የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ምን እያሉ ነው?

Thursday, 03 July 2014 12:33

በድንበሩ ስዩም

 

ከትናንት በስቲያ ሰኞ ዕለት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት አሰናጅነት የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ህገ-መንግሥቱን እንዲያውቁት፣ በውስጡም ያለውን ፍሬ ነገር እንዲገነዘቡት የሚያስችል ስልጠና በራስ ሆቴል አዳራሽ ተዘጋጅቶ ነበር። በዚሁ ስልጠና ላይ ሕገ-መንግሥቱን በተመለከተ ጥናት ያቀረቡት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የሆኑት የተከበሩ አቶ ካሳ ተክለብርሃን ነበሩ።

እርሳቸው የሕገ-መንግስቱን ልዩ ልዩ ባህሪያት ረዘም ላለ ሰዓት ካስረዱ በኋላ መድረኩ ለጥያቄና ለውይይት ክፍት ተደረገ። ተሰባሳቢዎችም ሕገ-መንግሥቱን መሰረት አድርገው ከሙያቸው ጋር በተገናኘ አያሌ ጥያቄዎችን አንስተዋል። እኛም የተነሱትን ጥያቄዎችና አስተያየቶች አለፍ አለፍ እያልን እናቀርባቸዋለን።

ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል ለዛሬ የመረጥነው የማስታወቂያ ባሙያውና ጋዜጠኛው ሳምሶን ማሞ እና የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሐት የሰጧቸውን ሃሳቦች ነው። ሳምሶን ማሞ ኢትዮጵያ በታሪኳ ሀብታም የሆነችበት ዘመን የለም የሚል አቋም አለው። “ትልቅ ነበርን”. . .የሚባለው አባባል ሁሉ ብዙም እንደማይገባው ገለጸ የሚከተለውን ሃሳብ አቅርቧል።

ሳምሶን ማሞ

እውነታውን በመነጋገር ወደ ተሻለ ነገር መሸጋገር አለብን ብዬ አምናለሁ። ከሁሉም በላይ ግን ይህን ሕገ-መንግሥትና የኪነ-ጥበብ ባለሙያውን በተመለከተ ነው መልዕክት ማስተላለፍ የምፈልገው። እርስዎ (ካሳ ተክለብርሃን) የተናገሩትን ነገር የበለጠ ማስተማር የሚችለው ይሔ የስነ-ጥበብ ባለሙያ ነበር። ይኸ የሥነ-ጥበብ ባለሙያ ግን በዚህ መንግሥት ውስጥ ተካቷል ብዬ መናገር አልችልም። ለምሳሌ አጠገቤ ሙሉዓለም ታደሰ አለች። ሃያ ዓመት ሰርታ በ1400 ብር ደሞዝ የተባረረች ሰው ነች። ስለዚህ ቆመን ደግሞ ከምንም ነገር በላይ መንግሥት የሚፈልገውን ነገር ለማስተላለፍም ቢሆን ከዚህ የተሻለም ነገር የለም። መንግሥት ይሄን የሥነ-ጥበብ ባለሙያውን የበለጠ አክብሮት ቢሰጠው ኖሮ አሁን ሁኔታዎቹ የመረዳት ችግር እና ግራ መጋባት /Confusion/ ባለበት ሀገር ውስጥ ይሄን ግልፅ ለማድረግ ከዚህ የኪነ-ጥበብ ባለሙያ የተሻለ መንግሥት ምንም አቅም አልነበረውም። ነገር ግን ይሄ የጥበብ ባለሙያ በተለያዩ መንገዶች እየተጎዳ ነው።

ለመኖር በሚያስችል ሁኔታ ላይ ነው ያለው ብሎ ለመናገር አይቻልም። ቢያንስ መንግሥት በብዙ መስኮች ብዙ ለውጦች እያመጣና የጥበብ ባለሙያው ዛሬ የደረሰበት የኮፒ ራይት ችግር እንኳን ሊፈታለት አልቻለም። ዛሬም አንድ ካሜራና አንድ ውስኪ፣ በዚህ በጣም በሰለጠነ መንግሥት ውስጥ እኩል የሚቀረጡበት ሀገር ላይ ነን።

ሌላው ባለሙያ ደግሞ ገንዘብ ያው ሀብታም ከመሆን የተሻለ ጥቅም ፣ የተሻለ እድል እየተሰጠው ነው። ለምንድን ነው በኛ ላይ የተፈረደው? ለማስተማርም መንግስት የሚፈልገውን ነገር በዚህ ባለሙያ ለመጠቀም ይህንን ባለሙያ መንከባከብ ያስፈልጋል። የባለሙያው መብት ሊከበርለት ይገባል።

