የታላቁ አርቲስት ሃይማኖት ዓለሙ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ትናንት ተፈፀመ

Wednesday, 24 September 2014 11:59

በጥበቡ በለጠ

 

ሃይማኖት ዓለሙ በኢትዮጵያ የቴአትር መድረክ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ከሚባሉት ተርታ የሚቀመጥ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ገና ቴአትር እንደ ሙያ ተቀባይነት አግኝቶ ባልተስፋፋበት ወቅት ሃይማኖት ባህር ተሻግሮ አሜሪካ ሜኔሶታ ውስጥ በዚሁ ሙያ የማስተርስ ድግሪውን ተቀብሎ ወደ ሀገሩ የመጣ ነው። ከዚያም ከብዙ ግርግር በኋላ ወደ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ተቀላቀለ። ብዙ ግርግር ያልኩት ሃይማኖት በቴአትር ጥበብ የማስተርስ ድግሪውን ይዞ ሲመጣ የሚቀጥረው አጣ። የዚያን ጊዜ በዚህ የትምህርት ደረጃ ማስታወቂያ አልወጣም ነበር። ታዲያ ሃይማኖት በጉዳዩ ቢበሳጭም ሌላ አማራጭ ፈለገ። ሌላ የሥራ እድል ቃኘ። ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ሔደ። በሕዝብ ግንኙነት ሥራ ተቀጠረ። በኋላ ደግሞ አብዮት ፈነዳ። የዚህን ጊዜ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን የቴአትር ቤቱ ዳይሬክተር ሆነ። አራት አይናው ፀጋዬ ባለሙያዎችን ከየቦታቸው እየሰበሰበ አመጣ። ሃይማኖት ዓለሙን ወደ ብሔራዊ ቴአትር ቤት አመጣው። ከዚያም የአርት ዳይሬክተር አደረገው። እጅግ ድንቅ የሚባሉ የትወና ጥበቦችን ማሳየት ጀመረ።

በወቅቱ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ደበበ እሸቱ እና ሃይማኖት አለሙ ገናና ተዋናዮች ሆነው የመጡበት ጊዜ ነበር። የዛሬ ጉዳያችን ሃይማኖት አለሙ ስለሆነ ወደ እርሱ ላምራ።

ኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን የጀርመናዊውን የበርቶሌት ብሬሽትን Mother courage የተሰኘውን ቴአትር በድንቅ የአተረጓጎም ስልት እናት አለም ጠኑ ብሎት ኢትዮጵያዊኛ ለዛ ሰጥቶት ወደ መድረክ አመጣው። በዚህ ቴአትር ውስጥ ሃይማኖት አለሙ እስረኛውን ዳምብልን ሆኖ ነበር የሚሰራው። ወጋየሁ ንጋቱ ደግሞ ጅሎ ሞሮን ሆኖ ይተውናል። ደበበ እሸቱ ገራፊውን ገብረየስ ወክሎ ይጫወታል። ሌሎችም ብርቅዬ ተዋናዮችን ቴአትሩ ይዟል። በዚህ በእናት አለም ጠኑ ቴአትር ውስጥ ሃይማኖት አለሙ የትወና ብቃቱን አሳይቶበታል።

ሃይማኖት የወከለው ገፀ-ባሪ ፈሪ ነው። ቦቅቧቃ ነው። ነገር ግን ሊያጠቁት የፈለጉት ሰዎች ጀግና ነው ብለው ከነበላይ ዘለቀ ጋር እንዲታሰር አድርገውታል። አንድ ቦቅቧቃን ጀግና ነው ብለው ከጀግናው፣ ከአማጩ፣ ከጦረኛው፣ ከአስፈሪው፣ ከአርበድባጁ. . . በላይ ዘለቀ ጋር አንድ እስር ቤት አስቀምጠውታል። በዚህ ብቻም አይደለም፤ ምስጢር አውጣ እየተባለም ይገረፍ ነበር። ታዲያ ሲገረፍ እንዲህ አለ።

“የሚሉኝን ቢያጡ፣ የሚያደርጉኝ ቢጠፋቸው ጀግና ነው ብለው ከጀግና ጋር አስረው ገረፉኝ። እኔ ጀግና አይደለሁም። ጀርባዬስ ለምን በጅራፍ ይገረፋል?” የሚል ሃሳብ የያዘ ቃለ-ተውኔት ያሰማል ዳምብል (ሃይማኖት አለሙ)

