ፕሮፌሰር ዓሊ መሐዙሪ - የጥቁር ሕዝቦች ሊቅ

Wednesday, 22 October 2014 12:22

ከ1926 - 2007 ዓ.ም

 

በጥበቡ በለጠ

 

በጐረቤት ሀገሯ ኬኒያ ውስጥ በተለይ ሞምባሳ ተብላ በምትታወቀው የወደብ ከተማ እ.ኤ.አ በ1933 ዓ.ም የተወለዱ ናቸው ዓሊ መሐዙሪ። አባታቸው በእስልምና ሀይማኖት ውስጥ የታወቁ ቃዲ (ዳኛ) ነበሩ። ዓሊ መሐዙሪ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን የተማሩት በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ነበር። ከዚያም ማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመማር ከጥቁር ምድር ውስጥ የተገኙ ትልቅ ምሁር ለመባል የበቁ ናቸው።

ፕሮፌሰር ዓሊ መሐዙሪ በዑጋንዳ ውስጥ ባለው ማካሬሬ ዩኒቨርሲቲ ውስጥም አስተምረዋል። አያሌ የአፍሪካን መሁራንን ያፈሩ ሰው ነበሩ። ከዚያም በነ ኢዲያሚን ዳዳ፣ እና በነ ፕሬዝደነት አቦቴ አምባገነናዊ ድርጊት አህጉሪቱን ለቀው ወደ አሜሪካ አቀኑ። እዚያም በልዩ ልዩ የዩናይትድ ስቴትስ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በመግባት አስተምረዋል። በዓለም ላይም አነጋጋሪው (አጨቃጫቂው) ምሁር እየተባሉም ይጠራሉ።

አጨቃጫቂው ምሁር የተባሉበት ምክንያት የሚያነሷቸውና ትክክል ናቸው ብለው የሚያምኑባቸውን ለየት ያሉ ጉዳዮችን በድፍረት የሚናገሩ በመሆናቸው ነው። ለምሳሌ አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ስለ ኢራን ያላቸው አመለካከት የተለየ ነው። ኢራን የኒውክሊየር መሣሪያዎችን ልታመርት ነው። የኒውክሊየር፣ የባዮሎጂካል ንጥረ ነገሮችን የያዘ አውዳሚ መሣሪያ አላት እየተባለ ሀገሪቱን በአሉታዊ መልክ መጥራትና መፈረጅ ተደጋግሞ የሚነገር ነው። በዚህም ሳቢያ ኢራን ላይ ማዕቀብ መጣል እና ሀገሪቱ ላይ የተለያዩ ተፅዕኖዎችን መፍጠር ለነ አሜሪካ የዕለት በዕለት ስራ ሆኗል። ታዲያ ይህን ድርጊት በግላጭ ከሚቃወሙ ታላላቅ ምሁራን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ፕሮፌሰር ዓሊ መሐዙሪ ናቸው።

ፕ/ር ዓሊ መሐዙሪ የእነ አሜሪካ እና የሌሎች የምዕራባዊያን ጫና ልክ አይደለም ባይ ናቸው። ኢራን ኒውክሊየር ብታመርትስ ለምን ትከለክላላችሁ? እናንተስ ብትሆኑ የኒውክሊየር መሣሪያ አምራቾች አይደላችሁም ወይ? እያሉ ይሞግታሉ።

ፕ/ር ዓሊ ለዚህ የአሜሪካ እና የኢራን ግጭት የሚሰጡት መፍትሔ ኒውክሊየርን የሚችል ሁሉ ያምርት፣ ሁሉም የኒውክሊየር ባለቤት ከሆነ ፍርሃት የለም። አንዱ የበላይ ሌላው የበታች ሆኖ የሚፈራበት ሁኔታ አይፈጠርም ባይ ናቸው። አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ እስራኤልና ሌሎችም ሀገሮች እንዳላቸው ሁሉ ኢራንም፣ ግብፅም፣ ሌላውም የዓረብ አገር ቢኖረው ጥፋቱ ምንድን ነው እያሉ የሚከራከሩ ዓለምአቀፍ ምሁር ናቸው።

ዓሊ መሐዙሪ በዚህ ክርክራቸው በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ አጨቃጫቂው ምሁር በመባል ይጠቀሳሉ። ብዙዎች የምዕራብ አስተሳሰብ ያለባቸው ምሁራን የዓሊ መሐዙሪን አመለካከት አይቀበሉትም። ሰውየው ለአሸባሪዎች መፈልፈል ምክንያት ናቸው እየተባሉም የጐሪጥ የሚያዩዋቸው አልጠፉም።

