You are here:መነሻ ገፅ»ኪነ-ጥበብ
ኪነ-ጥበብ

ኪነ-ጥበብ (262)

 

በጥበቡ በለጠ

በቅርቡ በኤግዚብሽን ማዕከል በተካሄደው ንባብ ለሕይወት የመጻህፍት አውደ-ርእይ ላይ ሴቶችና ስነ-ጽሁፍ የሚል ርእስ ተነስቶ ጥናት ቀርቧል፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ደራሲያን፣ ሴቶችን እንደ ገጸ-ባህሪ ሲቀርጹ እንዴት ተጠቅመውባቸዋል የሚለውን ርእሰ ጉዳይ በተመለከተ የስነ-ጽኁፍ ምሁሩ የኮተቤው የሻው ተሰማ ጥናት አቅርበዋል፡፡ ከዚያ በፊት ደግሞ የሚዲያ ባለሙያዋና ንባብ ለሕይወት አዘጋጆች መካከል አንድዋ ኤሚ እንግዳ፤ ስለ ኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ታሪክና ማንነት አጭር ዳሰሳ አድርጋ ነበር፡፡ ኤሚ እንግዳ ለንባብ ለሕይወት የስነ-ጽሁፍ ጉባኤ ላይ በጽሁፍ ያዘጋጀችውን ጥናት አሳጥረን  በሚከተለው መልኩ አቅርበንዋል፡፡

በአማርኛ ቋንቋ ለሴት ፀሐፊዎች “ደራሲያት” ሲባል፣ ለወንዶቹ ደግሞ “ደራሲያን“ በማለት ትርጉም የሚሰጡ ሰዎች አሉ፡፡ የቃሉ አጠራር የመጣው ከግዕዝ ቋንቋ እንጂ ከአማርኛ ቋንቋ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የሆኖ ሆኖ በ1970ዎቹ እና ሰማኒያዎቹ ውስጥ በኢትዮጵያ የሴት ፀሐፊያት መድረክ ላይ ቦግ ብለው ከሚታዩት ስመጥር ደራሲያት መካከል ፊርማዬ ዓለሙ በዋናነት ትጠቀሳለች፡፡ ፊርማዬ ዓለሙ ሴቶች ከማጀት ወደ አደባባይ እንዲወጡ እና ልዩ ልዩ ሙያቸውንም እንዲያሳዩ ይፋ በሆነበት ዘመን እርሷ ወጣት ነበረች፡፡ ይህን ወጣትነቷን በመጠቀም የሴቶቹን ወደ አደባባይ መምጣት እሰየው እያለች በየመድረኩ ግጥሞቿንና የስነ-ፅሁፍ ሥራዎቿን ይዛ እየወጣች አ.ኢ.ሴ.ማን በአንስታያት (በሴቶች) ዘንድ ማህበራቸው እንደሆነ እያሳወቀች መጣች፡፡ አ.ኢ.ሴ.ማ ማለት አብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር ማለት ነው፡፡ በዘመነ ደርግ የተቋቋመ ነው፡፡

ፊርማዬ ዓለሙ በአንድ ወቅት ቃለ-መጠይቅ ሳደርግላት እንዳጫወተችኝ ከሆነ በዘመነ ደርግ በተለይም “እድገት በህብረት“ በሚል መሪ ቃል ወጣቶች በየገጠሩ ተሰማርተው ለሀገራቸው ኢትዮጵያ ልማት የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ ፕሮግራም ነበር፡፡ እርሷም ከነዚያ ወጣት ዘማቾች መካከል አንዷ ነበረች፡፡ እንደዘመተችም በአንድ የገጠር ከተማ ውስጥ ከጓደኞቿ ጋር ትደርሳለች፡፡ ያ ከተማ ህዝቡ የሚገበያይበት የገበያ ቦታ አለው፡፡ ገበያው ዕድሜ ልኩን ተጠርጐ አያውቅም ትላለች ፊርማዬ፡፡ “እናም እድገት በህብረት የዘመትነው ወጣቶች ማንም ሳያዘን ይህንን ገበያ ማፅዳት አለብን ብለን በአንድ አዳር የዘመናት ቆሻሻ ስንጠርግ ነጋ“ በማለት ያወጋችኝ ጨዋታ አይረሳኝም፡፡

ፊርማዬ ዓለሙ ይህንን ትዝታዋን የተናገረችበት ምክንያት በአሁኑ ዘመን ካለው ከወጣትነት ወይም ከአፍላነት ጋር አያይዛ ስታነፃፅር ነበር፡፡ አሁን ያለው ወጣት ለሀገር፣ ለወገን፣ ለድሃ፣ ለተራበ፣ ቤቱ ለፈረሰበት፣ ለተፈናቀለ... ወገኑ ሆ ብሎ በወኔ የመነሳት ባህሪ አይታይበትም የሚሉ አስተያየቶች የሚንፀባረቁበት ወቅት ስለነበር ነው ትዝታዋን ያወራችው፡፡ ወጣትነት ጀግንነት ነው፤ ወኔያምነት ነው፤ ከተፎነት ነው፤ የማይደፈረውን ግርዶሽ በትኜ እወጣበታለሁ የሚባልበት ዕድሜ ነው እያለች ፊርማዬ አውግታኛለች፡፡ ዛሬ ንባብ ለሕይወት ታላቅ የመጻሕፍት አውደ ርእይና ጉባኤን ሰበብ በማድረግ  የርሷን ዘመን እና ያለፉትን የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያት የብዕር ተጋድሎ አወጋችኋለሁ፡፡

ፊርማዬ ዓለሙ የተወለደችው ጥቅምት 21 ቀን 1948 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ ነው፡፡ በአባቷ በአቶ ዓለሙ ገ/ማርያም እና በእናቷ በወ/ሮ የሺ መካከል ጋብቻ ቢመሰረትም ልጅ ግን አልወለድ አለ፡፡ እናም ልጅ ባለመውለድ ምክንያት አቶ ዓለሙ እና ወ/ሮ የሺ ሊፋቱ ሆነ፡፡ ፊርማውን ለማስቀደድ ሽማግሌዎች ተሰበሰቡ፡፡ የአቶ ዓለሙ እና የወ/ሮ የሺ ጋብቻ የመፍረሻው ቀን ነው፡፡ ነገር ግን በዚያው እለት ወ/ሮ የሺ ምራቃቸውን ደጋግመው ሲተፉ እና ሲያቅለሸልሻቸው ከሽማግሌዎቹ መካከል አንደኛው ያያሉ፡፡ ጉዳዩ ክፉኛ አጠራጠራቸውና “ቆይ ይሄ የፊርማ መቅደዱ ስነ-ሥርዓት ለሌላ ጊዜ ይቀጠር“ ይሏቸዋል፡፡ “ወ/ሮ የሺ የምትተፋው ምራቅ ወፍራም ነው፡፡ እኔ በሆዷ ቅሪት የያዘች ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ፍቺው የተወሰነ ጊዜ ይቆይና ይታይ“ ይላሉ፡፡ እናም ሽምግልናው በዚህ ይቋጫል፡፡ ከወራት በኋላ እንደተጠረጠረው ወ/ሮ የሺ ቅሪት ነበሩ፡፡ ሆዳቸውም እየገፋ መጣ፡፡ ልጅ ባለመውለድ ምክንያት ሊፈርስ የነበረው ጋብቻ እደገና ቆመ፡፡ ከዘጠኝ ወር በኋላ ወ/ሮ የሺ ሴት ልጅ ተገላገሉ፡፡ አባቷ አቶ ዓለሙ እናቷ ወ/ሮ የሺ ያቺን ሴት ልጅ “ፊርማዬ“ ብለው ጠሯት፡፡

ለአባት እና ለእናቷ ጋብቻ መፅናት ፊርማ የሆነችው ይህች ገጣሚት፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን እዚያው ሆሳዕና ጊምቢቹ አንደኛ ደረጃ፣ ሆሳዕና ራስ አባተ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃና ሆሳዕና ልጅ አበበ ወልደሰማዕት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃለች፡፡ ቀጥላም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብትገባም በወቅቱ በነበረው በእድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ በሐረርና በሆሳዕና አካባቢዎች ዘመተች፡፡ ከዘመቻውም በኋላ ወደ ነርሶች ማሰልጠኛ ትምህርት ተቋም ገብታ ነበር፡፡ እሱንም አቋርጣ ወጣች፡፡ ከዚያም በጥር ወር 1969 ዓ.ም በካርታ ሥራዎች ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ እስከ ዕለተ ሞቷ ድረስ የድርጅቱ ባልደረባ በመሆን የህዝብ ግንኙነት ክፍል ውስጥ አገልግላለች፡፡ ፊርማዬ ዓለሙ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስነ-ጽሁፍ በዲፕሎማ የተመረቀች ሲሆን የዲግሪ ትምህርቷን ደግሞ ተምራ ጨርሳ በመመረቂያ አመቷ ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው፡፡

ፊርማዬ ዓለሙ በስነ-ፅሁፍ ስራዎቿ በተለይም በወግ ፅሁፎች፣ በስነ-ግጥም እና በአጫጭር ልቦለዶቿ ታዋቂ ነበረች፡፡ ስራዎቿ በበርካታ በግልና በመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ የሴት ፀሐፍት ውስጥ ከ1970ዎቹ እስከ ዕለተ ሞቷ ማለትም እስከ ጥር 7 ቀን 1993 ዓ.ም ግንባር ቀደም ሆና የምትጠራ ነበረች፡፡ ከሁሉም ተግባሯ ደግሞ የሚበልጠውን ጉዳይ የያዘው በየቤቱ የስነ-ፅሁፍ ስራቸውን አምቀው የያዙ ሴቶችን ወደ አደባባይ ወጥተው እንዲታወቁ ያደረገችው ተጋድሎ በሰፊው ይጠቀስላታል፡፡

ይህ ተግባሯ ቀጣይነትም እንዲኖረው የሴት ደራሲያንን ማህበር ከጓደኞቿ ማለትም ከአረጋሽ ሰይፉ እና ከመቅደስ ጀንበሩ ጋር በመሆን በ1989 ዓ.ም መሠረተች፡፡ አረጋሽ ሰይፉ እጅግ የተዋጣላት ገጣሚ ስትሆን ዛሬ በህይወት የለችም፡፡ ነገር ግን እነዚህን የስነ-ፅሁፍ ባለሙያዎች የመሠረቱት ማህበር ዛሬ በርካታ ሴቶች ተሰባስበውበት ትልልቅ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ሌሎችም ሴቶች በማህበር የመደራጀት ጥቅምን በመረዳት እንደየፍላጐታቸው ማህበር እየመሰረቱ የስነ-ፅሁፍ ሥራዎቻቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ ፊርማዬ፣ አረጋሽና መቅደስ ለሴት ፀሐፍቶች በማህበር ተደራጅተው እንዲቋቋሙ ፈር ቀዳጆች ናቸው፡፡

ፊርማዬ ልዩ የሚያደርጋት የመሠረቱትን የሴት ደራሲያን ማህበርን ሥራዎች ለማከናወን ከወርሃዊ ገቢዋ ወጪ  እያደረገች መቆየቷ ነው፣ ጓደኞቿ የሚናገሩት፡፡ የሴት ደራሲያን ማህበር “የግጥም ምሽት“ በማለት ለበርካታ ጊዜ የስነ-ፅሁፍ ስራዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ አንድ ቀን ደግሞ “የግጥም ምሽት“ የሚለው “ግጥም በማለዳ“ በሚል መጠሪያ ተቀየረ፡፡ ዛሬ በስፋት የሚካሄደው ይሄው “ግጥም በማለዳ“ የሚለው መርሃ ግብር ነው፡፡ ይህ እንዴት ተጀመረ?

ፊርማዬ ዓለሙ በአንድ ወቅት እንደነገረችኝ ከሆነ፣ “ግጥም በማለዳ“ የሚለውን መጠሪያ ያወጡት የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩትና ዛሬ በውጭ ሀገር በስደት የሚገኙት  አቶ ብርሃነ መዋ ናቸው፡፡ እርሳቸው ይህን ስያሜውን ሊያወጡለት የቻሉት ደግሞ ፊርማዬ ዓለሙ ወደ ቢሯቸው ሄዳ እንዲህ ትላቸዋለች፡- “ሴት ፀሐፍቶች ተሰባስበን ግጥሞቻችንን የምናቀርብበት መርሃ ግብር አለን፡፡ ይህም “ግጥም ምሽት“ ይባላል፡፡ አንተም እዚያ ላይ የክብር እንግዳ ሆነህ እንደትገኝልን ነው“ በማለት ግብዣዋን ታቀርባለች፡፡ አቶ ብርሃነም፡-

“ፊርማዬ?“አሏት፡፡

“አቤት“ አለቻቸው ደንግጣ፡፡

“እናንተ ደግሞ የግጥም ምሽት ብቻ ነው የምታውቁት“ አሏት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው፡፡

“እና ምን እናድርግ ታዲያ?“ አለቻቸው እሷም ግራ ገብቷት፡፡

“ግጥም በማለዳ ለምን አይሆንም? ግጥምን በምሽት ብቻ ያደረገው ማነው? በማለዳስ ለምን አይሆንም?“ አሏት አቶ ብርሃነ መዋ፡፡

ፊርማዬ አዲስ ሃሳብ አገኘች፡፡ እውነትም ለምን በማለዳ አይሆንም ብላ ጀመረችው፡፡ እስከ አሁንም ይህ ፕሮግራም እንደቀጠለ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ሴቶች ደራሲያን ሲነገር ብዙውን ግዜ ቀደም ስላሉት የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ያን ያህል አይወሳም፡፡ እነ ፊርማዬ ዓለሙ ዘንድ የደረሰው የሴት ፀሐፍት የኋላ ታሪክ ብዙ ጉዳዮችን ያሳለፈ እንቅስቃሴ አለው፡፡ እነርሱንም በጥቂቱ እናነሳሳቸው ዘንድ ግድ ይለናል፡፡

ገና በማለዳው በ1898 ዓ.ም ማለትም የዛሬ 110 ዓመት ላይ ከሴት ፀሐፍት ውስጥ ብቅ ያለች ኢትዮጵያዊት እናገኛለን፡፡ ይህች ሴት አስቴር ገኖን ትባላለች፡፡ በ1898 ዓ.ም በኦሮምኛ ቋንቋ መጽሐፍ አዘጋጅታለች፡፡ መጽሐፉ የመጽሐፍ ቅዱስን ሃሳብ በመያዝ መንፈሳዊ ጉዳዮችን በውስጡ የያዘ ነው፡፡ ስለዚህ አስቴር ገኖን እስካሁን ባለው መረጃ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ሴት ደራሲ ልንላት እንችላለን፡፡

ከርሷ በመቀጠል መጽሐፍ አያሳትሙ እንጂ በሴቶች ትምህርትና እውቀት በቅኔ እውቀታቸውን በቅኔ መምህርነታቸው የጎጃሟ እማሆይ ገላነሽ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለቂያ ጀምሮ ያበረከቱት አስተዋፅኦ አይረሳም፡፡ እማሆይ ገላነሽ አይነስውር ሴት ነበሩ፡፡ በዘመናቸው ለሴቶች አዳጋች የነበረውን ትምህርት ተምረው ለትልቅ ደረጃ የበቁ ነበሩ፡፡ እናም የኢትዮጵያ ሴቶች ታሪክ ሲጠቀስ በጉልህ ብቅ የሚሉ ናቸው፡፡

ከርሳቸውም በመለጠቅ ከ1920ዎቹ ጀምሮ ለብዙ አመታት የኢትዮጵያ ሴቶችን የብዕር ተጋድሎ ያሳዩት ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ ናቸው፡፡ የከንቲባ ገብሩ ልጅ የሆኑት ወ/ሮ ስንዱ ትምህርታቸውን በጀርመን እና በስዊዘርላንድ ተምረዋል፡፡ ሀገራቸው ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ወራሪዎች መዳፍ ስር በገባች ወቅት በግጥሞቻቸው አርበኞችን በማበረታታት እና ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት በተደረገው ርብርብ ከሴቶች ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱ አርበኛ ነበሩ፡፡ በርካታ የስነ-ፅሁፍ ሥራዎች ያሏቸው ወ/ሮ ስንዱ በደሴው እቴጌ መነን ት/ቤት እና በአዲስ አበባው እቴጌ መነን የሴቶች ት/ቤት የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ዳይሬክተር ነበሩ፡፡ የፓርላማ አባልም በመሆን ለሴቶች እኩልነት የተደረገውን እንቅስቃሴ ከፊት ሆነው የመሩ መሆናቸው በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ በስነ-ግጥም፣ በቴአትር፣ በታሪክ፣ በልቦለድ እና በሌሎችም በርካታ ፅሁፎቻቸው ዘመን ተሻጋሪ ስራዎችን አበርክተው ያለፉ ናቸው፡፡

እንግሊዞች መቅደላ ላይ ጦርነት ገጥመው አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ሲሰው፣ ልዑል ዓለማየሁ እና ወርቅነህ የተባለ ልጅ የእንግሊዝ ወታደሮች ወደ ሀገራቸው ይዘዋቸው ሄደው ነበር፡፡ ወርቅነህ የተባለው ልጅ በኋላ አድጐ ዶክተር ወርቅነህ ወይም በኢትዮጵያዊያን አጠራር ሐኪም ወርቅነህ የሚባሉት ናቸው፡፡ ልጃቸው ሣራ ወርቅነህም በኢትዮጵያ ሴት ፀሐፊያን ዘንድ ከፊት ከሚሰለፉት ውስጥ አንዷ ናት፡፡ ገና በማለዳው በ1933 ዓ.ም የእንግሊዝ ፀሐፌ ተውኔት የሼክሲፒርን ቴአትር “ማዕበል“ በሚል ርዕስ ተርጉማ ያቀረበች ደራሲት ናት፡፡

ከሣራ ወርቅነህ ደራሲነት በመቀጠልም በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴት የሬዲዮ ጋዜጠኛ የሚባሉት ወ/ሮ ሮማንወርቅ ካሣሁን ለሴቶች ፀሐፍት መጐልበት ያበረከቱት ውለታ ሰፊ ነው፡፡ በ1940ዎቹ መግቢያ ላይ “ማኅቶተ ጥበብ“፣ “ስለ ልዕልት ፀሐይ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ“ በሚሉት እና በሌሎችም መጽሐፍቶቻቸው ከሴቶች መድረክ ደምቀው ይታያሉ፡፡

ወደ 1950ዎቹ ስንመጣ ደግሞ የሴት ፀሐፍት ቁጥር እየጨመረ ይመጣል፡፡ በተለይም ወጣቷ ሽቶ መዝገቡ፣ ወደርየለሽ ከበደ፣ ወደርየለሽ ማይክል፣ ፅጌ አዳፍሬ፣ መሰረት መንገሻ እና ሸዋንግዢው በላይነህ ግንባር ቀደም ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ የሽቶ መዝገቡ “ሰው በመሆኔ ደከምኩ 1959፣ የወደርየለሽ ማይክል “ከንፈር መጣጭ 1959፣ የፅጌ አዳፍሬ፣ “የፍቅር ጮራ የህብረት ከተማ1956፣ የመሰረት መንገሻ “የአልቤርጎው ፈላስፋ 1957 እና የሸዋን ግዢው በላይነህ “የህሊና ድጋፍ ምክር ከወቀሳ1953 የተሰኙት የጥበብ ስራዎች የኢትዮጵያን የሴት ፀሐፍት እንቅስቃሴ ወደፊት ያራመዱ ናቸው፡፡ ሌሎችም ፀሐፍት በዚሁ ዘመን መስመሩን ተቀላቅለዋል፡፡

በ1960ዎቹም ይህ የብዕር አብዮት እየተስፋፋ መጣ፡፡ አያሌ ሴቶች የኢትዮጵያን ስነ-ፅሁፍ ተቀላቀሉት፡፡ ለምሳሌ ዘውድነሽ ዓለሙ “ኡኡ አናውቃትም እንዴ 1960፣ እልፍነሸ ወ/ቂርቆስ “የሴት ክብሯ በባሏ 1960፣ የደስታ ገብሩ “ምኞቴ“ 1963፣ ጥሩነሽ ይመር “አስደናቂው ህፃን 1960፣  አስቴር ፍስሐ “ሰናይት“1963፣ ዘውዲቱ አሸብር “ትዕግስት መከረኛዋ 1960፣ መስዋዕት ሙሉአለም “አብረን እንሞታለን 1963፣ አስራት አየለ “የመኖር ትርጉም1960፣ ጥሩነሽ ይመር “ጊዜና ሰው 1961፣ እና ሌሎች በርካታ ሴቶች በድርሰት ዓለም ጐልተው መውጣት ጀመሩ፡፡ አየለች በቀለ፣ በለጠች ሲሳይ፣ መጠነወርቅ ሣሙኤል፣ መቅደስ አስናቀ ይህን ዘመን ካበለፀጉት ደራሲያት መካከል ናቸው፡፡

ዘመነ ደርግ ሲመጣ ጐላ ብሎ የታየው የሴት ደራሲያት ቁጥር የመመንመን አደጋ ገጥሞት ነበር፡፡ ነገር ግን የዛሬዋ የሴት ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት የሆነችው የምወድሽ በቀለ በ1971 ዓ.ም “አብዮታዊ ግጥሞች በሚለው ስራዋ ብቅ አለች፡፡ የሴቶቹ እንቅስቃሴም እየሰፋ መጣ፡፡ ዛሬ በአሜሪካን ሀገር የምትገኘው የመድረክ ሰውና ገጣሚ ዓለምፀሐይ ወዳጆም በ1970ዎቹ ጐልተው ከወጡት ፀሐፍት መካከል አንዷ ናት፡፡ የርሷም የመጀመሪያዋ የግጥም ሥራ “ጽጌረዳ ብዕር“በሚል ርዕስ በ1977 ዓ.ም በታተመው የልዩ ልዩ ፀሐፊዎች መድብል ውስጥ ሥራህ ህያው“ የሚለው ግጥሟ ተካቷል፡፡

ከዚህ በኋላ እነ ፊርማዬ ዓለሙ፣ መቅደስ ጀንበሩ፣ አረጋሽ ሰይፉ፣ ፀሐይ መላኩ፣ ውዳላት ገዳሙ፣ ሙሉ ሰለሞን፣ ሌሎችም በርካታ ሴቶች የኢትዮጵያን ስነ-ፅሁፍ ተቀላቀሉት፡፡ እዚህ ላይ አንዲት ፈፅሞ የማትረሳ ገጣሚትና ሰዓሊ ማስታወስ ይገባናል፡፡ ዛሬ በሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ የስዕል ጥበብ መምህርት የሆነችው ገጣሚ ከበደች ተክለአብ “የት ነውበሚለው የግጥም መድብሏ ወደር ያልተገኘላት ባለቅኔ ተብላለች፡፡ በግጥሞቿ 11 አመታት በሶማሊያ እስር ቤት በሰቆቃ ያሳለፈችበትን ታሪክ ፍፁም ውበትን በተላበሰ መልኩ ያቀረበችባቸው ናቸው፡፡

