You are here:መነሻ ገፅ»ኪነ-ጥበብ
ኪነ-ጥበብ

ኪነ-ጥበብ (257)

 

 

በጥበቡ በለጠ

 

 

ይህች ምድር ብዙ አይነት ሞት አስተናግዳለች። ግን ጣፋጭ አለ ምን አይነት ሞት ነው? የሚጣፍጠው መራራ ሞት እና ጣፋጭ ሞት ልዩነታቸው ምንድን ነው?

ኢትዮጵያዊው አርበኛ እና ሰማዕት፣ ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ ሀገራቸውን ከወረራ ለመከላከል ሲዋጉ ቆይተው፣ ጦርነቱ እየገፋ መጣ። የህይወት ትንቅንቅ ውስጥ ተገባ። እርሳቸው ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን አሰቡ። ለኢትዮጵያ ሲባል፣ ለሕዝቦችዋ ሲባል፣ ሕይወትን መስጠት ሞት አይባልም። ይህ ሞት ጣፋጭ ሞት ነው አሉ። እናም ለዚህ ጣፋጭ ሞት ከፋሽስት ኢጣሊያ ጋር ተፋልመው 1929 ዓ.ም ሰማዕት ሆነዋል። ዛሬ ስለ እሳቸው ላጫውታችሁ ቀጥሎ ያለውን ጉዳይ እንደመንደርደሪያ ልጠቀምበት።

እዚሁ መዲናችን አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ጉዳዩ የተፈፀመው በአንድ እጅግ ውድ ነው በሚባልበት በግል ት/ቤት ውስጥ ነው። በት/ቤቱ ውስጥ የጥያቄና መልስ ውድድር ይካሔድ ነበር። ጠያቂው ለተረኛዋ ተጠያቂ የሚከተለውን ጥያቄ ያቀርባል፡-

አፄ ቴዎድሮስ የተሰውበት ቦታ ምን ተብሎ ይጠራል? ይላል

 

ተጠያቂዋ ማሰብ ጀመረች። ዓይኖችዋን ወደ ላይ ሰቀለቻቸውና አሠበች። ቶሎ ልትመልስ አልቻለችም። እንደገና ጠያቂውን ተመለከተችው። ቀጥላ ጥያቄው ይደገምልኝ አለች። ጥያቄው ተደገመላት።

 

አፄ ቴዎድሮስ የተሰውበት ቦታ ምን ተብሎ ይጠራል? አላት።

ልጅት ጠያቂውን ትክ ብላ ተመልክታ ጥያቄው አልገባኝም አለችው። ጠያቂውም ምኑ ነው ያልገባሽ? አላት። እርሷም--እ-- ይሔ የተሰውት የሚለው ምንድን ነው? የተሠውት ማለት ምን ማለት ነው? አለችው።

 

ጠያቂው የተሰውት ማለት መስዋዕት የሆኑበት ማለት ነው። መስዋት ደግሞ ራስን ለአንድ አላማ አሣልፎ መስጠት፣ መሞት፣ ሕይወትን መስጠት፣ በአጠቃላይ  ሞት ማለት ነው። እናም አፄ ቴዎድሮስ የሞቱበትን ቦታ ነው የተጠየቅሽው አላት።

ልጅቷም በጣም ገረማት። ደነገጠች። ግራ በገባው አኳኋን አፄ ቴዎድሮስ ሞተዋል እንዴ? መቼ ነው የሞቱት? ብላ ጥያቄውን በጥያቄ ድብልቅልቁን አወጣችው። ይህች ልጅ አፄ ቴዎድሮስ እስከ አሁን ድረስ በሕይወት ያሉ ነው የሚመስላት።

 

ጥፋቱ ማን ዘንድ ነው? የዛሬ 150 ዓመት ያለፉትን እኚህን የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ንጉሥ ልጅቱ እንዳታውቅ ያደረጋት ምንድን ነው? የትምህርት ሥርዓቱ ነው? ቤተሰቧ ነው? ማሕበረሰቡ ነው? መገናኛ ብዙሃን ናቸው? ልጅቷ ራሷ ተወልዳ አድጋ ለዚህ ጥያቄና መልስ እስከምትደርስ የት ነበረች? ኢትዮጵያ ውስጥ ነበረች? ብቻ ሁሉንም ነገሮች ማየትና መመርመር ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የእንግሊዝ የእግር ኳስ ክለቦችን ተጨዋቾች ምን በልተው እንዳደሩና የየዕለት ሕይወታቸውን የሚተነትን ትውልድ እንደ አሸን ባፈራንበት ወቅት ታላላቅ መገለጫዎች የሆኑትን ነገስታቶቻችንን ግን እየዘነጋናቸው መጥተናል። ኢትዮጵያዊነት በብዙ መልኩ እየተሸረሸረ ነው።

 

ይህን ጉዳይ ያስታወሰኝ ከሰሞኑ ለሕትመት የበቃው እና አያሌ ሕዝብ በታደመበት ሥነ-ሥርዓት ለምርቃት የበቃው የደጃዝማቸ ገብረማርይም ጋሪ ጐዳና/አባ ንጠቅ ገብሬ/ አጭር የሕይወት ታሪክ /1866-1929/ የተሰኘው መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ የታላቁን ኢትዮጵያዊ አርበኛ የደጃዝማች ገብረማርያምን ሕይወት የሚያስቃኝ ነው። በደጃዝማች ገብረማርያም ስም እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ አንድ ታዋቂ ት/ቤት አለ።

ይህም ሊሴ ገብረማርያም ይሰኛል። የተከፈተው በ1939 ዓ.ም ነው። የዚህ ት/ቤት መጠሪያ የሆኑት በ1929 ዓ.ም ከፋሽስት ኢጣሊያ ጋር በተደረገው ጦርነት ብዙ ጀብዱ ሠርተው ሕይወታቸውን ለሐገራቸው በክብር ለሰጡት ለደጃዝማች  ገብረማርያም ነው። ግን ብዙ ሠው ይሕን ታሪክ አያውቅም። እዚያም ሊሴ ገብረማርያም ት/ቤት ውስጥ የሚማሩት ተማሪዎችና አንዳንድ መምሕራንም አያውቁትም።

 

አንዱን ወጣት ት/ቤቱጋ አግኝቼው ጠየኩት

ይሕ ሊሴ ግብረማርያም የሚባለው ት/ቤት የማን ነው? አልኩት

የፈረንሣዮች ነው አለኝ።

 

መጠሪያ ስሙ ግን ሊሴ ገብረማርም ነው የሚለው። ሊሴ ገብረማርያም ማን ናቸው? አልኩት። ወጣቱም የሚከተለውን አለኝ፡-

ምናልባት ሊሴ የሚባለው ሰው አባቱ ገብረማርያም ይሆናሉ። እናም ት/ቤቱ ሊሴ የሚባለው ፈረንሣዊ የከተፈተው ይመስለኛል አለኝ።

ልጁ ምን አጠፋ? ታሪኩን ከየት ያምጣ? ማን ነገረው?

 

በመሠለኝ ማውራት ጀመረ። ብዙዎች በመሠለኝ ያወራሉ። ታሪክ ነጋሪ ጠፋ። ታሪክ አድማጭ ጠፋ። እናም ታሪክ ሰሪ ትውልድም ማየት ያዳግተዋል።

ወደ ዋናው ርዕሠ ጉዳዬ ልምጣ። የዛሬው ባለታሪካችን ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ ጐዳና ናቸው። በስማቸው አዲስ አበባ ውስጥ ሊሴ ገብረማርያም ተብሎ በ1939 ዓ.ም ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ት/ቤት ከፍተውላቸዋል። ስማቸው ሕያው ቢሆንም ታሪካቸው ብዙም አልተነገረለትም።

 

በቅርቡ ወጣቱ የታሪክ ፀሐፊ ፍፁም ወልደማርያም እና ስሜነህ በትረ ዮሐንስ በጋራ በመሆን የኚህን ኢትዮጵያዊ ጀግና የሕይወት ውጣ ውረድ የደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ ጐዳና /አባ ንጠቅ ገብሬ/ አጭር የሕይወት ታሪክ /1866-1929/ በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሣትመዋል። መጽሐፉ 206 ገፆች ያሉት ሲሆን በስምንት ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው።

 

መጽሐፉ በስማቸው በሚጠራዉ በሊሴ ገብረማርያም ት/ቤት ውስጥ ነው የተመረቀው። በዕለቱ የቀድሞው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኘሬዚደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ እና ታላቁ የኢትዮጵያ ታሪክ ፀሐፊ ኘሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እና ባለቤታቸው ሪታ ፓንክረስት እንዲሁም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማሕበር ፕሬዚደንት ልጅ ዳንኤል መስፍን እና አርበኞች በእንግድነት ታድመዋል። የሊሴ ገብረማርም ት/ቤት ምክትል ርዕሠ መምህር እና አያሌ ታዳሚያን ነበሩ። አኔም የመድረኩ መሪ ስለነበርኩ ስለ መጽሀፉ አንዳንድ ነገሮችን ላጫውታችሁ።

 

ኢትዮጵያ አፄ ቴዎድሮስ የጀመሩላትን የሥልጣኔ ዱካ እየተከተለች በአዲስ የለውጥና የአንድነት ጐዳና የምትሮጥበት ዘመን አብቅቶ፣ በምትካቸው አፄ ዮሐንስ ሲተኩ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ውስጥ፣ ወደ ጅማ በሚወስደው መንገድ ላይ፣ ከቱሉ ቦሎ ከተማ 30 ኪ.ሜ ያህል ከዋናው መንገድ ገባ ብላ በምትገኘው ስፍራ ላይ ባለችው አገምጃ ውስጥ ልዩ ስሟ ሰርቦ ኦዶ ኮሎ በምትባል ቦታ አንድ ብላቴና ወደዚህች ምድር መጣ። አቶ ጐዳና እና ወ/ሮ ሌሎ ጉቴ ለቤተሰባቸው 13ኛው ልጃቸውን የተገላገሉት በ1866 ዓ.ም ገደማ ነበር። የልጃቸውንም ስም ገሜሳ አሉት። ገሜሳ ማለት በኦሮምኛ ቋንቋ መልካም እንደ ማለት ነው። ገሜሳ ክርስትና ሲነሣ መጠሪያው ገብረ ማርያም ሆነ ይለናል መጽሀፉ። ሲቀጥልም፡-

 

ከታወቁት የሮቢ ጐሣ የባላባት ወገን የተገኙት ገብረ-ማርያም የትውልድ ሀረጋቸው በአባታቸውም ሆነ በእናታቸው በኩል የኦሮሞ ብሔር እንደሆነ በአገምጃ አካባቢ የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ።

 

ገብረማርያም የተወለዱት ብሎም የሕፃንነት እድሜያቸውን ያሣለፉት በአቀበታማው በኦዳ ኮሎ መንደር ነበር። ይህ መንደር በአካባቢው ላይ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር አመቺ ስለነበር ብላቴናው ገብረማርያም በዚያ አቀበታማ መንደር ላይ ዘወትር በወፍ በረር የሰዎችን እንቅስቃሴ ይከታተሉም እንደነበር እንዳንድ የአካባቢው ሽማግሌዎች ዛሬም ወደ ኃላ መለስ ብለው ያስታውሣሉ። ታዲያ የእዚ ጊዜው ብላቴና የሕፃንነት ጊዜቸውን ያሣለፉባቸው ሁለት የሣር ክዳን ቤቶቸ እና በከፍተኛ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በባለስልጣንነት ብቻ ሣይሆን በአገር ሽማግሌነት ፍትህ ይሰጡበት ነበር እየተባለ የሚነገርለት ትልቅ ዋርካ ዛሬም በአካባቢው ላይ ቤት ለመስራት ከነበራቸው ፅኑ ፍላጐት የተነሣ በነበራቸው የሥራ ጫና ሣይጨርሱት በጅምር የቀረ የግንብ መሠረት ዛሬም ትናንትን እያስታወሠ ተቀምጧል።

 

የቤተሰቡ የመጨረሻ ወንድ ልጅ የነበሩት ገብረ ማርያም በወጣትነት እድሜቸው የተሟላ ስብዕና እና የቤተሰብ ፍቅር እንደነበራቸው ይነገራል። ለዚህም ወላጅ አባታቸው አቶ ጋሪ ጐዳና ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ በውርስ ምክንያት በቤተሠቡ መካከል አለመግባባቶች ተከስተው ነበር። ታዲያ ይህን አለመግባባት ለመፍታት ወጣቱ ገብረ ማርያም ወንድሞቼ፣ ታላላቆቼ በመሆናችሁ የውርስ ክፍያ ውስጥ የእኔን ድርሻ ጨምራችሁ በመውሰድ በሰላም ተካፈሉ። የሚል ሀሣብ በመሠንዘራቸው የተነሣ በቤተሠቡ መካከል ተከስቶ የነበረው ችግር በሰላም ሊፈታ ችሏል። ይህንን እጅግ የሚያቀራርብ እና ቤተሰባዊ ፍቅርን የሚያለመልም አስተያየት በማቅረባቸው በቤተሰቡ ዘንድ በመልካም አርአያነት ሲታወሡ ይኖራሉ። ይህንንም ጉዳይ አስመልክቶ የወንድማቸው የአቶ ቡሊ ጋሪ ተወላጆች ዛሬም ኦዳ ኮሎን በእንግድነት ለሚጐበኟት እንግዶች ሁሉ በኩራት እንደሚናገሩ የታሪክ መጽሀፋቸው ያወሳል።

 

ወጣቱ ገብረማርያም እንደ አካባቢው ባሕልና ልማድ በቤተሠቦቻቸው እንክብካቤ በሚያድጉበት ዘመን /በ1870 ዎቹ አካባቢ መሆኑ ነው/ እነዚያ አመታት ለሸዋው ንጉሥ ምኒልክ የግዛት ማስፋፊያ ዘመቻዎችን ነድፈው ይንቀሣቀሱ የነበሩባቸው ዘመናት ነበሩ። በዚህም የተነሣ አካባቢው አልፎ አልፎ በመንግሥት ሠራተኞች እና በአካባቢው ተወላጆቸ መካከል ግጭት ይከሠት እንደነበር በታሪክ ድርሣናት ተመዝግቦ ይገኛል። የምዕራብ ሸዋም ተወላጆች በምዕራብ ኢትዮጵያ የግዛት የማስፋፋቱን ተግባር ሊፈፅም ለመጣው የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ጦር በቀላሉ እጃቸውን የሚሠጡ አልነበሩም።

 

ቀደም ሲል በዚያው በአገምጃ እና በአካባቢው የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን እና የደጃዝማች ባልቻ ሳፎን ታሪክ በዝርዝር ሊያስታውሣቸው ያልቻለ አያሌ ወጣቶችን ሕይወት የቀየረ የታሪክ አጋጣሚ የገብረማርምን ታሪክ ይቀይር ዘንድ የግድ ሆነ።

 

በአንድ ወቅት አካባቢውን ሊያስስ በመጣ የንጉሥ ምኒልክ ጦር አገምጃ ትያዛለች። በበቂ ሁኔታ ወታደራዊ መሣሪያ የታጠቀ እና ልምድ ባላቸው መሪዎች የሚመራው የመንግሥት ጦር በአካባቢው ሕብረተሰብ ላይ አሸናፊነትን ለመቀናጀት የሚቸግረው አልነበረም። ከነዚህ ዘመቻዎች በአንዱ ውስጥ ወጣቱ ገብረማርያም ፊታውራሪ ዘመንፈስ ቅዱስ በሚባል የጦር መሪ ተይዘው በቅርብ ወደተቆረቆረችው አዲስ አበባ ከተማ ይወሠዳሉ።

 

ጉዞው አዲስ አበባ ላይ አልተቋጨም። መሃል ሸዋ ቡልጋ አውራጃ ውስጥ ወደሚገኘው ወደ ኢቲሳ ተክለ ሃይማኖት ገደም ተወሰዱ። ይህ ቦታ ወጣቶች ለሚቀጥለው ኃላፊነት በታማኝነት እንዲበቁ ለማድረግ የሚቀረፁበት ሥፍራ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በቤተ ክህነት አካባቢ በመሥፈር የተዋህዶን ኃይማኖት እየተማሩ የአዕምሮ ብልፅግና እንዲያገኙ የቤተ-መንግሥት ሥርዓት ያዝም ነበር። ለዚህም ይመስላል በአሣዳሪያቸው በዘመንፈስ ቅዱስ የቅርብ ተቆጣጣሪነት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የተደረገው። በዚህም የተነሣ ማንበብና መፃፍ ብቻ ሣይሆን ጥልቀት ያለው የሃይማኖትና የኢትዮጵያ ታሪክ እውቀት ሊቀስሙ መቻላቸውን መገመት ተገቢ ይሆናል። በዚህም ጊዜ ሣይሆን አይቀርም፤ የመጀመሪያው ስማቸው የነበረው ገሜሳ ተቀይሮ በክርስትና ስማቸው ገብረማርያም በሚል ስም መጠራት የጀመሩት በማለት የህይወት ታሪካቸውን የጻፉት እነ ፍጹም ይገልጻሉ።

 

ይህ የቤተ-ክህነት ትምህርት በገብረማርያም ሙሉ የሕይወት ዘመን ውስጥ ትልቅ ቦታም እንደነበረው ከታሪካቸው መረዳት ይቻላል። ለዚህም እንደ አብነት ብንጠቅስ በመንግስት ሥራ በከፍተኛ ባለሥልጣንነት ማዕረግ ተቀጥረው ያገለግሉ በነበሩበት ዘመን ለግል ጉዳዮቻቸው ማስፈፀሚያ ይጠቀሙበት የነበረው ማሕተም ገብረማርያም ተዋሕዶ ይል እንደነበር በቃል የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙ መጽሐፉ ያስረዳል።

 

ገብረማርያም ይህንን የቤተ-መንግሥትና የቤተ-ክህነት ትምህርት ለማጠናቀቅ ኢቲሳ በነበሩበት ወቅት ስለቤተሰቦቻቸው  ሁኔታ ምንም አያውቁም ነበር። በዚህም በቤተሰቦቻቸው ዘንድ በሕይወት እንደሌሉ ታምኖ ወላጆቻቸው እና ዘመዶቻቸው እጅግ አዝነው እንደነበር አንዳንድ ሽማግሌዎች ይናገራሉ።

 

ረጅም ጊዜ የፈጀውን ትምህርታቸውንና የተላመዱትን የቤተ-ክህነተ ትምህርት አጠናቀው ወደ ትውልድ መንደራቸው ተመለሱ። የልጅነት ስማቸው ገሜሳ ጋሪን በገብረማርም ቀይረው ወደ ትውልድ መንደራቸው አገምጃ ብቅ ያሉት የጐፈር ሚካኤል የበአለ ንግሥ እለት ነበር። እናታቸው ወ/ሮ ሌሎ ጉቴ በዚህ ዕለት ጠፍቶ የነበረው ልጃቸው ስለተመለሰላቸው የአካባቢውን ማሕበረሰብ በታላቅ ደስታ እና ክብር ተቀብለው እንዳስተናገዷቸው ይነገራል።

 

ገብረማርያም የተወሠኑ ጊዜያት ያህል ከቤተሰቦቻቸው ጋር ካሣለፉ በኃላ ወደ መሐል ሸዋ በመመለስ ከዘመንፈስ ቅዱስ ጋር በመሆን የቤተ-ክህነት ትምህርታቸውን በሚገባ ተከታትለው አጠናቀቁ። በዚህን ጊዜ በልጅነት እድሜያቸው ያውቋቸው ለነበሩት ለበጅሮንድ ባልቻ ሳፎ /አባ ነፍሶ/ እንዲያገለግሉ እናታቸው በጅሮንድ ዘንድ ይወስዷቸዋል። ባልቻ ትውልዳቸው እዚያው አገምጃ ስለሆነ የአንድ አገር ሠዎቸ ናቸው። ገብረማርም ለባልቻ የተሠጡት በዚሁ ምክንያት ይሆናል ብሎ መገመት ተገቢ ነው። በጅሮንድ ባልቻም በወቅቱ የቤተ-መንግሥቱ ገንዘብ እና ግምጃ ቤት ሹም ስለነበሩ የቤተ-መንግሥቱን ሥርአት በማስተማር ታማኝ ወታደር ብቻ ሣይሆን ብቁ አስተዳዳሪም እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል ተብሎ ይገመታል።

 

ሰለ ደጃዝማች ገብረማረያም የሕይወት ታሪክ የተዘጋጀው የነ ፍፁም ወልደማርያም መጽሐፍ የታላቁን ጀግና እና ሰማዕት ኢትዮጵያዊ ታሪክ ቀደም ባለው ውብ ትረካ ይጀምራል።

 

በምኒልክ ጦር በልጅነታቸው ከትውልድ መንደራቸው ተማርከው የሄዱት ገብረማርያም በቤተ-መንግስት ስርዓት ተኮትኩተው ካደጉ በኃላ ለአቅመ አዳም ደርሠው ልክ በ22 አመታቸው በ1888 ዓ.ም የአድዋ ጦርነት ታወጀ። እርሣቸውም ለጋ ወጣት ስለነበሩ ከደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ ጦር ጋር ወደ አድዋ ዘመቱ። በአድዋ ጦርነት ላይም ከባልቻ ጐን ሆነው ታላቁን የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ድል የሆነውን ጦርነት በድል ካጠናቀቁ የዚህች ሀገር ታላላቀ ጀግኖች መካከል አንዱ ናቸው።

 

በመጽሐፉ ውስጥ ጳውሎስ ኞኞ ጆርጅ በርክሌይን ጠቅሶ The Campaign of Adowa and the Rise of Menilik (የአድዋ ዘመቻ እና የምኒልክ አነሣስ) በተሰኘው ርዕሡ ስለ አድዋ ጦርነት ሲያትት እንዲህ በማለት የምስክርነት ቃሉን አስፍሮ ነበር፡-

 

ሃያ ሺ ያህል ወታደሮች ያሉበት የኤሮፓ/አውሮፓ/ ጦር በአፍሪካ ሠዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ። በኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ በውስጥ እንደ አድዋው ያለ ጦርነት የለም። በእልቂቱ በኩል 25ሺ ሰዎች በአንድ ቀን ጀምበር የሞቱበት እና የቆሰሉበት ነው። ፖለቲካና ታሪክ አበቃ። በአፍሪካ ውስጥ ታላቅ ኃይል መነሣቱ ታወቀ። የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ። ጥቁሩ ዓለም በአውሮፓውያን ላይ ሲያምፅና ሲያሸንፍ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። አበሾች አደገኛ ሕዝቦች ስለመሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተፅፎላቸዋል። --አሁን የሁሉንም ፍላጐት አድዋ ዘጋው።

 

እንዲህ አይነት ውብ የሆኑ የአድዋን ድል ካስገኙ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ የሆኑት ደጃዝማች ገብረማርያም ከጦርነቱ በኃላ ወደ ሐገር ግንባታውና ወደ ማስተዳደሩ ስራ ገቡ።

 

አፄ ምኒልክ የአስተዳዳሪነት ሹመት ሲሰጡ ለደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ ሲዳሞን፣ ባሌን እና ሐረርጌን በቅደም ተከተል ሲሰጧቸው፣ ደጃዝማች ገብረማርም የባልቻ ምክትል ሆነው የማስተዳደር ስራ ውስጥ ገቡ። ከምኒልክ ሞት በኃላም በልጅ እያሡ ዘመነ መንግስት የውስጥ የፖለቲካ ውጥረቶች ተከስተው ስለነበር ለገብረማርም ጥሩ አልነበሩም። ኢትዮጵያም በኢያሱ በዘውዲቱ እና በተፈሪ መካከል በነበረ የፖለቲካ ሽኩቻ ስትታመስ ቆይታ ወደ በኃላ የመረጋጋት ሁኔታ ሲመጣ ግንቦት 20 ቀን 1922 ዓ.ም ገብረማርያም በደጃዝማችነት ማዕረግ የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ሆነው ተሾሙ።

 

ደጃዝማች ገብረማርም ሐረርጌን ከተረከቡ በኋላ አያሌ ቁም ነገሮችን ሠርተዋል። ሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት እጅግ ሠፊ በመሆኑ እና የኢትዮጵያም የምስራቅ ጀንበር በመሆኑ ሐገርን ከጠላት ወረራ የመጠበቅ ልዩ ልዩ ከተሞችን የማዘመን የንግድ ማዕከል በማድረግ ረገድ የአንበሣውን ድርሻ የሚወስዱት ደጃዝማች ገብረማርም ናቸው። በአሁኑ ሱማሌ ክልል ውስጥ ያሉትን ከተሞች በመመስረትና በማሣደግ ደጃዝማች ገብረማርያም ብዙ ወጥተዋል ወርደዋል፣ ዋተዋል። የምስራቅ ኢትዮጵያ ቀኝ እጅ ሆነው ኢትዮጵያን አገልግለዋል።

 

ቀጥሎም የአገር ግዛት ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ኢትዮጵያን በቅርበት እና በከፍተኛ ኃላፊነት ማገልገል ማስተዳደር የገብረማርያም መገለጫ ሆነ። ከዚያም በልዩ ልዩ ገብረሰናይ እንቅስቃሴዎች ላይ በዋናነት ተሣታፊ ነበሩ። ከ1927 ዓ.ም ጀምሮም የፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር ዝግጅት እና ትንኮሣ  ስታደርግ ሕዝብን በማደራጀት በማንቃት እና ከውጭ ሀገር የመሣሪያ ግዢ ለማከናወን በተዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ ዋነኛው ሠው ነበሩ።

 

ከዚያም ወረራው መጣ። ደጃዝማች ገብረማርያም በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ በኩል የመጣውን የፋሽስት ወራሪን በክብረመንግሥት /አዶላ/፣ ዋደራ፣ ነገሌ ቦረና፣ ተፈሪ ኬላ፣ ይርጋለም፣ ዶሎ… የመሣሠሉትን ቦታዎች ከጠላት ለማስለቀቅ ብርቱ ተጋድሎ አድርገዋል። በተለይም ከራስ ደስታ ዳምጠው ስር በመሆን ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ፣ ደጃዝማች መኮንን ወሰኔ፣ ደጃዝማች ደባይ ወልደአማኑኤል፣  ፊታውራሪ ታደሰ ነገሜ እንደነበሩ ታሪክ ፀሐፊው አቶ በሪሁን ከበደ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ታሪክ በተሠኘው መጽሐፋቸው ውስጥ ገልፀዋል።

 

እነዚህና በርካታ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ለዚህች አገር ዜጐች ክብር ሲሉ ተዋድቀዋል፣ ቆስለዋል፣ ሞተዋል። በደቡብ ኢትዮጵያ ለነበረው የኢጣሊያ ወረራ፣ ከበረሃ በረሃ እየተንከራተቱ በውሃ ጥም ጉሮሮዋቸው ደርቆ አንዱ የሌላውን ሽንት እየጠጣ ኢትዮጵያን ሲጠብቁ ኖረዋል። በተለይ ለፋሽስት ኢጣሊያ ያደሩ ባንዳዎች፣ እንደ ራስ ደስታ ዳምጠው የመሣሠሉ ታላላቅ ሰዎችን አስገድለዋል። ባንዳዎች ራስ ደስታ ዳምጠውን ተሰቃይተው እንዲሞቱ አድርገዋል።

 

ደጃዝማች ገብረማርያም በብዙ የደቡብ አውደ ውጊያዎች ከተሣተፉ በኃላ ቆሠሉ። መቁሠላቸውን ምክንያት አድርገው ከጦርነቱ አላፈገፈጉም። ይበለጥ ገፉበት። ጦርነቱን የምትጣፍጥ ሞት ይሉታል። ለሀገር እና ለሕዝብ መሞት የምትጣፍጥ ሞት ነው ይላሉ ደጃዝማች ገብረማርያም።

 

በመጨረሻም ወደ ትውልድ መንደራቸው በመምጣት ከፋሽስት ኢጣሊያ እና ከባንዳዎች ጋር ጦርነት ገጠሙ። ጦርነቱ የመጨረሻቸው እንደሆነ ገመቱ። ከዚያም የሚከተለውን ንግግር አደረጉ።

 

-    ዛሬ ሠርጌ ነው። ለውድ አገራችን ለኢትዮጵያ እና ለሰንደቅ አላማችን ግዳጄን ፈፅሜ ሕይወቴን አሣልፋለሁ። ከዚህ እልፍ አልልም። የመጨረሻ ትግሌ ዛሬ የሚጠናቀቅ ይመስለኛል። ሩጫዬን አበቃሁ። ጠላት እጄን አይጨብጥም። እንደማየው ጠላት ዙሪያችንን ከቦናል። በዛሬው ቀን በምናደርገው የሞት የሽረት ውጊያ ላይ ለመሣተፍ የማትችሉ ከአጠገቤ ለመለየት ትችላላችሁ። እኔ ቁስለኛው እግሬ ሊያራምደኝ አያስችለኝም። ውጊያው የጠነከረ መሆኑን ስታውቁ ባመቻችሁ መንገድ ሁሉ ሾልካችሁ እስከወደቃችሁ ድረስ በአገራችሁ ጉራንጉር በወንዞቻችሁ ሸለቆዎችና ዱር ግቡ። ሕያው እግዚአብሔር ይከተላችሁ።

 

ከዚህ ንግግር በኃላ ከመጀመሪያው ጀምረው በጦርነቱ ያልተለያቸውን የወንድማቸውን ልጅ ሻቃ በቀለ ወያ እና ቀኛዝማች በየነ ጉደታን መርቀው ካሠናበቱ በኃላ በተካሔደው ከፍተኛ ፍልምያ በሚያውቁት መንደር አንዱ ባንዱ ላይ እየተፈራረቀ የሚመጣውን አጥቂ ጠላት ሲያንገበግቡት ውለው ከጠላት በተተኮስ ጥይት ተመተው ወደቁ።

የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ክቡር ደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ የካቲት 18 ቀን 1929 ዓ.ም ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ክብር ሕይወታቸውን ሠጥተዋል።

 

ኢትዮጵያ ነፃ ከወጣች በኃላ በ1939 ዓ.ም ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እዚህ ቸርችል አደባባይ ላይ ተገማሽሮ የሚገኘውን የፈረንሣይ እና የኢትዮጵያን ወዳጅነት የሚገልፀውን ት/ቤት ሊሴ ገብረማርያም በማለት በሰማዕቱ አርበኛ በደጃዝማች ገብረማርያም ስም ሰየሙት። እስከ አሁንም ት/ቤቱ በርካታ ተማሪዎችን በማስተማር ለታላላቅ ቁም ነገር ያበቃ ነው።

 

በአጠቃላይ ሲታይ፣ ደራሲ ፍፁም ወልደማርያም እና ስሜነህ በትረ ዮሐንስ ያዘጋጁት የደጃዝማች ገብረማርያም ጋሪ ጐዳና /በፈረሰ ስማቸው አባ ንጠቅ ገብሬ/ አጭር የሕይወት ታሪክ /ከ1866-1929 ዓ.ም/ ውብ መጽሐፍ ነው። የሐገር እና የሕዝብ ባለውለተኞችን በሚገባ የዘከረ የታሪክ መጽሐፍ ነው። አዘጋጆቹን በጣም አደንቃቸዋለሁ። ሰማዕታቱ ላይ የተቆለለውን አፈር እያራገፉ ከአፈሩ ማዶ ያለውን ውብ ታሪኮቻቸውን አካፍለውናል። የልጅ ልጆቻቸው ዶ/ር ጀንበር ተፈራ እና አቶ ፍስሀ ተፈራ ብሎም መላው ቤተሰቦቻቸው የሰማዕቱን ታሪክ ህያው አድርገዋል።

ጥበቡ በለጠ

የዘንድሮው የብሔር ብሔረሠቦች ቀን ነገ ሐሙስ ሕዳር 29 ቀን 2009 ዓ.ም በሐረር ከተማ ይከበራል። ሐረር በምስራቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛዋ የኢትዮጵያ የንግድ፣ የኢኮኖሚ፣ የባሕል፣ የዲኘሎማሲያዊ ወዘተ አገልግሎት ስትሰጥ የቆየች ጥንታዊት ከተማ ነች። አንዳንዶች የኢትዮጵያ ፀሐይ መውጫ ይሏታል። ምስራቅ በመሆኗ መሠለኝ። ሌሎች ደግሞ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋር ያገናኟታል። ፀሐዩ ንጉሥ የሚባሉት አፄ ኃይለሥላሴ የተወለዱት ኤጀርሳ ጐሮ ሐረር ነው። ስለዚህ የፀሐይ መውጫ ናት እያሉ የፃፉም አሉ። በዘንግ የሚገዛ የኢትዮጵያ ንጉስ ከወደ ምስራቅ ይመጣል የሚባልም ትንግርት አለ። መቼ እንደሚመጣ ባይታወቅም ለብዙ ዘመን እየተጠበቀ ነው።

እናም ሐረር ታሪካዊትም ከተማ ነች። እድሜ ጠገብ የሆኑ ብዙ ታሪኮች የሚወሡባት የብዙ ብሔሮች ድብልቅ ከተማ፣ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ናት እያሉ የቀድሞ ፀሐፊዎች ብዙ ብለውላታል።

እድሜዋን ከአንድ ሺ አመት በላይ እየቆጠረች ሼህ አባድርን የዘመናዊት ሐረር መስራቿ አድርጋ እየጠራች ብዙ ስልጣኔዎችን እና ባሕሎችን እያፃፈች የኖረች እዚህች ምስራቃዊት ከተማ ላይ ትንሽ እንቆያለን።

ሐረር የከተማ ባሕል የበዙባት ናት። ብዙውን ጊዜ ባሕላዊ ድርጊቶችና ልማዶችን ከገጠር እያነሣሣን እናወጋለን። ነገር ግን ሐረር ከተማ ውስጥ የከተማ ባሕል ነው ሠፍኖ የሚገኘው። መፍቱሃ ዘከሪያ አብዱላሂ ኑር የተባለ ፀሐፊ 366 ገጽ ያለው የከተማ ባሕል መፍለቂያ ሐረር ጁገል የሚል መጽሐፍ አሣትሟል። መጽሐፉ አጠቃላይ የሐረርን ታሪክ የሚያወሣ ግሩም ሆኖ የተዘጋጀ ነው።

