የዜማ ሊቁ አበበ መለሰ ኩላሊት ተለገሰው

Thursday, 16 October 2014 14:19

በጥበቡ በለጠ  

በኢትዮጵያ ውስጥ በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ብቅ ያለ የሙዚቃ ዜማ በማመንጨት በማፍለቅና በመፍጠር ወደር ያልተገኘለት ከያኒ አበበ መለሰ ለረጅም ጊዜ በሕመም ሲሰቃይ ቆይቷል። የሕመሙ መንስኤ ደግሞ ሁለቱም ኩላሊቶቹ መስራት በማቆማቸው ምክንያት በሕይወት የመቆየቱም ሁኔታ አጠራጣሪ ነገሮች ውስጥ ገብቶ ነበር። የእርሱን ሕይወት መልሶ ለማዳን ደግሞ አድናቂዎቹ፣ የስራ ባልደረቦቹና ወዳጆቹ የገቢ ማሰባሰብ ርብርብ አድርገውም ነበር። በመጨረሻም አበበ መለሰ ኩላሊት የሚለግሰው ሰው ካለ ጫፍ ላይ ያለችው ህይወቱ መልሳ እንደምትለመልም ተነገረ።

ለአበበ መለሰ ኩላሊት የሚለግሰውን በጎ ፈቃደኛ ለማግኘትም እንቅስቃሴ ተጀመረ። ሳሙኤል ተስፋዬ የተባለ ወጣት የአበበ መለሰን ህይወት ለመታደግ ቆርጦ ተነሳ። አንዱን ኩላሊቱንም ለመለገስ ፈቃደኝነቱን ገለፀ።

ከትናንት በስቲያ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በዋሽንግተን ሆቴል የአበበ መለሰ ሕክምና አስተባባሪዎች መግለጫ ሰጥተዋል። ዳዊት ይፍሩ፣ ንዋይ ደበበ፣ ኃይልዬ ታደሰ፣ ዮሴፍ ገብሬ እና ፍሰሃ ዘሩ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። መግለጫው እንደሚያመለክተው ደግሞ አበበ መለሰ የኩላሊት ንቅለ ተከላ በእስራኤል ሀገር ውስጥ በስኬት ተከናውኖለታል ተብሏል።

መግለጫ ከሰጡት የአበበ መለሰ የህክምና አስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆነው ድምፃዊ ኃይልዬ ታደሰ እጅግ ደስታ ተሰምቶት ሲናገር ተስተውሏል። በተለይ ደግሞ ኩላሊት ማን እንደለገሰ የተጠየቀው ኃይልዬ ሲናገር፡- “የአበበ መለሰን ህይወት የታደገው ወጣት ሳሙኤል ተስፋዬ እንደሚባል የተናገረ ሲሆን ይህ ወጣት ያደረገው ልገሳም እጅግ የሚያስመሰግነው መሆኑን ጠቅሶ፣ የኢትዮጵያን የሙዚቃ ታላቅ ሊቅ ከሞት ወደ ሕይወት መመለሱን ተናግሯል። በአሁኑ ወቅትም ኩላሊት ለጋሹ ሳሙኤል ተስፋዬ ከሆስፒታል መውጣቱን እና አበበ መለሰም በጥቂት ቀናት ውስጥ ህክምናውን ጨርሶ እንደሚወጣ ተናግሯል።

ሌላው የአበበ መለሰ ጤና እንዲሻሻል ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩትና ከአስተባባሪዎቹም አንዱ የሆኑት አቶ ፍስሃ ዘሩ ለፕሮግራሙ አዘጋጆች የተሰማቸውን ደስታ ሲገልፁ ተደምጠዋል።

“ይህ የህይወት ጉዳይ ስለሆነ፣ እንደገና የመወለድና የመፈጠር ነገር ስለሆነ ከምንም ደስታ በላይ ስለሆነ ስሜቴን መቆጣጠር አልቻልኩም። አንዳንዴ በደስታ የምታለቅስበት ነው የኔ ስሜት” በማለት ተናግረዋል። አያይዘውም ሲናገሩ፣ “አበበ መለሰ ስሜቱ የልጅ ስሜት ሆኖ ራሱን መቆጣጠር የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ነበር። ያ ሁኔታ በጣም ትልቅ ነገር ነው። ሕይወትን ከማዳን በላይ ምን አለ? እኔ እንባዬን መቆጣጠር አልችልም” ብለውም አልቅሰዋል አቶ ፍሰሃ ዘሩ።

አቶ ፍሰሃ ዘሩ ስለ አበበ መለሰ እና ኩላሊት ስለለገሰው ወጣት ሳሙኤል ተስፋዬ የጤና ሁኔታም መግለጫ ሰጥተዋል። እርሳቸውም የሚከተለውን ብለዋል።

“አቤ መስከረም 21 ቀን ነው ኦፕራሲዮን ያደረገው። ኦፕሬሽኑም ለአምስት ሰዓታት ያህል ነው የተደረገው። ኩላሊት የለገሰው ሳሙኤል ተስፋዬ ደግሞ ለሁለት ሰዓታት ነው ኦፕራሲዮኑ የፈጀበት። አቤ መስከረም 21 ኦፕራሲዮን ተደርጎ፣ የነቃው ደግሞ መስከረም 22 ቀን ነው። መስከረም 22 ጠዋት ከአቤ ከራሱ አንደበት “በጣም ተሳክቷል” የሚል ድምፅ ወጣ። አበበ እስራኤል ሀገር ከሄደበት ዘመን ጀምሮ እንደዚያች ቀን ተደስቶ ድምፅ አውጥቶ አያውቅም” ብለዋል። አያይዘውም ሲናገሩ፡-

“የነበረው ትልቁ ፈተና ልጁን ከዚህ አገር ልኮ አበበ ዘንድ ማድረስ ነበር። አንድ ዓመት ከሰባት ወር ፈጅቷል። ልጁን ማስመርመሩ፣ እዚያም እስራኤል ሀገር ከሔደ በኋላ ልዩ ልዩ ምርመራዎችና ሂደቶችን ለማለፍ አምስት ወራትን ፈጅቷል። ከአበበ መለሰ አንደበት ከተገኘው መረጃም የታከመበት የእስራኤሉ ሆስፒታል በኩላሊት ላይ ካደረጋቸው ህክምናዎች መካከል በጣም ስኬታማው እንደሆነ መግለፃቸው ተደምጧል። አበበ መለሰ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ በሕዝብ ርብርብ ብቻ ሳይሆን፣ የኩላሊት ለጋሽ በማግኘቱ ብቻ ሳይሆን ህያው ፈጣሪ እግዚአብሔር ከርሱ ጋር በመሆኑ ረድቶት ነው” በማለት አቶ ፍሰሃ ዘሩ ተናግረዋል።

የሙዚቃ ዜማ ሊቁ አበበ መለሰ ሕክምና በሚከታተልበት እስራኤል ሀገር ውስጥ አሁን በጣም ጥሩ በሚባል የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል። የሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም በአበበ መለሰ ስኬታማ ሕክምና የተሰማውን ደስታ እየገለፀ፣ ከያኒው ከታመመ ጊዜ ጀምሮ በርካታ አስተዋፅኦ ሲያድጉ የነበሩትን አካላት ሁሉ እያመሰገነ፣ በተለይ ደግሞ ኩላሊቱን የለገሰውን ወጣት ሳሙኤል ተስፋዬን በአክብሮት ያመሰግነዋል። 

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
13630 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us