ14ኛው ክፍለ ዘመን የተፃፈው ይኸው የሮማ ኤፒክ ብትሮይ መውደቅ በኋላ ስለነበረው Aeneid ስለተባለው ጀግና የተፃፈ ነው።

Tasso የተባለው ፀሐፊም Jerusalem delivered የተሰኘ ኤፒክ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፅፏል። ኤፒኩ የክሩሴድ /የመስቀል/ ጦርነትን የሚያሳይ እና የየሩሳሌምን ነፃ መውጣት የሚገልፅ ነው።

Paradize lost እና Paradize regain የተሰኙትም መፃህፍት ከዚህ ሰልፍ የሚቀላቀሉ ናቸው።

ዛሬ ዛሬ ግን የኤፒክ ፅሁፎች አይፃፉም። ጀግና ደራሲ ስለጠፋ ነው የሚሉ አሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ ይህን ስነ-ፅሁፍ ሳትሞክረው እስከ አሁን ድረስ አለች። አንድ የኤፒክ ጀግና ትወልድ ይሆን?

 

በጥበቡ በለጠ

ከነገ በስቲያ አርብ መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም ከምሽቱ 11፡30 ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ውስጥ የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ግጥም እና በገና 3 የሥነ -ጽሑፍ ምሽት የተሰኘ ፕሮግራም ይካሔዳል።

ፕሮግራሙን ያዘጋጀው ኢጋ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ሲሆን የዘንድሮውም መርሃ ግብር ለሦስተኛ ጊዜ እንደሚካሔድ ለሰንደቅ ጋዜጣ በላከው መግለጫ ጠቁሟል። በዚሁ አርብ ምሽት ላይ በሚካሔደው ዝግጅት ወጣት እና አንጋፋ ገጣሚያን እንደሚሳተፉ የገለፀ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ ሰለሞን ሳህለ፣ ደምሰው መርሻ፣ መስፍን ወ/ተንሳይ፣ ምልዕቲ ኪሮስ፣ ምንተስኖት ማሞ፣ ረድኤት ተረፈ እና ሌሎችም እንደሚገኙበት ገልፆልናል። ከዚህም በተጨማሪ የግልና የቡድን የበገና ድርደራ (ከ20 በላይ በሚሆኑ የበገና ደርዳሪዎች፣ የቡድን የመሰንቆ ጨዋታ ወግ፣ እንጉርጉሮ እና ሌሎችም የኪነ-ጥበብ ዝግጅቶች በመሶብ የባህል ሙዚቃ ቡድን ታጅበው እንደሚቀርቡ ተገልጿል። በዚህም ዝግጅት ላይ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ተገኝቶ እንዲታደም ጥሪ ቀርቦለታል።

 

በድንበሩ ስዩም

 

የካቲት 9 ቀን 2009 ዓ.ም ከዚህች ዓለም በሞት ተለይተው፣ የካቲት 14 ቀን 2009 ዓ.ም ስርዓተ ቀብራቸው በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተ-ክርስትያን የተፈፀመው ታላቁ የኢትዮጵያ የታሪክ ሊቅ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች እየተዘከሩ ነው። ባለፈው እሁድ መጋቢት 17 ቀን 2009 ዓ.ም ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ከኢትዮጲስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በብሔራዊ ቤተ-መፃህፍትና  ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አዳራሽ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን የተመለከተ ዝግጅት አቅርቦ ነበር።

 

ይኸው ዝግጅት የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን የሕይወት ታሪክ ከውልደት እስከ ሞት እና የሪቻርድ ፓንክረስት ስራዎችን የሚዳስስ መርሃ ግብር ነበር። በዚህም መሠረት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ከሪቻርድ ፓንክረስት ጋር የቅርብ ትውውቅ ስላለው እና ስለ እርሳቸውና ቤተሰባቸውም ከዚህ ቀደም ዶክመንተሪ ፊልም ስለሰራ፣ ጥናትም ስላደረገ የሪቻርድ ፓንክረስትን ታሪክ ከውልደት እስከ ፍፃሜ አቅርቧል። በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ እና ጥናት ባለስልጣን የማይዳሰሱ ቅርሶች ከፍተኛ ኤክስፐርት የሆነው ኃይለመለኮት አግዘው ደግሞ የሪቻርድ ፓንክረስትን ስራዎች ዳሰሳ አድርጓል። ኃይለመለኮት አግዘው የታሪክ፣ የቋንቋ እና የኪነ-ሕንፃ ባለሙያ ሲሆን ከዚህ ቀደምም በሪቻርድ ፓንክረስት ስራዎች ላይ ልዩ ልዩ ጥናትና ምርምሮችን ማድረጉ ይታወቃል። መድረኩን በአጋፋሪነት ሲመራው የነበረው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ እና የታሪክ ባለሙያ የሆነው ሰለሞን ተሰማ ጂ ነው። ዝግጅቱ እጅግ ደማቅ ሲሆን፤ የታዳሚው ቁጥርም ከአዳራሹ በላይ ሆኖ በርካታ ሰዎች ቆመውና መሬት ላይ ቁጭ ብለው ሲከታተሉት ቆይተዋል።

 

እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 3 ቀን 1927 ዓ.ም ለንደን ውስጥ የተወለዱት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ገና የዘጠኝ ዓመት ሕፃን ሳሉ ጀምሮ በኢትዮጵያ ፍቅር የወደቁ፣ ዕድገታቸውና መንፈሳቸው በሙሉ በኢትዮጵያ ታሪክ እና ማንነት ላይ እስርስር ብሎ ለታላቅ ደረጃ መብቃታቸው በመድረኩ ላይ ተነግሯል።

 

እናታቸው ሲልቪያ ፓንክረስትም ኢትዮጵያ በፋሽስት ኢጣሊያ በተወረረችበት ወቅት ሙሉ በሙሉ ስራቸውን ትተው የኢትዮጵያ አርበኛ የሆኑ ናቸው። ሲልቪያ ፓንክረስት ኢትዮጵያን ከፋሽስቶች መንጋጋ ስር ፈልቅቆ በማውጣቱ እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ከኢትዮጵያ አርበኞች ጋር በመሆን ነፃነታችንን የሰጡን የሪቻርድ ፓንክረስት እናት ናቸው ተብሏል።

ልጃቸው ሪቻርድ ፓንክረስትም እድሜ ዘመኑን በሙሉ የኢትዮጵያን ታሪክ ሲያጠና፣ ሲመረምር፣ ሲፅፍ የኖረ የምንግዜም ባለታሪክ እንደሆነ በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

 

ሪቻርድ ፓንክረስት ከሰራቸው እጅግ አያሌ ከሆኑ በርካታ ጉዳዮች መካከል፣ የኢትዮጵያን ጥናትና ምርምር ተቋምን መመስረት፣ የመጀመሪያው ዳይሬክተርም ሆኖ ማገልገል፣ ከዚያም እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ ይህንን ተቋም ሲያገለግል የነበረ የታሪክ ጀግና መሆኑ ተነግሮለታል።

 

ከዚህ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ዘመናት እየተዘረፉ የሄዱ ቅርሶች የት እንደሚገኙ፣ በማን እጅ እንዳሉ ጭምር በዝርዝር ጽፈው አጋልጠዋል። የአክሱም ሐውልትን እና የአፄ ቴዎድሮስን የአንገት ክታብ፣ ጐራዴ እና ልዩ ልዩ ቅርሶች እንዲመለሱ ብርቱ ትግል አድርገው ማሳካታቸው ተነግሯል።

 

ኢትዮጵያን የተመለከቱ የታሪክ ሠነዶችን በማሰባሰብ እና ቅርስ አድርጐ በማስቀመጥ ረገድ ለትውልድ እና ለሐገር ያበረከቱት ወደር የማይገኝለት አስተዋፅኦ በመድረኩ ላይ ተነግሯል።

ሪቻርድ ፓንክረስት ከ22 በላይ መፃሕፍትን ኢትዮጵያ ላይ የፃፉ፣ ከ17 በላይ መፃሕፍትን የአርትኦት ስራ ያከናወነ እና ከሌሎች ጋር ያዘጋጁ፣ ከ400 በላይ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳዮች ጥናትና ምርምር የፃፉ፣ በልዩ ልዩ ጋዜጦችና መፅሔቶች ላይ ኢትዮጵያዊ ታሪኮችን ሲያስነብቡ 60 ዓመታትን የሰሩ የዘመናችን ባለ ግዙፍ ሰብዕና ነበሩ በማለት ተነግሮላቸዋል።

 

ከጥናት አቅራቢዎቹ አንዱ የሆነው ኃይለመለኮት አግዘው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ እንዲሆኑ ከዚህ ቀደም የቀረበውን አቤቱታ ይፋ አድርገዋል።

ኘርፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት የኖቤል ሽልማት እንዲሰጣቸው ከዚህ ቀደም ለድርጅቱ ደብዳቤ ተፅፎ እንደነበር ኃይለመለኮት አግዘው ገልጿል። ይህንን ሪቻርድ ፓንክረስት እንዲሸለሙ ጥያቄ የጠየቁት ዶ/ር ገላውዲዮስ አርአያ፣ አቶ ጳውሎስ አሠፋ፣ አቶ ዳንኤል ግዛው፣ አቶ አፈወርቅ ካሡ፣ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ የዛሬ 8 ዓመት ኘሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ሊሸለሙ ይገባል በሚል የፃፉትን ደብዳቤ ኃይለመለኮት አቅርቦታል።

 

በደብዳቤው መሠረት ኘ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት የሰው ልጅ መብት ተቆርቋሪ መሆናቸውን ይገልፃል። የ82 አመቱ ሪቻርድ አሁንም በጣም ጠንካራ ፀሐፊ የታሪክ ተመራማሪ ከአውሮፓ መጥቶ በደም ለማይዛመዳቸው ሕዝቦችና አገሮች ብዙ የሠራ ብዙ ውለታ የዋለ ታላቅ ሠው መሆኑን ደብዳቤው ይገልፃል። ይህ ሠው በኛ አመለካከት የኖቤል ሽልማት ሊያገኝ የሚችልበት ትልቅ ውለታ ያበረከተ ሠው መሆኑን መመስከር እንችላለን የሚል ሀሣብ ያለው ደብዳቤ መፃፉን ኃይለመለኮት አቅርቧል።

 

ይህን ለኖቤል የሽልማት ድርጅት የፃፉት ሠዎች በእድሜ ትልልቆች የሆኑ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ጠንቅቀው የሚረዱ ሠዎች ናቸው።

ኃይለመለኮት ሲገልፅ ሪቻርድ ፓንክረስት የኢትዮጵያን ጥናትና ምርምር ተቋምን መስርተው ብዙ ማስረጃዎችን ሰብስበው ኢትዮጵያ የብዙ ሺ ዓመታት ባለታሪክ መሆኗን አሳይተዋል፣ አስነብቧል። አንዳንዶች በተሳሳተ አመለካከት ኢትዮጵያን የመቶ ዓመት ታሪክ ያላት አገር ናት እያሉ መናገራቸው እና መፃፋቸው ኃይለመለኮት አግዘው የተሳሳተ መሆኑን የሪቻርድ ፓንክረስት ስብስብ ሥራዎች ይመሰክራሉ ብሏል። በዕለቱ ተጋብዘው ከመጡ ሰዎች መካከል የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የቤተ-መፃህፍቱ ባለሙያ አቶ ዳንኤል ማሞ የሚከተለውን ብለዋል።  