በመጽሐፉ እንደሚያብራራው በአፍሪካ ቀንድ በኢትዮጵያ በስተምስራቅ ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ 527 ኪ.ሜ ርቀት ላይ እንዲሁም ከዘይላ 264 ኪ.ሜ፣ ከበርበራ 336 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሐረሪዎች መናገሻ መዲና ሐረር ጌይ ትገኛለች።

በአክሱም ዘመነ መንግሥት የአዶሊስ ወደብ ከፍተኛ እውቅና የነበረው ቢሆንም በአረቦችና በአክሡማዊያን በተደረገው ውጊያ/ጦርነት/ ወደቡ ሲዳከም እውቅና ያገኘው የዘይላ ወደብ መሆኑ ይታወቃል።

የዘይላ መገኛ ቦታ ሰሜን ምዕራብ ሶማሊያ እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ከበዋት የምትገኝው ወደብ ነች። ቀይ ባሕር የኢሲያ እና አፍሪካ ሕዝቦች የሚኖሩበት ምድር የሚለይ ባሕር ነው። እነዚህ ሁለት ሕዝቦችንም የሚያገናኘው ሲዊዝ ካናል እና ባብል መንደብ የሁለቱን ሕዝቦች ከብዙ ሺ አመታት በፊት በመሐከላቸው የባሕልና የእምነት ትስስርና አንድነት ፈጥሮላቸዋል።

አዶሊስ እና በርበራ ወደብ ከግሪኮች እና ሮማዊያን ያገናኛቸው እንዲሁም በብል አልመንደብ ከሕንድ ውቂያኖስ በኩል ከፐርሺያ የባሕር ወሽመጥ አቋርጠው በአካባቢው ከሚገኙ አገሮች ጋር ከፍተኛ የንግድ ስራን ያከናውኑ ነበር። ለአገራችን ከተለያዩ አካባቢዎች ይህን የግንኙነት መስመር ይጠቀሙ እንደነበር ሔሮዱተስ በነበረበት ከ500 ከክርስቶስ ልደት በፊት የጠቀሠው ሲሆን፣ ሮማውያንም የፑንት ነገድ ብለው ይጠሯት ነበር። ፑንት ማለት ከፖርቹጊስ ግብፆች ለኢትዮጵያ የሰጧት ስያሜ እንደሆነ የታሪክ ምሁራን ይገልፃሉ በማለት መፍቱሐ ዘከሪያ ፅፏል።

በሐረር ታሪክ ላይ ከተፃፉት መጽሐፍት መካከል የእንግሊዛዊው የሰር ሪቻርድ በርተን በዋናነት ተጠቃሽ ነው። በርተን እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 3 ቀን 1855 ዓ.ም ወደ ሐረር በድብቅ የገባ ተጓዥ፣ ተመራማሪ እና ደራሲ ነው። ወደ አስር ቀናት ሐረር ውስጥ ቆይቶ First Footsteps in East Africa የተሰኘ መጽሐፍ አሣትሟል። ስለ ጀጐል ግንብ እና ስለ አጠቃላይ የሐረር ጉዳይ ለአለም በስፋት ያስተዋወቀ መፅሃፍ ደርሷል።

ከዚያም በመለጠቅ በርካታ ፀሐፊያን ሐረርን በስፋት አስተዋውቀዋል።

የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ የሆነችው ሲልቪያ ፓንክረስት እና ልጇ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በሐረር ዙሪያ በርካታ ጉዳዮችን ፅፈው አሳውቀዋል። Harar - From the Rise of the Tewodros to the Founding of Addis Ababa` ከተሰኘው መፅሐፋቸው ጀምረው፤ ምስራቃዊቷን የኢትዮጵያ ፀሐይ በሰፊው  ገልፀዋታል።

በኢትዮጵያ ታሪክ የእንግሊዝኛ አማርኛ ትልቁን መዝገበ ቃላት በማዘጋጀት የሚታወቁትና በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈው ፕሮፌሰር ዎልፍ ሌስላው የሐረሪን ሕዝቦች ታሪክ፣ ቋንቋ እና ባህል በስፋት ካጠኑ ምሁራን መካከል እርሳቸው ተጠቃሽ ናቸው። Ethymological Dictionary of Harari ከተሰኘው ጥልቅ የጥናትና ምርምር መፅሐፋቸው በተጨማሪ ሐረር ላይ ሙሉ መረጃ ኖሮን እንድናወራ የሚያደርጉ የኢትዮጵያ የቋንቋ ተመራማሪ ነበሩ።

Braukamper,u. የተባለ ተመራማሪ የሐረርን የእስልምና ሐይማኖት ታሪክ እና በውስጧ ያሉትን የማምለኪያ፣ የአድባራት፣ እና የቀብር ስፍራዎችን ሁሉ በተመለከተ ያዘጋጀው መፅሐፍ ሐረርን የበለጠ እንድናውቃት እንድንጠጋት የሚጋብዘን ነው። ደራሲው Notes on Islamicization and the Muslim shrine of the Harar plateau በሚል ሀምቡርግ ጀርመን ውስጥ እ.ኤ.አ በ1983 ዓ.ም ያሳተመው መፅሐፍ የዕውቀት አድማሳችንን ሰፋ ያደርግልናል።

ለሐረር ሕዝብ እና ባጠቃላይ ለምስራቅ ኢትዮጵያ ታሪክ ዋነኛው ተንታኝ የሆኑት ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያን የሚዘነጋ የለም። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በተለይም በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ የሚሰሩት ፕሮፌሰር አሕመድ፣ ትውልዳቸው ሐረር ከመሆኑ ጋር ከልጅነት እስከ ዕውቀት በሐረር ጉዳይ ላይ ያካበቱት ዕውቀት ከማንም ጋር የሚወዳደር አይደለም። ሐረርን ጓዳ ጎድጓዳዋን እየፈታቱ የሚተነትኑ፣ ብዙ የፃፉ፣ መረጃ የሰበሰቡ፤ ሐረር ላይ ለሚያጠና ሙሉ መረጃ የሚሰጡ ትሁት ምሁር ናቸው።

በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ አያሌ ጥናቶች ስለ ሐረር ተሰርተዋል። ጉባኤ በሚካሔድበት ወቅት በየጊዜው ሐረር ላይ የጥናትና ምርምር ጽሑፎች ይቀርባሉ። ሁሉንም መጥቀስ አልችልም። ግን በርካቶች ሐረር ላይ ጽፈዋል፣ ተፈላስፈዋል።

እነዚህ የምርምር ፅሁፎች ናቸው ሐረርን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) አማካይነት በጀጎል ግንቧ አማካይነት የአለም ሕዝብ ሁሉ ቅርስ እንድትሆን አድርገዋታል። ይሄን ተከትላ የፊልም ባለሙያዋ ኤሚ እንግዳ፣ እኔን እና ሌሎችንም በርካታ ባለሙያዎችን በማሳተፍ በ1999 ዓ.ም ለሐረር ሚሊኒየም (እስራ ምዕት) አንድ ዓለማቀፍ ዶክመንተሪ ፊልም ሐረር ላይ ሰራች። ፊልሙ Deremesheh:- Humans and Hyenas at Harar Ethiopia በአማርኛ ደርመሸህ የሰው ልጅ እና ጅብ በሐረር ኢትዮጵያ ይሰኛል። በተለያዩ ሀገራት ታይቶ ተቀባይነት አግኝቷል።

ሐረር ከዚህ ሌላም በተለይ በጅቦቿ በጣሙን ትታወቃለች። ጅብን በተመለከተም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልትመዘገብ ብዙ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው።  

ሐረር ውስጥ የአሹራ በአል ይከበራል። በዚህ በአል ላይ ጅቦች ገንፎ እንዲበሉ ይደረጋል። ጅቦች ለምን ገንፎ በሉ በሚሉትና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ሐረርን መሰረት አድርገን ዛሬ ስለ ጅቦች እንጨዋወታለን።

ጅብ ልብ የለውም ይባላል። ጉልበቱ ደግሞ አይጣል ነው። የኛ ማኅበረሰብ ደግሞ ልዩ ነው። ለዘመናት ሲተላለፍ በመጣውም አምልኮ ምክንያት ከእንስሳትና ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ምልኪያ እርግፍ አድርጐ ባለመተው ዛሬም ድረስ በተለይ ከጅብ ጋር የተሳሰረ ግንኙነት አለው።

በደቡባዊው የሀገራችን ክፍል ጅብ አይናቅም። ከጅብ ጋርም ፀብ አያስፈልግም፣ ጅብን መሳደብም ሆነ መናቅ ጥሩ አይደለም። ከእርሱ ጋር አንባጓሮ አደጋ ውስጥ ይከታል እየተባለ ይነገራል። እንግዳ ሰውም ሲመጣ ጅብን ማክበር እንዳለበት ይነገረዋል። ጭራሽ “ጐንዶሮ” በሉ ይባላል ለጅብ። “ጐንዶሮ” ማለት “ባንተ መጀን”፣ “አንተን አከብራለሁ”፣ “አንተን እወዳለሁ” እንደማለት ነው ጅብን።

አንድ ጊዜ ለሥራ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ በተለይም አለታ ወንዶ የምትባል ከተማ መዳረሻ አካባቢ ነበርኩ። እናም አንድ ጅብ መንገድ ላይ ሞቶ ተገኘ። እኔን ያስደነገጠኝና የገረመኝ ክስተት ተፈጠረ። ህዝቡ ቢላዋ ይዞ ወደ ሞተው ጅብ ዘንድ ይሯሯጣል። የጉዳዩ ሁኔታ ይበልጥ ስላስደነቀኝ እኔም ቴፔን ይዤ ጠጋ አልኩ። ህዝቡ ያንን ጠረናም እንሰሳ እየተረባረበ ይመትረዋል። ግፊያው መጯጯሁ ለጉድ ነበር። ጉዳዩ በእውነት አልገባኝም ነበር። አንድ ወጣት ከዚያ በትርምስ ከሚደበላለቀው ቦታ እጁ በደም ተነክሮ ወጣ።

“ተመስገን ጌታዬ፣ ተመስገን ጌታዬ እስከ ዛሬ ድረስ ያላገኘሁትን አገኘሁ” እያለ በደስታ ያብዳል። ምን አግኝቶ ነው ብዬ እየፈራሁ ተጠጋሁት። ወጣቱ የመለሰልኝ ከጅቡ ሆድቃ ውስጥ ሜሪኩሪ ያገኘ ያህል ነበር። ምንድን ነው አልኩት። የጅቡን ቅንድብ ወሰድኩት አለኝ። ምን ይሠራልሀል አልኩት። ሳቀብኝ። ማወቅ ፈልጌ ነው ንገረኝ አልኩት። እስከ ዛሬ አታውቅም አለኝ። ባውቅማ አልጠይቅህም ነበር ስለው “ይሄኮ በቃ በክታብ አስረከው አንገትህ ላይ ካንጠለጠልከው እንቅልፍ የሚባል ዘሩ ይጠፋል። ለእንቅልፍ መከላከያ ያገለግላል። ሌላው ሰው መተኛት ካልፈለገ ይሄን ታውሰዋለህ፣ ለቃልቻ ሁሉ በደህና ገንዘብ ትሸጠዋለህ” አለኝ።

ህዝቡ የጅቡን ሰውነት እየበለተ ተቀራመተ። ለቡዳ መድሃኒት፣ ለሌባ መከላከያ፣ ለተለያዩ በሽታዎች ፈውስ የሚያገለግሉ የጅብ የሰውነት ክፍሎች ተወስደው አለቁ። ህዝቡ ግማሹ እጁን በግርግሩ ቆርጧል። ሲተራመስ። በህይወቴ ካስገረሙኝ ክስተቶች አንዱ ሆኖ ያለፈ ድርጊት ነው።

በጣም ከደነቀኝ ሁኔታ ውስጥ ከጅቡ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ ያልተወሰደው ልቡ ብቻ ናት። ልቡ ፈሪ ናት አትጠቅምም ብለው በህሊናቸው ስላሰቡ ነው። ለመሆኑ ይሄ ባህል እንዴት መጣ? መምጣቱ ብቻ አይደለም የሚያስገርመኝ። እንዴት እስከ ዛሬ ድረስ ያሉ ወገኖቻችን እንዲህ እየተራኮቱ የሚፈፅሙት ድርጊት ሆኖ ቆየ?

ሌላ አይነት ጅብ ደግሞ አለ። ከሰው ጋር ተላምዶ ከሰው ጋር ሳይጣፋ አብሮ የሚኖር። እነዚህም ሐረር ከተማ ውስጥ የሚገኙት አያሌ ጅቦች ናቸው። የሐረር ጅቦች ደግሞ የሚገርሙ ናቸው። ጭራሽ ለዓለም ህዝብ የቱሪዝም መስህብ ተብለው የሚቀርቡ ናቸው።

የሐረር ጅቦች ከሰው አፍ ላይ መጥተው የሚጐርሱ ሰውን የማይተናኮሉ ፍፁም ለማዳዎች ናቸው። ለምን ለማዳ ሆኑ ብዬ ስጠይቅ በርካታ ምክንያቶችን ስሰማ ቆይቻለሁ። የሐረር ጅቦችን ታሪካዊ ምስጢር ዛሬ አጫውታችኋለሁ።

ሐረር ውስጥ ጅብን ስጋ የማብላት ልምድ ተጀመረ ተብሎ የሚታሰበው ገራገሩና የመጀመሪያው ምክንያት ጥንት የጀጐል ግንብ ሲገነባ ለከተማው ንፅህና ሲባል ከየቤቱ የሚጣሉ የምግብ ትራፊዎችንና ቆሻሻዎችን እንዲለቃቅሙ በግንቡ ዙሪያ ለጅቦች ማስገቢያ የሚሆን ሽንቁሮች ተሰሩ። ጅቦችም ከመሸ በኋላ ጀጐል ውስጥ በመግባት ሲለቃቅሙ አድረው ሲነጋጋ ይወጣሉ። እነዚህ ሽንቁሮች በሐረሪ “ወረባ ኑዱል” በመባል ይጠራሉ።

ሌላውና አስገራሚው ሁኔታ ደግሞ የሚከተለው ነው። ይህም የሐረር ጅብና የሐረር ሰዎች በአንድነት በዓል አክብረው የሚያሳልፉበትም አጋጣሚ አለ። ይህ በዓል “የአሹራ በዓል” በመባል ይታወቃል። በዓሉ የሚከበረው በአመት አንዴ ሲሆን፤ በበዓሉ ላይ የሐረርን ጅቦች ገንፎ የማብላት ሥነስርዓት ይካሄዳል። ይህ ወቅት በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ሲሆን ሁሉም ህዝብ እንደራሱ ልማድና ባህል አክብሮት እንደሚያሳልፍ ተነግሮኛል።

በዓሉ በዓረባዊያን የካላንደር አቆጣጠር መሠረት የአዲስ አመት መግቢያ መጀመሪያ ወር በሆነው በሙሀረም ወር ውስጥ ሲሆን በኢትዮጵያዊያን ካላንደር መሠረት ከጥር 8 እስከ 10 ድረስ ይከበራል።

በዚህ በዓል ላይ ለምን ጅቦችን ገንፎ ማብላት እንደተጀመረ የተለያዩ ታሪኮች ይነገራሉ። በክልሉ ባህል ቢሮ የሚታተመው “አቤጅ” መጽሔት እንደሚገለፀው “… በአንድ ወቅት ኃይለኛ ድርቅ ተከስቶ ነበር። በዚህ ጊዜ ጅብ ከእንስሳት አልፎ ሰውንም እየበላ አስቸገረ። ታዲያ አንዲት ሴት ይህ ሁኔታ ቢያሳስባት መላ ዘየደች። ቀደም ብላ ገንፎ ሰራራችና ጅቡን ጠበቀችው። እሱም እንደለመደው ለእራቱ የሚበላውን ሰው ፍለጋ ሲመጣ ሴትዬዋ ገንፎውን ሰጠችው። ጅቡም ገንፎውን በልቶ ወደ መጣበት ተመለሰ”

 ከዛን ጊዜ ጀምሮ ድርቁም ካለፈ በኋላ በየአመቱ ጅብን ገንፎ የማብላት ልምዱ ቀጠለ።

ከሐረር መስጊዶች በአንደኛው ውስጥ ያገኘኋቸው የሃይማኖት አባት ደግሞ እንዳወሱኝ ጉዳዩን ከእምነት ጋር ያገናኙታል። ይህም ታሪክ በኖህ መርከብ ላይ ይጀምራል። ኖህ የሰውንና የአራዊትን ዘር ከጥፋቱ ለማዳን በመርከብ ይዞ ይጓዛል። የሰው ዘርና አራዊቶች ለረጅም ጊዜ ጉዞ ያደርጋሉ። በቆይታቸውም ጊዜ የሚበሉት ነገር እየተመናመነ ይመጣል። በመጨረሻም ከሚጠጣ ውሃ በስተቀር የሚበላ ይጠፋል። በኖህ መርከብ ላይ ረሃብ ነገሰ። እናም አንዲት ሴት ብልሃት ታመጣና ገንፎ ሠርታ የሰውንና የአራዊትን ዘር ረሃባቸውን ታስታግሳለች። በዚህ ጊዜ ጅብ ብቻ ገንፎውን ሳይበላ ይቀራል። ሴትየዋ አዝና ትለማመጠውና ብረትድስት ውስጥ የቀረውን ገንፎ ጠራራርጋ አጣፍጣ ትሰጠዋለች። ከዚያም በላ። በዚህ የተነሳ ነው ጅብን ገንፎ የማብላቱ ሥነስርዓት የተጀመረው ባይ ናቸው።

ብቻ ከሁለቱ በአንዱ ምክንያት የሐረርን ጅቦች ገንፎ የማብላቱ ሥነስርዓት ይካሄዳል። ይህ እንደ አውዳአመት ሁሉ የሚከበር በዓል ነው። መጪው አመት የደስታ፣ የዕድገትና የሠላም እንዲሆን መመኘት ነው። በዚህ በዓል ላይ የተለያዩ ድርጊቶች ይፈፀማሉ።

በመጀመሪያ ከመምሸቱ ቀደም ብሎ ሁሉም ነዋሪ በየቤቱ ገንፎ ያዘጋጃል። ያንንም ገንፎ ቤተዘመድ፣ ከተጋበዙ እንግዶች ጋር ይበላል።

ከዚያ ቀጥሎ እየመሸ ሲመጣ ወጣቶችና ህፃናት ከተማውን እየዞሩ “ዊርሻኞ” የተባለውን ባህላዊ ጭፈራ ይጨፍራሉ። በየመጠጥ ቤቱና በሌሎችም ቤቶች እየገቡ ቅሎችን እየሰበሩ ያንኑ የዊርሻኞች ዘፈናቸውን ይዘፍናሉ። በመጨረሻም የቤቱ ባለቤቶች ለልጆቹ ገንፎ ይሰጧቸውና ይበላሉ። ልጆቹም የበሉበትን ቤት ጭፈራና ምርቃት እንደጨረሱ አሁንም እየጨፈሩ ወደ ሚቀጥለው ቤት ይሄዳሉ።

ቅል ሰበራው ደግሞ የሚከናወንበት ምክንያት አንዲት ሴት በወገቧ ልጅ አዝላ በአንድ እጇ ቅል አንጠልጥላ ስትሄድ መንገድ ላይ ሰዎች ያገኟታል። ወዴት እንደምትሄድ ሲጠይቋት የያዘችውን መጠጥ የሚዘጋጅበትን ቅል ለመስበር እየሄደች እንደሆነ ትነግራቸዋለች። እነሱም ለምን? ብለው ሲጠይቋት ይህ ያዘልኩት ልጅ የመጠጥ ውጤት ነው። … ልጄ ብዙ መጠጥ ጠጥቶ ሰክሮ መጥቶ እኔን እናቱን ደፈረኝ። እናም የልጄን ልጅና ወንድም አርግዤ ወለድኩ በማለት ስትነግራቸው በጣም አዘኑ። ቀጥሎም የያዘችውን ቅል በአንድነት ሰበሩት በማለት አፈታሪኩ ያስረዳል።

በዚህ ጭፈራ ላይ ወጣቶቹ

ዊርሽ ያኞው

ዊርሽ ይሰበር

ዊርሽ ያኞው

ገል ይሰበር

በማለት ያዜማሉ። ትርጉሙ የሚያሰክረው፣ የሚጠጣበት ሸክላ ይሰበር። መጪው አሹራ አመት በሠላም ያድርሰን እንደማለት ነው።

ከዚህ በኋላ ጭፈራው አብቅቶ ሁሉም ወደ ቤቱ ሲሄድ ሌሊቱን ደግሞ ጅቦችን ገንፎ የማብላት፣ በሐረሪዎች ሹር የሚባለው ሥነስርዓት ይቀጥላሉ። ይህ ሥነስርዓት በሐረሪዎች አጠራር “አዎች” ተብለው በሚጠሩት አድባራት ውስጥ ይከናወናል። አዎች ማለት በመልካም ሰብዕናቸው ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉና አርአያነት ያለው ተግባር ለፈፀሙ የሚሰጥ መጠሪያ ሲሆን በህይወት ባይኖሩም በአካባቢው እንዲታወሱ የሚደረግበት እስላማዊ ባህል ነው። ይህ መጠሪያ ለወንዶች “አዎች” ለሴቶች ደግሞ “ኢናያች” የሚል ስያሜ አለው። አዎች የሚቆምላቸው ወይም የሚገነባላቸው ግለሰቦች፡-

-    በእስላማዊ ሃይማኖት መሠረታዊ እውቀት ላስፋፉ

-    ህዝብ በማስተዳደርና በጦር አመራር ብቃት ለነበራቸው

-    ህዝቡን በመልካም የስራ ባህል ላስተባበሩና አርአያ ለሆኑ ግለሰቦች ነው። ከነዚህ ውስጥ አው አባድር አንድ የሐረሪዎች ታላቅ መንፈሣዊ ሰው ናቸው።

አዋቾች የሚታወቁበት የተለያዩ መግለጫ ወይም ምልክት ያላቸው ሲሆን ተፈጥሮአዊ በሆኑ ነገሮች ማለትም እንደ ዛፍ፣ አለት፣ ወንዝ እና የመሳሰሉት እንዲሁም በሰው በተገነባ ነገር እንደ መቃብር፣ ፀሎት ቤት ሲሆኑ ምንም ምልክት የሌላቸው አዋቾችም አሉ።

ዝግጅት የሚደረግባቸው አዋቾች ወይም አድባራት ብዛት በቋሚነት የማይታወቅ ቢሆንም ዋናዋናዎቹ አው ሐኪም፣ አው አቦከር፣ አብድልቃድር ጀይላን፣ እና አው ኑጉሥ እንደሆኑ ይነገራል። ከነዚህ ውስጥ አው ሐኪም ዋናው አዋች እንደሆኑ ይነገራል። ከነዚህ ውስጥ አው ሐኪም ዋናው አዋች ሲሆን ሐኪም ጋራ በተሰኘው ተራራ ላይ ይገኛል። በዚህ ተራራ ላይ ሆነውም ቁልቁል የሐረርን ሙሉ ገፅታ መመልከት ይችላል።

በአሚርነት ሐረርን ያስተዳደሯት አው አባድር ከሩቅ ምስራቅ በመጡበት ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ እረፍት አድርገው እንደነበረ ይነገራል። አው ሐኪምም አው አባድርን ተከትለው ከመጡት ምዕመናን መሀል አንዱ ነበሩ። በእስልምና ሃይማኖት መሠረት በሰብአዊነት መፍረድን፣ ህግ አዋቂነትን ያስተማሩ ታላቅ ሰው ነበሩ። ህዝቡም በፍትህ ጉዳይ ያማክራቸውና እርዳታቸውንም ይጠይቅ ነበር።

የአሹራ በዓል በሚከበርበት እለት ሴቶች በትልቅ ጉርድ በርሜል ገንፎ እያገነፉ ይጨፍራራሉ፤ ያዜማሉ። ወንዶች ደግሞ ጫት እየቃሙ ቁርአን በመቅራት ዱአ ያደርጋሉ፤ ወይም ይፀልያሉ።

ግን ለመሆኑ የጅብ ገንፎ መብላት በሳይንሱ እንዴት ይታያል የሚለውን ሃሳብ ስናየው፣ ጅብ የሚበላው ይሄ ነው ተብሎ የሚፈረጅ ነገር የለም። ጅብ ብዙ ነገሮችን ይበላል። ፍራፍሬዎችን ሁሉ ይመገባል። ስለዚህ ገንፎ መብላቱ ያን ያህል አያስደንቅም ያሉኝ የእንስሳት ሣይንስ ተመራማሪ አሉ።

ለማንኛውም ሐረር ውስጥ ገንፎው ተዘጋጅቶ ሲጠናቀቅ በመጀመሪያ ፀሎት ላይ ለነበሩት ወንዶች ይሰጣል። ከዛ በኋላ ደግሞ ገንፎውን ያገነፉት ሴቶች ተሰብስበው ይቀምሳሉ። ይህ እንዳለቀ ገንፎውን ጅቦቹ እንዲበሉ የማሰናዳት ስራ ይቀጥላል።

በአው ሐኪም አዋች ገንፎው የሚደረገው ከዋናው ግቢ ወጣ ብሎ በሚገኝ የድንጋይ አለት ላይ ነው። ድንጋዩ በሳህን ወይም በገበቴ ቅርፅ ወደ ውስጥ ተቦርቡሮ የተዘጋጀ ሲሆን በየአመቱ ገንፎው የሚደረገው በዚህ ድንጋይ ላይ ነው።

በአው አቦከርም ቀደም ሲል ገንፎው በድንጋይ ላይ ይደረግ የነበረ ቢሆንም በአካባቢው የነዋሪው ቁጥር ስለጨመረና ቤቶች ስለተሰሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገንፎውን በትልቅ ሳፋ ላይ በማድረግ በዛው በአቦከር ግቢ ውስጥ ጅቦቹን ማብላት ተጀምሯል።

ገንፎው ተዘጋጅቶ ሲያልቅ አካባቢው ፀጥታ ይሰፍንበታል። በተለይ እየመሸ ሲመጣ ያ በሰው ግርግር ድብልቅልቁ የወጣው አካባቢ ፀጥ ረጭ ይላል። አሁን ጅቦቹ የተዘጋጀላቸውን አሽትተው በመምጣት አመታዊ በዓላቸውን ያከብራሉ። ገንፎውን ይቋደሳሉ። የአቦከር አዋች አስተዳዳሪ ወይም ላዚም የሆኑት ሼህ መሀመድ ሁጁ አቦከር እንደሚሉት ጅቦቹ የተዘጋጀላቸውን ገንፎ የሚመገቡበት የራሳቸው የሆነ ሥነስርዓት አላቸው።

ጅብ በሰውነት አቋሙ በሣይንሳዊ አጠራር ካኒድ ከተሰኙት ዝርያዎች ጋር ቢቀራረብም የሚመደበው ግን ሄርፔስታይድ ከተሰኙ የእንስሳት ምድብ ውስጥ ነው።

ከስነ-ቃል አንፃር ጅብ ብዙ ነገር ይባልለታል።

-    ጅብን ለመግደል ከአህያ ተጠለል።

-    ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ።

-    ጅብ አጥንት ባየበት ይመላለሳል።

-    ጅብ ጥጆችን ጠብቅ ቢባል ይጠፋብኛል አለ።

-    ጅብ ምን ይመስላል ቢሉ አፉ ይነክሳል እግሩ ያነክሳል።

-    ጅብ እንደ ጉልበቱ ልብ የለውም።

-    የጅብ ውበቱ ፍርሃቱ።

-    ጅብ እንደ አባቱ ይዘረጥጥ አህያ እንደ አባቱ ይፈረጥጥ።

-    አያ ጅቦ ሳታመሃኝ ብላኝ።

-    ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል።

እንዲህ ሁሉ የሚባልለት ጅብ ሐረር ውስጥ ለየት ባለ መልኩ በአሹራ በዓል ላይ ተገልጿል። በዘንድሮው የአሹራ በአል ጅቡ መጥቶ ገንፎውን ስለበላ አመቱ የሰላም ሆኖ እስካሁን ዘልቋል። የሰላም ዘመን ይሁንልን! መልካም የብሄረሰቦች ቀን ይሁንላችሁ!¾

ቪቫ ካስትሮ!

December 01, 2016

 

በጥበቡ በለጠ

በስፓኒሽ እና በጣሊያን ቋንቋ “ቪቫ” ማለት ለዘላለም ኑር ማለት ነው። ካስትሮ ለዘላለም ኑር ሲባሉ ቆይተዋል።

ከዓለም መሪዎች ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን በቀጥታ በመደገፍ እና በክፉ ቀን ከጎናችን በመቆም እጅግ ግዙፍ ውለታ ውለዋል ተብለው የሚጠቀሱት የኩባው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮ ሩዝ ናቸው። ልክ እንደ እርሳቸው ሁሉ የኩባ ወጣቶችና ምሁራን፣ በአጠቃላይ ኩባዊያን ለኢትዮጵያ ያበረከቱት ውለታ እንዲህ በቀላሉ ከፍለን የምንወጣው አይደለም። ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮም በሕይወት ዘመናቸው፣ በቁመናቸው እያሉ “ካስትሮ ላደረጉልን ሁሉ እናመሰግንዎታለን” ብለን አላመሰገናቸውም። ግን አንዲት አስገራሚ ኢትዮጵያዊት እናት ለካስትሮ በግላቸው ምስጋና ልከዋል። ታሪኩ እንዲህ ነው፡-

በ1990 ዓ.ም አካባቢ ነው። አንዲት ኢትዮጵያዊት እናት ልጃቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በድግሪ ይመረቃል። ልጃቸው የአካል ጉዳተኛ ስለነበር ያንን ሁሉ ችግር ተቋቁሞ ከዩኒቨርስቲ መመረቁ እኚህን እናት በእጅጉ አስደስቷቸዋል። እናቲቱ ይህን ልጅ አስተምሮ ከዩኒቨርስቲ ለማስመረቅ አቅም አልነበራቸውም። አቅም የሆናቸው ጉዳይ፣ ቀደም ሲል የወለዷቸው ሁለት ወንድ ልጆች በዘመነ ደርግ ወደ ሀቫና ኩባ ሔደው ተምረው መጥተው እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ስራ እየሰሩ፣ እናታቸውን እየጦሩ፣ ይሄን ወንድማቸውን አስተምረው ከዩኒቨርስቲ እንዲመረቅ ያደረጉት እነዚህ ሁለቱ ወንድሞቹ ናቸው። እነሱ ባይኖሩ እኚህ እናት ይሄን ሶስተኛ ልጃቸውን ለወግ ለማዕረግ ማብቃት አይችሉም። ምክንያቱም የልጆቹ አባት ለኢትዮጵያ ሲል በጦርነት ሕይወቱን አጥቷል። እናት ሶስት ወልደው ብቻቸውን ቀርተዋል። የባላቸውን ጡረታ ሕይወትን ለማስቀጠል አይበቃም። ዙሪያው ገደል ሆነባቸው። ሶስት ልጆችን ምን አደርጋለሁ? እያሉ ሲያስቡ የፊደል ካስትሮ መንግስት ሁለቱን ትልልቅ ልጆች ወደ ኩባ ወስዶ፣ እንደ እናት እና አባት ሆኖ አሳደጋቸው።

ኢትዮጵያዊቷ እናት በጣም ገረማቸው። የማያውቁት ፊደል ካስትሮ ልጆቻቸውን እንዴት ወሰደ? ለምን አስተማረ? ለምን አሳደጋቸው? ለምን ለወግ ማዕረግ አበቃቸው? የት ያውቀኛል? ችግሬን መከራዬን እንዴት ተረዳው? አንድ ቀን እንኳን አይቶኝም ሆነ አይቼው የማላውቀው ፊደል ካስትሮ ልጆቼን ወስዶ፣ አሳድጎ፣ አስተምሮ፣ መሀንዲስ እና ዶክተር አድርጎ እንዴት ላከልኝ? ለእሱ የምከፍለው ውለታ ምንድን ነው? እያሉ ለረጅም ጊዜ ተጨንቀዋል።

እነዚህ ሁለት ልጆቻቸው ኩባ ተምረው ኢትዮጵያ መጥተው፣ ስራ ይዘው፣ እናታቸውን አንቀባረው በምቾት ማኖር ከጀመሩ ቆይተዋል። ለእናታቸው ቤት ሰርተዋል። ከመሐረባቸው የሚፈቱት ገንዘብ እንዳይቸግራቸው አድርገዋል። እቤት ውስጥ በችግር ምክንያት ቁጭ ያለውን የአካል ጉዳተኛ ወንድማቸውን አስተምረዋል። ከማስተማርም አልፎ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንዲመረቅ ዋናውን ድርሻ ተወጥተዋል። የዚህ ሁሉ ደስታ እና ስኬት ዋነኛው ፈጣሪ ፊደል ካስትሮ ሩዝ ናቸው።

እናም እኚህ ኢትዮጵያዊት እናት ስለ ካስትሮ ደግነት ቢያስቡት ቢያስቡት ለቸርነቱ፣ ለቀናኢነቱ የሚከፍሉት ውለታ አጡ። ነገር ግን አንድ ጉዳይ እጃቸው ላይ ነው። ይህም ስለ ካስትሮ የተሰማቸውን ስሜት በደብዳቤ መግለፅ። ደብዳቤ ፃፉ። የደብዳቤው ይዘትም የሚከተለው ነበር።

