ይድረስ ለኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር

Wednesday, 20 August 2014 13:29

ግልባጭ ለበዓሉ ግርማ ወዳጆች በሙሉ  

 

በድንበሩ ስዩም 

አሁን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርን በመምራት ላይ የሚገኙት አዲሶቹ ተመራጮች አያሌ የሥራ እቅዶችን እንዳለሙ አውቃለሁ። ለሥራም ያላቸው ተነሣሽነት የላቀ መሆኑንም በተለያዩ አጋጣዎች ተገንዝቤያለሁ። ታዲያ ከያዟቸው የ2007 ዓ.ም እቅዶች መካከል አንድ ሌላ እቅድም እንዲያካትቱበት ከአደራ ጭምር ልጠይቃቸው እወዳለሁ። ጉዳዩ ደግሞ እነሱንም ያስከፋል ወይም ተስፋ ያስቆርጣል ብዬም አላስብም። ስለዚህ የምታካትቱትን እቅድ ብጠቁማችሁስ!

በዚሁ ጋዜጣ እና በተለያዩ ድረገፆች ላይ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ መሰወር ብሎም ግድያውን በተመለከተ አንዳንድ ፍንጮችን ተፅፎ አይቻለሁ። በ1976 ዓ.ም በየካቲት ወር የደረሰበት የጠፋው በዓሉ ግርማ እንደተረሸነ ሙሉ በሙሉ መናገር ይቻላል። ግን ማን እንዳስረሸነው፣ ማንስ ያንን ትዕዛዝ ተቀብሎ እንደረሸነው እስከ አሁን ድረስ የሚታወቅ ነገር የለም።

የበዓሉ ግርማ ባለቤቱ እና ልጆቹ ላለፉት 30 ዓመታት ይህን በመሰለው ተወዳጅ ሰው ሀዘን ውስጥ ወድቀው ይገኛሉ። እስኪ ሁላችንም በኛ ቤት ላይ፣ በራሳችን ላይ የደረሰ አድርገን እንቁጠረው፤ ሃዘኑ እጅግ መራር ነው። እነዚህ ቤተሰቦች የበዓሉን ገዳይ ይፈልጋሉ። የበዓሉን አጽም ይፈልጋሉ፣ የት እንደወደቀ ማወቅ ይፈልጋሉ። ግን እስከ አሁን ድረስ የሚነግራቸው የሕግ ተቋም፣ ወይም የደራሲ ማህበር አልያም መርማሪ ቡድን አላገኙም።

እነዚህ ቤተሰቦች የኢትዮጵያ ህዝብ አካል ናቸው ካልን በሃዘናቸውም ወቅት አለንላችሁ ልንላቸው ግድ ይለናል። በፍርድ ቤት የተሞከረው ክስም የትም ሳይደርስ ምርመራም ሳይደረግበት ቆሟል። ስለዚህ ይህ ጉዳይ በዚሁ መቀጠል አለበት ወይ? ዝም ዝም ተብሎ ይታለፍ ወይ?

መቼም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በሕይወት እስካለ ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ነገር ቢያደርግ በታሪክም ሆነ በትውልድ ዘንድ የማይረሳ አስተዋፅኦ አበርክቶ ማለፍ ይችላል። ደራሲያን ማህበር ሊያደርግ የሚችለውን ሃሳብ ልጠቁም።

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከልዩ ልዩ የማህበረሰቡ ክፍሎች የተወሰኑ ሰዎችን አውጣጥቶ አንድ ኮሚቴ ሊያቋቁም ይችላል። ይህ ኮሚቴ ደግሞ “የበዓሉ ግርማን መሰወር አፈላላጊ ኮሚቴ” ወይም ሌላ ርዕስ ሊሰጠው ይችላል። በኮሚቴው ውስጥ ደግሞ በምርመራ ችሎታቸው የሚታወቁ ሰዎችን፣ በዚያ ስርዓት ውስጥ የነበሩ የደህንነት ሰዎችን ብሎም አንዳንድ ምስጢር አዋቂዎችን አፈላልጎ ኮሚቴ ቢያዋቅር እና ኮሚቴውንም ወደ ስራ ቢያስገባው በአጭር ጊዜ ውስጥ የበዓሉ ግርማን የመጨረሻ ፍፃሜ ማግኘት ይቻላል።

የበዓሉ ግርማ አሟሟትን በተመለከተ አጣሪ ኮሚቴ ስለሌለ ነውጂ ብዙ ነገር ማወቅ እንደሚቻል ፍንጭ ተሰጥቷል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ደራሲ አበራ ለማ እና ሌሎችም ሰዎች ስለ በዓሉ ግርማ የሚፅፉት ጉዳይ ነገሩን የበለጠ ከማወሳሰብ ውጭ ፋይዳ የሌለው መላ ምት እየሰነዘሩም ይገኛሉ።

