You are here:መነሻ ገፅ»ኪነ-ጥበብ
ኪነ-ጥበብ

ኪነ-ጥበብ (217)

በጥበቡ በለጠ

      ተናገር አንተ ሐውልት

                በግርማ ታደሰ 1964 ዓ.ም

ተናገር አንተ ሐውልት

ተናገር አንተ ሐውልት አንተ አክሱም ያለኸው

አስከ ዛሬ ድረስ ብዙ ጉድ ያየኸው፤

አንተ ህያው ደንጊያ ብዙ ያሣለፍከው።

ሦስት ሺ ዘመናት እዚያ ተገትረህ

እስቲ ያየኸውን ንገረኝ ዘርዝረህ

እኔ ብዕር ይዤ ታሪክ ልፃፍልህ።

       ንገረኝ! ንገረኝ! አንተ ጥርብ ደንጊያ

       እስከ አሁን የቆምከው ሁሉን አርገህ ትብያ

       ተናገር አንተ ሀውልት ታሪክ ኢትዮጵያ

       ያነፁህ መሐንዲስ ያሳነፁህ ንጉሥ

       እነዚያ የሠሩህ ላባቸው እስኪፈስ

       እነዚህ ሁሉ አልፈው በፍፁም ተረስተው

       ምን ልትሠራ ነው አንተ የተገተርከው?

ተናገር አንተ ሐውልት አክሱም ላይ የቆምከው

በሞቴ! ንገረኝ፣ ተናገር አንተ ሐውልት

እንደምን አቆሙህ ጠረቡህስ እንዴት

ንገረኝ ምስጢሩን ዛሬ እንድንሠራበት።

ታዲያ ያ ሁሉ እውቀት፣ ያ! አንተን የሠራ

የት ገባ ንገረኝ? አስቲ በል እኮ አውራ፤

ተናገር አንተ ሐውልት ማንንም አትፍራ።

አንተን ያነፁ እጆች አንተን የጠረቡ

ንገረኝ አንተ ሐውልት የት ገባ ጥበቡ

በል እስቲ አትሸሽገኝ ንገረኝ የት ገቡ?

       ተብለህ ይሆን ወይ ለሰው አትናገር

       ያንተን ጊዜ ጥበብ፣ ያንተን ጊዜ ምስጢር

       ይበልጥ ተሠርቶ እንዳትፎካከር

       ጡብ ድንቅ! እየተባልክ አንተ ብቻ እንድትኖር?

       ንገረኝ አንተ ሀውልት ግዴለም ተናገር።

እስቲ ልጠይቅህ እረ ለመሆኑ

ያነፁህ መሐንዲስ እነማን ይሆኑ?

አልጋው ላይ ማን ነበር፤ ንጉሥ ወይም ንግሥት

ያኔ ስትሠራ አንተ የአክሱም ሐውልት፤

ንገረኝ እባክህ ታሪክ ልማርበት

አንተን ሠርቶ ማቆም ስንት አመት ወስደ

ስንት ሙያተኛ በኃይል ተገደደ፤

በሌትር ቢሰፈር ስንት ላብ ወረደ?

      ሦስት ሺህ ዘመናት እዚያ ስትገተር

      እንዴት አይደክምህም? ወድቀህ አትሠበር?

      ሦስት ሺህ ክረምቶች የጣሉት ዶፍ-ዝናብ

      መብረቅ ነጐድጓዱ ስንት አገር የሚያወድም፤

      እንዴት ወይ አልመቱህ ወይ አላሟሙህም?

      ተናገር አንተ ሀውልት እስቲ ግድየለህም?

      ምን ምኑን ቀብተው ምን አርገው አኖሩህ?

      ዘላአለም እንድትቆም ሁልጊዜ አዲስ ሆነህ

      እስቲ ስንት ጊዜ መሬት ተናወጠች

      በአክሱም አካባቢ አንተ እንደቆምክ እዚያች

      እንዴት ተቋቋምከው? ምነው አልሆንክ አንዳች?n

በድንበሩ ስዩም

ይህ ከላይ የምትመለከቱት ምስል የፀሐፌ ተውኔቱ ኃይሉ ፀጋዬ ነው። ኃይሉ ፀጋዬ ምን አንፏቀቀው? ለምን ተንፏቀቀ? ለመንፏቀቅ ያስገደደው ትልቅ እምነት ምንድን ነው? በመንፏቀቁ ምን አገኘ? ምን አጣ? እያልኩ ማሰብ ከጀመርኩ ሠነባበትኩ።

 

ኃይሉ ፀጋዬ ለምን ተንፏቀቀ?

ኃይሉ ፀጋዬ በኢትዮጵያ የቴአትር አለም ውስጥ ከ30 አመታት በላይ ስም እና ዝና ያለው ነው። ደራሲ ነው። ይህ ቃል ከባድ ነው። በውስጡ ብዙ ነገሮች አሉት። አንድ ሰው ደራሲ ነው ሲባል እላዩ ላይ ግዙፍ ስብዕናዎች በአይነ ሕሊናችን ይመጣሉ።

 

ደራሲ ማለት የአንዲት ሐገርን ታሪክ፣ ባሕል፣ ፍልስፍና፣ ጥበብ፣ ንባብ ወዘተ ጠንቅቆ ያወቀ ማለት ነው። ይህ እንግዲህ ሲዘረዘር ትርጉሙ የትየለሌ ነው።

 

አንድ ደራሲ የሐገሩን ታሪክ ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው ሲባል ትልቅ ጉዳይ ነው። ሐገሩ የወጣች የወረደችበትን፣ ጓዳ ጐድጓዳዋን፣ በርብሮ የተረዳ ሰው መሆን አለበት። ምክንያቱም በድርሰት ስራዎቹ ውስጥ የሚፅፈው ነገር በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ስለ ሀገሩ ነው። ስለዚህ ሐገር የሚለው ትልቁ ምስል ደራሲው ምናብ ውስጥ በሰፊው ተንዠርጐ ይኖራል ተብሎ ይታሰባል።

 

ደራሲ የሐገሩን ባሕል ያውቃል የሚል እምነት አለ። ባሕል የሚለው ቃል በራሱ እጅግ ሠፊና ጥልቅ ነው። የማሕበረሰብ መገለጫ ነው ባሕል፤ አለባበስ፣ አነጋገር፣ ቋንቋ፣ ዘፈኑ፣ እስክስታው፣ አበላሉ፣ አጠጣጡ፣ ሌሎችም ተዘርዝረው የማያልቁ ጉዳዮችን ይዟል። ባሕል ቁሣዊና መንፈሣዊ በመባልም በሁለት ይከፍሉታል። በዘርፉ ውስጥ ጥልቅ ምርምር ያደረጉ ሊቃውንት። በቁሣዊም ሆነ በመንፈሣዊው ገለፃ እጅግ ብዙ ዝርዝሮች አሉት። እናም አንድ ደራሲ ይህን ሁሉ ጓዝ የሚያውቅ ነው ተብሎ ይታሰባል። ምክንያቱም የሚፅፈው ነገር ስለ ሰው ነው። የሚፅፈውም ለሰው ነው። ደራሲ የባሕል እስረኛ ነው ይባላል። ደራሲ ብለን የምንጠራው ሰው የባሕል አዋቂያችን ነው።

 

ደራሲ የሐገሩን ፍልስፍና እና ስነ-ልቦና ጠንቅቆ የሚያውቅ ነው ተብሎም ይታሠባል። የሚፅፈው የሰውን ልጅ ባሕሪ ነው። በሣላቸው ገፀ-ባሕሪያት አማካይነት ፀብ አለ፣ ፍቅር አለ፣ አስተሣሰብ አለ፣ ታሪክ አለ፤ ውልደት አለ፤ እድገት አለ፤ ሞት አለ። የደራሲ ምናብ የሚያግደው ነገር ስለሌለ ከሞት በኃላ ስላለው ጉዳይም ሊፅፍ ይችላል። ስለዚህ ደራሲ የምንለው ሰው በውስጡ እነዚህን ጉዳዮች የተሸከመ ነው።

 

ደራሲ ምናበ ሠፊ ነው። ምናብ የምንለው በእንግሊዝና ፈረንጆቹ (Imagination) የሚሉትን ነው። ከጥቂት ሰበዟ ጉዳይ ተነስቶ መጨረሻ የሌለው፣ ከአድማስ ወዲያ ማዶ ሁሉ የሚሔድ ሃሣብ ነው። ደራሲ የዚያ ሃሣብ ባለቤት ነው። ደራሲ የምናብ ሰው ነው።

 

ደራሲ አንባቢ ነው። በውስጡ ያሉት የኑሮ ሴሎች ካላነበቡ ታሪክን፣ ባሕል፣ ፍልስፍናን፣ ስነ-ልቦናን ማወቅ አይችሉም። ንባብ የደራሲው መተንፈሻ እና መንቀሣቀሻ ሞተር ነው። እናም ደራሲ አንባቢ ሰው ነው ተብሎ ይታሰባል። ካላነበበ አይፅፍም!

 

ደራሲ ስሜተ ስሱ (Sensitive) ነው ተብሎ ይታሠባል። ስሜተ ስሡ ስንል ለሌላው ሰው ምንም የማይመስል ነገር፣ ደራሲን ይኮሠኩሠዋል። እንቅልፍ ይነሣዋል። ትንሿ ነገር ደራሲ ዘንድ ስትደርስ ግዙፍ ሆና ልትታይ ትችላለች። አንዳንድ ሰዎች የደራሲን ስሜተ ስሱነት ሲገልፁ፣ ቆዳው ከውስጥ ወደ ውጭ የተገለበጠ ሰው ነው ይላሉ። በደራሲ አእምሮ ውስጥ ተራ ነገር ተብሎ የሚታለፍ ጉዳይ የለም። ለዚህም ነው ስሜተ ስሱ ነው የሚባለው።

 

ደራሲ አስታዋሽ ነው። ትልቅ የማስታወሰ ችሎታ ያለው ሠው ነው። እነዚህን ከላይ ያነሣናቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ማስታወስ የሚችል ነው። ካላስታወሰ ታሪክ መፍጠር አይችልም። መፃፍ አይችልም። ስለዚህ በማስታወስ ችሎታው ከማሕበረሰቡ ውስጥ ልቆ የሚገኝ ሰው ማለት ደራሲ። ደራሲ ይህን ሁሉ ነገር ታሪክ ፈጥሮ መፃፍ የሚችል ሰው ነው። ከሌላው ሰው በእጅጉ የሚለየውም የመፃፍ ችሎታው ነው። ፀሐፊ ነው። እነዚህ የደራሲነት መገለጫዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። አንድ ደራሲ የምንለው ሰው እነዚህ መገለጫዎች አነሰም በዛ ይኖሩታል። ሁሉም ደራሲ በእኩል መልክ የደራሲነት መገለጫ አላቸው ተብሎ ባይታሰብም ደራሲ የምንለው ሰው ግን የነዚህ ነጥቦች መገለጫ ነው።

 

ወደ ተነሣንበት ነጥብ እንመለስ። ኃይሉ ፀጋዬ ደራሲ ነው። ያውም ፀሐፌ ተውኔት (Playwright) ነው። በርካታ የመድረክ፣ የሬዲዮ፣ የቴሌቪዥን ቴአትሮችን እና ድራማዎችን የፃፈልን ሰው ነው። አሁንም እየፃፈ የሚገኝ ባለሙያ ነው። ይህ ሰው የደራሲነት መገለጫ ናቸው ብለን ከላይ ባነሣናቸው ነጥቦች ውስጥ ያለፈ ነው። ያውም አንጋፋ ደራሲ ብለን የምንጠራው ከያኒ ነው። ይህን ሰው መሬት ላይ ሲንፏቀቅ ብናየው ግራ ልገባ እንችላለን። እኔ ግራ ገባኝ። ኃይሉ ፀጋዬን ምን አንፏቀቀው?

 

በEBS ቴሌቪዥን ላይ የአፍታ ጨዋታ በሚል አንድ ኘሮግራም አለ። ይህ የአፍታ ጨዋታ የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ሠዎችን እየጋበዘ የተለያዩ ድርጊቶችን እንዲፈፅሙ የሚያደርግ ነው። አላማው ማዝናናት ነው። የሚያዝናናባቸው ጨዋታዎች ደግሞ ድሮ የወላጆች ቀን በየ ት/ቤቱ ሲከበር ሕፃናት ተማሪዎች የሚያቀርቧቸው ጨዋታዎችን ባብዛኛው ይዟል። ብዙዎቹ የልጆች ጨዋታዎች ናቸው።

 

እንደ ኃይሉ ፀጋዬ አይነት ሰብዕናዎች ብርቅ ናቸው። በርካታ ቴአትሮችን የፃፈ ሰው በመገናኛ ብዙሃን ሲቀርብ ከአንደበቱ ማር እንጠብቃለን። ከድርጊቱ ትልቅ ጥበብ እንጠብቃለን። ይህን አጥተን ያ ደራሲ ያልነው ትልቁ ሰው በሚሊየኖች ፊት ቀርቦ ከርሡ የማይጠበቅ ድርጊት ውስጥ ሲገባ ለደራሲነት የሠጠነውን ትርጉም ድራሹን ያጠፋብናል። ኃይሉ ፀጋዬ ወርዶ ባይንፏቀቅ መልካም ነበር።

 

የኪነ-ጥበብ ሰዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ታዋቂ የሚባሉ ሰዎች፣ ደራሲያን የሚቀርቡባቸው መድረኮች በራሣቸው የትልልቅ ርዕሰ ጉዳዮች መነሻ መሆን አለባቸው። ከማይመጥኗቸው ሜዳ ውስጥ ዘለው ወርደው ገብተው መጫወት የሰብዕና ጉድለት ያመጣል። በማሕበረሰቡ ውስጥ ትልልቅ ቦታ የተሰጣቸው ሠዎች ከማይመጥኗቸው ኘሮግራሞች ውስጥ እየቀረቡ ሰብዕናቸውን ሲያላሽቁት ማየት ከጀመርን የቆየን ይመስለኛል። ይህ ጉዳይ መሻሻልና አንድ ቦታ ላይ መቆም አለበት። ታላላቅ የምንላቸው ሰዎቻችን ከታላቅነት መንበራቸው እየተነሡ ሲንፏቀቁ ማየት ያለብን አይመስለኝም። እንዲህ አይነት ድርጊቶች ታላላቅ ብለን ቦታ የሠጠናቸውን መስሎች ያጠፉብናል።

 

በዚህች ሀገር ውስጥ ሀዲሰ አለማየሁ የሚባል ደራሲ መጥቶ ሔዷል። በዚህች ሐገር ውስጥ ፀጋዬ ገ/መድህን የሚባል ደራሲ መጥቶ ሔዷል። በዚህች ሀገር ውስጥ ብርሃኑ ዘሪሁን የሚባል ደራሲ መጥቶ ሔዷል። በዚህች ሐገር ውስጥ አቤ ጉበኛ የሚባል ደራሲ መጥቶ ሔዷል። በዚህች ሐገር ውስጥ የሰብዕና ግርማ ሞገሳቸው ገዝፎ እያበራ፣ ብርሃን የሚያሣየን ማንነቶች ሞልተው ተርፈውናል። በነርሱ የብርሃን ውጋገን ውስጥ ሆነን ሌላ ትልልቅ የሰብዕና መብራቶች መሆን አለብን። ሕዝብ ፊት ቀርበን መንፏቀቅ ደራሲ የሚባለውን ትልቁን ማማ ያናጋብናል።n

    

 

በጥበቡ በለጠ

 

“ቃና” ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ እየሆነ የመጣ ነው። በየቤቱ ቃና ይከፈታል። እናቶች ሕፃናት ልጆቻቸውን በቤት ውስጥ ከመንከባከብ ዝግ እንዲሉ፣ የቤት ውስጥ ስራ እንዳስፈታቸው የሚናገሩ ብዙ ወዳጆች አሉኝ።

አንድ ጓደኛዬ ሲነግረኝ፣ ባለቤቱ ሁልጊዜ ከ11፡30 በኋላ ትደውልለት ነበር። ከቢሮ ወጣህ? የት ደረስክ? ታክሲ አገኘህ? ተመችቶሃል? አሁን እምኑጋ ናችሁ? ምን ሰርቼ ልጠብቅህ? ሩዝ አለ፣ ሰላጣም አለ፤ የተፈጨ ስጋም ይኖራል… ወዘተ እያለች ትደውልለት ነበር-ውድ ባለቤቱ። ነገር ግን ቃና ቴሌቪዥን የፊልም ስርጭቱን ከጀመረ በኋላ መደወል አቆመች። ጭራሽ ሳትደውልለት ከቤት ይደርሳል። ባለቤቱም እየገረማት፣ የግድግዳ ሰዓቱን ቀና ብላ እየተመለከተች ስንት ሰዓት ሆኖ ነው የመጣኸው? ከመቼው ደረስክ? እያለች ትጠይቀዋለች። ቃና ቴሌቪዥን ባሏን ሁሉ እያስረሳት ነው።

ሻይ፣ ውሃ፣ ምግብ እሣት ላይ ጥደው በቃና ቴሊቪዥን ፈዘው ጉዳት ያደረሱ ሰዎችም ታሪክ እየተነገረ ነው። “ቃና ውስጤ ነው” የሚለው ማስታወቂያ ብዙ የሠራ ይመስላል። 

 

ለመሆኑ ቃና ምንድን ነው?

ታዋቂ ሰዎች እየቀረቡ የሕይወቴ ቃና የተጀመረው…. እያሉ እጅ እግር የሌለው ማስታወቂያ እየሠሩ ነው። ከታዋቂው ሙዚቀኛ፣ ዲስኩረኛ ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) ጀምሮ ድምፃዊ ፀደንያ ገ/ማርቆስ፣ ተዋናይት ሜሮን ጌትነት እና ሌሎችም “የሕይወቴ ቃና ለውጥ የጀመረው….” እያሉ እንሰማለን። ለመሆኑ “የሕይወቴ ቃና” የሚሉት አማርኛ ምንድን ነው? ቃና ቴሌቪዥንን ለማስተዋወቅ ሲባል ብቻ ‘የሕይወቴ ቃና ለውጥ የጀመረው….’ እየተባለ ማውራት ምን ይሉታል። ይህ ቋንቋን አለማወቅ ነው? ወይስ የተከፈለበት ማስታወቂያ ብቻ ስለሆነ ነው?

 

ደስታ ተክለወልድ አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በተሰኘ መፅሐፋቸው ውስጥ በገፅ 1180 ላይ ቃና ለሚለው ቃል የተለያዩ ዝርዝሮችን በፍቺነት አቅርበዋል።

 

መቀኘት           መንገር፣ መስጠት፣ መግለፅ ቅኔን

ቃና፤ (ቃነየ)       የዜማ፣ የመጠጥ፣ ጣዕም። በግዕዝ ግን ዜማ ማለት ነው። ንስርንና ምስርን ተመልከት

ቃና              ጌታችን ውሃን ወይን ጠጅ ያደረገበት አገር በገሊላ አውራጃ ያለ።

ቃና              የቀበሌ ስም በቡልጋ ውስጥ ያለ ስፍራ ጉባኤ ቃና የተጀመረበት

 

ቃናው ተለወጠ      ጣዕሙ ሌላ ሆነ።

 

ታዲያ የነጋሽ አበራ ሞላ፣ የነ ሜሮን ጌትነት፣ የነ ፀደንያ ገ/ማርቆስ እና ሌሎችም የሕይወታቸው ቃና ለውጥ የትኛው ይሆን? የዜማው ነው? የመጠጡ ነው? የጣዕሙ ነው? ወይስ ደግሞ ጌታችን ውሃን ወይን ጠጅ ያደረገበት በገሊላ አውራጃ ያለው ቦታ ነው? የሕይወታቸው ቃና ለውጥ ምናልባት በቡልጋ ውስጥ ያለ ስፍራ ጉባኤ ቃና የተጀመረበት ይሆን? ወይስ ጣዕማቸው ሌላ የሆነበት ነው? ቃና ትርጉሙ የቱ ይሆን?

 

እንዴትስ ሁሉም አርቲስት እየተነሳ “የሕይወቴ ቃና ለውጥ የመጣው…” እያለ ይናገራል። እነዚህ አርቲስቶች የራሳቸው የሆነ መለያ ቀለም የላቸውም? እንዴት ሁሉም ሕይወታቸው በቃና እና በለውጥ ውስጥ ተዋወቀ? አርቲስቶች ምን ሆኑብኝ ብዬ ቢጨንቀኝ ነው የጠየኩት።

 

ቃና ቴሌቪዥን ስርጭት የጀመረ ሰሞን ተቃውሞ አዘል መግለጫዎችና የጋራ አቋሞች በሰፊው ይደመጡ ነበር። ለምሳሌ በኪነ-ጥበብ ሙያ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ከሚያነሷቸው ቅሬታዎች አንዱ ቃና ለሀገር ውስጥ ፊልሞች እና ባለሙያዎች ቅድሚያ አይሰጥም፤ እንዳለ የባሕር ማዶ ፊልሞችን ተርጉሞ ነው የሚያቀርበው የሚል ነው። አንዳንድ ታዋቂ ፀሐፊያን ደግሞ ቃና ቴሌቪዥን ሌላ መጤ እና ደባል ባህሎችን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳያሰርግ ስጋታቸውን ይገልፃሉ። በቃና ቴሌቪዥን አማካይነት በሚተላለፉ ባሕር ማዶአዊ ፅንፎች አማካይነት ግብረ-ሰዶማዊነት፣ አደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚነት፣ ወንጀለኝነት፣ ነውጠኝነት፣ ረብሸኝነት እና ሌሎችም ጐጂ ልማዶች በኢትዮጵያውያን አዕምሮ ውስጥ እየሠረጉ እንዳይገቡ ምን የተደረገ መከላከያ ዘዴ አለ? ብለው የተጨነቁ አሉ። ሌሎች ደግሞ ስለ መጪዋ ኢትዮጵያ የሚያስቡ አሉ። በአሁኑ ወቅት ቃና ቴሌቪዥን በሚያሰራጫቸው ፊልሞች አማካይነት ወላጆችም ልጆችም በቤት ውስጥ ተጥደው እየተመለከቱ ነው። በየትኛውም ዓለም አዲስ ባሕልና አስተሳሰብ ሠርገው የሚገቡት በፊልምና በልዩ ልዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ነው። እናም ቃና በሚያስተላልፋቸው ፊልሞች አማካይነት ወደፊት የምናገኘው ኢትዮጵያዊ አሁን ካለበት ማንነቱ ያፈነገጠ እና የሌሎችን ማንነት የተሸከመ ሊሆን ይችላል ብለው ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

 

ለዚህ አዲስ መጤ ባህል እጃቸውን አስገብተው እያስተዋወቁ ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያዊ መገለጫ አላቸው ተብለው በማኅበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያላቸው እንደ አርቲስት ስለሺ ደምሴ /ጋሽ አበራ ሞላ/ የመሳሰሉ ሰዎች ናቸው። ‘የሕይወቴ ቃና ለውጥ’ የጀመረው እያሉ በማይገጥም የቋንቋ ገለፃ፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የቃና ፊልሞች ላይ ተሰክቶ እንዲኖር ይሰብካሉ።

 

ቃና ምን አጠፋ?

ቃናማ ያጠፋው ነገር የለም። ወደ ኢትዮጵያ የገባው እንደ አንድ የቴሌቪዥን አማራጭ ሆኖ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ይወዳል። ያንን የሚወደውን ታሪክ ደግሞ በራሱ ቋንቋ ተርጉመን እናቅርብለት ብለው የሚፈልጓቸውን ፊልሞች ተጨንቀው ተጠበውበት በግሩም የጥራት ደረጃ ተርጉመውም አቀረቡ። በአሁኑ ወቅት ከሁሉም የቴሌቪዥን ስርጭቶች በተሻለ ሁኔታ የኢትዮጵያዊያንን ቀልብ ለመግዛት ችሏል። እንደ አንድ የሚዲያ ቢዝነስ ካየነው የቃና ቴሌቪዥን አዋጭ በሆነ ስራ ውስጥ ተሰማርቷል።

 

ከዚህ በተረፈ ደግሞ የተለያዩ የባህል ጉዳዮችንም እያሰረገብን መሆኑም መታወቅ አለበት። ለምሳሌ ፈረንጅ ሁሉ የተሻለ አስተሳሰብ አለው ብለው የሚገምቱ ሠዎች አንድ ነገር ያወቁ ይመስለኛል። ለካ ፈረንጅ ውስጥም ወሬኝነት፣ ተንኮል፣ በመርዝና በሸር መጠላለፍ፣ አሳባቂነት፣ ምቀኝነት፣ አሉባልታ ወዘተ መኖሩን ከፊልሞቹ ተረድተዋል። ከዚህ ሌላ ደግሞ የማያውቋቸውን የጥፋት ድርጊቶችንም ከፊልሞቹ እየወሰዱ መሆኑን መካድ አይቻልም።

 

ቃና ምን አጠፋ ብዬ፣ ምንም አላጠፋም የሚል የራሴውኑ ምላሽ በድፍረት ሠጥቻለሁ። ምክንያቴ ደግሞ ቃና የመጣው ለቢዝነስ ነው። የሚዲያ ቢዝነስ ይዞ። ይህን የሚዲያ ቢዝነስ ይዞ ሲመጣ ግን ኢትዮጵያ የምትባልስ ሀገር እንዴት ተቀበለችው? ምን አይነት የሚዲያ ሕግ እና ማዕቀፍ አላት? ሚዲያዎች ኢትዮጵያዊነት ማንነትን እንዳያፈርሱት፣ እንዳይደረምሱት ምን የተቀመጠ መመሪያ፣ ደንብ፣ ስርዓት አለ?

 

ቃና የመጣው ኢትዮጵያዊ የቤት ስራችንን ሳናጠናቅቅ ነው። ተዝረክርከን እያለ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ባህር ማኦአዊ ማንነትን ይዞብን ብቅ አለ። ቃና የመጣው እኛ ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር እና ማንነቷን በትውልዱ ዘንድ መገንባት ተስኖን ሳለ ነው። ለምሳሌ FM ሬዲዮ ጣቢያዎቻችንን ብንቃኝ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን ጨዋታ ማውራት፣ መተንተን፣ መቦትለክ፣ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኗል። በሬዲዮ የሚተላለፉ የእግር ኳስ ጨዋታዎች እንግሊዞች ናቸው። ወጣቱ በሰመመን ከእንግሊዝ ሊጐች እና ተጫዋቾች ዘንድ እንዲኖር በሰፊው ተሰርቷል። እነዚህ የስፖርት ፕሮግራሞች ደግሞ በታላላቅ የንግድ ኩባንያዎች ስፖንሠር የሚደረጉ ናቸው። ሌሎች የሬዲዮ ፕሮግራሞችም አሉ። የማኅበረሰቡ እና የኢትዮጵያዊነት ታላላቅ ዕሴቶች ላይ እየተረማመዱ የሚያጠፉ። እነርሱም ብቅ ባለው የሚዲያ ነፃነት ውስጥ ገብተው ኢትዮጵያዊነትን ሲጨፈላልቁ ሃይ፣ ተው ያላቸው አልነበረም። በእነዚህ ክፍተቶች ውስጥ የቃና መምጣት አያስገርምም።

 

ለመሆኑ ይህ ኢትዮጵያዊነት ኢትዮጵያዊነት እያልን የምንደሰኩርለት ነገርስ በራሱ ምንድን ነው? ኢትዮጵያ ምንድን ናት? ምን አይነት ኢትዮጵያዊነት እንዲገነባ ነው የምንፈልገው? እነዚህ ጥያቄዎች ሊቀርቡ ይችላሉ። ጥያቄዎቹ ትክክል ናቸው። መልሳቸውም እጅግ ሰፊ እና ጥልቅ ነው። ምክንያቱም የተጠየቀው ማንነት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ነው። እንዴት ይመለስ?