“የተከበሩ ፊደል ካስትሮ፤ ከጤናዎ እንዴት ነዎት? ቸርነቱ የማያልቀው መድኃኒአለም ጤናዎንና እድሜዎትን ያርዝምልኝ። ባለቤቴ በጦርነት ላይ ሞቶ ሶስት ልጆቼን ብቻዬን ይዤ አምላኬን እማጠነው ነበር። የነዚህ ልጆች እጣ ፈንታ ምን ይሆን? ያንተው ፍጡር ናቸው። አንተው ጎብኛቸው፤ አንተው ተመልከታቸው፤ እኔማ ባዶ ቀርቻለሁ እያልኩ አምላኬን እማጠነው ነበር። ለቅሶዬን ሰምቶ እርስዎን እንደ መልአክ አድርጎ ላከልኝ። ባላሰብኩትና ፈፅሞ ባልገመትኩት ሁኔታ እርስዎ ሁለት ልጆቼን ወስደው አሳድገው አስተምረው ለወግ ለማዕረግ አብቅተው ላኩልኝ። እርስዎን ማን ልበልዎት? እቤቴ ውስጥ ሰተት ብሎ የገባውን ጨለማ ሕይወት በብርሃን የቀየሩልኝ እርስዎ ነዎት። አምላክ እርስዎን ባይልክልኝ ምን እሆን ነበር? ሁለቱ ልጆቼ እርስዎ ዘንድ ተምረው መጥተው እኔን እና እቤት ውስጥ በሕመም ምክንያት የቀረውን ወንድማቸውን አስተምረው ለቁም ነገር አበቁት። ከሁሉም በላይ የሚያስደስተኝ ደግሞ መጨረሻው ምን ይሆን እያልኩ ዘወትር የማለቅስለትን ትንሹን ልጄን ወንድሞቹ አስተምረውት ሰው ሆኖ ሳየው ከመደሰቴም በላይ በደስታ አለቅሳለሁ። የልጆቼን ሰው መሆን በሕይወት እያለሁ በማየቴ ለአምላኬ ያለኝ ዕምነት እና ፅናት ሃያል ሆነ። አምላክ እርስዎን ልኮ ቤቴን ከሀዘን ወደ ደስታ ለወጠው። የተከበሩ ፊደል ካስትሮ፣ እርስዎን ምን ብዬ ላመስግን? ምን ላድርግሎት? ውለታዎ በምድር ላይ ተከፍሎ የሚያልቅ አይደለም። አምላክ ራሱ ይክፈልዎት። እኔማ ከምስጋና በቀር ምን ላድርግልዎ? ብቻ እርስዎን የሚመጥን ምንም ባይኖረኝም አሁን የፊታችን ሐምሌ 7 ቀን ለሚመረቀው ልጄ እና ለእርስዎ፤ እኔ በእጄ ፈትዬ ያዘጋጀሁት የሀገሬ የኢትዮጵያ ኩታ ጋቢ አለ። ለእርስዎ ክብር የፈተልኩትን ይህን ጋቢ እና ይህን ታላቅ የምስጋና ደብዳቤ በቀጥታ እንዲደርስዎት ለኤምባሲዎ አስረክቤያለሁ። ጤናና ዕድሜ ቸሩ መድኀኒአለም አብዝቶ ይስጥልኝ።

                አክባሪዎ የነ - የወንድወሰን ኃይሌ

$1-    የፍቅሬ ኃይሌ

$1-    የዘርይሁን ኃይሌ

እናት ወ/ሮ አስካለ ብርሃኔ

           ፊርማ

             ቀን ሰኔ 27 ቀን 1990 ዓ.ም

ይህ የምስጋና ደብዳቤ እና ኩታ ጋቢ ለኤምባሲው ተሰጠ። ኤምባሲው ደብዳቤውን በስፓኒሽ ቋንቋ ተርጉሞ ከኩታው ጋቢ ጋር ወደ ሐቫና ኩባ ላከው። ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ እጅ ደረሰ። ደብዳቤውን አነበቡት። እጅግ በጣም ደስ አላቸው። ካስትሮ አዲስ አበባ ወደሚገኘው ኤምባሲያቸው ደወሉ። የወ/ሮ አስካለ ብርሃኑ ሶስተኛ ልጅ ዘሪሁን ኃይሌ ከዩኒቨርስቲ የሚመረቅበትን ቀን ጠየቁ። ቀኑ ለካስትሮ ተነገራቸው። ካስትሮም ትዕዛዝ ሰጡ። “አሁን የምልክላችሁን ደብዳቤ የወ/ሮ አስካለ የልጃቸው የምረቃ ቀን እቤታቸው ሔዳችሁ አንብቡላቸው” አሉ። ከዚያም ፕሬዚዳንት ካስትሮ የሚከተለውን ሀሳብ ያለውን ደብዳቤ ለወ/ሮ አስካለ ብርሃኔ ላኩ።

“የተከበሩ ወ/ሮ አስካለ፤ ለላኩልኝ የምስጋና ደብዳቤ እና በራስዎ እጅ የሰሩልኝ የኢትዮጵያን ኩታ ጋቢ በስጦታ ስላበረከቱልኝ በራሴ ስም እና በኩባ ሕዝብና መንግስት ስም የተከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ውድ ወ/ሮ አስካለ፤ አንድ ነገር ልንገርዎ። እስከ ዛሬ ድረስ ከብዙ ሶሻሊስት ሀገሮች ውስጥ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ልጆችና ወጣቶች መጥተው ኩባ ተምረዋል። ከዚያም ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ግን አንድም ወላጅ የምስጋና ደብዳቤ ልክ እንደርስዎ አላከልኝም። የእርስዎ ደብዳቤ ሲደርሰኝ እና ሳነበው ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል። በጣምም አመሰግንዎታለሁ። እርስዎንም እንዲህ እንዲደሰቱ እና ህይወትዎ የተቃና እንዲሆን ምክንያት ስለሆንን ተደስቻለሁ። ልጆቹም ጥሩ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው ደስታው የሁላችንም ነው። የዛሬዋ ቀንም የእርስዎ እና የልጆችዎ የደስታ ቀን ናት። እኔም በዚህ በደስታዎ ቀን አንድ የግብዣ መልዕክት ልኬልዎታለሁ። ለአንድ ወር ያህል ወደ ኩባ መጥተው እረፍት አድርገው እንዲዝናኑ እና ከእኔም ጋር በአይን ለመተያየት ሙሉ ወጪዎ ተሸፍኖሎት ወደ ኩባ እንዲመጡ ጋብዤዎታለሁ።

                አክባሪዎ ፊደል ካስትሮ የኩባ ፕሬዚዳንት”

ይህ የዚህች ሀገር ታሪክ ነው። ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ በኢትዮጵያዊያኖች ጓዳ ጎድጓዳ ውስጥ ገብተው ብዙ ድጋፍ ያደረጉ ታላቅ መሪ ነበሩ።

በዘመነ ደርግ ከአምስት ሺ በላይ የኢትዮጵያን ልጆች ወስደው ኩባ ውስጥ አሳድገው፣ አስተምረው፣ በድግሪ፣ በማስተርስ እና በዶክተሬት ድግሪ እያስመረቁ ሙሉ ሰው አድርገው የላኩ የልብ ወዳጅ ነበሩ።

ኢትዮጵያን በሶማሊያ አምባገነን መሪ በዚያድ ባሬ ጦር በተወረረችበት ወቅት ፕሬዚዳንት ፈደል ካስትሮ ወታደሮቻቸውን እና የጦር መሳሪያ ወደ ኢትዮጵያ በመላክ በደም፣ በአጥንት እና በሕይወት የተሳሰረ የኢትዮጵያን ፍቅር የገለፁ መሪ ናቸው። አሜሪካ በዚያን ወቅት ከዚያድ ባሬ ጎን ቆማ ኢትዮጵያን ስታስወርር፣ ስታስገድል፣ ለወራሪዎች የጦር መሳሪያ ስትረዳ ነበር። ኩባ፣ የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት እና የመን ከኢትዮጵያ ጎን ነበሩ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኩባዎች ከጦርነቱ ፊት ቆመው መስዋዕት በመሆን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በአጥንታቸው ክስካሽ አስከብረዋል። ካስትሮ በጦርነቱ የሞቱ (የተሰው) የኢትዮጵያን የጦር ሠራዊት አባላት፣ ልጆቻቸውን ወደ ኩባ በመውሰድም አሳድገው አስተምረዋል። በዚህም ታሪክ ፈፅሞ የማይዘነጋው ውለታ ለኢትዮጵያ ያበረከተ መሪ ፊደል ካስትሮ ሩዝ ሁሌም ይታወሳሉ። ካስትሮ ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን ብዙ ጥረዋል።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም ያንን ወቅት በመፅሐፋቸው ውስጥ እንደሚከተለው ይገልፁታል።

“ጓድ ፊደል ካስትሮ ከምክትል ፕሬዘዳንታቸው ጋር፣ ጓድ አብዱል ፈታህ ከፕሬዚዳንቱ ጋር አራት ሆነው መጡ። ከስብሰባው በፊት ወደ እኛ የመጡበት ምክንያት “ሱማሌዎች ይህ ውይይት እንዳይሳካ የማይፈጥሩት ችግር ስለሌለና ምናልባትም የእናንተን ትዕግስት የሚፈታተን የብልግናና የዘለፋ ቃላቶችን ከመሰንዘር ስለማይመለሱ በናንተ በኩል እስከ መጨረሻው ትዕግስታችሁን እንጠይቃለን” አሉን። በእኛ በኩል ምንም አይነት ችግር እንደማይፈጠር በማረጋገጥና በማበረታታት መልሰን ሸኘናቸው።. . . የሶማሌያው መሪ ማንንም ሳያነጋግር ወይም ሳይጨብጥ አዳራሹ ማዕከል ሜዳ ላይ ሁለት እጁን ሱሪ ኪሱ ከቶ ዘለግ ባለ ድምጽ፡- “ሁለት ስቱፒድ የሆንን ህዝቦች አስቸግርናችሁ አይደለም?” በማለት ተናግሮ ወደ መቀመጫው ሲያመራ ከአነጋገሩ በላይ ጠቅላላ ሁኔታው፣ ኩራቱና ትዕቢቱ ደሜን ስላፈላው፣ ለትዕግስቴ ዳርቻ አይኖረውም ብዬ ለራሴ ቃል የገባሁት ሰውዬ “የራስህን ስቱፒድነት ተናገር! እኛ ግን አንተን ወይም እናንተን አይለንም!” ስለው አስተናጋጆቹ ደነገጡ። ዚያድ ባሬ ያልኩትን ያልሰማኝ ይመስል “ምንድን ነው ያለው?” እያለ ሰዎቹን ሲጠይቅ አስተውለው ነበር (ገፅ 354)

ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም እና በእርሳቸው የአስተዳደር ዘመን ውስጥ የነበሩ ባለስልጣናት በሙሉ በፃፏቸው መፃህፍት ውስጥ ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ለኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት፣ በጦርነትም ወቅት ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም፣ ሕዝቦቿንም በመደገፍ የሚስተካከላቸው ሰው እንደሌለ መስክረዋል።

እ.ኤ.አ. ኦገስት 13 ቀን 1926 ቢራን በተባለች ቦታ የተወለዱት ፊደል ካስትሮ፣ ኩባን ለ47 ዓመታት በሶሻሊስት ፓርቲ ፍልስፍና መርተዋል። ቆራጥ ታጋይ፣ ለአመኑበት ጉዳይ እስከ መጨረሻው በፅናት የሚቆሙ፣ የአሜሪካንን የዘመናት ተፅዕኖ ተቋቁመው የኖሩ የክፍለ ዘመኑ ትልቅ ባለታሪክ መሪ ነበሩ።

እኚህ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅ የፊታችን እሁድ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው በኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት አደባባይ ላይ ይታወሳሉ። የዝክር ዝግጅቱንም ያስተባበሩት ወደ ኩባ ሔደው ተምረው የመጡ ወደ አምስት ሺ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያንና ቤተሰቦቻቸው ናቸው። የአስተባባሪው ኮሚቴ ሊቀመንበር ይብራህ መሀሪ እንደገለፁት፣ በዚህ የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ ኩባ ስትረዳቸው የነበሩ የበርካታ ሀገራት አምባሳደሮችና ባለስልጣናት ጭምር እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ባለፈው አርብ ሕዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም በዘጠና ዓመታቸው ያረፉት የቀድሞው የኩባ ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ከኢትዮጵያ አልፈው ለሌሎቹም የአፍሪካ ሀገራት ነፃነት ብዙ አስተዋፅኦ አድርገዋል። እናም ትውልድ የማይዘነጋቸው የክፉ ቀን ደራሽ መሪ ናቸው። ነብስ ይማር ብለናል።

 

በጥበቡ በለጠ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖት ውስጥ አንድ ትልቅ ታሪክ አለ። ፈጣሪ ለሙሴ የሰጠው አስርቱ ትዕዛዛት የተፃፈበት ጽላት መኖሪያው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ ያውም አክሱም ጽዮን ነው። በየዓመቱ ሕዳር 21 ቀን ጽዮን ትነግሳለች። አያሌ ምዕመናን ወደ ስፍራው ይጓዛሉ። በዓሉን በዚህችው ከተማ እና ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ያከብራሉ።

ጽላተ- ሙሴን ይዛ ከድህነት እና ከረሃብ ከስደት ያልወጣችው ኢትዮጵያ፣ ትልቅ የሆነ መንፈሳዊ ሀብት ደግሞ አላት። ይህም ሐይማኖቷ ነው፤ ለሺ ዘመናት ጠብቃ ያኖረችው ሐይማኖት የሐገሪቷን አንድነት አፅንቷል። ኢትዮጵያ በነፃነት እንድትኖር አድርጓል።

ዛሬ ሕዳር 21 ቀን ነውና እስኪ ስለ ጽላተ ሙሴ የተወሰኑ ነገሮችን እንጨዋወት።

የፊልም ባለሙያዋ ኤሚ እንግዳ በአክሱም፣ በጽዮን ማርያም እና በጽላተ-ሙሴ ላይ አንድ ዶክመንተሪ ፊልም ሰርታለች። ፊልሙ ከአምስት ዓመታት በላይ የፈጀ እና አያሌ አስገራሚ ሰነዶችን የያዘ ነው። በፊልሙ ውስጥ የእኔም ተሣትፎ ስለነበር በቅርበት አውቀዋለሁ። እናም ከእርሱ በመነሳት እንዲህ ብንጨዋወትስ፡-

ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪኰች ሀገር እንደሆነች ተደጋግሞ ተደጋግሞ የተነገረ ሀቅ ነው። ኢትዮጵያ ራሷን ለውጭው ዓለም ለማስተዋወቅ ብዙም ጥረት ባታደርግም፤ ነገር ግን ከቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች መካከል አንዷ ሆናለች። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ማለትም /ዩኔስኮ/ የዓለም አስደናቂ ቅርሶች በማለት የመዘገባቸው የቱሪዝም መስህቦች 21 ደርሰዋል። እነዚህም ዘጠኝ ቋሚ ቅርሶች ሲሆኑ 12 ደግሞ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፎች ናቸው። እነዚህን ጥንታዊ የብራና ፅሁፎች ዶክመንተሪ ቅርስ /documentary Heritages/ በሚል መዝገብ ውስጥ አስቀምጧቸዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቅርሶቿን ለማስተዋወቅ በርትታ ብትሰራ ደግሞ እጅግ ብዙ አስገራሚ ነገሮችን ማስመዝገብ ትችላለች። ግን በዚያ ዘርፍ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ያን ያህል ጐልቶ አይታይም።

ኢትዮጵያ አሉኝ ከምትላቸው እጅግ አስገራሚ ቅርሶች መካከል የእምነት መገለጫ የሆነው ጽላተ-ሙሴ አንዱ ነው። ይህ ፅላት ከሦስት ሺ ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ ሲነገር ቆይቷል። በርካታ የእምነትና የታሪክ ተመራማሪዎችም አያሌ ማስረጃዎችን እየጠቀሱ ፅላቱ በኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን አረጋግጠዋል።

ይሁን እንጂ ይሄ በክርስትናው ዓለም ውስጥ ያሉ የዓለም ህዝቦች ሁሉ መገለጫ የሆነውን ፅላት በተመለከተ ልዩ ልዩ ፊልም ሰሪዎች፣ የልቦለድና የቴአትር ፀሐፊዎች፣ አርኪዮሎጂስቶችና ተመራማሪዎች የተለያዩ ኀሳቦችን ሲሰጡ ኖረዋል። አሁንም ይመራመራሉ።

አንዳንዱ ደግሞ ጽላተ-ሙሴን መሠረት አድርጐ ልብ ወለድ ሁሉ ይፅፋል። የፈረደባቸው ደግሞ በየሀገሩ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ እያደረጉ አንዴ አገኘነው ሲሉ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የተመራመሩበት ሁሉ ሀሰት ነው ተብለው ውድቅ የተደረገባቸው ጊዜያት ነጉደዋል።

በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች ደግሞ ይህን ፅላት ከኢትዮጵያ እንወስደዋለን ብለው የውጭ ሀገር ሰዎች የተለያዩ ደባዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል። ነገር ግን ኢትዮጵያዊያኖች ለሀገራቸውና ለሃይማኖታቸው ባላቸው ቀናኢነት ማንም ድርሽ እንዳይል እያደረጉ በጀግንነት ቆይተዋል። በሀገሪቱ ውስጥ በተነሱ ታላላቅ ጦርነቶችም መካከል ፅላቱ አደጋ ውስጥ እንዳይገባ ብዙ ርብርብ ተደርጐ ቆይቷል።

በአንድ ወቅት ደግሞ Ron Wyatt የተባለ አሜሪካዊ አርኪዮሎጂስት ፅላተ-ሙሴን በእስራኤል ጐሎጐታ ውስጥ ቆፍሬ አገኘሁ ብሎ ተናገረ። ፊልምም ተሰራለት። በተለይ እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም የተቀረፀው የዚህ አርኪዮሎጂስት ግኝት በወቅቱ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር። ይሄ ነገር እውነት ይሆን ብለው ብዙዎች መጠየቅ ጀምረው ነበር። እውን ጽላተ-ሙሴ ጐሎጐታ ውስጥ ተቆፍሮ ተገኝቷል?

ጉዳዩ ብዙ አነጋጋሪ ነገሮችን የያዘ ነው። አርኪዮሎጂስቱ Ron Wyatt ለማሳመኛ እንዲመቸው ብሎ ሌሎች በርካታ ጉዳዮችንም እያያዘ ተናገረ። በፊልም እያስደገፈ ፅላቱን አግኝቸዋለሁ አለ። ከፅላቱ ጋርም የተለያዩ የእስራኤል ቅርሶችን አገኘሁ እያለ ብዙ ተናገረ። ሚዲያዎችም ጉዳዩን እየተቀባበሉት አራገቡት። ነገር ግን በመጨረሻም የRon Wyatt የአርኪዮሎጂ ግኝት ከፅላቱ ጋር ተያያዥነት እንደሌለው ተነገረ። ይሁን እንጂ ይህ አሜሪካዊ የሰራው ስራ ውዥንብር ፈጥሮ ማለፉ የማይታበል ሀቅ ነው።

ግርሃም ሀንኩክን ጨምሮ በርካታ ተመራማሪዎችና ፀሐፊዎች ደግሞ መፅሐፍ ከማሳተም አልፈው በፅላተ-ሙሴ ላይ ዶክመንተሪ ፊለሞችን ሰርተዋል። ግርሃም ሀንኩክ The Sign & the Seal በተሰኘው ታዋቂ መፅሐፉ ፅላተ-ሙሴን በዓለም ላይ መፈለጉን ይናገራል። ብዙ ሀገራት ፈልጓል፣ ተመራምሯል። የአርኪዮሎጂ ውጤቶችን የታሪክ ሰነዶችን አገላብጧል። በመጨረሻም ወደ ኢትዮጵያ መጣ። ኢትዮጵያ ውስጥ ምርምር አደረገ። ወደ አክሱም ፅዮን ማርያም ገደም ሄደ። ቀሳውስቱን አገኛቸው። አወራቸው። ጽላቱ አክሱም ውስጥ ፅዮን ማርያም ቤተ-ክርስትያን ቅፅር ግቢ ውስጥ ባለች ልዩ ህንፃ ውስጥ እንዳለች አስረዱት። ልየው አላቸው። ለማንም እንደማይታይና እጅግ ጥብቅ በሆነ ጥበቃ ላለፉት ሦስት ሺ ዓመታት መኖሩን ነገሩት።

ግርሃም ሀንኩክ የኢትዮጵያን የታሪክ ሠነዶች አየ። ፅላቱ እንዴት ከእየሩሳሌም ወደ ኢትዮጵያ መጣ ብሎ ታሪክ ፈተሸ። ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚኖሩት ቤተ-እስራኤላውያን ታሪክም አወቀ። ፅላቱ ከነርሱ ጋር እንደመጣም አመነ። እናም በመጨረሻ ላይ ግርሃም ሀንኩክ ፅላተ-ሙሴን በኢትዮጵያ ውስጥ አገኘሁት ብሎ ፃፈ። ዶክመንተሪ ፊልምም ተሰራለት። በዓለም ላይ እጅግ ከተሸጡ መፃህፍት አንዱ ይኸው The sign & the seal የተሰኘው የግርሃም ሀንኩክ መፅሐፍ ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያንም በከፍተኛ ሁኔታ ያስተዋወቀ ነው።

ግርሃም ሀንኩክ በሌሎች ኢትዮጵያውያን በተመለከቱ ዶክመንተሪ ፊልሞች ላይም ማብራሪያ የሚሰጥ ሰው ነው። በዚሁ በፅላተ-ሙሴ ላይ በተሰራ The lost ark of the covenant በተሰኘ ፊልም ላይ ፅላቱ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን ተናግሯል። ከዚህም ባለፈ በልዩ ልዩ ታላላቅ ጉባኤዎች ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን ይናገራል። Earth Keeper በተሰኘ ዶክመንተሪ ፊልምም የኢትዮጵያ ጉዳይ ይጠቀሳል።

የፅላተ-ሙሴን ታሪክ በተመለከተ አያሌ ፊልሞች ተሰርተዋል። በመሠራትም ላይ ናቸው። አንዳንዶቹ አጨቃጫቂ መረጃዎችን ይዘዋል። አብዛኛዎቹ መረጃዎችና ዶክመንተሪ ፊልሞች ኢትዮጵያ ሚስጢራዊት ሀገር መሆኗን ገልፀው፤ ፅላቱም በዚህችው አገር ውስጥ እንደሚገኝ መስክረዋል። እነዚህ ፊልሞች በጣም ደስ የሚሉ እና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው ናቸው።

ጣና ቂርቆስ ላይ፣ ዝዋይ ሐይቅ ላይ፣ አክሱም ላይ የተሰሩ እጅግ የሚገርሙ ዶክመንተሪ ፊልሞች አሉ። ሁሉም አንድ የሚያደርጋቸው ደግሞ ፅላተ-ሙሴን ፍለጋ ነው። ሌሎች ፊልሞች ደግሞ አሉ። አለምን እየዞሩ መጥተው ኢትዮጵያን ማሳረጊያቸው ያደረጉ። እነዚህን አስገራሚ ፊልሞች በተከታታይ እናቀርብላችኋለን። የኢትዮጵያ አስተዋዋቂዎች ናቸውና። 

 

በጥበቡ በለጠ

ባለፈው ቅዳሜ ነሀሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በአቤል ሲኒማ ውስጥ እጅግ የተደሰትኩበትን መርሀ ግብር በመታደሜ ነው ዛሬ ላወጋችሁ ብቅ ያልኩት። መርሀ ግብሩ የበጎ ሰው ሽልማት ነው። እነዚህ በጎ ሰዎች ለሀገራቸውና ለህዝባቸው መልካም ተግባር ያከናወኑ ናቸው። አብዛኛዎቹ በሕይወት እያሉ ለዚህ ሽልማትና እውቅና መብቃታቸው ሌላው በጣም ጥሩ ጎኑ ነው። ይህ ሽልማትና እውቅና ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በተከታታይ ለአራተኛ ጊዜ መጓዝ መቻሉ በራሱ የወደፊቱን ተስፋ ያበራልናል። ምክንያቱም በሀገራችን ውስጥ በተለይ ሽልማትን በተመለከተ ሁሌ ብቅ እያለ ድርግም የሚልበትን ሁኔታ ላስተዋለ ሰው ይህ የበጎ ሰው ሽልማት ተስፋን ይሰጣል። ሽልማት የሚባለው መንፈስ ሁሉ የጠፋበት ዘመን ላይ ነበርን። በአንድ ጊዜ ብዙ ሺ ገበሬዎች ሚሊየነሮች ሆኑ ተብሎ ሲሸለሙ እናይና በአመቱ ደግሞ ብዙ ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን በአስከፊ ረሀብ ውስጥ ናቸው የሚል ዜና ይመጣል። እናም የሽልማት ትርጉሙ የጠፋብኝ ያን ሰሞን ነበር።

በዚህ በዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማት ላይ 33 ኢትዮጵያዊያን ሽልማትና እውቅና አግኝተዋል። እሰየው ይባላል። ሰው ማለት ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋ እለት የሚባል አባባልም በሀገራችን አለ። ውድ ኮሚቴዎች ደግ አድርጋችኋል። ደግ ደጉን ያድርግላችሁ!

ከሽልማቶቹ ውስጥ ለየት ያለው የቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረስላሴ ዘብሄረ ቡልጋ ነበሩ። ዛሬ በሕይወት የሌሉት እኝህ የፊደልና የእውቀት አባት በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ እና አርበኝነት ውስጥ ግዙፍ ታሪክ ያላቸው ናቸው። ከ30 ዓመታት በላይ ውብ ድምጽ ይዞ በክብር የቆየው ድምጻዊ ጸሀይ ዮሀንስ የ1970 ዓ.ም ቀዳማይ ዘፈኑን ማንበብና መጻፍ ዋናው ቁም ነገሩ… እያለ ሲያቀነቅን የተስፋ ገብረስላሴን መንፈስ ከፍ አድርጎታል። የኛንም መንፈስ ከፍ አድርጎልናል።

ፊደሉን ሳየው መልሰው ያዩኛል

ሌላው ሲያነባቸው እኔን ይጨንቀኛል

የዘመድ ሰላምታ ሲመጣ ደብዳቤ

መርዶ እየመሰለኝ ሲደነግጥ ልቤ

ማንበብና መጻፍ ዋናው ቁም ነገር…

(ጸሐዬ ዮሐንስ)

ስለ ተስፋ ገብረስላሴ አንዳንድ ነገሮችን እንጨዋወት። በሙዚቃ ጸሐዬ ያጅበናል።

አንድ ህፃን ልክ አራት አመት ሲሞላው ከፊደል ገበታ ጋር መተያየት ይጀምራል። ' በል፣ ' በል... እየተባለ ይረዳል። የዓለምን ምስጢር፣ ውጣ ውረድ በፊደሎች መቁጠር ይጀምራል። እነዚያ ፊደሎች እየሰፉ እየተገጣጠሙ ሲመጡ ቃል ሆነው ሀሳብ ያስተላልፋሉ። ሀሣብ ደግሞ ብዙ አይነት እውነታዎችን በውስጡ የያዘ ነው። የህይወት ጉዞ እንግዲህ ተጀመረ።

በሀገራችን ኢትዮጵያ በየቤታችን ውስጥ ሀሁ ያስቆጠሩን ማናቸው ብንባል ብዙ ሚሊዮኖች አንድ ላይ “ተስፋ ገ/ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ” የሚል መልስ እንሰጣለን። ምክንያቱም በዚያ በጨቅላ ጭንቅላታችን ለመጀመሪያ ጊዜ ማንበብ የጀመርነው ከሀሁ' ቀጥሎ የተስፋ ገ/ሥላሴ ስም ነውና። ዛሬም ድረስ በዚሁ የህይወት ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያችንና ዜጐቿ እየቀጠሉ ነው። እናም ስማቸውን ትውልድ እየተቀባበለ እየጠራ እየተማረባቸው የዘመን ኬላን እየሰበረ የሚምዘገዘገው ስም ባለቤት ተስፋ ገ/ሥላሴ ማን ናቸው?

በርግጥ ዛሬ የምናወራው እንደ አባትም እናትም ሆኖ ያሳደገንን የፊደል ገበታ አዘጋጅተውልን ወደ ማይቀረው ዓለም የተሰናበቱትን እኝህ ሰው ታላቅ የታሪክ ውቅያኖስ ያላቸው ናቸው። ከዚያ ታሪካቸው ነው ጭልፍ እያደረግን የምንጨዋወተው።

ዛሬ የብዙ ጥበበኞች እና የጥበብ አድናቂዎች መታደሚያ የሆነው የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤትን ከመሠረቱት ጐምቱ ኢትዮጵያዊያን መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ቀኛዝማች ተስፋ ገ/ሥላሴ በሰሜን ሸዋ በቡልጋና በረኸት ተድላ ማርያም ወረዳ ክታብ ወይራ አክርሚት ከተባለ ቀበሌ ከአባታቸው ከመምህር ገብረ ሥላሴ ቢልልኝ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ሥዕለ ሚካኤል ወልደ አብ በ1895 ዓ.ም ታህሳስ 24 ቀን ተወለዱ።

እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ፊደል ቆጠሩ። ወላጆቻቸው ታዲያ ከትምህርቱ ይልቅ ከብቶች እያገዱ እንዲያገለግሏቸው በመሻታቸው አያታቸው መምህር ቢልልኝ ከወላጆቻቸው ነጥቀው እንዲያስተምሩላቸው ለመምህር ገብረ አብ ወስደው ሰጧቸው።

መምህር ገብረ አብም የቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ የአያታቸው የመምህር ወልደ አብ ደቀ መዝመር ስለነበሩ በደስታ ተቀበሏቸው። ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ በመምህር ወልደ አብ ዘንድ ንባብ፣ ዳዊትና ውዳሴ ማርያም መልክአ ማርያምና መልክአ ኢየሱስ ሰአታት ዘሌሊት አጠናቀው ተማሩ። ግብረ ዲቁናንም በሚገባ አጥንተው እንደጨረሱ አዲስ አበባ መጥተው ከአቡነ ማቴዎስ ዘንድ የዲቁና ማዕረግ ከተቀበሉ በኋላ ተመልሰው አገራቸው ቡልጋ ገብተው በአክርሚት ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን በዲቁና ማገልገል ጀመሩ።

ከዚሁ የ80 ቀን መታሰቢያ ከተዘጋጀላቸው ጽሁፍ ታሪካቸውን መረዳት እንደሚቻለው “አባታቸው መምሬ ገብረ ሥላሴ ቢልልኝ ከቅስና ሙያቸውና ከግብርና ሥራቸው ውጭ በትርፍ ጊዜያቸው ብራና እየፋቁ ከዕፅዋት ቀለም እያነጠሩ የፀሎትና ለአብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት የሚሰጡ መጽሀፍ ድጓና ሌሎችንም መፃህፍት ይፅፉና ያበረክቱ ስለነበር እሳቸውም በቤተ-ክርስቲያን አካባቢ በግብረ ዲቁና እያገለገሉ ሳለ የወላጅ አባታቸውን አሠረ ፍኖት በመከተል የፍየል ቆዳ በእንጨት ወጥረው እየፋቁ፣ በመድመፅ እየደመፁ፣ ብራናውን በወሳፍቻ እያሰመሩ፣ ቀለሙን ከልዩ ልዩ እፀዋት እያነጠሩ በመቃ ብዕር እየፃፉ፣ የዘወትር ፀሎት ስአታት ዘሌሊት ገበታ ሐዋርያ ሌላም መፃህፍትን እየፃፉ በማራባት ወገናቸውን ጠቅመው ራሳቸውም መጠቀም ጀምሩ” ይላል።

ተስፋ ገብረ ሥላሴ የ15 አመት ወጣት በነበሩበት ወቅት በ1909 ዓ.ም አዲስ አበባ መካነ ሥላሴ የሚገኙት ከአጐታቸው ከሊቀ ጠበብት ዘንድ መጥተው ለጥቂት ጊዜ ዕረፍት ካደረጉና ከተማውንም ከተለማመዱ በኋላ በጊዜው በአዲስ አበባ የዕፅዋት ችግር ስላልነበረ ቀለሙን ከልዩ ልዩ እፀዋት እየቀመሙና እያነጠሩ በዚያው በመቃ ብዕር ቀርፀው በ1910 ዓ.ም የፊደላትን ሆሄያት እየፃፉ በዝርግ ክርታስ እየለጠፉ በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ላራዳ በማዞር አንድ ፊደል በአንድ መሐለቅ መሸጥ ጀመሩ በማለት ዛሬም ድረስ ሆነ ወደፊትም ስማቸውን በክብር የሚያስጠራው ስራቸው መወሳት ይጀምራል።

የመርሐ ጥበብ ማተሚያ ቤት እንደተቋቋመ “እውቀት ይስፋ ድንቁርና ይጥፋ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” የሚለውን ኃይለ ቃል አርእስት በመስጠት ፊደልን፣ ፊደለ ሐዋርያትንና አቡጊዳን በሦስት ረድፍ እያዘጋጁ በማሳተም በመላ ኢትዮጵያ ማሰራጨት ጀመሩ። እናም በመላ ገጠሪቱ የሚኖር የኢትዮጵያ ህዝብ ከፊደል ሆሄያት ጋር ዓይን ለዓይን ተያየ።

የብርሐንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሲቋቋም ከሽያጩ ሩብ እየከፈላቸው የጋዜጣና የበራሪ ጽሁፎችን ሽያጭ በኮንትራት በመያዝ መሸጥ መጀመራቸውን ያለፈ ታሪካቸው ያወሳል።

ከዚህ ባለፈ ደግሞ ራሳቸውን ችለው ለመንቀሳቀስ ባላቸው ፅኑ ፍላጐት የተነሳ በ1921 ዓ.ም በዘመኑ የነበሩት የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስ በቤተ-ክህነቱ ግቢ ውስጥ ቦታ ሰጧቸው። ከዚያም በሰው ሃይል የሚሠራ የማተሚያ ማሽን ገዝተው ከፊደል ጀምሮ ያሉትን የንባብ መሣሪያ የፀሎትና የሃይማኖት መፃህፍትንና እንዲሁም ከራሳቸው አዕምሮ የሚፈልቀውን የስነ-ጽሁፍ፣ ግጥሞችና እንደነ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ያሉ የዘመኑ ታዋቂ ደራሲያን የፃፉትን ግጥሞችንና የጊዜውን ሁኔታ የሚጠቁሙ ዝርው ጽሁፎችን በበራሪ ወረቀቶች እያተሙ መሸጥ ጀመሩ።

ተስፋ ገብረ ሥላሴ በተለይም የሚታወቁበት ሌላው ገጽታቸው ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ልትወር በምትዘጋጅበትና እንቅስቃሴም በጀመረችበት ወቅት ህዝቡ ተደራጅቶ ወራሪዎችን እንዲከላከል ከነ ዮፍታሐ ንጉሤ ጋር በመሆን ብዙ የሠሩ ባለውለታ ናቸው። በተለይም ደግሞ በትጋታቸው የተነሳ በእጃቸው ባስገቡት የህትመት መሣሪያ የተነሳ በራሪ ፅሁፎችን በማተም “ኢትየጵያ ልትወረር ነው። ልጆቿ የሆናችሁ ሁሉ ተነሱ አድኗት” እያሉ ከፍተኛ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ከአርበኞች ማህደር ውስጥ ስማቸውን በወርቅ ቀለም የሚያፅፍላቸው ነው።

በተለይም ደግሞ በነበራቸው የስነ-ግጥም ችሎታ ልክ የዛሬ 79 አመት ከኢትዮጵያዊያን ሁሉ ፀረ-ፋሽስታዊ ትግል እንዲያካሂዱ የሚከተለውን ወኔ ቀስቃሽ ግጥም ጽፈዋል።

 

ከባህር እየወጣ መጣልን ዓሣው፣

በሰይፍ እየመተርን ባረር እየቆላን ፈጥነን እንብላው

ጥንት አባቶቻችን ምግባቸው ይህ ነው፣

ምነው ያሁን ልጆች ዝምታው ምንድነው?

