የአፈወርቅ ተክሌ ቪላ አልፋ

Wednesday, 03 September 2014 14:04

ከእመቤት በላይ 

 

እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የኢትዮጵያ መኩሪያ የነበሩ ታላቅ ከያኒ ናቸው። በአለም የኪነ_ ጥበብ መድረክ ከሃምሣ አመታት በላይ እንደ ብርቅ ከዋክብት ሲታዩ የነበሩት እኚህ ጥበበኛ ማክሰኞ ሚያዚያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም በ80 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል። ነብሣቸውን ይማርልን ብዬ ወደ አሣነፁት ኪነ_ ሕንፃ ጐራ ልበልና ትንሽ ወግ ላጫውታችሁ።

አፈወርቅ ተክሌ በአዋሣ ሃይቅ ዳርቻ እና እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በኪነ_ ሕንፃ ውበታቸው ልዩ የሆኑ ግንባታዎችን አካሒደዋል። ለዛሬ ግን እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ስላለው አስደማሚው ቤታቸው ላጫውታችሁ። በአገነባብ ጥበቡ ፍፁም ኢትዮጵያዊ ውበትና ለዛ ተላብሶ የተገማሸረው ይህ ቤት “ቪላ አልፋ” በሚል መጠሪያ ይታወቃል። ለመሆኑ ይህ መጠሪያ ስሙ ከየት መጣ

“ቪላ አልፋ” የሚለው ስም ለአርቲስቱ አፈወርቅ የወጣለት ገና ት/ቤት እያለ ነው። አልፋ ያሉት የሚወዳቸው ኘሮፌሰሩ ናቸው። ኘሮፌሰሩ በቀላሉ ለሁሉም ተማሪ የሚገኙ አልነበሩም። የእኒህን ሰው ቀልብ ለመሣብ አፈወርቅ የወሰደው እርምጃ ብልጠት የተሞላት ነበር። በፈተና ወቅት ለተጠየቀው ሣይሆን ላልተጠየቀው ጥያቄ መልስ መስጠት። አፈወርቅ ለፈተና የሠጠው መልስ ክፍል ውስጥ ተነቦ በተማሪዎች ፊት ሲገመገም፣ ሁሉም ተማሪዎች ለፅሁፉ ዜሮ ሠጡት። ኘሮፌሰሩ ግን የአፈወርቅ ብልጠት ስለገባቸው “አልፋ ፕላስ ያገኛል” አሉት። “አልፋ የሚለው ቃል ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአፈወርቅ የቅፅል ስም ሆኖ ቀረ። ወደ አገር ቤት ሲመለስም ለሠራው ቤት “ቪላ አልፋ ስቱዲዮ” የሚል ስያሜ ሠጠው በማለት ፀሐፌ-ተውኔቱ እና ገጣሚው አያልነህ ሙላት ይገልፃል። አያልነህ ሙላት የአፈወርቅ ተክሌ የረጅም ጊዜ ጓደኛ ሲሆን፣ አርቲስቱም ከዚህ አለም በሞት በተለዩ ወቅት እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ አጭር የሕይወት ታሪክ የምትሠኝ መፅሔት አዘጋጅቶ ነበር። እኔም ይህችን መፅሔት ዋቢ አድርጌ የአፈወርቅ ተክሌን ቪላ አልፋ ላስተዋውቃችሁ።

ይህ ቪላ አልፋ በጠቅላላ ሃያ ሁለት ክፍሎች አሉት። እያንዳንዷም ክፍል አርቲስቱን እንዲያስታውሱት በሚፈልጋቸው መልካም ነገሮች ተውቧል።

