እየተቀዛቀዘ የመጣው የኢትዮጵያዊነት ባህል

Thursday, 06 November 2014 09:11

ሰው ግደሉ ሰው መግደል ይበጃል፣

ይዋል ይደር ማለት ጠላት ያደረጃል

በጥበቡ በለጠ

     በቅርቡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት የሚታወቁትን ዶ/ር ብርሃኑን እናእኔን፣ ወ/ሮ እመቤት ደጀኔ የተባለች በስውዲን ሀገር የምትኖር ሴት ምሳ ጋበዘችን የተጋበዝንበት ምክንያት ደግሞ The sole African Alphabet ወይም “ብቸኛው የአፍሪካ ፊደል” ስለተሠኘው መጽሐፍ እግረ መንገዳችንን ለመጨዋወት ነው መጽሐፉን ያዘጋጁት ደግሞ ዶ/ር ፍቅሬ ዮሴፍ ሲሆኑ፤ አሳታሚዋ ወ/ሮ እመቤት ደጀኔ ናቸው በምሳ እያዋዛን ስለመጽሐፉ አጠቃላይ ይዘት ተወያየን ጨዋታችን ከሀገራችን የፊደል ታሪክ ተነስቶ እያደገ መጣ በዚህ አጋጣሚ ዶ/ር ብርሃኑ አንድ ግብዣ አቀረቡልን “በሚቀጥለው ሳምንት አንዲት ከጣሊያን ሀገር የመጣች ዘፋኝና ተመራማሪ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ስለ “ፉከራ” የተለያዩ ዜማዎችንና ግጥሞችን ታቀርባለች” አሉን ግብዣው ጥሩ ነበር

     “ፉከራ” የሀገራችን የዜማ ቅርስ ነው ይሁን እንጂ በደንብ ስላልሰራንበት ዛሬ እየደበዘዘ የመጣ ታሪክእንዳለው በጨዋታችን ወቅት ተነሳ ይህች ከጣሊያን ሀገር የመጣች ሴት ይህን ጥንታዊ ቅርሣችንን ልታስታውሰን ነው በዚሁ የምሳ ግብዣ ላይ ወ/ሮ እመቤት አንድ ጥያቄ ለዶ/ር ብርሃኑ አቀረበች ፉከራ፣ ቀረርቶ እና ሽለላ ልዩነታቸው ምንድን ነው? አለች ዶ/ር ብርሃኑም በጣም ጥሩ ጥያቄ መሆኑን ገለፁላት ግን ልዩነታቸውን ጥርት አድርገው እንደማያውቁት ገለፁላትእኔ ደግሞ በሆነ አጋጣሚ በልዩነታቸው ላይ የተወሠነ ነገር ስለማውቅ አጫወትኳቸው በተለይ ዶ/ር ብርሃኑ በጣም ደስ አላቸውእናም በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተወሰነ ነገር እንድጽፍበትና በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ ጣሊያናዊቷ ስትፎክር እኔ ደግሞ ስለ ፉከራ፣ ቀረርቶ እና ሽለላ ልዩነቶች ገለፃ እንድጽፍ አዘዙኝ ጉዳዩ ላይ ብስማማም ፈረንጇ በምታቀርብበት ወቅት ከተማ ውስጥ ስላልነበርኩ ጥናቴን በጽሁፍ አድርጌ ለዶ/ር ብርሃኑ ሰጠኋቸው ዛሬ የማጫውታችሁ ስለነዚሁ የፉከራ፣ የቀረርቶ እና ሽለላ አንድነትና ልዩነት ነው ምክንያቱም መዘንጋት የሌለባቸው የኢትዮጵያዊያን ልዩ መገለጫዎች ናቸውና

           አስታጥቀኝና ከአንገቴ ድረስ፣

ግንባር ግንባሩን ብዬው ልመለስ

**         **         **

አዳኙ ቆፍጣና ልቡ የነደደው፣

ገና በልጅነት መግደል የለመደው

**         **         **

እምቢ አሻፈረኝ እኔ አልሆንም ባንዳ፣

የታሠበው ይሁን ያበጠው ይፈንዳ!

