የአሜሪካ ታሪክ ፀሐፊዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሞተውን ዜጋቸውን አፋልጉን ይላሉ

Wednesday, 30 July 2014 12:28

በድንበሩ ስዩም

 

 

ጆን ሮቢንሰን

 

 

የአሜሪካ ታሪክ ፀሐፊዎች ወደ ኢትዮጵያ መመላለስ ከጀመሩ ቆይተዋል። ምክንያቱም አንድ ዜጋቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ፣ እዚህችው ኢትዮጵያ ውስጥ ሞቶባቸዋል። ግን አስከሬኑ ያረፈበት ቦታ የቱጋ እንደሆነ እስከ አሁን ሊያውቁ አልቻሉም። የሚጠቁማቸውንም አጥተዋል። ለሚጠቁማቸው ደግሞ ተገቢውን ወሮታ እንደሚፈጽሙም ይናገራሉ።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ደግሞ በቅርቡ በፋና ኤፍ ኤም 98.1 ሬዲዮ ጣቢያ በአዲስ ጣዕም የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ሰውዬው (አሜሪካዊው) በጣም ወዳጄ ነበረ፤ ከአሜሪካ ቢመጣም ዘሩ ግን ከኢትዮጵያ ነው። እዚህ ኢትዮጵያ ውሰጥ ያሉትን የእሱን ቤተሰቦች ሁሉ በአንድ ወቅት እንዲገናኙ አድርጌያቸዋለሁ፤ ሰውየው የቅርብ ወዳጄ ነው፤ ይላሉ። ለመሆኑ ይህ አሜሪካዊ ማን ነው? የአዲስ ጣዕም የሬዲዮ ዝግጅትን ዋቢ አድርጌላችሁ ዛሬ ስለዚሁ አሜሪካዊ ጉዳይ አጫውታችኋለሁ።

በአሜሪካ ውስጥ ባሉ ጥቁሮች በሙሉ ስሙ እና ዝናው ሁሌም ይነገራል። ይህ ሰው ራሱን በራሱ ያስተማሪ የመጀመሪያው ጥቁር አውሮፕላን አብራሪ እንደሆነ ይነገርለታል።

በአሜሪካ ውስጥ ጥቁር ሆኖ የራሱ የአውሮፕላን በረራ ት/ቤት የከፈተ ፓይለት ነው። የራሱ የሆነ የአውሮፕላን ማረፊያ ያለው እንደነበረም ይነገርለታል። በኑሮውም በወቅቱ በአሜሪካ ውስጥ ከነበሩ ጥቁሮች የተሻለ እንደነበርም የሕይወት ታሪኩን የሚመራመሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ይህ ሰው ኮ/ል ጆን ሮቢንሰን ይባላል። ሰውየው አስገራሚ የሆነ የሕይወት ታሪክ አለው። ኮ/ል ጆን ሮቢንሰን በ1920ዎቹ ዓመታት ውስጥ ከአሜሪካን ሀገር ቴስቲግያን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በቴክኖሎጂ ኢንጂነሪንግ ይመረቃል። ከዚያም ከፍተኛ የሆነ የአውሮፕላን አብራሪነት ፍቅር ያድርበታል።

አብራሪ ለመሆን ደግሞ የቆዳ ቀለሙ ጥቁር በመሆኑ እና በወቅቱ በአሜሪካ ውስጥ ጥቁሮች ለእንደዚህ ላለ ትልልቅ ትምህርት ተቀባይነት የላቸውም ነበር። የበረራ ት/ቤቶች ሁሉ ቢያመለክት አልቀበልህም አሉት።

ተቀባይነት ቢያጣም ተስፋ አልቆረጠም፤ ጆን ሮቢንሰን። በመጨረሻም አንድ ዘዴ ፈጠረ። ዘዴው ደግሞ ወደ አውሮፕላን በረራ ት/ቤት የሚያስገባውን መንገድ በቀጭኑ የሚከፍትለት ነበር። ጆን ሮቢንሰን በአሜሪካ ውስጥ በሚገኘው የአውሮፕላን በረራ ት/ቤት ውስጥ በጽዳት ሠራተኛነት ተቀጠረ።

ይህ ሰው በቴክኖሎጂ ኢንጂነሪንግ ትምህርቱ ድግሪ እያለው በጽዳት ሰራተኛነት የተቀጠረው ለአውሮፕላን በረራ እውቀት ያለውን ትልቅ ፍቅር ለመግለጽ እና ቀረብ ብሎም ለማየት ነበር።