ዓሊ መሐዙሪ ወደ እስልምና ሀይማኖት ፍልስፍናቸው ጠልቀው የገቡትም ከኒውዮርኩ የመንትያ ህንፃዎች መፍረስ እና ከኦሳማ ቢንላደን (ከአልቃይዳ) ጋር ተያይዞ ከመጣው አመለካከት ጋር ተያይዞ ነው። የሙስሊም ሀይማኖት ተከታዮች ሁሉ ማሸማቀቅ ልክ አይደለም፤ እስልምና እና አሸባሪነት በፍፁም የሚገናኙ አይደሉም ባይ ናቸው ዓሊ መሐዙሪ።

ጭቆና ሲበዛ አመፅ ማካሄድ የተለመደ ነው። አመፅን ተቃውሞን ከአሸባሪነት ለየት አድርጐ ማስቀመጥ አለብን ባይ ናቸው። የምዕራባዊያንን አመለካከት የሚቃወሙ ሙስሊሞችን ሁሉ አሸባሪ ማለት ትክክል አይደለም የሚል ፍልስፍና አላቸው። እንደውም ጉዳዩ ብዙ እንዳይምታታ ብለው ጥናት ሰርተው አስነብበዋል። ሙስሊሙም ሆነ የምዕራብ አስተሳሰብ አቀንቃኙ እንዳይምታታባቸው በማለት የተቃውሞ ስነ-ምግባርን የሚያሳይ ጽሁፍ አበርክተዋል። ጽሁፉ Ethics of Violence የሚሰኝ ሲሆን፤ ስለ አመፅ ስነ-ምግባር የሚሰብክ ነው።

ፕሮፌሰር ዓሊ መሐዙሪ አሜሪካ ውስጥ በሚገኘው ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካን ባሕልና ጥንታዊ ስልጣኔ ለረጅም ዓመታት ሲያስተምሩ የቆዩ ናቸው። የእርሳቸው የቅርብ ጓደኛ የሆኑት ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር አየለ በክሪ እንደሚያስረዱት፣ ዓሊ መሐዙሪ “ዓለም አቀፉ ዓሊ” The Global Ali ተብለው የሚጠሩ እንደሆነም ይመሰክሩላቸዋል። የሚፅፉትና የሚናገሩት ነገር ሁሉ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ አከራካሪ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆኑን ነው የሚገልፁት።

በተለይ ደግሞ የጥቁር ሕዝቦች በሙሉ ተሟጋች በመሆን በዚህ በአለንበት ዘመን ከፊት የሚሰለፉ ሰው ነበሩ ዓሊ። ፕ/ር ዓሊ፣ የጥቁሮች ስልጣኔ እና ማንነት የከሰመው የቅኝ ገዢዎች ወረራ እና ጭካኔ የተሞላበት አገዛዝ በአፍሪካ ምድር ላይ በትሩን በማኖሩ መሆኑን በማስረዳት አያሌ የጥናትና የምርምር መጽሐፍትን አሳትመዋል። በሕይወት ዘመናቸው ከ40 በላይ መጽሐፍትን በማሳተም የሚታወቁት ዓሊ መሐዙሪ የአፍሪካ እና የአፍሪካዊያን ቋሚ ተከራካሪ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

የአፍሪካ ስልጣኔ ከየትኛውም የዓለማችን ክፍል ስልጣኔ ቀድሞ የታየ ነው በማለት ያስረዳሉ። አፍሪካን ያልሰለጠነ እና ኋላ ቀር ነው ብሎ ለሚያስበው የምዕራባዊያን አስተሳሰብ የሚያስረዳ የሚያስተምር የተጨበጠ ማስረጃ በመፃፍ የሚታወቁት እኚህ ምሁር አያሌ ጉዳዮችን አበርክተው አልፈዋል።

በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኛቸውንም በርካታ ታሪኮችን በአፍሪካ መነጽር እያዩ ጽፈዋል። አፍሪካ በሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችም ቢሆን ቀዳማይ አህጉር መሆኗን ይናገራሉ። እስልምና በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ሲጀምርና ከፍተኛ ግጭት ውስጥ በገባበት ወቅት ሰላማዊ መቀመጫው አፍሪካ ነበር። የነብዩ መሐመድ ልጆችና ቤተሰቦች ሸሽተው የመጡትና የኖሩት ብሎም እስከ ሕይወታቸው ፍፃሜ ድረስ በሰላም የኖሩት አፍሪካ ውስጥ ያውም ኢትዮጵያ መሆኑን ሁሉ አበክረው የፃፉ ምሁር ናቸው። በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ በእጅጉ የሚታወቀው ቢላል፣ በተለይም እስልምናን “አላህ ዋኩበር” በማለት ለሰው ልጆች ሁሉ ድምፁን ከፍ አድርጐ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጀው ከአፍሪካ ምድር በተለይም ከኢትዮጵያ የተገኘው ቢላል መሆኑን ያስረዳሉ። ከኢትዮጵያም በመለጠቅ የእርሳቸው የትውልድ ሀገር የሆነችው ኬኒያ በሞምባሳ ወደቧ በኩል የእስልምና ሃይማኖት በሰላም ገብቶ በሰላም የሚኖር የሰላም ተምሳሌት የሆነ ሃይማኖት መሆኑንም ጽፈዋል።

ከዚሁ ከእስልምና ሃይማኖት ፍልስፍና ሳንወጣ ዓሊ መሐዙሪ ለዓለም ካበረከቱት አስተሳሰብ አንዱ የሃይማኖቱ የምሁራን ሰነዶች የሚገኙት እዚሁ አፍሪካ ውስጥ ነው በማለት የፃፉትም አስተሳሰብ ነው። አፍሪካዊቷ ሀገር ማሊ ደግሞ በዚህ ትጠቀሳለች። ማሊ ውስጥ የምትገኘው “ቲምቡክቱ” ተብላ የምትታወቀው ከተማ የፕላኔታችን የእስልምና ሃይማኖት ቤተ-መዘክር እንደሆነች ዓሊ መሐዙሪ ጽፈዋል።

በዚህ አነስተኛ ከተማ ከሰባዎቹ መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተፃፉ የእስልምና ሃይማኖት ሰነዶች ይገኛሉ። በእነዚህ ሰነዶች ውስጥ ፍልስፍና፣ ሳይንስ፣ ሃይማኖት፣ የሂሳብ ቀመር፣ ጂኦግራፊ፣ ህክምና፣ ታሪክ እና ሌሎችም የእውቀት ዘርፎች በሙሉ ያሉበት እንደሆነ ያስረዳሉ። ስለዚህ አፍሪካ በሃይማኖቱም ረገድ ቀደምት ስፍራ የሚሰጣት እንደሆነ ይገልፃሉ።

በክርስትናው ሃይማኖትም ቢሆን፤ የዓለማችን ቁንጮ ተብላ የምትጠራው አፍሪካ ናት የሚል አመለካከት አላቸው። በዚሁ በክርስትያን ሃይማኖት ውስጥ ትልቅ መገለጫ የሆነው ፈጣሪ በራሱ እጅ ጽፎበታል የሚባለው አስርቱ ትዕዛዛት አሉበት ተብሎ የሚታመነው ፅላተ-ሙሴ የሚገኘው እዚሁ አፍሪካ (ኢትዮጵያ) ውስጥ እንደሆነ ዓሊ መሐዙሪ በየአደባባዩ ይናገራሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የብዙ የክርስትያን ሃይማኖት አድባራት እና ገዳማትን የገነባች የቆረቆረች፣ አያሌ የሃይማኖት ፈላስፎችን የፈጠረች፣ የራሷን ፊደልና ማንነት ለዓለም ያሳየች ትልቅ አፍሪካዊት ሀገር እንደሆነችም ዓሊ መሐዙሪ በልዩ ልዩ ጽሁፎቻቸው ገልፀዋል። አሜሪካ የምትባል ሀገርን ክርስቶፈር ኮሎምበስ ከማግኘቱ በፊት ኢትዮጵያ የራሷ ስልጣኔዎች የነበሯት ስርዓተ መንግስትም ኖሯት በዓለም የስልጣኔ ጐዳና ውስጥ እያበራች የምትጓዝ እንደነበረች ሁሉ ጽፈዋል።

ይህንን ጉዳይ እና ለሎችንም የፕ/ር ዓሊ መሐዙሪን አበርክቶዎች ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም የክብር ዶክትሬት ድግሪ ሰጥቷቸው ነበር። በዚህ የክብር ዶክትሬት ድግሪ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተውም ንግግር አድርገው ነበር። የመሰላቸውን እና ያመኑበትን ነገር ከመናገር ወደኋላ የማይሉት ፕ/ር ዓሊ መሐዙሪ አሁን ያለነውን ኢትዮጵያውያንንም የሚጐንጥ ንግግር አሰምተዋል።