የእነዚህን በርካታ ሴቶች ታሪክም እየተከታተሉ በ1960ዎቹ ውስጥ በመነን መጽሔት ይፅፉ የነበሩት ጋዜጠኛ እሌኒ ፈጠነም በዚህ አጋጣሚ ይጠቀሳሉ፡፡ በ1979 ዓ.ም የደራሲያት ተሳትፎ በሚል የመመረቂያ ፅሁፏን የሰራችው አጋረደች ጀማነህም ይህን ታሪክ እንድናውቀው ሰፊ ድጋፍ አድርጋለች፡፡ የፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት “The Ethiopian Women in Former Times” የተሰኘው ጥናታቸውም ለዚህ ፅሁፌ ከፍተኛ እገዛ አድርጐልኛል፡፡

ዛሬ ይህን ታሪክ እንዳቀርብ ምክንያት የሆነኝ ንባብ ለሕይወት የመጻሕፍት አውደ-ርዕይ እና ጉባኤ ነው፡፡ ይህ ዝግጅት በየአመቱ እየፋፋ እና እየጎለበተ እንዲያድግ እንዲለመልም እኛ የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ኢትዮጵያ በስነ-ጽሁፍና በታሪክ እጅግ ሀብታም የሆች አገር ናት፡፡ ሀብትዋ ታሪኳ እና ስነ-ጽሁፎችዋ ናቸው፡፡ ታዲያ ንባብ ለሕይወትን እኛ እንክዋን ብናልፍ ቀጣዩ ትውልድ የሚቀባበለው መሆን አለበት፡፡ እርስ በርሳችን መሞጋገስ አይሁንብኝ እንጂ ዋና ስራ አስኪያጂያችን ቢኒያብ ከበደ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡

****                   ****               ****

የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ

ቅዳሜ ይመረቃል

በታዋቂው የሥነ-ጽሑፍ ምሁር ተጽፎ የተዘጋጀው የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ሐረግ የተሰኘው መጽሐፍ የፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ውስጥ ይመረቃል፡፡

መጽሐፉ በይዘቱም ሆነ በሚያነሳቸው ልዩ ልዩ ሃሳቦች የመነጋገሪያ አጀንዳ እንደፈጠረ ይነገራል፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት በኦሮሞ እና በአማራ ብሔረሰቦች መካከል የተለያዩ ግጭቶች ሲከሰቱ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ በዚሁ በፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ ሁለቱ ብሔረሰቦች ከአንድ አካባቢ በተለይም ከጐጃም የተፈጠሩ መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ መጽሐፉ ሁለቱም ብሔረሰቦች እጅግ የተቀራረበ ዝምድና ያላቸው እንደሆነ የተለያዩ ታሪኮችን /Mythology/ን መሠረት አድርጐ የተሰራ የጥናትና የምርምር ውጤት መሆኑ ይነገራል፡፡

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት መግለጫ፣ በመፅሐፋቸው የምረቃ በዓል ላይ ራሳቸው እንደሚገኙ እና ለሚነሱ ሃሳቦችና ጥያቄዎች መልስ እንደሚሰጡም ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰር ፍቅሬ አክለው እንደተናገሩት ከሆነ ሁሉም የመፃሕፍት አንባቢያን በስፍራው ተገኝተው መፅሐፋቸውን እንዲመርቁላቸው ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡   

በጥበቡ በለጠ

በበርካታ የረጃጅም ልቦለድ መፅሐፍቶች በእጅጉ ታዋቂ የሆነው ደራሲ አዳም ረታ የንባብ ለሕወይት የ2008 ዓ.ም የወርቅ ብዕር ተሸላሚ በመሆን ተመረጠ።

አዳም ረታ ላለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ውስጥ በተለይም በልቦለድ ድርሰት አፃፃፍ በየጊዜው ነጥሮ በመውጣት፣ በአዳዲስ ሥራዎችና ሕትመቶች ብቅ እያለ የአካባቢን ቀልብና መንፈስ የገዛ ደራሲ መሆኑም ተነግሮለታል።

አዳም በተሰጠው የጽሁፍ ጥበብ ረጃጅም ልቦለዶች በመድረስ አያሌ አንባብያንን የፈጠረ ደራሲም መሆኑ ተመስክሮለታል። አዳም ረታ በአማርኛ የልቦለድ ሥነ-ፅሁፍ ውስጥ በተለይ በዚህኛው ዘመን ከሚጠሩት ፀሐፍት መካከል ከፊት ተሰላፊ እንደሆነም ይታወቃል። አዳም ረታ በልቦለድ አለም ውስጥ አምራች ደራሲ /Productive Author/ የሚባል አይነት ሰው ነው።

የአዳም ረታ የልቦለድ አፃፃፍ ዘውግ እና ዘዴ በአማርኛ ሥነ-ፅሁፍ አለም ውስጥ ማስተማሪያ ጭምር ሆኖ የሚያገለግል ነው። ገና ከማለዳው በ1980ዎቹ መግቢያ ላይ ማሕሌት ብሎ ካሳተማት የአጫጭር ልቦለዶች መድብል መፅሐፉ በተጨማሪ አያሌ ረጃጅም ልቦለዶችን በማሳተም ይታወቃል። ማሕሌት የተሰኘችው መፅሐፍ በአጫጭር የልቦለድ አፃፃፍ ቴክኒክ ውስጥ መማሪያ የሚሆኑ አያሌ ርዕሰ ጉዳዮችን በመያዝ ትታወቃለች። ማሕሌት በተለይም ተምሳሌትነት /Symbolism/ በስነ-ፅሑፍ ውስጥ እንዴት ይገለጻል የሚባለውን ጥያቄ የምትመልስ ጥሩ ምሳሌ ሆና ትጠቀሳለች። ከዚህ ሌላ የአማርኛ ቋንቋን ለልቦለድ ፅሁፍ አጠቃቀምንም በተመለከተ አዳም ረታ ብዙ የሚጠቀሱለት ጣፋጭ የአገላለፅና የትረካ ክሂል ያለው የዘመናችን ምርጥ ደራሲ መሆኑም ተነግሮለታል።

አዳም ረታ ብዙ ወጣቶችን በሥነ-ፅሑፍ ግለት እና ሙቀት ያነቃቃ፣ የሥነ-ፅሁፍ ማወያያ፣ ማድመቂያ የሆነ የዚህ ዘመን ባለ ወርቃማ ብዕረኛ ነው። እናም የ2008 ዓ.ም የንባብ ለሕይወት ታላቅ የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ ደራሲ አዳም ረታን የወርቅ ብዕር ተሸላሚ አድርጎታል።

ባለፈው እሁድ ሐምሌ 17 ቀን 2009 ዓ.ም በኤግዚቪሽን ማዕከል የመፃህፍት አውደ- ርዕይ ላይ ሽልማቱ የተበረከተ ሲሆን፤ አዳም ነዋሪነቱ በውጭ አገር በመሆኑ ወንድምየው በሽልማት ስነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝቶ ተቀብሎለታል። ሽልማቱንም የሰጡት ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት ናቸው። 

በጥበቡ በለጠ

 

በጀርመን የባህል ተቋም ውስጥ ላለፉት በርካታ ዓመታት የኪነ-ጥበብ ጉዳዮችን በማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉት ወ/ሮ ተናኘ ታደሰ የ2008 ዓ.ም የንባብ ለሕይወት ዝግጅት ላይ ተሸላሚ ሆኑ። ወሮ ተናኘ አያሌ የሥነ-ፅሁፍና የኪነ-ጥበባት መድረኮችን ያቀናጁና፣ ውጤታማ የሆኑ ሴት ናቸው ተብሏል። ታሪካቸውም እነዲህ ቀረበ።

“የዛሬ 13 ዓመት በታላቁ ኢትዮጵያ ሰዓሊ እና ገጣሚ ወይም ገጣሚ እና ሰዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ ሕይወትና ስራዎች ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ ጥሪ ቀረበ። ጥሪው የቀረበው በጀርመን የባህል ማዕከል (ጎተ ኢኒስቲቲዩት) ነው። በርካቶች ወደ ስፍራው አመሩ። አዳራሹ ጥቅጥቅ ብሎ ሞላ። መላወሻ ቦታ ጠፋ። መድረኩ ላይ ለማወያየት ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ እና ዛሬ በሕይወት የሌለው ሰዓሊ ዮሐንስ ገዳሙ ቁጭ ብለዋል።

ታዲያ በዚህ የታዳሚዎች ብዛት እና ስሜት ድብልቅልቅ ባለበት መድረክ ላይ ወ/ሮ ተናኘ ታደሰ ወደ መድረኩ ፊት መጡ። ለታዳሚውም የመክፈቻ ንግግር አደረጉ። እንዲህም አሉ።

“ዛሬ እዚህ የተሰባሰብነው ለአንድ ታላቅ አላማ ነው። እንደምታውቁት ገብረክርስቶስ ደስታ ከሀገሩ ከተሰደደ በኋላ ጀርመን ይኖር ነበር። እነዚያን ድንቅ ስዕሎቹን ለጀርመን መንግስት በአደራ ሰጥቶ ወደ አሜሪካ ተሰደደ። አደራ ሲሰጥ ግን አንድ ነገር ተናግሯል። ሐገሬ ሰላም ከሆነች ስዕሎቹን ወደ ሐገሬ መልሱልኝ በማለት ተናዟል። እርሱ ወደ አሜሪካ ሔዶ ኦክላሆማ ውስጥ ሕይወቱ አልፋ እዚያው ተቀብሯል። በኑዛዜው መሠረት ስዕሎቹ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ልክ በዛሬዋ ዕለት እቅስቃሴ የምንጀምርበት ወቅት ነው። ይህ የዛሬው ጉባኤችን የረጅሙ አላማችን መነሻ ነው። ከዚህ በኋላ በገብረክርስቶስ ደስታ ስራዎችና ማንነት ላይ ሰፊ ውይይት እያደረግን በመጨረሻም እነዚያ ስዕሎቹ ወደ ሐገራቸው መጥተው የሀገሪቱ ቅርስ የሚሆኑበትና የእሱንም ስም ለዘላለም የሚያስጠሩበት ስፍራ ላይ ለማኖር የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። እንደ ዘመቻ ቁጠሩት። ሀ ብለን የጀመርነው እንቅስቃሴ ፍፃሜው የገብረክርስቶን ኑዛዜ እውን ማድረግ ነው። እናም የዛሬው ውይይት በይፋ ተጀምሯል”

በማለት ወ/ሮ ተናኘ ታደሰ ተናገሩ።

ከተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ እና ሰዓሊ ዮሐንስ ገዳሙ በተጨማሪ፣ ዶ/ር ፈለቀ አዘዘ፣ ዶ/ር ዮናስ አዳማሱ፣ አቶ አስፋው ዳምጤ፣ ሰዓሊ በቀለ መኮንን፣ ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፣ ሰዓሊ ደስታ ሐጎስ፣ የሥነ-ጽሁፍ ምሁሩ ዛሬ በሕይወት የሌለው ብርሃኑ ገበየሁ፣ ደራሲና ገጣሚ ነብይ መኮንን፣ ብርሃነመስቀል ደጀኔ እና ሌሎችም በርካታ ምሁራንን እየጋበዙ ወ/ሮ ተናኘ ውይይት አደረጉ። በውጭ ሀገራትም እንደነ ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላን፣ ወሰኔ ወርቄ ኮስሮቭን የመሳሰሉ ሰዎች ገብረክርስቶስ ላይ እንዲናገሩ መድረክ አመቻቹ። በመጨረሻም የጀርመን መንግሥት እነዚህ ስዕሎች ወደ ሐገር ቤት እንዲገቡ ሊፈቅድ የሚችለው ደረጃውን የጠበቀ ሙዚየም ወይም ጋላሪ ሊዘጋጅላቸው ነው ተባለ። ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ ከዚሁ ሃሳብ ጋር ተስማምተው ዛሬ የገብረ ክርስቶስ ማዕከል በሚል የሚጠራው ሙዚየም ተዘጋጀለት። ከዚያም የጀርመን መንግስት ተጠየቀ። ብዙ ነገሮች መሟላታቸውን በማመኑ የጀርመን መንግስት የገብረ-ክርስቶስ ስዕሎች ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ እንዲገቡ ፈቀደ።     

ዛሬ በሐገራችን ውስጥ ካሉት ብርቅና ድንቅ የጥበብ መዘክሮች ከሆኑት ውስጥ አንዱ ይህ የገብረክርስቶስ ደስታ ማዕከል ነው። ታዲያ ይህ ማዕከል እዚህ እንዲደርስ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር የጀርባ አጥንት ሆነው የሰሩ ናቸው። ታዲያ እኚህ ታላቅ ባለውለታ ብናመሰግናቸውስ?

ወ/ሮ ተናኘ ታደሰ ይህን ብቻ አይደለም የሰሩት። እጅግ በርካታ የጥበብ ድግሶችን በጀርመን የባህል ተቋም ውስጥ ሲያሰናዱ፣ ሲያስተባብሩ እና አያሌ ለውጦችን ሲያመጡ ቆይተዋል።  

የታላቁን ባለቅኔ የደበበ ሰይፉን ሕይወትና ስራዎቹን በጥልቀት የታየበትን “የደበበ ሰይፉ ምሽት” በማለት ሰፊ ዝግጅት አካሂደዋል።

የታላቁን የሥነ-ፅሁፍ ምሁር የዶ/ር ዮናስ አድማሱን ስራዎችና ሕይወት የሚያስቀኝ “የዮናስ አድማሱ ምሽት” በሚል አዘጋጅተዋል።

የፈላስፋው ባለቅኔ የሰይፉ መታፈሪያ ፍሬውን ሕይወትና ስራዎች የሚያስቃኝ ዝግጅት አቅርበዋል።

በርካታ ሰዓሊያንን ከሐገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት እንዲመጡ በማድረግ በየጊዜው የስዕል አውደ-ርዕይ እና ውይይት እንዲደረግ ቁልፍ ሚና ነበራቸው።

ዛሬ በስነ-ግጥሙ መስክ ሰፊ እውቅና ያላቸውን ወጣቶቹን እነ ምስራቅ ተረፈን፣ አበባው መላኩን፣ ደምሰው መርሻን፣ ሜሮን ጌትነትን እና ሌሎችንም ወደ መድረክ በማምጣት “ወጣት ድምፆች” በሚል መጠሪያ ዝግጅት ደግሰው እነዚህ ልጆች ወደፊት ታላላቅ ገጣሚያን እደሚሆኑ የዛሬ 13 ዓመት በይፋ የተናገሩ ናቸው። ውጤቱንም በስፋት ያየነው ነው። ገጣሚዎቹ እውነትም የተባለላቸውን ሆነዋል።

ወ/ሮ ተናኘ ታደሰ፣ በታሪክ፣ በስነ-ፅሁፍ፣ በሳይንስ፣ በልዩ ልዩ መስኮች ላይ ውይይት እዲደረግ መድረክ የሚያመቻቹ ብቻ ሳይሆኑ ይህን ስራቸውን በሚሰሩበት ወቅት ወጣቱ የውይይት መድረክ ያጣበት ጊዜ ነበር።

በንባብ ላይ በርካታ ውይይቶችን አድርገዋል። ንባብ ሀገርና ዜጋን ወደ ተሻለ ደረጃ ማምጫ መንገድ መሆኑን ሰፊ ስራ ሰርተዋል። እዚህ ዘርዝረን የማንጨርሳቸውን አያሌ ተግባራት አከናውነዋል።

በመሆኑም ንባብ ለሕይወት የ2008 ዓ.ም ዝግጅት ላይ ልዩ ተመስጋኝ ሆነው፣ ለትውልድና ለሀገር ላበረከቱት አስተዋፅኦ ዕውቅና ስንሰጣቸው በታላቅ ደስታ ነው።”

በማለት አዘጋጆቹ ተናግረውላቸዋል። ወ/ሮ ተናኘ ታደሰ የ2008 ዓ.ም የንባብ ለሕይወት ዝግጅት ላይ ለኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ተሸላሚ ሆነዋል። 

በጥበቡ በለጠ

 

አጼ ቴዎድሮስ በተሰውበት መቅደላ አምባ ላይ ላለፉት አመታት ትምህርት ቤት በነጻ በማሰራት፣ ለልጆች የትምህርት ቤት ዩኒፎርም በማሰፋትና ቤተ-መጻሕፍት ለልጆች በመክፈት ከፍተኛ አስተዋጽዎ ያደረገው አቶ ታደሰ ተገኝ ንባብ ለሕይወት የ2008 ዓ.ም ተመስጋኝ ዜጋ ሆኖ ሽልማት ተሰጠው።

ታደሰ በዓለም የምግብ ድርጅት ውስጥ ትልልቅ ኃላፊነት ካላቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነው። በአንድ ወቅት መቅደላ አካባቢ የምግብ እጥረት ተከስቶ አካባቢውን ለማጥናትና ከዚያም የሚያስፈልገውን እርዳታ ለመለገስ በታደሰ ተገኝ የሚመራ የመስሪያ ቤቱ ልዑክ ወደ አካባቢው ይሄዳል።

ታደሰ ተገኝ መቅደላ አካባቢ ሲደርስ በሚያየው ነገር ሊያምን አልቻለም። ያቺ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ መናገሻ ቦታ የነበረች፣ ያቺ ኢትዮጵያዊያን ሀገራችንን ለእንግሊዝ መንግሥት አንሰጥም ብለው ጀግኖች የወደቁባት፣ ያቺ ታላቁ መሪ አፄ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ ክብር ብለው ሽጉጣቸውን ጠጥተው የተሰውባት ታሪካዊት ቦታ ተራቁታለች። መቅደላ የመኪና መንገድ የላትም። የመቅደላ ልጆች ት/ቤት የላቸውም ነበር። በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሁፍና የጥበብ ማዕከል የነበረችው መቅደላ፣ ታደሰ ተገኝ ሲሄድባት ት/ቤትም የለባትም ነበር። ጭራሽ በምግብ እጥረት ተመታ ነዋሪዎቿ የእርዳታ ያለህ የሚሉበት ወቅት ነበር።

ታደሰ ተገኝ በሚያየው ነገር አዘነ። ግን አዝኖ ብቻ ዝም አላለም። ከንፈሩን መጦ ችላ አላለም። ይልቅስ ራሱን ጠየቀ። እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ምን ማድረግ እችላለሁ ብሎ አሰበ። ይህን የኢትዮጵያን የታሪክ ማማ አሁን ካለበት ችግር ለማላቀቅ የራሴን አስተዋፅኦ ላበርክት ብሎ ሃሳብ ነደፈ።

የመቅደላን ታሪካዊ ሕዝቦች ሊያያቸው አቀበቱን ሊወጣ ተራራውን ሊያያዘው ተነሳ። የመቅደላም ነዋሪዎች አዲሱን እንግዳቸውን ሊያስተናግዱት በቅሎ አቀረቡለት። አንዴ በእግሩ፣ አንድ ጊዜ በበቅሎ እያለ መቅደላ አምባ ላይ ከረጅም ሰዓታት ጉዞ በኋላ ወጣ። ታሪካዊው መቅደላ መድሐኒአለም ቤተ-ክርስቲያን አርጅቷል። አንዳንድ ጐኑ ረጋግፏል። የአፄ ቴዎድሮስ ወታደሮች የወደቁበትና የተቀበሩበት ስፍራ ነው። ታሪካዊው ሴፓስቶፖል መድፍም ዝም ብሎ ቁጭ በማለት የታሪክ ሂደትን ይታዘባል። የመቅደላ ልጆችም ተኮልኩለው ወጡ። ታደሰ ተገኝ የተባለውን የመሀል ሀገር ሰው አዩት፣ ተዋወቁት። አባቶች እናቶች ታደሰን አስተናገዱት። ከመሀል ሀገር ሄዶ የሚያያቸው የሚጠይቃቸው ሰው ስለሌለ ታደሰ ተገኝ ብርቅ ሆነባቸው።

ታደሰም የመቅደላን ነዋሪ ደግነት፣ ልበ ቀናነት፣ ታሪካዊነት እና አሁን ያለበትን አስከፊ ድህነት ሲያይ ስሜቱ ተነካ። እስከ እለተ-ሞቴ ድረስ ከናንተ ጋር ነኝ አላቸው።

ታደሰ ተገኝ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ የነበረው የዓለም የምግብ ድርጅትን እና የመቅደላን ነዋሪዎች በማስተባበር “ምግብ ለስራ” በተባለ መርሃ-ግብር ወደ መቅደላ አምባ የሚያስኬድ ጥርጊያ መንገድ አሰራ። በዚህ የመኪና መንገድ ላይ የታደሰ ተገኝ ቶዮታ ላንድክሩዘር መኪና ጥሩንባዋን እያሰማች ለመጀመሪያ ጊዜ መቅደላ አናት ላይ ወጣች። ተአምር ተባለ። መኪና አይተው የማያውቁት የመቅደላ ልጆች ሲደነቁ፣ ሲገረሙ፣ ሲደሰቱ ሰነበቱ።

ታደሰ በዚህ ብቻም አልቆመም። የመቅደላ ልጆች ት/ቤት ሊኖራቸው ይገባል፤ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ተማሪዎች መደበኛ ተማሪ መሆን አለባቸው ብሎ ተነሣ። ፈለገ-ብርሃን የተሰኘ የበጐ አድራጐት ማኅበር መስርቶ ጓደኞቹን እና ወዳጆቹን አስተባብሮ መቅደላ አምባ ላይ ት/ቤት ማሰራት ጀመረ። በመጨረሻም መቅደላ አናት ላይ የት/ቤት ደውል መሰማት ጀመረ። የመቅደላ ልጆች ታደሰ ተገኝ በሚባል ሰው ረዳትነት የት/ቤት ዩኒፎርም ለብሰው፣ ደብተር፣ መፃህፍትና የትምህርት ቁሳቁሶችን ይዘው መደበኛ ተማሪዎች ሆኑ።

