ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ትራጄዲ ምን አለ?

Wednesday, 12 November 2014 15:19

በጥበቡ በለጠ

 

ከአንድ ሳምንት በፊት ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን አንድ ጽሁፍ ጀምሬ ነበር። ጽሁፉ ደግሞ ዛሬ በሕይወት የሌሉት መስፍን ዓለማየሁ እና ደምሴ ጽጌ ከፀጋዬ ጋር ያደረጉትን ውይይት መሠረት አድርጐ የተፃፈ ነው። እነዚህ የኢትዮጵያ ደራሲያን ጠያቂዎቹም ተጠያቂውም ዛሬ ሦስቱም በሕይወት የሉም። የዛሬ 22 ዓመታት ግን አብረው ቁጭ ብለው አውግተው ነበር። ወጋቸው የማይጠገብ በመሆኑ ነበር እኔም መልሼ ለሰንደቅ አንባቢያን ማቅረቤ። ይሁን እንጂ ባለፈው ሳምንት ከአቅም በላይ በሆነ ችግር የጽሁፉ ሁለተኛ ክፍል ሳይወጣ ቀረ። በዚህ ሳቢያም ቁጥራቸው የበረከተ አንባቢዎቼ እየደወሉ ወቀሱኝ። ጥፋቱ የእኔ በመሆኑ ይቅርታዬን አቅርቤ ወደ ዛሬው የነ ፀጋዬ ወግ እቀጥላለሁ። ወጋቸውን ለዛ ብለው በሚጠሩት መጽሔታቸው ላይ በ1985 ዓ.ም አትመውታል።

ፀጋዬ ተውኔቶችህ ምነው የሐዘን ድባብ በዛባቸው?

ሲባል የሰጠው መልስ

“የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራ ተሸካሚ ነው” አለ በተከዘ ድምጽ። “በተደጋጋሚ የጦርነት ድግስ ይደገስለታል። ድግሱ አዳራሽ ውስጥ ‘ሆ’! ብሎ ገብቶ ይቃጠላል። ለዚህ፣ በእኔ አስተያየት የተለያዩ ምክንያቶች አሉት።

“ልቡ ውስጥ የምታበራዋን ነፃነት የሚላትን እሳት ለራሱ ለማስቀረት ጦርነት ውስጥ ገብቶ ይቃጠላል። አንገቱን ቀና አድርጋ የምታንቀሳቅሰው ይህች ነፃነት ወዳድነቱ ነች። ይህችን በውስጡ የምትነድ ባህሪውን ገዢዎቹ ለራሳቸው ጥቅም ያውሉዋታል። ሁለት ባላባቶች ማዶ ለማዶ ያዋጉታል። ከውጭም ጠላት ሲመጣባት ያው ነው። ነፃነቱን እጅግ ይወዳል። በዚህም ከሌላው ይለያል። መከራውን ችሎ አንጀቱን ቋጥሮ ባዶ እግሩን ያለስንቅ፣ ያለ ደመወዝ ለነፃነቱ ይሞታል። በወንድሞቹ በአፍሪካዊያን ዘንድ፣ በጐረቤቶቹ በዓረቦች ዘንድ ያስከበረውም ይሄው ባሕሪው ነው። ዛሬም ቢሆን ያው ባሕሪው ይታያል። እፎይ ብሎ አያውቅም። የሚያጫርሰው አመራር ሁልግዜም ይከሰታል።

“በውስጥ ለራሳቸው ጥቅም እርስ በርሱ ያፋጩታል። በውጭም ለነፃነቱ ቀናኢ ስለሆነ እሱን ለሞት አጋፍጠው እንደገና አናቱ ላይ ፊጥ ይላሉ። በዚህም አጥንቱን ይሰበሩታል።

“እኔ ደግሞ አንድ ገበሬ አጠገብ ቁጭ ብዬ እ-ህ ማለትን እወዳለሁ። ከአንድ አርበኛ፣ ከአንድ ወታደር፣ ከአንዲት የወታደር ሚስት፣ ከአንድ ቄስ፣ ከአንድ ሼህ…. ከሁሉም እህ ብዬ እማራለሁ።