 

ዳንኤል ማሞ

አስር አመት ሆኖኛል ከርሣቸው ጋር ስሰራ። ተቋሙ ኢትዮጵያዊ የሆኑ መፃሕፍትን ከየትም እየፈለገ ይገዛል። አንዳንድ መፃሕፍት 120 ሺብር እና 130ሺ ብር የሚያወጡ ናቸው። ይህን ደግሞ ከመንግስት ባጀት መግዛት አይቻልም። ስለዚህ ሪቻርድ ፓንክረስት ከተለያዩ ግለሠቦችና ተቋማት ገንዘብ እየፈለጉ ተቋሙን በመፃሕፍትና በመረጃ ያበለፀጉ ናቸው። ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሰበሰብ አድርገው መፃሕፍት ገዝተውልናል። እርሣቸው ሔደው የሚያንኳኩት በር ሁሉ

 

 ይከፈትላቸዋል። ምክንያቱም ገንዘቡ ከመፃሕፍት ውጭ ከታለመለት ጉዳይ ውጭ እንደማይባክን ስለሚታወቅ ሁሉም ሠው ሪቻርድ ፓንክረስት ላይ እጁ ይፈታል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ምስሶ እና ማገር ሆነው እዚህ ያደረሱት ኘሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ናቸው።

ሪቻርድ ፓንክረስት የኢትዮጵያን ብራናዎች ቅርሶች መፃሕፍት ሠነዶች ያሠባሠቡ ኢትዮጵያ ታሪኳ ቅርስ አድርገው ለትውልድ አስቀምጠው ያለፉ የምን ግዜም የኢትዮጵያ ወዳጅ ናቸው።

የአውቶብስ ቲኬት ሣይቀር እየሠበሠቡ እንደ ቅርስ የሚያስቀምጡ ከትንሽ እስከ ትልቅ ጉዳዮችን ሠብስበው ያስቀመጡ ሠው ናቸው።

 

ፓንክረስት ኢትዮጵያዊነት በደማቸው ውስጥ የሠረፀ ነው። ሪቻርድ ፓንክረስት እንደ ዲኘሎማት ሆነው ኢትዮጵያን የጠቀሙ ናቸው። የብሪቲሽ ሙዚየም የቴዎድሮስን የአንገት ክታብ እንዲመለስ ያደረጉ ናቸው። የአክሡም ማስረጃዎችን ሠብስበው ኢትዮጵያ የብዙ ሺ አመታት ሀውልት አስመልሠዋል። እንግሊዞች የአፄ ቴዎድሮስን ጐራዴ ለኬንያ ሙዚየም ሠጥተው ነበር። ይህ ኢትዮጵያዊያንና ኬኒያን ለማጣት ይመስላል። ግን ሪቻርድ ፓንክረስት እንደ ዲኘሎማት ሆነው ነገሩ ውስጥ ገብተው ጐራዴው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ አድርገዋል ይላል ዳንኤል ማሞ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ቤተ-መፃሕፍት ኃላፊ።

 

 

***        ***        ***

 

በኢጣሊያ ፋሺዝም

በኢትዮጵያ አይሁዶችን የማስፈር ዕቅድ

በኃይለመለኮት አግዘው

ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረች በኋላ ትከተለው የነበረው መርህ የሀገሪቱን አንድነት በማዳከም የከፋፍለህ ግዛ መርህ ነበር። ፋሺዝም የሩቅ ጊዜ ዓላማ ማስፈፀሚያው የኢትዮጵያ ሕዝብ እርሱ በእርሱ እንዲጫረስ ብሎም በሚፈጠረው  ክፍፍል አገሪቱን አዳክሞ ለመግዛት ይህም ካልተቻለ እርሱ በፈጠረው ዘርና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ አወቃቀር ትናንሽ መንግስታት ተፈጥረው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ማክሰም ነው። ለዚህ እኩይ ዓላማ ማስፈፀሚያ በገንዘብ የተደለሉ ኢትዮጵያውያን ባንዶችና ቡልቅ ባሾች ለቄሳር ተገዙ የሚል ልፈፋቸውን በሰፊው አስተጋብተዋል። በአዲስ አበባ፣ በአስመራ፣ በጎንደር በከተማው ውስጥ የነጭና ጥቁር ሰፈር በአፓርታይድ መልክ ከልለው ተንቀሳቅሰዋል። በዚያን ጊዜም ይሁን በአሁኑ ሰዓት ያለው የኢትዮጵያ ትውልድ ግን ከፋሺዝም ጀርባ የነበሩ ዕቅዶችን ጠንቅቆ አያውቅም። የዛሬይቱ ኢትዮጵያም እንዲህ በቀላሉ ለአሁኑ ትውልድ የተላለፈች ሳትሆን አያት አባቶቻችን ብዙ መስዋዕትነት ከፍለውባት ነው። የዳግማዊ አፄ ምኒልክ መንግስት በአካባቢው ከነበሩ የቅኝ ገዢ ኃይሎች ተሟግቶና ተከራክሮ ግዛቱን ባያሰፋ ኖሮ ምስራቅ ኢትዮጵያ ሶማሊያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ኬንያ፣ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሱዳን፣ ሰሜን ኢትዮጵያም ለኢጣሊያዋ የኤራትራ ኮሎኒ የመሆን ዕድላቸው ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው። የኢትዮጵያ አርበኞች በአገር ቤት ያደርጉት የነበረው የአልገዛም ባይነት ተጋድሎ ፍሬ እያፈራ መምጣቱና  አፄ ኃይለስላሴ በአውሮፓ ከእነ ሲልቪያ ፓንክረስትና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የዲፕሎማሲ ትግል ማካሄዳቸው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆና ለአሁኑ ትውልድ እንድትተላለፍ አድርጓል። ፋሺስቶች የከፋፍለህ ግዛው መርህ እያራመዱ ቅኝ በያዟት ኢትዮጵያ አይሁዶችን የማስፈር እቅድ ጠንስሰው ነበር። ይህ ኢትዮጵያን ለአይሁዶች መስፈሪያነት የማዋል ዕቅድ የከሸፈው የዳበረ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና በነበራቸው ኢትዮጵያውያን አርበኞች ያላሰለሰ ተጋድሎና በራሳቸው በአይሁድ ምሁራን እምቢተኝነት ነው።  እዚህ ላይ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የአውሮፓ ጉዞ በዲፕሎማሲው መስክ የነበረው አስተዋፅኦ ቀላል አልነበረም።

 

አይሁዶችን  በኢትዮጵያ የማስፈር ዕቅድ

አይሁዶችን  በኢትዮጵያ የማስፈር ዕቅድ ከ1936 እስከ 1943 በሚል ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትስት ከ45 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ኦብዘርቨር /Ethiopia Observer/ ባስነበቡት ፅሁፍ የሙሶሎኒ ኢትዮጰያን በ1935 እ.ኤ.አ መውረርና ወረራውን ተከትሎ በተለይም በፋሺስት ኢጣሊያና በናዚዋ ጀርመን ውስጥ የተቀሰቀሰው ፀረ-ሴማዊ (አይሁድ) እንቅስቃሴ ለተለያዩ ፀረ-አይሁድ ዕቅዶች መጠንሰስ በተለይም አይሁዶችን በገፍ በኢትዮጵያ የማስፈር  ዕቅድ እንዲፀነስ የሐሳብ መሰረት ጥሏል።

 

ሐረርጌንና የእንግሊዝ ሶማሌላንድን ማጣመር

ይህ ወቅት በአውሮፓ ኢጣሊያ ውስጥ ነዋሪ የነበረው ፉሩንበርግ የተባለ አይሁዳዊ ሐረርጌንና እንግሊዝ ሶማሌላንድን በማዋሃድ በአፍሪካ ቀንድ ለአውሮፓውያን አይሁዶች መንግስት  መፈጠር አለበት የሚል ሃሳብ አቅርቧል።

በፈረንሳይ አገር የሚታተም ለተምፕ የተሠኘ ጋዜጣ በምስራቅ አፍሪካ ኢጣሊያ በቅኝ በያዘችው የአቢሲኒያ መሬት አይሁዳውያን ቢሰፍሩበት ምንም ዓይነት ቅሬታ የሌላት መሆኑን ከማተቱም በላይ ሉዓላዊ የሆነ የአይሁዳውያን መንግስት ከአቢሲኒያ መሬት ላይ ተቆርሶ እንዲሰጠው ጠይቋል። ፉረንበርግ የኢጣሊያ ምስራቅ አፍሪካ ጀርመን ፈረንሳይ ኢጣሊያና ስፔን ካላቸው ስፋት የሚወዳደር ትልቅ ግዛት እንደመሆኑ በዚህ ትልቅ መሬት ውስጥ እጅግ ጥቂት ህዝብ የሚኖርበት ከመሆኑም ባሻገር ይህም ህዝብ ተበታትኖ የሰፈረ በመሆኑ በተለይም አቢሲኒያ (ኢትዮጵያ) በተለያዩ የተፈጥሮ ሐብቶች የበለፀገች  ድንግል መሬት ናት ሲል ካተተ በኋላ  ኢትዮጵያን ከፍልስጥኤም ጋር አነፃፅሮ አቅርቧል። ፉረንብርግ  ፍለስጥኤም እጅግ በጣም ጠባብ መሬት በመሆኗ በተለይም የአይሁዶች ጠላቶች በሆኑት የአረብ ፅንፈኞች ከፍተኛ የሆነ ታቀውሞና ግጭት (ጦርነት) ያጋጥማቸዋል ካለ በኋላ በኢትዮጵያ ግን ኢጣሊያ እስካለች ድረስ የአይሁዶችን መስፈር የሚገዳደር ምንም ዓይነት ተቃዋሚም ሆነ ተፃራሪ ኃይል አያጋጥምም ብሏል።

 

“በምስራቅ አፍሪካ ተራሮች የአይሁዶች ጠንካራ የስራ ባህል ክህሎትና የገንዘብ አቅም በኢኮኖሚ ጠንካራ የሆነች አዲሲቷን ጽዮናዊት እስራኤል ከዘመናት እንግልትና ስቃይ በኋላ ይመሰርታል። ይህም በፀረ አይሁድ እመቃዎች ከፍተኛ እንግልት ለደረሰባቸው አይሁዶች ታላቅ ተስፋ ነው” ብሏል።

 

የሂትለሯ ጀርመንም ከውስጥ ችግሮቿ አንዱ የሆነውን የአይሁዶችን በኢትዮጵያ መስፈር አይሁዶችን ከመፍጀቷ ቀደም ብሎ ምንም ያህል አሳሳቢ ያልሆነ ስትል ድጋፏን ገልፃ ነበር።