እኔን ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ ለማድረግ መንግሥት አንዲት ብር ኢንቨስት አላደረገም። በራሴ ፍላጎትና በራሴ መልካም ፈቃድ ነው 20 ዓመት ሙሉ ይሔንን መንግሥት እደግፋለሁ። የተሻለ መንግሥት ነው ብዬ ስለማስብ ነው። ይሔ ማለት ግን ችግር የለበትም ብዬ አንድም ቀን አስቤ አላውቅም። በተለይ በዚህ በእኛ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከምንም ነገር በላይ ለባለሙያው ትኩረት ሰጥቶ መንግሥት አንዳችም እርምጃ አልተራመደም። ከዚህ በፊትም አቋሜ ነው። አሁንም መንግሥት እየሰራ አይደለም። ይሔ ባለሙያ ተፈርዶበታል። ስለዚህ ባለሙያውን ልትንከባከቡ ይገባል። ይሔ ባለሙያ ለዚህ ሥራ ከሚገባው በላይ መስዋዕትነት እየከፈለ ነው። አሁንም ጭምር።

ሰርፀ ፍሬስብሐት

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሚለው እስከ አሁን ድረስ ስለ ተነጣጠሉ ነገሮች ይወራል። ስለ ልዩነት ያወራና አገናኝቶ የሚያስረውን አንድነት /Unity/ን ይረሳዋል። እዚህ ከፊት ለፊቴ ትልቅ የሙዚቃ አቀናባሪ ሰው ቴዎድሮስ መኮንን /ቴዲ ማክ/ አለ። እኔና እሱ ብሎም ሌላው የኪነ-ጥበብ ሰው በሚግባባበት መንገድ ብንሔድ ነጠላ ነጠላ ድምፆች ብቻቸውን ምንም የሚሰሩት ነገር የለም። ሙዚቃ ውስጥ ሀርመኒ የሚባል ፅንሰ ሃሳብ አለ። ሁሉንም አንድ ላይ የሚያደርግ ሁኔታ ነው። ያ ሲመጣ ነው ሙዚቃው ህብረ ወደሚባል ነገር ይቀየርና ድምፁ የተሟላ የሚሆነው። የኢትዮጵያ ሙዚቃ ወደ ኋላ የቀረው በምን ምክንያት ነው ተብሎ ትችት ሲነሳ እንኳን ነጠላ ስለሆነ ነው እየተባለ የሚተቸው። የሀርመኒ /የህብር/ ነገሮችን መጨመር አለበት ይባላል። ይሄ ለጥበቡ በጣም ጠቃሚ ነው።

እንግዲህ አንድ የሚያገናኝ ሴግመንት አለ ማለት ነው። ይህም ሀርመኒ ነው። ይህን የስነ-ጥበብ ፅንሰ ሃሳብ እንውሰደውና ብሔር፣ ብሔረሰቦች ህዝቦች የሚሉት የተነጣጠሉ ነገሮች በጣም ተደጋግመው ተወርተው የሚያስተሳስረው አንድ ነገር የቀረ ይመስለኛል። ይህም “ዜጋ” የሚለው ቃል ይመስለኛል። በኔ አመለካከት ነው። ስለ ልዩነት /Diversity/ ይህን ሁሉ ካወራን፣ ሁሉን የሚያስተሳስር አንድ ነገር ማውራት ያለብን ይመስለኛል። አንድ ስለሚያደርገን ነገር ማውራት አለብን። ሕገ-መንግሥት እዚህ ላይ ትንሽ ክፍተት ያው ይመስለኛል። የብዙዎችም ትችት ወደዚሁ የሚያደላ ይመስለኛል።

ሌላው ጎርበጥ የሚያደርጉ ቃላት አሉ። ለምሳሌ መቻቻል የሚለው ቃል። ብዙ ጊዜ ሲተች እሰማለሁ። ለምሳሌ አረፈሞተ የሚለውን ስንጠቀመው ሞተ ትንሽ ደስ አይልም። አረፈ የሚለው የተሻለ ስለሚሆን የሟችን ክብር ስለሚገልፅ ቃሉ ይመረጣል። መቻቻል የሚለው እኔ አሉታዊ ነገር እንዳለው ነው የምገነዘበው። ቻለው፣ መቻል ነው፤ እንግዲህ ምን ታደርገዋለህ ከሚለው አስተሳሰብ ጋር ይገናኛል። ስለዚህ መሆን ያለበት መገናዘብ የሚል ቃል ነው። መገናዘብ የሚል ትልቅ ቃል እያለ መቻቻል የሚለው ቃል ተመራጭ አይመስለኝም።

ሌላው እስከ መገንጠል የምትለዋ ቃል እስከ አሁን ድረስ እንደረበሸች ነች ብዬ ነው የማስበው። እስከመነጠል ትንሽ ላላ ያደርገዋል፤ ግን ስሜቱ ያው ነው። ግን መነጠል ከመገንጠል የተሻለ ቃል ይመስለኛል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
16842 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us