እዚህ የመቅደላ አፋፍ ላይ እየወጣች የምትመጣው የታደሰ ተገኝ መኪና ናት።

አፄ ቴዎድሮስ ከመላው ኢትዮጵያ የሰበሰቧቸው ታላላቅ የብራና ጽሁፎችና ታሪኮች የተቀመጡት መቅደላ ላይ ነበር። ቴዎድሮስ መቅደላን የጥናትና የምርምር ማዕከል ሊያደርጓት አስበው ነበር። እነዚህ የኢትዮጵያ ቅርሶች በእንግሊዝ ወታደሮች ተዘርፈው በበርካታ ዝሆኖች ተጭነው ከሀገር ከወጡ 147 ዓመታት አለፉ።

የእንግሊዝ ሀገሩ ገናና ጋዜጣ ‘ፋይናንሻል ታይምስ’። ጋዜጣው በአንድ ወቅት ከመቅደላ አምባ ስለተዘረፉት የብራና ጽሁፎች ሰፊ ሽፋን ሰጥቶ ነበር። እንደ ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ዘገባ፣ በእንግሊዝ ወታደሮችና በእንግሊዝ መንግስት በ1860 ዓ.ም ከመቅደላ የተዘረፉ የብራና ጽሁፎች ወደ ለንደን መጥተዋል ይላል። እነዚህ የብራና ጽሁፎች በገንዘብ ቢተመኑ ሁለት ቢሊዮን ፓውንድ እንደሚያወጡ ጋዜጣው ያትታል። ይህን ሁለት ቢሊየን ፓውንድ በአሁኑ ምንዛሬ ወደ ብር ስንቀይረው ከ63 ቢሊየን ብር በላይ ነው። መቅደላ ይህን ያህል ቅርስ ተዘርፋለች። የዛሬዋ መቅደላ ባዶ ነች። ኦና ናት። ድህነትና ጐስቋላነት ክፉኛ ተጫጭኗታል። ከውስጧ ግን 63 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ቅርሶችን ተዘርፋለች።

ታዲያ ይሕቺን መቅደላ ወደ ነበረችበት ታሪክ ለመመለስ ታደሰ ተገኝ ብዙ ውለታ እያደረገ በመሆኑና በሌሎችም የኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ት/ቤትና ቤተ-መጻሕፍት በማሰራት ያበረከተውን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባት ንባብ ለሕይወት የ2008 ዓ.ም ልዩ እውቅና እና ምስጋና ብሎም ሽልማት ሰጥቶታል። ሽልማቱን የተቀበለውም ከኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት እጅ ነው።

 

በጥበቡ በለጠ

አንባቢ ሰው ረጅም እድሜ ይኖራል የሚል አባባል አለ። ለምን ቢባል እርሱ ያልኖረበትን፣ ያለፈበትንም ዘመን ጭምር በመፃህፍት ውስጥ ስለሚያገኝ ያልተፈጠረበትንም ዘመን መኖር ይቻላል በማለት ያብራራሉ። ሰኔ 30 የንባብ ቀን ተብሎም በደራሲያን ማሕበር ተሰይሟል። ንባብን ከሕይታችን ጋር እንድናቆራኝ እነ ቢኒያም ከበደ “ንባብ ለሕይወት” ብለው በሰፊው እየሰሩበት ነው። ነገ ታላቅ የንባብ አውደ ርዕይ በኤግዚቢሽን ማዕከል ይከፍታሉ። እሰየው፣ ደግ አደረጋችሁ እላቸዋለሁ።

በሀገራችን ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ መፃህፍቶቻቸው ስለ ንባብ አስፈላጊነትና ጣፋጭነት ሲያስረዱን የቆዩት ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ንባብ ትልቅ የህይወት መሠረት እንደሆነ ብዙ ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ክፉኛ ከምንተችበትና ከምንናቅበት ባህሪያችን ዋነኛው ለንባብ ያለን ትኩረት አነስተኛ መሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አንባቢ ትውልድ እንደሌለ በጥናት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ከ70 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያ አንድን መፅሀፍ የምታትመው ግፋ ቢል ሦስት ሺ ቅጂ (ኮፒ) ነው። ይሄ ማለት ደግሞ በየትኛውም ዓለም የመጨረሻ ዝቅተኛ ኮፒ መሆኑ ይታወቃል።

ሀገራት አንድን መፅሀፍ በብዙ መቶ ሺ ኮፒዎችና በሚሊዮኖች እያሳተሙ ለህዝባቸው መንፈሳዊ ልዕልና ለሀገራቸውና ለደራሲዎቻቸው ገቢና የበለጠ ለስራ መነሳሳትን እየፈጠሩ ነው። እኛ ግን የቱጋ ነን? መልሱ አስደንጋጭ ነው።

በየሀገሩ በአመት በብዙ ሺ የሚቆጠሩ መፃህፍት ይታተማሉ። ሀገራችን ግን ከህትመቱም ከንባቡም ባይተዋር ሆና ትገኛለች። እባክሽ ኢትዮጵያ ንቂ!

አንድ ታዋቂ ደራሲ ምን አሉ፡- 'የሰው ልጅ የተመራባቸው አስተሳሰቦች ሁሉ በመፃህፍት ገጽ ውስጥ ተመዝግበዋል። ማንበብ መቻል እነዚህን ከአእምሮ የመነጩ ውድ የሆኑ ሀብቶች ለመውሰድ የሚያስችለውን ቁልፍ እንደመያዝ ነው።' ሲሉ ገልፀዋል።

ሀሳባቸውን ሲያጠነክሩም መፅሀፍትን በጥራዝ የተሸፈኑ ህይወት አልባ ወረቀቶች ናቸው ብሎ መገመት ስህተት ነው፤ መፃህፍት ህይወት አላቸው፤ እንዲያውም አንድን መፅሀፍ መግደል አንድን ሰው እንደመግደል ይቆጠራል ይባላል።

“አንድን ሰው የገደለ አንድን አስተዋይ ፍጡር ገደለ፤ አንድን መፅሀፍ የገደለ ግን ማስተዋልን እራሱን ገደለ” በማለት ስመ ጥሩው ፀሐፊ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ የእውቀት አውራራ ጐዳና በሚለው ፅሁፋቸው ገልፀዋል።

በዓለም ታሪክ ውስጥ የተመዘገቡ የአእምሮ ስራዎች ሁሉ በመፃህፍት ውስጥ ተመዝግበዋል። መፃህፍት መላውን የዓለምን መንግሥትና ሞገሱን የምንመለከትባቸው መነፅሮች ናቸው።

በሀገራችን ኢትዮጵያ የራሳቸውን የቅንጦት ኑሮ በመተው ህዝባቸው ለንባብና ለእውቀት እንዲታትር ቀን ከሌት ለፍተው ያለፉ ታታሪ ሰዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ዛሬ ስማቸውን ደጋግሜ የማነሳው ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ ናቸው። ሻምበል አፈወርቅ የጥላሁን ገሠሠ ምርጥ ዘፈን የሆነችውን “የትዝታዬ እናት” የተሰኘችውን ግጥም ፀሐፊ ናቸው። ከ20 ያላነሱ መፃህፍትን አሳትመዋል። ከነዚህም ውስጥ “ታላላቅ የፍቅር ታሪኮች”፣ “ጠቅላላ ዕውቀት”፣ “ታላላቅ አስደናቂ ታሪኮች” የተባሉት መፃህፍት ይገኙበታል። ስለ ንባብ ጠቀሜታ በየመፅሐፍቶቻቸው ሳያወጉን አላለፉም።

በመፃህፍት ገጽ ውስጥ የህንድ ተቋራጮች ቀንና ሌሊት ያለማቋረጥ በመዶሻ ድምፅ ሳያሰሙ ህንፃዎችን ይገነባሉ። ሰዓሊዎች ይስላሉ፣ ገጣሚዎች ይቀኛሉ፤ ፈላስፎች ይፈላሰፋሉ፤ ተራኪዎች ይተርካሉ... የጦር መሪዎችም ያለ ድምፅና ያለ ደም መፋሰስ በድል ይገሠግሳሉ ተብሏል።

በጥቂት ቃላት ከተሞች ተመስርተው ስልጣኔዎች ተስፋፍተው እንዴት እንደተራመዱ እንረዳለን። በህሊናችን አይኖች አትኩረን ብንመለከት ታላላቅ ዩኒቨርሲቲዎችና የትምህርት ሸንጐዎች ሊሰጡን የሚችሉት ልክ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች የሚሰጠንን አይነት እውቀት ነው - ይኸውም - ማንበብን ያስተምሩናል። ይላሉ አፈወርቅ።

የዓለም ገዥ የሆነው የሰው ልጅ ዘር የሆንን ሁሉ ጠቅላላው የዓለም ጥበብ በውርስ ተላልፎልን የግላችን እናደርገው ዘንድ በአጠገባችን ሆኖ እስክንረከበው ይጠብቀናል። በአሶርና በግብፅ የመጀመሪያዎቹ በሸክላ ላይ የተቀረፁ ፅሁፎች ከቀረቡበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ላለው ጥበብ ብቻ ሳይሆን የታላላቅ ምሁራን ባህሪም እንኳን ሳይቀር በመፃህፍት ውስጥ ተከማችቶ ይገኛል።

ከሰዎች ሁሉ የብልሆች ብልህ የጀግኖች ጀግና፣ የቅንነት ምንጭ የነበሩት ታላላቅ ሰዎች በሞት የተለዩን ቢሆንም፣ በህይወት በኖሩበት ዘመን ያፈሩት ውጤት ሁሉ እንዳለ በመፃህፍት ውስጥ ሰፍሯል። አንጐላቸው ፈርሷል። ግን ያፈሩት እውቀት ህያው ሆኖ በርካሽና ቶሎ በሚገኝበት ስፍራ ላይ ተቀምጧልና በድንቁርና ለመኖር ማመካኛ ምንም መንገድ ሊኖር አይችልም።

ታታሪው ደራሲ ሻምበል አፈወርቅ፣ በማንበባችንም እንዳንኩራራ፣ ጉረኛ እንዳንሆን፣ ትዕቢተኛ፣ ያለእኔ አዋቂ የለም እያልን ቡራ ከረዩ እንዳንል ልዩ ልዩ ምሳሌዎችንም እየሰጡን ያለዝቡናል።

ለምሳሌ ግሪካዊው ፈላስፋ ሶቅራጥስ፣ የእውቀት ሰው መሆኑን አልገለፀም ግን የገለፀው አለማወቁን የሚያውቅ መሆኑን ነው።

ታላቁ የሮማ ፈላስፋ ኤፑቴክተስ ሲገልፅ፣ “የእውቀትን ሸማ ጠርዟን እንኳን አልነካኋትም” ብሏል።

አይዛክ ኒውተን የፍጥረት ዓለምን የስበት ሕግ ገለፀ። ቴሌስኮፕን አሻሻለ፤ የባህርን ከፍና ዝቅ ማለት ሰበቡን ተረዳ። የጅራታም ኮከቦችን የጉዞ ፈር አጠና። ማቲማቲክስንና ስነ-ሃይማኖትን ተመራምሮ ገለፀ። ነገር ግን ይህ ሰው ይህን ሁሉ እውቀትና ክብር ይዞ በጣም ትሁት ሰው ነበር በማለት የንባበ ጉረኛ እንዳንሆን ይመክሩናል።

ከዚህ ሌላ ትምህርት አይገባኝም፣ እኔና ትምህርት ሆድና ጀርባ ነን እያሉ ተስፋ ቆርጠው ለተቀመጡም “ንቁብዙ ጊዜ አላችሁ። እናንተም ካነበባችሁ ትልቅ ደረጃ ትደርሳላችሁ” በማለት ከባዶ ተነስተው ትልቅ ደረጃ የደረሱትን ሰዎች እየጠቃቀሱ ሰብዕናቸውን ያጐለብታሉ።

ሚልተንና ሆሜር ዓይነስውሮች ነበሩ። ፔሬስኮ የተባለም “የሜክሲኮ መወረር” የተባለውን መፅሀፍ የደረሰ ሰው፣ የዓይኑ ብርሃን ተዳክሞ የሚፅፍበትን ወረቀት እንኳን ማየት ተስኖት በነበረበት ወቅት በመከራ ያነብ ነበር። እነዚህ ሰዎች ታሪካቸው ዘመናትን አቋርጦ በሰው ልጆች ዘንድ ህያው ሆኖ የሚኖረው በንባባቸውና በፅሁፋቸው ነው። የኛው ጳውሎስ ኞኞ የተማረው እስከ አራተኛ ክፍል ነው። ግን በማንበብ ብቻ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ታሪክ ፀሐፊ፣ ወገኛ... ሆኖ ታላቅነቱን አስመስክሮ አልፏል።

የቻርልስ ዳርዊን አባት የልጁን ደደብነት ተመልክቶ ቤተሰቡን አሰዳቢ ይሆናል ሲል ገምቶ ነበር፤ ግን ተሳትቷል... በኋላ ዘመኑ ይህ ልጅ ዳርዊን የዓለምን አስተሳሰብ ለመለውጥ የቻለውን የኤቮሉሽንን የዘገምተኛ ለውጥን መላምት ለመግለፅ የበቃ ምሁር ሆኗል። እናም አእምሮአችሁን የዘጋችሁ ንቁ አንብቡ ይሉናል አዋቂዎቹ።

ናፖሌዎን ቦናፖርት የዕድገት ተስፋ እንደሌለው የተቆጠረ ወጣት ነበር። በተማረበት የወታደራዊ አካዳሚ ውስጥ ከክፍሉ 42ኛ ነበር የወጣው። በመጠንከሩ ደግሞ ልዕለ ሰብአዊያን ሆኖ ዘመኑን አሳልፏል። ስለዚህ ሁላችንም ራሳችንን ለብቁ ነገር እንድናደረስ አንብቡ ይሉናል። ያነበበ ፈሪ አይሆንም፤ ያነበበ በየትኛውም ቦታ አይሸማቀቅም፣ ያነበበ የዓለም ፓስፖርት ያለው ነው የሚሉ ሞልተዋል።

መፃህፍት የዓለም የስልጣኔ ፎርሙላዎች ናቸው። ስልጣኔ ማለት እነርሱ ውስጥ ያለው ቁም ነገር ሲተነተን ሲተገበር የሚመጣ ውጤት ነው። ለዚህም ነው በዓለም የመጡና የሚመጡም ጠቢባን ለመፃህፍት ያላቸው ፍቅር ወደር የሌለው።

ለምሳሌ ጅቦን የተባለው የታሪክ ፀሐፊ “በቅድሚያ ያደረብኝን የማይናወጥ የማንበብ ፍቅር፣ በህንድ አገር የሀብት ቅርሶች እንኳ ቢሆን አልለወጠውም” ሲል ተናግሯል።

‘የሁለት ከተሞች ወግ’ የተሰኘው መፅሀፍ ደራሲ ቻርልስ ዲክንስ ከማንኛውም ከሚፈታተነው ችግር ሁሉ የሚያስጥለው ያደረበት የመፃህፍት ፍቅር መሆኑን ገልጿል።

ሲሴሮ የተባለው ሮማዊ በመፃህፍቶቹ መሀል ለመኖርና ለመሞት ይችል ዘንድ ያለውን ሁሉ እንደሚሰጥ ተናግሯል። ይህ ሰው ትቶ ካለፋቸው ገለፃዎቹ መካከል 'አንድን መፅሀፍ እቤት ውስጥ ማስገባት፣ ለቤቱ ነፍስ እንደመስጠት ይቆጠራራል' ብሏል።

ፌኔሎን የተባለው ደራሲም መፅሀፍቶቼን ወይም ለመፃህፍት ያለኝን ፍቅር በአንድ መንግሥት አገር እንኳን አለውጠውም ብሏል።

ሰር ዋልተር ስኮት ከመሞቱ በፊት በተሽከርካሪ ወንበር ወደ መፃህፍት ቤቱ እንዲወስዱት አድርጐ ከነዚህ ህይወቱን በሙሉ ካልተለያቸው ወዳጆቹ ሊለያይ መሆኑን አስታውሶ ምርር ብሎ በማልቀስ ተሰናብቷቸዋል።

አሌክሳንደር ስሚዝ የተባለው የስኮትላንድ ባለቅኔ ሲናገር “አትክልት በሚገኝበት መስክ ላይ ቀናቶችን አሳልፋለሁ፤ ሌሊቶችን ደግሞ በመፅሀፍት ቤቴ አሳልፋለሁ” ብሏል።

አንድ የመፃህፍት ቤት ከማንኛውም ሀብት የበለጠ በመሆኑ ምንም የሚወዳደረው አይገኝም። ስለዚህ ማንም ከእኔነቱ ጥልቀት በመነጨ ፍላጐት እውነትን ደስታን ማስተዋልን ሳይንስን ወይም ሃይማኖትን እደግፋለሁ የሚል ሰው የግድ መፃህፍትን የሚያፈቅር መሆን አለበት ይላሉ ታታሪ ምሁራን።

አንዲት ሴት ስለ ህይወት ባላት አመለካከትና የመንፈስ ፅናት የተነሳ “ከዓለም በጣም አስደናቂ የሆነች የሰው ልጅ ዘር አባል” ለመባል በቅታለች። ስሟ ሄለን ኬለር ይባላል። የማየትና የመስማት ችሎታ አልነበራትም። ለብዙ አመታትም መናገር ወይም ድምፅ ማሰማትም እንኳን አትችልም ነበር። ግን ከግምት በላይ በሆነ ጥረት በዳበሳ አጥንታ ለማንበብ ከቻለች በኋላ ከፍ ያለ ማስተዋልን ገበየች።

ወይዘሪት ኬለር፣ ራድክሊፍ ላይ በ1904 ከተመረቀች በኋላ በጣም ጠቃሚና ስመ-ጥሩ ለመሆን በቃች። በየታላላቅ አዳራሾች ንግግር በማድረግና በልዩ ልዩ ርዕሶች ላይም ሰፋ ያሉ ፅሁፎችን ፃፈች። ይህች ሴት ምንም እንኳን በተፈጥሮ ብዙ የተነፈጋት ብትሆንም የማዳንና የማጠንከር ምንጭ በሆኑት በመፃህፍት ተረድታ ህይወቷን የተሟላ አይንና ጆሮ ካላቸው ግን የራሳቸውንና የልባቸውን ስጦታ ለማሰራት ካልቻሉ ሰዎች በተሻለ ሁኔታ ጠቃሚ እንዲሆን አደረገች። የቴዲ ለምባዲና ..ለሄለን ኬለር..

መጪው ዘመን አዲስ አመት የምንይዝበት ነው። ግን ሳናነብ፣ ሳናውቅ፣ ውስጣችን አዲስ ነገር ሳይኖር አመታት አይፈራረቁብን። እናንብብ። ቃል እንግባ “በወር ቢያንስ አንድ መፅሀፍ እናንብብ፤ በወር ቢያንሰ አራት መፃህፍት እንግዛ።” መጪውንም ዘመን በዚሁ እንቀጥል።

 

አንባቢ ሆይ……

በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መፃህፍትን እያሳተሙ ይገኛሉ። ባለፉት 10 አመታት ውስጥ እየታየ ያለው የመጽሀፍት ህትመትና ስርጭት ከባለፉት ጊዜያት ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ መጥትዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ፣ በመፈንቅለ መንግስት ላይ፣ በሳይንስ ላይ፣ በልቦለድ፣ በግጥም፣ በአጭር ልቦለድ ወዘተ. ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መፃህፍት ይታተማሉ። ይህን ክስተት ያዝኩና ልዩ ልዩ ደራሲያንን እና የመፃህፍት ቤት ባለቤቶችን ቀጥተኛ ባልሆነ መልክ ጥያቄ ሳቀርብላቸው እና ስወያያቸው ነበር የሰነባበትኩት።

ጥያቄው ለምን መፃህፍቱ አንባቢን አልሳቡም? በራራሳቸው አንባቢን የሚጠሩ አይደሉም የሚሉ አሉ። ነገር ግን ይህ አባባል ዝም ተብሎ ወዲያው የሚጣል ባይሆንም በኛ ሀገር ሁኔታ የሚያስኬድ አይደለም። ምክንያት ቢጠየቅ መተንተን ይቻላል ይላሉ ይሄን ሀሳብ የሚሞግቱት።

ገና ከጥዋቱ የንባብ ልምድ የሚባል ነገር ያልተገነባባት ሀገር ነች። ስንቶቻችን ነን በቀን የተወሰነ ሰዓት ለንባብ የምንሰጠው? ለመሆኑ በህይወት ዘመናችንስ ምን ያህል መፅሀፍት አንብበናል? ብንባል አፋችንን ሞልተን የምንመልሰው ነገር አለ? ጉዳዩ አጠራጣሪ ነው ለብዙዎቻችን::

ደህና ኑሮ አለን እንበል፤ ቤት ሠራን፤ እዚያ እቤታችን ውስጥ የንባብ ክፍል፤ የመፃህፍት ክፍል፤ ብለን የሠራን ስንት እንሆናለን? ነገሩ ባዶ ነው። ካለንባብ የተገነባች ስብዕና ደግሞ የህይወትን መራራ እና ጣፋጭ ገጽታ ሳታውቅ እንዲሁ በከንቱ ዓለም ላይ ስትዋትት የምትኖር ናት ይባላል። ንባብ ብዙዎቻችን የለንበትም።

እዚህ ጐረቤት ኬኒያ ልውሰዳችሁ። ልብ አድርጉ፤ ኢትዮጵያን በስተደቡብ እንደጨረሳችሁ ኬኒያ ትገባላችሁ። ኬኒያውያን ሁለት ጐምቱ ጋዜጦች አሏቸው። አንደኛው ዴይሊ ኔሽን ይባላል። ሌላኛው ደግሞ ዘስታንደርድ ይሰኛል።

ዴይሊ ኔሽንም ሆነ ዘስታንደርድ በየቀኑ የሚታተሙ ባለብዙ ገጽ ጋዜጦች ናቸው። ለምሣሌ ዴይሊ ኔሽን ብቻውን በየቀኑ ወደ 200 ሺህ ኮፒ ይሸጣል። አንዱ ጋዜጣ በኢትዮጵያ ሦስት ብር ነው። ዘስታንደርድ ደግሞ ወደ 60 ሺህ ኮፒ ታትሞ በየቀኑ ይሸጣል። ኬንያ ውስጥ ያሉ ጋዜጦች ብቻ በቀን 800 ሺህ ህዝብ ገዝቶ ያነቧቸዋል። ይሄ ለጋዜጣ ብቻ ነው።

