ኢትዮጵያ- የጥንታዊ ጥበብ መፍለቂያ ሀገር

Wednesday, 27 August 2014 11:13

በድንበሩ ስዩም

    ከሰሞኑ በቢቢሲ ቴሌቪዥን ድረ-ገጽ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ኪነ ህንጻዎች ጥበብና ታሪክ በፎቶ ግራፍ የተደገፈ ማስተዋወቂያ ቀርቧል፡፡ ኢትዮጵያ በቀደመው ዘመን ድንጋይን እንደ ወረቀት እያጣጠፉ ተአምራዊ ኪነ-ህንጻዎችን ሰርታ ዛሬም የአለም ቱሪስቶች እየመጡ ሲጎበኙ ሲደነቁ ኖረዋል፡፡

    ኢትዮጵያ- የጥንታዊ ጥበብ መፍለቂያ ሀገርበዚህ ርዕስ ዙሪያ እጅግ በርካታ ቦታዎች ይጠቀሳሉ። ምናልባትም ብንዘረዝራቸው ከአንድ ግዙፍ መፅሐፍ በላይ ይወጣቸዋል። ነገር ግን የቴአትር ጥበብ እና የኪነት ጮራው እንዲበራ ደማቅ ሆነው ከበሩ ቦታዎች ደግሞ አስገራሚ ጥበብ የታየበትን የሀገራችንን ክፍል በሚቀጥለው ፅሁፍ ቀስ እያልን እንደርስበታለን።

እንደ ታላቁ የኪነ-ጥበብ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ወደኋላ ሄደን የዛሬ ሁለት ሺ ዓመት በፊት ሥለነበሩት የቴአትር ጅማሮዎች የምንጠቃቅሰው ታሪክ ባይኖርም፤ የ17ኛውን መቶ ክፍለዘመን የኢትዮጵያን ስልጣኔ ተመርኩዘን የምንጫወተው ግን ይኖረናል። ኢትዮጵያ ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ሃይማኖት በእጅጉ የተጫናት እና ሃይማኖታዊ አስተዳደርም ጐልቶ የሚታይባት ሀገር ነበረች። ለምሳሌ የ11ኛውን እና የ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ደግሞ እጅግ የሚገርም የሃይማኖት መንግስት የመሰረተችበት ወቅት ነበር። በዚሁ በ11ኛው እና በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩት የዛጉዌ ዘመነ መንግስት አስተዳደሮች ፍፁም ክርስቲያናዊ ከመሆናቸውም በላይ የሀገሪቱ መሪዎች ቄሶች ነበሩ።

    የዚያው ዘመን ገናና የኢትዮጵያ መሪ የነበረው ቅዱስ ላሊበላ ንግስናን ከቅስና ጋር አጣምሮ የያዘ ሰው ነበር። ንጉስ ሆኖ አገርና ህዝብ ይመራል፤ ቄስ ሆኖ ደግሞ በአብያተ-ክርስቲያናት ውስጥ ያገለግላል። ከላሊበላ በፊትም ሆነ በኋላ የነበሩት የዛጉዌ ነገስታት ቄሶች እና ንጉሶች ናቸው። ለምሳሌ ከላሊበላ በፊት የነበሩት ቅዱስ ሐርቤይ፣ ቅዱስ ይምርሃነክርስቶስ እና ሌሎችም ንጉሶችና ቄሶች ነበሩ። ከላሊበላ በኋላ የነገሠውም ቅዱስ ነአኩቶለአብ ቄስና ንጉስ ነበር። እነዚህ መሪዎች በዚህ በሃይማኖታዊ ሰውነታቸው ሰርተው ካለፉዋቸው ነገሮች መካከል የእምነት ኪነ-ሕንፃዎችን እና መልካም አስተዳደርን እንደሆነ ታሪካቸው ያወሳል።

