ኢትዮጵያዊቷ ቤተ- እስራኤላዊት ዶ/ር

Wednesday, 08 October 2014 12:58

እስራኤል ውስጥ በተለይ ከኢትዮጵያ የሄዱ ቤተ-እስራኤላዊን በርካታ ቁጥር እንዳላቸው ይታወቃል። በተለያዩ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የተጓዙት እነዚህ ህዝቦች በአሁኑ ወቅት ልጆቻቸው አድገውና ተምረው በእስራኤል የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የባህል ህይወት ውስጥ በመግባት የበኩላቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

በውትድርናው መስክም በተለያዩ ታላላቅ ማዕረጎች ላይ የደረሱ አሉ። በፖለቲካውም መስክ በልዩ ልዩ የስልጠና እርከኖች ላይ የደረሱ እንዲሁም በአምባሳደርነት የተሾሙ ቤተ-እስራኤላዊያን ይገኛሉ። በኢንቨስትመንት እንዲሁም በኪነ-ጥበባት መስክ አያሌ ቤተ-እስራኤላዊያን መድረኩን ተቆጣጥረውት ይገኛሉ።

ሰሞኑን እስራኤል ውስጥ በሰፊው የሚታወቀው ‘The Jewish week’ ተብሎ የሚታወቀው መገናኛ ብዙሃን ደግሞ አንዲት የኢትዮጵያን ቤተ-እስራኤላዊት ታሪክ እና የወደፊት ህልሟንም ይዞ ወጥቷል። ወጣቷ የኢትዮጵያ ቤተ-እስራኤላዊት ዶ/ር ራሔል ነጋ ትባላለች። ይህች የህክምና ባለሙያ ዕድሜዋ ገና 29 ሲሆን በዚህ ዕድሜዋም በበጎ ተግባር ሥራ ላይ እንደተሠማራች ተዘግቧል። በጎ ተግባርን ባሕል እናድርገው በማለትም ትናገራለች።

ዶ/ር ራሔል በሲናይ ተራራ ላይ በሚገኘው በማናታን ሆስፒታል ለልብ ህሙማንና ሌሎችም በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገለች መሆኗ ተገልጿል። ስለዚህችው ወጣት የህክምና ሰው የተፃፈው የወደፊት ህልሟን ማድረግ የምትፈልገው በጎ ተግባሯ ነው። ይህም በእስራኤል ውስጥ የሚገኙ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ዜጎችን፣ አቅመ ደካሞችን በበጎ ፈቃደኝነት የህክምና አገልግሎት መስጠትን ዋና ተግባሯ አድርጋለች።

እስራኤል በዓለም ላይ ካሉ ሀገሮች በህክምና ጥበቧ ከቀዳሚዎቹ መካከል እንደምትገኝም የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህን የጎለበተ የህክምና ጥበብ ወደ ሌሎችም በእድገትና ስልጣኔ ወደ ኋላ የቀሩ ናቸው ተብለው በሚታሰቡ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት ለመለገስ ዶ/ር ራሔል ተነስታለች።

በተለይ ደግሞ እንደ እርሷ ያሉ የህክምና ባለሙያዎችን በማስተባበር ወደ ኢትዮጵያ እና ሌሎችም ሀገሮች በመዘዋወር በበጎ ፈቃደኝነት የህክምና አገልግሎት ለመስጠት እንደምትንቀሳቀስም ገልጻለች።

እንደ ዶ/ር ራሔል ነጋ ገለፃ የህክምና ሙያ ባለሙያዎች በየጊዜው ነፃ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ትመክራለች። ሐኪም ማለት ከፈጣሪ በታች ያለ የሰውን ልጅ ህይወት ጠባቂ ነው። ታዲያ ይህ ህይወት ጠባቂ ሰዎችን ገንዘብ እያስከፈለ ብቻ ማከም የለበትም። ገንዘብ የሌላቸውን አቅም ደካሞችን ደግሞ በፈጣሪ የተሰጠውን የህክምና ጥበብ ተጠቅሞ ሊረዳቸው ይገባል ስትል ተናግራለች።

በዓለማችን ላይ ያሉ አያሌ ሰዎች ለሞት የሚጋለጡት ተገቢ የሆነ የህክምና አገልግሎት ስለማያገኙ መሆኑን የምትናገረው ራሔል፣ በተለይ ደግሞ መታከሚያ አጥተው በገንዘብ ችግር ምክንያት ለከፋ አደጋ የሚጋለጡት ዜጎች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ታወሳለች።

    እንደ እርሷ አባባል በተለይ በሶስተኛው ዓለም ያሉ የህክምና ባለሙያዎች በዓመት ለተወሰኑ ጊዜያት ለህዝባቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸውና በዚህም የሰው ልጆችን መታደግ እንደሚችሉም የኢትዮጵያ ቤተ-እስራኤላዊቷ ዶ/ር ራሔል ነጋ ትመክራለች።

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
9805 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us