ይህን የንባብ ልምድ ኬኒያዊያን ያዳበሩት እንደሁ በዋዛ አይደለም። በቅድሚያነት የንባብ ተቋማት ተብለው የሚታወቁት የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ናቸው። ህፃናት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ንባብን እንዲያዘወትሩ እንዲመራመሩ፣ ሲያወሩም ካነበቡት ሐረግና ዐ.ነገር እየመዘዙ እንዲጠቀሙ በአንክሮ ይመከራሉ፤ ይበረታታሉ። ይሄ ልማድ ታዲያ አንባቢ ማህበረሰብ በሰፊው አፍርቷል።

በኛ ሀገር ላይ ስናየው ደግሞ ይሄ እየተገነባ አይደለም። ለምሣሌ ያህል በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ልዩ ልዩ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ቤተ-መፃህፍቶች ዘንድ ሄጄ ነበር። አንባቢዎች በቤተ-መፃህፍቶቹ ውስጥ ካለመታየታቸው ሌላ የመፃህፍቱንም አቅርቦት ስናይ በተለይ ከልዩ ልዩ ደራሲያን የታተሙ ድርሰቶችን በጭራሽ አለማስገባታቸው ግራ ነው የሆነብኝ። የሚመለከታቸውን የትምርት ርዕሳነ መምህራንን ስጠይቅ የተለያየ መልስ ይሰጡኛል።

አንደኛው ከመማር ማስተማሩ ሂደት ጋር በቀጥታ ስለማይዛመዱ ያን ያህል በልቦለዶች ትኩረት ሌሎች መፃህፍት ግዢ ላይ እንደሚያተኩሩ ገልፀውልኛል። ንባብ ማለት የሰውን ልጅ በየትኛውም የሙያም ሆነ የትምህርት መስክ ቢኖር በማንበቡ ሳቢያ የሚጐዳበት ነገር የለም ይባላል፤ እናንተ ይሄን እንዴት ታዩታላችሁ ብያቸዋለሁ?።

ተማሪዎች የቀለም ትምህርታቸውን የሚያዘናጋቸውን ነገር አንፈቅድም አሉኝ። ግንኮ ሲጀመር የመምህራኑስ የንባብ ልምድ ምን ቢሆን ነው ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው። እናም ዋናው ችግር ሆኖ የተገኘው በአስተዳደር ላይ ያሉትም ሀይላት ተማሪዎቻቸው አእምሮ ውስጥ ይህን ታላቅ ነገር እንዴት ያስርፁት፡

በእርግጥ ልጆች ከእነርሱ ዕድሜ ውጪ ያለን መፅሀፍ ሁሉ ያንብቡ ማለታችንም አይደለም። በእውቀታቸውና በልካቸው የተፃፉ ልዩ ልዩ ድርሳኖችን ቢያዩ የወደፊት ህይወታቸው ብዙ አማራራጮችን እንዲያዩ እና ውስብስቧን ዓለም እየተቀላቀሉ ሲሄዱ ያለፈውንና የአሁኑን ዘመን በንባብ እንዲሁም ደግሞ በኑሮም እየደጋገፉ መጪው ጊዜ ብርሃን እንዲሆን ያድርጉላቸው ነው የምንለው።

ደራሲያኑ ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴርንና ባህል ሚኒስቴርን ይወቅሳሉ። እነዚህ ሁለት ተቋማት በዋናነት ይህን ተግባር ሊወጡ የሚገባቸው እንደሆነ በአፅንኦት ይናገራሉ።

ትምህርት ሚኒስቴር መፃህፍቱ እንደየብቃታቸው እየተመዘነ በየት/ቤቱ ተሠራጭተው ተማሪዎች እንዲያነቧቸው፣ እንዲመራመሩባቸው ካላደረገ ይህ ተገቢ አይደለም ብለው ይተቻሉ። አንባቢ ትውልድ እንዲስፋፋ፣ እንዲበዛ ማድረግ የሚችለው ትምህርት ሚኒስቴር ነው። እናም ይህን ተግባር ስራዬ ብሎ እንዲገፋበት ጥሪም አቅርበውለታል።

ሌላው ተወቃሽ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነው። ይህ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ኢትዮጵያዊያን ደራሲዎች የፃፏቸውን ልዩ ልዩ ድርሳኖች አንባቢ እጅ እንዲገባ እና እንዲነበብ መታገል አለበት ይላሉ።

ለምሳሌ የመፃህፍት ባዛርን በማዘጋጀት፣ የልዩ ልዩ ተቋማት ሠራተኞች መፃህፍት ገዝተው እንዲያነቡ ዘዴዎችን ቢቀይስ አንዱን ታላቅ ኃላፊነት እንደተወጣ እንቆጥርለታለን ብለውኛል።

ከእነዚህ መፃህፍትን በስፋት ሊያነቡ ይችላሉ ተብለው ከሚጠበቁት ተቋማት ውስጥ መከላከያ አንዱ ነው። ለምሳሌ ጦሩ ባለበት ቦታ ሁሉ አነስተኛ የመፃህፍት መደብሮች እንዲኖሩ ቢደረግ፣ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች የማናጅመንት ሰዎች ጋር በመገናኘት በመስሪያ ቤቶቻቸው የንባብ ክፍል መፃህፍት እንዲሸጡ፣ ሠራተኛው በቀላሉ እንዲያቸው ቢደረግ ጥሩ መሆኑን ይጠቁማሉ።

ከዚህ ሌላም የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ የተለያዩ የመፃህፍት ማስታወቂያ ፕሮግራም ቢኖረው መልካም መሆኑን እና መጪው ጊዜም ደራሲያን የበለጠ እንዲጐለብቱ የተሻለ ስራ ይዘው እንዲመጡ አሁን ያወጡት ወጪ የግድ ተመልሶ ወደ ኪሳቸው መግባት አለበት። እንዲህ ካልሆነማ እጀ ሰባራ የምንሆነው ሁላችንም ነን።

ደራሲያን ማህበር ደግሞ በአዲስ መልክ ከተዋቀረ ጀምሮ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በጣም አበረታች ነው። ነገር ግን የሚመለከታቸው አካላት ሁሉም ከጐኑ ካልቆሙ በአንድ እጅ ማጨብጨብ ነው የሚሆነው። በቅርቡ ማህበሩ የመፃህፍት አውደ ርዕዮችን ማድረግ ጀምሯል። ይህ በጣም ሊበረታታ የሚገባው ነገር ነው። ግን አውደ ርዕዮች በሚደረጉበት ወቅት ሰፊ ዝግጅትና አቅም ይጠይቃሉ። ስለዚህ ጥራት ያለው አውደ ርዕይ ለማካሄድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መወያየት ይጠይቃል። ከዚህ አንጻር ነገ ሀምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማዕከል ለሁለተኛ ጊዜ የሚከፈተው ንባብ ለሕይወት የመፃህፍት አውደ ርእይ ጥሩ ምሳሌ ነው። ኤግዚቢሽኑ በርካታ መሟላት ያለባቸውን ጉዳዮች ቀደም ሲል ለረጅም ጊዜ ሲዘጋጅባቸው ስለነበር ብዙ ጠንካራ ጎኖች አሉት። ይህ ንባብ ለሕይወት የመጻሕፍት አውደ ርዕይ ከሁሉም አካላት ከፍተኛ ድጋፍ ሊደረግለት የሚገባ ነው። ምክንያቱም እውቀት ላይ ስለሚሰራ ነው። ቀሪውን ከሀምሌ 14 እስከ 18 በኤግዚቢሽን ማዕከል ተገናኝተን እናወጋለን።¾

በድንበሩ ስዩም

 

የ2007 እና የ2008 ዓ.ም የንባብ አምባሳደሮች ተብለን 12 ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊያት ከተመረጥን እነሆ አንድ ዓመት ሞላን። ከፊታችን ሐምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በሚከፈተው ሁለተኛው የንባብ ለሕይወት የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ ላይ ይሄ የአምባሳደርነት ማዕረጋችን ለሌሎችም ኢትዮጵያዊያን ይሰጣል። ይህ ማለት የኛ ይነጠቃል ማለት አይደለም። እኛም የቀድሞው አምባሳደሮች መባላችን አይቀርም። ማዕረጋችን አይወሰድብንም። እኛ እንተገብረው የነበረውን ሥራ ሌሎች ደግሞ ይወስዱታል። እንደ ዱላ ቅብብል እየተቀባበልን የንባብን ጉዳይ በሀገራችን እናሙቀው፣ እንነጋገርበት፣ እናንብብ፣ እንንቃ፣ እንወቅ፣ አንደንዝዝ… እያልን ሕዝባችንን የማዘመን ተግባር እናከናውን ነው ነገሩ። አዘጋጆቹ ጥሩ ተዘጋጅተዋል፤ መልካሙን ሁሉ አድርገዋል።

መጽሐፍት ዓለም ሁሉ የቀየሩ የስልጣኔ ዋና ቁልፎች ናቸው። ዓለም እዚህ የደረሰችው መፃሕፍት ታትመው ነው። የሰው ልጅ የዕውቀት ብልፅግና፣ ልዕልና፣ ሃያልነት፣ ግርማ ሞገሱ ሁሉ ከመፃሕፍት ጋር የተቆራኘ ነው። መፃሕፍት የሌለውና የማያነብ ሰው ባዶ ቤት ውስጥ፣ ምንም ነገር በሌለበት ብቻውን እንደሚኖር ፍጡር ይቆጠራል። የሚያናግረው ሰው እንደሌለው፣ የሚያየው፣ የሚያልመው ሃሳብ እንደሌለው ፍጡር ይቆጠራል። ማንበብ የሰው ልጅ መሆንን ይጠይቃል። ሰው ፣ ሰው ለመሆን ማንበብ አለበት። ካለበለዚያ ብዙ ነገሮችን ከሌሎች እንሰሳት ጋር ይጋራል። የሰው ባህሪያትን ያጣል።

የዓለም የሥልጣኔ አውራ ከነበሩት አገራት መካከል አንዷ የነበረችው ሐገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ የሥልጣኔ ውራ ሆናለች። የዚህ ምክንያቱ ሌላ አይደለም። የዕውቀት ማነስ፣ ያለማንበብ ችግር የፈጠረብን አበሳ ነው። ሌላው ዓለም የበለጠን በማንበቡ ነው። ንባብ የሕይወት መሠረት ነው። በጋዜጠኞች በቢኒያም ከበደ እና በአንተነህ ከበደ የሚመራው የዘንድሮው “ንባብ የሕይወት” የተሰኘው ታላቅ የመፃሐፍት አውደ-ርዕይም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ያለባትን የማንበብ ችግር ለመቅረፍ የተደረገ ሙከራ ነው። እሰየው ደግ አደረጋችሁ፤ ወደፊትም በርቱ፣ ጠንክሩ ልንላቸው ይገባል። ዕውቀት ላይ የሚሰራን ማንንም ሰው ትውልድ ያመሰግነዋል።

የመፃሕፍት አውደ ርዕይ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ ይታይባቸዋል። ደራሲ ዳንኤል ወርቁ “ኢትዮጵያ ታንብብ”፣ “አዲስ አበባ ታንብብ” እያለ በተደጋጋሚ ያደረገው ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ውጤት እየታየበት ይመስላል። ነገር ግን በአንዳንድ የመፃሐፍት አውደ-ርዕይ ላይ ደግሞ የራሴ የሆኑ ቅሬታዎች አሉኝ።

መፃሕፍት ክቡር ነገሮች ናቸው። ውስጣቸው ዕውቀት አለ፣ ሰው አለ፣ ታሪክ አለ፣ ፈላስፋ አለ፣ ሊቅ አለ፣ ፈጣሪ አለ፣ ኧረ ምን የሌላ ነገር አለ? ስለዚህ የክብር ቦታ ያስፈልጋቸዋል። በአንዳንድ አውደ ርዕዮች ላይ እጅግ የቆሸሸ ስፍራ ላይ መፃሕፍት ተደርድረው “አውደ-ርዕይ” ሲባል ቅር ይለኛል። መፃሕፍት እንደ ስደተኛ በድንኳን ውስጥ መቀመጥ የለባቸውም። የክብር ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል።

ለምሳሌ የስዕል አውደ-ርዕይ ሲኖር ታላላቅ ሆቴሎችና ጋለሪዎች ክፍት ይሆናሉ። ለስዕል ጥበብ የተከፈቱ ሆቴሎችን፣ ጋለሪዎችን፣ አዳራሾችን ለመፃሕፍትም ማስከፈት ይገባል። የመፃሕፍት አውደ-ርዕዮች ሕፃናት ከወላጆቻቸው ጋር መጥተው የሚቦርቁባቸው ቦታዎች መሆን አለባቸው። ሚሊኒየም አዳራሽ፣ ሸራተን ሆቴል፣ ሂልተን ሆቴል፣ ጊዮን ሆቴል ወዘተ የመፃሕፍት አውደ-ርዕዮች እንዲካሄዱባቸው ማድረግ ይገባናል። መጠየቅ፣ በር ማንኳኳት፣ ማስከፈት የሁላችንም ተግባር መሆን አለት እላለሁ።

መፃሕፍትን ይዘው ድንኳን እያፈሰሰባቸው፣ ጐርፍ ከስራቸው እየሄደ፣ ብርድ እያንዘረዘራቸው የሚያስጐበኙ ሰዎችን ማየት የለብንም። መፃሕፍት ትልልቅ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል።

የዘንድሮው “ንባብ ለሕይወት” አውደ ርዕይ በኤግዚቢሽን ማዕከል መካሄዱ ከላይ ያነሳኋቸውን ችግሮች በሰፊው ይቀርፋል የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም መፃሐፍትን በሰፋፊ አዳራሾች ውስጥ ሰብሰብ ብለው የምናይበት ስፍራ በመሆኑ፣ ሕፃናትም ወደ ስፍራው ሲመጡ እንደልባቸው የሚቦርቁበት እና የሚያነቡበት ቦታ በመኖሩ ይህ አሰራር መለመድ ያለባት ተግባር ነው። አውደ-ርዕዩንም መሠረት አድርጐ ታሪካዊ መጽሔት ማሣተምና ማሰራጨትም የዚህ አውደ-ርዕይ ተግባር በመሆኑ ለመፃሕፍት ያለንን አመለካከት ከፍታ ይሰጠዋል።

አምና በዚህ ወቅት የንባብ ለሕይወት የመፃሕፍት አውደ-ርዕይ አዘጋጆች የተለያዩ የሐገር ውስጥ እና የውጭ አገር ጠቢባን ስለ ንባብና መፃሕፍት የተናገሯቸውን ሃሳቦች ሰብሰብ አድርገው በመጽሔታቸውና በኤግዚቢሽን ማዕከል ልዩ ልዩ ስፍራዎች ለሕዝብ ዕይታ አቅርበዋቸው ነበር። ውድ አንባቢዎቼም እነዚህን ጥቅሶች እያነበባችሁ ከራሳችሁ ጋር እንድትነጋገሩ ብተዋችሁስ?

ኢትዮጵያችን ውስጥ አለማንበብ ብዙ ነገር እየጎዳን ነው። ባለማንበባችን አለምን የምናይበት ማንጸሪያ የለንም። ራሳችንን ከሌላው ጋር አስተያይተን እኛ የቱጋ እንደምንገኝ ማወቅ አንችልም። በዚህም የተነሳ መንገዳችን ጉዟችን ወደየት እንደሆነ መለየትም አንችልም። ባለማንበባችን ርዕይ (vision) እናጣለን። ባለማንበባችን ሰው የመባላችን ምክንያት ይጠፋል።  

“ማንበብ ትልቅ ሀብትን ያጎናፅፋል። እስከዛሬ በአለማችን ላይ ስለተከሠቱ እና በሌሎች ሰዎች ስለተሰሩ ነገሮች በሙሉ ማወቅ የምንችለው ማንበብ ስንጀምር ነው።” አብርሃም ሊንከን

“በህይወቴ ማወቅ የምፈልጋቸው ነገሮች በሙሉ መፀሀፍቶች ውስጥ አሉ። የኔ ምርጥ ጓደኛ ብዬ የምቀርበው ሰው ያላነበብኩትን መፀሀፍ “እንካ አንብብ” ብሎ የሚሰጠኝ ነው።” አብርሃም ሊንከን

 “እዚህ ምድር ላይ ግዜ የማይሽረው ደስታን የሚሰጠን ብቸኛው ነገር መፀሀፍ የማንበብ ልምድ ነው። ሁሉም ደስታዎቻችን በወረት ከእኛ ሲለዩን መፀሀፍ የማንበብ ልምዳችን ግን ዘወትር ደስተኞች ያደርገናል።” አንቶኒ ትሮሎፔ

“ዘወትር ባነበብኩኝ ቁጥር ውስጤ የነበረውና ያለው ትልቁ የመቻል አቅም ይቀሰቀሳል።” ማልኮም ኤክሥ

“የኔን የግል ህይወት ብቻ ሳይሆን በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችን ህይወት መለወጥ የቻሉ ሀሳቦችን መተግበር የቻልኩት መፀሀፍ በማንበቤ ነው።” ቤል ሑክሥ

“መፀሀፍን የሚያነብ ሰው በህይወት ውጣ ውረዱ አያማርርም። ሠዎች ለምን ጎዱኝ፣ ለምንስ አያስቡልኝም ብሎም ሌሎችን አይወቅስም። ከሌሎች ጋርም አይቀያየምም ምክንያቱም መፀሀፍ የሚያነብ ሰው ለራሱ ስኬትና ደስተኛነት ራሱ ብቁ ነውና ከሌሎች ምንም ስለማይጠብቅ።” ባሮው

“ዛሬ ላይ ያለህ ማንነት የዛሬ አምስት አመት ከሚኖርህ ማንነት ጋር ፍፁም ለውጥ ሳይኖረው ተመሳሳይ ነው። ግን በነዚህ አመታቶች ውስጥ መፀሀፎችን ካነበብክ አዎ! ከአሁኑ ይልቅ የዛሬ አምስት አመት የተሻለ ማንነት ይኖርሃል።” ቻርሊ ጃንሥ

“ለአንድ ሠው መፀሀፍ ስትሸጥ የሸጥከው ብዙ ወረቀቶችን፣ የተፃፈበትን ቀለምና ጥራዙን አይደለም። ለርሱ የሸጥክለት ዋናው ነገር ሙሉ የሆነ አዲስ ህይወትን ነው።” ክርስቶፈር ሞርሌይ

“በዚህ ዘመን በየትኛውም ሁኔታ በጣም ግዜ የለኝም፣ እረፍት የለኝም ብለህ የምታስብ ቢሆን እንኳን ለማንበብ የግድ ግዜ መስጠት አለብህ። ይህን አላደረክም ማለት ግን በገዛ ፍላጎትህ ራስህን አላዋቂ እያደረከው ነው ማለት ነው።” ኮንፊሽየሥ

“ድሮ ልጅ ሣለሁ ወደ ትምህርት ቤት ስሔድ ዘወትር አፍንጫዬን በመፀሀፍ ደብቄ ነበር። ይኸው ዛሬ ላይ ታዲያ እዚህ ለመድረሴ ዋና ምክንያት ሆኖኛል።” የሙዚቃ አቀንቃኙ ሱሊዮ

“መፀሀፍትን በሚገባ ማንበብ ማለት በድሮ ዘመን ይኖር ከነበረ በጣም አስተዋይ ሰው ጋር መወያየት ማለት ነው።” ሬኔ ዴካርቴሥ

“አዎ! የሚታኘክ ማስቲካ ለማምረት ከምናወጣው ወጪ በላይ ለመፀሀፍቶች ብዙ ወጪን ባናወጣ ኖሮ ይህች ሀገራችን እንዲህ የሠለጠነችና የዘመነች አትሆንም ነበር።” አልበርት ሀባርድ (አሜሪካዊ)

“ከየትኛውም ነገር በላይ ትልቁንና ከፍተኛውን ደስታ የማገኘው ሳነብ ነው።” የፋሽን ዲዛይነሯ ቢልብላሥ

“ማንበብ ከቻልክና አንዴ ማንበብ ከጀመርክ በቃ አንተ ነፃነት ያለህ ሠው ነህ።” ፍሪድሪክ ዳግላሥ

“ለመኖር ከፈለክ መፀሀፍ አንብብ።” ጉስታሽ ፍላውበርት

“መፀሀፍን ከማቃጠል የባሰ በርካታ ወንጀሎች አሉ። ከነዚህ መሃል መፀሀፍትን አለማንበብ አንዱ ትልቁ ወንጀል ነው።” ጆሴፍ ብሮድስኪ

“አላዋቂነትንና ችኩልነትን የምንዋጋበት ብቸኛው ወሳኝ መሣሪያ ማንበብ ነው።” ሌኖርድ ቤይንሥ ጆንሰን

“ዛሬ ያነበበ ነገ መሪ ይሆናል።” ማርጋሪት ፉለር

“መፀሀፍን የማያነብ ሠው ማንበብን ከነጭርሱ ከማይችል ሠው በምንም አይሻልም።” ማርክትዌይን

“በርካቶቻችን መፀሀፍ አንባቢ መሆን እንፈልጋለን። የምናነበው ግን ጥቂቶች ብቻ ነን።” ማርክ ትዌይን

“እኔ የተወለድኩት ማንበብ ከሚገቡኝ ግና አንብቤ ከማልጨርሣቸው የመፀሀፍት ዝርዝሮች ጋር ነው።” ማውዲ ኬሲ

“ለአንድ ጨቅላ ልጅ መፅሐፍ እንዲያነብ ከማድረግ በላይ ልንሠጠው የምንችለው ትልቅ ሥጦታ የለም።” ሜይ ኤለን ቼሥ

“አንድ መፀሀፍ ባነበብን ቁጥር እዚህ ምድር ላይ በሆነ ቦታ ለኛ አንድ በር እየተከፈተልን ነው።” ቬራናዛሪያን

“ለኔ ህይወት ማለት ጥሩ መፀሀፍ ማለት ነው። የበለጠ ወደ ውስጡ በገባን ቁጥር የበለጠ ትርጉም እየሰጠን ይመጣል።” ሀሮልድ ሱሽነር

“እስከዛሬ በህይወቴ ካገኘኋቸው ምክሮች ትልቁ እውቀት ሀይል ነው። ማንበብ ደግሞ አማራጭ የሌለው ተግባር ነው የሚለው ነው።” ተዋናይ ዳቪድ ቤይሊ

“የህይወታችን ትልቁ ደስታ መፀሀፍ ከማንበብ የሚገኝ ነው ብዬ በድፍረት ላውጅ እችላለሁ። ወደፊት እኔ የራሴ መኖሪያ ቤት ሲኖረኝ አንድ ጥሩ ላይብረሪ በውስጡ ካላካተትኩኝ ምን እንደሚውጠኝ አላውቅም።” ደራሲ ጆን ኦውስተን

