ፀጋዬ ገ/መድህን ስለ ራሱ፤ ፀጋዬ - ስለ ሎሬትነቱ

Wednesday, 29 October 2014 14:51

በጥበቡ በለጠ

 

ዓለም ብዙውን ጊዜ በግርምት ውስጥ ነች፡፤ መውጫና መግቢያዋ አይታወቅም። በትንሽ ዓመታት ርቀት ላይ አብረውን የነበሩ ሰዎች በአፀደ ሥጋ እንደዋዛ ተለይተውን ሲያልፉ እናያለን። ለምሳሌ የዛሬ 20 ዓመታት ግድም ኢትዮጵያዊ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ደራሲ መስፍን አለማየሁ እና ደራሲና ጋዜጠኛ ደምሴ ፅጌ አንድ ላይ ያወጉ ነበር። በተለይ መስፍን አለማየሁና ደምሴ ፅጌ፣ ፀጋዬ ገ/መድህንን ቃለ-መጠይቅ አድርገውለት ነበር። እነዚህ ሶስት ሰዎች በብዙ ነገሮች ዙሪያ ቁጭ ብለው ይፈላሰፉ ነበር። ዛሬ ግን ሶስቱም የሉም። ሶስቱም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ይህን የጋራ ጨዋታቸውን ባካሔዱ በ15 ዓመታት ጊዜያት ውስጥ ነው። ሶስቱም ዛሬ ባይኖሩም በመስከረም ወር በ1985 ዓ.ም ለዛ ብለው በሚጠሩት መፅሔታቸው ላይ ያወጉትን አጠር አድርጌ ላቅርብላችሁ።

ፀጋዬ ስለ ትውልዱ

“የተወለድኩት በ1929 ዓ.ም የፋሽስት ወረራ በተጀመረ በስድስተኛው ወር ነው። የልደቴ ቦታ ባዳ አቦ ትባላለች። ከአምቦ 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ የምትገኝ የጅባትና ሜጫ ገጠር። ባዳ ተራራ ግርጌ የሚገኘው የአባባ ቤት ሲቃጠል እናቴና እህቴ ከባንዳ ተታኩሰው በአርበኞች እርዳታ የእኔንና የራሳቸውን ነፍስ ከአዳኑ በኋላ እናቴ እኔን ይዛ ወደ አያት ቅድመ- አያቶቿ ቀዬ ተሰደደች።

“ይሔኔ ነው እንግዲህ ውሃም እንደ እሳት በኔ ውስ ሠረፀ የምለው። ውሃም ልክ እንደ እሳት ከልጅነቴ ጋር ተቆራኝቶ ነው የሚታየኝ። እና በዚያ በሽሽቱ ወቅት በደንዲ ሃይቅ ዳርቻ ስለነበር ያለፍነው ከዚያን ጊዜ ወዲህ የእሳትና የውሃ ነፀብራቅ የማይለየኝ ኃይል ሆኗል። ለዚህም ይመስለኛል የውሃ ኃይል እንደ እሬቻና ጥምቀተ ባሕር የሚስበኝ። ቀይ ባሕር ውስጤ ነው ያለው። የባሕር ለዘብተኛ ውዝዋዜ ከፍተኛ ሰላም ይሰፍንብኛል። ውሃ የሚናግረኝ ይመስለኛል። ከብቸኝነት ያላቅቀኛል። ያደኩባቸው የጉደና ፏፏቴ፣ የሁሉቃ ወንዝ ሰላምና ፀጥታ ይሰጡኛል። በልጅነቴ ከቤት ስጠፋባቸው “ሂዱና ውሃ ዳር ፈልጉት” ነበር የሚባለው። ደሴቷ ላይ ያላቸውን ቤተክርስቲያን ለመሳለም ከቤተሰቦቼ ጋር በሕፃንነቴ በወንጭ ሀይቅ ላይ በጀልባ ተመላልሻለሁ። ለዚህ ነው የውሃ ስርዓቶች በተነፃፃሪ በውስጤ ሰርፀዋል የምለው።