የባህሩ ዓሣ ወጥቶ ከጐሬው፣

አጥማጁ አንቆ እንጂ ስጋውን ይብላው።

በማለት በመላው ኢትዮጵያ ፅፈው አሠራጭተው ታጋዮች እንዲነቃቁ አድርገዋል።

ተስፋ ገ/ሥላሴ የዛሬ 16 ዓመት ከሚወዷት ኢትዮጵያ በሞት በተለዩበት ወቅት ተፅፎ ከቀረበው የህይወት ታሪካቸውና እንዲሁም በይፋ ከሚታወቀው የአርበኝነት ህይወታቸው ሰውየው በጣም ብርቱ ኢትዮጵያዊ ነበሩ።

በ1928 ዓ.ም ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር ጦርነት ባወጀችበት ወቅት ጠላት አንዳንድ የኢትየጵያን ባለስልጣናት ባላባቶች አገራቸውን ለማስካድና በስለላ ስራ ለማሰማራት በገንዘብ እየደለለ የማታለል ሙከራ በሚያደርግበት ጊዜ ቀኛዝማች ተስፋገብረ ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ የዓፄ ምኒልክን ፎቶ ግራፍ የፅሁፋቸው አርማ በማድረግ በአድዋው ጦርነት ጊዜ ጀግኖችና ታማኞች የምኒልክ የጦር አበጋዞች የጐራው ገበየሁና ደጀዝማች ታፈሰ አባ ትንታግ፣ ባልቻ አባነፍሶ የኢትዮጵያ ጋሻ መከታ በመሆን በአላጌ በመቀሌ በአድዋ የሰሩትን የጀግንነት ሙያ በመከተል በታማኝነት የዜግነት ግዴታ መወጣት እንጂ ለገንዘብ ብሎ አገር ለጠላት አሳለፎ መስጠት እጅግ አሳፋሪ መሆኑን በመግለፅ የሚከተለውን ግጥም አቅርበዋል።

 

... የተረገመ ነው አገሩን የካዳ፣

ክብሩን ነፃነቱን አበሻን የጐዳ።

ከኢትዮጵያ ከሐበሻ ጠላት ጉቦ የበላችሁ፣

የትነው የምትበሉት አገር ሳይኖራችሁ።

ያልታመኑ ሌቦች ከሹመት ተሽረው፣

አገሪቷን ይምሩ ታማኞች ተመርጠው።

ይህን ግጥም ፅፈው በመላው ኢትዮጵያ እንዲሠራጭ አደረጉ። በዚህም የተነሳ ባለስልጣናቱ አብዛኛዎቹ ሆድ ባሳቸው አጉርመረሙ። እናም ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴን የሚጐዱበትን የህግ ክፍተት መፈለግ ጀመሩ።

በወቅቱ ማንኛውም በፅህፈት መሣሪያ ማሽን ተባዝቶ የሚሠራጭ ፅሁፍ የፅህፈት ሚኒስቴር ሳያየውና ሳይፈቅድ ወደ ህዝብ ማስገባት እንደማይቻልና ወንጀልም እንደሆነ የሚደነግግ ህግ ወጥቷል። ንጉሠ ነገሥቱም ጉዳዩን ሳያውቁት ነው ተፅፎ የተሠራጨው። እናም ተስፋ ገብረ ሥላሴን መጉጃ መንገድ ተገኘ።

ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ በአዲስ አበባ የሚገኙ ከሆነ ከከተማው ከንቲባና የፀጥታው አስከባሪ በባላምባራስ በኋላ ራስ አበበ አረጋይ እጅ ታስረው እንዲቀርቡ ሲታዘዝ በከተማው የማይገኙ ቢሆን ግን የአገር ግዛት ሚኒስትሩ ደጃዝማች ገብረማርያም ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴን ካሉበት ቦታ አስፈልገው አስረው እንዲያቀርቡ ታዘዙ።

በየክፍላተ አገሩ ታትሞ የተሰራጨው ፅሁፍም ተለቅሞ እንዲመጣ ታዘዘና መፅሀፍ ሻጮችም ሁሉ ከተሠራጨው ፅሁፍ ጋር ተይዘው ታሰሩ። ይህ እንግዲህ የበጅሮንድ ተክለሀዋርያት ተክለማርያም “ፋቡላ የአውሬዎች ኮሜዲያ” የተሰኘው ተውኔታቸው በ1913 ዓ.ም በንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ከታገደ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ከፍተኛ የመንግሥት ዘመቻ የተደረገበት የተስፋ ገብረ ሥላሴ ፅሁፍ ነው ማለት ነው። ሀሳብን የመግለፅ መብት አፈና ሀገራችን የጀመረችባቸው አስቀያሚ ደንቦች ናቸው።

ከዚሀ ጋር በተያያዘም የተስፋ ገብረ ሥላሴ ቤተሰቦችም ወደ ዘብጥያ እንዲወርዱ ተደረገ። መኖርያ ቤታቸውም ሳይቀር ታሸገ። ተስፋ ገብረ ሥላሴ ደግሞ ለስራ ጉዳይ ሐረርጌ ጨርጨር ሄደው ነበርና እዛው ያሉበት ቦታ ተያዙ። በሰንሰለትም ታስረው በቀጥታ ንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን ፊት ቀረቡ። ንጉሡም ጠየቁ። ለመሆኑ ይህንን ፅሁፍ የት ሆነህ ፅፈህ ነው ያሰራጨኸው አሏቸው። ተስፋም መለሱ። አቡነ ቄርሎስ ግቢ አሉ። ጉዳዩ አሳሳቢ ሆነ። የሀገሪቱ ጳጳስ አቡነ ቄርሎስም ተጠሩ።

ጃንሆይም እዝን ብለው አባታችን እንደምን በብፁዕነትዎ ግቢ ወንጀል ተሠራ' ብለው ጠየቋቸው። ጳጳሱም መንፈሣዊ ልዕልና የነበራቸው ሲሆኑ እንዲህም ብለው መለሱ። “አገራችሁን አትክዱ ከጠላት ጉቦ አትቀበሉ ብሎ ስለሰበከ ይህም ወንጀል ነው?” ሲሉ መልስ ሰጡ።

ጃንሆይም የፅሁፍ ነገር በደንብ መጣራት አለበት በማለታቸው ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብጥያ ወርደው እንዲቆዩ ተደረገ። ምርመራ በሚደረግበት ወቅት ስድስት ወራትን በእስር ማቀዋል። በሀገራችን ኢትዮጵያም በፃፈው ስነ-ግጥም ለመጀመሪያ ጊዜ በእስር ፍዳ ያየ ፀሀፊ በመባል በታሪክ ተመዝግበዋል።

ተስፋ ገብረ ሥላሴ ከእስር የተፈቱት የኢጣሊያ ፋሽስቶች እየገፉ በሚመጡበት ጊዜ ሁለተኛ ያለመንግሥት ፈቃድ አንዲህ አይነቱን እያተመ ለህዝብ እንዳያሰራጭ ሁለት ዋስ ጠርቶ ይፈታ ተባሉና ምህረት ተደርጐላቸው ከእስር ተፈቱ።

ከዚያም ወራሪዎች ሰሜናዊ ኢትዮጵያን እየያዙ ሲመጡ እና የሽብር ወሬዎችን ሲነዙ ተስፋ ገብረ ሥላሴ በደረሰባቸው እንግልት ተማረው ቁጭ አላሉም። ወዲያውም 'የኢትዮጵያ ፋና' የሚል በራሪ ወረቀት እየፃፉ ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን እንዲከላከሉ አበክረው ሲወተውቱ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያም በፋሽስቶች እጅ ስትወድቅ መጀመሪያ ከታሰሩ ሰዎች መካከል ተስፋ ገብረ ሥላሴ አንዱ ናቸው። ለኢጣሊያ ያደሩ ባንዳዎች ህዝብን ቀስቃሽ ፅሁፎችን ያሰራጭ ነበር ብለዋቸው ጠቆሙ። እናም ጉዳያቸው ተጣርቶ ግራዚያኒ ፊት ችሎት ላይ ቀረቡ። ባጋጣሚ የቀረቡባቸው የማስረጃ ፅሁፎች ዋና ዋናዎቹ ባለመሆናቸው ከግራዚያኒ መንጋጋ ለጥቂት አመለጡ።

ሞገስ አስገዶም እና አብረሃም ደቦጭ በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ሲወረውሩ ከእነርሱ ጋር ወዳጅነት አላቸው ተብለው አደጋ እንዳይደርስባቸው ቤተሰብ ወዳጅ ወተወታቸው። እናም አፍንጮ በር አካባቢ የተቀበረ የመንግሥት መሣሪያ መኖሩን ስለሚያውቁ ከታማኝ ነጋዴዎች ጋር ተነጋጋረው እሱን አስወጥተው ወደ ቡልጋ በመጓዝ ከአርበኞች ጋር ተቀላቅለዋል።

ቀኛዝማች ተስፋ በጦር ሜዳው ትግል ውስጥም ሳሉ እንግሊዝ ሀገር ካሉት ከጃንሆይ ጋር ይፃፃፉ ነበር። አንዴ ግን አብረዋቸው ጠላትን ይፋለሙ የነበሩት ራስ አበበ አረጋይ እኔ ሳላውቅ እንዴት ደብዳቤ ትፃፃፋለህ ብለው እንዳሰሯቸውም በታሪክ ተመዝግቧል። ባጋጣሚ ደግሞ ፋሽስቶች ያንን የጦር ግንባር ሲያጠቁ ተስፋ ገብረ ሥላሴን እስር ቤት ያገኛቸዋል። አዲሳባ ይዘዋቸው መጥተው ለረጅም ቀናት በእስር ድጋሚ አሰቃይዋቸው። በኋላም ተፈተው ከአርበኞች ትግል ጋር ተቀላቀሉ።

በ1933 ዓ.ም በውጭም ሆነ በውስጥ ያሉ የኢትዮጵያ አርበኞች ኢጣሊያን ከትምክህት ወረራዋ አጨናግፈው ሀገራቸውን ተረከቡ። ቀኛዝማች ተስፋም ወደ ሰላማዊ ሀገራቸው ሊመለሱ ሆነ። ግን በሰው ጉልበት ይሰራራ የነበረው ያ የፅህፈት መሣሪያቸው፣ ያ ኢትዮጵያዊያኖችን” ሲያነቃቃ እና ሲያስተምር የነበረ ማተሚያቸው በጣሊያኖች ተወርሶ ለሌላ ማተሚያ ቤት ተሰጥቶ ነበር። እርሳቸውም ተስፋ ባለመቁረጥ በአዲስና በጋለ መንፈስ ተነሳስተው “ድንቁርና ይጥፋ ዕውቀት ይስፋ፣ ይህ ነው የኢትዮጵያ ተስፋ” በማለት በሌላ ማተሚያ ቤት እያሳተሙ የወገናቸውን እውቀት ለማጐልበት ደፋ ቀና ሲሉ ቆይተዋል።

ከዚያም የህትመት መሣሪያ ከውጭ በማስመጣት የበለጠ በእጥፍ አድገው መንቀሳቀስ ጀመሩ።

ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ ኢትዮጵያዊው ጉተንበርግ ናቸው። የህትመት ማሽንን ከመጠቀም አልፈው ይጠግኑታል፣ ያስተካክሉታል። ፋና ወጊ የማተሚያ መሣሪያ ባለቤት ናቸው።

በተለይም ደግሞ ለሀገራቸው ካበረከቷቸው ታላላቅ ስራዎች ውስጥ እኔን ሁሌም እንዳከብራቸው የሚያደርገኝ በልዩ ልዩ ጊዜ በወራሪዎች የተዘረፉ የኢትዮጵያ አብያተ-ክርስቲያናት ቅርሶች ተረስተው እንዳይቀሩ በተለያየ ዘመን እያሳተሙ በስፋት አሠራጭተዋል። ቅጂያቸው በጣም ትንሽ የሆነ ቅዱሳት መፃህፍት የብራና ፅሁፎችን በመፅሀፍ መልክ እያደረጉ ለታሪክ ትተው አልፈዋል።

የፅሁፍ ስራ፣ የፊደል ቆጠራ፣ የንባብ ችሎታ፣ ሲያሳድጉ፣ የሚሊዮን አማኞች የነፍስ ምግብ ሲያዘጋጁ የኖሩት እና ኢትዮጵያ በእውቀት አደባባይ ባለውለታዬ ብላ የምትጠራቸው ቀኛዝማች ተስፋ ገብረ ሥላሴ ግንቦት 26 ቀን 1992 ዓ.ም በተወለዱ በ97 አመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ይህንንም በጐ ተግባራቸውን በመመልከት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በመቶ አመት ውስጥ ለኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ከፍተኛ ውለታ ከዋሉ ግለሰቦች መካከል በግንባር ቀደምትነት መርጧቸው ረቡዕ ግንቦት 29 ቀን 1999 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም አዳራሽ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እጅ ለባለቤታቸውና ለልጆቻቸው ሽልማት እንዲሰጥ አድርጓል።አሁን በቅርቡ ከሀምሌ 14 እስከ 18 2008 ዓ.ም በተካሄደው ንባብ ለሕይወት በተሰኘው ትልቅ የመጻህፍት አውደ-ርእይ ላይ በሕይወት ባይኖሩም የሰሯቸው ድንቅ ተግባራት ዘላለማዊ ስለሚያርጋቸው “ተስፋ ገብረስላሴ ሕያው ናቸው” በማለት ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል። ባሳለፍነው ቅዳሜ ነሀሴ 28 ቀን 2008ዓ.ም በተካሄደው የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት ስነ-ስርአት ላይ ተስፋ ገብረስላሴ ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል። የእርሳቸው ስም ሲነሳም መድረኩ እጅግ ደምቋል። ድምጸ መረዋው ከያኒ ጸሐዬ ዮሀንስ “ማንበብና መጻፍ…” የተሰኘውን የ1970 ዓ.ም ዘፈኑን ሲያንጎራጉረውማ ታዳሚያን በደስታ ሲቃ ውስጥ ገቡ።¾

 

(ክፍል አራት)

ከ1966-1983

በጥበቡ በለጠ

ሶስተኛው ዘመን ከ1966 ዓ.ም እስክ 1983 ዓ.ም ያለው ሲሆን ይህ ዘመን ከቀደምት ሁለት ወቅቶች የሚለየው የርዕዮተ ዓለም ለውጭ የመንግሥት ቅርጽና መዋቅርን ለውጥን ያስከተለ ሥልጣንን በጠመንጃ አፈሙዝ የተረከበ መንግሥት መሆኑ ነው። በ1966 ዓ.ም ለጥቂት ወራት በአገሪቱ ውስጥ ይህ ነው የማይባል የኘሬስ ነፃነት የታየበት ወቅት ነበር። ይህ የኘሬስ ነፃነት ደግሞ የመጣው በሕግ ድጋፍ ሳይሆን በታሪክና በጊዜ አጋጣሚ ነው። በዚህ ወቅት የግል ኘሬሶች በብዛት ቢታዩም የመንግሥትም ኘሬስ በጣሙን ነፃ ነበር። ጋዜጠኞችም  እራስን ዕቀባ /ምርመራ/ ሰልፍ ሰንሲርሽፕ/ ማድረግ የተውበት ወቅት ነበር ማለት ይቻላል። ይህ ወቅት ግን አልዘለቀም። በ1967 ዓ.ም በታወጀው አዋጅ መሠረት ቀደም ብለው የነበሩ የግል ኘሬሶች መዘጋት /መታገድ/ ጀመሩ።

መስከረም 1968 ዓ.ም በወጣው አዋጅ መሠረት ማንኛውንም የኘሬስ ውጤት ያሳተመ ድርጅት ለማስታወቂያና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ሶስት ቅጅ ማስረከብ እንዳለበት ያስረዳል። ይህን ባይፈጽም አሳታሚ ወይም ባለቤት በ1948 ዓ.ም የወጣው ሕግ ተፈፃሚ ይሆንበታል የሚል ነው። ከዚህ እንደምናየው የቅድመ ምርመራ ጉዳይ ተመልሶ መምጣት ብልጭ ብሎ የነበረውን የኘሬስ ነፃነት በአንዴ ድባቅ እንደመታው ነው። በ1972 ዓ.ም በሻለቃ ግርማ ይልማ የወጣውና ሀያ ስድስት /26/ ነጥቦችን የያዘው የኢንፎርሜሽን መመሪያ ደግሞ ለኘሬሱ ጉዞ ትልቅ ጫና ፈጥሯል። ይህ መመሪያ የሶሻሊስት አገሮች ወዳጅነት እንዲያጠናክር የአብዮቱን ታላቅነት እንዲያሳይ ተደርጐ የተቀረፀ ስልት ነው። በዚህ ምክንያት የምርመራው ባሕሪ ካለፈው የበለጠ እንዲጠናከር ሆኗል።

እንደ ከዚህ ቀደሙ በ1980 ዓ.ም መስከረም በሕገ መንግሥት ደረጃ በአንቀጽ 47 ሥለ ኘሬስ ነፃነት በቁጥር 1 ላይ

1 የኢትዮጵያውያን የንግግር፣ የጽሑፍ፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ትእይንተ ሕዝብ የማድረግ በማሕበር የመደራጀት ነፃነት የተረጋገጠ ነው።

/1980 ሕ.መ. አንቀጽ 47 ቁጥር 1/

ይህ ሕገ መንግሥት ተሻሽሎ ከወጣው ከ1948 የተሻለ ቢመስልም የተጨመሩ ሕጎች /መብቶች/ ለመኖራቸው ማለት ነው/ ነገር ግን ቀደም ሲል የወጣው መሰል አዋጅ ተግባራዊ እንዳልሆነ ሁሉ ይህም ሕገ-መንግስት በአገሪቱ የኘሬስ ነፃነት ላይ አወንታዊ /ተግባራዊ/ የሆነ ለውጥ አላመጣም። በተቃራኒው የዚህ ዘመን ምርመራ ቀደም ካለው የበለጠ ጠንካራ ነበር።

ከ1964 እስከ 1968 ድረስ በምርመራ ዋና መመሪያነት የነበረው በ1968 መምሪያ መሆኑ ቀርቶ በአገልግሎት ደረጃ እንዲዋቀርና ተጠሪነቱም ለቋሚ ተጠሪ እንዲሆን ተደርጎ ነበር። በዚህ ዘመን ከፍተኛ የሆነ የሥነ ጥበባት እንቅስቃሴ በመኖሩ የምርመራው ፈርጅ እንዲሁ ሰፍቷል። በዚህም መሠረት ምርመራውን የሚያከናውነው አካል በሁለት ዋና ዋና ክፍሎቸ ተከፍሎ እያንዳንዱ ክፍል ሁለት ንዑሣን ክፍሎች የያዘ ነበር።

በዚህ ዘመን ኘሬሱ እንዳያድግ በዋነኝነት ማነቆ የሆኑት ጉዳዮችን በዋናነት ቅድመ ምርመራ መኖር፣ የኘሮፓጋንዳው ወገናዊነት ያለው ርእዮት የማይከተሉትን በከፍተኛ ሁኔታ መቃወም፣ ለሌሎች አዲስ ሀሳቦች ዝግ መሆን፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ የሕትመት ፈቃድና ሰጭ ሌላውና ዋናው በረጅም ግዜ የማሕበረሰባችን ልማድ የሆነው ምሥጢራዊነት በተገባው ሁኔታ ለመንግሥት ጋዜጠኞች እንኳ መረጃ የመስጠት ልምድ አለመኖር ዋናዎቹ ናቸው። ምንም እንኳ ቀደም ባሉት ሕጎች ነፃ የመምሰል ፈቃድ ቢኖርም በተግባር ደረጃ እውን ሆኖ አለመታየቱ ትልቁ ችግር ነው።

ከ1983-1991

ሌላውና አራተኛው ከ1983 እስከ 1991 ነው። ይህ ወቅት እንደ አዲስነቱ የሚከተለው ርዕዮት ከቀደሙት መንግሥታት የተለየ በመሆኑ የመንግሥቱ አወቃቀር የተለየ ነው። ይህ መንግሥት በተቋቋመበት ወቅት በ1983 ሐምሌ የሽግግር ወቅት ቻርተር አውጥቶ ነበር። በዚህም ቻርተር በቀዳሚነት ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት ብቻ ሳይሆን በሠላም የመሠብሰብ የመቃወምና የፈለገውን እምነት የማራመድ መብቶች መረጋገጣቸው ተደንግጓል። ይህንም አስከትለው በርካታ የግል ኘሬሶች መውጣት ጀምረው ነበር። በኒህ የግል ኘሬሶች ግፊትም በ1985 የኘሬሶች ለረዘመ ወቅት መታየታቸው ይህንን ዘመን ትንሽ ከቀደምቱ የተሻለ ቢያስመስለው በወጡት ሕጎች ግልጽነት መጓደል እና አሁንም በመንግሥት ኘሬሶች ላይ የሚታየው የኘሮፖጋንዳ ሥራ ብቻ እንዲሁም መረጃ የማግኘት ችግር በተለይ ለግሉ ኘሬስ በተጨማሪም የግል ፕሬሶች የስርጭት አድማስ በህግ ባይከለከልም በአፈጻጸም ረገደር ግን ከዋናው መዲና እምብዛም በይፋ አለመሠራጨት ወዘተ.. ለኘሬሱን ነፃነት ችግር በመፍጠር ረገድ ዋነኞቹ ናቸው።

በአዋጅ ቁጥር 34/1955 ስለኘሬስ ነፃነት በወጣው አዋጅ አንቀጽ 13 ቁጥር 1 እና 2 መሠረት ማንኛውም የኘሬስ ውጤት በተሰራጨ ከሀያ አራት/24/ ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለሚመለከተው አካል ሁለት ቅጅ ማስረከብ አለበት የሚል ነው። /ነጋሪት ጋዜጣ 52ኛ ዓመት ቁጥር 8/ ይህን አይነት ተመሳሳይ ሕግ ቀደም ብሎ በ1927 ዓ.ም ከዛም በ1968 ከወጣው አዋጅ ጋር ተመሣሣይነት አለው። የኒህ አዋጆች ተግባር ቅድመ ምርመራን ለማከናወንና በስርጭት ላይም ካሉ የኘሬሱ ውጤቶች ለማገድ ይረዳ ዘንድ ነው። ስለዚህም ምንም  እንኳ በዚሁ በኘሬሱ ሕግ 34/1985 መሠረት አንቀጽ 3 ቁጥር 2 ላይ

“የቅድሚያ ምርመራና ማናቸውም ሌላ ተመሳሳይ ገደብ በዚህ አዋጅ ተከልክሏል።”

/ስለኘሬስ ነፃነት የወጣ ሕግ 34/1985 ዓ.ም አንቀጽ 3 ቁጥር 2/

ይህን ዘመን አጠር አድርገን ስንመለከት ከሌላው ጊዜ የተሻለ የሚባልለት ነው። ነገር ግን ቀደም ተብሎ እንደተገለፀው የመንግሥት ኘሬስን ከመንግሥት አፋኝነት አለመውጣት፣ የመረጃ የማግኘት ችግርና በሰበብ ባስባቡ ማለትም በሕጉ አሻሚነት የጋዜጠኞች መንገላታት ይታይበታል።

በአጠቃላይ በአራቱም ዘመን ያለው የኢትዮጵያ የኘሬስ ነፃነት የማግኘት ጉዳይ ለውጥ እየመጣ ሔዷል። ነጻነቱ ተሰጥቷል። ነገር ግን በፕሬሱ እና በመንግስት መካከል በየጊዜው ግጭቶች እየታዩ ብዙ ጉዳት ደርሷል። ጋዜጠኞች መንግስትን ይከሳሉ። በህገ-መንግስቱ የሰጠውን የፕሬስ ነጻነት አያከብርም እያሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ትልቁ የፕሬስ ነጻነት በሌሎች ትንንሽ ደንቦችና መመሪያዎች ተሸርሽሯል ይላሉ።

የህትመት መገናኛ ብዙሀን

በሶስት ታሪካዊ ዘመናት የነበራቸው ሚና

በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን /1966 በፊት/

ጋዜጣ በአለም ላይ እየተስፋፋ ለመምጣት ወደ አምስት ምዕተ አመታትን አስቆጥሯል። በአፍሪካም ከመቶ አርባ አመት በፊት በሚሲዮናዊያን አማካይነት በምዕራባዊው ክፍል እንደተጀመረ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ኢትዮጵያ ውስጥም ወደ መቶ ሃያ አመት እንዳስቆጠረ ይነገራል። በኋላም “አእምሮ” በሚል ርዕስ በ1895 ዓ.ም የመጀመሪያው አማርኛ ጋዜጣ እየታተመ ለስርጭት መብቃቱም ይታወቃል።

የኢንፎርሜሽን ስራ በኢትዮጵያ እንዴት እንደተጀመረ እንመልከት አቶ አብዲ አሊ የኢንፎርሜሽን ነፃ ፍሰት ወይም ነፃነት ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በተባለው ጥናታዊ ፅሁፋቸው ላይ የኢንፎርሜሽን ስራ አዋጅ በ1934 በፅህፈት ሚኒስቴር ሥር የኢንፎርሜሽንና ኘሮፓጋንዳ ክፍል ተቋቁሞ በማዕከላዊ መንግስት ቁጥጥርና አመራር መከናወን እንደተጀመረ ያስረዳሉ። በተጨማሪም ከዚህ በኋላ የተለያዩ ስሜት ያላቸው ድርጅቶች ኢንፎርሜሽንን እንዲዘግቡና እንዲያሠራጩ እየተባለ መጠሪያ ሲሠጣቸው እንደቆየ ያወሣሉ። በመጨረሻም በ1956 ዓ.ም ማስታወቂያ ሚኒስቴር የሚል ስያሜ በተሠጠው አካል የኢንፎርሜሽን ስራ ራሱን በቻለ ድርጅት ሥር እንዲተዳደር ተደረገ።

በ1958 የሀያ አምስተኛ አመት አዋጅ ቁጥር 23 ማስታወቂያ ሚኒስቴር የቱሪዝምን አስተዳደር ደርቦ እንዲሠራ ስልጣን ተሠጠውና የማስታወቂያና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተባለ። በዚህም መሠረት አንዳንድ ተግባሮች ተሠጡት። እነሡም።

ሀ. በንጉሠ ነገስቱ መንግስት ግዛት ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ኢትዮጵያና ሕዝቧን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች ጽሁፎች ለማዘጋጀት፣ ለማሣተምና ለሕዝብ መግለጫዎች ለማውጣት የመጀመሪያ ሀላፊነቱ ከመሆኑም በላይ በዚህ ሥራ አፈፃፀም ከቀሩት አግባብ ካላቸው ሌሎች ሚኒስቴሮችና የመንግስት ባለስልጣን መ/ቤቶች ጋር በመተባበር ይሠራል።

ለ. መንግስት ሥልጠናቸው ኘላኖች ኘሮግራሞች አላማዎችና ተግባሮች ሕዝቡ በሚገባ እንዲረዳ ዋና ሀላፊ ነው።

ሐ. አግባብ ካላቸው ሌሎች ሚኒስቴሮችና የመንግስት ባለስልጣን መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር በንጉሠ ነገሥቱ መንግስት ግዛት ውስጥም ሆነ ከግዛት ውጭ ስለሚገለፁትና ስለሚታተሙት የመንግስት ማስታወቂያዎች ኃላፊ ነው።

መ. የግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ባለቤቶችንና ሥራውንም ለማካሔድ የሚያስችል ፈቃድ ወረቀት /ላይሠንስ/ ይሠጣል።

ሠ. ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የሚገቡት የታተሙ ጽሁፎችና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታተሙትም ሁሉ የሕዝቡን ግብረገብነት/ሞራል/የማያበላሹ ወይም የሕዝቡን ፀጥታ የማይጐዱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሀላፊ ነው፡

ምንም እንኳን እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ሀላፊነት ቢሠጡትም ቀስ በቀስ ግን የኢንፎርሜሽን አፈናው እየተበራከተ መምጣቱን ማየት እንችላለን። አቶ አብዲ አሊ ቀደም ሲል በጠቀስነው ጥናታቸው ላይ “ማስታወቂያና መርሐ-ብሔር ሚኒስቴር ያለፋት አሥር አመታት” በሚል የቀረበውን ሪፖርት በመጥቀስ እንዳይተላለፋ ማዕቀብ የተጣለባቸው ነገሮች ወደ ሀያ ስድስት መድረሳቸውን ያስረዳሉ። እኔም ለአጠቃላይ ግንዛቤ እንዲረዳ ከዚሁ ሪፖርት ያገኘኋቸው ገደቦች እንዳሉ ለማቅረብ ወደድኩ።

$11.  የንጉሠ ነገስቱን አገዛዝና ዘውድ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት የሚነካ

$12.  የንጉሣዊያን ቤተሰቦችና የሚኒስትሮችን ክብር የሚነካ

$13.  የሥራ ፈት ብዛት

$14.  የአሠሪና ሠራተኛ ግጭት

$15.  የተማሪዎች ሁከት

$16.  የግብር ጭማሪ

$17.  የኑሮ ውድነት

$18.  የደምወዝ ጭማሪ

$19.  አድማን የሚመለከት ጽሁፍ

$110.ሥለ መሬት ሥሪት

$111.ወታደራዊ ጉዳይ /ስትራቴጂክ ቦታዎች የወታደር ደምወዝ/ የሠራዊት በጀት ወዘተ

$112.የሀይማኖት ልዩነት

$113.የጐሣ ልዩነት

$114.አንድን የውጭ አገር መንግስት አቋም የሚነካ

$115.የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን አቋም የሚነካ

$116.የኢትዮጵያን ሕዝብ ሞራል ዝቅ የሚያደርግ

$117.የኢትዮጵያን አንድነት የሚለያይ

$118.የሴተኛ አዳሪዎችን ብዛት የሚገልፅ

$119.የለማኞችን ብዛት የሚገልፅ

$120.ብልግናን የሚገልፁ ጽሁፎች

$121.የኢትዮጵያን በጀት የሚመለከቱ ጽሁፎች

$122.መንግስት ያወጣውን ኘላን ያለአግባብ የሚተች

$123.የሰውን ሥም ያለ አግባብ የሚያጐድፍ

$124.የኢትዮጵያን የኑሮ ሁኔታ ከሌሎች ሀገሮች ጋር በመጥፎ ሁኔታ የሚያወዳድር

$125.የሌላው ሀገር የሶሻል ፍልስፍና/አይዲዮሎጂ/ ለማስፋፋት የሚሞክር ጽሁፍ

$126.የፓርላማ አባሎች በየጊዜው የሚያደርጉትን ክርክር የሚያብራራ ጽሁፍ

እነዚህ እንዳይገለጡ ግድብ የተጣለባቸው ናቸው። እንግዲህ አንድ የኘሬስ ውጤት የማህበረሰቡን ችግርና መፍትሔውን የፖለቲካ አቅጣጫውን ወዘተ መግለጽ ካልቻለ በፍፁም የኘሬስ ነፃነት አለ ማለት አይቻልም። ጋዜጠኛው በሥራ ፈቱ ብዛት ላይ የግብር ጭማሪን የሴተኛ አዳሪን መበራከት ወዘተ ላለመለከተ፤ ካልተቸበት፣ ካላወያየበት ታዲያ የሱ ፋይዳ ምኑ ላይ ነው? ብለን መጠየቃችን አይቀርም።

በተለይ የቀድሞ ጋዜጦችን በምናነብበት ጊዜ በጠቅላላ ዜናዎች የቤተመንግስት ዜና ሆነው እናገኛቸዋልን። ንጉሡ እንግዳ ሲቀበሉ፣ የስምምነት ጉዳዮችን ሲፈርሙ፣ ጉብኝት ሲያደርጉ፣ የራት ግብዥ ላይ ወዘተ ጉዳዮችን በፊት ገጾቻቸው ላይ ይዘው ይወጣሉ። የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ በማናቸውም የኘሬስ ውጤቶች ላይ እንዳይታይ ተጽእኖ ነበረ ማለት ይቻላል። ዋናው አላማ እሣቸውን አግዝፎ ማሣየት እንደነበር የሚናገሩ አሉ። አንድ በደርግ ጊዜ የተፃፈ ሪፖርት እንደሚያትተው ከሆነ ሀሠትም ይፃፍ እንደነበረ ያስረዳል። ለምሣሌ ንጉሱ በ1946 ዓ.ም አሜሪካን በጐበኙበት ወቅት በኒውዮርክ ቆይታ አድርገው ነበር። እንዲያርፉ የተደረገው በዋልዶርፍ ኦስትሪያ ሆቴል ሲሆን በዚያን ዘመን የማስታወቂያ ሚኒስቴርን ተግባር ይቆጣጠርና አመራር ይሠጥ የነበረው ቦርድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት ንጉሥህ ሆቴል ገቡ ብለን እናወራለን ስለዚህ በእንግሊዝኛው እውነተኛ ወሬ ይወራ፣ በአማርኛው ግን  ቤተመንግስት ተብሎ ይነገር በማለት በሠጠው ውሣኔ መሰረት ዋልዶረፍ ኦስቶሪያ ቤተ-መንግስት ገቡ ተብሎ እስከመነገርና ጉልህ የሆኑ ውሸት እስከመዋሸት ተደርሶ እንደነበር ያትታል። በርግጥ ለዚህ አባባል ሌላ መረጃ ላገኝለት አልቻልኩም።

