የክብር ዶክትሬቱ እና ሽልማቱ እንዴት? ወደየት?

Wednesday, 23 July 2014 17:14

ከሰሞኑ በሀገራችን ውስጥ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለዓመታት ያስተማሯቸውን ተማሪዎች ሲያስመርቁ እንደሰነበቱ ሁላችንም የምናውቀው ሐቅ ነው። ከምረቃ ሥነ-ሥርዓታቸው ጐን ለጐን ደግሞ የክብር ዶክትሬት ድግሪ ይገባቸዋል ብለው ላመኑባቸውም ግለሰቦች ካባውን አጥልቀውላቸዋል። ሰፊ የሚዲያ ሽፋንም አግኝተውበታል። ይሁን እንጂ ይህ የክብር ዶክትሬት ድግሪው ጉዳይ አሳሳቢና አንገብጋቢ ሆኖ የታየበት ሁኔታም በመታየቱ፣ በመከሰቱ ጉዳዩን በዛሬ ጽሁፌ ልዳስሰው ወደድኩ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ለማኅበረሰባቸው እና ለሀገራቸው ታላላቅ ተግባራትን ያከናወኑ ጐምቱ ግለሰቦችን ማበረታታት፣ ያበረከቱትን ትልልቅ አስተዋፅኦ እያነሳሱ ለትውልድ አርአያ የሚሆኑበትን መንገድ የሚከፍት ተቋም የለም ማለት ይቻላል። ታላላቅ ሰዎቻችንን የምንሸልምባቸው ለትውልድ የከፈሉትን መስዋዕትነት የምንዘክርበት የተመቻቸበት ሁኔታ ፈጽሞ የለም ማለት ይቻላል።

በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት በሙያቸው አንቱ የተባሉ ሰዎች በትልቅ ሥነ-ሥርዓት ከንጉሡ እጅ የብር እና የሠርተፊኬት ሽልማቶችን ሲቀበሉ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። ሽልማቱም በወቅቱ ትልቅ እንደነበር እና የተሸላሚዎቹንም ህይወት በመጠኑ እንደሚቀይር ይነገራል። ከዚሁ ጐን ለጐን ደግሞ እውቅናው በራሱ ትልቅ ጥቅም ነበረው። እናም ይህ በጐ ጅምር ብዙም ሳይጓዝ ደርግ “ቲሪሪም ቲሪሪም” እያለ መጣ። “ስር ነቀል” አዋጅ አወጣ። ኢትዮጵያ ትቅደም፣ አቆርቋዧ ይውደም! ቡርዣዎች፣ ፊውዳሎች፣ የመሬት ከበርቴዎች ይውደሙ! ብሎ ፎከረ። እናም በወቅቱ እንኳን ስለ ሽልማት ሊወራ ይቅርና ጉዞው አብዮት ሆነ። አዲሲቷ ኢትዮጵያ በአብዮት ማዕበል ተዋጠች።

በኋላ ደግሞ ነገሮች እየረገቡ፣ ውጥረቶችም ቀዝቀዝ የማለት ነገር ሲመጣ በስነ-ግጥም ውድድር ያሸነፉ፣ በስዕል ውድድር ያሸነፉ ወዘተ እየተባለ ትንንሽ ሽልማቶችን እና ወታደራዊ ኒሻኖችን የመሸለም እንቅስቃሴ መጣ። ያ እንቅስቃሴ ደግሞ በወቅቱ ለነበረው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የሚያግዙ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎችን መሸለም ላይ ያተኮረ ነበር። ለታላላቅ ፍልስናዎች፣ ለታላላቅ አመለካከቶች፣ የሰውን ልጅ ህይወትና የኑሮ መንገዶችን ለሚቀይሱ አርቆ አሳቢዎች፣ የራሳቸውን ግላዊ ህይወት ትተው ለማኅበረሰቡ ህይወት መቀየር ሌት ተቀን የሚዋትቱትን ሰዎች የመሸለሙ የማክበሩ ሁኔታ በእጅጉ የተቀዛቀዙበት ወቅት ነበር። የሚያሸልመው ለአብዮቱ ምን ሰራህ? ምን ሰራሽ? የሚለው ትልቁን ቦታ የያዘበት የታሪክ አጋጣሚ ታይቶ አልፏል።