ፍልስጥኤም ለሁለት መሰንጠቋ አሳስቧቸው ለነበሩ አረቦች ይህ ታላቅ ዜና ነበር። ይህ ዕቅድ ለረዥም ጊዜ ከፅዮናውያን ጋር የነበራቸውን ቅራኔ የሚያረግብ በመሆኑ በተለይም የፍልስጥኤም መሬትን ለሁለት መሰንጠቅ የሚያስቀር በአይሁዶችና በአረቦች በኢየሩሳሌም ላይ የይገባኛል ጥያቄንም ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ የሚፈታ መስሎ ስለታያቸው በተለይም  ሞሶሎኒ  ይህንን ለመፈፀም መነሳቱ የእስልምና ደጋፊና ጥቅም አስከባሪ ሆኖ ታየ። “አይሁዶችከባለመሬቶቹ (ከአቢሲኒያውያን) ጋር ምንም ዓይነት ውጊያ ሳያስፈልጋቸው በኢጣሊያ መንግስት ድጋፍ  ከሺዎች ዓመታት መበታተን በኋላ በተፈጥሮ ሀብት እጅግ የበለጸገ መሬት ባለቤት ባለአገር ይሆናሉ።” በሚል ተስፋ ሞሶሎኒ የአረቦችንና የእስልምና እምነት ተከታዮችን ድጋፍ ያሰባሰበበት ነበር።

በኢጣሊያ በኩል የአኦስታው መስፍን ይህንኑ አይሁዶችን በኢትዮጵያ የማስፈርን ዕቅድ ጥናት እንዲያቀርብ እንዲያስፈፅም በኅዳር ወር1938 እ.ኤ.አ ኮሎኔል ጁዜፔ አዳሚን ባዘዘው መሰረት ረፖርቱን ለአኦስታው መስፍን አቅርቧል።

የዚህኑ ኮሎኔል የግል ማስታወሻ የጠቀሱት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እንደገለጹት፡-

ከፍተኛ የሆነ ልዩ ተልእኮ ተስጥቶት እንደነበረ የሚያትተው አዳሚ የተሰጠው ተልዕኮ 1400 አይሁዶችን ማስፈር የሚያስችል ስፍራ፣ ስፍራውም ከወባ እና መሰል በራሪ ተባዮች የጸዳ የፄፄ ዝንብ የማይገኝበት ውሃ ገብ የሆነ ወይና ደጋ የአየር ፀባይ ያለው ከዋና መንገድ ብዙም ያልራቀ በተለይም ምንም ዓይነት እምነት የሌላቸው ነዋሪዎች በብዛት ያሉበት ስፍራ ወይም ጥቂት የኦርቶዶክስ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ወይም ጥቂት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ያሉበት ስፍራ ተመራጭ መሆኑን አትቶ ይህም የእዚህ እምነት ተካታዮች  ከአይሁድ እምነት ተካታዮች ጋር ግጭት እንዳይፍጠር እንደሚረዳ አስረድቶት በዚህም መሰረት ኮሎኔል አዳሚ ሪፖርቱን እንደሚከተለው አቅርቧል።

 

 

የቦረና ዞን ለአይሁድ ሰፋሪዎች

አዳሚ ለአይሁዶች የመረጠው ስፍራ የአሁኑን በኦሮሚያ ክልል የሚገኘውን  የቦረና ዞን ነው። ከኬንያ ድንበር ወደ ኢትዮጵያ 100 ኪ.ሜ ወደ ውስጥ ገባ ብሎ የሚገኝ ቦረና የተባለው ስፍራ የተመረጠ ስፍራ መሆኑን በሪፖርቱየገለፀው ኮሎኔል አዳሚ ቦረና የአየር ፀባዩ ተስማሚ አፈሩ ለምና ሁሉን የሚያበቅል መሬት ከመሆኑ ባሻገር በሰፊ መሬት ጥቂት ሰዎች የሚኖሩበት በመሆኑ ለአይሁዶች ሰፈራ እጅግ ተስማሚ የሆነ አካባቢ መሆኑን አትቷል። እንደ ኮሎኔሉ ሪፖርት ዞኑ የ 8000 ስኩየር ኪሎሜትር ስፋት ያለው ሲሆን ይህም የፍልስጥኤምን መሬት  ግማሽ የሚያህል ነው። በ1200 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ የሚገኘው ይህ መሬት የዳዋ ገናሌ ወንዝ የሚገኝበት ከመሆኑ በላይ ለከብቶች እርባታ፣ ጥጥ እርሻና እና የጉሎ ዘይት ምርት እንዲሁም በትምባሆ እርሻና በሌሎችም አካባባው ከፍተኛ የመልማት አቅም ያለው መሆኑን ኮሎኔል  አዳሚ በታህሳስ 5 1938 የቀረበውን ሪፖርት የአኦስታው መስፍን  ለሞሶሎኒ አቅርቧል።

ዚሁ በታህስስ 1938 እ.ኤ.አ በኒውዮርክ የሚታተመው የአይሁድ ሰራተኞች ድምፅ  በዚህ የኢጣሊያ እቅድ ላይ ተሳልቋል  ኤስ ኤተለሰን የተባለ አይሁዳዊ ጋዜጠኛ  "እጓለማውታን መሆን ጥሩ ነው" በሚል ርዕስ ባስነበበው ፅሁፍ

"ታላላቅ መንግስታትና ሉዓላዊ ነን የሚሉ አገሮች የሚከራከሩለት ነገር ቢኖር በህግ የተጠበቀላቸውን የተከለለ መሬትና ሉዓላዊነት መንከባከብና መጠበቅ ነው። አይሁዶች ተፈናቃዮች ግን የፈለጉትን መሬት መርጦ የመውሰድ መብት አላቸው። ሂዱና   ሞቃታማውንና ወበቃማውን  የጉያናን መሬት ውሰዱ ቢባሉ ምን ችግር አለ? በደስታ ይቀበሉታል። ሌላው ደግሞ ተነስቶ ሂዱና በምስራቅ አፍሪካ ደኖች ውስጥ ከ ፄፄ (ከቆላ) ዝንብ ጋር የመኖር ምርጫ አለህ ከተባለ ምን ችግር አለ? ሄዶ ሰፍራል ተፈናቃይ ሁሉም ነገር ሁሉም አገር በእጁ ነው።በእውነት አገር አልባ እጓለማውታን   መሆን መልካም ነው።" ሲል በእቅዱ ላይ ተቃውሞ አሰምቷል።

 

ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ (ወለጋና ኢሉባቦር) 

አንደኛውና ዋነኛው አይሁዶችን በምስራቅ አፍሪካ የማስፈር እቅዶች ደጋፊ የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ፍሬድሪክ ዴላኖ ሩዝቬልት ነበሩ። ሩዝቬልት አሜሪካንን ከታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት ያወጡ ለሁለተኛው የአለም ጦርነት ማብቃት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ቢሆንም አይሁዶችን በኢትዮጵያ በማስፈር እቅድ ላይ ተሳታፊ ነበሩ።

ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት በኢትዮጵያ ለሚሰፍሩ አይሁዶች የመረጡላቸው ስፍራ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያን ወለጋ ኢሉባቦርና ከፋ አካባቢን ሲሆን በአጠቀላይ ደቡብ ኢትዮጵያ ለዚህ ተስማሚ በመሆኑ ጉዳይ ላይ በተለይም የአሜሪካ አይሁዶችን በዚያ አካባቢ የማስፈሩ ምኞት ነበራቸው።

 

ጣና ሐይቅና አካባቢው

በወቅቱ የታተመ ኒዎዮርክ ታይምስ ጋዜጣ  20000 የሚሆኑ አይሁዳውያን በጣና አካባቢ መስፈር የሚኖረውን ጠቀሜታ በመግለፅም አትቶ ነበር። ኒዎዮርክ ታይምስ  አትዮጵያ ቁጥራቸው አምስት ሚለዮን የሚሆኑ አይሁዳውያንን በጣና ሐይቅ አካባቢ የማስፈር አቅም አላት። ይህ ሃምሳ ሺ ስኩዬር ማይልስ ስፋት ያለው አካባቢ ብዙ ሰፋሪ የሌለበት ከመሆኑ ባሻገር በዚህ መሬት ላይ ቡና  ስንዴ የተለያዩ የፍራፍሬ ዓይነቶች ጥራጥሬዎችን ማምረት ይቻላል ሲል ሃሳቡን አቅርቦ ነበር። በኡጋንዳ የመስፈር እቅድ የተከተለው በኢትዮጵያ የነበረው እቅድ በመክሸፉ ነው። ሪቻርድ ፓንክረስት ይህንን የመሰሉ ብዙ የታሪክ ፀሃፊዎች ያልዳሰሱትን ርዕስና በኢትዮጵያ ላይ ሲቃጡ የነበሩ ድብቅ ዕቅዶችን ለህዝብ በማጋለጥ በኩል ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

 ከዚህ ቀደም በዶ/ር ገላውዴዎስ አርአያና ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ የሚመራ ቡድን ፓንክረስት እና ቤተሰባቸው ለኖቤል የሰላም ሽልማት መታጨት እንዳለባቸው በመጥቀስ ሙከራ ተደርጎ እንደነበር የሚታወስ ነው። በዚህ አጋጣሚ መታሰቢያ ሳናደርግላቸው ያለፉ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ሰፊ ጥናት ያካሄዱ ፕሮፌሰር ሱቬን ስቬን ሩቤንሰን ፕሮፌስር ዶናልድ ክረሚ ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደአረጋይ ፕሮፌሰር ስርግው ሀብለስላሴ እንዲሁም ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት ዶ/ር ብርሐኑ አበበ ዶ/ር ዓለሜ እሸቴ ዶ/ር ዘውዴ ገብረስላሴ ፕ/ር ዶናለድ ሌቪን ፕ/ር ሃሮልድ ማርከስ ፕ/ር ሁሴን አህመድ የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ታሪክ ምሁራን መታሰቢያ እየተደረገ በስራዎቻቸው ላይ መወያየት አለብን።

በአሁኑ ሰዓት ይህ በእነዚህ ታላላቅ የታሪክ ምሁራን የተጀመረው ታሪክን በሳይንሳዊ መንገድ የማስተማር የትውልድ ቅብብሎሽ በእነፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ ዶ/ር ተካልኝ ወልደማሪያም ዶ/ር ተሰማ ተአ፣ ዶ/ር በለጠ ብዙነህ፣ ዶ/ር ሽመልስ ቦንሳ ፕሮፌሰር ዴቪድ ቻፕልን ዶ/ር ውዱ ጣፈጠን በመሳሰሉ የታሪክ ምሁራን ወጣት ኢትዮጵያውያንን በመቅረፅ ረገድ ላቅ ያለ ሚና ተጫውተዋል። ለታሪክ ትምህርት አግባብ ያለው ስፍራና ቦታ ልንሰጠው ይገባል። በአሉባልታዎችና በበሬ ወለደ ማስረጃ የሌላቸው ተረቶች ወጣቱ ትውልድ መወናበድ የለበትም።