     እነዚህ ከላይ የሠፈሩት ባለ ሁለት ስንኝ ግጥሞች በተለያየ የዜማ ቅርፅ ውስጥ ሲገቡ የተለያየ ስያሜ ያገኛሉእንዳየናቸው ከሆነ ከግድያ ጋር፣ ከአተኳኰስ እና ከጦርነት ከአደን ጋር የተያያዘ ይዘት አላቸው ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ወኔ ለመስጠት፣ ለመገፋፋት እና ለማዋጋት የሚቀሰቅስ መልዕክት አላቸው ኢትዮጵያም በታሪኳ ጦርነት ባካሄደችባቸው ወቅቶች ሁሉ እነዚህ የአገጣጠም ስልቶች ውለታ አስቀምጠዋል አርበኞች በየአውደ ግንባሩ እንዲጓዙእና በወኔ እንዲዋጉ በማድረግ የፉከራ፣ የቀረርቶ እና ሽለላ አስተዋፅኦ መዘንጋት የሌለበት ታሪክ ይመስለኛል አሁን እንኳን ስላለፈው የጦርነትና የጀግንነት ታሪክ ስንተርክ በእነዚህ የሙዚቃ ስልቶች ማጀቡ በስፋት ይዘወተራልእስኪ ልዩነቶቻቸውን በጥቂቱ እንቃኝ

     ደስታ ተክለወልድ በታላቁ መዝገበ ቃላቸው “ፉከራ”ን ሲገልፁ የሚከተለውን ብለዋል “ፎከረ፣ ሞያን፣ ዠብድን ገለጠ ቆጠረ፣ አስረዳ፣ አካኪ ዘራፍ፣ ገዳይ እዚያ ገዳይ አለ” በማለት ያብራሩታል

     እንደ ደስታ ተክለወልድ ሁሉ ኪዳነወልድ ክፍሌ ደግሞ ፎከረ የሚለውን የግዕዝ ቃል፣ “መደንፋት፣ ሙያን መናገር፣ ማውራት፣ ሙያን መተንበይ፣ መመከት፣ ግዳይ መጣል፣ ሰለባ መቁጠር” በማለት ያብራሩታል

     ከሳቴ ብርሃንም በመዝገበ ቃላቸው ፉከራን ሲያስረዱን፤ “የጀግኖችን ስራ እያወሱ መፎከር ነው” ይሉታል

     ማህተመ ስላሴ ወ/መስቀል ደግሞ “ፉከራ ወይም ድንፋታ ጀግኖች ለገዢዎቻቸው ወይም ለአለቆቻቸው ከፍ ያለ ድምፅ በማሰማት ወኔያቸውን የሚገልፁበት የጦር ግጥም ነው” በማለት የሰጡት ትንታኔ ዛሬም ድረስ በመዝገበ ቃላቸው ውስጥ አለ

     በቅርቡ በሞት የተለዩን ታዋቂው ባለቅኔ ዓለማየሁ ሞገስ ደግሞ፤ “ቀረርቶ በኋላ ግጥምን እያንደቀደቁ ሲወርዱ ፉከራ ይባላል” ብለዋል ምሳሌም ሲያስቀምጡ የሚከተለውን ጽፈዋል

