ስለ ዘመን

Wednesday, 17 September 2014 14:19

የኢትዮጵያውያን አቆጣጠርና
የአውሮፓውያን አቆጣጠር ልዩነት

 

 

በድንበሩ ስዩም


 

      “መስከረም” ከግዕዙ “ከረመ” ከሚለው ግስ የተባዛ ነው ይባላል። ሌሎች ሲናገሩ መነሻው “መሰስ-ከረም” (ክረምቱ መሰስ ብሎ ማለፉን)፣ ወይም “መዘክረ-ዓ.ም” (የዓመት መታወሻ) ይባላል፤ በማለት የሚገልጹ አሉ።
     ኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠሯ የተለየበት ምክንያት በየአመቱ የሚነሳ ጥያቄ ሆኖ እስከአሁን ድረስ አለ። አያሌ ሊቃውንትም በዚህ ረገድ ማብራሪያና መግለጫ ሲሰጡ ኖረዋል። ለዛሬ ደግሞ የመናገሻ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት ካዘጋጀው ጦማር ስለዚሁ ጉዳይ የሚለውን ላቋድሳችሁ።
     በኢትዮጵያውያንና በአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር መካከል በርካታ መሠረታዊ የሚባሉ ልዩነቶች ይታያሉ። ለዚህም ይመስላል ብዙዎች ዘመን መለወጫ በመጣ ቁጥር ጥያቄ ያነሳሉ። ኢትዮጵያዊያን ዕለተ ቀመርን ወይንም ዘመን መለወጫን የምናደርገው በመስከረም ሲሆን የአውሮፓውያን የዘመን መለወጫ፤ ታህሳስ /December/ 29 ልደትን አክብረው ጥር /January/ 1ቀን ዘመን መለወጫቸው ነው።
      በኢትዮጵያውያን ዓመተ ምህረታችን 2005 ሲሆን የነሱ 2013/2014 ይሆናል። ይህም የሰባት ዓመት ከስምንት ወር ልዩነት ይኖረናል። ኢትዮጵያዊያን ሁሉንም ወራት በሠላሳ ቀናት ከፍለን አስራ ሁለት ወር ከ 5 ቀን ጳጉሜ አድርገን ስንቆጥር፤ አውሮፓውያን ግን 28፣ 30፣ 31 በማድረግ 365 ቀኑን አስራ ሁለት ወር ብቻ በማድረግ ይቆጥራሉ። ከላይ የተመለከትናቸው ዋና ዋና ልዩነቶች ሲሆኑ ከዚህ ቀጥለን እነዚህ ልዩነቶች ለምን እንደተፈጠሩ ባጭሩ እንመለከታልን።


የዘመን መለወጫ ልዩነት

 