ለዛሬ መልሳችንን እናጥበው። የምናጠበው ወይም ሰብሰብ የምናደርገው ከቃና ቴሌቪዥን ጋር ስለተያያዘ ነው። ጉዳያችን አንድ ነው። ቃና ነው።

 

ቃና ቴሌቪዥን ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚሠራጭ የፊልም ጣቢያ ነው። ተፈቅዶለት በነፃነት በየቤታችን ገብቶ የባሕር ማዶን ፊልም ያስኮመኩመናል። ነገር ግን እዚህ ኢትዮጵያ ውሰጥ ከባድ ከሆኑ ስራዎች መካከል ፊልም ዋነኛው ነው። ምክንያቱም የኢንቨሰትመንት ፈቃዱ በራሱ ፊልምን አያበረታታም። ለምሳሌ ዘመናዊ የፊልም መስሪያ ቁሳቁሶችን እንደ ካሜራ፣ ኮምፒውተር፣ መብራት፣ የማባዣ ማሽኖች፣ ፕሮጀክተር ወዘተ የመሳሰሉትን ቁሳቁሶች ወደ ሀገር ቤት ማስገባት አዳጋች ነው። ከፍተኛ ታክስና ቀረጥ ይከፈልባቸዋል። ስለዚህ የኢትዮጵያ የፊልም እንቅስቃሴ ከብዛት ወደ ጥራት መምጣት አልቻለም። ባለህበት እርገጥ ሆኗል። ለአመታት በተዳከመው ኢትዮጵያዊ የፊልም እንቅስቃሴያችን ላይ ቃና ቴሌቪዥን ሙሉ በሙሉ ባህር ማዶአዊ የሆኑ ፊልሞችን ይዞ ሲመጣ፣ ድሮም ሕመም ላይ የነበረው የኢትዮጵያ የፊልም እንቅስቃሴ ወደ መቃብሩ ጫፍ ማዘንበሉ አይቀርም። ለእኔ አንዱ የኢትዮጵያዊነት መፍረስ ምንጩ ይህ ይመስለኛል።

 

ሌላው የመፍረስ አደጋ ደግሞ፣ ፊልሞች ተሠርተው ለሕዝብ የሚቀርቡበት መንገድ በራሱ አዋጭ አለመሆኑ ነው። ኢትዮጵያዊ ፊልም ሠሪዎች ብቃት በሌላቸው የፊልም መሣሪያዎች ፊልሞቻቸውን ከሠሩ በኋላ ለሕዝብ ዕይታ ሲያቀርቡ የአዳራሽ ኪራዩ፣ ለመንግስት የሚከፈለው የትርፍ ግብር እና የትኬት ሽያጭ ግብር ተደማምረው ሴክተሩን ውጤታማ አያደርጉትም። በዚህ ምክንያት ፊልም ደግሞ ደጋግሞ የሚሰራ ፕሮዲውሰር ኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ሁሉም ጀምሮ ያቆማል። ወገቡን ይሰበራል። በዚህ በተሸማቀቀ የፊልም ኢንደስትሪ ውስጥ ቃና ቴሌቪዥን ብቅ አለ። 24 ሰዓት ሙሉ የባህር ማዶ ፊልሞችን ሲያቀርብ ያ በሰቀቀን የኖረው ኢትዮጵያዊ ፊልም መክሰም መሞት ይጀምራል። ይህም ሌላው የኢትዮጵያዊነት መፈራረስ ምክንያት ነው።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ ፊልም ለመቅረፅ ካሜራ ተይዞ ሲወጣ መንገድ ላይ የቆመው ፖሊስ ሁሉ ከልካይ ነው። ምንድነው የምትሰሩት? ፈቃድ አምጡ! ይላል። ቆመጡን እያስተካከለ ካሜራ የሚቀማ፣ የሚያግድ መንገደኛና ፖሊስ የበዛበት ሀገር ነው። ሁሉም ከልካይ ነው። በእንዲህ አይነት መከራ ውስጥ እየታለፈ ነው ኢትዮጵያዊ ፊልም ይሰራ የነበረው። ይሄ ጉዳይ ሳይሻሻል እና የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪዎች እንደልባቸው በነፃነት መስራት ባልቻሉበት ወቅት ቃና ቴሌቪዥን የባህር ማዶ ፊልሞችን ይዞ በኢትዮጵያ አየር ላይ እንደ ልቡ ናኘበት። ታዲያ ኢትዮጵያዊነት እየተሸረሸረ አይሄድም?

 

ሌላም ጉዳይ አለ። ኢትዮጵያ ውስጥ ፊልም ለመስራት ወይም በፊልም ስራ ውስጥ ለመሰማራት የሚፈልግ ሰው ሀሳቡን አቅርቦ የባንክ ብድርም ሆነ ስራውን ለማከናወን የሚያስችለውን የፋይናንስ ድጋፍ ማግኘት አይችልም። ፊልም ሰሪው ከራሱ ኪስ በምትወጣ ገንዘብ ነው ወደ ፊልም ስራ የሚገባው። ይህ ሁኔታ ኢንደስትሪው እንዳያድግ ከፍተኛ ጫና ከፈጠሩ ጉዳዮች አንዱ ነው። ፊልምን የሚደግፍ ሲስተም የለንም። ይህን ድጋፍ ሳያገኝ ብቻውን በሚውተረተር ኢትዮጵያዊ ፊልም ላይ ቃና መጣበት። የኢትዮጵያ ፊልም የግዱን ይሞታል።

 

ቃና ቴሌቪዥን ሲመጣ እኛ የችግር ኮተታችንን ሳናራግፍ ነው የደረሰብን። ለምሳሌ ፊልም ሠሪዎቻችን ራሳቸው ተጠያቂዎች ናቸው። እስከ አሁን ድረስ የተሰሩ ሀገርኛ ፊልሞችን ሰብሰብ አድርገን ብንመለከት ዕውን ኢትዮጵያዊ ሆነው አናገኛቸውም። በኢትዮጵያ ደም እና ወዝ ብሎም ዘር የተፈጠሩ አይደሉም። የሀገራቸውን ባህልና ማንነት የሚያንፀባርቁ አይደሉም። በሆሊውድ ፊልሞች ተፅዕኖ ስር የወደቁ ነበሩ። ታዲያ ይህን ለማሻሻል ብርቱ ጥረት ሳይደረግ ቆይቷል። ይህ መዝረክረክ እያለ ቃና ቴሌቪን መጣ። ኢትዮጵያዊነትን ሳንገነባ የሌላ ሀገር ማንነት የኢትዮጵያን አየር ተቆጣጠረው። ቃና ናኘበት። እናም ኢትዮጵያዊ ማንነት ክስመት ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው።

 

ኢትዮጵያ የግል የቴሌቪዥን ሚዲያ ሳይኖራት ለረጅም አመታት አንቀላፋች። ዛሬም ድረስ ከዚሁ ሀገር በቀል የሆኑ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሏትም። ከመንግስት ውጭ ያሉት የቴሌቪዥን ስርጭች በሙሉ ከውጭ ሀገር ወደ ውስጥ የሚሰራጩ ናቸው። ከውስጥ የሚመነጭ የማንነት ቴሌቪዥን የለንም። ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ተደራጅተው ወደ ውስጥ የሚሰራጩ ናቸው። ዳያስፖራ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ናቸው ያሉን። ሀገርኛ የሉንም። ያሉት የመንግሰት ልሣን የሆኑት ብቻ ናቸው EBC1፣ EBC2፣ EBC3፣ የአማራ፣ የኦሮሞ እና ሌሎችም አሉ። ሁሉም ጉዳያቸው ተመሳሳይ ነው። የመንግሥት ልሣኖች ናቸው። ነፃ አይደሉም። ብዙ ያገለገሉ ቢሆኑም፤ አሰልቺ ይዘት ያላቸው ናቸው። በዚህ መሰላቸት ውስጥ ቃና ቴሌቪዥን መጣ። አብዛኛው ሰው ሪሞት ኮንትሮሉን ወደ ቃና አዞረ። ምሬቱን የሚያስታግስለት አማራጭ መጣ። “ቃና ውስጤ ነው” አለ። ኢትዮጵያዊነት በስርዓት ሳይቀርብ ለአመታት በመቆየቱ ምክንያት ሕዝቡ ወደ ሌሎች ማንነት እና ባህል ገባ። ቃና አየሩ ላይ ናኘ። ማን ይመልሰው? ማን ይቆጣጠረው? በተሰላቸ ተመልካች ውስጥ እራስን ማስረሻ /Fantasy/ ይዞልን መጣ።

 

ቀድሞ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እየተባለ የሚጠራው ትልቅ ተቋም፣ በኋላ መጠሪያውን ትቶ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ብሎ ራሱን ሰየመ። በስሙ አጠራር ብዙዎች አዘኑ። ለኢትዮጵያ ሕዝብ “…. ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን” ማለት ምን ማለት ነው? ትርጉሙ ምንድን ነው? እየተባለ ክፉኛ ተተቸ። ከእሱ በኋላ የመጣው ቴሌቪዥን ጣቢያ መጠሪያ ስሙን “ቃና” ብሎ መጣ። ሌላው ደግሞ “ናሁ” አለ። ብቻ በእነዚህ የተምታቱ ግርግሮች መካከል ኢትዮጵያዊ ስም እና መጠሪያ ይዘው የመጡት “ቃና” እና “ናሁ” ቴሌቪዥኖች የሕዝቡን ዝንባሌ ተቆጣጠሩት። በተለይ ቃና ሕዝቡን፣ ሌላ አልሰማም፣ አላይም አስብሎታል።

 

ሌላው አንገብጋቢ ጉዳይ የሃይማኖት ነገር ነው። በኢትዮጵያ የብሮድካስቲንግ ሕግ የሃይማኖት ተቋማት በሀገሪቱ ውስጥ የቴሌቪንም ሆነ የሬዲዮ ስርጭት እንዳይከፍቱ ያስገድዳል። ወይም ይገድባል። ስለዚህ ሃይማኖታዊ ጉዳይ በሬዲዮም በቴሌቭዥንም የተከለከለባት ሀገር ናት። ግን በቃና ቴሌቪዥን አማካይነት የሕንድን አምልኮ፣ ከራማ፣ አውሊያ… ቁጭ ብለን በቤታችን እንኮመኩማለን። ቃና የሌሎች ሀገሮችን እምነት፣ አስተሳሰብ፣ ማንነት፣ አምልኮ እንደ ልቡ በኢትዮጵያ አየር ላይ ሲያሰራጭ እኛ ግን የራሳችንን የዕምነት ተቋሞች ፍልስፍና ማሰራጨት አንችልም። ግን ለምን? ለምን እንዲህ ይሆናል? ማነው የከለከለው? ኢትዮጵያ የክርስትናውም ሆነ የሙስሊሙ እምነት ተከታይ ሀገር ናት። አንዱ አንዱን ሳይነቅፍ ለምን የሬዲዮም ሆነ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አይፈቀድላቸውም? ባለመፈቀዱስ ምክንያት የሚመጣው ተፅዕኖ ግምት ውስጥ ገብቷል።

 

ዛሬ ቃና ቴሌቪዥንም ሆነ ሌሎቹ ቴሌቪዥኖች የውጭ ሀገር እምነቶችን በልዩ ልዩ ዘዴ ወደ ሀገር ውስጥ እያሰራጩት ይገኛሉ። እኛ ደግሞ የራሳችን ተገድቦብናል። ታዲያ የኢትዮጵያዊነት የመፍረስ አደጋ ይሄ አይደለም? የራስን እምነት ዘግቶ የሌሎችን መቀበል አደጋ አይደለም? ኢትዮጵያስ ከውስጥዋ በጐለበቱ ሃይማኖቶችዋ ጐልታ ካልወጣች ሀገር ትሆናለች? የነ ቃና ቴሌቪዥን ስርጭቶች በማንነት፣ በኢትዮጵያዊነት ላይ የሚያመጡት አደጋ ከእነዚህ ነገሮች ጋር የተገናኙ ናቸው። እኛ የቤት ስራችንን በስርዓት ባለመስራታችን የተነሳ በድንገት የሌሎች ሀገራት ማንነት በሕፃናት ልጆቻችን ላይ መጥቶ ወደቀባቸው። አየራቸውን ተቆጣጠረባቸው። ዛሬ የሚበሉትና የሚተነፍሱት ከሀገር ውስጥ በመነጨ የኪነ-ጥበብ ስራ ሳይሆን፣ ቃና በሚያሰራጨው የባዕዳን ማንነት ነው።

 

ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ የምታራምደው ስርዓት ቋንቋን መሠረት ያደረገ ሬደራሊዝም ነው። ሁሉም ብሔረሰቦች በራሳቸው አፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲማሩ፣ እንዲዳኙ፣ እንዲያስተዳድሩ ተፈቅዷል። በዚህም የተነሳ ማዕከላዊ የሆነ የጋራ ቋንቋ ሳይኖራቸው 25 አመታት ተቆጥረዋል። ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ የላትም። አማርኛ ቋንቋ የፌደራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ እንጂ ብሔራዊ ቋንቋ አይደለም። ስለዚህ የአማርኛ ቋንቋ ጠቀሜታ በብዙ ቦታዎች ተገድቦ ኖሯል። በዚህም ምክንያት ዛሬ አማርኛ ቋንቋ የማይናገሩ የ25 ዓመት ወጣቶች ብዙ ናቸው። በዚህም ምክንያት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ እኩል የሚወያዩበት ጉዳይ እየጠፋ ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ፓርላማ የሚወያየውና ሀሳቦችን የሚያፀድቀው በአማርኛ ቋንቋ ነው። ይህን የፓርላማ ውይይት በአማርኛ እየተካሄደ ቋንቋውን ባለመማራቸው የማይሰሙ ኢትዮጵያዊያን ብዙ ናቸው። አሁን ደግሞ የሚከፈቱት ቴሌቪዥኖች በሙሉ በአማርኛ ነው።

 

ስለዚህ በፖለቲካዊ ጫና ምክንያት አማርኛን ያልተማሩ ወጣቶች ዛሬ ከሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ጋር እኩል መራመድ አልቻሉም። በመሆኑም በብሔራዊ አንድነት ላይ ብዙ ሳንሰራ ቴሌቪዥኖቹ እያጥለቀለቁን ነው። አማርኛን መንግሥት ብሔራዊ ቋንቋ ሳያደርገው በራሱ ጉልበት ብሔራዊ ቋንቋ ሆኗል። ስለዚህ በሁሉም ትምህርት ቤቶች መሰጠት ያለበት ቋንቋ መሆኑን ማንም ሊረዳው የሚገባበት ወቅት ነው። የኢትዮጵያዊነት ገመድ በብሔራዊ ቋንቋ ውስጥ መተሳሰር አለበት። እንዲያ ከሆነ አንወድቅም።

 

በአጠቃላይ ሲታይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ስርጭቶችን ማግኘቱ እሰየው የሚያሰኝ ነው። ምርጫው እጁ ላይ በያዘው ሪሞት ኮንትሮል መሆኑ በጣም ከሚያስደስቱኝ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። የፈለገውን ይመርጣል። ተገዶ አያይም አያዳምጥም። ይህ ትልቅ ስኬት ነው። ታዲያ ይህ ስኬት እንዳለ ሆኖ ከላይ ያነሳኋቸውን የኢትዮጵያዊነት መሠረቶች ላይ የቤት ስራችንን መስራት ይገባናል። ለሀገር ውስጥ ፊልም ሰሪዎች ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፣ በሀገር ቤት ውስጥ ቴሌቪዥን ስርጭት መክፈት ሊፈቀድ ይገባል፣ ሃይማኖቶች የቴለቪዥንና የሬዲዮ ፕሮግራሞችን እንዲያቀርቡ መፈቀድ አለበት። ሌሎችንም ጉዳዮች በሰከነ መልኩ ቁጨ ብለን ስርዓት የምናስይዝበት ወቅት ነው።n    

 

በጥበቡ በለጠ

ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም ታሪክ ውስጥ እጅግ የተለየች ዕለት ነች። ምክንያቱም አንድ ንጉሥ በጠላት ወታደሮች ሐገሩ ተወርራ፣ የሚያደርገው ቢያጣ ከሐገሩ ውጭ በባዕድ ሀገር ተሰድዶ፣ በመጨረሻም ከአምስት ዓመታት በኋላ በውጭም በውስጥም ድል አድርጎ ወደ ሐገሩ በመምጣት፣ የጠላቶቹን ባንዲራ አውርዶ፣ የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ የሰቀለ፣ ከዚያም ለሐገሩ ሕዝብ ንግግር ያደረገባት ዕለት ፈፅሞ የተለየች ነች።

ኢጣሊያ በ1888 ዓ.ም አድዋ ላይ በግማሽ ቀን ጦርነት የውርደት ማቅ መከናነቧ ሲቆጫት ሲያንገበግባት ኖሯል። እናም ከ40 ዓመታት በኋላ በ1929 ዓ.ም ቂሟን ለመወጣት ኢትዮጵያን ወረረች። ኢትዮጵያ ደግሞ ገና የሽግግር ወቅት ላይ የነበረች በመሆኑ የተደራጀ መንግሥት እና ጦር አልነበራትም። ፋሽስት ኢጣሊያ ደግሞ አሉ የተባሉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን መርዝ ከሚተፉ አውሮፕላኖች ጋር ይዛ ኢትዮጵያን ወረረች።

ወረራው የተደራጀ ስለነበር በቀላሉ ሊቀለበስ አልቻለም። ስለዚህ ንጉሠ ነገስቱ እዚሁ ሆነው የከፉ ነገር ከሚመጣ ወደ ውጭ ወጥተው መታገልን የዘመኑ ሹማምንቶች እንደ አማራጭ መከሩ። እናም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከመንበረ ስልጣናቸው ተነስተው ኢትዮጵያን ለቅቀው ወደ እንግሊዝ ተሰደዱ። ሀገር አልባ ሆኑ።

ኢጣሊያም የኢትዮጵያን መንግሥት ተቆጣጠረች። ሮም በደስታ ተቀጣጠለች። ኢትዮጵያዊያንን ደግሞ ለሁለት ተከፈሉ። አብዛኛው በአርበኝነት ተሰማራ። ቀሪው ደግሞ ለኢጣሊያ ፋሽስቶች ባንዳ ሆነ። አርበኞቹ ፋሽስቶችን ለመፋለም በዱር በገደሉ ተሰማሩ። ጦርነቱ በየፈፋው ይካሄድ ጀመር። ኢጣሊያ በመርዝ ጋዝ አርበኞችን መፍጀት ጀመረች። ሕጻናት፣ ሴቶችና እናቶች አረጋውያን አለቁ። በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ብቻ ከ30 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪ ፋሽስቶች ጨፈጨፉ።

በስደት ያሉት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ደግሞ “ሐገሬን አድኑልኝ” እያሉ ከአለም መንግሥታት ጋር ይሟገታሉ። ሰሚ አጡ። ነገር ግን እንደ ሲልቪያ ፓንክረስት ያሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ከኢትዮጵያው ንጉሥ ጎን ቆሙ። ሲልቪያ ፓንክረስት እንግሊዛዊት ናት። የኢትዮጵያ በፋሽስቶች መወረር ያንገበገባት ሴት ናት። እናም ስራዋን ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጋ በማቆም ከኢትዮጵያው ንጉሥ ጎን በመቆም የኢትዮጵያ አርበኛ ሆነች። New Times and Ethiopian News የተሰኘ ጋዜጣ ማሳተም ጀመረች። ጋዜጣው በየሳምንቱ ለእንግሊዝ ፓርላማ አባላት የሚበተን ነው። ቀሪው ደግሞ ለሌሎች ታላላቅ ሰዎች የሚሰጥ ነው። ጋዜጣው ኢትዮጵያ ውስጥ ፋሽስቶች እየፈፀሙ ስላሉት አሰቃቂ ግፍ የሚገልጽ ነው። እንደ እንግሊዝ ያሉ ታላላቅ መንግሥታት ይህን ግፍ እንዲቃወሙ የሚቀሰቅስ ነው። በመጨረሻም የእንግሊዝ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጎን ቆሞ ፋሽስቶችን እንዲፋለም አደረገች። ሲልቪያ ፓንክረስት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ። በኢትዮጵያ የጨለማ ዘመን ወቅት ብርሃን ሆና ከወደ እንግሊዝ የወጣች ፀሐይ ናት።

እናም ጦርነቱ ተፋፋመ። አርበኞች በየጦር አውድማው ድል በድል መሆን ጀመሩ። የእንግሊዝ ጦርም ከጎናቸው ቆመ። አምስቱ የመከራ አመታት ሊያበቃ ሆነ። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም በሱዳን፣ በኦሜድላ አድርገው ከብዙ ሺ ሰራዊት ጋር ሆነው እየተዋጉ ወደ አዲስ አበባ መጓዝ ጀመሩ። ድል በድል እየሆኑ መጋቢት 28 ቀን 1933 ዓ.ም ደብረማርቆስ ከተማ ደረሱ። በዚህ ዕለት የኢትዮጵያ አርበኞች እና እንግሊዛዊው ጀነራል ካኒግሀም አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። ይሁን እንጂ ድሉ ድል የሚሆነው ንጉሠ ነገስቱ ሲመጡ ነው።

ደብረ ማርቆስ ላይ ለ20 ቀናት ከቆዩ በኋላ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ተደረገ። ተአምራዊ ታሪካዊ ጉዞ ነው። የተሰደደ ንጉሥ፣ ሀገር አልባው ንጉሥ ወደ ዙፋኑ ሊመጣ ነው። ጉዞው ተደርጎ አዲስ አበባ አናት ላይ፣ እንጦጦ አናት ላይ፣ ጃንሆይ ብቅ አሉ።

ጃንሆይ የሰሌዳ ቁጥሯ HA411 በሆነች አውቶሞቢል ጠቆር ያለ ካኪ ዩኒፎርም ለብሰው፣ በደረታቸውና በትከሻቸው ለይ የማርሻል መለዮአቸውን አድርገው፣ በራሳቸው ላይ የቡሽ ባርኔጣ ደፍተው በመኪናዋ ላይ ቆመዋል።

አምስት ዓመት ሙሉ በዱር በገደሉ ሲፋለም የነበረው የአበሻ ጦር የተሰደደውን ንጉሡን ሊቀበል በነቂስ ወጥቷል። በመንገዱ ዳርና ዳር የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጨናንቋል። ሕዝቡ አምስት ዓመት ሙሉ የተለየውን ንጉሥ ለማየት በደስታ ፍካት እልልታውን ያስነካዋል።

የጃንሆይ መኪና ከፊትና ከኋላ ሆነው የሚያጅቡት ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ የእንግሊዝ ጀነራሎችና መኮንኖችም ጭምር ናቸው። ሞተር ሳይክሎች፣ ብስክሌቶች፣ ዩኒፎም ያደረጉ ወታደራዊ ሰልፈኞች፣ አርበኞች. . . ውብ በሆነ ሰልፍ ከፊትና ከኋላ አጅበዋቸዋል። የራስ አበበ አራጋይ 15ሺ ጦር በጀግንነት ወኔ እያቅራራ ሰልፉን ያደምቀዋል። ምድሯ ቀውጢ ሆናለች።

ጃንሆይን ተከትለው የመጡ በርካታ ጋዜጠኞችም ይራወጣሉ። ዶክመንተሪ ፊልም ሰሪዎች ካሜራዎቻቸውን ጠምደዋል።

ጃንሆይን የያዘችው አውቶሞቢል በዚህ ሁሉ አጀብ መሐል ስትጓዝ የሐበሻ ድምፅ ከምን ግዜውም በላይ በእልልታ አስተጋባ። ፀሐዩ ንጉሥ ከነግርማ ሞገሳቸው በፈገግታ እና በደስታ መኪናዋ ላይ ሆነው ሕዝባቸውን ሰላም ይሉታል። ምላሹ ደግሞ እጥፍ ነው። ግማሹ ያለቅሳል።

“ጃንሆይ በጣሊያን ፋሽስቶች ድል ሆነው እጅግ በመረረ ሀዘን ተኮማትረው የለቀቋትን አገራቸውን በለቀቁባትና በአለቀሱባት ቀን ድል አድርገው በደስታ ባህር ተውጠው ጠላታቸውን አስለቅቀው፣ የድል አክሊል ተቀናጅተው በድል አድራጊነት በታላቅ ደስታና ናፍቆት ተሰልፎ በሚጠብቃቸው ሕዝብ መሀል አልፈው ከታላቁ ቤተ-መንግሥታቸው ደረሱ።

የእንግሊዙ የዜና ወኪል የሆነው ጋዜጠኛ ለትየር መቅረፀ ድምፁን ለአቶ ይልማ ደሬሳ ሰጣቸው። እርሳቸውም ሲናገሩ፣ “ኢጣሊያኖች እኛን ለመግደልና ንብረታችንን ለመዝረፍ የዛሬ አምስት አመት ከከተማችን በገቡበት ዕለት በእግዚአብሔር ትክክለኛ ዳኝነትና በእንግሊዞች አጋዥነት ዛሬ ንጉሠ ነገስታችን ተመልሰው ከመናገሻ ከተማቸው ገብተዋል” አሉ።

ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ንጉሠ ነገስት ዘኢትዮጵያ ስዩመ እግዚአብሔር፣ በዚህች የቀኖች ሁሉ ድንቅ ቀን፣ ሚያዚያ 27 ቀን  1933 ዓ.ም የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ሰቀሉ። አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ ቀስተ ደመና ሰማይ ላይ ተውለበለበ። የሀበሾች የነፃነት ቀን ነው አለ። ከዚያም ጃንሆይ፣ “የሰማይ መላዕክት የምድር ሰራዊት” በሚል ርዕሰ የፃፉትን ንግግር ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሰሙ። የንግግሩ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው።

 

 

ኢትዮጵያ ነፃ የወጣች ቀን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ያደረጉት ንግግር

ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም

የሰማይ መላዕክ የምድር ሠራዊት ሊያስቡት እና ሊያውቁት ይቻላቸው ባልነበረ፤ በዚህ በዛሬ ቀን ቸር እግዚአብሔር በመካከላችሁ ለመገኘት ስላበቃኝ በሰው አፍ የሚነገር ምስጋና የሚበቃ አይደለም። ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁ ልነግራችሁ እና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ ያዲስ ታሪክ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው። በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈፀም ያለብን አዲስ ሥራ ይጀመራል።

በኢትዮጵያ ላይ በአለፉት ዘመናት የደረሰባትን መከራ ለማስታወስ ስንፈልግ ከዚህ ጋር የተያያዘውን ታሪኳን ብቻ በአጭር እንናገራለን። ከብዙህ ሺህ ዓመት የበለጠ ነፃነቷን ጠብቃ የምትኖር ኢትዮጵያ ኢጣሊያ ከጥንት ጀምሮ በነበራት አጥቂነት የኢትዮጵያን ነፃነት ለማጥፋት ስለ ተነሣች በ1888 ዓ.ም በአድዋ ላይ ጀግኖችዋ ጦርነት አድርገው ነፃነትዋን አዳነች። በአድዋ ላይ ለተደረገው ጦርነት ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል ብቻ አይደለም። ነገር ግን ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን ለመግዛት ኢጣሊያ የነበራት ያላቋረጠ ምኞት ሲጠብቅ የነበረውን ምክንያት ያገኘ መስሎት ነበር። ኢጣሊያ በአድዋ ድል ከሆነች በኋላ እውነት ለምን ድል አደረገኝ በማለት በኢትዮጵያ ላይ በአፍ ወዳጅ መስላ ስታዘጋጀው የነበረውን ምንም የአውሮጳ ያለፈው ታላቁ ጦርነት ቢያቋርጣት በአለፉት ዘመናት ገልጣለች።

ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የአጥቂነት ጦርነት ባደረገች ጊዜ ምንም እንኳን በጦር መሣሪያ ተወዳዳሪ አለመሆናችንን ብናውቀው በግፍ አገራችንን ለመንጠቅ የመጣብንን ጠላት መከላከል የተገባን ሥራ ስለሆነ በነበረን አቅም ተከላከልን። የዓለም ሕግ በከለከለውም መሣሪያ በጋዝ ጭስ ህዝባችንን የምትጨርስብን ቢሆን ወደ አለም መንግሥታት ለማስማትና ፍርድ ለመቀበል ሔድን። ነገር ግን ኢጣሊያ ያነሣችው ጠብ በአለም ላይ ሁሉ የሚዘረጋ ስለሆነ አለምን አሁን ከደረሰባት ጥፋት ለማዳን ለመንግስት መሪነት የተቀበሉ ሁሉ የሚጣጣሩበት ዘመን ስለነበረ ይህ እሣት እንዳይቃጠል በአለም ስምምነት እንዲገኝ ሲደክሙበት ቆዩ። በዚህ ዘመን የልብ ወዳጃችን የሆነችው ታላቂቱ ብሪታኒያ በመልካም ወዳጅነት ተቀብላን ቆየች። በዚያም ያለ ፍርድና ያለ ርሕራሄ በከንቱ ደማቸው በኢጣሊያ እጅ የሚፈሰውን ያገሬን ሰዎችና በከንቱ የሚቃጠሉትን አድባራትና ቤተ-ክርስትያናት በሰው አገር ተሰደው ባገራቸውም ላይ በዱር በገደልና በጫካ መከራና ስቃይ ያዩ የነበሩትን በአሳብ ሣንለያቸው በሥራ ቆየን። በነዚህ አመታት ውስጥ ኢጣሊያ በጭካኔ የፈጃቻቸው ወጣቶችና ሴቶች ካሕናትና መነኮሳት ስንት ናቸው? በ1929 ዓ.ም የየካቲት ሚካኤል እለት በአዲሰ አበባ ከተማ ብቻ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በሦስት ቀን ውስጥ ማለቃቸውን ታውቃላችሁ። በአካፋ እና በዶማ በቤታቸው ውስጥ እንዳሉ ከሕፃናት ልጆቻቸው ጋራ በእሣት የተቃጠሉት፣ ታስረውም በረሃብ እና በውሃ ጥም ያለቁት ደማቸውና አጥንታቸው አቤቱታውን ሲያቀርብ ቆየ። ይህ እንደዚህ ያለው የአረመኔና የጨካኝነት ሥራ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን የባሰውን በቀሩት በሌሎች በኢትዮጵያ አውራጃዎች ውስጥ ሲሠራ እንደነበረ ማንም የሚያውቀው ነው። ተይዞ ያልተደበደበ ያልተረገጠና ያልተዋረደ ያልታሰረ አይገኝም።

አሁን በፊታችን ወዳለው ወደ አዲሱ ታሪክ እንተላለፋለን። የዛሬ አምስት አመት ልክ በዛሬዩቱ ቀን የፋሽስት ወታደር ከዋናው ከተማችን ገባ። ቀጥሎም ሙሶሊኒ በኛ አገር በኢትዮጵያ ውስጥ የሮማን ኢምፓየር አቁሜያለሁ ብሎ ለአለም አስታወቀ። አቀናሁላችሁ ብሎ ያስታወቀውም አገር ለዘላለም በጁ የሚኖር በመስሎት አምኖ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግንነት በታሪክ የታወቀ ነው። ነገር ግን ለሕዝባችን የሚያስፈልገውን የዘመኑን መሣሪያ የምናገባበት ጠረፍ ባለመኖሩ ምክንያት ለማግኝት ሳይቻለን ቀረ። ሙሶሎኒ በሠራው ሥራ 52 መንግሥታት ፈረዱበት። እርሱ ግን ይሕንን የግፍ ሥራውን ተመካበት። ፍርዳቸውን ከምንም አልቆጠረውም። የአለፉት አምስት አመታት ለእናንተ ለሕዝቦቼ የጨለማ ጊዜያቶች ነበሩ። እናንተ ግን ተስፋ ሳትቆርጡ ጥቂት በጥቂት እየጀመራችሁ በኢትዮጵያ ኮረብቶች ላይ ተሰማራችሁ። በነዚህ አምስት አመታት እናንተ የኢትዮጵያ አርበኞች ማናቸውንም መከራና ጭንቀት ችላችሁ ነፃነታችሁን ስለ ጠበቃችሁ ወደ ተሰማራችሁባቸው ተራሮች ለመምጣት ጠላታችን ከቶ ሊደፍር አልቻለም። ምንም እንኳን አገሩን ለማቅናት ባይቻል የያዘውን አሰለጥናለሁ በማለት ብዙ ሺ ሚሊዮን ሊሬ አፈሰሰ። ይህን ሁሉ ገንዘብ በማውጣቱ የታጠቀውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁኔታ ከፍ ለማድረግና ወይም የሰራውን ግፍ ለማሻሻል አልነበረም። ነገር ግን በቅድስት አገራችን በኢትዮጵያ የፋሽስት ኰሎኒ ለማቆምና እሱ እንዳሰበው የጭካኔ አገዛዝ ለመትከል ነበር። የኢትዮጵያን ዘር ለመጨረስ ተጣጣረ እንጂ ምንም ለአንድ ነፃ መንግሥት ከባድ ቀንበር ሆኖ የሚቆጠር ቢሆን የማንዳ ወይም የኘሮቴክትራ አስተዳደር እንኳ አላሰበላትም።

ነገር ግን ይህ በብዙ ሺ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብና የተዘጋጀው የጦር መሣሪያ ሁሉ ሙሶሊኒ ላሠበው መንገድ መዋሉ ቀርቶ በፍፁም ላላሠበው ጉዳይ ሆነ። ኢጣሊያ ድል ከሆነችው ከፈረንሣይ ላይ የተቻላትን ያህል ለመንጠቅ አስባ ጦርነት ለማድረግ መቁረጧን በገለጠች ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ያጓዘችው ሰው፣ የላከችው ገንዘብና መሣሪያ ከልክ ያለፈ ነበር። የሰበሰበችው ደንበኛ ጦር ቁጥር ከ150 ሺ አያንስም። የተከበብኩ እንደሆነም ብላ የብዙ አመት ስንቅ አከማችታ ነበር። በዚሁ ባዘጋጀችው የጦር መሣሪያ በመተማመን ማንም ሊያሸንፈኝ አይችልም ብላ ስለተመካች የፋሽስት መንግሥት የቶታሊታሪያን አገዛዝ ባገራችን ውስጥ ለመትከል ጀምሮ ነበር። ነገር ግን የፋሽስት መንግሥት ያላሰበው ነገር መጣ። ለዛሬው ዘመን ጦርነት ዋና አስፈላጊ የሆነው የተዋጊነት መንፈስ በናንተ ተገለጠ።

ጀግንነትና ርሕራሔ ያለው የአንድ አገር ሕዝብ ከመሆናችሁ ጋር እርስ በርሳችሁ በመረዳዳታችሁና የጦር ዕቅድ በማወቃችሁ በመሣሪያና በጦር ሠራዊት ከናንተ እጅግ ከፍ ያለውን ጠላት ለማጥፋት በቃችሁ።

ለሰው ልጅ የነፃነት መብት ሲሉ በሌላ ክፍል ይዋጉ የነበሩት የእንግሊዝ ወታደሮች ኢትዮጵያን ለመርዳትና ነፃ ለማውጣት እስኪዘጋጁና እስኪታጠቁ ድረስ ጊዜ አስፈልጓቸው ነበር። የኢትዮጵያ አርበኞች ግን በመላው ኢትዮጵያ መገናኛ መንገዱን እየቆረጣችሁ ጠላታችንን እያስጨነቃችሁ ከየምሽጉ እንዳይወጣ አደረጋችሁት። ምንም እንኳ የተማመነበት ወታደር ቁጥሩ እጅግ ብዙ ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ እሱንና አገዛዙን ከዳር እስከ ዳር እንደ ጠላው በቶሎ ተረድቶ ይህን በመሰለ አገርና ሕዝብ መካከል መኖር የማይቻለው መሆኑ ታወቀው። እንደ ልማዱም የመርዝ ጋዝ ቦምቡን እየጣለ የአረመኔነትና የጭካኔ ሥራውን እየሠራ ውስጡ በመነመነ በላይነት እኖራለሁ ብሎ ለማሰብ የማይቻል ሆነበት። በያለበት ከቦ የያዘው ወታደር ከርሱ የበለጠ ኃይለኛ ባላጋራ መሆኑን ተረዳው። ይህንንም ባላጋራውን ለመግጠም ያቺኑ ተርፉ የነበረችውን ድፍረትና ገንዘቡን ሁሉ አጠፋ። ከዚህ በኃላ በኢትዮጵያ የምጠጋበት ደህና ቦታ አገኝ እንደሆነ በማለት ሞከረ። ነገር ገን አንድም የሚጠጋበት ቦታ አላገኝም።

ጊዜው ሲደርስ የቃል ኪዳን ረዳታችን ታላቁ የእንግሊዝ መንግሥት ጠላታችንን በሚገባ ለመውጋት ተደራጀ። እኔም ይሕን እንዳውቅሁ ወታደሮቼን ይዤ በምዕራብ በኩል ከሚዋሰን እሩቅ ከሆነው አገር ከሱዳን ተነስቼ ወደ ማህል ጐጃም ገባሁ። ጠላታችን በጐጃም መሬት ብርቱ ምሽጐችና ኃይለኞች ወታደሮች' አውሮኘላኖችና መድፎችም የነበሩት የኛንና የጠላታችንን ወታደሮች ቁጥር ስንገምተው የአብላጫው ከፍተኛነት የኛ አንድ የርሱ 20 ይሆን ነበር። ከዚህ በቀር ደግሞ እንደ ፈቃዳችን የምናዝዝበት መድፍና አውሮኘላን አልነበረንም። የእኔ በአርበኞቹ መካከል መገኘት ብቻ ብዙ ሺ ሰው በአንድ ጊዜ ሣበ። የጠላታችንም ፍርሃቱና መጨነቁ በዚያው መጠን እየበዛ ሔደ። ወታደሮቼ እየገሰገሱ የጠላታችንን መገናኛ መንገድ እየቆረጡ ወታደሮቹንም እያባረሩ ከአባይ ወዲያ ማዶ አባርረው ወደ ሸዋ እና ወደ ቤጌምድር ሲከታተሉ ሣሉ የእንግሊዝ ኢምፔሪያል ወታደሮች ማንም ሊተካከለው በማይችል ሁኔታ እየገሠገሡ ዋና ከተማችንን መያዛቸውንና በስተሰሜን በኩል ወደ ደሴ፣ ከበስተ ደቡብ በኩል ወደ ጅማ፣ የመግፋታቸውን ደስ የሚያሰኝ ወሬ ሰማሁ። እንደዚሁም ከሱዳን የዘመቱት ወታደሮች እጅግ በሚያስደንቅ ኃይል የከረንን ምሽግ አፍርሰው የጠላትን ጦር በፍፁም ድል አደረጉት። እኔም ወደ ዋናው ከተማዬ የምገባበት ጊዜ ስለደረሰ ጠላታችንን ለማባረር በየቦታው ተበታትነው የነበሩትን ወታደሮቼን ሰብስቤ ዛሬ በዋናው ከተማዬ ተገኘሁ። ወታደሮቼን እየመራሁ በመንገዴ ላይ የነበረው ጠላት ድል እየሆነ እስከዚህ በመዳረስና የጋራ ጠላታችንን ኃይል በመስበሬ ደስታዬ ሳይቋረጥ ይመነጫል። የፋሽት መንግሥት ጥሎት በሸሸው ቤተ-መንግሥቴ ውስጥ ዛሬ በመካከላችሁ በመገኘቴ ሁሉን ቻይ ለሆነ አምላክ የማቀርብለት የልብ ምስጋና ሊወሰን አይችልም።

ያገሬ ኢትዮጵያ ሕዝብ፡-

ዛሬ ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ እልል እያለች ምስጋናዋን የምታቀርብበት፣ ደስታዋን ለልጆችዋ የምትገልፅበት ቀን ነው። የኢትዮጵያ ልጆች ከባዕድ የመከራ ቀንበርና ከዘላለም ባርነት ነፃ የወጡበት ቀንና እኛም አምስት አመት ሙሉ ተለይተነው ከነበረው ከምንወደውና ከመንናፍቀው ሕዝባችን ጋር ለመቀላቀል የበቃንበት ቀን ስለሆነ ይህ ቀን የተከበረና የተቀደሰ፣ በያመቱም ታላቁ የኢትዮጵያ በአል የሚውልበት ነው። በዚህም ቀን ለሚወለዱት ላገራቸው ነፃነት፣ ለንጉሠ ነገስታቸውና ለሰንደቅ አላማቸው ክብር ከአባቶቻቸው የተላለፈውን ጥብቅ አደራ አናስወስድም በማለት መስዋዕት ሆነው ደማቸውን ያፈሠሡትን፣ አጥነታቸውን የከሰከሡትን ጀግኖቻችንን እናስታውሣለን። ለነዚህም ጀግኖቻችን የኢትዮጵያ ታሪክ ምስክር ይሆናል።

ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ በዝርዝር ተነግረውና ተቆጥረው የማያለቁ ያገኘናቸው መከራና ሥቃይ ትምሕርት ሆነውና ሠራተኛነት፣ አንድነት፣ ሕብረትና ፍቅር በልባችሁ ተፅፈው ለምናስበው ለኢትዮጵያ ጉዳይ ረዳቶች ለመሆን ዋና ትምሕርት የሚሰጣችሁ ነው። ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ከእንግዲህ ወዲያ የማትነጣጠሉ በሕግ ፊት ትክክለኛነትና ነፃነት ያላችሁ ሕዝቦች እንድትሆኑ እንፈልጋለን።

አገር የሚለማበትን' ሕዝብ የሚበለፅግበትን' እርሻ' ንግድ' ትምሕርትና ጥበብ የሚሰፉበትን፣ የሕዝባችን ሕይወቱና ሀብቱ የሚጠበቅበትን፣ ያገር አስተዳደርም ባዲሱ ሥልጣኔ ተለውጦ ፍፁም የሚሆንበትን ይህን ለመሰለው ለምንደክምበት ሥራ አብሮ ደካሚ መሆን አለባችሁ።

ይህንን እግዚአብሔር በቸርነቱ የሠራልንን ሥራ መጀመሪያ የቃል ኪዳን ረዳታችን የእንግሊዝ መንግሥት ያረገልንን ውለታ ለመመለስ ኢምፔሪያል ትሩኘ የተባሉት ወታደሮች ወደ ሌላ የጦር ግንባር ተዛውረው የጋራ ጠላታችንን ለማጥቃት እንዲችሉ ማድረግና፣ በጦር ሠራዊትም አንድናግዝ የሚያስፈልግ ሆኖ ሲገኝ በመርዳት፣ ሁለተኛም በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ሐይማኖትን የሚያስከብርና የሚጠብቅ መንግሥት በማቋቋም የሕዝብንና የሕሊናን ነፃነት በመፍቀድ ለሕዝብና ለሐገር የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ብርቱ ምኞታችንና አሣባችን ነው።

አሁን በመጨረሻው ለናንተ ለሕዝቤ የማስታውቃችሁ ዛሬ የሁላችን የደስታ ቀን መሆኑን ነው። ዛሬ ጠላታችንን ድል የመታንበት ቀን ነው። ስለዚህ በሙሉ ልባችን ሁላችን ደስ ይበለን ስንል ደስታችን በክርስቶስ መንፈስ እንጂ በሌላ አይሁን። ለክፉ ክፉ አትመልሱ። ጠላት እንደወትሮው ልማድ እስከዚህ መጨረሻ ሰዓት ድረስ ሰራው ያለ የጭካኔና የግፍ ሥራ አትሥሩ። ተጠንቀቁ። ጠላቶቻችን በእጃቸው ያለውን መሣሪያ እንዲያስረክቡና በመጡበት መንገድ ተመልሰው እንዲሔዱ እናደርጋለን። ደራጐንን የገደለ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የእኛም የባለ ቃል ኪዳን ረዳቶቻችንም የጦር ሠራዊት ባልደረባ ነውና ይህን አዲስ የተነሣውን የሰውን ልጆች የሚያስጨንቀውን እግዚአብሔርን የማያምን ጨካኝ ዘንዶ ለመቃወም እንድንችል ለዘላለም ፀንቶ በሚኖር ወዳጅነትና ዝምድና ከባለ ቃል ኪዳን ረዳቶቻችን ጋራ እንተሳሰር። እነርሡንም እንደ ዘመድና ወዳጅ ተመልክታችሁ ደግነት እና ቸርነት እንድታሳዩዋቸው አደራ እላቸኋለሁ።

                  

                  ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ

                   ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ

                   ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም

                          አዲስ አበባ

በጥበቡ በለጠ

 

የዛሬ ሃምሳ ዓመት በጃማይካዊያን ዘንድ እጅግ ልዩ ወቅት ነበረች። ምክንያቱም እንደ አምላካቸው የሚያዪዋቸውና የሚቆጥሯቸውን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በዓይናቸው ያዩበት ዓመት ነው። ኪንግስተን ጀማይካ ውስጥ የራስታዎች መሲህ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገስት ዘኢትዮጵያ ከሰማይ ወደ ምድር በአውሮፕላን ወረዱ። ምድር ቀውጢ ሆነች።

እ.ኤ.አ ሚያዚያ 21 ቀን 1966 ዓ.ም የራስ ተፈሪያዊያን ዓመት ተብሎ ይጠራል። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን በአይናቸው ያዩበት፣ እኚሁ ንጉስ ጀማይካን ከረገጡ በኋላ ሀገሪቱ እና ሕዝቦቿ ተባርከዋል ብለው ያመኑበት ወቅት ነው። በዓለም ላይ ያሉ የራስ ተፈሪያዊያን ተከታዮች አብዛኛዎቹ መሲሃቸውን ለማየት ኪንግስተን ከተሙ። ታላላቅ ስም እና ዝና ያላቸው ሰዎችም ቀደም ብለው ኪንግስተን ገብተዋል። ግዙፎቹ የዓለማችን ሚዲያዎች ኪንግስተንን አጨናንቀዋል። ሰማዩ የራስታዎችን መሲህ ሊያመጣ ሲል ድንገት ዳመና ወረረው። ለበርካታ ዓመታት የዝናብ ቆሌ የራቀው ኪንግስተን እርጥብ ዝናብ ማውረድ ጀመረ። አየሩ ጀማይካ ላይ ተቀየረ። እውነትም መሲሁ መጣ ብለው የበለጠ አመኑ።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ኪንግስተን ላይ ከምትታየው ቀስተ ደመና ጋር ተመሳሰለ። የሀገሬ ሰው የማርያም መቀነት የሚለው ቀስተ ደመና የኢትዮጵያም ሰንደቅ አላማ ነበር። ይህ ሰንደቅ አላማ ኪንግስተን ላይ በየቦታው ይውለበለባል። ራስታዎች ደግሞ የጭንቅላታቸው ቆብ፣ ልብሳቸውና መላ ተፈጥሮአቸውን ከዚህ ሰንደቅ አላማ ጋር የማያያዝ ልማድ አላቸው። እናም የካሪቢያኗ ሀገር ጀማይካ በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ተሽሞንሙናለች። ሰማዩ ላይ እንደ እርጉዝ ምጥ አለ። ከዚያ ሰማይ ላይ የሚወርደው አውሮፕላን ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ይዟል። ለራስታዎች የእምነታቸው መስተዋት። የችግርና የመከራቸው መግፈፊያ መሲህ ናቸው። እናም በአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ እና በሞአ አንበሳ የተሽሞነሞነው ግዙፉ የኢትዮጵያ አውሮፕላን የኪንግስተንን አየር ሞላው።

የዚያን ጊዜ ፓሊሳዶስ አውሮፕላን ማረፊያ /Palisadoes Airport/ የሚባለውና አሁን ደግሞ Manley International Airport ላይ እጅግ በርካታ ሕዝብ ሰማዩን አንጋጦ ሲያይ ሽንጠ ረጅሙ አውሮፕላን እየተምዘገዘገ መጥቶ ከሠፊው መስክ ላይ አረፈ። ከዚያ በኋላ ፖሊስ የለ፤ ፀጥታ አስከባሪ የለ፤ ሁሉም ወደ አውሮፕላኑ ሮጠ። የመጣው ጉዳይ መሲሃቸው ነውና። ምድሯ ራደች።

የአውሮፕላኑ መሠላል መጥቶ ከተገጠመ በኋላ ጃንሆይ ከውስጥ ብቅ ሲሉ ኪንግስተን ጦዘች። የራስታዎች ደስታ የሚገለፀው በሙዚቃ ነውና ሬጌው በየቦታው ይቀልጥ ጀመር።

ይህ ሳምንት ልዩ በመሆኑ በጥቂቱ እናወጋበታለን። የራስታዎችና የኢትዮጵያ ቁርኝት በእጅጉ የጠበቀበት ወቅት በመሆኑ ትኩረት ልሰጥበት ወደድኩ።

ለመሆኑ ጃማይካዊያንና ኢትዮጵያን ምን እንዲህ አስተሳሰራቸው። በጃንሆይ እስከ ማምለክስ ድረስ ምን አመጣቸው?

በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ያደረጉት አደፍርስ አየለ የተባሉ ፀሐፊ በአንድ ወቅት እንደገለፁት፣ ባለፈው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ፣ በአሜሪካ አህጉር የሚገኙ ጥቁሮች በነጭ ገዢዎቻቸው የሚደርስባቸውን ጭቆና በማጤንና የጥቁሩን ሕዝብ የከረረ የነፃነት ትግል በመገንዘብ ወደ አገራቸው ወደ ኢትዮጵያ፣ ወደ አሕጉራቸው ወደ አፍሪካ ይመለሱ ዘንድ ጥሪ እንዳስተላለፉ የራስታ ንቅናቄ አባላት ይጠቅሳሉ ይላሉ ፀሐፊው። አክለውም፤ ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኢትዮጵያዊነት፣ በኢትዮጵያ አምላክ፣ በኢትዮጵያ የተባበሩት የአፍሪካ መንግሥታት ማዕከልነት የሚያምኑት ራስታዎች ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ለእናት አገራችን እንሞታለን በሚል አቋም ለዘመቻው ዝግጁ እንደነበሩ ይገለፃል።

“አንዲት ኢትዮጵያ፣ አንድ አምላክ፣ አንድ አላማ፣ አንድ እድል” የሚል ዕምነት ያላቸው ራስታዎች የምኒልክ ክለብ የተባለ እንቅስቃሴ እ.ኤ.አ. በ1937 ዓ.ም የጀመሩትም የሰይጣን እና የጭቆና ኃይላት የሆኑት የ“ባቢሎን” መሪዎች (በፋሽዝም መልክ) ኢትዮጵያን መውረራቸው ስላስቆጣቸው መሆኑንም አጥኚው አቶ አደፍርስ ይገልፃሉ።

አጤ ምኒልክ ቀደም ሲል በአውሮፓና በመካከለኛው ምስራቅ ባርያ ፈንጋዮች ወደ አዲሱ ዓለም (አሜሪካ) የሸጡዋቸው ጥቁሮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ያቀረቡት ጥሪ በራስ ተፈሪያውያን ማኅበረሰብ እምነት ማርክስ ጋርቪይን በመሳሰሉ የጥቁሮች መሪ ውስጥ አዲስ እምነት ፈጠረ። ራስ ተፈሪ ሠው ነኝ ቢሉም አምላክ ናቸው የሚል ፍልስፍና የተሠራጨው እርሳቸው በ1923 ዓ.ም እንደነገሡ ሰሞን ነው።

ራስታዎች በኢትዮጵያ ጥንታዊነትና የቀደምት የሰው ልጅ መነሻነትዋ፣ በሥልጣኔ መሠረታዊ ቤት መሆንዋ፣ በኢትዮጵያ ታላቅነት፣ አንድነትና ገናናነት ታላቅ እምነት አላቸው። “ኢትዮጵያ አትበጣጠስም፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም። ጥቁር ሁሉ ኢትዮጵያዊ መሆን አለበት፤ ኢትዮጵያ እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠን ጽዮን ናት እንደሚሉ የአጥኚው ጽሁፍ ያስረዳል።

የራስ ተፈሪያዊያን እምነት ያስፋፋው ማርክስ ጋርቬይ ነው። ጋርቬይ የተወለደው እ.ኤ.አ ነሐሴ 7 ቀን 1887 ዓ.ም ሲሆን፤ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በሳል እየሆነ መጣ። ምክንያቱ ደግሞ አባቱ መፃህፍት አንባቢ እና ተመራማሪ በመሆኑ የአባቱን ፈለግ እየተከተለ ገና በልጅነቱ አያሌ መፃህፍትን አነበበ። በዚህም ጊዜ በዓለም ላይ ያለውን ፍትሐዊነት፣ እኩልነት እና ታሪክን ሁሉ ማወቅ ጀመረ። በወቅቱ ደግሞ ጥቁር የሆኑ ሕዝቦች እንደ ሰው ልጅ ፍጡር አይታዩም ነበር። እጅግ ተጨቁነው በባርነት ሰንሰለት ተሳስረው መከራ የሚያዩበት ወቅት ነበር። በንባብና በትምህርት እየዳበረ የመጣው ማርክስ ጋርቬይ ይህን አስከፊ ሕይወት ለመቀየር ተነሣ።

ከ1912 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተዘዋወረ ጥቁሮችን ማደራጀት እና ለእኩልነታቸውም እንዲታገሉ መቀስቀስ ጀመረ። የቅስቀሳውንም መጠሪያ እየቀያየረ እና ማደራጀት በሚያስችለው መንገድ ሁሉ ይሰይም ነበር። ለምሳሌ Black nationalism (ጥቁር ብሔርተኛ) ወይም Pan Africanism (የአፍሪካ ጥምረት፣ ታላቅነት) እያለ ይጠራ ነበር።

ታዲያ ለነፃነትም ምሳሌ ያስፈልጋልና የነፃነት ተምሳሌት ሆና በወቅቱ ለነበሩ ጥቁሮች የምትቀርበው ኢትዮጵያ ነበረች። ጥቁር ሁሉ በባርነት ስር በወደቀበት ወቅት ለትግል ማነሳሻ ታገለግል የነበረችው ኢትዮጵያ መሆኗ በታሪክ ተፅፎ ይገኛል። በተለይ ደግሞ አድዋ ላይ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በቅኝ ገዢዎች ላይ ያሳረፉት በትር ጭቆናን እና ባርነትን አሽቀንጥሮ መጣያ ምሳሌ ተደርጐ በጥቁሮች አንደበት ተደጋግሞ ተነሣ። በነገራችን ላይ በዚያን ወቅት ጀማይካዊያን ቅኝ ገዢዎችን “ሰይጣን” ናቸው በማለት ይጠሯቸው ነበር። ሰይጣን ማለት ኮሎኒያሊስቶች ናቸው የሚል ጽኑ እምነት ነበራቸው። በአፄ ምኒሊክ የሚመራው ጦር ታቦታትን ይዞ አድዋ ላይ ከትሞ፣ ፀሎት አድርጐ፣ ወደ ጦርነት ገብቶ፣ በግማሽ ቀን ውስጥ የኢጣሊያን ሠራዊት ድምጥማጡን አጠፋ። ሰይጣን ተሸነፈ ተብሎ በአሜሪካ ባሉ ጥቁሮች በተለይ በጀማይካዎች ዘንድ ታመነ። ያሸነፈው ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር ነው። እነማርክስ ጋርቬይ በኢትዮጵያ ላይ ማመን ማምለክን መቀስቀሻ መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር። የአድዋ ድል የእምነት መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያም የመላው ጥቁር ሕዝቦች የትኩረት አቅጣጫ ሆነች።