“መፀሀፎች ወረት የማያውቁ ምርጥ ወዳጆች ናቸው። እጅግ መልካም አማካሪዎችና የችግር ግዜ ደራሾችም ናቸው። እንዲሁም ከምንም በላይ ታላቅ መምህር ናቸው።” ቻርሊ ኢሊዬት

“ማንበብ ከምንገምተው በላይ ዘላቂ የሆነ ደስታን ነው የሚሰጠን።” ላውራቡሽ

“መልካም ህይወት መኖር ከፈለግን ዛሬ ነገ ሳንል ማንበብ መጀመር አለብን።” ሞርታይመር አልዴር

“አንድ ሠው ምን አይነት ማንነት እንዳለው ያነበባቸውን መፀሀፎች አይቶ መናገር ይቻላል።” ራልፍ ዋልዶ ኤመርሠን

“አንድ ባህል ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዳይተላለፍ ከተፈለገ መፀሀፎችን ማቃጠል አያስፈልግም። ይልቅ ሠዎቹ መፀሀፍ ማንበብን እንዲያቆሙ ማድረግ በቂ ነው።” ራይ ብራድበሪ

“የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለአካላችን የሚጠቅመውን ያህል ንባብም ለአእምሯችን ይጠቅማል።” ሪቻርድ ስቲላ

“ሸረሪቶች እንደተወለዱ በተፈጥሮ ድርን የመስራት ክህሎትን እንደሚያገኙ ሁሉ ህፃናትም ሲወለዱ የመናገር ጥበብና ችሎታ አብሯቸው ይወለዳል። ግና ማንበብ መቻልን እኛ ነን ልናለማምዳቸውና ልናስተምራቸው የሚገባን።” ስቴቨን ፒንከር

“መርከበኞች በአንጸባራቂ ደሴት ላይ ከሚያገኙት ሀብት በላይ ብዙ ሀብት የሚገኘው መፅሀፍቶች ውስጥ ነው።” ዋልት ዲስኒ

“አንተ ጋር ሲመጡ መፀሀፍ በእጃቸው ያልያዙ ሠዎችን በፍፁም አትመን።” ሊሞኒ ስኒኬት

“ለማንበብ ግዜ የለኝም ካልን ለማውራትና ለመፃፍ እንዴት ግዜ እናገኛለን?” ስቴቨን ኪንግ

“ህፃናት እንደሚያደርጉት ለመገረም ብለው መፀሀፍን አያንብቡ። ለመማርም ሆነ ህልመኛ ለመሆንም ፈልገው አያንብቡ። ይልቅ አዎ! ለመኖር ሲሉ ነው ማንበብ ያለብዎት።” ጉስታቮ ፍላውበርት

“እኔና ጥቂት ሰዎች ስለራሳችን መልካም ነገር የምናስበውና ጥሩ ስሜት የሚሠማን መፀሀፍ ስናነብ ነው።” ጄን ስሜይሊ

“ከመናገርህ በፊት አስብ። ከማሠብህ በፊት አንብብ።” ፍራን ሌቦውትዝ

“የልጆቻችንን ቀጣይ ህይወት ብሩህ ልናደርግላቸው የምንችልባቸው ጥቂት መንገዶች አሉ። ከነዚህ መንገዶች መሃል ሠፊውና አስተማማኙ በውስጣቸው የንባብ ፍቅርን መዝራት ነው።” ማያ አንጄሎ

“መፀሀፍ ማንበብ ነገሮችን እንድንረዳ ብቻ ሳይሆን ሌሎች እኛን በቀላሉ እንዲረዱን ይጠቅመናል።” ጆን ግሬን

“አንተ ያላነበብከውን መፀሀፍ አንብብ ብለህ ለልጅህ አትስጠው።” ጆርጅ በርናንድ ሾው

“አንተ ወይም እኛ የማናውቃቸው ነገሮች በሙሉ መፀሀፍት ውስጥ እንዳሉ እናውቃለን?” ሲድኒ ስሚዝ

“እኔ አንብቤ ባስቀመጥኳቸውና በማነባቸው መፀሀፎች ካልተከበብኩ እንቅልፍ በፍፁም አይወስደኝም።” ጆርጅ ሉዊሥ በርጌሥ

“አንዳንድ መፀሀፎች የፈለግነውን እንድናስብ ነፃ ያደርጉናል። አንዳንድ መፀሀፍት ደግሞ ከጭንቀታችን ነፃ ያደርጉናል።” ራልፍ ዋልዶ ኤመርሠን

“ምናባችንን ከተኛበት የሚቀሠቅስልን ሞተር መፀሀፍ ማንበብ ነው።” አለን ቤኔት

“በአሁኑ ሰአት እየተቃጠሉ ካሉ መፀሀፍት በላይ የሚያሳስበኝ በአሁኑ ሰዓት እያልተነበቡ ያሉ መፅሀፎች ናቸው።” ጁዲ ብሉሜ

“ልጆቼ ወደፊት ሲያድጉ ማንበብ የሚወዱና ለእናታችን ትልቅ መፀሀፍ መደርደሬ እንስራላት ብለው የሚጨነቁ ቢሆኑ ደስታዬ ወደር አይኖረውም።” አና ክዊድሰን (የኒዮርክ ታይምስ ፀሃፊ)

“መፅሀፍት ማለት መቼም ቢሆን የማይርቁን፣ የማያስቀይሙን፣ የማይከዱንና መቼም ቢሆን ተስፋችንን የማያጨልሙብን ወዳጆቻችን ናቸው።” ቻርልሥ ኤሊዮት

“ከውሻ ውጪ የሠው ልጅ ታማኝ ወዳጅ መፀሀፍት ናቸው። ከውሻ ጋር ወዳጅ ስንሆን ግን የማንበብ እድላችን በጣም ያነሠ ነው።” ጉርቾ ማርክሥ

“በመመገቢያ ጠረጴዛህ ላይ መፀሀፎች ይሙሉ። ከዛም በጣም ደስተኛ ትሆናለህ። ትራስህም መፀሀፍቶችን ይሁኑ ከዛም ፍፁም የሠላም እንቅልፍ ትተኛለህ።” ፊይዶር ዶስቶኸስኪ

“መፅሀፍ ማለት በኪሳችን ይዘነው የምንዞረው በመልካም ፍሬዎች የተሞላ እርሻ ነው።” ቻይናውያን

“መፅሀፍ ስናነብ ወደ ውስጣችን በጣም ጠልቀን በመግባት ስለራሳችን የበለጠ ብዙ ነገሮችን ማወቅ እንጀምራለን።” ዊልያም ሀዝሊት

“ትንሽዋ የመፅሀፍ መደርደሪያ እስከዛሬ በአለማችን ላይ ከቀረቡ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በላይ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሃሣቦችን ይዛለች።” አንድሪው ሮስ

“ለአንድ ሰአት ብቻ ካነበብክ ወይም የማንበብ ልምድ ካለህ መጨነቅህ አይቀርም። ከሁለት ሰአታት በላይ የማንበብ ልምድ ካለህ ግን በምድር ላይ እንዳንተ ደስተኛ ሰው አይኖርም።” ቻርለስ ዴ ሴኮንዳት

“ከአጠገብህ ፋኖስ ለኩሰህ ወይም ሻማ አብርተህ ቁጭ ብለህ መፀሀፍ ማንበብን የመሰለ ምን ነገር አለ? አስበው በዚያ በምታነብበት ሰዓት ሌላው ቀርቶ እዚህ ምድር ላይ አብረውህ ያልነበሩትን የቀድሞ ትውልድ ሰዎችና አብረውህ የማይኖሩትን የመጪው ትውልድ ሰዎችን ማውራት ትችላለህ። ይህ ደግሞ ከምንም በላይ ትልቅ ዋጋና ትርጉም ያለው አስደሳች እሴት ነው።” ኬንኮ ዮሺዳ

“ሠዎች ህይወትን አንድ የሆነ ነገር ነው ብለው ይገልፃሉ። ለእኔ ግን ህይወት ማለት ማንበብ ማለት ነው።” ሎጋን ስሚዝ

“ማንበባቸውን ተከትሎ በየዘመናቸው ታላቅ ስራን የሰሩ ጀግኖች ቁጥራቸው ስንት ይሆን?” ሔነሪ ዳቪድ

“መፅሀፍትን ስናነብ አእምሯችን ራሱን የቻለ አንድ አስደሳች ኮንሰርት ተዘጋጀለት ማለት ነው። ታዲያ አእምሯችን ደስተኛ በሆነበት ሰዓት ደግሞ የሚያስባቸው ሃሣቦች ምን ያህል ጠቃሚና የጠለቁ እንደሆኑ ሁላችንም እናውቃለን።” ስቴፋኒ ማላርሜ

“መፅሀፍ የሚያነቡ ሠዎች ብቸኝነት አያጠቃቸውም።” አጋታ ክርስቲ

“መፅሀፍ ማንበብ ነፍስን ያክማል።” በቴክሳስ ላይብረሪ መግቢያ ላይ የተፃፈ

“መፅሀፍ የሌለበት መምሪያ ቤት ማለት መስኮት የሌለበት ቤት ማለት ነው።” ሎነሬች ማን

“ሠው መንፈሱን መመገብ የሚችለው መፀሀፍትን በማንበብ ብቻ ነው።” ኤድዊን ማርክሃም

“የተራበ ከብት ሳር ሲግጥ የሚሰማውን ደስታ ይህል ነው የሠው ልጅም መፅሀፍትን ሲያነብ ከፍተኛ ደስታን የሚያገኘው።” ሎርድ ቸስተርፌልድ

“አንድ ሠው ለልጁም ሆነ ለመላው ማህበረሰብ ከሚሰጠው ስጦታዎች ሁሉ ትልቁ አንብቦ ሰዎችን እንዲያነቡ ማስቻሉ ነው።” ካርል ካጋን

“ልጆቻችንን ዝም ብለን አይደለም አንብቡ ብለን እንዲያነቡ ማድረግ ያለብን። ይልቁንም በማንበባቸው በጣም ደስተኞች እንዲሆኑና ደጋግሞ የማንበብ ፍቅር እንዲያድርባቸው የሚያደርጉ ነገሮችንም አብረን ማድረግ ይጠበቅብናል።” ካትሪና ፒተርሠን

“ከየትኛውም መዝናኛ በላይ እንደማንበብ ዋጋው ርካሽ ሆኖ በቀላሉ የሚያዝናና ነገር የለም። ደግሞም በማንበብ እንደሚገኘው ዘለቄታዊ ደስታ ሌሎች መዝናኛዎች ዘላቂ ደስታን አይሠጡም።” ሌዲ ሞንታኑ

“እኔ ዘወትር የማስበው በቀጣይ ስለማነበው መፀሀፍ ብቻ ነው።” ሮኦልድ ዳህል

“መፅሀፍትን ማንበብ መታደል ነው። ምክንያቱም ባነበብን ቁጥር አለማችንን በሚገባ እናውቃታለንና።” ኒል ጌይንማን

የሀገር ውስጥ ሰዎች አባባል ስለንባብ

“ማንበብ የአአምሮ ምግብ ነው፤ ዋናው የአእምሮ ምግብ!”  ደራሲ ስዩም ገ/ህይወት

“ማንበብ ህይወትን የምንቀይርበት ትልቅ መሳሪያ ነው። ያለ ንባብ ህይወትን በአግባቡ መምራት አይቻልም።” አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው

“ማንበብ የእውቀት ብርሃን ነው። ስለዚህ ባነበብን ቁጥር ውስጣችንም ሆነ በዙሪያችን ያለው ውጫዊ ነገር በሙሉ በብርሃን የተሞላ ይሆናል።” ሰአሊ አንዷለም ሞገስ

“ሰው ምግብ ሳይበላ እንደማይውለው እኔም ሳላነብ አልውልም። ምክንያቱም ማንበቤ እኔን ከምንም ነገር በላይ ተጠቃሚ አድርጎኛል።” ሀይለልዑል ካሳ (የባንክ ባለሙያ)

“ንባብ ያልታከለበት ግንዛቤ ግልብ ያደርጋል።” ደራሲ በአሉ ግርማ

“መፅሀፍትን ማንበብ ታሪክህን በሚገባ እንድታውቅ ያደርግሀል። ታሪክህን ስታውቅ ደግሞ ራስህን ታውቃለህ።” አምባሳደር ዘውዴ ረታ

“በዚህች ጥንታዊ ሀገር መፅሀፍትን መፃፍ ብቻ ሳይሆን ማንበብ፣ ማስነበብ፣ ማስፃፍ፣ ሲነበቡ መስማት ጭምር የተከበረ ነገር ነበር።” ደራሲ/ዲያቆን/ ዳንኤል ክብረት

“ማንበብ በሁሉም ነገር ምልዑ ሆነን እንድንንቀሳቀስና ከግዜው ጋር አብረን እንድንራመድ ያስችለናል።” ፍቅር ተገኑ (የፀጉር ውበት ባለሙያ)

“ማንበብ እኮ ሁሉን ነገሮች ያንተ እንዲሆኑ ያደርጋል። ስታነብ ትዝናናለህ። ማንበብህን ተከትሎ ደግሞ ስለሁሉም ነገር ማወቅና መረዳት ትጀምራለህ።” ድምፃዊ ፀሃዬ ዮሀንስ

“ማንበብ ያልኖርነውን ትላንት ዛሬ ላይ መኖር እንድንችል ያደርጋል። ከዛ ካልኖርንበት ዘመን እንኳን ጓደኞች እንዲኖሩን፤ የነርሱንም ያህል ዘመኑን የኖርነው ያህል እንዲሰማን ያስችላል።” ደራሲና ጋዜጠኛ ዳዊት አለሙ

“መፅሀፍ ያጣ አእምሮ፤ ውሃ ያጣ ተክል ማለት ነው። ሰው ራሱን አውቆና ችሎ እንዲኖር መፀሀፍ ማንበብ በእጅጉ ይጠቅማል።” ንጉሴ ታደሰ (መምህር)

“ማንበብ ከባይተዋርነት ያድናል። ባነበብን ቁጥር በአለም ላይ ስላሉ ነገሮች ስንሰማም ሆነ ስናይ አዲስ አይሆንብንም። ወዳጆችን ለማፍራትም አንቸገርም። ማንበብ የሙሉነት መስፈርት ነውና።” ገጣሚና ጋዜጠኛ ፍርድያውቃል ንጉሴ

“ማንበብ አእምሮን አያስርብም። የሚያነብ ሰው ዘወትር ንቁና በአስተሳሰቡ የበለፀገ ነው።” ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ)

“እውቀቴን ሁሉ ያገኘሁት በማንበብ ነው። በአጭሩ ማንበብ አዋቂ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ሰው ያደርጋል።” ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ

“ማንበብ ፍፁም ደስተኛ ያደርጋል። እስከዛሬ ባላነብ ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር? እያልኩ ዘወትር አስባለሁ።” ህዝቅያስ ተፈራ (የህግ ባለሙያ)

“ማንበብ በጣም ያዝናናል። በየትኛውም ግዜ የሚወጡ መፅሀፍትን ማንበብ የሃሳብ ሀብታም ያደርጋል።” ተዋናይ ዋስይሁን በላይ

“እኔ ማታ ማታ አነባለሁ። ሁሌ አንብቤ ሳድር በጣም ደስተኛ ከመሆኔም በላይ የደንበኞቼን ባህርይ እንድረዳ ረድቶኛል።” ካሳሁን ፈየራ (የታክሲ ረዳት)

“ማንበብ በየትኛውም ነገር ላይ ተፈላጊውን ተፅዕኖ መፍጠር እንድትችል ያደርግሃል። ከሰዎች ጋርም በቀላሉ እንድትግባባ መንገዱን ይጠርግልሃል።” እድሉ ደረጀ (የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች)¾

 

በርካታ መፅሐፍትንና ወጎችን በመፃፍ የሚታወቀው ዲ/ን ዳንኤል ክብረት አዲስና “እጨጌ ዕንባቆም” ከየመን እስከ ደብረሊባኖስ” የተሰኘ ርዕስ የተሰጠውን ትርጉምና ሐተታ አዘል መጽሐፍ የፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 9 ቀን 2008 ዓ.ም ከቀኑ 8፡30 ሰዓት ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ሊያስመርቅ ነው። ይህ መጽሐፍ የ16ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያን ታሪክና አስተዳደር ጨምሮ ብዙ ምስቅልቅል ጦርነቶችና ከፍተኛ የነበረውን የህዝቦች እንቅስቃሴ ይዳስሳል ተብሎለታል። በአግዮስ አሳታሚና አከፋፋይ ለአንባቢያን የቀረበው ይህ መፅሐፍ ሲመረቅ በዕለቱ ስለመፅሐፉ የታሪክ ምሁራንና ሊቃውንት ገለፃ ያደርጋሉ፤ ውይይትም ይካሄድበታል ሲሉ አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።

                                    

በጥበቡ በለጠ

 

ኢትዮጵያ ውስጥ አያሌ ሐይማኖቶች ቢኖሩም በዋናነት ግን ክርስትና እና እስልምና ይጠቀሳሉ። ሁለቱም ሃይማኖቶች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ተከታዮች አሏቸው። ሁለቱም ሃይማኖቶች መሠረታቸው ከውጭ ሀገር ቢሆንም ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ግን የራሳቸውን ማንነት እና መገለጫ ይዘው ነው።

የራሳቸው መገለጫን ይዘው ነው የገቡት ሲባል ኢትዮጵያዊ ሃይማኖቶች ናቸው ለማለት ፈልጌ ነው። ሁለቱም ሃይማኖቶች በጦርነት ወይም በግዴታ (በተፅዕኖ) ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የተስፋፉ አይደሉም። እንደውም ኢትዮጵያዊያኖች ፈቅደውና ደስ ብሏቸው ወደ ሀገራቸው ይዘዋቸው ገብተዋል በማለት የተለያዩ ደራሲያን ፅፈዋል።

ለምሳሌ የክርስትናውን ሃይማኖት ታሪክ ስናነብ መነሻችን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሐዋርያት ስራ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ ኢትዮጵያዊ አለ። ይህም ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ነው። ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ወደ እየሩሳሌም ሔዶ ተጠምቆ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተመልሶ የክርስትናን ሃይማኖት አስፋፍቷል። ጃንደረባው በወቅቱ የኢትዮጵያን ንግሥት የገንዘቧ አዛዥ ነው ይባላል። ይህ ማለት በአሁን አጠራር የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ሚኒስትር እንደማለት ነው። ስለዚህ ካለማንም ተፅዕኖ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሃይማኖቱን ወደ ሀገሩ ይዞ ገብቶ አስፋፍቷል ማለት ይቻላል።

ከዚህ በተጨማሪ አንድ ኢትዮጵያዊ ንጉስንም ማንሳት ይቻላል። አፄ ባዜን ይባላል። ይህ ንጉስ ከአክሱም ዘመን ነገስታት አንዱ ነበር። እየሱስ ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ባዜን ኢትዮጵያ ውስጥ ገናና መሪ ነበር። ታዲያ የእየሱስን መወለድ ሲሰማ በጣም ደስ ብሎት ሠራዊቱን አሰልፎ ወደ እየሩሳሌም እንደሄደ ታሪኩ ያወሳል። እዚያም እንደደረሰ የዓለም ጌታ ተወልዷል ደስ ብሎኛል ብሎ የወርቅ ስጦታዎችን አበርክቶ ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተመልሶ ለስምንት ዓመታት ነግሷል። በዚህም ጊዜ ክርስትናን ለሀገሩ ህዝብ አስተዋውቋል፣ አስተምሯል የሚሉ ፀሐፊዎች አሉ።

በአጠቃላይ ሲታይ ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ የመጣው እንደ ሌሎቹ ሀገሮች በጦርነት እና በቅኝ አገዛዝ ተፅዕኖ አይደለም። ኢትዮጵያዊያኖች ራሳቸው ወደውና ፈቅደው ተቀብለው ከዚያም በራሳቸው ባህልና አስተሳሰብ አስፋፍተውታል።

በእስልምናውም ሃይማኖት ብንመጣ ከዚህ የተለየ ነገር አናገኝም። እንደውም የእስልምናው ደግሞ ብዙ አስገራሚ ነገሮች አሉት። ሃይማኖቱ በብዙ መልኩ የኢትዮጵያዊያኖች ሆኖ እናገኘዋለን። ታሪኩ እንዲህ ነው።

በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ታላቁ ነብይ፣ ነብዩ መሐመድ ይጠቀሳሉ። እርሳቸውም በተወለዱ ጊዜ ገና በህፃንነታቸው እናታቸው እንዳረፉባቸው ይገለፃል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሞግዚቶች ይቀጠሩላቸዋል። ከተቀጠሩት ሞግዚቶች መካከል ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ እሙአሚን አል ሐበሻ ይጠቀሳሉ። እሙአሚን አልሐበሻ በነብዩ መሐመድ ህይወት ውስጥ ትልቅ ታሪክ አላቸው። እሙአሚን ነብዩ መሐመድን እንደ እናት ሆነው ጡት እያጠቡ እንዳሳደጓቸው ታሪክ ያወሳል። በዚህም ምክንያት ነብዩ መሐመድ ስለ ኢትዮጵያ ማንነት እና ታሪክ እንደራሳቸው ሀገር አውቀው ነው ያደጉት እየተባለ በልዩ ልዩ መፃህፍት ውስጥ ተጠቅሷል።

አንዳንድ መፃሕፍት እንደሚያወሱት ከሆነ ነብዩ መሐመድ በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእስልምናን ሃይማኖት ለማስፋፋት በተነሱ ጊዜ አብረዋቸው የተሰለፉት ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑም ይገልፃሉ። እንደ እናት ሆነው ያሳደጓቸውን እሙአሚን አል ሀበሻን ተከትለው የሄዱ ኢትዮጵያዊያን ስለነበሩ በነብዩ መሐመድ እንቅስቃሴ ወቅት እንደ ጠባቂ እና አማኝ ሆነው እስልምና ሃይማኖት ኢትዮጵያዊያን አስፋፍተውታል ተብሎ ተፅፏል።

በዚህ ምክንያት ነው ነብዩ መሐመድ ቤተሰቦቻቸው ለአደጋ ሲጋለጡባቸው “ወደ ኢትዮጵያ ሒዱ። እዚያ በሰላም ትኖራላችሁ። መልካም ንጉስ አለ” ብለው ቤተሰቦቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ የላኩት። ነብዩ መሐመድ እንዲህ ያሉበት ምክንያት ቀደም ሲል በኢትዮጵያዊቷ እሙአሚን አልሐበሻ አማካይነት በማደጋቸው ኢትዮጵያን ጠንቅቀው ያውቋታል ማለት ነው።

ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ ከተባሉት የነብዩ መሐመድ ቤተሰቦች መካከል ሴት ልጃቸው ሩቅያ፣ ባለቤቷ ዑስማን ኢብን አፉን፣ የአጐታቸው ልጅ ጃፋር አቡጠሊን፣ የአክስታቸው ልጅ ዘበይር አቡኑልአዋምና ነብዩን እንደ እናት ጡት አጥብተው ያሳደጓቸው እሙአሚን አል ሐበሻ ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች አክሱም አካባቢ ነጃሺ ተብሎ በሚታወቀው ጥንታዊ መስጊድ ውስጥ አርፈው በሰላም ኖረዋል።

ከሁሉም በላይ የሚበልጠው ደግሞ የቢላል ታሪክ ነው። ቢላል ቤተሰቦቹ ከኢትዮጵያ የሄዱ ናቸው። ኢትዮጵያዊ ነው ማለት ነው። አንድ ቀን ነብዩ መሐመድ ቢላል በመረዋ ድምፁ ሲዘይር ይሰሙታል። እናም አስጠርተውት ከእርሳቸው ጋር ይሆናል። በኋላም በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝብን ለፀሎት የጠራው ቢላል ነው። ትልቅ ጉብታ ላይ ወጥቶ “አላህ ዋክበር” በማለት የእስልምናን ነፃነት ያወጀ፣ ሙስሊሞችን በሙሉ በፀሎት የሰበሰበው ኢትዮጵያዊው ቢላል ነው።

እነዚህን ታሪኰች ስናይ ኢትዮጵያዊያን ምን ያህል ከነብዩ መሐመድ ጋር የነበራቸውን የጠበቀ ግንኙነት እና የእስልምናን ሃይማኖት ለማስፋፋት ያደረጉትን ተጋድሎ ያሳያል። እንደሚባለው ከሆነ ቢላል እስልምናን በመቀበል በዓለም ላይ ሦስተኛው ወይም አራተኛው ሰው ነው እየተባለም ይነገራል።

በአጠቃላይ ሲታይ የእስልምናን ሃይማኖት በማስፋፋትም ሆነ በመቀበል የኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ እጅግ በጣም ትልቅ ነው። ነገር ግን ይህ ጉዳይ ብዙ እውቅና ያልተሰጠው እና ጥቅም ላይ ያልዋለ ነው። ለምሳሌ ከእነዚሁ ታሪኮች ተያይዞ ትግራይ ውስጥ ያለው አልነጃሺ መስጊድ እስልምና ሃይማኖት ገና በዓለም ላይ ሲቆረቆር አብሮ የሚጠቀስ ነው። ስለዚህ ቦታው እንደ መካ መዲና ባይሆንም፤ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ግን ቅዱስ ስፍራ ተብሎ የሚጠቀስ ነው። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የነብዩ ልጆችና ቤተሰቦች ያረፉበት ከመሆኑም በላይ እስልምና እንዲኖር እንዲበለፅግ፣ ክፉ እንዳይነካው መሸሸጊያና ማቆያ ሆኖ ያገለገለ በመሆኑ ነው።

የነብዩ መሐመድ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ብዙ የሚባልበትም ነው። ለምሳሌ ነብዩ በተለያየ ጊዜ ለኢትዮጵያው ንጉስ ደብዳቤዎችን መላካቸው ይነገራል። ከዚህ በተጨማሪም አያሌ ስጦታዎችን እና እጅ መንሻዎችንም ለግሰዋል። ዶ/ር ሀሰን ሰኢድ ባቀረቡት አንድ ጥናት ላይ እነዚህን የተላኩትን ስጦታዎች ይዘረዝሯቸዋል። እነዚህም ጥቁር ሙሉ ልብስ፣ የወርቅ ቀለበት፣ የአበሻ ፈርጥ ያለበት ሦስት አንካሴዎች፣ ሽቶ፣ የአበሻ በቅሎዎች እና ሌሎችም ይገኛሉ። እነዚህን ቅርሶች በደንብ መመርመርና ማጥናት ይጠበቅብናል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የእስልምና ሃይማኖት መንፈሳዊም ሆኑ ቁሳዊ ቅርሶች ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘታቸው ሀገሪቱም ሆነች ምዕመኑ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሳያገኙ ዘመናት እየከነፉ ነው።

ለምሳሌ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የተመሠረቱ የእስልምና ተቋማት በራሳቸው ታሪካዊ ናቸው። ከብሔረሰቦቻችን መካከል የአርጐባውን፣ የሐረሪውን፣ የቤኒሻንጉሉን፣ የአፋሩን፣ የሱማሌውን እና የኦሮሞውን እስልምና እና እሱን ተከትሎ ያለውን ባህላዊ አተገባበር ማጥናቱና እንደ ቅርስ ማስፋፋቱ ትልቅ ፋይዳ አለው።

ወደ ሐረርና አካባቢዋ ስንሄድ የሐረሪዎችን እና የሐረር ኦሮሞዎችን የጋራ የሆነ እስላማዊ ቅርስ እናገኛለን። የአያሌ መስጊዶች ደብር የሆነችው ሐረር እስልምናን ከተቀበለች ከአንድ ሺ ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ሼህ አባድር እና ተከታዮቻቸው የሐረርን ምድር ከረገጡባት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ባለው ጊዜ አያሌ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች ተፈጥረዋል። ለምሳሌ ‘አሹራ’ ተብሎ የሚታወቀው እስላማዊ በዓል በሐረር ውስጥ በተለየ መልኩ ይከበራል። ይህም ጅቦችን ገንፎ በማብላትና ከጅቦች ጋር ሠላማዊ ኑሮ ከመመስረት ጋር የተገናኘ ልዩ የአከባበር ስርዓት አለው። ይሄ ኢትዮጵያዊ የሆነ የሙስሊሞች ባህላዊ ቅርስ ነው።

ወደ ወሎ ስንጓዝ ደግሞ መንዙማው ልብን ውክክ እያደረገ በሚንቆረቆረው የወለዬዎች ድምፅና ምርቃት ታጅቦ ይቀርባል። በሙዚቃው ዓለም ይሄ ሌላኛው መንፈሣዊ ስልት ነው። የወለዬዎች የሆነው ይህ ሙዚቃዊ ስልት ብዙ ሊባልለት የሚችል ነው። ዓለም አቀፋዊቷ ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው /ጂጂ/ ይህንን የመንዙማ የሙዚቃ ስልት ወስዳ በአሁኑ ጊዜ ልዩ ልዩ ዘፈኖቿን ሠርታበታለች።

ከመንዙማው ባልተናነሰ የድሬ ሼህ ሁሴን ታሪክም አንዱ አካል ነው። ወደ ድሬ ሼህ ሁሴን ስንጓዝ ግጥምና ዜማ አውራጆች ከልዩ ልዩ ቦታዎች እየመጡ ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት እና ዓመታዊ ክብረ በዓል የሚያከብሩበት ስርዓት በእስልምና ሃይማኖታችን ውስጥ የሚገኝ ቅርስ ነው።

ወደ ባሌ ስንጓዝም የሶፍ ዑመር ዋሻ አካባቢ የሚደረጉ ባህላዊ ድርጊቶች እና ክብረበዓሎች ሌላኛው ገፅታችን ናቸው። በዚህ ቦታ ላይም ሶፍ ዑመር የተባሉት የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ እና ቅዱስ የሚባሉ ሊቅ በስፍራው ይኖሩ ነበር። የእኚህን ሰው ገድል ለማድነቅ እና ፈጣሪያቸውን ለማመስገን በየዓመቱ አያሌ የሙስሊም ሃይማኖት ተከታዮች ወደ ስፍራው በማምራት ይገናኛሉ። በጋራ ይፀልያሉ።

ከነዚህ ሌላም በርካታ እስላማዊ ቅርሶች በሐገራችን ውስጥ አሉ። ሁሉንም መጠቃቀስ ባንችልም እነዚህ ይበቁናል። ግን ሳይጠቀስ የማያልፈው ደግሞ በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚገኙት ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ባህላዊ አለባበሳቸውም ቅርስ ነውና መጠናት እንዳለበት ዶ/ር ሐሰን ሰኢድ ይመክራሉ።

በ2004 ዓ.ም በቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለስልጣን አማካይነት በታተመው ቅርስ በተሰኘው መጽሔት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ ክፍል የዓረብኛ ንዑስ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ መሐመድ ሰዒድ አብደላ “ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡ የኢትዮጵያ እስላማዊ የሥነ-ጽሑፍ ቅርሶች” በሚል ርዕስ አንድ ጥናት አቅርበው ነበር። በዚህም ጥናታቸው ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገቡትን የእስልምና ሃይማኖት መፃህፍት ጠቅሰዋል።

ከነዚህ መፃህፍት መካከልም ከዛሬ 700 ዓመታት በፊት የተፃፈውን፣ ሺሃቡዲን ዓብዱ አልቃድር (ዓረብ ፈቂህ) የአሕመድ ግራኝ መዋዕለ ዜና ፀሐፊው “ፋቱህ ዓል ሐበሻ” በሚል ርዕስ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፃፈው፣ ዳውድ አቡ በከር እ.ኤ.አ. በ1818 አካባቢ የፃፏቸው በርካታ እስላማዊ መፃህፍት፣ ቡሽራ መሐመድ የተባሉ ሊቅ በ1863 እ.ኤ.አ የፃፏቸውን ኢትዮጵያዊ መፃህፍቶች፣ በ1881 እ.ኤ.አ መሐመድ ጀማል አደን አልዓሊ (አባ ወልዬ) በድርሰት ስራዎቻችው አያሌ ነገሮችን መፃፋቸው ተገልጿል። ሑሴን ሐቢብ (ባሆች) እ.ኤ.አ በ1916 ዓ.ም ከሃይማኖት አባትነታቸው በላይ በርካታ መፃህፍትን አዘጋጅተዋል።

ሐጂ ጃዕፈር በዓረብኛና በአማርኛ ቋንቋ እ.ኤ.አ 1936 አካባቢ መፃፋቸው እና ሸምሰዲን መሐመድ እ.ኤ.አ 1924፣ ሰኢድ ኢብራሂም ያሲን (ጫሎች) በ1940ዎቹ የፃፏቸውና ሌሎችም ተጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ ሙስሊሙ ኅብረተሰብም ሆነ መንግስት እንዲሁም የቅርስ ወዳጆች የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በእነዚህ ከላይ በተጠቀሱት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ የማስተዋወቅና የመጠበቅ ተግባር ይጠበቅባቸዋል።

መልካም የረመዳን ጾም ፍቺ - ረመዳን ከሪም¾ 

 

ፕ/ር አፈወርቅ ገ/እየሱስ

በጥበቡ በለጠ

በአንድ ወቅት “የኢትዮጵያ ደራሲያን እና የኢጣሊያ ወረራ” በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ ማቅረቤ ይታወሳል። በዚህ መጣጥፍ ውስጥ በተለይም ይህን የግፍ ወረራ ለመመከት እና ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ደራሲዎች ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። በቅርቡም ሚያዚያ 27 ቀን 2008 ዓ.ም በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በጋዜጠኛ ሕሊና አዘዘ ተጋብዤ ከደራሲ አበረ አዳሙ ጋር ሆነን 75ኛ አመት የአርበኞች በአልን መሰረት በማድረግ፣ የእለቱ ለት የኢትዮጵያ ደራሲያን በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ስላበረከቱት አስተዋጽኦ ለማቅረብ ሞክረናል። በወቅቱ ለፋሽስት ኢጣሊያ ያደረውን አፈወርቅ ገ/እየሱስን በተመለከተ የተናገርኩትን መሰረት አድርጎ ወዳጄ የፊልም ባለሙያው ያሬድ ሹመቴ ጥያቄ ጠይቆኝ ነበር። ለእርሱም ሆነ ለሌሎች አንባቢዎቼ የፕሮፌሰር አፈወርቅን ታሪክ ባጭሩ ላብራራ ነው።

በትምህርት ደረጃው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ላይ ደርሷል። በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ “ነጋድራስ” የሚሰኘውን ማዕረግ ተቀብሏል። ይህ ሰው አፈወርቅ ገ/እየሱስ (ዘብሔረ ዘጌ) ይባላል። አፈወርቅ ገ/እየሱስ ጦቢያ የምትሰኘውን የልቦለድ መጽሐፍ በ1900 ዓ.ም ያሳተመ ደራሲ ነው። ጦቢያ በአፍሪካ ውስጥ በራስ ቋንቋ ከተፃፉ ልቦለዶች ሁሉ የመጀመሪያ ነች። በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ መሠረት የጣለው አፈወርቅ ገ/ እየሱስ ሌሎችንም መፃህፍት አሳትሟል። ሁለተኛ መጽሐፉ ደግሞ “አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ” በሚሰኝ ርዕስ አሳትሟል። ልዩ ልዩ አጫጭር ልቦለዶችን እና ታሪኰችን በመፃፍ በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ግንባር ቀደሙን ቦታ የሚወስድ ነው።

አፈወርቅ ገ/እየሱስ የተወለደው ጣና ውስጥ ከሚገኙት ደሴቶች መካከል “ዘጌ” ተብላ ከምትታወቀው ቦታ ሐምሌ 3 ቀን 1860 ዓ.ም ነው። አባቱ ገብረእየሱስ ድንቄ ሲባሉ እናቱ ደግሞ እመት ፈንታ ትሁን ይሰኛሉ። ገና በልጅነቱ ጣና ውስጥ የሚገኙትን ገዳማት የግድግዳ ላይ ስዕሎች እያየ እና በእነርሱ እየተመሰጠ ከዚያም የስዕል ፍላጐቱ እና ችሎታውም እያደገ መጥቶ የስዕል ብሩሽ ከእጁ የማይለይ ሰዓሊ ሆነ። በትምህርት አቀባበሉም እጅግ ተስፋ የተጣለበት ታዳጊ ሆነ።

አፈወርቅ ለእቴጌ ጣይቱ የቅርብ ዘመድ ነበር። እቴጌ ጣይቱም ጐንደር እያሉ በልጅነቱ አፈወርቅ ተሰጥኦ ያለው ታዳጊ መሆኑን ስለተገነዘቡ በ1875 ዓ.ም ከአጤ ምኒልክ ጋር ከተጋቡ በኋላ አፈወርቅን ወደ አዲስ አበባ አስመጡት። እዚህም አዲስ አበባ የስዕል ስራውን እየሰራ የቤተ-መንግስት ልጅ ሆኖ ቆየ። አጤ ምኒልክም አቅርበው ያጫውቱት ነበር። ልጁ አእምሮው ሰፊ ስለሆነ ወደ አውሮፓ ሄዶ ቢማር ብዙ ስልጣኔዎችን ወደ ሀገሩ ይዞ ይመጣል ብለው በማመን ሄዶ እንዲማር ተፈቀደለት።

መስከረም 24 ቀን 1880 ዓ.ም ምፅዋ ደረሰ። ከዚያም በመርከብ ተሳፍሮ ኔፕልስ ወደብ ጣሊያን አገር ደረሰ። በመጀመሪያ የተማረው የጣሊያንኛን ቋንቋ ነው። ከዚያም Istituto Internazionale di Tomino በተባለ ኰሌጅ ትምህርቱን ቀጠለ። የአውሮፓንም ስልጣኔ በኪነ-ጥበብ ውስጥ ተማረ። አፈወርቅ ወደ አውሮፓ ከመሄዱ ሦስት ዓመት በፊትም የአውሮፓ መንግስታት በርሊን ከተማ ተሰብስበው አፍሪካን ለመቀራመት ተስማምተው ነበር። ሚያዚያ 25 ቀን 1880 ዓ.ም ጣሊያኖች ከኢትዮጵያ ጋር የውጫሌን ውል ተፈራረሙ። የኢጣሊያ ጋዜጦችም ፃፉበት። ጣሊያኖች ተደሰቱ። አፈወርቅ ገ/ እየሱስ ደግሞ ውሉን ሲያነበው አንቀፅ 17 ችግር ያለበት እንደሆነ ተገነዘበ። አንቀፁ የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት አሳልፎ የሚሰጥ ነው በማለት አፈወርቅ ገ/ እየሱስ ለትምህርት በሄደበት ሮማ ውስጥ ተቃውሞ ማስነሳት ጀመረ። ይህ አንቀፅ የተጭበረበረ ነው በማለት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያውን ተቃውሞ ያስነሳው አፈወርቅ ገ/ እየሱስ ነው።

የሸዋው ንጉስ ዳግማዊ ምኒልክ ጥቅምት 25 ቀን 1882 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ሙሉ በሙሉ ነገሱ። ይህን ንግስናቸውን ለማብሰር በደጃዝማች መኰንን ወ/ሚካኤል (በኋላ ራስ) የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ አውሮፓ ሄደ። ለአፈወርቅም ጥሩ አጋጣሚ ሆነለት። የልዑካን ቡድኑን አገኛቸው። ሁሉንም ነገር አጫወታቸው። የውጫሌው ውል አንቀፅ 17 ተጭበርብሯል አላቸው። ይህን አደገኛ ደባ መቋቋም ባለመቻሉም ለምኒልክ ደብዳቤ ፃፈ። በዚህ ብቻም አላቆመም፤ ትምህርቱን ጥሎ ከልዑካን ቡድኑ ጋር አብሮ ተመልሶ ወደ ሀገሩ መጣ። ይህም የሆነው ህዳር 26 ቀን 1882 ዓ.ም መሆኑን ታዋቂው ሰዓሊና ሀያሲ እሸቱ ጥሩነህ ፅፎታል።

ከዚህ በኋላ አፈወርቅ ገ/እየሱስ በለኰሰው ኀሳብ ምኒልክና ጣይቱም በመስማማታቸው እንዲሁም በተለይ ጣይቱ እጅግ በመበሳጨታቸው የአድዋ ጦርነት ተቀሰቀሰ። አፈወርቅ ገ/እየሱስም የአድዋን ጦርነት የመጀመሪያዋን ቀስቃሽ ኀሳብ በማመንጨት ዋነኛው ተጠቃሽ ነው።

ኢትዮጵያም የአድዋን ጦርነት በአንድ ቀን ድል አድርጋ ጥቁር ለመጀመሪያ ጊዜ የነጭን መንግስት አሸናፊ ተብሎ በዓለም መዝገብ ተፃፈ። የጦርነቱ ለኳሽም አፈወርቅ ገ/እየሱስ እንደሆነ ይታወቃል። ታዲያ ይህ ታላቅ ሰብዕና የነበረው ሰው ፋሺስት ጣሊያን ከ40 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን ስትወር የጣሊያኖች ባንዳ ሆኖ ፋሽስቶች ኢትዮጵያን ለዘላለም እንዲገዙ ከጐናቸው ቆመ። የዚያን ወቅት ማለትም ከ1923 ዓ.ም እስከ 1928 ዓ.ም ድረስ አፈወርቅ በኢጣሊያ የኢትዮጵያ ቆንሲል ነበር።

በኢጣሊያ የአምስት ዓመታት ወረራ ውስጥ አፈወርቅ በፋሽስቶች ዘንድ እጅግ የተከበረ ባንዳ ሆነ። ጣሊያኖችም የመጨረሻውን ማዕረግ ሰጡት። “አፈ ቄሳር” አሉት። በፕሮፌሰርነቱ፣ በነጋድራስነቱ ለሀገሩ ኢትዮጵያ ብዙ የታገለው ይህ ሠው እንደገና ደግሞ ለኢጣሊያኖች አድሮ “አፈ ቄሳር” ተባለ።

ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ወርረው አምሰት ዓመታት በቆዩባቸው ጊዜያት ሁለት የአማርኛ ሕትመቶችን ለህዝብ ያሰራጩ ነበር። አንደኛው “የሮማ ብርሐን” የተሰኘ መጽሔት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ “የቄሳር መንግስት መልዕክተኛ” የተሰኘ ጋዜጣ በአማርኛ ቋንቋ ይዘጋጁ ነበር። ፕሮፌሰር፣ ነጋድራስ፣ አፈ ቄሳር አፈወርቅ ገ/እየሱስ ዋና አዘጋጅ ነበር። በእነዚህ ሕትመቶች ላይ ለኢጣሊያ ያደሩ ታላላቅ የኢትዮጵያ ፀሐፊያንና ደራሲያን ስራዎቻቸውን ያቀርቡ ነበር። ጣሊያን ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ የመጣ እንጂ ወራሪ አይደለም፤ አርበኞች በየጫካው እየተሯሯጣችሁ ከምትዋጉ ወደ ሠላም በመምጣት ከጣሊያን መንግስት ጋር ስሩ እያሉ ይፅፉ ነበር። ከእነዚህም ውስጥ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ እና ደራሲ ከበደ ሚካኤልም ይገኙበት ነበር።

ለዛሬ ጽሁፌ ግን ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገ/እየሱስ ከፃፋቸው እጅግ በርካታ አርቲክሎች መሀል “አርባ ዓመት አለጥቅም አለፈ” በሚል ርዕስ መጋቢት 4 ቀን 1930 ዓ.ም “የቄሳር መንግስት መልዕክተኛ” ከተሰኘው ጋዜጣ ላይ ያሰፈረውን እንድታነቡት እጋብዛችኋለሁ። የአድዋን ጦርነት የለኰሰ ይህ ታላቅ ደራሲ ከአርባ ዓመት በኋላ ደግሞ እንዴት ለጣሊያኖች እንዳደረ የሚያሳይ ጽሁፍ ነው። እንዲህ ይነበባል፤

“ከአድዋ እስከ ማይጨው ጦርነት ድረስ ልክ አርባ ዓመት ሆነ። ኢትዮጵያ በኢጣሊያ እጅ ከገባች ልክ ሃያ ሁለት ወር ሆነ። በዚያ በሃያ ሁለት ወር ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰራችውን ስራ ያደረገችውን መልካም የሚያስደንቅ ነገር ሁሉ አይቶታል። ትልቅ ተአምር ነው። ከምፅዋ እስከ ጅማ፣ እስከ ወለጋ፣ ከሐረር እስከ ጐንደር፣ ከጐንደር እስከ ቦረና፣ እስከ ሉግ፣ በየአገሩ ሁሉ የተሰራውን መንገድ በዓይናችን አየን። በዓይናችን ቀርቶ በወሬ ሰምተነው ቢሆን አናምንም ነበር። አውሪውንም አባይ እንለው ነበር።