እንደ እርሳቸው አባባል፣ ኢትዮጵያዊያን አፍሪካዊነታችንን በትክክል የተቀበልን ሰዎች እንዳልሆን ተናግረዋል። ሌሎች የአፍሪካን ሕዝቦች ገሸሽ እንደምናደርግ እና በራሳችን የግል ደሴት ላይ ብቻ እንደምንኖር የሚያመላክት ንግግር አድርገዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ምድር ሆና ሳለ፣ ለአፍሪካ አህጉር የቀደምት ስልጣኔ መመኪያ ሆና ሳለ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን ራሳችሁን ከአፍሪካ ጥቁሮች ነጥላችሁ የማየት አዝማሚያ አላችሁ በማለት ልክ ልካችንን ነግረውናል። ያውም በራሳችን ግብዣ ላይ ተገኝተው። ለዚያውም የክብር ዶክትሬት የሰጠናቸው ቀን!

አንዳንድ ሰዎች ይህን የፕ/ር ዓሊ መሐዙሪን ንግግር ምሁራዊ ድፍረት በማለት በአዎንታዊ መልኩ ይጠቅሱታል። ሳይፈሩ፣ ሳይሸማቀቁ ያመኑበትን ነገር በመናገር የሚመጣውን የሚቀበሉ ናቸው ይሏቸዋል። በኢትዮጵያ ግብዣ ላይ ኢትዮጵያን የሚወቅሱ ብለውም የፈረጇቸው አሉ።

የፕ/ር ዓሊ መሐዙሪን ንግግር አጥብቀው የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያንም አሉ። እንደውም ከዚሁ የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ስነ-ስርዓታቸው ላይ ከተናገሩት ንግግር በመነሳት የጥናትና የምርምር ሰነድም ተዘጋጅቶ ቀርቧል። የተዘጋጀው በኢትዮጵያ የጥናትና ምርምር ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ነበር። እንደ ጥናቱ ገለፃ የፕ/ሩ አባባል ስሜታዊነት የጐላበት እንደሆነ ይናገራል።

በአጠቃላይ ግን ፕ/ር ዓሊ መሐዙሪ የመሰላቸውን ያሰቡትን እና የመኑበትን ነገር በግላጭ የሚናገሩ፣ ምሁራዊ ድፍረት የተሞሉ ሊቅ እንደነበሩ የሚያውቋቸው ይመሰክሩላቸዋል።

ከእኚሁ የጥቁር ሕዝቦች የሊቃውንት ፊት አውራሪ ከሆኑት ከፕ/ር ዓሊ መሐዙሪ ስራዎች ውስጥ የአፍሪካን ጥንታዊ ስልጣኔ የሚያስረዳው ስራቸው The African የተሰኘው ዶክመንተሪ ፊልማቸው ነው። የአፍሪካን አህጉር ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ በሙሉ እየተዘዋወሩ የሰሩት ድንቅ ፊልም ነው።

በዚህ ፊልም ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ የሚያወጉት ጐንደር ሔደው፣ ከአፄ ፋሲል የተገማሸረ ቤተ-መንግስት ላይ ቆመው የኢትዮጵያን ስልጣኔ፣ የአፍሪካን ስልጣኔ ያስረዳሉ። ከኪነ-ሕንፃ አሰራሩ ብርቅዬነት የብዙ ነገሮች ተምሳሌት ከሆነው የጐንደር ከተማ ላይ ሆነው የሚናገሩት፣ በተለየ የአፍሪካ አህጉር በ17ኛውና በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በሙሉ በቅኝ ግዛት ስር ሲወድቁ ጐንደር ላይ ግን ኢትዮጵያ ነፃ መንግስት መስርታ ከፍተኛ ስልጣኔ ውስጥ መግባቷን ለማብሰር (ለመጠቆም) የፈለጉበት ትዕይንት ነው።

The Africans የተሰኘው ይኸው ዶክመንተሪ ፊልማቸው 8 ተከታታይ ክፍል ያለው ረጅም ታሪክ የያዘ ነው። የተሰራው እ.ኤ.አ በ1986 ዓ.ም ሲሆን፤ እነ BBCን ጨምሮ በርካታ የዓለማችን ቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሳይተውታል።

ፕ/ሮ ዓሊ መሐዙሪ ከሰሞኑ በ81 ዓመታቸው አሜሪካ ውስጥ አርፈው፣ አስከሬናቸውም ወደ ትውልድ ሀገራቸው ወደ ኬኒያ ሞምባሳ መጥቶ ከትናንት በስቲያ ስርዓተ-ቀብራቸው ተፈጽሟል። አፍሪካም ታላቁ ምሁሯን አጥታለች።¾

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
12622 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us