አቅራ አቅራ አለኝ ቀረርቶ እወዳለሁ፣

የነካኝንማ እኔ ምን አውቃለሁ

አንድድበት ቆስቁስበት ካልጋመ አይጋግርም፣

ወንድ ልጅ ካልከፋው አያንጐራጉርም

አልሸልልም አላቅራራም ብዬ መሐላ ነበረብኝ፣

አንጐራጉራለሁ እየጐደለብኝ

በማለት ታላቁ ባለቅኔ ዓለማየሁ ሞገስ ገልፀዋል

ያዕቆብ ገ/ኪዳን ደግሞ ከጐንደር ከሰበሰቧቸው ፉከራዎች ውስጥ የሚከተሉትን ስንኞች እንመልከት፤

ገዳይ ቆንጥር ለቆንጥር፣

ትንሽ ለነፍሱ የማይጠረጥር

አለው በሽታ የጦር አመል፣

ጠላት እንደእንጨት የመመልመል

ተኩሶ የማይስት ከሳበ ምላጭ፣

ባፉ አገባበት እንደእንጥል ቆራጭ

    ይህ ከላይ የሰፈረው ግጥም በዜማ እና በጥሩ ድምፅ ታጅቦ ሲቀርብ በሰዎች ውስጥ የሚያሳድረውን ወኔ የመቀስቀስ ተልዕኮ ማሰብ እንችላለን ቀስቃሽና ወኔ ሰጪ ግጥም ነው ተዋጊው ደረቱን ገልብጦ የጦር አውድማ ውስጥ ጥልቅ እንደሚል ግልፅ ነው

አስታጥቀኝና ከአንገቴ ድረስ፣

ግንባር ግንባሩን ብዬው ልመለስ

ስጠኝ ጠብመንጃ ከጥይት ጋራ፣

ግዝት ያርግብኝ ሞት እንዳልፈራ

     እነዚህ ግጥሞች በባህሪያቸው ከጦርነትና ከተኩስ ጋር የተያያዙ ናቸው ምናልባት ኢትዮጵያዊያን በየዘመናቱ የመጡባቸውን ወራሪ ኃይሎችእየመከቱ ድባቅ ያደረጉት በእንደነዚህ ዓይነት ወኔ ቀስቃሽ ፉከራዎች ሊሆን ይችላል፤ ግን በዚህ ዘርፍ ጥናት ቢደረግ ብዙ ጉዳዮችን ማግኘት የሚቻል ይመስለኛል ያዕቆብ ገ/ኪዳን ካደረገው ግጥሞችን የመሰብሰብ ትልቅ ስራ በተጨማሪ ማለቴ ነው

     እስኪ አሁን ደግሞ ቀረርቶ ስለሚባለው ሌላኛው የኢትዮጵያ ቅርስ እንመለስ ቀረርቶ ምንድን ነው?

ደስታ ተክለወልድ በመዝገበ ቃላቸው እንዳሰፈሩት ከሆነ፤ “ቀረረ፣ የጦር ግጥም ገጠመ፣ አጉራራ፣ ቀረርቱ፣ ሽለላ፣ የጦር ዘፈን” በማለት ይተነትኑታል

     ዓለማየሁ ሞገስ ደግሞ፤ በ1954 ዓ.ም ባሳተሙት “የአማርኛ ግጥምና ቅኔ ማስተማሪያ” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደገለፁት፣ “ቀረርቶ ጐበዝ ሞቅ ሲለው በየተራራው የሚለቀው ነው” ብለውታልእንግዲህእዚህ ላይ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፤ ጐበዝ ሞቅ የሚለው መቼ ነው? ሞቅ ሲለው ማለት ምንድን ነው? ሞቅ ማለት ስካር ነው ወይስ ደስታ? በእርግጥ የባለቅኔው የዓለማየሁ ሞገስ ማብራሪያ ለብዙ ትንታኔና ገለፃ ክፍት በመሆኑ ይህ ነው የሚባል እርግጠኛ መደምደሚያ ላይ መድረስ ያዳግታል

     ከዓለማየሁ ሞገስ በተሻለ ሁኔታ ቀረርቶን ያብራራው ያዕቆብ ገ/ኪዳን ነውእርሱእንደሚለው፤ “ቀረርቶ የሰዎችን ወኔ ለማነሳሳትና ለመቀስቀስ ብሎም ወደ ድርጊት እንዲያመሩ ለማድረግ የሚጠቀሙበት ዜማ ለበስ መሣሪያ ነው” ይለዋል በይዘቱም በደልንና ችግርን በመቁጠር፣ ጠላትን በመጠቆም፣ ፈሪንና ሰነፍን በማንኳሰስ፣ ጀግናንና ጐበዝን በማወደስ ለተግባር እንዲነሱ የሚቀሰቅስ መሆኑን ይገልፃል ስለ ቀረርቶ በፃፈው መግለጫ