    ከ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ደግሞ ስልጣን ወደሸዋ ነገስታት ከመጣ በኋላ፣ ከኪነ-ህንፃ ግንባታ ይልቅ ወደ ሥነ-ጽሑፉ አቅጣጫ ማዘንበል በስፋት ታየ። ሸዋዎች አያሌ መፃህፍትን እና ታሪኰችን በመሰነድ የሚስተካከላቸው የለም። እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ የሃይማኖት አጥባቂነትም እንደ ዛጉዌው ዘመነ መንግስት ወቅት እንደሆነም ጭምር ነው። ለምሳሌ አፄ ዘርአያዕቆብ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን እጅግ ከማጥበቁም በላይ ከሃይማኖቱ ያፈነገጡ ዜጐችን ይገድል እንደነበር ታሪኩ ያወሳል። ግድያውን ደግሞ በራሱ ልጆች ላይም አከናውኗል። ከሃይማኖት አፈንግጣችኋል ብሎ ልጆቹን የገደለ መሪ ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ የፅሁፍ ጥበብን በማስፋፋት ስመ ገናና ሆኖ የሚጠራ የኢትዮጵያ መሪ ነው። እንዲያውም “ደራሲው ንጉስ” እየተባለም ይጠራል።

    አፄ ዘርአያዕቆብ በርካታ መፃህፍት በመድረስ የሚታወቅ የኢትዮጵያ መሪ ነው። ዛሬ እንደ ብርቅ የሚታዩት ጥንታዊ የብራና ፅሁፎች በዓለም የሥነ-ጽሑፍ መድረክ ላይ ስሙን በእጅጉ ያስጠሩታል። አፄ ዘርአያዕቆብ እጅግ አጥባቂ ሃይማኖተኛ መሆኑን “ተዐምረ ማርያም” የተሰኘውን የብራና መጽሐፍ ሲያዘጋጅ የዓይኑን እንባ ከቀለም ጋር እያላቆጠ የማርያምን ስም የፃፈ ደራሲ ነው። በእርሱ ዘመን ማለትም በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተፃፉት እነዚህ ታላላቅ ቅርሶችም እጅግ የተጠበቁ ውድ ንብረቶች ሆነዋል።

    ከአፄ ዘርአያዕቆብ በኋላም የተከተሉት መሪዎች ሃይማኖትን እንደ ዋና መመሪያዎች አድርገው ቆይተው ነበር። በዚህም የተነሳ ዓለማዊ የሆኑት እንደ ሙዚቃ፣ ዳንስ፣ ጭፈራ፣ ቴአትር ወዘተ የመሳሰሉት ነገሮች በወቅቱ ጫና በዝቶባቸው እንደነበር መገንዘብ እንችላለን።

    በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግን ሀገሪቱ አንድ አስደንጋጭ ነገር ገጠማት። ከወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ በቱርኰች እየተደገፈ የመጣው የግራኝ አህመድ መነሳት ሀገሪቷን ከላይ እስከ ታች ያናውጣት ገባ። የግራኝ አህመድ ሠራዊት ክርስቲያናዊ አመራር የነበረውን የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግስት እያፈረሰ ወደ ሰሜን መገስገስ ጀመረ። በተለይም እዚህ ሞጆ አካባቢ “ሽምብራ ኩሬ” ተብላ በምትታወቀው ስፍራ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት ክፉኛ ተጠቃ። ከዚያ በኋላ የግራኝን ጦር የሚመክተው እና የሚመልሰው ኃይል በመጥፋቱ የሰሜን ጉዞው እየተሳካ መጣ።

    ግራኝ አህመድ የወሎን ግዛት ያዘ። በጐጃም፣ በጐንደር በትግራይም ሠራዊቱ ሰርጐ ገባ። በጣም የሚገርመኝ አንድ ታሪክ አለ። ይህም ግራኝ አህመድ ወሎ ውስጥ ያደረገው አንድ ታሪክ አለ። ይህም ግራኝ አህመድ ወሎ ውስጥ ባደረገው ዘመቻ የቅዱስ ላሊበላ አብያተ-ክርስትያናት’ጋ ደረሰ። እነዚያ ዛሬም ድረስ የሰውን ልጅ የሚያማልሉት ኪነ-ህንፃዎች ጦረኛውን ግራኝ አህመድንም አስደነቁት። ዝም ብሎ ያያቸው ነበር። እንዴት እንደታነፁ ግራ ገባው። ግን ብዙ ጊዜ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ ይህንንም ቤተ-ክርስትያን አቃጥላለሁ አለ። የላሊበላ ህዝብ ተሰባሰበ። ግራኝም ምን ልትሰሩ ነው የመጣችሁት አላቸው። ህዝቡም እነዚህን አብያተ-ክርስትያናት ከማቃጠልህ በፊት መጀመሪያ እኛን አቃጥለን አሉት። ግራኝም ለማቀጣጠል እሳት ለኩሶ ነበርና እንዲህም አላቸው። “ከናንተ ውስጥ ደፋር ካለ እስኪ እዚህ እሳት ውስጥ ይግባ” አላቸው። አንዲት ሴት ጥልቅ ብላ ገባች። ግራኝም በጣም ገርሞት ሴትየዋ ከእሳቱ ውስጥ እንድትወጣ አደረጋት። ፊቷ ተለብልቦ ነበር።