“ከምፅዋ ጅማ ወይም ወለጋ ወይም ከፋ ወይም ሐረርና ጅጅጋ በእግር የሚጓዙት ሆኖ ቢሆን በአንድ ዓመት አይደረስም ነበር። ዛሬ ግን በኢጣሊያ ትጋት መንገድ ሁሉ ተሰርቶ ሐር የተነጠፈበት መስሎ ለስልሶ በካምዮንና በአውቶሞቢል ቢሆን ቀድሞ የአንድ ዓመት ወይም በአንድ ዓመት ተመንፈቅ ጉዞ አያልቅ የነበረው ጐዳና በሃያ አራት ሰዓት ይደረስ ጀመረ። ኢትዮጵያ በኢጣሊያ እጅ ሳትገባ ግን መንገድ መራቅ ብቻ አልነበረም። በረሃው ጥማቱ ሰውንም ከብቱንም ይጨርሰው ነበር።

“በደጋው ደግሞ ዝናብ ጭቃው ማጡ ከብቱን አጋሰሱን ውጦ ያስቀረው ነበር። እስንት አጋሰስ ጭነቱ ከማጥና ከዥቅዥቅ ተከቶ ለማውጣት ተቸግሮ ከዚያው ዓይኑ እያየ እስንቱ ሙቶ ሲቀር፣ ትንሽ ወንዝ ስንቱን ሠው እየጠለፈ ይወስድ ነበረ። የዛሬ ስምንት ዓመት አባይ በድንገት ሞልቶ ከጐጃም ወደ ሸዋ ለክህነት የሚሻገሩትን ሰባ ስምንት አሽከሮች (ወጣቶች) ታቦት ለማስባረክ የሚሄዱትን ቄሶች ጨምሮ ታቦት በጀርባቸው እንዳዘሉ ጠርጐ መውሰዱን ሁላችንም እናውቃለን። ይሄ ሁሉ ሲደረግ ያገራችን ንጉሶች ምንም ቅር ሳይላቸው ለሚመጣውም ጊዜ ሠው ለማዳን አንድ ድልድይ ለመስራት ሳያስቡ ቀሩ። የኢጣሊያ መንግስት ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቀምበትን ሁሉ ነገር በጥቂት ጊዜ አደረገ። ተንግዲህ የሚያደርገው ነገር እንዴት ብሎ ይቆጠራል።

“አዱአ ላይ ድል ከማድረግ ድል መሆን ይሻለን ነበር። ነገሩን መርምሮ ያላወቀ ሠው ኢትዮጵያ አዱአ ላይ ቀናት፤ ድል አደረገች ይል ነበረ። ብልህና መርማሪ ሠው ግን ኢትዮጵያ አዱአ ላይ ድል ሆነች እንጂ ድል አልነሳችም። ኢትዮጵያ የቀናት ማይጨው ላይ ነው። ስለምን? ኢትዮጵያ ከዛሬ አርባ ዓመት ጀምራ በኢጣሊያ እጅ ሆና ቢሆን በዚህ በጥቂት በሃያ ሁለት ወር በኢትዮጵያ ውስጥ በተደረገው ሥራ በአርባ ዓመት ለመስራት ይቻል የነበረውን በኀሳብ ገመድ እምንለካው ቢሆን ዛሬ ኢትዮጵያ እንደ ፈረንጅ አገር ታምር ትለመልም ትሰማ ትሰለጥን ነበር። ይሄ እርግጥ ነው። ዛሬ ማን ነው በኢጣሊያ መምጣትና ኢትዮጵያ በኢጣሊያ እጅ በመሆንዋ ደስ ያላላቸው? መንግስት ካቀረባቸው ከአጤ ኃይለስላሴ እና አብረው ተከትለዋቸው የሄዱትም ተከትለው በመሄዳቸውና በሞኝነታቸው መጠጠት አይቀራቸውም። ይሄ እርግጥ ነው። እንኳንስ ሌላ ምቀኝነትና ቅናት ባይኖር አጤ ኃይለስላሴም መጥተው ኢትዮጵያ በኢጣሊያ እጅ ተገባች ወዲህ የተሰራውን ሁሉ ዕፁብ ድንቅ የሚያዩ ቢሆን እስንት ደስ ባላቸው! እስንት ባደነቁ! እስንትስ ያለፈውን መንግስታቸውን በናቁ ነበር?

ሄት ነበርሽ?

“የትግሬው አጤ ዮሐንስ በህይወታቸው ሳሉ አንድ ጊዜ ደብረ ታቦር፣ አንድ ጊዜ ቦሩ ሜዳ፣ አንድ ጊዜ መቀሌ ወይም አዱዋ (አድዋ) ይከትሙ ነበር። አንድ ቀን ይላላ ወጡና አንዲት ለከተማ መስሪያ የምትሆን ቁብታ አዩና ደስ አለቻቸው። አስተዋሉ አስተዋሉና ሄት ነበርሽ? (እስከ ዛሬ ሳላስተውልሽ) አሉ ይባላል። ይህችው ቁበታ ዛሬም ሄት ነበርሽ ነው ስሟ። አሁን እንደዚሁ ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ በኢጣሊያ አገዛዝ እና በሚሰራው ነገር ደስ ስላለው ሄት ነበርሽ ኢጣሊያ እስከ ዛሬ ድረስ? ምነው ቀደም ብለሽ አትመጪም ኑሯልን እያሉ በመዘግየቷ ይጠጠታል። ደስታው ብዙ ነው። ስለምን የኢጣሊያ አገዛዝ ለድሃ ምቹ ነው፤ ትክክል ነው አላደላም። ገባር እንደ ቀድሞው ምጣድ አይሸከም። እህል አይጭን፤ ዱቄት አይፈጭ፣ አጥር አያጥር፣ ቤት አይሰራ፣ ማገር አይማግር፣ ድንኳን አይጭን - አይተክል። ይሄ ሁሉ መከራ አለበት። የኢጣሊያ አገዛዝ ሁሉ በሥርዓት፣ በትዕግስት፣ ሁሉ በደግነት። አፍ እንዳመጣ ያዙት ግረፉት የለ። ከሌባ በቀር እሰሩት የለ። ሁሉም በትክክል ሁሉም በፍርዱ ነው። በዚህ ሁሉ የተነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ ማይጨው ካሳውን አገኘ። ተካሰ።”

ሲከዱት የማይክድ፣ ሲጠሉት የማይጠላ የለም

“ሰው ሆኖ የገዛ አገሩን፣ የገዛ ወንዙን፣ እንደናት እንደባቱ አድርጐ የማይወድ የለም። ይሄ ከተፈጥሮ የመጣ ነገር ነው። ማንም ያውቀዋል። ነገር ግን ያገር ፍቅር መበርታቱ ድሃው አዛኝ ገዢ ሲያገኝ ጊዜ፣ ትክክል ፈራጅ ሲያገኝ ጊዜ፣ ታላቅና ታናሽ ወዳጅና ጠላት፣ ኃይለኛና ሰነፍ፣ ድሃና ሐብታም ሳይለይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ሳያጓድል የሚፈርድ ንጉስ ሲያገኝ ጊዜ ነው። ከእግዚአብሔር በታች ታቦት
እና የአባት ሀገር ናቸው የሚወደዱና የሚመለክባቸው። ሃይማኖትን የሚያበረታ ታቦትንና አገርን የሚያስከበር መልካም ንጉስ ነው። ታቦትን እና አገርንም የሚያስረክስ ንጉስ ነው። ታቦት ተረከሰ ደግሞ ንቁዝ የዱር እንጨት የወንዝ አለት ነው። እንደገና እስቲባረክ ድረስ ሊቀድሱበት አይበቃም።

“የተቀደሰችውን ኢትዮጵያን ያረከሷት ንጉሶችና ባለሟሎች አገረገዥዎች መኳንንቱ መሳፍንቱ ናቸው። ህዝቡን፣ ገባሩን መናቅ ብቻ አይደለም፤ ወሰንተኛ እንጂ ታገሩ ኢትዮጵያ የተወለደ አያስመስሉትም ነበር። ህዝቡን ከአገሩ ፍቅር ያፈራቀቁት እነሱ ናቸው። ከኢትዮጵያ የተፀነሱ እና የተወለዱ እነሱ ብቻ እንጂ የቀረው ህዝብ ከመጣበት አያውቅም ነበር። ወይም ከሠው አይቆጥሩትም ይንቁት ነበር።

“ስለዚህ ቤት ካልበሉበት ባዶ ድንኳን የረከሰ ቤተ-ክርስትያን አካል ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ይሄን ሁሉ ጡር ያንን ሁሉ ግፍ እየተሸከመ ሲኖር ቆይቶ በመጨረሻ አመረረና እንባውን ወደ ሰማይ እየረጨ ኸረ በቃ በለን፤ ኸረ የውነተኛው ለድሃ የሚያዝን ፍርድ የማያጓድል ንጉሥ አውርድልን አምላካችን እያለ እግዚአብሔርን ለመነ፣ ተማጠነ። እግዚአብሔርም ምንም ዝግተኛ ቢሆን ጆሮው ሰሚ፣ ልቡ ሰፊ፣ የነገሩትን የማይረሳ ነውና ኑሮ ኑሮ አሁን ገና ይሄው ታላቅ የማያዳላ ለትንሽ ለታላቅ የማይል የማያዳላ ሚዛን ንጉስ ከንጉስም ንጉስ፣ የኢጣሊያን ንጉስ ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ቄሣር አድርጐ ሰጠነ። ለዚህ ለትክክል ንጉስ ለዚህ ለኢጣሊያ ንጉስ፣ ለኢትዮጵያ ቄሳር እኛም በቅንነት በነብይነት በታላቅ መታመን ማገልገል መገዛት ይገባናል። እንዲህ እንደሆነ በጣም እንጠቀማለን። ኢትዮጵያም ለዘላለሙ ያልፍላታል፤ ለዘላለሙ የታደለች ትሆናለች።” በማለት ይህ ታላቅ የኢትዮጵያ ደራሲ ፅፏል።

አፈወርቅ ገ/እየሱስ ምንም እንኳ የኢጣሊያን ኃያልነት የሚያመለክቱ ጽሁፎችን በቄሣር መንግስት መልዕክተኛ ላይ ቢያሰፍርም፣ አንድ ለሀገራችን አዲስ ጉዳይ እግረመንገዱን አስተዋውቋል። ጋዜጣው ዘመናዊ የጋዜጣ አዘገጃጀት ቅርፅ የያዘ ነበር። ከእርሱ በፊት የነበሩት ጋዜጦች የማይከተሉትን ቅፅ፣ ቁጥር፣ ቀን፣ የተዋጣለት የቋንቋ አጠቃቀምን ወዘተ በተግባር ላይ አውሏል። የዚህ ታላቅ ደራሲ የህይወት መጨረሻው ክፍል እጅግ በአሳዛኝ ሁኔታ ተጠናቋል። የቋንቋ እና የሥነ-ጽሑፍ ምሁሩ ዶ/ር አምሣሉ አክሊሉ፣ አጭር የኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ በሚል ርዕስ በፃፉት ጥናት፣ የአፈወርቅን የመጨረሻ የህይወቱን ክፍል በሚከተለው መልኩ አስቀምጠውታል።

“አፈወርቅ ገ/እየሱስ ነፃነት እንደተመለሰ የኢጣሊያ ፕሮፖጋንዳ መሣሪያ በመሆናቸው ተይዘው በመጀመሪያ ሳይፈረድባቸው በፀሐፊ ትዕዛዝ ወልደመስቀል መኖሪያ ቤት ከታሰሩ በኋላ ፈፅመውታል የተባለው ወንጀል ምን እንደሆነ በሕግ ተረጋግጦ አስፈላጊውን ፍርድ እንዲያገኙ ለመንግስት ስላመለከቱ ጉዳዩ ለፍርድ ቀርቦ በኋላም ለዙፋን ችሎት ቀረበ። ዳኞች ከተቹበት በኋላ በሞት እንዲቀጡ ሲበይኑ ጥፋትህን ታምናለህ ተብለው ሲጠየቁ “ምንም ጥፋት የለብኝም፤ የሸዋ ፍርድና የጉንዳን መንገድ ነው። አንዱ ያለውን ተከትላችሁ ነው፣ አዎ ያላችሁ” ካሉ በኋላ ንጉሱ የሞቱን ቅጣት አሻሽለው ወደ እድሜ ልክ እስራት ተለውጦለታል ብለው ሲያስታውቁ በችሎት ተሰብስቦ የነበረው ህዝብ ሁሉ ለጥ ብሎ እጅ ሲነሳ ነጋድራስ አፈወርቅ ግን ቀጥ ብለው ቆመው ቀሩ” በማለት ዶ/ር አምሳሉ ይገልፃሉ። ጽሁፋቸውንም ሲቀጥሉ የሚከተለውን አክለዋል።

“እዚያ ከነበሩት አፈንጉስ ዘውዴ፤ ‘ምነው ነጋድራስ ምህረት ሲደረግልህ እጅ አትነሳም እንዴ?' ቢሏቸው፤ ‘አፈወርቅ ይታሰር ተባለ እንጂ ይፈታ ተባለ እንዴ? ለምንድን ነው እጅ የምነሳው? ለእኔ መሞት ይሻለኝ ነበር። ይህ ምህረት ሳይሆን ከሞት የከፋ የቁም ስቃይ እንድቀበል የተደረገ የግፍ ፍርድ ነው።' ብለው መልስ ሰጧቸው” ሲሉ ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ፅፈዋል።

ታላቁ የአፍሪካ ደራሲ አፈወርቅ ገ/እየሱስ ከተፈረደበት በኋላ ጅማ ውስጥ ልዩ ስሙ ጅሬን በተባለ ቦታ ታስሮ ብዙ ጊዜ ቆየ። በመጀመሪያ እነዚያ ብዙ ያነበበባቸው ዓይኖቹ፣ ከጐንደር እስከ አዲስ አበባ፣ ከዚያም አውሮፓ ሄዶ ስልጣኔን የተመለከተባቸው ዓይኖቹ ፈሰሱ። ታወሩ። ጤናውም ታወከ። ቤት ንብረቱ ተወረሰ። ሊያሳትማቸው ያዘጋጃቸው ልዩ ልዩ ጽሁፎቹ ከጥቅም ውጪ ተደረጉ። ቤተሰቡ የሚበላው የሚጠጣው አጣ፤ ነጣ። በመጨረሻም ያ ታላቅ ደራሲ እዚያች እስር ቤት ውስጥ ከሰውና ከአጫዋቾቹ እንደተገለለ ብቻውን ሆኖ መስከረም 14/15 ቀን 1940 ዓ.ም በ79 ዓመቱ ዓለምን ተሰናበተ። 

    

በ1980ዎቹ አጋማሽ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ የስነ-ጽሁፍ መምህሬ ዛሬ በሕይወት የሌሉት ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ብዙ ብዙ ነገር አስተምረውኛል። ኢትዮጵያን ከአፈጣጠርዋ ጀምሮ አሁን እስከ ደረሰችበት ታሪክ ደሜ ውስጥ ከከተቱ ሰዎች መካከል አንዱ እሳቸው ናቸው። አጭር የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ታሪክ ብለው ባዘጋጁት ያልታተመ ጥራዝ እስካሁን ኢትዮጵያዊነትን እማርበታለሁ።ግን ኢትዮጵያዊነት ከየት ይገኛል? መወለድ ብቻውን ኢትዮጵያዊ ቢያሰኝም፣ እንደ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ያሉ ምሁራን የሚመግቡትን መጻሕፍት ማንበብ ደግሞ የዜግነት መንፈስን ከፍ ያደርጋል። ወደ ዋናው ነጥቤ ልመለስና እኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ምሁር በአንድ ወቅት ስለ አበሻነት እና ኢትዮጵያዊነት ሲያስተምሩን ነበር። ቀደም ሲልም በ1976 ዓ.ም ባዘጋጁት  ጥናታቸው ላይ ማለትም አጭር የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ ታሪክ በተሰኘው መጽሀፋቸው  አበሻ እና ኢትዮጵያዊነት ምን እንደሆነ ገልጸዋል። ከ15 አመታት በፊት የአበሻ እና የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ሲያከራክር ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ የሚከተለውን መጣጥፍ አዘጋጁ። ክርክሩን አቀዘቀዙት። ፈጣሪ ነብሳቸወን በገነት ያኑርልኝ እያልኩ ጽሁፉን ብጋብዛችሁስ።

 

ያገራችን መጠሪያ አበሻ ወይንስ ኢትዮጵያ

በዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ

 

እነዚህ ሁለት ስያሜዎች ለብዙዎቻችን ጎልተው አይታዩንም ይላሉ። ይህም ያለ ምክንያት አይደለም። ጊዜውን በውል ሰፍሮ ቆጥሮ መናገር ባይቻልም ከጥንት ጀምሮ በተለዋዋጭነት ለአገራችን መጠሪያ ስንገለገልባቸው ቆይተናል። የውጭ አገርና ያገራችን ታሪክ ፀሐፍያን አንደኛው በተለዋዋጭነት ሲጠቀሙባቸው እናገኛለን። እንዲህም ሲያደርጉ በኢትዮጵያና በአበሻ መካከል ልዩነት እንዳለ አስበው አይደለም። ለምሳሌ ጀርመናዊው ሊቅ ኢያብ ሉዶልፍ ስለኢትዮጵያ ታሪክ የጻፈውን መጽሐፍ ርዕስ “The History of Ethiopia or the kingdom of the Abessins” ብሎ ሰይሞታል። ሌላው ጀርመናዊ ደራሲ “Edward Ruppel” በአገራችን ውስጥ ስላደረገው ጉዞ ሲጽፍ “Reise nach Abyssinie”  ወደ አበሻ አገር ጉዞ በሚል ርእስ ጽፏል። ”Hayatt” የሚባለው ፀሐፊ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሲጽፍ ‘The Abyssininan Church’ በሚል ርዕስ ጽፏል። በሌላ በኩል የሄድን እንደሆን ስለኢትዮጵያ የጻፉ የአረብ ደራስያንን ስንመለከት በማንኛውም ጊዜ ኢትዮጵያ የሚለውን ስያሜ ተጠቅመውበት አያውቁም። ለነሱ ኢትዮጵያ ማለት ሐበሻ ነበር፤ አሁንም በአብዛኛው ይኸው ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያን ወርሮ የነበረውን አሕመድ ግራኝን በጦርነቶቹ ሁሉ ተከትሎት ይዞር የነበረው አረባዊው የታሪክ ሰው ሺሓቡ ዲን ስለጦርነቱ በጻፈው “ፉቱሕ አል ሐበሻ” የአበሻ ወረራ በሚለው መጽሐፉ ለአገራችን የተጠቀመበት ስም ሐበሻ እንጂ ኢትዮጵያ አይደለም።

 

በቅዱስ ቁርአንም የአገራችን ስም ሐበሻ እንጂ ኢትዮጵያ የሚል አንድም ቦታ አናገኝም። አንድ ምሳሌ እንጥቀስ። ነቢዩ ሙሐመድ በጥሪያቸው መጀመሪያ ዘመን ከቁሬይሽ ነገድ ጋር አለመግባባት ስለተፈጠረ ተከታዮቻቸውን  ከቁሬሽ አደጋ ለማዳን ወደ ኢትዮጵያ እንዲሰደዱ ሲያዟቸው እንዲህ ብለዋቸዋል “ወደ ሐበሻ ብትሄዱ በርሱ ጥላ ከለላ ሥር ያሉ ሰዎች የማይሰደዱበት ንጉሥ ታገኛላችሁ። የጽድቅ አገር ናት ስለዚህም እግዚአብሔር ከጭንቃችሁ ይታደጋችኋል።”

 

አንድ ትዝ የሚለኝ ግሩም አጋጣሚ አለ። ምናልባትም እዚህ ላስረዳ ለፈለኩት ሐሳብ ጠንካራና ተጨባጭ ማብራሪያ ሊሆን ይችል ይሆናል። ቋንቋና አፈታሪክ ታሪካዊ መረጃዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያጠራጥር ነገር አይደለም። ከዚህም የተነሣ ነው ለአፋዊ ሥነ ጽሁፍ ዋጋ ሰጥተን በከፍተኛ ደረጃ የምናጠናቸው። ታሪኩ እንዲህ ነው፤ ሦስት የትምህርት ጓደኞቼና እኔ የነፃ የትምህርት ዕድል አግኘተን ካይሮ ግብፅ ውስጥ እንማር በነበርንበት ጊዜ አንድ ቀን እራታችን በታወቀው የካይሮ አውራ ጎዳና በቫሪዐ ፉአድ በስተግራ በኩል ስንሸራሸር በዚሁ መንገድ በስተቀኝ በኩል የኛን አገር ሰዎች የሚመስሉ ወጣቶች እንደኛው በእግራቸው ሲንሸራሸሩ አየን። ወዲያው ከነሱ አንደኛው ከፍ ባለ ድምጽ ወደኛ እየጠቆመ እኒያ እማዶ ያሉት ልጆቸ አበሾች ናቸው አለ። ከዚያ በኃላ እነሱ መንገዱን ተሻግረው ወደኛ ሲመጡ እኛም የትራፊኩ መብራትና የእግር መንገደኞች ማቋረጫው መንገድ ወደኋላ ስለነበረ ወደኋላ ሄደን ጠበቅናቸውና ተገናኝን። ኋላ ስንተዋወቅ የኢትዮጽያ አየር መንገድ ሠራተኞች መሆናቸውን ተረዳን። እዚህ ላይ የአንባቢዎቼን አስተያየት ለመመለስ የምሻው ወደሚከተለው ቁም ነገር ነው፤ ያ ወጣት በግብፅ አውራ መንገድ አይቶን እኛን አበሾች ሲል እኛ የተለየን የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች መሆናችንን ማመልከቱ አልነበረም። በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያውያን ማለቱ ነበር። ለዚህም ጥሩ ማስረጃ የሚሆነው አበሾች ብሎ ከጠራን ውስጥ አንዱ ጉራጌ፣ ሁለታችን አማሮችና ሌላኛውን አራተኛው ኦሮሞ ነበር።

 

