የድፍረት ፊልም ድፍረት አበራሽ በቀለ ስንት ጊዜ ትደፈር?

Wednesday, 10 September 2014 10:35

በድንበሩ ስዩም

ልክ የዛሬ ሣምንት ነሐሴ 28 ቀን 2006 ዓ.ም ከ10 ሰዓት ጀምሮ ብሔራዊ ቴአትር ቤት አካባቢ በከፍተኛ የፀጥታ ቁጥጥር ስር ዋለ። በቁጥጥር ስር የዋለበት ምክንያት “ድፍረት” የተሰኘ ፊልም ስለሚመረቅ በዚህም ምረቃ ላይ ባለሥልጣናት፣ አምባሳደሮችና ታላላቅ ሰዎች ለመታደም ወደ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ስለተጓዙ ነው። እነዚህ ሁሉ ትልልቅ ስብዕናዎች ወትሮም ባልተለመደ ሁኔታ ለድፍረት ፊልም እንዲህ ከያሉበት ነቅለው መምጣታቸው ራሱ አነጋጋሪ ነገር ነበር። ምክንያቱም ፊልም ስለሚወዱ ነው ወይስ በሌላ ምክንያት እያልኩ ሳሰላስል ነበር። ብቻ ቴአትር ቤቱ ከተለመደው ሁኔታ ለየት ባለ መልኩ በእጅጉ ደምቋል። ቀይ ምንጣፍ ተዘርግቷል። ቆነጃጅት ሞዴልስቶች እንግዶችን ሲቀበሉ ቆዩ። አዳራሹ ሞላ። ታዳሚዎች ቦታቸውን ያዙ። ያ በጉጉት የሚጠበቀው ድፍረት ፊልም ሊጀመር ሆነ።

ይህን ድፍረት የተሰኘውን ፊልም ፕሮዲዩስ እንዳደረገችው የሚነገርላት በአለማችን ላይ እጅግ ዝነኛ ከሆኑት የፊልም ተዋናይቶች መካከል በግንባር ቀደምነቷ የምትታወቀው አንጀሊና ጆሊ ነች። አንጀሊና የድፍረት ፊልም ኤግዝኪቲቭ ፕሮዲውሰር ወይም አንጡረ ገንዘቧን አውጥታ ያሰራች ነች ተብሎ ሲነገር ቆይቷል። ስለዚህ ፊልሙ በባለቤትነት የአንጀሊና ጆሊ ነው ተብሎ ይታሰባል። የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር ደግሞ ኢትዮጵያዊው ዘረሰናይ ብርሃኔ መሀሪ ነው።

ስለዚህ የአንጀሊና ጆሊ ስም እና ዝና በአለም ላይ የናኘ በመሆኑ ድፍረት የተሰኘ ፊልም ፕሮዲዩስ አደረገች እየተባለ በመነገሩም የፊልሙ ስምም እንደዚያው ገነነ። የተለያዩ ሁለት አለማቀፍ ሽልማቶችንም አገኘ ተባለ። በየድረ-ገፁ ሰፊ ሽፋን ተሰጠው።

የዚህ ፊልም ርዕሰ ጉዳይ ደግሞ የኢትዮጵያ ጉዳይ በመሆኑ አያሌ ኢትዮጵያዊያንም ሊመለከቱት ወደዱ፤ ናፈቁ። ለዚህም ነው ፊልሙ በሀገሩ ኢትዮጵያ ለመታየት ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት። በዚህ ቀን አንጀሊና ጆሊ እና ባለቤቷ ብራድ ፒት ይመጣሉ ተብሎ ወሬ የተናፈሰ ቢሆንም በመጨረሻም ሁለቱም ከያኒዎች አልመጡም። ለዚህ ደግሞ የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር በሰጠው መልስ ኢቦላን ፈርተው ነው ያልመጡት ብሏል።