በዘመነ ኢሕአዴግ ደግሞ የሽልማት ነገር ብዙ መልክና ፈርጅ ይዞ መጣ። ምክንያቱም ሽልማት ወጥነት ያጣ እና መልከ ብዙ ሆኖ መጣ። ለምሳሌ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ገበሬዎችን ሲሸልሙ መዋል የአንድ ወቅት ክስተት ሆኖ ታየ። ገበሬዎች ተሸልመው አያውቁም፣ አርሶ አደሩ ተረስቷል፣ ለዘመናት አልተሸለመም በሚል በሺዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎች ሲሸለሙ የሚውሉበት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። መቼም እንዲህ አይነት አሸላለም ደግሞ ግራ ማጋባቱ አይቀርም። ሽልማት የሚባለውን ነገር ረከስ ያደርገዋል። ምክንያቱም ሽልማት ማለት ከማኅበረሰቡ ውስጥ ነጥረው የወጡ ጥቂቶችን ትኩረት ያደረገ እንጂ ለሁሉም መሸለም አሰልቺነቱም ጐልቶ ይታይ ነበር።

በዚሁ በእኛ ዘመን ውስጥ የአሸላለም ስርዓቱም ወጣ ገባ የሚል እና ቋሚነት የሌለው ሆኖ የታየበትም ክስተቱ ተፈጥሯል። በአንድ ወቅት ብሔራዊ የሽልማት ኮሚቴ ተቋቋመ ተብሎ እና አስናቀች ወርቁን፣ ሙሉአለም ታደሰን እና የመሳሰሉት ሰዎች የተሸለሙበት ሁኔታ ተከስቶ ነበር። ይህ የሽልማት ድርጅት በብሔራዊ ደረጃ መጣ ተብሎ ብዙዎች ተደስተው ነበር። ነገር ግን ይህም ድርጅት አንድ ሽልማት ሰጥቶ ብን ብሎ ጠፋ። በታሪክ ውስጥም ተወቃሽ ሆኖ አልፏል።

ይህን የሽልማትን ክፍተት ያዩ ትንንሽ የግል ተቋማት ደግሞ ሽልማት እንስጥ እያሉ በየጊዜው የሚነሱበትም ክስተት ተፈጥሯል። በፊልም፣ በቴአትር፣ በሥነ-ጽሁፍ ወዘተ ሽልማት እንስጥ የሉና አንዴ ሰጥተው የሚከስሙ ተቋማት በርካቶች ናቸው። እነዚህ የግል ተቋማት ደግሞ በብዙ ችግሮች የተተበተቡ ናቸው። አንደኛው አደረጃጀታቸው ግለሰባዊ አመለካከት ላይ ብቻ ያተኮሩ በመሆናቸው፣ የአቅም እና የፋይናንስ ውስንነት ያለባቸው በመሆናቸው ብሎም ቁርጠኝነትና ዘላቂነትን ይዘው ባመነሳታቸው ብቅ ብለው ጥፍት ማለትን የለመዱ ናቸው። ከመንግስት አካልም ድጋፍ የሚያደርግላቸው የለም።

ሀገር ውስጥ ሽልማት ሲጠፋ ከወደ ውጭ ሀገር ሽልማት አገኘን ብለው የሚመጡ ሰዎችም በረከቱ። አነዚህ ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸለምን ብለው በሀገራቸው ማኅበረሰብ ላይ ልዩ መሆናቸውን ለማሳየት ትልቅ ጥረት አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛሉ። ማዕረጋቸው ደግሞ “እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት….” የሚል ሆነ። ግማሹ በስዕል ስራዬ ተሰጠኝ ይላል፤ ግማሹ ደግሞ ባልተለመደ ሁኔታ በህክምና የተሰጠኝ ነው ይላል። ነገሩን ስንመረምረው ግን ብዙ አስገሪሚ ጉዳዮችን በውስጡ የያዘ ነው። አሁን አሁን ደግሞ “ሎሬት” ተብያለሁ የሚሉ የሕግ ባለሙያም ብቅ ብለዋል። ስለሎሬት ማዕረግ ምንነት እና አሰጣጥ ወደፊት ሰፋ ያለ ነገር ለማቅረብ እሞክራለሁ።