ታዲያ ነጭ ተማሪዎች ብቻ በበዙበት በዚህ ት/ቤት ጆን ሮቢንሰን ጥቁር የጽዳት ሠራተኛ ሆኖ ተማሪዎች በሚማሩበት ክፍል ጠጋ እያለ የሚማሩትን በአንክሮ ያዳምጣል። ያዳመጠውን ደግሞ በተለያዩ ቁርጥራጭ ወረቀቶች ላይ እየፃፈ ማስታወሻ ያስቀምጣል። ነጭ ተማሪዎች የሚጥሏቸውን ጽሁፎችና መፃህፍትም እየሰበሰበ ያነባል።

መቼም ከዚህ ሁሉ ጉዳይ በኋላ አንድ ተአምር የሚፈጠር ይመስላል። ይህ ሰው ቀደም ብሎ የተማረው የሜካኒካል እና የቴክኖሎጂ ኢንጂነሪንግ ትምህርት ተደምሮበት የአውሮፕላን አብራሪነትን የቲዎሪ ትምህርት ተማረ። የአብራሪነቱን ትምህርት ሲማር ማንም አላየውም። ተደብቆ ጨረሰው።

በመጨረሻ ግን አንድ ነገር ተፈጠረ። ጆን ሮቢንሰን የቴክኖሎጂ ትምህርቱን እና የበረራ ትምህርቱን ሲያቀናጀው ለአውሮፕላን በረራ የሚያገለግሉ ነገሮች ሁሉ መፍጠር ጀመረ። ይህንንም በተግባር አሳየ።

ከዚህ በኋላ የበረራ ትምህርት ፈተና ላይ እንዲቀመጥ ተደረገ። በዚህ ትምህርቱም ውጤታማ ሆኖ ተደነቀ። ተወደሰ። ራሱን በራሱ አስተምሮም የአውሮፕላን አብራሪ እና የአውሮፕላን ቴክኒሽያንም ሆኖ በአሜሪካ ውስጥ ገናን ሆነ።

ጆን ሮቢንሰን በመጨረሻም አንድ ነገር አሰበ። ጥቁሮች የበረራ ትምህርት የሚማሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለብኝ ብሎ ተነሳ።

የጆን ሮቢንሠንን ታሪክ በተለያዩ ሀገሮች እየተዘዋወረ በማጥናት ላይ የሚገኘው አፍሪካ አሜሪካዊው የታሪክ ተመራማሪ የሆሽኋ እስራኤል በአሁኑ ወቅት እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ይገኛል። ይህ የታሪክ ተመራማሪ ሲናገር፤ ጆን ሮቢንሰን በአሜሪካ ውስጥ የሚገኘውን የተስቴጂን የአየር ኃይልን የመሠረተ እና የአየር ኃይሉም አባት ነው ይለዋል።

እንደ ሆሽኋ ገለፃ ጆን ሮቢንሠን በርካታ የጦር አውሮፕላን አብራሪዎችን በአሜሪካ ውስጥ አስተምሯል። እርሱ ያስተማራቸው አብራሪዎች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚ ላይ የተካሄደውን የአውሮፕላን ድብደባ የመሩ ናቸው። ለአሜሪካ ትልቅ ውለታ የዋሉ አየር ኃይሎች የዚህ ሰው ተማሪዎች መሆናቸውን ይናገራል።

በአሜሪካ ውስጥ እንዲህ ታዋቂ የሆነ የበረራ ሊቅ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥቶ እንደ ሞተ እና እዚህም እንደተቀበረ ይነገራል። ለመሆኑ ኮ/ል ጆን ሮቢንሠን ወደ ኢትዮጵያ ለምን መጣ? ለምን ሞተ? የት ተቀበረ? የሚሉትና ሌሎችም ጉዳዮች የዛሬ መነጋገሪያ አጀንዳዎቻችን ናቸው።

ኮ/ል ጆን ሮቢንሰን የጥቁር ህዝቦችን ጭቆና እና መከራ የሚከላከል፣ ለጥቁሮች መብት መከበር የቆመ ነበር። ታዲያ በአንድ ወቅት ዶ/ር መላኩ በያን የተባሉ በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሐኪም በመሆን የተመረቁት፣ ወደ ጆን ሮቢንሰን ዘንድ ይሄዳሉ። ወቅቱም 1927 ዓ.ም ነበር። ከዚያም አንድ ነገር ነገሩት።

“ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ልትወረር ነው። ኢጣሊያ ብዙ ዝግጅት እያደረገች ነው። ስለዚህ አንተም የተቻለህን እርዳን” ይሉታል።