ነሐሴ 28 ቀን 2006 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር ቤት ይህን ፊልም ለመመረቅ ከ1200 ታዳሚያን በላይ ቁጭ ብለዋል። የፊልሙ ባለቤት አንጀሊና ጆሊ ከምትኖርበት ከዩናይትድ ስቴትስ በስካይፒ ለብሔራዊ ቴአትር ቤት ታዳሚያን በድምጿ መልዕክት እያስተላለፈች ነው። ይህን ያልተነገረለት የኢትዮጵያ ታሪክ እዩት እያለች ተረከች። መልካሙንም ተመኘችልን። በመጨረሻም ያ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ድፍረት ፊልም ተጀመረ። ትንሽ እንደተጓዘ ድንገት ፊልሙ ቆመና ጨልመው የነበሩት የአዳራሹ መብራቶች በሩ። ያልተለመደ ሁኔታ ስለነበር ሁሉም ድንግጥ አለ። የፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር ዘረሰናይ ወደ መድረኩ መጣ። ምን ሊናገር ነው ተብሎ ሲጠበቅ አንድ ያልተለመደ ጉዳይ ተናገረ። “ፖሊሶች መጥተው ፊልሙ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ታግዷል ብለዋል። ስለዚህ እዚህ ላይ ማቋረጥ እንገደዳለን። ነገሮች ሲስተካከሉ በሌላ ጊዜ እንገናኛለን” ብሎ ይቅርታ ጠይቆ ታዳሚውን አሰናበተ።

ብዙ የተወራለት፤ በየቦታው በሽልማት መንበሻበሹ የተነገረለት ድፍረት ፊልም የከፍታ ጣሪያ ላይ ከወጣ በኋላ ድንገት ሽምድምድ አለ። ለመሆኑ ፊልሙ ለምን ታገደ? ከድፍረት ፊልም በስተጀርባ ምን ችግር አለ? የሚሉትን ነጥቦች ለማየት እሞክራለሁ።

ድፍረት የተሰኘው ይኸው (የአንጀሊና ጆሊ) ፊልም የታሪኩ መሠረት እና የጀርባ አጥንት ወይም የታሪኩ እስትንፋስ የሆነው የዛሬ 18 ዓመት እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተ አንድ አስገራሚ ታሪክ ነው። ታሪኩ ሙሉ በሙሉ እውነት ነው። ድፍረት ፊልምም የዚህን እውነተኛ ታሪክ ሁኔታ ነው ወደ ፊቸር ፊልምነት ቀይሮት የሰራው። ታሪኩ እንዲህ ነው።

የዛሬ 18 ዓመት አንዲት አበራሽ በቀለ የምትባል የ14 ዓመት ታዳጊ ወጣት አርሲ ውስጥ ቀርሳ በምትባል ከተማ ከቤተሰቦቿ ጋር ትኖር ነበር። አንድ ቀን ወደ ትምህርት ቤት ደብተሯን ይዛ ስትሔድ ድንገት በፈረሰኞች ትከበባለች። ከዚያም በፈረሳቸው ላይ አፈናጠዋት ይዘዋት ይነጉዳሉ። ሰዋራ ቦታ ወደሚገኝ ቤት ያስገቧትና ከፈረሰኞች መካከል አንደኛው የ14 ዓመቷን አበራሽን ይደፍራታል፤ ክብረ-ንፅህናዋን ይወስዳል። አበራሽም በማታውቀው ሰው እንደተጠለፈች ትገነዘባለች። ይህ ሰው በተደጋጋሚ የወሲብ ጥቃት ይፈፅምባታል። አበራሽ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ በዚያች ቤት ትቆያለች። በመጨረሻም ከዕለታት በአንዱ ቀን ታግታ ከምትደፈርበት ቤት ታመልጣለች። ስታመልጥ ደግሞ በቤት ውስጥ ያገኘችውን ጠመንጃ ይዛ ነበር። ታዲያ ባመለጠችበት ሰዓት ጠላፊዎቿ ነቁ። እንደገና ሊይዟት ወደ አበራሽ በቀለ ዘንድ መሮጥ ጀመሩ። እሷም እንዳይዟት ለማምለጥ እግሬ አውጭኝ እያለች ትበራለች። እነሱም እንደሚታደን አውሬ ያዛት እያሉ ይከተላሉ። በመጨረሻም ድጋሚ ሊይዟት፤ ሊጠልፏት ተቃረቡ። አበራሽ በቀለ ስንት ጊዜ ትጠለፍ? ስንት ጊዜ ትደፈር? ስንት ጊዜ ካለ ፍላጎቷ፣ ካለ ፈቃዷ ትጠቃ? አበራሽ ከዚህ ጉድ የሚያላቅቃት አንድ አማራጭ በእጇ አለ። ጠመንጃ! ቆም አለች። በእጇ ላይ ያለውን ጠመንጃ ሊይዛት ወደተቃረበው ሰው ላይ ተኮሰች። ሊይዛት የነበረው ሰው ወደቀ። ሕይወቱም አለፈች። ያ ሰው የጠለፋት፣ ያለፍላጎቷ የደፈራት፣ ክብረ-ንፅህናዋን የገሰሰው ሰው ነበር። አበራሽ በቀለም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለች።