“እናቴ ወ/ሮ ፈለቀች ዳኜ ኃይሉ በአስራ ሶስት ዓመቷ ነው አባቴን ገብረ- መድህን ሮባ ቀዌሳን ያገባችው። የጣራ ምድር አማራ ነች። በልጅ እያሱ ጊዜ የፊት አውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ቶር ንጉሥ ሚካኤልን ለማገድ ሲሔድ አባቴ በጦሩ ውስጥ ነበሩ። “የሃምሳ አለቃ ይባል ነበር በዚያን ጊዜ ሹመት። ታዲያን አንኮበር ሲቃጠል ቤት ንብረታቸው የተቃጠለባቸው ሰዎች ለየትልልቁ ሰው ይከፋፈሉና የናቴ ቤተሰቦች ለአባቴ ይሰጣሉ። ከዚያ ፊትአውራሪ ኢብሳ ሴት አያቴን ልጅሽን ለወንድሜ ስጪ ይሉና እናቴ አባቴን ታገባለች።

“የሁለት ባሕሎች ውጤት- አካል ሆኜ ነው ያደግሁት” ድልድይ ሆንኩኝ። አፍ የፈታሁት በኦሮሚኛ፣ እርባታ የጀመርኩት ደግሞ የግዕዝ ግሥ በመግሰስ ነበር። በጠላት ወረራ ጊዜ ካህናቱ የናቴ ወንድሞች ከጠራ ስለሚመጡ ማምሻዬ ከነርሱ ጋር ነበር።

“ከልጅነቴ ጋር ተቆራኝቶ በውስጤ ያደገ አንድ ሌላ ሶስተኛ ነገር አለ። ዋርካ ነው። ግዙፍ ባሕርያት ከግዙፍ ዋርካ ጋር ይመሳሰልብኛል። ወይም ዋርካ በትልልቅ ሰው። ከአክስቴ ቤት ፊት ለፊት ‘የልጆች እናት’ የምትባል የሾላ ዋርካ ነበረች። ጠዋት ከእንቅልፌ ነቅቼ አይኔን እየጠራረግሁ ብቅ ስል ‘ሀዳ ኢጆሌ’ ተሞልታ ፊቴ ድቅን ትላለች። ላይዋ ላይ የሚፈነጩ ወፎች ዝማሬም መንፈሴን ያድሰዋል።

“ትንሽ ራቅ ብሎ ደግሞ ቦሎ ወንዝ ዳር ‘ሀርቡዳራ’ የምትባል ሾላ ነበረች። እሷም ለኔ ልዩ ተምሳሌት ነበረች፤ ለትልቅነት። ምን ያደርጋል ታዲያ ‘በአብዮቱ’ ሰዎች ሲሰለጥኑ ነው ይባላል፤ ሁለቱንም ቆርጧቸው። የኔንም ወሽመጥ አብረው ቆረጡት። እንደዚያ ጊዜ ተማርሬ አላውቅም።

“እኔ ግን ይሔው ሕይወቴን በሙሉ የዋርካን አድርባይነት፣ የዋርካን ታሪካዊ ቅዱስን በረገጥኩት የአፍሪካ ምድር ሁሉ ተመልክቻለሁ። ዋርካ አድባር፣ ሽማግሌና ጎምቱ አሮጊት አድባር፣ እነዚህ ሁሉ እስከዛሬ ድረስ የዋርካ- የአድባር አምላኪ አድርገውኛል።

“በዚህ አምሳል ብሔራዊ ቴአትር ግቢ ውስጥ ከፊት ለፊት በኩል ያለው ትልቅ ግራር ለኔ አድባሬ ነው። በጃንሆይም ሆነ በደርግ ጊዜ ማዘጋጃ ቤትም ሆነ ‘ሥልጡን’ ነኝ ባዮች ሊቆርጡት በተነሱ ቁጥር ከኔ ጋር ጦርነት ነበር። ኡ! ኡ! ነው የምለው። ወይም ‘ሀዳራው’! እና ለኔ የዚህ የዋርካ ነገር ከጊዜ፣ ከንጋት፣ ከጨለማ ከጀምበርም ማዶ ነው። የዋርካ፣ የውሃና የእሳት በኔ ላይ መስረፅ ከቶም በላዬ ላይ የማያልፍ ኃይል ነው ያለው። ይህ ነው ለኔ ቅኔ። ይህ ነው ለኔ የቅኔ ግንድ።