      ኢትዮጵያዊያን ዘመን የምንለውጠው መስከረም አንድ ቀን /ዕለተ ቀመር/ ነው። መስከረም የዘመን መለዋጫ የሆነበት ምክንያት፡- በዚህ ወር ቀኑና ሌሊቱን እኩል የሚሆኑበት ነው። ቀኑ ሙሉ 12 ሰዓት ሌሊቱም ሙሉ 12 ሰዓት ይሆናል። ምክንያቱም ከመስከረም 26 እስከ ታህሳስ 26 ድረስ ፀሐይ በምድር ወገብ አካባቢ ስለምትሆን የቀኑን ርዝማኔ እኩል ይሆናል።
      በሀገራችን ይህ በዓል ለመከበሩ የሚቀመጡ እውነታዎች ሲኖሩ ይኸውም፤ በዚህ ወር ንግሥት ሳባ ኢየሩሳሌም ደርሳ የጠቢብ ሰሎሞንን ጥበብ አድንቃ ስትመለስ ዕንቍ ለጣትሽ ብሎ በርካታ የከበሩ ዕንቍ በስጦታ የተበረከተላት በዚህ ወር በመሆኑ የዘመን መለወጫ በመስከረም አንድም እናደርጋለን። በዚህም የተነሳ መስከረም አንድ ቀን እንቁጣጣሽ በመባል ይታወቃል። መሳ10÷1 ፀሐይ የ365 ቀናትና ጉዞዋን ፈፅማ አንድ ብላ የምትጀምረው በዚህ ወር ነው።
      አንድም፡- የክረምቱ /የጨለማው/ ወራት የሚያበቃበትና ወርሃ ጽጌ የሚጀምርበት ወር በመሆኑና
አንድም፡- ኖህና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃ ድነው ምድር መድረቋን /አበባና ፍሬ መስጠቷን/ የተመለከተው በዚህ ወር ነበር። ዘፍ. 8÷8 በዓመቱም /ከ12 ወር በኋላ/ የዘመን መባቻ መጀመሪያ ወይም የዘመን መለወጫ አድርጎ አክብሯል። ኩፋሌ 24÷7 “በመጀመሪያ ወር መባቻ ለራሱ መርከብ ይሠራ ዘንድ ታዘዘ በእርሷም ምድር ደረቀች።” እንዲሁም እግዚአብሔር በዚህ ወር ለሙሴ የዘመን መለወጫ ይሆን ዘንድ አዞታል። ዘሌ 23÷53
     እግዚአብሔር ለእስራኤል በአዘዘው ሥርዓት መሠረት ከግብፅ በወጡበት በሰባተኛው ወር የሚከበር በዓል ነው። በክርስትናው ዘመን እስከ ዐሥራ አንደኛው ክ/ዘመን ድረስ ዓለም በአንድነት በዚህ ወር በመጀመሪያው ዕለት ያከብር ነበር። ነገር ግን ጎርጎርዮስ ሰባተኛ /1073-1035/ የዘመን መለወጫ ከልደት በዓል ጋር እንዲያያዝ በማለት ወደ ጥር አዞረው በዚሁ መሠረት የምዕራቡ ዓለም በጥር ወር ሲያከብር የምሥራቅ ግን እስካሁን መስከረምን አለቀቁም በዚህ ወር አዲስ ዓመታችን ከሚጀምሩ መካከል ግሪክ፣ ሩስያና ሮማንያ ተጠቃሾች ናቸው። ለኢትዮጵያና ለእስክንድሪያ ቤተ ክርስቲያንም ይኸው መስከረም ወር አዲስ ዓመታቸው መባቻ /መግቢያ/ ነው። በዚህም መሠረት ቤተክርስቲያናችን ዕለቱን እስከዚህ ያደረስን በማለት እግዚአብሔርን የምታመሰግንበት የአጽዋማትና የበዓላትን /የዐዋድያቱን/ የምታውጅበት ፍሬ ምድርን ባረካ የአዲሱ ዓመት አገልግሎት አሐዱ ብላ የምትጀምርበት ታላቅ በዓል ነው።

 

የሰባት ዓመት ከስምንት ወር ልዩነት ለምን ተገኘ?

 