ከዚያም የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ይህን ጉዳይ ሰማ። ማህበሩ ለአበራሽ በቀለ ጥብቅና ቆመ። ከብዙ ጊዜ ክርክር በኋላ አበራሽ ነፃ ወጣች። ነፃ የወጣችበት ምክንያት ራሷን ለመከላከል በወሰደችው እርምጃ ነበር።

ይህ ከላይ የሰፈረው ታሪክ እውነተኛው የአበራሽ በቀለ ታሪክ ነው። ወደ ዝርዝሩ ስንገባ አበራሽ በቀለ ብዙ መከራ የደረሰባት የ14 ዓመት ጉብል ነበረች። ከምትኖርበት ቀርሳ እስከ ዛሬ ድረስ በስደት ነው ተሸሽጋ ያለችው። አበራሽ አሳዛኟ የዚህ ማህበረሰብ አካል ነች። የመደፈርን እጣ ፈንታ ተሸክሜ አልኖርም ብላ ለህሊናዋ ነፃነትና አርነት የቆመች የሴቶች ተምሳሌት ነች።

የዚህችን ልጅ ሙሉ ታሪክ የዛሬ 15 ዓመት አለማቀፉ ቴሌቭዥን ጣቢያ BBC የ50 ደቂቃ ግሩም የሆነ ዶክመንተሪ ፊልም ሰርቶ ለአለም አሰራጨው። አበራሽ ከ15 ዓመታት በፊት ከገጠሯ ቀርሳ ተነስታ የአለም ህዝብ የመነጋገሪያ አጀንዳ የሆነች የጥቃትና የነፃነት አርአያ ሆነች። የBBCቴሌቭዥንም በሰራው School Girl Killer በተሰኘው ዶክመንተሪ ፊልም ምክንያት ለአበራሽ በቀለ ድጋፍና እርዳታ ያደርግላት እንደነበር ባለታሪኳ ራሷ ሰሞኑን በሬዲዮ ፋና አዲስ ጣዕም ተብሎ በሚጠራው የሬዲዮ ዝግጅት ክፍል ከ18 ዓመታት በኋላ መግለጫ ሰጥታለች።

አሁን ደግሞ ወደ መነሻችን እና ዋና ርዕሰ ጉዳያችን ወደሆነው ድፍረት ፊልም እንምጣ። ድፍረት የተሰኘው ፊልም ታሪኩ የተፃፈውና ዳይሬክት የተደረገው በዘረሰናይ ብርሃኔ መሀሪ ነው። “በዚህ ፊልም ውስጥ ያለው ታሪክ ሙሉ በሙሉ የኔ ነው። የኔን ታሪክ ሳያስፈቅደኝ ፊልም ሰርቶበት ማሳየት አይችልም። እኔ በታሪኩ ምክንያት ላለፉት 18 ዓመታት ተሸሽጌ ነው የምኖረው። በከፍተኛ ችግር ውስጥ ነኝ። እንደገና ካለኔ እውቅና ታሪኬ ፊልም ሆኖ ሲወጣ የተረሳው ነገር ደግሞ መነጋገሪያ ሆነ። እኔን በበቀል የሚፈልጉኝ የሟች ቤተሰቦች አሉ። ይሔ ፊልም ደግሞ ደህንነቴም እንደገና አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደርገኛል” የሚል ሃሳብ ያለው ንግግር በአዲስ ጣዕም የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ስትናገር ተደምጣለች።