“ቪላ አልፋ” ጐብኚ እንደልቡ ተዟዙሮ ስዕሎችን የሚያይበት፣ የሚዝናናበት፣ ስለ ኪነ_ጥበብ የሚያስብበት፣ ወደ መሬት ሲያይ የአበቦችን መአዛ የሚያሸትበት፣ በግድግዳዎች ላይ የተሠሩ የጥበብ ስራዎችን አይቶ የሚያደንቅበት፣ ቀና ሲል ደግሞ ሰማዩንና ደመናውን ተመልክቶ የሚደሠትበት፣ በአጠቃላይ የኪነ-ጥበብ ስሜት አድሮበት እንዲሔድ የሚያደርግ የጥበብ ቤት ነው። በግቢው አካባቢ አንዳንድ ስጦታዎች አሉ። እነዚህም አርቲስቱ ወደ ውጭ ሀገር በሔደ ቁጥር ለኪነ-ጥብብ ሥራዎቹ አክብሮት ካሏቸው ሰዎች የተደረጉለት ስጦታዎች ናቸው። አፈወርቅ ቪላውን የሰራበትን ምክንያት ሲናገር፣ ለፈጠራ ሥራዎቹ በቂ ቦታ ለማግኘት እንጂ፣ በአንድ ቤተ መንግሥት በመሠለ ትልቅ ቪላ ዉሰጥ መኖር ፈልጌ አይደለም። ከውጭ ሀገር ትምህርቴን ጨርሼ ወደ ሐገሬ ስመለስ ከገጠሙኝ ችግሮች አንዱ የሥዕል ማሣያ ጋለሪ አለመኖር ነው ብሏል።

አሁን ደግሞ እስኪ ወደዚሁ ውብ ቤት ውስጥ እንግባ

መጀመሪያ ላይ የምናገኘው ዋናውን የእንግዶች መግቢያ በር ነው። በበሩ ግራና ቀኝ ሁለት የባንዲራ መስቀያዎች አሉ። የሀገር መሪዎች በሚመጡበት ጊዜ የኢትዮጵያ ባንዲራና የእንግዳው አገር ባንዲራዎች ይሰቀሉባቸዋል። ከበሩ አካባቢ ሣንወጣ ወልደ ነጐድጓድ የሚል የአፈወርቅ ተክሌ አርማ አለ። ከበሩ በስተቀኝ በኩል ደግሞ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔር መፍራት ነው” የሚል ጥቅስ አለ። በመፅሐፍ መልክ በተዘጋጀ ቅርፅ ላይ ተፅፏል። ይህም አርቲስቱ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት፣ ቤቱ ደግሞ የፈጠራ ምንጭ መሆኑን ይገልፃል።

የበሩን መሃል ይዘው ሲሄዱ በኢትዮጵያ ላይ “ክፉ አትይ ክፉ አትስማ ክፉ አትናገር” የሚል መልዕክት የሚያስተላልፉ ቅርጾች በኢትዮጰያ ሰንደቅ አላማ ቀለማት ተውበው እናያለን።

በዚህ ቪላ ውስጥ ያለፈውንና የአሁኑን፣ እንዲሁም የወደፊቱን የእናት አገር ታሪክ፣ ባሕልና ቅርስ የሚያሣዩ፣ እፁብ ድንቅ የሆኑ ስዕሎች ቅርፃ ቅርሶችን ያገኛሉ። የኢትዮጵያ ብቻ ሣይሆን የአፍሪካ ሕዝቦች ታሪክ፣ ባህልና ቅርፅ ጭምር የሆኑ ስራዎች የፈለቁበት የዚህ ብርቅዬ አርቲስት መኖርያና ስቱዲዮ በሆነው በቪላ አልፋ ውስጥ ነው።

የአፈወርቅ ተክሌ የመጀመሪያ ትምህርቱ ሥነ ስዕል፣ ሁለተኛው ትምህርቱ ሥነ ቅርፃ ቅርፅ ሶስተኛው ደግሞ ክላሲካል አርክቴክቸር ነው። በዚህም መሠረት ይህ ቪላ ከሐገራችን የጐንደርን፣ የአክሱምን፣ የላሊበላን፣ የሶፍ ዑመርን፣ ድሬዳዋ የሚገኘውን የጥንቱን ዋሻ ተምሣሌት አድርጐ ያስገነባው ነው።

አፈወርቅ ተክሌ ለሐረር ከተማ ልዩ ፍቅር ነበረው። ሐረር ከተማ ውስጥ አንደኛ የራስ መኮንን ሐውልት፣ ሁለተኛ በወቅቱ የወታደር አካዳሚ የነበረው የመስታወት ስዕል የአፈወርቅ ስራዎች ናቸው። በእነዚያ የሥራ ወራት ቆይታው ለአርቲስቱ ልዩ ደስታ ይሠጡት የነበሩት ስምንቱ የሐረር ግንብ በሮች ናቸው።

