የተወዳጁ የወግ ደራሲ መስፍን ሐብተማርያም የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈፀመ

Wednesday, 16 July 2014 12:04

በጥበቡ በለጠ

 

በኢትዮጵያ ደራሲያን ታሪክ ውስጥ መስፍን ሐብተማርያም የራሱን አሻራ እና ቀለም አስቀምጦ ያለፈ ከያኒ ነው። መስፍን ሐብተማርያም የወግ ፀሐፊ (ቀማሪ) ነበር። በዘመኑ የወግ ፅሑፎችን ከመፃፍ አልፎ ለሕትመት እንዲበቁ ያደረገ ፈር ቀዳጅ ደራሲ ነበር። ከማሳተምም አልፎ የራሱን ወጎች በኢትዮጵያ ሬዲዮ ለረጅም ሳምንታት በመተረክ “ወግ” የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ በሀገሪቱ ውስጥ ጥሩ አድርጎ የተከለ በኋላም ዘሩን ያስፋፋ ሰው ነው። ዛሬ በርካታ ወጣቶች የወግ መፃሕፍትን እያሳተሙ ሰፊ የንባብ ሽፋን ያገኙት፣ ደራሲ መስፍን ሐብተማርያም የዘራት የወግ አዝመራ አሽታ እና ለምልማ በመውጣቷ ነው። ይህ የወግ ቀማሪ የነበረው መስፍን ሐብተማርያም ከትናንት በስቲያ ከዚህች ዓለም በሞት ተለይቶ ትናንት ሐምሌ 8 ቀን 2006 ዓ.ም አያሌ ወዳጅ ዘመዶቹ እና ቤተሰቦቹ በተገኙበት ሥነ-ሥርዓት ቀብሩ በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል።

መስፍን ሐብተማርያም በብዕሩ ከሚከትባቸው የወግ ጽሁፎች በተጨማሪ እንዲሁ በእርስ በርስ ግንኙነትም ወቅት ጨዋታ አዋቂ፣ ለዛ ያለው ተናጋሪ ወይም አንደበተ ጣፋጭ ሰው ነበር። ጨዋታ የማያልቅበት፣ በጨዋታዎቹ ውስጥ ደግሞ የቀልድና የአስቂኝ ጉዳዮች በስፋት የሚያዘወትር ሰው ነበር። መስፍን በኢትዮጵያ ሥነቃል “ከአፉ ማር ይዘንባል” የሚባል አይነት ሰው ነበር። እንዲህ አይነቱን ሰው ፈረንጆቹ Humorist የሚሉት አይነት ነው፡ መስፍኔ ሲያወራ ሁሉም ሰውነቱ ይናገራል፣ ይተርካል።

መስፍን ሐብተማርያም በማህበራዊ ግንኙነቱና በእርስ በርስ ተጫዋችነቱም አይረሴ ትዝታዎቹን አስቀምጦ ያለፈ አንደበተ ጣፋጭ ሰው ነበር።

ደራሲ መስፍን ሐብተማርያም የቤት ስሙ “ሞጆ” ይባላል። ሞጆ ሲሉትም ፊቱ ላይ የሚታየው ፈገግታ እና እሱንም ተከትሎ ስለ ሞጆ እና አካባቢዋ የሚተርከው ነገር ፈፅሞ አይረሳም።

መስፍን የተወለደው ሞጆ ከተማ የካቲት 25 ቀን 1937 ዓ.ም ነበር። አባቱ አቶ ሐብተማርያም ሞገስ ሲባሉ፣ እናቱ ደግሞ ወ/ሮ ደስታ አየለ ይባላሉ። ወደ ትምህርት አለም የገባውት በ1941 ዓ.ም ነው፤ በዚያን ጊዜም ያው ፊደል እና ንባብን የተማረው የቤተ-ክርስትያን ትምህርት ነው፤ እዚያም እስከ 1942 ዓ.ም ቆየሁ ሲል ከዓመታት በፊት የተናገረው ድምፁ ከእጄ ላይ ያስረዳኛል። ከዚያም በመለጠቅ እዚያው ሞጆ ውስጥ ከ1942 ዓ.ም ጀምሮ የአንደኛ እና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ቀጠለ። በኋላ ደግሞ ወደ ስምንተኛ ክፍል ሲዘዋወር ከሞጆ ከተማ ወደ አምቦ ከተማ ሔደ። አምቦ ከተማም ተምሮ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቀቀ። ከዚያም በወቅቱ የነበረውን ፈተና በጣም ጥሩ ውጤት በማምጣት በ1958 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ዩኒቨርስቲ ተቀላቀለ።

በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የተማረው ደግሞ ቋንቋ እና ሥነ-ፅሁፍን ነበር። የዩኒቨርስቲ ትምህርቱንም በ1962 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ፅሁፍ ትምህርት ክፍል በማዕረግ ድግሪውን አገኘ። መስፍን ሐብተማርያም ድግሪውን ካገኘ በኋላ ለሁለት ዓመታት ያህል በመምህርነት ካገለገለ በኋላ ወደ ውጭ ሀገር የትምህርት እድል አግኝቶ ሔደ። የሔደው ወደ ካናዳ ሲሆን፣ ቫንኮቨር ከተማ በሚገኘው “ዩኒቨርስቲ ኦፍ ብሪትሽ ኮሎምቢያ” ከሚሰኘው ዩኒቨርስቲ መማር ጀመረ። ከዚያም ዩኒቨርስቲ በፈጠራ ፅሁፍ /Creative Writing/ በተሰኘው የትምህርት መስክ የማስተርስ ድግሪውን አገኘ።

መስፍን ሐብተማርያም ወደ ካናዳ ሔዶ የተማረውን የፈጠራ ፅሁፍ አፃፃፍን እና በተለይ ደግሞ “በሥነ-ፅሁፍ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያዊያን ያን ያህል አዘውትረው በማይታዩበት የትምህርት መስክ መመረቁ ከፈር ቀዳጆቹ መካከል ግንባር ቀደሙ ያደርገዋል።

ከካናዳ ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን አጠናቆ ከመጣ በኋላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማስተማሩን ቀጠለ። በዚህም ጊዜ ልዩ ልዩ የትምህርት ኮርሶችን በመስጠት በማስተማር ይታወቃል። መስፍን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እያስተማረም በኢትዮጵያ ሬዲዮ እና የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥም ይሰራ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

መስፍን ሐብተማርያም ከማስተማሩ ባሻገርም በኢትዮጵያ ሥነ-ፅሁፍ ውስጥ በእጅጉ ተወዳጅ የሆኑትን መፅሐፍቶቹን ማሳተም ጀመረ። በህትመት ደረጃ የመጀመሪያው የሆነችው “የቡና ቤት ስዕሎችና ሌሎም ወጎች” የምትሰኘዋ ነች። በዚህች መፅሐፍ ውስጥ የተነሱት ርዕሰ ጉዳዮች በዘመኑ በአንባብያን ዘንድ በእጅጉ ተወዳጅ ነበሩ። በተለይ ደግሞ ራሱ መስፍን ሐብተማርያም ወጎቹን በኢትዮጵያ ራዲዮ በራሱ ድምፅ ግሩም አድርጎ ሲተርካቸው ደግሞ ተቀባይነታቸው እያደገ ሔደ።

ይህ “የቡና ቤት ስዕሎችና ሌሎችም ወጎች” የተሰኘው የመስፍን መፅሐፍ እንደታተመ የመግቢያ አስተያየት የሰጠው ታዋቂው የሥነ-ፅሁፍ ሊቅ እና ባለቅኔው ደበበ ሰይፉ ነበር። ደበበ በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እጅግ ታዋቂ መምህር ከመሆኑም ባሻገር የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርንም በፕሬዚዳንትነት ይመራ ነበር። እናም ስለ መስፍን መፅሐፍ የሚከተለውን ብሎ ነበር፡-

“በዚህ መፅሐፍ ውስጥ መስፍን መልካም የሚባሉ ወጎችን አቅርቦልናል። የሚወያይባቸውን ጉዳዮች በሚገባ ከማወቁ ጋር በጉዳዮቹ መነሾነት ወደ ወጎቹ የገቡትን ሰዎች ድርጊትና አባባል በብሩህ አእምሮ እንዳስተዋለውና እንደተረዳውም ሊያስገነዝበን የቻለ ይመስለኛል። በድክመታቸው ሳያመር እኛን ተደራሲያኑንም ሳያስመርር በግርምት ትንሽ ጠንከር ሲልም ለትዝብት ያህል ብቻ ስቀን ተቀብለን ስቀን እንድንሸኛቸው ያደርገናል። ይህ በራሱ ቀላል አይደለም።”

ሲል ደበበ ሰይፉ ስለ መፅሐፉ መግቢያ ፅፎለታል።

መስፍን ሐብተማርያም እና ደበበ ሰይፉ የቅርብ ጓደኛሞች ነበሩ። ደበበ ሰይፉ ሚያዚያ 16 ቀን 1992 ዓ.ም ከዚህ ዓ.ም በሞት እንደተለየ ተክቶ ታደሰ የሚባል የሥነ-ፅሁፍ ተማሪ ለድግሪ መመረቂያ ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ የጥናት ወረቀት ማዘጋጀት ነበር። እናም ተክቶ ያዘጋጀው የመመረቂያ ጽሁፉ በባለቅኔው ደበበ ሰይፉ ህይወትና ሥራዎች ዙሪያ ያጠነጠነ ነበር። በወቅቱ ለጥናት አቅራቢው ለተክቶ ታደሰ፣ ስለ ደበበ ሰይፉ ስራ እና ማንነት ሰፊ መረጃ የሰጠው መስፍን ሐብተማርያም ነበር። መስፍን ስለ ደበበ ሲናገር፣ የፈጠራ ሰው /Innovative/ ነበር ይለዋል።

መስፍን ሐብተማርያም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርነቱ በ1976 ዓ.ም በገዛ ፈቃዱ መልቀቁን ይናገራል። ከዚያ በኋላ ግን ህይወት ብዙም የተመቸው ሰው አልነበረም። የህይወት ውጣ ውረዶች ምስቅልቅሎች አጋጥመውታል። ግን እሱ በነዚህ ሁሉ የህይወት ጫናዎች ውስጥ ሆኖ ፍካትን፣ ደስታን፣ ሳቅን፣ ጨዋታን የሚያዘወትር ሰው ነበር። ግን መስፍኔ ለምን ከዩኒቨርስቲ ለቀቀ?