በዚህ ጊዜ እስረኞችን የሚገርፈው ደግሞ ገራፊው ገብረየስ (ደበበ እሸቱ) ነበር። ገብረየስ እንዲህ አለ።

“ዳምብል፤ የአንተ ጀርባ በጅራፍ፣ የእኔ ጀርባ ደግሞ በታሪክ እንደተወቀሱ ይኖራሉ” ይለዋል።

ቴአትሩ በውስጡ አያሌ ቁም ነገሮች ያሉበትና ፍልስፍናዊ አስተሳሰቦችን የሚያንፀባርቅ ነው። በዚህ ትልቅ ቴአትር ውስጥ ችሎታውን በድንቅ ብቃት አስመስክሯል ሃይማኖት።

ከዚህ ሌላም በኢትዮጵያ የቴአትር አለም ውስጥ ከፍተኛ ተፅእኖ ፈጣሪ የሚባለው የመድረክ ሥራ ቴዎድሮስ የተሰኘው የፀጋዬ ገ/መድህን ቴአትር ነው። ፍቃዱ ተክለማርያም ቴዎድሮስን ወክሎ ከመጫወቱ በፊት ሃይማኖት ዓለሙ የአፄ ቴዎድሮስን ገፀ-ባህሪ ወክሎ በኢትዮጵያ የቴአትር መድረክ ላይ ከአይን ያውጣህ የሚያሰኝ የአተዋወን ብቃት እንዳሳየ በወቅቱ የነበሩ ፅሁፎችና እማኞች ያስረዳሉ።

በቴዎድሮስ ቴአትር ውስጥ የአፄ ቴዎድሮስ ባሕሪ ከባድ የሚባል ነው። ይህንን ባሕሪ ወክሎ ለረጅም ሰዓታት መድረክ ላይ መቆየትም ሌላው የብቃት ደረጃ ነው። እኚህ ጀግናን መሪ ውስጣዊ ውስብስብ አስተሳሰቦችን ተላብሶ በመተወን ሃይማኖት አለሙ ፈር ቀዳጅ ተዋናይ ነው።

“ይልቅስ ተረት ልንገርሽ፣ የተላከ ከእንግሊዝ ዘንድ

እጅህን ስጥ አለኝ ፈረንጅ፣ እጅ ተይዞ ሊወሰድ፣

ምን እጅ አለው የእሳት ሰደድ?

አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ።

            .

            .

            .

እያለ ሃይማኖት ዓለሙ በኢትዮጵያ የቴአትር መድረክ ላይ ናኝቶበታል።

ሃይማኖት ዓለሙ ከተወናቸው ድንቅዬ ቴአትሮች መካከል ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት የተሰኘውን የባለቅኔውን ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ቴአትር ይገኝበታል። ይህ ቴአትር መሠረታዊ መቼቱ /Setting/ ሐምሌ 21 ሌሊት ለ6 ሰዓት ሩብ ጉዳይ፣ 1928 ዓ.ም ነው። ስፍራው አዲስ አበባ፣ ገነት ልዑል ቤተ-መንግስት፣ ዛሬ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስ ያኔ፣ የኤል ማርሻሉ ሮዴልፍ ግራዚያኒ፣ ለኢጣሊያ መንግስት የኢትዮጵያ እንደራሴ መኖሪያ ቅጥር ግቢ ነው እያለ መቼቱን ፀጋዬ አስተዋውቆታል። በዚህ ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት በተሰኘው ቴአትር ውስጥ ወጋየሁ ንጋቱ አቡነ ጴጥሮስን ወክሎ ይተውናል። ሃይማኖት ዓለሙ ደግሞ ሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻን ወክሎ ይጫወታል። ወጋየሁ የአቡነ ጴጥሮስን ለሀገር፣ ለወገን፣ ለአላማ፣ ለእምነት መሞትን መሰዋትን ግሩም አድርጎ በድንቅ ብቃት ተውኗል። ሃይማኖት አለሙም የሹባሽን ለኢጣሊያ ያደረን እኩይ ባህሪ ወክሎ ምርጥ የትወና ችሎታውን አሳይቷል። ሎሬት ፀጋዬ ይህን ሃይማኖት አለሙ ወክሎ የሚጫወተውን ገፀ-ባሪ ሁለንተናውን እንዲህ ይገልፀዋል።