እስኪ አንድ የቀረርቶ ግጥም እንመልከት፤

በደን በበረሃ ባሸለመ ለምለም፣

እቀፊኝ ደግፊኝ አንተርሺኝ የለም

አዳኙ ቆፍጣና ልቡ የነደደው፣

ገና በልጅነት መግደል የለመደው፣

ተኩሶ ተኩሶ እጁ መነመነ፣

አዳኙ ቆፍጣና እንኳን የኛ ሆነ

    እንግዲህ ቀረርቶም ቢሆን ከወኔ ቀስቃሽ ርዕሰ ጉዳዮች ጋር የመገናኘት ባህሪ አለው ማለት ይቻላልታዲያ በፉከራ እና በቀረርቶ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው ብሎ የመጠየቅ ጉዳይ አይቀሬ ነው ልዩነታቸው ምንድን ነው?

     ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ቀረርቶ እንድን ነገር ዘርዘር ባለ መልኩ የማቅረብ ስልት አለው ፉከራ ግን ከላይ ከላይ ጠቆም ጠቆም እያደረገ የመሄድ ፀባይ እንዳለው ይወሳል በግጥም አደራደሩ ደግሞ ፉከራ ፍሰት እንዳለውም ይገለፃል

እስቲ ልጀምር ትንሽ ፉከራ፣

መቼም ይሄ ነው የጀግና ስራ

ጥጃ ስደዱ ላም እናገናኝ፣

ከጀግና ጐበዝ ደህና እንገናኝ

     በሌላ መልኩ ፉከራ እና ቀረርቶ በአገጣጠም ስልታቸውና በምጣኔያቸው እንደሚለያዩ ያዕቆብ ይገልፃል ይህ ክፍል ሙያዊ ትንታኔ ስለሚኖረው ማብራሪያ አልሰጥበትም ግን በአገጣጠማቸው መለያየታቸውን ከግንዛቤ ማስገባት ይጠቅመናል ከዚህ ሌላ ልዩነታቸው ተብሎ የሚገለፀው በክዋኔ /Performance/ የመለያየታቸው ሁኔታ ነው ይህ ማለት አንዱ ቀድሞ የሚመጣ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ቀዳሚውን ተከትሎ እንደሚመጣ ይገለፃል

ማህተመ ስላሴ ወ/መስቀል የሁለቱን ልዩነት እንዴትእንዳስቀመጡት የሚከተለውን አባባላቸውን እንመልከት፤

    “… ቀረርቱና ፉከራ አይለያዩም፤ ቀረርቱ ይቀድማል ፉከራ ወይም ድንፋታ ይከተላል ይህንን አተኩረን ያየን እንደሆነ፤ ሽለላ ጠብ መጫሪያ፣ የነገር ማንሻ ይመስላል ሸላዮቹ ጀግኖችን በማመስገን በመንቀፍና በመግሰፅ፣ ወጣቶችን አነቃቅተው የመንፈስ ብርታትን ከአስገኙ በኋላ እንኳን የወንዶችን የሴቶችንም ቢሆን የቆራጥነት ወኔያቸውን ይቀሰቅሱበታል ብለዋል

     ያዕቆብ ገ/ኪዳን ደግሞ የፉከራንና የቀረርቶን ልዩነት ሲገልፅ የሚከተለውን ብሏል፤ “ቀረርቶ፤ እንነሳ፣ ተጠቃን፣ ተበላን፣ ተዋረድን፣ ግፍ በዛብን፣ ጐበዝ ማነህ፣ ፈሪ ማን ነህ? በለው እያለ ሲቀሰቅስ ፉከራ ደግሞ አለሁልህ፣ እናቃጥላለን፣እኛእንበልጣለን፣ አድርጌዋለሁ፣ አደርገዋለሁ በማለት ምላሹን የሚሰጥ ሆኖ እናገኘዋለን”በማለት ይገልፃል   አያይዞም፤ ቀረርቶ ደምን የሚያፈላና የሚያሞቅ፣ የሚያስቆጣ ሲሆን፤ ፉከራ ደግሞ የዚህ ምላሽ ነውና ራሱ ፍላት ነው ይለዋል ባህሪያቸውም ይህንን እንደሚፈቅድ ጥናቱ ያሳያል