ይህ ሲባል ግን እንደው በደፈናው ሕትመቶቹ ምንም አልሠሩም ነበር ለማለት አይደለም። በውስጥ ገጾቻቸው ውስጥ ስለ ኪነጥበብ፣ ስነጽሁፍ ታሪክን፣ ማህበራዊ ኑሮን የተመለከተ ወዘተ ነገሮችን በዘመኑም ሆነ እስካሁን ድረስ ትልቅ ስምና ዝና በነበራቸው ሠዎች ይፃፍ ነበር። ጳውሎስ ኞኞ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ አሣምነው ገብረወልድ፣ በአሉ ግርማ፣ ሙሉጌታ ሉሌ ወዘተ የሚያዘጋጇቸው ጽሁፎች አሁንም ድረስ የሚደነቁ እንደሆኑ ለመረዳት ይቻላል።

እንዲሁም በ1966 ዓ.ም ግድም ጋዜጦችና መጽሔቶችን ውስጥ ደፋር የጋዜጠኝነት ስራ እንደተከናወነ ይነገራል። ለምሣሌ በኢሊባቡር ሕዝብ ለስድስት አመታት በተከታታይ ያወጣው የልማት ገንዘብ ለልማት ሣይሆን ለግል ጥቅም በመዋሉ መንግስት ጉዳዩን እንዲያጠና የሚጠይቅ ጽሁፍ መውጣቱ /አዲስ ዘመን መጋቢት 12/66/፤

በዚያን ጊዜ በነበረው የአገር ግዛት ሚኒስቴር ሦስት ሚሊዮን ብር መባከኑን በመግለፅ ሁኔታው እንዲመረመር ሠራተኞች ያቀረቡት አቤቱታ የሠራተኛውንም ችግር በሚመለከትም እንደ ንጉሡ አንጡራ ሀብት ይታይ የነበረውን የአዶላ ወርቅ ማዕድን ሠራተኞች ችግር የሚገልፅ ፅሁፍ መውጣቱ አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/66/፤

 በአዋሽ ሸለቆ የሚገኘው ለም መሬት ለልማት እየተባለ የግል ባለሀብቶች በመከፋፈላቸው የአካባቢው ሕዝብ ለስደት መጋለጡን አዲስ ዘመን ያወጣው ጽሁፍ እንዲሁም የአፋር ተወላጆች ይህንኑ በሚመለከት ያቀረቡትን አቤቱታና /አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን እና 11/66

 የድሬዳዋ ከተማ ሕዝብ ያቀረበውን አቤቱታ ማውጣት /አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 66 /ለምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።

 እነዚህ ጽሁፎች ገና በመግቢያዬ ላይ ያሠፈርኳቸውን የመንግስት ማዕቀቦችን ጥሠው የወጡ ናቸው። ያተኮሩትም በሕዝቡ ሕይወት ላይ ስለሆነ በአርአያነታቸው የሚጠቀሱ ሆነው ተገኝተዋል። ለዚህም ይመስላል ለውጡ እንዲፋጠን አጋዥ ሆነዋል የሚባለው። ከዚህ በተጨማሪም ጋዜጠኞች ከንጉሡ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንኳን ሊጠየቅ ታስቦ የማይታወቀውን የንጉሡን የስልጣን ዘመን ጠይቀው ንጉሡ ታይቶባቸው የማይታወቀውን ሀይለኛ ቁጣ አሰምተዋል። ከኢትዮጵያ ሬዲዮ የድምጽ ላይብረሪ ውስጥ በተገኘው መረጃ መሠረት ጋዜጠኞች ሙያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ሲጥሩ ተስተውለዋል።

በሌላ መልኩ ስናይ የህትመት ውጤቱ ብዛት እጅግ አሣሣቢ ደረጃ ላይ እንደነበረም መረዳት ይቻላል። የሚታቱሙት ጋዜጦች ቁጥር ከሕዝቡ ቁጥር ጋር ፈጽሞ የመቀራረብ ባህሪ እንኳ አልነበራቸውም። ተረዳ አሊ የኘሬስ ነፃነትና አጠቃቀሙ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በሚለው ጥናታዊ ወረቀታቸው ላይ እንዳሠፈሩት የዙፋኑ መንግስት አስከተገረሠሠበት መስከረም 1967 ዓ.ም ድረስ የሁለቱ እለታዊ ጋዜጦች /አዲስ ዘመንና ኢትዮጵያን ሄራልድ/ ሥርጭት 30 ሚሊዮን ሕዝብ እንዳላት በሚገመት ሀገር በቅደም ተከተል 10,000 እና 8,000 የነበረ ሲሆን የጋዜጣው አንባቢ ብዛት ከ1,000 ኢትዮጵያውያን መካከል ሁለት ሠዎች ነበሩ ብለዋል። ከዚህ ሌላ መረዳት የምንችለው መሀይምነት እጅግ ባስከፊ ሁናቴ ላይ እንደነበር ነው።

ዘመነ ደርግ

በዚህ ዘመን የአብዮት እርምጃ ግቡን እንዲመታ በሚል መገናኛ ብዙሃንን የኘሮፖጋንዳው መረማመጃ እንዳደረገው የሚታወቅ ነው። ደርግ ቀድሞ የነበረውን የምርመራ ክፍል ይበልጥ በማጠንከር የሶሻሊዝም ማበብን የማርክስ ኤንግልስና ሌሊን መርሆችን ብቻ በማስተጋባት እንዲወሠን አድርጓል። ሌሎች ሀሣቦችና አመለካከቶች ፀረ አብዮተኛ የሚያሠኙ በመሆናቸው በጋዜጠኛው ላይም ከባድ ጫና የተጣለበት ወቅት ነበር።

ተረዳ አሊ ጥር 29 እና የካቲት 2 ቀን 1987 ዓ.ም መገናኛ ብዙሀን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በተሠኘው ሲምፖዚየም ላይ የኘሬስ ነፃነትና አጠቃቀሙ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት የደርግ ወቅት እንዲህ ይጠቅሱታል።

“ከ1966 ዓ.ም በኋላ በተቋቋመው ወታደራዊ መንግስት ወቅትም የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን በሚኒስቴር በኩል ከመንግስትና ከፓርቲው የሚተላለፉት ርዕዮተ አለማዊ መመሪያዎች መሠረት በመንቀሣቀስ ስለ አብዮቱ አላማዎችና ሥኬታማነት ድሎችና ስለገጠሙት ችግሮች በመስበክ የኘሮፓጋንዳ ሥራዎች ማካሔድ ከተግባሮቹ መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ነው” በማለት ያስረዳሉ።

ይህ ስርአት አዲስ በግል የጋዜጣ ሕትመት ውጤቶችን ለመፍቀድ ሕልምም የነበረው አይመስልም። ምክንያቱም የነበሩትንም ጋዜጦች ሰበብ አስባብ እየፈጠረ ሥለዘጋ ነው። ለምሣሌ ያህል ሰረገላ የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ዋና ማደራጃ ይታተም የነበረው ጋዜጣ በየካቲት ወር 1975፣ ብርሃን መካነ እየሱስ ድርጅት ይታተም የነበረው መጽሄት መጋቢት 23 ቀን 1973ዓ.ም፣ እና ጐህ መጽሔት መስከረም 20 ቀን 1970 ዓ.ም ፀረአብዮት ይዘት አለባቸው ተብለው በመንግስት ትዕዛዝ ከህትመት ታግደዋል።

ደርግ የኘሬስ ውጤቶችን ባብዛኛው የሚጠቁመው ኘሮፓጋንዳ አላማው እንደነበር ግልፅ ነው። ይህ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ቢሆንም በዘመኑ ተፅፈው የተቀመጡ መረጃዎች ራሣቸው እንዳስቀመጡት ኘሬስ ማንኛውንም የአብዮታዊው መንግስት ፖሊሲና መመሪያ ሰፊው ሕዝብ በሚገባ እንዲረዳና ለተግባራዊነቱ እንዲነሣ ለማድረግ ያልተቆጠበ የቅስቀሣና የኘሮፓጋንዳ ስራ አካሂዷል። መጽሔቶችና ጋዜጦች በአብዮቱ ፍንዳታ ማግስት የወጣውን ሶሻሊዝም መመሪያ መሆኑን የሚገልፀው አዋጅ እንዲሁም የእድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ የማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅቶች የገጠር መሬት የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግሥት ያደረገውንና ሌሎችንም አዋጆች ለማስተዋወቅ ፀረአብዮት ሐይሎችንም ተቋም አብዮቱ በድል አድራጊነት እንዲወጣ ለማድረግ በኘሬስ እንደልቡ ተጠቅሞበታል።

ደርግ ሚዲያውን እንደፈለገ ለፈለገው አላማ እንደተጠቀመበት ራሱ በደንብ ይመሠክራል። በ1976ዓ.ም  ጽፈው ባቀረቡት ሪፖርት ላይ “የአብዮቱ አላማዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ኘሬስ ትልቁን ሚና ተጫውቷል” በማለት ይገልፃሉ። ለዚህም እማኝ የሚሆን ከየካቲት 1967 ዓ.ም ጀምሮ ጋዜጦችን የሠፊውን ሕዝብ የመደብ ትግል ለማገዝ በሚል ሀሣብ ለጀመረው አብዮት ማራመጃ አድርጓቸዋል። “በቅድሚያ ማህበረሰቡ የአካባቢውን እንቅስቃሴ መንስኤና አቅጣጫ ለማስረዳት ሲባል በህብረተሰብአዊነት ጉዞ የሚል አምድ የከፈተ ሲሆን ጭሠኛውን የመሬት ባለቤት እናደርጋለን በሚለው ሀሣባቸው የተነሣ ገበሬዎቹ በህብረ-ተሰብአዊ ጉዞ የሚል ተከፍቶም አንደነበረ ማወቅ ተችሏል። ወጣቶች በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ተሠማርተው ወገናቸውን መረዳትና ከሠው ሕይወት መማር አለባቸው በሚለውም ሀሣብ የተነሣ የዘማች የሥራ መመሪያ ማብራሪያ የሚል አምድ ተከፍቶ ዘማቾች ሊያከናውኑ የሚገባቸውን ተግባር በማስመልከት ጋዜጦች ብዙ አስተዋጽኦ እንዳደረጉለት ደርግ ይመሠክራል። የመስመሩ ትግል ተፈጽሞ በነበረበት ወቅት ሣይንሣዊውን መንገድ የሚከተለው ወገን በአሸናፊነት እንዲወጣ የአብዮት መድረክ የተሠኘ አምድ በመክፈት ሠርቶ አደሩ በውይይት ለማሌ ሣይንስ እውቀቱን እንዲያዳብርና የአብዮቱን ጠላቶች የርዕዮተ አለም ክስረት እንዲያውቅ ተችሏል።” በማለትም ያስረዳል።

ከነዚህ ሌላ በርካታ አምዶችንም ከፍቶ አላማውን ለማሠራጨት ይጠቀም ነበር። ለምሣሌ ገበሬው ከአብዮቱ ጐራ ተሰልፎ እንዲታገል ለማነሣሣት በተፈለገው አላማ ላይ ወዛደሩና ገበሬው የተሰኘ አምድ ተከፍቷል። እንዲሁም ወጣቱ የአብዮቱ ቀኝ እጅ እንዲሆን ወጣትና አብዮት የተባለ ሌላም አምድ በማውጣት ጋዜጦች ሥለ አብዮቱ እንቅስቃሴዎች ብቻ ቀን ከሌት እንዲወተውቱ አድርጓቸዋል። በዚህም መሠረት የማስታወቂያና መርሐ-ብሔር ሚኒስቴር ያለፉት አሥር ዓመታት የትግልና የዕድገት በሚል ርዕስ በ1976 ዓ.ም የተፃፈው ሪፖርት ላይ የተቀመጠው እንዲህ ያወሣል።

አብዮታዊ መንግስት የ1968 ዓ.ም ሚያዚያ ወር የብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት ኘሮግራም ካወጣ በኋላ አላማውን ተረድቶ በኘሮግራሙ ውስጥ የተነደፉትን አበይት ጉዳዮች ለሠፊው ሕዝብ በማስረዳትና ለተግባራዊነታቸው ቆርጦ እንዲነሣ ያልተቆጠበ የኘሮፓጋንዳ የቅስቀሣ ተግባር አከናውኗል። ብሎ ካተተ በኋላ በመቀጠልም

ኘሬስ ዛሬም ሠፊው ሕዝብ አብዮታዊው መንግስት ያወጣቸውን የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎትና የአካባቢው ሚሊሽያ ማቋቋሚያ አዋጆችን ተግባራዊ እንዲያደርግና የመከላከያ ሀይላችንን ሕዝባዊ መሠረት ለማረጋገጥ ከፍተኛ የቅስቀሣና ኘሮፓጋንዳ ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛል።

ስለዚህ የኘሬስ ሚዲያ በወቅቱ ያንፀባርቅ የነበረው ከአንድ አቅጣጫ የሚነፍሰውን የፖለቲካ ንፋስ እንጂ በሌሎች ሕዝቡ ማወቅ በሚገባው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አያተኩርም ነበር ማለት ይቻላል። የጋዜጦች የፊት ገጾች በአለም ላይ ሶሻሊዝም እና ኢሠፓ ብቻ እንዳሉ ሁሉ ይዘው የሚወጡት ከነሱ ጋር የተያያዘ ነገር ብቻ ነበር። ሥለዚህ የኘሬስ ነፃነት በወቅቱ ጭላንጭሉም አይታይም ማለት ይቻላል።

አቶ አብዲ አሊ ባቀረቡት ጥናት የዘመኑን ሁኔታ ለማስረዳት (Caputo 1938 P.A) በመጥቀስ እንዲህ ይላሉ እንደ ሀይለስላሴ ሁሉ በደርግ አገዛዝም ኘሬስ ይመረመር ነበር። ማፈንገጥና ተቃዋሚነት የፀረ አብዮተኛነት መግለጫ ተደርጐ ይቆጠር ነበር። በማለት አስቀምጠውታል።

በደርግ አገዛዝ ሚዲያው ምን ያህል ተፅእኖ እንደነበረበት የምንረደው በ1974 ዓ.ም የኢንፎርሜሽ ፖሊሲ መመሪያን ተግባራዊ ለማድረግ የፊልም፣ የፎቶግራፍ፣ የሬዲዮና የፅሁፍ ድጋፍ አጠቃቀም የወጣ የአሠራር ስልት በሚል ርዕስ የወጣው መመሪያ ልክ እንደ ሀይለስላሴ ዘመን ሁሉ 26 ደንቦችን አስቀምጧል። ይህ መመሪያ በታህሳስ ወር 1973 ዓ.ም የወጣውን የማስታወቂያና መረሃ-ብሔር ሚኒስቴር የኢንፎርሜሽን ፖሊሲ መመሪያ መሠረት በማድረግ ዝርዝር የአሠራር ሥልት ያወጣበት ነው። ከነዚህም መመሪያዎች መካከል የጽሁፍ ሽፋን እንዲሠጣቸው የተወሠኑት ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው።

$11.  በመንግስትና በኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሠፓአኮ) ኘሮቶኮል አማካይነት የመንግስት ወይም የኢሠፓአኮ እንግዶች ሆነው ሲጋበዙ

$12.  ሚኒስትሮች ኮሚሽነሮች ቋሚ ተጠሪዎች ወደውጭ ሀገር ሲሄዱና ሲመለሱ

$13.  በመ/ቤቶችና በድርጅቶች ደረጃ ለሚዘጋጁ ሴሚናሮች

$14.  የአ.አ.ዩ ከሚያስመርቃቸውና የደርጉ የቋሚ ኮሚቴና የኢሠፓአኮ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባሎች በሚመረቁበት እንዲሁም በልዩ ትዕዛዝ ለሚቀርቡት ትዕዛዝ ብቻ

በማለት ሌሎች 22 ደንቦችንም አስቀምጧል። ከነዚህም መመሪያዎችና ደንቦች ብዛት አማካይነት በሕትመት ጥራት ላይ ከፍተኛ ጫና አስከትሏል። እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው ጉዳዩች የሚያስረዱት በወቅቱ የነበረው የኘሬስ መዳከም ሁኔታ የሚያስረዱ ናቸው። ቅድመ ምርመራም ዋናው ጉዳይ ነበር። በደርግ ጊዜ በርግጥ ጥቂት የሚባሉ በጐ ተግባሮችን ተጫውቷል ብለን የምንጠራቸው ጉዳዩች አሉ።

$11.  በሀገሪቱ ሥር ሰዶ ከፍተኛ ችግር የነበረውን መሀይምነት ለማጥፋት ኘሬስ በጐ ሚና ተጫውቷል። ከማሃይምነት ተላቀው ማንበብና መፃፍ የቻሉ ጐልማሶችን ወጣቶችን.. ፎቶ ግራፋቸውንና ጽሁፎቻቸውን በማውጣት እንዲሁም አጠቃላይ የመሠረተ ትምህርቱን እንቅስቃሴ ለማጐልበት የወሠደው እርምጃ ደህና ናቸው ከሚባሉት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሣል።

$12.  መኖራቸው እንኳ አይታወቁ የነበሩት ብሔረሰቦች በዘመነ ደርግ መታወቃቸው ጥሩ ነበር። ባህላቸውን፣ አካባቢያቸውን እና ጠቀሜታቸውን መግለጽ መልካም ነበር። እርቃናቸውን ይሄዱ የነበሩት ልብስ መልበስ እንዲለምዱ የለበሰ ሰው ሲያዩ የሚሸሹ የነበሩ ከሠዎች ጋር መልካም ቀረቤታ እንዲኖራቸው ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመስጠት ኘሬስ በጐ ሚና ነበረው ማለት ይቻላል።

የሆኖ ሆኖ እነዚህ ብቻቸውን ለኘሬስ ሥራ በጐ ተግባር አከናውነዋል ማለት አይቻልም። ምክንያቱም አያሌ የማህበረሰቡ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመሠብሠብ ወዘተ መብቶች በመነፈጋቸው የኘሬስ እንቅስቃሴም የቀጨጨበት ዘመን ነበር ማለት ይቻላል።

ከዚህ ሁሉ በኋላ የመጣው አዲስ መንግስት ኢሕአዴግ ነው። ፕሬስ በዘመነ ኢሕአዴግ ምን እንደሚመስል ሌሎቻችሁንም እንድትጽፉበት እጋብዛችኋለው።

 

 

 

****                                        ****                                           ******

 

ለአዲሱ ዓመት ልዩ የኪነጥበብ ምሽት ተዘጋጀ

በሙዚቃ መሳሪያ የታጀቡ የግጥም ስራዎች፣ አዲስ ዓመትን የሚዘክር ትውፊታዊና ሙዚቃዊ ቴአትር፣ መነባነብና ዲስኩሮች የሚቀርብበት ልዩ የአዲስ ዓመት የኪነ-ጥበብ ምሽት በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ተሰናዳ። ሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2008 ዓ.ም ከምሽቱ 11፡30 ሰዓት ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በተሰናዳው በዚህ ልዩ የኪነጥበብ ፕሮግራም ላይ የግጥም ስራቸውን የሚያቀርቡት ገጣሚያን አበባው መላኩ፣ ኤፍሬም ስዩም፣ በረከት በላይነህ፣ ምስራቅ ተፈራ እና ዘላለም ምህረቱ ናቸው ተብሏል። በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ሰዓሊያን የምሽቱን ድባብ የሚያሳይ የስዕል ስራ የሚያቀርቡ ሲሆን፤ የጨረታ ስነስርዓትም ይኖራል። የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ሀበሻ ሮትራክት ክለብና የፊደል ገበታ የቲቪ ፕሮግራም ሲሆኑ፤ የመግቢያ ዋጋውም አንድ እሽግ ደብተር (ደርዘን ደብተር) ወይም 100 ብር መሆኑን ተናግረዋል። ከዝግጅቱ የሚገኘው ገቢ ሙሉ በሙሉ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ታዳጊ ተማሪዎች የሚበረከት ነው ሲሉም አዘጋጆቹ ገልፀዋል።¾

 

በጥበቡ በለጠ

(ክፍል 3)

1983 ዓ.ም እንደመነሻ

የደርግ መንግሥት ሥልጣኑን ከለቀቀ በኋላ በምትኩ የተተካው የኢህአዲግ መንግሥት በ1983 ዓ.ም ላይ መገናኛ ብዙሀን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ነፃ የሆነ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉና ሕዝቦች ሀሣባቸውን በነፃ መግለፅ እንዲችሉ ፈቀደ። ከዚሁ ጋር በዋናነት የሚጠቀሰው የቅድመ ሕትመት ምርመራ የመቆሙ ጉዳይ ሲሆን ማንኛውም አታሚ የሚጠየቀው አትሞ ባወጣው ጽሑፍ እንዲሆን የተደረገበት ወቅት ነው።

በዚያን ወቅት በርካታ የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን፣ ልዩ ልዩ ባህላዊ፣ ሐይማኖታዊ፣ ልቦለድ፣ ስፖርት ነክና የሙያ ማህበራትን የውስጥ ጉዳዮች ንግድና ማስታወቂያ ሕፃናትን ማስተማርና ማዝናናትን የሚዳስሱ እንዲሁም ፖሊሣዊና የዜና አገልግሎት ተግባርን በማካተት የሚያከናወኑ በርካታ የጋዜጣ የመፅሔት የቪዲዩ ፊልሞች፣ የፊልም ምርት እና የድምፅ ቀረፃ ሥራዎች በመንቀሣቀስ ላይ ይገኛሉ። (ልሣነ ማስታወቂያ ገፅ 18)

በዚህ ዘመን የታየ ከፍተኛ ዕድገት ቢኖር የሕትመት ሥራ የመሥፋፋት ሁኔታ እና ብዙ አንባቢያን የማንበብ ፍላጐታቸውን ለማርካት የመቻላቸው ጉዳይ ነው። በዘመኑ ማንኛውም የመፃፍ ፍላጐት ያለውና በኘሬስ ስራ ላይ መስራት የሚፈልግ ሁሉ በህትመት ሥራ መሣተፍ ሲችል በአንባቢ በኩል ደግሞ በርካታዎች አንባቢ የመሆን ዕድሉን አግኝተዋል። በሕትመት ጥበብ በኩል የሄድን እንደሆነ  ጥበቡ በከፍተኛ ሁኔታ ለውጥ አምጥቶ እንደነበር እንገነዘባለን። ብዙዎች የሚዲያ ባለቤት ሆነው ስራ ጀመሩበት ዘመን ነበር። አያሌ ሀሳቦችና አመለካከቶች ይንጸባረቁ የነበሩበት ዘመን አሁን በቅርቡ እዚህ አገር ውስጥ ታይቶ ነበር።

ከዚህ ውጭ የፎቶ ግራፍ ጥበብ የጽሑፍ ቀረፃ ጥበብ .. ወዘተ አያሌ ነገሮች ከህትመትና ከአሣታሚ ማደግ ጋር አብረው ያረጉ ጉዳዩች ተያይዘው መጥተዋል። ይህም ዕድገት የጋዜጠኛውን ብዛት እንዲጨምር የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። በዚህ መሠረት በ1987 ዓ.ም የወጣው ልሣነ ማስታወቂያ መጽሔት እንደሚገልፀው 283 የኘሬስ ሥራ ፈቃዶች ተሰጥተው 54ቱ ፈቃዶች ተመላሽ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 229 ፈቃዶቸ በግለሰቦችና ድርጅቶች እጅ መሆናቸውን ያሳያል። የኘሬስ አዋጅ ወጥቶ ስራ ላይ ከዋለ በኋላ ከ1984 ዓ.ም እስክ 1986 ዓ.ም በወጡ የሕትመት ውጤቶች ዙሪያ ባደረኩት ዳሰሳ መሠረት በተጠቀሰው ዘመን ወደ ሀምሣ አምስት የሚጠጉ ጋዜጦችና ወደ 90 የሚጠጉ መጽሔቶች ሕትመት ላይ እንደነበሩ  ብዛታቸውን አግኝቻለሁ።

እኒህን የሕትመት ውጤቶች በአጠቃላይ ስንገመግማቸውና ስንከፋፍላቸው አጠቃላይ የህብረተሰብ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የፍቅር፣ የስፖርት.. ወዘት የመሣሠሉትን ነገሮች በዋናነት የሚመለከቱ ናቸው። ከተጠቀሱት ብዛት ያላቸው የሕትመት ውጤቶች ውስጥ ከመጽሔት 70 በመቶው የተቋቋሙት በ1985 ዓ.ም ሲሆን 18 በመቶው በ1984 ዓ.ም እና 12 በመቶው በ1986 ዓ.ም የተቋቋሙ መሆናቸውን ለመረዳት ችያለሁ።

 ከጋዜጣ አንፃር ስንመለከት ደግሞ 51 በመቶውን በ1985 የተቋቋሙ፣ 38 በመቶው ደግሞ በ1986 የተቋቋሙና ቀሪው 11 በመቶ በ1984 ዓ.ም የተቋቋሙ መሆናቸውን ለማየት ይቻላል። ከዚህ ውጭ አብዛኞዎቹ ጋዜጦች ሣምንታዊ ጋዜጦች ሲሆኑ አልፎ አልፎ በሁለት ሣምንትና በወር የሚወጡ ጋዜጦች አሉ። ይህ እንኳን አብዛኛውን በስፖርት ጋዜጦች ላይ የሚታይ ባህሪ ነበር።

የመፅሔቶቹን የተመለከትን እንደሆነ በአጠቃላይ በወርሃዊ መጽሔቶች እንደሆነ ለመረዳት ችለናል። የቋንቋ ስርጭትን በተመለከተ ደግሞ ለሁለቱም የሕትመት ዓይነቶች ውስጥ በዋናነት አማርኛ ቋንቋ አገልግሎት ላይ የዋለ ሲሆን በተጨማሪ ደገሞ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ጥቅም ላይ ስውል ይታያል። በተለይ በጋዜጦች ላይ ደግሞ ኦሮምኛና ትግርኛ ከሁለቱ ቋንቋዎቸ በተጨማሪ አገልግሎት ላይ መዋል የቻሉ ቋንቋዎች ናቸው።ይህ ከዚህ በላይ ለማየት የሞከርነው እስከ 1986 ዓ.ም በሕትመት ላይ የነበሩትን ሙጽሔቶችና ጋዜጦች /በግሉ ክፍል/ ሲሆን በቀጣዩቹ ዓመታት የሕትመት እንቅስቃሴያቸውን ያቆሙና አዲስ የጀመሩም ያጋጥማሉ። በተለይ ላቆሙት ጋዜጦች በመንግሥት በኩል የሚሠጥ አስተያየት ሲኖር በግሉም ክፍል ትንሽ ገረፍ ገረፍ አድርጐ ማለፍ ጠቀሜታው የጐላ ነው። ከዚህ በላይ ያነሣሁትን ጉዳይ ይዤ ወደ አንድ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ወደሚሠሩ ሠራተኛ ጐራ ብዬ  ነበር 1992 ዓ.ም። ጥያቄዬም የሕትመት ሥራቸውን ላቋረጡ የግሉ ኘሬስ ክፍሎች በመንግሥት በኩል የሚሠጥ ምክንያት ካለ እንዲያብራሩልኝ በጠየኳቸው መሠረት፤

1.  በአብዛኛው ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በተፈቀደው የሕትመት ሥራ እንቅስቃሴ መሠረት አብዛኞች በሙያው ያልሠለጠኑ ሠዎች ሙያውን ሣያውቁ በዘፈቀደ በመሠማራታቸው ፉክክሩን መቋቋም እንዳቃታቸው፤

2.  ጋዜጣው እንዴት መቋቋም እንደሚችል አለማወቃቸው፤

3.  መጀመሪያውኑ ሲቋቋሙ በጥናት አለመቋቋማቸው፤

4.  ምን ማቅረብ እንዳለባቸውና ይዘው የሚቀርቡት ነገር ምን ሆኖ የሕዝብን ስሜት አግኝተው ለመሸጥ አለማወቃቸው፤ የመሣሠሉ ምክንያቶችን ሠጥተውኛል።

 በአንፃሩ ደግሞ በግሉ ኘሬስ በኩል የሚነሱ ምክንያቶች አሉ። እኒህን ሁለቱን በማነፃፀር በሚቀጥለው ክፍል የምንለመከተው ሆኖ ወደ ዋና ጉዳያችን ስንመለሰ በተከታዩቹ አመታት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ጀምረው ያቆሙ አሊያም አዲስ የጀመሩ የሕትመት ውጤቶችን እናገኛለን። ለዚህም ማነፃፀሪያነት ይረዳን ዘንድ በ1987 ዓ.ም በማስታወቂያ ሚ/ር ልሣን ላይ የወጣውን ሪፖርት መመልከት ጥሩ ይመስለኛል። በሪፖርቱ መሠረት የኘሬስ ፈቃድ ወስደው በእጃቸው ካደረጉት 229 ፈቃድ ጠያቂዎች ውስጥ 84ቱ ባገኙት ዕድል በመጠቀም በንቁ እንቅስቃሴ ላይ መገኝታቸውን በወቅቱ የወጣው ሪፖርት ያመለክታል። እኒህም ሕትመቶች የሚካሄዱት በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በአማርኛና ሐረሪ፣ በአማርኛና ዐረብኛ እንዲሁም በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ሲሆኑ፣ የሥርጭታቸው ወቅት ዕለታዊ፣ ሣምንታዊ፣  የ15 ቀንና ወርሃዊ ነው።

መጽሔቶችን በተመለከተ ደግሞ የሚታተሙበት ቋንቋ፣ ተዘጋጅተው የሚቀርቡበት ቋንቋ፣ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በዐረብኛ ሲሆን ወርሃዊ የሶስት ወርና ከዚያም በላይ የሆነ የሥርጭት ወቅትን በመያዝ ያካሄዳሉ። ከላይ በሪፖርቱ ዋናው ክፍል 84ቱ በንቁ እንቅስቃሴ ላይ መገኘታቸው ቢገለፅም በዝርዝር የቀረቡት ግን 48 ጋዜጦች፣ 14 መጽሔቶች በአጠቃላይ 62 የሕትመት ውጤቶች ናቸው።

በሚኒስቴሩ ሪፖርት መሠረት ከላይ የተጠቀሱት ጋዜጦች የስርጭት መጠን እንደሚከተለው ቀርቧል።

የስርጭት መጠን

ተ.ቁ

የኘሬስ ዓይነት

የስርጭት መጠን

ከፍተኛ

ዝቅተኛ

1

ወቅታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ ጉዳዮች እንዲሁም አስገራሚ ዜናዎችን የሚዘግቡ  ጋዜጦች

13500

3000

2

ወቅታዊ ፖለቲካዊ ማሕበራዊ ጉዳዩች እንዲሁም አስገራሚ ዜናዎችን የሚዘግቡ  መጽሔቶች

10000

7000

3

በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየታተሙ የሚወጡ ጋዜጦች

2200

250

4

የፖለቲካ ድርጅት ልሣን ጋዜጦች

15000

2000

5

የስፖርት ጋዜጦች

13000

3000

6

የሐይማኖት /መንፈሣዊ /ጋዜጦች

7000

3000

7

የሐይማኖት መንፈሣዊ መጽሔቶች

10000

4000

8

የሕፃናት ጋዜጣ

3000

3000

በሶስተኝነት የጋዜጦች የመጽሔቶች የሕትመት እንቅስቃሴን ለማነፃፀር እንዲረዳን ለጥናት የያዝኩት ወቅት ከ1987 ጀምሮ እስከ  1991 ዓ.ም ወቅት ቢሆንም ቅሉ መፈለግ በቻልኩባቸው አካባቢዎች ዕለታዊ ሁኔታን መዝግቦ የመያዝ ሁኔታ ያልተለመደና ደካማ እንቅስቃሴ ስለሆነ መቶ በመቶ የተሟላ መረጃ ነው ባይባልም አብዛኛው መስረጃ ተካተውበታል። በዚህ መሠረትም እስከ ግንቦት 90 ድረስ በህትመት ላይ የነበሩ ጋዜጦች ብዛትና ዝርዝር ለማግኘት ችያለሁ። በመሆኑም እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ ወደ 86 የሚጠጉ ጋዜጦች፣ በአጠቃላይ በግል፣ በመንግሥት፣ በሀይማኖታዊ ድርጅቶች፣ በድርጅት ልሣኖች የሚገኙ ሕትመት ላይ እንደነበሩ ለማወቅ ችያለሁ።

 በመጽሔት በኩል ደግሞ በሕትመት ላይ ያሉትን በትክክለኛ አሀዝ መግለፅ ባይቻልም ከዚህ መረጃ ተነስተን የየራሣችንን ተቀራራቢ ግምት መሥጠቱ የሚያዳግት አይመስለንም። ለመጽሔት በኩል በግሞ አሁን በሕትመት ላይ የሚገኙት የሀይማኖታዊ ድርጅቶች መጽሔቶች ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ  የድርጅት መጽሔቶች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ከዚህ ውጭ ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን የሚዳስሱት በጣም ጥቂት እንደሆኑ ነው ለመረዳት የቻልነው። በአጠቃላይ ከ26-30 መጽሔቶች በሕትመት ላይ እንደነበሩ ነው መረጃው የሚያመለክተው። ይህ አሀዝ ግን የተለያዩ መ/ቤቶችንና ተቋሞችን የህትመት ሥራ የሚያጠቃልል አይደለም።

በሕትመት እንቅስቃሴ ውስጥም ቦሌ ማተሚያ ቤት፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ የሜጋ ህትመት ኢንተርኘራይዝ፣ ብራና ማተሚያ ቤት በዋናነት የሚሣተፉ ሲሆን በጋዜጦች ሕትመት ረገድ በተጠና ጥናት 46 በመቶ በብርሃንና ሠላም ማተሚያ ቤት፣ 36 በመቶ በቦሌ ማተሚያ ቤት፣ 9 በመቶ በሜጋ የህትመት ኢንተርኘራይዝና 9 በመቶ በብራና ማ/ቤት ይታተሙ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

የኘሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ

የፕሬስ ነጻነት ማለት የሀገር ነጻነት ማለት ነው እያሉ የሚያስተምሩ የጋዜጠኞች መማሪያ የሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች በርካቶች ናቸው። ነጻ ሀገር ነጻ ፕሬስ ይኖራታል ተብሎ ይታመናል። ይህ ደግሞ አንጻራዊ ነው ብለው ከወዲያ በኩል የሚሞግቱም አስተሳሰቦች አሉ። አለምን በተለያዩ የአስተሳሰብ ካምፖች ከፋፍለው የምስራቁ እና የምእራቡ አስተሳሰብ በማለት ፕረሱንም እንደየ አገሩ ባህልና ልማድም የሚሸነሽኑት አሉ። ስለዚህ ፕሬስ ሙሉ በሙሉ ነጻ ነው ብለን አፋችንን ሞልተን የምንገልጽባቸው አገሮች ብዙም አይደሉም። ግን ሁሉም ነጻ መንግስታት ፕሬሶቻቸውን በነጻነት ያለ አፋኝ እና አታካች ህጎች እንዲለቋቸው መምህራን ይናገራሉ።

ፕሬስን ከሰው ልጅ የመተንፈሻ አካላት አንዱ እንደሆነ ከሚነገርለት ከሳንባ ጋር እመሳሰሉ የሚያስተምሩ ዩኒቨርሲቲዎች በርካቶች ናቸው። የሰው ልጅ ስርአት ሚኖረው የመተንፈሻ መሳሪያው ፕሬስ ሲኖረው ነው የሚሉም አሉ። ፕሬስ ከሌለ ሁካታ፣ ድንፋታ፣ ግርግር፣ ውዥንብር፣ ያለመረጋጋት ወዘተ ይፈጠራል እያሉ በርካቶች ከዚህ ቀደም ጽፈዋል። ስለዚህ ፕሬስ ህዝብን አደብ መስገዢያ ነው ማለትም ይቻላል። ስለ ፕሬስ ብዙ የፍልስፍና አባባሎች ሁሉ አሉ። የበርካታ አስተያየቶች ማዕከል ነው። በምንግስት አወቃቀር እንክዋን ንጉሳዊ፣ ሪፐብሊክ፣ ወታደራዊ፣ ሀይማኖታዊ ወዘተ እየተባለ ይከፋፈላል። ከርሱ ጋር ተያይዞም የፕሬስ አስተሳሰብም ይገለጻል። ጉዳዩ ሰፊ ነው። ወደፊት ብዙ እንነጋገርበታለን። ለአሁን ግን ሀገራችንን በታሪክ ውስጥ እንቃኛት።

ፕሬስ ከ1917-1923 ዓ.ም በኢትዮጵያ

ወደ ሀገራችን ሥንመጣ የኘሬስን ታሪክ በአራት ከፍልን ማየቱ ምን ህል ነፃ ሆኗል አልሆነም የሚለውን ለማወቅ ያስችለናል። የመጀመሪያው የማተሚያ መሣሪያ ወደ ሀገራችን በተለይ አዲሳባ ከገባበት ወቅት አንስቶ እስክ 1913 ያለው ወቅት ሲሆን፣ በዚህ ወቅት አገሪቱ የምትመራበት ሕገመንግሥት በይፋ ባይታወቅም ዘመናዊነት የተጀመረበት ንግሥት ዘውዲቱ አገሪቱን ከአልጋወራሹ ጋር የሚያስተዳድሩበት ወቅት ነበር። በዚህ ወቅት ይታተሙ የነበሩ ሁለት ጋዜጦች ሲሆኑ፣ አእምሮ እና ብርሃንና ሰላም ናቸው።

 አእምሮ አብዛኛው ስለ ንግሥት ዘውዲቱ የሚያወራ ጋዜጣ እንደነበር ጥናት ያረጉ ይናገራሉ። ብርሃንና ሰላም ደግሞ ስለ አልጋወራሹ የሚያወሣ ነበር ይላሉ። በዚህ ዘመን ቀደም ተብሎ እንደተጠቀሰው ይህ ነው የሚባል ሕግ መንግሥት ባይኖርም ወደ ሰባት የሚደርሱ ምኒስትሮች ቀደም ብለው በዳግማዊ አፄ ምንሊክ መሾማቸው ይታወሣል። ይህም ዘመናዊ የሆነ የአሰራር ስልት ለመቀየር ከተጀመሩት ጅማሮዎች አንዱ ነበር። ታዲያ የዚህ ሕገ መንግሥት አለመኖር በኘሬስ ደረጃ በወቅቱ አንዳንድ ሥራዎች በነፃ እየተዘጋጁ ይወጡ ነበር። ምንም እንኳ ከወጡ በኋላ ንግሥቲቱን አስቀይመዋል ተብሎ ስራዎቹ የመሰብሰብ አደጋ ቢያጋጥማቸውም በጥቅሉ በዚህ ዘመን የነበረውን የሕግ ተጽእኖ ሣይሆን ለኘሬሱ ማደግ የመሪዎቹ እና የአንዳንድ ትልልቅ ባለስልጣናት ተጽእኖ ብቻ ነበር የሚታየው።

ፕሬስ ከ1923-1966 ዓ.ም በኢትዮጵያ

ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ከ1923-1966 ያለውን ሂደት ስንመለከት ለየት ያለ ሁኔታ እናገኛለን። ከ1923 ዓ.ም ለሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕገ-መንግስት ተቀረፀ። ይህ እንግዲህ ንጉስ ኃ/ሥላሴ ንግሥና የተቀበሉበት ዓ.ም ነው። በዚህ ሕገ-መንግስት ውስጥ በ26ኛው አንቀጽ እንደተቀመጠው

“ሕግ ከሚፈቅድበት ጊዜ በቀር የኢትዮጵያ ተወላጅ የሚጻጻፈውን ጽሁፍ ማንም ሰው ቢሆን ሊመረምርበት አይችልም።”

/ውለታው ባዬ፣ የ1923 ዓ.ም ሕገ-መንግስትን ጠቅሶ እንዳስቀመጠው /

ይህ አንቀጽ እንደሚያመለክተው የተብራራና ሰፋ ያለ ነገር ስለኘሬስ ባያስቀምጥም፣ ማንም ሰው ያለ ቅድመ ምርመራ እንደልቡ መጻፍ እንደሚችል ነው። ይህ ቢሆንም ግን ሕጉ መቼና በምን አይነት ሁኔታ ምርመራን እንደሚፈቅድ አይገልጽም።

ይህንን ሕገ-መንግስት ድንጋጌ ተከትሎ  የኘሬስ ውጤቶችን በተመለከተ በአዋጅ ደረጃ የካቲት 7/1927 ዓ.ም ጋዜጣንም ሆነ ማተሚያ ቤት ለማቋቋም ፈቃድ እንደሚያስፈልግ ታወጀ። ህጉ ይህንን ሳያሟላ ሁለቱንም ማቋቋም እንደማይችል ያስረዳል። ከዚህም በተጨማሪ የግለሰቦችን ስም ማጥፋት፣ መንካት፣ በህግ የተከለከለ እንደሆነና ይህንንም የፈፀመ ኘሬስ ስሙ ለጠፋበት ሰው በኘሬሱ ላይ አጸፋውን በኘሬሱ ኪሣራ ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ መልስ የመስጠት መብት እንዳለው ይገልጻል። ከዚህም ባሻገር የኘሬስ ውጤቶች ከታተሙ ሁለት ቀን /48 ሰዓት/ ከማፉ ቀድሞ ሶስት ቅጅ ለሚመለከተው የመንግስት መሥሪያ ቤት መሥጠት አለበት።

ይህ መሥሪያ ቤት የወጡትን ጽሁፎች በመመልከት እንዳይሰራጩ የማገድ ብሎም አሳታሚ ድርጅቶችን የመዝጋት መብት ሲኖረው ከውጭ ሀገር የሚመጡ የኘሬስ ውጤቶችን መርምሮ እንዳይያስራጩም የማድረግ መብት አለው።

እስካሁን እንዳየነው በሂደት የኘሬሱ ሕግ እየጠበቀ፣ ነፃ የመሆን አዝማሚያው እየቀነሰ እንደመጣ እንመለከታለን።

ከ1927 ዓ.ም ጀምሮ ፈቃድ በመስጠትና በማገድ ስልጣን ተሰጥቶት የነበረው ለመንግስት አካል ነበር። በ1934 ዓ.ም ደግሞ ሥልጣኑ በተለይ ቅድመ ምርመራን በማስጀመር በሀላፊነት የጽሕፈት ሚኒስቴር እንዲያከናውነው ተደርጓል። በመለጠቅ በ1935 ዓ.ም በወጣው ሕግና መመሪያ መሠረት ቅድመ ምርመራው በሀገር ውስጥ የሚዘጋጁ የኘሬስ ውጤችን እና ከውጭ  የሚገቡ የኘሬስ ውጤቶችን ብቻ ሣይሆን ፊልምና ቲያትርንም እንዲያጠቃልል ሆኗል። በዚህም ወቅት ማናቸውም የኘሬስ ውጤቶች የሕትመት ቤቱን ስም የመግለጽ ግዴታ  ነበረባቸው። የፊልምና የቲያትር መርማሪው በከፊልም ሆነ በምስሉ ማገድ ሲችል የቀደሚውን ቁጥር የመወሰንም መብት ነበረው።

ይህን ሕግ ለተላለፈ ከ1927 ዓ.ም ጀምሮ ማለት ነው በብር እስክ 500 /አምስት መቶ ብር /ወይም 6 /ስድስት/ወር እስራት አልያም ሁለቱም ውሳኔ ተግባራዊ እንደሚሆን ሕጉ ያስቀምጣል። በየወቅቱ ተሻሽለዋል እየተባለ የሚወጡ መመሪያዎች የኘሬሱን ነጻነት ከቀድሞው በበለጠ እያጠበቡት ነው የመጡት። ይህ ቢሆንም እንኳ በ1948 ዓ.ም ሕገ-መንግስት. ራሱ ተሻሽሎ ሲወጣ በምእራፍ ሶስት አንቀጽ 41 የኘሬስ ነፃነት እንዳይገደብ የሚደነግግ አዋጅ እናገኛለን።ይህንንም በመርህ ደረጃ የተቀመጠ እንደሆነ ነው በጉልህ ተከታትለው የሚወጡ ሕጐችና መመሪያዋች የምናየው።

“በመላው የንጉሠ ነገሥት ግዛት ውስጥ በሕግ መሠረት የንግግርና የጋዜጣ ነፃነት የተፈቀደ ነው።” /ሕ.መ. 1948 አንቀጽ 41/

በሌላ በኩል ይህንኑ ሕግ የሚያጎለብት ሕገ-መንግስትን መሠረት በማድረግ በ1952 የፍታብሔር ሕግ ወጥቷል።

ይህም ማንኛውም ሰው የማሰብና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት አለው። ይህንን ሀሳቡን ሊቀንሱበት የሚችሉት የሌሎችን መብቶቸ የማክበር ግዴታዎች መልካም ባህልንና ሕጐችን አክብሮ የመጠበቅ ግዴታዎች ናቸው። /ፍ.ብ.ሕ.1952/

በ1948 ዓ.ም የወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግም መገናኛ ብዙሀንን በተመለከተ ባወጣው ሕግ፡-

 “በሚያጠራጥር ምክንያት ለሕዝቡ መገለጻቸው በሕግ በቂ በሆነ ምክንያቶች ወይም ለዚህ በግልጽ ለተሰጠ ውሳኔ በተለይ የተከለከሉ ካልሆነ በስተቀር ያንድ ትችት ውሣኔ መግለጫ ወይም በታረመ እቅድ የወጣ ያንድ ሰው እውነተኛ መግለጫ የሕግ አውጪዎችን፣ የአስተዳዳሪዎችን፣ የፍርድ ባለስልጣኖችን፣ ክርክር ወይም ቃለ ጉባኤ ያተመ፣ ያስታወቀ፣ የገለጠ ደራሲ ወይም ጽሁፍ አታሚ ወይም ተናጋሪው አይጠየቅም።”

/ወ.መ.ሕ. አንቀጽ 47 '1948/

የ1948 ዓ.ም ሕገ-መንግስት መሠረት አድርገው የወጡት 1952 ፍ.ብ.ሕግም ሆነ የ1948 ወ.መ.ሕግ አስከተወሰነ ደረጃ ለኘሬሱ ነፃነት ድጋፍ ይሰጣሉ። ነገር ግን ፍ.ብ.ሕ. እንደ አብነት ወስደን ያየን የግለሰቦችን መብት ማከበር ሲባል እንዴት ነው? ግለሰቡ የሚሠራውን አሥነዋሪ ድርጊት ባለመግለጥ ነው።  በተለይ በመንግሥትና በሕዝብ ሀብትና ንብረት በስልጣን ከለላ ያሉ ሰዎችን ብንወስድ ይህ ነውር ቢኖርባቸውና ቢወጣ ክብርና መብታቸውን ተነካ ማለት ነው። መልካም ባሕል የምንለው ምን እና ምን እስከምን ድረስ እኒህን የመሳሰሉት ሕጎች አሁንም ግልጽት የጐደላቸው ይመስላል። ከዚህም በተጨማሪ በዚያን ዘመን የነበሩ የኘሬስ ውጤቶች እንደሚያስረዱት ከአንዱ ወገን የቀረቡ በመምራት ላይ ያሉትን አካላት በተለይም ንጉሡን የሚያሞካሹ አልፎም ወደ መመለክ ደረጃ የሚያዘጋጁ ዝግጅቶች ሲሆን በወቅቱ የነበሩትን የማሕበረሰቡን ችግር እምብዛም የማያንፀባርቁ ናቸው።

በ1960 ዓ.ም በፀሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ጠ/ሚኒስቴርና የጽሕፈት ሚኒስቴር አማካይነት የግል ኘሬሶች መውጣት አንደሚችሉ ይፋ አድርገዋል። ማንኛውም የግል ኘሬስም ለማቋቋም ለሚፈልጉ ፈቃድ እንደሚሰጥ ቢያስታውቁም ከዚህ ቀደም ብለው በ1950ዎቹ የተቋቋሙ የግል ኘሬሶች ግን ነበሩ። በመሠረቱ ከዚህ ቀደም ብሎ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን በጠቅላላው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ቢሆኑም እንኳ የግል ኘሬስ እንዲቋቋም የሚፈቅድም ሆነ የሚከለክል ሕግ ባለመኖሩ አዲስ ነበር ለማለት ይቻላል።

በአጠቃላይ ከ1923 እስከ 1966 ዓ.ም በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የኘሬስ ገደብ ስናይ በሁለት በኩል ከፍለን ብናይ የተሻለ ይሆናል። አንደኛው በሕጉ አሻሚነትና በመንግሥት ተጽእኖ ምክንያት እድገት ተገድቧል። ለዚህም በዋነኝነት እንደምክንያት የሚጠቀሱት ቅድመ ምርመራ በኘሬስ ስራዎች ላይ ጋዜጠኛው ሊያዘጋጀው የሰበውን ነገር በበላይ አካላት ትእዛዝ መሆን፣ ከትእዛዙ ፈቀቅ ሲል ቢያነስ የቦታ መዛወር፣ የደረጃና የደሞዝ ቅነሳ ሲበዛ ከሥራ መባረር በዋናነት ከሚጠቀሱት ከፊሎች ናቸው። ሁለተኛው የጋዜጠኞች የሙያ ብቃት ለጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር አለመገዛት ነው። በዋነኝነት በማባበያና በድለላ መሸንገል ደጎማዎችን መቀበል ሲሆን ሥርአቱ በጥቅሉ ጋዜጠኞችንም ሲመለምል ታማኝነታቸው የተረጋገጠላቸው የሥርዓቱ ማገር ሊሆኑ የሚችሉትን ነው። ይህ ሲባል ግን በዘመኑ ሙያቸውን ባገኙት ክፍተት የተጠቀሙ ጋዜጠኞች የሉም ማለት ግን አይደለም።

“የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ጋዜጠኞችን ይፈራ እንደነበር ግን የወደደ መሥሎ በሚያደርጋቸው መደለያዎች ይበልጥ ይታወቃል። ከሚታወቅባቸው ፐርዳይም መስጠት፣ በዓመት ቦነስ ከመስጠት ጋር ቤተመንግሥት ይሠሩ ለነበሩ ጋዜጠኞች ጫማ ከነ ሙሉ ልብስ ይሰጥ ነበር። ከዚያም አልፎ ለጥቂቶች ቤተመንግሥታዊ ግብርና እና ሌሎችም መደጎሚያዎቸ ይሰጥ ነበር።”

/ውለታው ባዬ የደነቀ ብርሀኑ ጥናታዊ ጽሁፍ ጠቅሶ እንዳስቀመጠው/

ፕሬስ ከ1966 በኋላ በኢትዮጵያ

(ይቀጥላል)¾

 

(ክፍል ሁለት)

በጥበቡ በለጠ

የአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመነ መንግሥት

አፄ ኃ/ሥላሴ የሥልጣን መንበሩን ከተረከቡ በኋላም ይህ የሕትመት እንቅስቃሴ ቀጥሎ መዋሉን ነው የምንረዳው። ከዚህ ዘመነ መንግሥት በፊት የነበሩት የማተሚያ ቤቶች በዋናነት ይንቀሣቀሱ የነበሩት በእጅ ሲሆን ይህ ለጋዜጣ ሥራ እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር ማወቅ ተችሏል። በመሆኑም አፄ ኃ/ሥላሴ እ.ኤ.አ በ1923 ዓ.ም የማተሚያ ቤት እንዲከፈት አደረጉ። ይህም መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ መንግሥት አልጋ ወራሽ የልዑል ራስ ተፈሪ ማተሚያ በመባል ይታወቅ ነበር። ማተሚያ ቤቱ በወቅቱ ሲቋቋም በ30 ያህል ሠራተኞች ገ/ክርስቶስ ተክለ ሀይማኖት በሚባል ሰው ተቆጣጣሪነት ይሠራ ነበር። ይህ ሰው በስዊድን ሚሲዮን በአስመራ  የተማረ ሰው ነበር። ይህ የማተሚያ ቤት ወዲያውኑ ብርሃንና ሠላም የሚል ሥያሜ  ወጥቶለት ጋዜጦችንና መፅሐፎችን ማተም ቀጥሏል። ይህ ዓመት በሕትመት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስራ የተሠራበትና ተጠቃሽ ዓመት እንደሆነ ይነገራል።

 

በዚህ መሠረትነትም በ1917 በማተሚያ ቤቱ ስም የተሠየመው ጋዜጣ መታተም ጀመረ። ይኸው ብርሃንና ሰላም የተባለው ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት ይሠራ የነበረው ገ/ክርስቶስ ተ/ሀይማኖት የተባለው የማተሚያ ቤቱ ተቆጣጣሪ ሲሆን ጋዜጣው በሣምንት እየታተመ ይወጣም ነበር። ይህ ጋዜጣ በ500 ቅጂዎች ያህል ይታተም የነበረና የስርጭቱም ሁኔታ ይካሄድ የነበረው በሁለት ፈረሰኞች አማካኝነት እንደነበር ታሪክ ይናገራል።

 

ከብርሀንና ሰላም ጋዜጣ መመስረት ጥቂት ጊዜ በኋላም በየሣምንቱ እየታተሙ የሚወጡ ጋዜጦች ቁጥር 3 ደረሰ። ሁለቱ ቀደም ብዬ የጠቀስኳቸው አእምሮ እና ብርሃንና ሰላም ሲሆኑ፣ ሶስተኛውና በፈረንሣይኛ የሚታተመው ኩሪየር ዳ ኢትዮጵ የሚባለው ነበር። ብርሃንና ሰላም በጊዜው ገናና የነበረ ጋዜጣ እንደነበር ስቴፈን ጋሴል The beginning of printing in Abyssinia በተሰኘው መጽሐፋቸው ጠቅሰዋል። ይህንንም ለማስረዳት የብርሐንና ሰላም 500 ቅጂ ስርጭትን፣ ከአእምሮ የሁለት መቶ ቅጂ ጋዜጦችን በማወዳደር አቅርበዋል። ከብርሀንና ሠላም ማተሚያ ቤት ሌላ፤ ጐሐ ጽባህ በተባለው ማተሚያ ቤት ደግሞ ከሣቴ ብርሃን የሚባል ጋዜጣ እየታተመ ይወጣ እንደነበር ታውቋል። ይህ ግን ወዲያውኑ በፋሽስት ወረራ ምክንያት እንደተቋረጠ  ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።

በኢጣሊያ ወረራ ዋዜማ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰባት ያህል ማተሚያ ቤቶች በአዲስ አበባ እንደነበሩ ሪቻርድን ፓንክረስት Foundation of Education. በተባለው መጽሐፋቸው ጠቅሠዋል። እነዚህም ማተሚያ ቤቶች፡-

 

 

1ኛ የመንግሥት ማተሚያ ቤት የነበረውና አፄ ሚኒልክ የከፈቱት

2ኛ የኮሪ የሬ ደ ኢትዮፒየ ኘሬስ በ1906 ዓ.ም የተቋቋመው፣

3ኛ የአፄ ኃ/ሥላሴ ማተሚያ ቤት የነበረው ብርሀንና ሰላም /1917/

4ኛ ጐሐ ጽባሕ በ1919

5ኛ ሔርሚስ ማተሚያ ቤት በ1919 የተቋቋመና ‘ለ ኢትዮጵፒየ ኮሜርሺያሌ’ የሚባል ጋዜጣን የሚያትም

6ኛ ሉክ /LOUC/ ማተሚያ ቤት በአርመናዊው ኤች ባግዳሳሪያን /H. Bagdassarian/

7ኛ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት በ1927 ዓ.ም በሁለት ሌሎች አርመናውያን በኢ.ጀራሂያን እና ጂ. ጀራሂያን E. Djerrahian and G. Djerrahian   የተቋቋሙት ናቸው።

 

በዚህ ጊዜም ከሰባት የማያንሱ ጋዜጦች የነበሩ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አራቱ በአማርኛ ቋንቋ የነበሩ ሲሆን፣ ሁለቱ በፈንሣይኛ እና አንዱ በጣሊያንኛ ቋንቋ ይታተሙ ነበር። የአማርኛ እትሞቹ ሶስት ሣምንታዊ ሲሆኑ፣ እነዚህም የመጀመሪያውና አንጋፋው አእምሮ ሲሆን፣ በአራት ገጽ ይታተም ነበር። ሌላው ብርሃንና ሰላም ሲሆን፣ በካሻዱያ የሚመራው የብላቴን ጌታ ህሩይ አጥቢያ ኮከብ ሁለቱም ባለ ስምንት ገጽ ናቸው። አጥቢያ ኮከብ የተመሠረተው በ1927 ዓ.ም ሲሆን በተከታዩ ዓመታት ከሳቴ ብርሃን የሚባል ባለ ስምንት ገጽ ወርሀዊ ጋዜጣ እንደተቋቋመ ማወቅ ተችሏል። ከውጭ ቋንቋ ጋዜጦችም በሣምንት ሁለት ቀን የሚወጣው ባለ ስምንት ገጽ ጋዜጣ ለ ኤሪዩሪ ዳ ኢትዮጲ የተባለና ለኢትዮጵያ ኮመርሽያል የተባለ ሣምንታዊ የፈረንሣይኛ ጋዜጣ ከ12 እስከ 14 ገጽ በመያዝ ይታተሙ ነበር። ኤል ኖቲዛሪዮ /EI Notiziario / የተባለ በየአስራ ምስት ቀኑ የሚወጣ የጣሊያንኛ ጋዜጣ ከ6 እስከ 8 ገጾችን በመያዝ ከ1926 ዓ.ም ጀምሮ መውጣት ጀምሮ ነበር። ከዚህ ውጭ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ሁለት የውጭ ጋዜጦች መታተም ጀምረው ነበር። እኒህም የመጀመሪያው ኤቲዮፒኮስ ኮስሞስ /Aithiopikos Kosmos/ የተባለ በፒ.ኬ. ቨሪኒዮስ /P.K. vryennios ከ1920 እስከ 1924 ዓ.ም ድረስ የታተመው ሣምንታዊ ጋዜጣ እና ኢቲዮፒካ ኒያ /Aithiopika Nea/ የተባሉት ጋዜጦች ናቸው።

 

ከዚህ በላይ በጥቅሱ ለማየት የሞከርነው በሀገር ውስጥ የታተሙትን የህትመት ውጤቶች ሲሆን፣ ከሀገር ውጭ ኢትዮጵያዊ ጋዜጣዎች ከ1928 ዓ.ም በፊት ይተታሙ ነበር። ከነዚህ ውስጥ በመጀመሪያ የታተመው በአውስትራላዊው ዶ/ር ኤሪክ ቬይንዚንግ /Dr. Eric Weinzing አንዳንዴ አይቶኘየን ኮረስፖንደንዝ /Aithiopien-Korrespondenz/ በመባል የሚታወቀው ነው። ይህ ጋዜጣ በጀርመንኛ በእንግሊዝኛ እና በፈረንሣይኛ የተፃፉ መጣጥፎችን የያዘና ተከታታይነት በሌለው መልኩና በተለያዩ ቦታዎች የታተም ነበር። ለመጥቀስ ያህልም በፓሪስ፣ በቪየና በ1919፣ በአዲስ አበባ ከ1920-1921 በፓሪስ እስከ 1924 ይታተሙ ነበር። የዚህ ጋዜጣ ዋና ዓላማ ተደርጐ የተገለፀውም ኢትዮጵያ በአውሮፓውያን ዘንድ የበለጠ እንድትታወቅ ለማስቻልና ከሌሎች ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ትስስር የበለጠ ለማጠናከር የሚል ነበር። ከዚህ ሌላ ለ ኢትዮጵያ ኖቪል /Le Ethiopia Nauvell  በፈረንሣዊው A. Natailer እየተዘጋጀ በየሁለት ወሩ የሚቀርበው ሲሆን፣ ሌላው ኢትዮጵያ Ethiopia የተባለው ከፓሪስ የሚመጣው ወርሃዊ እትም ነበር።

 

ከጦርነቱ በፊትና በኋላ በጣም ብዙ ጋዜጦች በውጭ ሀገር ኢትዮጵያውያን በተመለከተ እንደተቋቋሙ ታውቋል። ከዚህ መሀልም ዘቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ የተባለ ጋዜጣ በዶ/ር መላኩ በያን አዘጋጅነት በኒወዩርክ ውስጥ ይታተም ነበር። ዶክተር መላኩ በያን አሜሪካ ውስጥ በህክምና ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረቁ ኢትዮጵያዊ ሲሆን በዘመናቸው ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ አፍሪካ አንድነት የሚታገሉ ታላቅ ሰው ነበሩ። ፋሽስት ኢጣሊያን ከኢትዮጵያ ምድር ለማባረር ከታገሉ ታላላቅ ምሁራን መካከል አንዱ ናቸው። የእርሳቸውም ጋዜጣ በኢትዮጵያ የፕሬስ ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ ነው። ሌላው ለቮክስ ኢትዮ /La Voix DE l’Eth./ የተሰኘው ጋዘጣ ለአጭር ጊዜ ከ1928 እስከ 1929 በፈረንሣይ ይታተም ነበር።

 

 

በኢትዮጵያ የጋዜጣ ታሪክ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው በእንግሊዛዊቷ የኢትዮጵያ አርበኛ በሲልሺያ ፓንክረስት አማካይነት ይታተም የነበረው ኒው ታይምስ ኤንድ ኢትዮጵያን ኒውስ /New Times and Ethiopian News/ የተሰኘው ጋዜጣ ነው። ለሃያ ዓመታት ከ1929 ዓ.ም እስከ 1949 ዓ.ም ታትሟል። ይህ ጋዜጣ  በመጀመሪያ ለንደን ከተማ ውስጥ ይታተም ነበር። አላማው ኢትዮጵያን ከኢጣሊያ ወረራ ማላቀቅ ነበር። የትግል ጋዜጣ ነበር። ሲልቪያ ፓንክረስት ዋና አዘጋጅ ነበረች። እነ ተመስገን ገብሬ ከሱዳን ገዳሪፍ ሆነው እንደ ሪፖርተር ወሬ አቀባዮች ነበሩ። ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት በተደረገው ርብርብ በታሪክ ውስጥ ሁነኛ ቦታ የሚሰጠው የክፉ ቀን ደራሽ ጋዜጣ ነው። ዛሬ አዲስ ዘመን እያልን የምንጠራው የመንግስት ጋዜጣ ስያሜውን ያገኘው New Times ከተሰኘው የሲልቪያ ፓንክረስት ጋዜጣ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል። እናም ሲልቪያ ፓንክረስት በኢትዮጵያ የአርበኝነት፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የማንነት ጉዳዮች ላይ ከሰራቻቸው አበርክቶዎች ባልተናነሰ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥም ያበረከተችው ውለታ ገና ብዙ ዘመን ይዘከራል።

 

 

ከላይ ለማየት እንደሞክርነው እስከ 1928 ዓ.ም ድረስ በርከት ያሉ ጋዜጦች መውጣት ቢችሉም ከ1928 ዓ.ም በኋላ ግን ይህ ሁኔታ ሊቀጥል አልቻለም። ይህም ሊሆን የቻለው በአምስት ዓመቱ የኢጣሊያ ወረራ ምክንያት እንደሆነ ግልጽ ነው።

ከ1928-1933ዓ.ም በቆየው የኢጣሊያ ፋሽስት ወረራ የኢትዮጵያ መገናሃ ብዙኃን እንቅስቃሴ እድገት ለአምስት ዓመት ያህል ተስተጓጉሏል። በመሆኑም ከዚህ በፊት የነበሩት የሀገሪቱ የኅትመት ውጤቶች ችግር ላይ ወደቁ። ከዚያም የኢጣሊያ የኘሮፓጋንዳ ማሠራጫ የነበሩት የቄሣር መንግሥት መልዕክተኛ እና የሮማ ብርሃን የተባሉት ጋዜች ወደ ሕትመት መጡ። የነዚህ ጋዜጦች ዋና አዘጋጅ የነበሩት ፕሮፌሰር/ነጋድራስ/ አፈወርቅ ገብረእየሱስ ዘብሄረ ዘጌ ናቸው። እኚህ ሰው በኢትዮጵያ ስነ-ጽሁፍ አለም ውስጥ የመጀመሪያውን ልቦለድ ጦቢያን ያሳተሙ ታላቅ ሰው ነበሩ። የተማሩት ኢጣሊያ ውስጥ ነው። የውጫሌን ውል ጣሊያኖች አዛብተው የጻፉትን ያጋለጡ ትልቅ ሰው ነበሩ። ምን እንደነካቸው ሳይታወቅ በ1929 ዓ.ም ለኢጣሊያ ባንዳነት አደሩ። ታላቁ ሰብእናቸው ተገፈፈ። ግን በታሪክ ውስጥ በጋዜጣ አዘገጃጀት ክፍል የባንዳ ቢሆንም የሚጠቀስ ስራ አበርክተዋል።

 

 

በሌላ በኩል ደግሞ ባንዲራችን የተሰኘው የጦር ሜዳ ጋዜጣ በአማርኛና በአረብኛ ይሠራጭ ነበር። ይህ ጋዜጣ ዓላማው የኢትዮጵያን አርበኞች የጦር ሜዳ ውሎ ማብሠሪያ ነበር። ይህ ባንዲራችን የተሠኘው ጋዜጣ ከጠላት መባረር በኋላ 1933 ዓ.ም ላይ ስሙን ወደ ሰንደቅ ዓላማችን ቀይሮ በየሣምንቱ መታተም ቀጥሏል። ከላይ የተጠቀሰው የወራሪው መንግሥት ልሣን የነበረው የቄሣር መንግሥት ጋዜጣ በአብዛኛው ስለ ቄሣር መንግሥት ገናናነት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ለቄሣር ለጥ ሰጥ  ብሎ መገዛት እንዳለበት የሚያሳስብ ይዘት ያለው ጋዜጣ ነው።

 

በኢጣሊያ ወረራ ወቅት በሀገር ውስጥ የነበሩት ጋዜጦች ቢታገዱም በጐረቤት ሀገሮች በአማርኛ ቋንቋ እየታተሙ ወደ ሀገር ውስጥ በሥውር የሚሠራጩ ጋዜጦች ነበሩ። ምናልባትም እኒህን ጋዜጦች የሚያዘጋጁት እንደ ተመስገን ገብሬ ያሉ በስደት የሄዱ ኢትዮጵያውያን ሣይሆኑ አይቀሩም ተብሎ ይገመት ነበር። ከዚህም መሀከል ከላይ የአርበኞች የትግል ጥንካሬ በመግለጽ በኩል የጠቀሰነው ባንዲራችን በኋላም ሰንደቅ ዓላማችን የተሰኘው አንዱ ነበር። ባንዲራችን እስከ ጥር 1933 ዓ.ም ድረስ በካርቱም ውስጥ ሀያ ስምንት ጊዜ ታትሞ በሀገር ውስጥ እንደተሠራጨ የተፃፉ ጽሑፎች ያስረዳሉ። ከነፃነት በኋላም ከሚያዚያ 1 ቀን 1933 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ በሣምንት ሁለት ጊዜ ረቡዕና ቅዳሜ ዕለት እየታተመ መውጣቱን ቀጥሎ ነበር።

 

ፋሽስት ኢጣሊያ ከሀገር ከተባረረች በኋላም አንድ ተጨማሪ የአማርኛ ቋንቋ ጋዜጣ እንደተመሠረተ ማየት ይቻላል። ይህም ጋዜጣ እስካሁን በሕትመት ላይ ያለው አዲሰ ዘመን ጋዜጣ ነው። በጊዜው ንጉሱ የተቋረጠውን የልማት እንቅስቃሴ እንዲቀጥልና ሕዝቡ በአዲስ መልክ እንዲነሣሣ መሻታቸው ይህንንም የሚያስፈጽምላቸው ጋዜጣ ስላስፈለጋቸው አንድ ጋዜጣ እንዲቋቋም አዘዙ። ሰብስቤ ዓለሙ ስለ አዲስ ዘመን ጋዜጣ አመሠራረት ባደረጉት ጥናት ላይ እንደገለፁት ንጉሡ ትዕዛዙን ያስተላለፉት በጊዜው ለነበሩት ጋዜጠኛ ለወልደ ጊዩርጊስ ወልደ ዮሐንስ ነበር። ወ/ጊዩርጊስም ሌሎች የበታች ሹሞችንና ጋዜጠኞችን ሰብስበው አዲስ ይውጣ ለተባለው ጋዜጣ ስም ብርሀንና ሰላም ይባል ሲል ሀሣብ አቀረቡ። ተሰብሣቢዎቹም በርዕሱ ላይ ተቃውሞ በማሰማታቸው ወ/ጊዩርጊስ ያዘጋጅት ርዕስ ካለ እንዲያቀርቡ ይጠየቃሉ። ወ/ጊዩርጊስም አዲስ ልደትና አዲስ ዘመን የተሰኙ ሁለት ርዕሶችን አቀረቡ። ከብዙ ክርክር በኋላ አዲስ ዘመን የሚለው ስም የተሻለ መስሎ ስለተገኘ ለጋዜጣው ተመረጠ። ንጉሡም ስያሜውን ስለአፀደቁት አዲስ ዘመን ተብሎ ተሰየመ የሚል  እንደምታ ያለው ጽሑፍ ቀርቧል።