     “ሹምባሽ ባሻ አባ ግርሻ፣ የሰላሳ ሶስት ዓመት ጎልማሳ፣ ቀጠን፣ ረዘም ያለ፣አቋቋመ መልካም፣ ሾጤ የጮሌ ጭራቅ፣ የጋኔል ልዝብ፣ የጊዜ ብልጥ፣ ንቁ፣ አንደበተ ምዝን፣ ወገኑን ናቂ፣ ለራሱ አዋቂ፣ እማይነደው፣ እማይበርደው፣ ዓይነ ግትር፣ ልበ ጥጥር፣ ጨለሄ አበሻ ነው። በዝግታ ፈገግ ሲል፣ ግንባሩ በዘልማድ የሚሳብ ላስቲክ እንጂ ከህይወት የሚፈልቅ ወዝነት የለውም። ምርር አርጎ የሚጠላው የለውም፤ የሚንቀው ሞልቶታል፤ ልቡ ወዶ አያውቅም። ልዝብነቱንና ንፉግ ራስ ወዳድነቱን በቁጠባ ስለሚጠቀምበት፣ የተመዘነ አስተያየት አለው ብለው በስህተት የሚያምኑበት ስለሚበዙ፣ ያአያሌ ሰው ልብ አኮላሽቶ አባክኗል። ጊዜን በጊዜ፣ ዕድልን በዕድል፣ አመዛዝኖ፣ አመጣጥኖ ይገዛል ይሸጣል ይነግዳል እንጂ አያምንም አይታመንም፣ አይወድም አይጠላም፣ አይስቅም አያለቅስም። ቂም ቢይዝ ተፈጥሮ ለሞት በሚላት ሕይወት እንጂ በሰው አይደለም፤ በስልጣን እንጂ በእውነት አያምንም፤ ወዳጅነቱ አደጋ ነው፤ መሳሪያነቱ ፍቱን ነው። በጎነትን በከንቱነት የሚያዛምድ፣ ለመበለጥና ለመጠቀም የማይመለስ፣ የቅንነት ገፊ፣ የመቅሰፍት ሊቅ ነው። ሮፊልፎ እንኳ መሳሪያነቱን ቢያደንቅም ባህርዩ ይዘገንነዋል። ውልደቱ፣ አነሳሱ አይታወቅም፤ አጨራረሱም አይታወቅም። ይህም አመጣጡ፣ ጴጥሮስን በማግባባት፣ በማሳሳት ወይም በመሸጥም ቢሆን፣ ለግራዚያኒ ለፖለቲካ መሳሪያ ለማድረግ ነው። የሱ ድልና ትግል የአእምሮ እንጂ የደምና የልብ ሕዋስነት የለውም”

ይለዋል ፀጋዬ ገ/መድህን። እንግዲህ ሃይማኖት አለሙ ይህን በተንኮልና በሸር የተገማመደ ገፀ-ባህሪን ነው ወክሎ እንዲሰራ የተመረጠው። ታዲያ በዚህ ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት ቴአትር ውስጥ እነዚህን የተገማመዱ ባህሪ በድንቅ የአተዋወን ችሎታው በስኬት የጨረሰ የኢትዮጵያ ብርቅዬ ተዋናይ ነበር።

ሃይማኖት አለሙ ከትወና ችሎታው ሌላ የግጥም አነባነብ ስልቱ፣ የመድረክ አመራር ብቃቱ፣ የማስታወቂያ ባለሙያነቱ፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎውና የደራሲነት ብሎም የዳይሬክተርነት ተሰጥኦው በጣም ትልቅ ነበር። ኢትዮጵያ ሃይማኖት አለሙ ያለውን ችሎታ ሳትጠቀምበት አልፏል ማለትም ይቻላል።

የዚህ ብርቅዬ ተዋናይ ስርዓተ ቀብሩም ትናንት (መስከረም 13 ቀን 2007 ዓ.ም) በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ቤተ-ክርስትያን አያሌ አድናቂዎቹ ጓደኞቹ፣ ተማሪዎቹ፣ ቤተሰቦቹ በተገኙበት ስነ-ሥርዓት ተፈፅሟል።

ትናንት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ በተካሔደው የሃይማኖት አለሙ የቀብር ሥነ-ሥርዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትሪያሪክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ተገኝተው ፀሎተ-ፍትሃቱን የመሩ ሲሆን፣ ሌሎችም ብፁአን አባቶችና የቤተ-ክርስትያኒቱ ቀሳውስትም ተገኝተዋል። የቀድሞው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር መሐመድ ድሪል እና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለሃይማኖት አለሙ የመጨረሻውን አሸኛኘት አድርገውለታል።

በስርዓተ ቀብሩ ላይ የህይወት ታሪኩን ያነበበው የዘመናት ጓደኛውና የሙያ አጋሩ የሆነው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ነው። እንደ ደበበ አቀራረብ ሃይማኖት ዓለሙ የተቀበረው ስጋው እንጂ የጥበብ መንፈሱ ገና ብዙ ዘመን ትኖራለች፤ ህያው ነች ብሏል።

የሃይማኖት ዓለሙ የህይወት ታሪክ እንደሚናገረው የተወለደው እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ከአባቱ ከአቶ ዓለሙ ዱኪ እና ከእናቱ ከወ/ሮ ዘነበች ገ/ስላሴ ነበር። እድገቱም የቤተሰቦቹ የእርሻ መሬት በነበረበት ሆለታ ነው። እድሜው ለትምህርት ሲደርስ ቤተሰቦቹ በሚኖሩበት ሆለታ በሀገር ልምድ መሠረት የአማርኛ ትምህርቱን ተከታትሏል።