እንዲህ ምሳሌ ሆና ታገለግል የነበረችው ኢትዮጵያ ተመልሳ በኢጣሊያኖች ወረራ ሥር በ1928 ዓ.ም ወደቀች። የፋሽስት ኢጣሊያ ሠራዊት ኢትዮጵያን ተቆጣጠረ። ንጉሡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከስልጣናቸው ተነስተው ተሰደዱ። አገር አልባ ሆኑ።

አርበኞች ቅኝ ገዢዎችን (በጀማይካዊያን አጠራር ሰይጣኖችን) ለመፋለም በዱር በገደሉ ገቡ። ጥቁሮች ሁሉ ተስፋ ያደረጉባት የነፃነት ምድሪቱ ኢትዮጵያ ደግሞ ስትወረር የሞራል መነካት አስከትሎባቸው ነበር። መሲሁ ከምስራቅ በኩል ከኢትዮጵያ ይመጣል እያሉ እምነትን ማቀንቀን የጀመሩት ራስ ተፈሪያዊያን ግራ የተጋቡበትም ዘመን ነበር። ግን በአምስት ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ አርበኞች በተስፋፊዎችና በቅኝ ገዢዎች ላይ ድልን ተጐናፅፈው ነፃነታቸውን መልሰው ሲቀበሉ የጥቁሮቹ የእምነት እና የነፃነት ትግል በከፍተኛ ደረጃ ተነቃነቀ።

ሊግ ኦፍ ኔሽን ላይ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግርም “ነብይ” አሰኛቸው። የራስ ተፈሪያዊያን እምነት እየጐለበተ መጣ። ማርክስ ጋርቬይ የጥቁር ሕዝቦችን አንድነትና ለነፃነታቸው የሚደረገውን ትግል በመምራት በእጅጉ የታወቀ ሰው ነው። Negro Improvement Association and Pan African Communities League ወይም የጥቁሮች ብልፅግና ማኅበርና የአፍሪካ ማኅበረሰብ የጥምረት ሊግ እያሉ ትግሉን አፋፋሙት። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም በዓለም አደባባይ ከነ ግርማ ሞገሳቸው ገዝፈው ብቅ አሉ። ዝናቸው ናኘ። ጥቁር ሕዝብን ሁሉ መሰብሰብ ጀመሩ። የአፍሪካን አንድነት ለመመስረት ተነስተው መሠረቱት። ጀማይካውያን ቀደም ሲል መሲሁ ጥቁርን ይሰበስባል የሚል እምነትም ያቀነቅኑ ስለበር ውስጣቸው ያለው ነገር ሁሉ እውነት ሆነላቸው። ስለዚህም በጃንሆይ ማመን ለራስ ተፈሪያውያን ዋነኛው ማጠንጠኛ ሆኖ አረፈው።

 

የራስታዎች እምነት

ራስታዎች በእምነታቸው ጽኑ ናቸው። እንዴት በሰው ታምናላችሁ ሲባሉ አይቀበሉም። ኃይለሥላሴ ሰው አይደሉም መሲህ ናቸው የሚል እምነት አላቸው። መሞታቸውንም አይቀበሉም። በአንድ ወቅት ራሳቸውን ንጉሥ ኃይለሥላሴን የዓለም ጋዜጠኞች ስለዚሁ ጉዳይ ጠይቀዋቸው እኔ መሲህ ሳልሆን ሰው ነኝ ብለዋል። ጀማይካዎቹ ደግሞ አመኑባቸው። ምን ይደረግ እምነት የራስ ነውና እንጠብቅላቸዋለን። በአጠቃላይ ግን በአንድ ወቅት የራስታዎች እምነት ተብሎ የተፃፈ ጽሁፍ አግኝቼ በማስታወሻ ደብተሬ ላይ ለጥፌው ይገኛል። እናም እምነቱ 11 ነጥቦችን ይዘረዝራል። እነሡም፡-

1.  ራስታዎች እርስ በርሳቸው ሲወያዩና በቡድን ሲነጋገሩ ይውላሉ። ወንድማማች ይባባላሉ። አለዚያ ግን ማዕከላዊ የሆነ መዋቅራዊ፣ ድርጅታዊ ወይም ሕግጋት፣ ነባቤ አእምሮ የላቸውም። አባላቱ ሊከተለቸው የሚገባ የሃይማኖት ሥርዓቶች የሉአቸውም።

2.  መዋቅር የሌለው የዚህ ሃይማኖት መገለጫ የሚሆነው ሕያው የሆነ አምላክ በእያንዳንዱ ሠው ውስጥ መስረፅ ነው። እያንዳንዱም ሠው በቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚገናኝ ይገልጣል። የእያንዳንዱ ሠው አካል መከበር የሚገባው ስለሆነ ቤተክርስትያን ወይም ሌላ የአምልኮ ስፍራ አስፈላጊ አይደለም ይላሉ። እያንዳንዱ ሠው በውስጡ አምላክ ስላለው ክፉውንና በጐውን ሊወስን እንደሚችል ይገልፃል።

3.  የራስ ተፈሪያውያን እምነቶች ማዕከላዊ ነጥቦች ሁለት ናቸው። አንደኛው ራስ ተፈሪ (ቀ.ኃ.ሥ) ሕያው አምላክ መሆናቸው ሲሆን፣ ይህም በብዙ መፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅስ የተደገፈ ነው ይላሉ። ይህ ደግሞ እግዚአብሔር ጥቁር ለመሆኑ በማስረጃነት ይቀርባል። የአምላክ ጥቁር መሆን ለራስ ተፈሪያውያን ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው። ጥቁረቱ ከቅድስና ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ይቀርባል። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የእንቅስቃሴው ማዕከልነት የመጽሐፍ ቅዱስን ድጋፍ ያገኘ እና የተረጋገጠ መሆኑን ያምናሉ። በተለይም የንጉሡ ጥቁርና ኢትዮጵያዊ መሆን እምነታቸውን የበለጠ ያጠነክረዋል። መጽሐፍ ቅዱስም አምላካቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚወለድ ያረጋግጣል ብለው ያምናሉ።

4.  ጥቁር ሕዝብ በኢትዮጵያ እንደሚሰበሰብና ጥቁር ሕዝብ በሙሉ ኢትዮጵያዊ ነው ብለው ያምናሉ። ጥቁር ሕዝብ በሙሉ በተባበሩት የተባበሩት የአፍሪካ መንግሥታትን በኢትዮጵያ ማዕከልነት ማቋቋም እንዳለበትም መታገል አለብን ይላሉ።

5.  “እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እውነተኛይቱ የአፍሪካ ጽዮን አድርጐ መርጧታል። የጥንታዊ የሠው ዘር መፍለቂያ የዓለም ሥልጣኔ መነሻ ናት።”

6.  በራስታዎች እምነት መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተፃፈው በአማርኛ ቋንቋ በድንጋይ ላይ ነው። አውሮፓውያን አማርኛን አስተካክለው ስለማያውቁ ትርጉሙን ማበላሸታቸውንም ይገልጣሉ።

7.  የምዕራብን ሥልጣኔ “ባቢሎን” ይሉታል። የጭቆና ምንጭ፣ የባርነት መንስኤ ነው ይላሉ። በሌላ አገላለፅም ባቢሎን ማለት ጨቋኝ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት፣ መንግሥትና የጥቁሩ ሕዝብ መጨቆኛ መሣሪያ ሁሉ ማለት ነው።

8.  መጽሐፍ ቅዱስን እያነበቡ ለማስረዳት የሚሞክሩት ኢትዮጵያ የጥቁሮች ገነት መሆንዋን ነው። እግዚአብሔር ሕያው እንደመሆኑ ሁሉ፣ በሰዎች ውስጥ ማደሩን ይገልጣሉ። እውነተኛይቱም ገነት በምድር ላይ እንደምትገኝ ያብራራሉ።

9.  ስለ ሞት ያላቸው እምነት ደግሞ ለየት ያለ ነው። ሰዎች ከሞቱ በኋላ እንደገና ይወለዳሉ የሚል ቀጥታ አገላለጥ ባይኖራቸውም በብዙ ትውልድ ዘመን በልዩ ልዩ ቅርፅ እንደገና እንደሚከሰቱ ያምናሉ። ስለዚህ ሙሴ፣ ሰለሞን፣ ዮሐንስ መጥምቁ…. አንድ ሰው ናቸው፤ እነሡም ጥቁሮች ናቸው ብለው ያምናሉ።

10.በራስታ እምነት ወንድ በሴት ላይ የበላይነት አለው። ሴቶች ወንዶችን ወደ ፈተና የማያገቡዋቸው ናቸው የሚል አሉታዊ አመለካከት አላቸው። ይሁንና ሴት የባልዋ ብቻ ንግስት ናትም ይላሉ። የወሊድ ቁጥጥር የመጽሐፍ ቅዱስን ፍልስፍና እንደሚቃረን፣ የእስራኤልን ዘር አበዛዋለሁ የሚለውን መለኮታዊ ቃል እንደሚፃረር ይገልጣሉ።

11.ራስታዎች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማና የፓን አፍሪካኒዝም ምልክት የሆነ ቀለም ያደመቀው ልብስ፣ መልበስን እንደ ፍልስፍናቸው ማብራሪያ ይቆጥሩታል።

በአጠቃላይ ሲታይ ራስታዎች ከኢትዮጵያ ጋር እጅግ የጠበቀ ቁርኝት አላቸው። የኢትዮጵያ አፈር የተባረከ ነው ይላሉ። ምድሪቱ ፀጋ ናት የሚሉ አሉ።

ሰሞኑን የጀማይካዊ ኪንግስተን ከተማ የሃምሳ አመት ታሪክ በደማቅ ሁኔታ አክብራለች። ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ኪንግስተን የረገጡበትን ቀን። አያሌ ዶክመንተሪ ፊለሞች ይህንኑ ቀን መሠረት አድርገው ተሠርተዋል። በርካታ መፃህፍት ታትመዋል። ሙዚቃዎች ተቀንቅነዋል።

ከሰሞኑ በተከበረው ሃምሳኛ ዓመት ላይ የንጉሥ ኃይለሥላሴ የልጅ ልጅ የሆኑት ልዑል ኤርሚያስ ሣህለሥላሴ በከብር እንግድነት ተገኝተው ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ተሰጥቶታል።n  

 

በጥበቡ በለጠ

 

ይህ ከላይ የምትመለከቱት ፎቶ የጥላሁን ገሠሠ እና የኔ ነው። ፎቶው እኔ ስዘፍን ጥላሁን ገሠሠ የሚያዳምጠኝ ይመስላል። አስቡት፤ እኔ ዘፋኝ ሆኜ ጥሌ ሲያዳምጠኝ፤ ብቻ ይህን ፎቶግራፍ የተነሣነው ታህሳስ 4 ቀን 1995 ዓ.ም ነው። ቦታው መሿለኪያ በሚገኘው በጥላሁን ገሠሠ የነዳጅ ማደያ ጣቢያ ውስጥ ባለችው በግሉ ቢሮ ውሰጥ ነው። 13 አመታት። ጊዜው ይነጉዳል። ጥሌ እራሱ ከተለየን ሰባት አመታት ተቆጠሩ። ልክ የዛሬ ሰባት አመት የኢትዮጵያው የሙዚቃ ንጉሥ ዜና እረፍቱ ተሰማ!

 

የዛሬ ሰባት አመት እሁድ ምሽት በትንሳኤ ቀን አርፎ፣ ሰኞ ማለዳ ላይ ሚያዚያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም ጥላሁን ገሠሠ ሞተ ሲባል ማን ይመን? ይሔን ወሬ እንዴት ማመን ይቻላል? ምክንያቱም ከሃምሣ ስድስት አመታት በላይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ እጅግ እየተወደደ የኖረ ጽምፀ መረዋ፣ ሐገር ወዳድ፣ በአቋሙ የሚፀና ምርጥ ከያኒ እንደዋዛ ተለየን ብለን እንዴት እንመን? ግን ዜናው መራር እውነት ነበር።

 

አንድ ከያኒ በሕዝብ ልብ ውስጥ ለዘላለም ከሚኖርባቸው ምክንያቶች መካከል ለሐገሩ፣ ለወገኑ ያለው ፍቅር እና ይሔንንም ፍቅሩን የሚገልፅበትም መንገድ ነው። ከዚህ አንፃር ደግሞ ጥላሁን ገሠሠ የሐገር ፍቅር ሞዴል ነው። የጥላሁን መገለጫ ኢትዮጵያ ናት። ገና ከጥንት ከጥዋቱ ያቀነቀናት ዘፈኑ ዛሬም ሕያው ናት፡-

 

ጥላ ከለላዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ

ኩራት ይሰማኛል ካንቺ መፈጠሬ

 

 እያለ የዛሬ 50 አመታት ዘፍኗል። የዘፈኗ ግጥም ደራሲ ኢዮኤል ዮሐንስ ነበሩ።

ጥላሁን የኢትዮጵያን ፍቅር ሲያዜም የፍቅሮች ሁሉ ታላቅ ፍቅር ሆኖ ኃይል አለው። እሱ ራሱ ኢትዮጵያን ሲጠራ ዐይኖቹ በአራቱም ማዕዘን ዕንባውን መቆጣጠር ይሣናቸዋል።

 

ትዝታው ገንፍሎ ዕንባዬ እያነቀኝ

የሀገሬ ሽታ ጠረኑ ናፈቀኝ

 

እያለ እያለቀሰ ይዘፍናል። እኛንም ያስለቅሰናል።

ጥላሁን ኢትዮጵያ የምትባልን ሐገር 56 አመታት ሙሉ በዜጐቿ ልብ ውስጥ ሲገነባ የኖረ ከያኒ ነው። ለምሳሌ ሐገሬ ኢትዮጵያ በሚለው ዘፈኑ ሌላ የፍቅር ዕንባውን እያነባ ነበር የሚዘፍነው፡-

 

ሐገሬ--ኢትዮጵያ--ለምለሟ አበባዬ

ሳይሽ እርግፍ እርግፍ ይላል ዕንባዬ

 

 እያለ አልቅሶ ያስለቅሰናል።

ጥላሁን ኢትዮጵያን የፍቅር ወጥመድ፣ የፍቅር መገለጫ፣ ተምሣሌት፣ አድርጐ በድምጹ፣ በፊቱ፣ በተክለሰውነቱ፣ በሁለመናው ይገልፃታል። ኢትዮጵያ የፍቅር ቁንጮ ሆና ብቅ ትላለች።

 

ክብሬ እናቴ ሐገሬ የእኔ መመኪያዬ፣

አንቺው ነሽ ኢትዮጵያ መከታ ጋሻዬ።

 

እያለ ሲያዜም አብሮት የማያነባ የለም። የዚህችን አገር ዜጐች በሐገራቸው ፍቅር እያስተሣሠረ፣ በጥበብ እያጣመረ፣ ኢትዮጵያን ያኖረ ታላቅ ከያኒ ነው። ሰው ለሀገሩ ኢትዮጵያ ራሱንም ማንነቱንም እንዲሰጥ የማድረግ አንዳች ኃይል ያላቸውን ዜማዎች እንዲህ እያለ ያንቆረቁራል፡-

 

“ጥቃትሽን ከማይ በሕይወቴ ቆሜ፣

ስለ ክብርሽ እኔ ልሙት ይፍሰስ ደሜ።”

 

ሐገር ማለት መስዋዕትነት የሚከፍሉላት ረቂቅም ግዑዝም ሆና የምትቀርብ ናት። ሰዎች ቢመጡም ቢሔዱ የጥላሁን ሐገር/ኢትዮጵያ/ ሁሌም እንደምትኖር፣ ገና… ገና ብዙ ዘመናት ታሪኳ፣ ገድሏ እንደሚዘከርላት ጥላሁን ያዜማል።

 

“ታሪክሽ ተወርቶ ባያልቅም ባጭሩ፣

በሕይወት ያሉት ሊቆች ይመሰክራሉ።

ጥንት ያለፉትንም በጀግንነታቸው፣

ታሪክ አይረሳውም ይነሣል ስማቸው።

 

ምን አይነት ግጥም፣ ምን አይነት ዜማ፣ ምን አይነት ድምፅ፣ ምን አይነት አቀራረብ እንደሆነ መግለፅ ያቅተኛል። ገጣሚው፣ ዜማ አውጭውና ድምፃዊው ፍፁም የተዋሃዱበት ልዩ ሙዚቃ። ኢትዮጵያ እየረቀቀች እየገዘፈች ወደ ላይ የምትወጣበትና ያረገች እስኪመስለን ድረስ ጥላሁን በእንባው እየታጠበ ይመሠክርላታል።

ጥላሁን ገሠሠ ለዚህች ኢትዮጵያ ብለን ለምንጠራት ታሪካዊት ሐገር እና የጀግኖች ደብር ለሆነች ምድር “አጥንቴም ይከስከስ” እያለ ሲያዜም ሁሌም ሰው አብሮት ያዜም ነበር።

 

አጥንቴም ይከስከስ ደሜም ይፍሰስላት

ይህቺን አገሬን ጭራሽ አይደፍራትም ጠላት

 

እያለ በታላቅ ወኔ፣ በታላቅ ግርማ ሞገስ ብቅ ሲል ምድር ቀውጪ ትሆን ነበር።

 

ጥንት አባቶቻችን ዛሬም ልጆቻቸው

ጀግንነት ወርሰናል ከደም ከአጥንታቸው።

ስለዚህ አንፈራም ግዴለንም እኛ

ቆርጠን ተነስተናል እኔን ትተን ለእኛ

 

ይህን የጥላሁን ገሠሠ አስገምጋሚ የሐገር ፍቅር ወኔ የሚሰማው ሴት ወንዱ፣ ሕፃን አዋቂው ሁሉ ሌላ የከፍታ መንፈስ ውስጥ ገብቶ ሲዋኝ ዛሬም በአይነ ሕሊናዬ ይመጣል።

 

የሐገሬ ጀግኖች ሴት ወንዱ ታጠቁ

ከእንግዲህ ለጠላት አንተኛም ንቁ።

ጀግንነት እንደ ሆነ የአባቶቻችን ነው

ህብረታችን ፀንቷል ድል መምታት የኛ ነው።

 

የጥላሁን ገሠሠ እና የኢትዮጵያ ፍቅር የተገማመደ፣ የተሣሠረ፣ የተቆላለፈ ግን ደግሞ የጠነከረ አለት ነው። በምንም አይተካም።

አንድ ግዜ 1993 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ ኢትዮጵ በተሰኘ ታዋቂ መጽሔት ላይ ቃለ-መጠይቅ ተደርጐለት ነበር። ጋዜጠኛው አንድ አስደንጋጭ ጥያቄ ለጥላሁን አቀረበለት። እንዲህም አለው፡-

 

ኢትዮጵ፡- አንድ ነገር ትዝ አለኝ። በ1985 ዓ.ም ይመስለኛል አንተ ወደፊት በሉለት ይለይለትን እየዘፈንክ፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ምስልህን ወደ ኃላ ሲመልስ ታይቷል። ያን ሁኔታ ስትመለከት ምን ተሰማህ?

 

ጥላሁን፡- እኔ ጥላሁን!? ---ጦር ግንባር ሆኜ ተጀምሮ እስኪጨረስ ድረስ ወደፊት እንጂ ወደ ኃላ አልልም! የተንቀለቀለ እሣት ውስጥ ገብቻለሁ። ወደ ኃላ ያልኩበት ጊዜ የለም። ምናልባት ተቃራኒው ክፍል ያን ታክቲክ ይጠቀምበት ይሆናል እንጂ እኔ ወደፊት ብዬ ወደኋላ እየሸሸሁ ምን አይነት መዋጋት ይሆናል!-- በሀገሬ ላይ ለሚመጣው ነገር!--አሁንም ቢሆን ወደፊትም ቢሆን!ወደፊት እንጂ ወደኋላ እንደማልል እንድታውቅ እፈልጋለሁ።

 

ኢትዮጵ፡- መልካም ጥላሁን !--አንተ የምትጨምረው ነገር ወይም ለማለት የምትፈልገው ነገር ካለ እድል ልስጥህ

ጥላሁን፡-ምንም የምጨምረው ነገር የለም። ግን አሁን አንተ ስትጠይቀኝ-- ትንሽ የተሰማኝና የደም ስሮቼን ልታቆመው የቻልከው በአሁኑ አነጋገርህ ነው። እና--

 

ኢትዮጵ፡- እኔ እኮ አይደለሁም ያ…

ጥላሁን፡- ገባኝ!-- ባዮቹም ቢሆኑ ደካሞች ናቸው። እኔ ወደኃላ ብዬም አላውቅም። ምናልባት ይሄን ለማለት የሚፈልግ ካለ ይበል። እኔ ግን ምን ግዜም!-- ደረቴን እንጂ ጀርባዬን ለጥይት ሰጥቼ አልኖርኩም። ያን ሁሉ--ለጥይት እየጋበዝኩ-- እኔ ራሴን ወደኃላ?!--እንዴት ይታሰባል?!---ሊሆን የማይችል ነገር ነው!

 

(ኢትዮጵ መጽሄት መጋቢት ወር 1993)

ጥላሁን ገሠሠ እንዲህ አይነት ወኔያም ከያኒ ነው። ጀግና ነው። በየጦር ግንባሩ እየሔደ ደረቱን ለጥይት ሠጥቶ የሚዘፍን ድምፃዊ አርበኛ ነበር።

 

በ1995 ዓ.ም እቢሮው ሔደን ቃለ-መጠይቅ ያደረግንለት ቀን ዛሬም ትዝ ትለኛለች። ከኔ ጋር ሁለት ጓደኞቼ አብረውኝ ነበሩ። አንዱ ጋዜጠኛ አብይ ደምለው ሲሆን ሁለተኛው ድሮ ጐበዝ የጋዜጣ አዘጋጅ የሆነውና አሁን ደግሞ የባንክ ሰራተኛ የሆነብን ሙሉጌታ አያሌው ነው። ከጥላሁን ጋር  ግማሽ ቀን ያህል ውብ ጊዜ አሣለፍን። ከዚያም በተደጋጋሚ እንገናኝ ነበር። ብዙ ቃለ-መጠይቅ አድርገንለታል። አሁንም ከአብይ ጋር ስንገናኝ የጥላሁንን ድምጹን እየሰማን ከትዝታው ጋር እናወጋለን።

 

ዛሬ ዜና ዕረፍቱ የተሰማበት ቀን ነውና እስኪ ስለ ጥላሁን ወግ እናውጋ። ጥላሁን የሕዝብ ልጅ ነው። ገና ከ13 አመቱ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ እናትና አባት ሆኖ ያሣደገው ነው። በኢትዮጵያ ሕዝብ አንቀልባ ላይ ሆኖ ያደገ ነው። ታዲያ እንዲህም ሆኖ ጥላሁን ምስጢርም ነው። ተፈትቶ ያላለቀ። ሆድ ይፍጀው ሆኖ ኖሮ ያለፈ። ዛሬም ሆድ ይፍጀው የሆነ።

 

አንገቱ በስለት ተቆርጦ ከሞተ ደጃፍ እና አፋፍ ላይ በተአምር ተርፎ ሆድ ይፍጀው የሆነ ሰው ነው። ጥላሁንን ማን ነው አንገቱን የቆረጠው? ምስጢሩ ለሕዝብም ለሐገርም ሆድ ይፍጀው ሆኖ ቀርቷል። ግን እኮ መርማሪ አጥቶ ነው  እንጂ አደጋውን የፈፀመው አካል ይታወቃል። ጥላሁንን አንገቱን በስለት ያስቆረጠው አካል በፖሊስ የምርመራ ማሕደር ውሰጥ ይገኛል። በእለቱ ድርጊቱን የፈፀመው አካል ማን እንደሆነ የፖሊስ መዝገብ ውስጥ ይገኛል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ። ግን ጥላሁን ገሠሠ ያንን አካል መግለፅ ስላልፈለገ ጉዳዩ ታፍኖ ዛሬም ድረስ አለ።

 

የጥላሁን ገሠሠ የሕይወት ታሪክን በተመለከተ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበር፣ የኢትዮጰያ የሙዚቃ ንጉስ በሚል ርዕስ ጥላሁን ከሞተ በኃላ የችኮላ ስራ ሠርቶ አሣትሟል። ዘካሪያ አሕመድም የጥላሁንን የሕይወት ታሪክ ከቤተሰቡ ያገኝሁት ሰነድ ነው ብሎ አሣትሟል። ኤሚ እንግዳ ደግሞ ጥላሁን ከሞተ በኃላ ‘The King’s Farewell’ የተሰኝ ዶክመንተሪ ፊልም ሰርታለች። በአማርኛ የንጉሡ ሽኝት እንደ ማለት ነው። ሁሉም የራሣቸው ደካማና ጠንካራ ጐኖች ቢኖሯቸውም ‘የሆድ ይፍጀው’ ነገር እስከ አሁንም እንደ ተዳፈነ ነው።  

 

ጥላሁን ገሠሠ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለማሳደግ የመስዋዕትነት ትግል ካደረጉ ከያኒያን መካከል በግንባር ቀደምትነት ስሙ የሚጠራ ነው። ምክንያቱም ለሙዚቃ ጥበብ ትልቁን ድርሻ እያበረከተ ለዚህ ልፋቱ ደግሞ የሚያገኛት የወር ደመወዝ እጅግ አስገራሚ ነበረች።

 

ለምሳሌ በ1949 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ስለ ጥላሁን ገሠሠ የተፃፈውን ደብዳቤ መመልከቱ ብቻ ብዙ ግንዛቤ ያስጨብጠናል። የፃፈው ደግሞ ባሕልና ማስታወቂያ ሚኒስቴር ነው። እንዲህ ይላል፡-

“ስለ አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ወልደ ኪዳን ከ1946-1949 ዓ.ም ቋሚ ሠራተኛ ስለመሆናቸውና በየወሩ የሚያገኙት ደሞዝ ልክ እንዲገለፅላችሁ በጠየቃችሁት መሰረት፣

 

-    በየወሩ ብር 30 ደሞዝ ይከፈላቸው የነበረ ሲሆን

-    ቋሚ ሠራተኛ መሆናቸውን የሚገልፅ ማስረጃ ያላገኘን መሆኑን እንገልፃለን”

ከሰላምታ ጋር

 

 

ጥላሁን ገሠሠ መድረክን እና ሕዝብን እንዲሁም ሀገርን እያስደሰተ የሚከፈለው የወር ደመወዝ 30 ብር ብቻ ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ ቋሚ ሠራተኛ ይሁን፣ አይሁን አይታወቅም። እርሱም ስለ ገንዘቡ እና ስለ ስራው ቅጥር የሚያስብ አልነበረም። የእርሱ ጭንቀት የተዋጣለት ሙዚቃን መድረክ ላይ መጫወት ነው።

 

ጥላሁን ገሠሠ በነ ጀነራል መንግስቱ ንዋይ ተፅዕኖ ወደ ክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ እንዲቀላቀል ተደረገ። እዚያ ሲገባ በተወሰነ መጠን ደሞዙ ተጨመረለት። የህይወት ታሪኩን በሚገልፀው መፅሐፉ ውስጥ ጥላሁን ገሠሠ ክቡር ዘበኛን ሲቀላቀል እንዲህ በማለት ገልጾታል።

 