     የጎርጎርዮሳዊያን አቆጣጠር ስንመለከት ብዙው ነገር የተዘበራረቀ ወጥነት የሌለው እንደሆነ እንመለከታልን። በወራቱ ውስጥ ያሉት ቀናት የተለያዩ መሆን እና የጌታን ልደት ለማክበር መነሻ ያደረጉት ታሪክን እንጂ ቅዱሳን መጻሕፍትን አለመሆኑ ነው። የጌታን ልደት ሊያከብሩ የተጠቀሙት ሮም ከተመሠረተች ስንት ዓመት አንደሆነ በማስላት ነው። ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ሮም ከተመሠረተች 753 ዓመቷ ነው በማለት ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቆጥረዋለወ። ይህም ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ 5508 ዓመተ ዓለም ነበር ማለት ነው። ነገር ግን ቤተክርስቲያን የጌታ (ጽንሰት) የቆጠረችው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 5500 ዓመተ ዓለም ዓመተ ፍዳ ከተፈፀመ በኋላ ያለውን አድኖናል በማለት ነው። ከዚህ ጊዜ በኋላ ያለውን ዓመት ምህረት በማለት የጌታ(ጽንሰት) መሆኑን ታስተምራለች። ለዚህም መሠረት ያደረገችው ቅዱሳን መጻሕፍት ነው።
     “በሀሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድሕክ ውስተ መርኀብከ- 5 ቀን ተኩል ሲፈፀም አድንሃለሁ።” አንዲት ቀን ለእግዚአብሔር እንደ አንድ ሺህ ዘመን ነው። መዝ 89÷4፤ 2ጴጥ 3÷8 ይህም ማለት 5ሺህ 5 መቶ ዘመን ሲፈፀም አድንሃለው የሚለውን አምላካዊ ቃሉን መሠረት በማድረግ ልደተ ክርስቶስን እናከብራለን። ይህ ቀን መድኃኒታችን ከድንግል ማርያም የተፀነሰበት ቀን ቀኑም መጋቢት 29 በዘመነ ዮሐንስ በዕለተ እሑድ ነው። ይህ ቀን እንዲሁ በዋዛ የተደረገ ሳይሆን ሐዋርያው ቀዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው በጽኑ ቀጠሮ ነው። ወአመ በፅሐ ዕድሜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ ወተወልደ እምብእሲት - የዘመኑ ፍፃሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ልጁን ላከ ገላ 4÷4 በማለት የገባው ቃል በተፈፀመ ጊዜ መጥቶ እንዳዳነን ተናግሯለል።
     እንደ ቤተክርስቲያን ይህ ዓይነት ልዩነት የተገኘው በዓመተ ምህረት ብቻ ሳይሆን ከጥንት ማለትም ከጌታችን ልደት በፊት ጀምሮ የመጣ ነው። ልዩነቱም በኦሪት አማካኝነት የተከሰተ ሲሆን ኦሪት አራት ጊዜ ተፅፏል። የመጀመሪያው ሙሴ የፃፈው ሲሆን ኦሪት ዘሌዋውያን ይባላል። ሁለተኛው ኦሪት ዘሊቃውንት ሲሆን ይኸውም በጥሊሞስ 70 ሊቃውንት ሰብስቦ የብሉይ ኪዳን ሊቃውንት የብሉይ ኪዳን መጽሓፍትን ከዕብራይስጥ ወደ ቅብጥ /ግሪክ/ ሲያስተረጉም የተፃፈ ስለሆነ ኦሪት ዘሊቃውንት ተብሏል። ስልምናሶር የተባለ ንጉሥ 10 ነገድ ማርኮ በሰማሪያ አስፍሯቸው መቅሰፍት ሲጨርሳቸው ምክንያቱን ሲጠይቁ ያዕቆብ አቡነ እግዚአብሔር አምላክነ የማይል በሰማሪያ አይኖርም ሲሉት ምናሴ ካህን ልኮላቸው አስተምሯቸዋል።
     አንተኑ ተዐቢ እምያዕቆብ አቡነ ዘወሀበነ ዘንተ ዐዘቅተ አንተ ከያዕቆብ አባታችን ትበልጣለች ብላ ሳምራዊቷ ሴት ጌታን የጠየቀችው በዚህ ምክንያት ነው። ዮሐ 4÷1 ካህኑ ምናሴም ኦሪትን የፃፈላቸው ኦሪት ዘአይሁድ ነው። አይሁድ የክርስቶስ ሰው መሆን በፅኑ ተቃውመው ጌታን ሰቅለውታል። ከእሱ በኋላ የተነሳው ቀዳሚ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ ስለ ክርስቶስ ሰው መሆን ሲያስተምር ጊዜው ሳይደርስ ደረሰ ፣ ሥጋ ሳይለብስ ለበሰ ትላለህ ብለው በእስጢፋኖስ ላይ ተነሱበት። እሱም መጽሐፈ ብሉይን አውጥቶ ሱባዔ አበውን ቆጥሮ /በትንቢተ ÷ያለውን ተርጉሞ/ ረታቸው። በዚህም ጊዜ የዘመናት አቆጣጠር ዝብርቅርቁ ወጥቷል። የኛይቱ ቤተክርስቲያን ትምህርተ እስጢፋኖስን ተቀብላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 5500 ዘመን ሲፈፀም መጥቶ አዳነን በማለት ታስተምራለች።
የአስር ቀን ልዩነት ለምን ተገኘ?
      ሌላው የዘመን ልዩነት ያመጣው በጎርጎርዮሳዊያን አቆጣጠር ፀሐይ የምትዞረው 365 ቀን ከአምስት ሰዓት ነው ይላሉ። ቤተ ክስቲያናችን ደግሞ 365 ቀን ከ6 ሰዓት ወይንም ከ15 ኬክሮስ ነው ትላለች። ስለዚህ በየዓመቱ እነዚህ አንድ አንድ ሰዓታት አጠራቅመው የቀን ልዩነት እንዲኖር አድርገዋል። ለምሳሌ በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር መስከረም አንድ ቀን ነው። ስለዚህ የቀናት ልዩነት የተከሰተው በዚህ ምክንያት ነው።
የወራት መዛባት
      ጎርጎርዮሳዎያን ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ወራቶቻቸው ዝብርቅርቅ ያለ ነው። በእያንዳንዱ ወራት ውስጥ ያሉ የቀናት ብዛት የተለያዩ ናቸው። በየካቲት /February/ ወር 28 ቀናት ሲኖሩት ሌላውን ሰባቱን ወራት 31 ቀን የቀሩትን አራት ወራት 30 ቀን በማድረግ 365 ቀናቱን ይፈጽማሉ።
      ኢትዮጵያዊያን ግን 12ቱን ወራት ሙሉ ሰላሳ ቀን አድርገን የተቀረውን ጳጉሜን 5 ቀን በማድረግ 13ኛ ወር ትሆናለች። ፀሓይ የምትዞረው 365 ቀን ከ6 ሰዓት /15 ኬክሮስ/ ስለሆነ እነዚህን 6 ሰዓታት ወይንም 15 ኬክሮስ በአራት ስናባዛው አንድ ቀን /24 ሰዓት/ ይሆንና በ4 ዓመት አንድ ጊዜ በዘመነ ሉቃስ ጳጉሜ ስድስት ትሆናለች። ይህም ሁኔታ እንደ አውሮፓውያኑ የተዘበራረቀ እንዳይሆን አድርጎታል።
      የአውሮፓውያን የወራት ስያሜ መሠረት ያደረጉት ያመልኳቸው የነበረውን ጣዖታት (አማልክት) እንዲሁም የታዋቂ ሰዎችን ስም በመጠቀም ነው።