ሃይማኖት ዘመናዊ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንንና በኮተቤ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ትምህርት ቤት አጠናቆ፣ የከፍተኛ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ አሜሪካን ሀገር አቀና። እዚያም የትምህርት እድል አግኝቶ ከሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ የአንደኛ ድግሪውን በከፍተኛ ክብር ተቀበለ። ይህ ዩኒቨርስቲ የሰጠውን ፌሎውሽፕ ተጠቅሞ ሁለተኛ ድግሪውን በክብር ለማግኘት ችሏል። ለምረቃው ያቀረበው የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን የዋርካው ሥር ንግርት (ኦዳ ኦክ ኦራክል) ዩኒቨርሲቲውንም እንዲወክል ተመርጦ በበርካታ ቦታዎች ተውኔቱ እንዲታይ ተደርጓል። ሃይማኖትም የቴአትር አምባሳደርነቱን የጀመረው ያኔ ነው በማለት የህይወቱ ታሪኩ ይናገራል።

ሃይማኖት አለሙ ናይጄሪያ ላይ በተካሔደው በመጀመሪያ የአለም የጥቁር ህዝቦች የባህል ፌስቲቫል ላይ ሀገራችንን ወክሎ የሄደው የባህል ቡድን አባል ሆኖ ነው። ኢትዮጵያ ተካፋይ በሆነችበት በሁለተኛው የአለም የጥቁር ህዝቦች የባህል ፌስቲቫልም ላይ በናይጄሪያ የቀረበውን “ትግላችን” የተባለውን የማይም ድራማ ድርሰት በማዘጋጀት ሀገራችን ኮከብ ሀገር ተብላ እንድትሰየም ካደረጉት ባለሙያዎች አንዱ ሃይማኖት አለሙ እንደነበርም ተገልጿል።

ይህ “ትግላችን” የተሰኘው ድራማ በኩባ -ሐቫና ላይ በተካሔደው የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ሲጋበዝ፣ ቡድኑን መርቶት የሔደው ሃይማኖት ነበር። በመድረኩ ላይ ሃይማኖት ጓንታላሚራ የተባለውን እውቅ የኩባ ሙዚቃ በታወቁት ዝነኛ መሪ በፊደል ካስትሮ ፊት በመጫወት ከፍተኛ ዝናን ለራሱ፣ ክብርና ኩራት ለሀገሩ ማጎናፀፉን በቀብሩ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተነግሮለታል።

ሃይማኖት ከቴአትር ጥበብ ክህሎት ባሻገር የሀገር ፍቅር ናፍቆቱን የሚሰጠው፣ መንፈሱን የሚያረጋጋው፣ ሙዚቃ በመጫወት ነበር። ይህንንም ሙዚቃ የሚጫወተው እራሱን በራሱ ጊታር አስተምሮ ችሎታውን አዳብሮ ነው። በቅርቡም ከታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪ ከቴዲ ማክ (ቴዎድሮስ መኮንን) ጋር የሀገር ሰብ ሙዚቃዎችን ሰርቶ ወደማጠናቀቁ ደረጃ ነበር። ሃይማኖት ድምጻዊም ነበር ማለት ነው።

ሃይማኖት አለሙ በአሜሪካን ሀገር ሎሳንጀለስ ላይ እ.ኤ.አ. በ1988 ዓ.ም በተካሔደው በሼክስፒር ድርሰቶች አተዋወን ውድድር ላይ በመሳተፍ የኢራ አልድሪጅ አዋርድ ተሸልሟል። በ1989 በሎሳንጀለስ የአል ካሚኖ ዩኒቨርስቲ የፋክልቲ አባል በመሆን የሼክስፒርን ተውኔቶች አስተምሯል፤ አዘጋጅቷልም።

ሃይማኖት አለሙ የአንድ ወንድ ልጅ እና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበር። የአምስት የልጅ ልጆች አያት፣ የአንድ ልጅ ቅድመ አያት ለመሆን መብቃቱም ተገልጿል።

ታላቁ አርቲስት ሃይማኖት አለሙ ባደረበት ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ መስከረም 9 ቀን 2007 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።

     የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ለቤተሰቦቹ፣ ለልጆቹ፣ ለአድናቂዎቹ እና ለወዳጆቹ በሙሉ የተሰማውን ሀዘን እየገለፀ መፅናናትን ይመኛል።

ይምረጡ
(8 ሰዎች መርጠዋል)
16720 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us