 

በጥበቡ በለጠ

ሰሞኑን በከፍተኛ የስራ ውጥረት ውስጥ እያለሁ አንዲት ትልቅ እንግዳ ከደቡብ አፍሪካ መጣችብኝ። ትልቅ ባለውለታዬ ነች። ሐገርዋ ደቡብ አፍሪካ የዛሬ 13 አመት ለትምህርት ስሄድ በሐገርዋ አብራኝ ተምራለች። የወራት የደቡብ አፍሪካ ቆይታዬንም እንዳይሰለቸኝ ያደረገች ትጉህ ጋዜጠኛ ነች። ቀስተ ዳማናዊትዋ ደቡብ አፍሪካን /The rainbow nation/  እንደ ራሴ አገር መስላ የታየችኝ እንደዚህች አይነት መልካም ሰዎች በውስጥዋ ስላሉ ነው። የሐገርዋን ደቡብ አፍሪካን ታሪክ ጠንቅቄ እንዳውቅ ያደረገችውን ይህችን ጉብል ዛሬ እስዋንና ስራዋን አስተዋውቃችኋለሁ።

ደቡብ አፍሪካዊቷ ዜል ኤልሲ በአፍሪካውያን ‘ባሪያዎች' ላይ ዶክመንተሪ ፊልም በመስራት ላይ ነች። ሀገሯ ደቡብ አፍሪካ ሙሉ ዙሪያዋን በህንድ ውቂያኖስ የተከበበች ሀብታም ሀገር ብትሆንም በዚህ ውቅያኖስ መታጠሯ ደግሞ ሌላም ጉዳት አስከትሎባት ኖሯል። ይህም ከዛሬ 300 አመት በፊት ጀምሮ በውሃ ላይ የጉዞ መሠረታቸውን አድርገው የሚጓዙ ሀገር አሳሾች ከአውሮፓ ተነስተው ሲያስሱ አንድ ለም የሆነ ምድር ያያሉ። ለብዙ ወራት መሬት ሳያዩ፣ መሬትም በጣም ስለናፈቀቻቸው ለማረፍ ሲሉ የመርከባቸውን መልህቅ ያቺ በደስታ ወዳዪት ምድር ላይ ጣሉ። መሬቷንም ሄደው ሳሙ። ምድር ሆይ የተባረክሽ ነሽ አሏት። ለእረፍት ቁጭ ያሉባት ሀገር ደቡብ አፍሪካ ናት። መሬቷ ለም ነው። በውስጧ እምቋ የያዘው ደግሞ ተአምር ነው። የዓለም የከበሩ ማዕድናት ሁሉ የሚገኙት በዚህች ቦታ ነው። አውሮፓውያኑን ገረማቸው። ዛሬ “ፖርት ኤልዛቤት” ተብላ በመትታወቀው የደቡብ አፍሪካ የጫፍ ከተማ የገቡት ሰዎች ወደ ውስጥ መስረግ ጀመሩ።

 

ደቡብ አፍሪካ እነርሱ ከመጡባት አውሮፓ በላይ በመአድናት የተንቆጠቆጠች በወርቅ፣ በአልማዝ፣ በሜርኩሪ፣ በታንታለም ወዘተ. የከበረች ምርጥ ምድር በመሆኗ የአውሮፓ ሰፋሪዎች ከያሉበት ተጠራሩ። እየተከማቹ መጡ። ከተለያዩ ሀገሮች በመምጣታቸውም የአንድ የአውሮፓን ሀገር የቅኝ ግዛት መንግሥት ማቋቋም አልቻሉም። ወይ የእንግሊዝን፣ ወይ የፈረንሣይን፣ ወይ የኔዘርላንድን ወዘተ. መንግሥት ብሎ መመስረት ከባድ ሆነባቸው። ምክንያቱም ሁሉም ገናና የአውሮፓ አገሮች ደቡብ አፍሪካን የዛሬ 300 አመት ከበዋታልና ነው። ስለዚህ የሰፋሪዎች (settlers) መንግሥት መሠረቱ። ከሁሉም ሀገሮች የተውጣጡት ፈረንጆች የነጮች መንግሥት አቋቋሙ። ከዚህ በኋላ ለጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያን የመከራና የሲኦል ኑሮ ጡጫውን አጠንክሮ ሲመጣ፣ ለነጮቹ ደግሞ ገነት ምድር ላይ ተቋቋመች። ተፈጥሮም በሰው ልጆች ላይ የምትከተለውን ህግ አዛብታ ጥቁር ደቡብ አፍሪካዊያንን ለ300 አመታት እጅግ በድላቸው ኖረች።

ከዚህ በኋላ ደቡብ አፍሪካ የባሪያ ንግድ እጅግ የሚጧጧፍባት፣ ሀብቷ የሚመዘበርባት እና በጣም የሚገርመው ደግሞ የተቋቋመው የነጮች መንግሥት ለራሱ እንዲመቸው ለማድረግ ሀገሪቱን ከየትኛውም የአውሮፓ ከተማ ለማስበለጥ እየገነባ የነበረው መሠረተ ልማት ዛሬም ድረስ እነ ኬፕታውንና ደርባንን የመሰሉ ውብ ከተሞች አውሮፓ ውስጥ ማግኘት እንዳይቻል አድርገዋል።

ወደ ዋናው ነጥቤ ልመለስ። ዜል የዛሬ 300 አመት ደቡብ አፍሪካ ከረገጡት ነጮች የዘር ሐረግ የምትመዘዝ ናት። ከአንዱ ገናና ሀገርም የመጡት ፈረንጆች ቤተሰብ ብትሆንም ወደኋላ ሄዳ ያንን የዘር ግንዷን ቆጥራ መመፃደቅ አትፈልግም። እርሷ የምታውቀው ደቡብ አፍሪካዊት መሆኗን ብቻ ነው። የቆዳዋ ቀለም ፈረንጅ ቢሆንም ሌላ የምታውቀው የለም። ሀገር ወዳድ ደቡብ አፍሪካዊት ዜል።

 ዜል የምታስገርም ሴት ነች። ስትናገርም እንዲህ ትላለች፡- እናትና አባቴ ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ በምትሰቃይበት ወቅት ከጥቁሮች ጋር ሆነው የዘር መድልዎን ሲያወግዙ የኖሩ ናቸው። ሠልፍ የሚወጡት ከጥቁሮች ጋር ነው። በዚህ ብቻም አላቆሙም። በተለይ ከምሽቱ 12 ሰዓት ሲሆን ሁሉም ጥቁሮች ከነ ኬፕታውን፣ ደርባን፣ ፕሪቶሪያ፣ ጆሀንስበርግ፣ ፖርት ኤልዛቤት ወዘተ. እንዲወጡ ይደረጋል። ምሽቱን ለነጮቹ ይለቃሉ። በምሽት ከተሞች ውስጥ የተገኘ ጥቁር ይታሰራል ይገደላል። ይህ መከራ ለ300 አመታት ኖሯል። ግን የዜል ቤተሰቦች የጥቁሮቹ የትግል አጋሮች በመሆናቸው እንደ ጥቁሮቹ ሁሉ ማታ ማታ ከከተሞች ውጪ ከጥቁሮች ደቡብ አፍሪካዊያን ጋር በመሆን ነው የሚኖሩት። እናም የማንዴላው ANC አባላት መካከል የዜል ቤተሰቦች በጣም የታወቁ ናቸው። ዜልም ተወልዳ ያደገችው በጥቁሮች መካከል ነው።

ደቡብ አፍሪካ ነፃ ስትወጣ እንደ ዜል ቤተሰቦች አይነት የሆኑ በርካታ ነጮች በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ክብርና ሞገስ አግኝተዋል። ዜልም ብትሆን የቤተሰቦቿ ልጅ ናትና ነብስ ካወቀችበት ጊዜ ጀምሮ ልዩ አትኩሮቷ ጥቁሮች ላይ ነው።

ዛሬ ዜል ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ካሉ ታዋቂ ጋዜጠኞች መካከል አንዷ ናት። በምትሰራበት SABC (South African Broadcast Corporation) ውስጥ ልዩ ትኩረቷ የጥቁሮች ህይወት ቢሆንም፣ ማንዴላ የፈጠሯትን የጥቁሮችና የነጮች ሀገር የሆነችውን ደቡብ አፍሪካም የቀለሞች ውህደት ወደ ሌላ ስልጣኔ እንዲያሸጋግራት ደፋ ቀና እያሉ ከሚሠሩ ታታሪ ሰዎች መካከል አንዷ ናት። ነጮች ባለፉት 300 እና ከዚያም በላይ በነበሩት ዘመናት ውስጥ በጥቁሮች ላይ ያደረጉትን በደል በማስታወስ ይህም እንዳይደገም ትምህርታዊ በሆነ መልኩ በጥንቃቄ ስራዋን የምትወጣ ባለሙያ ናት።

እናም Slave Coast Line በሚል ርዕስ በተለይ የባህር በር ያላቸውን ወይም የነበራቸውን ሀገሮች በመዞር ዶክመንተሪ ፊልም በመስራት ላይ ነች። ደቡባዊውንና ምዕራባዊውን አፍሪካ በርካታ ጥናት ያደረገች ሲሆን ብዙም ያልገፋችበት ምስራቅና ሰሜን አፍሪካን ነበር። እነሆ ዛሬ ከዚህች ምርጥ አፍሪካዊት ጋር ቆይታ እናደርጋለን።

ዜልን የማውቃት በህይወት አጋጣሚ በተከሰተ ገጠመኝ ነው። የዛሬ አስራ ሶስት አመት ከሰባት የአፍሪካ ሀገራት ተውጣጥተን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የትምህርት ዕድል ተሰጥቶን ተሰባስበን ነበር። በቁጥር 11 ነን። ከነዚህ ውስጥ ሁለት ደቡብ አፍሪካዊያን ነበሩ። አንዱ ሴፖ የተባለ ጥቁር አፍሪካዊ የSABC ጋዜጠኛ ሲሆን ሁለተኛዋ ዜል ናት። አብዛኛዎቻችን ከተለያዩ ሀገሮች የመጣን ቢሆንም እስከ ህይወት ፍፃሜ ድረስ የማይረሳውን የደቡብ አፍሪቃን ውብ ፍቅር ልቤ ውስጥ የከተቱት እነዚህ ሁለት ወጣት ጋዜጠኞች ነበሩ።

የህንድ ውቅያኖስን ታኮ የሚገኘውና ከፖርት ኤልዛቤት በመኪና የሁለት ሰዓት ተኩል መንገድ የሆነው እና የደቡቦች ደቡብ የሚባለው ግርሀም ስታውን ከተማ ውስጥ ግዙፉ ሮድስ ዩኒቨርስቲ ከተለያየ ባህልና ታሪክ ውስጥ ተመዘን የወጣን ጋዜጠኞችን ሰብስቦናል። ከመካከላችንም በቀለም ፈረንጀ የነበረችው ዜል ፍፁም ትህትና እና የሰው ፍቅር የሰጣት እናቶች እንደሚሉትእርብትብት ናት።