“ለምሳሌ የእኔ ደሞዝ 40 ብር ሲሆን፣ እውቋና ሕዝብን ከመቀመጫው ትፈነቅለው የነበረችው የብዙነሽ በቀለ ደሞዝም 80 ብር ነበር። የእሷ እንዲያውም እጅግ ከፍተኛ ደሞዝ በመሆኑ እንቀናባት ነበር። በተረፈ ለቡድኑ ስም እንጂ ለግል ስምና ዝና ማን ተጨንቆ? ምክንያቱም ኑሮ በጣም ርካሽ ነው። ለምሳሌ ሽንጥ ሥጋ አምስት ብር፣ አንድ መለኪያ ውስኪ 0.05 ሳንቲም፣ ቆንጆ እራት 0.30 ሳንቲም፣ ኩንታል ማኛ ጤፍ 24 ብር፣ ኬክ 20 ሳንቲም መግዛት እንችላለን። ስለዚህ ደሞዝ ተጨመረ፣ ቀረ ምን ያስጨንቃል? ብሏል።

 

 

ጥላሁን ገሠሠ የኖረበትን ዘመን እያወደሰ፣ እያቆለጳጰሰ እያደናነቀ የኖረ ሰው ነው። ምንም መከራ እና ስቃይ ቢደርስበትም ተማሮ አይገልጸውም። ለዚህም ነው ሁሉም ነገር በቂዬ ነው እያለ ምድረ ላይ ያለ ሀብት እና ንብረት ሳያፈራ ያለፈው። ሐብት ንብረቴ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው እያለ ኖሯል።

 

እነ ጀነራል መንግስቱ ንዋይ እና ገርማሜ ንዋይ በታህሳስ ወር 1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አድርገው ሳይካላቸው ቀርቷል። ታዲያ በዚያ ወቅት ጥላሁን ገሠሠን የፀጥታ ሰዎች ወደ ኮልፌ በመሔድ በቁጥጥር ስር አዋሉት። ከዚያም ከኮልፌ እስከ አራተኛ ክፍለ ጦር ድረስ በሰደፍና በርግጫ እየደበደቡት አመጡት። ጥላሁን ምን ቢያደርግ ነው እንዲህ የተደበደበው ማለታችሁ አይቀርም። ጉዳዩ ብዙ አስገራሚ ነገሮች አሉት።

 

በ1995 ዓ.ም ጥላሁን ገሠሠ ቃለ-መጠይቅ አድርጌለት ለአዲስ ዜና ጋዜጣ በሰጠው አስተያየት ጀነራል መንግስቱ ንዋይ ባይወልዱኝም እንደ አባት እና ወላጅ ሆነው ስርዓት ይዤ ለተሻለ ደረጃ እንድበቃ ብዙ የጣሩልኝ ሰው ናቸው። እኔም ወላጆቼ በቅርበት በአጠገቤ ስለሌሉ እርሳቸውን እንደ አባት ነበር የምቆጥራቸው። ከርሳቸው ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበረኝ። በዚህ የተነሳ እና በዘመኑ “ጩኸቴን ብትሰሚኝ” እያልኩ ዘፍኜ ነበር። በነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ከመፈንቅለ መንግስቱ መክሸፍ በኋላ እኔም ተይዤ በጥፊ፣ በርግጫ፣ በሰደፍ እየተመታሁ ከኮልፌ እስከ አራተኛ ክፍለ ጦር ድረስ መጣሁ። እዚያ ስደርስ ጀነራል ፅጌ ዲቡ ተረሽነው አስከሬናቸው አስፋልት ላይ ተዘርግቷል። እርሳቸውም በጣም የማከብራቸውና የማደንቃቸው ሰው ነበሩ። እንደተራ ሰው መንገድ ላይ ተዘርግተው ሳይ የራሴን ድብደባ እና ሕመም ረሳሁት። ይዘውኝ የመጡት ወታደሮች መንገዱ ላይ የተዘረጉት አስክሬኖች ላይ ውጣባቸው አሉኝ። ይህ እንዴት ይሆናል ብዬ ብጠይቃቸው አናቴን በሰደፍ መቱኝ። ከዚያ ያደረኩትን አላውቅም። በመጨረሻም እስር ቤት ተልኬ ብዙም ጉዳት ሳይደርስብኝ ተለቅቄያለሁ” ብሏል።

 

ጥላሁን ገሠሠ በርካታ ችግሮች በሕይወቱ ላይ እየተጋረጡ ሲመጡ ተቋቁሞ የኖረ ነው። ሀገሩ ኢትዮጵያን አንድም ቀን የመክዳትና የመራቅ ሁኔታን ሳያሳይ አፈሯን፣ ምድሯን፣ ህዝቧን፣ ታሪኳን፣ ማንነቷን እያወዳደሰ 68 ዓመታት ኖሮባት በክብር የተሸኘ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉስ ነው።

 

ጥላሁን ገሠሠ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁሉ ብሔራዊ አርማቸውን እንዲወዱ፣ ብሔራዊ ማንነታቸውን እንዲያከብሩ፣ የሀገር ፍቅር ዜማዎችን ሲያቀነቅን የኖረ እና ኢትዮጵያ ሐገሩን ከፍ ከፍ ሲያደርግ የኖረ ተወዳጅ ድምፃዊ ነው።

 

ጥላሁን ገሠሠ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ የሀገሩን ዜጎች ሁሉ በያሉበት እየዞረ የሚያስደስት ተወዳጅ ከያኒ ነው። ለምሳሌ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ በሚካሄደው የኢትዮጵያዊን የእግር ኳስ ጨዋታ ላይ ከምስረታቸው ጀምሮ ለ17 ተከታታይ አመታት አንድም ጊዜ ሳያቋርጥ ወደ አሜሪካ እየሔደ ተሰባስበው የሚጠብቁትን የሀገሩን ልጆች ያስደስት ነበር። የሚገርመው ይሄ ብቻ አይደለም። በስኳር ሕመም የተነሳ አንድ እግሩ ከተቆረጠ በኋላም ያስለመድኳቸውን ሙዚቃ አላቆምም ብሎ በዊልቸር እየተገፋ ወደ መድረክ ወጥቶ አዚሟል፤ አስደስቷል። በዊልቸር እየገፋው ወደ መድረክ ያመጣው ደግሞ እጅግ የሚወደው የሙያ ጓደኛው መሐሙድ አህመድ ነው።

 

 

አንድ ወቅት ማለትም በ1995 ዓ.ም የሙያ ጓደኛው የሆነው መሐሙድ አህመድ ለጥላሁን ገሠሠ ያለውን ወዳጅነት ስጠይቀው የሚከተለውን ብሏል። “እኔና ጥላሁን አንድ ቀን ወደ ወሊሶ ሔደን ነበር። ወሊሶ አያቱ አሉ። እርሳቸውጋ ተጫውተን ስንወጣ ጥላሁን ገሠሠን ሰላም የሚለው ሰው በዛ። በረንዳ ላይ ከሁሉም ጋር ይጫወታል። በዚህ ጊዜ አያቱ እኔን ወደ ጓሮ ወሰዱኝና ሳር ከመሬት ነጭተው በእጄ አሲያዙኝ። ከዚያም እንዲህ አሉኝ። “በምድር የሰጠሁክን በሰማይ እቀበልሃለሁ። ጥላሁን እናትም አባትም የለውም። እህት ወንድም የለውም። ያለኸው አንተ ነህ። ልጄን አደራ። አንተ ነህ ወንድሙ፤ አንተ ነህ ያለኸው! ብለውኛል። ይሔን ታሪክ ለጥላሁን ገሠሠ ነግሬው አላውቅም። ገና ዛሬ ለናንተ መናገሬ ነው። ግን ሁልጊዜ ይሄ አደራ አብሮኝ ስላለ ጥላሁን ገሠሠ በሄደበት ሁሉ እኔ ከጀርባው አለሁ። የአደራ ጓደኛዬ ነው። (ከለቅሶ ጋር)

 

 

ጥላሁን ገሠሠ ሌላም አስገራሚ ትውስታ አለው። በዚሁ በ1995 ዓ.ም በሰጠው ቃለ -መጠይቅ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያምን በጣም እንደሚወዳቸው ተናግሯል። ለምን ወደድካቸው ተብሎም ተጠይቆ ነበር። ሲመልስም እርሳቸው ለእሱ (ለጥላሁን ገሠሠ) አክብሮትና ፍቅር እንዲሁም አድናቆት ስለነበራቸው እንደሆነ አውስቷል። በተለይ ጦር ሰራዊቱ ወደሚገኝበት ግንባር እነ ጥላሁን ገሠሠ ሊዘፍኑ በሚጓዙበት ወቅት ፕሬዝዳንቱ ጥላሁን ገሠሠን ይጠሩትና ምክር እንደሚሰጡት፣ አንዳንዴ ደግሞ እራትም ሆነ ምሳ በቤተ-መንግስት እንደሚጋብዙት ጥላሁን ገሠሠ ተናግሮ ነበር። በነዚህ ምክንያቶች ለፕሬዝዳንት መንግስቱ ፍቅር አለኝ ብሏል።

 

 

የጥላሁን ገሠሠን የሕይወት ታሪክ በሚዘክረው መፅሀፍ ውስጥ ደግሞ ጥላሁን ገሠሠ ደቡብ አፍሪካ ሆስፒታል ውስጥ እግሩ ተቆርጦ ነበር። በዚህ በእግሩ መቆረጥ ክስተት ውስጥ አንድ አስገራሚ ነገር ተከሰተ። ጥላሁን እንዲህ ያስታውሰዋል።

“የአንድ ቀኑ የስልክ ጥሪ ግን የሚደንቅ ነበር። ካረፍንበት ሆቴል ምሳ ለመብላት ሮማን ተሽከርካሪ ወንበሬን እየገፋች ወደ ምግብ አደራሹ ሄድን። እንደደረስንም ከምግብ በፊት የምወስዳቸውን መድሃኒቶች ሮማን እረስታ ኖሮ ለማምጣት ተመልሳ ወደ መኝታ ክፍላችን እንደደረሰች ስልኩ መጮኽ ይጀምራል። አንስታም ‘ሀሎ’ ስትል የሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለማርያም ረዳት እንደሆነና ሊቀመንበር መንግስቱ እኔን ማነጋገር እንደሚፈልጉ ይነገራታል። እሷም ከአምስት ደቂቃ በኋላ መልሰው እንዲደውሉ ትነግራቸውና ስትበር ወደ አለሁበት በመምጣት፣ “ሊቀመንበሩ በስልክ ሊያነጋገሩህ ይፈልጋሉ” አለችኝና ይዛኝ ወደ መኝታ ክፍላችን ሔድን። እንደገባንም ስልኩ ይጮኻል። ሮማን ስልኩን አንስታ አቀበለችኝና ሃሎ! ስል፣ “መንግስቱ ኃይለማርያም ነኝ ጓድ ጥላሁን! እንኳን እግዜር አተረፈህ” አይዞህ! ለሀገርህ በሚገባ ሰርተህበታል” ከዚህ በኋላ ማራቶን አትሮጥበት፤ ተወው ይቆረጥ! በርታ አሉኝ። ማመን ነው ያቃተኝ። እኔም ስለ ደወሉልኝ ምስጋናዬን አቅርቤላቸው በዚሁ ተለያየን።n

በጥበቡ በለጠ

ይህ ጽሁፍ የክፍሉ ታደሰ ነው። ክፍሉ ታደሰ በ1960ዎቹና 70ዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ /ኢሕአፓ/ ተብሎ የሚታቀውን የፖለቲካ ድርጅት የመሰረተና ከመሪዎቹም አንዱ የነበረ ነው።በ1960ዎቹ መጀመሪያ ከአውሮፓ የከፍተኛ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ሀገሩ የመጣው ክፍሉ፤ ከሞት አፋፍ ላይ በተአምር እየተረፈ ዛሬም ድረስ በህይወት ያለ የዚያ ትውልድ አደራጅና መሪ ነበር።ክፍሉ ላለፉት 36 አመታት እና አሁንም በውጭ ሀገር ነው የሚኖረው።ከኢሕአፓ አመራሮች በህይወት የቀሩት እጅግ ጥቂቶች ናቸው። ከነዚያ ውስጥ ክፍሉ አንዱ ነው። በህይወት በመኖሩ የኢሕአፓን ታሪክ ያ ትውልድ በሚል ርእስ በሶስት ተከታታይ ግዙፍ ቅጾች አሳትሟል። ቀደም ባለውም ጊዜ በእንግሊዝኛ ቋንቋ The Generation የተሰኘ መጽሀፍ ስለ ኢሕአፓ ታሪክ አሳትሟል። መጽሀፎቹ በአንባቢያን ዘንድ በእጅጉ የሚፈለጉ ናቸው። ውስጣቸው ብዙ ታሪክ አለ። ትዝታ አለ። ትውልድ አለ። ሞት አለ። ስቃይ አለ። ፖለቲካው፣ አብዮቱ፣ ትግሉ፣ ሽኩቻው…..መአት ነገሮችን የያዘው የክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ መጽሀፍ አስገራሚም የህይወት ገጠመኞችንም እናገኝበታለን። ዛሬ ለንባብ የምጋብዛችሁ ክፍሉ ታደሰ ከአዲስ አበባ ከተማ እንዴት ጠፍቶ እንደወጣ የተረከበትን አስገራሚ ገጠመኝ ነው።

***           ****          ****

ዘመኑ ራቅ ይላል። በ1969/70 ዓ.ም ላይ። የወጣት ሬሳ በየመንገዱ፤ በየጥጋጥጉና በየግድግዳው የሚጣልበት። እኔም አዲስ አበባን ለቅቄ መውጣት ነበረብኝ።ፎቶግራፋቸው በየማዕዘኑ ተበትኖ፤ በተገኙበት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከተወሰነባቸው ሰዎች መሀል አንዱ ነበርኩ። መንግስት የበተናቸውንና የተለጠፉትን ፎቶግፎች ማ እንዳየና ማ እንደሚያውቀኝና እንደማያውቀኝ ግምቱ እንኳን አልነበረኝም። ብቻ አንድ ነገር እንደነበረኝ አውቃለሁ። የወጣትነት ልበ ደፋርነት! አስታውሳለሁ ጥቂት ቀደም ሲል አንድ የማዘወትርበት ቡና ቤት የምትሰራ ሴት፤ ከእኔ ጋር ለሚገናኝ የኢህአፓ አባልን እንዳይቀርበኝ እንዲያውም መጥፎ ሰው ስለሆንኩ እንዲርቀኝ ትነግረዋለች። የት ታውቂዋለሽ ብሎ ይጠይቃታል። ቀበሌ ፎቶግራፌን እንዳሳያት ትነግረዋለች። በዚያ ጊዜ ቀበሌዎችበየቡና ቤት እየዞሩ ለቡና ቤት ሰራተኞች ፎቶግራፎች ካሳዩ በኋላ ድንገት ሰውዬው የሚመጣ ከሆነ ስልክ እንዲደውሉ መመሪያ ይሰጡ ነበር። ታዲያ ጉዋደኛዬ እንደእኔው በትግሉ ውስጥ ነበርና፤ ምስኪን ተራ ነጋዴ ነው። እሱን ማነው የሚፈልገው ብሎ ሊያሳምናት ሞከረ። ለእኔም ጉዳዩን አጫወተኝ። አስፈላጊውን ጥንቃቄ አደረግሁ።

 

ወደ ጀመርኩት ጉዳይ ልመለስና አዲስ አበባን መልቀቅ ነበረብኝ። ለማደሪያነት ወደተዘጋጀልኝ ቤት ሄድኩ። መርካቶ መኪና ተራ አጠገብ ነበር ቤቱ። ቤት ማለት ይቻል እንደሆነ አላውቅም፤ በረት ልበለው!ደግሞ የከብት ማደሪያ አልነበረም። እንደመጋዘን መሳይ ነው።የደረቁ የከብት ቆዳዎች እዚህና እዚያ ተሰቅለዋል።መጋዘኑ በወጉ ግድግዳ አልነበረውምና ነፋስ ያስገባል። በዚያ በረት ውስጥ ያደርነው ሶስት ነበርን። አንደኛውና የቤቱ ባለቤት /የአባቱ መጋዘን ይመስለኛል/ ሙሂዲን ይባላል፤ ሁለተኛው ደግሞ ባልሳሳት አዛርያስ በሚል ስም ነው የተዋወቀኝ።ይኸኛው እስከ ቅርብ ጊዜ በአሜሪካ በአንድ ከፍተኛ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ እንደነበር አውቃለሁ። የሁለቱም ስም የድርጅት እንጅ እውነተኛ ስማቸው አይመስለኝም። ሁለቱም በአዲስ አበባ የኢህአፓ ከፍተኛ አመራር አባላት ነበሩ። ያንን ሌሊት በጥንቃቄ አደርን። ሁለታችን ስንተኛ አንዳችን በመጠበቅ።

 

ጠዋት ላይ ተነሳሁና ወደ ክፍለ ሀገር አውቶቡስ መሳፈሪያ ሄድኩ። መናኸሪያውን ጨምሮ ዙሪያ ገባው በወታደርና በአሳሽ ቡድን ተጥለቅልቋል። የአሳሽ ቡድኑ ዋና ስራ በተቃዋሚነት የሚጠረጥሯቸውን መያዝ ነው። ወደ ክፍለ ሀገር አውቶቡስ መሳፈሪያ አመጣጣቸውም ተቃዋሚ ተሳፋሪዎችን ለመያዝ ነው ። እንደ እኔ ዓይነቱን ማለት ነው። ከያዙ በኃላ የፈለጉትን እርምጃ ይወስዳሉ። ደስ ካላቸው እዚያው ይገድላሉ። ጠያቂ የለባቸውም።የኢሕአፓ አባልን ገደለ ተብሎ ሰው አይከሰስም።አበጀህ ይባላል እንጅ።

 

ከበባ መኖሩን ስረዳ ቅጽበታዊ በሆነ መንገድ ውሳኔ መውሰድ እንዳለብኝ ተረዳሁ። ዙሪያ ገባው ስለተከበበ ከዚያ መውጣት ከቶም የማይቻል እንደነበር ተገነዘብኩ። መሳፈሬን ተውኩና በአካባቢው እንደነበሩ ሌሎች ሰዎች ወሬ ተመልካች ለመሆን ወሰንኩ። እንደእኔው ብዙ ሰዎች ነበሩና እኔ የወሰድኩት እርምጃ ከሌሎች የተለየ አልነበረም። ወሬ የሚመለከቱ ሰዎች ምንም የሚፈሩት ነገር የለም የሚል ትርጉም ስለነበረው አሳሾቹ አያተኩሩባቸውም። አሳሾቹ አጠገብ ቀረብ ብዬ ስመለከት ዶ/ር ዓለሙ አበበን አየሁ። በህቡእ ትግል አብረን ሰርተናል። እንደ መሪ ከማያቸው ሰዎች አንዱ ሲሆን በፖለቲካ መደራጀት ስንጀምር እኔ የተሳተፍኩበትን የመጀመሪያ ቡድን የመሰረተው ዶ/ር ዓለሙ አበበ ነበር። በ1961 ዓ.ም እሱ ወደ ሀገር መግባቱ ነበርና እኛን አደራጅቶ መሄድ አስፈላጊ እርምጃ ነው ብሎ የገመተ ይመስለኛል። ታዲያ በ1969/70 ዓ.ም ሁኔታዎች ተቀያይረዋል። ዶ/ር ዓለሙ የመንግስት ወገን፤ እኔ ተቃዋሚ፤ እሱ አሳዳጅ፤ እኔ ተሳዳጅ፤እሱ አሳሽ፤ እኔ ታሳሽ ሆነናል።

 

ልክ ዶክተሩን ሳይ አደጋሸተተኝ። እዚያው መኪና ተራ ፊት ለፊት ከሚገኝ አልቤርጎ ሄድኩና መኝታ ያዝኩ። ዘና ብዬ ወንበር እንዲሰጡኝ ጠየቅሁና ደጃፉ ላይ ተቀመጥኩ። ይህን ያደረግሁበት ምክንያትም የምሸሸግ እንዳይመስላቸውና እንዳይጠረጥሩ ለማድረግ ነበር። ልክ በራፉጋ ቁጭ ስል አጎቴ ከየት መጣ ከየት ሳልለው አጠገቤ ደረሰ። መሰወሬን የሚያዉቅ ቢሆንም እዚያ ቦታ በዚያ ሰዓት ምን አደርግ እንደነበረ ጨርሶ ሊገባው የሚችል አልነበረም። በአጠገቤ እያለፈ ዞር ብሎ እንኳን ሳያይ ሄደ። ወደ ግራም ሆነ ወደ ቀኝ ገልመጥ አይልም። ፍዝዝ ብሎ ወደፊት ብቻ ነበር የሚመለከተው። ከላይ እስከታች ጥቁር ለብሷል። ሁለት ልጆቹን ቀይ ሽብር ቀምቶታል። አንደኛው መኩሪያ ተገኝ ይባላል። አቃቂ በሚገኝ የአብዮት ጥበቃ በዱላ ተቀጥቅጦ ነው የሞተው። መኩሪያን በቀበረ በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ነበር ሌላኛው ልጁ አሸናፊ ተገኝ ከሌሎች የኢህአፓ አባላት ጋር የተያዘው።የመንግስት ወታደሮች የተያዙትንልጆች አቶ ተገኝ ቤት አመጧቸው። አጎቴም ልጄ ሊፈታ ነው ብሎ ደስ ሳይለው አልቀረም። ልጆቹ ወደተያዙበት ክፍል ወስዷቸው። በሆዳቸው አጋደሟቸው። አቶ ተገኝም ወደ ክፍሉ እንዲገባ ተጋበዘ። ገብቶ ቆመ። ወዲያውኑ ወታደሮቹና አብዮት ጥበቃ አባላቱ የቶክስ እሩምታ ከፈቱ። ወጣቶቹ በሆዳቸው የተንጋለሉበት ቀሩ። አቶ ተገኝ የቆመበት ደርቆ ቀረ። አልጮኸም። አላለቀሰም።ትንሽ ቆየት ብሎ ሌሎች ህፃናት ልጆቹን ይዞ መጣና እነዚህንም ረሽኗቸው አለ። ከዚህ አጋጣሚ በኃላ ልሳኑ ተዘጋ። ታዲያ በአጠገቤ ያለፈው ይህ አጋጣሚ ከሆነ ከጥቂት ሳምንታት በኃላ ነበርና በምን ሁኔታ ውስጥ እንደነበረ ገምቻለሁ። ላናግረው ፈለግሁ። ይሁንና ሁኔታውን እንዴት ሊቀበለው እንደሚችል መገመት ከባድ ሆነብኝና ተውኩት። አቶ ተገኝ አሳሽ ቡድኑን ከመጤፍ የቆጠረ አይመስልም። ብቻ ፍዝዝ እንዳለና ወደ ግንባር እየተመለከተ መንገዱን ቀጠለ። አሳሽ ቡዱኑም እስከ እኩለ ቀን ድረስ አካባቢውን ሲያምስ ውሎ ሄደ። ስራው ውጤታማ ይሁን አይሁን አላወቅሁም። እኔ ተርፌ ቤርጎዬ ገባሁ። አልወጣሁም። ተከርችሜ ውዬ አደርኩ። በበነጋው አውቶቡስ ተሳፈርኩ። ከእኔ ጋር ሌላ የኢህአፓ አባል ነበረና እየተጠባበቅን ነበር የምንሄደው።እንጂ በአደባባይ አንነጋገርም። ይጠብቀኛል፤ እጠብቀዋለሁ። ይህ ጓደኛዬ ኤርትራዊ ሲሆን ቤተሰቦቹ እስላሞች ነበሩ። የተሳፈርኩበት አውቶቡስ ጎሃ ጽዮን ደርሶ ለምሳ ውረዱ ተባልን። ጓደኛዬ ለምሳ ወዴት እንደሄደ አላወቅሁም። እኔ መኪናው ከቆመበት ራቅ ብዬ በመሄድ አንድ ምግብ ቤት ገብቼ ምሳ ጠየቅሁ። ከየት መጣ ከየት ሳልለው አንድ ሰው “አንተ የክርስቲያን ቤት ነውኮ” አለኝ። ዘወር ብዬ ስመለከት ሰውየውን ጨርሶ አላውቀውም። እኔ የነበርኩበት አውቶቡስ ውስጥ የነበረው ሰው መሰለኝ። ትዝ ሲለኝ ማንነቴን ለመቀየር ብዬ የእስላም ኮፍያ አድርጌአለሁ። የለበስኩትም ነጋዴ የሚያስመስል ሳሪያን ኮትና ሰፋ ያለ ሱሪ ነበር። ላየኝ ሰው የከሰረ የእህል ነጋዴ ነበር  የምመስለው። ሰውዬው ለምን እንደዚያ እንደተናገረ ወዲያው ገባኝና ያላወቀ በመምሰል “እረባክህ ቢስሚላሂ” አልኩኝ። ወደ በሩ ወጣሁና ሌላ ምግብ ቤት ፍለጋ ጀመርኩ። ሰውዬውም አምቦውሃ ገዝቶ ሲበር ሄደ።እሱ ሲሄድልኝ ኮፍያዬን አውልቄ በፊት ወደነበርኩት ቤት ተመልሼ በመግባት ምሳዬን በላሁ። አውቶቡስ ልሳፈር ስል ምግብ ማግኘት አለማግኘቴን ሰውየው ጠየቀኝ። ሌላ ቦታ ሄጄ በላሁ ብዬ ዋሸሁ።

 

ሰውየው ለምንና እንዴት ሊያውቀኝ እንደቻለ በመጠራጠሬ አውቶቡሱ ውስጥ ምን ያህል እስላሞች እንዳሉና እነማን እንደሆኑ ቀስ ብዬ አጠናሁ። እኔ ልለያቸው የቻልኩት ስምንት ያህሉን ነበር። እነዚህ ጨርሶ የማላውቃቸውና የማያውቁኝ እስላሞች ለእኔ በህይወት መትረፍ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።ዝርዝሩን ወደኃላ አነሳዋለሁ። አውቶቡሱ ጉዞ ቀጥሎ ብዙም ሳንርቅ አውቶቡሱ በረሃ ላይ ተሰበረ። እኔና ጉዋደኛዬ በጥቅሻ ተነጋገርንና ራቅ ብለን ሄደን ምን እናድርግ አልን። ሰው እንደሚሆነው ለመሆን ወሰን። ከጓደኛዬ ተለይቼ አውቶቡሱ ወደነበረበት ሄድኩ። አልተሰራም።ሙስሊም የሃይማኖት ወገኖቼ ሲፈልጉኝ ነበር። ለካስ ገና ከሩቅ ሲያዩኝ “የት ጠፋህ አንተ እስላም” ብለው ምግብ ጋበዙኝ። በላሁ። እስላሙ የኢህአፓ ጉዋደኛዬ የሚላስ የሚቀመስ አላገኘም። እኔ ስጋበዝ ያያል። ዝም ነው እንጅ ምን ሊያደርግ ይችላል።

 

አሁንም አውቶቡሱ አልተሰራም። ምሳ ሰዓት ደረሰ። እስላም ወዳጆቼ ምሳ ጋበዙኝ። በላሁ። የለመደች ጦጣ አሉ፤ ተነስቼ ልሄድ ስል ያ መጀመሪያ የእስላም ቤት ነው ያለኝ ሰው ሰላት እናድርግ/እንስገድ/አለኝ። ዓይኔ ፈጠጠ። ከደርግ ተሸሽጌ ለ26 ወራት አዲስ አበባ በተቀመጥኩበት ጊዜ ብዙ ቦታ ረግጫለሁ። ጉራጌ እስላሞች ቤት ኑሬአለሁ። ሰላት ሲያደርጉ አይቻለሁ። ይሁንና ስነ-ስርዓቱን ጠንቅቄ አልተረዳሁም። ታዲያ አሁን ሰላት እናድርግ ሲለኝ ሰውዬው ባልተጠረጠረው እንዳለው ሆነ።