ከዚያም በመለጠቅ ጥቁር የሆኑ ህዝቦች ሁሉ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የምታካሂደውን ወረራ እንዲቃወሙ ጥሪ ተላለፈ ።

ጆን ሮቢንሰን ግን የተለየ ነገር አደረገ። የበረራ ማሰልጠኛ ት/ቤቱን ዘጋው። ስራውን አቆመ። አውሮፕላኖቹንም አቆማቸው። ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጐ ወደ ኢትዮጵያ መጣ ይላል የታሪክ ተመራማሪው ሆሽኋ እስራኤል።

ኢትዮጵያ ሲመጣም የሀገሪቱን ድንበር የኢጣሊያ ፋሽስቶች ሰብረው እየገቡ ነበር። ወራሪዎቹ ከምድር ውጊያ ይልቅ በሰማይ እየበረሩ በአውሮፕላን ከፍተኛ ድብደባ ያደርጋሉ። የመርዝ ጋዝ ጣሉ። ህፃናትና ሴቶችን፣ አዛውንቶችን፣ ወጣቶችን ፈጁ። በአውሮፕላን ድብደባ ከፍተኛ ግፍ ሲፈፀም ጥቁር አብራሪው ጆን ሮቢንሰን ተመለከተ።

እሱም በሙያው ኢትዮጵያን ሊያገለግል፤ በአውሮፕላን እየበረረ አፀፋዊ ምላሽ ሊሰጥ አሰበ። ኢትዮጵያ በወቅቱ የነበሯት አውሮፕላኖች ለጦርነት የማያገለግሉ፣ መሣሪያ የማይዙ እና እጅግ ደካሞች ነበሩ። በዚህ የተነሳ ያሰበው ሊሳካ አልቻለም። በኋላ ሌላ ዘዴ ጠየቀ። ለጦርነት የሚያገለግሉ አውሮፕላኖች እንዲመጡ ጠየቀ። ነገር ግን በወቅቱ ለሁለቱም ሀገሮች ምንም አይነት የጦር መሣሪያ እንዳይሸጥ ፍርድ ስለተሰጠ የጦር አውሮፕላኑም ሊመጣ አልቻለም። ኢጣሊያ ግን የጦር አውሮፕላን ራሷ ስለምታመርት እንደልቧ እያመጣች በኢትዮጵያ ላይ ውድመት አስከተለች።

ንጉሡም ተሠደዱ። ጆን ሮቢንሰንም በልዩ ልዩ የጦር ግንባሮች እየተገኘ የተቻለውን ቢያደርግም ሙያውን ግን ሊጠቀምበት አልቻለም። በመጨረሻም ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ አብረውት ከመጡት ጥቁሮች ጋር ሆኖ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። ይሁን እንጂ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ሲል በጦርነቱ ቆስሎም ነበር።

ወደ አሜሪካ ሲመለስ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ አሜሪካውያኖች ለኢትዮጵያ ሲል መዋጋቱን እና ያሳየውን አጋርነት በማድነቅ የአቀባበል ስነ-ስርዓት አካሄዱለት። እርሱ ግን በከፍተኛ ቁጭት ውስጥ ወደቀ። በአውሮፕላን እየበረረ ለኢትዮጵያ መዋጋት አለመቻሉ አበሳጨው። ይሁን እንጂ ጥቁሮች ሁሉ ጦርነቱን እንዲያወግዙ ጥሪውን ማስተላለፉን በወቅቱ አላቆመም።

በመጨረሻም በኢትዮጵያ አርበኞች ትግልና ከውጭም ሀገር ከሚታገሉ ደጋፊዎች ትብብር ኢጣሊያ ተሸነፈች። ኢትዮጵያ ድል አደረገች። መንግስቷም ቆመ።

በዚህ ጊዜ ንጉሡ አሁንም ጥሪ አደረጉ። ኢትዮጵያን የሚወዱ ሁሉ ወደ ሀገሪቷ እየመጡ በእውቀታቸው እንዲያገለግሏት ጠየቁ።

ኮ/ል ጆን ሮቢንሠን ግን ፈጥኖ ምላሽ የሰጠ ሰው ነበር። ወደ ኢትዮጵያ ወዲያው መጣ። ቁጭቱን ሁሉ ሊወጣ ወስኖ ተነሳ።

የኢትዮጵያን ወጣቶች በአውሮፕላን በረራ እና ጥገና ለማሰልጠን የመጣ የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ ሆነ። ኢትዮጵያውያንን በማሰልጠን የተሻሉ አብራሪዎች እንዲሆኑ ቀን ከሌት መስራት ጀመረ።