የሽልማት ጉዳይ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ባለበት ዘመን ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ደግሞ የክብር ዶክትሬት ድግሪ መስጠት ጀመሩ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለውጭ ሀገር ዜጐች እና ለኢትዮጵያዊያንም የክብር ዶክትሬት በመስጠት ፈር ቀዳጅ ሆኖ ብቅ አለ። ሽልማቱ የሚሰጣቸው ሰዎች ለሀገራቸውና ለወገናቸው ብዙ የሰሩ ሰዎችን መርጦና አንጥሮ የሚያወጣ ነው ይባላል። ጉዳዩም ለሴኔት ቀርቦ ከፀደቀ በኋላም የሚሰጥ እንደሆነ ይገለፃል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከውጭ ሀገር እያስመጣቸው የክብር ዶክትሬት ድግሪ የሚሰጣቸው ሰዎች የአመራረጥ መስፈርቱ ምንድን ነው? ሰዎቹ ከኢትዮጵያ ጋር ባላቸው ግንኙነት ነው ወይስ ለራሳቸውና ለተወለዱበት ሀገር ላበረከቱት ውለታ ነው? እየተባለ ሲጠየቅ ቆይቷል፤ እስከ አሁን ግን መልስም ያላገኘ ነገር ነው። ወደ ሀገር ውስጥም ስንመጣ ጅማሮው ጥሩ ነበር። እርስ በርስ የሚጣረሱ ጉዳዮችም አሉበት። ለምሳሌ በአንድ ወቅት በሥነ-ጽሁፍ ችሎታቸው አንቱ የተባሉትን ሐዲስ አለማየሁን እና ከበደ ሚካኤልን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል። ሐዲስ አለማየሁ ሽልማቱ በሚሰጣቸው ቀን ተቆጥተዋል። ምክንያቱ ደግሞ ሽልማቱ በተሰጣቸው ወቅት በጣም አርጅተዋል፣ መንቀሳቀስ አይችሉም። አቅም የላቸውም። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሄድ አይችሉም። ዶክተሬቱ የተሰጣቸው እቤታቸው ድረስ ተሒዶ ነው። በወቅቱ ሀዲስ ተቆጡ። “ከደከምኩ በኋላ ነው ወይ የምትሰጡኝ? በደህና ጊዜ አቅም ባለኝ ወቅት ብትሰጡኝ ጥሩ ነበር” አሉ ሀዲስ። ግን ዩኒቨርሲቲው አክብሮ ስለሰጣቸው ታላቁን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የከበደ ሚካኤል ጉዳይ ላይ ጥያቄ ያስነሱ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ ከበደ ሚካኤል በስነ-ጽሁፍ ዓለም ውስጥ ለትውልድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም በሌላ መልኩ ደግሞ ሰውዬው ለኢጣሊያ ወራሪዎች ያደሩ ባንዳ እንደነበሩ ይታወቃል። ሀገር በጠላት ስትወረር ከወራሪ ጋር ሆነው ሀገራቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። ስለዚህ የክብር ዶክትሬቱ አይገባቸውም የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ነበሩ፤ አሁንም አሉ።

ታላቁ ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ እና ወ/ሮ ንጋቷ ከልካይም የክብር ዶክትሬት ድግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተሰጣቸው ሥነ-ሥርዓትም ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው። ጥላሁን ገሠሠ ስለተሰጠው ምንም አይነት ቅሬታ ጐልቶ አልወጣም ነበር። ምክንያቱም ይገባዋል፣ የሚል አስተያየት ስለነበር ነው። ጥያቄው የመጣው ግን ወ/ሮ ንጋቷ ከልካይ የተሸለሙበት አግባብ በደንብ የተመረመረ አይደለም የሚሉ አስተያየቶች በወቅቱ ተሰንዝሯል። የንጋቷ ከልካይ የሙዚቃ አበርክቶ፣ ሲደመር የኢጣሊያ ወረራ በሚል ቢታይ፣ ቢመረመር ጥሩ ነበር ይላሉ ጉዳዩን የታዘቡት አስተያየት ሰጪዎች።