     ሌላው የፉከራ እና የቀረርቶ ልዩነት በእንቅስቃሴ ወቅት የሚከሰት ሁኔታ ነው ፉከራ ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ ሲኖረው፣ ቀረርቶ ደግሞ ረጋ ማለት ይታይበታል

     በሌላ መልኩም ልዩነት እንዳላቸው ይገልፃል ይህም በሙዚቃ መሣሪያ አጃቢነት በኩል ስናየው፤ ቀረርቶ የተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች ሲያጅቡት፣ ፉከራ ግን ወኔው የመጣ ሁሉ እየዘለለ በመግባት ካለሙዚቃ መሣሪያ ሊፎክር ይችላል

እምቢ አሻፈረኝ እኔ አልሆንም ባንዳ፣

የታሰበው ይሁን ያበጠው ይፈንዳ!

**         **         **

በለሳ አፋፍ የወደቀ አንበሳ፣

ነገር መጣ ሲሉት እዩት ሲሳሳ

አገራችን ጐንደር ሰሜን አርማጭሆ፣

እንዲያውም ያምረናል እንኳን ጥይት ጮሆ

ጐበዝ ጥይት ግዛ ጐበዝ አልቤን ግዛ፣

በናት ሀገርና በሚስት የለም ዋዛ

     በመጨረሻም ስለ “ሽለላ” የተሰጠውን ማብራሪያ እንመልከት ደስታ ተክለወልድ በመዝገበ ቃላቸው ሽለላ ለሚለው ቃል በሰጡት ማብራሪያ፤ “ሸለለ፣ አቅራራ፣ ጃሎ መገን አለ፣ የጦር ግጥም ገጠመ፣ መሸለል ማቅራራት” በማለት ይገልፁታል በጦርነት ግዜም የሚዜም መሆኑን ይናገራሉ

     ከሳቴ ብርሃን ደግሞ ሲገልፁ፤ “ሽለላ /መሸለል/ አቅራራ፣ የጦር ዘፈንን ሸለለ፣ አቅራራ ወይም ወታደር በጌታው ፊት በግብር ላይ ወይም በጨዋታ ቤት ሲጫወት የጀግኖች ወኔ ለማነቃቃት ሸለለ” ይሉታል

     ማህተመ ስላሴ ወ/መስቀል በ1961 ዓ.ም ባሳተሙት “ባለን እንወቅበት” በሚለው መጽሐፋቸው፤ “ቀረርቶ ወይም ሽለላ ማለት የጦርነት ዘፈን ነው፤ ወይም ወታደር በጌታው ፊት በሰልፍ መካከልና በዜማ የሚሰማ ቃል ነው” ብለውታል

በፈረንጆቹ አገር የጦርነት መዝሙር /War Song/ የሚባል ዜማ አለ በተወሰነ መልኩ ከእኛ ፉከራ፣ ቀረርቶ እና ሽለላ ጋር የመመሳሰል ነገር ቢኖረውም፤ ልዩነታቸው ግን ሰፊ ነው

     በአጠቃላይ እነዚህ የኢትዮጵያ ብቸኛ የሆኑ የዜማ እና የግጥም ስልቶች ዛሬ ዛሬ ከዓይንም ከጆሮም እየጠፉ ነው ወጣቱ ትውልድም የተዋቸው ይመስለኛል ወደፊት እነዚህ ቅርሶቻችን እንዲኖሩልን ከበርካታ የሙዚቃ ባለሙያዎቻችን በተጨማሪ ከእጅጋየሁ ሽባባው ጂጂ እና ከቴዲ አፍሮ ብዙ እጠብቃለሁ ጂጂ - አድዋ በሚለው ዘፈኗ ስልቶቹን በተወሰነ መልኩ ተጠቅማባቸዋለችታዲያ ሙዚቃው ውብ ነበር

ይምረጡ
(60 ሰዎች መርጠዋል)
17788 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us