በቆይታችንም ወቅት እያንዳንዳችን የወደፊት ርዕያችንና እየሠራንም ስላለናቸው ጉዳዮች ተወያይተናል። ከሁሉም ለየት ያለው የዜል ፕሮጀክት ነበር። ድርጅቷ SABC በመደበላት በጀት ደቡባዊና ምዕራባዊ አፍሪካን የባሪያ ፍንገላ ታሪክ ሰርታ መጨረሷንና ወደፊትም ወደኛዋ ታሪካዊት ምድር ምስራቅ አፍሪካ እንደምትመጣ ቀልድ የሚመስል ጨዋታ አወጋችን።

ትምህርታችን ካለቀ በኋላ ሁላችንም ወደየመጣንበት ተበታተንን። ግን ሁል ጊዜ መፃፃፋችን (E-mail) መደራረጋችን አልቀረም። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ግን ዜል ኢትዮጵያን እንደ ጦስ ዙሪያዋን ስታስስ ነው የቆየችው። አንድ ጊዜ ሞሮኮ ነኝ ትላለች። ሌላ ጊዜ አልጄሪያ፣ ቀጥሎ ግብፅ፣ ከዚያ ሱዳን፣ ከዚያ የመን፣ ቀጥላም ሱማሌ ላንድ፣ ኬኒያ እያለች ታሪክ መቆፈር ከጀመረች ቆየች።

በወርሃ ጥር አንድ ሰፊ E-mail  ፃፈችልኝ። የፃፈችው ባጭሩ እንደሚገልፀው“ሀገርህ ኢትዮጵያ የምትገርም ናት፤ በየሄድኩባቸው ቦታዎች ታሪክ አላት። የእርሷ ስም በሁሉም ቦታ አለ። ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያ በባርያ ንግድ ትታወቃለች። የሚገርመው ግን ሌሎች ሀገሮች በአውሮፓውያን ቅኝ ተገዝተው ነበር፤ የባሪያ ፍንገላ የሚደረገው። ያንተ ሀገር ግን የራሷ ነገሥታት በነፃነት ቢኖሩም ግን የባሪያ ንግድ ያጧጡፉ ነበር። አሁን አንድ ትልቅ ውለታ ዋልልኝ። መቼም እንዳስቸገርኩህ አውቃለሁ። በመጋቢት ወር ላይ ሀገርህ ኢትዮጵያ እመጣለሁ። እስከዚያው ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የባሪያዎች ታሪክ ወይም ፍንገላ የተፃፉ ዶክሜንቶች ካሉ አጭር ጥናት ስራልኝ። ወሮታውን ስመጣ እከፍላለሁ” ይላል።

እኔ እስከ ዛሬ ድረስ በርካታ የሀገሬን ታሪክ ሳነብ ሆን ብዬ ባርነት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ነበር? በማለት አስቤውም ሆነ አንብቤው አላውቅም። እናም ለመጀመሪያ ጊዜ ባርነት ላይ ዜል አሳሰበችኝ። የት ልሂድ? ምን ላንብብ? ለዜል ደግሞ፣ አይደለም የባሪያን ታሪክ፣ ባሪያ ቢሆኑላት የማታስቀይም ልበ ንፁህ ደቡብ አፍሪካዊት ነች።

ከወርሃ ጥር የጀመርኩ እስካሁን ድረስ የሀገሬን የባሪያ ፍንገላ ታሪክ እየፈለኩ ነው። ሰውዬው “የአላህን መኖር በምን አወክ?” ሲባል የመለሰው መልስ “ያላሰብኩት ቦታ ሲያውለኝ” ብሎመመለሱ ይነገራል። እኔም ባርነትን እንዲህ እለፋበታለሁ ብዬ አልሜውም አላውቅም። እናም የዜል መምጫ እየደረሰ ነው። የኔ የባርነት ጥናት ደግሞ እራሴውኑ አስገርሞኛል። እጃችን ላይ የነበረውን ታላቅ ታሪክ ሳንሠራበት ሩቅ ሀገር ተወልዳ ያደገችው ባይተዋሯ ዜል ታላቅ ዶክመንተሪ ልትሠራበት ነው። በእርግጥ የዜል ስራ ለራሷም ሆነ ለሀገራችን እውቅና ጉልህ ሚና ቢኖረውም የኛ ህይወት ግን ክፉኛ ያሳዝነኝ ገብቷል። እነ ዜል ከደቡብ አፍሪካ ተነስተው በየሀገሩ እየዞሩ ታላላቅ ዶክመንተሪዎች ሲሠሩ እኛ ኢትዮጵያዊያን የሚያስጨንቀን ነገር የጨው መወደድ፣ የበርበሬ መናር፣ እና ልዩ ልዩ ሀሳቦች ናቸው። የሀሳቦች ልማት ማምጣት አለብን።

ለመሆኑ ምን ተጠንቶ ነው ዜል የምትመጣው? ዜል ከኔ የምትፈልገው የባሪያ ንግድ በየትኞቹ ነገሥታት ዘመን ላይ ነበር? የባሪያስ ገበያ የነበረው የት ነው? የባሪያዎች ማህበራዊ ታሪካዊ ህይወት ምን ነበር? የባሪያ ንግዱን ይረከቡ የነበሩ ነጋዴዎች እነማን ነበሩ? ወዘተ. የሚል ነው። በእርግጠኝነት እንዲህ ነው ብሎ መናገር የሚያስችል ታሪክ ለመፃፍ የሚያስችሉ መረጃዎችን ላለፉት ሦስት ወራት መሰብሰቤ አልቀረም። ታላቁን የሀገራችን ታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትን መጻህፍት ማንበብ ግድ ብሎኛል። ግን እንዴት ሆኖ ነው ዶከመንተሪ ፊልም የሚሆነው እያልኩ ሳሰላስል ቆይቻለሁ። ብዙ ዘዴዎችን ብቀይስም ዜል እሱ አያሳስብህ፤ እውነተኛውን ታሪክ ግን አደራጅልኝ አለችኝ። የኔ ችግር የምስል ችግር ነው። ፊልም ምስል Image! Image! Image! ይባላልና ነው።

መቼም የሀገራችን ታሪክ ለመፃፍ ስንነሳ ከየት እንደሚጀመር ግራ ያጋባል። ግራኝ መሀመድና ተከታዮቹ አብዛኛዎቹን የሀገራችንን የታሪክና የእምነት ሰነዶች ስላወደሟቸው ታሪካችንን የምንመዘው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አይቶን ሄዶ ብዙ ስለፃፈብን ፖርቹጋላዊው ቄስ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ነው።

አልቫሬዝ በዘመኑ በአይኑ ያየውን ሲገልፅ ባሪያዎቹ በግብርና፣ በሸክም፣ በቤት ስራ ጌቶቻቸውን እንደሚያገለግሉጽፏል። መልካቸው የጠቆሩም ሰዎች ባሪያዎች እንደሚባሉ ጠቁሟል። አብዛኛዎቹም ከደቡብና ምዕራባዊ ኢትዮጵያ ክፍሎች እንደሚመጡ የፃፈ ሲሆን የሚደርስባቸውንም መከራ አብራርቷል። በዚያን ዘመን ባሪያዎች ይኮላሹ እንደነበር ታሪክ ያስታውሳል። ፀሐፊዎቹ እንደሚሉት ባሪያዎቹ ሲኮላሹ በህይወት ከሚተርፈው ይልቅ የሚሞተው እንደሚበልጥ ገልፀዋል።

ባሪያዎች እንደ ዕቃ ገበያ ላይ ታስረው ይሸጡ ነበር። እጅና እግራቸው አምልጦ እንደሚጠፋ እንስሳ ታስሮ ለገበያተኛ ይቀርቡ ነበር። በዚሁ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ላይ የነበሩ የባሪያ ንግዶች እንደነበሩ Marco Polo-The Travels of Marco Polo መጽሐፉ ገልጿል። በዚያን ዘመን ማለትም በ17ኛው መቶ ተጓዥ የነበረው ጣሊያንያዊው Giacomo Baratti u1670 The Late Travels of S.Giacoma Baratti in to the Remote Country of the Abyssinian በተሰኘው መጽሐፉ የቱርክ ወታደሮች ክርስትያን የሆኑትን ኢትዮጵያዊያን ባሪያዎች እየገዙ እንደሚወስዱ ያትታል።

በሁለቱ ፀሐፊዎች አባባል ደንበኛ የባሪያ ንግድ መጧጧፊያ ቦታ የነበረችው በቀይ ባህር፣ ዘይላ፣ በርበራ ማለትም በኤደን ሰላጤ ወደ ዓረብ ሀገራት ይጓጓዙ እንደነበር ጽፈዋል።

በግዕዝ የተፃፈው ገድለ ዜና ማርቆስም ወደ ሀገራችን ለንግድ የሚመጡትን የገበያውን ሁኔታ ጽፏል።

ሃርጊጐ - ከምፅዋ በተቃራኒ በኩል የምትገኝ የባሪያ ንግድ ወደብ ነበረች።

ቤይሉል - ከአፋር በስተደቡብ የምትገኘ የባሪያዎች መነገጃ እንደነበረች በ1648 ዓ.ም የየመኑ መልዕክተኛ አንባሳደር ሀሰን ኢብን አህመድ አል-ሃይሚ የአቢሲኒያን ነጋዴዎች ሁኔታ ፅፎበታል።

ዘይላ - በምስራቅ በኩል የምትገኝ ናት። በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፖርቹጋሉ ፀሐፊ Bernando Pereira  ተመልክቶ እንደፃፈው የዝሆን ጥርስና የባሪያዎች ገበያ ማየቱን ገልጿል።

በርበራ - እስካሁን የሚያገለግል ወደብ ነው። በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የመጣው Nicolode conti  የገበያውን ሁኔታ በሰፊው ገልጿል።

ዳሞት - ይህች ደግሞ እዚህ ጐጃም ውስጥ የምትገኝ ቦታ ናት። ባሪያዎች ከያሉበት ተሰባስበው የሚሸጡባት የሀገር ውስጥ የገበያ ማዕከል እንደነበረች አልቫሬዝ ገልጿታል።

እንፍራንዝ - ጎንደር ውስጥ ያለች ወረዳ ነች። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ከሸዋ ወደ በጌምድር ሲዘዋወር የባሪያ ንግዱም ማዕከልነት ወደዚያው ተሸጋገረ። ቦታው ለሱዳን ቅርብ በመሆኑ እንፍራዝም ለባሪያ ንግድ መቀባበያ አመቺ ቦታ እንደነበረች ፈረንሣዊው ፖንሴት በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገልጿል።