የክብር ዶክትሬት ጉዳይ እንዲህ እያለ ወደ ሌሎችም የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች መዛመት ጀመረ። ዩኒቨርሲቲዎቹ በየክለሉ የሚገኙ ስለሆነ ክልላዊም የሆነ አደረጃጀት አላቸው። ለምሳሌ ለኦሮምኛ ቋንቋ ሙዚቃ ከፍተኛ ውለታ የዋለው አሊ ቢራ ኦሮሚያ ውስጥ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ድግሪ ሰጥቶታል። በቅርቡ ደግሞ የጐንደር ተወላጅ የሆነችው ታላቋ ድምፃዊት አስቴር አወቀን፣ ጐንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷታል። መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የዛሬ 94 ዓመት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የትግራይ ተወላጅ ለሆኑት ለነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ የክብር ዶክትሬት ድግሪ ሰሞኑን ሰጥቷል። ጉዳዩ ክልላዊ አስተሳሰብም እየያዘ የመጣም ይመስላል። አስቴርን የኦሮሚያ ዩኒቨርሲቲ ቢሸልማት፣ ዓሊ ቢራን የጐንደር ዩኒቨርሲቲ ቢሸልመው እና ገብረ-ሕይወት ባይከዳኝን ደግሞ የጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ ቢሸልመው ጉዳዩ ኢትዮጵያዊኛ በሆነ ነበር።

በዚህ ዘመን ሌላ አንድ አሳፋሪ እና አስቀያሚ ነገርም ተከስቷል። ሳሙኤል ዘሚካኤል የሚባል አጭበርባሪ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን እየበረጋገደ በመግባት ለመምህራንና ለተማሪዎች ንግግር እያደረገ፣ ስልጠና እሰጣችኋለሁ እያለ ሲያጃጅላቸው የቆየበትንም ክስተት መዘንጋት የለብንም። ዩኒቨርሲቲዎቻችን ራሱን ሳሙኤል ዘሚካኤልን መስለው የቆዩበት የታሪክ አጋጣሚም ተከስቷል። “ዶክተር ነኝ፣ ኢንጂነር ነኝ” ብሎ አፋቸውን አስከፍቶ ሲጫወትባቸው የቆየ ነው። እናም ይህ የሚያሳየው ዩኒቨርሲቲዎቻችን ከፍተኛ የሆነ ችግር በውስጣቸው ያለ መሆኑን ነው። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለሳሙኤል ዘሚካኤል የክብር ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሁሉ የሰጠበት አሳፋሪ ክስተትም ገጥሟል። እናም ከነዚህ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ውስጥ የክብር ዶክትሬት ማግኘት በራሱ የሚያስደስትም አይደለም። የራሳቸው ክብር በወረደበት ወቅት እነርሱ የክብር ዶክትሬት መስጠታቸው አያኮራም። ያጠራጥራል።

ዘንድሮ የተሰጡትን የክብር ዶክትሬቶች ጉዳይ ላነሳሳና የዛሬውን ጽሁፌን ልቋጨው። ከጐንደር ልጀምር። ጐንደር ዩኒቨርሲቲ አቶ ተፈራ ዋልዋን ጨምሮ ለአስቴር አወቀም የክብር ዶክትሬት ድግሪ ሰጥቷል። አቶ ተፈራ በዝና ሳውቃቸው ምክንያታዊ ናቸው ይባላል። አለአግባብ አንድ ነገር ሲደረግ ሲያዩ ይሄ ለምን እንዲህ ሆነ ብለው የሚያፋጥጡ ናቸው ይባል ነበር። የጐንደር ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ሁሉ የትግል ጓደኞቻቸው በተለየ ሁኔታ እርሳቸውን መርጦ የክብር ዶክተር ሆነዋል ሲላቸው ዝም ማለታቸው አስገርሞኛል። ስለ እርሳቸው የሰማሁትን ሰብዕናቸውን የሚፃረር ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ለአስቴር አወቀም የተሰጠው ዶክትሬት አነጋጋሪ ነው። አስቴር አወቀም ሆነች ቤተሰቦቿ የሽልማቱ ቀን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አልተገኙም። ምናልባት በሽልማቱ አላመኑበትም ይሆን? ከሁሉም በላይ ግን ጐንደር ዩኒቨርሲቲ ለአስቴር አወቀ ሲሸልም ከድምፃዊያን ሁሉ በላይ አድርጓት ነው። እርግጥ ነው አስቴር በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ደረጃዋ የላቀ ነው። ግን ከማን ጋር ነው የተወዳደረችው? መስፈርቱ ምን ነበር? አስቴር ለሀገሯ፣ አስቴር ለማኅበረሰቧ ምን አደረገች? ምን አስተዋፅኦ ነበራት? አስቴር ከህዝቧ ጋር ምን አይነት ግንኙነት አላት? በሚሉትና በሌሎችም ጉዳዮች መፈተሽ ነበረበት። ለምሳሌ አስቴርና መሐሙድ አህመድ ተወዳድረዋል? መሐመድን የሚያክል የድምፃዊያን ቁንጮን ረስቶ ሌላ ድምፃዊን መሸለም በራሱ ተገቢ ነው? 50 ዓመታት ሙሉ ከመድረክ ሳይወርድ፣ የህዝቡን ሐዘኑንም ደስታውን አብሮ ሲጋራ የነበረን ድምፃዊ ገሸሽ ማድረግስ ከዩኒቨርሲቲዎቻችን ይጠበቃል?