 

 

 1. በአውሮፓውያን መጀመሪያ ወር ጃንዋሪ /January/ በኢትዮጵያውያን ጥር ይባላል። ጃኑስ /Janus/ በሚባለው የሮማውያን ጣዖት ስም የተሰየመ ነው።
 2. ሁለተኛው ፌብሩዋሪ /February/ በእኛ የካቲት ሲሆን ቃሉ የተወሰደው ፌብሩዋሬ /Februare/ ከሚለው የላቲን ቃል ሲሆን መንፃት /መዘጋጀት/ ማለት ነው። ይህም ስያሜ የተሰጠው በጁሊየስ ቄሳር ዘመነ ነበር። በጁሊያን አቆጣጠር ዘመን መለወጫ በመጋቢት /Marhc/ ስለሆነ በዚህ ወር ለአዲስ ዓመት የሚዘጋጁበት ነው። ስለዚህ ፌብሩዋሬ ወይንም መዘጋጀት ብለውታል።
 3. ሦስተኛው ወር ማርች /Marhc/ በእኛ መጋቢት ይባላል። ማርቲቭ /MARTIVE/ ወይንም የማርስ ጌታ / honor of mars / ከሚል ቃል የወሰዱት ሲሆን ይህም የጦርነት አምላካቸውን /gods of war/ ለማስታወስ የሰየሙት ነው።
 4. አራተኛው ወር አፕሪል/April/ በእኛ ሚያዝያ ሲሆን አፍሮዳይት ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የሰየት ነው።

 


     ሰባተኛ ወር ኦክቶበር /Aphrodite/ ስምንተኛ፣ ኖቨምበር /May/ ዘጠነኛ፣ ዴሴምበር /Maria/ አስረኛ ወር ይሆናል።
ከዚህ የምንረዳው የወራት ስያሜ የተሰጠው በጁሊያን አቆጣጠር ጊዜ መሆኑን ያሳየናል።
የዕለታት ስያሜ ልዩነት
     ኢትዮጵያውያን ቀኖቻችንን የሰየምነው በሥነ ፍጥረት ላይ ተመስርተን ነው።

 

 

 1. እሑድ አሐደ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አንድ አደረገ የመጀመሪያ ሆነ ማለት ነው። በዚህ ቀን ፍጥረታት መፈጠር ስለጀመሩ እሑድ ተብሏል።
 2. ሠኑይ /ሰኞ/ ሠነየ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም ሁለት አደረገ ማለት ነው። ለሥነ ፍጥረት ሁለተኛ ስለሆነ ሰኑይ /ሰኞ/ ተብሏል።
 3. ሠሉስ/ማግሰኞ/ ሠለሰ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ሦስት አደረገ ማለት ነው። ማግሰኞ የሚለው የሰኞ ማግስት ማለት ነው።
 4. ረቡዕ ረብዐ /አራት አደረገ/ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ለሥነ-ፍጥረት አራተኛ ቀን ማለት ነው። 
 5. ሐሙስ ሀመሰ /አምስት አደረገ/ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ለሥነ-ፍጥረት አምስተኛ ቀን ማለት ነው። 
 6. ዓርብ ዓረበ ከሚል ግስ የተገኘ ሲሆን ተካተተ ማለት ነው። ፍጥረት እሑድ መፈጠር ጀምረው ዓርብ ስለተካተቱ /ተፈጥረው ስለተፈፀሙ/ ዓርብ ተብሏል።
 7. ቅዳሜ ቀዳሚ ሲሆን ሰንበተ ክርስቲያን ከሆነችው ከዕለተ እሑድ ቀድማ ስለምትገኝ ቀዳሚት ሰንበት /ቅዳሜ/ ተብላለች።