አፈወርቅ የቀለም ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ፣ ለስድስት ወራት በተለያዩ አገሮች ተዟዙሮ ተግባራዊ ጥናቶችን አድርጓል። በዚያን ወቅት ፈረንጅ ሀገር እንዲቀር የተለያዩ ሃሣቦችና ጥያቄዎች ቀርበውለት ነበር። ለነዚህ ጥያቄዎች አፈወርቅ የሠጠው መልስ ንጉሰ ነገስቴን ስሠናበት ወደ ሃገሬ ተመልሼ ሕዝቤን እንደማገለግል ቃል ገብቻለሁ የሚል ነው። ንጉሱም ሲሸኙን የመከሩን ፈረንጅ ሀገር የምትሔዱት ሰፋፊ መንገዶችንና ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን አይታችሁ ተመልሣችሁ ስለ እነሱ እንድትነግሩን አይደለም፤ በኢጣሊያ ፋሽስቶች የወደመችን ሀገር ስንገነባ ከጐናችን ቁማችሁ እንድትረዱን እንጂ ብለው ነው።

የአፈወርቅ ተክሌ የሥራ ቦታ መግቢያ እንደ መንግሥተ ሠማያት በር ጠባብና ሰወር ያለች ናት። ለዚህች ጠባብ በር አልፎ ወደ ስቱዲዮ ሲገባ ወደ አንድ ገዳም ወይም ወደ አንድ ቤተ-መቅደስ እንደ መግባት ያህል ይቆጠራል። የፈጠራዎቹ ሁሉ መፍለቂያ በሆነው በዚህ ስቱዲዮ ውስጥ ቆም ብለን ስንመለከት፣ የተጀመሩ፣ ወደ ማለቁ ደረጃ የደረሱ፣ በብዙ ዐውደ ርዕዮች ገና ያልታዩ ሥራዎችን እናገኛለን። አብዛኛዎቹ ስራዎቹ ለብዙ አመታት የተለፋባቸው ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው፣ በመስታወት ሊሰሩ የሚችሉ ከኢትዮጵያ አልፈው አፍሪካ የተጓዘችበትንና የወደፊት አቅጣጫዋን ጭምር የሚጠቁሙ ትንሽ ትንበያዎችን በውስጣቸው የያዙ ናቸው። ስዕሎቹን ለማረም አፈወርቅን የሚያግዙት መስታወቶች በየክፍሉ ማዕዘናት ተሰቅለዋል። የእነዚህ መስታወቶች ተግባር ስዕሎቹን ገልብጠው ማሣየት ነው።

አፈወርቅ ተክሌ እንግዳ የሚቀበልበት፣ የሚዝናናበትና ራት የሚጋብዝበት ሣሎንና ምግብ ቤቱም ቢሆን በስዕል የደመቁ ናቸው። ቪላ አልፋ በአጠቃላይ የሥዕል ቤት ነው። የአርቲስቱ ስዕሎች መኖሪያ ቤት ነው። ምግብ ቤት የነበሩት መኝታ ቤት ይሔዳሉ፤ መኝታ ቤት የሔዱት ስቱዲዮ ይገባሉ። በአዲስ አይንና በአዲስ ሁኔታ እንዲያያቸው ስለሚፈልግ ሁል ግዜ ያዟዙራቸዋል።

አፈወርቅ ተክሌ ለመጀመሪያ ጊዜ 200 ታላላቅ የአገር መሪዎች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ ሣይንቲስቶች፣ ደራሲያን፣ ሰአሊያን ተመርጠው ስማቸውና ታሪካቸው ተፅፎ ወደ ጨረቃ ሲላክ የአፈወርቅ የሕይወት ታሪክ ተፅፎ ወደ ጨረቃ ተልኳል፡ የተላከው ግልባጭም በምግብ ቤቱ ውስጥ ልዩ ቦታ ተሰጥቶት መቀመጡን እያልነህ ይገልፃል።