 

በዚህ መሠረትም አዲስ ዘመን ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ ወጣ። በዚህ ጋዜጣ የመጀመሪያ ገጽ ላይም ይህ ቀን ላዲሲቱ ኢትዮጵያ ያዲስ ቀን መክፈቻ ነው ሲሉ ግርማዊነታቸው ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም በተናገሩት መሠረት አዲስ ዘመን ተብሎ ተሰየመ የሚል ቃል ተጽፎ ይገኛል። ይህ ጋዜጣ ከግንቦት 30 ቀን 1933 እስከ ታህሳስ 1954 ድረስ በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜ ሲታተም ቆይቶ ከታህሣሥ 1951 ጀምሮ በየቀኑ /ከሰኞ በቀር/ እየታተመ እስከ አሁን በማገልገል ላይ ይገኛል።

 

አዲስ ዘመን በኋላም በስያሜው የቀድሞውን ቃል አዋጅ ነጋሪ ለመዘከር የተሰየመውና የመንግሥትን ደንቦችና ሌሎችንም ኦፊሴላዊ መግለጫዎችን እትም የሚያወጣው የመንግስት ጋዜጣ ነጋሪት ጋዜጣ በሚል ተሰይሞ በ1935 ዓ.ም በይፋ ታትሞ መውጣት ጀምሯል።

 

ሌላው ደግሞ የዚሁ አዋጅ ነጋሪ እንግሊዝኛዊ ስያሜ ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ በ1935 ዓ.ም ተቋቁሞ ይገኛል። የዚህ ጋዜ አዘጋጅ የነበረው እንግሊዛዊው ጆን ሲምኘሰን ሲሆን፣ ለውጭ ሀገር አንባቢዎችና ጐብኝዎች ጠቃሚ የዜና ምንጭ እንዲሆን ስለ ኢትዮጵያና ስለሕዝቧ ለብዙ ሰዎች ማስተማር እንዲቻል… ወዘተ ለመሣሠሉት ተግባሮች ታስቦ የተጀመረ ጋዜጣ ነው። ሔራልድ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያን አዘጋጆች መዘጋጀት የጀመረው ከሕዳር 14 ቀን 1951 ዓ.ም ጀምሮ ነው።

 

 

ከዚህ ውጭ ከነፃነት በኋላ በ1933 ዓ.ም መታተም የጀመረውና ለውጭ ዲኘሎማቶች የወሬ ምንጭ እንዲሆን ታስቦ መንግሥት በሁለት ቋንቋዎች በአንግሊዝኛና በፈረንሣይኛ የሚያሣትመው ዴይሊ ኒውስ የተባለው ጋዜጣ ይገኛል። በተጨማሪም በጊዜው አያሌ ጋዜጦችና መጽሔቶች በሕትመት ላይ ነበሩ። ከነዚህም ውስጥ ለመጥቀስ ያህል ብርሃንና ሰላም 1934 ዓ.ም፣ የዛሬዩቱ ኢትዮጵያ 1945 ዓ.ም፣ ቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ 1948 ዓ.ም፣ መነን 1948 ዓ.ም፣ ወታደርና ዓላማው፣ ድምጸ ተዋህዶ፣ ዜና ቤተ-ክርስቲያን 1939 የመሣሰሉት ከብዙ በጥቂቱ  የሚጠቀሱ ናቸው።

በማተሚያ ቤት ደረጃም የአ.አ የንግድ ም/ቤቶች፣ አርቲስቲክ፣ የንግድ፣ የሸዋ፣ የሴንትራል፣ የመርሐ ጥበብ፣ የትንሣኤ፣ የተስፋ ገብረስላሴ፣ የኢትዮጵያ፣ የቅ/ጊዮርጊስና የኮከብ ማተሚያ ቤቶች ይጠቀሣሉ።

 

በዚህ ዘመን እስከ 1950ዎቹ አጋማሽ ድረስ የሕትመት ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፍቶ የሚገኝበት ወቅት ሲሆን በዘመኑ ከፍተኛ የሕትመት ምርት የተገኘበት ወቅት እንደነበር ማጤን ይቻላል። አሁን በመንግሥት የመገናኛ ብዙሀንነት የሚታወቁት ጋዜጦች የዚህ ዘመን ውጤቶች መሆናቸውንም ልብ ይሏል።

 

ከ1950ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የአፄ ኃ/ሥላሴ መንግሥት ከፍተኛ ውጥረት ላይ የነበረበት ወቅት ነው። የገበሬዎች ተከታታይ አመጽ፣ የተማሪዎች ጉምጉምታ፣ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ … ወዘተ የመሣሠሉት ክስተቶች የመንግሥቱን ሕላዊ እያሣጠሩት መጥተው ወደ ለውጥ በመገፋፋት የአፄውን መንግሥት ከሥልጣን በማውረድ በሀገሪቱ የወታደራዊ አገዛዝ እንዲሠፍን ሁኔታዎች የተመቻቹበት ወቅት ነው 1950ዎቹ። ቀስ በቀስ ንጉሱ ስርአት ተገረሰሰ። አብዮት መጣ። አዲስ የአብዮት መዝሙሮች ተቀነቀኑ። ኢትዮጵያ ወደ ያልታሰበ ጎዳና መጓዝ ጀመረች።

 

ፕሬስ ከ1966-1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ

ይህ ዘመን ከላይ ገረፍ ገረፍ አርገን በጠቃቀስናቸው አብይ ሁኔታዎች ምክንያት ለረጅም ጊዜ ሀገሪቱን ሲገዛ የነበረው ንጉሣዊ አገዛዝ የወደቀበትና በምትኩም ወታደራዊ አገዛዝ የሠፈነበት ወቅት ነው። ደርግ በ1966 ዓ.ም ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ በተለይ ለአገዛዙ ያመቸው ዘንድ የተለያዩ መዋቅሮችን መዘርጋት የጀመረበት ወቅት ነበር። በዚህ ዘመን በተለየ መልኩ በመጥፎ ሁኔታ የሚዘከረው የነጭ ሽብርና የቀይ ሽብር ጭፍጨፋዎች የተካሔዱበት ሀገሪቱ ተከታታይ በሆነ ድርቅ የተጐዳችበት፣ ሀገሪቱ የማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለምን መከተል የጀመረችበት፣ በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል በወቅቱ ተገንጣይ ከተሠኙ ቡድኖች ጋር ከፍተኛ ውጊያ ይደረግ የነበረበት፣ እንደ አፄው ዘመን መንግሥት ያልተሣካ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተደረገበት ወቅት መሆኑ ከሚጠቀሱት አጠቃላይ ክስተቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

 

ይህንን ሁኔታ መሠረት በማድረግ በወቅቱ የነበረውን የመገናኛ ብዙኃን እንቅስቃሴ ስንመለከት ሁሉም የመገናኛ ብዙኋን በሠራተኛው ፓርቲ ቁጥጥር ስር በማስታወቂያና ብሔራዊ መምሪያ መሪነት መንቀሣቀስ የጀመሩበት ወቅት ነው።

በ1969 ዓ.ም ደርግ የኢንፎርሜሽን ዘርፎችን ለመቆጣጠር እንዲያመቸው ከድርጅትነት ወደ መምሪያ ዝቅ አድርጐ በተማከለ አሠራር እንዲወድቅ ወስኖ የሚቆጣጠረውን አካልም ማስታወቂያና መርሃብሔር ሚኒስቴር ብሎ እንዲሰየም አደረገ። (ልሣነ ማስታወቂያ ገጽ-17)

 

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አጠቃላይ የመንግሥትና የግል ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ይመዘግባል፤ ያስተዳድራል፤ ይቆጣጠራል፤ በተጨማሪም የራዲዮና የቴሌቪዥን፣ የኦዲዮ ቪቶዋል አገልግሎትና አገራዊ ዜናዎችን /Domestic News/ የሚዘግበውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ይቆጣጠራል። የዜና ይዘቶች በሚ/ር ደረጃ ባሉ የመረጃ ክፍሉ ኮሚቴ አባሎች ደንብና ሥርዓት የሚታዘዙ ነበሩ። በመንግሥት በኩል በህትመት ውጤቶች ወደ ሀገር ውስጥ መግባትና መሠራጨት ላይ የሚደረጉ ገደቦችም ሌላ የማቀበያ ዘዴዎች ነበሩ።

 

ለምሣሌ ያህልም በ1970ዎቹ የመገናኛ ብዙሀን በሀገሪቱ ስለደረሰው የድርቅ ሁኔታ በተለይም ደግሞ በስሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ስለነበረው ሁኔታ መዘገብ አይችሉም ነበር። ለዚህ ምክንያትም ሕዝቡ ስለድርቁ የማወቅ ዕድል አላጋጠመውም ነበር። ለዚህ  መገናኛ ብዙሃን ነፃ በሆነ መንገድ ሀሣባቸውን ከመግለጽ የመንግሥቱ የኘሮፖጋንዳና የቅስቀሣ መሣሪያ በመሆን የሕዝቡን የማወቅ የማስተማርና የማዝናናት ሁኔታ ሳያሟሉ ቀሩ።

 

 

እኒህን ሁኔታዎች ከተመለከትን በኋላ ፊታችንን ወደ ጋዜጦች መለስ ያደረግን ንደሆነ በዚህ ዘመን የምናገኛቸው ብቸኛ ዕለታዊዎች ቀድሞ በተጠቀሰው ዘመን የተቋቋሙት የአማርኛ ቋንቋ አዲስ ዘመን እና የእንግሊዝኛው ቋንቋው ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ ናቸው። አዲስ ዘመን በወቅቱ በ30.000 ቅጂዎች የሚታተምና አንዳንዴ በተለያዩ ምክንያቶች ወይም የመንግሥት ክብረበዓላት ማለት ይቻላል በእጥፍ አድጐ የሚታተም ነበር። የእንግሊዝኛው ዘ ኢትዮጵያ ሄራልድ ደግሞ በ6500 ቅጂ የተወሰነ አካሄድ  ነበረው። ከዚህ ውጭ በትግረኛ ቋንቋ የሚታተም ህብረት የተባለ ዕለታዊ ጋዜጣ በአስመራ ከተማ የነበረ ሲሆን ይህ ጋዜጣም ወደአራት ሺህ ቅጂዎች አካባቢ ይሠራጭ ነበር። አራት ሣምታዊ ጋዜጦች በማስታወቂያና መርሃብሔር መምሪያ ይታተሙ ነበር። እኒህም አል ዓለም በአረብኛ ቋንቋ፣ በሬሣ በኦሮምኛ ቋንቋ፣ ኢትዮጵያ እና የዛሬዩቱ ኢትዮጵያ ሁለቱም በአማርኛ ቋንቋ ነበሩ።  ሌላው በዘመኑ ተጠቃሽ የነበረው ሳምንታዊ ጋዜጣ ከፍተኛ ቅጂን በማሣተም ይታወቅ የነበረውና በሠራተኛው ፓርቲ /ኢሠፓ/ ይታተም የነበረው ሠርቶ አደር ጋዜጣ ነው። የዚህ ጋዜጣ የሥርጭት መጠን ወደ 100,000 (መቶ ሺ) አካባቢ ይደርስ እንደነበር ይገለጻል። ፓርቲው በተጨማሪ መስከረም መጽሔት Theoretical quarterly ያሳትም ነበር። ፖሊስና የወታደሩ ክፍልም በሁለት ሣምንት የሚወጣ ህትመት ሲኖራቸው፣ የኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያንም በበኩሏ ማዕዶት እና ትንሣኤ የሚባሉ ሁለት የህትመት ውጤቶች ነበሯት።

በወቅቱ የነበረው የጋዜጦች ሥርጭት የተመለከትን እንደሆነ በቂ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስችላል። ይህም በዋናነት በትራንስፖርት እጥረት እንደነበር ነው የምንረዳው። በጊዜው ከነበሩት 101 አውራጃዎች ውስጥ አርባ አምስት ያህሉ ዕለታዊ ጋዜጦችን የማንበብ ዕድል የላቸውም ነበር። ከነዚህ የህትመት ውጤቶች ውስጥ አዲስ አበባ ከሁለቱ ዋና ጋዜጦች 50 በመቶውን ስትወስድ፣ በእንግሊዝኛ ከሚታተመው ደግሞ 80 በመቶውን ትወስድ ነበር። እዚህ ላይ ግን ከትራንስፖርት ችግር ባሻገር ማጤን የቻልኩት ሌላ ነገር አለ። ይህም ምን ያህል ነው ማንበብ የሚችለው ህዝብ የሚለውን ነው። በእርግጥ የዘመኑ አንድ አብይ ባህሪ ማንበብና መፃፍ የሚችለው ሕዝብ ቁጥር መጨመሩ ነው። ይኸውም በዋናነት በመሠረት ትምህርት ዘመቻ አማካኝነት የተደረገ ለውጥ ሲሆን ይህንን ያህል ማስመካት ደረጃ ላይ አድርሶ የሚያናግር ግን አልነበረም። በመሆኑም ከትራንስፖርት እጥረት ባሻገር የሕዝቡ በወጉ አለመማር የጋዜጣዎችን ተነባቢነት እንደሚቀንሠውና ይህም በወቅቱ የተከሠተ ጉዳይ እንደ ነበር ነው የተረዳሁት።

ከዚህ ሌላ በወቅቱ በመንግሥት በኩል የሚደረጉትን የቁጥጥር ጫናዎች ተቋቁመውና ጥሰው ወደሀገሪቱ የሚገቡ አያሌ የህትመት ውጤቶች ነበሩ። ይህም ሊሆን የቻለበት ዋናው ምክንያት በዋና ከተማዋ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና መ/ቤቶች በዋናነት በከተማዋ የመኖራቸው ጉዳይ ነው።

 

ከዚህ በተጨማሪ ብዙ የውጭ የዜና ወኪሎች ከአዲስ አበባ ዘገባዎቻቸውን ያስተላለፉ ነበር። አጃንስ ፍራንስ ኘሬስ AFP እና ሬውተርስ Reuters የዜና ዘጋቢዎች ነበሯቸው። ነገር ግን የሁለቱም የዜና ወኪል ዘጋቢዎች በ1970ዎቹ ውስጥ ከሀገር እንዲወጡ ተደርገዋል። ከዚህ ሌላ ታስ /Tass /APN እና (USSR) And (Germany ANSA (Italy) Tanjug (Yougoslavia) Preensa Latina (Cuba) እና Xinhua News Agency (China) የተባሉ የዜና ወኪሎች ነበሩ። የማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሚ/ር ለውጭ ጋዜጠኞች የመግብያ ፈቃድ የሚሠጥ ሲሆን የጋዜኞቹ እንቅስቃሴ ግን በከፍተኛ ሁኔታ በክትትል ሥር የነበረበት ወቅት ነበር።

 

በግንቦት 1981 ዓ.ም የተደረገውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ለመዘገብ የመጡ ሁለት የBBC ጋዜጠኞችና አንድ የሬውተር ፎቶግራፍ አንሺ ያለምንም ምክንያት ከሀገር እንዲወጡ መደረጉ ሲታወስና ከላይ ከተባረሩት ከአጃንስ ፍራንስ ኘሬስና ከሬውተርስ ዘጋቢዎች ጋር ደምረን ስናየው በወቅቱ የነበረው መንግሥት ከምዕራባውያን ጋር የነበረው ግንኙነት በመልካም ሁኔታ የሚወሣ እንዳልሆነ ይታመናል።

 

ከዚህ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ የነበረውን የሕትመት እንቅስቃሴ የተመለከትን እንደሆነ ከአብዮቱ ፍንዳታ በፊት የነበረው ሠፊ የሕትመት እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ እየከሠመ መጥቶ ጥቂትና በጣት ሊቆጠሩ ከሚችሉት የሠራተኛው ፓርቲ ኘሮፓጋንዳ ማካሔጃዎች በስተቀር እንዳይታተሙ ታግደዋል። ከነዚህም መሀከል መነን መጽሔት አዲስ ስዋርን፣ ኢትዮጵያን ሚረር፣ ጐህ፣ ሲጠቀሱ ከላይ ላነሳነው የኘሮፓጋንዳ ሥራ ማስረጃነትም የሠርቶ አደርን ከአሥራ አምስት ቀን ወደ ሣምንታዊነት መለወጥና የቅጂ ብዛት በእጥፍ የማደጉን ሁኔታ ማጤን ይቻላል።¾

 

(ክፍል አንድ)

በጥበቡ በለጠ

ዛሬ ይህንን ጽሑፍ እንዳሰናዳ ከገፋፉኝ ጉዳዮች አንደኛው ሙያዬ ስለሆነ ነው። ሁለተኛው በየጊዜው ብቅ እያለ እንደገና ክስም በማለት ብልጭ ድርግም የሚለውን ፕሬሳችንን አስኪ ከውልደቱ እስከ ጉልምስናው እንየው፤ እንፈትሸው፤ ከዚያም አወላለዱን እና አስተዳደጉን አይተን እንምከረው እናቃናው ብዬ በማሰብ ነው። ፕሬስ አራተኛው የመንግስት አካል ነው እየተባለ ስለሚቆጠር ይህንን ታላቅ ክብሩን ይዞ እንዲቆይም ከማሰብ ነው ወደ ጽሁፉ ዝግጅት የገባሁት። በነገራችን ላይ ይህን ጽሁፍ በ1980ዎቹ ዓ.ም አጋማሽ ከዩኒቨርሲቲ ጓደኞቼ ማለትም ከብሩክ መኮንን፣ ከአለምሰገድ ባስልዮስ እና ከአለማየሁ ጌታቸው ጋር በመሆን በቡድን (በጋራ) ሰራነው። ቀጥሎም በአንድ ወቅት በውጭ ሀገር ስማር “Free press in Ethiopia” በሚል ርእስ አስፋፍቸው በመጻፍ ለትምህርቴ ማጠናቀቂያ ያገለገለኝም ነው። ለዛሬ ግን ከሰፊው ጽሁፍ ውስጥ ለጋዜጣ አንባቢዎቼ የተጨመቀውን ሀሳብ በተከታታይ አቀርብላችሁና እንወያያለን፤ እንጻጻፋለን።

 

1-1 ሕትመት ቅድመ 1923 ዓ.ም ታሪካዊ ዳራ

በአጠቃላይ ሰለሕትመት ሥራ ስናወራ ኢትዮጵያዊ በሆነ ቋንቋ የሕትመት ሥራ ተሠርቶ የሚገኘው  በአለም የማተሚያ መሣሪያ በተፈለሰፈበት ምእት ዓመት መሆኑን መዛግብት ያስረዳሉ። ይህም የዘመኑ የሕትመት ውጤት በ1530 ዓ.ም ላይ የተገኘ ሲሆን ጥንታዊ በሆነው የኢትዮጵያ ቋንቋ ግዕዝ በጣሊያን ሮም ከተማ የታተመ ነበር። የአለምን የሕትመት እንቅስቃሴ ስናጤን ወደ ሀገራችንም መለስ ብለን ስንመለከት አንድ ተያያዥነት ያለው ነገር እንመለከታለን። ከጆን ጉተንበርግ የማተሚያ መኪና መፈልሰፍ ጋር ተያይዞ በተለያዩ የአለም ክፍሎች በዋናነት የሚሠሩት የሕትመት ውጤቶች በአብዛኛው ሐይማኖታዊ ዳራ ያለቸው እንደሆነ ይታወቃል። ኢትዮጵያዊ በሆነው ቋንቋ በ1530 የታተመውም የኢትዮጵያ መጽሐፍ፣ የሰለሞንን መዝሙር ይሰኛል። አሣታሚውም ዮሐን ፖትከን ይባላል። ይህን መጽሐፍ ያሣተመው የኢትዮጵያን ፊደል በቫቲካን ይኖሩ ከነበሩ ኢትዮጵያውን መነኮሣት ተምሮ በማህተም እንዲቀረጽ በማድረግ ነው። ይህ ፊደልም እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የአውሮፓ ማተሚያ ቤቶች ይገለገሉበት እንደነበር ተጽፎ ይገኛል። አንዳንድ ጽሁፎች ደግሞ ዮሐን ፖትከን የመጀመሪያው እትም በጀርመን ኮሎኝ ከተማ እንደገና ታተመ ይላሉ። በተጨማሪም የአዲስ ኪዳን ትርጉምም በ1548 በዚያው በሮም ከተማ በግዕዝ ታትሞ እንደወጣ ያሣያሉ።

 

ከዚህ በላይ ኢትዮጵያዊ በሆነ ቋንቋ ስለህትመት የጠቃቀስኩት ነገር፣ ምንም እንኳን ሕትመት በኢትዮጵያ ውስጥ ለመስፋፋት ረጅም ጊዜ የፈጀበት ቢሆንም እንኳን፣ በውጭ ሐገራት ቀደም ብሎ የመጀመሩን ጥቆምታ ለመስጠት ያህል ሲባል እንጂ ሌላ ክርክር ለመፍጠር ያህል አይደለም። ከዚህ ጋር ተያይዞም ይህንኑ የተጠቀሰውን የሕተመት ውጤት በመጀመሪያ እገሌ አሣተመ፤ አይ እገሌ ብለንም ለመከራከር ለማከራከርና ውሣኔ ለመስጠትም አይደለም። ብቻ የሕትመት ውጤት ኢትዮጵያዊ በሆነ ቋንቋ ቀደም ብሎ የተጀመረ ሥራ መሆኑን ልብ ይሏል።

 

ስለዚሁ ስለሕተመት ሥራ ትንሽ ገፋ በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሩን ሁኔታ ስናጤን ከሃይማኖት ጋር ተያይዞ እናገኘዋለን። ይህም በ17ኛው ክፍለ ዘመን የፖርቹጋል ሚስዮናዊዎች ለሃይማኖታዊ እንቅስቃሴአቸው ለመጠቀም ወደ ኢትዮጵያ እንዳስገቡት ነው የምንረዳው።

 

የኘሬስ የሕትመት ሥራ በምሥራቅ አፍሪካ የተጀመረው በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን መንግሥት እንደነበር ይታወቃል። ይህም ሎሬንዞ ቢያንኬሪ /Lorenzo Biancheri/ በተባሉ የኃይማኖት አባት የተጀመረ ሲሆን አባት ሎሬንዞ ለአቢሲኒያ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ተመድበው ሲመጡ በፈረንሣይ ለአንቶኒ ዲ አባዲ የተሠራውን አንድ ትንሽ የሕትመት መሣሪያና የአማርኛ ታይኘ ይዘው ወደ ምፅዋ እንደመጡ ሪቻርድ ፖንክረስት ስለሕትመት ሥራ በሚያወሱለት መጽሐፋቸው ይገልፁታል። አባ ቢያንኬሪም የሕትመት ሥራቸውን ለመቀጠል ራሣቸውን የአፄ ቴዎድሮስ አታሚ ብለው እንደሰየውሙና በ1857 መጀመሪያ አካባቢ ስለ አማረኛ ሰዋሰው ስልት አንድ መጽሐፍ እንዳሣተሙ ተገልጿል። እንዲሁም በ1872 ዓ.ም በከረን የላዛሪስት ማሲዮን ሠዎች የአማርኛና የግዕዝ ሠዋሰው መጽሐፍ አሳትመዋል።

 

 ማተሚያ ቤት በማቋቋም ረገድም በ1878 ዓ.ም ሞንኰሎ ላይ ትንሽ ማተሚያ ቤት በመክፈት የስዊድን ሚሲዮኖች ተጠቃሽ ናቸው። በወቅቱ ይህ የማተሚያ ቤት የተቋቋመበት ሥፍራ በኢትዮጵያ መንግሥት አሥተዳደር ስር ያልነበረና የግብፅ መንግሥት የሚያስተዳድረው እንደነበር ነው የተገለፀው።

 

ነገር ግን በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የመጀመሪያ የኘሬስ ስራ ተደረጐ እንዲቆጠር ያስቻለው June 1884 ዓ.ም የተደረገው ስምምነት ነው። በወቅቱ ይህ ስምምነት ተደርጐ የነበረው በኢትዮጵያ በኩል በአፄ ዮሐንስ እና በግብፅ፣ በእንግሊዝ ተወካዮች መካከል ነበር። በስምምነቱ መሠረትም ቦጐስ አውራጃ በአጠቃላይ ከረንን ጨምሮ በኢትዮጵያ መንግሥት መተዳደር እንዲችል ተደርጐ ነበር። ለዚህ ነው በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በ1872 በላዛሪስት ሚሲዮን ሠዎች የተቋቋመው የሕትመት ሥራ በ1884 ዓ.ም የመጀመሪያ ነው የተባለው። ቢሆንም በ1888 ከረን በጣሊያን ወረራ ስራ በመውደቋ ይህ ማተሚያ ቤት ለጣሊያን ወታደራዊ ቅስቀሣ የሚያገለግሉ ጽሑፎችን በጣሊያንኛና በአማርኛ ማተሙን ቀጠለ። ከጥቂት ጊዜ በኋላም ማተሚያ ቤቱ በካቶሊክ ሚሽኖች ሥር በመሆን ወደ አሥመራ ከተማ ተወሰደ።

 

የመጀመሪያው ኃይማኖታዊ ያልሆነ ሕትመት ኢጣሊያ በቅኝ ግዛት ወደቡን ከተቆጣጠረች ብዙም ሣይቆይ በ1885 የኢጣሊያ ወታደራዊ ኘሬስ በሚል ተቋቋመ። እንደ ፋማ ጋሊ /Fama Galli/ አገላለጽም ማተሚያው ሣልቫቶሬ ከተባለ ኢጣሊያዊ ድርጅት የመጣ ሲሆን ከማተሚያ መሣሪያው ጋር አንድ የአሥራ ሰባት ዓመት ሠራተኛ /Printer/ እና ስድስትና ሰባት ረዳት ሠራተኞች አብረው መጥተው ነበር። ሙሉ በሙሉ በጣሊያንኛ ይታተሙ የነበሩት የዚህ ማ/ቤት የሕትመት ውጤቶች ብዛት ያላቸውን መጽሐፎች ቢያጠቃልልም እንኳን፣ በዋናነት ሕግጋትን፣ ሥርዓትን፣ ወታደራዊ መመሪያዎችንና ትዕዛዞችን ያዘሉ ነበሩ።

 

ከጥቂት ዓመታት በኋላ ግን የመጀመሪያው የንግድ ማተሚያ ቤት በምፅዋ በ1884 ተቋቋመ። በሚካኤል እና ጓደኞቹ አማካኝነት /ባለቤትነት ለኤርትራዮ / L’Ertreo/ የተባለ በሣምንት የሚወጣ አሥተዳደራዊ ጋዜጣ መውጣት ጀመረ። ቀጥሎም በዚሁ ዓመት በሰኔ ወር ኮሪየሬ ኤሬትራዮ የሚባል ሣምንታዊ የፖለቲካና የንግድ ጋዜጣ/ እንደ ልማት የዜና ማሠራጫ አገላለፅ/  መፅሔት ይታተም እንደነበር ማወቅ ተችሏል።

 

ሌላው የአፄ ሚኒሊክ ዘመን መንግሥት የሕትመት ዕድገት ተብሎ የሚጠቀሰው የመተሚያ ቤት በአዲስ አበባ መቋቋሙና ብዙም ሳይቆይ የጋዜጣ ስራ የመጀመሩ ጉዳይ ነው። ካውንት ግሌቼን የሚባል ሰው ምንም እንኳን የሠጠው መረጃ ከሌለ ምንጭ ሊረጋገጥ ባይችልም የአማርኛ መሣሪያ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በፈንሣዊ ነጋዴ ከ1890 ዓ.ም ቀደም ብሎ የመጣና በሥራ ላይ ያልዋለ መሆኑን ገልፃል።

ኢትዮጵያ ጥንት ከነበረችበት ኋላ ቀር አስተዳደር በመጠኑም ቢሆን ተላቃ ዘመናዊ አስተዳደር ማግኘትና የሥልጣኔ ፋናን መቋደስ የጀመረችው በአፄ ሚኒልክ ዘመነ- መንግሥት እንደሆነ የታሪክ ምስክር ያስረዳል። የቴሌኮሚኒኬሽን፣ የፖስታ፣ የመኪና አገልግሎት የባቡር…ወዘተ አዳዲስ የሥልጣኔ ፍለጎች ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን ከፍተኛውን ሚና ተጫውተው አልፈዋል። ከሁሉ በላይ ግን በቀዳሚነት ሊወሣ የሚገባው የሕትመት ሥራ ጥበብ በኢትዮጵያ የመጀመሩ ጉዳይ ነው። ለዚህ ሁሉ ግን ቀዳሚ ተጠቃሽ አፄ ምኒልክ እንደሆኑ አሌ ሊባል አይችልም።

“ዘመናዊ የጋዜጣ ሥራና ዝግጅት የተጀመረው ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊ ጐዳና ባሰማሩት በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጊዜ ነው።” በማለት ልማት የዜና ማሠራጫ ዘዴ በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ በ1959 በማስታወቂያ ሚኒስቴር ታትሞ የወጣው ጽሑፍ የዓፄውን ልፋት ከግምት ውስጥ በማስገባት ጽፏል።

 

 ይህንን ዘመን ከሌሎች አይነተኛ ተጠቃሽ እንዲሆን ካስቻሉት ሁኔታዎች መሀከል ታላቁ የሕትመት ሥራ መጀመሩ ነው። ይህ በራሱ ታላቅ የእዕድገት ደረጃ መሆኑን ልብ ይሏል። ለዚህም ማጠናከሪያ ይረዳ ዘንድ የዜና አወጣጥና አሠረጫጨት ሂደትን እስከ ተጠቀሰው ጊዜ ድረስ መመልከቱ በቂ ይሆናል።

 

ይህን ዓይነት ዘመናዊ የብዙሃን መገናኛ ዘዴዎች ከመስፋፋታቸው ጋዜጠኝነትም ራሱን የቻለ ሙያ በመሆኑ በፊት አዋጅ መልዕክት ዜና ወዘተ ለሕዝብ ይተላለፍ የነበረው በቃል እንደነበር መረጃዎች ይናገራሉ።

 

በማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሚኒስቴር የዜና ማሠራራጫ ዘዴ በኢትዮጵያ የተሰኘው መጽሐፍ በገጽ 3 ላይ እንዲሕ ይላል፡-

“ነጋሪቱ ተጉሰመ፣ ከሰገነቱም ላይ ቆሞ የነበረው ሰው አዋጅ /አዋጅ/…ሲል ጮኸ ተናገረ። የነጋሪቱን መጎሰምና ስማ!... ስማ!...የሚለውን አዋጅ ያዳመጠው ሕዝብ አዋጁን ለመስማት ከሰገነት ዙሪያ ተሰበሰበ። ይህም በሰገነት ላይ ቆሞ የሚናገረው አዋጅ ተናጋሪ በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የዜና ማሠራጫ ሆኖ ሊገመት የሚችል ነው።”

ይህ በቃሉ አዋጅ አዋጅ ተብሎ ይተላለፍ የነበረው የዜና ማሠራጨት ሂደት ቀስ በቀስ እያደገ ሄዶ በቁም ጽሑፎች በመታገዝ በእጅ እየተፃፈ መሠራጨት ጀመረ። ለዚህም ተጠቃሽ የሚሆኑ የተለያዩ ግለሰቦች ናቸው። አንደኛው ብላታ ገ/እግዚአብሔር ሲሆኑ ሁለተኛው ከንቲባ ደስታ ናቸው።

 

ሪቻርድር ፓንክረስት The Fondation of Education በሚለው መጽሐፋቸው ስለዚሁ ጉዳይ ሲጠቅሱ፣ የመጀመሪያው የአማርኛ ጋዜጣ በእጅ ይፃፍ የነበረውና በየሣምንቱ ይወጣ የነበረው ሲሆን፣ ይህም ይፃፍ የነበረው በብላታ ገ/እግዚአብሔር እንደነበር ጠቅሰዋል። ሪቻርድ ፓንክረስት A.D Roberts ን  ጠቅሰው እንደጻፋት /እኚህ ሰው ይህንን አይነት ጽሑፍ ከ1893 በፊት እየፃፉ እንደሚያሠራጩና በሣምንትም ሀምሳ ቅጂዎች ያህል እንደሚያሠራጩ ጠቅሰዋል።

 

በሌላ በኩል ደግሞ ታፈሰ በላይ ጋዜጠኝነት በሚል ርዕስ በፃፉት መጽሐፋቸው በእጅ የመፃፍና የማሠራጨቱን ቅድሚያ የሚሰጡት ለከንቲባ ደስታ ነው።

ከዚሁ በፊት ከንቲባ ደስታ ይባሉ የነበሩ በቁም ጽሕፈት እየፃፉ ለቤተ-መንግሥቱ ሰዎች ጥቂት የጋዜጣ ቅጽ ያላቸው ወረቀቶች ያድሉ ነበር። የብእር ድምፅ የተባለውን ጋዜጣ ከንቲባው ያድሎ የነበሩት በ1896 ገደማ እንደነበረ ይነገራል። (ገጽ 6)

 

እዚህ ላይ በዋናነት ማየት የሚቻለው የዜና ማሠራጨቱ ሂደት ከአዋጅ ነጋሪ ባለቃል ወደ ቁም ፀሐፊ መሸጋገሩን ነው። ብላታ ገ/እግዚአብሔርም ሆኑ ከንቲባ ደስታ አሊያም ሁለቱ ለአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የተጠቀሱበት የጋራ ጉዳይ አላቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ የወሬ ማሠራጨቱን ሥራ በእጅ ጽሑፍ ማድረግ መቻላቸው። በመሆኑም የዜና ማሠራጨት ሂደት ከቃል ወደ ጽሑፍ ያደገበት ደረጃ መሆኑ ተጠቃሽ ነው።

 