“ሁሉም አንደበታቸው እንባ አዘል ነው። እሮሮ ያፈልቃል ልሳናቸው። ሕይወታቸው ሁሉ ብሶት ነው። ይሄ ነው በአጠቃላይ የሀገሪቱ ገፅታ። ብዕሬን ወደ ትራጄዲ የሚስበውም ይሄ ነው። በልጅነቴ ቅኔ መምህሬ እግር ስር ቁጭ ስልና ሲያቀርቡኝ ሙያቸውን ሊቀበል የሚችል አዕምሮ አለው ብለው ልጃቸው ሲያደርጉኝ ውስጣቸውን ያሳዩኛል። ያው በአበሻ እሮሮ የተሞላ ውስጣቸውን … ትዝ ይለኛል፤ ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተዘግቶ ለመጀመሪያ የክረምት ዕርፍት ወደ ወላጆቼ ዘንድ ስሄድ የቅኔ መምህሬን ለመጠየቅ ወደ ቤታቸው ጐራ ብዬ ነበር። ያመጣሁላቸውን እጅ መንሺያ ቡና ይቼ ስገባ በተመስጦ ያነቡ ነበር። ገብቼ ስሜያቸው ስቀመጥ ንባባቸውን ለመጨረስ አቀረቀሩ። በመሀል አንዲት ወፍ ከበሩና ከጣሪያው መሀል በርራ ትወጣለች። መምህሬ ቀና ብለው፡-

“ምንድን ነው እሱ አሁን በሮ የወጣው ፀጋዬ?” ብለው ጠየቁኝ።

“ወፍ” አልኳቸው።

“አይ ለወፍም ትከብዳለች” አሉኝ።

“አሞራ” ስላቸው

“ለአሞራ ትቀላለች” አሉኝ።

“ቡላላ” ስላቸው

“እርግብ ማለትህ ነው?” አሉኝ።

“አየኸው ምን ያህል ንቁና አስተዋይ እንደሆኑ? በኋላ እምቡሽቡሽ ጠላ ሚስታቸው ሰጥተውን እየጠጣን ስንጫወት ቆይተን ስለ ኑሮና ጤንነታቸው ስጠይቃቸው፡-

“ ‘አየህ ፀጋዬ’ አሉኝ፤ ‘መምህርና ወደል አህያ አንድ ነው። ወደል አህያ ከባዝራ ጥሩ በቅሎ ይደቀላል። ያቺ ሲናር በቅሎ ለቤተ-መንግሥት ትታጫለች። ልዑላንም ነገስታትም ይቀርቧታል። ቀይ ጃኖ ትለብሳለች። በመረሸት ታጌጣለች። የሚያበላት ወንድ አሽከር ይቆጠርላታል። ያ ወደል አህያ አባቷ ግን በፍልጥ እየተደበደበ፣ ድንጋይም አፈርም ይሸከማል። እኔ የመንፈስ አባትህ ወደል አህያ ነኝ። አንተ ግን ይሄው አጊጠህ አምሮብሀል እሰየው አሁንም እደግልኝ’ ብለው መረቁኝ። እርግጥ ብለዋል። መምህሬ በስተርጅና ሳያልፍላቸው በበሽታና በድህነት ተሰቃይተው ነው ያለፉት። በየቦታው የሕዝቡን ገጽታ ፈልፍለህ ስታይ ትራጄዲ ነው የምታገኝ። ግን ይህን ሁሉ መከራ ተሸክሞ መኖሩ በጣም ያስደንቀኛል። ቶሎ የማሸነፍ ገጽታው ነው ሁሌ ብዕሬን ወደ ትራጄዲ የሚመራው። ቅኔዬ ከዚህ ጭንቀት የመላቀቅ እምቢታና (ፕሮቴስት) አቤቱታ ነው።”

(ይቀጥላል)

 

 

