ኦዲዮ-ቪዥዋል በሕገ-ወጦች መስፋፋት ምክንያት የአባላቴ ቁጥር ቀነሰ አለ

Saturday, 12 October 2013 11:51

የኢትዮጵያ ኦዲዮ-ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር አባላት በሕገወጥ ቅጂዎች መስፋፋት ምክንያት ቁጥራቸው እየቀነሰ መምጣቱን የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ዕቁባይ በርሄ ባሳለፍነው ቅዳሜ ምሽት በጣይቱ ሆቴል፤ ጃዝ አምባ መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አስታወቁ። በ2001 ዓ.ም 246 የነበረው የአባላቱ ቁጥር በአሁኑ ወቅት አሽቆልቁሎ 75 መድረሱንም ተናግረዋል።

ማኅበሩ ባለፉት 10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ መጥፎም ጥሩም የሚባል ጊዜን አሳልፏል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ተገኙ ባልናቸው ድሎች ስንዘናጋ ሕገ-ወጥ አሳታሚዎችንና የቴከኖሎጂ ስርቆቶችን በጋራ እንዋጋለን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። በወቅቱም ማኅበሩ ከተቋቋመ በኋላ ባለፉት 10 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ባካሄዳቸው ሦስት ድንገተኛ ክትትሎች 4 ሚሊዮን የሚደርሱ ሕገ-ወጥ የሲዲና የካሴት ቅጅዎችን ማግኘቱን አስታውሰው፤ ይህም በ20 ብር ሽያጭ ለገበያ ቢውል ራሱ ወደ 8 ሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ በሕገ-ወጦቹ ተዘርፏል ብለዋል። በዚህም እንደማኅበሩ እምነት ከሆነ እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት ሕገ-ወጦች ከ10 በመቶ አይበልጡም ተብሏል።

በሕገ-ወጦቹ እንቅስቃሴ ተስፋ የቆረጡ የማኀበሩ አባላት ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰና እየጨመረ የሚመጣ መሆኑን የጠቆሙት የኦዲዮ-ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር ፕሬዝዳንቱ አቶ ዕቁባይ በርሄ እንደምሳሌም ሲጠቅሱ በ1994 ዓ.ም አካባቢ 85 የሚደርሰው የአባላቱ ቁጥር የሕገ-ወጥ ቅጂዎቹን መስፋፋት ተከትሎ በ1995 ዓ.ም ቁጥሩ ወደ 39 መድረሱን አስታውሰዋል። አክለውም በ1996 ዓ.ም ለስድስት ወራት የዘለቀውን የሙዚቃ ሕትመት መቋረጥ አድርገው እንቅስቃሴውን ሲያጠናክሩ የማኅበሩ አባላት ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ 76 መድረስን አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅትም የአባላቱ ቁጥር እስከ 2001 ዓ.ም ድረስ የተመዘገቡት 246 የደረሱ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም መበራከት ምክንያት አድርገው የሕገ-ወጦችን ወደ 75 ቁጥራቸው ወርዷል። ሕገወጥነትን አጥብቀን መዋጋታችንን እንቀጥላለንም ብለዋል። አያይዘውም የምሽቱን የለዛ አድማጮች ሽልማት ዝግጅት አመስግነው መሠል የሽልማት ዝግጅቶች ለአርቲስቶቹ ብርታት ይሆናልና እንዲቀጥል ተመኝተዋል።

 

Last modified on Saturday, 12 October 2013 11:54
ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
9450 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us