ጨዋታው እንዲህ ነው። የገጠር ሰው ነው። ከሚስቱ ይፋታል።ትከሰዋለች። ከቀጠሮ ቀን በፊት አቦካቶው/ጠበቃው/ ይመክረዋል። እንዲህ ሲሉህ እንዲህ በል፤ ይህንን ሲጠይቁህ ይህንን መልስ እያለ ቀኑ ደረሰና ሰውዬው ዳኛ ፊት ቀረበ። ስሙን ተጠየቀ። መለሰ። የሚስቱን ስም ተጠየቀ። ወደ መሬት አቀረቀረ። ወደ ላይ አንጋጠጠ። ትንሽ ቆየ። የሚስት ስም ከየት ይምጣ!? እንደ አብዛኛው የገጠር ሰው ሚስቱን በስሟ ጠርቷትም አያውቅም። አንቺ ነው የሚላት። ታዲያ ወደ አቡካቶው ዞር ብሎ “ጌታው ባልተጠረጠረው መጡብን” አለ ይባላል።

 

እኔ ባላሰብኩትና ባልጠረጠርኩት መንገድ ፈተና ገጠመኝ። ሰላት የማያደርስ እስላም ምን ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል ባላገናዝብም ገበናዬ ሊጋለጥ ሆነ። እጅግ ፈጣን በሆነ መንገድ አሳማኝ መልስ መስጠት ነበረብኝ።“ጉዞ ላይ ሰላት ማታ ብቻ ነው የማደርገው” አልኩት። ይመነኝ አይመነኝ አላወቅሁም። ብቻ አየት አደረገኝና ስግደቱን ቀጠለ። ከአጠገቡ ራቅሁ። ተጠራጥሮአል መሰለኝ ጥቂት ቆየት ብሎ የት እንደምሄድ ጠየቀኝ።“ጎንደር” አልኩት። ከእነማን ዘንድ አለኝ። የሆነ ሰው ስም ሰጠሁት። አወቀው።“ክርስትያን ነውኮ” አለኝ።“የጋብቻ ዘመድ” ነው አልኩት። አሁንም አመለጥኩ ወይም ያመለጥኩ መሰለኝ።

 

አውቶቡሱ ተሰርቶ ጉዞውን ቀጠለ። ጎንደር ከተማ ከመድረሳችን በፊት ጥቂት ኪሎሜትር ሲቀረን የአብዮት ጥበቃ አባላት አስቆሙን። ሰው ሁሉ ከአውቶብስእንዲወርድ ከተደረገ በኃላ እየተፈተሸና መታወቂያውን እያሳየ እንዲገባ ተደረገ። እኔና ሌላ አንድ ሰው አትሳፈሩ ጠብቁ ተባልን። እንዳልሳፈር የከለከለኝ የአብዮት ጥበቃ ሃላፊው ሽባባው የሚባል ነበር። መታወቂያ ደብተሬን አልተጠራጠረም። መታወቂያ ደብተሬ ከሰሜን ሸዋ ከአንድ ትንሽ የገጠር ከተማ/ገምዛ/ የወጣች ናት። ያጠራጠረው መሸኛ ደብዳቤው ነው። የፋይል ቁጥር የተስተካከለ አልነበረም። ወይም የሚጎድለው ነገር ነበር። ሽባባው ስለችግሩ ጠየቀኝ። ማንበብና መፃፍ የማልችል ምስኪን ሰው ሆኜ ቀረብሁ።“እኔ ምን አውቃለሁ የሰጡኝን ነው ተቀብዬ የመጣሁት” አልኩ። ሌላው አውቶቡስ ውስጥ እንዳይገባ የተከለከለው ሰው ለጦርነት ጅጅጋ ዘምቶ የመጣ ዘማች ነው። አዲስ አበባ ደውሎ እንደሚያጣራ ሽባባው ነገረን።

 

ኢህአፓው ጓደኛዬ ደነገጠ። አጠገቡ የተቀመጠውን ሰው ከሁኔታው ባለስልጣን ወይም የፀጥታ ሰራተኛ ይሆናል ብሎ ገመቶ ነበርና “ይሄን ምስኪን እስላም ያዙትኮ”ይለዋል። ለሾፌም ተመሳሳይ ነገር ነገረ። እስላሞቹም ግልብጥ ብለው ከአውቶቡሱ ወረዱ። ይሄ ምስኪን እስላም ምን አደረገ እያሉ። ሽባባው የሚበገር አልሆነም።አልለቃቸውም አለ።እስላም ወገኖቼ፤ ሾፌሩ፤ የፀጥታ ሠራተኛው ሁሉም በአንድነት ተንጫጩ። እኔ ነገር ዓለሙ የዞረበት ነጋዴ መስዬ ጥጌን ይዤ ቆሜአለሁ። ለሚያየኝ ሳላሳዝን አልቀርም። ሽባባው ልቡ ራራ።“ሂድ ግባ ለሁለተኛው እንደዚህ ዓይነት ወረቀት ይዘህ እንዳትንቀሳቀስ!” አለኝ። እሺ አልኩ። ሽባባው ፊቱን ወደ ሚሊሽያው አዙሮ “አንተን አለቅህም! ገና ከአዲስ አበባ አጣራለሁ” አለው። ሚሊሽያው ሰውነቱ ፈርጠም ያለ ሲሆን እንደ ሽባባው ያለ የመንደር አውደልዳይ እኔን ዘማቹን እንዴት ሊጠይቀኝ ይችላል የሚል ስሜት አድሮበታል መሰለኝ ሽባባው የሚጠይቀውን በስነ-ስርዓት አይመልሰም። ያበሻቅጠዋል። የአካባቢው ንጉስ ነኝ ብሎየሚያስበው ሸባባው፤ ስለተደፈረ በጣም ተናደደ።እልህ ውስጥ ገባ። ነገርን ነገር እየወለደ ሚሊሽያውም ተናደደ። ተሳደበም። ሚሊሽያው  ቀረ። አውቶቡሱ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ሾፌሩም ጭምር ለእሱ መቅረት ቁብ አልሰጡም። አውቶብሱም ተንቀሳቀሰ። ሁሉም ደስ አለው። ለጥቂት ደቂቃዎች ያህል ምስኪኑ እስላም የውይይት ርእስ ሆነ።

 

ጎንደር ከተማ ነው።የተለያዩ ስራዎች አከናውኜ በከተማው ከታወቀ አንድ ኢህአፓ አባል ጋር እየተወያየን በጉራንጉር መንገድ እንዳለን ከበስተኋላዬ ድምጽ ሰማሁ። እኔን አልመሰለኝም። ገልመጥ ብዬ ካየሁ በኃላ መንገዴን ቀጠልኩ። ብቻ ከአንድ ሱቅ በራፍ ላይ አንድ ሰው ቆሞ አየሁ። ሰውየው ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጣራል። ሰውዬው ተጠጋን።“አንተ እስላም፤ አንተ እስላም” ይላል። እኔ እስላምነቴን ረስቼዋለሁ። ለማንኛውም ተጠራጠርኩና ዳግመኛ ዞር አለኩ። አብሮኝ የነበረው የኢህአፓው ሰውም እንደእኔው ዞር ብሎ ቆመ። አንተ እስላም እያለ ይጣራ የነበረው ሰው ወደ እኔ መምጣቱን በቅጽበት አቆመ።የቆመበት ደርቆ ቀረ። እረ!እረ! አለ። ከላይ እንደገለጽኩት አጠገቤ የነበረው በጎንደር የታወቀ የኢህአፓ አባል ነበር።ደግሞም እስላም ነበር። የአውቶቡሱ ጓደኛዬን እኔ ከዚህ ሰው ጋር ስሄድ ማየቱ ጭንቅላቱን መታው መሰለኝ ምንም አላለም። ፊቱን አዙሮ ተመልሶ ወደ ሱቁ ገባ።ተከተልኩት።ሰላም ልለው። ሰላምታዬን አልመለሰልኝም። ምን ያሰላስል እንደነበረ ግን ገምቻለሁ። እንደ እንቆቅልሽ ሆነውበት ለነበሩ ለብዙ ጥያቄዎች መልስ ሳያገኝ አልቀረም።

 

በጥበቡ በለጠ

 

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በቴሌቪዥን የማየው የቢራዎች ማስታወቂያ እያሣሠበኝ መጥቷል። የቢራን ምርት በኢትዮጵያዊነት፣ በጀግንነት፣ በአይነኩኝም ባይነት፣ በተከበረው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ላይ ማስተዋወቅ እየተለመደ መጥቷል። ኢትዮጵዊነትን ከቢራ ጋር ማቆራኘት እየቆየ ሲሔድ ምን ሊፈጥር እንደሚችል ሁላችሁም የራሣችሁን ግምት መውሰድ ትችላላችሁ።

ግን ሐገር ማለት ምንድን ነው?

ይህ ጥያቄ ለዘጠና ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ቢቀርብ መልሱ ምን ሊሆን ይችላል?አሁን በቅርቡ በተደጋጋሚ በተላለፉት የቢራ ማስታወቂያዎች አማካይነት ከሔድን ሐገር ማለት ቢራ ነው የሚል መልስ ልናገኝ እንችላለን። እርግጥ ነው ቀልድ ይሁን የምር ማረጋገጥ አልቻልኩም እንጂ ሕፃናት በሚማሩበት በአንድ ክፍል ውስጥ በዚህ በአድዋ 120ኛ አመት መምህሩ ተማሪዎቹን አንድ ጥያቄ ይጠይቃቸዋል አሉ። ጥያቄው በአድዋ ጦርነት ኢትዮጵያዊያን የተዋጉባቸው መሣሪዎች ምንድን ናቸው? የሚል ነበር። አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ቢራዎች እየጠሩ መልስ ሰጡ ብሎ አንዱ ወዳጄ የሠማውን አጫወቶኛል። ጉዳዩ የተጋነነ ወሬ አይደለም። እውነት ሊሆን ይችላል ምክንያቱም ማስታወቂያዎቹ በልጆች አእምሮ ውስጥ ይህን የሀገርን እና የቢራን ቁርኝት ሊፈጥሩ ይችላሉ። የኢትዮጵያ የብዙ ሺ አመታት ታሪክ የሚያስተዋውቀው በማጣቱ ይኸው ቢራዎች እየተረባረቡበት ነው።

ጥያቄውን ለሁለተኛ ጊዜ ላቅርበው፤ ሐገር ማለት ምንድን ነው?

ከሦስት አመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት ክፍል ውስጥ ተጋብዤ ነበር። የተጋበዝኩበት ምክንያት መቀሌ ከተማ ሕዳር 29 ቀን ለሚከበረው የብሔር ብሄረሰቦች በዓል ላይ ለሕዝብ የሚቀርበውን ቴአትር አይተን እንድንገመግመው፤ አስተያየት እንድንሰጥ ነው። ይህ እንግዲህ ቴአትሩ ለሕዝብ ከመቅረቡ በፊት ተጣርቶ እንዲወጣ የተደረገ ሙከራ ነው። ሙከራውን በጣም አደንቃለሁ።

ቴአትሩ ሐገር ማለት--- የሚሰኝ ነው። ደራሲዎቹ አሁን የብሔራዊ ቴአትር ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆነው ጓደኛዬ ተስፋዬ ሽመልስ እና የፋና ብሮድካስቲንግ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ብሩክ ከበደ ናቸው። ቴአትሩ ሙዚቃዊ ነው። በቴአትሩ ውስጥ ዋና ገፀ-ባሕሪ የሆነችው፤ የተወከለችው፤ ኢትዮጵያን ሆና የተሣለችው ገፀ-ባሕሪ ሐገር ማለት እናንተ ናችሁ ትላለች። ሐገር ማለት ሰው ነው ትላለች። ሐገር ማለት አፋር ነው፤ ሐገር ማለት ሐረሪ ነው፤ ሐገር ማለት ሲዳማው ነው፤ ሐገር ማለት እያለች በዚያ ቴአትር ላይ እያዜመች ትተውናለች። ሐገር ማለት ሰው ነው፤ ሰው ነው ሀገር ትለናለች። የቴአትሩ ዋና ማጠንጠኛው ሐገር ማለት ሰው ነው የሚለው ጉዳይ ነው።

እውነት ሐገር ማለት ምንድን ነው?

ሀገር ማለት ሰው ብቻ ነው ብዬ በግሌ አላምንም። ምክንያቱም ሀገር በጣም ረቂቅ ጉዳይ ነው። ለምሣሌ ኢትዮጵያ ከምትባለው ሀገር ወጣ ብለን ሌላ ሀገር እንኑር። በውጭ ሀገር በመቆየታችን ምን ይሆን የሚናፍቀን? በርግጥ ሁላችንም አንደስሜታችን የምንናፍቀው ነገር ይለያያል። አንዳንድ ሰው ያደገበት፣ የቦረቀበት ሜዳው፣ ዳገቱ፣ ሸንተረሩ ሊናፍቀው ይችላል። ሌላው ደግሞ የሚዋኝበት ወንዝ ሊናፍቀው ይችላል። አንዳንዱ ደግሞ ምግቡ እንጀራው፣ ጮማው፣ ሽሮው፣ ጨጨብሣው፣ ቅቤው ድልሁ-- ሊናፍቀው ይችላል። አንዳንዱ ከብቱ፣ እንስሣቱ፣ ፈረስ ግልቢያው ወዘተ ሊናፍቀው ይችላል። አንዳንዱ ሰው ሊናፍቀው ይችላል፤ ወንድሙና እህቱ፣ እናቱ፣ አባቱ፣ ጓደኛው--። ስለዚህ ሀገር ማለት እነዚህና ሌሎች ብዙ ሚሊየን ነገሮች ማለት ነው። ሀገር ማለት ሰው ብቻ አይደለም! ሀገር ረቂቅ ነው።

ዛሬ ዛሬ ሀገር ማለት ቢራ እየሆነ በመተዋወቅ ላይ ነው። የሐገራችን ቢራዎች ሀገርን የምርታቸው ማስተዋወቂያ እያደረጉት መጥተዋል። ምናልባት ስለ ሀገር የሚያወራ በመጥፋቱ ይሆን? ሀገር ስለምንለው ጉዳይ ምስክር ሲጠፋ፣ ድምፁን ከፍ አድርጐ የሚናገር፣ የሚያወጋ በመክሰሙ ቢራዎች አጀንዳውን ይዘው መነሣታቸው ይሆን? ያውምኮ በግጥም እና በታሪክ ላይ እየተቀኙ ነው የሚያቀርቡት።

የቢራ ማስታወቂያዎች እየገረሙኝ ከቆዩ አመታት እያለፉ ነው። ለምሣሌ የሸገር ሬዲዮ 102.1 ባለቤቶች እና ጋዜጠኞች የሆኑት ተወዳጆቹ መአዛ ብሩ እና ተፈሪ ዓለሙ ቢራን ሲያስተዋውቁ ስንሰማ ድንቅ ይለናል።---“ከተማ ያደምቃል፤ ፀብ ያርቃል!”--እያሉ ቢራን ያስተዋውቃሉ። አይገርሙም?

እውነት ግን ቢራ በምን ተአምር ነው ፀብ የሚያርቀው? ሰው እንዳይጣላ፣ እንዳይጋጭ ቢራ መጠጣት አለበት? ላለፉት 20 አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ እርቅ የሚል ፖለቲካዊ ጥያቄ መቀንቀን ከጀመረ ቆይቷል። ቢራ ፀብ ያርቃል ከተባለ ትርጉሙ ብዙ ነው። የፀባችንን ጉድጓድ ሁሉ ይደፍናል። እናም ቢራ እንጠጣ ወደሚል ድምዳሜ ይወስዳል። ይህን ቢራ ፀብ ማራቁን በተመለከተ ማስታወቂውን የሰሩልን ታላላቅ ጉዳዮችን በሬዲዮ የሚያቀርቡልን ጐምቱ ባለሙያዎች መሆናቸው ሀዘናችንን ያብሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆኑት አቶ ወርቅነህ ጣፋ ሰሞኑን ይህን የቢራዎች የተሣሣተ ማስታወቂያ በተመለከተ የተናገሩት ጉዳይ አለ። ለምሣሌ “ከሺ ሰላምታ አንድ ሜታ!” የሚሰኘውን የማስታወቂያ ገለፃ ጠቅሰው ተችተዋል።

 

በጣም የሚገርመው ቢራን ከሺ ሰላምታ አስበልጦ ማቅረብ፣ ቢራን ፀብ ያርቃል ብሎ መናገር ብቻ አይደለም ስህተቱ፤ ይሔን ስህተት ተቀብሎ ለዘጠና ሚሊየን ሕዝብ በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን የሚያስተላልፈው ጣቢያ ምን አይነት አስተሣሰብ በውስጡ ቢኖረው ነው? ብዬም እጠይቃለሁ። ማሕበራዊ ኃላፊነትን (Social Responsibility) ያለመወጣት ችግር በሰፊው ይታያል።

ለምሳሌ በሕዝብ ዘንድ በሙዚቃው ልዩ ቃና በእጅጉ የሚወደደው ጋሽ አበራ ሞላ (ስለሺ ደምሴ) “ያምራል ሀገሬ” የሚሰኝ፤ ነብስን የሚገዛ ሙዚቃ ሰርቶ ነበር። ታዲያ ምን ያደርጋል ብዙም ሳይቆይ ይህን የመሰለውን ሙዚቃውን ለቢራ ማስታወቂያ ሲያውለው ሳይ፤ አርአያ ይሆናሉ ብዬ የማስባቸው ሰዎች እየተመናመኑብኝ መጡ።

 

የቢራ ጉዳይ የአዲስ አበባን ስታዲየም ሣይቀር እንደ ካንሰር ወርሮት ይገኛል። የሲጋራን ማስታወቂያ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ከአለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች እንዲወገዱ ያደረጉ ኢትዮጵያዊ ናቸው። እርሳቸው ከ25 አመታት በፊት ከዚህች አለም በሞት ሲለዩ የራሣቸው ሀገር ኢትዮጵያ ብሔራዊ ስታዲየሟ በመጠጥ ቤቶች ተወረሮ ቢራና ድራፍት እንደልብ የሚጠጣበት ቦታ ሆኗል። ብሔራዊ ቡድናችንም ውጤት እየራቀው ከውድድር ውጭ እየሆነ ከመጣም ቆይቷል። ድሮስ በአሸሼ ገዳሜ እና በአልኮል ከተከበበ ብሔራዊ ስታዲየም ውስጥ ምን አይነት የድል ውጤት ሊገኝ ይችላል?

 

ሌላው በጣም አስገራሚው ጉዳይ የብሔራዊ ቡድናችን ስም እና ቢራ ተመሣሣይ መሆናቸው ነው። ዋልያዎቹ ስፖንሰር የሚደረጉት በዋልያ ቢራ ነው። ለመሆኑ ብሔራዊ ቡድናችን እና የቢራው መጠሪያ ለምን ተመሣሣይ ሆነ? በኢትዮጵያ የንግድ ስያሜ ውስጥ ተመሣሣይ ስሞች ፈፅሞ አይፈቀድም። ዋልዎቹ እና ዋልያ ቢራ እንዲህ መመሣሠላቸው ብሔራዊ ቡድናችንም ከቢራ ጋር መቆራኘቱ ተገቢ ነው ትላላችሁ? ይድነቃቸው ተሰማ ይህን ቢያዩ ምን ይሉ ይሆን? የወቅቱም የኢትዮጵያ ፉት ቦል ፌደሬሽን ለኘሬዘዳንትነት የተመረጡት አቶ ጁነይዲን ባሻ ቀድሞ የሐረር ቢራ ፋብሪካ ዋና ሥራ አሥኪያጅ የነበሩ ናቸው። ምርጫውም ከወደ ቢራ አካባቢ መሆኑ ትንሽ ያስገርማል። ምናልባት የእርሣቸው የቀድሞ ኃላፊነታቸው ተፅዕኖ አድርጐ ይሆን ብሔራዊ ቡድናችን እና ስታዲየማችን በቢራ ንግድ እና ስም የተሳሠሩት።

 

ባጠቃላይ ሲታይ የቢራ ማስታወቂያዎች በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኃላፊነት በጐደለው መልኩ እየተሰሩ ይገኛሉ። ይህንንም ድርጊታቸውን ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢዎቻችን ካለምንም ተቃውሞ ለአድማጭ ተመልካቾች እያስተላለፉ ነው። በጉዳዩ የተቆጣው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ለሚዲያዎቹ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ልኮላቸዋል። ከረፈደም ቢሆን እርምጃው መውሰዱ ተገቢ ነው።

 

ሳጠቃልለውም፤ እርግጥ ነው ቢራ ፋብሪካዎች ለሀገር ኢኮኖሚ የሚኖራቸው ድርሻ ቀላል አይደለም። ብዙ የስራ እድል ከፍተዋል። እኔ እንኳን የማውቀው የቀድሞው ሐረር ቢራ ፋብሪካ ውስጥ በርካታ የሐረር ከተማ ነዋሪ ስራ እየሰሩ ይተዳደሩበታል። ቢራ ለመዝናናትም ያገለግላል። ግን ሐበሻ ቢራ እና ዋልያ ቢራ በሚያስተዋውቁበት ደረጃ ከሀገር ጋር አይቆራኝም።

 

በጥበቡ በለጠ

ጤፍ የኢትዮጵያዊያን ባሕላዊ ምግብ ነው እየተባለ ለብዙ ሺ አመታት አብሮን ቆየ። አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያዊያን እጅ ወጥቶ የአለም ቁጥር አንድ ተፈላጊ ምግብ እየሆነ ነው። አለም ፊቱን ወደ ጤፍ አዙሯል። እኛ ዘንድ ደግሞ ከጤፍ ጋር ያለን ዝምድና በብዙ ምክንያት እያሽቆለቆለ ነው። ለዛሬ መነጋገሪያ ይሆነን ዘንድ “ጤፍ የኛ በረካ” በሚል ርዕስ ሰሞኑን የታተመው የበለቀች ቶላ መጽሐፍ ነው።

 

በቀለች ቶላ ስለ ጤፍ ጥቅም መናገር፤ መወትወት፤ ማውራት፤ መፃፍ ከጀመረች አመታት ተቆጥረዋል። ጤፍ በንጥረ ማዕድናት እጅግ የበለፀገ ነው፤ በሐገራችን የእርሻ ባሕል ውስጥም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት ይገባል እያለች ትናገር ነበር። ከአራት አመታት በፊትም ጥበብና እፎይታ በተሰኘ በሬዲዮ ፋና የሬዲዮ ኘሮግራም ላይ አቅርበናት የጤፍን ተአምራዊ ሊባል የሚችል ጠቀሜታ አያሌ ማስረጃዎችን እጠየቀሰች ታስረዳን ነበር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአለም ታላላቅ የምርምር ማእከላት ስለ ጤፍ ጥቅም አጥንተው ይፋ የሆኑ መግለጫዎችን ሰጡ። የኘላኔቷ ግዙፍ ሚዲያዎች የሚባሉት እነ ኒው ዮርክ ታይምስ'ዋሽንግተን ፖስት' ቢቢሲ' ዴይሊ ሜል እና ሌሎችም እየተቀባበሉት ስለ ጤፍ ተአምራዊነት ዘገቡ።

 

በአሁኑ ወቅት የጤፍ ጉዳይ ለየት እያለ መጥቷል። ምክንያቱም ሌሎችም ሀገሮች እያመረቱት ይገኛሉ። ሲያመርቱት ደግሞ ወትሮም ከምናውቀው በተለየ መልኩ ነው።ለምሳሌ Costa Concentrados Levantinos የተባለ እ.ኤ.አ በ1887 ዓ.ም የተቋቋመ ኩባንያ AMANDIN በሚል የንግድ ስም ጤፍን በጁስ መልክ ፈሣሽ አድርጐት የሚጠጣ አድርጎት ይዞ መጥቷል። ጤፍ ግሉቲን ተብሎ ከሚጠራው በተለይ ስንዴ ውስጥ ከሚገኘው ንጥረ ነገር የፀዳ በመሆኑ የአለም ሕዝብ ከግሉቲን ነፃ (gluten free) እያለው ጤፍ ላይ ተረባርቧል። አንድ ኪሎ ጤፍም እስከ 200.00 የኢትዮጵያ ብር በውጭው ዓለም እየተሸጠ ይገኛል።

 

ዛሬ በአለም ላይ ስለ ጤፍ ጥቅም የሚነግሩን ከእኛ ይልቅ ሌሎች አለማት ሆነዋል። እነ በቀለች ቶላን የመሣሠሉ በኢትዮጵያ አዝእርት እና እፀዋት ላይ ጊዜና ጉልበታቸውን እውቀታቸውን የሚያፈሱትን ምሁራን ሚዲያዎቻችን ሰፊ ሽፋን ስለማይሰጧቸው ነገራችን ሁሉ ከእምቧይ ካብነትም በተጨማሪ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል ሆኖ ቀረ። በአሁኑ ወቅትም ጤፍ የኮፒ ራይቱ ጉዳይ ወደ አውሮፓ ደች ገብቷል። ጤፍ የኢትዮጵያ ልዩ መታወቂያዋ አዝእርት ሆኖ ሣለ ልክ ከአውሮፓ የተገኝ ይመስል ኮፒ ራይታችን ሲወሰድ ከዚህ በላይ ምን ያስቆጫል?!

 

የጤፍ ታሪክ እንደሚያወሣው ከአምስት ሺ አመት በፊት በኢትዮጵያ እንደተገኘ ይነገራል። ኢትዮጵያዊያኖች ከሣር ዘሮች መካከል ይህን ተክል ለምግብነት መጠቀም ጀምረው ይህን ሁሉ ዘመንም ከቤታቸው ከማዕዳቸው ውስጥ ጠብቀው በማቆየታቸው አስገራሚ እንደሆኑ የተለያዩ ሚዲያዎች ገልፀዋል። ለምሣሌ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ሣይኖር በኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛው ባሕላዊ ምግብ ሆኖ መቆየቱ አስገራሚ ነው ይሉታል።

 

ጤፍ ለጤና ተስማሚ፤ ከብዙ በሽታዎች የሚከላከል፤ የሰው ልጅ ጠባቂ እንደሆነም የስነ-ምግብ አጥኚዎች ይገልፃሉ። እንዲሁም ብለውታል፡-

Teff is a cereal first grown in Ethiopia 5000 years ago. It is rich in fiber carbohydrates and minerals (calcium, iron and magnesium). It is highly appreciated by sports practitioners for its properties in helping to restore energy levels.