ሌሎች የገበያ ማዕከሎችን በዘመኑ በአይናቸው ብሌን የተመለከቱ ፀሐፊያን ያስረዱናል። ኢትዮጵያ ከስልጣኔዋ ወደ ቁልቁል ልትንደረደር በተዘጋጀችበት ጊዜ ወደ ጎንደር መጥቶ እቴጌ ምንትዋብ ቤተ-መንግሥት ውስጥ አምስት አመት ተቀመጠ የሚባለው እስኮትላንዳዊው ጀምስ ብሩስ ከ200 አመታት በፊት በፃፈው Travel to discover the source of the Nile በተሰኘው መፅሐፉ ይሸጡ የነበሩት ባሮች አብዛኞዎቹ ክርስትያኖች እንደነበሩና ይጋዙ የነበረበትም ስፍራ ወደ ሙስሊም አገሮች መሆኑን ገልጿል። እንደ ብሩስ አባባል ከሆነ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በጎንደር ቤተ-መንግሥቶች ባሉ ልዩ ልዩ ክፍሎች ውስጥ አያሌ ባሪያዎች እንደነበሩ ያየውን ጽፏል። ከነዚህ ውስጥ የ17 እና የ18 አመት ወጣት የሆኑትና ንቃት የሚታይባቸውን ባሪያዎች የጎንደር ነገሥታት ልዩ ልዩ ትምህርትና ስልጠና ይሰጧቸው እንደነበር ጀምስ ብሩስ ጽፏል።

ጎንደር የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ከሆነች በኋላ ደግሞ ወደዚያ ለሽያጭ የሚጋዙት ባሪያዎች መብዛት ጀመሩ። ቀጥሎ ደግሞ ጭራሽ መዋለድ ሁሉ ጀመሩ። በ1624 ዓ.ም ከነገሡት ከአፄ ፋሲል ጀምሮ እስከ አፄ ኢዮአስ ድረስ ባሉት 150 አመታት ውስጥ ጎንደር ውስጥ የተከማቹት ባሪያዎች የዘር ግንድ ሁሉ እንደነበራቸው በ1898 ዓ.ም ፈረንሣዊው Antoine d'Abbadi Geographic de 1'Ethiopia በተሰኘው መጽሐፉ ገልጿል። እንደ አባዲ አባባል ከሆነ የባሪያዎቹን የመጀመሪያ ተጋቢዎች እናትና አባታቸው ወይም የመጀመሪያ ወላጆቻቸው 'ቀናጅ' እንደሚባሉና የነርሱ ልጆች ደግሞ 'አመለጥ'ሲባሉ፣ የልጅ ልጆች ደግሞ 'አሰለጥ'ይባሉ ነበር ሲል ገልጿል። እንዲሁም ደግሞ የነርሱ ወላጆች የሆኑትን ማለትም የባሪያዎቹ 1/8ኛ የዘር ግንድ የሚባሉት 'ፈናጅ'ተብለው እንደሚጠሩ አባዲ ገልጿል።

ሩፒል በ1838 Reise in Abyssinian በተሰኘው መፅሀፉ እንደገለፀው በሰሜን ኢትዮጵያ በነበሩ ባለፀጋ ቤተሰቦች ውስጥ በርካታ ባሪያዎች እንደነበሩና ህይወታቸውንም ጽፏል።

Pearce Nathaniel በ1820 በፃፈውA small but True Account of the ways and manners of the Abyssinians  በተሰኘው መጽሐፉ በ1831 ዓ.ም The life and Adventures of Nathaniel Pearce  ተብሎ በታተመለት መጽሐፉ ውስጥ ስለ ሀገራችን የባሪያ ታሪክ ተፅፏል። በታሪኩ ውስጥ እንደተገለፀው ነገሥታቱ ራሳቸው የባሪያን ንግድ የሚቃወሙ አልነበሩም። ፒርስ ራስ ወልደሥላሴን በመጥቀስ፣ እኚህ ባለስልጣን ራሳቸው በርካታ ባሪያዎች በዙሪያቸው ነበሩዋቸው ብሏል።

ጐባት u1850 Journal of a Three Year's Residence in Abyssinia በተሰኘው ፅሁፍ ውስጥ እንደገለፀው በሰሜን ኢትዮጵያ ከወንዶች ይበልጥ ሴቶች በባርነት ላይ እንደነበሩ ፅፏል። አንድ ሰው ባለጠጋ ነው የሚባለውም ብዙ ባሪያዎች ሲኖሩት እንደሆነ ፅሁፉ ያብራራል።

ሀሪስ በ1844 ዓ.ም The Highlands of Ethiopia በተሰኘው መፅሀፉ ደግሞ ሸዋ ውስጥ በእያንዳንዱ ገበሬ ቤት ሁሉ ባሪያዎች እንደነበሩ ገልጿል። ከዚህ ሌላ ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ እህል ብቻ የሚፈጩ 300 ሴት ባሪያዎች እንደነበሯቸው ተገልጿል። ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጠላ ጠማቂዎች፣ ውሃ ቀጂዎች፣ እንጨት ፈላጮች ወዘተ. ነበሩ ብሏል።

ፕራፕግ በ1867 ዓ.ም Travels Researches and Missionary Labors በተሰኘው መጽሐፉ በ18 አመቱ ስለተሸጠው ባሪያ የሚያስታውሰውንጽፏል። ዲልቦ ከተባለው እናርያ አካባቢ ካለው ስፍራ በባርያ ፈንጋዮች የተያዘው ወጣት ወደ ማግራ ተወሰደ። ከዚያም አጋብጃ በተባለ ስፍራ በአርባ አሞሌ መሸጡን ጽፏል። ቀጥሎም ገዥው ጐና ወደተባለው የሶዶ አካባቢ ወሰደው። ገዥው እንደገና ሊያትርፍበት እንደገና ገበያ ላይ አስቀመጠው። አንዱ የባርያ ገበያተኛ መጣና አትርፎ ገዛው። ከዚያም እራሱ ደግሞ ወደ ሸዋ የደራ ገበያ አምጥቶት 80 አሞሌ ሸጠው። ከዚያም ሌላው ገዢ ደግሞ ወስዶት ከፍተኛ ገበያ አለበት ተብሎ ከሚጠራው አልዩ አምባ ከተባለው ስፍራ ሸጠው። አሁን ገና ባሪያውም በገንዘብ ተሸጠ። ይህም 12 ማርያ ትሬዛ ነበር ያወጣው። ገበያው እንዲህ እየተቀባበለው በመጨረሻም ንጉሥ ሳህለሥላሴጋ ተሽጦ እንደመጣ Krapf ፅፏል። ይህን ሳነብ ባሪያን ምን ያህል ተወዳጅ ቢሆን ነው ብዬ አስበዋለሁ።

ለመሆኑ የባርያ ንገድን ነገሥታት ለምንድን አላስቆሙትም? በዚያ በሩቁ ዘመን ፍትሃነገሥት የነገሥታት ህግ የተሰኘ መጽሐፍ አለ። እርሱስ ስለዚህ የባርያ ንግድ ምን ይላል? በእርግጥ ፍትሃነገሥት የባርያን ንግድ አጥብቆ ይቃወማል። ክርስትያኖች ባርያን መሸጥና መለወጥ እንደማይገባቸውጽፏል። እ.ኤ.አ በ1607-32 የነገሡት አፄ ሱስንዮስ የባርያ ንግድን የሚቃወሙ ነበሩ።

ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች እየተጋዙ ወደ አውሮፓና ኤዥያ ተሽጠው በመጨረሻ ደግሞ ከአንበሳ ጋር እያፋለሟቸው ይዝናኑባቸው ነበር። “ሰቆቃው አፍሪካ”ሊባል የሚችል ዘመን አፍሪካውያን አሳልፈዋል። ዛሬ ጥቁሯ ግብፅ፣ ጥቁሯ ህንድ፣ ጥቁሯ አሜሪካ... የዚያን ጊዜ ታሪኮች ናቸው።

ለመሆኑ ሃይማኖቶች ክርስትናና እስልምና ስለ ባርነት ምን ይላሉ? ሀገራችን ኢትዮጵያም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በገጠሯ ውስጥ የባሪያ ንግድ ታጧጡፍ ነበር። 1970-71 ላይ ነው የቆመው የሚሉ አሉ። ጉዳዩን ወደ ውስጥ እየገባሁበት ነው። በመረጃ አግዙኝ። ዜል ልትመጣብኝ ነው። የባሪያዎች ደምና ነብስ እንዳይወቅሰን የምናውቀውን እንስጣት።

 

በጥበቡ በለጠ

 

ደራሲ ሲጠፋ፣ ደራሲ ሲሠወር አገር ባዶ ይሆናል። እኔም ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ የምገባው ደራሲ ሲጠፋ ነው። ደራሲ ማለት ሐገር ነው። በውስጡ የዚያች ሐገር ሕዝብ' ባሕል' ፖለቲካ አስተሣሠብ ስነ-ልቦና አሉት። የደራሲ ደም እና አጥንት ውስጥ  የሐገርና የሕዝብ ታሪክ አለ። እናም አንድ ደራሲ የዚህ ሁሉ ጉዳይ ተሸካሚ ነው። ይህን ሸክሙን ይዞብን ከሔደ በርግጥም ተጐጂዎቹ እኛ ነን። ደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታም ያንን በውስጡ ያለውን የሕዝብና የሐገር ታሪክ ይዞብን የት እንደገባ አጣሁ። ደራሲና ጥበበኛስ አይሠደድ ትላለች ገጣሚት ሜሮን ጌትነት። እናም ዛሬ ፍቅረማርቆስ ደስታን ያያችሁ ንገሩን እባካችሁ እላለሁ።

 

ደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ በልዩ ልዩ የድርሰት ስራዎቹ ይታወቃል። በተለይ ደግሞ የሐመር ብሔረሰብ ላይ መሠረት አድርጎ የፃፋቸው ልቦለዶቹ ደራሲውንና ማህበረሰቡን ታዋቂ አድርገውታል። “ከቡስካ በስተጀርባ” የተሰኘው ልቦለድ መፅሐፍ በደቡብ ኦሞ ዞን ውስጥ የሚገኙትን ሐመሮችን እና አጎራባቾቻቸውን ውበትና ለዛ ባለው ቋንቋ በመግለፁ ፍቅረማርቆስን ጠንካራ የብዕር ሰው አድርጎታል።

 

ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከደቡብ ክልል መንግስት ጋር በመተባበር “ሕያው የጥበብ ጉዞ” በሚል ርዕስ የፍቅረማርቆስን መጽሐፍ መሰረት በማድረግ የጉዞ ዝግጅት አድርጎ ነበር። ፍቅረማርቆስም በጉዞው ላይ ነበር። እኔም ከ50 ከሚልቁ ተጓዦች መካከል አንዱ ስለነበርኩ ሐመሮችን እና ፍቅረማርቆስን አንድ ላይ ሆነው ለማየት አጋጣሚው ተፈጠረልኝ።

 