የፀጋዬ ገብረመድኅን ዋና ዋና ተውኔቶች ዝርዝር

  1. ንጉሥ ዳዮኒስስና ሁለቱ ወንድሞቹ 1949 (ዓ.ም) አፄ ኃይለስላሴ በተገኙበት በ16 ዓመት እድሜው በአምቦ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ ከመማሪያ መጽሐፉ ተወስዶ በራሱ አዘጋጅነት በመድረክ የቀረበ ቴአትር፣ ይህ ቴአትር ፀጋዬ ገና በለጋ እድሜው ከንጉሡ ሽልማት ያገኘበትና የቀረ ዘመኑን አቅጣጫ የወሰነ ቴአትር ነው።
  2. ኦዳ ኦክ ኦራክል (Oda Oak Oracle)1957 ዓ.ም በጥንታዊት ኩሻዊት ኢትዮጵያ ባሕልና እምነት ላይ ተመስርቶ የተፃፈ የእንግሊዝኛ ተውኔት፣ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ታትሞ በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በአሜሪካ በካናዳና በኬኒያ፣ በናይጄሪያ፣ በታንዛንያ በመድረክ የታየ ተውኔት
  3. አዝማሪ (Azmari)1967 ዓ.ም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተጽፎ በለንደን ኤድንበርግ የታተመ
  4. ቴዎድሮስ (Theodros)1960 ዓ.ም በታሪክ የምናውቀውን የቴዎድሮስን የተስፋ ጉዞ ሕልምና አሳዛኝ ውድቀት የተተረከበት በአማርኛ ቅኔ የተፃፈ ታሪካዊ ትራጄዲ
  5. ኮሊዥን ኦቭ አልታርስ (Collision of Altars) 1961 በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በካሌብ ዘመነ መንግስት የነበረችቱን ኢትዮጵያ አቅርቦ የሚያሳይ ተውኔት
  6. አፍራካ ከባራ 1993 - 2006 (Afraca Kbara) ያልተጠናቀቀ በአፍሪካዊ ሥነ-ባሕል ጥናት ላይ ያተኮረ መጽሐፍ፤ ይህ ጽሑፍ ፀጋዬ ከፀሐፌ ተውኔትነት ወደ አንትሮፖሎጂ በመሻገር ታሪክን ሲመረምር የኖረበትና በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገልፀው የኖረ ያልታተመ ሥራ ነው።
  7. ሌላው አዳም 1944 ዓ.ም በንግድ ሥራ ት/ቤት ተማሪ ሳለ ተፅፎ በት/ቤቱ መድረክ ብቻ የቀረበ
  8. የደም አዝመራ ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ዘመን ስለተፈፀመ ግፍና ስለፈተናው ዘመን የሚያሳይ ተውኔት። 1944 ዓ.ም በንግድ ሥራ ት/ቤት ተማሪ ሳለ በት/ቤቱ መድረክ የቀረበ
  9. በልግ 1950 ዓ.ም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር የቀረበ
  10. የሾህ አክሊል 1952 ዓ.ም በቀድመው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር የቀረበ
  11. አስቀያሚ ልጀገረድ1952 ዓ.ም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር የቀረበ
  12. ጆሮ ደግፍ 1952 ዓ.ም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር የቀረበ። አንድ ጆሮው በጆሮ ደግፍ ያበጠ ለመስማት የሚቸገር ሥራው ስልቻ ማልፋት የሆነ ወጣት ታሪክ ነው። ልፋ ያለው በሕልሙ ሥልቻ ሲያለፋ ያድራል እንዲሉ ተውኔቱ የከንቱ ልፋት ምሳሌ ይመስላል። ፀጋዬ በዚህ ተውኔት ሳቢያ በሳንሱር ሹማምንት እንደተጠየቀበት ይነገራል።
  13. ሊስትሮ 1953 ዓ.ም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር የቀረበ
  14. እኝ ብዬ መጣሁ1953 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር የቀረበ ወደ እንግሊዝ አገር ለትምህርት ሂዶ ሳለ ስለታዘበው በባሕል ግዴታ ዘመናዊነትና ትሁት ሆኖ ለመታየት ሲባል በሀሰት ፈገግታ ሲያገጥጡ ስለመዋል የተፃፈ ተውኔታዊ ምፀት።