 

ይህን የፃፈው ጤፍን እንደ ጁስ፤ እንደ ወተት አሽጐ የሚሸጠው ኩባንያ ነው። ጤፍ የዛሬ አምስት ሺ አመታት በኢትዮጵያ እንደበቀለ፤ በፋይበር ንጥረ ነገር የበለፀገ፤ በሀይል ሰጭ እና በሚኒራል የበለፀገ፤ ካልሲየም፣ አይረን እና ማግኒዚየምን የያዘ ምግብ መሆኑን ይገልፃል። በተለይ ለስፖርተኞች ከፍተኛ ሀይል ሰጭ ምግብ መሆኑን ኩባንያው ይመክራል። እንግዲህ ጤፍ ቀን ወጥቶለታል ማለት ይቻላል።

 

ዛሬ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ከተሞች ፓን ኬኮች እና በርገሮች በጤፍ መሠራት፤ መበላት ጀምረዋል። ሚዲያዎቹ የኢትዮጵያ ጤፍ በመጪዎቹ ጥቂት አመታት ዋናው ተፈላጊ ምግብ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ፅፈዋል፡-

 

እኛ ምን እያደረግን ነው? የጤፍን ምርት እያሣደግን ነው? ትኩረት ሰጥተነው የወደፊቱ የሐገሪቷ ዋነኛው የኤክስፖርት ምርት ለማድረግ እየሠራን ነው? ለመሆኑ ግብርና ሚኒስቴር እና መንግሥትስ ስለ ጤፍ አጀንዳቸው ነው? እስካሁን ባየሁትና በታዘብኩት ነገር መጽሐፉም ዝም ቄሱም ዝም ብለዋል። ነገር ግን እንደ በቀለች ቶላ አይነት ወኔያም እና የሐገር ተቆርቋሪዎች ስለ ጤፍ ብዙ እያስተማሩን ነው።

 

በቀለች ቶላ ከዚህ ቀደም በ2004 ዓ.ም በእንግሊዝኛ ቋንቋ Injera Variety From Crop Diversity  ብላ ስለ ጤፍ እንጀራ መፅሃፍ አሣትማለች።

በአማርኛ ቋንቋ ደግሞ በአይነት እንጀራ የሚል መፅሐፍ ስለ ጤፍ እንጀራ መጽሃፍ አሣትማ አስነብባናለች።

 

ከዚሀ ሌላ ስለ ዕፅዋት ለሕፃናት እና ለታዳጊዎች ብላ መፅሃፍ ለልጆች አሣተመች። ቀደም ብላም ለኢትዮጵያ ገበሬዎች በማሰብና በመቆርቆር ለእንሰሣት እንክብካቤ የተሰኘ መጽሐፍ አሣትማለች። በየሰው ቤት መጥፋት የሌለበትንም ሕክምና በቤታችን፡- የቤት ውስጥ ባሕላዊ ሕክምና በተፈጥሮ መጽሃኒት ብላ ግሩም የሆነ መጽሐፍ አሣትማለች።

 

እንደ በቀለች ቶላ አይነት ለወገን ለሐገር ተብሎ የሚፈጠሩ ሰዎች አሉ። እሷ የተፈጠረችው ለሀገር ነው። እናም ዛሬ ደግሞ ጤፍ የኛ በረካ ከአጃቢዎቹ ጋር ብላ መፅሃፍ ይዛልን መጥታለች። እውነትም በረካ።

 

በባሕላችን እንጀራ ይስጥሽ፤ እንጀራሽ ከፍ ይበል፤ እንጀራ ይውጣልሽ፤ እንጀራሽ ይለምልም እየተባለ ይመረቃል። ሕፃን ልጅ ተወልዶ ክርስትና ተነስቶ ሲመጣ እንጀራ ተዘርግቶ እሱ ላይ ይንከባለላል። እንጀራው የተቀና፤ ሕይወቱ የለመለመ እንዲሆን ነው። እናም በቀለች ቶላ ያ እንጀራ የሚሠራበትን ጤፍ እንዲህ ነው ብላ ልታሣውቀን ይህን መፅሃፍ አዘጋጀችው።

 

በበቀለች ቶላ መጽሐፍ ውስጥ ከምናገኛቸው ቁም ነገሮች መካከል ጤፍ ለአውሮፓ ምግቦች እንዴት እየዋለ እንዳለ የምትገልፅበት መንገድ ነው። እንደ እርሷ ገለፃ የጤፍ ዱቄት ብቻውን ወይም እንደ አስፈላጊነቱ ከሌላ ዱቄት ጋር ተቀይጦ ለፒዛ፣ ለፒታ፣ ለፖን ኬክለኬ፣ ለመኮረኒ፣ ስፓጌቲ፣ ቴላቴሊ፣ ኖዱልስ፣ ላዛኛ እና ለሌሎችም ይሆናል ትላለች። ስታብራራም እጅግ የተወደዱት የአውሮፓ ምግቦች ፓስታ እና ማካሮኒን ትጠቅሣለች። እነዚህ ምግቦች አሠራራቸው የተለመደው ከስንዴ ነው። ፓስታን ወይም የማካሮኒ ዱቄትን ለማዘጋጀት ብዙ አማራጮች መኖራቸውን በማስታወስ በሚከተለው መልኩ አዘገጃጀቱን ፅፈዋለች።

·         የጤፍ ዱቄት ከስንዴ ዱቄት ጋር አመጣጥኖ ማዘጋጀት

·         የጤፍ ዱቄት ከአጃ ዱቄት ጋር አመጣጥኖ ማዘጋጀት

·         የጤፍን ዱቄት ከጠይሙ አጃ ጋር ትሪቲካሌ ዱቄት ጋር ማመጣጠን'

·         ጤፍን ከበክዊት ጋር በእኩል መጠን ቀይጦ አንድነት ማስፈጨት። /በክዊት የተክል አይነት ነው።/

እንደ በቀለች ገለፃ፤ ጤፍን እና በክዊት የተባለውን ተክል አብሮ በመቀላቀል ፓስታ እና ማካሮኒን የመሣሠሉ ምግቦችን አያሌ ጥቅሞች ባሉት በጤፍ መተካት እንደተቻለ ታብራራለች።

 

የጤፍ ምጥን ፍሌክስ Flakes

በበቀለች መጽሐፍ ውስጥ ከምናገኛቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ስለ ፍሌክስ ነው። ፍሌክስ ለምሣሌ የተለመደው የበቆሎ ፍሌክሰ Corn Flakes ነው። ፍሌክስ በስሎ ያለቀለት ስለሆነ ማብሰል ሳያስፈልግ ወተት ወይም ሻይ በላዩ ላይ በማፍሰስ የሚበላ ነው። በቀለች ስትገልፅ ስነ-ምግቡም የተሻሻለ እና ተስማሚ የሆነ ፍሌክስ ለማዘጋጀት ጤፍ፣ አጃ እና በቆሎ በእኩል መጠን አመጣጥኖ ማዘጋጀት ይቻላል ትላለች።

ለምሳሌ፣ በቤት ውስጥ ለማዘጋጀት እንኳን ይቻላል ብላለች። ይህም በሚከተለው መልኩ ነው።

·         ጤፍን በሸክላ ምጣድ አብስሎ ማመስ

·         በቆሎውን ለ48 ሰዓት መዘፍዘፍና፣ ለ36 ሰዓት ማጐንቆል፣ መቀቀል፣ ማድረቅ፣

·         አጃን ለ10 ሰዓት መዘፍዘፍ፣ ለ12 ሰዓት ማጐንቆል፣ መቀቀል፣ ማድረቅ፣

ሁሉንም ቀይጦ ማስፈጨት። ይህ የበሰለ ዱቄት ነው። ይህንን ዱቄት በስሱ በውሃ በማቅጠን በሚመች ቅርፅ ማውጫ አውጥቶ በፀሐይ ሙቅት ማድረቅ። ይህ የጤፍ ምጥን ፍሌክስ ምንም ስኳር ሣይደረግበት ጣፋጭ ይሆናል። ከውጭ ሀገር የሚገቡት የፍሌክስ አይነቶች በውድ ዋጋ እንደሚሸጡ የታወቀ ነው። የተመጣጠነ የጤፍ ፍሌክስ ፋብሪካን ማቋቋም እንዴት ያለ ጥቅም ሊያስገኝ እንደሚችል አርቃችሁ ገምቱ ትለናለች ደራሲዋ በቀለች ቶላ ጤፍ የኛ በረካ በተሰኘው መፅሐፍዋ

 

የጤፍ ዱቄት ለኬክ ስራ

በቀለች ስትፅፍ፤ ኬኮች በብዙ አይነት ይጋገራሉ ትላለች። የኬክ ባልትና በሁሉም የኢትዮጵያ ትልልቅ ከተሞች ሞልቶ መትረፉንም ታስታውሠናለች። ሆኖም ኬኮች ሁሉ የሚጋገሩት በተለምዶ በዋናነት ፉርኖ ዱቄት የሚባለው ከፋብሪካ የተገኘ የስንዴ ውጤት እና የተለያዩ ቅመሞች፣ ወተት፣ እንቁላል፣ በአንድነት ተደርጐ ነው። ነገር ግን ኬክ፣ ፓንኬክ፣ ማፈን፣ ዋፍልስ፣ ብስኩት፣ ፒዛ፣ እና ሌሎችንም ከጤፍ ዱቄት ወይም ጤፍ ከፉርኖ ዱቄት ጋር ተመጥኖ ማዘጋጀት ይቻላል ትላለች። ለማዘጋጀትም የተመጠነውን ጤፍ እንዴት መጠቀም እንዳለብን በሚከተለው መልኩ አስቀምጣዋለች።

·         ጤፍ ከሩዝ ጋር በእኩል መጠን ተቀይጦ፤/1፡1/

·         ጤፍ ከአጃ ጋር ተመጣጥኖ ተፈጭቶ /2፡1/

·         ጤፍ እና አማራንተስ ቀይጦ ማስፈጨት፤/3፡1/

·         ጤፍ እና በክዊት የተባለውን ተክል በእኩል መጠን ማስፈጨት፤/1፡1/

እንደሚገባ ትገልፃለች። እናም ጤፍ የኛ በረካ ወደ ዘመናዊ የሰው ልጅ የአመጋገብና የአጠቃቀም ምዕራፍ ውስጥ እየገባ መሆኑን ከበቀለች መጽሐፍ ውስጥ መረዳት እንችላለን።

 

እንጀራ ለጤፍ ተስማሚ እንዲሆን

እንጀራን እንደ ሰው ፍላጐት እና ጤንነት ተስማሚ አድርጐ መጋገር እንደሚቻልም በመጽሐፏ ውስጥ ተገልፆአል። ለምሣሌ ለጤናው በብረት እና ካልሲየም ማዕድን የዳበረ ምግብ ያስፈልግሃል የተባለ ሰው ከፍተኛ ካልሲየምና የብረት ምጥን እንዲኖረው ሰርገኛ ወይም ቀይ ጤፍ ላይ ቀይ ዳጉሣ፣ አማራንተስ /ካቲላ/' ሽንብራ፣ አኩሪ አተር፣ ካሳቫ፣ ተመጣጥኖ የተጋገረ ምጥን እንጀራ ቢያገኝ ይሻለዋል በማለት ሙያዊ ምክሯን ትለግሣለች ።

 

በብረት እና ካልሲየም ማዕድን የዳበረ ምግብ እንድትበላ የተባለ ሰው ዝቅተኛ የካልሲየምና ዝቅተኛ የብረት ምጥን ህላዊ እንዲኖረው በሩዝ ላይ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ገብስ ወይም ጐደሬ ተመጣጥኖ የተጋገረ ምጥን እንጀራ ቢያገኝ ይሻለዋል ትላለች ደራሲዋ።

 

የተሻለ ካልሲየም ኖሮት ነገር ገን ብረቱ ዝቅተኛ እንዲሆን ያስፈለገ እንደሆነ ነጭ ጤፍ ላይ የጐደሬን ሥር ድርቆሽ ወይም የደረቀ ቆጮ መጣጥኖ ማዘጋጀት እንደሚረዳም ትገልፃለች።

 

አነባበሮ ወይም እንጀራው ከፍ ያለ ኘሮቲን እንዲኖረው ጤፍ ላይ ጥቁር ስንዴን፣ አኩሪ አተር፣ ሽንብራ ወይም ካቲላን አመጣጥኖ መጨመር።

 

አነባበሮ ወይም እንጀራው ዝቅተኛ ኘሮቲን እንዲኖረው ነጭ ጤፍ ላይ ሩዝ፣ በቆሎ ወይም ማሽላ መጨመር፣ ከቶም ጥራጥሬ መተው ነው። የጨጓራ ሕመም ያለበት ሰው አንድ ለሊት ተቦክቶ የተጋገረ የበቆሎ እንጀራ እንደሚስማማውም በቀለች ቶላ ትገልፃለች።

 

በሌላ መልኩ ደግሞ ብዙም ያልተነገረለት የጤፍ ችግርና ቀውስ ስለሚያመጣም ጉዳይ በቀለች ፅፋለች። ለምሣሌ ጤፍ በአለም የተደነቀበት በማዕድን ይዞታው ጭምር ነው። በብረት፣ በካልሲየም እና በሌሎችም ማዕድናቱ ሀብታምነት ነው። በአገራችን ኢትዮጵያም የከተማ ነዋሪዎች በስፋት የሚመገቡት የጤፍ እንጀራን ነው። ታዲያ ለምንድን ነው ብዙ ሰዎች በአጥንት መሣሣት (ኦስቶኘሮሲስ Osteoporosis) የሚጐዱት? በማለት በቀለች ቶላ ትጠይቃለች። ምክንያቱ ምን ይሆን? እንጀራ እየተመገብን በላዩ ላይ ምን ጨምረን እየበላን ነው? ምን ጨምረን እየጠጣን ነው? የጤፍን ንጥረ ምግብ ጠቀሜታ ከጥቅም ውጭ ያደረግነው ምን ጨምረን ነው? ይህ ነው ትልቅ አገራዊ ጥናት የሚያስፈልገው ነው ትላለች በቀለች ቶላ። ስታብራራም፡-

 

ኒውትሪሽናል ሂሊንግ ከተባለ መፅሐፍ ካነበብኩት አንድ ምሣሌ እነሆ ትላለች። ሻይ እና ቡና ሰውነት የካልሲየም ማዕድን ወደ ሰውነት እንዳይሰርግ/እንዳይወሰድ/ ያግዳሉ ይላል። በዚህ መሰረት የምንመገበው የጤፍ እንጀራ የቱንም ያህል በማዕድን የበለፀገ ቢሆን እኛው በላዩ ላይ በምንጠጣው ሻይ እና ቡና ምክንያት አይጠጋንም ማለት ነው ስትል አዲስ አተያይ አምጥታለች ደራሲዋ። ለአጥንት መሣሣት እራሣችንን ያጋለጥነው በተመገብነው እንጀራ ላይ ስንትና ስንት ሲኒ ቡና ወይም ሻይ መጠጣታችን አንዱ ነው ማለት ይቻላል በማለት ደራሲዋ በቀለች ቶላ ለበርካታ ጊዚያት ልዩ ልዩ ጉዳዮችን መርምራ የደረሰችበት ውጤት ያሣያል። በዚህ ዘመን እንደ ማወቅ፣ እንደ መራቀቅ፣ አድርገነው በቁርስ፣ በምሣ እና በእራት ላይ ቡና ሻይ--ሌላም ጠቃሚ ያልሆኑ መጠጦች ምግቦች የጉዳታችን ምንጮች እንደሆኑ በቀለች ቶላ ትጠቁመናለች። አቤት እግዚኦ! ስለ ጤና ስትሉ! ለቡና እና ሻይ ሰዓት አብጁለት፤ ከምግብ ሰዓት ቢያንስ እስከ 4 ሰዓት ራቅ አድርጉት ብላ ትመክረናለች።

በሌላ መልኩ ደግሞ ይኸው በማዕድናት የበለፀገ ነው የምንለው ጤፍ የበለጠ ጠቃሚ እንዲሆን ከሌሎች ሰብሎች ጋር ተቀላቅሎ ለምግብነት ቢቀርብ የበለጠ ጠቀሜታው እንደሚጐላ ደራሲዋ ትገልፃለች። ጤፍን ከበቆሎ፣ ከሩዝ፣ ከማሽላ፣ ከዳጉሣ ወዘተ ጋር መቀላቀል ጥቅሙን ከፍ ያደርገዋል ብላ ፅፋለች። በተለይ ከዳጉሣ ጋር! የዳጉሣን ጥቅም ከዚህ ቀደም ሰምተነው ወይም አንብበነው በማናውቀው ሁኔታ በቀለች እንዲህ ትገልፀዋለች።

 

ዳጉሳ/የእህል አውራ/፤ በወይና ደጋ እና እርጥበት ቆላማ ማሽላ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ይበቅላል። በአንድ የምርት ወቅት የሚዘመር የእህል ዘር ሲሆን አበቃቀሉ የአክርማ ሣር ይመስላል ትላለች። የሚያፈራው አናቱ ላይ እንደ ጣት በተዘረጉት መስመሮቸ ውስጥ ነው። ዳጉሣ ነጭ፣ ቀይ፣ ቀይ-ቡኒ እና ጥቁር ወይም ቀይ እና ነጭ ቅይጥ አይነትዎች አሉት። ነጩ በገበያ ላይ በብዛት አይገኝም። ነጩ ምናልባትም የሚገኘው በሰሜን ጐንደር አዲአርቃ ወረዳ ውስጥ፤ በትግራይ ቆላማ አካባቢዎች እና በባሕርዳር ዙሪያ ይሆናል። ቀዩ ወይም ቀይ ቡኒው በጐጃም፣ በወለጋ በቅርቡ ደግሞ በሻሸመኔ ዙሪያ በብዛት ይገኛል።

ዳጉሣ በኢትዮጵያ ትኩረት ያልተሰጠው ለጠላ መጠጥ ብቻ የተተወ ነው። ነገር ግን ከዚህ ወደ ህንድ የተወሰደው ዳጉሣ እንዴት ያለ አልሚ ምግብ ይሠራበታል በማለት በቀለች ታስቆጨናለች። ቫንደና ሼቫ/ታዋቂዋ ሕንዳዊት የኦልተርኔት ኖቤል ባለሎሬት/አንድ ቀን አዲስ አበባ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሸ ባደረገችው ንግግሯ ውስጥ እንዲህ ብላ ነበር፡- “ዳጉሣን ከናንተ አገር ቅድመ-አያቶቻችን ወደ ሕንድ አመጡት። እጅግ የተወደደ ምግብ ይሠራበታል። እናንተ ግን አባት አልባ እህል አደረጋችሁት---” አለች። መቼም ያን እለት ንግግሯን ለመስማት እዚያ የነበረው ሰው ትዝ ይለዋል። ከነምልክቱ ለምን እና እንዴት እንደሆነ ባላውቅም የዚያን እለት እሷ ንግግር እያደረገች ሣለ አንድ ትልቅ ድመት ከጣሪያ ላይ ከመድረኩ ፊት ተምዘግዝጐ ወደቀ። እኔ ደንግጨ ከምፅፍበት ቀና ስል ድመቱ በፍጥነት ተነስቶ ከመድረክ ኋላ ገባ። ቫንዳና ከቶም ንግግሯን አላቆረጠችም ነበር በማለት በቀለች ታስታውሣለች። ጉዳዩ ትልቅ ነው። ጉዳዩ ከኢትዮጵያ ሔዳ ሕንድን በምግብ ንጥረ ነገር ስላበለፀጋት ዳጉሣ ነው።

 

ዳጉሣ ድርቅን በእጅጉ መቋቋም ይችላል ትላለች በቀለች። በ2007 ዓ.ም በተከሰተው የዝናብ እጥረት ሌሎች ሰብሎች ተበላሽተው ሣለ ዳጉሣ ልምላሜውን እንደጠበቀ መቆየቱንም ታስታውሣለች። ለምሣሌ በነሃሴ ወር መጨረሻ ላይ በሻሸመኔ ዙሪያ ባሉት ቆላማ ወረዳዎች ውስጥ የነበረው የዳጉሣ ልምላሜ ልዩ እንደነበር ትገልፃለች።

 

ዱጉሣ እጅግ ጠቃሚ ምግብ መሆኑን ታሣስበናለች። የያዘው የካልሲየም እና ብረት ማዕድን ከጤፍ በእጅጉ ይበልጣል ትላለች። ጤፍ በካልሲየም እና ብረት የበለፀገ ነው የሚሉት የዳጉሣን ይዘት ባለማወቃቸው ነው። በአገራችንም ሆነ በአለም ደረጃ እውቅና የሚገኝበት ዘመን ሩቅ አይሆንም በማለት የመፅሃፉ አዘጋጅ በቀለች ቶላ ትገልፃለች።

 

ጤፍ ከሌሎችም ሰብሎች ጋር ተቀላቅሎ እንዴት ለጤና ተስማሚ እንደሚሆን የበቀለች መጽሐፍ ያስረዳናል። መፅሐፏ ስለ ጤፍ እና ተጓዳኝ ንጥረ ነገሮቹ ሰፊ እውቀት ከማስጨበጡም በተጨማሪ ሁላችንም ስለ ራሣችን ስለ ሀገራችን ስለ ታሪካችንም ማወቅ የሚገቡንን ጉዳዮች ሰብሰብ አድርጐ የያዘ ነው።

 

ደራሲዋ በቀለች ቶላ የጤፍን ሃያልነት እና ጠቀሜታን ብቻም አይደለም የፃፈችው። በጤፍ ጉዳይ ላይ ጐልተው የታዩ የሚታዩ ችግሮችንም ገልፃለች። እነዚህን ችግሮች በሰባት ክፍሎች ዘርዝራ ፅፋለች፡-

 

አንደኛ፡- ዛሬም ቢሆን ጤፍ የሚታረሰው፣ በሚዘራው፣ የሚታጨደው እና የሚወቃው እጅግ አድካሚ       በሆነ አሠራር ነው። ይህ የገበሬውን ቤተሰብ አባላት ድካምና እንግልት እጅግ ያበዘዋል። እንዲሁም የቤት እንስሣትን በእርሻ  እና በውቅያ የሚያሰቃይ ሂደት አለው።

 

ሁለተኛ፡- ጤፍ በዋናነት ለእርሻ ይውላል። አብዛኛው የኢትዮጵያ ከተማ ነዋሪዎች ያለ ጤፍ ሌላው ሰብል እንጀራ የሚሆን አይመስላቸውም። እንጀራ ዱቄት ከጤፍ ሌላ በብዙ አማራጭ በብዙ   መጠን ተመርቶ መቅረብ ነበረበት። የእንጀራ ምጣድ እና የእንጀራ ጋገራ ቴክኖሎጂ እራሱ ብዙ መሻሻል ይቀረዋል።

 

ሦስተኛ፡- የጤፍ ምርት እና ምርታማነት የሚፈለገውን ያህል አልተሻሻለም። እኛ ባለንበት ስንረግጥ ሌሎች ሀገራት ከእኛ በበለጠ ምረታማነትን አሻሽለው አምርተው ተጠቃሚ ሆነዋል።

 

አራተኛ፡- ለጤፍ እርሻ፣ ለጤፍ ዘር በመስመር መዝሪያ ለማረሚያ የተሻሻለ የእጅ መሣሪያ ወይም ማሽን የለም። ለማጨዳ፣ ለመውቂያ፣ ለማበጠሪያ የተሻሻለ ነገር የለም። ያው ድሮ የነበረው ነው። በሌሎች አገራት ለጤፍ አመራረት እና ለጤፍ ምግብ አሠራር ብዙ እደ ጥበባት ሥራ ላይ ውለዋል። በእኛ ዘንድ አይታወቅም።

 

አምስተኛ፡- ጤፍ በጣም ከፍተኛ ዋጋ የሚገኝበት የአለም ሰብል/ምግብ/ሆኗል። እኛ ወደ ገበያው ለመግባት ገና ብዙ ይቀረናል።

 

ስድስተኛ፡- ጤፍ ላይ ሰፊ ትምህርት አይሰጥም። ገበሬውን ያካተተ የጐሉ ጥናቶች አልተደረጉም።

ሰባተኛ፡- ጤፍን ለአገሪቱ ገፅታ ግንባታ በደንብ አልተጠቀምንበትም ትላለች በቀለች ቶላ

በቀለች ቶሎ እነዚህን በጤፍ ላይ የጐሉ ችግሮችንም ለመቅረፍ ምን ይደረግ ብላ የመፍትሔ ሃሣቦችን ሠንዝራለች።

 

ከነዚህ መፍትሔዎች መካከል አድካሚ የእርሻ ስራን በአዲስ እና በተሻሻለ አሠራር መቀየር እንዳለበት ትጠቁማለች። ይህም አስተራረስን የሚያቃልል ቴክኖሎጂ፤ በመስመር መዝራትን የሚያፋጥን ማሽን፤ አረምን የሚያቀል ዘዴ፤ አጨዳን፣ ውቅያን፣ ብጠራን የሚያቃልሉ ቴክኖሎጂዎቸ፤ ጤፍን በበልግ ዝናብ በመስኖ አመቱን ሙሉ እና በስፋት መዝራትን ያካተተ ስራ በትጋት መስራት እንደሆነ ትጠቁማለች። በሌላ መልኩም የጤፍ ምርታችንን አሻሽለን በአለም ገበያ ተሣታፊ መሆን የሚያስችል ሥራ ተግቶ መጀመር እንደሚያስፈልግም ትገልፃለች፡ በውጭ ሀገራት የዳበሩ የጤፍ አመራረትን ለእኛ ሀገር በሚያመች መንገድ መጠቀም ሌላው አማራጭ መሆኑንም ትጠቁማለች። ከዚህ ሌላ ጤፍ የኢትዮጵያ ልዩ መለያ ስለሆነ በአለም አቀፍ መድረኮች በሰፊው ማስተዋወቅ እንደሚገባ ደራሲዋ በቀለቸ ቶላ አፅንኦት ሰጥታ ትገልፃለች።n

 

ክፍል ሁለት

በጥበቡ በለጠ

ታላቁ ደራሲ ዲፕሎማት እና አርበኛ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ የዛሬ 14 አመታት ግድም ዘለዓለማዊት ነፃና አንድ ኢትዮጵያ በሚል ርዕስ የፃፉትን ፅሁፍ ማቅረባችን ይታወሣል። በዚያ ፅሁፍ ውስጥ ኢትዮጵያ መንግስት ከመሰረተችበት ዘመን አንስቶ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረሰ ያሣለፈቻቸውን ውጣ ውረዶች ከሚጣፍጠው ብዕራቸው አንብበናል። ዛሬ ደግሞ የዚያው ፅሁፍ ቀጣይ የሆነው መጣጥፋቸው ኢትዮጵያ ከአፄ ኃይለሥላሴ በሁዋላ ምን እንደገጠማት ያሳዩናል። ከአፄ ኃይለሥላሴ በኋላ ደርግ እና ኢሕአዴግ መጥተዋል። ደራሲ ሀዲስ እነዚህን ስርአቶች እንዴት ተመለከቷቸው? ምን ታዘቡ?  ምን ተሰማቸው? ጽሁፉን ስናነብ ብዙ ጉዳዮችን እናገኛለን።

 

ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የአለም አቀፍ ሕግ ያጠኑት ታላቁ ደራስያችን ሀዲስ ዓለማየሁ፤ ኢትዮጵያን በበርካታ ጉዳዮች አገልግለው ያለፉ የምን ግዜም ባለውለተኛ ናቸው። ተዝቆ በማያልቀው የዕውቀት የሥራ እና የእድሜ ተሞክሯቸው የታዘቡትን ኢትዮጵያ ከአፄ ኃይለሥላሴ በሁዋላ ምን እንደሆነች እንዲህ ፅፈዋል።

 