በ1993 ዓ.ም ሚኪያስ ጌታቸው የሚባል የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ-ፅሁፍ ተማሪ የመመረቂያ ጽሁፉን ያዘጋጀው፣ የደራሲ መስፍን ሐብተማርያም የህይወት ታሪክ እና የወግ ሥራዎቹ በሚል ርዕስ ነበር። ታዲያ በዚህን ጊዜ ሚኪያስ ጌታቸው ለመስፍን አንድ ጥያቄ አቅርቦለት ነበር። ይህም ከዩኒቨርስቲ መምህርነትህ ለምን ለቀቅክ? የሚል ነበር። መስፍንም ሲመልስት የሚከተለውን ብሏል፡-

“ በኢትዮጵያ ሬዲዮም፣ በኩራዝ አሳታሚ ድርጅትም እሰራ የነበረው በዩኒቨርስቲ ስራዬ ላይ ደርቤ ነበር፤ እናም እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ጊዜዬን ተሻሙብኝ። ጥሩ በማስተማር አምናለሁ በቂ ዝግጅት በማድረግም፤ እናም ያኔ በዚህ ላይ በጣም እጠጣ ነበር። አልኮል የሚበቃኝ ሰው አልነበርኩም። እናም እራሴን መጣል ጀመርኩኝ። በዚህ የተነሳ የማስተማር ስራዬን በገዛ ፈቃዴ በ1976 ዓ.ም ባስገባሁት ማመልከቻ መሰረት ለቀኩኝ።”

በማለት መስፍን ተናግሯል።

ከዩኒቨርስቲ በኋላም የተለያዩ መስሪያ ቤቶችና ተቋማት ውስጥ በግሉ ሲሰራ ቆይቷል።

መስፍን ሐብተማርያም ገና ከተማሪነት ህይወቱ ጀምሮ ከ1951-1960 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይቀርቡ የነበሩ “የኮሌጅ ቀን ግጥሞች” ውስጥ ተሳታፊ እንደነበር ገዛኸኝ ፀጋው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ባዘጋጀው መድረክ ላይ በአንድ ወቅት ገልጿል። እንደ ገዛኸኝ አባባል መስፍን በዘመኑ የሚያቀርባቸው ግጥሞቹ ወጣቶች በብዕር ያደርጉት የነበረውን የትግል አቅጣጫ ወደ ሌላ የመራ እንደሚመስለው ተናግሯል።

መስፍን ሐብተማርያም በብዙዎች ዘንድም በጣም ተወዳጅ ሰው ሆኖ ያለፈ ነው። የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበርም የዛሬ አራት አመት 65ኛ የልደት በዓሉን በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በደማቅ ሥነ- ሥርዓት አክብሮለታል። አንጋፋው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርም ለመስፍን ክብር ሲባል የተለያዩ መድረኮችን አዘጋጅቶለታል።

ትናንት በተፈፀመው የዚህ ታላቅ ደራሲ ስርዓተ ቀብር ላይ የሕይወት ታሪኩን ያነበቡት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ ሲሆኑ እርሳቸውም ስለ ደራሲው ሲገልፁ በዚያ በወታደራዊው ዘመን እና የአንድ ርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ በሚንፀባረቅበት ወቅት፣ መስፍን ሐብተማርያም አንባቢያንን እያሳቀ፣ እያዝናና እያስተማረ ለትውልድ ውለታ የዋለ ደራሲ መሆኑን ተናግረዋል።

መሰፍን ሐብተማርያም ከመጀመሪያ መፅሐፉ በተጨማሪም አውዳመት፣ የሌሊት ድምፆች፣ አዜብና ሌሎች አጫጭር ድርሰቶችን አሳትሟል። በወግ አፃፃፍ ስልቱ ለኢትዮጵያ ሥነ ፅሁፍ በር የከፈተ ፊት አውራሪ ደራሲ ነበር።

መስፍን ሐብተማርያም የሁለት ወንዶችና የአራት ሴት ልጆች አባት እንደነበረም የህይወት ታሪኩ ይናገራል። የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም በዚህ አንጋፋ የወግ ፀሐፊና ተራኪ ሞት የተሰማውን ሐዘን እየገለፀ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ ለቤተሰቡም መፅናናትን ይመኛል።

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
9869 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us