ኦሮምኛ እና አማርኛ ለፀጋዬ

“በኦሮምኛና በግዕዝ ግሥ እርባታ ምላሴን ስለፈታሁ ወደ አማርኛ ስመጣ ምንም ችግር አልገጠመኝም። ለዚህም ይመስለኛል የቅኔ አስተማሪዎቼ ብርቅዬ ልጅ ለመሆን የበቃሁት። የመምህራኔና ጓደኞቼ ‘እንዴት ይህ የጎረምቲ ኦሮሞ በገዛ አማርኛችን፣ በገዛ ቅኔያችን ሊበልጠን ቻለ?’ እያሉ ይገረሙ ነበር። የቅኔ መምህሬ የዲማው ባለቅኔ አለቃ ማዕምር ዮሐንስ ግጥሞቼን ክፍል ውስጥ ራሳቸው ቆመው ነበር የሚያነቡት። ከልጃቸው ከመዝሙር ማዕምር ይበልጥ እኔ ነበርኩ ልጃቸው። ምነው እንደ ፀጋዬ በሆንክልኝ ነበር የሚሉት ልጃቸውን። ወደ ፈረንጅ ት/ቤት ከገባሁ በኋላ የአስተማሪዎቼ ፍቅርና አድናቆት አልተለየኝም። አምቦ ማዕረገ ሕይወት ት/ቤት ሳለሁ የዳይሬክተራችን ሚስት ሚስዝ ሃቺንግስ በየወላጆች ቀን በአላት በእንግሊዝኛም ግጥም እንድፅፍ ታበረታታኝ ነበር። እና ገና ዝቅተኛ ክፍል ሳለሁ ባሏ ንግግር በሚያደርግባቸው አጋጣዎች ሁሉ ፀጋዬ ይተርጉምልህ ትለው ነበር። ያን ያህል ነበር ለኔ ያላት አመለካከትና ግምት።

“አዲስ አበባ ገብቼ መፃፍ ስጀምር ነው ጣር የመጣብኝ። አዲስ አበባ በርታ አይልም። እዚህ ብዕርህ ካንፀባረቀ አይንህ ይፍሰስ ነው። በ1959 ዓ.ም የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሽልማት የሥነ-ፅሑፍ ተሸላሚ ሆንኩ። 29 ዓመቴ ነበር። ያኔ ታዲያ አለቃዬ የነበሩት ሰው፣ ‘አይ ፀጋዬ እንኳን ደስ አለህ አልልህም። ከእንግዲህ መከራ ገባህ እግዜር ያውጣህ! ያሉኝ አይረሳኝም።’

“በሌላው አለም የብዕር ሰው አይቸገርም ባይባልም፣ እዚያ ራሱን በራሱ አምጦ ወልዶ መብራት ሲጀምር በርታ፣ አሁንም ያሳድግህ! ኑርልኝ ይሉታል። በዚህ አይነት ነው እነ ራሴን፣ እነ ሼክስፒር፣ እነ ፑሽኪን፣ እነ ሚልተን፣ እነ በርናርድሾ ራሳቸውን ሊሆኑ የበቁት። እኛ ዘንድ ግን ከገደሉት በኋላ ነው፤ ትልቅነቱን የሚቀበሉት። ዮፍታሔን፣ አቤን፣ መንግስቱን፣ በአሉን. . . ሁሉንም ከገደሏቸው በኋላ ነው ኑሩልን ያሏቸው። ዮፍታሔ ዘጠኝ ቴአትሮችን ፅፎ ዛሬ አንዱም የለም። ስሙ ብቻ እንጂ የተረፈን ብዕሩ የታለ? ይህንን ስል ማማረሬ ብቻ አይደለም። የባሕላችንን መራራ ጎን በአደባባይ አብጠርጥረን፣ የቁስላችን ሰንኮፍ አሳይተን ባደባባይ ካላወጣነው ለነገው የሥነ-ፅሑፍ ትውልድ ማስተማሪያ አናስቀርለትም። እንደኛው እንዳይሆን ለመጠበቅ ነው። አንደኛ ጉድጓድ እንዳይባል ድልድዩን ልንሰራለት ይገባል። በደህና እንዲልፈው ጉድጓዱን ማሳየት አለብን።”