በዘመነ ደርግ አበራ ለማ እና መሰሎቻቸው ሰዎችን የሚያስገድሉ የቀበሌ ካድሬዎች እንደነበሩ ክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ በተሰኘው መፅሐፉ ከ20 ዓመታት በፊት አጋልጦታል። የክፍሉ ታደሰ መፅሐፍን እንደ ተዓማኒ ምንጭ አድርጌም የወሰድኩበት ምክንያት፤ ክፍሉ ራሱ ኢ.ሕ.አ.ፓን (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲን) ከመሰረቱት እና በከፍተኛ አመራር ውስጥ ከነበሩት ቁንጮዎች መካከል ግንባር ቀደሙ በመሆኑ ነው። በተለይ ክፍሉ የአዲስ አበባውን የኢሕአፓ ትግል የሚመራ በመሆኑ የደርግ ገዳዮች እነማን እንደነበሩ በግልጽ ፅፎታል። ስለዚህ አበራ ለማ በደርግ ውስጥ ከነበሩ አስገዳይና ገዳዮች መካከል እንደነበረበት ክፍሉ ታደሰ ፅፎበታል።

ስለዚህ አበራ ለማ በበዓሉ የመጨረሻ የህይወት ፍጻሜ ላይ ሰሞኑን እየፃፈ ያለው ነገር ራሱን ከደሙ ነፃ አውጥቶ ሌሎችን እየወነጀለም ይገኛል።እንዲህ አይነት አካሔዶች የበዓሉ ግርማን ገዳዮች ዲካ የሚያጠፋ ስለሆነ ሌላ የተደራጀ አካሔድ ያስፈልጋል። ይህ አካሔድ ደግሞ በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በኩል ቢመራ፣ ቢደራጅ ውጤታማ ይሆናል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።

ደራሲያን ማህበር ይህን ኃላፊነት ሲያስተባብር ብዙ መገለጫዎች በውስጡ ይዞ ነው። አንደኛው በዓሉ ግርማ ማለት የድርሰት ቁንጮ ነው። የደራሲያን ተምሳሌት ነው። እንዲህ ዓይነት ታላቅ የጥበብ ዋርካ በቀላሉ ተገንድሶ ወደቀ ተብሎ ዝም ብሎ መቀመጥ ከማናችንም አይጠበቅም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በዚህ ሂደት ውስጥ መሳተፉ የሚያሳየን ነገር ቢኖር አንድ ደራሲ እንደ ተራ ነገር የትም ወድቆ የማይቀር መሆኑን፣ ፈላጊ እንዳለው፣ ወዳጅ እንዳለው ማሳየት የሚቻልበትም ተግባር ነው። እርግጥ ነው በዓሉ ግርማ ሲፅፍ እንዲህ ብሎ ነበር፡፤ “ሀቀኛ ደራሲ አድናቂዎች እንጂ ወዳጆች የሉትም” ብሏል። ይህ አባባል እንዴት እሱ ራሱ ላይ ይፈፀማል? ባጠቃላይ ሲታይ ኮሚቴው ተቋቁሞ የበዓሉን ፍፃሜ እና ብሎም የት እንደወደቀ በማወቅ ለቤተሰቦቹም እረፍት ለኢትዮጵያ ህዝብም ደራሲነት ማለት ተራ ነገር እንዳልሆነ ማሳያም ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።

የበዓሉ ግርማ እናት አንድ ልጅ ብቻ ነው የወለዱት። እሱም በዓሉ ነው። አንድ ለናቱ! ግን ይህ ሰው በጨካኞች እጅ ወድቆ የት እንደገባ ሳይታወቅ 30 ዓመታት ነጎዱ። እናቱ አንድያ ልጃቸው የት እንደገባ፣ ማን እንደገደለው ሳያውቁ እጅግ በሚያሳዝን የሃዘን ማቅ ውስጥ ኖረው ሕይወታቸው አልፋለች። በዓሉ ወንድም እህት ስለሌለው የሚፈልገው አጣ ብለው አዝነው አልፈዋል። እኛ ደግሞ አድናቂዎቹ ብቻ ሳንሆን ወዳጆቹ፣ ወንድሞቹ፣ እህቶቹ፣ ፈላጊዎቹ፣ ሆነን ለትውልድ አርአያነታችንን ማሳየት አለብን። የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ይህን ኃላፊነት ቢወስድ በጣም ጥሩ ታሪክ ያቆያል ብዬ አስባለሁ።

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
11879 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us