ሐመሮችና ፍቅረማርቆስ ደስታ እጅግ ይዋደዳሉ። በእጅጉ ይከባበራሉ። ፍቅረማርቆስ ደስታ ውልደቱም ሆነ እድገቱ ከሐመሮች በጣም በሩቅ በምትገኘው ጎጃም ውስጥ ነው። ግን የእህል ውሃ ነገር ሆነና የጎጃሙ ጉብል ትምህርቱን ከዩኒቨርስቲ ሲያጠናቅቅ መምህር ሆኖ ወደ ደቡብ ኦሞ ዞን ያመራል። በወቅቱ ቦታው እጅግ ኋላ ቀር /ሪሞት/ የሚባል እንደነበር ይታወቃል። ፍቅረማርቆስን ግን ማረከው። ወደ ሀመሮች መንደር ዘለቀ። የሐመሮች ጓዳ ጎድጓዳ ውስጥ ገባ። ጎጃሜው በሀመሮች ውስጥ ተዋዋጠ።

ፍቅረማርቆስ ደስታ በሐመር ብሔረሰቦች ማንነት ውስጥ ራሱን ከተተ። ሐመሮችም ተቀበሉት። ወደ ውስጣቸው አስገቡት። እናም ይሔ የሩቅ አገር ሰው በሐመሮች ፍቅር ተነድፎ ሲቀላቀላቸው እነርሱም በባህላቸው መሰረት የሐመር ብሔረሰብ አባል ሊያደርጉት ተማከሩ። የሐመር ባሕል እጅግ ተወዳጅ ሰው ከመጣ ጡት አጣብቶ የብሔረሰቡ አባል የማድረግ የቆየ ዘልማድ አለው። እናም ፍቅረማርቆስ በሐመር ባሕል መሰረት እናትና አባት ተሰጥቶት የሐመሮች አባል ሆነ። ወንድምና እህቶችም ከዚሁ ብሔረሰብ አገኘ። ፍቅረማርቆስ ለሐመሮች ልዩ ሰው፤ ተወዳጅ ሰው ሆነ።

 

በሐመሮች ፍቅር ተነድፎ የወደቀው የሳይንስ መምህር የሆነው ፍቅረማርቆስ፣ ስለነዚሁ ድንቅዬ ማህበረሰቦች ለሌላው ላላያቸው ማህበረሰብ ሊያካፍል ብዕሩን ይዞ ተነሳ። በመጨረሻም “ከቡስካ በስተጀርባ” - ድንግል ውበት፣ የተሰኘ ባለ 150 ገፅ መጽሐፍ በጥቅምት ወር በ1987 ዓ.ም አሳተመ። መጽሐፉ ልቦለድ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ መሰረት ያደረገው በተጨባጭ ባህላዊ ርዕስ ጉዳዮች ላይ ነው። ሐመሮች ምን አይነት ህዝቦች እንደሆኑ ልቦለዳዊ ቀለም ሽው ሽው አድርጎበት ፈካ ብለው እንዲታዩ አደረጋቸው።

 

ፍቅረማርቆስ ደስታ የሐመሮች የእድሜ ልክ ድልድይ ሆነ። ሐመሮችን ከሌለው ከቡስካ በስተጀርባ ማዶ ካለው የዓለም ህዝብ ጋር አገናኛቸው። ሐመሮችን ለማየትና ከነርሱ ጋር ለመጨዋወት ብዙ ሰዎች የጉዞ አቅጣጫቸውን ወደዚያ አደረጉ። ሐመሮች ገናና ሕዝቦች ሆነው የጥበበኞችን ልብ መስረቅ ጀመሩ። ፊልም ለመስራት፣ ሙዚቃ ለማቀነባበር፣ ስለ ባህልና ቋንቋ ለማጥናት አያሌዎች ሐመሮችን መረጡ። መሸጋገሪያ ድልድዩ የፍቅረማርቆስ ደስታ የብዕር ትሩፋቶች ነበሩ።

የፍቅረማርቆስ ደስታ መጽሐፍ በ1987 ዓ.ም “ከቡስካ በስተጀርባ” -ድንግል ውበት -ተብላ ለህትመት ስትበቃ የማስተዋወቂያ ፅሁፍ መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ናቸው። እርሳቸውም ሲገልፁ የሚከተለውን ብለዋል፡-

 

“ፍቅረማርቆስ በዚህ ቀዳሚ ድርሰቱ ከሐመሮች ጋር ኖሮ፣ ማዕዳቸውን ተቋድሶ፣ ውሃቸውን ጠጥቶ፣ በአፋቸው ተናግሮ በአጠቃላይ እነሱን ሆኖ መልሶ ይሔው እንዲህ ናቸው ይለናል። ባልተወሳሰበ አገላለፅ የተተረከ ብሩህነት ያለው፣ የገፀ-ባህሪያቱ ድርጊትና ማንነት የሚታይበት፣ ታሪኩን እስከ ማብቂያው እንድንከታተል የሚያደርጉ አጋጣሚዎችና ሁነቶች ያሉበት ልብ-ሰቃይ ድረሰት ነው።” በማለት ተ/ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው ይገልፁታል።

 

ከዚህ መጽሐፍ ህትመት በኋላ ብዙ ኢትዮጵያዊያን እና የሌሎች ሀገሮች ሰዎችም ሐመሮችን አወቁ። የሐመሮች የቅርብ ወዳጆች ሆኑ። ሐመሮች በብዙ ሰዎች ቤት ታሪካቸው ገባ። ከቡስካ ተራራ ማዶ እና ከቡስካ ተራራ ግርጌ ያሉት ሀመሮች የሰውን ቀልብ ገዙት። ዛሬ ከዋናዎቹ የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዱ ሐመሮች ሆነዋል። ከዓለም ጋር በስፋት ያገናኛቸው ድልድይ ደግሞ ፍቅረማርቆስ ደስታ ነው።

 

ይሔ የሐመሮች ውህድ የሆነው ፍቅረማርቆስ ከአያሌ ደራሲያንና ጋዜጠኞች ጋር ሆኖ በሐመሮች መካከል ከሶስት ዓመታት በፊት ወደ ደቡብ ኦሞ ዞን ተጉዞ ነበር። በተለይ አያሌ ሐመሮች በሚገኙበት ቱርሚ ከተማ ውስጥ ህዝቡ ግልብጥ ብሎ በመወጣት ፍቅረማርቆስ ደስታን እና አብረውት የመጡትን ደራሲያን ተቀበሏቸው። በወቅቱ ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር ፍቅረማርቆስ ለሐመሮች ልዩ የቤተሰብ እንግዳቸው ነበር። ቱርሚ ቀውጢ ሆነች።

 

ቱርሚ አካባቢ የሚኖሩት ሐመሮች ቆለኛ ሲሆኑ ዲመካ ተብሎ በሚጠራው ከተማ እና ከቡስካው ተራራ ግርጌ ያሉት ሐመሮች ደግሞ ደገኞች ናቸው። ወደ እነርሱም ዘንድ አምርተን ነበር። በአጠቃላይ ግን ሐመሮች ውስጥ ፍቅረማርቆስ ደስታ ልዩ ስብእና ያለው ተከባሪ ሰው ነበር።

ታዲያ ይሔ ደራሲ ሐመሮችን በዚህ ሁኔታ ከጎበኘናቸው በኋላ ሐገር ለቆ ጠፋ። በአሁኑ ወቅት አሜሪካ ውስጥ እንደሚኖር ይነገራል። የፖለቲካ ጥገኝነትም ጠይቋል ተብሏል። ድንገት ከሐመሮች ጉያ ወጥቶ የጠፋ የሐመሮች ተወዳጅ ልጅ ነው።

 

ከሰሞኑ ደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ ትውስ ያለኝ በብዙ ምክንያት ነው። ነገር ግን በዋናነት በኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የቋንቋና የባህል ታሪክ ላይ ያዘጋጀሁትን ጥናት ስመለከት ከሀመሮች ርዕስ ውስጥ ገባሁ። ሀመሮች ሲነሱ ፍቅረማርቆስም አብሮ ብቅ ይላል። ለእኔ ደግሞ ብዙ መረጃም የሰጠኝ ሰው እርሱ ነበር። የሀመሮች መዝገብ በተገለጠ ቁጥር ፍቅረማርቆስ ደስታ ብቅ ይላል።

 

ሐመሮች ፈጣሪ አላቸው። የሐመሮች ፈጣሪ /እግዚአብሔር/ ቦርጆ ይባላል። ቦርጆ ለሐመሮች መሬትን፣ ሰማይን፣ የሰው ልጅንና ከብቱን እንስሣቱን ሁሉ ፈጥሯል። በሐመሮች እምነት ቦርጆ ጥሩ ጥሩ ነገሮችን ነው የሚያደርገው። አልፎ አልፎ ብቻ ድንቅን፣ ወረርሽኝን እና ሌሎች ችግሮችን ቦርጆ ይልክባቸዋል። ይሔ ደግሞ የሚሆነው ቦርጆ ሲቆጣ ነው። ሕዝቡን ሲቀጣ አንዳንዶች ቦርጆ ቢቆጣ ነው ፍቅረማርቆስ ከሐመሮች ጉያ ወጥቶ በነጮቹ አለም መኖር የጀመረው ይላሉ።

 

በሐመሮች ባህላዊ እምነት ውስጥ ‘ቢታ’ ተብሎ የሚጠራ መላእክ አለ። ይህ መላእክ የሐመሮች የሐይማኖት መሪ ነው። ቀያሽ ነው። ሐመሮችና ፈጣሪያቸው ¢ቦርጆ¢ ሲቀያየሙ በመሀል ሆኖ የሚያስታርቅና የሚያግባባ ነው። ለሐመሮች የሚለምንላቸው ከፍፁሙ ፈጣሪያቸው ጋር ለማገናኘት ነው። እናም ቦርጆ እንዴት ፍቅረማርቆስን ከነርሱ አርቆ አስቀመጠው? የእምነት ድልድያቸው ቢታ ወደ ፈጣሪያቸው ቦርጆ ዘንድ ቀርቦ የፍቅረማርቆስን ጉዳይ ያቀርብላቸው ይሆናል። ፍቅረማርቆስ እንኳን ከሐመሮች ከእኛም ዘንድ በጣሙን ከራቀ ቆየ። ድምፁም ወሬውም ጠፍቷል።

 

ሐመሮች ቁጥራቸው 46ሺ 532 ሲሆን ከዚህ ውስጥ 38ሺ 354 ህዝብ አንድ ቋንቋ (ሐመርኛ) ብቻ የሚናገርና የሚሰማ /Monoligual/ ነው። ቋንቋቸው ከአፍሮ ኤዥያቲክ ምድብ የሚቀመጠው ኦሞቲክ ተብሎ የሚጠራ ነው። አርብቶ አደሮች የሆኑት እነዚህ ሕዝቦች በቀላሉ መጤን/አዲስ ሰውን/ የሚቀበሉ ናቸው። ፍቅር ሰጥተው ፍቅር መቀበል የሚችሉ ናቸው። የቡስካ ተራሮችን የሚያሞቅላቸው የነበረው ፍቅረማርቆስ ደስታ ስውር ስላለባቸው ቦርጆን በቢታ አማካይነት መጠየቃቸው አይቀርም።

 