    ግራኝ አህመድ በነዚህ በላሊበላ ኪነ-ህንፃዎች ተደንቆ ስለነበርና እንዲሁም የላሊበላ ነዋሪዎች ስላሳዩት ቁርጠኝነት እና መስዋዕትነት ተደንቆ እሳቱንም አስጠፍቶ አብያተ-ክርስትያናቱን ምንም ሳያደርጋቸው ጉዞውን ቀጠለ። አንዳንዶች የኪነ-ህንፃው ጥበብ ስለማረከው ነው ወደ ጥፋት ያልገባው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ የህዝቡን ስሜት ተረድቶ ነው፤ ቢያቃጥላቸው ኖሮ ወዲያው የሚደርስበት ውርጅብኝ ነበር በማለት ይናገራሉ። ብቻ ታሪክ ፀሐፊቷ ሲልቪያ ፓንክረስት Ethiopia a cultural history በተሰኘው መጽሐፏ ውስጥ ይህን ከላይ የጠቀስኩትን ታሪክ የግራኝ አህመድን ውሎ እየተከታተለ የሚፅፈውን አረብ ፋቂን እማኝ ጠርታ ገልፃለች።

    ጉዞውን ወደ ሌሎቹ የሰሜን ኢትዮጵያ ግዛት ያደረገው ግራኝ መላው ኢትዮጵያን ሊቆጣጠር እጅግ በጣም ትንሽዬ ቦታ ብቻ ቀረችው። የሸዋ ነገስታቶች ጦርነቱን እየሸሹ ጣና ሐይቅ ውስጥ ወደሚገኙት ገዳማት እና አድባራት መሽገዋል። ጦራቸው ደግሞ ከጐንደር ከተማ በትንሹ ወጣ ብላ በመትገኘው ዘንታራ በር ተብላ በምትታወቀው ቦታ ጦርነት ተጀመረ። በወቅቱ ኢትዮጵያን ይመራት የነበረው አፄ ገላውዲዮስ ነበር። እናም ለ15 ዓመታት የቆየው የግራኝ አህመድ ጦርነት በዚህችው ስፍራ ተጠናቀቀ። የካቲት 13 ቀን 1570 ግራኝ ተገደለ ብለው ፀሐፊዎች አስቀምጠውታል። ግራኝ የኖረው ከ1500 እስከ 1570 ዓ.ም እንደነበር የገለፁ አሉ።

    ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ መልክ እና አመለካከት ይቀየራል። በጦርነቱ መግፋት ጣና ደሴት አካባቢ የመጡት የሸዋ ነገስታት መንግስታቸውን በዚያው በጐንደር ዙሪያ ማፅናት ጀመሩ። ሳይታሰብ ጐንደር ከተማ የነገስታት፣ የቀሳውስት፣ የመምህራን፣ የወታደሮች፣ የልዑላን መሰባሰቢያ ሆነች። መንግስት ጐንደር ላይ ረጋ።

    በዚህች በጐንደር ዙሪያ ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የጐንደር ስርወ መንግሰት /Gonderian Kingdom/ የተሰኘ አዲስ ስርዓት በአፄ ሰርፀድንግል (1543-1590) ተመሠረተ። ዛሬ ጐንደር ከተማ መግቢያ 40 ኪሎ ሜትር ሲቀረው የሚታየው ቤተ-መንግስትም በዚያን ዘመን የተሰራ ነው። ከዚያም አፄ ሱስንዮስ የኢትዮጵያን አመራር ተረክበው ቆይተው በካቶሊክና በኦርቶዶክስ እምነቶች መካከል ከፍተኛ ፀብ ተነሳ። በወቅቱ የልዩ ልዩ ሃይማኖት ተከታዮች ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ስለገቡ አንዳንድ አስተሳሰቦችም የተቀየሩበት ወቅት ነው። እነ ፈላስፋው ዘርአያዕቆብ እና የእርሱ ተማሪ የሆነው ወልደሕይወትም በዚህ ዘመን የተፈጠሩ ፈላስፋዎች ናቸው።