የአፈወርቅ ተክሌ የፀሎት ቤት ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነው። ሥዕል ሲጀምር፣ ሥዕል ሲጨርስ፣ ወደ ጉዞ ሲሄድ፣ ከጉዞ ሲመለስ፣ ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚቀርብበት የፀሎት ቤት አለው። አፈወቅር ስለ ፀሎት ቤቱ ሲናገር፣ የፈጣሪዎች ሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር መሆኑን የማስታውሰው፣ እዚህ ፀሎት ቤቴ ውስጥ ገብቼ ስፀልይ ነው … ይል እንደነበር አያልነህ ሙላት ፅፎታል። ከታላላቅ ሰዎች የተሰጡ ገፀ በረከቶች በፀሎት ቤቱ ይገኛሉ። ከግብፅ፣ ከሩሲያና ከግሪክ ኦርቶዶክሶች፣ የታላላቅ የሃይማኖት አባቶች፣ ከጳጳሣት… ከመሣሠሉት እንግዶች የተሠጡ ሽልማቶች በፀሎት ቤቱ ውስጥ አሉ።

የቪላ አልፋ የመጨረሻው ፎቅ ሠገነቱ ነው። የተፈጥሮ ውበት፣ ተራሮች፣ የጠራው ሠማይና ደመና፣ ክዋክብት፣ ጨረቃ የሚያዩት እዚህ ሠገነት ላይ ሆኖ ነው። በአብዛኛው በአርቲስቱ ስራዎች ላይ የምናስተውላቸው ዳመናዎች ከዚህ ሠገነት ላይ ሆነው በግልፅ ይታያሉ። ከዳር እስከ ዳር ደመናዎችን በስፋት ለማጥናት ይህ ቦታ ጥሩ እድል ይሰጣል።

አፈወርቅ ቀደም ባሉት ዘመናት በዚህ ሠገነት ላይ በየወሩ የፓርቲ ድግስ ያዘጋጅበት ነበር። በቅርብ ወዳጆቹ ተጠርተው ፈንጠዝያ ያደርጉበታል። ሻምፓኝ ይከፈታል። ሙዚቃ ተከፍቶ ይደነሣል። አንዳንድ ግዜም ሮማንቲክ የሆነ ቦታ ስለሆነ ገጣሚያን ግጥሞቻቸውን ያነቡበታል። በአፈወርቅ የመጨረሻው ጊዜ አካባቢ ደግሞ አርቲስቱ የሚያስደስተው ከሰገነቱ ሆኖ የራሱን የግቢ አትክልቶች ከላይ ካሉት የተፈጥሮ ዳመናዎች ፣ከዋክብት ፀሐይና ጨረቃ ጋር አጣምሮ ያያል።

የሰገነቱ ሥነ ሕንፃ የተሠራው የአንኮበር ከተማን እንዲያስታውስ ተደርጐ ነው። አፈወርቅ የልጅነት ትዝታውን በዚህ መልክ ያስታውሰው ነበር። ያ ውበት በሕሊናው ተቀርጾ ስላደገ እኔም በአቅሜ 42 ደረጃዎችን በቤቴ ውስጥ ገነባሁ። እነዚህን አርባ ሁለት ደረጃዎች ከተወጡ በኋላ በዚህ ሠገነት ላይ ሆነን የምናያቸው ተራሮች በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉት ናቸው ይል ነበር።

አፈወርቅ ተክሌ ከ100 በላይ አለም አቀፍ ሽልማቶችን የተቀበለ፣ እጅግ ውድ የሚባሉ የከበሩ ሽልማቶችና ስጦታዎችን ሰብስቦ ቪላ አልፋ ውስጥ ያስቀመጠ፣ ታላላቅ የስዕል ስራዎቹን በገንዘብ የማይለወጡ ብሎ ያስቀመጠበት፣ በምንም ማካካሻ የማይለወጠውን ይህን ቪላ አልፋ ገንብቶ አልፏል። በኘላኔታችን ላይ እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የሚለውን ማዕረግ ተቀብሏል።

     አፈወርቅ ተክሌ ጥቅምት 12 ቀን 1925 ዓ.ም ከናቱ ከወ/ሮ ፈለቀች የማታወርቅ እና ከአባቱ ከአቶ ተክሌ ማሞ በጥንታዊቷ ከተማ በአንኮበር ተወለደ። ማክሠኞ ሚያዚያ 2 ቀን 2004 ዓ.ም በሕክምና ላይ እንዳለ መሞቱ ተነገረ። ሥራዎቹ ግን የዘመን ኬላን እያሣበሩ ገና በመጪዎቹ ትውልዶች ውስጥ ስምና ዝናውን ሲያስጠሩት ይኖራሉ።

ይምረጡ
(14 ሰዎች መርጠዋል)
13422 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us