ሌላው የዕድገት ደረጃ ይህ በቁም ጽሕፈት ይሠራ የነበረው የጋዜጣ ሥራ ወደ ሕትመት የመሸጋገሩ ጉዳይ ነው። ከዚህ በላይ እንደተመለከትነው ምንም እንኳን የሕትመት ጥበብ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመስፋፋቱ ተጠቃሽ የሚሆኑት የውጭ ሀገር የሀይማኖት ሥራ ሠሪዎች /ሠባኪዎች/ ቢሆኑም ቅሉ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ በሆነ መልኩ የተጀመረው ግን ተጠቃሽ በሆኑት ንጉሥ አፄ ምኒሊክ ዘመን ነው። በአገሪቱ የገባው ሥልጣኔ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዳበረ ሲመጣ የቁም ጽሕፈትም ወደ ዘመናዊት ሕትመት መሸጋገር የጀመረ ሥልጣኔን በወጉ መቀበል እንዲቻልም የመንግሥት ሥራ ሙሉ በሙሉ በጽሕፈት መካሄድ እንዲችል ሁኔታዎች ተመቻቹ።

 

በዚህ ዘመንም የመጀመሪዎቹ የታወቁ ሁለት መጽሔቶች ተዘጋጅተው እንዲቀርቡ በማድረግ ረገድ ዋናው የሥራ መሪ አፄ ምኒልክ እንደነበሩ ከላይ የተጠቀሰው በማስታወቂያ ሚኒስቴር የተዘጋጀው መጽሐፍ ይገልፃል። የመጀመሪያው ሰው ተብለው የተጠቀሱትም አባ ማሪ በርናርድ የተባሉ የፍራንሲስ ካን ሚሲዩናዊ ናቸው።

 

እኒህ ሰው “…በ1833 ዓ.ም ገደማ በሐገር የቆዳ በሽታ ሐኪም ቤት አቋቁመው ሲሠሩ ቆይተው በ1893 ዓ.ም “ላ ስሜን ኢትዮጲ” የተባለ ሣምንታዊ ጋዜጣ በፈረንሣይኛና አማርኛ ፎኒኦግራፍ በተባለ መሣሪያ እያተሙ ያወጡ ነበረ። የጋዜጣውም ዋና ጥረት የቆዳ በሽታን በማጥፋት ድጋፍ ለማግኘት ነበር። ቀጥሎም እኚሁ ሰው በ1898 ዓ.ም አንድ ትንሽ ማተሚያ ቤት ስላገኙ ሥራቸው የንግድንም ሥራ እንዲያጣምር በማድረግ በሚገኘው ትርፍ ሐኪም ቤቱን ለማካሄድ የጠቀሙ ነበር።”

ይህንንም የሕትመት እንቅስቃሴ አፄ ምኒሊክ በሰሙ ወቅት ከልብ መደሰታቸውንና አሣታሚውንም በአውሮፖ ስለነበሩት የማተሚያ ቤቶች ማጥናት እንዲችሉ ለማድረግ ወደ ሮም በመልዕክተኛነት እንደለኳቸውና ሲመለሱም የማተሚያ ቤት ሥራቸውን ወደ ድሬደዋ አዛውረው በስፋት እንደቀጠሉ ነው የታወቀው። ከዚህ በተጨማሪም አባ በርናርድ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ለማተሚያ ቤት ሙያ እንዳሠለጠኑና የተለያዩ ሙያዊ ሥራዎችን እንደሠሩ ይነገርላቸዋል። ነገር ግን በመጀመሪያው የአለም ጦርነት ሳቢያ አባ በርናርድ ወደ ሀገራቸው በመሔዳቸው የሕትመቱ ሥራ መስተጓጉል እንደገጠመው ታውቋል።

 

በሌላ በኩል በግሞ ሙሴ ከሸዲያ የተባሉ የግሪክ ነጋዴ አባ በርናረድ “ላ ሰሜን ደ ኢትዮጲ” የተባለውን ጋዜጣ በሀረር ከተማ ማሣተም ከጀመሩ ከሁለት ዓመት በኋላ /1895/ የመጀመሪያውን የአማርኛ ቋንቋ ጋዜጣ ማሣተም ጀመሩ። ይህ ጋዜጣም በአጼ ምኒልክ የወጣለት ስም አእምሮ የሚል ሲሆን፣ በእጅ ተጽፎ በ4 ገጽ እና በ24 ቅጂዎች ያህል የሚሠራጭ ነበር። ነገር ግን ታፈሰ በለጠ ጋዜጠኝነት በሚለው መፅሐፋቸው እንደጠቀሱትና ሌሎች ፍሑፎችም ለማመልከት እንደሚሞክሩት የሙሴ ካሻዲያ አእምሮ የመጀመሪያ መባሉ ተቀባይነት ያለው አይመስልም። ምክንያቱም ከላይ የተጠቀሱት የሁለቱ ሰዎችም ሆነ የኢ.ካ ሻዲያ አእምሮ በእጅ እስከተፃፈ ድረስ ቅድሚያውን ማግኘት ያለባቸው ከላይ ከተጠቀሱት ከሁለት አንዱ መሆን አለባቸውና ነው።

 

እዚህ ላይ መጠቀስ የሚገባው ጋዜጦቹ በእጅ መፃፍ የጀመሩበት አመት እንደ ፀሐፊዎች ሁሉ የተምታታና በእውነት ይህ ነው ለማለት የሚያስቸግር ነው። ነገር ግን አሁንም በዋናነት የሕትመት ሥራ ሂደቱን መመልከቱ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ወደ ሕትመት ገብተን ስንመለከት የኢ.ካሻዲያ ባለ ሀያአራት ቅጂ ጽሑፍ ጋዜጣ ፓሊዩግራፍ የተባለ መሣሪያ በመገኘቱ 200 ቅጂ ድረስ መድረስ መቻሉን መገንዘብ እንችላለን።

አፄ  ምኒልክም በዚህ የሕትመት እንቅስቃሴ የበለጠ በማሰባቸውና እንቅስቃሴው በቋሚነት መቀጠል እንዲችል በመፈለጋቸው በ1898 ዓ.ም ለካሻዲያ አንድ የማተሚያ ቤት አቅርበውላቸው ነበር። ነገር ግን ለጊዜው አእምሮ ጋዜጣ በገንዘብ እጥረት ምከንያት መቀጠል ባለመቻሉ ማተሚያ ቤቱ የመንግስት አዋጆችንና የንግድ ሕትመቶችን ብቻ ለመሥራት ተገዶ ነበር። ይህም ሁኔታ እስከ 1907 የአእምሮ እንደገና መታተም ድረስ የዘለቀ ነበር። ከዚህ በኋላም በሕትመት ለመቀጠል የቻለው ለሁለት አመታት ብቻ ሲሆን በ1909 እንደገና ሊቋረጥ ችሏል። ምክንያት ተብሎ የተገለፀውም የጋዜጣው አዘጋጅ የጀርመን ደጋፊ መሆኑና ከኢትዮጵያውያን ባለሥልጣኖች ጋር አለመስማማቱ ነው። ከዚህ በኋላም ለ3ኛ ግዜ የሕትመት እንቅስቃሴውን የጀመረው በ1917 ዓ.ም እንደነበርና አሁንም የአዘጋጅነቱን ስራ የሚሰሩት ካሻዲያ እንደነበሩ ተገልጿል።

$1-       ከዚህ በኋላ በ1898 ዓ.ም “ለ ሲመር” የተባለ የፈረንሳይ ጋዜጣ

$1-       ከ1905 -1908 ደግሞ የስዊድን ሚሲዮናውያን መልዕክተ ሰላም የተባለ ጋዜጣ በትግሬኛ

$1-       የተባበሩት የጦር ቃል ኪዳን መንግሥታት ደግሞ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት የጦር ወሬ የተባለ ጋዜጣ በአማርኛ

$1-       ብላቴን ጌታ ኅሩይ ደገሞ ጎሀ ጽባህ የተባለ ስለ ልዩ ልዩ ድርሰቶች የሚያትት መጽሔት

$1-       የአዲስ አበባ የግሪክ ተወላጆች ኢትዮጲ ኮስሞሥ የተባለ ሣምንታዊ ጋዜጣ በ500 ቅጂ

እያተሙ ያሠራጩ ነበር። እኒህ የተጠቀሱት ብቻ ናቸው በጊዜው የነበሩት የሕትመት እንቅስቃሴዎች ለማለት ሳይሆን በዋና ምሣሌነት ለመጥቀስ ያህል የቀረቡ እንደሆነ መግለጽ እወዳለሁ።

 

1-2 ፕሬስ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት

ይቀጥላል…

 

 

በጥበቡ በለጠ

በቅርቡ በኤግዚብሽን ማዕከል በተካሄደው ንባብ ለሕይወት የመጻህፍት አውደ-ርእይ ላይ ሴቶችና ስነ-ጽሁፍ የሚል ርእስ ተነስቶ ጥናት ቀርቧል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ደራሲያን፣ ሴቶችን እንደ ገጸ-ባህሪ ሲቀርጹ እንዴት ተጠቅመውባቸዋል የሚለውን ርእሰ ጉዳይ በተመለከተ የስነ-ጽኁፍ ምሁሩ የኮተቤው የሻው ተሰማ ጥናት አቅርበዋል፡፡ ከዚያ በፊት ደግሞ የሚዲያ ባለሙያዋና ንባብ ለሕይወት አዘጋጆች መካከል አንድዋ ኤሚ እንግዳ፤ ስለ ኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ታሪክና ማንነት አጭር ዳሰሳ አድርጋ ነበር፡፡ ኤሚ እንግዳ ለንባብ ለሕይወት የስነ-ጽሁፍ ጉባኤ ላይ በጽሁፍ ያዘጋጀችውን ጥናት አሳጥረን  በሚከተለው መልኩ አቅርበንዋል፡፡

በአማርኛ ቋንቋ ለሴት ፀሐፊዎች “ደራሲያት” ሲባል፣ ለወንዶቹ ደግሞ “ደራሲያን“ በማለት ትርጉም የሚሰጡ ሰዎች አሉ፡፡ የቃሉ አጠራር የመጣው ከግዕዝ ቋንቋ እንጂ ከአማርኛ ቋንቋ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የሆኖ ሆኖ በ1970ዎቹ እና ሰማኒያዎቹ ውስጥ በኢትዮጵያ የሴት ፀሐፊያት መድረክ ላይ ቦግ ብለው ከሚታዩት ስመጥር ደራሲያት መካከል ፊርማዬ ዓለሙ በዋናነት ትጠቀሳለች፡፡ ፊርማዬ ዓለሙ ሴቶች ከማጀት ወደ አደባባይ እንዲወጡ እና ልዩ ልዩ ሙያቸውንም እንዲያሳዩ ይፋ በሆነበት ዘመን እርሷ ወጣት ነበረች፡፡ ይህን ወጣትነቷን በመጠቀም የሴቶቹን ወደ አደባባይ መምጣት እሰየው እያለች በየመድረኩ ግጥሞቿንና የስነ-ፅሁፍ ሥራዎቿን ይዛ እየወጣች አ.ኢ.ሴ.ማን በአንስታያት (በሴቶች) ዘንድ ማህበራቸው እንደሆነ እያሳወቀች መጣች፡፡ አ.ኢ.ሴ.ማ ማለት አብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር ማለት ነው፡፡ በዘመነ ደርግ የተቋቋመ ነው፡፡

ፊርማዬ ዓለሙ በአንድ ወቅት ቃለ-መጠይቅ ሳደርግላት እንዳጫወተችኝ ከሆነ በዘመነ ደርግ በተለይም “እድገት በህብረት“ በሚል መሪ ቃል ወጣቶች በየገጠሩ ተሰማርተው ለሀገራቸው ኢትዮጵያ ልማት የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ ፕሮግራም ነበር፡፡ እርሷም ከነዚያ ወጣት ዘማቾች መካከል አንዷ ነበረች፡፡ እንደዘመተችም በአንድ የገጠር ከተማ ውስጥ ከጓደኞቿ ጋር ትደርሳለች፡፡ ያ ከተማ ህዝቡ የሚገበያይበት የገበያ ቦታ አለው፡፡ ገበያው ዕድሜ ልኩን ተጠርጐ አያውቅም ትላለች ፊርማዬ፡፡ “እናም እድገት በህብረት የዘመትነው ወጣቶች ማንም ሳያዘን ይህንን ገበያ ማፅዳት አለብን ብለን በአንድ አዳር የዘመናት ቆሻሻ ስንጠርግ ነጋ“ በማለት ያወጋችኝ ጨዋታ አይረሳኝም፡፡

ፊርማዬ ዓለሙ ይህንን ትዝታዋን የተናገረችበት ምክንያት በአሁኑ ዘመን ካለው ከወጣትነት ወይም ከአፍላነት ጋር አያይዛ ስታነፃፅር ነበር፡፡ አሁን ያለው ወጣት ለሀገር፣ ለወገን፣ ለድሃ፣ ለተራበ፣ ቤቱ ለፈረሰበት፣ ለተፈናቀለ... ወገኑ ሆ ብሎ በወኔ የመነሳት ባህሪ አይታይበትም የሚሉ አስተያየቶች የሚንፀባረቁበት ወቅት ስለነበር ነው ትዝታዋን ያወራችው፡፡ ወጣትነት ጀግንነት ነው፤ ወኔያምነት ነው፤ ከተፎነት ነው፤ የማይደፈረውን ግርዶሽ በትኜ እወጣበታለሁ የሚባልበት ዕድሜ ነው እያለች ፊርማዬ አውግታኛለች፡፡ ዛሬ ንባብ ለሕይወት ታላቅ የመጻሕፍት አውደ ርእይና ጉባኤን ሰበብ በማድረግ  የርሷን ዘመን እና ያለፉትን የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያት የብዕር ተጋድሎ አወጋችኋለሁ፡፡

ፊርማዬ ዓለሙ የተወለደችው ጥቅምት 21 ቀን 1948 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ ነው፡፡ በአባቷ በአቶ ዓለሙ ገ/ማርያም እና በእናቷ በወ/ሮ የሺ መካከል ጋብቻ ቢመሰረትም ልጅ ግን አልወለድ አለ፡፡ እናም ልጅ ባለመውለድ ምክንያት አቶ ዓለሙ እና ወ/ሮ የሺ ሊፋቱ ሆነ፡፡ ፊርማውን ለማስቀደድ ሽማግሌዎች ተሰበሰቡ፡፡ የአቶ ዓለሙ እና የወ/ሮ የሺ ጋብቻ የመፍረሻው ቀን ነው፡፡ ነገር ግን በዚያው እለት ወ/ሮ የሺ ምራቃቸውን ደጋግመው ሲተፉ እና ሲያቅለሸልሻቸው ከሽማግሌዎቹ መካከል አንደኛው ያያሉ፡፡ ጉዳዩ ክፉኛ አጠራጠራቸውና “ቆይ ይሄ የፊርማ መቅደዱ ስነ-ሥርዓት ለሌላ ጊዜ ይቀጠር“ ይሏቸዋል፡፡ “ወ/ሮ የሺ የምትተፋው ምራቅ ወፍራም ነው፡፡ እኔ በሆዷ ቅሪት የያዘች ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ፍቺው የተወሰነ ጊዜ ይቆይና ይታይ“ ይላሉ፡፡ እናም ሽምግልናው በዚህ ይቋጫል፡፡ ከወራት በኋላ እንደተጠረጠረው ወ/ሮ የሺ ቅሪት ነበሩ፡፡ ሆዳቸውም እየገፋ መጣ፡፡ ልጅ ባለመውለድ ምክንያት ሊፈርስ የነበረው ጋብቻ እደገና ቆመ፡፡ ከዘጠኝ ወር በኋላ ወ/ሮ የሺ ሴት ልጅ ተገላገሉ፡፡ አባቷ አቶ ዓለሙ እናቷ ወ/ሮ የሺ ያቺን ሴት ልጅ “ፊርማዬ“ ብለው ጠሯት፡፡

ለአባት እና ለእናቷ ጋብቻ መፅናት ፊርማ የሆነችው ይህች ገጣሚት፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን እዚያው ሆሳዕና ጊምቢቹ አንደኛ ደረጃ፣ ሆሳዕና ራስ አባተ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃና ሆሳዕና ልጅ አበበ ወልደሰማዕት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃለች፡፡ ቀጥላም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብትገባም በወቅቱ በነበረው በእድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ በሐረርና በሆሳዕና አካባቢዎች ዘመተች፡፡ ከዘመቻውም በኋላ ወደ ነርሶች ማሰልጠኛ ትምህርት ተቋም ገብታ ነበር፡፡ እሱንም አቋርጣ ወጣች፡፡ ከዚያም በጥር ወር 1969 ዓ.ም በካርታ ሥራዎች ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ የድርጅቱ ባልደረባ በመሆን የህዝብ ግንኙነት ክፍል ውስጥ አገልግላለች፡፡ ፊርማዬ ዓለሙ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስነ-ጽሁፍ በዲፕሎማ የተመረቀች ሲሆን የዲግሪ ትምህርቷን ደግሞ ተምራ ጨርሳ በመመረቂያ አመቷ ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው፡፡

ፊርማዬ ዓለሙ በስነ-ፅሁፍ ስራዎቿ በተለይም በወግ ፅሁፎች፣ በስነ-ግጥም እና በአጫጭር ልቦለዶቿ ታዋቂ ነበረች፡፡ ስራዎቿ በበርካታ በግልና በመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ የሴት ፀሐፍት ውስጥ ከ1970ዎቹ እስከ ዕለተ ሞቷ ማለትም እስከ ጥር 7 ቀን 1993 ዓ.ም ግንባር ቀደም ሆና የምትጠራ ነበረች፡፡ ከሁሉም ተግባሯ ደግሞ የሚበልጠውን ጉዳይ የያዘው በየቤቱ የስነ-ፅሁፍ ስራቸውን አምቀው የያዙ ሴቶችን ወደ አደባባይ ወጥተው እንዲታወቁ ያደረገችው ተጋድሎ በሰፊው ይጠቀስላታል፡፡

ይህ ተግባሯ ቀጣይነትም እንዲኖረው የሴት ደራሲያንን ማህበር ከጓደኞቿ ማለትም ከአረጋሽ ሰይፉ እና ከመቅደስ ጀንበሩ ጋር በመሆን በ1989 ዓ.ም መሠረተች፡፡ አረጋሽ ሰይፉ እጅግ የተዋጣላት ገጣሚ ስትሆን ዛሬ በህይወት የለችም፡፡ ነገር ግን እነዚህን የስነ-ፅሁፍ ባለሙያዎች የመሠረቱት ማህበር ዛሬ በርካታ ሴቶች ተሰባስበውበት ትልልቅ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሌሎችም ሴቶች በማህበር የመደራጀት ጥቅምን በመረዳት እንደየፍላጐታቸው ማህበር እየመሰረቱ የስነ-ፅሁፍ ሥራዎቻቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ፊርማዬ፣ አረጋሽና መቅደስ ለሴት ፀሐፍቶች በማህበር ተደራጅተው እንዲቋቋሙ ፈር ቀዳጆች ናቸው፡፡

ፊርማዬ ልዩ የሚያደርጋት የመሠረቱትን የሴት ደራሲያን ማህበርን ሥራዎች ለማከናወን ከወርሃዊ ገቢዋ ወጪ  እያደረገች መቆየቷ ነው፣ ጓደኞቿ የሚናገሩት፡፡ የሴት ደራሲያን ማህበር “የግጥም ምሽት“ በማለት ለበርካታ ጊዜ የስነ-ፅሁፍ ስራዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ አንድ ቀን ደግሞ “የግጥም ምሽት“ የሚለው “ግጥም በማለዳ“ በሚል መጠሪያ ተቀየረ፡፡ ዛሬ በስፋት የሚካሄደው ይሄው “ግጥም በማለዳ“ የሚለው መርሃ ግብር ነው፡፡ ይህ እንዴት ተጀመረ?

ፊርማዬ ዓለሙ በአንድ ወቅት እንደነገረችኝ ከሆነ፣ “ግጥም በማለዳ“ የሚለውን መጠሪያ ያወጡት የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩትና ዛሬ በውጭ ሀገር በስደት የሚገኙት  አቶ ብርሃነ መዋ ናቸው፡፡ እርሳቸው ይህን ስያሜውን ሊያወጡለት የቻሉት ደግሞ ፊርማዬ ዓለሙ ወደ ቢሯቸው ሄዳ እንዲህ ትላቸዋለች፡- “ሴት ፀሐፍቶች ተሰባስበን ግጥሞቻችንን የምናቀርብበት መርሃ ግብር አለን፡፡ ይህም “ግጥም ምሽት“ ይባላል፡፡ አንተም እዚያ ላይ የክብር እንግዳ ሆነህ እንደትገኝልን ነው“ በማለት ግብዣዋን ታቀርባለች፡፡ አቶ ብርሃነም፡-

“ፊርማዬ?“አሏት፡፡

“አቤት“ አለቻቸው ደንግጣ፡፡

“እናንተ ደግሞ የግጥም ምሽት ብቻ ነው የምታውቁት“ አሏት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፡፡

“እና ምን እናድርግ ታዲያ?“ አለቻቸው እሷም ግራ ገብቷት፡፡

“ግጥም በማለዳ ለምን አይሆንም? ግጥምን በምሽት ብቻ ያደረገው ማነው? በማለዳስ ለምን አይሆንም?“ አሏት አቶ ብርሃነ መዋ፡፡

ፊርማዬ አዲስ ሃሳብ አገኘች፡፡ እውነትም ለምን በማለዳ አይሆንም ብላ ጀመረችው፡፡ እስከ አሁንም ይህ ፕሮግራም እንደቀጠለ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ሴቶች ደራሲያን ሲነገር ብዙውን ግዜ ቀደም ስላሉት የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ያን ያህል አይወሳም፡፡ እነ ፊርማዬ ዓለሙ ዘንድ የደረሰው የሴት ፀሐፍት የኋላ ታሪክ ብዙ ጉዳዮችን ያሳለፈ እንቅስቃሴ አለው፡፡ እነርሱንም በጥቂቱ እናነሳሳቸው ዘንድ ግድ ይለናል፡፡

ገና በማለዳው በ1898 ዓ.ም ማለትም የዛሬ 110 ዓመት ላይ ከሴት ፀሐፍት ውስጥ ብቅ ያለች ኢትዮጵያዊት እናገኛለን፡፡ ይህች ሴት አስቴር ገኖን ትባላለች፡፡ በ1898 ዓ.ም በኦሮምኛ ቋንቋ መጽሐፍ አዘጋጅታለች፡፡ መጽሐፉ የመጽሐፍ ቅዱስን ሃሳብ በመያዝ መንፈሳዊ ጉዳዮችን በውስጡ የያዘ ነው፡፡ ስለዚህ አስቴር ገኖን እስካሁን ባለው መረጃ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ደራሲ ልንላት እንችላለን፡፡

ከርሷ በመቀጠል መጽሐፍ አያሳትሙ እንጂ በሴቶች ትምህርትና እውቀት በቅኔ እውቀታቸውን በቅኔ መምህርነታቸው የጎጃሟ እማሆይ ገላነሽ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለቂያ ጀምሮ ያበረከቱት አስተዋፅኦ አይረሳም፡፡ እማሆይ ገላነሽ አይነስውር ሴት ነበሩ፡፡ በዘመናቸው ለሴቶች አዳጋች የነበረውን ትምህርት ተምረው ለትልቅ ደረጃ የበቁ ነበሩ፡፡ እናም የኢትዮጵያ ሴቶች ታሪክ ሲጠቀስ በጉልህ ብቅ የሚሉ ናቸው፡፡

ከርሳቸውም በመለጠቅ ከ1920ዎቹ ጀምሮ ለብዙ አመታት የኢትዮጵያ ሴቶችን የብዕር ተጋድሎ ያሳዩት ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ ናቸው፡፡ የከንቲባ ገብሩ ልጅ የሆኑት ወ/ሮ ስንዱ ትምህርታቸውን በጀርመን እና በስዊዘርላንድ ተምረዋል፡፡ ሀገራቸው ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ወራሪዎች መዳፍ ስር በገባች ወቅት በግጥሞቻቸው አርበኞችን በማበረታታት እና ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት በተደረገው ርብርብ ከሴቶች ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱ አርበኛ ነበሩ፡፡ በርካታ የስነ-ፅሁፍ ሥራዎች ያሏቸው ወ/ሮ ስንዱ በደሴው እቴጌ መነን ት/ቤት እና በአዲስ አበባው እቴጌ መነን የሴቶች ት/ቤት የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ዳይሬክተር ነበሩ፡፡ የፓርላማ አባልም በመሆን ለሴቶች እኩልነት የተደረገውን እንቅስቃሴ ከፊት ሆነው የመሩ መሆናቸው በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ በስነ-ግጥም፣ በቴአትር፣ በታሪክ፣ በልቦለድ እና በሌሎችም በርካታ ፅሁፎቻቸው ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን አበርክተው ያለፉ ናቸው፡፡

እንግሊዞች መቅደላ ላይ ጦርነት ገጥመው አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ሲሰው፣ ልዑል ዓለማየሁ እና ወርቅነህ የተባለ ልጅ የእንግሊዝ ወታደሮች ወደ ሀገራቸው ይዘዋቸው ሄደው ነበር፡፡ ወርቅነህ የተባለው ልጅ በኋላ አድጐ ዶክተር ወርቅነህ ወይም በኢትዮጵያዊያን አጠራር ሐኪም ወርቅነህ የሚባሉት ናቸው፡፡ ልጃቸው ሣራ ወርቅነህም በኢትዮጵያ ሴት ፀሐፊያን ዘንድ ከፊት ከሚሰለፉት ውስጥ አንዷ ናት፡፡ ገና በማለዳው በ1933 ዓ.ም የእንግሊዝ ፀሐፌ ተውኔት የሼክሲፒርን ቴአትር “ማዕበል“ በሚል ርዕስ ተርጉማ ያቀረበች ደራሲት ናት፡፡

ከሣራ ወርቅነህ ደራሲነት በመቀጠልም በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት የሬዲዮ ጋዜጠኛ የሚባሉት ወ/ሮ ሮማንወርቅ ካሣሁን ለሴቶች ፀሐፍት መጐልበት ያበረከቱት ውለታ ሰፊ ነው፡፡ በ1940ዎቹ መግቢያ ላይ “ማኅቶተ ጥበብ“፣ “ስለ ልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ“ በሚሉት እና በሌሎችም መጽሐፍቶቻቸው ከሴቶች መድረክ ደምቀው ይታያሉ፡፡

ወደ 1950ዎቹ ስንመጣ ደግሞ የሴት ፀሐፍት ቁጥር እየጨመረ ይመጣል፡፡ በተለይም ወጣቷ ሽቶ መዝገቡ፣ ወደርየለሽ ከበደ፣ ወደርየለሽ ማይክል፣ ፅጌ አዳፍሬ፣ መሰረት መንገሻ እና ሸዋንግዢው በላይነህ ግንባር ቀደም ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ የሽቶ መዝገቡ “ሰው በመሆኔ ደከምኩ 1959፣ የወደርየለሽ ማይክል “ከንፈር መጣጭ 1959፣ የፅጌ አዳፍሬ፣ “የፍቅር ጮራ የህብረት ከተማ1956፣ የመሰረት መንገሻ “የአልቤርጎው ፈላስፋ 1957 እና የሸዋን ግዢው በላይነህ “የህሊና ድጋፍ ምክር ከወቀሳ1953 የተሰኙት የጥበብ ስራዎች የኢትዮጵያን የሴት ፀሐፍት እንቅስቃሴ ወደፊት ያራመዱ ናቸው፡፡ ሌሎችም ፀሐፍት በዚሁ ዘመን መስመሩን ተቀላቅለዋል፡፡

በ1960ዎቹም ይህ የብዕር አብዮት እየተስፋፋ መጣ፡፡ አያሌ ሴቶች የኢትዮጵያን ስነ-ፅሁፍ ተቀላቀሉት፡፡ ለምሳሌ ዘውድነሽ ዓለሙ “ኡኡ አናውቃትም እንዴ 1960፣ እልፍነሸ ወ/ቂርቆስ “የሴት ክብሯ በባሏ 1960፣ የደስታ ገብሩ “ምኞቴ“ 1963፣ ጥሩነሽ ይመር “አስደናቂው ህፃን 1960፣  አስቴር ፍስሐ “ሰናይት“1963፣ ዘውዲቱ አሸብር “ትዕግስት መከረኛዋ 1960፣ መስዋዕት ሙሉአለም “አብረን እንሞታለን 1963፣ አስራት አየለ “የመኖር ትርጉም1960፣ ጥሩነሽ ይመር “ጊዜና ሰው 1961፣ እና ሌሎች በርካታ ሴቶች በድርሰት ዓለም ጐልተው መውጣት ጀመሩ፡፡ አየለች በቀለ፣ በለጠች ሲሳይ፣ መጠነወርቅ ሣሙኤል፣ መቅደስ አስናቀ ይህን ዘመን ካበለፀጉት ደራሲያት መካከል ናቸው፡፡

ዘመነ ደርግ ሲመጣ ጐላ ብሎ የታየው የሴት ደራሲያት ቁጥር የመመንመን አደጋ ገጥሞት ነበር፡፡ ነገር ግን የዛሬዋ የሴት ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት የሆነችው የምወድሽ በቀለ በ1971 ዓ.ም “አብዮታዊ ግጥሞች በሚለው ስራዋ ብቅ አለች፡፡ የሴቶቹ እንቅስቃሴም እየሰፋ መጣ፡፡ ዛሬ በአሜሪካን ሀገር የምትገኘው የመድረክ ሰውና ገጣሚ ዓለምፀሐይ ወዳጆም በ1970ዎቹ ጐልተው ከወጡት ፀሐፍት መካከል አንዷ ናት፡፡ የርሷም የመጀመሪያዋ የግጥም ሥራ “ጽጌረዳ ብዕር“በሚል ርዕስ በ1977 ዓ.ም በታተመው የልዩ ልዩ ፀሐፊዎች መድብል ውስጥ ሥራህ ህያው“ የሚለው ግጥሟ ተካቷል፡፡

ከዚህ በኋላ እነ ፊርማዬ ዓለሙ፣ መቅደስ ጀንበሩ፣ አረጋሽ ሰይፉ፣ ፀሐይ መላኩ፣ ውዳላት ገዳሙ፣ ሙሉ ሰለሞን፣ ሌሎችም በርካታ ሴቶች የኢትዮጵያን ስነ-ፅሁፍ ተቀላቀሉት፡፡ እዚህ ላይ አንዲት ፈፅሞ የማትረሳ ገጣሚትና ሰዓሊ ማስታወስ ይገባናል፡፡ ዛሬ በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ የስዕል ጥበብ መምህርት የሆነችው ገጣሚ ከበደች ተክለአብ “የት ነውበሚለው የግጥም መድብሏ ወደር ያልተገኘላት ባለቅኔ ተብላለች፡፡ በግጥሞቿ 11 አመታት በሶማሊያ እስር ቤት በሰቆቃ ያሳለፈችበትን ታሪክ ፍፁም ውበትን በተላበሰ መልኩ ያቀረበችባቸው ናቸው፡፡

የእነዚህን በርካታ ሴቶች ታሪክም እየተከታተሉ በ1960ዎቹ ውስጥ በመነን መጽሔት ይፅፉ የነበሩት ጋዜጠኛ እሌኒ ፈጠነም በዚህ አጋጣሚ ይጠቀሳሉ፡፡ በ1979 ዓ.ም የደራሲያት ተሳትፎ በሚል የመመረቂያ ፅሁፏን የሰራችው አጋረደች ጀማነህም ይህን ታሪክ እንድናውቀው ሰፊ ድጋፍ አድርጋለች፡፡ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት “The Ethiopian Women in Former Times” የተሰኘው ጥናታቸውም ለዚህ ፅሁፌ ከፍተኛ እገዛ አድርጐልኛል፡፡

ዛሬ ይህን ታሪክ እንዳቀርብ ምክንያት የሆነኝ ንባብ ለሕይወት የመጻሕፍት አውደ-ርዕይ እና ጉባኤ ነው፡፡ ይህ ዝግጅት በየአመቱ እየፋፋ እና እየጎለበተ እንዲያድግ እንዲለመልም እኛ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ኢትዮጵያ በስነ-ጽሁፍና በታሪክ እጅግ ሀብታም የሆች አገር ናት፡፡ ሀብትዋ ታሪኳ እና ስነ-ጽሁፎችዋ ናቸው፡፡ ታዲያ ንባብ ለሕይወትን እኛ እንክዋን ብናልፍ ቀጣዩ ትውልድ የሚቀባበለው መሆን አለበት፡፡ እርስ በርሳችን መሞጋገስ አይሁንብኝ እንጂ ዋና ስራ አስኪያጂያችን ቢኒያብ ከበደ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡

****                   ****               ****

የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ

ቅዳሜ ይመረቃል

በታዋቂው የሥነ-ጽሑፍ ምሁር ተጽፎ የተዘጋጀው የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ሐረግ የተሰኘው መጽሐፍ የፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ውስጥ ይመረቃል፡፡

መጽሐፉ በይዘቱም ሆነ በሚያነሳቸው ልዩ ልዩ ሃሳቦች የመነጋገሪያ አጀንዳ እንደፈጠረ ይነገራል፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት በኦሮሞ እና በአማራ ብሔረሰቦች መካከል የተለያዩ ግጭቶች ሲከሰቱ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በዚሁ በፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ ሁለቱ ብሔረሰቦች ከአንድ አካባቢ በተለይም ከጐጃም የተፈጠሩ መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ መጽሐፉ ሁለቱም ብሔረሰቦች እጅግ የተቀራረበ ዝምድና ያላቸው እንደሆነ የተለያዩ ታሪኮችን /Mythology/ን መሠረት አድርጐ የተሰራ የጥናትና የምርምር ውጤት መሆኑ ይነገራል፡፡

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ፣ በመፅሐፋቸው የምረቃ በዓል ላይ ራሳቸው እንደሚገኙ እና ለሚነሱ ሃሳቦችና ጥያቄዎች መልስ እንደሚሰጡም ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰር ፍቅሬ አክለው እንደተናገሩት ከሆነ ሁሉም የመፃሕፍት አንባቢያን በስፍራው ተገኝተው መፅሐፋቸውን እንዲመርቁላቸው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡   

Page 6 of 19

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us