  15. ጩሎ 1954 ዓ.ም በቀድሞው በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር የቀረበ ተውኔት ነው። ጩሎ ተላላኪና አሽከር ማለት ሲሆን፤ በዚያን ዘመን በየቤቱ በዕለት ጉርሳቸው ድርጐ በጩሎነት የሚያገለግሉ ታዳጊ ልጆች በየቤቱ ነበሩ። በዚቀኛው ጆሮ ተውኔት ከያኒው ራሱን እንደ ጩሎ ቆጥሮ ሶኖ ኢዮ ማሞ ቂሎ፣ ቀን እንደጌታ ማታ እንደ ጩሎ እያለ እሺ ጌታዬ ብለው የሚያድሩበትን የዘመኑን የመንግሥት ቅጥረኛ ሕይወት በምፀት ሲፀየፍ እንሰማዋለን። ጩሎ ካልታተሙ ቴአትሮቹ አንዱ ነው።
  16. ኮሾ ሲጋራ 1954 ዓ.ም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር የቀረበ
  17. የእማማ ዘጠኝ መልክ 1954 ዓ.ም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር የቀረበ
  18. የፌዝ ዶክተር 1955 ዓ.ም ከሞልየር (Doctore in spite of Himself) በተዛማጅ ትርጉም ተተርጉሞ የተዘጋጀ ቧልታይ ተውኔት።
  19. ታርቲዩፍ 1956 ዓ.ም ከሞልየር (Tartuffe) በተዛማጅ ትርጉም ተተርጉሞ ለመድረክ የቀረበ በካሕናት ሕይወት ላይ የሚያተኩር ቧልት ለበስ ትችት ነው።
  20. ኦቴሎ1957 ዓ.ም ከዊሊያም ሼክስፒር በተዛማጅ ትርጉም ተተርጉሞ በቀ.ኃ.ሥ. ቴአትርና በአዲስ አበባ የባሕል አዳራሽ በመድረክ የቀረበ።
  21. ንጉሥ ሊር 1961 ዓ.ም ከዊሊያም ሼክስፒር በተዛማጅ ትርጉም ተተርጉሞ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር በመድረክ የቀረበ
  22. ማክቤዝ1961 ዓ.ም ከዊሊያም ሼክስፒር በተዛማጅ ትርጉም ተተርጉሞ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር በመድረክ የቀረበ።
  23. ክራር ሲከርር1962 ዓ.ም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር በመድረክ የቀረበ
  24. ሀሁ በስድስት ወር 1966 ዓ.ም በቀድሞው ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር በመድረክ የቀረበ
  25. አጽም በየገፁ 1966 ዓ.ም
  26. እናት ዓለም ጠኑ 1966 ዓ.ም
  27. አቡጊዳ ቀይሶ1968 ያልታተመ አብዮታዊ ቴአትር የሀሁ በስድስት ወር ተከታይ
  28. መልዕክት ወዛደር 1972 ዓ.ም ያልታተመ አብዮታዊ ቴአትር የአቡጊዳ ቀይሶ ተከታይ
  29. ጋሞ1974 ዓ.ም ያልታተመ አብዮታዊ ቴአትር ለጥቂት ጊዜ በመድረክ ታይቶ የታገደ ቴአትር ነው። ፀጋዬ በዚህ ተውኔት በሳንሱር ሹማምንት እንደተጠየቀበት ይነገራል።
  30. ዘርዓይ ድረስ 1975 ዓ.ም ባለ አንድ ገቢር ታሪካዊ ተውኔት በኢትዮጵያዊው ጀግና በዘርአይ ድረስ ገድል ላይ የሚያተኩር ታሪካዊ ተውኔት
  31. ሀምሌት 1976 ዓ.ም (Hamlet) ከዊሊያም ሼክስፒር በተዛማጅ ትርጉም ተተርጉሞ በብሔራዊ ቴአትር በመድረክ የቀረበ፤
  32. ዚቀኛው ጆሮ 1977 ዓ.ም በአበራ ጆሮ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ቅኔ ለበስ ቴአትር ለአንድ ጊዜ ብቻ በኢሠፓ አዳራሽ ቀርቦ የታገደ።
  33. ምኒልክ 1982 ዓ.ም በዳግማዊ ምኒሊክ ዘመን ላይ ያተኮረ ታሪካዊ ተውነት
  34. ሀሁ ወይም ፐፑ 1984 ዓ.ም በደርግ መንግሥት ውድቀት ማግስት ስለተፈጠረው የትንሳኤ ወይም የውድቀት መንታ መንገድ የቀረበ ተውኔታዊ ምርጫ። ሀሁ ወይም ፐፑ ትንሳኤ ወይም ጥፋት፤

(ምንጭ፤ ምስጢረኛው ባለቅኔ 2006፣ በሚካኤል ሽፈራሁ)

(ከገፅ 357 - 361)

ይምረጡ
(10 ሰዎች መርጠዋል)
10665 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us