ኢትዮጵያ ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በኋላ

ከሀዲስ ዓለማየሁ

ወታደሩ የመንግሥቱን ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ አሥራ ሰባት አመት ሙሉ በኢትዮጵያ የደረሰው ችግርና መከራ በረዥም ታሪክዋ ደርሶ የማያውቅ እጅግ መራራ ነው። በዚያ አስራ ሰባት አመት በኢትዮጵያዊያን መሀከል የተነሣው የእርስ በርስ ጦርነት የብዙ ኢትዮጵዊያን ሕይወትና ንብረት ያጠፋ ከመሆኑ ሌላ እጅግ ብዙ ኢትዮጵያዊያንን ወጣቶችን የእድሜ ልክ አካለ ስንኩላን አድርጐ አስቀርቷል። በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎ ጥግ ፍለጋ ወደ ባዕዳን ሀገሮች እንዲሰደዱ አድርጓል። የተረፉትን ኢትዮጵያዊያን በድህነት አዘቅት ውስጥ ጥሎ በጠቅላላው አገሪቱን ለረሃብና ለከፋ ችግር ምሳሌ ሆና የምትጠቀስ አድርጓታል። ይህ የርስ በርስ ጦርነት ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያጠፋውን አጥፍቶ የተረፈውን ከዚህ በላይ በተመለከተው ጣእር ውስጥ የሚኖር ከመሆኑ አልፎ አሁን ከዚህ ሁሉ የባሰ ደግሞ ኢትዮጵያን ራሱዋን አንድነትዋና ህልውናዋ እንደተጠበቅ የሚኖር መሆን አለመሆኑን በሚያጠራጥር ደረጃ አድርሷታል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ወታደሩ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሮ ልማት አፋጥኖ ለማሣደግ ብዙ ሺ አመታት የሀገሪቱን ነፃነትና አንድነት ጠብቆ ያኖረውን የርስ በርስ ጦርነት ጀመረ። የዚያ የርስ በርስ ጦርነት ተፈላሚዎች ልዩ ልዩ እንደመሆናቸው ምክንያቶቹም ልዩ ልዩ ሆነው ይገኛሉ። ከነዚህ ምክንያቶቹ አንዱ፣ “ርእዮተ ዓለም” /አይዲዮሎጂ/ ሁለተኛው፣ “የስልጣን ሽሚያ” /የስልጣን ሽኩቻ/ ሦስተኛው፣ “የብሔሮች ጉዳይ” /ብሔሮች የራሳቸው እድል በራሳቸው የመወሰን መብት/ የሚሉት ናቸው።

 

ሀ. ርዕዮተ ዓለም

የወታደር ደርግና ምሁራን አማካሪዎች ሥልጣን እንደያዙ የሚመሩበት “ርዕዮተ ዓለም” መጀመሪያ፡- “የኢትዮጵያ ሕብረሰባዊነት” ሁዋላ እሱን ትተው “ኮሚኒዝም ለሕዝብ መብትና እኩልነት የቆየ ርእዮት ዓለም ነው” እየተባለ ይሰበክለት የነበረ ከመሆኑም ሌላ መስኮብና ቻይናን ባጭር ጊዜ ከእርሻ አምራችነት ወደ ፋብሪካ አምራችነት ያራመደ ነው  ይባል ስለነበር ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡት ሀገሮችና እንዲሁም በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ኑሮ ልማት ወደ ሁዋላ የቀሩት አገሮች መሪዎች የሚበዙት አገራቸውን አፋጥኖ ለማልማት የሚያስችላቸው ኮሚኒዝም መሆኑን አምነው መቀበላቸውን በማየት የኛ ምሁራንና የሱን ሃሣብ ደግፈው የቀድሞውን መንግሥት አውርደው ሥልጣን የያዙት ወታደሮች ኮሚኒዝም መመሪያቸው ያደረጉ በዚሁ ቀና መንፈስ ሊሆን ይችላል።

 

ነገር ግን እንኳንስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ወታደሮች፤ ከውጭ ሀገር ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን እየጨረሱ ተመልሰው ለደርግ አማካሪዎች ከሆኑት የኢትዮጵያ ምሁራንም በጣም የሚበዙት ስለ ኮሚኒዝም መጽሐፍ ካነበቡትና በቃል ከሰሙት ኘሮፓጋንዳ በቀር በመስኮብና በቻይና ዘለግ ላለ ጊዜ ኖረው ሕዝቦቻቸውን የሚኖሩበትን ሁኔታ የተመለከቱ አልነበሩም። ስለዚህ ኮሚኒዝም ከመሃፍና ከቃል ኘሮፖጋንዳ አልፎ በገቢር ሲተረጐም ምን እንደሚያስከትል ሳያውቁ አገራቸውን በጨለማ መንገድ መርተው በከፋ ችግር ውስጥ መጣላቸው ብርቱ በደለኞች የሚያደርጋቸው ነው። ነገር ግን እነሱ ለሰሩት በደል አሥራ ሰባት አመት ሙሉ አይቀጡ ቅጣት የተቀጣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው።

 

በመሠረቱ ኮሚኒዝምም ሆነ ወይም ሌላ ርዕዮተ ዓለም ካንድ አገር ሕዝብ እምነት ባሕልና ልማት ደረጃ ጋር የማይስማማ በመሆኑ ሕዝቡ የማይቀበለው ቢሆንና በሀይል ቢጭኑበት አገርን ወደፊት በማራመድ ፈንታ ወደ ሁዋላ መጐተትን፤ በሀብት ፈንታ ድህነትን፤ በሰላም ፈነታ ሁከትን አስከትሎ መጨረሻ ወደ ታቀደው ግብ ሊያደርስ የማይችል መሆኑ ባለንበት ጊዜ እየታየ ነው።

 

ለ. የሥልጣን ሽሚያ

ወታደሩ ራሱን ደርግ ብሎ ሰይሞ ስልጣን እንደያዘ፣ ከምሁራኑ ተከፋፍለው ከሱ ጋር ለመስራት ሲስማሙ ሌሎች፣ ወታደሩ ስልጣኑን ለሠላማዊው ክፍል/ለነሱ/ አስረክቦ ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲመለስ ጠየቁ። ነገር ግን ወታደሩ ሥልጣን የማይለቅ መሆኑን ስለታወቀና ምሁራኑንም በጥያቄያቸው ስለፀኑ፣ ይህ የሥልጣን ሽሚያ/ የስልጣን ሽኩቻ/ ባስነሣው የእርስ በርስ ጦርነት እጅግ የሚያሰቅቅ እልቂት ከደረሰ በሁዋላ፣ ወታደሩ አሸንፎ ስልጣኑን ሲያጠናክር፣ ምሁራኑ በሀገር ውስጥም፣ ወደ ውጭ ሀገርም ተበተኑ። ከዚያ፣ መጀመሪያ ደርጉን አስወግዶ የመንግሥቱን ሥልጣን ለመያዝ ከተነሱት ምሁራን መካከል ይብዛም ይነስ በቡድን በቡድን ተደራጅተው የእያንዳንዶቹ ቡድኖች አላማ፡- እነሱ እንደሚሉት ደርግን አስወግዶ ሥልጣን መያዝ ሲሆን፣ ሌሎች ቡድኖቸ አላማቸው “የብሔሮች ጉዳይ” የሚባለው መሆኑን ገለፁ።

 

ሐ. የብሔሮች ጉዳይ

“ብሔረሰቦች የራሣቸውን እድል እስከ መገንጠል ድረስ በራሣቸው የመወሰን መብት” የሚለው' ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከስልጣናቸው ከመውረዳቸው በፊት ጀምሮ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል፣ “ዘዬ” ሆኖ ሲነገር ይሰማ የነበረ ነው። እንዲህ ያለው ለአንድነትና ለሠላም ጠንቅ የሆነ ሀሣብ፣ በነፃ መንግሥታት ሕገ-መንግሥት የማይገኝ በመሆኑ፣ መሠረቱ ሲጠየቅ፣ ተማሪዎቹ “ሌኒን ብለዋል” ከማለት በቀር ሌላ ማስረጃ አያቀርቡም። ነገር ግን፣ የብሔረሰቦች የራስን እድል እስከ ነፃነት ድረስ በራስ የመወሰን መብት የታወቀ መሠረቱ ሌላ  ነው።

 

ከመጀመሪያውና ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በሁዋላ፣ ድል አድራጊዎች መንግሥታት፣ ሁለቱን የአለም ማሕበሮች/ሊግ ኦፍ ኔሽንና የተባበሩት መንግሥታት ማሕበርን/ በየተራ አቋቁመው፣ ድል የተመቱትን መንግሥታት ቅኝ ግዛቶች፣ እኒያ በሁለት ማሕበሮች በሞግዚትነት እንዲጠየቁ አደረጉ። ማሕበሮቹ በፈንታቸው፣ ከአንዳንድ መንግሥታት ጋር ስምምነት እያደረጉ የሞግዚትነቱን ተግባር ለኒያ መንግሥታት ሲያስተላልፉ፣ በስምምነቱ ውስጥ ሞግዚት፣ አስተዳዳሪዎች፣ በሞግዚት ለሚያስተዳድሯቸው ብሔረሰቦች ሊያደርጉ የሚገባቸው ተዘርዝረዋል። በዚያ ዝርዝር ውስጥ፣ ከተመለከቱት ግዴታዎች አንዱ፣ ያለማምዱዋቸውና፣ ከዚያ በሁዋላ፣ ብሔረሰቦች በራሣቸው ምርጫ፣ ሙሉ ነፃነታቸውን እንዲያገኙ ሲጠየቁ እንዲሰጡዋቸው አስተዳዳሪዎች ግዴታ ገብተዋል።

 

ስለዚህ፣ “ብሔረሰቦች የራሣቸውን እድል በራሣቸው ለመወሰን መብት አላቸው” የሚባለው፣ መሠረቱ በዚህ እንደተመለከተው፣ ቅኝ ግዛት ለነበሩት ነው እንጂ፣ ለነፃ መንግሥታት ክፍለ አገሮች አይደለም። እንዲውም፣ የተባበሩት መንግሥታት ማሕበር ቻርተር፣ አንቀፅ 78፣ የሞግዚት አስተዳዳሪዎች በሞግዚትነት ለሚያስተዳድሯቸው ብሔረሰቦች ሊያደርጉ የሚገባቸውን ከዚህ በላይ እንደተመለከተው በዝርዝር ካስታወቀ በሁዋላ፣ “ይህ ከዚህ በላይ ስለ ቅኝ ግዛቶች የተባለው፣ የተባበሩት መንግሥታት ማሕበር አባሎች ለሆኑ ነፃ መንግሥታት አገሮች አይሆንም” ይላል። ስለዚህ፣ “የነፃ መንግሥታት ክፍል የሆኑ ብሔረሰቦች የራሣቸውን እድል እስከ መገንጠል ድረስ በራሣቸው የመወሰን መብት አላቸው” የሚባለው፣ ሕጋዊ መሠረቱም፣ ተቀዳሚም የሌለው በመሆኑ፣ ተቀባይነት ሊኖረው የሚገባ አይደለም። እንዲሁም ከጥቅሙ እና ጉዳቱ ወገን ሲመለከቱት ኢትዮጵያንም ብሔረሰቦችንም ከመጉዳት በቀር፣ ማናቸውንም ስለማይጠቅም፣ በምንም መንገድ የሚቀበሉት አይደለም።

 

የብሔረሰቦች መገንጠል የሚያስከትለው

ከሁሉ በፊት በኢትዮጵያ የሚኖሩት ብሔረሰቦች ተለያይተው የራሣቸውን ነፃ መንግሥታት የሚያቋቁሙ ከሆኑ፣ በኢትዮጵያ ፈንታ፣ የኒያ ብሔረሰቦች ብዙ ትናንሽ መንግሥታቶች ይኖራሉ እንጂ “ኢትዮጵያ አትኖርም” ማለት ነው። በልዩ ልዩ ጊዜ ከየአቅጣጫው፣ መጀመሪያ በአንድነት ገብተው፣ በሁዋላ ከሀገሪቱ ነዋሪዎች ጋር ባለቤቶች ሆነው የኖሩት ብሔረሰቦች፣ በኢትዮጵያ ፈንታ ትናንሽ ነፃ መንግሥታቶቻቸውን ሲያቋቁሙ፣ እሱዋ መጐዳት ብቻ ሣይሆን ጭራሹኑ ትጠፋለች ማለት ነው። ግን እነሱም አይጠቀሙም። እኒያ ሃይላቸውን በማስተባበር በክፉ ጊዜ ከብርቱ ጠላቶች ጋር እየተጋደሉ የኢትዮጵያን ነፃነትና አንድነት አስከብረው፣ ለራሣቸው ብቻ ሣይሆን፣ ለጥቁር ህዝብ ሁሉ መኩሪያ እንድትሆን አድርገው ያኖሩ ብሔረሰቦች፣ ዛሬ ያ ክፉ ቀን አልፎ ደህና ቀን በወጣበት ጊዜ፣ እሱዋ እንድትጠፋ ማድረጉ፣ እነሱንም የሚጐዳ እንጂ የሚጠቅም አይደለም።

 

የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች አብረው እስከኖሩ ድረስ ሀብታቸውንና ኃይላቸውን እያስተባበሩ የውጭን ጠላት አሸንፈው በነፃነት እንዲኖሩ እንዲሁም፣ የሀብትና የእውቀት ሀይላቸውን በማስተባበር አገራቸውን የጋራ አልምተው፣ ድህነትን እና ሁዋላ ቀርነትን ለማሸነፍና የምቾት ኑሮ ለመኖር ይችላሉ። የየራሣቸውን ትናንሽ ነፃ መንግሥታት ያቋቋሙ እንደሆነ ግን፣ ሁሉም የተፈጥሮ ሀብት የታደሉ ባለመሆናቸው፣ ድህነትንና ሁዋላ ቀርነትን ለየብቻ ታግለው አሸንፈው፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ኑሮ በኩል የሚገጥማቸውን ችግር ለመወጣት አይችሉም። ከዚህ ሌላ፣ ምናልባትም ከዚህ የከፋ ደግሞ፣ ልዩ ልዩ ጐረቤት ብሔረሰቦች ነፃ መንግሥታቸውን ሲያቋቁሙ የሚገጥማቸውን ችግር፣ የወሰን፣ በየውስጣቸው የሚኖሩ ትናንሽ ጐሣዎች፣ የወንዝ፣ ውሃ እና ሌሎች የሚያገናኙዋቸው ነገሮች የሚያስከትሉት መዘዝ ነው። በተለይ  የወሰን ጉዳይ በጐረቤት ሀገሮች መካከል የሚያስነሣው ጥል ወደ ጦርነት መርቶ የሚያስተላልቅና መጨረሻው ምን እንደሚሆን፣ አስቀድሞ መገመት የማይቻል፣ በጣም የሚያስፈራ ነው።

 

የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ለቀው፣ የአፍሪካ ሀገሮች ነፃነታቸውን እንዳገኙ፣ የአፍሪካ መንግሥታት ያንድነት ድርጅት ሲያቋቁሙ፣ ምንም እንኳ የአውሮፖ ቅኝ ገዥ አፍሪካን ሲከፋፍሉ፣ ክፍያው የጐሣን መስመር የተከተለ ባይሆን፣ “ቅኝ ገዥዎች የተካለሉት የጐረቤት ሀገሮች ወሰን የፀና ይሆናል” የሚል መግለጫ በቻርተራቸው አግብተው የተፈራረሙ፣ የወሰን ጥል የሚያስከትለውን መዘዝ በመፍራት ነው። በሱማሌ እና በኢትዮጵያ መሀከል በወሰን ምክንያት በየጊዜው፣ የመጨረሻው ደርግ ሥልጣን እንደያዘ የተነሱት ብዙ ጦርነቶች፣ ከሁለቱም ወገን የብዙ ሰው ሕይወትና ብዙ ሃብት ከጠፋ በሁዋላ፣ ጦርነቶችን ያስነሣው የወሰን ችግር አሁንም ፍፃሜ ሣያገኝ እንደተንጠለጠለ ሆኖ፣ አንዱ ወይም ሌላው ወገን የተመቸ አጋጣሚ አግኝቶ እስኪያነሣ የሚጠብቅ ነው። ስለዚህ፣ በወሰን ምክንያት፣ በጐረቤት መንግሥታት፣ በተለይ አዲስ በሚቋቋሙ ትንንሽ መንግሥታት መሀከል የሚነሣ ጦርነት፣ ለኢኮኖሚና ለማህበራዊ ኑሮ ማሻሻል ሊውል የሚገባውን ሀብት እየበላ፣ ከሁለቱ የሚዋጉ ወገኖች ሕዝቦች የሚጨርሰውን ከጨረሰ በሁዋላ፣ የተረፉትን በድህነት አዘቅት ውስጥ የሚጥል በመሆኑ፣ በጠቅላላ ችግሩ ሊወጡት የማይቻል፣ “ሲጠጉ ገደል” ነው።

 

ዛሬ፣ በሀብት፣ በሀይልና በስልጣኔ ለየራሣቸው ገናና ታሪክ ያላቸው ታላላቅ መንግሥታት በሊቃውንታቸው አስጠንተው፣ ለየብቻ ከመኖር፣ ባንድነት መኖር የሚጠቅም መሆኑን በማመን፣ አንድ ለመሆን በሚሠሩበት ጊዜ፣ አንድ አገር አፍርሶ ብዙ ትናንሽ የጐሣ መንግሥታት ለመፍጠር ማሠብ፣ እኒያን ትናንሽ መንግሥታት ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች የሚጐዳ እንጂ የሚጠቅም አለመሆኑን፣ አሁን እዚህ እንደተመለከተው፣ የአለም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ጠበብት ያረጋገጡት ነው። ባገራችን፣ በብዙ “ስም” ለተሰየሙት ቡድኖች ግን፣ ለጊዜው የታያቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ተለያይተው የየራሣቸው ትናንሽ ነፃ መንግሥታት ቢያቋቁሙ፣ በእያንዳንዱ ትናንሽ ነፃ መንግሥታት ውስጥ በሚኖረው ሕዝብ ላይ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ችግር ሣይሆን፣ ለነሱ ለጊዜው የታያቸው፣ የነፃነትን ስም ማግኘትና፣ በዚያ ስም የስልጣን ባለቤት መሆኑ፣ ነው። የብሔረሰቦችን የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሮ ከማሻሻሉ ወገን ሲታይ ግን፣ ምን ግዜም ቢሆን፣ ለየብቻ ተነጣጥሎ ከመስራት፣ ሀብትን፣ እውቀትንና ሌላ ሀይልን ሁሉ ባንድነት አስተባብሮ መስራቱ የበለጠ የሚጠቅም መሆኑ የታወቀ ነው።

 

በብዙ “ስም” የተሰየሙትን ቡድኖች፣ የኢትዮጵያ አንድነት ፈርሶ በሱ ፈንታ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች የየራሣቸውን ነፃ መንግሥታት እንዲያቋቁሙ ከሚፈለግባቸው ምክንያቶች አንዱ ለየብሔረሰቡ የነፃነትን የክብር ስም መስጠቱ፤ ሁለተኛው እነሱ እንደሚሉት ከብሔረሰቦች መሀከል ያማራው ክፍል ሌሎችን ጨቁኖ መኖሩ ናቸው። ነገር ግን፣ ነፃነት፣ ለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች፣ ዛሬ እነዚህ ቡድኖች አግኝተው የሚሰጡት፣ አዲስ ሣይሆን፣ ባለፈው ረጅም ታሪካቸው ከጠላት ጋር እየታገሉ ይዘውት የኖሩት ነው። እርግጥ፣ አገሪቱ አንድነትዋንና ነፃነትዋን ለመጠበቅ በነበረባት ያላቋረጠ ትግል ምክንያት፣ ይህ ረዥም የነፃነት ሕይወት፣ አንድ ብሔረሰብ ከሌላው ሳይለይ፣ አማራው፣ ትግሬው፣ ኦሮሞውና ሌሎችም ሁሌ፣ የድህነትና የኃላቀርነት ኑሮ እየኖሩ ያሣለፉት ነው።

በጤና ጥበቃ፣ በትምህርት፣ በመገናኛ፣ ወይም በሌላ በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ኑሮ ልማት አማራው ከሌሎች ብሔረሰቦች የተሻለ፣ ወይም ሌሎች ብሔረሰቦች፣ ከአማራው የከፋ አገልግሎት አግኝተው አያውቁም። ስለዚህ በብዙ “ስም” የተሠየሙት ቡድኖች የሚሠጡዋቸው ምክንያቶች እውነት ካለመሆናቸው ሌላ፣ የብሔረሰቦች ነፃ መንግሥታት አቋቁሞ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚበቁ አይደሉም። ከብሔረሰቦች መካከል አንዱ ያየለ፣ ሌላው የበደለ አይደሉም እንጂ፣ መስለው ቢታዩ እንኳ፣ የሁሉም መብት በትክክል የሚጠበቅበትን መንገድ መሻት ነው እንጂ፣ ከነዚህ ብሔረሰቦች፣ ብዙዎችን በአንድነት እየተቀበለች አስተናግዳ፣ ሁዋላም ባለቤት አድርጋ የኖረችና፣ ብሔረሰቦችንም በፈንታቸው ኃይላቸውን አስተባብረው ከውጭ ጠላት ጋር እየታገሉ በነፃነት ያኖሩዋትን ታሪካዊ አገራቸውን አሁን ለማጥፋት መነሣት፣ ለዚህ አድራጐት ባለቤት በሆኑት ክፍሎች ላይ፣ በተከታታይ ትውልዶች የሚያስፈርድባቸው፣ እነሱም ሁዋላ የሚያስፀጽታቸው ይሆናል።

 

ደግሞ ከዚህ ሌላ ሊረሳ የማይገባው አቢይ ነገር፣  ከምስራቅና ከሰሜን ምስራቅ በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ሴማውያንም፣ ሁዋላ ከደቡብ ከገቡት ካማውያንም፣ መጀመሪያ ሲገቡ አገሪቱን ባዶዋን ያገኙዋት መሆናቸው፣ እስከዚያ ድረስ ኢትዮጵያን “ኢትዮጵያ” አስኝተው ያኖሩዋት የካም ነገዶች በየቦታው የነበሩባት መሆናቸው ነው። እነዚህ ከምስራቅና ከሰሜን ምስራቅ፣ እንዲሁም ከደቡብ የገቡት፣ መጀመሪያ በእንግድነት፣ ኃላ ባገሪቱ ከነበሩተ ነዋሪዎች ጋር ተዋልደውና ተዛምደው፣ ባለቤት ሆነው ነው አብረው የኖሩ። ታዲያ፣ የሚያስገርመው ደግሞ፣ ዛሬ ኢትዮጵያን አጥፍተው የየራሣቸውን ነፃ መንግሥታት መፍጠር ከሚፈልጉት የሚበዙት፣ እኒህ መጀመሪያ በእንግድነት ገብተው፣ ሁዋላ ባለቤት የሆኑት ክፍሎች ናቸው።

 

ማጠቃለያ

ከዚሀ በላይ ከ1-6 ቁጥሮች የተዘረዘሩትን ለማጠቃለልና ወደፊትም ሊደረግ የሚገባውን ለመጠቆም ያክል፣ ከዚህ የሚከተለውን ባጭሩ ተመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ጥንታዊትና በየጊዜው ከየአቅጣጫው የመጡትን ልዩ ልዩ ነገዶች እየተቀበለች፣ በውስጥዋ ከነበሩት ብሔረሰቦች ጋር እየተዋለዱና እየተዛመዱ፣ ባሉበት ሆነው እንዲኖሩ ያደረገች እንጂ ከመቶ አመት ወዲህ የተፈጠረችና፣ የሌሎችን አገር ወርራ ቅኝ ግዛት ያደረገች አየደለችም። በውስጥዋ የሚኖሩት ብሔረሰቦችም/አማራው፣ ትግሬው፣ ኦሮሞው፣ወዘተ/ ተባብረው ነፃነታቸውንና አንድነታቸውን ለመጠበቅ ከውጪ ጠላት ጋር እየታገሉ ሁሉም በድህነት፣ ወይም አንዱ ገዥ ሌላው ተገዥ ሆኖ አያውቅም። ከኢትዮጵያ ብሔረሰቦች መሀከል አማራው ገዥና ጨቁዋኝ፣ ሌሎች ተገዥዎችና ተጨቁዋኞች ሆነው የኖሩ አስመስለው የሚያወሩ፣ በኢትዮጵያዊያን መሀከል ስምምነቱ ጠፍቶ ወደ መለያየት እንዲደርሱ የሚፈልጉ ጠላቶችዋና፣ ይህን የተንኮል ወሬ፣ አምነውም ይሁን ሣያምኑ ተቀብለው፣ ለየብሔረሰቡ ነፃ መንግሥታት ገዥዎች ለመሆንና የሥልጣን መወጣጫ፣ መሣሪያ ማድረግ የሚፈልጉ የልዩ ልዩ “ቡድን” መሪዎች ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች፣ ከዚህ በላይ በቁጥር 6 እንደተመለከተው፣ በወሰንና በሌሎች የጋራቸው በሆኑ ጉዳዮች በየጊዜው በሚነሣ የርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የብዙ ሰው ሕይወትና ብዙ ሃብት በማጥፋት ፈንታ ሠላም አግኝተው፣ በተናጠል ማድረግ የማይቻለውን፣ የሀብትና የዕውቀት ኃይላቸውን በማስተባበር፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሯቸውን አልምተው፣ ከቤተሰብ ማሕበር ወደ መንደር ማሕበር፣ ከመንደር ማሕበር አልፎ ወደ አለማቀፋዊ ማሕበር በመሻገር ላይ መሆኑ ይታያል። ታዲያ በዚህ ጊዜ፣ ብሔራዊ ማሕበርን አፍርሶ ወደ መንደር ማሕበር ለመመለስ ማሰብ የታሪክን ጉዞ ወደ ኃላ ለመመለስ እንደማሰብ የሚቆጠር ይሆናል።

 

ስለዚህ፣ የኢትዮጵያ አንድነትና የብሔረሰቦችዋን ተገቢ ጥያቄ ለማስማማት፣ የመንግሥቱን ሥልጣን በሁለት ከፍሎ፣ አንደኛው የመካከለኛው መንግሥት ሥልጣን፣ በጠቅላላው፣ የኢትዮጵያ ነፃነትና አንድነት የሚጠበቅበትን፣ ብሔረሰቦች፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ኑሮ፣ እርስ በርሣቸው የሚገናኙበትና፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማሕበራዊ ኑሮ፣ ከውጭው አለም ጋር የምትገናኝበትን ሁኔታ የሚመለከት ይሆናል። የብሔረሰቦች ሥልጣን፣ በየክልላቸው ውስጥ፣ የፖለቲካን የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሯቸውን ማስተዳደርና፣ ከዚያ ማስፈፀሚያ፣ ከክልላቸው ውስጥ ግብር መሠብሰብን፣ እንዲሁም ከፈለጉ፣ በየክልላቸው ውስጥ ቋንቋቸውን፣ ባሕላቸውንና ሌላ የግል መለያቸው የሆነውን ሁሌ የመጠበቅና የማዳበር መብት ይመለከታል። የማዕከላዊውን መንግሥትና የብሔረሰቦችን ሥልጣን አከፋፈል ለመጠቆም ያክል እዚህ የተመለከተው፣ ብሔረሰቦች ሁሉ ተካፋይ የሚሆኑበት የማዕከላዊው መንግሥት ምክር ቤት በዝርዝር በሚያወጧቸው ሕጐች የሚወሰን ይሆናል።

 

የመንግሥቱ ሥልጣን በሁለት የተከፈለ መሆኑ፣ የሕዝቡን መብት የሚጠብቅና በሕግ የተወሰነ ይሁን እንጂ፣ እንዲሁ በቆየ ልማድ፣ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ፣ ብሔረሰቦች በየክልላቸው በኩል፣ የዘር መስመራቸውን ተከትለው በሚወራረሱ ገዥዎችና እነሱ በሚሾሙዋቸው መኳንንት ነበር የሚተዳደሩት። ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር የነበራቸው ግኑኙነት፣ በገዥዎቻቸው በኩል ነበር። ያሁኑ አካፋፈል ከጥንቱ የሚለየው የማዕከላዊው መንግሥትና የብሔረሰቦች መብትም፣ ግዴታም ተዘርዝሮ በሕግ የሚወሰን መሆኑ ነው። ይህ አይነት የሥልጣን አከፋፈል፣ በዘመናዊ አነጋገር፣ የፌዴሬሽን ሥርአት የሚባለው ነው። ፌዴሬሽን ሥርአት፣ የኢትዮጵያ አንድነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለብሔረሰቦች የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሮ ልማትንም ሰላምንም የሚያመጣ በመሆኑ ለሁለቱም ወገኖች የሚበጅ ነው።n


Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100
Page 5 of 16

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us