ፀጋዬን ‘ሎሬት’ ያለው ማን ነው?

      የብዕር ግንባር ቀደምትነትን ብልጭታ ፈር በመቅደድ፣ የራሴን የቅኔ አደራደር ስታይል በመቀየስ ማለትም ብዙዎች ‘የፀጋዬ ቤት’ የሚሉትን የስምትዮ ቤት የቅኔ አደራደር በማስላትና ተቀባይነትን አግኝቼ ሌሎችም በዚያው መጠቀም በመጀመራቸውና በየ ት/ቤቱ እንደ ‘ቡሔ በሉ ቤት’፣ እንደ ‘ወዳጅ ዘመዴ ቤት’፣ እንደ ‘ወል ቤት’ ወዘተ፣ የራሱን የቻለ ቤት ለመሆን በመብቃቱ እንዲሁም እንደነ ‘ኦቴሎ’፣ ‘ማክቤዝ’፣ ‘ሃምሌት’ ያሉ የሼክስፒርን ተውኔቶች በተመጣጣኝ ክላሲክ ቋንቋ በመተርጎም አማርኛም ከአለም ታላላቅ ቋንቋዎች የሚመጣጠን መሆኑን በማስመስከሬ፣ በከፍተኛ የቋንቋ አካዳሚ ደረጃ ብቻ የሚደረስበትን ግስን ከግስ አማጥቆ አዲስ ግስ የመፍጠርና የማስቀበልን ልምድ በመቀየሴ፣ ለአንድ አህጉር ሕዝብ የሚሆን መዝሙር በመድረስ ረገድ የተሳካ ተግባር በማከናወኔ- ማለትም የአፍሪካ መሪዎች ሁሉ የሚዘምሩትን መዝሙር በኔ ቃል ቀራፂነት፣ በኬንያው የሙዚቃ ሰው በዶ/ር ኪሞሌ የዜማ አቀናባሪነት፣ በጋናዊው ፕሮፌሰር ኢንቲኪያ ዘፈን ቀራፂነት የአፍሪካን ሕዝብ መዝሙር በመድረስ ከአፍሪካ መሪዎች ምስጋና፣ አክብሮትና ሽልማት በመቀበሌ፣ ገና የ29 ዓመት ወጣት እያለሁ ከብዙ አንጋፋ ምሁራና የብዕር ሰዎች መሀል ተመርጬ ለቀ.ኃ.ሥ. ዓለም አቀፍ ሽልማት በመብቃቴ፣ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በየጊዜው የተለያዩ ሽልማቶችን አለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ብሔራዊ ሽልማቶችን በማግኘቴ (የጎልድ ሜርኩሪ አድ ፐርሰንም ሽልማት፣ የሴኔጋል ሪፓብሊክ የፈረሰኛ ኒሻን ወዘተ. . .) በሌሎች ቋንቋና የታሪክ ጥናትና የምርምር ሥራዎችና ጥረቶች ሳቢያ ሊደረስበት የቻለ፣ በአፍሪካ አንጋፋዎች የተሰየመ ሎሬትነት ነው እንጂ እኔ ለራሴ የሰጠሁት ስያሜ ወይም ቅፅል አይደለም”። (ይቀጥላል)

ይምረጡ
(22 ሰዎች መርጠዋል)
17820 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us