በሐመሮች ባህል ምርቃትና እርግማን አለ። ምርቃት ¢ፊቴ¢ ይባላል። እርግማናቸው ኤርባ ይባላል። ለፍቅረማርቆስ ምርቃት ሲያዥጎደጉዱለት በአይኔ አይቻለሁ። ከሐገርና ከሐመሮች ርቆ መቆየቱ ምርቃት ይሁን እርግማን ለይቶ ማወቅ አይቻልም። ነገር ግን ከጉያቸው የወጣው ደራሲ ፍቅረማርቆ የምርቃታቸውና የፍቅራቸው ተፅእኖ ወደ ስድስት መፃህፍትን እንዲያሳትም አድርጎታል። ወደ አራት የሚጠጉ ኢትኖግራፊክ ዶክመንተሪ ፊልሞችን ሰርተዋል።

 

ሐመሮች መጪውን ዘመን አርቀው ይተነብያሉ። በእድሜ የገፉ አባቶች መጪውን ዘመን አሻግረው ያያሉ። የሰማይ ላይ ከዋክብትን እና ጨረቃን በመቃኘት ውሳኔ ያስተላልፋሉ። ኬንድ የተባለ ቦታ ሐመሮች እንዲሰበሰቡ ያደርጋሉ። ህዝቡ ከመጣ በኋላ ስለ ከዋክብት ሁኔታ ያስረዳሉ። በሐመር ባህል መሰረት ወንድና ሴት ከዋክብቶች አሉ። ወንዱ ¢ኢዚንሄኔ¢ ሲባል፣ ሴቷ ደግሞ ኢዚኒማሆ ትባላለች። ሁለቱ ከዋክብት በፀሐይ ዙሪያ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ተረድተው አባቶች ስለ ሐመሮች መፃኢ ግዜ ይናገራሉ። ሐመሮች ስነከዋክብት አስትሮኖመሮች ናቸው። የስነ-ፈለክ ተመራማሪዎች። እናስ ከዋክብቱ ስለ ደራሲ ፍቅረማርቆስ ደስታ ምን ብለዋቸው ይሆን? ለምን ጠፋ?

 

ከሜሮን ጌትነት

ሕልማችን ዕውን እንዲሆን

ራዕያችን እንዲሳካ

ምኞታችን እንዲጨበጥ

ስኬታችን እንዲለካ

ግባችን ከግቡ ደርሶ

የሚባል ይኅው ሰመረ

አብረን ብንሆን ነበረ

አንተም ልሂድ ትላለህ

ይሄው የሄደው ሄዶ ቀርቶ

አልተመለሰ ከወጣ

እኛም ውስጥ ሆነን አልታገልን

የሄደው ለውጥ አላመጣ

አንድ እንጨት አይነድም ሆኖ

በጭስ ታጥናለች ሀገር

ነደን ብርሃን የምንሆን

አብረን ብንሆን ነበር

***          ***          ***

አንተን አምኜ ነው የኖርኩ

ድንክዋኔን በእምነት የተከልኩ

አንተን ብዬ ነው የኖርኩ

ከትብት ሀገሬ የተውኩ

እንዴት እንዴት ብታስብ ነው

ራስህን ከምድርህ የነቀልከው

ምን አይነት ሰይጣን ሹክ ብሎህ ለአፍታ ስደት ናፈክ

ያንን ሁሉ ጭነት አስጭነህ

እኔን ባለስንቅ ያደረክ

እንደመሸበት መንገደኛ ባዶ እጄን ነኝ ብለህ አልክ

ባዶ እጅ ------ባዶ እጅ ምንድን ነው ላንተ ንገረኝ እስኪ በሞቴ

አንተ ሃያል ባለቅኔ አንተ የጥበብ አባቴ

ንገረኝ ------ንገረኝ እስኪ ፍቺውን ምን ማለት ነው እጀ ባዶ

ጥበብህ አፍርታ በገሀድ ድፍረትህ እውነትን ወልዶ

በአንተ አንዲት ቃል ተሸብሮ የባለጋራ ጉልበት ርዶ

ጆሮ ለባለቤቱ ባዶ፡ ደከመኝ ብለህ ታይ ማዶ

ቀለም የሞላው ብእር የጨበጠ ብእረኛ

እንዴት

***          ***          ***

አየህ አንተ ድካም አታውቅም

አንተ ድካም አታወቅም!

ስደት ነውርህ ሽሽት ሞትህ ነው አምናለሁ

ተሸነፍኩኝ እንዳትለኝ አንተን አይቼ ቆሜያለሁ

ባንድ እጅ አይጨበጨብ ታውቃለህ

ዝምታ ውጦታል ሀገር በርታ በርቺ ብንባባል

አብረን ብንሆን ነበር

ማንም ሰው ይሰደድ

ማንም ሰው ከሀገር ይውጣ

ጥበበኛ ሲጎድል ቀዬ ነው የሚቀጣ

ባንዲራ ነው የሚፈዝ መዝሙር ቅጥ የሚያጣ

ጥበበኛ ሲጎድል ከያኒ ሲታጣ

ሀገር ነው የሚጎድል ቀዬ ነው የሚቀጣ

ባንዲራ ነው የሚፈዝ መዝሙር ቅጥ የሚያጣ

ሁሉ ሰው ቢሰደድ ህዝብ ሁሉ ቢሰደድ የሀገሩ ነዋሪ

ጸሀፊ ሰው ይቅር ለወሬ ነጋሪ

ተባብለን ነበር እኔ እንደ ተማሪ

አንተ እንደ አስተማሪ

ድሮ… ድሮ…

***          ***          ***

ህዝብ ሁሉ ቢሰደድ የሀገር ነዋሪ

ጸሀፊ ሰው ይቅር ለወሬ ነጋሪ

ተባብለን ነበር እኔ እንደ ተማሪ አንተ እንደ አስተማሪ

ዛሬ ምን ተገኝቶ ልብህ የሸፈተ

ወኔህ ምን ከድቶት ነው የተንሸረተተ

ወንድምዬ

ሰውም ሀገርም አይስማ

እኔም አልንገር ለራሴ

መሸሽ አማረው ብዬ የሀገር ጥበብ ለራሴ

እኔ--- እኔ እንክዋን የትናንት ልጅ ደረት ነፍቼ

ባንተ ስም ነው የምጠራው ባንተ ስም ተለክቼ

ባንተ ስፋት ባንተ እውቀት ባንተ ሀሳብ ተከልዬ

እንዴት ምርኩዜን ልጣል ባልረባ ሀሳብ ተከልዬ

እንዴትስ ይስማ ጆሮዬ የተስፋ ቆረጠ ወሬ

አንተ ባቆምከው ምሰሶ ሲለካ ማገር አስሬ

እኔስ ማን አቆመኝና በማን ስም እውነት ዘርቼ

በጽናት ኖርኩኝ እላለሁ ተሸነፍክን ሰምቼ

አንድ አይፈርድም ታውቃለህ

ፍትህ ፈልጓል ሀገር

ትውልድ የሚኮራው አብረን ብንሆን ነበር።

***          ***          ***

ዘመናችን እንዲኮራ እድገታችን እንዲጸና

ተስፋችን የሚያብብ አድጎ አንተ ስትኖር ነውና

ሀማሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሆኖ ሸክሙ በዝቷል ሀገር

ችግራችን የሚፈታው በብእራችን ነበር

ቀለም እንኳ ባይኖረን ወረቀት ከሀገር ቢጠፋ

በደማችን የምንጽፈው የነገ ትውልድ ተስፋ

እኔና አንተን ያኖረናል የጻፍንለት ቀን ሲወጣ

አንተ ብቻ ልሂድ አትበል ሀገር ጥለህ አትውጣ!

***          ***          ***

በሬውም ያው ሜዳውም ያው ባዶ

በሀገሩ በሬ ነው የሀገሩን ሰርዶ

መንገዱ እንኳን እሾህ በዝቶት ምንም ጫማ ባይኖረን

ብቻዬን ልሂድ አትበል እንጥረገው አብረን

ልሂድ አትበለኝ መሸኘት አልወድም

አንተም ግፊያ ፈርተህ ዛሬ አትሰደድም

ጥበብ ጀግናን እንጂ ፈሪን አትወድም

ልሂድ አትበለኝ መሸኘት አልወድም

አንተም ግፊያ ፈርተህ ዛሬ አትሰደድም

ጥበብ ጀግናን እንጂ ፈሪን አትወድም

ስማማ ወዳጄ

በርቀት መጠን ነው ድምጽም የሚሰማ

መሄድክን ተውና ይልቅ እንስማማ

ጠብታ ውሀ ነው ድንጋይ የሚበሳ

ጩህ ዝም ብለን ህዝብ እስከሚነቃ ሀገር እስኪነሳ

እስኪያልፍልን ድረስ ቀን እስከሚወጣ

ታሪክ እየከተብን እኔና አንተ እንኑር ተተኪ እስኪወለድ ሌላ እስኪመጣ

እስኪያልፍልን ድረስ--------- እስኪያልፍልን ድረስ

ጀንበር ወጥታ እስክናይ

እባክህ አትሂድ እንሁን አንድ ላይ

ማንም ሰው ይሰደድ ማንም ከሀገር ይውጣ

ባለቅኔ ሲጎድል ከያኒ ሲታጣ

ሀገር ነው የሚጎድል ቀዬ ነው የሚቀጣ

ባንዲራ ነው የሚፈዝ መዝሙር ጣዕም የሚያጣ

ስለዚህ

አንድ ላይ እንኑር

እባክህ አትሂድ

እባክህ አትውጣ

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመፃህፍትና ቤተመዛግብት ኤጀንሲ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የምንባብ ሳምነትን አዘጋጀ። “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” በሚል መሪ ቃል በአሶሳ ከተማ ከየካቲት 25 እስከ 28 ቀን 2009 ዓ.ም በተዘጋጀው በዚሁ የምንባብ ሳምንት የተለያዩ የሥነ ፅሁፍ ውጤቶች ዓውደ ርዕይ፣ የመፃህፍት ሽያጭና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የፓናል ውይይቶች ተካሂደዋል። ለዚሁ ፕሮግራም ከአዲስ አበባ የተጓዙ የመፃህፍት ሻጮች በርካታ መፃህፍትን ለአካባቢው ህብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ አቅርበዋል።

 

 የከተማዋ ነዋሪዎችም በዚሁ የንባብ ሳምንት ተሳታፊ እንዲሆኑና የመፀሃፍት ግዢን እንዲያከናውኑ ተከታታይ በሆነ መልኩ በተሽከርካሪ ድምፅ ማጉያ ጥሪ ሲደረግ ሰንብቷል። የስነፅሁፍ ወድድርም ተካሂዶ አሸናፋዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ኤጀንሲው በሀገሪቱ የምንባብ ባህልን ለማዳበር በሀገሪቱ የተለያዩ ክልል ከተሞች በመዘዋወር መሰል የንባብ ሳምንትን ያካሂዳል። በዚሁ በአሶሳ ከተማ በተካሄደው የንባብ ሳምንት በንባብ ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊ ተቋማት፣ተማሪዎች፣ምሁራን፣ ደራሲያን እና ተጋባዥ እንግዶች እንደዚሁም የተለያዩ ሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

Page 4 of 19

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us