በዚህ ምክንያትም ፍርድ ቤት ከሰሰች። ፍርድ ቤቱም ፊልሙ ለህዝብ እንዳይታይ፣ እንዳይመረቅ የእግድ ትዕዛዝ ሰጠ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ከብሔራዊ ቴአትር ቤት የምረቃ ስነ-ሥርዓት ላይ ድፍረት ፊልም እንዲቆም የተነገረው። እናም ድፍረት ቆመ። ታገደ።

የድፍረት ፊልም ደራሲና ዳይሬክተር ዘረሰናይ ብርሃኔ መሀሪ ለአዲስ ጣዕም አዘጋጅ በሰጠው መግለጫ ይህ ታሪክ የአበራሽ ብቻ አይደለም። የብዙ የኢትዮጵያ ሴቶች ታሪክ ነው። በወቅቱ በልዩ ልዩ ሚዲያዎች ስለቀረበ የሕዝብ ታሪክ ነው። ይህን ታሪክ ወስጄ እንደፈለኩ ልፅፍበት ላስተምርበት መብት አለኝ የሚል ሃሳብ ሰንዝሯል።

ባለታሪኳ አበራሽ በቀለ ደግሞ ይህን አባባል ትሞግታለች። ይህ ታሪክ የሕዝብ ታሪክ አይደለም። የኔ ታሪክ ነው። በ14 ዓመቷ የተጠለፈች። በ14 ዓመቷ የተደፈረች፤ በ14 ዓመቷ ጠመንጃ ይዛ ከጠላፊዋ ቤት ያመለጠች፤ በ14 ዓመቷ ጠላፊዋ ደግሞ ሊደፍራት፣ ሊጠልፋት ሲል እምቢኝ ብላ ጠመንጃ ተኩሳ የደፈራትን የገደለች ሌላ ባለታሪክ ካለች ትምጣ። የዚህ ታሪክ ባለቤት እኔ ነኝ፤ ብላለች አበራሽ በቀለ።

ጉዳዩ የመነጋገሪያ አጀንዳ ከፍቷል። ዘረሰናይ እንደሚለው ከሆነ የአበራሽን ታሪክ ማንም ሰው እንደልቡ በነፃነት ካለ እሷ ፈቃድ ፅፎ ሊጠቀምበት፣ ፊልም ሰርቶ ሊያገኝበት፣ ሊሸለም ሊሞገስበት ይችላል ወይ? የአበራሽ ታሪክ ራሱ ያልተፃፈ ድንቅ ስክሪብት ነው። እሷ ሳትፈቅድ ይህን የሕይወት ስክሪብቷን መውሰድ ይቻላል ወይ?

በድፍረት ፊልም ዙሪያ በርካታ አነጋጋሪ ጉዳዮች አሉ። ዘረሰናይ ብርሃኔ መሀሪ ከአበራሽ ሌላም ክስ መጥቶበታል። ከሳሹ ደግሞ አቶ ፍቅሬ አሸናፊ የተባሉ ሰው ናቸው። ሰውየው የሕግ ባለሙያዋ የወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ወንድም ናቸው። እርሳቸው ደግሞ የስክሪብቱ መነሻ ሃሳብ የኔ ነው የሚል ክስ ይዘው ፊልሙ እንዲታገድ ከአበራሽ በቀለ ጋር ሆነው ዘረሰናይን ከሰዋል።

