124 መጽሐፍት በአንድ ቀን ተመረቁ

Thursday, 03 July 2014 12:37

በድንበሩ ስዩም

ይህ የ124 መጽሐፍት ቁጥር እና ህትመት በእጅጉ ብዙ ነው። ሁሉም መፃሕፍት በአንድ ቀን ለምረቃ በቁ ሲባል ደግሞ ነገሩ ራሱ አስገራሚ ይሆናል። የእነዚህ መጽሐፍት ምረቃ ደግሞ የማንበብና የህትመት ባህሉ ባደገባቸው ታላላቅ ሀገራት ውስጥ ባለመሆኑ ደግሞ ግርምታችንን ከፍ ያደርገዋ። 124 አዳዲስ መፃሕፍት ለህትመት በቅተው ሰኞ ዕለት እዚሁ አዲስ አበባ በብሔራዊ ቴአትር ቤት አዳራሽ የተመረቁት በእኛው ሀገር ነው። አሳታሚያቸው ደግሞ አስቴር ነጋ ጀነራል ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ/ ማህበር ነው።

የተለያዩ 124 መጽሐፍትን አንድ ጊዜ አሳትሞ ለንባብ ማድረስ ትልቅ ጥንካሬ፣ ተናቦ መስራትን፣ ቁርጠኝነትን፣ ልፋትን፣ ትጋትን በእጅጉ ይጠይቃል። እነዚህ መፃሕፍት ደግሞ የትምህርት መረጃዎች እና የመማርያ መፃሕፍት ናቸው። በዚህ አይነት መልኩ የሚዘጋጁ መፃሕፍት ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄን የሚጠይቁ ናቸው። ከስህተት መፅዳት አለባቸው። የሆነ ጥንቃቄን የሚጠይቁ ናቸው። ከስህተት መፅዳት አለባቸው። እድሜን፣ እውቀትን፣ አስተሳሰብን ወዘተ መሰረት አድርገው መዘጋጀት ስላለባቸው ደግሞ ኃላፊነቱ የተደራረበ ነው።

እነዚህ 124 የተለያዩ መፃሕፍትን አስቴር ነጋ ጀነራል ቢዝነስ ሊያሳትም የቻለው ትምህርት ሚኒስቴር ለተማሪዎች የመማሪያ እና የመርጃ መፃሕፍትን ለማሳተምና ለተማሪዎች ለማሰራጨት ባወጣው ክፍት ጨረታ ድርጅቱ በማሸነፉ ምክንያት ነው። ጨረታውን ያሸነፈበትን ኃላፊነት ተቀብሎም ጥራታቸው የተጠበቁ መፃህፍትን አሳትሞ አዘጋጀ። ሰኞ ዕለት ከ10፡30 ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር ቤት የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎች በታደሙበት እና ሌሎችም እንግዶች፣ በተለይም መፃሕፍቱን ያዘጋጁት ምሁራን፣ ጥሪ የተደረገላቸው ደራሲያን እና ታዋቂ ሰዎች በስፋት በታደሙበት ስነ-ስርዓት ምረቃው ተካሂዷል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያሰሙት የአስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆኑት መምህር ዘነበ ደነቀ እንደተናገሩት፣ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ የትምህርት ዓለም ውስጥ ብቻ ከ400 በላይ መፃሕፍትን አሳትሞ ማሰራጨቱን ገልጸዋል። መምህር ዘነበ አክለው እንዳወሱት ከሆነ የመፅሐፍቶቹም የትኩረት አቅጣጫዎች፣ ለአፀደ ሕፃናት፣ ለአንደኛ ደረጃ እና ለሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ ለሚማሩ ተማሪዎች የሚያገለግሉ እንደሆነ አመልክተዋል። ከዚሁ ጎን ለጎንም መፃህፍትን በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችም እያሳተሙ ለተማሪዎችና ለመምህራን እነደሚያሰራጩ ገልጸዋል።

አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት በተለይ በትምህርት ላይም ሆኑ ከትምህርት ውጭ ሆነው በልዩ ልዩ ሙያ ውስጥ ላሉ ሰዎች መገልገያ የሚሆኑ የተለያዩ መዝገበ ቃላትን በማሳተም በኢትዮጵያ የእውቀት መርጃ ህትመትና ስርጭት ውስጥ ግንባር ቀደሙን ተግባር እየተወጡት መሆኑም ይነገራል። ዛሬ ከየሰው ቤት የማይጠፉትን “ሜሪት” የተሰኘውን መዝገበ ቃላት ጨምሮ ሌሎችንም መዝገበ ቃላቶችና የቃላት መፍቻዎችን በማሳተም ረገድ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ትልቅ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

የአስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት የኦፕሬሽን መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ደራሲውና ሃያሲው አቶ ጌታቸው በለጠ ስለ 124ቱ መጽሐፍቱ የህትመት ጉዞ በተመለከተ ስኬቱን እና ተግዳሮቱን በምረቃ በአሉ ላይ ለተገኙት ታዳሚያን አቅርበዋል። እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ፣ ከነዚህ ሰኞ ዕለት ለምረቃ ከበቁት መጽሐፍት በተጨማሪ በቅርቡ ታትመው የሚሰራጩ 106 ያህል የትምህርት መጽሐፍት እንዳሉም ጠቁመዋል።

ከሁሉም በላይ የሚገርመው ግን እነዚህ ከ200 በላይ የሆኑት የትምህርት መጽሐፍት እየተባዙ ሲታተሙ ቁጥራቸው ከ70 ሚሊዮን በላይ ቅጂ እንዲሆኑ መወሰኑ እና ይህንንም እጅግ ግዙፍ ኃላፊነት ለመወጣት አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑ ነው። ከ70 ሚሊዮን በላይ ቅጂ መፃሕፍትን አሳትሞ ማሰራጨት ግዙፍ ስራ ነው። ትልቅ የሕይወት ታሪክ ነው።

እነዚህ መፃሕፍት Galaxy Reference Series በሚል ርዕስ የተዘጋጁ ሲሆን፣ የጥራት ደረጃቸውን ለመጠበቅ ሲባል ህተመታቸው የተከናወነው በሕንድ ሀገር ነው። ምክንያቱ ደግሞ መፃሕፍቶቹ ከእዚህ ቀደም ከነበሩት የትምህርት መርጃ መፃሕፍት ህትመት በተለየ መልኩ ባለቀለም በመሆናቸው እና በሀገራችን ውስጥ ያለው የቀለም ህትመት እና ጥንቃቄም አስተማማኝ ባለመሆኑ በሕንድ ሀገር እንዲታተሙ ተደርገዋል።

አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት እነዚህን መፃሕፍት ከ700 በላይ ወረዳዎችና ከተሞች እየተዘዋወረ ለተማሪዎች ያሰራጫል። ትምህርት ሚኒስቴርም መፃሕፍት በጥራትና በጥንቃቄ ተዘጋጅተው ለተማሪዎች እንዲደርስ ለማድረግ ያሳየው ቁርጠኝነትም እንዳስመሰገነው አስተያየት ሰጪዎች ለሰንደቅ ገልጸዋል።

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
12103 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us