ደግሞ ወደ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ እንሒድ። መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የዛሬ 94 ዓመታት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝን የክብር ዶክትሬት ሰጥቷቸዋል። ይሄ ጉዳይ ያልተለመደ ቢሆንም ጥያቄዎችን ግን ያስነሳል። ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው፣ ብዙ ስራ ሰርተው ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩት ሰዎች መካከል ገብረህይወት ባይከዳኝ እንዴት ተመረጡ? ከሙታን መካከል እርሳቸውን ለመምረጥ መነሻው ምንድን ነው? መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ሙታንን መሸለም ከጀመረ የቱ ጋ ነው የሚያቆመው? ከየትስ ነው የሚጀምረው? ብዙ ጥያቄዎች አሉት። ነገ ደግሞ እነ ሉሲን (ድንቅነሽን) መሸለም አለብን የሚል ዩኒቨርሲቲም ሊመጣ ይችላል።

ኢትዮጵያ የብዙ ታላላቅ ሰዎች እዳ የበላች ናት ይላል አንድ ወዳጄ። ለዚህች ሀገር ብዙ ሰርተው፣ ህይወታቸውንም ሰጥተው ያለፉ ብዙ ናቸው። ባለዕዳ የሆነች ሀገር ናት። አልሸለመቻቸውም። ግን ከሞቱ በኋላ “ዶክተር” ማለት ከጀመርን ከገብረህይወት ባይከዳኝ ጀምረን ወደየት ነው የምንሄደው? ሐገሪቱ ያልከፈለችውን የልጆቿን ዕዳ ለመክፈል ከፈለገች ብዙ አማራጮች አሉ። ለምሳሌ በገብረህይወት ባይከዳኝ ስም አንድ ኮሌጅ ቢከፈት፣ በዮፍታሔ ንጉሴ ስም፣ በተመስገን ገብሬ ስም፣ በበዓሉ ግርማ ስም፣ በአቤ ጉበኛ ስም፣ በብርሃኑ ዘሪሁን ስም፣ በአፈወርቅ ተክሌ ስም፣ በፀጋዬ ገ/መድህን ስም፣ በአክሊሉ ለማ፣ በጌታቸው ቦሎዲያ ወዘተ ወዘተ ስሞች ዘላለማዊ ማስታወሻዎችን ልንሰይምላቸው ሐውልቶችን ልንቀርጽላቸው እንችላለን። በነገራችን ላይ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ በህይወት የሌለን ሰው ማስታወሱ፣ መሸለሙ የሚያስደንቀው ቢሆንም ከላይ በዘረዘርኳቸው መንገዶች ሊያስታውሳቸው ቢሞከር ደግሞ የተሻለ ነበር።

በሩጫውም ዓለም መሠረት ደፋርና ጥሩነሽ ዲባባ የተሸለሙበት ዓመት ነው። አሁንም ጉዳዩ ለጭቅጭቅ ክፍት ሆኗል። ኢትዮጵያ ሌሎችም ተአምረኛ አትሌቶችን ያፈራች ነች። እነርሱስ ሲዘለሉ አያሳፍርም። እነዚህን አትሌቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁ ሆነው እንዲወጡ ብዙ የማሰኑ አሰልጣኞች ሁሉ እፊታችን ድቅን ይሉብናል።

በመጨረሻም ማንሳት የምፈልገው ዩኒቨርሲቲዎቻችን እንዲህ ዓይነት የሰው ምርጫ ውስጥ ሲገቡ ብዙ ነገሮችን ማየት መመርመር ይገባቸዋል። ከዩኒቨርሲቲ ውጭ ያሉ ባለሙያዎችንም አካተው ጥናትና ምርምር አድርገው መሸለም የሚገባውን ሰው አንጥረው ማውጣት መቻል አለባቸው። ካለበለዚያ ትልቁ ማዕረግ እየረከሰ፣ እየረከሰ እንዳይመጣ ያሰጋል።   

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
11893 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us