ድፍረት ሌላም አነጋጋሪ ነገሮች አሉት። በፊልሙ ውስጥ በዋናነት ታሪኩ የተሰራው ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ አበራሽ በቀለን (የፊልም ስሟ ሂሩት) እሷን ከእስር ለማስፈታት የሚጥሩትን፣ የሚዳክሩትን ውጣ ውረድ የሚያሳይ ነው። በድፍረት ፊልም ውስጥ ወ/ሮ መአዛ፣ የአበራሽ በቀለ (የሂሩት) ጠበቃ ሆነው ነው የሚታዩት። ፊልሙ መአዛ አሸናፊን በአበራሽ ሕይወት ውስጥ አግንኖ ሲያወጣ የሚያሳይ ነው። እውነታው ግን ይሄ አይደለም። የዛሬ 18 ዓመት የአበራሽ ጠበቃ ሌላ ሴት ናቸው። ዛሬ በህይወት የሉም። ወ/ሮ መአዛ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር እንጂ የአበራሽ ጠበቃ እንዳልሆኑ ይነገራል። ድፍረት ፊልም ላይ ግን ጠበቃ ሆነው ቀርበዋል።

ድፍረት ፊልም ወደ አንድ ሚሊዮን ዶላር እንደወጣበት ዘረሰናይ ብርሃኔ መሀሪ ይገልጻል። የፊልሙ ፕሮዲዩሰር አንጀሊና ጆሊ ነች እየተባለ ሲነገር ቆይቷል። አሁን አሁን ደግሞ ዘረሰናይ ሲናገር አንጀሊና ለፊልሙ ምንም ሳንቲም አላወጣችም። ፊልሙን ስለወደደችው ስሟን እንድንጠቀምበት ጠየቅናት፤ ፈቀደችልን። ስለዚህ በስሟ ለመጠቀም እንደ ኤግዝከቲቭ ፕሮዲዩሰር አድርገን ተጠቀምንበት ሲል ከፊልሙ ምርቃት አንድ ቀን በፊት ዘረሰናይ እንደተናገረ የአዲስ ጣዕም የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጆች ገልጸዋል። እውነት አንጀሊና ጆሊ ብሯን ሳታወጣ፣ በባዶ ሜዳ ነው ሕዝብ የምታሳስተው? ብለን እንድንጠይቅም ያደርጋል። ይህን ዘረሰናይ የሚናገረውን ነገር እንዴት መቀበል ይቻላል? በዚህ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠት ያለባት ራሷ አንጀሊና ጆሊ ነች። ፊልሙን እሷ ፕሮዲዩስ እንዳደረገችው በየአደባባዩ ሲነገር ቆይቶ አሁን ደግሞ ሸራፋ ሳንቲም አላወጣችበትም እየተባለ ነው። ይህ የአመቱ ሌላው አስገራሚ ታሪክ ነው። እውነት ከሆነ ደግሞ አንጀሊና ጆሊ አጭበርባሪ እና ዋሾ ሴት መሆኗ ነው።

    ይህ የሰሞኑ ትልቅ መነጋገሪያ አጀንዳ የሆነው ድፍረት ፊልም ገና ተመዘው ያላላቁለት ጉዳዮች አሉ። አበራሽ በቀለ እና ፍቅሩ አሸናፊ የክሳቸው መጨረሻ ምን ይሆን? ድፍረት ፊልም ስንት ብር ወጣበት? ስንት ብርስ አገኘ? አንጀሊና ጆሊ እና ድፍረት ፊልም እውነተኛ ግንኙነታቸውን ማነው የሚያስረዳን? አበራሽን ሳያስፈቅዳት ታሪኳን የደፈረው ማን ነው? እነ አበራሽ በቀለ መክሰስ ያለባቸው አንጀሊና ጆሊን ነው ወይስ ዘረሰናይን? የፊልሙ ባለቤት ማን ነው? በነዚህና በሌሎች አስገራሚ ጉዳዮች ላይ ሳምንት እመለስበታለሁ።

ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
13029 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us