የአውሮፕላን በረራን በይፋ በማስተማሩ ኢትዮጵያም በታሪኳ ውስጥ የመዘገበችው የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ ፓይለት ኮ/ል ጆን ሮቢንሠን በዚህች ሀገር ያበረከተው ውለታ ትልቅ ሆኖ ይጠራል።

ዛሬ የአፍሪካ መኩሪያ የሆነው አየር መንገዳችን እዚህ ለመድረሱ የመጀመሪያውን ጥንስስ የጠነሰሱት እነ ኮ/ል ጆን ሮቢንሰን ናቸው። ምክንያቱም አያሌ አብራሪዎችን አሰለጠኑ። የአውሮፕላን ጥገና ባለሙያዎችን አስተማሩ።

ታዲያ እንዲህ እያደረገ ውለታ የዋለልን ኮ/ል ጆን ሮቢንሰን አንድ ቀን ማለትም 1948 ዓ.ም በአደጋ ለተጐዱ ኢትዮጵያውያን ደም ለማድረስ አውሮፕላኑን አስነስቶ ሲበር እክል ገጠመውና ተከሰከሰ። ሆስፒታል ቢሄድም ሊተርፍ ባለመቻሉ ሕይወቱን ለኢትዮጵያ ሰጠ። ኢትዮጵያን ወደደ፤ በኢትዮጵያ ውስጥም ሞተ። ቀብሩም በኢትዮጵያ ውስጥ ተካሄደ።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ በርካታ ታሪክ ተመራማሪዎች ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ትልቅ ፍተሻ ማድረግ ከጀመሩ ቆይተዋል። ፍተሻቸው ደግሞ ኮ/ል ጆን ሮቢንሰን የተቀበረበትን ቦታ ማግኘት ነው። እስከ አሁን ድረስ የመጡት ተመራማሪዎች የተቀበረበትን ቦታ አላገኙም።

በአሜሪካ ውስጥ ታሪክ ፀሐፊ የሆነው አንድሪው ሎውረንስ በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ይህን የመቃብር ቦታ ሲፈልግ ነበር።

አንድሪው ሲናገር፤ በርካታ ተመራማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የኮ/ል ጆን ሮቢንሰንን መቃብር ቢፈልጉም እንዳላገኙት ይናገራል። እርሱም ቢሆን ጉለሌ በሚገኘው የውጪ ሀገር ዜጐች በብዛት ወደሚቀበሩበት ቦታ ለሦስተኛ ጊዜ መጥቶ ቢፈልግም መቃብሩን ሊያገኝ አልቻለም። ለአምስት ሰዓታት ያህል በየጊዜው ቢፈለግ ሊያገኘው አልቻለም። ከአሜሪካ ድረስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ለዚህች ሀገር ሲል ህይወቱን ያጣው አብራሪ መቃብሩ እንዴት ይጠፋል እያለ ወቀሳም እያቀረበ ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ የታሪክ ተመራማሪዎቹ አሜሪካውያን የኮ/ል ጆን ሮቢንሰንን የቀብር ቦታ የሚያሳያቸው ሰው ከተገኘ በሚያሳትሟቸው መፃህፍት ላይ ከታላቅ ምስጋና ጋር ውለታ እንደሚከፍሉ ይገልፃሉ።

ከሁሉም በላይ ግን፣ ሆሽኋ እስራኤል ሲናገር፤ የዚህን ሰው ታሪክ ትውልድ ማወቅ አለበት። አንዲት ሀገር በውጪ ወራሪ ስትጠቃ ቆሜ አላይም ብሎ ሀብትና ንብረቱን ጥሎ የመጣ፤ ለኢትዮጵያ የሞተ የቁርጥ ቀን ወዳጅ ነው። ይህ ሰው የጥቁር አሜሪካውያንን እና ኢትዮጵያውያንን ልዩ የፍቅር ትስስር ማሣያ ምሳሌ ነው በማለት ጽፎለታል፤ ይናገርለታልም።

እነዚህን የታሪክ ተመራማሪዎች ለማስደሰት እና ውለታቸውንም በትንሹ ለመክፈል የኮ/ል ጆን ሮቢንሰንን የቀበር ቦታ ፈልገን ብናገኝላቸው መልካም ነው። ቀብሩ የተፈፀመው ጴጥሮስ ወጳውሎስ በተሰኘው አካባቢ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይምረጡ
(7 ሰዎች መርጠዋል)
12415 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us