ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ምን ነካቸው?

Wednesday, 20 August 2014 13:25

በድንበሩ ስዩም     

 

ኢትዮጵያዊ ሆኖ የፊልም ትምህርትን በስፋት ተምረው ከዚያም ጥቁሮች በስፋት በሚገኙበት ሀዋርድ ዩኒቨርስቲ የፊልም ጥበብ መምህር የሆኑት ኃይሌ ገሪማ ናቸው። ኃይሌ ገሪማ አባታቸው ገሪማ ታፈረ በጣም ታዋቂ የታሪክ ፀሐፊ እና የቴአትር ድርሰት ቀማሪም ነበሩ። ጥበብን ከአባታቸው በኩል በስፋት የወረሡት ኃይሌ ገሪማ ደግሞ ስመ ገናና ከሆኑ የኢትዮጵያ የጥበብ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። ይሁን እንጂ ፕ/ር ኃይሌ ገሪማ በየጊዜው በሚሰጧቸው ቃለ-መጠየቆች የኢትዮጵያን ሕዝብ ይወቅሳሉ፣ ይተቻሉ ብሎም (ቃሉ ቢያስጠላኝም) ይዘልፋሉ።

በቅርቡ በE.B.S ቴሌቭዥን ላይ በሰይፉ ፋንታሁን ዝግጅት ላይ ቀርበው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የትችት መዓት ሲሰነዝሩ አምሽተዋል። የፕሮግራሙ አዘጋጅ አድዋ ስለሚሰኘው ፊልማቸው ይጠይቃቸዋል። ፕ/ር ኃይሌ ብዙውን ጊዜ አድዋ ብለው በሰሩት ፊልም ሲጠየቁ መልሳቸው ቁጣ ነው፤ ከፊልሙ ይልቅ ወደ ሌላ ነገር ትኩረት አድርገው ሃሳብ ያስቀይሳሉ። ፊልሙን ትተው የኢትዮጵያን ህዝብ ይወቅሱበታል፤፤

ጉዳዩ እንዲህ ነው። ፕ/ር ኃይሌ አድዋ ብለው የሰሩት ፊልም ሃሳቡ ጥሩ ቢሆንም ብዙ ትችት ያመጣባቸው ነው። ምክንያቱ ደግሞ እርሳቸውን ከሚያክል የፊልም ባለሙያ አድዋ ላይ የተጠበቀው ስራ ትልቅ ነበር። ነገር ግን የተጠበቀውን ያህል ባለመሆኑ የተለያዩ ሰዎች በግላቸውም ሆነ በፅሁፉ አስተያየት አቅርበውበታል። ፊልሙ ችግር አለበትና።

በፊልሙ ውስጥ ትንታኔ የሚሰጡት ፕ/ር እንድርያስ እሸቴ ናቸው። ይህ ደግሞ የሆነው የፕ/ር ኃይሌ ጓደኛ በመሆናቸው ብቻ ነው ተብሎም ነበር። እርግጥ ነው አድዋ ላይ ፕ/ር እንድርያስ እንዴት ተመረጡ? አድዋ ላይ የሰሩት ጥናት ምንድ ነው? በሚሉትና በሌሎችም ጉዳዮች ፊልሙ ይተቻል።

ከዚህ ሌላ ፊልሙ በፎቶ ግራፎች የተሞላ ነው። ስዕሎችን ነው የሚያሳየን። አድዋ ላይ ከቦታው ላይ ሆኖ የሚያሳየን ነገር እጅግ ኢምንት ነው። ታላቁ የአድዋ ድል ትልቅ ፊልም አልተሰራለትም!

በፊልሙ ውስጥ እነዚህ ችግሮች ስላሉ ኃይሌ ሲጠየቁ ደግሞ ችግሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር እንደሆነ አድርገው ያቀርባሉ። ህዝቡ ብር ስላልሰጠኝ አድዋን ግሩም አድርጌ አልሰራሁትም! ሕዝቡ በተለይ ዋሽንግተን ዲሲ ያለው ለቢራ ለውስኪ ማንቃረሪያ ገንዘቡን እየረጨ አድዋን ስሰራ ገንዘብ አልሰጠኝም! እያሉ የፊልሙን ችግር በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ይላክካሉ። ሕዝቡ ምን አደረገ? ስለ አድዋ ፊልም እሰራለሁ ብለው የተነሱት እርሳቸው፤ ሙያው የእርሳቸው፤ ትምህርቱ የእርሳቸው፤ ታዲያ ሕዝቡ ምን ያደርግ? ለምን ይወቅሱታል?

ፕ/ር ኃይሌ እርሳቸው ራሳቸው በአ.አ.ዩ ውስጥ የፊልም ዲፓርትመንት ለመክፈት በሚደረገው ጥረት ላይ ብዙም ሙያዊ ድጋፍ አላደረጉም። ኃይሌ ገሪማ በተለይ ዋሽንግተን ዲሲ ውስ የሚኖሩትን ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ወቅሰዋቸዋል። በየካፌው ካፑቺኖ እያንቃረሩ የሚውሉ ዋጋ ቢሶች መሆናቸውን በድፍረት ተናግረዋል። ኃይሌ ያልገባቸው ነገር አለ። ይህ ሁሉ በስደት እውጭ የሚገኝ ህዝብ ሀገሩ ኢትዮጵያንና ህዝቡን ቤተሰቦቹን በኢኮኖሚው ረገድ እየደጎመው እንደሚገኝ ነው። ዛሬ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ገንዘብ በተለይ ኢትዮጵያዊያኖች ወደ ሀገራቸው የሚልኩት ገንዘብ ዋልታና ማገር ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ኃይሌ ገሪማ ግን ለእኔ ፊልም ገንዘብ አልሰጡኝም ብሎ የወቀሳ ሃበላ ያወርዱበታል። እኔስ ለሕዝቡ ምን ሰራሁ ብለው ራሳቸውን መጠየቅ ይገባቸዋል።

ፕ/ር ኃይሌ ገሪማ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲመጡ በሙያቸው እንኳን አንድ ቀን ለወጣቶች ስልጠና ሰጥተው አያውቁም። ነገር ግን የኢትዮጵያን ወጣት ፊልም ሰሪዎችን በማንቋሸሽ እና በመተቸት የሚቀድማቸው ደግሞ የለም። እርሳቸው የኢትዮጵያ ፊልም እንዲያድግ ከጎን ሆነው በሙያቸው ማገዝ ሲጠበቅባቸው ከዚያ ይልቅ በትችት ሲቀጠቅጧቸው ይደመጣሉ።

በዚሁ በፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ቃለ-መጠይቅ ከታዘብኳቸው ነገሮች ደግሞ ስለ ልጆቻቸው እና ስለ ኢትዮጵያ ልጆች የተናገሩት ነው። የእርሳቸውን ልጆች በስርዓታቸውና በሁለንተናቸው ወደር የማይገኝላቸው እንደሆኑ እየተናገሩ፣ በአንጻሩ ደግሞ ሌሎች የኢትዮጵያ ወጣቶች ደግሞ ያው አይረቤ መሆናቸውን በተለያዩ መንገዶች ይገልፁልናል።

በመጨረሻም እንደው ለፕ/ር ኃይሌ የማስተላልፈው ነገር ቢኖር በተቻላቸው መጠን ራሳቸውን ችለው ቢናገሩ ጥሩ ነው። ጉዳዩን ሕዝብ ላይ አይጫኑት! ሕዝቡ ስንቱን ይሸከም? ኧረ በቃው!

ይምረጡ
(11 ሰዎች መርጠዋል)
12612 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us