    አፄ ፋሲል በ1624 ዓ.ም መንበረ ሙሴውን ሲይዙ የኢትዮጵያ አስተዳደር በብዙ መልኩ ባሕሪውን ቀየረ። ለምሳሌ ነገስታት ቤተ-መንግስታቸውን የሚያንፁበት ግቢ ውስጥ ቤተ-ክርስትያንን አብሮ ማነፅ የተለመደ ነው። አፄ ፋሲል ግን ጐንደር ላይ በሰሩት ቤተ-መንግስታቸው ቅፅር ግቢ ውስጥ ቤተ-ክርስትያን አላሳነፁም። ያሳነፁት ከቤተ-መንግሰት ውጭ ነው። ይህ አካሄድ የጐንደር ሥርወ መንግስት መለያ ሆነ። ከፋሲል በኋላ የመጡት የጐንደር ነገስታት አፄ ዮሐንስ፣ አፄ አድያምሰገድ እያሱ፣ አፄ ዳዊት እና አፄ በካፋ ቤተ-ክርስትያን ያሰሩት ከቤተ-መንግስታቸው ውጭ ነው። ስለዚህ ሃይማኖት በሰፊው ያልተጫነው ስርወ መንግስት ተመሠረተ የሚሉ አሉ። ምክንያቱም እነ ቅዱስ ላሊበላ እና እነ አፄ ዘርአያዕቆብ እጅግ አጥባቂ ኦርቶዶክስ ከመሆናቸው አንፃር ይህ የጐንደር ሥርወ መንግስት ደግሞ የላላ ነበር የሚሉ ጥናቶች አሉ።

    በዚህም ምክንያት ይመስላል የጐንደሩ ንጉስ አፄ ዳዊት በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ አንድ የልዩ ልዩ የኪነ-ጥበብ ውጤቶችን ማቅረቢያ አዳራሽ ያሰሩት። ይህ አዳራሽ በእንግሊዝ አውሮፕላኖች በኢጣሊያ ወረራ ወቅት በቦምብ ተደብድቦ ጣሪያው የፈረሰ ቢሆንም፤ ዛሬም ድረስ የበርካታ ቱሪስቶችን ቀልብ እየሳበ በጐንደር ከተማ ውስጥ ተገማሽሮ ይታያል።

    አያሌ የጐንደር ፀሐፊያን ይህ አዳራሽ በጐንደር ዘመን ውስጥ የነበሩ ጥበበኞች የሙዚቃ፣ የዝማሬ፣ የሽብሸባ፣ የተውኔት እና የመሳሰሉትን ትርኢቶቻቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ ነው። የተገነባውም እ.ኤ.አ ከ1716-1721 ዓ.ም ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ “ቴአትር” በዚህ አዳራሽ ውስጥ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ ቀርቦ ነበር ወይ? የሚለው ጥያቄ ብዙ ጥናት የሚጠይቅ ነው። አዳራሽ እና መድረክ በተገነባበት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ቴአትር አልነበረም ብሎ መናገር ተአማኒነት ያሳጣል። ቴአትር ነበረ ብሎ ለመናገር ደግሞ የተፃፈ ተውኔት /Script/ ያስፈልጋል። ግን ጉዳዩ ለጥናትና ምርምር ክፍት መሆን አለበት። የኢትዮጵያ ቴአትር የተጀመረው በበጅሮንድ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም በ1906 ወይም በ1913 ዓ.ም ብሎ ድርቅ በማለት ለማሳመን ከመሞከር ይልቅ እነዚህን የመሳሰሉ የጥበብ ቅሪቶች ላይ ቢጠና ውጤት ይገኛል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።

    በነገራችን ላይ ይህን የጥበባት አዳራሽ ያሰሩት አፄ ዳዊት ጐንደር ውሰጥ የሚገኘውን እጅግ ውብ በሆነ የስዕል ጥበባት ያሸበረቀውን ደብረብርሃን ስላሴ የተሰኘውን ቤተ-ክርስቲያን ለሁለተኛ ጊዜ ያሰሩ ናቸው። ስዕሎቹ በዓለም የስዕል ታሪክ ውስጥ First Gonderian Art እና Second Gonderian Art እየተባሉ ይጠራሉ።

ይምረጡ
(16 ሰዎች መርጠዋል)
13272 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us