ቢሊየነሮቹ ተዋናዮች

Wednesday, 09 July 2014 13:32

በዓለማችን ላይ በኪነ-ጥበቡ ዘርፍ የገንዘብ ዝውውሩ እና ልውውጡ በእጅጉ እያደገ የመጣው በፊልም ኢንደስትሪው ላይ ነው። ፊልም ከፍተኛ በጀት ተይዞለት ከመሠራቱም በላይ ለተዋናዮች የሚከፈለው ገንዘብም ከጊዜ ወደ ጊዜ በእጅጉ እያደገ በመምጣት ላይ ነው።

በአሜሪካው ሆሊውድ ውስጥ በሚሰሩት ፊልሞች ላይ መሳተፍ ማለት በአንድ ጊዜ ህይወትን መቀየር ነው እየተባለም ይነገራል። ከሰሞኑ ዓለም አቀፉ የሚዲያ ተቋም CNN ባወጣው ዘገባም ሰዎችን ባለፀጋ ከሚያደርጉ ሥራዎች አንዱ ፊልም እንደሆነ ገልጿል።

Leading Women /መሪዎቹ ሴቶች/ በሚል ርዕስ እንደተዘገበው ከሆነ በሀብታሞቹ ተርታ ከተቀመጡት ሴቶቹ መካከል የሆሊውድ ፊልሞች ላይ በተደጋጋሚ የተሳተፉት እንደሆነ ፅፏል።

ስለ ዓለማችን ባለጠጐች እየተከታተለ የሚጽፈው ፎርብስ መጽሔት እንደሚገልፀው በዚሁ በፊልም ዓለም ውስጥ በገንዘብ ክፍያ የተሳካላቸው ሴቶች በሚል ርዕስ የስም ዝርዝራቸውን አውጥቷል። በዚህም መሠረት በቁጥር አንድ ላይ የተቀመጠችው ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት አንጀሊና ጆሊ ናት።

እንደ ፎርብስ መጽሔት ገለፃ አንጀሊና ጆሊ “The Tourist” በተሰኘው ፊልም ላይ በመተወኗ ብቻ የተከፈላት ገንዘብ 33 ሚሊየን ዶላር ሲሆን፤ ይህን ወደ ብር ስንመነዝረው ወደ 660 ሚሊዮን ብር ይሆናል ማለት ነው። ይሄ ብር ለአንጀሊና ብቻ የተከፈላት ሲሆን፤ እንደየተዋረዳቸው ደግሞ ሌሎችም እንደዚሁ ይሸለማሉ።

አንጀሊና ጆሊን በሐብት እርከኗ ወደ ላይ ካስወጧት ነገሮች መካከል ይሄው ከፊልም ጋር ያላት ቁርኝት ነው። እንደ መጽሔቱ ገለፃ፣ አንጀሊና ፕሮዲዩስ ያደረገችው In the Land of Blood and Honey የተሰኘው ፊልምም የሀብት መጠኗን ወደ ቢሊየነሮቹ ተርታ አስቀምጧታል። ለምሳሌ Kung Fu Panda 2 በተባለው ፊልም ላይ አንጀሊና ድርሻዋ ሰፊ ነው። ከዚህ ፊልም የተጣራ ገቢ ለማግኘት ሒሳቡ ተሰልቶ ተቀምጦ ነበር። በዚህም መሠረት ፊልሙ 165 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ትርፍ እንደሚያስገባ ተገልጿል።

የፊልም ጥበብ ኢንደስትሪ ሆኗል እየተባለም የሚነገረው በዚሁ ምክንያት ነው። ከፍተኛ የገንዘብ መጠን በውስጡ ስለሚዘዋወርበት ከጥበብነቱ ባሻገር ኢንደስትሪ ለመባል በቅቷል። እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገሮች ደግሞ በተለይ በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመኖራቸው የመዝናኛው ክፍል በሰፊው ስለሚተዋወቅ እና የህዝብንም ምላሽ በቀላሉ ማግኘት ስለሚቻል ጉዳዩ ተመንድጐ አድጓል። ከፊልሙም ሌላ የመዝናኛውም ክፍል ወደ ኢንደስትሪ አድጐ ዛሬ የመዝናኛ ኢንደስትሪ /ኢንተርቴይመንት ኢንደስትሪ/ እየተባለ በመጠራት ላይ ነው።

እንደው ከሰሞኑ CNN Leading Women ብሎ በፊልሙ ዓለም ከዘረዘራቸው ሴቶች መካከል ሌሎቹንም እንጠቃቅስ። ታዋቂዋ ተዋናይት ጄኔፈር ላውረንስ ከአንጀሊና ጆሊ በመቀጠል ትልቋ ተከፋይ ሆናለች። ጄኔፈር ላውረንስ “It Girl” በተሰኘው ፊልም 26 ሚሊየን ዶላር ወይም ወደ 520 ሚሊየን ብር ተከፋይ ነበረች።

የCNN ዘገባ እንደሚያመለክተው በሆሊውድ ውስጥ ከፍተኛ ተከፋይ ናቸው ብሎ የ10 ሴቶች ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል። በዚህም መሠረት፡-

- አንጀሊና ጆሊ            33 ሚሊየን ዶላር ተከፋይ

- ጄኔፈር ላውረንስ         26 ሚሊየን ዶላር ተከፋይ

- ክርስቲን ስትዋርት       22 ሚሊየን ዶላር ተከፋይ

- ጄኔፈር አኒስቶን         20 ሚሊየን ዶላር ተከፋይ

- ኤማ ስቶን             16 ሚሊየን ዶላር ተከፋይ

- ቻርሊዝ ቴሮን           15 ሚሊየን ዶላር ተከፋይ

- ሳንድራ ቡሎክ           14 ሚሊየን ዶላር ተከፋይ

- ናታሊ ፖርትማን        14 ሚሊየን ዶላር ተከፋይ

- ሚላ ኩኒስ              11 ሚሊየን ዶላር ተከፋይ

- ጁሊያ ሮበርትስ          10 ሚሊየን ዶላር ተከፋይ

እንደሆኑ ተዘግቧል።

      ይህ እንግዲህ የሚያሳየው ኪነ-ጥበብ በእጅጉ እያደገ እየተመነደገ የመጣበትን ሁኔታ ነው። በሀገራችን ኢትዮጵያም ከጊዜ ወደ ጊዜ አያሌ ወጣቶች እየተመሰጡበትና እየገቡበት ያለው የፊልም ጥበብ የተሻለ እንዲሆን አያሌ ነገሮቹ ሊሰሩለት ይገባል። ፊልሞቻችን ከተራ እና ከአልባሌ ርዕሰ ጉዳዮች እየወጡ አብዛኛውን ህዝብ ያማከሉ ቁም ነገር እና ረብ ያላቸው ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ዝግጅት ክፍላችን ይመኛል።

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
16574 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us