 


    አውሮፓውያን ግን ቀኖቻቸውን የሰየሙት ልክ እንደ ወራቶቻቸው ሁሉ በጣዖቶቻቸውና በአማልክቶቻቸው ስም ነው።

 

 

 1. ሰንዴይ /Sunday/ ማለት የፀሓይ ቀን ማለት ነው። በፀሓይ ያመልኩ ስለነበር የፀሓይ ቀን ማለት ብለውታል።
 2. መንዴይ /Mon-day/ የጨረቃ ቀን ማለት ሲሆን በጨረቃ ስለሚያመልኩ የሰየሙት ነው።
 3. ቲዮስዴይ /tues-day/ ቲዮ የሚባል የጦርነት አምላክ ስለነበራቸው ለሱ ማስታወሻ የሰየሙት ነው።
 4. ዌድንስዴይ /Wednes-day/ የታላቁ አምላክ የዎደን ቀን በማለት ሰይመውታል።
 5. ተርስዴይ /Thurs-day/ ቶር በሚባለው የነጎድጓድ አምላክ ስም ደይመውታል።
 6. ፍራይዴይ / Fri-day / የታላቁ አምላክ የዎደን ሚስት ስሟ ፍሪግስ ይባል ስለነበር ለሷ መታሰቢያ እንዲሆን ፍራይደይ ብለውታል።
 7. ሳተርዴይ /Satur-day/ የሰማይ ኮከብ የሳተርን የከዋክብት ቀን ማለት ሲሆን በከዋክብት ያመልኩ ስለነበር ሳተርዴይ ብለውታል።

 


የሰዓታት ልዩነት

 


      ጎርጎርዮውያን 365 ቀን ከ5 ሰዓት ከማድረጋቸውም በተጨማሪ ከፀሐይ ዙሪያ ጋር በተያያዘ በቀኑ ውስጥ ያሉት ሰዓታት ወጥነት የላቸውም። አውሮፓውያን በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ /ከምድር ወገብ/ ከላይ ስለሚገኙ ፀሐይ በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ስትሆን ቀኑ በመርዘም ሌሊቱ ያጥራል፤ በደቡባዊ ንፍቅ ክበብ ስትሆን ቀኑ በመርዘም ሌሊቱ ረዝሞ፤ ቀኑ ያጥራል። እኩል 12 ሰዓት ቀን 12 ሰዓት ሌሊት የሚሆንበት ጊዜ በጣም ትንሽ ነው፤ ይህም ፀሐይ በምድር ወገብ አካባቢ በምትሆንበት ጊዜ ብቻ ነው።
      የኢትዮጵያውያን ሰዓት ግን ሁልጊዜም በ12 ሰዓት የተከፈለ ነው። ቀኑ ሙሉ 12 ሰዓት ሌሊቱን ሙሉ 12 ሰዓት ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኘው በምድር ወገብ አካባቢ በመሆን ነው።
የኢትዮጵያ ሰዓት የሚጀምረው ከሣልሲት /ከቅጽበት ነው/
    60 ሣልሲት= 1ካልዒት /150ው ካልዒት አንድ ነው/
    60 ካልዒት = 1 ኬክሮስ ነው
    60 ኬክሮስ = 1 ዕለት ወይም 24 ሰዓት ይሆናል።
    60 ደቂቃ = 1 ሰዓት ነው
    የአውሮፓውያን በየጊዜው የሰዓቱ መለዋወጥ በኢትዮጵያውያንና በአውሮፓውያን አቆጣጠር መካከል ልዩነት እንዲመጣ ሳያደርግ አይቀርም የሚል መላምት መኖሩን ሳልገልጽ አላልፍም።
     መልካም አዲስ ዘመን ይሁንልን።

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
11696 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us