ማንኛውም አጥርቶ አሳቢና ሁኔታዎችን ጥሩ አድርጎ ለመመልከት ለሚሻ ሰው ያ ወጣት አበሻ ባለበት ጊዜ በሕልሙም ሆነ በውኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለምንኖር የተለየን ሰዎች መናገሩ አልነበረም። በአጠቃላይ ስለ አገሩ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያውያን መናገሩ ነበር። እኛ ኢትዮጵያውያን ከአያሌ ዘመናት በፊት ጀምረን ስለራሳችን እርስ በርሳችን ስንነጋገር አበሻ እያልን እንነጋገራለን እንጂ እኛ ስለሀገራችን በጽሑፍም ሆነ ይፋዊ መግለጫ ስንሰጥ ኢትዮጵያዊያን እንጂ አበሾች አንልም። በየጊዜው እርስ በርሳችን በምናካሂደው ውይይት ጨዋታ ወዘተ እኛ አበሾች፤ ያበሻ ነገር' ያበሻ ልብስ' ያበሻ ቀጠሮ' ያበሻ ምግብ' ስም ስናወጣ አበሻ ጣይ' /አበሻ ፀሐይ/፣ አበሹ፣ ያበሻው ንጉሥ እንላለን። እንዲህ በምንልበትም ጊዜ በአስተሳሰባችን ላይ የተለየ ብሔረሰብ ለማመልከት ብለን አይደለም።

 

እንግዲህ ይህን የቋንቋ አጠቃቀም ጣጣ ወደጎን ትተን አበሻና ኢትዮጵያ የዚችው የኛው አንዲቱ አገር መጠሪያ መሆኑን እናስተውል። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ትንሽ ማብራሪያ እንስጥ።

 

እላይ በመጠኑም ቢሆን ለመጠቆም እንደሞከርኩት አበሻ፣ ሐበሻ የሚለው ስያሜ የተገኘው ታሪክ እንደሚነግረን ከደቡብ ዐረቢያ ወደ አፍሪቃ ቀንድ ፈልሰው ከመጡ ብዙ የደቡብ ዐረቢያ ነገዶች ካንዱ መጠሪያ ነው። የዚህ ነገድ ስም ኋላ በምሥራቁ ዓለም ለመላዋ አገራችን መጠሪያ እየሆነ ሄዷል። ለምሳሌ ይህ ስም በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ገናና በነበረው የአክሱም ንጉሥ በዔዛና የደንጊያ ጽሑፎች ላይ ተቀርፆ ይገኛል። ይህ ንጉሥ የሸፈቱበትን ያካባቢውን ግዛቶቹን አሸንፎ ማስገበሩን ሲናገር ስለ ስም ማዕረጉ እንዲህ ብሎ ይጽፋል፡- ዔዛና የአክሱም፣ የሕምያርም፣ የካሱና የሐበሸትም፣ የረይዳንም፣ የሰልሔንም፣ የጽያሞም ንጉሠ ነገሥት የማሕረም ልጅ በጠላቶቹ የማይሸነፍ እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን የሚከተለውን ታሪካዊ ሐቅ ነው። ይህ የአክሱም ጽሑፍ ልሳነ ሦስት ሲሆን የተጻፈባቸውም ቋንቋዎች በሳብኛ በጥንቱ ግዕዝና በግሪክኛ ነው። በግሪኩ ጽሑፍ ላይ በሐበሸት ፋንታ ኢትዮጵያ በሚል ተተክቶ እናገኛለን። ይህን ካልን ዘንዳና ስለ ሐበሻ አመጣጥ እንደተናገርነው ሁሉ ስለ ኢትዮጵያም አመጣጥ ባጭሩ እንናገር።

 

ስመ ጥሩ የግሪክ ባለ ታሪክ ሆሜር ከግብጽ በስተደቡብ ያሉትን የአፍሪቃ አገሮች ሁሉ በደምሳሳው ኢትዮጵያ ብሎ ጠርቷቸዋል። ይህም ከጊዜ ብዛት የሌሎችም የአፍሪቃ አገሮች መጠሪያ መሆኑን አቁሞ የኢትዮጵያ ብቻ እየሆነ ሄዷል። አብዛኞቹ አውሮጳውያንም የሆሜርን ፈለግ በመከተል አገራችንን ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከሐበሻ ይልቅ ወደ ኋላ ጊዜ በብዛት እየገነነ የመጣ ይመስላል። ይህም አገራችን ከምዕራባዊው ዓለም ጋር ይበልጥ ግንኙነት ማድረግ ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ሊሆን ይችላል። ዋናው ቁም ነገር ግን ከብዙ ምእተ ዓመታት ጀምሮ ሁለቱም ስያሜዎች ያገራችን መጠሪያዎች መሆናቸው ነው። ከዚህም የተነሣ ነው አንዳንድ የኢትዮጵያ ነገሥታትና መሪዎች ለአውሮጳ አቻዎቻቸው መሪዎች በሚጽፏቸው ደብዳቤዎች በሐበሻ ፋንታ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ብለው ሲጽፉ የነበረው። በአንጻሩ ግን ለምሥራቅ መሪዎች በሚጽፉበት ጊዜ ኢትዮጵያ ከሚለው ስያሜ ይልቅ አበሻ/ሐበሻ የሚለውን ይመርጡ ነበር። ይህን ሐሳብ ለማብራራት የሚከተለውን ሁኔታ እንይ፤ ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ አራተኛ ለማንኛውም የዓለም መሪ በጻፏቸው ደብዳቤዎች በሳቸው ጊዜ ኦፊሴላዊ የነበረውን ኢትዮጵያ የሚማለውን ስም ከማዕረጋቸው ጋር ሲጠቅሱ በማኅተማቸው ላይ ግን ዐረብኛም ስለነበረው ሐበሻ የሚለውንም ስያሜ ጨምረው ይጽፉ ነበር። ለምሳሌ የደብዳቤዎቻቸው መግቢያ እንዲህ የሚል ነው።

 

ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን፣ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ካሉ በኋላ በማኅተማቸውም ላይ ይኸው ይደገምና ነገር ግን በዐረብኛ ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን እንዳለ ሆኖ ንጉሠ ነገሥት ከሚለው ቀጥሎ በ “ዘኢትዮጵያ” ፋንታ “የሐበሻ” የሚል ይገኝበታል። እንዲህ ማድረጋቸውም የምዕራቡንም የምሥራቁንም ርዕሰ ብሔሮች በሚያውቁት ቋንቋ ለማስተናገድ መሆኑ ግልጽ ነው።

 

እንግዲህ እላይ የተጠቀሰውን ሐተታ እንደ መግቢያ ካስቀመጥኩ በኋላ ይህን መጣጥፍ እንድጽፍ ወደ አነሣሣኝ ወደ ዋናው ምክንያቴ ልመለስ።

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምዕራባውያን ፀሐፊዎች ሁለቱ ስያሜዎች ማለትም ሐበሻና ኢትዮጵያ የተወሰኑ የሀገራችን ክፍሎች መጠሪያ እንደሆኑ ያለ ሀፍረት ሊነግሩንና ሊያሳምኑን ይፈልጋሉ። እንደነሱ አባባል ሐበሻ ማለት በትግራይና /ኤርትራን ጨምሮ/ በአማራ ከፍተኛ ቦታዎች የሚኖሩ ሕዝቦች መጠርያ ስም ነው ይሉናል። ከዚህም በመነሳት ሐበሻ ነፍጠኛ፣ ጦረኛና ጨቋኝ የገዥ መደብ አንደሆነ ይናገራሉ። ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ እንዳጋጣሚ እኔም በተካፈልኩበት አንድ ጥናታዊ ጉባኤ አንድ የውጭ አገር ሰው ባቀረበው ወረቀት ላይ ይህን ሐሳብ ሲያስተጋባ ሰምቻለሁ። የሰውየውን ማንነት በወግ ስለማውቅ ብዙም አልተደነቅሁበትም። ግን ስለተናገረው ጉዳይ የጉባኤው ተሳታፊዎች ከነበሩት ብዙ ምሁራን  ኢትዮጵያውያን ውስጥ ማንም ሰው አስተያየት አለመስጠቱ በጣም ደንቆኛል፤ ገርሞኛል። ይህ ሰው ባቀረበው ወረቀት ባለማፈር ያበሻ ነፍጠኞች ባካሄዱት ወረራ የሚል አገላለጽም ነበረው። የአበሻ ነፍጠኛ ሲል ሰውየው የንጉሡ ወታደሮች ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው። እንግዲህ አበሻ የሚለው ትግሬውንና አማራውን ብቻ ማለት ከሆነ ሰውዬው ባልገባው ወይንም በማይገባው ጉዳይ ላይ ዘላብዷል ማለት ነው። ነፍጠኛ ማለት አንዳንድ የአመለካከት ድኅነት የሚያጠቃቸው ወገኖች እንደሚያምኑት ሳይሆን ጠመንጃ ይዞ የሚዋጋ ወታደር ከማለት በስተቀር ሌላ ተጨማሪ ብሔረሰብን የሚገልጽ አባባል አይደለም። የኢትዮጵያ ነገሥታት ወታደሮች ከእነዚህ ብሔረሰቦች የተውጣጡ ሰዎች ብቻ ነበሩ ማለት የኢትዮጵያን ታሪክ በወግ አለመረዳት ነው። አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፤ በ14ኛው ክፍለ ዘመን ነግሦ በነበረው በዐምደ ጽዮን ታሪክ ውስጥ ስለ ዐምደ ጽዮን ሠራዊት ቅንብር እንዲህ የሚል ታሪክ እናገኛለን፤ “ሸሹም ስላችሁ ከፍርሐት የተነሣ ነው ብላችሁ አታድንቁ፤ ምክንያቱም የሸዋ፣ የዳሞት፣ የጎዣም፣ የትግሬና የብጉና፣ የአምሐራ ሠራዊትና የኢትዮጵያ ሠራዊት ሁሉ በመላ ቢሰበሰብ በእግዚአብሔር ኃይል ካልሆነ በስተቀር በፊታቸው ሊቆም ስለማይቻል ነው።” ሌሎችም ተመሳሳይ ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል። ይሁንና የኢትዮጵያ ነገሥታት ወታደሮች ከነዚህ ሁለት ብሔረሰቦች ብቻ የተውጣጡ ነበሩ ማለት ኢትዮጵያን በሃይማኖት ለመለያየትና ለማዳከም እንደሚሞክሩት ሁሉ በብሔረሰብም ለመከፋፈል የሚፈጥሩት ዘዴ ነው። ሁኔታዎችን ቀረብ ብለን ካየን የዚህ መሠሪ አከፋፈል ምንጭ የአውሮጳ ሚሲዮናዊያን ናቸው። የነዚህ ቡድኖች ዋና ዓላማ እምነታቸውን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን ድብቅ ዓላማም አላቸው። ይኸውም ደካማ ኢትዮጵያን ፈጥሮ እንዳሻቸው መግዛትና ማዘዝ እንዲያስችላቸው ማድረግ ነው።

 

ወደዋናው ጉዳይ ልመለስና ነፍጠኛ ማለት ማንኛውም ንጉሡን ወይም የጦር መሪውን ተከትሎ ጦር ሜዳ የሚገኝ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ኢትዮጵያ ጦር ከሁሉም ብሔረሰብ እየተውጣጣ ይመሠረት እንደነበረ ማስረጃ ማቅረብ አያሻም። አንቱ የተባሉትም የጦር መሪዎች የልዩ ልዩ ብሔረሰብ ወገን እንደነበሩ እናውቃለን። ለመሆኑ ኢትዮጵያውያን በሙያቸውና በአገር ወዳድነታቸው ሲገለግሉ የነበሩትን እነ ባልቻ አባ ነፍሶን፣ እነ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን፣ እነ ጎበና ዳጨን፣ እነ ገረሱ ዱኪን፣ እነ አበበ አረጋይን፣ እነ አበበ ዳምጠውን እና እነ ደስታ ዳምጠውን ሌሎችም በጣም ብዙዎች ከየትኛው ክፍል ልንመድባቸው ይሆን? አበሻ ወይስ ኢትዮጵያ?

 

ጥያቄው እንግዲህ እንዲህ ያለው ችግር ለምን ተፈጠረ በሚለው ላይ ነው። አመዛዛኝ አእምሮ ያለው ሰው ይህ ጥያቄ የማያሻማ መልስ እንዳለው ፈጥኖ ይረዳል። ችግሩ ያለው ሐቁን ሸፋፍነው ሌላ የራሳቸውን ወይንም የፈረንጆችን ሕልም እውን ለማድረግ በሚሞክሩት ዘንድ ብቻ ነው። እንግዲህ ዋናውን ጉዳይ ጉልህ አድርገን ማቅረብ ያለብን ይመስለኛል። ለምንድን ነው ምዕራባውያን በአበሻና በኢትዮጵያ መሀከል ልዩነት ፈጥረው ልብወለድ ታሪክ የሚነግሩንና እንድናምንላቸው የሚፈልጉን ለሚለው ዋናና መሠረታዊ ጥያቄ መልሱ ይህ ነው። የወደፊት ተስፋቸውን በጣሉባት ገና ባልተበላችውና በድንግሏ የውስጥ አፍሪቃ አህጉር ጠንካራና አይበገሬ መንግሥት እንዲነሣ አይሹም። ከዚህም የተነሣ የተከፋፈለችና ደካማ ኢትዮጵያ /ወይንም ሌላ የአፍሪቃ አገር/ ለሕልማቸው ማስፈፀሚያ ጥሩ መስክ ሆና ያገኙዋታል። አንዲት ጠንካራ ሀገር “እምቢ! ይህ መብቴ ነው! ከናንተ ጋር የምዋዋለው እና የምደራደረው ጠቅሜንና መብቴን አስጠብቄ እንጂ የናንተን ፈቃድ ብቻ ለመፈፀም አይደለም። ግንኙነታችን ሁሉ በኩልነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት” እንድትላቸው አይሹም። እነርሱ በርካሽ ያመረቱትን የፋብካዎቻቸውን ምርት በውድ ዋጋ ለኛ ሸጠው የኛን የእርሻ ውጤት ባልባሌ ዋጋ ሊቀሙን ይሻሉ። ይህም ዓይኑን ያፈጠጠ ዝርፊያ መሆኑን ማንም አስተዋይ አይስተውም። እንዲህ ያለውን የሽንገላ ዘዴያቸውን ባለፈው ምእተ አመት ተጠቅመውበታል፤ ባሁኑ ጊዜ ግን ፈጽሞ የማይታለም እየሆነባቸው ነው የሄደው። ስለዚህም ሌላ ዘዴ መፈለጉ አማራጭ ያልነበረው መንገድ ነበር፡ ይህም የከፋፍለህ ግዛ ማኪያቬሊያዊ ፍልስፍና ለዕድላቸው መፈተኛ እያረጉ ስለኢትዮጵያ በሚናገሩበት መድረኮች ሁሉ ደጋግመው እያነሱት ነው። እንዲህ ባለውም ዓይኑን ባፈጠጠ የሽንገላ ዘዴያቸው ሊያታልሉን የሚችሉት የሚሉንን አምነን የተከፋፈልንላቸው እንደሆነ ብቻ ነው።

 

ምዕራባውያን አፍሪቃን ሲቀራመቱ ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ዕጣ እንድትሆን ወስነው ነበር። ይህም ከግፍና ከአመጽ የተነሣ እንጂ ሌላ ምክንያት አልነበረውም። በሁለቱም አገሮች መካከል የብዙ ሺ ኪሎ ሜትር የርቀት ልዩነት አለ። ስለዚህም ኢትዮጵያንና ኢጣልያንን የሚያገናኛቸው ምንም ዓይነት የጂኦግራፊ ጉርብትና የለም። ሆኖም ግን ኢጣልያ ኢትዮጵያን በላቀ የጦር ኃይል አሸንፋለሁ በማለት የዐድዋን ጦርነት አካሄደች። በዚያን ጊዜ አንደማንኛውም ወቅት ሁሉ ጠንካራና አይበገሬ ኢትዮጵያ ግንባሯን ሳታጥፍ የኢጣልያ ሽንፈት ለአውሮጳ ትልቅ ውርደት ነበር።

 

አንባቢ ሆይ አስተውል! እንግዲህ በጦርነት ያልቀናውን ዕድል በሌላ ዘዴ መሞከሩ ጥሩ ብልሃት መሰሎ ለምዕራባውያን ስለታያቸው ምሁሮቻቸው #አበሻ$ ና #ኢትዮጵያ$ የሚለውን የቆየ ስያሜ አዛብተው መጠቀም ጀመሩ። የሚገርመው አንዳንድ ወገኖቻችን ይህን ውስጠ መርዝ አከፋፈል ሳይመረምሩ እያስተጋቡ ነው። አንዳንዶቹ እንደዚህ ያለውን የከፋፍለህ ግዛ ሴራ ለምን እንደተጠነሰሰ ቢያውቁትም በዚህ አማልክቶቻቸው ባወጡላቸው የከፋፍለህ ግዛ ዘዴ በመጠቀም አገርን ገንጥሎ /እንደ ኤርትራ/ ለመግዛት ያላቸውን ምኞች እውን ለማድረግ እንደሚረዳቸው ስለሚያምኑና እስልጣን ኮርቻ ላይ ለመንጠላጠል ስለሚፈልጉ ከማንም ይበልጥ ያናፍሱታል። ነገር ግን ካለፉትና ከቅርብ ታሪካችን አለመማር ነው እንጂ በቅርቡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ተቀስቅሶ በነበረው ግጭት ትምህርት ቢወስዱ ኖሮ አበሻና ኢትዮጵያ እያሉ አገራቸውን ከመከፋፈል ቢቆጠቡ ጥሩ ነበር። በዚህ ግጭት ይህ የአበሻ ነፍጠኞች ጣጣ ነው ብሎ የኢትዮጵያን ሕዝብ እጁን አጣምሮ አልተቀመጠም። ጢስ እንደገባበት ንብ ሆ ብሎ ተነሥቶ ተዋድቆና ደሙን አፍስሶ አገርን ከወራሪ ታደጋት።

 

ይህን ካልኩ በኋላ የኢትዮጵያ ችግር እምኑ ላይ ነው ወደሚለው ጥያቄ ሊሂድና አንዳንድ ሐሳብ ልሰንዝር። ኢትዮጵያ በአበሻና በኢትዮጵያ የመከፋፈሉ ዓላማ አገሪቱን ለማዳከምና ያሏትን አሜን ብላ የምቅበቀል ደካማና ጥገኛ አገር ለመፍጠር መሆኑን በመጠኑም ቢሆን ተገንዝበናል። የዚህ አከፋፈል ውጤትም ጨቋኝና ተጭቋኝ የሚለውን መደብ ፈጥሮ እርስ በርስ ለማቃቃርና ለማጫረስ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ ችግር ያለው በገዥና በተገዥ መደብ መካከል ባለው ቅራኔ እንደሆነ ማንም አስተዋይና በኢትዮጵያዊነቱ/ በአበሻነቱ የሚያምን ዜጋ ጥሩ አድርጎ ይረዳዋል። በማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔረሰብ ውስጥ ጨቋኝም ተጭቋኝም የኅብረተሰብ ክፍል ነበር፤ አሁንም ይኖራል።/ሶሻሊስት ሆኜ ሳይሆን ሐሳቤን በወግ ሊገልጽልኝ ስለቻለ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ችግር እዚህ ላይ ነው እንጂ ሌላ ሐተታ እየፈለጉ ማሳዘኑ የትም አያደርስም። ለአንዱ ብሔረሰብ ልዩ ስም እየሰጡ ጨቋኝ፤ ሌላውን ተጨቋኝ ማድረግ ከተጨባጩ እውነታ ጋር ስለማይሄድ የትም አያደርሰንም፤ ከእውነታው እየራቅን ትዝብት ላይ ከመውደቅ በስተቀር።

 

ይህ የጨቋኝና የተጨቋኝ ፍትህ አልባ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈታ የሚችለው በኔ እምነት በበጎ የማያስቡልን ወገኖች እንደሚያላዝኑት ሳይሆን ወደፊት በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል በሚቋቋመው ፍትሕና ርትዕ የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርአተ ማህበር ሲነግሥ ብቻ ነው።

 

ይህም እውን የሚሆነው እያንዳንዱ ዜጋ ያለ ተጽእኖ እንደራሴውን ወክሎ መርጦ እሱን ወክሎ በሚያቋቁመው የወኪሎች ሸንጎ አማካኝነት ነው። በሕዝብ ምርጫ የሚቋቋመውም ሕዝባዊ ሸንጎ የሚሾመው የአገር መሪ ለተወሰነለት ጊዜ ብቻ አገልግሎ ሥልጣኑን ለተተኪው በማስረከብ ምንም እና ማንንም ሳይፈራ የኅብረተሰቡ አባል ሆኖ መኖር የሚችል መሆን ያለበት ሲሆንና ሥልጣን በያዘበት ዘመን ዓይነ ውሀው ካላማረ ወዲያው ከሥልጣን ወርዶ ላደረገውም ጥፋት ተጠያቂ የሚሆንበት ሥርዓት ሲቋቋም ነው።

 

በኔ እምነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊታገልለት ሊያቋቁመው የሚገባው እንዲህ ያለውን ሥርዐተ ማኅበር ነው። የተለቀቀ ገንዘብ ሌብነትን ያስተምራል እንደሚባለው ሁሉ የተለቀቁ ሥልጣንም እንዲሁ ያባልጋል፤ መረንም ይለቃል። ልጓም የሌለው ፈረስ እንደልቡ እንደሚፏልል ሁሉ ቁጥጥር ያነሰውና በሕዝብ እውነተኛ የበላይነት የማያምን መሪ እንዲሁ እንዳሻኝ ልሁን ይላል።

 

ስለዚህ የኢትዮጵያ ችግር ያለው በጨቋኝና በተጨቋኝ የኅብረተሰብ አባላት መካከል ካለው ቅራኔ የተነሣ እንጂ አበሻ' ኢትዮጵያ ነፍጠኛ 'ትምክሕተና እየተባለ ሕዝብን ለመበታተን 'ለማቃቃርና ለማፋጀት ከሚደረገው ሙከራ የመነጨ አይደለም።

 

ሐሳቤን ከመቋጨቴ በፊት አንድ ተጨማሪ ነገር ልወርውር። አስተዋይ አዕምሮ ያለውን ልጠይቅ። ለመሆኑ ጨቋኝና ነፍጠኛ እያሉ የሚጠሩት ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ የተለየ ምን ጥቅም አግኝቶ ይሆን? ይህን ያህልስ ጥላቻ የሚሰነዝርበት?

በመጨረሻም የአበሻንና የኢትዮጵያን ስያሜ ጉዳይ በጥንቃቄ መመርመርና ማየትና ዓላማውም ምን እንደሆነ ዓይነ ኅሊናችንን ከፍተን ማየት ይኖርብናል። በአገራችን ህልውና ላይ የተሰነዘረ የጠላቶቻችን ለያይተህና የአዳክመህ ግዛ መሣሪያም መሆኑን በወግ አንረዳ። እስከመቸስ እየተታለልን እንኖራለን?¢

Page 7 of 19

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us